የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 1 | አጨራረሱ እንደ አጀማመሩ ድንገተኛና ያልተጠበቀ የሆነዉና ለመወሳት ያልታደለዉ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

ይህ ጽሁፍ የኤርትራን የእብሪት ወረራ ለመመከት በቆራጥነት ሲፋለሙ ለወደቁ የጀግናዉ መከላከያ ሰራዊታችን አባላትና በሻእቢያ የግፍ ጭፍጨፋ ሰለባ ለሆኑ የአይዴር ት/ቤት ህጻናት ማስታወሻ ይሁን፡፡ በተጨማሪም እንደወጣ ሳይመለስ ለቀረዉና የምንግዜም የአየር ኃይላችን ጀግናና የኢትዮጵያ ኩራት ለሆነዉ ለኮ/ል በዛብህ ጰጥሮስ መታሰቢያ ይሁን፡፡  

Highlights:-

+ የኢትዮጵያ ህዝብ በነበሩት ስርአቶችም ሆነ በመንግስታቱ ላይ ደስተኛ ሆኖ ባያዉቅም በሃገሩ ሉአላዊነት ላይ ግን ተደራድሮ አያዉቅም፡፡ በሶማሊያ ጦርነትም ሆነ ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ጦርነት ወቅት የታዬዉ የህዝብና የመንግስት አንድነት መነሳሳት በብዙ መልኩ ተመሳሳይ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጦርነት ግን ጠንከር የሚል ይመስለኛል፡፡

+ ለኢትዮኤርትራ ጦርነ አነስተኛ ግምት የሠጠነዉ ይመስላል፡፡ በጦርነቱ ላይ ያደረግነዉ ተጋድሎ የከፈልነዉ መስዋእትነትና የደረሰብን ጉዳት ሁሉ ገና በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲህ በቀላሉ መዘንጋት ነበረበት አላስብም፡፡ ከኤርትራ ጋር ገና ያልተቋጨ ብዙ ጉዳይ እያለን በቀላሉ ሊዘነጋ አይገባዉም፡፡

+ ሰራዊታችን ለሰራዉ አኩሪ ገድልና ለከፈለዉ መስዋእትነት ሃዉልት ባይቆምለት እንኳን ቢያንስ ህዝቡ ስለ ልጆቹ ጀግንነት እንዲያዉቅ፤ መጭዉ ትዉልድም እንዲማርበት ተደርጎ የማይዘገበዉስ ለምንድነዉ? የሻዕቢያ መንግስት እንደሆነ በሱ ጠብ ጫሪነት ተጀምሮ በሱ ሽንፈት ስለተጠናቀቀዉ ጦርነት ማዉራትና መተረክ ስለማይችል ከዚያ ይልቅ በየጊዜዉ ለህዝቡ የሚያሳየዉ የዉ የድሮዉን ደርግ ጋር ተደርጎ የነበረዉን የናቅፋን፤ የአፋበትን ፤የከረንን ፡የምጽዋን ወዘተ ዉጊያ ላይ ሰራሁ ስለሚለዉ ገድል ብቻ ነዉ፡፡

ስለ ባድመ ጦርነት ግን ሻዕቢያ ብዙ ሲያወራ አይደመጥም፡፡ ያን ማድረግም አይጠበቅበትም፡፡ ምክንያቱም  በባድመ ጦርነት ምንም የሚያኮራ ታሪክ ለሌለዉ ማዉራት አይችልም፡፡ እኛ በኩል ግን ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ጦርነት በአስደናቂ ገድሎች የታጀበና አኩሪ ታሪክ የተሰራበት ሆኖ እያለ ብዙ ሊባልበት ሲገባ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም መባሉ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ትላንት በጦርነቱ ወቅት ድንቅ አመራር ሲሰጡ የነበሩ ጄኔራሎች፤ የመንግስት አመራሮችም፤ ጋዜጠኞችና ታሪክ ምሁራን  ዛሬ በህይወት እያሉ ያልተነገረ ታሪክ ነገ ይነገራል ብዬ አላስብም፡፡

+ በአንድ ወቅት ከጦርነቱ በኋላ የጦርነቱ ግምገማ መሰል ነገር ተጀምሮ በኋላ አቅጣጫዉን እየሳተ ጣት መጠቋቆም ሲመጣ እንዲቆም መደረጉ ይታወቃል፡፡ ምስጢራዊነቱን ለመጠበቅ ከተፈለገ ቢያንስ በሚመለከታቸዉ ከፍተኛ አመራሮች ደረጃ እንኳን ግምገማ ማድረግ እየተቻለ ጭራሽ ለማድረግ አልተፈለገም፡፡ ለመሆኑ በጦርነቱ አሸናፊዎቹ እኛ ለመሆናችን ማረጋገጫ ለሚጠይቁንስ እንዴት ነዉ የምናስረዳዉ? ስለ ትላንቱ ጦርነት በሚገባ ሳንገመግም ነገ ከኤርትራ ጋር ለሚኖረን ሌላ ዙር ጦርነትስ እንዴት ነዉ መዋጋት የምንችለዉ?

+ እኛ ብቻ ሳንሆን ኤርትራዉያን ራሳቸዉ ጠንቀቄዉ የሚያዉቁትን ሽንፈታቸዉን እኛ ደጋግመን ስላወራንና ስለፎከርን  ትርጉም አይኖረዉም፡፡ ትልቅ ትርጉም ሊኖረዉ ይችል የነበረዉ ጦርነቱን ከአነሳሱ እስከ ፍጻሜዉ በሚገባ በመገምገም ትምህርት ወስደንበት ቢሆን ነበር፡፡ ያለፉ ጦርነቶችን ጠንካራና ደካማ ጎናችንን በጥንቃቄ ሳንገመግም ከኤርትራም ሆነ ከሌላ ባላጋራ ጋር ወደፊት ለሚገጥመን ጦርነት በድሮዉ ያረጀ አሰተሳሰብ ወደ ጦርነቱ ልንገባ ስለምንገደድ ገና ሳንዋጋ ለሽንፈት የሚዳርገን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

+ ለመሆኑመከላከያ ሰራዊታችን አባላት የምርምር ጽሁፎችን የሚያቀርቡበት አዳዲስ የጦርነት ንድፈሃሳቦችና ተሞክሮዎች፤ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር ትዉዉቅ ለመድረግ የሚረዱ፤ የዩንቨርስቲ ምሁራንና የምርምር ተቋማት በመከላከያና በደህንነት ጉዳይ ላይ የጥናት ጽሁፎችን የሚያቀርቡበት፤ ሰራዊታችንን ስለሃገሩ ብሄራዊ ደህንነት የዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲና ስለ ብሄራዊ ጥቅም እንዲያዉቅ የሚያግዝ  አንድ እንኳን የህትመት ዉጤት አለዉ? ዘጠና ሚሊዮን ህዝብን የሚወክልና በቢሊዮኖች የሚገመት ዓመታዊ ባጄት ያለዉ ግዙፍ መከላከያ ተቋም ከስምንት ገጽ የማትበልጥወጋገንከምትባል አነስተኛ ጋዜጣ ዉጭ በመከላከያ የሚዘጋጅ ሌላ ወታደራዊ መጽሄት አለዉ እንዴ? ከኢትዮጵያ ጦር ኃይል ዉጭ በመከላከያ አባላት ብቻ ሳይሆን በሲቪሉ ህብረተሰብም የሚነበብ ወታደራዊ መጽሄት ለዉ ሌላ አገር አለ እንዴ?

+ መንግስትን እየመራ ያለዉ ኢህአዴግ በትግሉ ወቅትደርግን የሚያህል ግዙፍ ሰራዊት ሸነፍኩበት ምስጢር…..” እያለ ሲነግረን የነበረዉ ከአያንዳንዷ ዉጊያ በኋላ ቁጭ ቢለዉ መገማገማቸዉን ነበር፡፡ እኛም በኢህአዴግ ጉብዝና ተደንቀን እንደ ኢህአዴግ ለመሆን ስንፍጨረጨር እንዳልነበርን ዛሬ ያን የመሰለ ለግምገማ አመቺ የሆነ ጦርነት ለመገመግም ችላ ማለቱ ግራ ቢያጋባን አይፈረድብንም፡፡

+ በገዥዉ ፓርቲ ዉስጥ በተፈጠረዉ መከፋፈል ፓርቲዉን አደክሞና የህዝብ አመኔታን አሳጥቶት ለነቅንጀትና ኢዴፓ መጫወቻ ለመሆን የዳረገ ጦርነት ነዉ፡፡ ታዲያ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ሁኔታ የዳረገንን ጦርነት ሳንነጋገርበት ፤ሳንገመግመዉ በሚዲያ ሰፊ ዘገባ ሳይሰራበት እንደተራ ክስተት ተድበስብሶ ሲቀር እንዴት አያስፋም?

—-

መቅድም

በዚህ ጽሁፍ በቅርብ ግዜ ታሪካችን ዉስጥ ሀገራችን ስላስተናገደችዉ ትልቁ ጦርነት፤ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፤ እናወጋለን፡፡ ጦርነቱ በሻእቢያ ድንገተኛ ወረራ የተጀመረ ነዉ በመባሉ እንዴት ድንገተኛ ሊሆን ቻለ? የሚል አብይ ጥያቄም አንስተን መነጋር የዜግነት መብታችን ይፈቅድልናል፡፡  

በዚህ ጽሁፍ የምነካከካዉ አጀማመሩ ብቻ ሳይሆን ፍጻሜዉም “ድንገተኛ“ ስለሆነዉ አስገራሚ ጦርነት ነዉ፡፡  የምንነጋገረዉ “Leaders can lose battles, but only soldiers can win them.” የተሰኘዉን የአሜሪካኖች አባባል ትክክለኛነት በተግባር ያረጋገጥንበት ጦርነት ነዉ፡፡  

ይህ ጦርነት በታሪካችን ካጋጠሙን ጦርነቶች ሁሉ በተለየ ከዝግጅቱ ጀምሮ በአካሄዱም ሆነ አፈጻጸሙ ላይ ግልጽነት የጎደለዉና የሀገሪቱ አመራርንም እርስበርስ ያጋጨ ወደፊትም በሚገባ መጥራት በሚገባቸዉ በርካታ አወዛጋቢ ኩኔቶች የተሞላ አስገራሚ ጦርነት ነዉ፡፡  ኤርትራን ወይ አስከመጨረሻዉ አልተዋጋናት አልያም በሚገባ አልተደራደርናት አንዱንም በአግባቡ በስኬት መጨረስ አቅቶን ሁሉም ነገር ዳር ሳይደርስና የህዝብን እርካታ ሳይፈጥር በክሽፈት የተጠናቀቀበት ጦርነት ነዉ፡፡

በዚህ ጽሁፍ ስለጦርነቱ መነሾም ሆነ ስለጦርነቱ አካሄድ ዝርዝር ታሪክ ለመተረክ አልሞክርም፡፡  ከአቅሜ በላይ ነዉና፡፡ ዝርዝር ታሪኩን ለታሪክ አጥኚዎችና ለሚመለከታቸዉ የመንግስት ሃላፊዎች ትቼ በእኔ በኩል አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን በጦርነቱ ዙሪያ አንዳንድ ጉዳዮችን ብቻ እያነሳሁ አስተያየት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ ጦርነቱ እንዴት ባለ መንገድ ተከናወነ በሚለዉ ጉዳይ ላይ ሌሎች በጦርነቱ ዉስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸዉና ዝርዝር መረጃዉን የማግኘት የተሻለ ዕድልና ብቃቱም ያላቸዉ በሚገባ ይጽፉበታል ብዬ ስለማስብ በእኔ በኩል ዋነኛ ትኩረት የማደርገዉ ከጦርነቱ ወታደራዊና ቴክኒካዊ ጣጣ ዉጭ በሆኑ አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ነዉ፡፡  

በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ስነሳም አስካሁን ይህ ጦርነት ተገቢዉ ትኩረት ማጣቱ በፈጠረብኝ ቁጭት አቅሙና የተሟላ መሬጃ ያላቸዉ ታሪክ ጸሃፊዎችና በመከላከያና በደህንነት ጉዳይ ባለሙያ የሆኑ ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥተዉ በጉዳዩ ላይ ግምገማዊ ጥናት እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መከላከያ ሚኒስቴር ለሰራዊታችን አባላት ለተሞክሮ በሚረዳ መንገድ በድፍረት እንዲገመግመዉ ለማሳሳብም ጭምር ነዉ፡፡

መቼም የኤርትራ ጉዳይ ንቀን ብንተወዉም ሊተወን ያልቻለ የጀርባ ህመም ሆኖብናልና በሱ ላይ መነጋገሩ አይከፋም፡፡  እኔም ይሄን ጉዳይ ይዤ መቅረቤ ወቅታዊ አጀንዳ ነዉ ከሚል መንፈስ ተነሳስቼ ነዉ፡፡  በተረፈ በጽሁፉ ዉስጥ አንዳንድ ጉዳዮችን የተረዳሁበት አግባብ በግል የሚያስከፋቸዉ ቢያንስ የማያስደስታቸዉ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ በተጨማሪ ጦርነቱ ከተካሃደ ከሃያ ዓመታት በኋላም “ጥብቅ ወታደራዊ ምስጢር!” በሚል ሽፋን ዝምታን ለሚመርጡ ሰዎች ስለ ጦርነቱ የሚያዉቁትን እንዲያካፍሉን እጋብዛለሁ፡፡  

በተረፈ ሃሳቤን በአጭሩ መቋጨት ባለመቻለ ምክንያት ጽሁፉ አለቅጥ በመርዘሙ በተለያዩ ክፍሎች ለመክፈል ተገድጀአለሁ፡፡  ሁሉም የጸሁፉ ክፍሎች ለአመቺነቱ ተብሎ በተለያዩ ክፍሎች ከመከፈሉ ዉጭ ዋናዉን ጉዳይ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን መነሻ የሚያደርጉ በመሆናቸዉ እርስበርስ ቁርኝት ያላቸዉ ሲሆን በተጨማሪ የአንባቢን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱ ክፍል ራሱን ችሎ ሊነበብ በሚችል መንገድ የተዘጋጀ መሆኑን ለአንባቢ መግለጽ እወዳለሁ፡፡  በተረፈ  የሀገር ሉአላዊነት፤ የመከላከያና የደህንነት ጉዳይ  ላይ ለመነጋገገር ፍላጎት የማጣት ችግር እንዳለ ስለማዉቅ አንባቢ ስለ ስፖርት፤ ስለ ፍቅርና ስለ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች የተጻፉ ጽሁፎች በማንበብና በሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ  የሚያተኩሩ  አሰልቺና አታካች የሚመስሉ ጉዳዮች መካካል ያለዉን ልዩነትና ፋይዳዉን በሚገባ እንዲያጤን በዚህ አጋጣሚ አሳስባለሁ፡፡

መግቢያ

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዝም ብሎ ጦርነት ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገሩ ድንገተኛ የሆነ አስገራሚ ጦርነት ነዉ፡፡  ሳናስበዉ በድንገት መወረራችን ሳያንስ ሳናስበዉ በድንገት አቋርጠን የወጣንበት አስገራሚ ጦርነት ነዉ፡፡  ሁልግዜም ከጦርነት አዙሪት ወጥታ ለማታዉቀዉ አገራችን ወደንና ፈቅደን ራሳችን ቆስቋሽ ሆነን የጀመርነዉ አንድም ጦርነት በታሪካችን አለመኖሩና ሁልግዜም ተጠቂና ተጎጂ መሆናችን ያለፉ ጦርነቶችን የሚያመሳስላቸዉ ቢሆንም እንደ ኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ግን አስገራሚ ገድል ተሰርቶበትና የተዋጣለት የጦርነት አመራር ብቃትም ታይቶበት እያለ ነገር ግን ለመወራትና ለመነገር የተነፈገ ብቸኛ ጦርነት ነዉ፡፡  

ምናልባትም አስቀድመን እንዳሰብነዉ ጠላትን አስከመጨረሻዉ ያለ መደምሰሳችን ጉዳይ ከሆነ በታሪካችን በተደጋጋሚ የታየ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ይሄ ጉዳይ በታሪካችን ቢያንስ ከዚያ በፊት ሁለት ግዜ አጋጥሞናል፡፡  አንዱ በአድዋ ጦርነት ወቅት ጣሊያንን እከመጨረሻዉ አሳደን ሳንደመስስ መረብን አሻግረን ብቻ የተዉንበት፤ ሁለተኛዉ ደግሞ የሶማሊያ ወራሪ ጦርን አስከመጨረሻዉ አሳደን አለመደመስሳችን ናቸዉ፡፡  

በሶስቱም ወቅቶች ከአቅማችን በላይ የሆነ በቂና አሳማኝ ምክንያቶች ስለነበሩ በዚህ ጉዳይ የሚወቀስ አመራር ሊኖር የሚገባዉ አይመስለኝም፡፡  ምኒልክም መንግስቱም ሆኑ መለስ በዚህ ጉዳይ ሊወቀሱ አይገባቸዉም፡፡  

የኢትዮ -ኤርትራን ጦርነት ልዩ የሚያደርጉት ጥቂት ዓይነተኛ መገለጫዎች  አሉት፡፡

* ድንገት ገብተን ድንገት ጥለን የወጣነዉ አጨራረሱ እንደ አጀማመሩ ድንገተኛ የሆነ ጦርነት፤

* የጋራ ጠላታቸዉን በጋራ ለዓመታት ታግለዉ ካስወገዱ በኋላ ለአንድ አስር ዓመት እንኳን እንደመንግስት በሰላም ሀገር ሳያስተዳድሩ በቀድሞ ወዳጆች መካካል የተካሄደ ጦርነት መሆኑ፡

* ከሁለት ዓመት ባልበለጠ አጭር ግዜ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ መስዋእት የሆኑበት ጦርነት፤

* በወታደሮቻችን ደምና ላብ ያመጣነዉን ድል በተልካሻ ደፕሎማሲ በደካማ ፖለቲከኞች ምክንያት ድሉን የተነጠቅንበት ጦርነት፤

* ወታደራዊ የጦር ሜዳ ድል ዘላቂ ሰላም ካላመጣ በስተቀር ትርጉም አንደማይኖረዉ በተግባር ያረጋገጥንበት፤

* ለዓመታት ባደረጉዉ ሰፊ ዝግጅት እጅግ ተማምኖ በነበረዉ የሻዕቢያ ላይ በአጭር ግዜ ዝግጅት ድል የተገኘበት እጅግ አስደናቂ የዉጊያ ጥበብና የጦርነቱ አመራር  ብቃት የታየበት፤

* ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚያኮራ ገድል ተሰርቶበት ነገር ግን በታሪክ ተገቢዉን ስፍራ ያልተሰጠዉ ዕድለቢስ ጦርነት.. መሆኑ ወዘተ ናቸዉ፡፡

Photo - Ethiopian soldiers emerge from a trench on a hilltop overlooking the northern Ethiopian [Credit: AFP, 2005]
Photo – Ethiopian soldiers emerge from a trench on a hilltop overlooking the northern Ethiopian [Credit: AFP, 2005]

1/ የጉዳዩ ወቅታዊነትና በተለይ በአሁኑ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ማዉሳት ያስፈለገበት ምክንያት

ስለ ከ18 ዓመት በፊት ስለተከናወነዉ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ለመጻፍ ስነሳ ይህን የተረሳና ለዉይይት አጀንዳነት ተነፍጎ የቆየ ጉዳይን “አሁን ላይ ማስታወስ ለምን አስፈለገ?” የሚሉ ወገኖች እንደሚኖሩ ሳልገምት ቀርቼ አይደለም፡፡  በእርግጥም ከተካሄደ ሁለት አስርት ዓመታት ሊሞላዉ ጥቂት ብቻ ስለቀረዉ የኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት  ከስንት ዘመን በኋላ ይሄን ያረጀ ጉዳይ አሁን ላይ ማንሳቱ ፋይዳዉ ላይታየን ይችላል፡፡  

ጉዳዩ ግን አንዳንዶቻችን እንደምናስበዉ ያለቀለትና ያረጀ ያፈጀ ጉዳይ ሳይሆን ወደፊትም ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለንና እርስ በእርሳችን ሊያጣላን የሚችል ገና ያልተቋጨ ብሄራዊ አጀንዳና የሉአላዊነት ጉዳይ ነዉ፡፡ ለማንኛዉም ይህን ጉዳይ አሁን ላይ እንዳቀርብ ምክንያት የሆኑኝ ጥቂት ምክንያቶች መጥቀስ የሚገባን ይመስለኛልና እነሆ፤

* ኤርትራ እኛ እንደጠበቅነዉ ከጠብ አጫሪነት ተግባሯ ለአፍታም ለመታቀብ አለመፈለጓና ይልቁንም ከቀድምዉ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሏ፤

* ኤርትራ እስትራታጂያዊና ታሪካዊ ጠላታችን ከሆነችዉ ግብጽ ጋር ከቅርብ ግዜ ጀምሮ ጠንከር ያለ መቀራረብ መጀመሯ

* ለኛ መልካም አመለካከት ለሌላቸዉ አረብ አገሮች በአሰብና አካባቢዉ ላይ የጦር ካምፕ  እንዲመሰርቱ መፈቀዷ፤

* ኤርትራ መሬቷን ለባእዳን አገራት በማከራየትና ዉስን ከሆነዉ የማእድን ምርት ሽያጭና ዉጭ አገር ከሚኖሩ ዜጎቿ የምታገኘዉን የዉጭ ምንዛሪ ተጠቅማ የተጣለባትን ማዕቀብም ሳያግዳት ወታደራዊ አቅሟን እያጠናከረች ነዉ የሚለዉ መረጃ መሰማት፤

* ይልቁንም በሀገራችን ላይ ጦርነት ያወጁ የተለያዩ ተጣቂ አማጺ ቡድኖችን መጠለያ በመስጠት ስልጠናና ሎጂስቲካዊ ድጋፍ በማድረግና ወደ ኢትዮጵያ ሰርገዉ እየገቡ አደጋ እንዲያደርሱ በማሰማራት ተደጋጋሚ ያልተሳኩ ሙከራዎች ማድረጓና ወደፊትም ቢሆን ከዚህ ድርጊቷ እነደማትቆጠብ ብቻ ሳይሆን አመቺ ግዜ ጠብቃ ወደ አጠቃለይ ጥቃት ልትገባ እንደምትችል ከበፊቱ ይልቅ አሁን ግልጽ እየሆነ መምጣቱ

* አጠቃላይ ሁኔታዉ ያሳሰባቸዉ ወገኖች በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ መጻፍ መጀመራቸዉ በራሱ የጉዳዩን አሳሳቢነትና ወቅታዊነት አመላካች ነዉ፡፡

መንግስታችንም ቢሆን የኤርትራ ድርጊት የበለጠ ያሳሳበዉ መሆኑን አንዱ በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተናገሩት ንግግር ማሳያ ነዉ፡፡  በክቡር ጠ/ሚኒስትራችን አንደበት ሲነገር እንደሰማነዉም ኤርትራን በሚመለከት አስካሁን የነበረዉ  አካሄዳችን ብዙም ዉጤታማ ባለመሆኑ መንግስት ሌላ ተለዋጭ ፖሊሲ በመቅረጽ ሂደት ላይ መሆኑን ነዉ፡፡  በኤርትራ አዋሳኝ የሆነዉ የትግራይ ህዝብም ቢሆን በኤርትራ ትንኮሳ መማረሩን በመግለጽ አደብ የሚያስገዛ መፍትሄ እንዲወሰድ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩን በይፋ አስከመጠየቅ ደርሰዋል፡፡  

ኤርትራን የሚመለከተዉ ቀጣዩ ፖሊሲ ይዘቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አሁን ላይ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡  አዲሱ ፖሊሲ ምንም ይሁን ምን ሊቀየር የማይችል እዉነታ ግን አለ፡፡  እሱም የመከላከያ ሰራዊታችንን ሁለንተናዊ አቅም በማሳደግ ለማይቀረዉ ጦርነት ከመዘጋጀት ዉጭ ለደህንነታችን የተሻለ ዋስትና አለመኖሩ ነዉ፡፡ ተጨባጭ የሆነ የመከላከያ አቅም ፈጥረን አስተማማኝ ወታደራዊ ቁመና ይዘን መገኘት ይኖርብናል፡፡ 

በሌላ በኩል አዲሱ የመንግስት ፖሊሲ በማንኛዉም መንገድ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት የማያደርግ ከሆነ ተቀባይነት አይኖረዉም የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸዉ፡፡  የባህር በር ጥያቄ እንደ ቀድሞዉ በሰበብ አስባቡ ወደ ጎን የሚገፋ አንዳይሆን ወቅቱ የግድ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አዲሱ ፖሊሲያቸዉ ይህን ቁልፍ ጉዳይ በአጀንዳነት ማካተቱን እርግጠኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡

በተረፈ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአንድ በኩል ዛሬዉኑ እርምጃ ካልወሰድን ለሚሉ ጦርነት ናፋቂ በሆኑ ጀብደኞች ምክር ተገፋፍተዉ ያልተገባ እርምጃ እንዳይወስዱና እንዲሁም ምንም ችግር አይኖርም የሚሉ አዘናጊና ልፍስፍስ አስተያየቶች ተጫጭኖአቸዉ መዘናጋት እንዳይፈጠር በቅድሚያ ማሳሰብ የዜግነት ግዴታችን ነዉ፡፡

ይህ ጉዳይ በተለይ በአሁኑ ወቅት መነሳቱ ለምንድነዉ? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳም አዉቃለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ ከዓመታት በፊት መነሳት የነበረበት ግን ደግሞ በቁምነገር ባለመቆጠሩ ሳይነሳ የቀረ ጉዳይ በመሆኑ አሁን በሁሉም አቅጣጫ ስጋት ባጠላበት ወቅት ላይ ነቃ እንድንል ያደርገናል ከሚል ነዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ በዙሪያችን ወዳጅ ባልሆኑ ኃይሎች ከበባ ዉስጥ እየገባን በመሆኑ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት አለብን፡፡ የኛ ሰላም ወዳድነታችን የታሪካዊ ጠላቶቻቸንን አንጀት ሊያራራልን አልቻለም፡፡ አልሻባብ፤ኤርትራና ግብጽ የሚፈጥሩብን ስጋት ሳያንሰን እነ ኳታር፤ቱርክ፤ሳዉዲ አረቢያ፤ኢራን ፤ኢራቅ አረብ አምሬትስ ወዘተ የመሳሰሉ አገሮች በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ያለወትሮአቸዉ በከፍተኛ ጥድፊያ የጦር ሰፈር እየገነቡ ነዉ፡፡ 

ያን ተከትሎ በኤርትራ፤በጂቡቲና በሶማሊያ ያልሰፈረ ምድረ አረብ የለም፡፡ ጂቡቲ ላይ ጦር ሰፈር ያላቸዉ ፈረንሳይ፤አሜሪካና ቻይናም ሁኔታዉ በኛ ላይ ሊፈጥር ስለሚችለዉ ስጋት ደንታ ያላቸዉም አይመስሉም፡፡ ትንሽ በሁኔታዉ መረበሽ የታየባት ኢስራኤል ብቻ ነች፡፡ እሷም ብትሆን መጨነቋ ለራሷ ብላ እንጂ የኛ ደህነነት አስግቷት አይደለም፡፡ 

በተለይ ኤርትራ በዚህ አጋጣሚ ያልጠበቀችዉን ዶላር ማፈስ ከጀመረች ወዲህ ኢሳይያስና ባለስልጣኖቻቸዉ ያለወትሮአቸዉ  ወደ ዉጭም ወጣ ወጣ ማለት መጀመራቸዉና ከግብጾች ጋርም አብረዉ ሲዶልቱ እንደነበር መዘገቡ ለነገ ምን እየተደገሰልን እንደሆነ በማሰብ መስጋታችን አይቀርም፡፡

ይህ ሁሉ እየሆነም መከላከያ ሰራዊታችን የጸጥታ ችግር በታየበት ጎረቤት አገር ሁሉ እየተላከ የነሱን ሰላም ለማረጋገጥና በተዘዋዋሪ መንገድም  ቢሆን ለኛም ደህንነት የስጋት ምንጭ የሆኑ ኃይሎችን እዚየዉ ከምንጩ ለማድረቅ እየተንቀሳቀሰ አኩሪ ስራ እየሰራ እንደሆነ እናዉቃለን፡፡ የደቡብ ሱዳን ጉዳይም ለብቻዉ ሲታይ ከኤርትራም ያለነሰ የስጋት ምንጭ ሊሆንብን እንደሚችል ገና ከአሁኑም ደህንነታችንን የሚፈታተኑ ምልክቶች መታየታቸዉ አልቀረም፡፡

ይህ ሁሉ እያለም እዚህም እዚያም በየስርቻዉና በየጎጡና መንደሩ በየዞኑና በየክልሎች በሰበብ ባስባቡ የሚነሱ የርስበርስ መቆራቆዝና የህዝቦች ግጭት ለሻዕቢያና መሰሎቹ እንደመልካም አጋጣሚ የሚቆጠር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ይህን የመሰሉ የዉስጥ ችግሮቻችን ለመፍታት እየተጠቀምን ያለነዉ ዜዴ ፍጥነት የጎደለዉ መሆኑ ሲታሰብ ለወደፊቱ ለአንድነታችን እንቅፋት እንዳይሆን መስጋታችን አይቀርም፡፡

በዚህ ምከንያትም መላዉ የጠፋቸዉ ዜጎች ከየማህበራዊ ሚዲያዉ እንደ ልብ የሚገኘዉን ወሬ ከዚህም ከዚያም እየቃረሙ እዉነቱንና ሃሰቱን በደንብ እንኳን ሳያጣሩ በስጋት መንፈስ “ነገ ምን ይፈጠር ይሆን?” እያሉ እርስበርሳቸዉ በጭንቀት መነጋገራቸዉ አልቀረም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያዉም ግልጽ የዉጭ ጥቃት ሊኖር ይችላል ከሚል ስጋት በመነሳት በመንግስት ወይም በመከላከያ አካባቢ የተለየ የጦርነት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆንም ለማረጋገጥ ሲጠይቁና ሲያጠያይቁ ይታያሉ፡፡

መከላከያችን በምን ያህል ደረጃ ሉአላዊነታችንን ለመጠበቅ ዝግጁ እንደሆነም ለማወቅ የሚሞክሩም አሉ፡፡ መንግስት ለመከላከያ ሰራዊታችን የትኛቹን አዳዲስ ትጥቆች ገዝቶ እንዳስታጠቀም ለማወቅ ይኳትናሉ፡፡ ምናልባት ኤርትራ ድጋሚ ብትተናኮለን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት የሚያበቃን በቂ ዝግጅት እንዳለን ለማወቅ ብዙ ይደክማሉ፡፡ በተለይ  ከህዳሴዉ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽና ኤርትራ ተባብረዉ ለጠብ ቢፈልጉን ወይንም የህዳሴ ግድባችን ላይ አንዳች ደባ ለመፈጸም ቢቃጡ ለመከላከልም ሆነ የአጸፋ እርምጃ ለመዉሰድ የሚያስችለን አቅም እንዳለን ለማጣራት ብዙ ይሞከራል፡፡  

መቼም ህዝብ ሲጨንቀዉ ብዙ ያስባል፡፡ የሚያሳዝነዉ ግን የህዝቡን ስሜት ተረድቶ የሚያጠግብ ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጥ ባለስልጣን አለመኖሩ ነዉ፡፡  ለህዝቡ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ስለሚገኝበት ሁኔታ፤ አቅሙን ለማሳደግ አስካሁን ምን እንደተሰራ ፤ ለወደፊቱም ምን ለመስራት እንደታሰበ ፤ በአካባቢያችን ካንዣበበዉ ስጋት አንጻር በምን ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ የሚያስረዳ አንዳችም አካል የለም፡፡

የሀገሪቱ ፓርላማም ቢሆን ሰራዊታችን ስለሚገኝበት ሁኔታ በቦታዉ ተግኝቶ ለማጣራት ከመሞከር ይልቅ የመከላከያ ባለስልጣናት በስንት ግዜ አንዴ በሸንጎዉ አዳራሽ ተገኝተዉ የሚሰጡትን ገለጻ ከማዳመጥ በስተቀር ለምን እንዲህ አልተደረገም? ለምንስ ይሄ ሆነ? የሚባልበት አሰራር አልተለመደም፡፡ የሀገሪቱ ህግ አዉጭ አካል  የሀገሪቱን የደህንነት ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ  ለመረዳት የሚያስችለዉ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገዉ የራሱ የሆነ ሌላ አማራጭ የመረጃ ምንጭም የለዉም፡፡

የሀገሪቱ የግል ሚዲያዎች የመከላከያና የደህንነት ጉዳይ ላይ የራሳቸዉን ነጻ ዘገባ ለመስራት ፈጽሞ የሚመርጡት ነገር አይደለም፡፡ በሀገራችን ከሁሉም ከፍተኛዉ ስልጣን አካል የሆነዉ የሀገሪቱ ህግ አዉጭ አካል (ፓርላማ) የደህንነትና ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበተን ያህል አልፎ አልፎ ካልሆነ በስቀተር የመከላከያን ሁኔታ ከስር ከስሩ አዘወትሮ ስለማይከታተል አንድ ቀን ስለ ኤርትራ ድጋሚ ወረራ ወይም ስለግብጽ ጥቃት መሰንዘር ከዜጎች ጋር እኩል ለመጀመሪያ ግዜ በዜና ለማድመጥ እንዳይገደድ እሰጋለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆን የቱንም ያህል ኑሮ ቢከብደዉም፤ “ዲሞክራሲ!” የምትባለዋ ነገር አልሟላ እያለች ቢታስቸግረዉም ሀገሩ ሰላም ትሁን እንጂ በሌላዉ ነገር ብዙም የሚማረር ህዝብ አይደለም፡፡ ምንም ባይሟላለት ምንም ያህል በኑሮዉ ቢማረር ምንግዜም በመንግስት ተስፋ የማይቆርጥ እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ከቶ ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ህዝቡ በጭራሽ በይቅርታ የማያልፈዉ ጉዳይ ቢኖር የሀገሩ ሉአላዊነት ጉዳይ ነዉ፡፡ በሀገሩ ሉአላዊነት መደፈር ላይ ምንም ዓይነት ተልካሻ ምክንያትና ሰበብ እንዲነገረዉ አይሻም፡፡ ለዚህም ነዉ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የሆነ አሳሳቢ ነገር በሰማ ቁጥር መብከንከኑ፡፡

2/ የኢትዩኤርትራ ጦርነት የሕዝብና የመንግስት አንድነት እንደገና የታደሰበትና የህዝቡ አልበገር ባይነት በድጋሚ የተረጋገጠበት አጋጣሚ ነበር፡፡

የኢትዮ–ኤርትራ ጦርነት ሳንፈልገዉ የተቃጣብን መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም ነገር ግን መላዉን ህዝብ በአንድነት እንደ አንድ ሰዉ ሆኖ እንዲቆም ማድረግ ያስቻለ አንድ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ በእኔ እድሜ ይሄኛዉ ሁለተኛ አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያዉ በ1969 ዓ/ም ሲሆን የሶማሊያ የእብሪት ወረራ እንደተሰማ መላዉ ህዝብ በቁጣ የተነሳበት ወቅት ነበር፡፡

ህዝቡ በዚያን ጊዜ በደርግ ስርአት ግራ ተጋብቶ በቀይ ሽብር  እርምጃ ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ወቅት ላይ ነበር ጦርነቱ የተጀመረዉ፡፡ ህዝቡ ለአገዛዙ (ለደርግ) ጥላቻ እንደነበረዉ ባይካድም  ነገር ግን ይህን ጥላቻዉን ለጊዜዉ ወደ ጎን አድርጎ ከመንግስት ጎን በመቆም ለዘመቻዉ እንደ አንድ ሰዉ ሆኖ  በጋራ ተንቀሳቅሷል፡፡ (እንደ ኢህአፓና መኢሶን ከሃዲ ከሆኑ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ዉጭ)፡፡ ስለዚህ የኤርትራ ወረራ ለእኔ በህይወቴ ለሁለተኛ ጊዜ ህዝብ በሉአላዊነቱ ላይ የማይደራደር መሆኑን ያሁበት አጋጣሚ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በነበሩት ስርአቶችም  ሆነ በመንግስታቱ ላይ ደስተኛ ሆኖ ባያዉቅም በሃገሩ ሉአላዊነት ላይ ግን ተደራድሮ አያዉቅም፡፡ በሶማሊያ ጦርነትም ሆነ ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ጦርነት ወቅት የታዬዉ የህዝብና የመንግስት አንድነት መነሳሳት በብዙ መልኩ ተመሳሳይ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጦርነት ግን ጠንከር የሚል ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ እችላለሁ፡፡

2.1/ ከሶማሊያ ጋር ያደረግነዉ ጦርነት በብዙ መጥፎ አጋጣሚዎች የተሞላ ነበር

በወቅቱ ጠንካራ የሚባል ማእከላዊ መንግስት ያልነበረበትና ህዝብና መንግስት  የማይደማመጥበት  እጅግ መጥፎ ጊዜ ነበር፡፡ የሶማሊያ  ወረራ ባካሄደችብን  ወቅት አገሪቱ እጅግ ዉስብስብ ሁኔታ ዉስጥ ስለነበረች ጦርነት ለማካሄድ የሚያስችላት ፤ፖለቲካዊ ፤ወታደራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲዊ  አመቺ ሁኔታዎች ጨርሶ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶቹን የወቅቱን ሁኔታዎች ለማስታወስ ያህል፤

* በአብዮትና በጸረአብዮት ፤በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር እርስበርስ ስንፋጅና ስንተላለቅ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ህዝቡም ሆነ ወጣቱ ከመንግስት ጋር ዓይንና ናጫ የሆነበት ወቅት ነበር፡፡ ማንም ከማንም ጋር የማይስማማበት ይልቁንም ለግዲያ የሚፈላለግበት ወቅት ነበር፡፡ የአንድ እናትና አባት ልጆች በፖለቲካ አቋም ልዩነት እርስበርስ ለግድያ አመቺ ጊዜ የሚጠብቁበት፤ የመንግስት አመራሮችና የደርግ ባለስልጣናት አንዱ ሌላዉን ባለማመኑ ሰበብ እየፈለጉ የሚገዳደሉበት፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ነጭና ቀይ ሽብር እየተባባሉ አርስበርስ የሚጨራረሱበት መጥፎ ጊዜ ነበር፡፡ በዚያ መጥፎ ጊዜ ሁሉም ስለራሱ እጣፋንታ እርግጠኛ ባልነበረበትና ለራሱ ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጵያ ጭራሽ የሚያስብላትና የሚያስታዉሳት ባልነበረበት ወቅት ነበር ጦርነት የተከፈተብንም፡፡

* መላዋ ኤርትራ በአማጽዉ ኃይል (ሻእቢያ) ከአስመራና ከምጽዋ በስተቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በቁጥጥር ስር  ዉላ አስመራንም ተቆጣጥረዉ ከዛሬ ነገ ነጻነታቸዉን ያዉጃሉ ተብሎ በሚሰጋበት ወቅት ነበር ሶማሊያ ወረራ ያደረገችዉ፡፡ በተጨማሪ እንደ ኢዲዮን የመሳሰሉ ታጣቂ ቡድኖችም የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረጉ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡

* አንዳንድ በወቅቱ የነበሩ የመንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሶማሊያን ወረራ በግልጽ በመደገፍ የገዛ ህዝባቸዉን በማደናገርና ሰራዊታችን ወራሪዉን ጦር አምርሮ እንዳይዋጋ በማሻጠር ታሪክ ይቅር የማይላቸዉን በደል ሲፈጽሙ የነበረበት ወቅት ነዉ፡፡ ተራዉ ተዋጊ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የጦሩ አዛዦች ሳይቀሩ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በመታቀፋቸዉ የድርጅት ስሜት ስየተጫጫናቸዉ የሰከነ አመራር ለመስጠትም ተነሳሽነቱ ያልነበራቸዉ ነበሩ፡፡ የአገራቸዉን ሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ከአገዛዙ ከደርግ ለይተዉ ማዬት የተሳናቸዉ ፖለቲከኞች  ህዝቡ ለመንግስት ድጋፍ እንዳይሰጥና ሰራዊቱም እንዳይዋጋ ለማድረግ ብዙ ጥረዋል፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ ሰርገዉ በመግባት እንዳይዋጋ ቅስቄሳ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ምርጥ አዛዦችን እየነጠሉ ከጀርባ ተኩሰዉ በመግደል ከፍተኛ በደል ፈጽሟል፡፡ በዚያ ሁኔታ ዉስጥ ነበር ከሶማሊያ ወራሪ ጦር ጋር ሰራዊታችን ተፋልሞ ሉአላዊነታችንን ያስከበረዉ፡፡

* በወቅቱ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ብዛት ከአራት ክፍለ ጦር የማይበልጥና በሰዉ ኃይልም ቢሆን 35 ሺህ አካባቢ ብቻ የነበረና ለዚያዉም በመላ ሀገሪቱ እንደጨዉ የተበተነ በትጥቅ ደረጃም ከታዬ እጅግ አሮጌ መሳሪያ የታጠቀ ነበር ፡፡ በአንጻሩ ለአስራ አራት ዓመታት በዘመናዊ መሳሪያ ሲደራጅ የቆየዉን የሶማሊያን ወራሪ ግዙፍ ሰራዊት ለመመከት የምንችልበት አቅም አልነበረንም፡፡ አገራችን ግልጽ ወረራ ተቃጥቶባትና በሶማሊያ ጦር ህዝባችን አየተጨፈጨፈ በነበረበት ሰዓት ስለጉዳዩ የተሟላ መረጃ የነበራትና የረዥም ዘመን ወዳጃችን  የነበረችዉ አሜሪካ ሌላዉ ቀርቶ አስቀድመን ለከፈልናት $100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘቡን ተቀብላ መሳሪያዉን ግን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ራሳችን ለመከላከል እንዳንችል በመደረጋችን ሌላ አማራጭ መፍትሄ የጠፋበት ወቅት ነበር፡፡ አሜሪካ ይባስ ብላ በሳዉዲ አረቢያ በኩል $200 ሚሊዮን እርዳታ ለሶማሊያ እንዲደርሳት እንዳደረገች ይታወቋል፡፡ የሶማሊያን  የጦር ዝግጅት ደረጃንና የኛን ለጦርነቱ ያለመዘጋጀት  በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችለን  አንዱ ማሳያ የሶማሊያ ጦር ወረራዉን በጀመረ በጥቂት ወራት ዉስጥ ያን ሁሉ ርቀት ተጉዞ እስከ ሐረርና ድሬዳዋ መድረስ መቻሉ ነዉ፡፡

* የጊዜዉ መንግስት (ደርግ) ዘዉዳዊዉን ስርአት አስወግዶ ስልጣን ከያዘ ገና ሁለት ዓመት እንኳን ባልሞላበትና  ራሱም እንደ መንግስት ባልተጠናከረበት ወቅት ላይ የተሰነዘረ ወረራ ነበር፡፡

* ደርግ ጁኒየር በሆኑ መኮንኖችና የበታች ሹሞች የተቋቋመና ሰፊ የጦርነት ተሞክሮ የነበራቸዉን ሲኒየር መኮንኖችን፤  ጄነራሎችንና ኮሎኔሎችን ግማሹን ያለጊዜያቸዉ በጡረታ አሰናብቶ፤ ግማሾቹን አስሮና ገድሎ ሰራዊቱን አመራር አልባ ባደረገበት ወቅት ነበር ጦርነቱ የተነሳዉ፡፡

አገራችን በወቅቱ ደርግ ይከተለዉ በነበረዉ የተዛባ የርዕዮተዓለም አቅጣጫ ምክንያት ለዘመናት የቅርብ አጋራችን የነበረችዉ አሜሪካ ፊቷን ማዞሯ ሳያንስ በምትኩ ሌላ አጋር የሚሆነን ወዳጅ አገር ባላዘጋጀንበትና ደርግም ራሱ እንደ መንግስት በሌሎች መንግስታት በደንብ እዉቅና ባላገኘበት ወቅት ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ሶማሊያ ለወረራ እየተዘጋጀች መሆኑን ደርግ ከሰባት ወራት በፊት ጀምሮ መረጃዉ ቢኖረዉም አጋር የሚሆነዉ አንድም አገር አስቀድሞ ባለማዘጋጀቱና የዉጭ ድጋፍ ሊያሰጠዉ የሚችል ዲፕሎማሲያዊ ስራም መስራት ባለመቻሉ በሁሉም ነገር ተበልጠን እጃችንን አጣጥፈን ወረራዉን ተቀበልነዉ፡፡

በኋላ የጎረፈዉ ወታደራዊም ሆነ ዲፕሎማሲዊ ድጋፍ (ሶቭየት ህብረት ፤ኩባ፤ የመን፤ምስራቅ ጀርመን) እጅግ ዘግይቶ ቢሆንም ለሉአላዊነታችን መከበር ትልቅ እገዛ አድርጎልናል፡፡ በዚህም ባለዉለታችን ናቸዉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት  በሰዉ ኃይሉም ሆነ በትጥቁ ደካማ ሆኖ እንዲቆይ በማድረግ ለሶማሊያ ወረራ እንድንጋለጥ በማድረግ ረገድ ንጉሱም ጭምር ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ ይህ ሲባል ንጉሱ አንዳችም ጥረት አላደረጉም በሚል አሰተሳሰብ አይደለም፡፡

አጼ ኃይለሥላሴ በወቅቱ እጅግ ዘግይተዉም ቢሆን የሶማሊያ አዝማሚያ ሲላሰጋቸዉ የጦር መሳሪያ ፍለጋ በ1965ዓ/ም የወቅቱ ወዳጃቸዉና ዋነኛ የመሳሪያ አቅራቢያቸዉ ወደነበረችዉ አሜሪካ አቅንተዉ ፕሬዝዳንት ኒክሰንን ቢማጸኑም “ሱማሊያ አትወጋችሁም” በሚል ማጽናኛ ይሁን ማዘናጊያ አንድም መሳሪያ ሳይሰጧቸዉ ነዉ ያሰናበቷቸዉ፡፡ ንጉሱ በዚህም ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ሩሲያ በማቅናት ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርቡም የሩሲያ ባለስልጣናትም ከአሜሪካ ጋር የተመካካሩበት ይመስል ልክ አሜሪካኖች እንዳሉት “ሶማሊያ አትወጋችሁም” የሚል መልስ ነበር ለንጉሱ የሰጡት፡፡ ንጉሱ በመጨረሻ ወደ ቻይና በመብረር ጥቂት መሳሪያዎች ከማግኘት በስተቀር የረባ ድጋፍ ሳያገኙ ቀሩ፡፡

ንጉሱ መሳሪያ በነጻ ወይንም በብድር ማግኘት እንደማይችሉ ዘግይተዉም ቢሆን በመረዳታቸዉ በገንዘብ መግዛት ይሻላል በሚል እንደምንም የዉጭ ምንዛሪ  አፈላልገዉ ለአሜሪካ መንግስት ቅድመ ክፍያ ቢያደርጉም የተጠየቁት መሳሪያዎች ወደ ሀገር ቤት ከመግባታቸዉ በፊት ንጉሱ ከስልጣን ወረዱ፡፡ ከዚያ በኋላ አሜሪካ ለጥቂት ጊዜ የተወሰኑ መሳሪያዎችን መስጠቷ ባይቀርም ነገር ግን የካርተር ወደ ስልጣን መዉጣት ተከትሎና ደርግ በተከታታይ በወሰዳቸዉ እርምጃዎችና በተከተለዉ የሶሻሊስት ርዕዮተዓለም በመከፋት በአጸፋዉ አሜሪካ አንዳችም መሳሪያ ለኢትዮጵያ እንደማታቀብል አስታወቀች፡፡ የሶማሊያ ለወረራ መዘጋጀት  ከጥርጣሬ በላይ ተግባራዊ በሆነበትና የአሜሪካ የረዥም ዘመን ወዳጅ የሆነችዉ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ወረራ ተፈጽሞባት እያዩ አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ ፊታቸዉን አዞሩ፡፡

በአጭር ጊዜ ዉስጥ 90% የሚሆነዉ የኦጋዴን ግዛታችን በሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ዉሎም አሜሪካ ልታግዘን አልሞከረችም፡፡ ደርግ የኋላ ኋላ ከሶሻሊስቱ ጎራ የመሳሪያና ፖለቲካዊ ድጋፍ ስለጎረፈለት በመልሶ ማጥቃት ሉአላዊነታችንን በማስመለስ አስመስጋኝ ስራ መስራቱ ባይቀርም ሃላፊነት እንዳለበት መንግስት ሲታይ ግን በሀገሪቱ ዉስጥ ፈጥሮ በነበረዉ ምስቅልቅል ሁኔታ ምክንያት በመጀመሪያ ሰባት ወራት ሶማሊያ ላደረሰችብን  አንገት የሚያስደፋ ዉርደት በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም፡፡ የሀገሪቱ ሉአላዊነት በጠላት ተደፍሮ እያለ በአንድነት መቆም የተሳነዉን የመንግስት ስርአት የፈጠረዉ ደርግ በመሆኑ ተጠያቂ ቢሆን አይበዛበትም፡፡  አገሪቱን ወዳጅ አልባ ያደረጋት ደርግ በመሆኑ ጭምር ነዉ፡፡

2.2/ በሱማሊያ ወረራ ወቅት ህዝቡ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጥላቻ በሰራዊቱ ላይ ደግሞ ጥርጣሬና ፍርሃት ነበረዉ

የሶማሊያዉ ወረራ ከመነሳቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ጀምሮ ህዝቡ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጥላቻ መኖር ብቻ ሳይሆን በሰራዊቱ ላይም ቢሆን የነበረዉ አመለካከትም በፍርሃትና በጥርጣሬ የተሞላ ነበር፡፡ በራሱ በደርግ አመራር ዉስጥም ሳይቀር ከፍተኛ ልዩነትና የመጠፋፋት መንፈስ ነፍሶ አንዱ ሌላዉን በዓይነ ቁራኛ የሚጠብቅበት ወቅት ነበር፡፡

የኤርትራ ጉዳይም ሊያበቃለት የመጨረሻዉ ጫፍ ላይ የደረሰበት ወቅት የነበረና የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊትም ጦርነት ለማካሄድ የሚችልበት አንዳችም አቅም ያልነበረዉና አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በሚነዙት አፍራሽ ፕሮጋንዳ ሰራዊቱን በመከፋፈል ጠንክሮ እንዳይዋጋ ያደረጉ ክስተቶች የተሞሉበት ወቅት ነበር፡፡ ለማስታወስ እንኳን በሚያስጠላ ደረጃ  የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና መንግስቱ ኃይለማሪያምን ለይተዉ ማዬት ያልቻሉት እነ ኢህአፓና መኢሶን ወራሪዉን ሰራዊት በመደገፍና በኛ ሰራዊት ላይ በማሻጠር በአገርና በህዝብ ላይ የፈጸሙትን ታሪክ ይቅር የማይላቸዉን ደባ ስናስታዉስ በወቅቱ የተሟላ የመንግስትና የህዝብ አንድነት መንፈስ ነበር ለማለት ያዳግታል፡፡

የማይካድ ነገር ሀዝቡ የሀገሩ ሉአላዊነት ጉዳይ ሆኖበት መንግስትን እየጠላም ቢሆን ለሉአላዊነት የሚደረገዉን ተጋድሎ ሙሉ በሙሉ በመደገፍ ሴት ወንድ ሳይባል በነቂስ ወጥቶ የተጠየቀዉን ሁሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በአጭር ግዜ ዉስጥ በመቶ ሽህ ዩሚቆጠር ሚሊሽያ ሰራዊት አሰልጠኖ አስታጥቆ ማዝመት የተቻለበት ከፍተኛ ብሄራዊ መነሳሳት የታየበት አጋጣሚ ነበር፡፡

ያሁኑ ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ጦርነት ከምንግዜም የበለጠ መላዉን ህዝብ በወራሪዉ የሻዕቢያ ሰራዊት ላይ በአንድነት ማቆም ያስቻለ የመንግስትና የህዝብ አንድነት ከምንግዜም በላይ የተረጋገጠበት ታላቅ ታሪካዊ አጋጣሚ ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ የሻዕቢያን የድፍረት ወረራ ተከትሎ በጊዜዉ የነበሩት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለህዝቡ ጥሪ ባደረጉለት መሰረት ጥሪዉን እንደሰማ ኦሮሞዉ፤ ትግራዩ፤ አማራዉ፤ ሶማሌዉ፤ ጉራጌዉ ፤ኮንሶዉ ፤ደራሼዉ ፡ጋሞዉ፡ ወላይታዉ፤ ሲዳማዉ አፋሩና ጋምቤላዉ ወዘተ አንዱ ሌለዉን ሳይቀድሙኝ ልቅደም በሚመስል ሩጫ ጦር ግንባር ለመገኘት የበቃበት ወቅት ነበር፡፡

እንደ ደርግ ወቅት የግዴታ አፌሳ የለ! በግድ ዝመት የለ! በግድ ለጦርነቱ ገንዘብ አዋጣ የለ! ህዝቡ ራሱ ልጆቹን መርቆ ከላከ በኋላ ጭራሽ ይሄም አንሷል ብሎ ሰንጋ በሬና የፍዬል ሙክቱን እየነዳ ጦር ግንባር ምሽግ ድረስ የመጣበት ወቅት ነበር፡፡ ከአፋርና ከሶማሌ ክልል ልጆቻቸዉንና ባሎቻቸዉን ለማበረታታት ያን ሁሉ አገር አቆራርጠዉ ጦር ግንባር ድረስ የሚመጡ ዜጎች ብዙ ነበሩ፡፡

በዉጭ አገር የሚኖሩ የመንግስት ተቃዋሚ የነበሩት ሳይቀር ከአሜሪካ ከአዉሮፓ ከመካከለኛዉ ምስራቅ በቡድንና በግል እየመጡ በየጦር ግምባሩ እየዞሩ ሰራዊታችንን ሲያበረታቱ ማዬትን የመሰለ የሚያስደስት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ከታዘብኩትና እጅግ ከአስገረሙኝ ሁኔታዎች ዉስጥ አንዱ እድሜያቸዉ ለዉትድርና ብቁ የማያደረጋቸዉና በዚህ ምክንያት ላንመለመል እንችላለን ብለዉ የተጠራጠሩ ወጣቶች ሰራዊት ጭነዉ ወደ ጦር ግንባር በሚያመሩ መኪናዎች ላይ እየተንጠላጠሉ ጦር ግንባር ድረስ በገዛ ፈቃዳቸዉ የመጡ በርካታ ወጣቶች እንደነበሩ አስታዉሳለሁ፡፡

3/ አገራችን ከኤርትራ ጋር ያደረገችዉ ጦርነት ለበርካታ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች መከሰት አጋጣሚና ምክንያት የሆነ ታሪካዊ ጦርነት ነዉ

ጦርነቶች አዉዳሚ ባህሪያቸዉ እንዳለ ሆኖ አንዳንዴ የጦርነቱን ፍጻሜ ተከትሎ በሌላ ጊዜ ብዙም የማይጠበቁ ለየት ያሉ ሁኔታዎች በሀገሪቱ ዉስጥ መከሰት ምክንያት ሲሆኑ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ በእኔ እይታ ትልቅ ፋይዳ አላቸዉ ብዬ ከማስባቸዉ መካከል ጎላ ጎላ ያሉትን ለአብነት ያህል ቀጥዬ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

* የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርአት ህዝቡንበጠባብ ጎሰኝነት ስሜት እርስበርስ እንዲቃቃር ስላደረገ አንድ ችግር  ቢፈጠር አገሪቷ ከመቅፅበት ትበታተናለች እንዳልተባለ የመንግስትንና የህዝብን አንድነት የስርአቱንም ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያስቻለ አንድ አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡

* የኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታ ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት በቅድሚያ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ያደረገዉ ጥረትና ለሰላም ያሳየዉ ቁርጠኝነት አገራችንን በዉጭዉ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትና ተሰሚነት እንድታገኝ አስችሏል፡፡

* ከጦርነቱ መከሰት ጋር ተያይዞ በመንግስት ፖለቲካ አመራር አካባቢ በተለይም በገዢዉ ፓርቲ ዉስጥ ለተከሰተዉ እርስ በርስ መከፋፈል ዋነኛዉ መንስኤም ይሄዉ ጦርነት መሆኑን የሚታወቅ ነዉ፡፡ በተጨማሪ በመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችና በሀገሪቱ የሲቪል አመራር መካከልም ጤናማ ግኑኝነት እንዳልነበር ይልቁንም የሲቪልወታደር ግንኝነቱ ትልቅ ክፍተት ያለዉ እንደነበር ያመላከተ አጋጣሚ ነዉ፡፡ ገዢዉ ፓርቲም ችግር እንዳለበት ተረድቶ ራሱን በሚገባ እንዲፈትሽና አንዳንድ ማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሲላስቻለዉ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በፊት ያልነበረዉን ጥንካሬ በሂደት ይዞ እንዲገኝ ማድረግ ያስቻለ ክስተት ይመስለኛል፡፡

* በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥም ከጦርነቱ በፊት ብዙ ግምት ያልተሰጣቸዉ በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች፤ የመብት ጥሰቶችና አድሎአዊ አሰራሮች በበላይ አመራሮች ቸልተኝነት መፍትሄ ሳይሰጣቸዉ ተከማችተዉ የነበሩበትና የጦርነቱ ማብቃት ተከትሎ በተደረጉት የተሃዲሶ እንቅስቃሴዎችና ሰፋፊ ግምገማዎች ታፍነዉና ወይም ችላ ተብለዉ የነበሩ የተከማቹ  ችግሮች በከፍተኛ ጥረት ሊቀረፉ የቻሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በነበሩ ግምገማዎች ይፋ የተደረጉ ችግሮችን ዓይነትና ብዛት ለታዘበ ሰዉ ይሄን ሁሉ ችግር ተሸክሞ ሰራዊታችን በጦርነቱ እንዴት ሊያሸንፍ ቻለ? ብሎ መደነቁ አይቀርም፡፡

* ከደርግ ዉድቀት በኋላ የቀድሞዉን ሰራዊት ሳያካትት በአዲስ መልክ ለተቋቋመዉ መከላከያ ሰራዊት ብቃቱን ለመፈተሽ ያስቻለ ትልቅ አጋጣሚም ነበር፡፡ መንግስት የሀገሪቱን ነባር ሰራዊት አፍርሶ አገሪቱን ለአደጋ ተጋላጭ አድርጓል የሚሉ ትችቶች በፊት በተደጋጋሚ ሲነሱ እንዳልነበር ከጦርነቱ በኋላ ስለዚህ ጉዳይ እምብዛም ሲነገር አልተደመጠም፡፡ በጦርነቱ ወቅት በርካታ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ፈቃደኛና ብቁ ሆነዉ የተገኙት ተመልምለዉ የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንዳደደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዉጭ ሀገር በጥሩ ደሞዝ በሙቸዉ ተቀጥረዉ ጥሩ ኑሮ ሲኖሩ የነበሩ የአየር ኃይል ፓይለቶች ሀገራቸዉ መወረሯን እንደሰሙ ጨርቄን ሳይሉ ገስግሰዉ በመድረስ በጦርነቱ ላይ አኩሪ ስራ ሰርተዋል፡፡ በዚህ መንገድ ከዉጭ ከመጡት መካካል ዛሬም ድረስ በአየር ኃይሉ ዉሰጥ እያገለገሉ የሚገኙ ፓለቶች አሉ፡፡

* የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ጦር ከማዝመቱ በፊት ከሱዳን፤ ከየመንና በጅቡቲ ጋር እየተጋጨና የሽብር ተግባራትን በተደጋጋሚ በመፈጸም ቀጠናዉን እያወከ መሆኑን እያወቁ ምእራባዉያን መንግስታት በኤርትራ መንግስት ላይ አንዳችም ግሳጼም ሆነ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማስጠንቀቂያ ሊሰጡት አልሞከሩም፡፡ የሻዕቢያ መንግስትም በዚህ ተበረታትቶና የልብ ልብ ተሰምቶት በኢትዮጵያ ላይም ጦር በመስበቁ የኢትዮጵያ መንግስት ግን የኤርትራን ዉንብድና እንዲጋለጥ በማድረግ በተከታታይ ጠንከር ያሉ መዕቀቦች እንዲጣልባትና ከዓለም ማህበረሰብ እንድትገለል ለማድረግ አስችሎአል፡፡

* ከሁሉም በላይ ደግሞ የሻዕቢያ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብት በግላጭ መበዝበሩ ሳያንሰዉ በዚሁ በራሳችን ህዝብ መሃል ሆኖ ዜጎቻችንን በጠራራ ፀሐይ እያፈነ የዉንብድና ተግባር ሲፈጽም ህዝባችን እያዬ ከማዘንና ዉጭ ምንም ማድረግ ባልቻለበት ሁኔታ የተነሳዉ ይህ ጦርነት ይህን ሁሉ ህገወጥ ድርጊት ለማስቆም መልካም አጋጣሚ አልነበረም ማለት አይቻልም፡፡

* በኤርትራ መገንጠል (ራሷን የቻለች መንግስት በመሆኗ) በጣም ሲቆጩና ሲያዝኑና ኤርትራን የማታካትት ኢትዮጵያን ለመቀበል በጣም የተቸገሩ ኢትዮጵያዉያንን ብቻ ሳይሆን እንደ ዋዛ የተነጠሏትንየቀድሞ እናት አገራቸዉንኢትዮጵያንድጋሚ እንቀላቀል ይሁን? በሚል በተስፋ መኙ ለነበሩ ኤርትራዉያን  ጭምርዳግመኛ እንድ እንሆለንየሚለዉን ምኞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያዳፈነ መጥፎ አጋጣሚ ነዉ፡፡  

4/ ጦርነ የመከላከያ ሰራዊታችን ተጋድሎ ታሪክ ተገቢዉ ቦታ አልተሰጠዉም!

ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አነስተኛ ግምት የሠጠነዉ ይመስላል፡፡ በጦርነቱ ላይ ያደረግነዉ ተጋድሎ የከፈልነዉ መስዋእትነትና የደረሰብን ጉዳት ሁሉ ገና በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲህ በቀላሉ መዘንጋት ነበረበት ብዬ አላስብም፡፡ ከኤርትራ ጋር ገና ያልተቋጨ ብዙ ጉዳይ እያለን በቀላሉ ሊዘነጋ አይገባዉም፡፡

ሁላችንም እንደምናዉቀዉ በ1990 ዓ/ም ስለተቀሰቀሰዉ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት የሚያወሱ ጥቂት መጻህፍትና የተወሰኑ መጣጥፎች በስተቀር በተለይ በአማርኛና የጉዳዩ ባለቤት በሆነዉ በጦርነቱ ተሳታፊ የመከላከያ አባላትም ሆነ በመንግስት ባለስልጣናት ብዙ አልተጻፈም፡፡ ስለዚያ ጦርነት በግልም ሆነ በመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ብዙ የተወራበት አይመስለኝም፡፡ ፡ስለ ጦርነቱ የሚተርኩ ድርሳናት ጭራሽ የሉም ባይባልም በሚፈለገዉ መጠን አይመስለኝም፡፡ ለዚያዉም በዉጭ ቋንቋ የተጻፉት ይበዛሉ፡፡

ግን ለምን ይሆን ያን ያህል ልጆቻችን በጀግንነት የወደቁበትና  በርካታ ኢኮኖሚያዊ ዉድመትና ፖለቲካዊ መመሰቃቀል  ያስከተለ ጦርነት በታሪክ ፀሃፊዎች፤ በተመራማሪዎች ይሁን በወታደራዊ ጠበብቶች ወዘተ በተገቢዉ መንገድ አለመዳሰሱ? በተለይ ጦርነቱ ከአነሳሱ እስከ አፈጻጸሙ የነበረዉን ጠንካራና ደካማ ጎን ሙያዊ በሆነ መንገድ ገለልተኛ በሆኑ አካላት አለመገምገሙስ ለምን ይሆን?

አሜሪካ አንድ ወር ብዙም በማይበልጥ  አጭር ቀናት ስለተጠናቀቀዉና ይሄን ያህል ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ኪሳራ ባልከፈለችበት (በጦርነቱ የሞተዉ የአሜሪካ ወታደር ቁጥሩ ከአራት መቶ አይበልጥም) የመጀመሪያዉ የባህረ ሰላጤዉ  ጦርነት ላይ የሚተነተኑ በሺህ የሚቆጠሩ የምርምር ጽሁፎችና የታሪክ ዘጋቢ መጽሀፍት መጻፋቸዉን ላወቀ ሰዉ እኛ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖች ስለወደቁበትና ያለማቋረጥ ለሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ለጠየቀዉ ጦርነት  በጣት የሚቆጠሩ  መጻፍት እንኳን መነፈጋችን እጅግ ያስቆጫል፡፡  

አሁን አሁንማ  አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ስለጦርነቱ የሚነሳ ወግም ሆነ የርስበርስ ጭዉዉት ብዙም አይሰማም ፡፡ ሁሉም ነገር የተረሳና ምንም እንዳልተፈጠረ የተቆጠረ መስሏል፡፡ ነገር ግን በዚያ ጦርነት ላይ ልጆቻቸዉ መስዋእት የሆኑባቸዉና በዚያ ጦርነት ምክንያት ቤት ንብረታቸዉ የወደመባቸዉና ከቀያቸዉ የተፈናቀሉ በጦርነቱ ቀጠና አካባቢ የነበሩ ወገኞቻችን መቼም ቢሆን ይዘነጉታል ብዬ አላስብም፡፡

በመቀለ አይደር ትምህርት ቤት ህጻናት ላይ የደረሰዉ አረመናዊ ጭፍጨፋስ እንዴት ሊዘነጋ ይችላል? በጭራሽ ሊዘነጋ የማይችል ፤ሊዘነጋም የማገባዉ ነዉ፡፡ በርግጥ የመከላከያ ሰራዊታችን አሁንም በዚያዉ በኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ላይ ሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ በተጠንቀቅ ቆሞ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ስለምናዉቅ ሰራዊታችንንም ሆነ መንግስት ጉዳዩን ትቶታል ለማለት አያስደፍርም፡፡

እንደሚታወቀዉ መከላከያ ሰራዊታችን አስገራሚ በሆነ ጀግንነት በአጭር ጊዜ ዉስጥ ያሻዕቢያን ወራሪ ኃይል እየደመሰሰ የተወሰደበትን ሁሉ ለማስመለስ ሁለት ዓመት በላይ አልፈጀበትም፡፡ ያ ሁሉ ድል ያለ መስዋእትነት የመጣ እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ በጦርነቱ ስለተከፈለዉ መስዋእትነት መጠን በይፋ ባይነገርም ነገር ግን ቀላል የማይባል መስዋእትነት እንዳስከፈለን ለማንኛችንም ግልጽ ነዉ፡፡

ህዝቡን ያስከፋዉ የመስዋትነቱ መብዛት አይደለም፡፡ ለሀገር ሉአላዊነት በሚከፈል መስዋትነት ላይ በህዝባችን ዘንድ እንደ ጥያቄ የሚነሳ አይደለም፡፡ የህዝቡ መከፋት መነሾ የልጆቻቸዉን ደም ዋጋ በሚያሳጣ መልኩ ተገቢዉ ክብር አልተሰጠም በሚል ነዉ፡፡ ታዲያ ጥያቄዉ ለምንድነዉ ደራሲዎች፤ ጋዘጤኞች ፤ የታሪክ ጸሃፊዎች፤ወዘተ መጭዉን ትዉልድ ሊያስተምር  በሚያስችል ደረጃ በብዕራቸዉ መዳሰስ ያልፈለጉት የሚል ነዉ?

ለመሆኑ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተዉ መከላከያ ሚኒስቴርስ ጦርነቱን በሚመለከት ያደረገዉ ጥልቀት ያለዉ ግምገማስ ነበር? ስለጦርነቱ በባለሙያ አስጠንቶ ጠንካራና ደካማ ጎኑን ለይቶ ሰራዊቱ እንዲማርበት ያላደረገዉስ ለምንድነዉ? (ምናልባት ከቅርብ ግዜ ወዲህ አድርጎ እንደሆነ አላዉቅም)፡፡ እንዳይገመገም የሚከለክለን የተለየ ምስጢር ያዘለ ቢሆን ነዉ ወይንስ መገምገም የማይገባዉ ስለሆነ ነዉ?

ሰራዊታችን ለሰራዉ አኩሪ ገድልና ለከፈለዉ መስዋእትነት ሃዉልት ባይቆምለት እንኳን ቢያንስ ህዝቡ ስለ ልጆቹ ጀግንነት እንዲያዉቅ፤ መጭዉ ትዉልድም እንዲማርበት ተደርጎ የማይዘገበዉስ ለምንድነዉ? የሻዕቢያ መንግስት እንደሆነ በሱ ጠብ ጫሪነት ተጀምሮ በሱ ሽንፈት ስለተጠናቀቀዉ ጦርነት ማዉራትና መተረክ ስለማይችል ከዚያ ይልቅ በየጊዜዉ ለህዝቡ የሚያሳየዉ የቆየዉን የድሮዉን ከደርግ ጋር ተደርጎ የነበረዉን የናቅፋን፤ የአፋበትን ፤የከረንን ፡የምጽዋን ወዘተ ዉጊያ ላይ ሰራሁ ስለሚለዉ ገድል ብቻ ነዉ፡፡

ስለ ባድመ ጦርነት ግን ሻዕቢያ ብዙ ሲያወራ አይደመጥም፡፡ ያን ማድረግም አይጠበቅበትም፡፡ ምክንያቱም  በባድመ ጦርነት ምንም የሚያኮራ ታሪክ ስለሌለዉ ማዉራት አይችልም፡፡ በእኛ በኩል ግን ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ጦርነት በአስደናቂ ገድሎች የታጀበና አኩሪ ታሪክ የተሰራበት ሆኖ እያለ ብዙ ሊባልበት ሲገባ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም መባሉ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ትላንት በጦርነቱ ወቅት ድንቅ አመራር ሲሰጡ የነበሩ ጄኔራሎች፤ የመንግስት አመራሮችም፤ ጋዜጠኞችና ታሪክ ምሁራን  ዛሬ በህይወት እያሉ ያልተነገረ ታሪክ ነገ ይነገራል ብዬ አላስብም፡፡

ሻዕቢያ ስለ ናቅፋ ስለ ምጽዋ፤አፋበት፤ ስለ ከረን ወዘተ ለማዉራት የማይሰንፈዉን ያህል እኛም ከዚያ ባልተናነሰ ሁኔታ በርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት (ደርግን ለመጣል የተደረገዉን ትግል) ተሰራ ስለተባለዉ ገድል ሰፋ ያለ የአየር ሰአት ተሰጥቶት ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በከፍተኛ ግለትና ወኔ ስንተርክ ቆይተናል፡፡ ያ የደርግን ስርአት ለመጣል በተካሄደዉ ጦርነት የተሰራዉ ገድል የታሪካችን አንድ አካል በመሆኑ መተረኩ ማንኛችንንም አስከፍቶን አያዉቅም፡፡

ነገር ግን ቅር የሚያሰኘን ነገር የኤርትራን ወረራ ለመቀልበስ ስለተደረገዉ  ጦርነት  የዚያን አንድ አስረኛዉን ያህል እንኳን ለመተረክ አለመሞከሩ ነዉ፡፡ እንዲያዉም ስለዚያ ጦርነት በመንግስት ሚዲያ ሳይቀር ለመጨረሻ ግዜ የተነገረበትን ወቅት መቼ እንደነበር ለማስታወስም  አልችልም፡፡

ባለፈዉ ዓመት ይመስለኛል በርካታ ጋዜጠኞችና የጥበብ ሰዎች ከደርግ ጋር ጦርነት የተደረገባቸዉን ቦታዎች ለመጎብኘት ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸዉ ትልቅ ባጀትም ተመድቦ እንዲጎበኙ ተደርጎ ለበርካታ ሳምንታት ያለመቋረጥ ሲተርኩ ከርመዋል፡፡ እንደዚያ በመደረጉ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከደርግ ጋር የተደረገዉ ትግል የታሪካችን አንድ አካል በመሆኑ በሚገባ ሊዘገብ የሚገባዉ ነዉ፡፡ እኔም እያንዳንዱን የትግሉን ዘመን ትረካ በከፍተኛ ፍላጎት ነዉ ስከታተል የቆየሁት፡፡ ዛሬም ቢሆን እንደ አዲስ ታሪኩን ማንበብ ያስደስተኛል፡፡

ነገር ግን ጥያቄ የሚያስነሳዉ ራሱን የቻለ የጉብኝት ፕሮግራም ባይዘጋጅለት እንኳን ቢያንስ እግረ መንገዳቸዉን ከኤርትራ ጋር ጦርነት የተደረገባቸዉን ቦታዎችን እንዲጎበኙ ያልተደረገዉ ለምንድነዉ? የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ሌላዉ ቢቀር ጦርነቱ የተቀሰቀሰበትን ባድመን እንኳን ማስጎብኘትስ አይቻልም ነበር እንዴ?

ለመሆኑ በሻዕቢያ ጄቶች አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተደረገበትን አይደር ት/ቤትን ጎብኝተዋል? በሻዕቢያ ሆነ ተብሎ በፈንጂ የፈራረሰዉን ዛላምበሳንስ አስጎብኝተናቸዋል? የኤርትራን ወረራ ለመቀልበስ ከሰባ ሺህ የማያንሱ ጀግኖች የወደቁበትና በርካቶች አካለ ጎደሎ የሆኑበት ጦርነት ለመወራትና ለመነገር ስለማይመጥን  ነዉ ችላ የተባለዉ? እንዲህ በቀላሉ የሚዘነጋስ ነበር እንዴ የባድመ ጦርነት?

ስለኤርትራ ጦርነት ሲነሳ በርካታ ጠንካራ ጎኖች የመኖራቸዉን ያህል በሌላ ጊዜ ሊደገሙ የማይገባቸዉ ድክመቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነዉ፡፡ በየትኛዉም ጦርነት ቢሆን ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ድክመትም ሊኖር መቻሉ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ከሁሉም ትልቁ ጥፋት ግን ስለጦርነቱ ጭራሽ አይወራ አይነሳ የተባለ የሚያስመስለዉ ዝምታ ነዉ፡፡

በዚያ ጦርነት የወደቁ የኢትዮጵያ ጀግኖች ቢወደሱበት ፤የኢትዮጵያ  ህዝብ ለጠላት አይበገሬነቱን በድጋሚ ስላስመሰከረበት ስለዚያ ጦርነት መነገር ብቻ ሳይሆን ቅኔ ቢቀኝበት፤ ቢዘመርለትና ፊልም ቢሰራበት ፤መታሰቢያ ሃዉልት ቢቀረጽለት የሚከፋዉ ወይም መብቱ የሚነካበት ከመካከላችን ይኖር ይሆን? ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ጦርነት በታሪካችን ትልቅ ስፍራ የሚይዝ መቼም የማይዘነጋ ጦርነት ሆኖ እያለ ከድክመታችንና ከጥንካሬአችን ልንማር በሚያስችለን ደረጃ የሀገሪቱ መከላከያ አስካሁን በአግባቡ ያልገመገመበትስ  ምክንያት ምንድነዉ?

በአንድ ወቅት ከጦርነቱ በኋላ የጦርነቱ ግምገማ መሰል ነገር ተጀምሮ በኋላ አቅጣጫዉን እየሳተ ጣት መጠቋቆም ሲመጣ እንዲቆም መደረጉ ይታወቃል፡፡ ምስጢራዊነቱን ለመጠበቅ ከተፈለገ ቢያንስ በሚመለከታቸዉ ከፍተኛ አመራሮች ደረጃ እንኳን ግምገማ ማድረግ እየተቻለ ጭራሽ ለማድረግ አልተፈለገም፡፡ ለመሆኑ በጦርነቱ አሸናፊዎቹ እኛ ለመሆናችን ማረጋገጫ ለሚጠይቁንስ እንዴት ነዉ የምናስረዳዉ? ስለ ትላንቱ ጦርነት በሚገባ ሳንገመግም ነገ ከኤርትራ ጋር ለሚኖረን ሌላ ዙር ጦርነትስ እንዴት ነዉ መዋጋት የምንችለዉ?

ጦርነቱ ያለአንዳች ችግርና አንድም መስዋትነት ሳንከፈል አንድም ጉዳት ሳይርስብን እንደዋዘ የተገኘ እንዲመስል ለሚፈልጉ አንዳንድ ወገኖች ኤርትራ ገና እንደ ሀገርና እንደ መንግስት አንድ አስር አመት እንኳን እድሜ ባልነበራት ወቅት እንደዚያ ያንቆራጠጠችን ዛሬ ከሃያ ዓመታት በኋላ ልትደርስበት የምትችልበት ጦርነት የማካሄድ አቅም (war making capability) ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ከአስራ ስምንት ዓመታት በኃላ አሁን ያለችዋ ኤርትራ የድሮዋ ኤርትራ እንዳልሆነችና ለዛሬዋ ኤርትራ አቅም የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት በቅድሚያ ስለአለፈዉ ጦርነት በሚገባ መገምገም በተገባ ነበር፡፡

የጦርነት ግምገማ ደግሞ የመከላከያ ጄኔራሎች ማድረግ ሲፈለጉ የሚደረግ ስላልፈለጉ ደግሞ የሚተዉት ሊሆን አይገባዉም፡፡ ግምገማዉን መምራት የሀገሪቱ ፖለቲካ አመራር ሃላፊነት በመሆኑ መከላከያ ፍላጎት ባይኖረዉ እንኳን የሀገሪቱ ፖለቲካ አመራሩ(ጠቅላይ አዛዡ ፤መከላከያ ሚኒስትሩና የፓርላማ የመከላከያ ኮሚቴ) ግምገማዉን በራሱ አመራር ሰጭነት ማድረግ ይገባዉ ነበር፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን የኤርትራን ሰራዊት ረግጠን ፤አይቀጡ ቅጣት ቀጥተን አፈር ድሜ አስግጠን፤ ደምስሰን ወዘተ ዓይነት ፉከራዎች አንዳችም ጥቅም የላቸዉም፡፡

እኛ ብቻ ሳንሆን ኤርትራዉያን ራሳቸዉ ጠንቀቄዉ የሚያዉቁትን ሽንፈታቸዉን እኛ ደጋግመን ስላወራንና ስለፎከርን  ትርጉም አይኖረዉም፡፡ ትልቅ ትርጉም ሊኖረዉ ይችል የነበረዉ ጦርነቱን ከአነሳሱ እስከ ፍጻሜዉ በሚገባ በመገምገም ትምህርት ወስደንበት ቢሆን ነበር፡፡ ያለፉ ጦርነቶችን ጠንካራና ደካማ ጎናችንን በጥንቃቄ ሳንገመግም ከኤርትራም ሆነ ከሌላ ባላጋራ ጋር ወደፊት ለሚገጥመን ጦርነት በድሮዉ ያረጀ አሰተሳሰብ ወደ ጦርነቱ ልንገባ ስለምንገደድ ገና ሳንዋጋ ለሽንፈት የሚዳርገን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡  

ሌላዉ ቀርቶ በራሱ በመከላከያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ፕሮግራሞች እንኳን አልፎ አልፎ ስለጦርነቱ ለማዉሳት ያልበቃነዉ መናኛ ጉዳይ ስለነበረ ነዉ? ለምን ተገቢዉን ቦታ እንዳልሰጠነዉ ምክንያቱ ለእኔ  በጭራሽ አይገባኝም፡፡ ከዛሬ አራት አስርት ዓመታት በፊት በሶማሊያ የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት የተደረገዉን እልህ አስጨራሽ ጦርነት አስመልክቶ በሚገባ ተቀምሮ የተዘጋጀ የታሪክ ሰነድ ባለመኖሩ ስንቆጭ እንዳልነበርን ዛሬ እንደልብ መረጃ ማግኘት በሚቻልበት ዘመን ላይ ሆነን ከኤርትራ ጋር ስላደረግነዉ ጦርነት በመረጃ የተደገፈና በሚገባ ተቀምሮ የተዘጋጀ የታሪክ ሰነድ አለመኖሩ መልካም አይመስለኝም፡፡

በተለይም የሀገራችን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት በዋነኛነትም የከፍተኛ የአመራርነት የእስታፍ ኮሌጅ ሀገራችንን በተለያዩ ጊዜያት ከዉጭ ወራሪዎች ጋር ስላደረገችዉ ጦርነቶች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉበትና  ሰልጣኞችም የመመረቂያ ጽሁፍ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ለመሆኑ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት የምርምር ጽሁፎችን የሚያቀርቡበት አዳዲስ የጦርነት ንድፈሃሳቦችና ተሞክሮዎች፤ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር ትዉዉቅ ለመድረግ የሚረዱ፤ የዩንቨርስቲ ምሁራንና የምርምር ተቋማት በመከላከያና በደህንነት ጉዳይ ላይ የጥናት ጽሁፎችን የሚያቀርቡበት፤ ሰራዊታችንን ስለሃገሩ ብሄራዊ ደህንነት የዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲና ስለ ብሄራዊ ጥቅም እንዲያዉቅ የሚያግዝ  አንድ እንኳን የህትመት ዉጤት አለዉ? ዘጠና ሚሊዮን ህዝብን የሚወክልና በቢሊዮኖች የሚገመት ዓመታዊ ባጄት ያለዉ ግዙፍ የመከላከያ ተቋም ከስምንት ገጽ የማትበልጥ “ወጋገን” ከምትባል አነስተኛ ጋዜጣ ዉጭ በመከላከያ የሚዘጋጅ ሌላ ወታደራዊ መጽሄት አለዉ እንዴ?

ከኢትዮጵያ ጦር ኃይል ዉጭ በመከላከያ አባላት ብቻ ሳይሆን በሲቪሉ ህብረተሰብም የሚነበብ ወታደራዊ መጽሄት የሌለዉ ሌላ አገር አለ እንዴ? እኔ አስከማዉቀዉ ድረስ የለም፡፡ እንዴት አድርገን ነዉ ሰራዊቱን ነገ ለሚጠብቀዉ ለህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱ የምናዘጋጀዉ? ለመሆኑ በተጠቀሰችዉ “ወጋገን“ ጋዜጣም ሆነ በመከላከያ ሬዲዮና ቴሌቭዥኝ ፕሮግራሞች የሚቀርቡ ዝግጅቶችን ሌላዉ ህዝብ ይቅርና ራሳቸዉ ኃላፊነት ያለባቸዉ የመከላከያ ባለስልጣናት እንኳን በቅጡ ይከታተሉታል እንዴ?

መከላከያ ኃይላችንን ማዘጋጀት፤ ማስተማርና መገንባት ያለብን ነገና ከነገ ወዲያ ግብጽን ከመሳሰሉ ግዙፍና ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ካላቸዉ ስትራቴጂያዊ ጠላቶች ጋር ለሚጠብቀን ፈታኝ ጦርነት እንጂ ለትናንንሽ ተልእኮዎችና ከሽፍታ ጋር ለሚደረግ ገጭት ሊሆን እንደማይገባዉ ግልጽ ነዉ፡፡ ግን በዚያ መልኩ እየተሰራ አይመስለኝም፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላትን  ወቅቱ ከሚጠይቀዉ ልዩ ሁኔታ ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ማድረግ የምንችለዉ በትጥቅ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ ደረጃም እያዘመንና ከሌሎች ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ያለፉ ታሪኮች ልምድ ለመቅሰም ስንችል ነዉ፡፡ ለዚህም ሲባል ራሳችንን ለመፈተሸና የዉስጥ ገበናችን ለመመርመር ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ገና የተዘጋጀን አይመስለኝም፡፡ ከራሳችን የኋላ ታሪክ ለመማር ፍላጎት ቢኖረን ኖሮ ስንት ጀግና የወደቀበትን ጦርነት ችላ ባላልን ነበር፡፡

5/ ያለፉ ጦርነቶችን ገምግሞ ድክመትን በጸጋ ተቀብሎ ለወደፊቱ ትምህርት በመዉሰድ ረገድ አሜሪካ መማር የሚገባን ተሞክሮ

ታላቋ አሜሪካ ከቬትናም ጋር ሲታደርግ የቆየችዉንና በርካታ ወታደሮቿ አልቀዉባት በአሜሪካ ተሸናፊነት ስለተጠናቀቀዉ ጦርነት ያለምንም መደባበቅ ቁጭ ብለዉ ገምግመዉ፤ በርካታ መጽሀፍትን ጽፈዉበት፤ ፊልም ተቀርጾበት፤ ብዙ ነገር ተምረዉበት ለወታደራዊ ኮሌጆችና ዩንቨርስቲዎች ሳይቀሩ ሰፊ ምርምር ሲያደርጉበት ቆይተዋል፡፡ ከአርባ ዓመታት በኋላም፡ስለዚያ ጦርነት ሲተርኩ ልክ ዛሬ የተደረገ ያህል በጥልቅ ስሜት ተዉጠዉ ያለ አንዳች መሸማቀቅ ነዉ፡፡

አሜሪካኖች የቬትናምን ጦርነት እንደ ትልቅ ማስተማሪያ ነዉ የሚጠቀሙት፡፡ የአሜሪካ ጦር ኃይል ዛሬ ለደረሰበት ብቃት የቬትናምን ጦርነት እንደ ባለዉለታ ነዉ የሚቆጥሩት፡፡ ሌላ ጊዜ ሊያገኙ የማይችሉትን ትምህርት ነዉ የሰጣቸዉ፡፡

የአሜሪካ መንግስት ከቬትናም ጦርነት በኋላ በብሄራዊ ደህንነት ፖሊሲ፤በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች፤ በወታደራዊ አስተሳሰብና በጦር ኃይሉ አደረጃጀትና ቁመናና በሌሎች በርካታ ፖሊሲዎች ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ተገዷል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በወታደራዊ ኃይል አጠቃቀም ረገድ የህግ አዉጭዉንና የፕሬዝዳንቱን ስልጣን በሚመለከት የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ አስከማድረግ ድረስ ትኩረት ሰጥተዉ ሰርተዋል፡፡

አሜሪካና ታላቋ ብሪታንያ አስር ወታደር ሲሞትባቸዉ ስህተቱ ሌላ ጊዜ እንዳይደገም መፍትሄ ፍለጋ ፍዳቸዉን ይበላሉ፡፡ እኛ ስልሳና ሰባ ሺህ ጀግና ለወደቀበት ጦርነት ብዙ ትኩረት እንሰጥም፡፡ ለማንኛዉም ይህን ሃሳብ ለማጠናከር እንዲረዳኝ አሜሪካ ከቬትናም ጦርነት ከወጣች በኋላ ያለ አንዳች መደባበቅ ድክመቶቻቸዉን አንድ በአንድ እየነቀሱ በመዉጣት በርካታ ማስተካከያዎችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ በከፊል  የተወሰኑትን ቀጥዬ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

* የቬትናምን ሽንፈት ተከትሎ ህዝባቸዉ በሰራዊታቸዉ ላይ ከፍተኛ ንቀትና ጥላቻ አድሮበት ነበር፡፡ የአሜሪካንን ጥቅም ለማስጠበቅ የማይችል ሰራዊት ነዉ በሚል ወታደሮቻቸዉ ዓይንህን ለአፈር የተባሉበት ነበር፡፡ ለደረሰዉ ሽንፈት ጥፋቱ ያፖለቲካ አመራሩ ነዉ ወይንስ ጦር ኃይሉ ችግር ነዉ በሚል መልሱን ለማግነጥ ብዙ ደክመዋል፡፡

* የሀገሪቱ ፕሬዝዳነት ያለ ኮንግረሱ ፈቃድ ጦር ኃይሉን ከሀገር ዉጭ ለጦርነት መላክ የሚከለክልና ፕሬዝዳንቱ በጠቅላይ አዛዥነታቸዉ ጦር ኃይሉን ወደ ጦርነት ለማስገባት ምን ምን ቅደም ተከተሎችን በቅደሚያ ማሟላት እንዳለባቸዉ የሚደነግግና የፕሬዝዳንቱ ስልጣን ላይ ተጨማሪ ገደብ የሚጥል (war powers resolution) የተባለ አዲስ ድንጋጌ በሪቻርድ ኒክሰን ዘመን .. በኖቬምበር ወር 1973 / እስከማዉጣት ደርሰዋል፡፡ እንደሚታወቀዉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ያለ ኮንግሬሱ እዉቅናና ፈቃድ በተደጋጋሚ ጦር ይላቸዉን ወደ ጦርነት በማስገባት ይታወቃሉ፡፡ ይህ ደንብ የወጣዉ የአሜሪካ ጦር ቬትናምን ለቆ እንዲወጣ ከተደረገ ከሁለት ወራት በኋላ ነዉ፡፡

* አሜሪካ ያለምንም በቂ ምክንያት ያን ሁሉ ርቀት ተጉዛ በሰዉ አገር ላይ የከፈተችዉ ጦርነት የሕዝብ ድጋፍ ያልነበረወና መንግስትንም የሕዝብ አመኔታ ያሳጣ ነበር፡፡ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ሊንደን ጆንሰንም በድጋሚ ለመመረጥ እንኳን ያልደፈሩበት ትልቅ ዉርደት ነበር የደረሰባቸዉ፡፡

* በዚያ ጦርነት ሽንፈት ሳቢያ በአሜሪካ ለረዥም ዘመናት ሲሰራበት የቆዉ የብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎት ከቬትናም ጦርነት በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋረጥ ነዉ የተደረገዉ፡፡ ዛሬ በአሜሪካ ዉስጥ የግዴታ አገልግሎት የሚባል አሰራር የለም፡፡

* በጦርነቱ ወቅት ሲከተሉት የነበረዉ ወታደራዊ ዶክትሪን እጅግ የተዛባ መሆኑን ተረድተዉ ከጦርነቱ በኋላ በአዲስ ዶክትሪን እንዲቀየሩ አድርገዋል፡፡ መከላከያቸዉንም በአዲስ መልክ ለማዋቀር የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የጦር ኃይላቸዉ አወቃቀር፤ እዝና ቁጥጥሩ ሁሉ ዋጋ እንደለዉና በሌላ መስተካከል እንዳለበት የተረዱት የቬትናምን ጦርነት ከገመገሙ በኋላ ነዉ፡፡

* የቬትናም ጦርነት ትክክለኛና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፖለቲካዊ ዓላማ ሳይስቀምጡ በድፍረት የገቡበት ጦርነት ስለነበር ከፍተኛ የኃይል ብልጫ እያላቸዉም ጦርነቱን ማሸነፍ አልቻሉም፡፡

* የአሜሪካ ወታደሮች በጦርነቱ ወቅት የተከለከሉ የጅምላ ጨረሽ ጦር መሳሪያዎችን ሳይቀር ከመጠቀም አልፈዉ አንዳችም ትጥቅ ያልነበራቸዉን ሲቪል ህጻናትና በእድሜ የገፉ ሰዎችን ከቤት አውጥተዉ በጅምላ በመፍጨፍ የጦር ሜዳ ወንጀል የሰሩበትና በኋላ በሚዲያዎቻቸዉ ብርታት ሁኔታዉ ተጋልጦ ምንገስትም ትፋቱን አምኖ ለመቀበል የተገደበትና አጥፊዎችም የቀጡበት ሁኔታ ነበር፡፡

* በሲቪል ፖለቲከኞችና በወታደራዊ  ቃን መካከል የነበረዉ አለመግባበት ፤አለመደማመጥና በተለይም ፖለቲከኞች በጣም ዝርዝር የጦርነት አካሄድ ዉስጥ ሁሉ ያለአግባብ እየገቡ መበጥበጣቸዉና አላሰራ ማለታችዉ ለሽንፈቱ አንዱ መነሾ እንደነበር ተረድተዉ በሂደት እንዲስተካከል አድርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የነበረዉ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆንሰን ሳይቀሩ አጠቃለይ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ወይም ግብ ከማስቀመጥ ይልቅ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ዝርዝር ጉዳይ ዉስጥ በመግባት የትኛዉ ኮረብታ በአየር መደብደብ እንዳለበት ሁሉ ሳይቀር ዋሽንግተን (ኋይት ሃዉስ) ቁጭ ብለዉ መመሪያ ይሰጡ እንደነበር ተነግሮአል፡፡ በጦርነቱ ግንባር የተሰለፉ አዛዦች እያሉ በብዙ ሺህ ማይል ርቀት ላይ ሆነዉ መመሪያ ለመስጠት ያደረጉት ሙከራ ለሽንፈታቸዉ ዋናዉ ምክንያት እንደነበረ ይጠቀሳል፡፡

* የቬትናም ጦርነት ምክንያት በወቅቱ ሁለቱ ተፎካካሪ ኃይሎች የነበሩት አሜሪካና ሶቭየት ህብረት አዳዲስ የዉጊያ ጥበቦችንና የጦር መሳሪያዎችን ለመፈብረክና በተግባር ለመፈተሽ እድል ፈጥሮላቸዉ ነበር፡፡  

* በቬትናም ህዝብ ላይ የተጣለዉ ቦንብ ብዛት በሰዉ ልጅ የጦርነት ታሪክ ዉስጥ የዚያን ያህል ብዛት ያለዉ ቦንብ ተጥሎ አይታወቅም፡፡ በቬትና ላይ ብቻ የተጣለዉ የቦንብ ብዛት  በሁለተኛዉ የአለም  ጦርነት ባጠቃላይ በጥቅም ላይ ከዋለዉ ቦንብ ብዛት በእጅጉ የበለጠ ነበር፡፡ ለብዙ ቀናት ያለማቋረጥ በየቀኑ 1500 sorties በላይ (የዓይሮፕላን ምልልስ) እየተደረገ ነበር ሲቀጠቀጡ የነበሩት፡፡ ይሁን እንጂ የቬትናም ህዝብ ሁሉ ግፍ እየተፈጸመበት እስከመጨረሻዉ በቆራጥነት ተቋቁሞ አሜሪካ በሽንፈት ለቃ እንድትወጣ በማድረግ ባሳየዉ ጅግንነትና በመጨረሻም ሁለቱን ቬትናሞች ለማዋሃድ መቻላቸዉ ለዚህ ሁሉ ያበቃቸዉ ጥንካሬ ከምን የመነጨ እንደሆነ ለመረዳት ከጦርነቱ በኋላ ራሳቸዉ አሜሪካኖች ቬትናም ድረስ በመመላለስ ጥናት በማድረግ ምስጢሩ ላይ ለመድረስ ብዙ መድከም ነበረባቸዉ፡፡

* የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች፡ ፖለቲከኞች፤ ታሪክ ፊዎች፤ ሲቪልና ወታደራዊ የትምህርትና  የምርምር ተቋማት የሚዲያ ሰዎች ወዘተ ሁሉ ባደረጉት ያላሰለሰ የጋራ ጥረት ዛሬ የአሜሪካ ጦር ኃይል ለደረሰበት የማይበገር ቁመና ያበቃ የቬትናምን ጦርነት ሳይደባብቁ በግልጽ መገምገማቸዉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አሜሪካኖች ከዚያ ተምረዉ ከእያንዳንዱ ጦርነትና ዉጊያ በኋላ መገምገምና ምርምርና ጥናት ማድረግን እንደልማድ ይዘዋል፡፡ በቬትናም ጦርነት ጦስ ክብሩን ተገፎና ህዝባዊ ቅር ርቆት የቆየዉ የአሜሪካ ጦር ኃይል ዛሬ በአሜሪካ ህዝብ ዘንድ ከማንኛዉም በሀገሪቱ ዉስጥ ካሉት ተቋማት በበለጠ ከፍተኛ ከበረታ፤ተአማኒነትና ተቀባይነት ያለዉ ጦር ኃይሉ ለመሆን የበቃዉ  ራሱን ገምግሞ  በማረም ከቬትናም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ በገልፍ ጦርነት (ኢራቅ) የተሳካ ግዳጅ  ለመፈጸም በመብቃቱ እንደገና የተገፈፈዉን ክብርና ሞገሱን ሊያስመልስ በመቻሉ ነዉ፡፡

6/ ማጠቃለያ

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት በሚመለከት ትኩረት ተሰጥቶት አለመገምገሙና በሚዲያም ሆነ በሌሎች መድረኮች  ትኩረት መነፈጉ ጦርነቱ በታረክ የሚኖረዉን ትልቅ ስፍራ የሚያስቀር አይሆንም፡፡ ትላንት ቁጥር አንድ ወዳጅ የነበረችዉ ኤርትራ ጋር ጦር የተማዘዝንበት ምክንያት ምን እንደነበር፤ ለምንስ የኤርትራ ወረራ ድንገተኛና ያለተጠበቀ እንደሆነ፤ ለምንስ መንግስታችን ማንኛዉም መንግስት እንደሚያደርገዉ ተገቢዉን ጥንቃቄ እንዳላደረገ ፤ከጦርነቱ አወጣጣችን አወዛጋቢ የሆነበት ምክንያት በከፈልነዉ መስዋእትንት የሚመጣጠን ነገር ይዘን አልወጣንም የሚለዉ ጥያቄ ሊመረመርና ሊገመገም የሚገባዉ ነበር፡፡

ኤርትራን በሚመለከት ሌላ ፖሊሲ ያስፈልገናል ሲባል በቅድሚያ ከዚህ ቀደም ስለተፈጠረዉ ሁኔታ የማያዉቅና እንደ አዲስ የሚጠይቅ አዲስ ትዉልድ እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡ የኤርትራ ጉዳይ በኢህአዴግ የስልጣን ቆይታ ግዜ ዉስጥ የማይፈታ ለወደፊቱም የሚቀጥል ሊሆን ይችላል፡፡

ከመቶ ዓመት በፊት ኤርትራን በሚመለከት ምንሊክ ፈጸሙ ስለተባለዉ ስህተት ዛሬ ሂሳብ እንድናወራርድበት የተገደድንበትን ያህል ወደፊት ከኢህአዴግ በኋላ ለሚተካዉ መንግስት ዉዥንብር እንዳይፈጠርና የታሪክ ተጠያቂነትም እንዳይኖር በግልጽ የተብራራና ጥርት ያለ ነገር ማስረከብ ይገባናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደድንም ጠላንም የኤርትራን ጦርነት በሚመለከት በሚገባ መገምገምና ለታሪክ ማስቀመጥ ይኖርብናል፡፡

መንግስትን እየመራ ያለዉ ኢህአዴግ በትግሉ ወቅት “ደርግን የሚያህል ግዙፍ ሰራዊት ያሸነፍኩበት ዋንኛ ምስጢር…..” እያለ ሲነግረን የነበረዉ ከአያንዳንዷ ዉጊያ በኋላ ቁጭ ቢለዉ መገማገማቸዉን ነበር፡፡ እኛም በኢህአዴግ ጉብዝና ተደንቀን እንደ ኢህአዴግ ለመሆን ስንፍጨረጨር እንዳልነበርን ዛሬ ያን የመሰለ ለግምገማ አመቺ የሆነ ጦርነት ለመገመግም ችላ ማለቱ ግራ ቢያጋባን አይፈረድብንም፡፡

ጦርነቱ እንደሆን ባስከፈለን መስዋእትነት መጠን ከየትኛዉም ጦርነት የሚያንስ አይደለም፡፡ በዚህ ጦርነት ሳቢያ የደረሰብንን ሌላ ሌላዉን ኪሳራ ትተን የህይወት መስዋእትነት በመክፈል ደረጃ ብቻ ካየነዉ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ መዉደቃቸዉ ትንሽ ነዉ የሚባል አይደለም፡፡

ጦርነቱ አሳዛኝነቱ እንዳለ ሀኖ ለአንዳንዶች በረከት ይዞ የመጣ ነበር የሚመስለዉ፡፡ ምስጋና ለዚህ ጦርነት ይሁንና ባንድ ግዜ ለጄነራልነት ማእረግ የበቁ አሉ፡፡ እድሉን ያገኙትና  አጋጣሚዉን በሚገባ የተጠቀሙበት ጥቂቶች ደግሞ ጦርነቱ ሲያበቃ ባንድ ግዜ ወደ ሚለዮነርነት የተቀየሩም አይጠፉም፡፡ ከዚህም ሌላ ማእረግና ችሎታቸዉ አልጣጣም ብሎባቸዉ በጦርነቱ ላይ ከፍተኛ ዉድቀት በማስከተላቸዉና ሰራዊታቸዉን ያለአግባብ በማስጨረሳቸዉ ማእረጋቸዉ የተገፈፈ ለእስርም የተዳረጉና የተባረሩ አመራሮችም አሉ፡፡

በጦርነቱ ለዓመታት በረሃ አብረዉ ሲታገሉ ቆይተዉ ድርጅቱን ለስልጣን ያበቁ  ቁልፍ አመራሮች ከድርጅቱ ለመባረር  ያበቃቸዉ መዘዘኛ  ጦርነትም ነዉ፡፡  በሀገሪቱ ወታደራዊ እርከን ከፍተኛዉ የሆነዉን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ደረጃ የነበሩትና ሌሎችም እዉቅ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ያለ ፍላጎታቸዉ ከሰራዊቱ እንዲወገዱ ያደረገ ጠንቀኛ ጦርነት ነዉ፡፡

በገዥዉ ፓርቲ ዉስጥ በተፈጠረዉ መከፋፈል ፓርቲዉን አደክሞና የህዝብ አመኔታን አሳጥቶት ለነቅንጀትና ለእነ ኢዴፓ መጫወቻ ለመሆን የዳረገ ጦርነት ነዉ፡፡ ታዲያ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ሁኔታ የዳረገንን ጦርነት ሳንነጋገርበት፤ ሳንገመግመዉ፤ በሚዲያ ሰፊ ዘገባ ሳይሰራበት እንደተራ ክስተት ተድበስብሶ ሲቀር እንዴት አያስከፋም? ያስከፋል እንጂ! መንግስትና መከላከያ ስለዚያ ጦርነት  መገምገምም ሆነ መዉራት ባያስፈልጋቸዉ እንኳን ቢያንስ በዚያ ጦርነት ለወደቁት ጀግኖች ክብር ሲባል የግድ ማድረግ ነበረባቸዉ፡፡ ከዚህ በኋላ ይሄ ተግባራዊ ሆኖ እንደማየዉ  እተማመናለሁ፡፡

*********************

(የዚህን ፅሁፍ ቀጣይ ክፍሎች በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡     

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories