የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 5 | በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የኢፌዲሪ አየር ኃይል ተሳትፎ ዙሪያ አጭር ዳሰሳ

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ፣ ሁለተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክሦስተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ እና አራተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክማግኘት ይችላሉ)

Highlights 

*በባለፈዉ መንግስት የጀኔራልነት ማዕረግ የነበራቸዉ ከፍተኛ መኮንኖች ሳይቀሩ የኢፌዴሪን መከላከያ በማቋቋሙ ስራ ላይ ተጠምደዉ ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በርግጥ አንዳንደቹ “ከዚህ ቀደም ከተዋጋነዉ የወያኔ ሰራዊት ጋር አብረን አንሰራም” በሚል የቀረበላቸዉን ጥሪ  አንፈልግም ቢለዉ እምቢተኛ የሆኑ እንደነበሩ አዉቃለሁ፡፡…. በወቅቱ ታጋዮቹ አንዳንድ አስተዳዳራዊና ፖለቲካዊና የጥበቃ ስራዎችን ከመስራት ዉጭ በአብዛኛዉ የሃላፊነት ቦታ ላይ የነበርንነዉ ከቀድሞ ሰራዊት የመጣነዉ ነበርን፡፡ ታጋዮቹ አየር ኃይሉ ዉስጥ የነበረዉ ስራ ዉስብስብ ስለሆነባቸዉ ይሁን አይሁን ባለዉቅም አንዳችም የስልጣን ጉጉት አልነበራቸዉም፡፡ እንዲያዉም እጅግ አሳፋሪ የሆነ የስልጣን ሽኩቻ የነበረዉ እኛ አካባቢ ነበር፡፡

* አየር ኃይልን የማጠናከር ጉዳይ በሚገባ ታስቦበት መሰራት የተጀመረዉ ገና ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የባህር ዳር አየር ጣቢያ ለአየር ኃይል አገልግሎት ሊሰጥ በማይችል ደረጀ ሙሉ በሙሉ የፈራረሰ ስለነበር በርከታ ስራዎችን በአጭር ጊዜ በመስራት ለአየር ኃይል አገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን የተደረገዉ ደግሞ ጦርነቱ ከመጀመሩ ሁለት ዓመት አስቀድሞ ነበር፡፡….በተለይ አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት ሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) በሃላፊነት ተመድበዉ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አየር ኃይሉን ለማጠናከር ያደረጉት ጥረት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከበርካታ አገሮች ፕሮፖዛል ይዘዉ እንዲመጡ በማስደረግ ሲደረግ በነበሩት በበርካታዎቹ ድርድሮችና ገለጻዎች ላይ ለመገኘት በመቻሌ ሁኔታዉን በሚገባ አስታዉሳለሁ፡፡

* በድርድሩ ወቅት በተለይ የሩሲያ ልኡካን ድሮ እንደለመዱት የተለያዩ ማግባቢያና መስፈራራያ ሰበብ በመደርደር በግርግር ቶሎ አስፈርመዉ ለመሄድ እንደጓጉ ያስታዉቅባቸዉ ነበር፡፡ የሚያነጋግራቸዉ ሰዉ ስለ አየር ኃይል ግንዛቤ የለለዉ ገና ከበረሃ የመጣ መሆኑንም በቂ መረጃ ይዘዉ የመጡ ይመስለኛል፡፡  መጀመሪያ አካባቢ የንቀት አይነት ሁኔታም ይታባቸዉ ነበር፡፡ የሚያነጋግሩት ሰዉ የዋዛ ሰዉ አለመሆኑን ሲረዱ ነበር ትንሽ አደብ መግዛት የጀመሩት፡፡

* የሻዕቢያ ፓይለቶች ከታወር ጋር የሚያደርጉትን የሬዲዮ ልዉዉጥ ማወቁ መረጃዉን የበለጠ ግልጽ አንደሚያደርግ በመታመኑ ንግግራቸዉን ለማዳመጥ (ሞኒተር ለማድረግ) የሚያስችለን አንድም ሬዲዮ በወቅቱ በአየር ኃይሉ ዉስጥ ተፈልጎ በመጥፋቱ ከሲቪል አቭዬሽን አሮጌ ሬዲዮ በዉሰት ከተገኘ በኋላ ነዉ ዛሬ አገር ዉስጥ የሌለዉ ኮ/ል ፋንታ ኦላና የተባለዉ ፓይለት ከደብረዘይት ተልኮ እያንዳንዱን ንግግራቸዉን በመከታተል የተሟላ ሪፖርት ያቀረበዉ፡፡ ከዚያ በኋላ ነዉ የአየር መከላከያ ጥበቃዉ በከፍተኛ ደረጃ መጠናከር እንዳለበት የተወሰነዉ፡፡

* አየር ኃይላችን ከራሱም አልፎ አለምአቀፍ ተልእኮም የተወጣ ከአፍሪካ ብቸኛዉ አየር ኃይል ለመሆኑ በኮንጎ በ1954 እና በድጋሚ በ1959 ዓ/ም ከስዊድንና ከህንድ አየር ኃይሎች ጋር እኩል ግዳጅ ተሰጥቶት በብቃት ተወጥቶ የተመለሰበት ከሀገር ዉጭ የተደረጉ ግዳጆች አንድ አብነት ነዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ሌሎች የአፍሪካ መንግስታት ጸጥታ ችግር ሲያጋጥማቸዉ የኢትዮጵያን አየር ኃይል እገዛ እንዲያደርግላቸዉ ትብብር በመጠየቅ እገዛ ሲደረግላቸዉ እንደነበር ይታወቃለ፡፡

* የሀገራችን ምድርን መሰረት ያደረገዉ አየር መከላከያ ከተቋቋመበት ከ1971 ዓ/ም መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ በአየር መከላከያ ግዳጅ አወጣጥ አንጻር በታሪካችን በኢትዮ-ኤርትራዉ ጦርነት ላይ ካከናወነዉ የተሳካ ግዳጅ ጋር የሚመጣጠን ሌላ ወቅት መጥቀስ አይቻልም፡፡ እንዲያዉም ምድርን መሰረት ያደረገዉና በሳም ሚሳይልና (SAM) በዘመናዊ የቅኝት ራዳሮች የተደራጀዉ ይህ የአየር መከላከያ ከፍል ከተመቋቋመበት ወቅት ጀምሮ በተግባር አቅሙን ለመፈተን ያስቻለዉ አንድም የተሳተፈበት ጦርነትም አልነበረዉም፡፡ በሶማሊያ ጦርነት ወቅት መጨረሻ አካባቢ የተመሰረተ ቢሆንም ጦርነቱ ተጠናቆ ስለነበር ዋነኛዉ ስራዉ ሆኖ የቆየዉ በጂግጂጋ ሰፍሮ የነበረዉን የኩባ ሰራዊት ከመጠበቅ የዘለለ አልነበረም፡፡

* በአየር መከላከያዉ ረገድም ለስኬታማነቱ ዋነኛዉ ማረጋጋጫ ከአይደሩ ጥቃት ወዲህ አንድም የጠላት አይሮፕላን የአየር ክልላችንን ጥሶ መግባት ቀርቶ ወደ ድንበራችን ከ40 ከ/ሜ የቀረበበት ሁኔታ አስከመጨረሻዉ አለመፈጠሩ ነዉ፡፡ በአንጻሩ የኛ ተዋጊ አይሮፕላኖች በኤርትራ አየር ክልል ለግዳጅ ሲሰማሩ በሱ-27 ኢንተርፕተሮች ጥበቃ ስለሚደረግላቸዉ የሻእቢያ አየር ኃይል ሊያደናቅፈን አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል የምድር ኃይል ሰራዊት አንድ ወይም ሁለት አጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ከጠላት የአየር ኃይል ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ነዉ ግዳጁን ሲወጣ የነበረዉ፡፡

* ከሁሉም በላይ ለአየር ኃይላችን ድክመቶች ዋነኛ ምክንያት የሚመስለኝ በደርግ ግዜ የነበረዉ አየር ኃይል ወደ መጨረሻዉ አካባቢ በብዙ ረገድ ኃይሉ እየተመናመነ በመምጣቱ ክፉኛ ተዳክሞ የነበረበትና በስም ብቻ ካልሆነ በስተቀር የዉጭ ወረራን ለመመከት የሚያስችለዉ ተጨባጭ የሆነ አቅም ያልነበረዉ መሆኑ …. በዚህ ላይም በደርግ መዉደቂያ አካባቢ በቁጥር 22 የሚሆኑ አይሮፕላኖቹ ወደ ዉጭ ሀገር በሽሽት ሂዴት ስለተወሰዱ አየር ኃይሉ በተጨባጭ የነበረዉ አቅም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡

* ሀገራችን በደርግ ዘመንም ቢሆን ጸረ-ራዳር ሚሳይል የተገጠመለት አይሮፕላን አልነበራትም፡፡  ጸረ- ራዳር ሚሳይል የተገጠለት  አይሮፕላን መኖር  ዋናዉ ፋይዳ ኢላማን የመደምሰስ ዕድልን ከፍተኛ ማድረግ መቻሉ ብቻ ሳይሆን የኛን ፓይለቶችና አይሮፕላኖች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ማድረግ ስለሚያስችል ጭምር ነዉ፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት አይሮፕላኖች ኖረዉን ቢሆን ኖሮ አንድም የኤርትራን የቅኝት ራዳርና ሚሳይል መሪ ራዳር ባላስተረፍን ነበር፡፡

* በጄ/ል አበበ ብርታት ሱ-27 የተባሉ ዘመናዊ የኢንተርርሰፕተር አይውሮፕላኖችን መታጠቅ ችለናል፡፡ በተጨማሪ እነዚህኑ አይሮፕላኖችን ወደ ኢላማቸዉ ለመምራት የሚያገለግሉና እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ግራዉንድ ኢንተርሴፕሽን ራዳሮችን ለመታጠቅ በቅተናል፡፡ እንደዚሁም በሀገራችን የአየር ኃይል ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑትን የሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ ጦርነት መረጃ ማሰብሰቢያ መሳሪያዎችን (electronic intelligence) በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ተገዝተዉ በጦርነቱ ላይ ከፍተኛ አገልግሎት መስጠታቸዉ ይታወቃል፡፡

* ገና ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ አየር ኃይሉ ላይ ጥሩ ያልሆነ አመለካከት እንዳለ ይሰማል፡፡ እምነት የማይጣልበትና አደገኛ ቢያንስ አጠራጣሪ ተቋም ተደርጎ እንደሚታሰብም አዉቃለሁ፡፡ ይሄ አመለካከት ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ የነበረና በደርግ ግዜ ተጠናክሮ የቀጠለ ዛሬም ሊቀረፍ ያልቻለ ስር የሰደደ አመለካከት ነዉ፡፡ በአየር ኃይል አመራርነት የሚመደብ ሰዉ እንደ ጄ/ል አበበ(ጆቤ) ዓይነት ተደማጭነት ያለዉ ሰዉ ካልሆነ በስተቀር የበላይን አንድ ነገር ጠይቆ ለማስወሰን እንደሚቸግረዉ በተግባር ያየነዉ ነዉ፡፡

* ሻዕቢያ አሰቀድመዉ እንደገመቱት ከጥቂት ሳምንታት ዝግጅትግዜ በኋላ የኢፌድሪ አየር ኃይል ከሞላ ጎደል ዝግጁ መሆኑን በመረዳታቸዉ አጉል መንፈራገጥ ለመላላጥ እንዳይሆንባቸዉ በመስጋት አየር ኃይላችን በደረሰበት ላይደርሱና የአየር ክልላችንንም ድጋሚ ላይደፍሩ የተማማሉ ይመስል ይሄዉ አስከዛሬ ወደ ድንበራችን ዝር ሳይሉ ቆይተናል፡፡ ራሳችንን በሻዕቢያ ቦታ አስቀምጠን ስናየዉ በወቅቱ የሻእቢያ አየር ኃይል ድክመት የነበረዉ እኛ ላይ ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩ ሳይሆን ለዚህ ዓላማ እዉን መሆን የሚያበቃዉን ትጥቅ (አይሮፕላን) ያልነበረዉ መሆኑ ነዉ፡፡ በኃላ እንዳደረገዉ በወቅቱ ሚግ -29  አይሮፕላኖች ቢኖሩት ኖሮ በኛ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርሱብን እንደሚችሉ ለመረደት አያዳግትም፡፡

* በዚህ ምክንያም አየር ኃይላችን በጠላት ላይ ካደረሰዉ አካላዊ ጉዳት (physical damage) ይልቅ በጠላት ሰራዊትና አመራር ላይ ያደረሰዉ ስነሊቡናዊ ጉዳት (psychological damage) እጅግ ከፍተኛ እንደነበር አምነን ከመቀበል ዉጭ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ለወገን ሰራዊት ሞራል ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉም በበጎ ጎን ሊጠቀስ የሚገባዉ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን የአየር ኃይልን ሚና አለቅጥ አጋኖ ማየትም ሆነ ሚናዉን አሳንሶ የማየት ጉዳይ ሁለቱም አመለካከቶች ጎጂ በመሆናቸዉ ሊስተካከሉ ይገባል፡፡

—-

መግቢያ

በዚህች ርእስ ስር ከጦርነቱ በፊት በአዲስ መልክ በመደራጀተ ላይ የነበረዉ አየር ኃይላችንን ለድንገተኛዉ ጦርነት ለማብቃት ስለተደረጉ ጥረቶች፤ በጦርነቱ ላይ የነበረዉ ተሳትፎ፤በጦርነቱ ላይ በተለይ አየር ኃይላችን ላይ የታዩ ጠንካራና ደከማ ጎኖችና ለወደፊቱም ለሚጠብቀዉ  ከባድ ሃላፊነት ማድረግ በሚገባዉ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ነዉ፡፡

መቼም በዚህች አጭር ማስታወሻ ላይ የአየር ኃይሉን ዝርዝር የግዳጅ አፈጻጸም ለመተረክ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን እኔም የዚያ ዉጥን የለኝም፡፡ ይሄን መሰሉ ስራ በቡድን ተቀናጅቶ መሰራት ያለበት ግዙፍ  ስራ ስለሆነ እኔ አልሞክረዉም፡፡ እኔ ዋነኛ ትኩረት የማደርገዉ በዚያ ያለበቂ ዝግጅት በጥድፊያ ወደ ጦርነት ተገብቶ የሀገር ሉአላዊነት ለማስከበር በተደረገዉ የመከላከያ ሰራዊታችን እልህ አስጨራሽና አስመስጋኝ ተጋድሎ ዉሰጥ የአየር ኃይላችንን አስተዋጽኦ በመጠኑ ለማዉሳት ነዉ፡፡

አየር ኃይሉ በጦርነቱ ላይ ከአርሚዉ የበለጠ ወሳኝ ስራ ሰርቷል ከሚሉ ቅዠታሞች ጀምሮ አየር ኃይሉ በጦርነቱ አንዳችም የረባ ስራ አልሰራም ለማለት የሚቃጣቸዉ አንዳንድ ሰዎች ሃላፊነት በጎደለዉ መንፈስ ሲሰነዝሩ የነበረዉን የተዛባ አመለካከት ለማቃናት መሞከ ተገቢ መስሎ ሰለሚታየኝ በዚያ ላይም የተሰወሰነ ሙከራ ማድረጌ አይቀርም፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገራችን ከፍተኛ ወታደራዊ  አቅም እንዳላት ከምትታወቀዉ ግብጽ ጋር ወደፊት በሆነ አጋጣሚና ምክንያት ወደ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚለዉን ግምት ታሳቢ በማድረግ የጦር ኃይላችንን በተለይም የአየር ኃይላችን ሁለንተናዊ አቅሙን ከአሁኑ ለማሳደግ ጥረት መደረግ እንደሚገባ ለማስገንዘብ ጭምር ነዉ፡፡

ይህ ጽሁፍ ከዚህ በፊት በሌሎች ክፍሎች በጦርነቱ ላይ ከሰጠሁት አስተያየቶች ጋር በአንድነት የሚታይና የዚያ ቀጣይ ክፍል ተደርጎ እንዲወሰድ አንባቢን በቅድሚያ ለማሳሳብ እወዳለሁ፡፡

1/ ከጦርነቱ በፊት መንግስት አየር ኃይልን ከወደፊቱ ስትራቴጂያዊ ስጋት እንጻር በጠንካራ መሰረት ላይ መልሶ ለማቋቋም ሲያደርግ የነበረዉ ጥረት

የኤርትራ ወረራ ድንገተኝነቱ ለምድር ኃይሉ ብቻ ሳይሆን ለአየር ኃይሉም ጭምር እንደሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ ሀገሪቱ ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን መከላከያ ኃይል ሳታዘጋጅ በመቆየቷ ለአደጋ ተጋልጠንና ለጥቃት ተመቻችተን ተቀመጥን እየተባለ በመንግስት ላይ ሲሰነዘረዉ የቆየዉ ትችት በዋነኛነት ጎልቶ ይሰማ የነበረዉ አየር ኃይሉን በሚመለከት ነዉ፡፡

ትችቱ ከምድር ኃይሉ ይልቅ በአየር ኃይሉ ላይ መበርታቱ ያለ ምክንያትም አይደለም፡፡ ሁለት ምክንያቶችን መገመት እችላለሁ፡፡

አንደኛ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የሀገሪቱን መከላከያ አፈረሰ የሚለዉ ስሞታ ዋነኛዉ መነሻ አየር ኃይሉን የሚመለከት መሆኑና

ሁለተኛ ደግሞ አየር ኃይል በቅብብል በርካታ ዓመታትን በሚጠይቅ ጥረት የሚገነባ እንጂ በየግዜዉ እየፈረሰና እንደገና የሚደራጅና በአጭር ግዜ ተገቢዉን ብቃት ሊይዝ የማይችል በመሆኑና አየር ኃይሉ ከአፍሪካ ቀደምት አየር ኃይል ከመሆኑ አንጻር በርካታ አኩሪ ስራ የሰራ ሆኖ እያለ ለፖለቲካ ፍላጎት ተብሎ እንዲፈርስ ተደርጓል የሚለዉ ቁጭት የወለደዉ አመለካከት መበርታቱ ነዉ፡፡

ምክንያቱም የኢህአዴግ በአብዛኛዉ የቀድሞ ሰራዊትን በማያካትት መልኩ ያደራጀዉ የምድር ኃይል ሰራዊት ኤርትራም ሆነች ሌሎች አጎራባች አገሮች ከነበራቸዉ ሰራዊት በምንም መልኩ የማይተናነስ ስለነበር ኢህአዴግ የሀገሪቱን መከላከያ አፈረሰዉ የሚለዉ ትችት በዋነኛነት አየር ኃይሉን በሚመለከት እንደሆነ ይታወቃልና፡፡ የባህር ኃይል ጉዳይ እንደሆን ከባህር መዉጫ በር ጋር በቀጥታ የተቆራኘ በመሆኑ ኤርትራ ስትገነጠል አብሮ ያከተመና ያለቀለት ጉዳይ ስለነበር የባህር ኃይል መፍረስ ጉዳይ ብዙም እንደ ጥያቄ የተነሳ አይመስለኝም፡፡

ስለዚህ ለጦርነቱ ድንገተኝነትና አለመዘጋጀታችን ጉዳይ ሲነሳ አብዛኛዉ ህብረተሰብ ቀድሞ የታየዉ አየር ኃይሉን መሆኑ እርግጥ ነዉ፡፡ በተለይ የግንቦት 28 በመቀሌ ህጻናት ላይ የደረሰዉን ድርጊት የሰሙ ሁሉ እርር ድብን ቢለዉ ያዘኑበት ዋነኛዉ መነሾ ኢህአዴግ ያለአንዳች ምክንያት የ70 ዓመት አድሜ የነበረዉን አንጋፋ አየር ኃይል አፍርሶ ገና ትላንት ለመቋቋም ዳዴ በማለት ላይ ባለ ጀማሪ አየር ኃይል ተደፍረን ህዝባችንን ለጥቃት እጋለጠን በሚል ነበር፡፡

አንድ መታወቅ ያለበትና መካድም የማይገባ ነገር ቢኖር በአጭር ግዜ ለሚያጋጥም ጦርነት የሚሆን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚበላና ለአጎራባች አገሮችም የስጋት ምንጭ የሚሆን ግዙፍ ሰራዊት የማቋቋም ፍላጎት በመንግስት ደረጃ ገና ከመጀመሪያዉ አለመኖሩ እርግጥ ቢሆንም ነግር ግን ለሀገሪቱ ከስትራቴጂያዊ ስጋት አንጻር የግድ የሚያስፈልጋትን ያህል ዘመናዊ የሆነ መከላከያ ኃይል በሂዴት ለመገንባት መንግስት ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ ጥረት ሲያደርግ እንደነበረ ነዉ፡፡

መንግስት ከጦርነቱ በፊት ጀምሮ ለመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር አንዱ ማሳያ ደርግ እንደ ስርአት ሲወድቅ አብሮ ከተበተነዉ ከቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሰራዊት ዉስጥ ወታደራዊ ብቃቱና ፈላጎቱ ያላቸዉን በተለይ ከፍተኛ መኮንኖችን መልምሎ አዲሱን መከላከያ ሰራዊት በማደራጀትና በማሰልጠን ረገድ የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረጉንና በዚህም በርካታ አስመስጋኝ ስራዎች መሰራታቸዉ ነዉ፡፡

በባለፈዉ መንግስት የጀኔራልነት ማዕረግ የነበራቸዉ ከፍተኛ መኮንኖች ሳይቀሩ የኢፌዴሪን መከላከያ በማቋቋሙ ስራ ላይ ተጠምደዉ ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በርግጥ አንዳንደቹ “ከዚህ ቀደም ከተዋጋነዉ የወያኔ ሰራዊት ጋር አብረን አንሰራም” በሚል የቀረበላቸዉን ጥሪ  አንፈልግም ቢለዉ እምቢተኛ የሆኑ እንደነበሩ አዉቃለሁ፡፡

ከዚያ ዉጭ በሺህ የሚቆጠሩ ከቀድሞ ሰራዊት ተመልምለዉ የገቡ እንደነበር በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ በተለይ በአየር ኃይሉ ዉስጥ በአይሮፕላን ጥገና፤በበረራ፤በዘመቻ፤በአየር መከላከያና በሌሎች የአመራርና ስታፍ ሃላፊነት ስራዎች ጭምር በርካታ የቀድሞ ሰራዊት መኮንኖችና የበታች ሹሞች (ቴክኒሻኖች) ነበሩ፡፡ ዛሬም ድረስ በከፍተኛ የአመራር እርከን ደረጃ የሚገኙና ለጄነራልነት ማዕረግ የበቁ መኮንኖችም አሉ፡፡

ገና ከኤርትራ ጋር የጦርነት ወሬዉ እንኳን ባልነበረበትና እንዲያዉም የጦፈ ወዳጅነት ላይ በነበሩበት የሰላም ወቅት (ማለትም ከጦርነቱ አምስት ዓመት ቀደም ብሎ) ጀምሮ እኔ ራሴ የኮሚቴ አባል በነበርኩበትና ከቀድሞ ሰራዊት መካካል ብቁ የሆኑትን ወደ ስራ የመመለስ ስራ እንዲሰራ በተቋቋመዉ ኮሚቴ በኩል በርካታ መኮንኖችና ቴክኒሻኖች ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉን አስታዉሳለሁ፡፡

በአየር ኃይሉ ዉስጥ በተለይ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ በጣም ዉሱን በሆኑ የስራ መስኮች ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዉ የሥራ መደብና የሃላፊነት ቦታ ተይዞ የነበረዉ በቀድሞ ሰራዊት አባላት እንደነበር ማንም የሚክደዉ አይደለም፡፡ በአየር መከላከያም ሆነ በአቭዬሽን ሙያ ፓይለቱ ቴክኒሻኑም ሆነ የዘመቻ፤ የአስተዳደርና የጥገና ሙያተኛዉ ሁሉ የተለየ የጤና እክል፤የወንጄል ሪኮርድና የአቅም ችግር ከነበረባቸዉና እንዲሁም ራሳቸዉ በፈቃዳቸዉ አንፈልግም ብለዉ ከቀሩት በስተቀር ወደ ስራ መመለስ ሲገባዉ ያልተመለሰ ሰዉ አልነበረም፡፡

በወቅቱ ታጋዮቹ አንዳንድ አስተዳዳራዊና ፖለቲካዊና የጥበቃ ስራዎችን ከመስራት ዉጭ በአብዛኛዉ የሃላፊነት ቦታ ላይ የነበርንነዉ ከቀድሞ ሰራዊት የመጣነዉ ነበርን፡፡ ታጋዮቹ አየር ኃይሉ ዉስጥ የነበረዉ ስራ ዉስብስብ ስለሆነባቸዉ ይሁን አይሁን ባለዉቅም አንዳችም የስልጣን ጉጉት አልነበራቸዉም፡፡ እንዲያዉም እጅግ አሳፋሪ የሆነ የስልጣን ሽኩቻ የነበረዉ እኛ አካባቢ ነበር፡፡

የቀድሞ ስርአት ተጠቃሚ በመሆናቸዉ መኮንን የሚባል በዓይናችን አታሳዩን ከሚለዉ ጀምሮ የኢሠፓ ተራ አባላት የነበርነዉን ሁሉ ካላባረራችሁልን የሚሉ ባለሌላ ማእረግተኞች ብዙ ነበሩ፡፡ ሲቪሉም አካባቢ ፓይለት እንዳንሆን ተከልክለናል ዋና ክፍልም ሆነ መምሪያ ሃላፊ የሚሆኑት መኮንንች ብቻ ናቸዉ የሚሉ ሲቪሎችም ነበሩ፡፡ ከመኮንኖች ይልቅ እኛ ነን የበለጠ እዉቀት ያለን የሚሉ የበታች ሹሞች ብዙ ነበሩ፡፡

ታጋዮቹ ይሄን ሁሉ የኛን አስቀዬሚ ክስና ጭቅጭቅ በየዕለቱ መዳኘት እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸዉ ነበር፡፡ ጥሩነቱ ታጋዮቹ ትንሽ እየቆዩ ሲሄዱና እያንዳንዱን ሰዉ በስራዉ መገምገም ሲጀምሩ የስራዉን ባህሪይም እየተረዱ ሲመጡ ሲቀርብላቸዉ የነበረዉ ዉንጀላና ክስ ሁሉ ሃሰት መሆኑን ለመረዳት ችለዉ ነበር፡፡ በወቅቱ አየር ኃይልን ለማቋቋም ተመድበዉ የነበሩት ጄ/ል ሰለሞን በየነ የዚህ ዓይነቱን የማይረባ ክስ እየሰሙ ለማርገብ ብዙ ቢሞክሩም ቶሎ መስመር የያዘ አልነበረም፡፡

በእዉነቱ የቀድሞ ሰራዊት መካካል በርካታ ድስፕሊንና ስነምግባር የነበረቸዉ ብዙ ቢኖሩም በቁጥር ቀላል የማይባሉት እጅግ አሳፋሪ ባህሪይ የነበራቸዉ ነበሩ፡፡ ይሄን ሁሉ እያዩ ታጋዮቹ በሁኔታዉ ከመገረም በስተቀር ማንንም ከማንም ሳይለዪ ሁላችንንም ያለ አንዳች አድሎ በአንድ ዓይን ነበር የሚያዩት፡፡

ይህቺን ነገር ማስታወሴ በዚያን ወቅት የነበረዉን አስቀያሚ የሆነ የእርስበርስ ዉዝግብ ለማስታወስ ፈልጌ አይደለም፡፡ እሱ ራሱን የቻለ መጽሀፍ ይወጣዋል፡፡ ከዚያ ይልቅ መጥቀስ የፈለኩት በአየር ኃይሉ ዉስጥ አብዛኛዉ ሃላፊነት ቦታ የተያዘዉ ከቀድሞ ሰራዊት በመጣነዉ ሲሆን እንደዚያም ሆኖ ስልጣን አነሰን እያልን ስናስቸግር የነበርነዉ እኛ እንጂ እነሱ ታጋዮቹ እንደሆን ለስልጣን ጉጉት ጭራሽ ደንታም አልነበራቸዉም፡፡

ለማንኛዉም መንግስት እጅግ በርካታ የቀድሞ የአየር ኃይል አባላትን እንዲገቡ ማድረጉ እየታወቀ የቀድሞ ሰራዊትን ወደ ስራ እንዳይገቡ አድርጎ አየር ኃይሉን አዳክሞ ለጠላት ጥቃት አጋለጠን የሚለዉ ክስ ፍጹም መሰረተቢስ ክስ እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ እወዳለሁ፡፡

የጦር መሳርያንም በሚመለከት ኢህአዴግ የተረከበዉን እንዲጠገን ከማስደረግ ዉጭ ሊጠቀስ የሚችል የፈጠረዉ ችግር ነገር አልነበረም፡፡ ደርግ ሲወድቅ ኢህአዴግ ከተረከባቸዉ ወይም በግቢዉ ዉስጥ ካገኛቸዉ የአየር ኃይሉ ትጥቆች መካከል በደህና ሁኔታ ላይ ነበሩ ሊባሉ የሚችሉት ከቁጥር የሚገቡ አልነበሩም፡፡ አብዛኛዉ ትጥቅ በየስርቻዉ እንዳልባሌ ነገር የተጣለ ነበር፡፡

በአየር ኃይሉ ዉስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ ዉጭ ሆነዉ የቆዩ አይሮፕላኖች፤ራዳሮችና ሌሎች የአየር መከላከያ ትጥቆችን ወደ ስራ ለመመለስ ሰፊ ስራ ከመሰራቱም ሌላ በእጅ የነበሩትን ትጥቆች ዘመኑ ወደሚፈልገዉ ደረጃ ለማሳደግ (አፕግሬድንግ) እና ከተቻለም አዳዲስ ራዳሮች፤ሚሳይሎችና አይሮፕላኖችን ለመታጠቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዉጭ ሀገር ባለሙያዎችን በማስመጣት ጭምር  ጥናቶችና ድርድሮች በሰፊዉ ሲደረጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አየር ኃይሉን ለማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፕሮፖዛል ይዘዉ እንዲመጡ እየተደረጉ ከምስራቅ አዉሮፓ እንደ ቡልሪያ፤ሩሲያ፤ኡክሬይን፤ቤላሩሲያ ወዘተ የመሳሰሉት እንደሁም ከኢስራኤልና ከፈረንሳይ ጋር ንግግሮች ሲደረጉ እንደነበር የሚታወስ ነወ፡፡ በተለይ ከጦርነቱ መነሳት ቀደም ብሎ ሚግ -21 እና ሚግ -23 አይሮፕላኖችን የማዘመንና ጠግኖ ወደ ስራ ለመመለስ ታስቦ ከአስራኤል መንግስት ጋር ከ1988 ጀምሮ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነበር፡፡

ሆኖም ሀገሪቱ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት ስለገጠማት እስራኤሎች ገንዘብ እንደሌለን ሲያዉቁ በመሃል ስራዉን አቋርጠዉ ለመዉጣት ተገደዋል፡፡ ባጠቃላይ በደርግ መዉደቅና ጦርነቱ በተነሳበት ወቅት መካከል የነበረዉ ጊዜ በጣም አጭርና በቂ ያልነበረ በመሆኑ የመንግስትን ጥረት ፍሬዉን ለማዬት አላስቻለንም ሊባል ይችል ይሆናል እንጂ በቂ ጥረቶች አልተደረጉም የሚያሰኝ ግን አይደለም፡፡

የሀገሪቱን መከላከያ ለመገንባት ሲደረግ የነበረዉ ጥረትን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የአየር ኃይል አባል ስለነበርኩ ትኩረቴን በይበልጥ እዚያ ላይ አድርጌ የማዉቀዉን ብገልጽ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

አየር ኃይልን የማጠናከር ጉዳይ በሚገባ ታስቦበት መሰራት የተጀመረዉ ገና ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የባህር ዳር አየር ጣቢያ ለአየር ኃይል አገልግሎት ሊሰጥ በማይችል ደረጀ ሙሉ በሙሉ የፈራረሰ ስለነበር በርከታ ስራዎችን በአጭር ጊዜ በመስራት ለአየር ኃይል አገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን የተደረገዉ ደግሞ ጦርነቱ ከመጀመሩ ሁለት ዓመት አስቀድሞ ነበር፡፡

በወቅቱ በባህርዳር አየር ምድብ በሃላፊነት ተመድቤ ለሶስት ዓመታት ያህል የቆየሁበት በመሆኑ በሚገባ አስታዉሳለሁ፡፡ በወቅቱ አየር ጣቢያዉን የማዘጋጀት ስራ ቀንና ሌሊት በጥድፊያ ተሰርቶ ዝግጁ እንዲሆን መደረጉ ለኤርትራ ጥቃት ታስቦ አንዳልነበር መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ከኤርትራ ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት ላይ ስለነበርን ስለ ኤርትራ ስጋት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ከኤርትራ ይልቅ መቃቃር ወይም ግጭት የነበረዉ ከሱዳን ጋር ስለነበር ለዚያ ተብሎ እንደሆነ በርግጠኝነት አስታዉሳለሁ፡፡

ልክ እንደ ባህርዳሩ ሁሉ የመቐለዉም የአየር ማረፊያም አስፈላጊዉ የማስፋፋትና የማሻሻል ስራ ተሰርቶ ለአየር ኃይልም ጭምር እንዲያገለግል ተደርጎ የተዘጋጀዉና ተዋጊ ጄት ማሳረፍ መቻል አለመቻሉ በተግባር በበረራ የተረጋገጠዉም ከጦርነቱ አንድ ዓመት አስቀድሞ ነዉ፡፡ የመቀሌም ሆነ የባህርዳር አየር ጣቢዎች (አየር ምድቦች) በጦርነቱ ወቅት የሰጡትን የማይተካ ሚና ስናስታዉስ እነዚህ ጣቢያዎች ከጦርነቱ በፊት ዝግጁ ባይሆኑ ኖሮ በጦርነቱ ወቅት አየር ኃይላችን ተመልካች ከመሆን ዉጭ ሌላ አማራጭ አይኖረዉም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከነዚህ ከሁለቱ የአየር ጣቢዎች ዉጭ ካሉት ሌሎች አየር ጣቢያዎች  አይሮፕላን እያስነሱ በኤርትራ አየር ክልል ዉስጥ ግዳጅ ፈጽሞ ለመመለስ ርቀቱ ስለማይፈቅድ ነዉ፡፡

አየር ኃይሉን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቋቋም መንግስት ፍላጎት እንደነበረዉ የሚያሳዉ የሀገሪቱ ባለስልጣናት አየር ኃይል እየተገኙ ሲጎበኙና መመሪያ ሲሰጡ እንደነበረ ስለማዉቅ ነዉ፡፡ በዚሁ መሰረትም ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አየር ኃይልን እንደገና በተጠናከረ ሁኔታ ለማቋቋም እየተደረጉ የነበሩትን ስራዎች በአካል ተገኝተዉ በመጎብኘት ስራዉ የሚጣደፍበትን መመሪያ ይሰጡ እንደነበር ሳስታዉስ ከነዚህ ባለስልጣናት መካከል አሁን በህይወት የለሉት የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ የሽግግሩ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ፤ የቀድሞዉ ፓርላማ አፌጉባኤ አቶ ዳዊት ዮሀንስ፤ የሽግግሩ ዘመን መከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ፤ ከጦርነቱ ቀደም ብሎና በጦርነቱ መካከልም መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ወዘተ ይገኙበታል፡፡

በተለይ አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት ሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) በሃላፊነት ተመድበዉ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አየር ኃይሉን ለማጠናከር ያደረጉት ጥረት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከበርካታ አገሮች ፕሮፖዛል ይዘዉ እንዲመጡ በማስደረግ ሲደረግ በነበሩት በበርካታዎቹ ድርድሮችና ገለጻዎች ላይ ለመገኘት በመቻሌ ሁኔታዉን በሚገባ አስታዉሳለሁ፡፡

በወቅቱ አዲስ መንግስት መቋቋሙን የሰሙ ሀገሮች ሁሉ ላለመቀደም እየተሸቀዳደሙ ነበር የሚመጡት፡፡ ትልቁ ፈተና የነበረዉ በመንግስት በኩል ፍላጎት ያለመኖር ሳይሆን የዉጭ ልኡካኑ የሚጠይቁትን ያህል የዉጭ ምንዛሪ በወቅቱ ለማሟላት መንግስት አለመቻሉ ነበር፡፡

በድርድሩ ወቅት በተለይ የሩሲያ ልኡካን ድሮ እንደለመዱት የተለያዩ ማግባቢያና መስፈራራያ ሰበብ በመደርደር በግርግር ቶሎ አስፈርመዉ ለመሄድ እንደጓጉ ያስታዉቅባቸዉ ነበር፡፡ የሚያነጋግራቸዉ ሰዉ ስለ አየር ኃይል ግንዛቤ የለለዉ ገና ከበረሃ የመጣ መሆኑንም በቂ መረጃ ይዘዉ የመጡ ይመስለኛል፡፡  መጀመሪያ አካባቢ የንቀት አይነት ሁኔታም ይታባቸዉ ነበር፡፡  የሚያነጋግሩት ሰዉ የዋዛ ሰዉ አለመሆኑን ሲረዱ ነበር ትንሽ አደብ መግዛት የጀመሩት፡፡

ማስፈራራቱንና አጉል ማግባባቱን ተወት አድርገዉ ወደ ልምምጥና ልመና መሰል ነገር ጀምረዉ ነበር፡፡ በወቅቱ ሩሲያዉያን ራሳቸዉ ከፍተኛ ችግር ዉስጥ ስለነበሩ እኛን ከመለማመጥ ዉጭ ሌላ አማራጭ አልነበራቸዉም፡፡ ለማንኛዉም ሩሲያዉያኑ በወቅቱ ወታደራዊ ማእረጉን  እንኳን በሚገባ ሳያዉቁ ሲሽቆጠቆጡለት የነበረዉ ያ ሰዉ ጆቤ ነበር፡፡

Photo - Sukhoi Su-27 military jet of Ethiopian Air Force
Photo – Sukhoi Su-27 military jet of Ethiopian Air Force

2/ የአየር ኃይላችን በጦርነቱ ላይ የነበረዉ የግዳጅ አፈጻጸም በአጭሩ 

ከኤርትራ ጋር አየር ኃይሉ ስለአከናወነዉ የግዳጅ አፈጻጸም ለማዉሳት ከመሞከሬ በፊት በቅድሚያ በጦርነቱ ለተገኘዉ ዉጤት ሁሉ መሰረት የሆኑትን የተሰሩ ሰፊ የዝግጅት ስራዎችን በመጠኑ መጥቀሱ የግድ ነዉ፡፡ ጦርነቱ የተደረገዉ የተመቻቸ ሁኔታ በነበረበት ወቅት ስላልነበረ ዝም ተብሎ የተገባበት ጦርነት አልነበረም፡፡ የጠላት ወረራ ማድረግ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች ይህ ቀረሽ የማይባል የዝግጅት ስራዎች ሌትና ቀን ያለእረፍት ተሰርተዋል፡፡ እነዚህን በመጠኑም ቢሆን ሳይጠቅሱ ስለሌላዉ ግዳጅ አፈጻጸም ማዉሳት ተገቢ አይሆንም ፡፡

ከኤርትራ ወረራ ከተሰማ በኋላ በተለይ በመቐለና ባህርዳር ከዚህ በፊት ያልነበሩና ለግዳጅ የግድ መሟላት የነበረባቸዉ የኢንፍስትራክቼር ግምባታ ስራዎች በስፋት ተሰርተዋል፡፡ በሰሜን አየር ምድብም ሆነ በባህር ዳር የተሰሩ የዝግጅት ስራዎች እጅግ በርካታና እልህ አስጨራሽ ነበሩ፡፡

ለአየር ምድቦች፤ ለሚሳይል ክንፎችና አስኳሮኖች ማዘዣ ጣቢያ ግንባታ፤የአይሮፕላን መደበቂያ ባንከሮች፤ ከፍተኛ የመያዝ  አቅም ያላቸዉ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች፤ መጠጊያ መንገዶች ተለዋጭ ሳይትና፤ ለሰራዊቱ መመገቢያና መጠለያዎች፤ በርካታ ለሆኑ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች መትከያ የሚሆን ሳይት መረጣና መጠጊያ መንገድ አዘጋጅቶ ጠርጎና ደልድሎ በማዘጋጀት መሳሪያ አጓጉዙና ጠግኖ በመትከል ከዚያም ምድበተኛዉን አሰልጥኖ ለግዳጅ ማብቃት ወዘተ የመሳሰሉ አሁን ሲነገር እንደሚቀለዉ ሳይሆን አጅግ ፈታኝ የሆኑ ሰራዎች ተሰርተዋል፡፡

በተለይ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች ከየጥሻዉ ተለቅመዉ በነበረዉ ጥድፊያ ያለአንዳች ጥገና ወደ ግንባር የተላኩ ስለነበሩ በዉጊያ ሁኔታ ዉስጥ ሆኖ ጠግኖ ማዘጋጀት የቱን ያህል ከባድ እንደነበር በስራዉ የተሳተፉት በሚገባ ያስታዉሱታል፡፡ ግማሹ መሳሪያ ከጂግጂጋ፤ ሌላዉ ደግሞ ከአሶሳና ከመሃል አገር አጓጉዞ ግንባር አድርሶ ጠግኖ ማዘጋጀት እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ለአይሮፕላኖች የበረራ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የበረራ ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎች እንደ አዲስ መዘጋጀት ነበረባቸዉ፡፡ ከምድር ወደ አየር ከፓይለቱ ጋር በርቀት መነጋገር የሚያሰችል የተሟላ የግኑኝነት መሳሪም አልነበረንም፡፡

ከመረጃ አንጻርም የሻዕቢያ የአየር ኃይል ስለታጠቀዉ የዉጊያ አይሮፕላኖች ዓይነትና ብዛት ሲያከናዉኑ ስለነበረዉ የበረራ እንቅስቃሴአቸዉ የተሟላ መረጃ የነበረን አይመስለኝም፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያትም አጠቃላይ የመዘናጋታችን ነገር እንዳለ ሆኖ በተለይ ኤርትራን በሚመለከት  እንኳን በጠላትነት መፈረጅ ይቅርና በአጠራጣሪ ወዳጅ ደረጃ ያልተፈረጀች በመሆኗ ስለኤርትራ ወታደራዊ ቁመና ለማወቅ የተደረገ አንዳችም ሙከራ አልነበረም፡፡

በዚህ ምክንያትም ምናልባት ኤርትራ የአዲስ ሰልጣኞች በረራ ስልጠና ከማድረግ ባለፈ ለግዳጅ ወይም ለጦርነት የሚያዘጋጃቸዉ በረራ ዝግጅት እያደረጉ ስለመሆናቸዉ ማንም የጠረጠረ አይመስለኝም፡፡  ለመጀመሪያ ግዜ አድዋ አዲበራ አካባቢ ቅኝት ራዳር ተክለን የኤርትራ አይሮፕላኖች እያደረጉት የነበረዉን የግዳጅ ዝግጀት በረራ እንቀስቃሴ ያገኘነዉን መረጃ በቀጥታ ወደ አየር ኃይል ማእከላዊ ማዘዣ ጣቢያ (ደብረዘይት) እንዲተላለፍ ባደረግንበት ወቅት የአየር ኃይሉ አዛዥ ጄ/ል አበበ በዚያን ግዜ የተሰማቸዉን ስሜት ሳስታዉስ ስለኤርትራ አየር ኃይልና ሲያደርጉ ስለነበረዉ የበረራ እንቅስቃሴ እንግዳ መሆናችንን ያመላከተ ነበር፡፡

በወቅቱ በቦታዉ ሆኜ (አዲቤራ) ራዳሩን ስራ አስጅምሬ ወደ መቐለ እንደተመለስኩ ጆቤ ይፈልጉሃል ተብዬ በሬዲዮ አግኝቻቸዉ በቁጣ “እየቀለዳችሁ ነዉ ወይንስ ምንድነዉ ነገሩ፡፡ ምንድነዉ እያስተላለፉ ያሉት? ሲሉኝ ጭንቀታቸዉ ስለገባኝ መረጃዉ ትክክል እንደነበር ለማስረዳት ብሞክርም በጭራሽ አምነዉ ለመቀበል ባለመቻላቸዉ በቀጥታ ወዲያዉኑ ወደዚያዉ ተመልሼ እንድሄድና እኔ ባለሁበት እንዲተላለፍ ባዘዙኝ መሰረት ተመልሼ መሄድ የግድ ነበር፡፡

ታዲያ እዚያ ከደረስኩ በኋላ ከበፊቱ በበለጠ በርከት ባለ አይሮፕላን እየተደረገ የነበረዉን ልምምድ በቀጥታ ስናስተላልፍ ቆይተን ነዉ ስለ ኤርትራ አየር ኃይል ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ስለ መሆናቸዉ ግንዛቤ የተያዘዉ፡፡ ከዚያ በፊት የዚያ ዓይነት መረጃ አልነበረም፡፡ ስለ ኤርትራ አየር ኃይል ከቁምነገር ቆጥሮ ማንም የተጨነቀበት አልነበረም፡፡ የነበረዉ መረጃም ብዙም ያልተሟላ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ያልተጠበቀ ስለነበረ ነዉ መሰለኝ በሁሉም አመራሮች ዘንድ ትንሽ የመሸበር ነገር ተፈጥሮ ነበር፡፡

የሻዕቢያ ፓይለቶች ከታወር ጋር የሚያደርጉትን የሬዲዮ ልዉዉጥ ማወቁ መረጃዉን የበለጠ ግልጽ አንደሚያደርግ በመታመኑ ንግግራቸዉን ለማዳመጥ (ሞኒተር ለማድረግ) የሚያስችለን አንድም ሬዲዮ በወቅቱ በአየር ኃይሉ ዉስጥ ተፈልጎ በመጥፋቱ ከሲቪል አቭዬሽን አሮጌ ሬዲዮ በዉሰት ከተገኘ በኋላ ነዉ ዛሬ አገር ዉስጥ የሌለዉ ኮ/ል ፋንታ ኦላና የተባለዉ ፓይለት ከደብረዘይት ተልኮ እያንዳንዱን ንግግራቸዉን በመከታተል የተሟላ ሪፖርት ያቀረበዉ፡፡ ከዚያ በኋላ ነዉ የአየር መከላከያ ጥበቃዉ በከፍተኛ ደረጃ መጠናከር እንዳለበት የተወሰነዉ፡፡

በተፈጠረዉ መደነጋጋጥን ተከትሎ በኋላ ላይ በሀገሪቱ ዉስጥ የነበረዉ የአየር መከላከያ ትጥቅ ስልሳ ከመቶ (60%) የሚሆነዉ ተጓጉዞ ምስራቅ (በረሃሌና ቡሬ) አስከ ባድመ (ሰንበል) ድረስ ለሻዕቢያ መሹለኪያ ቀዳዳ እስኪጠፋ ድረስ በአየር መከላከያ እንዲታጠር ያደረግነዉ፡፡ በአጠቃላይ የሻዕቢያ ጥቃት ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በያንዳንዷ ፋታ ባገኘንበት ቀን ሁሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየተደማማረና እየተጠናከረ የሄደ ሰፊ የዝግጅት ስራዎች መሰረታቸዉ በኋላ ለተገኘዉ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጸኦ አድርጓል፡፡

እንደሚታወቀዉ የአትዮጵያ አየር ኃይል ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች አየር ኃይል የሚባል ነገር ሊኖራቸዉ ቀርቶ ራሳቸዉም ከቅኝ አገዛዝ ገና ባልተላቀቁበት ወቅት ማለትም ከ1936 ዓ/ም ጀምሮ ነበር በዘመናዊ መልክ የተቋቋመዉ፡፡ አየር ኃይላችን ከተቋቋመበት ወቅት ጀምሮ በበርካታ ግዳጆች ላይ ሲሳተፍ በመቆየቱ ሰፊ የጦርነት ተሞክሮ ያካበተና ስመ ገናና የነበረ ተቋም ነዉ፡፡

አየር ኃይላችን ከራሱም አልፎ አለምአቀፍ ተልእኮም የተወጣ ከአፍሪካ ብቸኛዉ አየር ኃይል ለመሆኑ በኮንጎ በ1954 እና በድጋሚ በ1959 ዓ/ም ከስዊድንና ከህንድ አየር ኃይሎች ጋር እኩል ግዳጅ ተሰጥቶት በብቃት ተወጥቶ የተመለሰበት ከሀገር ዉጭ የተደረጉ ግዳጆች አንድ አብነት ነዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ሌሎች የአፍሪካ መንግስታት ጸጥታ ችግር ሲያጋጥማቸዉ የኢትዮጵያን አየር ኃይል እገዛ እንዲያደርግላቸዉ ትብብር በመጠየቅ እገዛ ሲደረግላቸዉ እንደነበር ይታወቃለ፡፡

ለዚህም አብነት የሚሆነዉ በ1957 ዓ/ም በታንዛኒያ መንግስት በመሪዉ በጁሊየስ ኒየረሬ ጥያቄ አንድ ስኳድሮን የቅርብ አየር ድጋፈ ሰጪ T-28D አይሮፕላኖች ተልከዉ ከስድሰት ወር ላለላነሰ ግዜ ቆይተዉ የተመለሱበት ሁኔታ ተጠቃሽ ነዉ፡፡ የዛሬም የኢፌድሪ አየር ኃይልም በሶማሊያ በተለያዩ ግዜያት ተሰማርቶ ግዳጁን የተወጣ ሲሆን ዛሬም ድረስ በዳርፉርና በአብዬ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ሃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ይገኛል፡፡

ባጠቃላይ አየር ኃይላችን ከኤርትራ አየር ኃይል ጋር እኩል መመዘን የማይገባዉ በረዥም ዘመናት የዳበረ ተሞክሮ ያለዉ አየር ኃይል በመሆኑ የሚሰማራበት ተልእኮ አፈጻጸምም መመዘን ያለበት ከዚያ አንጻር ሊሆን ይገባል፡፡

ገና አዲስ አየር ኃይል ለማቋቋም ደፋ ቀና ስትል ከነበረችዉ ኤርትራ ጋር ባደረገዉ ጦርነት የነበረዉ ሚና ባይናቅም በጦርነቱ ዉጤት ላይ ከምድር ኃይሉ አንጻር ሲታይ የአየር ኃይሉ ድርሻ ዉስንነት እንደነበረዉ ግን መካድ አይቻልም፡፡ ለምድር ኃይሉ የቅርብ የአየር ድጋፍ ለማድረግ ብዙ ጥረት እንደተደረገ ይታወቃል፡፡ በአየር ማጓጓዣ ድጋፍ በማድረግ ረገድም ቀላል የማይባል ስራ ተሰርቷል፡፡ አየር ቅኝት በማድረግም የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ወደ ዉስጥ ወደ ኤርትራ ግዛት በጥልቀት በመግባት የተመረጡ ኢላማዎችን ለመምታት ጥረቶች ነበሩ፡፡

ነገር ግን ይሄን ሁሉ አድርጎም አየር ኃይሉ በጦርነቱ ሂዴት ላይ ወሳኝ የሆኑ ስራዎችን ስርቷል ለማለት ይቸግረኛል፡፡ በጥልቀት ገብቶ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸዉን ኢላማዎች ለመምታት የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በጠላት ላይ በተጨባጭ ያደረሰዉ ጉዳት ከባድ እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ ጠላት አይሮፕላኖቹን ከመሬት እንዳያሰነሳ ማድረግ  አልቻልንም፡፡ የጠላት እዝና ቁጥጥር ስርአቱ ከጥቅም ዉጭ እንዲሆን ባለማድረጋችን ጠላት አመራር መስጠቱን ለአፍታም ቢሆን አላቋረጠም፡፡ የአስመራ ዋናዉ ቤዝ (ራን ዌይ) ለመደብደም መሞከራችን ባይቀርም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረግ ግን አልቻልንም፡፡

በመጀመሪያዉ የአየር ኃይላችን ስምሪት ወቅት አስመራ በሚገኘዉ በአይሮፕላን ማኮብኮቢያ ሜዳዉ ላይ ጥቃት ባደረስን ጥቂት ደቂቃዎች ዉስጥ የሻዕቢያ አይሮፕላኖች ከዚያዉ ጣቢያ ተነስተዉ የኛን አይሮፕላኖች ተከትለዉ መቐለ ድረስ መምጣት ችለዉ ነበር፡፡ የአስመራዉን  አይሮፕላን ማረፊያ ሜዳዉንና የበረራ መቆጣጠሪያ ታወር ለጥቂት ቀናት እንኳን ከስራ ዉጭ ማድረግ ችለን ቢሆን ኖሮ በሻዕቢያ ላይ ከፍተኛ ዉድቀት ሊከተል ይችል ነበር፡፡

የጠላት ዒላማ አመራረጣችንና ስለጠላት ኢላማዎች የነበሩን መረጃዎች በአብዛኛዉ እንከን አይወጣላቸዉም፡፡ እነዚህ ኢላማዎች ያሉበት ድረስ ያለምንም እንቅፋት በፈለግነዉ ሰዓት  ጥቃት ለማድረስ ያገደን ኃይልም አልነበረም፡፡ በሻዕቢያ ግዛት ዉስጥ በሚገኝ የትኛዉም አካባቢ እንዳንደርስ የሻዕቢያ አይሮፕላኖች ሆነ አየር መቃወሚያ መሳሪያዎች እንቅፋት አልሆኑንም፡፡ አስመራ ብቻ ሳይሆን ሳዋ ማሰልጠኛ ድረስ ደርሰናል፡፡ ምጽዋ አካበቢም የኛ አይሮፕላኖች ደርሰዋል፡፡ አሰብና አካባቢዉም ከእኛ አይሮፕላኖች ዉጭ አልነበሩም፡፡

በጦር ግንባሮቹም ከምዕራብ አስከ  ምስራቅ በሁሉም ቦታ አየር ኃይላችን ነበር፡፡ ከፓይለቶቻችን መካከል ገና ወጣቶችና ልምድ የሚጎላቸዉ በርካታ ቢሆኑም ነገር ግን የነበራቸዉ ወኔና እልህ ከፍተኛ ነበር፡፡ ለህይወቱ የሳሳ አንድም አብራሪ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ድፍረታችንና እንደፍላጎታችን በያንዳንዱ ዒላማ ላይ በተጨባጭ ያደረስነዉ ጉዳት የሚያደማና ኢላማዉን በሚፈለገዉ ደረጃ ከጥቅም ዉጭ የሚያደርግ አልነበረም፡፡

በሌላ በኩል የወገን ተዋጊ እግረኛ ሰራዊት ወደ ዉስጥ ወደ ኤርትራ ግዛት በጥልቀት  እየገባና ከራሱ ድንበር እየራቀ ሲሄድ አልፎ አልፎም ቢሆን ለጠላት አይሮፕላኖች ጥቃት መጋለጡ አልቀረም፡፡ የጠላት ተዋጊ አይሮፕላኖች አመቺ ግዜ እየጠበቁና ፈራ ተባ እያሉም በእግረኛ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ ሰራዊታችንን ከጥቃት መታደግ አልቻልንም፡፡ ከሰራዊቱ ጋር አብሮ እየተንቀሳቀሰ ከጠላት አየር ጥቃት ሊጠብቀዉ የሚችል ተንቀሳቃሽ የሆነ የአየር መከላከያ ሽፋን ስላልነበረን የሻዕቢያ ደካማነት ባይረዳን ኖሮ በሰራዊታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ይችል ነበር፡፡

ባጠቃላይ ሲታይ አየር ኃይሉ እንደ ተልእኮ (task) ከፈጸማቸዉ ዉስጥ ጎልቶ የሚታየዉ ለምድር ዉጊያዉ የቅርብ የአየር ድጋፍ ለማድረግ ያደረገዉ ጥረትና በአየር መከላከያ አስከመጨረሻዉ የወገን አየር ክልልን ላለማስደፈር መቻሉ ነዉ፡፡ በሱ-27 ኢንቴርሰፕተር አይሮፕላኖችና ምድርን መሰረት ባደረገዉ አየር መከላከያ ክፍሎች መካከል የነበረዉ የተቀናጀ አሰራር ለአየር ክልላችን አስከመጨረሻዉ ሳይደፈር መቆየት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የሀገራችን ምድርን መሰረት ያደረገዉ አየር መከላከያ ከተቋቋመበት ከ1971 ዓ/ም መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ በአየር መከላከያ ግዳጅ አወጣጥ አንጻር በታሪካችን በኢትዮ-ኤርትራዉ ጦርነት ላይ ካከናወነዉ የተሳካ ግዳጅ ጋር የሚመጣጠን ሌላ ወቅት መጥቀስ አይቻልም፡፡ እንዲያዉም ምድርን መሰረት ያደረገዉና በሳም ሚሳይልና (SAM) በዘመናዊ የቅኝት ራዳሮች የተደራጀዉ ይህ የአየር መከላከያ ከፍል ከተመቋቋመበት ወቅት ጀምሮ በተግባር አቅሙን ለመፈተን ያስቻለዉ አንድም የተሳተፈበት ጦርነትም አልነበረዉም፡፡ በሶማሊያ ጦርነት ወቅት መጨረሻ አካባቢ የተመሰረተ ቢሆንም ጦርነቱ ተጠናቆ ስለነበር ዋነኛዉ ስራዉ ሆኖ የቆየዉ በጂግጂጋ ሰፍሮ የነበረዉን የኩባ ሰራዊት ከመጠበቅ የዘለለ አልነበረም፡፡

በርግጥ የአየር ኃይሉ መቀመጫ የሆነዉን ደብረዘይትና ዋና ከተማዋን አዲስ አባባን የድሬዳዋ አየር ምድብንና የአሰብ ወደብን የመጠበቅ ኃላፊነት በመወጣት ላይ የነበረዉ አየር መከላከያ  አንድም ግዜ የገጠመዉ የጠላት ጥቃት ሙከራ ወይም ስጋት  አልነበረም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ከኤርትራ ጋር ከተደረገዉ ጦርነት ዉጭ ከጠላት አየር ኃይል ጋር በመፋለም የሀገሪቱን የአየር ክልል ሲያስከበር የቆየዉ ተጠቃሽ  ኃይል የነበሩት የአየር ኃይሉ ኢንተርሰፕተሮች ነበሩ፡፡ በወቅቱ በሶማሊያዉ ወረራ ወቅት የአሜሪካ ስሪት የነበረዉን TP3-34D የተባለ የግራዉንድ ኢንተርሰፕሽን ራዳር ካራማራ ላይ በመትከል የኛን አይሮፕኖች ወደ ጠላት አይሮፕላን በመምራት ረገድ የተጫወተዉ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡

ስለዚህ ከኤርትራ ጋር ያደረግነዉ ጦርነት አየር መከላከያችን ለመጀመሪያ ግዜ በተግባር የተፈተነበትና እጅግ አኩሪ ስራ የሰራበት አጋጣሚ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በተለይም በሚሳይል ክፍሉና ከኢንተርሰፕተሮች መካካል የተፈጠረዉ ቅንጅት እጅገ የተዋጣለት እንደነበር በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ ይገባኛል፡፡

የጠላት አይሮፕላኖች ገና ከመሬት ሳይነሱ ጀምሮ በመከታተል ለጠላት ጥቃት እንዳችም ቀዳዳ ላለመክፈት የተደረገዉ ጥረት አስደናቂ ነበር፡፡ በተለይ በኢንተርሴፕቴር አይሮፕላኖች፤ በአየር መቃወሚያ ክፍሎችና በሚሳይል ዩኒቶች መካከል የነበረዉ ቅንጅት እጅግ የተዋጣለት ነበር፡፡

በተጨማሪ በሙያዉ ሰፊ ልምድ የነበራቸዉ የአየር መከላከያ አመራሮች የፈጠራ ክህሎቶቻቸዉን በመጠቀም በልማድ ከሚታወቁ የአየር መከላከያ አጠቃቀም መሪሆዎችና አስተሳሰቦች በተጨማሪ አዳዲስና ያልተጠበቁ አሰራሮችን በመተግበር የአየር ክልል ጥበቃ ስራዉ ዉጤታማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ከዚያች የተረገመች ግንቦት 28 ቀን ወዲህ አየር ክልላችንን አስከመጨረሻዉ ሳይደፈር  ቆይቷል፡፡

በመሰረቱ እንደ ነበረዉ ዝና ቢሆን ኖሮ የአየር ኃይላችን አቅም መመዘን የነበረበት ከጀማሪ የኤርትራ አየር ኃይል ጋር መሆን አልነበረበትም፡፡ በትክክል መመዘን ካለበትም፡-

1ኛ) ከአርባ ዓመታት በፊት (በ1969) የሶማሊያ ጦርነት ላይ ከሰራዉ ገድል ጋር በማነጻጻር ሊሆን በተገባ ነበር፡፡

2ኛ) መመዘን ካለበትም ከተቋቋመ ሰባ ዓመታት ያስቆጠረና ሰፊ የጦርነት ተሞክሮና ድርጅታዊ አቅም ያለዉ ተቋም ከመሆኑ አንጻር አሁን ላይ ሊደርስ ከሚችለዉ ቁመና ከግምት ገብቶ መሆን ነበረበት፡፡

3ኛ) ምናልባትም ጥሩ ማነጻጸሪያ ሊሆን የሚችለዉ ስትራቴጂያዊ ጠላታችን ከሆነችዉና ጠንካራ አየር ኃይል ካላት ግብጽ ጋር ወደፊት ከሚጠብቀን ጦርነት አንጻር ነዉ፡፡

ከዚያ ዉጭ ግን የኤርትራን ጦርነት ለብቻዉ ወስደን እንደማነጻጸሪያ ከተጠቀምን ከኤርትራ አየር ኃይል በብዙ እጥፍ የበላይነት እንደነበረን እኛ ብቻ ሳንሆን እነሱም ራሳቸዉ ሊመሰክሩት የሚችሉት ነዉ፡፡ ያ ግን አንድንኩራራ የሚያደርገን አይደለም፡፡

3/ በአየር ኃይል ግዳጅ አፈጻጸም ረገድ በጥንካሬ ሊጠቀሱ የሚችሉ ለስኬቱም አስተዋጽኦ ያደረጉ ዋነኛ ክንዉኖች

3.1/ በጥንካሬ የሚገለጹ የግዳጅ አፈጻጸሙ

አየር ኃይላችን ከጦርነቱ ድንገተኝነት የተነሳ በተለያዩ መልኮች ሊገለጽ የሚችል የዝግጅት ማነስ ቢኖርበትም አቅሙ በፈቀደ መጠን ሁሉንም ዓይነት የአየር ኃይል ተልእኮዎችን ለመተግበር ጥረት አድርጓል፡፡

ለምሳሌ የጠላትን ሰትራቴጂያዊ ኢላማዎችና ግዙፍ ተቋማትን ከጥቅም ዉጭ ለማድረግ ስትራቴጂያዊ ማጥቃት (strategic attack)፣ የተመረጡ ቁልፍ ኢላማዎችን በጥልቀት ገብቶ የመደምሰስ ተግባር (interdiction)፣ ለምድር ኃይሉ የቅርብ አየር ድጋፍ የመስጠት (close air support)፣ ኤሌክትኒክስ ጦርነት ማካሄድ (electronic warfare)፣ ከአየር ወደምድር የማጥቃት ተልእኮ (air to Ground attack)፣ ፈልጎ የማዳን ተልዕኮ (search and rescue)፣ የማጓጓዣ አገልግሎት (air transport)፣ ሻዕቢያ የቀበረዉን ፈንጂ የማምከን ተግባር፣ በአየር መከላከያ ግዳጅ ደግሞ በመከላከል ላይ ያተኮረ እጅግ የተሳካ ጸረ- አየር ዘመቻ(defensive counter air operation)፣ በተጨማሪ ጠንከር ያለ ዉጤት ባይገኝበትም አጥቂ የሆነ ጸረ- አየር ዘመቻ (offensive counter air operation)፣ ስለ ጠላት አየር ኃይል እንቅስቃሴ ወቅታዊ የሆነ መረጃ የማቀበልና የሀገሪቱ የአየር ክልል ዉስጥ የሚደረጉ አለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሲቪል አቭየሽን የማጓጓዣ በረራ እንቀስቃሴን ደህንነት የማስከበር ተግባራትን ሲያከናዉን ቆይቷል፡፡

በጦርነት ወቅት የሲቪል በረራ አገልግሎት ደህንነት ዋስትና መስጠት እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ማንም ሊገነዘብ የሚችለዉ ነዉ፡፡ እኛ ግን በጦርነቱ  ወቅት  በሌሎች አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ በሚካሄድበት ቀጠና ማለትም በትግራይ ክልልም አስከ መጨረሻዉ የአየር መንገድ የበረራ ስራ እንዳይስተጓጎል ለማድረግ የተደረገዉ ጥረት እጅግ አስመስጋኝ ነበር፡፡ እነዚህ የተዘረዘሩ ተልእኮዎች በአንድ ወይም በሌላ አጋጣሚ ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሮአል፡፡

የአየር ኃይላችን ዋነኛዉ ሃላፊነት ምድር ኃይሉን በማገዝ ከጠላት የአየር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆን በመጠበቅና የጠላትን ኢላማዎች አስቀድሞ በመደብደብ  ሰራዊታችን በአነስተኛ ኪሳራ ግዳጅ እንዲፈጽም ማስቻል ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ አየር ኃይሉ ለምድር ኃይሉ የቅርብ የአየር ድጋፍ በማድረግ የሰራቸዉ ስራዎች የሚደነቁ ነበሩ፡፡ አብዛኛዎቹ የግዳጅ በረራዎች ለቅርብ አየር ድጋፍ ለመስጠት የተበረሩ ነበር፡፡

አየር ኃይሉ በእጁ በነበሩት በቁጥር ዉስን በነበሩ ሚግ -21 እና ሚግ- 23 በመጠቀም በኤርትራ ክልል ዉስጥ የትኛዉም አካባቢ በጥልቀት በመግባት የጠላትን የጦርነት ማካሄጃ አቅም የሆኑትን ወታደራዊ ተቋማት ከጠቅም ዉጭ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በተለይ ተዋጊ ሄልኮፕተሮች በመጀመሪያዉም ሆነ በሁለተኛዉም የጦርነቱ ምዕራፎች ሁሉ አጅግ አደገኛ የሆኑ ግዳጆችን በጀግንነት በመፈጸም ታሪክ ከቶ የማይረሳዉ ስራ ሰርቷል፡፡

ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች በመጀመሪያዉ የጦርነቱ ምዕራፍ ብቻ አስራ አምስት ታንኮችና የጠላት ሰራዊት የጫኑ ካሚዮኖችን ጨምሮ በድምሩ አርባ ሰባት የተለያዩ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎችና ብረት ለበሶችን በማዉደም በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል፡፡ የጠላትን ግስጋሴም እንዲገታ አድርገዋል፡፡ በሁለተኛዉ ምዕራፍም ከአንደኛዉ ምዕራፍ ያልተናነሰ የጀግንነት ስራዎችን ሰርተዋል፡፡

አየር ኃይሉ በነዚህ አይሮፕላኖች ብቻ የሚሰራዉ ስራ በቂ እንዳልሆነ በመረዳት ለማጓጓዣ የሚያገለግሉ አንቶኖቭ የትራንስፖርት አይሮፕላኖች ላይ ቦንብ በመጫን ጠላት ባልጠበቀዉ ሰዓት በምሽት ድብደባ በማድረግ የሰሩት ስራ እጅግ የሚያኮራ ነዉ፡፡ እነዚህ አይሮፕላኖች እንደሌሎቹ ተዋጊ ጄት አይሮፕላኖች ከመቐለ ወይንም  ከባህር ዳር በመነሳት ሳይሆን  ከመሃል አገር ከደብረዘይት ተነስተዉ ያን ሁሉ አገር አቋርጠዉ ግዳጅ ፈጽመዉ በሰላም እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ የነዚህ አይሮፕላኖች ፓይለቶች መካካል ግማሾቹ ከጦርነቱ በፊት ከአየር ኃይል በጡረታና በዝዉዉር  ለቀዉ የሄዱ የሚገኙበት ሲሆን ሀገሪቱ ጦርነት ላይ መሆኗ እንደሰሙ ወደ አየር ኃይል በፍጥነት በመመለስ አኩሪ ስራ ሰርተዋል፡፡

በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት አየር ኃይላችን የምድር ኃላችንን የድል ግስጋሴ በማፋጠኑ ረገድ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ዘልቆ በመግባት የጠላትን አከርካሪ የሰበረ ሲሆን በአሰብ፤ በምጽዋ፤ በሳዋ፤ በመንደፈራ፤ በጾረና፤ በባድመ፤ በዛላአንበሣ፤ በቡሬና በሌሎችም ግንባሮች ባካሄደዉ የአየር ዘመቻ ግዳጁን በብቃት በመወጣት ታሪክ የማይዘነጋዉን ገድል ፈጽሟል፡፡ በተጨማሪ ከጠላት ጋር በመፋለም ላይ ያለዉን እግረኛ  ሰራዊታችንን ከጠላት የአየር ጥቃት በመጠበቅ ረገድም የተሰራዉ ስራ ቀላል አይደለም፡፡

በተለይም በጦርነቱ ማጠናቀቂያ ላይ ግንቦት 21-1992 ዓ/ም አስመራ የአየር ኃይል ቤዝን ለመደብደብና ከጥቅም ዉጭ ለማድረግ በከፍተኛ ሚስጥር ታቅዶ የተከናወነዉ ግዳጅ በብዙ  መለኪያ  መስፈርቶች አንጻር ሲመዘን እጅግ የተዋጣለት ነበር፡፡ በሂደት ከቀድሞዉ ጠንከር ያለ አየር መከላከያ መስርቶ የነበረዉን ጠላት አንዳችም አጸፋ እርምጃ መዉስድ እንዳይችል ተደርጎ በተመረጠ የበረራ መስመርና ከፍታ በከፍተኛ ሚስጥራዊነት የተከናወነዉ ይህ ዘመቻ እንኳን ለሻእቢያ ይቅርና እዚያዉ ለነበርነዉ አንዳንዶቻችን ፈጽሞ ያልጠበቅነዉ ከስትተት ነበር፡፡

እንደዚያ ዓይነት ከዝግጅቱ ጀምሮ አስከአፈጻጸሙ ድረስ እጅግ የተዋጣለት ዘመቻ ቀድም ሲል ጀምሮ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የጦርነቱን ዕድሜ በማሳጣር ረገድ ዓይነተኛ ሚና ለመጫወት በቻሉ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የመጨረሻዉ ዘመቻ ከአየር ኃይሉ አመራር ጀምሮ የዘመቻ ሙያተኞችም ሆነ ፓይለቶቻችን በጦርነቱ ሂዴት ተምረዉ በመጨረሻም የደረሱበትን የብቃት  ደረጃ በትክክል ያመላከተ ነዉ፡፡

በአየር መከላከያዉ ረገድም ለስኬታማነቱ ዋነኛዉ ማረጋጋጫ ከአይደሩ ጥቃት ወደህ አንድም የጠላት አይሮፕላን የአየር ክልላችንን ጥሶ መግባት ቀርቶ ወደ ድንበራችን ከ40 ከ/ሜ የቀረበበት ሁኔታ አስከመጨረሻዉ አለመፈጠሩ ነዉ፡፡ በአንጻሩ የኛ ተዋጊ አይሮፕላኖች በኤርትራ አየር ክልል ለግዳጅ ሲሰማሩ በሱ-27 ኢንተርፕተሮች ጥበቃ ስለሚደረግላቸዉ የሻእቢያ አየር ኃይል ሊያደናቅፈን አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል የምድር ኃይል ሰራዊት አንድ ወይም ሁለት አጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ከጠላት የአየር ኃይል ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ነዉ ግዳጁን ሲወጣ የነበረዉ፡፡

3.2/ ለስኬቱ ያገዙ እርምጃዎችና የኃይል አጠቃቀማችን

ለአየር ኃይሉ በእጁ የነበረዉን ዉስን አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሟጦ ለመጠቀም ያስቻሉት ለስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ የኃይል አጠቃቀምና  የዝግጅት ስራዊችን ከጦርነቱ ሂዴት እየተማረ በፍጥነት ድክመቱን በማረም አስፈላጊዉን አርምጃ ሁሉ በጥንቃቄ በመስራቱ ነዉ፡፡

ከነዚህ መካካል በጥቂቱ ለመገለጽ ያህል፡

* ከላይ ካለዉ ከአየር ኃይል አመራር ጀምሮ አስከ ታችኛዉ አሃድ ድረስ  የተቀናጀና እርስበርሱ የሚደጋገፍ አንድ ወጥ እዝና ቁጥጥርና ግኑኝነት ስርአት በመዘርጋት የተሻለ ዉጤት ተገኝቶበታል፡፡ ማእከላዊነት የጠበቀ የበላይ ቁጥጥርና የመረጃ ፍሰትን(centralised control) ራስን ችሎ ከሚደረግ የግዳጅ አፈጻጸም (autonomous mission execution)በማጣመር (combined)ለመስራት በመሞከሩ ዉጤታማ መሆን ችለናል፡፡

* የአየር ኃይሉ አካላት የሆኑ የበራረ ክንፎች (እስኳድሮኖች) የሚሳይልና  የአየር መቃወሚየ ክንፎችና ሌሎች ክፍሎች አንድ ወጥ ከሆነ የጋራ ማዘዣ ጣቢያ ወጥ ከሆነ አመራር (unified command) አመራር እንዲያገኙና የመረጃና የዉጊያ ቁጥጥሩም ወጥነት እንዲኖረዉ መደረጉ ለስኬቶቻችን ሁሉ ዋነኛዉ ምክንያት ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ በርግጥ በዚህ ረገድ በረራ ከፍሉና ምድርን መሰረት ያደረገዉ የአየር መከላከያ በአንድ እዝ መስጫ  አመራር እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ተግባራዊ እንዳይሆን  ሲከላከሉ የነበሩ አንዳንድ አመራሮች የነበሩ ሲሆን በኋላ ግን የተገኘዉን የተሳካ ዉጤት  ካዩ በኋላ መሳሳታቸዉን ሳደብቁ የገለጹ እንደነበሩ አስታዉሳለሁ፡፡

* ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ስለጠላት አየር ኃይል የሚገኙ መረጃዎችን በማጣራትና ትክክለኛነታቸዉን በማረጋገጥ መረጃዎችን ከታች ወደ ላይ ፤ከላይ ወደ ታችና ወደ ጎን እንዲሁም በግንባር ላሉ የምድር ኃይል ሰራዊት አመራሮች በፍጥነት እንዲደደርስ በማድረግ  የተሳካ ዉጤት ተገኝቷል፡፡

* አየር ኃይሉ ለተለያዩ ተግባራት የሚጠቀምባቸዉ መከላከለኛ አጭር ርቀት የመገናኛ  ሬዲዮኖች  ኋላቀርና ምስጢራዊነት የጎደላቸዉ  በመሆናቸዉ  ምክንያት  እጅግ መቸገራችን ባይቀርም በኋላ ላይ መከላከያ በግዥ ባስመጣቸዉ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የግኑኝነት ሬዲዮኖች መጠቀም ከጀመርን በኋላ በረዥም ርቀት መልእክት ልዉዉጥ ላይ የምስጥራዊነት የመጠበቅ ችግር ሙሉ በሙሉ ሊቀረፍ ችሏል፡፡ ሆኖም የቅርብ ርቀትና ከመሬት ወደ አየር  ከአብራሪዎች ጋር የሚደረገዉ  የዘመቻ ግኑኝነት ረገድ የምስጢር መጠበቅ የሚያስችል የግኑኝነት መሳሪያ አስከቅርብ ግዜ ድረስ እንዳልነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ከክፍሉ ከለቀቅኩ በኋላ ባሉት አመታት ዉስጥ ይሄ ችግር አስካሁንም ሳይቀረፍ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

* በጦርነቱ ወቅት ለግዳጅ አወጣጣችን ላይ የማይተካ አስተዋጽኦ ያደረገልን ሁኔታ ቢኖር  የጠላትን አየር ኃይል እንቀስቃሴ ገና ከመነሻዉ ጀምሮ ለመከታተል የቻልንበት ሁኔታ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆኑት የቅኝት ራዳሮቻችን ወደ ድንበር በማስጠጋትና ከጠላት እይታ ዉጭ የሆኑ ቦታዎችን በምስጢር በመምረጥ ለሃያ አራት ሰዓት ቁጥጥር በማድረግ አይሮፕላኖች ገና ከአስመራ እነደተነሱ በአንድ  ወይም ሁለት ደቂቃ ባነሰ አጭር ግዜ ዉስጥ መከታተል የምንችልበት ሁኔታ መፍጠራችን ነዉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ተጠቀሽ የሚሆነዉና ለአየር መከላከያ ግዳጅ አፈጻጸማችን ከፍተኛ እገዛ ያደረገልን የመገናኛ ሰራተኞቻችን የጠለፋ ሬዲዮኖችን በመጠቀም የሬዲዮ ጠለፋ በማድረግ የሻዕቢያ ፓይለቶች ገና ከመሬት ሳይነሱ ከመቆጣጠሪያ ታወር ጋር የሚያደርጉትን ንግግር በመጥለፍ የአየር መከላከያ ክፍሎችን በቅድሚያ በተጠንቀቅ እንዲገኙ በማድረግ ወደ ዉጊያ ለመግባት የሚያስፈልገንን ግዜ ለማሳጠር የተጠቀምንበት አሰራር ነዉ፡፡ በወቅቱ አመራር ደረጃ የነበርን ከጠለፋና ከራዳር የሚገኙ መረጃዎችን በማቀናጀት ለመጠቀም ሁኔታዉ ስላስቻለን ጠላት ድንገተኝነት ማትረፍ የሚችልበት አንዳችም ዕድል እንደሌለዉ ስለረተዳን በግዳጅ አፈጻጸማችን ላይ ትልቅ መተማመን ይሰማን እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡

* የጠላት አየር ኃይል ዝቅተኛ የበራራ ከፍታን ተጠቅመዉ ከራዳር እይታ ዉጭ በመምጣት ድንገተኛ ጥቃት እንዳያደርሱ ለማድረግ ከቅኝት ራዳሮቻችን በተጨማሪ ቁልፍ በሆኑ አካባቢዎችና የጠላት ምናልባታዊ መጠጊያ መስመሮች ላይ የዓይን ተመልካቾችን (vop) በማስቀመጥ አቀናጅተን መጠቀም በመቻላችን የበለጠ አሰተማማኝ ሁነታ ለመፍጠር ችለናል፡፡

* በአየር መከላከያ ግዳጅ አፈጻጸም ላይ አንዱ ፈታኝ ጉዳይ የጠላትንና የወገንን አይሮፕላን ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑ ነዉ፡፡ የቅኝት ራዳሮችና  የሚሳይል መሪ ጣቢያዎች በርቀት ያዩትን ኢላማ የወገን ይሁን የጠላት በትክክለኛዉ ወቅት ላይ መለየት ካልተቻለ የወገንን አይሮፕላንን እንደጠላት አይሮፕላን በመቁጠር አለአግባብ ሊመታ ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ አስከፊዉ ደግሞ በወገን ይዞታ ላይ ጥቃት ለማድረስ ተዘጋጅቶ የመጣን የጠላት አይሮፕላን የወገን ነዉ በሚል በስህተት ሳይመታ ጉዳት አድርሶብን ሊሄድ መቻሉ ነዉ፡፡

ይህ ችግር ብዙ አገሮች መፍትሄ ያጡለት የጋራ ችግር ነዉ፡፡ እኛም ብንሆን በጦርነቱ የመጀመሪያዉ ቀናት ወቅት በዚህ ረገድ ከስህተት አላመለጥንም፡፡ በኋላ ግን የችግሩን መነሻ ምክንያት በሚገባ በመገምገም በተለመዶ ስንጠቀምባቸዉ ከነበሩት positive identificaton method (ፖዜቲቭ አይደንፍኬሽን ሲስተም) ዉስጥ ከሚመደበዉ የጠላትና ወገን መለያ መሳሪያ (IFF) በተጨማሪ (procedural) የተቀናጀና የተናበበ አሰራር የሚጠይቀዉን ዜዴን አቀናጅተን መጠቀም ከጀመርን ወዲህ አንዳችም ችግር ሳይገጥመን አስከመጨረሻዉ መዝለቅ ችለናል፡፡

* በጦርነቱ ቀጠና ያለዉ የመሬት አቀማመጥ ተራራማና ወጣ ገባ የበዛበት በመሆኑና በእጅ የነበሩን  የቅኘት ራዳሮቻችን ቁጥርም ዉስንነት ተጨምሮ የቅኝት ራዳሮቻችን የእይታ ሽፋን (radar coverage) ላይ ክፍተት በመፈጠሩ ሁኔታዉ ለጠላት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥር መስጋታችን ባይቀርም በኋላ ግን እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ራዳሮችን በግዥ በማግኘታችን ከስጋት ተላቀናል፡፡ በኋላማ አንዱ በአንዱ ላይ በርቀትም ሆነ በከፍታ እርስበርስ የሚሸፋፈን (overlapped) የራዳር ፊልድ (radar field) መመስረት በመቻላችን ኢፎይታ ተሰምቶናል፡፡

የኤርትራ  አየር ኃይል ግን የኝን ያህል በቁጥርም ሆነ በዓይነት የበዙ ራዳሮችና የአየር መከላከያ ሚሳይል ስኳድሮኖች ሲላልነበሩዋቸዉ የአየር ክልል ጥበቃ ሽፋናቸዉ እጅግ የሳሳ ስለነበር የኛ  አይሮፕላኖች  ባሻቸዉ ግዜ ሁሉ ወደ ኤርትራ ጠልቀዉ በመግባት የፈለጉበት ደርሰዉ  ለመመለስ የሚያዳግዳቸዉ ነገር አምብዛም አልነበረም፡፡

* በጦርነቱ  ወቅት በጥንካሬ ሊገለጽ የሚገባዉ አንዱ ጉዳይ የአየር መከላከያን  የግዳጅ አፈጻጸም መሪሆዎች (air defense employement principles) በአግባቡ የተጠቀምንበት አግባብ ነዉ፡፡ በምስራቁም በምእራቡም ዓለም የሚታወቁ መሪሆዎች በተጨማሪ በየግዜዉ በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ አዳዲስና በጠላት ያልተገመቱ ዘዴዎችን መጠቀም በመቻላችን  ያስገኘልን ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ በአየር መላከላከያ ዩኒቶች የዘወትር ዝግጁነት አስተማማኝ ለማድረግ ያልተቋረጠና ተከታታይነት ያለዉ የዉጊያ ተረኝነት ስርአት በየደረጃዉ በመዘርጋት የተገኘነዉ ዉጤት ከፍተኛ ነዉ፡፡ የመሰረትነዉ የጥበቃ ስርአታችን እርስበርስ የሚሸፋፋን ከመሆኑም ሌላ  ጠላት አንድም ዕድል እንዳያገኝ ያደረገና ክፍተቱን ሁሉ የዘጋ አስተማማኝ ስርአት ነዉ የነበረዉ፡፡

በተጨማሪ ምድቡ ለጠላት በቅርብ ርቀት የሚገኝ መሆኑን ከግምት በማስገባት ወደ ዉጊያ የሚገባባትን የተጠንቀቅ ሰአት (reaction time) ለማሳጣር የሚረዱ ዜዴዎችን በሚገባ ተጠቅመናል፡፡ የተለያዩ አቅምና ባህሪይ ያላቸዉን መሳሪያዎች አቀናጅተንና አጣምረን ለመጠቀም ያደረግነዉ ጥረትም ከፍተኛ ዉጤት የሰጠ ነበር፡፡

* በጦርነቱ ወቅት የነበሩት የአየር መከላከያ አባላት ከቀድሞዉ ሰራዊት የተገኙ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ የቀድሞ ታጋይ የነበሩና ከ83ዓ/ም በኋላም ወደ ሰራዊቱ የተቀላቀሉት ሁሉ የሚያካትት በመሆኑ በአየር መከላከያ ግዳጅ አወጣጥ የተቀራረበ አቅም አለመኖሩን በመረዳት  ሁሉንም ምድብተኛ የግል አቅሙንና እንደ ዩኒት በጋራ ተቀናጅቶ የመዋጋት አቅም ለመፍጠር ታስቦ ሲሰራ የነበረዉ እልህ አስጨራሽ ስልጠናና ልምምድ ከፍተኛ ነበር፡፡

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ባለፈዉ የደርግ ዘመን ቢያንስ ለአስራ ሶስት ዓመት ባገለገልኩበት ወቅት አሁን የተሰራዉ ዓይነት ጠንካራ ስልጠናና ልምምድ ሲደረግ አላስታዉስም፡፡ በአጭር ግዜ ዉስጥ ሁሉም ምድብተኛና በየደራጀዉ የሚገኘዉ አመራር በታጠቀዉ መሳሪያና በተሰጠዉ ግዳጅ ከፍተኛ መተማመን እንዲሰማዉ ማድረግ ተችሏል፡፡

* በጦርነቱ ሁለተኛዉ ምዕራፍ ላይ ለኤሌክትሮኒክስ ዋር-ፌር የሚያገለግሉ እጅግ ዘመናዊ የኤለክትሪኒክ ጦርነት ማካሄጃ የቅኝት መሳሪያዎች በግዢ በመምጣተቻዉና በተጨማሪ የፈጠራ ችሎታን በመጠቀም አየር ኃይሉ ራሱ በሰራዉ የጃሚንግ መሳሪያ በመታገዝ የጠላትን ራዳርና የኤሌክትሪኒክስ መሳሪያዎች የተተከሉበትን ቦታ በመጠቆምና በሬዲየ አፈና በማድረግና ለአየር ኃይል አጥቂ አይሮፕላኖች ሁኔታዉን በማመቻቸት የተገኘዉ ዉጤት አኩሪ ነበር፡፡

* በጦርነቱ ማካሄጃ አቅማችን ላይ ዓይነተኛ ለዉጥ ያመጣዉ ዘመናዊ የኢንቴርሴፕቴር አዉሮፕላኖችን በግዢ መታጠቅ መቻላችን ነዉ፡፡ እነዚህ SU-27 የተባሉት እጅግ ዘመናዊ ኢንቴርሴፕር አይሮፕላኖች ከመጡ በኋላ ፓይለቶቻችን በአጭር ግዜ በተግባር መጠቀም በመቻላቸዉ የአየር ኃይሉ ግዳጅ አፈጻጸም ላይ ግልጽ የሆነ የበላይነት እንዲፈጠር አስችሎናል፡፡ እነዚህ አይሮፕላኖች ከታጠቅን ወዲህ ከሚሳይል ዩኒቶች ጋር በመቀናጀት የአየር ክልልችን በመጠበቅ ካደረጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በኤርትራ ክልል ዉስጥ በመግባት ለወገን አይሮፕላኖችና ሄልኮፕተሮች ከለላ ከመስጠታቸዉ ሌላ እግረኛ ሰራዊታችንን ከጠላት አይሮፕላኖች በመጠበቅ ረገድ ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡

* የአየር ኃይሉ አመራር እነዚህ ዘመናዊ አይሮፕላኖች በሌላ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ካልታገዙ በስተቀር የሚጠበቅባቸዉን ስራ አሟልተዉ መስራት እንደማይችሉ በመረዳቱ ባለ ሶሰት ዳይሜንሽን (3D) የሆኑ እጅግ ዘመናዊ የግራዉንድ ኢንቴርሴፕተር ራዳሮች በአጣዳፊ ሁኔታ በመግዛት ከታጠቅን በኋላ ኢንተርሴፕተሮችን ከመሬት ወደ ጠላት ኢላማ  በቀላሉ ለመምራት አስችሎናል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነዉ በተከታታይ በሁለት ቀናት ዉስጥ ሁለት የኤርትራን ሚግ 29 አይሮፕላኖች በመምታት እንዲጋዩ የተደረገበት አኩሪ ተግባር ለዚህ አባባል ምስክር ነዉ፡፡

* ፓይሌቶቻችን በጦርነቱ ቀጠና ወይም በግንባር ያለዉን የመሬት ገጽታ ጋር እንዲተዋወወቁ ለማድረግ በየግንባሩ የጉብኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸዉ ከአካባቢዉ መሬት አቀማመጥ ጋር በቅድሚያ እንዲተዋወቁ የተደረገበት ሁኔታም በጥንካሬ መገለጽ ያለበት ነዉ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ ፓይለቶች በግንባር ለማድረግ የታሰበዉን ጉብኝት ፋይዳ ባለመረዳት ምን ያስፈልጋል በሚል ላለመሄድ ሲያንገራግሩ እንዳልነበር በኋላ ግን ጉብኝቱ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

* በጦርነቱ ሂዴት ህዝቡን ከምናልባታዊ የአየር ጥቃት ለመታደግ እንዲቻልም የሲቪል መከላከል (civil defence) ስርአት በመዘርጋትና ጠላት ለጥቃትና ለበቀል የሚፈልጋቸዉን እንደ አድግራት የመድሃኒት ፋብሪካና የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የመሳሰሉት ግዙፍ ተቋማትን ለጠላት እይታ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከአካባቢዉ ጋር እንዲመሳሰሉ ለማድረግ በቦታዉ ተገኝተን በሰጠናቸዉ ምክር በመጠቀም በአጭር ግዜ የፋብሪካዉን የጣራ ቀለም በመቀየር  ያሳዩት ቀና ትብብር ለስራችን እጅግ ጠቅሞናል፡፡

በተጨማሪ በተጠቀሱት ፋብሪካዎች ማታ ማታ መብራት እንዳያበሩ የነገርናቸዉን ማሳሳቢያ በመጠቀም በመተግበር ለግዳጅ አወጣጣችን ላይ እገዛ አድርገዉልናል፡፡ ስለ ጠላት ወቅታዊ መረጃ ማግኘት እንዲችሉ መቐለ በሚገኘዉ የምድቡ ማዘዣ ጣቢያ የክልሉ ተወካይ በቋሚነት እንዲገኝ በማድረግ የጠላት የበራራ እንቀስቃሴን እየተለከታተሉ ለክልሉ እንዲያሳዉቁ ማድረግ ተችሏል፡፡ የትግራይ ክልል መስተዳደርም ሆነ በየቦታዉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለአየር ኃይል በተለይም ተነጣይ ለሆኑ ለአየር መከላከያ አሃዱዎች ሲያደርጉላቸዉ የነበረዉ ትብብርና ሲያሳዩን የነበረዉ ፍቅርና ከበረታ ለስራችን የማይተካ ትልቅ አቅም እንደፈጠረልን በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ ይገባኛል፡፡

መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ድጋፍ ካለዉ ጦርነትን ለማሸነፍ እንደማይሳነዉ በተግባር ማረጋገጥ ችለናል፡፡ መላዉ የሀገራችን ህዝብ ከሰራዊቱና ከመንግስት ጎን በመቆም ያደረገዉ ርብርብ እንዳለ ሆኖ በተለይ ጦርነቱ ሲካሄድ በነበረበት ቀጠና የነበረዉ ትግራይ ህዝብ ከዝግጀት ምእራፍ ጀመሮ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጥርጊያ መንገድ በመገንባት መረጃ በመስጠትና ለሰራዊቱ አባላት ፍቅር በማሳየት ያደረገዉ አስተዋጽኦ መቼም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

የክልሉ አመራር ለግዳጃችን አስፈላጊ የነበሩ የመንገድ መስሪያ ማሽኖችን በማቅረብ፤ ለምድብተኞች ድንኳና መጠለያ ኮንቴይነር እንዲሁም የዉሃ ማከማቻ ታንከሮች፤ ለመገናኛ መሳሪዎቻችን የኃይል ማመንጫ ጄነረተሮችን በማቅረብ ያደረጉልን ትብብር እጀግ ከፍተኛና በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ቢሆንም ለግዳጃችን መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ስገልጽ በታላቅ አክብሮት ነዉ፡፡ ፡

በአጠቃላይ በጦርነቱ ወቅት በተሰሩት በርካታ የተቀናጁ ስራዎች ምክንያት አየር ኃይላችን አኩሪ ስራ በመስራት አየር ክልሉ እንዳይይፈር በማድረግ ለጦርነቱ  ላገኘነዉ ድል የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

4/ አየር ኃይላችን የታዩበት የግዳጅ አፈጻጸም አብይ ጉድለቶች (ደካማ ጎናችን)

4.1/ በጦርነቱ ዝግጅት ላይ ለገጠሙን ችግሮች ሁሉ መሰረታዊ መነሻ ከደርግ የተረከብነዉ እጅግ የተዳከመ አየር ኃይል መሆኑ ነዉ

በጦርነቱ ሂደት የተስተዋሉት የድክመቶቻችን መነሻ ምክንያቶች ከሁለት ሁኔታዎች የመነጩ ይመስለኛል፡፡

አንደኛ የግንዛቤ እጥረት የፈጠረዉ ነዉ፡፡ በተለይ በወቅቱ የነበረዉ አመራር  በምድር ዉጊያ ሰፊ ተሞክሮ የነበረዉ ቢሆንም እንደ አየር ኃይል አመራር ከሌላ አገር አየር ኃይል ጋር ለሚደረግ ጦርነት የማዋጋት የቆየ ተሞክሮ ያልነበረዉና ይህ ጦርነት የመጀመሪያዉ ስለነበር ሁኔታዎችን በቅጡ አስከሚረዳ ግዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ነዉ፡፡

ሁለተኛ ከጦርነቱ ድንገተኝነት የተነሳ  ለጦርነት ብቁ የሚያደርገዉን ቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ በጥድፊያ ወደ ጦርነቱ ለመግባት በመገደዱ፤

ሶስተኛ መጀመሪያዉኑ በደርግ ዘመንም አየር ኃይሉ ለረዥም አመታት ባካሄደዉ የርስበርስ ጦርነት በፓይለትም በአይሮፕላንም እጅግ እየተመናመነና እየተዳከመ የመጣበትና በስርአቱ መዉደቂያ መጨረሻ ላይ ይባስ ብሎ በርካታ አይሮፕላኖቹንና አብራሪዎቹን በኩብለላ ያጣበት ሁኔታ በመፈጠሩ፤

አራተኛ መንግስት ከተቀየረ በኋላ በዉስን ደረጃም ቢሆን በፊት የነበረዉን የዉጊያ ቁመና ጠብቆ ከማቆየት ይልቅ ከተዋጊነት አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ አየር ትራንስፖርት ድጋፊ ሰጭነት የተቀየረበትና ዋነኛ ስራዉም የፕሪዜርቬየሽን (አቅቦ የማቆየት) ስራና በተወሰነ ደረጃም የጥናት ስራ ሆኖ በዚያ ላይ ተጠምዶ በመቆየቱ ተጨባጭ የሆነ የተዋጊነት አቅም አለመኖር የፈጠረዉ ችግር ነዉ፡፡

ከሁሉም በላይ ለአየር ኃይላችን ድክመቶች ዋነኛ ምክንያት የሚመስለኝ በደርግ ግዜ የነበረዉ አየር ኃይል ወደ መጨረሻዉ አካባቢ በብዙ ረገድ ኃይሉ እየተመናመነ በመምጣቱ ክፉኛ ተዳክሞ የነበረበትና በስም ብቻ ካልሆነ በስተቀር የዉጭ ወረራን ለመመከት የሚያስችለዉ ተጨባጭ የሆነ አቅም ያልነበረዉ መሆኑ በተለይም ለአየር ኃይሉ ግዳጁ ወሳኝ የነበሩት አይሮፕላኖችና ፓይለቶች በርስበርሱ ጦርነት ወቅት አማጽያንን ለመዉጋት ተብሎ የተዘጋጁ እንጂ ከዚያ ዉጭ ከሌላ አየር ኃይል ጋር ለሚደረግ ጦርነት ስላልነበረ በአብዛኛዉ አየር ኃይሉ ይዞት የቆየዉ አቅም እንደ ሀገር የማያስተማምንና ከተጨባጭ አቅሙ ጋር የማይጠጣም ትልቅ ስም ብቻ ይዞ እንዲቆይ የተደረገበት ሁኔታነዉ የነበረዉ፡፡

በዚህ ላይም በደርግ መዉደቂያ አካባቢ በቁጥር 22 የሚሆኑ አይሮፕላኖቹ ወደ ዉጭ ሀገር በሽሽት ሂዴት ስለተወሰዱ አየር ኃይሉ በተጨባጭ የነበረዉ አቅም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ እንግዲህ በዚህ መልኩ ተዳክሞ የቆየዉን አየር ኃይል ለጦርነቱ ለማዘጋጀት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነዉ፡፡ ስራዉ አዲስ አየር ኃይል የማቋቋም ያህል አስቸጋሪ ነበር፡፡

የኢፌድሪ መንግስት ከኤርትራ ጋር በነበረን ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ በማዉጣት በግዥ ያሟላቸዉ አብዛኛዎቹ አቅሞች (ትጥቆች) በፊት በደርግ ዘመን ያልነበሩ ናቸዉ፡፡ በደርግ ዘመን የነበሩት አይሮፕላኖች አብዛኛዎቹ እጅግ ያረጁና በመለዋወጫና በጥገና እጦት ከጥቅም ዉጭ ሆነዉ በየጥሻዉ ተጥለዉ የሚገኙ ነበሩ፡፡

አስቀድሜ እንደገለጽኩት በደርግ ዘመን አየር ኃይሉ ከነበሩት አይሮፕላኖች መካከል በቁጥር ሃያ ሁለት (22) የሚሆኑት በመጨረሻዉ የደርግ ዉድቀት ወቅት ወደ ዉጪ አገር የተወሰዱ በመሆናቸዉ እዚህ አገር ዉስጥ የቀረዉ ከቁጥር የሚገባ አልነበረም፡፡ ከአይሮፕላኖቹ ሌላ በርካታ አብራሪዎች ወደ ዉጭ አገር በሽሽት በመኮብለላቸዉ አየር ኃይሉ በተጨባጭ ይሄ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል እቅም አልነበረዉም፡፡

የአየር መከላከያ ትጥቅን በሚመለከትም የነበረዉ ሁኔታ ከአይሮፕላኖቹ የባሰ እንጂ የተሻለ አልነበረም፡፡ አብዛኛዎቹ የአየር መከላከያ ራዳሮችና ሚሳይል ጣቢያዎችና ሚሳይሎች ቀድሞዉኑ ምድብተኛ ያልነበራቸዉ በመሆናቸዉ ያለስራ በየጥሻዉ የትም ወዳድቀዉ የነበሩ ናቸዉ፡፡  እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ እያለን የተነሳዉ  ጦርነት  ላይ ፈጥነን መልስ ሰጪ ለመሆን ለአየር ኃይሉ አመራር በመጀመሪያዉ አካባቢ መያዣ መጨባጫዉ መጥፋቱ ለዚህ ነዉ፡፡ ደግነቱ ግን ይህ ሁሉ ችግር ግዜያዊ ችግር ነበር፡፡ ምክንያቱም የአየር ኃይሉ አመራር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አየር ኃይሉን በአጭር ግዜ ለቁምነገር ለማብቃት ችሎአል፡፡

የአመራሩንና የአየር ኃይል አባላትን በተለይም የአየር መከላከያ አባለትን ጥረት ከፍተኛ መሆን ጥሩ ማሳያ የሚሆነዉ ቀደም ሲል በደርግ ዘመን አየር ኃይሉ ዉስጥ ከነበሩት የአየር መከላከያ ትጥቆች ዉስጥ በሰዉ ኃይል አለመሟላት ችግር ምክንያት በወቅቱ በደርግ ዘመን ለግዳጅ መጠቀም ተችሎ የነበረዉ በአጠቃላይ 42% የሚሆኑ መሳሪያዎችን ብቻ ነበር፡፡ የቀሩት 58% የሚሆኑት በየጥሻዉ ወዳድቀዉ ነበር፡፡ በዚህ ጦርነትቱ ወቅት ግን  የኢፌዲሪ አየር ኃይል  በእጁ የነበሩት መሳሪያዎች በሙሉ በሙሉ (100%) ጠግኖ ለግዳጅ ዝግጁ ማድረግ መቻሉና የመሳሪያዉ ምድብተኞችን በሙሉ በጦርነቱ መካካል አሰልጥኖ ማዘጋጀት መቻሉ እጅግ የሚደነቅ ነበር፡፡

4.2/ ለጦርነቱ ያሰለፍነዉ ኃይል በቂ አለመሆን ትልቁ የገጠመን ተግዳሮት  ነበር

ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ተገቢዉ የኃይል ዝግጅት ባለመደረጉ አየር ኃይላችን በትጥቅ ዓይነትና ብዛት ረገድ በግልጽ የታየ ክፍተት ነበረበት፡፡ በእጁ የነበሩት የዉጊያ አይሮፕላኖች ብዛትና የነበሩበት የዝግጁነት ሁኔታ ከሌላ አገር ጋር ለሚደረግ ጦርነት ብቁ ነዉ ሊባል የሚያስችል አልነበረም፡፡

በወቅቱ በጦርነቱ ላይ ማሰለፍ የቻልነዉ አይሮፕላኖች ዓይነትና ብዛት፣ አይሮፕላኖቹ ባንድ ጊዜ መሸከም የሚችሉት የጦር መሳሪያና ተተኳሽ (ኦርዲናንስ) ዓይነትና ብዛት፣ አንድን ዒላማ ለማጥፋት በአንድ ጊዜ ለማሰለፍ የቻልነዉ የአይሮፕላን ቁጥር እንዲሁም በቀን ማድረግ የቻልነዉ የግዳጅ ምልልስ (sortie) ብዛት ዉስን ስለነበረ ተፈላጊዉን ዉጤት እንዳናመጣ አግዶናል፡፡ የኃይል ስምርታችን ተራ ጠብቆ የሚደረግ ነበር እንጂ በአንድ ጊዜ  (parallel operation) በሁሉም ቦታዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጠላትን ግራ ማጋባት የሚያስችለን አልነበረም፡፡

ዛሬ ጥቃት ማድረስ የታሰበዉ አስመራ ላይ ከሆነ ሌሎች የጠላት ኢላማዎች ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይሰጣቸዋል፡፡ አስመራም ቢሆን ተደጋጋሚ ምልልስ አይደረግበትም፡፡ በቀላሉ ከጥቅም ዉጭ መሆን የማይችሉ እንደ አይሮፕላን መሮጫ ሜዳና እንደ ባንከር ለመሳሰሉት ኢላማዎች (hard targets) በአንድ ጊዜ የምንመድበዉ ኦርዲናንስ ወይም ተተኳሽና አይሮፕላን ቁጥር እጅግ አነስተኛ ስለነበር የረባ ጉዳት ማድረስ አልቻሉም፡፡

እንደዚያም ሆኖ በጠላት ዒላማ ላይ ያደረስነዉን ጉዳት ለማወቅ የምንችልበት (target damage asssessment) ስርአትም ስላልነበረን ድብደባ የተከናወነበት ዒላማ ከጥቅም ዉጭ መሆን አለመሆኑን እርግጠኛ ሳንሆን ነዉ ትኩረታችንን ወደ ሌላ ዒላማ ስናዞር የነበረዉ፡፡ ለግዳጅ ዝግጁ ሆነዋል የተባሉት አይሮፕላኖቹ እጅግ ያረጁ በመሆናቸዉ አንድ ግዜ ግዳጅ ደርሰዉ ሲመለሱ ለዳግመኛ ግዳጅ ፈጥኖ መልሶ ለማዘጋጀት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር፡፡

ለድጋሚ ግዳጅ ማዘጋጀት ባለመቻሉ የታቀዱ ግዳጆች የሚሰረዙበት ወቅት ብዙ ነዉ፡፡ በአንድ ቀን ለግዳጅ ማሰማራት የቻልናቸዉ አይሮፕላኖች ምልልስ ወይም ሶርቲም በጣም ዉስን ነበር፡፡ ፓይለቶቻችን በሚመለከት የቀድሞ ታጋይ የነበሩና የበረራ ስልጠናቸዉን የጨረሱ ነገር ግን የግዳጅ ስምሪት ልምድ ያልነበራቸዉ በቁጥር በርካታ ቢሆኑም በሚገርም ሁኔታ ከተጠበቀዉ በላይ አስደናቂ የግዳጅ አፈጻጸም ዉጤት አስመዝግበዋል፡፡

ሁሉም ፓይለቶች አስፈላጊ ከሆነ በግዳጅ ላይ መስዋእት ለመሆን የቆረጡ ስለነበር ድፍረታቸዉ የሚገርም ነበር፡፡ እኛ የቸገረን የአይሮፕላኖቹ ቁጥር ማነስና በተጨማሪ ያሉትም ቢሆኑ አንድ ግዜ ግዳጅ ደርሰዉ ከተመለሱ ለድጋሚ ግዳጅ ለማዘጋጀት ባለባቸዉ ችግር ምክንያት  አዳጋች መሆኑ ነዉ፡፡

በወቅቱ በነበረዉ የአይሮፕላን ቁጥር ዉስንነት የተነሳ  በአንድ ግዜ ማሰለፍ የተቻለዉ የሚግ -23 ቁጥር አራት ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ በላይ የሚቻል አልሆነም፡፡ ይሄ ቁጥርም ቢሆን የሚሟላዉ አልፎ አልፎ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ አንድ ጠንካራ ኢላማ ለማዉደም በአንድ ግዜ የምናሰልፈዉ አይሮፕላን ቁጥር በቂ ስለማይሆን በሌላ ግዜ ለመምታት በሚደረግ ጥረት ጠላት ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቅ ድንገተኝነት ማትረፍ ስለማይቻል ፓይለቱን ለጠላት አየር መቃወሚያ ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡ ሻእቢያ ጠንካራ አየር መከላከያ ቢኖረዉ ኖሮ አንድም አይሮፕላን ባላስተረፈ ነበር፡፡

አየር ኃይላችን ከኤርትራ ጋር ያደረገዉን የግዳጅ አፈጻጸም ከሶማሊያ ጋር ከነበረዉ ጋር ለማነጻጸር ያህል በስልሳ ዘጠኙ የሶማሊያ ጦርነት ወቅት ሌሎች አይሮፕላኖች ሳይቆጠሩ በኤፍ -5 ኤ እና ኢ አይሮፕላኖች ብቻ በአንድ ቀን ብቻ በአማካይ አስከ ሃያ የአይሮፕላን ምልልስ (ሶርቲ) ይደረግ ነበር፡፡ ጦርነቱ በቆየባቸዉና የአየር ኃይሉን ተሳትፎ በጠየቁበት ከሀምሌ 1/1969 ዓ/ም አስከ መጋቢት 8/1970ዓ/ም ባለዉ ስምንት ወራት ግዜ ዉስጥ አየር ኃይሉ ሌሎች ግዳጆች ሳይጠቀሱ ለቅርብ አየር ድጋፍ ብቻ የተደረጉ በረራዎች 2400 ሶርቲዎች ደርሶ እንደነበር መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡

በፓይለቶች ብቃት አንጻርም ሲታይ ለምሳሌ ጄ/ል ለገሰ ተፈራ ብቻቸዉን በተለያዩ ቀናት ስድስት የሶማሊያን አይሮፕላኖች አየር በአየር ዉጊያ  መትተዉ የጣሉበት እንዲሁም ጄ/ል አምሃ ደስታ በአንድ ቀን ብቻ ስድስት ሶርቲ ግዳጅ መፈጸም የቻሉበት፤ አይሮፕላኖቹን ለድጋሚ ግዳጅ ፈጥኖ በማዘጋጀት ረገድም መጥቀስ ካስፈለገ አንድ ከዉጊያ የተመለሰ ጥንድ ኤፍ -5 እንደቆመ ነዳጅ ሞልቶ የጦር መሳሪያ እንደ አዲስ ተጭኖ፤ የአካል ፍተሻ ተደርጎለት ድጋሚ ለግዳጅ ዝግጀ ለማድረግ ከ15 ደቂቃ ባልበለጠ ግዜ ወስጥ (turn around time) ዝግጁ ማድረግ የተለመደ ነበር፡፡ ይህ ሰዓት ኢስራኤሎች በስድስቱ ቀን ጦርነት ለድጋሚ ግዳጅ ማዘጋጀት የቻሉበት አነስተኛዉ ሰዓት ነዉ፡፡

ከሶማሊያ ጋር በተደረገዉ አንድ አመት በላይ ባልቆየዉ ጦርነት ወቅት አየር ኃይላችን በድምሩ ሃያ አምስት (25) የሶማሊያን አይሮፕላኖች መትቶ መደምሰሱ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሶማሊያ አየር ኃይል ላይ የአየር የበላይነት (air superiority) ለመጎናጸፍ ከሁለት ሳምንት በላይ ግዜ አልጠየቀዉም፡፡ ከዚያ በኋላ የነበሩት ግዳጆች ሁሉ አየሩን የኛ አይሮፕላኖች እንዳሻቸዉ ለብቻ መቆጣጠር ያቻሉበት ሁኔታ (air dominance) ተፈጥሮ ነበር፡፡

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ አይሮፕላኖች በአየር በአየር ዉጊያ ሃያ ስድስት (26) የሶማሊያን አይሮፕላኖች መተዉ ሲጥሉ በዚሁ ሁሉ መካካል በጠላት  አይሮፕላን ተመትቶ የወደቀ የመጀመሪዉም የመጨረሻዉም የኛ አይሮፕላን ቢኖር ዳኮታ C-47 የማገጓጓዣ አይሮፕላን ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በወቅቱ ከተዋጊ አይሮፕላኖቻችን መካካል ሶስት ኤፍ-5ኤ እና ሶስት ኤፍ-5ኢ በድምሩ ስድስት አይሮፕላኖች ተመትተዉብን የወደቁ ቢሆንም ከመካከላቸዉ አንዳቸዉም በሶማሊያ አይሮፕላን አልተመቱም፡፡ ሁሉም ሊመቱ የቻሉት ከመሬት በተተኮሰ የአየር መቃወሚያ መሳሪያዎች ብቻ ነዉ፡፡

የሶማሊያ አየር ኃይል ላይ የበላይነት የተጎናጸፍነዉ የሶማሊያ አየር ኃይል እንደ ኤርትራ አየር ኃይል ደካማ ስለነበረ አይደለም፡፡ ሶማሊያ ከአስር ዓመታት በላይ ያዘጋጀቸዉና በስጦታም ከቀድሞዉ ወዳጇ ከሶቭየት ህብረት ያሻትን ሁሉ አይሮፕላን ሁሉ ታጥቃ ለዓመታት ዝግጅት ስታደርግ የቆየችዉ ጦርነት ነዉ፡፡ በወቅቱ ሶማሊያ ከቀድሞ ወዳጇ ከሶቭየት ህብረት ወታደራዊ አማካሪዎች እገዛ ያልተለያት ነበረች፡፡

የሶማሊያ አየር ኃይል ደካማ አለመሆኑ አንዱ ማሳያ በኛ ተመትተዉ የወደቁበት አሮፕላኖች ብዛት ሲታሰብ ታጥቆ የነበረዉ የአይሮፕላን ብዛት እጅግ ብዙ የነበረ መሆኑን ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የበላይነት ለማግኘት የቻለዉ ከሶማሊያ የበለጠ የአይሮፕላን ብዛ ስለነበረዉ ሳይሆን የፓይለቶቻችን በግልም ሆነ በቡድን የዉጊያ አፈጻጸም ብቃታቸዉ ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ ነዉ፡፡ ዋናዉ መተማማኛ አቅማችን የነበሩት ብቃትን ከጀግንነት ጋር አጣምረዉ የያዙት ፓለቶቻችን ሲሆኑ በተጨማሪ ድካምን የማያዉቁት ምርጥ ቴክኒሻኖቻችና አርቆ አሳቢና በዉጊያ የተፈነ የአየር ኃይል አመራር መኖር ነዉ፡፡

ይሄ ሁሉ ሲታሰብ ከኤርትራ ጋር ባደረግነዉ ጦርነት በአይሮፕላኖች ብዛትም ሆነ በቀን ምልልስ፤ በየእያንዳንዱ ኢላማ ላይ በተመደበ አይሮፕላን ብዛት፤ ለምድር ተዋጊዉ የቅርብ አየር ድጋፍ ለማድረግ በተደረገ ስምሪት ብዛት አንጻር ሲታይ አነስተኛ እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በዚህ ዓይነት በቁጥቁጥ በሚደረግ የግዳጅ በረራ በጠላት ላይ የከፋ ጉዳት ለማድረስ ከቶ እንደማይቻል ቀድሞዉኑ የሚታወቅ ነዉ፡፡ የታጠቃቸዉ አይሮፕላኖች ማነስ አጠቃላይ የዝግጅት እጥረት መኖር ሲታሰብ  በዚያን ወቅት በነበረ  አነስተኛ ዝግጅት አንጻር የተሰራዉ ስራ እጅግ አስመስጋኝ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ጦርነቱ ቶሎ ባይጠናቀቅ ኖሮ ለተጨማሪ ዝግጅት በቂ ግዜ ስለሚኖር  ከዚያ የበለጠ ስራ መስራት ይቻል አንደነበር ነዉ፡፡

4.3/ ለምድር ኢላማ የሚሆኑ አይሮፕላኖች ቁጥር ከሚፈለገዉ በታች መሆን እጅጉን ጎድቶናል

በጦርነቱ ወቅት  ለአየር ኃይል ግዳጅ አፈጻጸም ትልቅ እንቅፋት የሆነብን ለምድር ኢላማ (ground attack A/C) የሚሆኑ አይሮፕላኖች በቁጥር አነስተኛ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ የነበሩን ሚግ -23 አይሮፕላኖች ብዛትና ቦንብ የመሸከም አቅም (bomb load) ከሚፈለገዉ በታች ነበር፡፡ በዚህ ላይ በቀላሉ ወደ ኢላማቸዉ መምራት የምንችላቸዉ ፕረስሽን ጋይድድ ሙኒሽን (PGM- precision guided munition) በጭራሽ አልነበረንም፡፡

በጦርነቱ መካካል በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ተገዝተዉ የመጡት የኤሌክትሮኒክስ ዋር ፌር መሬጃ መሰብሰቢያ  መሳሪያዎች በጠላት ግዛት ዉስጥ የተተከሉ የራዳር ጣቢያዎችንና የሚሳይል መሪ ራዳሮችን አንዲሁም ለናቭጌሽን የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ባጠቃላይ ጨረር አመንጪ የሆኑ መሳሪዎችን ሁሉ የተተከሉበትን ቦታ (co-ordinate) ለማመላከት መሞከራቸዉ ባይቀርም እኛ ግን በነበረብን የአቅም ዉስንነት ምክንያት መረጃዉን በአግባቡ ልንጠቀምበት አልቻልንም፡፡

ምክንያቱም የነበሩን አይሮፕላኖች ጸረ- ራዳር ሚሳይል ወይም የራዲዮ ሞገድን ተከትለዉ የሚሄዱ ሚሳይሎች (anti radiation missile (ARM) የተገጠመላቸዉ ባለመሆናቸዉ በተለምዶ ለምድር ኢላማ በምንጠቀምባቸዉ ሚግ- 23 አይሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ራዳሮቹን ለመምታት አንዳንድ አደገኛ ሙከራዎች ከማድረግ ዉጭ ሌላ ማድረግ የምንችለዉ ነገር ስላልነበረን ነዉ፡፡

የጠላትን የአየር መከላከያ መሳሪያዎች እንደማንኛዉም የምድር ኢላማ ተጠግቶ በቦንብ ወይም በካሊቤር መሳሪያ መምታት የሚሞከር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኛን አይሮፕላኖች ገና ሳይጠጓቸዉ በርቀት መተዉ መጣል ይችላሉና፡፡ ጸረ-ራዳር ሚሳይል የተገጠመለት አይሮፕላን ቢኖር ግን ሚሳይሉ የጠላትን የራዳር ጨረር ተከትሎ በመሄድ በቀላሉ የመደምሰስ አቅም ስላለዉ የሚሳይል ተሸካሚዉ አይሮፕላን ወደ ኢላማዉ መጠጋት ሳያስፈልገዉና ፓይለቱንና አይሮፕላኑን ለአደጋ ሳናጋልጥ እንዲያዉም በኛዉ የአየር ክልል ዉስጥ በመሆን የጠላትን ራዳርና ሚሳይል ጣቢያ በርቀት ላይ ሆኖ ማዉደምና ከጥቅም ዉጭ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡

ሀገራችን በደርግ ዘመንም ቢሆን ጸረ-ራዳር ሚሳይል የተገጠመለት አይሮፕላን አልነበራትም፡፡ ጸረ- ራዳር ሚሳይል የተገጠለት አይሮፕላን መኖር ዋናዉ ፋይዳ ኢላማን የመደምሰስ ዕድልን ከፍተኛ ማድረግ መቻሉ ብቻ ሳይሆን የኛን ፓይለቶችና አይሮፕላኖች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ማድረግ ስለሚያስችል ጭምር ነዉ፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት አይሮፕላኖች ኖረዉን ቢሆን ኖሮ አንድም የኤርትራን የቅኝት ራዳርና ሚሳይል መሪ ራዳር ባላስተረፍን ነበር፡፡

በጦርነቱ መካከል ተገዝተዉ የመጡ በቁጥር በጣም ዉስን የነበሩ ሱ-25 አይሮፕላኖች የተጠቀሰዉን ዓይነት ጸረ ራዳር ሚሳይል ሊገጠሚላቸዉ የሚችል ስለነበር የነዚህ አይሮፕላኖች መገዛት እንደተሰማ ብዙ ተአምር ይሰራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በተከሰተዉ ተክኒካዊ ችግር ምክንያት ተስፋ አንዳደረግነዉ ሊሆን አልቻለም፡፡ የችግሩ መንስኤም የጠላትን የራዳር ጨረር አነፍንፎ የመብረር እቅም አለዉ የተባለለት ጸረ ራዳር ሚሳይል (ARM) የተገዛዉ አይሮፕላኑን ከሰራችዉ አገር ከሩሲያ ባለመሆኑ ሁለቱ መጣጣም ባለመቻላቸዉ እንደሆነ በወቅቱ ለማወቅ ችለናል፡፡

ከዛሬ ነገ ሚሳይሉን ተሸክሞ በመነሳት የሻዕቢያን ራዳሮች አንድ በአንድ ይለቅማል ብለን ብንጠብቅም ሊሆንልን አልቻለም፡፡ እንዲያዉም መቐለ ኤር ቤዝ ላይ አይሮፕላኖቹን በማቆም ሚሳይሉን በአካባቢዉ ከነበሩ የሚሳይል መሪ ራዳሮች ጋር ለማስማማት ብዙ ጥረት ቢደረግም እስከ መጨረሻዉ ሊሳካልን አልቻለም፡፡

የተጠቀሱት ሱ-25 የሚባሉት አይሮፕላኖች ለራዳር ኢላማ መጠቀም ባንችልም ለምድር ኢላማ ጥሩ ስራ ተሰርቶባቸዋል፡፡ በሀገራችን “ደርምስ” የሚል የቁልምጫ ስም የተሰጠዉ ይህ አይሮፕላን በሰሜን ግንባር የሚገኝ የጠላት ምሽግን በማደባየትና በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ የጠላትን የመድፍ ወረዳ በማዉደም በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል፡፡

በተጨማሪም በሰሜን ግንባር ከፎርቶ ወደ ሰንአፌ አግረ አዉጭኝ ቢሎ በሽሽት ላይ የነበረዉን የጠላት ሰራዊት እያሳደደ ደምስሷል፡፡ አዲኳላና እንዳጊዮርግስ እንዲሁም ከአይሞከር ሰሜን ምዕራብ ከምሽግ ጀርባ ዘልቆ በመግባት ጠላትን በመደብደብ ዉጤታማ ግዳጅ ፈጽሟል፡፡ በምእራብ ግንባርም በጉልችና ተሰነይ አካባቢ በነበረዉ የጠላት ሰራዊትና የዉጊያ ተሸከርካሪዎች ላይ ድብደባ በማድረግ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስ አድርጓል፡፡

አይሮፕላኑ በቁጥር በርከት ያለና ከመጀመሪያዉ የጦርነቱ ምእራፍ ጀምረን አስከመጨረሻዉ የጦርነቱ ፍጻሜ ድረስ ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ  ብዙ ስራ ሊሰራ በቻለ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ዘግይቶ በመገዛቱ ሳያንስ ቁጥሩም በቂ ስላልነበረ  የሚሳይል ስስተሙ እንከን ተጨምሮበት በዚህ አጭር ግዜ ብዙ ስራ ሰርቷል ለማለት አይቻልም፡፡

የተጠቀሰዉ ሱ-25 አይሮፕላን በጦርነቱ ላይ ለመጠቀም የቻልነዉ በቁጥር አንድ አይሮፕላን ብቻ ይመስለኛል፡፡ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት አይሮፕላኑ የተገጠመለት ተመሪ ሚሳይል ገና ከፋብሪካ ጀምሮ ችግር የነበረበት በመሆኑ የጠላትን የቅኝትና የሚሳይል መሪ ራዳር ጣቢያዎች በተመሪ ሚሳይል ለመምታት የነበረንን ፍላጎት ሊያሳካልን ባይችልም በጠላት ተሸከርካሪዎች ላይ የተሻለ ስራ እንደሰራ ይታወቃል፡፡

በግምገማ ያልተረጋገጠም ቢሆን ከነዚህ አይሮፕላኖች ግዥ ጋር በተያያዘ የሆነ የተድበሰበሰ ነገር በመኖሩም ብዙ ነገሩ በምስጢር ለመያዝ በመሞከሩም ጭምር ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን በጉዳዩ ላይ እንደ አጀንዳ ተነስቶ ምክክር የተደረገበት ግዜ አላስታዉስም፡፡

እነዚህ አይሮፕላኖች በመጡበት ወቅት ለነሱ እንክብካቤ ማድረግ የሚችል አስቀድሞ የተዘጋጀ የጥገና ቡድን ባለመኖሩ አማራጭ ሲጠፋ እንደመፍትሄ የተወሰደዉ በተለያዩ ቴክኒካዊ ችግሮች ምክንያት ከግዳጅ በረራ የተወገዱት የሚግ-21 አይሮፕላኖች ላይ የነበሩ ቴክኒሻኖችን ወደ ሱ-25 እንዳለ ማዞር ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ከሌሎች አይሮፕላኖች በተለየ እነሱን ለመንከባበከብ እጅግ አስቸጋሪም ነበር፡፡ በመጨረሻም ከጦርነቱ በኋላ ድጋሚ ለግዳጅ እንደማንጠቀምባቸዉ ሲታወቅ ምትክም ሳይገዛላቸዉ ወዲያዉኑ ከዉጊያ ዉጭ እንዲሆኑ በአመራሩ በመወሰኑ የሱ -25 ዕጣ ፋንታ በዚሁ አበቃ፡፡

በመሰረቱ የተጠቀሱት አይሮፕላኖች በጃችን ከነበሩት ከሚግ-23 በብዙ ረገድ የተሻሉ መሆናቸዉን የአምራቹ ፋብሪካ ቴክኒካዊ መረጃ በተጨማሪ በራሳቸዉ በሩሲያዉንና በሌሎቹ የምእራቡ አገራትም በሚገባ የሚታወቅና እኛም ብንሆን በተግባር ያረጋገጥነዉ ነዉ፡፡ ይህ አይሮፕላን (ሱ-25) በናቶ (NATO) ፍሮግ ፉት  (frogfoot) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከአሜሪካዉ A-10 (thunderbolt) ጋር ተመጣጣኝ አቅም ያለዉና በአንዳንድ ባህሪያቱ እንዲያዉም ብልጫ የነበረዉ በሌሎቹ ጉዳዮች ደግሞ አነስ ያለ አቅም የነበረዉ ነዉ፡፡

የዚህ አይሮፕላን አይነተኛ አቅም ከጠላት ራዳር እይታ በታች እጅግ  ዝቅ ብሎ በመብረር በጠላት ምሽግ ባንከርና ብረት ለበስ መሳሪያዎችን ለማዉደም ከፍተኛ ችሎታ ያለዉ መሆኑ ነዉ፡፡ የአይሮፕላኑ የነዳጅ ታንከርም ሆነ የፓይለቱ ኮክፒት ሆን ተብሎ እጅግ  ጠንካራ ከሆነ ቁሳቁስ የተሰራ በመሆኑ ከበድ ያለ ካሊበር ካላቸዉ የአየር መቃወሚያ መሳሪያዎች ዉጭ ቢመታም ብዙም ጉዳት አይደርስበትም የተባለለት ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም በሩሲያ ፓይሌቶች የሰማይ በራሪ ታንክ (flying tank) የሚል ማቆላመጫ ስም ተሰጥቶታል፡፡

አይሮፕላኑ በርካታ አገሮች የታጠቁትና በበርካታ ጦርነቶች ላይ ተፈትኖ የተዋጣለት እንደሆነ የተመሰከረለት ነዉ፡፡ ለምሳሌ የሶቭየት አየር ኃይል በአፍጋኒስታን ሲያካሂድ በነበረዉ ጦርነት ከስልሳ ሺህ ሺህ (60000) በላይ ሶርቲ በመብረር በግዳጅ ላይ ዉሏል፡፡ በቺችኒያም በአንድ ዓመት ግዜ ዉስጥ 5300 ሶርቲ የግዳጅ በረራ አድርጓል፡፡ በዩጎዝላቭያ፤በእራቅና በሶሪያ በኡክሬይን ወዘተ በተለያዩ ግዳጆች ላይ በጥቅም ላይ ዉሎ ብቃቱ ተመስክሮለታል፡፡ ሱዳንም ሳትቀር በዳርፉር ላይ  ያደረገችዉ ድብደባ በዚህ አይሮፕላን ተጠቅማ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አሜሪካኖች የዚህን አቻ የሆነዉን ኤ-10 አይሮፕላን አስከ 2022 ባለዉ ግዜ ዉስጥ ከግዳጅ ለማዉጣት እቅድ ያላቸዉ ሲሆን በአንጻሩ ሩሲያኖች ሱ-25ን ለወደፊትም ለመጠቀም ባላቸዉ ፍላጎት መሰረት በዚህ አይሮፕላን ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎችና የአፕግሬድንግ ስራዎች በስፋት እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ወደ ጦርነቱ ስንገባ ትልቁ የአቅም ዉስንነት የነበረዉ ለምድር ኢላማ ማጥቂያ የሚሆን የተሻለ አቅም ያለዉ አይሮፕላን አለመኖር መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለ የተጠቀሱት ሱ-25 አይሮፕላኖች ይሄን ክፍተት ይሸፍናሉ ተብለዉ ሲጠበቁ ለምን ከሚገባዉ በታች አነስተኛ ቁጥር እንደተገዙና ለምንስ ሚሳይሉና አይሮፕላኑን ከአንድ ቦታ እንዳልተገዛ በኋላም ማረም እየተቻለ ለምንስ ከኃይል ዉጭ እንዲሆኑ እንደተፈረደባቸዉ ግልጽ አይደለም፡፡ ዛሬ አየር ኃይላችን ለምድር ኢላማ የሚሆኑ አይሮፕላኖች ጉዳይ አዳዲስ ገዝቶ ለመታጠቁ ወይንም የነበሩትን አሻሽሎ እንደሆን በአጠቃላይ ይሄን ክፍተት በምን መንገድ እየፈታ እንደሆነ መረጃዉ የለኝም፡፡

4.4/ ለአየር መከላከያ የነበረዉ ግንዛቤ አናሳ መሆን

ሌላዉ ትልቁ በሂዴት ያስተካከልነዉ አንዱ ድክመታችን የነበረዉ ፓይለቶቻችን ሆኑ አመራሮች ለጠላት አየር መከላከያ የነበራቸዉ አጉል ንቀት ነዉ፡፡ ይህ ንቀት ለራሳችን አየር መከላከያም ከነበረን ዝቅተኛና የተዛባ ግምት የመነጨ ነበር፡፡ ስለ አየር መካለከያ በቂ ግንዛቤ አስክንይዝ ድረስ ብዙ ኪሳራ መክፈል ነበረብን፡፡ በኋላ በሂደት የታየዉን ዉጤታማ  ቅንጅት አስክንፈጥር ድረስ መጀመሪያ አካባቢ የነበረዉ ፍላጎት አነስተኛ ነበር፡፡

በወገን አየር ክልልም ሆነ በጠላት አየር ክልል ዉስጥ ፓይለቶቻችን ምድርን መሰረት ካደረጉ የአየር መከላከያ ክፍሎች ጥቃት ለመዳን መዉሰድ ስለሚገባቸዉ ጥንቃቄ እርምጃ ግንዛቤዉ አነስተኛ ነበር፡፡ የጠላት የአየር መከላከያ መሳሪያዎች ባሉበት ክልል ዉስጥ ወደ ጠላት ኢላማ በሰላም ደርሶና ግዳጅ ፈጽሞ በሰላም ለመመለስ የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን በሚመለከት ብዙዎቹ አያሳስባቸዉም ነበር፡፡ በአሳዛዥነቱ የሚታወሰን የጀግናዉ ኮሎነል በዛብህ ተመቶ በዚያዉ የመቅረት ክስተት መነሾ የጠላት አየር መቃወሚያን ጉዳይ ችላ በማለቱ እንደሆነ ሳስታዉስ በከፍተኛ ቁጭት ነዉ፡፡

በዛብህ በቂ ተሞክሮ ያለዉና በራሱም ላይ ከዚህ ቀደም ደርሶ እያለ ለስህተት የተዳረገዉ የአይደሩ ህጻናት ላይ የደረሰዉን አሰቃቂ ክስተት በቦታዉ ተገኝቶ ከተመለከተ በኋላ በተፈጠረበት የቁጭት ስሜት በመገፋፋት ከዚያ ስሜት ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ባልተላቀቀ ሁኔታ እያለ በመሄዱ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ከዚ በፊት በሶማሊያ ጦርነት የጣነዉን ስድስት አይሮፕላኖችና በኤርትራ በተካሄደዉ ጦርነትም ራሱንም ጨምሮ ከደርዘን በላይ የሆኑ አይሮፕላኖች ሁሉም ከምድር በተተኮሱ ጸረ አይሮፕላን መሳሪያዎች ተመትተዉ የወደቁ ስለመሆናቸዉ በዛብህ በሚገባ የሚያዉቅ ሆኖ እያሉ በድጋሚ ለዚህ አደጋ መጋለጡ እጅግ አሳዛኝ  ነዉ፡፡

በእዝ እና ቁጥጥር ረገድም በየግዜዉ ከድክመቶቻችን በፍጥነት እየተማርን በርካታ ያሻሻልነዉ ነገር ቢኖርም የመሰረትነዉ ኮማንድ ኤንድ ኮንተሮልና ኮሚኒኬሽን ስስቴሙ(C3) ምን ያህል ዉጤታማ ነበርን የሚለዉን ለመናገር ያዳግታል፡፡ ጄ/ል አበበ ራሳቸዉ ከጦርነቱ በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ አንስተዉ ሲናገሩ “የሻዕቢያ አየር ኃይል ደካማ በመሆኑ የመሰረትነዉን የእዝና ቁጥጥር ስርአት ዉጤታማነት በትክክል ለመለካት (ለመፈተሸ) አልቻልንም” ብለዉ ነበር፡፡

በጣም ትክክል ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ከራዳር የሚገኝ መረጃን ወቅታዊ ለማድረግ (real– time information) አንድ ጥሩ ጅማሮ የነበረዉ ከግራዉንድ ኢንትርሴፕሽን ራዳሩ የሚገኝ የራዳር መረጃን ለዚሁ ተብሎ በቪሳት ዲሽ አማካይነት ከቴሌ መስመር በመከራየት በቀጥታ ወደ ምድብ ማዛዣ ጣቢያና ወደ ደብረዘይት ማእከላዊ መዘዣ ጣቢያ በማስተላለፍ የመረጃ መዘግየትንና ስህተትን  በእጅጉ መቀነስ የተቻለ ቢሆንም ለዚህ የሚያገለግለዉ ስስተም ቴክኒካዊ ችግር አዘዉትሮ ይገጥመዉ ስለነበር ከጦርነቱ በኋላ ምትክ መፍትሔ ሳይበጅለት በብልሽት ብዙ ግዜ ቆይቶ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ባላዉቅም በጦርነት ወቅት ግን የሰጠዉ አገልግሎት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ አሰራር ከዚያ በፊት በአየር ኃይላችን ተሰርቶበት የማያውቅ አዲስ ዉጊያ አቅም ፈጣሪ ዜዴ ነበር፡፡

5/ በአየር ኃይል አጠቃቀም ረገድ መሰረታዊ ለዉጥ የሚሻ የተዛባ አመለካከታችን

5.1/ አየር ኃይላችን በጦርነቱ ላይ ደጋፊ ሚና እንጂ ለተገኘዉ ድል ላይ ወሳኝ ሚና አልነበረዉም  

በጦርነቱ ለተገኘዉ ዉጤት አርሚዉ ወሳኝ ሚና (decisive role) እንደነበረዉ መቀበል የማይፈልጉና እንዲያዉም ለጦርነቱ ድል መገኘት ወሳኝ ሚና የነበረዉ አየር ኃይሉ ነዉ ለማለት የሚቃጣቸዉ የአየር ኃይል አባላት እንደነበሩ አስታዉሳለሁ፡፡  እንኳን በእኛ አቅም ይቅርና በሌሎች አገሮችም ቢሆን አየር ኃይሉ አርሚዉን ተክቶ የድል አምጪ የሆነበት በጣም ጥቂት አጋጣሚዎች ብቻና ለዚያዉም እጅግ ግዙፍ አየር ኃይል ባላት አሜሪካና መሰሎቹ እንዲሁም በጦርነት የተፈተነ ምርጥ አየር ኃይል ባለቤት በሆነችዉ ኢስራኤል ደረጃ ብቻ ነዉ ፡፡

በባህረ ሰላጤዉ ጦርነት ወቅት አየር ኃይል ወሳኝ ሚና (dominant role) እንደነበረዉ አይካድም፡፡ በአለም ላይ እጅግ ግዙፍ የሚባል አየር ኃይል አየር መከላከያና ምድር ኃይል ከነበራቸዉ ጥቂት አገሮች ተርታ ትቆጠር የነበረችዉ የእራቅ ሰራዊት በጥቂት ሳምንታት ዉስጥ ፍርክስክሱ የወጣዉ በአየር ኃይል በደረሰበት ድብደባ ነዉ፡፤ በዩጎዝላቪያም የናቶ ጦር ጦርነቱን ጀምሮ ያጠናቀቀዉ በአየር ኃይል ብቻ ነበር፡፡

መሬት መቆጣጠር (መቆናጠጥ) አስፈላጊ ባልሆነባቸዉ ጦርነቶች ላይ አየር ኃይል ወሳኝ ሚና ቢኖረዉ አይደንቅም፡፡ በእኛና በኤርትራ መካከል በተካሄደዉ ጦርነት ግን በዚያ ደረጃ የሚታሰብ  አይደለም፡፡ ምክንያቱም የጦርነቱ ባህሪይ ራሱ ለዚያ የሚፈቅድ አልነበረምና፡፡ መሬት መቆጣጠርን እንደ ቁልፍ ድል ለሚቆጠርበት እንደ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አየር ኃይሉ የምድር ኃይሉን ድርሻ ሊተካ የሚችልበት እድል አልነበረዉም፡፡

በተጨማሪ አየር ኃይላችን በተጨባጭ መስራት የቻለዉ ስራም ቢሆን በጦርነቱ ወሳኝ ሚና ነበረዉ የሚያሰኝ አልነበረም፡፡ አየር ኃይላችን የአርሚዉን ጥረት በማገዝ እጅግ ጠቃሚ ሚና ሊጫወት እንደነበር ባይካድም ነገር ግን አርሚዉን ተክቶ ብቻዉን ድል ለማምጣት ችሏል የሚያሰኝ  ሁኔታ በጭራሽ አልነበረም፡፡

እንደሚታወቀዉ የሻዕቢያ ወረራ ድንገተኛነት ለአየር ኃይሉ ብቻ ሳይሆን ለአርሚዉም ጭምር ነበር፡፡ በመሆኑም ምድር ኃይሉ በአጭር ጊዜ ባደረገዉ ዝግጅት ለጦርነቱ ብቁ የሚያደርገዉን ተፈላጊዉን የዉጊያ ቁመና ለመያዝ ሲችል በአየር ኃይሉ በኩል ግን ሰፊ የዝግጅት ስራዎችን ለመስራት ጥረት መደረጉ ባይቀርም ነገር ግን የአርሚዉን ያህል የሚያስመካ ቁመና ፈጥነን ለመፍጠር ችለን ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡

ምክንያቱም አስቀድሞ ታስቦበት በደህና ጊዜ ያልተዘጋጀ አየር ኃይልን በጥቂት ወራት ዝግጅት ብቻ ለጦርነት ብቁ ማድረግ የማይቻል ስለሆነ ነዉ፡፡ ይህን ስል አየር ኃይሉን ለጦርነት ለማዘጋጀት አንዳችም ጥረት አልተደረገም፤ በጦርነቱም ጠቃሚ ድርሻ አልነበረዉም እያልኩ አይደለም፡፡ ብዙ ጥረት እንደተደረገና በጦርነቱም አኩሪ ስራ እንደሰራ አዉቃለሁ፡፡ እንዲያዉም የዚያን ወቅት አዛዥ የነበሩት ጄነራል አበበ ሊደነቁበት የሚገባዉ ትልቁ ተግባራቸዉ የሻእቢያ ወረራ ማድረግ ከታወቀ በኋላ በአጭር ግዜ አየር ኃይሉን ብቁ ለማድረግ የሳዩት ቁርጠኝነትና በጦርነቱም በተግባር ያስገኙት ዉጤት ነዉ፡፡

በጄ/ል አበበ ብርታት ሱ-27 የተባሉ ዘመናዊ የኢንተርርሰፕተር አይውሮፕላኖችን መታጠቅ ችለናል፡፡ በተጨማሪ እነዚህኑ አይሮፕላኖችን ወደ ኢላማቸዉ ለመምራት የሚያገለግሉና እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ግራዉንድ ኢንተርሴፕሽን ራዳሮችን ለመታጠቅ በቅተናል፡፡ እንደዚሁም በሀገራችን የአየር ኃይል ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑትን የሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ ጦርነት መረጃ ማሰብሰቢያ መሳሪያዎችን (electronic intelligence) በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ተገዝተዉ በጦርነቱ ላይ ከፍተኛ አገልግሎት መስጠታቸዉ ይታወቃል፡፡

የሄልኮፕተሮች ግዥ የተተኳሶች ግዥና በእጅ የነበሩ አይሮፕላኖችና የአየር መከላከያ  ትጥቆች ጠግኖ ወደ ግዳጅ ለማስገባት የተደረገዉ ጥረት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄም  ቢሆን የአየር ኃይል ግዳጅ አፈጻጸም በባህሪዉ እጅግ ዉብስብ የሆነና ሰፊ ልምድ የሚጠይቅ በመሆኑ ለጦርነቱ በጥድፊያ ያደረግነዉ ዝግጅት የሚፈለገዉን ያህል አቅም መፍጠር አስችሎናል ለማለት ያዳግታል፡፡ በዚህ ምክንትም በርካታ ጠንካራ ጎኖች የመኖራቸዉን ያህል በርካታ ጉድለቶችም እንደነበሩብን መደበቅ አይቻልም፡፡

5.2/ አየር ኃይላችን በጦርነቱ ለተገኘዉ ድል መምጣት ወሳኝ ሚና ባይኖረዉም ነገር ግን አቅሙ በፈቀደ መጠን ያደረገዉን አስተዋጽኦ እዉቅና አለመስጠት ትልቅ ስህተት ነዉ  

በኛ አካባቢ ምናልባት አሁን መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለዉጥ ተደርጎ ይሁን አይሁን መረጃዉ ባይኖረኝም ዋናኛ ቁልፍ ችግራችን ሆኖ የቆየዉ በጦርነቱ አየር ኃይል ሊያበረክት የሚችለዉን ድርሻ አሳንሶ የማየት ችግር ነበር፡፡ የአየር ኃይልን ድርሻ አጋኖ የማቅረብ አስተሳሳብ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ባይጠፋም ከዚያ ይልቅ እጅግ የጎዳን በከፍተኛ የመከላከያ አመራሮች  አካባቢም ሳይቀር የአየር ኃይሉ በጦርነቱ ወቅት የነበረዉን ጉልህ ድርሻ ለማኮሰስና ጭራሽ በበጎ ጎን እንዳይነሳ ሲደረግ የነበረዉ ጥረት ነዉ፡፡

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የአየር ኃይሉን የጦርነቱን ወቅት ሚና ዝቅ ለማድረግ ሲሞከር በማድመጤ እጅግ ማዘኔን መደበቅ አልችልም፡፡ አየር ኃይሉ በጦርነቱ ላይ ወሳኝ እንዳልነበርና ከአርሚዉ አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ባይካድም ነገር ግን ጭራሽ ዋጋ ማሳጣት ግን ተገቢ አይደለም፡፡ አየር ኃይሉን የተፈለገዉ ደረጃ ላይ ለማድረስ ሃላፊነቱም አቅሙም የነበራቸዉ አመራሮች ራሳቸዉን እንደባዕድ አድርገዉ በመቁጠር ስለ አየር ኃይሉ ድርሻ አኮስምነዉ ሲናገሩ መስማት ምቾት አይሰጥም፡፡

ገና ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ አየር ኃይሉ ላይ ጥሩ ያልሆነ አመለካከት እንዳለ ይሰማል፡፡ እምነት የማይጣልበትና አደገኛ ቢያንስ አጠራጣሪ ተቋም ተደርጎ እንደሚታሰብም አዉቃለሁ፡፡ ይሄ አመለካከት ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ የነበረና በደርግ ግዜ ተጠናክሮ የቀጠለ ዛሬም ሊቀረፍ ያልቻለ ስር የሰደደ አመለካከት ነዉ፡፡ በአየር ኃይል አመራርነት የሚመደብ ሰዉ እንደ ጄ/ል አበበ (ጆቤ) ዓይነት ተደማጭነት ያለዉ ሰዉ ካልሆነ በስተቀር የበላይን አንድ ነገር ጠይቆ ለማስወሰን እንደሚቸግረዉ በተግባር ያየነዉ ነዉ፡፡

ስለዚህ በየግዜዉ የሚመደቡ አመራሮች ከበላይ ጋር ላለመጣላት እያሉና ገና ለገና ጠይቀን አይፈጸምልንም በሚል ግምት አየር ኃይሉን ለማዘመን የሚያስችል አዳዲስ እቅዶችን አቅደዉ ለመፈጸም ፍላጎታቸዉ አነስተኛ ነዉ፡፡ በዚህ ላይ አየር ኃይሉ ለሀገሪቱ መከላከያ በሂዴት ወሳኝ ኃይል ማድረግ ይቻላል ከሚለዉ አመለካከት ይልቅ አየር ኃይሉ ሁልግዜም ከድጋፍ ሰጪነት በላይ የተሻለ ድርሻ እንዳይኖረዉ የመፈለግ የተዛባ አመለካከት በመኖሩ አየር ኃይላችን ደርሶ ማዬት እንደምንመኘዉ ባሰብነዉ ደረጃና ፍጥነት እንዳልሆነ በዉስጡ ያለፍነዉም ሆነ አሁንም እያገለገሉ ያሉት ጠንቅቄን እናዉቃለን፡፡

በሌሎች አገሮች  አየር ኃይሉ እያበረከተ ያለዉ ድርሻ ከፍተኛ መሆን ከምን የመነጨ እንደሆነ ለመረዳት መሞከር ያስፈልጋል፡፡ በኮርያ ጦርነት ወቅት አብዛኛዉ በሰሜን ኮርያ ላይ የደረሰዉ ጉዳት በአየር ኃይል በተሰነዘረ ጥቃት ነዉ የነበረዉ፡፡ የሰሜን ኮሪያ በጦርነቱ ከተገደለባት 47% ወታደሮች፤ 75 % ታንኮች፤ 81%ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች 72% መድፎች የተደመሰሱት በአየር ኃይል ነዉ፡፡ የኮሚንስቶቹ ማለትም የሰሜን ኮሪያ ኃይል እጅግ በተጠናከረበት ወቅት እንኳን አሜሪካኖች በጦርነቱ ለመዝለቅ የቻሉት በአየር ኃይላቸዉ ብርታት ነዉ፡፡

ስለዚህ ጉዳይ በቦታዉ የነበሩት የአሜሪካ ሰራዊት ዋና አዛዥ ሌ/ጄነራል ዋልቶን ዎኬር እንደተናገሩት “የአየር ድጋፍ  ባይኖር ኖሮ በኮሪያ ምድር መቆት ባልቻልን ነበር” ብለዉ ነበር፡፡ (“If it had not been for the air support that we received from the Fifth Air Force we would not have been able to stay in Korea.”).

በባህረሰላጤዉ ጦርነት ወቅትም  የአሜሪካ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት እዉቁ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ጄ/ል ኮሊን ፓዌል ሰለጦርነቱ በኮንግሬሱ ፊት ቀርበዉ ምስክርነታቸዉን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት አየር ኃይሉ የነበረዉን ወሳኝ ሚና አጽንኦት በመስጠት ነዉ፡፡

“Airpower is the decisive arm so far, and I expect it will be the decisive arm into the end of the campaign, even if ground forces and amphibious forces are added to the equation.”በወቅቱ ለህብረብሄሩ ጦር  እጃቸዉን የሰጡት የኢራቅ ወታደሮች እንደዚያ ለምርኮ ያበቃቸዉን ምክንያት ሲገልጹ ከምድሩ ይልቅ ከአየር የሚደርስባቸዉን ጥቃት በፈጠረባቸዉ ፍርሃት  እንደሆነ እማኝነታቸዉን  ሰጥተዉ ነበር፡፡

እዚህ ላይ መጥቀስ ያለብኝ ይህ በአየር ኃይልና በምድር ኃይል መካከል “እኔ እበልጥ እኔ” አጉል ፉክክር በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በኃያላኑ አገሮችም ያለ ችግር ነዉ፡፡ በልማዳዊ አስተሳሰብና በተጨባጭ ድርጊት መካካል ሁልግዜም ግጭት ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ (Cultural Conflict versus Reality) እንደሚሉት ማለት ነዉ፡፡. ለዓመታት ተቀባይነት አግኝቶ የቆየዉን “የምድሩ ጦር ሜዳ (battlefield) ለድል ወሳኝ ነዉ” የሚለዉን አመለካከት በሚጋፋ መንገድ “ሁሉንም ነገር በአየር ኃይል መጨረስ ይቻላል” የሚለዉ አዲስና እንግዳ የሆነ አመለካከት አወዛጋቢ ሆኗል፡፡

ለምሳሌ የአሜሪካን አርሚ ወታደራዊ ቁመና የሚገልጸዉ የ1995 እትም የሆነዉ ማኑዋል በግልጽ እንደሚያስቀምጠዉ ምንግዜም በጦርነቱ ለሚኖረዉ ድልም ሆነ ሽንፈት ወሳኝነት የሚኖረዉ በምድር የሚደረገዉ ዉጊያ ነዉ በሚል ነዉ፡፡ “Wars are won on the ground. Success or failure of the land battle typically equates to national success or failure. The culminating or decisive action of a war is most often conducted by land forces…. The application of military force on land is an action an adversary cannot ignore; it forces a decision.” እኛም ይሄን የምድር ዉጊያን ወሳኝነት  መቀበል እንዳለብን አስባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አየር ኃይል ሊኖረዉ የሚችለዉን በጎ ሚና አሳንሶ መመልከት እንደማይገባም መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የአየር ኃይሉን ሚና አለቅጥ አጋኖ ያለ አርሚዉ ብቻዉን ሁሉን ነገር መጨረስ እንደሚችል የመቁጠር የተዛባ አመለካከት ባልተናነሰ ሁኔታ ምድር ኃይሉን ያለ አየር ኃይሉ ተሳትፎ ብቻዉን  ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ ያለጥርጥር እንደሚችል ማሰብ ሁለቱም የተሳሳቱ ናቸዉ፡፡ በተለይ ምድር ኃይሉ ብቻዉን ሁሉን ጣጣ ችሎ ጦርነቱን መጨረስ ይችላል የሚለዉ ለድል ወሳኙም በምድር የሚደረግ ዉጊያ ብቻ ነዉ “only land combat can be decisive” የሚለዉ አመለካከት ምንጩ አየር ኃይሉን ሁልግዜም ድጋፍ ሰጪ ሆኖ እንዲቆይ ከመፈለግ የመነጨ ነዉ፡፡

ይህ አመለካከት የተዛባ መሆኑን የእንግሊዝ የሮያል አየር ኃይል ኮሞዶር የነበሩት አንድሬዉ ቫላንስ እንደሚገልጹት አየር ኃይሉ ሁልግዜ የምድር ኃይሉ አጋዥነት ሚና ላይ ብቻ ተወሰኖ መቀመጥ አለበት የሚባል አመለካከት  መሰረት የለሽ  መሆኑን ነዉ፡ (Air Commodore Andrew Vallance – “There is no factual basis to the belief that, in land campaigns, the purpose of aviation forces must always be to support the land forces.” )

5.3/ የአየር የበላይነትን የመጎናጽፍ አስፈላጊነት ላይ አስከዛሬም ያልተቀረፈ ሰፊ የግንዛቤ ችግር አለ

በጦርነቱ ወቅት በጠላት ላይ የአየር የበላይነት (air superiority) ማግኘት አለብን በሚል በእምነት ተይዞ አልተሰራም፡፡ የአየር የበላይነት ኮንሴፕትም ከነጭራሹ የነበረም አይመስለኝም፡፡ እንኳን በጦርነቱ ወቅት ይቅርና ከጦርነቱ በኋላም ስለአየር የበላይነት አስፈላጊነት ሲነሳባቸዉ በአንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች አካባቢ በእኛ ደረጃ የማይታሰብ የማይቻልና ቅንጦትም ተደርጎ ሲቆጠር እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ስለዚህ በጦርነቱ ወቅት የታየዉ የአየር ኃይሉ የበላይነት (ብልጫ) ታምኖበት የተደረገ ሳይሆን ሁኔታዎች ለእኛ የተሻሉ ስለነበሩ በሁኔታዎች ምቹነት አጋጣሚ የተፈጠረ ነዉ የምመስለኝ፡፡

በሌሎች ሰፊ የጦርነት ልምድ ባላቸዉ የምዕራቡም ሆነ የምስራቁ አገሮች የአየር የበላነትን በቅድሚያ ሳይጎናጸፉ ወይም አየሩን በሚገባ ሳይቆጣጠሩ ጦርነት ማካሄድ ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚያገልጥ ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ አበክረዉ ያስጠነቅቃሉ፡፡ የእንግሊዝ ወታደራዊ ጠበብቶች እንደሚሉት “For the side that does not control the air in modern conventional warfare, military operations on land, sea or in the air are extremely difficult to prosecute without significant risk of failure or large numbers of friendly casualties.”

በተመሳሳይ ሁኔታ ቪስካዉንት ሞንቶጎሞሪ (Viscount Montgomery) “If we lose the war in the air, we lose the war and we lose it very quickly.” በሚል አየሩን (ሰማዩን) መቆጣጠር አለመቻል ለዉድቀት እንሚዳርግ አጽንአት ሰጥቶ ገልጿል፡፡ እንግዲህ ይህን የአየር የበላይነት ማግኘት የሚቻልበት ዋነኛዉ  መንገድም አጥቂ የሆነ ጸረ አየር ዘመቻ (offensive counterair operation) በማድረግ  የጠላት አይፕላኖች ገና ከመሬት ሳይነሱ በመደምሰስ ነዉ፡፡ እናም ይህን ማሳካት ከተቻለ የወገን እግረኛ ሰራዊት ያለ አንዳች ስጋት ወይም የጠላት ተጸኢኖ ግዳጃቸዉን በአነስተኛ ኪሳራ ለመፈጸም ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የወገን አየር ክልልም ከጠላት የአየር ጥቃት ስጋት ነጻ ስለሚሆን ጠቀሜታዉ እጅግ የጎላ ይሆናል፡፡

ወደኛ ሁኔታ ስንመጣ በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለዉ በጦርነቱ ወቅት ለአየር ኃይላችን ቀጣይ ግዳጆች ሁሉ እጅግ ወሳኝ የነበረዉን ግን ደግሞ በሚገባ ሳንጠቀምበት ያመለጠን መልካም አጋጣሚ የነበረዉ ሰኔ 28 ቀን 1990 ዓ/ም በአስመራ  ኤርቤዝ ላይ ያደረግነዉ ድንገተኛ ጥቃት ወይም ኦፕሬሽን ነዉ፡፡ የአየር ኃይል አመራር የሻእቢያ  አይሮፕላኖች ገና ከመሬት ሳይነሱ እዚያዉ መሬት ላይ እያሉ ከጥቅም ዉጭ በማድረግ ለኛ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር አስቦ ያቀደዉ ይህ እቅድ እጅግ የሚደነቅና  እንደታሰበዉ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ዉጤት ማምጣት በቻለ ነበር፡፡

ሆኖም እቅዱ ግሩም ሆኖ እያለ በተግባር ግን በሚገባ ማሳካት አልቻልንም፡፡ አየር ኃይሉ በወቅቱ በነበረዉ የአቅም ዉስንነት የተነሳ በእጁ የነበሩትን አራት ሚግ-23 ቦንበር አይሮፕላኖችን በመጠቀም ከባህርዳር አየር ጣቢያ በማስነሳት ድንገተኛ ጥቃት ለማድረስ አቅዶ ነበር፡፡ ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ ከዚያችዉ ዉስን ከነበረዉ የአይሮፕላን ቁጥር ዉስጥ ሁለቱ አይሮፕላኖች በቴክኒክ ችግር ምክንያት ወደ አስመራ መሄድ ባለመቻላቸዉ ግዳጁን ለመወጣት የተሞከረዉ በሁለት አይሮፕላኖች ብቻ ነበር፡፡

አራቱም ፓይሌቶች የረዥም ግዜ የጦርነት ልምድ የነበራቸዉና አስመራን በሚገባ የሚያዉቁም ስለነበር ብዙ ተስፋ ተደርጎ  ነበር፡፡ ሆኖም በአራት አይሮፕላኖች ታስቦ የነበረዉን ግዳጅ በሁለት ብቻ እንዲሰራ በመደረጉ ይሄ ነዉ የሚባል የረባ ዉጤት አልተገኘበትም፡፡ ይሄን ስል አስመራ ኤርቤዙ ዉስጥ በወቅቱ ከነበሩ አይሮፕላኖች መካከል መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት ስላልነበር አይደለም፡፡ ዋናዉ ተልዕኮዉ ግቡን አልመታም እያልኩ ያለሁት የጠላትን አየር ኃይል በማኮላሸት  ለጥቂት ሰዓታት እንኳን ከዉጊያ ዉጭ (neutralize) ማድረግ ባለመቻላችን ነዉ፡፡

አይሮፕላን አስነስቶ ጠላት ወረዳ ዉስጥ ገብቶ መመለስን እንደብቸኛ ብቃት መለኪያ ለሚቆጥሩ አንዳንድ የዋህ ሰዎች ምናልባት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ በትክክለኛዉ መንገድ ከታየ ግን በጥቃት ሙከራዉ መጠነኛ ጉዳት ከማድረሱ በስተቀር እንደታሰበዉ የሻእቢያ አይሮፕላኖች ከመሬት እንዳይነሱ ማድረግ አለተቻለም፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነዉ የኛ አይሮፕላኖች አስመራ ደርሰዉ እንደተመለሱ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ከዚያዉ ከአስመራ ቤዝ የተነሱ የሻዕቢያ መለማመጃ አይሮፕላን አም.ቢ-339 በመጠቀም መቀሌ ድረስ የኛን አይሮፕላኖች ተከትለዉ በመምጣት በመቀሌ ኤርቤዝና በአይደር ት/ቤት ህጻናት ላይ ጉዳት ማድረሳቸዉ ነዉ፡፡

እንዲያዉም አስመራ ላይ ጥቃት አድርሶ ከተመለሱት  የኛ ፓይሌቶች መካከል አንዱ መቐለ ራንዌይ ላይ ይዞት የመጣዉ አይሮፕላን አጠገብ ቆሞ በነበረበት ሰዓት በሻእቢያ ጥቃት ሙከራ ለክፉ የማይሰጥ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰበት እናዉቃለን፡፡ እኛ እንደ እቅዳችን ከባድ ጉዳት አድርሰን ቢሆን ኖሮ የሻእቢያ አይሮፕላኖች በአጭር ቅጽበት ተነስተዉ  መቐለ ድረስ ተከትለዉ በመምጣት ጉዳት ሊያደርሱብን ባልቻሉ ነበር፡፡

እኔ እንደገባኝ  ሻዕቢያ ወረራዉን (ጦርነቱን) በምድር ቀድሞ ይጀምር እንጂ በአየር ኃይል ደፍሮ ጥቃት ለማድረስ ጠንካራ ፍላጎት የነበረዉ አይመስለኝም፡፡ የሻዕቢያ አመራሮች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ድሮ እንደሚያዉቁት ጠንካራ እንዳልሆነና በርካታ ጉድለቶች እንዳሉት ከበቂ በላይ መረጃዉ ቢኖራቸዉም አየር ኃይሉን አጉል ነካክተዉ ወደ ጦርነት ማስገባት ግን  የፈለጉ አይመስለኝም፡፡ ጦርነቱ ያለ አየር ኃይል ተሳትፎ እንዲከናወን የፈለጉ ይመመስለኛል፡፡

በተጨማሪ ገና በመቋቋም ሂዴት ላይ የነበረዉን አየር ኃይሏን ገመና ወይንም ድክመት ማጋለጥም ስላልፈለጉ በኋላ እንዳደረሁት መቐለ ድረስ ዘልቀዉ ለማጥቃት ዉጥን የነበራቸዉ አይመስለኝም፡፡ በኋላ ላይ ግን እኛዉ ራሳችን ቀድመን ያልተሳካና ብዙም ዉጤታማ ያልነበረ የአየር ጥቃት በአስመራ አየር ጣቢያ ካደረግን በኋላ ለበቀል መነሳሳታቸዉ አልቀረም፡፡

ሻዕቢያ የኛን አየር ኃይል ዝግጁ አለመሆን አንድ ግዜ ከተገነዘቡ በኋላ በሌላ ግዜ ዳግመኛ ሌላ እድል እንደማያገኙ በመረዳታቸዉ  የመለማመጃ አይሮፕላን በመጠቀም በአንድ ቀን ብቻ እየተመላለሱ በመቐለ ኤርፖርት፤ በከተማዉ እንብርት በሚገኘዉ የአይደር ት/ቤት ከዚያም አክሱም በጅምር ላይ በነበረዉ የበረራ መቆጣጠሪያ ታወር እንዲሁም በአዲግራት እህል ማከማቻ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሞክረዋል፡፡

ሻዕቢያ በወቅቱ በመለማመጃ አይሮፕላን ተጠቅሞ የረባ ጉዳት ማደረስ እንደማይችል ያዉቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሻዕቢያ አየር ኃይል ሙከራቸዉ ዉጤታማ ባይሆን እንኳን ቢያንስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘልቆ በመግባት ግዳጅ ፈጽሞ በሰላም መመለስ የሚችል አየር ኃይል ባለቤት መሆናቸዉን ለህዝባቸዉ ለማሳየት አስችሎአቸዋል፡፡ ከኢላማ አመራረጣቸዉ አኳያ ሲታይም የአይደር ት/ቤትና በከፊልም የአድግራቱ እህል ማከማቻና የመድሃኒት ፋብሪካ ከወታደራዊ ኢላማ ዉጭ በመሆናቸዉ በዚያ ላይ ጥቃት ለማድረስ ያደረጉት ሙከራ በጦር ወንጀለኛነት አለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት የሚያቆማቸዉ ነዉ፡፡

ከዚያ ዉጭ ግን በመቐለና የአክሱም አየር ጣቢያዎችን ለማጥቃት የደረጉት መከራ ብዙም ባይሳካላቸዉም ኢላማ አመራረጣቸዉ ትክክል ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እጅግ በቁጥር ዉስን በሆነ አይሮፕላን ተጠቅመዉ በአንድ ቀን በተለያዩ ኢላማዎች ላይ ለማጥቃት መሞከራቸዉ በጠንካራ ጎን ሊጠቀስላቸዉ የሚገባ ነዉ፡፡ ሻዕቢያ በመቐለ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲነሳሱ እንቅፋት ሊሆናቸዉ ይችል የነበረዉን የአየር መከላከያ ክፍሎችን በቅድሚያ ከጥቅም ዉጭ (neutralise) ለማድረግ ያልሞከሩት ባለማወቅ ሳይሆን በወቅቱ ሊቀናቀናቸዉ የሚችል ዝግጁ የሆነ የአየር መከላከያ ኃይል እንዳልነበረን መረጃዉ ስለነበራቸዉ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

ሻዕቢያ አሰቀድመዉ እንደገመቱት ከጥቂት ሳምንታት ዝግጅትግዜ በኋላ የኢፌድሪ አየር ኃይል ከሞላ ጎደል ዝግጁ መሆኑን በመረዳታቸዉ አጉል መንፈራገጥ ለመላላጥ እንዳይሆንባቸዉ በመስጋት አየር ኃይላችን በደረሰበት ላይደርሱና የአየር ክልላችንንም ድጋሚ ላይደፍሩ የተማማሉ ይመስል ይሄዉ አስከዛሬ ወደ ድንበራችን ዝር ሳይሉ ቆይተናል፡፡ ራሳችንን በሻዕቢያ ቦታ አስቀምጠን ስናየዉ በወቅቱ የሻእቢያ አየር ኃይል ድክመት የነበረዉ እኛ ላይ ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩ ሳይሆን ለዚህ ዓላማ እዉን መሆን የሚያበቃዉን ትጥቅ (አይሮፕላን) ያልነበረዉ መሆኑ ነዉ፡፡ በኃላ እንዳደረገዉ በወቅቱ ሚግ -29  አይሮፕላኖች ቢኖሩት ኖሮ በኛ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርሱብን እንደሚችሉ ለመረደት አያዳግትም፡፡

በወቅቱ የአየር ኃይሉ አመራር አጥቂ ጸረ የአየር ዘመቻ (offensive counter-air opperation) መሪህ መሰረት የጠላትን አየር ኃይል አቅም ገና ከመሬት ሳይነሳ በመደምሰስ ለቀጣዩ ለኛ ሰራዊት አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል በሚለዉ መሪህ  መስረት የወሰነዉ ዉሳኔና ዕቅድ እንከን የማይወጣዉና የአመራሩን ብልህነት የሚያሳይ በመሆኑ የሚያስተች ሊሆን  አይችልም፡፡ ቸግሩ ግን የአቅም ዉስንት በመኖሩ በተግባር እዉን ማድረግ አለመቻላችን ነዉ፡፡

ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ አስካሁንም ልገባኝ ያልቻለዉ ጉዳይ በሻዕቢያ ኤር ቤዝ ላይ ቀደምትነትን ወስደን ያደረግነዉን የጥቃት ሙከራ ለመደባበቅ የተሞከረበት ምክንያት ነዉ፡፡ ከኤርትራ ጋር በራሳቸዉ ቆስቋሽነት የተጀመረ ጦርነት ዉስጥ እንዳለን ይታወቃል፡፡ እኛ የጦርነቱ ሰለባ እንጂ የጦርነቱ ጀማሪ አለመሆናችንም በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ወደ ጦርነት የገባነዉ ሻዕቢያ ወረራ ከፈጸመብን ከግንቦት 4 1990 ዓ/ም ጀምሮ ነዉ፡፡ በድንበር አካባቢ ከአንድ ወር ላላነሰ ግዜም ከሞላ ጎደል በጦርነት ላይ ቆይተናል፡፡

ታዲያ አየር ኃይላችን ከነሱ ቀድሞ አስመራ ኤር ቤዝ ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩን እንደ ጦርነቱ ጀማሪ ያስቆጥርብናል ተብሎ ተሰግቶ ነዉ ወይንስ ሌላ ምክንያት ቢኖር ነዉ ለመደባበቅ የሞከርነዉ፡፡ እኛ በአየር ኃይል ጥቃት በማድረስ ቀዳሚ መሆናችን (pre-emptive attack) እነሱ ደግሞ አጸፋ እርምጃ የወሰዱ (retaliatory attack) መሆናቸዉን እንዳይገለጽ ብዙ መደከሙ ምክንያቱና አስፈላጊነቱ አስካሁንም ልገባኝ አልቻለም፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አዘዉትሮ ስሙ የሚጠቀሰዉ እዉቁ የጣሊያን ጄኔራል ጉሊዮ ዶት ( Giulio Douhet) ከበርካታ ዓመታት በፊት የጠላትን አይሮፕላኖች ገመሬት ላይ እንዳሉ ወይም ገና ከመሬት ሳይነሱ መደምሰሱ ያለዉን ጠቀሜታ የገለጸበት መንገድ ነዉ፡፡  “it is easier and more effective to destroy the enemy’s aerial power by destroying his nests and eggs on the ground than to hunt his flying birds in the air.”  የአሜሪካ ኤር ዶክትሪንም ስለዚህ ጉዳይ አበክሮ ይገልጻል፡፡  አየር ኃይል አይሮፕላኖች  መሬት ላይ ባበት ሁኔታ ች በቀላሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆነና ምንም ሊያደርግ የማይችሉ እንደሆነ “Air power is most vulnerable on the ground.” በሚል ይገልጸዋል፡፡

6/ ማጠቃለያ

በሚገባ የተዘጋጀ አየር ኃይል ለምድር ኃይሉ መከታና አጋዥ ከመሆኑም ሌላ ራሱን ችሎም በርካታ አኩሪ ስራ ሊሰራ ይችላል፡፡ ምንም ዝግጅት የሌለዉ አየር ኃይል በሆነበት ሁኔታ ከአቅሙ በላይ እንዲሰራ መጠበቅም አይቻልሞ፡፡ አየር ኃይላችን የተደፈረዉን ሉአላዊነቱን ለማስከበር ከኤርትራ ጋር የተፋለመዉ ባልተሟላ ሁኔታ ዉስጥ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነዉ፡፡

በዚህ ምክንያም አየር ኃይላችን በጠላት ላይ ካደረሰዉ አካላዊ ጉዳት (physical damage) ይልቅ በጠላት ሰራዊትና አመራር ላይ ያደረሰዉ ስነሊቡናዊ ጉዳት (psychological damage) እጅግ ከፍተኛ እንደነበር አምነን ከመቀበል ዉጭ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ለወገን ሰራዊት ሞራል ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉም በበጎ ጎን ሊጠቀስ የሚገባዉ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን የአየር ኃይልን ሚና አለቅጥ አጋኖ ማየትም ሆነ ሚናዉን አሳንሶ የማየት ጉዳይ ሁለቱም አመለካከቶች ጎጂ በመሆናቸዉ ሊስተካከሉ ይገባል፡፡

በተለይ የአመለካከቱ ዋነኛ ተሸካሚ ከፍተኛዉ አመራር መሆኑ የበለጠ አሳሳቢ ነዉ፡፡ በሚገባ ኢንቬስት የተደረገበት አየር ኃይል በችግር ግዜ ሀገሪቱን  ከአደጋ ይታደጋል፡፡ ለአየር ኃይሉ ለግዳጁ የሚያስፈልገዉን ሁሉ ሟማላት ባልቻልንበት ሁኔታ ሚናዉን አሳንሶ የማየት የተዛባ አመለካከት ሊቀረፍ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፡በሻእቢያ የተላከች መናኛ አይሮፕላን በአንዲት መጥፎ አጋጣሚ በአይደር ት/ቤት ህጻናት ላይ  የደረሰዉን ጭፍጨፋ ወይም ጉዳት የተመለከተ ሰዉ ለአየር ኃይል የንቀት አመለካከት በጭራሽ አይኖረዉም፡፡ ይህ አመለካከት ተስተካክሎ እንደሆን ወይንም አስከዛሬም እልተለወጠ እንደሆን መረጃዉ ባይኖረኝም የተሻለ ለዉጥ እንደሚኖር ግን እገምታለሁ፡፡ እንደዚያ እንዲሆንም ከልቤ እመኛለሁ፡፡

አየር ኃይላችንን ከእንግዲህ መገንባት ካለብን ከግብጽ ጋር ሊኖር የሚችለዉን ምናልባታዊ ጦርነት በሚመጥን መልኩ መሆን አለበት፡፡ የአየር ኃይልን አቅም የማሳደግ ስራ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የትኞቹም ጠንካራ አየር ኃይል መስርተዋል የሚባሉ አገሮች ለዚያ ስከት ለመብቃት ለበርካታ አመታት ጥረት በማድረግ እንጂ በአንድ ዓመት እዉን መሆን የቻለ አይደለም፡፡

እኛም ብንሆን ጠንካራ አየር ኃይል የመመስረት ዉጥናችንን  ባንድ ጊዜ እዉን ማድረግ ባንችልም ነገር ግን ቀስ በቀስ በላይ በላዩ እየጨመርን የምንፈልገዉ ደረጃ ላይ ማድረስ እንችላለን፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ዛሬ አገራችን ባህር ኃይል የላትም፡፡ በዚህ ምክንያትም አገራችን አንድ ትልቅ የመከላከያ አቅሟን ማጣቷ ግልጽ ነዉ፡፡ በአንጻሩ ከኛ በቅርብ ርቀት በሚገኘዉና እኛ ማዘዝ በማንችልበት ቀይ ባህር እንደልባቸዉ መንቃሰቀስ የሚችሉ ጠላቶች አሉን፡፡ ከኛ ጋር ወደፊት ለሚኖራቸዉ ጦርነት እንደ መንድርደሪየ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ለማንም ግልጽ ነዉ፡፡

ቀይ ባህርን መነሻ በማድረግ ከመርከብ በሚወነጨፍ ክሩዝ ሚሳይልም ሆነ በቀጥታ በአይሮፕላን የሚሰነዝር ጥቃትነ መመከት የሚንችልበት አንዳችም አማራጭ የለንም፡፡ ሁልግዜም ቀደምትነቱ የጠላት ስለሚሆን እኛ ተከላካይ ከመሆን ዉጭ በጠላት ላይ መወሰን የሚያስችለን እድል ዝግ ነዉ፡፡  ነገር ግን የባህር በር መዉጫም ሆነ ባህር ኃይል ባይኖረንም ይህንን ጉድለት በከፊልም ቢሆን ሊያካክስልን የሚችለዉ ብቸኛዉ አማራጭ አየር ኃይላችን ነዉ፡፡

“እንዴት አየር ኃይል የባህር ኃይልን ሚና ሊተካ ይችላል?” የሚል ጥያቄ ይነሳል ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸዉ የመከላከያ ሰዎች ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ወደዚያ ሃተታ መግባት አያሻኝም፡፡ ቢያንስ ግን አይሮፕላኖች በየብስ በባህርና የአየር ድንበር ሳይያግዳቸዉ ረዥም ርቀት ተጉዘዉ በአጭር ግዜ ግዳጅ ፈጽመዉ የመመለስ ብቃት ስላላቸዉ የባህር ኃይልን ሚና በተወሰነ ደረጃ ለመተካት ይችላሉ፡፡

ቢያንስ በቀይ ባህር እየተነሳ ለማጥቃት የሚሞክረዉን እዚያዉ ድረስ በመሄድ ለማምከን ወይንም ደግሞ ጠላት አየር ኃይል ወደምንሳሳላቸዉ ስትራቴጂያዊ ተቋሞቻችን ከመድረሱ በፊት በርቀት መትተን ለማስቀረት የምንችለዉ በአየር ኃይል ብቻ ነዉ፡፡ ለዚህም ነዉ ባህር ኃይል ባይኖረንም የባህር ሃይሉንም ድርሻ በከፊልም ቢሆን  ሊያካካስልን የሚችለዉ አየር ኃይል ነዉ ያልኩት፡፡

በአሁኑ ወቅት በመላዉ ዓለም የአየር ኃይል ሚና እየጎላ የመጣበት አንዱ መነሾ ይሄዉ ቀልጣፋነቱ ነዉ፡፡ ኢስራኤል በዙሪያዋ የከበቧትን ያን ሁሉ ጠላቶቿን ለመቋቋም ያገዛት ምናልባትም ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ያለዉ ጠንካራ አየር ኃይል ባለቤት መሆኗ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እኛም  ወደድንም ጠላንም ለወደፊቱ ከግብጽ ጋር ለሚኖረን ወሳኝ ፍልሚያ አየር ኃይል የሚኖረዉን ወሳኝ ድርሻ በመገንዘብ ካሁኑ የአየር ኃይላችንን ሁለንተናዊ አቅም መገንባት ይገባናል፡፡

ከግብጽ ጋር ወደፊት በማንኛዉም ወቅት የምንጠብቀዉ ጦርነት በምድር የሚደረግ ዉጊያ እንደማይሆን ግልጽ ነዉ፡፡ ስለዚህ ከዚያ አኳያ ከአሁኑ መዘጋጀቱ ብልህነት ነዉ፡፡ ለግብጽ የምናደርገዉ ዝግጅት አይር ኃይልን አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮረ ሆኖ ከዚህ ጎን ለጎን እንደ አማራጭ ሊታይ የሚችለዉና ከወጭዉም አኳያ እምብዛም ያልሆነዉ ከምድር ወደ ምድር የሚወነጨፉ ኮንቬንሽናል የሆኑ ታክቲካል ሚሳይሎችን እንዲኖሩን ማድረግ ነዉ፡፡

በዚህ ረገድ አስካሁን የተሰራ ስራ እንዳልነበር አዉቃለሁ፡፡ ከዚህ በኋላም ቢሆን ታስቦበት ከተሰራ በአጭር ግዜ እዉን ሊሆን የሚችል ነዉ፡፡ መከላከያ ጠንካራ የኢንጂኔርንግ አቅም እየገነባ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሄንን አቅም ለዚህ አይነቱ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ መጠቀም ያለበት ይመስለኛል፡፡

***********

(የዚህን ፅሁፍ ቀጣይ ክፍሎች በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories