ለስኳር ኮርፖሬሽን በቂ የአስተዳደር ስርዓት አልዘረጋሁም ~ አባይ ጸሐዬ (+video)

ለስኳር ኮርፖሬሽን በቂ የኮንትራክት አስተዳደር እና የቅንጅት መዋቅር፣ አለመዘርጋታቸውን እና ይህም የአመራር ድክመት መሆኑን የገለጹት አቶ አባይ ጸሐዬ፤ በሙስና ረገድ ግን ንጹህ መሆናቸውን ገለጹ።

አቶ አባይ ጸሐዬ በተለይ ከሆርን አፌይርስ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ ሙስናን የሚጠየፉና በግል ያከማቹት ሀብት እንደሌላቸው በአጽንኦት ገልጸዋል።

ከ2002-2005 ዓመት ድረስ ለ3 ዓመታት በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅነት የሰሩት አቶ አባይ ጸሐዬ፤ በስኳር ፕሮጀክቶች ግንባታ በርካታ ባለድርሻ አካላት እንደነበሩ ገልጸው፤ በዕቅድ ከተያዙት የስኳር ፕሮጀክቶች 6ቱ ለሜቴክ እንዲሰጡ የተደረገው በመንግስት ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ እሳቸው በስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ከ6ቱ ፕሮጀክቶች 2ቱ ከሜቴክ ተወስደው ለሌሎች ድርጅቶች መሰጠታቸውን እና በሳቸው ግዜ እላፊ ክፍያ(over payment) እንዳልተፈጸመ አውስተዋል። ያ አሰራር የተጀመረው እሳቸው ከለቀቁ በኋላ በመንግስት ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ እሳቸው መሬት የመስጠት ስልጣን እንዳልነበራቸው ገልጸው፤ በወቅቱ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ድንበር የሚያካልል ሳይሆን ማንም ገበሬ ሳይፈናቀል ሁሉም ባለበት እንዲቆይ እና ድንበሩ ወደፊት እንዲወሰን የሚያስቀምጥ እንደነበር ገልጸዋል።

ሱዳኖች በአጼ ኃይለስላሴ ግዜ በተፈረመ ስምምነት መሰረት ወደ300 ሺ ሄክታር ይገባናል በማለታቸው፤ መንግስት ደግሞ ያንን ለማድረግ ባለመሻቱ፤ ለግዜው ሁሉም ባለበት እንዲቆይ እና መፈናቀል ሆነ አዲስ ሰፈራ እንዳይኖር የሚያደርግ መግባቢያ ሰነድ እንጂ ምንም አስገዳጅነት እንደሌለው ተናግረዋል።

በነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ከታች ከቪዲዮው ይመልከቱ።

—–

*******

Daniel Berhane

more recommended stories