የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ)

እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ ፈፀሙት ተብለው በተጠረጠሩበት የሙስና ውንጀል ምክንያት ባለፈው እሮብ ጥር 15፣ 2011 ዓ/ም አዲስ አበባ በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ውስጥ እያሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ እስሩን የፈጸሙት ኣካለት በግልፅ ለማቅ ኣስቸጋሪ ቢሆንም አንዳንድ ሚድያዎች የአማራ ፖሊስ ልዩ ሐይል ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር እንደፈጸሙት ሲገልፁ በማሕበራዊ ሚድያ የተሰራጨው ፎቶ ግራፍ (ምስል) እንደሚያሳየው ደግሞ የልዩ ሓይል ፖሊስ መለዮ የለበሱ በርካታ አባላት አቶ በረከት ስምዖንን በቁጥጥር ስር ስያውሉ ያሳያል፡፡

የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ሁለቱም ባለስልጣኖች የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈፅመዋል ወይስ ኣለፈፀሙም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አይደለም (ምክንያቱም ዝርዝር ክሶች ይፋ ስላልሆኑና ስለጥፋተኛነታቸው የመወሰን ስልጣን የፍ/ቤቶች ስለሆነ)፡፡ ይልቁንስ የፅሑፉ ዓላማ ሁለቱም ባለስልጣኖች በአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል በቁጥጥር ስል እንዲውሉ መደረጉ አግባብ ካላቸው የስነ-ስርዓት ሕጎች (Procedural Laws) አንፃር ሲታይ ሕጋዊነት አለው ወይ? ፈፀሙት የተባለው ድርጊትስ በወቅቱ ስራ ላይ በነበሩት ሕጎች አንፃር በሙስና ወንጀል ሊያስጠይቃቸው ይችላል ወይ; የሚሉትንና ተያያዥ ነጥቦች ለመዳሰስ እና በዚሁ መሰረት የተወሰደው እርምጃ ያለው አንድምታ ምን ሊሆን ይችላል (ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ) የሚለውን መላምት ለማሳየት ነው፡፡

ይህ ፅሑፍ ለመፃፍ የሚከተሉትን ሕጎችና ከተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የተገኙ መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ነው፡፡

* የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት፤

* የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ፤

* የተሻሻለው የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነን ማቋቋምያ የወጣ ኣዋጅ ቁጥር 433/1997 ዓ/ም (በአዋጅ ቁጥር 883/2007 ዓ/ም እንደተሸሻለው)፤

* የተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ሕግ የወጣ ኣዋጅ ቁጥር 434/1997 ዓ/ም (በአዋጅ ቁጥር 882/2007 ዓ/ም እንደተሸሻለው)፤፤

* የሙስና ወንጀሎች ሕግ ኣዋጅ ቁጥር 881/2007 ዓ/ም፤

* የተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ሕግን (ማሻሻያ) ኣዋጅ ቁጥር 882/2007 ዓ/ም ፤

* የተሻሻለው የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነን ማቋቋምያ (ማሻሻያ) ኣዋጅ ቁጥር 883/2007 ዓ/ም፤ እና

* በተለያዩ የሚድያ አውታሮች እና የመንግስት አካላት የተሰጡ መግለጫዎች ይገኙበታል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ዋቢ ሕጎችና ማስረጃዎች መሰረት በማድረግ በአጠ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የተፈፀመው እስርና የሙስና ወንጀልን የመፈፀም ጥርጣሬ ወይም ክስ ሕጋዊነት እንደሚከተለው ለማየት ሞክርያለሁ፡፡

የሙስና ወንጀል ሲፈፀም ጉዳዩ የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የማን ነው?

በሙስና ወንጀል ዙርያ ወሰነ-ስልጣን (Jurisdiction) የማን ነው (የክልል ወይስ የፌዴራል ጠቅላይዓቃቤ-ሕግ)? የሚለውን በተመለከተ በሁለት መልኩ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው የሙስና ወንጀል ተፈፅሟል የሚል ጥርጣሬ ሲኖር ጉዳዩን የመመርመር ስልጣን ያለው የማን ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከምርመራ በኋላ ክስ የመመስረት ስልጣን የማን ነው የሚሉትን ናቸው፡፡ የመጀመርያውን ጥያቄ በተመለከተ አግባብነት ያላቸው ሕጎች ስለጉዳዩ የሚደነግጉት እንደሚከተለው ባጭሩ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

አዋጅ ቁጥር 433/1997 በአንቀፅ 7 ንኡስ-አንቀፅ 4 (እንደተሸሻለው) መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል መንግስት መስርያ ቤቶች፣ በፌዴራል መንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ወይም በፌዴራል መንግስት ህዝባዊ ድርጅቶች ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ (የፌዴራልም ሆነ የክልል) ህዝባዊ ድርጅቶች እንዲሁም የፌዴራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ በክልል መስርያ ቤቶች በሙስና ወንጀሎች ኣዋጅ ቁጥር 881/2007 ዓ/ም  እና በሌሎች ሕጎች ውስጥ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች ባለ ስልጣኖች፣ ወይም ሰራተኞች፣ ወይም በሌሎች ሰዎች ስለመፈፀማቸው ጥርጣሬ ሲኖረው የመመርመርና የመክሰስ ወይም እንዲመረመሩ የማድረግ ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከነዚህ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለው ከክልል መስርያ ቤቶች በስተቀር ማናቸውም በሙስና ወንጀሎች ኣዋጅ ቁጥር 881/2007 እና በሌሎች ሕጎች ውስጥ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች መፈፀማቸውን ጥርጣሬ ሲኖር ጉዳዩ የመርመርና የመክሰስ ስልጣን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሆኑን ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከላይ የተገለፁት የሙስና ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ወቅት የክልሎች ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል ከአዋጆቹ መረዳት የሚቻል ሲሆን እነዚህም በሁለት መልኩ ተለይተዋል፡፡ የመጀመርያው ምርመራ ማካሄድን ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 433/1997 ዓ/ም አንቀፅ 8 (1) የፌዴራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ወቅት ድርጊቱ ከባድ የሙስና ወንጀል (Grand Corruption) ካልሆነ በስተቀር እንደሁኔታው የክልሎች ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ጉዳዩን እንዲመረምሩ በከፊል ወይም አጠቃላለይ ሙሉ ውክልና በጠ/ዓቃቤ ሕግ በኩል ሊሰጣቸው እንደሚችል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተመሳሳይ ጉዳች ላይ የክልሎች ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ውክልና ሳያገኙ ምርመራ መጀመር እንደሚችሉና ይሁን እንጂ ምርመራ ስለመጀመራቸው ለጠ/ዓቃቤ ሕግ ወድያውኑ ማሳወቅ እንዳለባቸውና የፌዴራል ጠ/ዓቃቤ ሕግም ሪፖርቱን እንደደረሰው ጉዳዪን ራሱ የመመርመር ወይም ሪፖርት ላደረገው መርማሪ ኣካል (ኮሚሽን) ውክልና ሊሰጥ እንደሚችል በአዋጅ ቁጥር 433/1997 ዓ/ም አንቀፅ 8 (2 እና 3)፡፡ ከነዚህ ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው  ከክልል መስርያ ቤቶች በስተቀር ሌሎች የሙስና ወንጀሎች ያለ ጠ/ዓቃቤ ሕግ እውቅናና ውክልና መመርመር  እንደማይችሉ ነው፡፡

ሌላው የመክሰስ ስልጣን የሚመለከት ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 433/1997 ዓ/ም በአንቀፅ 9 (1) ላይ ጠ/ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ስልጣን ስር የሆኑት የሙስና ወንጀሎችን  በተመለከተ ለክልሎች ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የመክሰስ የውክል ስልጣን ሊሰጣቸው እንደሚችል ያሰቀምጣል፡፡ ሆኖም በዚህ አዋጅ (እንደተሸሻለ) አንቀፅ 9 (3) ላይ በግልፅ እንደተገለፀው የፌዴራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ በክልል መስርያ ቤቶች ከሚፈፀሙት የሙስና ወንጀሎች በስተቀር ከላይ እንደተገለፀው በፌዴራል መንግስተ የስልጣን ክልል ስር የሆኑት የሙስና ወንጀሎችን በተመለከተ በጠ/ዓቃቤ ሕግ ውክልና ካልተሰጠው በስተቀር ማንኛውም የመክሰስ ስልጣን ያለው ኣካል (የክልሎች ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ጨምሮ) መክሰስ እንደማይችል በማያሻማ መልኩ ይደነግጋል፡፡

ከላይ እንደተገለፀው የሙስና ወንጀሎችን የመመርመርና የመክሰስ መብት በተመለከተ ካሉት የሕግ ድንጋጌዎች ኣንፃር ሲታይ የአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን በአማራ ክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቁጥጥር ስር የመዋላቸውን ሕጋዊነት እንዴት ይታያል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ መሆኑ ያለበት ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ለመመለስ ሁለት የሕግና የፍሬ-ነገር ጥያቆዎች ማንሳት የግድ ይላል፡፡ የሕግ ጥያቄው ሁለቱም ሰዎች የተጠረጠሩቧቸው የሙስና ወንጀሎች የመመርመርና የመክሰስ ሕጋዊ ስልጣን የማን (የክልል ወይስ  የፌዴራል መንግስት) ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ የፍሬ-ነገርና የሕግ ጥያቄ አንድ ላይ የያዘ እንዲሁም አንደኛው ጥያቄ ላይ የሚኖረው መልስ ላይ የሚወሰን ሲሆን ወንጀሎቹን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን   የክልሎች ከሕግ የመነጨ ስልጣን አይደለም ከተባለ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች ስልጣኑን በውክልና ሰጠበት አለወይ የሚል ይሆናል፡፡ ጥያቄዎቹን እንደሚከተለው ለማየት ሞክርያለሁ፡፡

ሀ. ሁለቱም ሰዎች የተጠረጠሩቧቸው የሙስና ወንጀሎች የመመርመርና የመክሰስ ሕጋዊ ስልጣን የማን ነው?

በርግጥ ሁለቱም ሰዎች የተጠረጠሩቧቸው የሙስና ወንጀሎች ዝርዝር እርግጠኛ ሆኖ መግለፅ የሚያስችል በቂ ማስረጃዎች ለግዜው ባይኖሩም በተለያዩ የሚድያ አውታሮች እየወጡ ካሉት መረጃዎችና አንዳንድ መሰል ማስረጃዎች በመነሳት መላምት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ሰዎቹን የተጠረጠሩቧቸው የሙስና ወንጀሎች ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መነሳት ያለባቸው ሲሆን ጥያቆዎቹን እንደሚከተለው ማቅረብ ይቻላል፡፡

* ጥረት ኮርፖሬት  የአማራ ክልል መንግስት የልማት ድርጅት ነው ወይስ ህዝባዊ ድርጅት?

* ጥረት ኮርፖሬት  የአማራ ክልል መንግስት የልማት ድርጅት ነው ከተባለ በድርጅቱ የሚፈፀሙ  የሙስና ወንጀሎች በተመለከተ የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የማን ነው?

* ጥረት ኮርፖሬት  ህዝባዊ ድርጅት ነው ከተባለ በድርጅቱ የሚፈፀሙ  የሙስና ወንጀሎች በተመለከተ የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የማን ነው?

* ከላይ ላሉት ጥያቄዎች የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የፌዴራል መንግስት ነው ከተባለ የአማራ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን  ሁለቱን ተጠርጣሪዎች የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን ከወዴት አገኘው የሚሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡

የመጀመርያው ጥያቄ ስናይ ጥረት ኮርፖሬሽን እስከ ነሓሴ 2010 ዓ/ም በኢንደውመንት መልኩ የህዝብ ድርጅት (Public Organization) ሆኖ ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን በ ነሓሴ 2010 ዓ/ም ደግሞ  የአማራ ክልል መንግስት የልማት ድርጅት እንዲሆን ተወስኗል (ውሳኔው በሕግ እውቅና አግኝቶ ስለመመዝገቡ የተገለፀ ነገር የለም)፡፡ ስለሆነም ጥረት ኮርፖሬት እስከ ነሓሴ 2010 ዓ/ም ኢንደውመንት (የህዝብ ድርጅት) እንጂ የአማራ ክልል መንግስት የልማት ድርጅት ነበረ ማለት አይቻለም፡፡  በቀጣይ መታየት ያለበት ነገር  እስከ ነሓሴ 2010 ዓ/ም ተፈፀሙ የተባሉት ጥፋቶች ካሉ በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸውን? በሙስና ወንጀል ያሚያስጠይቁ ከሆነስ ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የማ ነው? የሚሉት ናቸው፡፡

በጥረት  ኮርፖሬት ከተመሰረተበት ግዜ ጀምሮ ቢያንስ እስከ መጋቢት25፣ 2007 ዓ/ም ድረስ የተፈፀሙ ጥፋቶች ካሉ  የሙስና ወንጀሎች ተብለው ሊያሰከስሱ የሚያስችሉ አይደሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተጠቀሰው ግዜ ማንኛውም ሰው በሙስና ወንጀል ተጠያቂ የሚሆነው ከመንግስት መስርያ ቤቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች በተመለከተ እንጂ ከግል ተቋማት፣ በህዝባዊ ድርጅቶች (የግብረ-ሰናይና ድርጅቶች፣ በሲቪክ ማሕበራት እንደጥረት ያሉ ኢንደውመንቶች፣ ወዘተ) በተያያዘ የሚፈፀሙ ጥፋቶች ብቻ እንደሆነ መጋቢት25፣ 2007 ዓ/ም የፀደቀው የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 ዓንቀፅ 34 ላይ በግልፅ ተደንግጓል፡፡

ይህ ደግሞ ድርጊቱ ሲፈጸም ወንጀል ተብሎ በሕግ ያልተደነገገ ጥፋት ሆኖ ሊያሰቀጣ የሚያስችል ኣይደለም (No Law-No Crime; No Crime-No Punishment) እና የወንጀል ሕግ ተጠርጣሪውን የሚጠቅም ካልሆነ በስተቀር ወደኋላ ተመልሶ ሊሰራ አይችልም (Non-retroactivity of Criminal Laws) ከሚሉት የወንጀል ፍትሕ መርሆዎች፣ የወንጀል ሕጋችን (ዓንቀፅ 5) እንዲሁም የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት (ዓንቀፅ 22) ስር በግልፅ ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ፈጸሙት ለተባለው ድርጊት በሙስና ሊከሰሱ የሚችሉት ድርጊቶቹ የተፈፀሙበት ቀን የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 ከፀደበት መጋቢት25፣ 2007 ዓ/ም  እስከ ተጠርጣሪዎቹ ከድርጁቱ ሓላፊነት የለቀቁበት 2010 ዓ/ም አጋማሽ ድረስ ከሆነ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ድርጊቶቹ በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቁ ከሆነስ ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የማን ነው? የሚለውን ስናይ ጥያቄው በሁለት መልኩ መመለስ ይቻላል፡፡ አንደኛው ጥረት ኮርፖሬት ከነሓሴ 2010 ዓ/ም የአማራ ክልል መንግስት የልማት ድርጅት እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ የተፈፀሙት ወንጀሎች የሚመለከት ሲሆን ይህም የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን ሙሉ በሙሉ የክልሉ ስልጣን ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለፀው ተጠርጣሪዎቹ ከሐላፊነታቸው የለቀቁት  ጥረት ኮርፖሬት በነሓሴ 2010 ዓ/ም የአማራ ክልል መንግስት የልማት ድርጅት እንዲሆን ከመወሰኑ በፊት ስለሆነ ከዚህ ጽሑፍ ጋር በተያያዘ ብዙም ጠቀሜታ የሌለው ነው (ተጠርጣሪዎቹ ሊጠየቁ የሚያስችላቸው የወንጀል ድርጊት ለመፈፀም የሚያስችል ሓላፊነት ላይ ስላልነበሩ)፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ፈጸሙት የተባሉው ጥፋት የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 ከፀደቀበት መጋቢት25፣ 2007 ዓ/ም  እስከ ተጠርጣሪዎቹ ከድርጁቱ ሓላፊነት የለቀቁበት 2010 ዓ/ም አጋማሽ ድረስ ከሆነስ የሚል ነው፡፡ በዚህ ግዜ ተጠርጣሪዎች ፈፀሙ ለተባሉት ድርጊት ከላይ እንደተገለፀው በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቃቸው ሆኖ ሳለ ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ  ስልጣጥን የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ እንጂ የአማራ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተገለፀው ተቋሙ በዚህ ወቅት የአማራ ክልል ህዝባዊ ድርጅት ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 433/1997 ዓንቀፅ 7 ንኡስ ዓንቀፅ 4 (እንደተሸሻለ) ህዝባዊ ድርጅቱ የክልል ቢሆንም ከአንድ በላይ ከሆኑ ክልሎች ተንቀሳቅሶ የሚሰራ ከሆነ ከድርጅቱ በተያያዘ የሚፈፀሙ ማናቸውም የሙስና ወንጀሎች የመመርመርና የመክሰስ  ስልጣን  የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ መሆኑን በግልፅ ይደነግጋል፡፡ እንደሚታወቀውም በጥረት ኮርፖሬት ስር የሚገኙት የንግድ ድርጅቶች በተለያዩ የሃገሪቱ አከባቢዎች በስፋት ተንቀሳቅሰው በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

ለ. የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እርምጃ ሕጋዊነት

አግባብነት ያላቸው ሕጎች የሚደነግጉት ከላይ እንደተገለፀው ከሆነ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ  ስልጣን  ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ይሆናል የዚሁ ፅሑፍ ትልቁ ጥያቄ፡፡ ከላይ በተ.ቁ. 1 እንደተገለፀው የሙስና ወንጀል ሲፈፀምና ይህ ጉዳይ የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የፌዴራል መንግስት በሚሆንበት ግዜ የክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች የመመርመርና የመክሰስ የውክልና ስልጣን ሊኖር ስለሚችልበት ሁኔታ አግባብነት ያላቸው ሕጎች ምን እንደሚደነግጉ አይተናል፡፡ በመሆኑም  የአማራ ክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን በውክልና መስራት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን በተለመለከተ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን ጥያቄ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ በውክልና እንዳላገኘ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ከዘገቡት ሃሳብ በመነሳት መረዳት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ ያክል ሸገር FM 102.1 እሮብ ጥር 16/2011 ዓ/ም በFacebook ገፁ እንደዘገበው የአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን በቁጥጥር ስር መዋል አስመልክቶ ምን መረጃ አላችሁ ሲል ለፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ ላቀረበው ጥያቄ የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ስለጉዳዩ  “የምናውቀው አንዳችም ነገር የለም ብለዋል” ሲል ይገልፃል፡፡ ይህ የሚያስረዳን እውነት ደግሞ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በጉዳዩ ዙርያ የተሰጠው ምንም የውክልና ስልጣን አለመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን በቁጥጥር ስር ያዋለበት አካሄድ ከስልጣኑ ውጭና ኢ-ሕጋዊ መሆኑ በግልፅ መረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ጉዳዩን ከመመርመር ጋር በተያያዘ ከላይ በተ.ቁ.1 ላይ እንደተገለፀው ክልሎች የሙስና ወንጅል ተፈፅሟል ብለው ባመኑ ግዜ ጉዳዩ ላይ ምርመራ ለመጀመር የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ ውክልና ማግኘት የግድ እንዳልሆነ የሚል ሀሳብ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ክልሎች ያለውክልና ምርመራ መጀመር የሚችሉ በሆንም እንኳ ምርመራውን በተመለከተ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ ወድያውኑ ማሳወቅና ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ሕጉ በግልፅ ያሰቀምጣል፡፡ አሰራሩ እንዲህ ሁኖ እያለ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ይህ የሕግ ድንጋጌ በመጣስ የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ ስለጉዳዩ ምንም እውቅና ሳይኖረው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ያደረገበት ሂደት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡  በተጨማሪ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር በጉዳዩ ዙርያ ለአማራ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ምርመራው ለወራት ሲካሄድ የቆየና  ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የማዋል ሂደቱ የዘገየው ከኦዲትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምርመራ እተደረገ ስለነበር መሆኑን መናገራቸው ልብ ስንል ይህ የሕግ ጥሰት ሆን ተብሎ የተፈጸመ መሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡

በአጠቃላለይ ሲታይ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን በአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በቁጥጥር ስር የዋሉበት አግባብ ከሕጋዊ ምክንያት ይልቅ ፖለቲካዊ ገፊ ምክንያት (political Motive) ያለው ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እርምጃው ለመውሰድ ስልጣን የለሌለው መሆኑ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ ለክልሉ ኮሚሽን እርምጃው እንዲወስድ ውክልና ያልሰጠ መሆኑ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ ስለጉዳዩ የሚያውቀው አንዳችም ነገር የሌሌ መሆኑ መግለፁና የፌዴራል መንግስት በመዲናዋ አዲስ አበባ የተፈፀመ እስር አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳሰማ፣አውቆ እዳላወቀ ስለጉዳዩ አይደለም መግለጫ ሊሰጥ የማያውቅ ሆኖ መቅረቡ ጉዳዩ የፖለቲካ ጨዋታ የተሞላበት ሞሆኑ መሆኑንና የፌዴራል መንግስትም ከጉዳዩ እራሱን ለማሸሽ እየሞከረ መሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

***********

Guest Author

more recommended stories