የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 3 | የኤርትራ ወረራ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ነዉ መባሉ አግባብ ነበር?

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ እና ሁለተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ ማግኘት ይችላሉ)

Highlights

* ‹‹ …ሻዕቢያ ከጦርነቱ አስቀድሞ ቀደም አድርጎ ሲያደርግ ከነበረዉ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅትና የሻዕቢያ አመራሮች ከበፊት ጀምሮ የሚታወቅ  የጠብጫሪነት ባህሪይ በመነሳት ትንሽ እንኳን አለመጠራጠር ትልቅ ስህተት ነዉ የሚል አቋም ያላቸዉም አሉ፡፡ ....ህዝቡ ስለጦርነቱ ሲሰማ መገረሙና መደናገጡ ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይልቁንም የመከላከያና የደህንነቱ አካላትና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝቡ ተሸለዉ መገኘት ሲገባቸዉ ህዝቡ ግራ ሲጋባ አብረዉ ግራ መጋባታቸዉ በፍጹም የማይጠበቅና መሆን የሌለበትም ነዉ፡፡››

* ‹‹መንግስታችን “የኤርትራ ወረራ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነበር” ሲል ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም “ከኤርትራም ሆነ ከሌላ ከዬትኛዉም ወገን ሊሰነዘርብን ለሚችል ጦርነት አስበንበትም ተዘጋጅተንበትም አናዉቅም፡፡ እንዲያዉም ለጦርነት ተብሎ የተዘጋጀ ሰራዊትም አልነበረንም” የሚል ሳይሆን ከኤርትራ ጋር ጦር ሊያማዝዝ የሚችል አንዳችም ዓይነት ቅራኔ፤ አለመግባባትና የጠላትነት ስሜት ስላልነበረ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል ብሎ ለማሰብ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት የለም የሚል ነዉ፡፡››

* ‹‹ከጦርነቱ በፊት በርከት ያለ የዉጭ ምንዛሪ አዉጥተን አዳዲስ መድፎች፤ አይሮፕላኖች፤ታንኮች፤ ሚሳይሎች ወዘተ አልገዛንም ይሆናል፡፡ …..ነገር ግን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማይጎዳና የአካባቢያችን የወደፊቱን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአንጻራዊነት አነስ ያለ ግን ደግሞ ብቃት የለዉ መከላከያ ተቋም ለመመስረት ጥረቶች እየተደረጉ እንደነበሩ መካድ አይቻልም፡፡››

* ‹‹ከጦርነቱ በፊት በነበረችዉ አጭር የሰላም ጊዜ ዉስጥ ሲሰሩ የነበሩ  የልማት እንቅስቃሴዎች ጦርነቱን ለመቋቋም ትልቅ እገዛ አድርጎልናል፡፡ ሻዕቢያ ለሰባት ዓመታት በድብቅ ሲዘጋጅ ለቆየበት ጦርነት እኛ በአጭር ጊዜ ዝግጅት በልጠን የተገኘንበት አንዱ ምስጢር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከኤርትራ ሲነጻጸር የተሻለ እንዲሆን ማድረግ በመቻላችን ነዉ፡፡ ….ጦርነቱ በልማት ጥረታችን ላይ ትልቅ እንቅፋት መሆን መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡ ለጦርነቱ ሲባልም በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የዉጭ ምንዛሪ ማዉጣታችንና የሀገራችን የመከላከያ ባጄት ከጂ.ዲ.ፒ. (GDP) 11 % በላይ መድረሱ ጦርነቱ ለልማታችን ምን ያህል እንቅፋት እንደነበር ያሳያል፡፡››

* ‹‹ በዘመናዊ ዉጊያ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ዝግጅት ያለማድረጉ ችግር ለምድር ኃይሉ ብቻ ሳይሆን በአየር ኃይላችንም ላይ የታዬ ትልቅ ጉድለት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጠላት አየር ኃይል ጋር ወደ ጦርነት የገባበት አጋጣሚ በታሪኩ ዉስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ይመስኛል፡፡ አንደኛዉ የዛሬ 40 ዓመት በፊት ማለትም በ1969 ዓ/ም ከሶማሊያ ወራር ጦር ጋር በተለይ ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር የተደረገዉ ጦርነት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ አሁን አያወሳን ባለነዉ ጦርነት ማለትም ከኤርትራ አየር ኃይል ጋር ነዉ፡፡››

* ‹‹ የኤርትራ ጦርነት እንደተጀመረ የዘመናዊ ትጥቅ ባለቤት ለነበረዉና ከተመሰረተ በርካታ አመታትን ላስቆጠረዉ አየር ኃይል ግን የራሱ ዶክትሪን ሰነድ ፈልጎ ማግኘትም አልተቻለም ነበር፡፡ አየር ኃይሉን ለጦርነት በማዘጋጀት ላይ ለነበሩት የወቅቱ አዛዥ ለጄ/ል አበበ (ጆቤ) ሁኔታዉ ቢያስገርማቸዉም የአሜሪካን ዶክትሪን ከኢንተርኔትና ከሌሎች መረጃዎች እያፈላለጉና መሰረታዊ በሆነዉ የአየር ኃይል ዶክትሪን (basic air doctrine) ላይ ይበልጥ ትኩረት በማድረግ በማስተርጎምና ከኛ ሁኔታ ጋር እያዛመዱ የሚመለከታቸዉ አመራሮች እንዲወያዩበት ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡››

* ‹‹ በተለያዩ ጊዜያት ሲደረጉ ከነበሩ አካባባዊ የሥጋት ትንታኔ ጥናቶች ኤርትራ እንደ ጠላት ቀርቶ በአጠራጣሪ ወዳጅ ደረጃ እንኳን አንድም ጊዜ አለመመደቧ የሚታወቅ ነዉ፡፡ እኔ ራሴ እንደማስታዉሰዉ ከጦርነቱ አንደ አመት ቀደም ብሎ የሀገራችንን የወደፊቱን አየር መከላከያ ሲስተም ለመዘርጋት መነሻ ጥናት እንዳቀርብ ታዝዤ በሰራሁበት ወቅት በካርታ ንድፍ ላይ የኤርትራን ኤር ቤዝ ምልክት የጠላት መለያ በሆነዉ በሰማያዊ ቀለም በማድረጌ የቅርብ አለቃዬ የነበረዉ ክፉኛ ተቆጥቶኝ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ አለቃዬ ራሱ ኤርትራን “ወዳጅ” ለማለትም ቸግሮት እንደነበረም ትዝ ይለኛል፡፡››  

* ‹‹ ከጦርነቱ በፊት በኤርትራና በኢትዮዮጵያ መንግስታት መካከል በብዙ ጉዳዮች የመተባበርና የወዳጅነት መንፈስ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ትንሽ በተለየና ጠንከር ባለ መንገድ ከኤርትራ ጋር ወዳጅነት መመስረቷ የሚጠበቅና ተገቢም ነበር፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወቅቱ አስገድዶአቸዉ ቢለያዩም አንድ አገር የነበሩ በመሆናቸዉ ከኬንያና ከሱዳን የበለጠ ወዳጅነት በመመስረቱ መንግስትን የሚያወቅስ አይደለም፡፡››

* ‹‹ የሻዕቢያ  መሪዎች እንደ እስራኤል ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል በመገንባት የሪጀኑ (የአካባቢዉ) ወሳኝ ሃይል ለመሆንና በኢኮኖሚ ደግሞ የምስራቅ ኤሽያዋን ሲንጋፖር ለማድረግ ማለማቸዉ የሚያስወቅሳቸዉ አይደለም፡፡ ….. ችግሩ ግን ይህን ህልማቸዉን እዉን  ለማድረግ ያሰቡበት መንገድ በኛ ኪሳራ መሆኑ ነዉ፡፡››

* ‹‹ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ሙሉ ድጋፍ ከማሳየት ዉጭ አንድም ጊዜ የኤርትራን ህዝብ ጥቅም የሚጎዳ ነግር አድርገዉ አያዉቁም፡፡ ይሁን እንጂ የኢህአዴግ ነባሮቹ ታጋዮች ለኤርትራ ገዢ ፓርቲ ለሻዕቢያ አመራሮች የነበራቸዉ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየና በጥላቻ የተሞላ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ሻዕቢያ ገና ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ አመለካከት የሚባል ነገር ያልነበረዉ ሰብአዊነትና ለህዝብ ከበረታ ያልነበረዉ አምባገነን ድርጅት እንደነበርና አሁንም መንግስት ከሆነም በኋላ ይህንኑ ባህሪይዉን ሳይቀይር በመቆየቱ የኤርትራን ህዝብ ለባሰ ጭቆና መዳረጉን በማዉሳት ለሻእቢያ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸዉ ለሚቀርቧቸዉ ሲገልጹ በቁጭትና በሃዘን ነበር፡፡ ››

* ኤርትራ ከኛ ስታገኝ የነበረዉና በኋላ የተቋረጠባት የገዛ ንብረቷ ስለነበረና ያንን ማግኘት ህጋዊ መብቷ ስለነበረም አይደለም፡፡ በፊት እንደዋዛ ያስለመድናትን ጥቅም በድንገት ስናቋርጥባት አንድም ሌላ አማራጭ ያልነበረዉ የኤርትራ አገዛዝ ከጦርነት የተሻለ ነገር ይኖራል ብሎ ስለማያስብ በኛ ላይ ጦርነት ቢከፍት ለምን ያስገርመናል? በእኛ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ህጋዊም ተገቢም እንዳልነበረ እንኳን እኛ ወረራ የፈጸመብን ሻዕቢያም ቢሆን ይሄን  አይረዳም ማለት አይቻልም፡፡ ችግሩ ያለዉ እኛ ዘንድ ነዉ፡፡ ይሄ እንደሚደርስ አስበን አለመጠርጠራችንና በቂ ዝግጅት በቅድሚያ አለማድረጋችን የኛ ድክመት ነዉ፡፡

* ‹‹በሽግግሩ ወቅት አየር ኃይላችን እንደገና በማቋቋም ስራ እንዲያግዙ በጊዜያዊነት በመንግስት ተመድበዉ የነበሩት ብርጋዲር ጄነራል ሰለሞን በየነ  ኤርትራም በበኩሏ አየር ኃይል ለማቋቋም ስታደርግ በነበረዉ ጥረት ኢትዮጵያ ማገዝ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ለመመካከር አስመራ ድረስ በመሄድ ከባለስልጣናቱ ጋር ሲመካከሩ ዓይን አዉጣዎቹ  የኤርትራ መከላከያ ባለስልጣናት ለጄነራሉ አቅርበዉ የነበረዉ ሃሳብ እጅግ የሚገርም ነበር፡፡ ያቀረቡትም ጥያቄ ደብረዘይት ያለዉ የአየር ኃይል ማስልጠኛ ተቋም እንዳለ ተነቅሎ እዚህ አስመራ ላይ ተቋቁሞ ለሁለቱም አገሮች ስልጠና ከአስመራ ላይ ይስጥ የሚል ነበር፡፡ ››

1/ የኤርትራ ወረራ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ነዉ ስለመባሉ

የሻዕቢያ ወረራ ጉዳይ ሲነሳ እስከዛሬም ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳዉ “ወረራዉን ያልጠበቅነዉና ድንገተኛ ነዉ” መባሉ ሲሆን በርግጥ ድንገተኛ ሊባል ይችል ነበር ወይ በሚለዉ ላይ በሁለት ጎራ የተከፈለ አቋም እንዳለ መገመት አያዳግትም፡፡

በወቅቱ ከነበረዉ ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለዉ ባንድ በኩል በሁለቱ አገራት መካከል መልካም ግኑኝነት የነበረ በመሆኑና ኤርትራ ከዚህ ግኑኝነት የበለጠ ተጠቃሚ ስለነበረች ይህን መልካም አጋጣሚ በምንም ምክንያት የሚያበላሽ የጠብ አጫሪነት ድርጊት  አትፈጽምም ብሎ መንግስት ማሰቡ ተገቢ ነበር የሚለዉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሻዕቢያ ከጦርነቱ አስቀድሞ ቀደም አድርጎ ሲያደርግ ከነበረዉ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅትና የሻዕቢያ አመራሮች ከበፊት ጀምሮ የሚታወቅ  የጠብጫሪነት ባህሪይ በመነሳት ትንሽ እንኳን አለመጠራጠር ትልቅ ስህተት ነዉ የሚል አቋም ያላቸዉም አሉ፡፡

የኤርትራ መንግስት ከአካባቢዉ አገሮች ጋር ሁሉ እንድ በአንድ ሲላተም ላዬ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር አንድ ቀን ለኛም አይቀርም ብሎ መጠርጠር ይገባዋል፡፡ እንደ ሀገር እዉቅና ካገኘ በአምስት አመታት ዉስጥ ከሁሉም አጎራባች አገሮች ጋር ጦር የተማዘዘ እንደ ኤርትራ አይነት ሌላ አገር በአፍሪካ ምድር የለም፡፡

ምናልባት እንደ ሀገር ከታወቀችበት ከ1948 ጀምሮ  ከዚህም ከዚያም የምትላተም አገር ብትኖር አስራኤል ብቻ ነች፡፡ እሷስ የግድ ሆኖባት ነዉ፡፡ ኤርትራ ግን አንድም ዉጫዊ ስጋት ሳይኖርባት ራሷ ነች ጠብ የምትጭረዉ፡፡ ኤርትራ ጦር ለመስበቅ ምንም የተለየ ሰበብ አያስፈልጋትም፡፡ ባሻት ግዜ ጥቃት መሰንዘር ነዉ ስራዋ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸዉ ከነበረዉ ጠንካራ ወዳጅነትና መደጋገፍ እንዲሁም ሁለቱም አገሮች ህዝቦች በጦርነት የተሰላቹ ስለነበሩ ሙሉ ትኩረታቸዉን ወደ ልማት ያደርጋሉ ከሚል ግምት በግኑኝነታቸዉ መካከል የተከሰቱ አንዳንድ አለመግባባቶችንም በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ እንጂ ለጦርነት መነሾ ምክንያት ሊሆኑ ባልተገባቸዉ ነበር ብንልም ነገር ግን መንግስት ካለበት ኃላፊነት አንጻር ተገቢዉን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መዉሰድ ይገባዉ እንደነበር ግልጽ ነዉ፡፡

አስቀድመን መጠንቀቃችን አስቀድመን እንድንዘጋጅ ስለሚረዳን ሻዕቢያ ለጥቃት እንዳያስብ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ካልሆነና አይኑን ጨፍኖ ጦርነትን ከመረጠም ጦርነቱን አንስተኛ በሆነ ኪሳራ በአጭር ጊዜ ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡ በሻዕቢያ ሰራዊት ላይም ከአሁኑ የከፋ ጉዳት ማድረስ በተቻል ነበር ፡፡

1.1/ የሻዕቢያ ወረራ ለምን ድንገተኛና ያልተጠበቀ ሆነ? ወይም ተባለ?

ስለ ኤርትራ ወረራ ማድረግ በኢትዮጵያ መንግስት በይፋ መግለጫ እሰከተሰጠበት ድረስ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ግምት በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የነበረ አይመስለኝም፡፡ ባድመ እንደምክንያት በተሰኘዉ መጽሀፋቸዉ እዉቁ የመረጃ ሰዉ ኮ/ል ተወልደ ገ/ተንሳይ ስለወረራዉ ያልተጠበቀ መሆን “…….አስደንጋጭ፤ ያልተገመተ፤ ከማይገመት ኃይል ምንም ዝግጅት ባልተደረገበት ወቅት ወረራ ተካሂዷል፤ ድንበራችን ተጥሷል፤ ሉአላዊነታችን ተደፍሯል፡፡ ……ህዝባችን በታንክ ሰንሰለት እየተረገጠ ነዉ” በሚል የወቅቱን ሁኔታ በአጭሩ ገልጸዉታል፡፡

ኮ/ል ተወልደ እንኳን የጦርነት ዝግጅትን የሚያክል ግዙፍ ክስተት ቀርቶ ጥቃቅን ጉዳዮች እንኳን እንደማያመልጣቸዉ ለምናዉቅ ሰዎች ልክ እንደኛዉና እንደ ቀረዉ ተራዉ ዜጋ የኢሳይያስን ወረራ ከኛ ጋር እኩል መስማታቸዉ እጀግ አስገራሚ ነዉ፡፡ ስለ ኮ/ል ተወልደ መነሳቱ ካልቀረ በዚህ አጋጣሚም በሳቸዉ ላይ የተሰማኝን አንዳንድ ቅሬታዎች መጥቀስ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡

ብዙዎቻችን እንድምናወቀዉ ኮ/ል ተወልደ ገ/ትንሳይ እድሜ ልካቸዉን በመረጃ ላይ ሲሰሩ የቀዩና በመረጃ ሙያ እጅግ የተካኑና በታታሪነታቸዉም መልካም ስም የነበራቸዉ ናቸዉ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ስለጠላት ሲደርሱን የነበሩ እጅግ ጠቃሚ መረጃዎች ሁሉ የሳቸዉና የሳቸዉ ባልደረቦች ጥረት ዉጤት እንደሆነ አዉቃለሁ፡፡

ይሁን እንጂ ኮ/ል ተወልደ በጻፉት አስቀድሜ በጠቀስኩት መጽሀፍ እንዴ መረጃ ሙያተኝነታቸዉና በጦርነት ሰፊ ልምድ እንዳለዉ የጦር ሰዉና ኃላፊነትና ተጠያቂነትም እንደነበረዉ የመከላከያ አመራር ለኢትዮጵያ ህዝብ ማሳወቅ የሚገባቸዉን ብዙ ሃቆች ሆን ብለዉ አድበስብሰዉ አልፈዋል፡፡ ኮ/ል ተወልደ በመጽሀፋቸዉ ዉስጥ ያልነካኩዋቸዉና የግድ ማንሳት ከነበረባቸዉ በርካታ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡

* የሀገሪቱ መከላከያ ተቋም የመረጃ ሃላፊ ሆነዉ እያለ ሻዕቢያና የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደገሱለት የነበረዉን የጦርነት ዝግጅት እንደማንኛዉም ተራ ዜጋ “አላዉቅም ፤ አልሰማሁም” ማለታቸዉ አጅግ አስተዛዛቢ ነዉ፡፡

* ከወረራዉ ድንገተኛነት የተነሳ መንግስት ተገቢዉን ወታደራዊ ዝግጅት ሳያደርግ በመቆየቱ ምክንያት በኛ በኩል ለተከፈለዉ መጠነ ሰፊ መስዋእትነት፤ በህዝቡና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ለደረሰዉ መንኮታኮትና የህዝባችን ህይወት መመሰቃቀል በአጠቃላይ በጦርነቱ ሰስለደረሰብን  ዘርፈ ብዙ ኪሳራ  አንድም ነገር ትንፍሽ አለማለታቸዉ፤

* በጦርነቱ መካከል ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች በሽሽት ላይ የነበረዉን የሻእቢያ ሰራዊት አሳደን መደምሰስ ሲገባን በይቅርታ (በቸልታ) የታለፈበት ሁኔታ፤ አንደኛዉ አጋጣሚ በ1991 ዓመተምህረት በዘመቻ ጸሀይ ግባት ሁለተኛዉ ደግሞ በጦርነቱ የመጨረሻዉ ምእራፍ በ1992 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ አስካሁንም ብዙ ሰዎችን ሲያወዛግብ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ኮሎነሉ ከዉገና ነጻ የሆነ የራሳቸዉን የግል አመለካከት መነሻ ያደረገ ሙያዊ ትንቴና ሊሰጡበት ይገባ ነበር፡፡

እሳቸዉ ግን አስቀድሜን ጠንቅቄን የምናዉቀዉን ታሪክ ደግመዉ ሊነግሩን ከመሞከራቸዉ  ዉጪ በዉሳኔዉ ተገቢነት ላይ የሳቸዉን አቋም ሊነግሩን ይገባቸዉ ነበር፡፡ ግን በዚያ መንገድ አላደረጉትም፡፡ በደርግ ዘመን ስንት መስዋእትነት ተከፍሎ የተገኘን ድል በኮ/ል መንግስቱ ትዕዛዝ ሰራዊቱ ለሻእቢያ አስረክቦ ይዞታዉን ለቆ ወደ ኋላ እንዲመለስ ሲደረግ ከነበረዉ አሳዛኝ ክስተት የአሁኑ ሁኔታ በምን እንደሚለይ ኮ/ል ተወልደ ሊነግሩን ይገባ ነበር፡፡

* በጦረነቱ የተከፈለዉን ያን ሁሉ ኪሳራ ዋጋ በሚያሳጣ ደረጃ በፍርድ መድረክ የተነጠቅነዉን መብት አስመልክተዉ የሚሰማቸዉን አስተያየት መስጠት ይገባቸዉ ነበር፡፡

* በጦርነቱ ስለከፈልነዉ መስዋእትነተና ስለደረሰብን አጠቃላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ አንዳችም ነገር ሳይጠቅሱ በዝምት አልፈዋል፤፤በተጨማሪ ስለኤርትራ ሰራዊት አቅም እጅግ አንኳሰዉና ደካማ አድርገዉ በአንጻሩ የኛን ሰራዊት አንዳችም አንከን እንዳልነበረዉ አድርገዉ የገለጹበት መንገድ በፍጹም አሰተማሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለ ጦርነት ጠንቅቆ ከሚያዉቅና  ስለእኛ ሰራዊትም ሆነ ስለኤርትራ በቂ መረጃ ካለዉ እንደ ኮ/ል ተወልደ ካለ ሰዉ የምንጠብቀዉ ሚዛናዊ የሆነ ግምገማ ነዉ፡፡ እሳቸዉ ግን ራሳቸዉን እንደ ወታደር ሳይሆን እንደ ካድሬ አድርገዉ በመቁጠር ወደ አንድ ወገን ያደላ አስተያየት ነዉ የሰጡት፡፡ ለመንግስትም ሆነ ለመከላከያችን ይበልጥ ይጠቅም የነበረዉ ሚዛናዊ የሆነ የሙያ አስተያየት ቢሰጡ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደጠበቅነዉ ሊሆን ባለመቻሉ እጅግ ተከፍተናል ፡፡

* እጅግ ያዘንበትና እሳቸዉን የታዘብንበት አንዱ ጉዳይ የሀገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት አንዳንዴ የወያነ ሰራዊት በሌላ ግዜ ደግሞ የኢህአዴግ ሰራዊት እያሉ በተደጋጋሚ መግለጻቸዉ ነዉ፡፡ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት የአንድ ድርጅት ሰራዊት አድርጎ ደጋግሞ ደጋግሞ መግለጽ በአጋጣሚ ወይም በስህተት ሳይሆን እንደዚያ እንዲሆን በመፈለግ ሆን ተብሎ የተገለጸ ነዉ ያስመሰለዉ፡፡

በተረፈ ኮ/ል ተወልደ በጦርነቱ አነሳስ፤ ሂደትና ፍጻሜ ላይ የሰጧቸዉ ግሩም የሆኑ ትንታኔዎችና ያቀበሉን መረጃዎች በጦርነቱ ላይ ስለመከላከያ ሰራዊታችን አኩሪ ገድል እንዲናዉቅ በማድረጋቸዉ እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አስቀድሜ በጠቋቆምኳቸዉ እንከኖች ምክንያት የኮ/ል ተወልደን ጥረት አሳንሶ እንደማየት እንዳይቆጠርብኝ ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡  ይህን ጉዳይ እዚህ ላይ ላብቃና አስቀድሜ ወደ ጀመርኩት የጦርነቱ ድንገተኝነት ላምራ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ወረራዉ ፈጽሞ ያልጠበቀዉና ያልገመተዉ ስለነበር ስለወረራዉ ሲሰማ መደንገጡና ግራ መጋባቱ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ህዝቡ መንግስት ከኤርትራ ጋር የፈጠረዉ ያልተለመደና ያልተመጣጠነ ግኑኝነት ባያስደስተዉም ግኑኝነታቸዉ ተበላሽቶ ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ግምት በጭራሽ አልነበረዉም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ስለጦርነቱ ሲሰማ መገረሙና መደናገጡ ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ይልቁንም የመከላከያና የደህንነቱ አካላትና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝቡ ተሸለዉ መገኘት ሲገባቸዉ ህዝቡ ግራ ሲጋባ አብረዉ ግራ መጋባታቸዉ በፍጹም የማይጠበቅና መሆን የሌለበትም ነዉ፡፡ ምክንያቱም የዘወትር ስራቸዉና ሃላፊነታቸዉ ስለሆነ ነዉ፡፡ ይህ ሆኖ እያለ መንግስት “ወረራዉ ያልጠበኩትና ድንገተኛ ነዉ” እያለ በተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ጥያቄ የሚነሳዉም እዚህ ላይ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ወረራዉ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ነዉ ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነዉ? ለመሆኑ እንደዚያ ማለትስ ነበረበት እንዴ? ኢህአዴግ የሀገር ሉአላዊነትንና የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት መረዳት የነበረበት ገና ድሮ በግንቦት 20/1983 ዓ/ም አራት ኪሎ የምኒሊክ ቤተ-መንግስት የገባ ዕለት መሆን አልነበረበትም እንዴ? ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ለመግዛት ሲያስብ ሃላፊነቱን እንዴት ነበር የተረዳዉ?

ለዚህ ዓይነት ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት መከላከያ ኃይሉም ከኤርትራም ሆነ ከሌላ ከማንኛዉም ወገን ሊሰነዘር ለሚችል ጥቃትም ሆነ ትንኮሳ አስቀድሞ መዘጋጀት ሲገባዉ “አልተዘጋጀሁም፤ አልጠረጠርኩም” ማለትስ ምን አመጣዉ? መንግስት ድንገተኛ ነዉ ሲል “ኤርትራን ጨምሮ ከየትኛዉም ወገን ሊሰነዘር ለሚችል ትንኮሳም ሆነ ጥቃት አስቀድሜ አልተዘጋጀሁም ነበር“ እያለን ነዉ? ወይንም “በወቅቱ ሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የሚባል ተቋም ጭራሽ አልነበራትም ነበር“ ማለትስ ነዉ? አንድ መንግስት የዜጎቹን ደህንነትና የሀገሪቱን ሉአላዊነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ሃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አንጻር “ኤርትራ ትወረኛለች ብዬ አላስብኩም ነበር” ማለቱስ ተቀባይነቱ ምን ያህል ነዉ?

መንግስት ወረራ መኖሩን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ዝም ብሎ ወደ ዉጊያ ከመግባት ይልቅ “ያልጠበኩትና ድንገተኛ” እያለ ያን ያህል ተጨንቆ እየደጋገመ መናገሩ ፋይዳዉ ምንድነዉ? የሚለዉ ጥያቄ መልስ የሚሻ ነዉ፡፡ በዚህ ላይ የእኔን ግምት ባጭሩ ለማስቀመጥ ልሞክር፡፡

የመንግስት ይህንን ነገር አለቅጥ የመደጋገሙ ምክንያት ጠላት ወረራ ያደርጋል ብሎ አስቀድሞ ተገቢዉን ጥንቃቄና ዝግጅት ሳይደረግ ወደ ጦርነት በድንገት በመግባትና አስቀድሞ አዉቆና ተዘጋጅቶ ወደ ጦርነት በመግባት መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ስለሚረዳ ይመስለኛል፡፡

ጉዳዩ በጦርነቱ የማሸነፍ ወይም የመሸነፍ ነገር አይደለም፡፡ አስቀድመን ሳንዘጋጅ ድንገተኛ ወረራ ተደርጎብንም ልናሸንፍ እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ሳይዘጋጁ በድንገት ወደ ጦርነት ተገብቶ በሚመጣ ድልና በደንብ ተዘጋጅቶና ታስቦበት ወደ ጦርነት በመግባት በሚመጣ ድል መካከል ሰፊ ልዩነት ይኖራል፡፡ ከሁሉም በላይ ተጠቀሽ የሚሆነዉ ታስቦበት የተገባ ጦርነት ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራዉ አነስተኛ የመሆን አድሉ ከፍተኛ መሆኑ ነዉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ለአብነት እንዲሆኑን የሚከተሉትን ጥቂት ነጥቦችን  እንመልከት፡-

አንደኛ፡- የጠላትን ሁኔታና ፍላጎት አስቀድሞ መረዳት ከተቻለ ወደ ጦርነት መግቢያ እድሎችን ሁሉ ለመዝጋት ሰፊ እድል ይኖራል፡፡ ያለምንም የህይወትም ሆነ የማቴሪያል ኪሳራ በድርድር በመፍታት ጦርነትን ማስቀረትም ይቻላል፡፡ በተጨማሪ የጠላት የጦርነት ፍላጎትን ለማምከንና “ጦርነት ስለማያዋጣኝ ይቅርብኝ” እንዲል ዲተር (deter) የማድረግ ሌላ እድልም ይኖራል፡፡

ሁለተኛ:- አስቀድሞ ባልተገመተ ወቅትና በጠላትነት ካልተፈረጀ ወገን በድንገት የሚሰነዘርን ጥቃት መክቶ ወደ ድል ለመምጣት የሚከፈለዉ ኪሳራ እጅግ የበዛ ይሆናል፡፡ በመንግስት ቸልተኝነት ምክንያት ተገቢዉ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ለደረሰዉ ጉዳት ሁሉ ተጠያቂ ከመሆን አድንም፡፡

ሶስተኛ:- ጦርነቱ በኛ ፍላጎት የተከናወነ ባለመሆኑ የማታ የማታ ድል ማድረግ ብንችል እንኳን ከጦርነቱ ይዘን የምንወጣዉ ወይም እንደ ጦርነት ግብ የምናስቀምጠዉ በጣም በትንሹ ይሆናል፡፡

አራተኛ፡- አስቀድሞ ባልተዘጋጀንበት ጦርነት አነስተኛ ኃይል ያለዉ ጠላትም ቢሆን ስትራቴጂያዊ ድንገተኝነት ማትረፍ ስለሚያስችለዉ በጦርነቱ የማሸነፍ እድላችንን በጣም አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሀገሪቱን ሉአላዊነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ይሄን ሃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ በህዝብ ተጠያቂነት መኖሩ የግድ ነዉ፡፡ በዚህ ድርጊቱም መንግስት ሃላፊነት የማይሰማዉ መንግስት ተደርጎ ስለሚቆጠር የህዝብ አመኔታ ማጣት ሊያስከትል ይችላል፡፡

እንግዲህ በነዚህና በሌሎችም እዚህ ባልተጠቀሱ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል መንግስት ከጦርነቱ በፊት፤ በጦርነቱ መካከልም ሆነ ጦርነቱ ካበቃ ከብዙ ዓመታት በኋላም ይሄንኑ ነገር እየደጋገመ መግለጹ፡፡ ለማንኛዉም ይሄ የኔ ግምት ስለሆነ ወደ ጀመርነዉ ጉዳይ እናምራ፡፡

መንግስታችን “የኤርትራ ወረራ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነበር” ሲል ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም “ከኤርትራም ሆነ ከሌላ ከዬትኛዉም ወገን ሊሰነዘርብን ለሚችል ጦርነት አስበንበትም ተዘጋጅተንበትም አናዉቅም፡፡ እንዲያዉም ለጦርነት ተብሎ የተዘጋጀ ሰራዊትም አልነበረንም” የሚል ሳይሆን ከኤርትራ ጋር ጦር ሊያማዝዝ የሚችል አንዳችም ዓይነት ቅራኔ፤ አለመግባባትና የጠላትነት ስሜት ስላልነበረ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል ብሎ ለማሰብ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት የለም የሚል ነዉ፡፡

በርግጥ አንዳችም የረባ ምክንያት ከሌለ ከባዶ መሬት ተነስቶ ወዳጅን እንደጠላት ማዬት የሚደገፍም አይደለም፡፡ ጥያቄዉ ግን ከኤርትራ ጋር አንዳችም አለመግባባትና ቅራኔ ወይም ዉዝግብ አልነበረም ወይ? የሚለዉ ነዉ፡፡

1.2/ መንግስት የሻእቢያ ወረራ ድንገተኛ ነዉ ሲለን ለዬትኛዉም ጦርነት አልተዘጋጀሁም ነበርእያለን ይሆን እንዴ?

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርብ ጊዜ የሚታሰብ ጠላት ኖረ አልኖረ መከላከያ ሰራዊቱን በቋሚነት የማደራጀት፤ የማስታጠቅ፤ የማሰልጠን፤ በዘመናዊ የዉጊያ አስተሳሰብ የማነጽና የዝግጁነት ደረጃዉን የሚያሳድጉ አስፈላጊ እርምጃዎችን ሁሉ የመዉሰድ ሃላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነዉ፡፡

ከዚህ አኳያ ሲታይ በቅርብ ጊዜ የሚጠበቅ ምናልባታዊ ጠላት ወይም ስጋት ላይ ያተኮረ ባይሆንም ወደፊት ሀገሪቱ ሊገጥማት ከሚችል ስትራቴጂያዊ ስጋት አንጻር በሚገባ ታስቦበት በተጠናናና ዘለቀታዊ አቅም በሚፈጥር መልኩ የሠራዊት ግንባታ እየተሰራ እንደነበር በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡

ከጦርነቱ በፊት በርከት ያለ የዉጭ ምንዛሪ አዉጥተን አዳዲስ መድፎች፤ አይሮፕላኖች፤ታንኮች፤ ሚሳይሎች ወዘተ አልገዛንም ይሆናል፡፡ የሀገሪቱ አቅም መሸከም ከሚፈቅደዉና ሀገራችንም በተጨባጭ ከሚያስፈልጋት በላይ ግዙፍ ሰራዊት መልምለንና አስልጥነን አላስመረቅን ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማይጎዳና የአካባቢያችን የወደፊቱን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአንጻራዊነት አነስ ያለ ግን ደግሞ ብቃት የለዉ መከላከያ ተቋም ለመመስረት ጥረቶች እየተደረጉ እንደነበሩ መካድ አይቻልም፡፡

ምናልባት ጥረቱ በቂ አልነበረም ወይንም ደግሞ  አዝጋሚ ነበር ከተባለ በዚህ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱን ያለ መከላከያ ባዶዋን በማስቀረት ለአደጋ አጋልጧት ነበር የሚለዉ የአንዳንድ ወገኖች ትችት ግን ሚዛናዊነት የጎደለዉ ይመስለኛል፡፡

የአፌዲሪ መንግስት ደርግ ከወደቀ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን በሀገር ግንባታ ወይም በልማት ላይ ማድረጉ በሁላችንም ዘንድ የሚታወቅና ተገቢም ይመስለኛል፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ይጠብቅ የነበረዉ ሌላ ጦርነት፤ ሌላ ግጭት፡ ሌላ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ስላልነበረ የሀገሪቱን ሀብት ለግዙፍ ሰራዊት ግንባታ ማዋልን ህዝብ የሚፈልገዉ ጉዳይም አልነበረም፡፡ በመሆኑም መንግስት የጦርነትን አጀንዳ ዘግቶ ሙሉ ትኩረቱን በልማት ላይ ማድረጉ የህዝብንና የሀገሪቱን ፍላጎት የተከተለና ወቅታዊ የሆነ ተገቢ እርምጃ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

መንግስት የእኛን ብሄራዊ ጥቅም የሚነካ አስከሌለና እኛም የሌሎችን ጥቅም አስካልጎዳን ድረስ ያለ ምክንያት ከመሬት ተነስቶ ጦር የሚሰብቅ ሀገር ስለማይኖር የግድ የሚያስፈልገንን ያህል መከላከያ ኃይል እየገነባን ከድህነት ለመዉጣት መጣር አለብን እንጂ ኢኮኖሚዉን የሚበላ ለአካባቢዉ አገሮችም የስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችል አለቅጥ የገዘፈ ሰራዊት አያስፈልገኝም ማለቱ የሚያስመሰግንና ተገቢም ይመስለኛል፡፡

በዚህ መሰረትም ከጦርነቱ በፊት ለጠንካራ መከላከያ ሰራዊት ምስረታ መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ የአቅም ግንበታ ስራዎች ሲሰሩ ነበር፡፡ ጥራት ያላቸዉ የስልጠና ስራዎችና የማሰልጠኛ ተቋማትን የማደራጀት ስራ፤ የግድ አስፈላጊ የነበሩ ኢንፍራስትራክቸር ግንባታ ፕሮጀክቶች፤ ከዉጭ ተጽእኖ ሊያላቅቅ የሚችሉ በደርግ ጊዜ ተጀምረዉ የነበሩ የጦር መሳሪያ እድሳትና ማምረቻ ተቋማትና የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን በአዲስ መልክ የማደራጀት፤ የማጠናከርና በጥናት ላይ የተመሰረተ ማስተካከያ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነበር፡፡

የጥናት፤ የምርምርና ስርጸት ስራዎችም ከሞላ ጎደል ለመስራት ተሞክሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአንድ መከላከያ ሰራዊት ብቃት የሚለካዉ በብዛቱና በትጥቁ ዓይነት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በህዝባዊ አመለካከቱና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በእምነት ተቀብሎ እሰከመጨረሻዉ መስዋእትነት ለመክፈል ባለዉ ቁርጠኝነት ጭምርም በመሆኑ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሰፊ የግንባታ ስራዎች ሲሰሩ ነበር፡፡

በተለይም ለህዝብ ከበሬታ ያለዉ፤ ለህገ-መንግስቱ በቁርጠኝነት የሚቆምና ድስፕሊንድ የሆነ ሰራዊት ለመመመስረት መንግስት ብዙ ተንቀሳቅሷል፡፡ አብዛኛዉ የመከላከያ ሰራዊት አባል የቀድሞ የኢህአዴግ ታጋይ የነበረና የመደበኛ ሰራዊት ቁመናና አሰራር ተሞክሮ ያልነበረዉ መሆኑ ሲታሰብ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በአዲስ መልክ ለማደራጀት ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች አበረታች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

እነዚህን ስራዎች ከጦርነቱ በኋላ በተጠናከረ መልኩ የመቀጠል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ጥረቱ የተጀመረዉ ግን ከጦርነቱ  በፊት በተለይም ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በህገ-መንግስቱ መሰረት በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላ ደግሞ ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ሲሰራ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱን ያለ ጠባቂ አስቀርቶ፣ ሰራዊቱን በትኖ፣ ራሳችንን የመከላከል አቅማችንን አዳክሞና ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎን ወዘተ የሚባሉ ክሶችና ትችቶች በተጨባጭ እየተሰራ ከነበረዉ ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ ቢያንስ ሲሰራ የነበረዉን ስራዎች በቅርበት ለሚያዉቁ ሰዎች ይህንን ትችት ለመቀበል ያዳግታል፡፡

ከጦርነቱ በፊት እኮ ቢያንስ ከ50 እሰከ 60 ሺህ አካባቢ የሚሆን የሰራዊት ኃይል ነበረን፡፡ ይህ ኃይል በወቅቱ ሻዕቢያ ለጦርነት ካዘጋጀዉ ሩብ ሚሊዮን (250ሺህ) አካባቢ ከሚገመት ሰራዊት አንጻር ሲታይ በቂ እንዳልነበረ ግልጽ ነዉ፡፡ ጦርነቱን በድል ለመወጣት በዚህ ኃይል ብቻ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻልም ማንም ሊገነዘብ የሚችለዉ ሃቅ ነዉ፡፡ ነገር ግን ጦርነት በሌለበትና ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ዉስጥ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ደሃ አገር 60ሺህ ሰራዊት ትንሽ ነዉ የሚባል አይደለም፡፡

ለነገሩ የኤርትራን የመጀመሪያ ወረራ ጥቃት መክቶ በማቆም የሻዕቢያን የመስፋፋት ህልም ያጨናገፈዉ ይሄዉ ሰራዊት እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሻዕቢያ ለሰባት ዓመታት የተዘጋጀበትን ጦርነት በተለይ የሰኔ 3/1990 የሻዕቢያን ማጥቃት ሰራዊታችን ሶስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ በማክሸፍ ኢሳይያስን ተስፋ በማስቆረጥ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በመክፈታቸዉ አደገኛ ስህተት እንደፈጸሙ እንዲረዱ ያደረጋቸዉ ይሄዉ አነስተኛ ኃይል በጀግንነት የፈጸመዉ እንጂ በተአምር የሆነ አልነበረም፡፡

Photo - An Eritrean tank destroyed in a battle with Ethiopian troops around Barentu town on May 20, 2000 [Getty Images/AFP]
Photo – An Eritrean tank destroyed in a battle with Ethiopian troops around Barentu town on May 20, 2000 [Getty Images/AFP]

2/ ከኤርትራ በተሻለ ኢኮኖሚ ላይ መገኘታችን ለጦርነቱ ትልቅ እገዛ አድርጓል

ጦርነትን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ሁሉ ለሟሟላት የጠንካራ ኢኮኖሚ መኖር የግድ ነዉ፡፡ በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ መንግስት ገና ከጅምሩ በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆዬቱ የሚታወቅ ሲሆን ይህ የልማት ስራ በኋላ ተገደን የገባንበት ጦርነትን በአሸናፊነት እንድንወጣ ትልቅ እገዛ እንዳደረገልን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ከጦርነቱ በፊት በነበረችዉ አጭር የሰላም ጊዜ ዉስጥ ሲሰሩ የነበሩ  የልማት እንቅስቃሴዎች ጦርነቱን ለመቋቋም ትልቅ እገዛ አድርጎልናል፡፡ ሻዕቢያ ለሰባት ዓመታት በድብቅ ሲዘጋጅ ለቆየበት ጦርነት እኛ በአጭር ጊዜ ዝግጅት በልጠን የተገኘንበት አንዱ ምስጢር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከኤርትራ ሲነጻጸር የተሻለ እንዲሆን ማድረግ በመቻላችን ነዉ፡፡

ጦርነቱ የማይቀር መሆኑ ከታመነበት በኋላ ያን ሁሉ ሰራዊት መልምለን፤ አሰልጥነን ያዘጋጀነዉ፤ ለጦርነቱ የሚያስፈልገንን ታንክ፤ መድፍ ፤ መገናኛ መሳሪያዎች፤ ጄት አይሮፕላኖች፤ ራዳሮች፤ ሚሳይሎች ፤ተሸከርካሪዎችና ተተኳሾች ወዘተ ሁሉ እንዳሻን መሸመት የቻልነዉ ገና በሰላሙ ጊዜ ከኤርትራ የተሻለ የዉጭ ምንዛሪ ክምችት ማድረግ በመቻላችን ነዉ፡፡ እነሱ ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በጦርነቱ መካከል መግዛት ከቻሉት በጥራትም በብዛትም የተሻለ ትጥቅ ገዝተን መታጠቅ ችለናል፡፡

ከኤርትራ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም (ኢኮኖሚክ ፖቴንሻል) ባይኖረን ኖሮ ጦርነቱን ማሸነፍ መቻላችንን አጠራጣሪ ሊያደርገዉ  ይችል ነበር፡፡ ጦርነቱ በልማት ጥረታችን ላይ ትልቅ እንቅፋት መሆን መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡ ለጦርነቱ ሲባልም በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የዉጭ ምንዛሪ ማዉጣታችንና የሀገራችን የመከላከያ ባጄት ከጂ.ዲ.ፒ. (GDP) 11 % በላይ መድረሱ ጦርነቱ ለልማታችን ምን ያህል እንቅፋት እንደነበር ያሳያል፡፡

እንደዚያም ሆኖ በጦርነቱ መካከልም በተቻለ መጠን ልማቱን ለማፋጠን መንግስት ጥረት ማድረጉን ለአፍታም አላቋረጠም ነበር፡፡ ጦርነቱ በእኛ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ኢኮኖሚያችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ማንሰራራት የቻለበት ምክንያትም አስቀድመን ለልማት ስናደርግ የነበረዉ ትኩረት ዉጤት ይመስለኛል፡፡ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ባይጠናቀቅ ኖሮ ኢትዮጵያ ከኤርትራ በተሻለ  ሁኔታ ዘለግ ላለ ጊዜ በጦርነቱ ዉስጥ ለመቆዬት የሚያስችላት እድል ነበራት፡፡

በአንጻሩ ኤርትራ የነበራትን ዉስን የሆነ ጥሪትም ለጦርነቱ አዉላ ስለነበረና ጦርነቱ ካበቃ በኋላም መጀመሪያኑ ትኩረት አድርጋ ያልሰራችዉ ኢኮኖሚ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ጭራሽ ተንኮታክቶ ህዝባቸዉን ለዳቦ ሰልፍ ዳርገዉታል፡፡  አስከዛሬም ከዚህ ችግር ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡

በእኛ በኩል ከጦርነቱ በፊት በልማት መጠመዳችን በጦርነቱ ወቅት በጦርነቱ ቀጠና ከነበረዉ ዉጭ ያለዉ ህዝባችን በጦርነት ላይ ባለች አገር መከሰቱ የግድ የሆነዉን የከፋ የኑሮ መመሰቃቀል ችግር ብዙም ሳይገጥመንና ህዝባችንን ለስቃይ ሳይዳርግ ጦርነቱን ለማጠናቀቅ ችለናል፡፡

በጦርነቱ ወቅት ወደ መሃል አገርና ወደ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ወዘተ ተዘዋዉሮ የተመለከተ የዉጭ አገር ጎብኚ ሀገሪቱ ጦርነት ላይ የነበረች መሆኑን የሚያሳብቅ አንድም የጦርነት ዘመን ሁኔታዎችን ለማዬት ስለሚቸገር “በእዉነት ሀገሪቱ ጦርነት ላይ ነች?” ብሎ ቢጠራጠር በጭራሽ አይደንቅም፡፡ መንግስት እንደ ደርግ ዘመን መላዋን ኢትዮጵያን ወደ ጦር ካምፕነት ሳይቀይርና ብዙ ትርምስ ሳይፈጠር ጦርነቱን አካሂዶ ማጠናቀቅ መቻሉ የሚያስመሰግነዉ ነዉ፡፡

የወቅቱ የሀገራችን የመንግስት አመራሮች እጅግ አሰልቺና የተራዘመ ጦርነት (ለ17 ዓመታት የዘለቀዉ ፀረ -ደርግ ትግል) በኋላ ገና ሰላምን ማጣጣም የጀመሩበትና የታገሉለትን የልማት ጥያቄን እዉን ለማድረግ ከፍተኛ ጉጉት ስላደርባቸዉ ከልማት ዉጭ ያሉ ሌሎች ጉዳዮች ላይ በቂ ትኩረት እንዳያደርጉ ተጽእኖ ሳያደርግባቸዉ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል፡፡

በተለይ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ ሲገልጹ እንዳዳመጥነዉ “የግድ ካልሆነና ልማታችንና ሰላማችንን የሚያስቆም መሆኑን እርግጠኛ ሳንሆን የትኛዉም ዓይነት ጦርነት ዉስጥ ተቻኩለን አንገባም„ የሚለዉ ጠንካራ አቋማቸዉና “የኛ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነዉ“የሚለዉ ቋሚ መፈክራቸዉ ምን ያህል ለልማት ቅድሚያ እንደሰጡና ለጦርነት ያላቸዉን የመረረ ጥላቻ  የሚያመላክት ነዉ፡፡ እንግዲህ ምናልባት መንግስት በልማት አጀንዳ ተዉጦ አካባቢዉን በደንብ እንዳይፈትሽ ተጽእኖ አድርጎበት ይሆን እንዴ? ብለን ብንጠራጠር ተገቢ ይመስለኛል፡፡

3/ አጠቃላይ መዘናጋታችን እንዳለ ሆኖ ወደ ጦርነቱ  ስንገባ በርካታ የዝግጅት ጉድለት ነበረብን

ተገቢዉን ትኩረት ተሰጥቶት ያልተሰሩና በክፍተት ሊታዩ የሚችሉ አንዳንድ ጉድለቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ የሀገሪቱን መከላከያ ኃይል በስትራቴጂክ ደረጃ ለሚታሰብ ምናልባታዊ ጠላት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የአቅም ግንባታ ከመስራት ጎን ለጎን በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ሊነሳ ለሚችል ጠላት (ተለይቶ የሚታወቅ ጠላት ባይኖርም) ፈጣን መልስ ሰጪ የሆነ ኃይል ዝግጅት ማድረግ ይገባ ነበር የሚለዉ አንዱ ነዉ፡፡

እንደዚሁም የመከላከያ ሰራዊቱ በፊት ይዞትና ለምዶት ከቆዬዉ የጉሬላ የዉጊያ አስተሳሰብ አዉጥቶ በዘመናዊ ወታደራዊ ዶክትሪን የሚመራ አዲስ የዉጊያ አስተሳሰብ ያለዉ ሰራዊት የመገንባት ስራ በጥልቀት አለመሰራቱ ሌላዉ ተጠቃሽ ክፍተት ነዉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ኮ/ል ተወልደ ገ/ትንሳይ አስቀድሜ በጠቀስኩት “ባድመ እንደ ምክንያት” በሚል ርአስ ስለ ጦርነቱ ጽፈዉ ለንባብ ባበቁት መጽሀፍ ላይ ከወረራዉ በፊት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የነበረዉ አንዱ ትልቁ ችግር ይሄ እንደ ነበር አጽንኦት ሰጥተዉ ገልጸዋል፡፡

ኮ/ል ተወልዴ በማስረጃነት የጠቀሱት የአሁኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኤታማጆር ሹምና በወቅቱ የግንባሩ አዛዥ የነበሩትንና የሻቢያን እብሪት ወረራ በማክሸፍ ለሀገር ባለዉለታ የሆኑት ጄ/ል ሳሞራ የኑስ በአንድ ወቅት በጦርነቱ ቀጣይ አካሄድ ላይ የተናገሩትን ንግግር ነዉ፡፡

በወገንና በጠላት መካከል ከፍተኛ የኃይልና የአስተሳሰብ ልዩነት አለ፡፡ ጠላት ከመደበኛ ዉጊያ አስተሳሰብ ፍጹም አልተላቀቀም፡፡ ይህንን አስተሳሰብ በማጎልበት ላይ ነዉ የነበረዉ፡፡ በኛ በኩል ከመደበኛ ዉጊያ አስተሳሰብ ወጥተን በጉሬላ አስተሳሰብ ላይ ነዉ የቆዬነው፡፡  ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር ጊዜ ያስፈልገናል፡፡”  ብለዉ ነበር ፡፡  

በመቀጠልም የኛ መከላከያ ሰራዊት በሰዉ ኃይል ብዛት የተበለጠ መሆኑን የጠቀሱበት ንግግራቸዉ ላይ እንዲህ ብለዉ ነበር፡፡

አሁን ያለን የኃይል ልዩነትም እጅግ በጣም የተራራቀ ነዉ፡፡ ከቻልንም መከላከል ብቻ ነዉ የምንችለዉ፡፡ ስለሆነም አሁን ራሳችንን እየተከላከልን እንዘጋጅ እንጂ አሁን ወደ ዉጊያ እንግባ የሚለዉ አስተሳሰብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልነበር  ያሉት፡፡  

ይህ በዘመናዊ ዉጊያ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ዝግጅት ያለማድረጉ ችግር ለምድር ኃይሉ ብቻ ሳይሆን በአየር ኃይላችንም ላይ የታዬ ትልቅ ጉድለት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጠላት አየር ኃይል ጋር ወደ ጦርነት የገባበት አጋጣሚ በታሪኩ ዉስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ይመስኛል፡፡ አንደኛዉ የዛሬ 40 ዓመት በፊት ማለትም በ1969 ዓ/ም ከሶማሊያ ወራር ጦር ጋር በተለይ ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር የተደረገዉ ጦርነት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ አሁን አያወሳን ባለነዉ ጦርነት ማለትም ከኤርትራ አየር ኃይል ጋር ነዉ፡፡

አየር ኃይላችን ከ1969ኙ የሶማሊያ ጦርነት በኋላ ከመደበኛ አየር ኃይል ጋር ድጋሚ ለመፋለም የበቃዉ በዚህ የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ላይ ነዉ፡፡ ከዚያ በፊት በመካከሉ በነበሩት ሃያ አመታት ዉስጥ አየር ኃይሉ ሲያደርገዉ የነበረዉ መደበኛ ያልሆነ ዉጊያ ማለትም ፀረ- ጉሬላ ዉጊያ ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ሻዕቢያም ሆነ የህወኃት/ኢህአደግ ሰራዊት የጉሬላ ሰራዊት የነበሩና አይሮፕላን ለመታጠቅ እድል ያልነበራቸዉ በመሆናቸዉ አየር ኃይሉ የዉጊያ ባህሪይም ይህንኑ የተከተለ መሆኑ የግድ ነበር፡፡

አየር ኃይሉ ሙሉ ትኩረቱ በመሬት ላይ ባለዉ የጠላት ጦር ማጥቃት ላይ በማድረግ የአየር ለአየር (air to air) የሚባል ዉጊያ ስላልገጠመዉ አስተሳሰቡ ሁሉ ፀረ- ምድር ዉጊያ (counter land warfare) ብቻ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ወቅት አየር ኃይሉ ሲገጠመዉ የነበረዉ ከፍተኛ ተግዳሮት ቢኖር ምድር ላይ ከተተከሉ የጠላት ፀረ-አይሮፕላን መቃወሚያ መሳሪያዎች (anti aircraft) ሲደርስበት የነበረዉ ጫና ነዉ፡፡

የኢህአዴግና የሻዕቢያ ሰራዊት ከደርግ አይሮፕላን ጥቃት ራሳቸዉን ለመጠበቅ እንቅስቃሴያቸዉን በገደብ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆኑም በኋላ ግን የአየር መቃወሚያ መሳሪያዎችን በስፋት መታጠቅ በመቻላቸዉ የአየር ኃይሉን አይሮፕላኖች ጭራሽ አላስደርስ ያሉበትን ሁኔታን መፍጠር ችለዉ ነበር፡፡  በዚያ የርስበርስ ጦርነት ወቅት በሻዕቢያም ሆነ በኢህአደግ አየር መቃወሚያ መሳሪያዎች ተመትተዉ የወደቁ አየር ኃይል አይሮፕላኖች በርካታ ነበሩ፡፡

አየር ኃይላችን ሰፊ የጦርነት ተሞክሮ የነበረዉና በተለይ ከሶማሊያ ጋር ባደረግነዉ ጦርነት በጥቂት ቀናት ዉስጥ ብቻ ከደርዘን በላይ የሶማሊያን አይሮፕላኖች በአየር-ለአየር ዉጊያ  መትቶ በመጣል አስደናቂ ገድሎችን በመፈጸሙ በምእራቡም ሆነ በምስራቁ ዓለም አድናቆትን አትርፎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ስንት ጀግና ፓይለቶችን ያፈራና ስንት ጦርነቶች ላይ የተሳተፈ አየር ኃይል ለምን የራሱ ኤር ዶክትሪን (air doctrine) እንዳልኖረዉ በጭራሽ ለመረዳት አልቻልኩም፡፡

ከኤርትራ ጦርነት በፊት አየር ኃይሉ ከሶማሊያ ጦርነት በኋላ ባሉት ጊዜያት (ለሃያ ዓመታት) ከሌላ አየር ኃይል ጋር ጦርነት ገጥሞ ስለማያዉቅና የዉጊያ አስተሳሰቡ ሁሉ በአንድ የዉጊያ አቅጣጫ ላይ ብቻ እንዲወሰን በመደረጉ ከዘመናዊ የአየር ኃይል ዶክትሪን ጋር አለመተዋወቁም ሆነ ትኩረት አድርጎ አለመሰራቱ በዚያ ምክንያት ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡

የኤርትራ ጦርነት ሲጀመር ከአርሚዉ ባልተለየ ሁኔታ አየር ኃይሉም የዘመናዊ ዉጊያ አስተሳሰብ ደሃ መሆኑ አስገራሚ ነበር፡፡ አየር ኃይሉ ከተመሰረተ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረና በርካታ ልምድ ያካበተ፤ ስመጥር የሆኑ  ጀግና ፓይሌቶችና አዛዦች የነበሩት  ቢሆንም  ይሄ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል የዉጊያ ዶክትሪንና አሰተሳሰብ ሳይኖረዉ ቆይቷል፡፡

በወቅቱ አየር ኃይሉ በዘመናዊ የዉጊያ አስተሳሰብ ረገድ ከአርሚዉ ተሸሎ ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንዲያዉም የአርሚዉ አብዛኛዎቹ ተዋጊዎችና አመራሮች የቀድሞ ታጋዮቸች የነበሩ በትግሉ የመጨረሻዎቹ  አመታት ላይ መደበኛ ካልሆነ የዉጊያ (Unconventional Warfare) አስተሳሰብ ተላቀዉ ከመደበኛ ዉጊያ አስተሳሰብ ጋር ከሞላ ጎደል ትዉዉቅ የነበራቸዉ ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ የኢህአዴግ ታጋይ ሰራዊት ወደ መንግስት መከላከያ ሰራዊትነት ከተቀየረ በኋላ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ትቶት ነዉ እንጂ በትግሉ መጨረሻ አካባቢ ራሱን ወደ መደበኛ ሰራዊት እየቀየረ  እንደነበር ይታወቃል፡፡ በትግሉ መጨረሻ አካባቢ የኢህአዴግ ወታደራዊ ቁመና ምናልባት አይሮፕላን ስላነበረዉ ካልሆነ በስተቀር አቋሙ የአንድ አገር መንግስት ከሚኖረዉ የመከላከያ ተቋም የሚያንስ አልነበረም፡፡

የኤርትራ ጦርነት እንደተጀመረ የዘመናዊ ትጥቅ ባለቤት ለነበረዉና ከተመሰረተ በርካታ አመታትን ላስቆጠረዉ አየር ኃይል ግን የራሱ ዶክትሪን ሰነድ ፈልጎ ማግኘትም አልተቻለም ነበር፡፡ አየር ኃይሉን ለጦርነት በማዘጋጀት ላይ ለነበሩት የወቅቱ አዛዥ ለጄ/ል አበበ (ጆቤ) ሁኔታዉ ቢያስገርማቸዉም የአሜሪካን ዶክትሪን ከኢንተርኔትና ከሌሎች መረጃዎች እያፈላለጉና መሰረታዊ በሆነዉ የአየር ኃይል ዶክትሪን (basic air doctrine) ላይ ይበልጥ ትኩረት በማድረግ በማስተርጎምና ከኛ ሁኔታ ጋር እያዛመዱ የሚመለከታቸዉ አመራሮች እንዲወያዩበት ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡

እንግዲህ በወቅቱ ከነበረዉ የጊዜ እጥረትና ከጉዳዩ ዉስብስብነት አንጻር ሲታይ አስተሳሰቡ በሚገባ በተፈለገዉ ደረጃ ተጨብጦ ነበር ለማለት ቢያስቸግርም ጥረት መደረጉ ግን በመልካም ጎኑ መጠቀስ ያለበት ነዉ፡፡ ስለዶክትሪን ስለተነሳ እግረ መንገዴን እዚያ ላይ አተኮርኩ እንጂ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ስንገባ አየር ኃይሉ በርካታ እጥረቶች እንደነበሩበት ለማንም ያልተሰወረና ግልጽ ነዉ፡፡

ነገር ግን በጦርነቱ ሂደት ራሱን እያስተካካለ የተሻለ ብቃት ለመያዝ ቻለ እንጂ እንደ አጀማመሩና እንደነበረበት ሁኔታ ቢሆን ኖሮ በተለይም ከደካማና ልምድ ከሌለዉ የኤርትራ አየር ኃይል ጋር መሆኑ በጀዉ እንጂ ከጠንካራ  አየር ኃይል ጋር ሆኖ ቢሆን ኖሮ ብዙ ችግር ሊገጥመን ይችል ነበር፡፡ ለማንኛዉም ይሄን ጉዳይ ያነሳሁት ወደ ጦርነቱ ስንገባ በዝግጁነት ረገድ ጉድለት እንደነበረብን ለመጥቀስ ያህል እንጂ ስለ አየር ኃይል ሁኔታ በዝርዝር ለመተረክ አይደለም፡፡

4/ ስለ ኤርትራ የነበረን ግምገማ የተዛባ መሆኑና ኢሳይያስን ከሚገባዉ በላይ ማመናችን

ስለ ጦርነቱ ሲወሳ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የነበረዉ ኤርትራ ኢትዮጰያ ላይ ወረራ ለመፈጸም የበቃችዉ ስለኛ በነበራት የተሳሳተ ግምገማ ምክንያት ነዉ የሚል ነዉ፡፡ በርግጥም የኤርትራ መሪዎች የግምገማ ችግር እንደነበረባቸዉ እኛ ብቻ ሳንሆን ራሳቸዉም ዘግይተዉም ቢሆን ለመረዳት የቻሉ ይመስለኛል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኤርትራ ከሰራችዉ ያላነሰ ምናልባትም የከፋ የግምገማ ችግር የነበረብን እኛ ነን፡፡ እነሱ ራሳቸዉ በቆሰቆሱት ጦርነት ሳቢያ በደረሰባቸዉ ዉርደት ምክንያት የግምገማ ስህተት መስራታቸዉን አምነዉ ሲቀበሉ እኛ ግን አስከዛሬም የሰራነዉን ስህተት ለመቀበልም ሆነ ስለጦርነቱ ለመነጋገር ፍላጎቱ አላሳየንም፡፡

በእኛ በኩል በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርተን ለወረራ ተመቻችተን መቆየታችን ትልቅ ስህተት ነበር፡፡ እነሱ የራሳቸዉ ያልሆነን ነገር ለመንጠቅ አስበዉና  ለትርፍ ፍለጋ ብለዉ ስህተት ሰሩ፡፡ እኛ ግን የራሳችንን ላለማስነጠቅ መስራት የሚገባንን ሳንሰራ በመቆየት እነሱ ከሰሩት የበለጠ ትልቅ ስህተት ሰራን፡፡ ስለ ኤርትራ መንግስት የነበረን የተሳሳተና የተዛባ ግምገማ እኛን ለስህተት መዳረጉ ብቻ ሳይሆን እነሱ ራሳቸዉንም ተሳስተዉ እንዲወሩን አደርገናቸዋል፡፡

እንደምንጠረጥራቸዉ ቢያዉቁ ኖሮ ለጥቃት አያስቡንም ነበር፡፡ ደካማ መስለን ባንታያቸዉ ኖሮ በአስርሺዎች ለሚቆጠሩ ጅግኖቻችን መዉደቅ ምክንያት የሆነዉን ጦርነት ባላስነሱብን ነበር፡፡ እኛን የጎዳን ከነሱ ስህተት ይልቅ የኛ ስህተት ነዉ፡፡ የኤርትራ መሪዎች በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርተዉ ወረራ እንዲፈጽሙብን የእኛ የተሳሳተ ግምገማ በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከወረራዉ በፊት መንግስታችን ማንኛዉም ሃላፊነት ያለበት መንግስት እንደሚያደርገዉ የአካባቢያችንን ሁኔታ የሚቃኝ  የስጋት ትንታኔ  አላደረገም ለማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓይነት ስራዎች ሲሰሩና ጥናቶችም ሲደረጉ እንደነበር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አዉቃለሁ፡፡ ምናልባት ሊነሳ የሚችለዉ ጥያቄ መንግስት በስጋት ትንታኔዉ ግምገማ ኤርትራን በምን ደረጃ ነበር የፈረጀዉ የሚለዉ ነዉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ሲደረጉ ከነበሩ አካባባዊ የሥጋት ትንታኔ ጥናቶች ኤርትራ እንደ ጠላት ቀርቶ በአጠራጣሪ ወዳጅ ደረጃ እንኳን አንድም ጊዜ አለመመደቧ የሚታወቅ ነዉ፡፡ እኔ ራሴ እንደማስታዉሰዉ ከጦርነቱ አንደ አመት ቀደም ብሎ የሀገራችንን የወደፊቱን አየር መከላከያ ሲስተም ለመዘርጋት መነሻ ጥናት እንዳቀርብ ታዝዤ በሰራሁበት ወቅት በካርታ ንድፍ ላይ የኤርትራን ኤር ቤዝ ምልክት የጠላት መለያ በሆነዉ በሰማያዊ ቀለም በማድረጌ የቅርብ አለቃዬ የነበረዉ ክፉኛ ተቆጥቶኝ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ አለቃዬ ራሱ ኤርትራን “ወዳጅ” ለማለትም ቸግሮት እንደነበረም ትዝ ይለኛል፡፡

የሀገራችን የብሄራዊ ደህንነት ስትራቴጂና የዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲ ከጦርነቱ በፊት ስለመዘጋጀቱ መረጃ የለኝም፡፡ ቢያንስ ይህ ጠቃሚ ሰነድ ለህዝብ በይፋ ለዉይይት የቀረበዉ ከጦርነቱ በኋላ በ1993 መጨረሻና 94 መጀመሪያ ላይ ይመስለኛል፡፡  በበኩሌ የዚያ ዓይነት ዶክመንት መኖሩንም ያወኩት በተጠቀሰዉ ወቅት  ነዉ፡፡

ይህ ሰነድ ስለኤርትራ በተገቢዉ መንገድ ትንታኔ የሰጠ ቢሆንም የዚህ ዓይነት ግምገማ ከወረራዉ በፊት የነበረ ስለመሆኑ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ምክንያቱም “ሳናስበዉ ፤ሳንጠረጥር፤ በድንገት ተወረርን” የሚባሉ ሰበቦችን መደርደር ባላስፈለገ ነበርና፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም አገሮች ጋር በሰላምና በወዳጀነት ተከባብሮ የመኖር፤ በሌላዉ አገር ሉአላዊ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ ይከተል ስለነበር እኛ የሌላዉን መብት አስካልነካን ማንም የኛን መብት ሊነካ አይነሳሳም የሚል እምነትም ስለነበረዉ የኤርትራን ጉዳይ በጥርጣሬ  ደረጃ እንኳን አለማዬቱና  አጎራባች አገሮችን በሙሉ አንዱንም ከሌላዉ ሳይለይ በጅምላ ወዳጅ አድርጎ መቁጠሩ ለዚህ ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የቱንም ያህል ሰላም ወዳድ ቢሆን  የኤርትራን  መንግስት የጸብ ጫሪነት ባህሪይ ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ለተከታተለዉ ሰዉ መንግስታችን ኤርትራን ከጂቡቲ፤ ከኬንያና ከሱዳን ጋር እኩል ማዬቱን ተገቢ ነበር አይልም፡፡ የሆኖ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ የነበረዉ አቋም ከጂቡቲ፤ ከኬንያ ወዘተ በተለዬ መልኩ በጥርጣሬ ዓይን ያለማዬቱ ጉዳይ የግምገማ ችግር ያመጣዉ ድክመት ካልሆነ በስተቀር መንግስት ሆን ብሎ ያደረገዉ ነገር አይመስለኝም፡፡

መንግስታችን ስለ ኤርትራ አመራሮች ክፉ ባህሪይ ገና ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ ጠንቅቆ ያዉቅ እንደነበር ነገር ግን ኤርትራን እንደ ጠንቀኛ ጎረቤት እንዳያይ ዓይኑን የጋረዱት ሁኔታዎች በመኖራቸዉ ምክንያት ለድንገተኛ ወረራ እንደተጋለጥን ለመረዳት አይከብድም፡፡

5/ ወረራዉን ድንገተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁኔታዎች

ከኤርትራ በኩል ለጥቃት ሊሰነዘርብን ይችላል ብሎ መንግስት እንዳያስብ ያደረጉና የወረራዉ ድንገተኛነትና ያልተጠበቀ መሆን የብዙ ሁነቶች ድምር ዉጤት ነዉ፡፡ መንግስታችንን  ለመዘናጋትም ሆነ ኤርትራን  እንዳይጠራጠር በማድረግ ጫና ያደረጉበት ሁኔታዎች ምን እንደነበሩ ግምቴን ቀጥዬ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

5.1/ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረዉ ግኑኝነት ሻዕቢያን ለጦርነት የሚያነሳሳ ገፊ ምክንያት ሊሆን አይችልም

ከጦርነቱ በፊት በኤርትራና በኢትዮዮጵያ መንግስታት መካከል በብዙ ጉዳዮች የመተባበርና የወዳጅነት መንፈስ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ትንሽ በተለየና ጠንከር ባለ መንገድ ከኤርትራ ጋር ወዳጅነት መመስረቷ የሚጠበቅና ተገቢም ነበር፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ ወቅቱ አስገድዶአቸዉ ቢለያዩም አንድ አገር የነበሩ በመሆናቸዉ ከኬንያና ከሱዳን የበለጠ ወዳጅነት በመመስረቱ መንግስትን የሚያወቅስ አይደለም፡፡ ግኑኝነቱ ወደ ኤርትራ ያደላ ይመስላልና ይስተካከል በሚል በወቅቱ ቅሬታና ጥርጣሬያቸዉን ሲገልጹ በነበሩ ወገኖችም ቢሆን ከኤርትራ ጋር እስከነአካቴዉ ወዳጅነት መመስረት የለብንም የሚል አስተያየት የተሰጠ አይመስለኝም፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ በነበራቸዉ ወታደራዊ የትብብር  ስምምነት መሰረትም ችግር ሲያጋጥማቸዉ በጋራ የመተጋገዝ ሁኔታ ነበራቸዉ፡፡ ለምሳሌ የካርቱም መንግስት የእስልምና አክራሪዎችን በማሰማራት ጉዳት ለማድረስ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ሁለቱም አገሮች በጋራ ተባብረዉ አደጋዉን ለመቀነስ ሞክረዋል፡፡ ሁለቱም መንግስታት ለሱዳን ነጻ አዉጭ ድርጅት(SPLA) በቅንጅት በጋራ እገዛ ያደርጉ ነበር፡፡

በተጨማሪ ለኮንጎዉ ሎሬንት ካቢላ በ1990 ዓ/ም ለስልጣን መብቃት ሁለቱም ድርጅቶች አስተዋጽኦ አድርገዉ ነበር፡፡ ለሱዳን ተቃዋሚ ቡድኖች ስብስብ ለሆነዉ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት (NDA) በጋራ የፖለቲካ እገዛ አድርገዋል፡፡ ሁለቱም አገሮች ከአሜሪካ ጋር በእኩል ደረጃ ወዳጅነት መስርተዉ እገዛ እያገኙ ነበሩ፡፡

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን በኢትዮጵያ ዉስጥ ከኢትጵያዉያኑ በተሻለ ሁኔታ ሃብት አፍርተዉ ይኖሩ ነበር፡፡ ለየትኛዉ ሌላ አገር ዜጋ በማይደረግ ደረጃ ለኤርትራዉያኑ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ ከባንክ እንዳሻቸዉ እንዲበደሩ ሁኔታዉ ተመቻችቶላቸዉ በዚህም እጅግ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራ ህዝብ ካደረገዉ ትብበር ጎልቶ የሚታየዉ ኤርትራ የራሷን ነጻ መንግስት ለመመስረት ለሚያስችላት ሪፌሬንደም ስትዘጋጅ የኤርትራን ህዝብ ነጻ የመሆን መብትና ፍላጎት ለማደናቀፍ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አንዳችም ሙከራ አለመደረጉ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ እገዛና ትብብር ማድረጉ ነዉ፡፡ እንዲያዉም ገዢዉን ፓርቲ “ኢህአዴግን “አስከሚያስተቸዉ ድረስ  ለሪፌሬንደሙ መተባበሩና ከሌሎች አገሮች ቀድሞ ለኤርትራ ነጻ መንግስትነት እዉቅና መስጠቱ ኤርትራ መንግስት በኩል በቀላሉ መታዬት የነበረበት ጉዳይ አልነበረም፡፡

ምናልባት የኢትዮጵያ መንግስት ከራሷ አካል ለተገነጠለችዋ ኤርትራ እዉቅና ባይሰጥ ኖሮ የኤርትራን መገንጠል ማስቀረት ባይቻል እንኳ ነገር ግን እንደ ሉአላዊ አገር ፈጥና እዉቅና ማግኘት መቻሏ እጅግ አጠራጣሪ ይሆን ነበር፡፡ ቢያንስ ዘለግ ያለ ጊዜ ሊጠይቅ ይችል ነበር፡፡ እንደአብነትም የሶማሊ ላንድን ሁኔታን እዚህ ላይ ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል፡፡ የኤርትራ መንግስት ግን ይሄን እንደ ትልቅ ትብብር ወይም ዉለታ የቆጠረዉ አይመስለኝም፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ገና ከመነሻዉ አቅሙ በፈቀደዉ ሁሉ እገዛ ማድረጉ እንደ ጥፋት ቆጥረዉት ካልሆነ በስተቀር  የኤርትራን ሉአላዊነት የሚጋፋ እርምጃ ወስዷል የሚል አንዳችም ትችት ወይም ክስ አልቀረበበትም፡፡ በወቅቱ የሻዕቢያ መንግስት ደርግን አሸንፎ አስመራ መቆጣጠር ከቻለ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ደገፈም አልደገፈ የኤርትራን ለብቻዋ መሆን ሊያስቀር የሚችልበት አንዳችም ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሪፈረንዴም መደረጉም ለሻዕቢያ ዓለም አቀፍ እዉቅና ለማግኘት ስለሚያግዘዉና በተጨማሪ ህጋዊ መንገድ የመከተል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የኤርትራ ነጻ አገርነት ጉዳይ ቀድሞዉኑ የደርግ መንግስት በተሸነፈ ጊዜ ያበቃለት ጉዳይ ነበር፡፡

በርካታ ኢትዮጵያዉያን ግን የኤርትራ ከእናት አገሯ እንዲህ እንደዋዛ መነጠል በወቅቱ  እጅግ ሲያንገበግባቸዉ እንዳልነበር ዉለዉ ሲያደሩና የኤርትራን አመራሮች ጋጠ ወጥነት ሲያዩ ግን  “ግልግል ነዉ” ነበር ያሉት፡፡ እንኳን ቀረብን ነበር ያሉት፡፡ ለነገሩ ሻዕቢያ የመገንጠል ሃሳቡን ቀይሮ አንድ ላይ እንሆናለን አንገነጠልም ቢሉ ቢሆን ኖሮ  ምን ዓይነት ወጥ መንግስትስና ስርአት መመስረት ይቻል ነበር?

ሁለቱ ድርጅቶች የተለያዬ ስርአት ለመመስረት በሚያስቡበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አገር ልትሆን ትችል ነበር? የአገሪቱን ገዢ ፓርቲ ሊሆን ይችል የነበረዉስ ሻዕቢያ ነዉ ወይስ ኢህአዴግ? የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ይሆን የነበረዉ የኢህአዴግ ወይስ የሻዕቢያ ሰራዊት ነበር? ግራ የሚያጋባና ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር፡፡ ለዚህም ነዉ በኋላ ሁኔታዉን ሲረዱ ብዙዎቹ ኢትዮጵያዉን “አረ እንኳን ያልሆነ “ለማለት የበቁት፡፡ እንዲያዉም አንዳንዶቹ ኢህአዴግን በዚህ ጉዳይ ክፉኛ ተቀይመዉ የነበሩ ሳይቀሩ የኢሳይያስን ድርጊት ካዩ በኋላ ኢህአዴግን “ደግ አደረገ” በማለት አመስግነዉታል፡፡

የሻዕቢያ  መሪዎች እንደ እስራኤል ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል በመገንባት የሪጀኑ (የአካባቢዉ) ወሳኝ ሃይል ለመሆንና በኢኮኖሚ ደግሞ የምስራቅ ኤሽያዋን ሲንጋፖር ለማድረግ ማለማቸዉ የሚያስወቅሳቸዉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንደ አንድ የሀገር መሪ ኢሳይያስም ለሀገራቸዉ ህዝብ መልካም ነገር ቢመኙለት ተገቢና የሚያስመሰግናቸዉም በመሆኑ ነዉ፡፡ እኛም የኢሳያስን ኤርትራን የመልማትና ታላቅ ሀገር የማድረግ ህልም አልተቃወምንም፡፡ ችግሩ ግን ይህን ህልማቸዉን እዉን  ለማድረግ ያሰቡበት መንገድ በኛ ኪሳራ መሆኑ ነዉ፡፡

ኤርትራን በኢንዱስትሪ ለማበልጸግ ሲያቅዱ ኢትዮጵያን በጥሬ ዕቃ ምንጭነት እንደሚጠቀሙ ታሳቢ በማድረግ ነዉ፡የዉጭ ምንዛሪ ለማግኘትም ከኢትዮጵያ ቡናና የቅባት እህሎች ወዘተ በኛዉ ብር እየገዙ ወደ ዉጭ መላክ እንደሚችሉ በጣም እርግጠኛ ሆነዉ ነዉ፡፡ ኢሳይስ ይህን ህልማቸዉን አልመዉ ብቻ አልተቀመጡም፡፡ በተግባርም ብዙ ተራምደዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ አመታት ያለመቋረጥ ግጠዉናል፡፡ ከዚያ በላይ ግን ልንተባበራቸዉ አልፈቀድንም፡፡ በዚህ ምክንያትም እኛን እያደሙ እነሱ የሚለሙበት አንዳችም ምክንያት ስለለለ ዘግይተንም ቢሆን አስቁመናቸዋል፡፡

ኤርትራ ከተገነጠለችበት እለት ጀምሮ ኢትዮጵያ የድሮ “ቅኝ ግዛቷን“ ኤርትራን መልሳ የማቋቋምና የማበልጸግ ሃላፊነትና ግዴታ ያለባት በሚያስመስል ደረጃ ኤርትራን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉና ያደረጉ በእኩልነት ላይ ያልተመሰረቱ ግኑኝነቶች ሲካሄዱ እንደነበረ በወቅቱ  ሁኔታዉን የተረዱ ዜጎቻችን  በሃዘንና በቁጭት ሲገልጹት የነበረ ነዉ፡፡ በጣም የሚገርመዉና የኤርትራን ባለስልጣናትን ዓይን አዉጣነትና አጭበርባሪነት የሚያሳዬዉ በወቅቱ በነበረዉ የተዛባ ግኑኝነት ከኤርትራ ይልቅ ኢትዮጵያ የበለጠ ተጠቃሚ ነበረች ሲሉ መደመጣቸዉ ነዉ፡፡

የኤርትራ ስግብግብነትና ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ገደቡን አልፎና ህዝቡን አበሳጭቶና የኢትዮጵያን መንግስትን አስቆጥቶ ዘግይቶም ቢሆን መንግስታችን አንዳንድ ማስተካከያ እርምጃዎችን መዉሰድ ሲጀምር “ኡኡ” ማለት የጀመሩት እነሱ ናቸዉ እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ ከቀድሞዉ ግኑኝነት የበለጠ ተጠቃሚዎቹ እኛ ሆነን ቢሆን ኖሮ መቆጣት ያለብን እኛ መሆን ሲገባን ሻዕቢያ የበቀል እርምጃ ሊወስድብንም ሆነ ጦርነት ሊያዉጅብን ባልተገባዉ ነበር፡፡

በሻዕቢያ ድርጊት ሲበግኑ የቆዩ ኢትዮጵያዉያን ከሻዕቢያ ጋር ወደ ጦርነት መግባታችን ሲሰሙ ከአንግዲህ የሻቢያን ዝርፊያና ብዝበዛን ያስቀራል በሚል እሳቤ ከፍተኛ ደስታ ነበር የተሰማቸዉ፡፡ ስለዚህ በኛ መንግስት በኩል የእነሱን መብትም ሆነ ሉአላዊነት የሚጎዳ አንዳችም ነገር አላደረግንም፡፡

5.2/ በወታደራዊ መስክም በመካከላችን የነበረዉ ትብብር ከኛ ይልቅ ኤርትራ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነበር

ኤርትራ ገና አዲስ ጎጆ ወጭ የነበረች በመሆኑ እንደ ሀገር ሊኖራት የሚገቡ ተቋማት ስለአልነበሯት ኢትዮጵያ እገዛ ማድረጓ የሚያስደንቅ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይብዛም ይነስም ከኤርትራ የተሻለ ሁኔታ ላይ ስለነበር ራሳቸዉን አስከሚችሉ በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ እጅግ ብዙ እገዛዎች ሲያደረግ እንደነበረ ይታወቃል፡፡

ከነዚህም አንዱ በወታደራዊ መስክ በተለይም አየር ኃይሏን በማቋቋምና በማደራጀት፣ የአየር ኃይል ጄት አብራሪዎችን በማሰልጠን ረገድ ኤርትራን ለማገዝ ኢትዮጵያ አሰተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ በወታደራዊ መስክ ኢትዮጵያ ለኤርትራ ያደረገችላት ትብብር ረገድ ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነገር ቢኖር ኤርትራ በማንአለብኝነት ተነሳስታ የየመን ህጋዊና ታሪካዊ ይዞታ የሆነዉን የሃኒሽ ደሴትን በኃይል ወርራ ከተቆጣጠረች በኋላ ኢትዮጵያ የአየር ኃይል አካል የነበሩ የአየር መከላከያ ክፍሎችን አሰብ ላይ ማስፈሯ ነዉ፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል በነበረዉ ወታደራዊ ስምምነት መሰረት አትዮጵያ በወቅቱ የአሰብ ወደብን ከአየር ጥቃት ለመታደግ የሚችል የአየር መከላከያ ክፍሎችን ልካ በአሰብ አካባቢ የአየር ክልል ጥበቃ በማድረግ ትብብሯን አሳይታለች፡፡ በወቅቱ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ ሚሳይሎችንና እና የቅኝት ራዳሮችን (serveillaence radars) የታጠቁ ሶስት የአየር መከላከያ ዩኒቶችን (anti aircraft missile squadrons) አሰብ ላይ አስፍራ እንደነበርና ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ በዚያ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ይህን እርምጃ የወሰደቸዉ ከኤርትራ ጋር በነበራት ወታደራዊ ስምምነት መሰረት ነበር፡፡ በዚሁ ስምምነት መሰረትም ኢትዮጵያ የኤርትራን ወረራ መደገፏ ብቻ ሳይሆን ሃኒሽ ደሴት የኤርትራ ንብረት እንደሆነ እዉቅና መስጠቷን በቅርቡ የወጣ አንድ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ለጦርነቱ እገዛ እንዲያደርጉ ተብሎ አራት ሄሊኮፕተሮችን በወቅቱ ኢትዮጵያ ለኤርትራ መስጠትዋም ተወስቷል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ሰለመፈራረሟ የሀገራችን ፓርላማ የሚያዉቀዉ ነገር አልነበረም፡፡ በፓርቲዉ ደረጃም ቢሆን ከጥቂት የህወሓት አመራሮች ዉጭ ሌሎቹ  ኢህአደግ አመራሮችም ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር አልነበረም ነዉ የተባለዉ፡፡  

የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕቢያን ለማገዝ ወደ አሰብ ጦር መላኩን ባወቁ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ ለኤርትራ ህገወጥ ድርጊት የተባበረችና ወረራዉንም የደገፈች ያህል ማስቆጠሩና ማስተቸቱ አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል ሁኔታዉን በቀና መንፈስ የተመለከቱ ወገኖች ኢትዮጵያ በብቸኝነት ስትጠቀም የነበረዉ አሰብ ወደብን ደህንነት ለማስጠበቅ ወይም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ተብሎ የተደረገ እንጂ የኤርትራን ወረራ ለመደገፍ ተብሎ አልነበረም የሚሉ አሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላና የየመንና የኤርትራ ዉዝግብም እልባት በማግኘቱ ኢትዮጵያ ጦሯን ማለትም የአየር መከላከያ ክፍሉን ከአሰብ ካስወጣችም በኋላ ኤርትራን በወታደራዊ- ቴክኒካዊ ጉዳዮች ማገዟን አላቋረጠችም ነበር፡፡  ለምሳሌ በአስመራ ዉስጥ ያለ ስራ ተከማችተዉ ይገኙ የነበሩና ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ የሶስት የአየር መከላከያ ስኳድሮኖች መሳሪያዎችን የሻዕቢያ አመራሮች አስጠግነዉ ለመጠቀም በነበራቸዉ ዉጥን መሰረት ከሩሲያና ከዩክሬይን ጋር ያደረጉት  ድርድር በዉጭ ምንዛሪ እጦት ሊሳካላቸዉ ባለመቻሉ የወቅቱ ወዳጇን ኢትዮጵያን ትብብር በመጠየቋና መንግስታችንም ጥያቄያቸዉን በመቀበል ተባብሯል፡፡

በዚሁ መሰረትም ለረዥም ዓመታት በዚህ ሙያ የተካኑትን የአየር መከላከያ ኢንጂነሮችንና ቴክኒሻኖችን አስመራ ድረስ በመላክ እዚያ ተከማችተዉ ይገኙ የነበሩትን የአየር መከላከያ መሳሪያዎች በሙሉ በሚገባ ጠግነዉና አስተካክለዉ ካስረከቡ በኋላ ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰዋል፡፡ የሻዕቢያ ባለስልጣናት በኢትዮጵያዉያኑን ባለሙያዎች በተሰራዉን ስራ እጅግ ከመደሰታቸዉ የተነሳ እንደምንም አግባብተዉና በገንዘብ አታለዉ እዚያዉ ሊያስቀሯቸዉ አንዳንድ ሙከራዎችን ከማድረግ ባይቆጠቡም እንዳሰቡት ግን ሊሳካላቸዉ አልቻለም፡፡

ከአስመራ እንደተመለሰ ስለሁኔታዉ ያጫወተኝ በወቅቱ የቡድኑ አባል የነበረና አሁን በህይወት የሌለ የአየር መከላከያ ሙያተኛ የሆነ ኮሎኔል ነዉ፡፡ ይህ የአየር መከላከያ አባል በወቅቱ የሻዕቢያ ዓላማና ዉጥን ምን እንደነበረ በዉል ለመረዳት ባይችልም አጉል ብልጣብልጥነታቸዉ ግን አበሳጭቶት ነበር፡፡

በነገራችን ላይ የተጠቀሱት እነዚህ መሳሪያዎች ባለፈዉ የደርግ መንግስት ወደ መጨረሻዉ አካባቢ በብዙ ሚሊዮን ዶላር በብድር ከሩሲያ ተገዝተዉ የመጡና ገና አንድ ዓመት እንኳን ያላገለገሉ የኢትዮጵያን አንጡራ ሃብት የነበሩ ናቸዉ፡፡ ሻዕቢያ በ1983 መጨረሻ ላይ አሰብን ከተቆጣጠረ በኋላ በመርከብ አጓጉዞ ወደ አስመራ ወስዶ ያከማቻቸዉ ናቸዉ፡፡

የኤርትራ መንግስት እነዚህን መሳሪያዎች ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ አዉጥቶ በሩሲያ ባለሙያዎች ካላስጠገነና ለዘለቀታዉም ወጣቶችን ሩሲያ ድረስ በመላክ ባለሙያዎችን እንዲያሰለጥኑለት ካላደረገ በስተቀር መቼም ቢሆን መሳሪያዎቹን ለመጠቀም እንደማይችል ሲገነዘብና የዉጭ ምንዛሪም እንደለለዉ ሲረዳ እንደአማራጭ የወሰደዉ አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት አሰልጣኞችን አስመራ ድረስ በመላክ ኤርትራዉያንን እንዲያሰለጥንላቸዉ ማድረግ ነበር፡፡

በዚህ መሰረትም ትብብር የጠየቁበት ደብዳቤ በኢፌድሪ አየር ኃይል በወቅቱ አዛዥ በነበሩት በሜ/ጄል አበበ (ጆቤ) በኩል ደርሶን አንዳንድ ዝግጅቶች በማከናወን ላይ እያለን ነዉ የሻዕቢያ ወረራ ማድረግ የተሰማዉ፡፡ በነሱ ጥያቄ መሰረት ተቻኩለን አሰልጣኞችን ልከን ቢሆን ኖሮ እዚያዉ ምርኮኛ ሆነዉ ሊቀሩ ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ሻዕቢያ ምን ያህል ልቡ የማይገኝ መሆኑን ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሌም ሳስታዉሰዉ ከሁሉም በላይ የሚያናድደኝ የሻዕቢያ ተንኮል ቢኖር አስመራ የነበረዉን የኛኑ መሳሪያ በእኛዉ ባለሙያዎች አስጠግኖና አሰልጥኖ መልሶ የኛኑ አይሮፕላኖች ለመምታት አቅዶት የነበረዉን  ሴራ ነዉ፡፡

ከኤርትራ ጋር የነበረዉ ወታደራዊ ትብብር በዚህ ብቻ ሳይገደብ አየር ኃይላችን ለኤርትራ የተለያዩ ትብብሮችን አድርጓል፡፡  ለኤርትራ የመጀመሪያዎቹ የሆኑትን ጄት አብራሪዎች እዚሁ ደብረ -ዘይት (ሐረር-ሜዳ) ላይ አሰልጥኖ እስመርቋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኛ ሄሊኮፕቴሮች አስመራ ዉስጥ በቋሚነት ተመድበዉ ለኤርትራ ባለስልጣናት በትብብር የማጓጓዣ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዉ ጦርነቱ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ብቻ ሲቀረዉ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱበት ሁኔታ የአጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህም ሌላ በሽግገሩ ወቅት አየር ኃይላችን እንደገና በማቋቋም ስራ እንዲያግዙ በጊዜያዊነት በመንግስት ተመድበዉ የነበሩት ብርጋዲር ጄነራል ሰለሞን በየነ  ኤርትራም በበኩሏ አየር ኃይል ለማቋቋም ስታደርግ በነበረዉ ጥረት ኢትዮጵያ ማገዝ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ለመመካር አስመራ ድረስ በመሄድ ከባለስልጣናቱ ጋር ሲመካከሩ ዓይን አዉጣዎቹ  የኤርትራ መከላከያ ባለስልጣናት ለጄነራሉ አቅርበዉ የነበረዉ ሃሳብ እጅግ የሚገርም ነበር፡፡

ያቀረቡትም ጥያቄ ደብረዘይት ያለዉ የአየር ኃይል ማስልጠኛ ተቋም እንዳለ ተነቅሎ እዚህ አስመራ ላይ ተቋቁሞ ለሁለቱም አገሮች ስልጠና ከአስመራ ላይ ይስጥ የሚል ነበር፡፡ ሻዕቢያ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ መጠየቁ ለኢትዮጵያ መንግስት ምን ያህል ንቀት እንደነበረዉ የሚያሳይ ነዉ፡፡

ለማንኛዉም በዚህና በሌሎች ባልተጠቀሱ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራን እንደራሱ አይቶ ያለባቸዉን ችግር ተረድቶ ያለአንዳች ክፍያ በብዙ ነገር ሊያግዛቸዉ መሞከሩ ወንድም ለሆነዉ የኤርትራ ህዝብ ያለዉን ቅን አመለካከት የሚያሳይ ካልሆነ በስተቀር ኤርትራን የሚያስከፋ ድርጊት አልነበረም፡፡ ለምንስ ተብሎ ጦርነት ትከፍትብናለች ተብሎ ይታሰባል?

5.3/ መንግስት ብቻ ሳይሆን መከላከያ ሰራዊታችን አባላትም ኤርትራ ህዝብ የጠላትነት አመለካከት አልነበራቸዉም  

ከጦርነቱ በፊት ኤርትራን እንደ ወዳጅ የማየት ነገር በመንግስት ደረጃ ብቻ የነበረ አቋም ሳይሆን በመከላከያ ሰራዊታችን አባላት ዘንድም ኤርትራን በጠላትነት የሚፈርጅ አመለካከት ጨርሶ አልነበረም፡፡ ደርግ ከወደቀ ከ1983 መጨረሻ ጀምሮ አብሮ የመስራት አጋጣሚ በፈጠረልኝ ምቹ ሁኔታ ያወቅኳቸዉ ነባር ታጋዮች በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ የኤርትራን ህዝብ በሚመለከት አንዳችም የጥላቻ አመለካከት አልነበራቸዉም፡፡

የኤርትራን ህዝብ ነጻነት በሚመለከትም የተቃዉሞ አመለካከት በጭረሽ አልነበራቸዉም፡፡ ይሄ ህዝባዊ አመለካከት ከላይ ያለዉ የድርጅታቸዉ መሪዎች እንደዚያ እንዲያደርጉ መመሪያ ስለሰጧቸዉ ሳይሆን ገና ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ በእምነት የያዙት የጸና አቋማቸዉና አመለካከታቸዉ መሆኑን ነዉ የተረዳሁት፡፡

የኤርትራ ሪፌሬንደም ሊከናወን አካባቢም ታጋዮቹ ከህዝቡ ጋር ይበልጥ የመቀራረብና በአንዳንድ ማህበራዊ ጉዳዮችም በአካባቢያቸዉ ካለዉ ህዝብ (ነዋሪ) ጋር  አብሮ መሳተፍና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸዉ ጉዳዮች ላይም በግልጽ መወያት የጀመሩበት ወቅት ስለነበር የሕዝቡን አመለካካት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስቻላቸዉ ይመስለኛል፡፡ በሪፌሬንደም ወቅት ከሚቀርቧቸዉ ነዋሪዎች ጋር በግል መወያዬት በመቻላቸዉ በህዝቡ ዉስጥ በስፋት ሲንሸራሸሩ የነበሩ አስተያየቶችን በማድመጥ በተለይ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ለምን ብዙ ሰዉ ቅሬታ እንደተሰማዉ ግራ መጋባታቸዉ አልቀረም፡፡

የኤርትራ ነጻ መዉጣት (መገንጠል)ላይ  አብዛኛዉ ህዝብ ደስተኛ እንዳልሆነና ይልቁንም ቅር መሰኘታቸዉ ሲገነዘቡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማስረዳት ጥረት ያደርጉ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ እንደሚታወቀዉ ብዙዎቹ ታጋዮች በወቅቱ ገና በወጣትነታቸዉ ትምህርት አቋርጠዉ ወደ ትግሉ በመቀላቀላቸዉ በትምህርት የገፉ ባይሆንም ነገር ግን በሚያምኑበት ጉዳይ ላይ በከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ ለማሳመን ሲሞክሩ ሳይ በጣም ይገርመኝ ነበር፡፡ ያኔ ያየሁባቸዉ ግልጽነት፤ ቅንነት፤ ህዝባዊ አመለካከት፤ በራስ የመተማመን መንፈስና አልበገር ባይነት ዛሬም እብሮአቸዉ ይኖር ይሆን?

የኢህአዴግ ታጋዮች በወቅቱ የሪፈሬንደሙን ፋይዳ እንደ ህዝብ የኤርትራን ህዝብ ፍላጎት መግለጫ መንገድ አድርገዉ ነበር የቆጠሩት፡፡ “ህዝብ ምንጊዜም የፈለገዉን መወሰን ይችላል፡፡ የኤርትራ ህዝብም ለነጻነቱ ለዘመናት ሲታገል ቆይቷል፡፡ ብዙ መስዋእትነትም ከፍሏል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ከእኛ ጋር መኖር ካልፈለገና ብቻዬን ልሁን ካለ ሊገደድ አይገባዉም” የሚል አመለካከት ነዉ የነበራቸዉ፡፡ ይሄ አመለካከት የሁሉም ታጋዮች  አመለካከት ይመስለኛል፡፡

ከዚያም በኋላ ኤርትራ በሪፌሬንደሙ መሰረት ተነጥላ እንደሀገር መታወቅ ከጀመረች በኋላም ይሄዉ ለኤርትራ ህዝብ የነበራቸዉ ቀና አመለካከት በፍጹም አልቀነሰም ነበር፡፡ እንዲያዉም ኤርትራ ወረራ ማድረጓ በይፋ ከመገለጹ አንድ  ወር ቀደም ብሎ በርካታ የአየር ኃይል አባለት በተገኙበት አንድ ሰብስባ ላይ በሆነ አጋጣሚ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንዱ ነባር መኮንን ስለ ኤርትራ መንግስት በጥላቻ የታጀበ አስተያዬት ሲሰጥ ሰብሳቢዉ ነባር ታጋይ ተናጋሪዉን መኮንንን “ትምክህተኛ  ነህ” በሚል በተሰብሳቢዎች መሀል ከፍተኛ ትችት ካደረሰበት በኋላ መኮንኑ ከስራ መታገዱን አስታዉሳለሁ፡፡

የሚያሳዝነዉ ደግሞ ለኤርትራ ጥብቅና ቀሞ የነበረዉ ይሔዉ አመራር (ሰብሳቢዉ) በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንት በግዳጅ ላይ እያለ በኤርትራ አየር መቃወሚያ ተመትቶ መስዋእትነት መሆኑ ነዉ፡፡ አጋጣሚዉ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ይሄን ጉዳይ ያስታወስኩትም አንዱን ለመተቸት ሌላዉን ለማድነቅ ሳይሆን ሰራዊታችን እሰከ ጦርነቱ ድረስ ለኤርትራ ህዝብ መልካምና ቀና አመለካከት እንደነበረዉ ማሳያ ይሆናል በሚል ነዉ፡፡

የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ሙሉ ድጋፍ ከማሳየት ዉጭ አንድም ጊዜ የኤርትራን ህዝብ ጥቅም የሚጎዳ ነግር አድርገዉ አያዉቁም፡፡ ይሁን እንጂ የኢህአዴግ ነባሮቹ ታጋዮች ለኤርትራ ገዢ ፓርቲ ለሻዕቢያ አመራሮች የነበራቸዉ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየና በጥላቻ የተሞላ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ሻዕቢያ ገና ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ አመለካከት የሚባል ነገር ያልነበረዉ ሰብአዊነትና ለህዝብ ከበረታ ያልነበረዉ አምባገነን ድርጅት እንደነበርና አሁንም መንግስት ከሆነም በኋላ ይህንኑ ባህሪይዉን ሳይቀይር በመቆየቱ የኤርትራን ህዝብ ለባሰ ጭቆና መዳረጉን በማዉሳት ለሻእቢያ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸዉ ለሚቀርቧቸዉ ሲገልጹ በቁጭትና በሃዘን ነበር፡፡

በአንድ በኩል የኤርትራን ህዝብ ነጻነትና መብት አክብሮ በሌላ በኩል ደግሞ የሻቢያን ፀረ- ህዝብነት መተቸት ተገቢ ቢሆንም በጣም ከሚያምኑት ሰዉ ጋር በግል የርስበርስ ጭዉዉት ካልሆነ በስተቀር በመድረክ ላይ በይፋ የዚህ ዓይነት አስተያት የተሰነዘረበት ወቅት አላስታዉስም፡፡ ታጋዮቹ በትግሉ ወቅትም ለኤርትራ ህዝብ ቀና አመለካከት ከመያዝና ከወታደራዊ አስፈላጊነት አኳያ በዉጊያ ወቅት ዉስን ለሆኑ ጊዜያት ከመተባበር ባለፈ ከሻዕቢያ ጋር በዓላማም በአመለካከትም የማይመሳሰሉና የማይጣጣሙ እንደነበሩ ነዉ፡፡

ስለዚህ በመንግስት ደረጃም ሆነ በሰራዊቱ ዘንድ የኤርትራን ህዝብ ነጻነት የሚጋፋ አንዳችም ደባ እንዳልተሰራ መረዳት ይቻላል፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት ከጦርነቱ በፊት ይቅርና አሁንም በሻዕቢያ ጦስ ብዙ ምስቅልቀል ሁኔታዎችና ብዙ መስዋትነት ከተከፈለም በኋላም ቢሆን ለኤርትራ ህዝብ አንዳችም ጥላቻ አላሳደሩም፡፡ ለዚህም ጥሩ ምስክር የሚሆነዉ ትላንት ሲወጉን የነበሩ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ሰራዊት፤ መንግስትና ህዝብ በማመን ሻዕቢያን እየከዱ በየዕለቱ ወደኛ በገፍ መጉረፋቸዉ ነዉ፡፡

5.4/ የኢትየጵያ መንግስት ባህሪይና የሚከተለዉ የዉጭ ግኑኝኘት ፖሊሲ ለኤርትራ የስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችል አልነበረም

የሁለቱም አገሮች ህዝቦች ለዘመናት ሲካሄድ በነበረ የርስበርስ ጦርነት እጅግ የተጎዱና ጦርነት የሚባል ነገር ያንገሸገሻቸዉ የነበሩ ስለነበር ለዬትኛዉም ዓይነት ሰበብ ተፈልጎ ለሚደረግ ጦርነት ህዝቡ ድጋፍ አይሰጥም የሚል አመለካከት በተለይ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል አስቀድሜ በገለጽኩት ዓይነት ጠንካራ የወዳጅነት ግኑኝነት በመኖሩ አልፎ አልፎ አንዳንድ አለመግባባቶችና አለመጣጣም መከሰቱ ባይቀርም ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያስገባ ቅራኔ ግን አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ሲከተለዉ የነበረዉና አሁንም አጠንክሮ የቀጠለበት የዉጭ ግኑኝኘት ፖሊሲ ከሁሉም ጋር በሰላም ተከባብሮ የመኖርና የሌላዉን ጥቅምና ሉአላዊነት ማክበር ከሚሏቸዉ የተለመዱ መርሆችም በላይ በመሄድ የዉጭ ዲፕሎማሲ ትልቁ ስራዉ ልማትን የሚያግዝና ኢኮኖሚን ማምጣት ነዉ በሚል ትክክለኛ መሪህ ከመከተል ዉጭ ኤርትራን የሚጎዳ አንዳችም ድርጊት አልፈጸመም፡፡

መንግስታችን ከሌላ ከዬትኛዉም አገር ጋር ኤርትራንም ጨምሮ በጠላትነት የማይተያይ በመሆኑ ለየትኛዉም የጎረቤት አገር በተለይም ለኤርትራ የስጋት ምንጭ የሚሆንበት አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ መንግስት ግዙፍ የሆነ ሰራዊት ግንባታ አለማድረጉና ደርግን ያሸነፈዉን ሰራዊቱን ግማሽ በግማሽ ቀንሶና አሰናብቶ በቂ ነዉ ብሎ ያሰበዉን ያህል መጠነኛ ኃይል በያዘበት ሁኔታ ለኤርትራ ስጋት የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡

መንግስት ለሌላ አገር ስጋት አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ራሱም ከየትኛዉም ወገን  የሚያሰጋኝ ነገር የለም በሚል አቋም በመደፋፈሩ ከጦርነቱ በፊት የተለየ ወታደራዊ  ግንባታ አላደረገም፡፡ ከጦርነቱ በፊት አንዳችም የጦር መሳሪያ ግዢ አልፈጸም፡፡ በወቅቱ ወታደራዊ ባጄቱ ራሱ እጅግ አነስተኛ የነበረ በመሆኑ መንግስት የተለዬ የጦርነት ዝግጅት እንዳልነበረዉ የሚያሳይ ነዉ፡፡

ሌላ ቀርቶ በኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ላይም ይህን ያህል ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል የተለየ ወታደራዊ ክምችት አልነበረም፡፡ በወቅቱ ከሁመራ እስከ ዛላአንበሳ ባለዉ ሰፊ መሬት ላይ ቢበዛ በድምሩ ከሁለት ብርጌድ የማበልጥ ሰራዊት ነዉ የነበረን፡፡ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ግንባታም ሆነ የጦርነት ዝግጅት አጠራጥሮአቸዉና አስግቶአቸዉ ሳንቀደም እንቅደም ብለዉ ነዉ ወረራዉን የጀመሩት እንዳይባል አስቀድሜ እንደገለጽኩት ለዚህ ጥርጣሬ የሚያበቃ በኛ በኩል አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ እንዲያዉም በተቃራኒዉ ወደ መዘናጋቱ ያደላ ዓይነት ሁኔታ ነዉ የነበረዉ፡፡

አስቀድሜ ለመጠቆም እንደሞከርኩት  በሁለቱ አገሮች መካከል መልካም ግኑኝነት የነበረና እንዲያዉም ኤርትራ ከኢትዮጵያ በበለጠ ከዚህ ግኑኝነት ተጠቃሚ እንደነበረች፤ በመንግስት ደረጃም ሆነ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ደረጃ ኤርትራን ለጦርነት የሚገፋፋ አንዳችም ሁኔታ አልነበረም፡፡ ባጠቃላይም ኤርትራን ለጦርነት የሚጋብዝ ምክንያት ይኖራል ብሎ  ለማሰብ የሚያስችል አንዳችም አሳማኝ ሁኔታ ስላልነበረ መንግስት ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ይችላል ብሎ አለመገመቱ በወቅቱ የነበረዉን እዉነታ ለመግለጽ ካልሆነ በስተቀር ለመሸፋፈን ወይንም ከትችት ለማምለጥ የፈጠረዉ ምክንያት  አይመስለኝም፡፡

6/ የሆነስ ሆነና ሌላዉ ቢቀር መጠንቀቅስ አይቻልም ነበር እንዴ?

አስቀድሜ በገለጽኳቸዉ ሁኔታዎች ምክንያት ወረራዉን ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነዉ ለመባል በቂ ምክንያት ነዉ ብንል እንኳን ሃላፊነት እንደሚሰማዉ መንግስት ቢያንስ መጠራጠርና መጠንቀቅስ አልነበረበትም ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ የግድ ነዉ፡፡

በኤርትራ የተሰነዘርብን ጥቃት ኢሳይያስ ድንገት ከእንቅልፋቸዉ ሲነቁ ድንገት ወስነዉ በዚያኑ ዕለት የፈጸሙት አይደለም፡፡ የትኛዉም ዓይነት ጦርነት እንደተረገጠ ፈንጂ ድንገት የሚፈነዳ አይደለም፡፡ ሰበብ ተፈልጎለት በሃሳብ ተጸንሶ አስፈላጊዉ ዝግጅት ተደርጎበት ፤ታቅዶና ታስቦበት ጊዜ ተወስዶ የሚደረግ ነዉ፡፡ ጦርነት ምናልባት እንደ ጥንቱ የሀገራችን ልማድ ሁለት በላጋራዎች አስቀድመዉ ጊዜና ቦታ መርጠዉ እዚህ ቦታ በዚህ ጊዜ እንገናኝ ተብሎ ፤እንደ ኳስ ጫወታ ዳኛ አቁመዉና ፍሽካ ተነፍቶ የሚጀምር አይደለም፡፡

ያለ ምክንያት የሚካሄድ አንዳችም ጦርነት የለም፡፡ ፖለቲካዊ ዓላማ የሌለዉ ጦርነትም በጭራሽ አይኖርም፡፡ የክላዉስዊዝ (Clausewitz) የጦርነት አስተምህሮም የሚያረጋግጠዉ ይህንኑ ነዉ፡፡ ወደ ጦርነት የምንገባዉ ያሰብነዉን ፖለቲካዊ ዓላማ ለማሳካት ነዉ፡፡ ጦርነት የራስን ፍላጎት በሌላዉ ለመጫን የሚደረግ የኃይል ድርጊት ነዉ፡፡ ጦርነት የሚመነጨዉ ወይም የሚቀሰቀሰዉም ከሆነ ፖለቲካዊ ዓላማ ነዉ (war springs from some political Purpose)፡፡

ጦርነት ለመቀስቀስ ፖለቲካ ዓላማዉ የግድ ትክክል መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ለጦርነት የሆነ ዓላማ መኖር ብቻዉን በቂ ነዉ፡፡ ጦርነት ከፖለቲካ ዓላማ መመንጨቱ ብቻ ሳይሆን ራሱ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያም ጭምር (political tool) ሆኖ ያገለግላል፡፡ ጦርነት የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ በመሆኑ ጦርነቱ  የፖሊሲ አዉጭዎችን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆን ይገባዋል (wars are deliberate instruments of policy, and in their essence reflect the motives of the policymakers.) የጦርነት ዋነኛዉ ገላጭ ባህሪም አጋጣሚ ወይም ዕድል ሳይሆን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያነቱ ነዉ፡፡  (The primary characteristic of war is not chance, but rather its nature as a political tool.)

እንግዲህ ከነዚህ ጥቂት መሪሆዎች (ጥቅሶች) መረዳት እንደሚቻለዉ የኤርትራ መንግስት ጦርነት ሲከፍትብን ይብዛም ይነስም ጦርነት ለመቀስቀስ በቂ የመሰለዉን ፖለቲካዊ ዓላማ ይዞና ከጦርነት መንገድ ዉጭ በሌላ በማናቸዉም መንገድ ማሳካት እንደማይችል ተገንዝቦና ያን ለማሳካትም የሚያስችለዉን በቂ ወታደራዊ ዝግጅት አድርጎ ነዉ፡፡

ከጦርነቱ ምን ለማግኘት እንደፈለገም በቅድሚያ አስቦበት ነዉ፡፡ ሊገጥመዉ የሚችለዉን ተግዳሮትም በሚገባ አስቦበት ነዉ፡፡ ዝም ብሎ ዘሎ ጦርነትን ያህል ነገር ዉስጥ አልገባም፡፡ ምናልባት ኤርትራ ድሮ የለመደችዉና በኋላ ያጣችዉ ወይም የተቋረጠባት አንድ የሆነ ጥቅም ይኖራል፡፡ ሰበቡ ለኛ ከግምት የማይገባና እርባና ቢስ ሆኖ ቢታዬንም ለነሱ ግን ጦርነት ለመቀስቀስ በቂ ምክንያት አድርገዉ ሊያስቡ ይችላል፡፡ ጦርነትን እንደ ችግር መፍቻ ብቸኛ መንገድ ለሚቆጥር እንዴ ኤርትራ ላለ መንግስት ጦርነት ለመቀስቀስ ማንኛዉም ምክንያት (ተልካሻም ቢሆን) በቂ ምክንያት ነዉ፡፡

የእነሱ ምክንያት እኛን እንዲያሳምነን መጠበቅ አይገባንም፡፡ ኤርትራ ከኛ ስታገኝ የነበረዉና በኋላ የተቋረጠባት የገዛ ንብረቷ ስለነበረና ያንን ማግኘት ህጋዊ መብቷ ስለነበረም አይደለም፡፡ በፊት እንደዋዛ ያስለመድናትን ጥቅም በድንገት ስናቋርጥባት አንድም ሌላ አማራጭ ያልነበረዉ የኤርትራ አገዛዝ ከጦርነት የተሻለ ነገር ይኖራል ብሎ ስለማያስብ በኛ ላይ ጦርነት ቢከፍት ለምን ያስገርመናል? በእኛ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ህጋዊም ተገቢም እንዳልነበረ እንኳን እኛ ወረራ የፈጸመብን ሻዕቢያም ቢሆን ይሄን  አይረዳም ማለት አይቻልም፡፡ ችግሩ ያለዉ እኛ ዘንድ ነዉ፡፡ ይሄ እንደሚደርስ አስበን አለመጠርጠራችንና በቂ ዝግጅት በቅድሚያ አለማድረጋችን የኛ ድክመት ነዉ፡፡

እንዲያዉም ኤርትራ መንግስት የነሱን ለጦርነት ዝግጅት እያደረጉ መሆን የኛ መንግስት አለመጠርጠሩ እጅግ ሳያስገርማቸዉ አይቀርም፡፡ ለነገሩ እኮ ኤርትራዉያን የጦርነት አዋጅ በገሃድ ያለማወጃቸዉ ካልሆነ በስተቀር በተቀረዉ ሁሉ ዝግጅታቸዉን ለመደበቅ ያደረጉት ሙከራ እምብዛም አልነበረም፡፡ የኛ ደደብነት ካልሆነ በስተቀር ፡፡  ለዚህም ነዉ የሻዕቢያ ጥቃት ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነዉ ለማለት የማይቻለዉ፡፡

6.1/ የሻዕቢያ አመራሮች ባህሪይ ብቻዉን ለመጠንቀቅ በቂ ነበር

የኤርትራን መንግስት በተለይም የመሪዉን የፕሬዝዳንት ኢሳይያስን ነባር ባህሪይን የሚያዉቅ ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ እንደሆነ ይረዳል፡፡ የኤርትራ ህዝብ ያን ያህል ዘመን ታግሎና ልጆቹን ገብሮ የተመኘዉን ሰላምና ልማት ገና በደንብ ሳያጣጥም ሻዕቢያ ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ስራዉን እንደመንግስት “ሀ” ብሎ የጀመረዉ እዚህም እዛም ጦርነት በመለኮስ ነዉ፡፡

ከሻዕቢያ ጋር እኩል በአንድ ሰሞን ሀገር የማስተዳደር ሃላፊነት የተቀበለዉ ኢህአዴግ በከተማና በገጠር ጤና ጣቢያና ሆስፒታሎችን ሲያቋቁም፤ ዩንቨርስቲና ኮሌጆችን ሲከፍትና የመገናናኛ አዉታሮችን ሲዘረጋ ህዝቡን ከድህነት በአጭር ጊዜ መላቀቅ ይገባኛል ብሎ በልማት ስራ ላይ ተጠምዲ ሲዉተረተር፤ አዲስ ህገመንግስት ሲያረቅና አዲስ ፌዴራላዊ ስርአት ሲመሰርት ፤ ዲሞክራሲን ለማስፋፋት የሚያግዙ ዲሞከራሲያዊ  ተቋማትን ሲያቋቁምና ከሞላ ጎደል ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ደፋ ቀና ስል ሻዕቢያ ግን ስራዉ ሁሉ ጦርነት ሆኖ ቁጭ አለ፡፡

በኤርትራ የነበረችዉ አንድ ለናቱ የተባለላትን ዩንቨርስቲም እስከነአካቴዉ ዘግቶ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛነት ቀየረዉ፡፡ መምህራንና ሀኪሞችን መሃንዲሶችን ማፍራት ሲገባዉ በየስድስት ወሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ብሄራዊ ዉትድርና ሰልጣኞችን ማስመረቅ ስራዬ ቢሎ ተያያዘዉ፡፡ ሀገሪቱ በሌላት የዉጭ ምንዛሪ የጦር መሳሪያ መሸመት ጀመረ፡፡ ለነጻነት ተብሎ ለተከፈለዉ መስዋእትነት ዉጤት ነዉ ብለዉ ለህዝቡ የሚያሳዩትና የደረሱበትን ዕድገት መጠን የሚለኩት ባስመረቁት ወታደር ብዛት ሆኖ ቁጭ አለ፡፡

አንድ ጊዜ የመንን ሌላ ጊዜ ሱዳንን ሲፈልጉ ደግሞ ጅቡቲን ያለምንም ምክንያት በመዉጋት የዓለም ህዝብን ግራ አጋቡ ፡፡ ኤርትራን የመሰለች ከህዝቧ የመንፈስ ጥንካሬ በስተቀር አንድም የሚቆጠር ሃብት የሌላትን አገር የሚመራ መንግስት ከልማት ይልቅ ጦርነት ላይ ትኩረት ያደርጋል ብሎ ማንም ሊገምት አይችልም፡፡

ኤርትራ ለሰላሳ ዓመታት በተካሄደዉ ጦርነት ስትፈራርስ የኖረችና ሊጠቀስ የሚችል አንዳችም ፋብሪካና ሌላዉ ቀርቶ ለግብርና ተስማሚ የሆነ አንድ ጋሻ የሚሞላ ለም መሬት የለላት አገር መሆኗን ለሚያዉቁ ታዛቢዎች ከኢትዮጵያ ተነጥላና ነጻ አገር ሆና በምን ተአምር ነዉ እንደ አገር ልትቀጥል የሚትችለዉ? ብለዉ ሲጨነቁ ኢሳይስ ግን ልማቱን ከማቀላጠፍ ይልቅ የጦርነት አጀንዳቸዉን አጠናክረዉ ቀጠሉበት፡፡

ኢሳይያስ ጦር ልከዉ በቀጥታ መዉጋት በማይፈልጉበት ጊዜ ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ሽብርተኛ ቡድኖችን በማስተባበር፡መጠለያ በመስጠት፤በማሰልጠን፤ በማስታጠቅና ለጥፋት ተልዕኮ በማሰማራት ሀገራችንን በሚችሉት ደረጃ ሁሉ ሲያደሙና ሰላማችንን ሲያደፈርሱ  ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ዲሞክራሲ ለጭላንጭል ያህል እንኳን የሌለባት፤ሰብአዊ መብት ጥሰት በየቀኑ የሚፈጸምባት ህገመንገስት፤ አማራጭ ፓርቲዎች ፤ምርጫ ወዘተ ብሎ ነገር ጭራሽ በማይታወቅበት አገር ህዝባቸዉን ሰጥ ለጥ አድርገዉ በባሪያ አሳዳሪ ስርአት አገዛዝ ስልት እየገዙ እንደሆነ በሚገባ የሚታወቅና ምስጢርም ያልነበረ አሁንም በባሰ ሁኔታ የሚታይ ድርጊት ነዉ፡፡

ኤርትራን አሁን የአለም ህዝብ የሚያዉቃት በሽብርተኝነት ነዉ፡፡ በአካባቢዉ በሪጂኑ የሆነ ቦታ ላይ የሽብር ድርጊት በተፈጸመ ቁጥር ሁሉ የኢሳይያስ እጅ እንደሚኖርበት በርግጠኝነት መናገር የተለመደ ሆኗል፡፡ ለሻዕቢያ ምስጋና ይግባዉና ኤርትራ በአሁኑ ወቅተት ከአፍሪካ ህብረትም ሆነ በመንግስታቱ ድርጅት እንደ አገር ጠንካራ ተሳትፎ የማታደርግና መሪዋም ዓይንህን ላፈር የተባሉ ከዓለም መድረክ የተገለለች አገር ሆኗለች፡፡ ኤርትራ ከቅርብ ጊዜዋ ደቡብ ሱዳንም ሆነ የሶማሊያ መንግስት ያህል እንኳን ትኩረት ያልተሰጣት አሳዛኝ አገር ሆናለች፡፡ የኤርትራ ህዝብ ወይ ከልማት ልማት የለዉ፤ ወይ ከሰላም ሰላም የለዉ፤ ብቻ ከአንዱም ሳይሆን ዕጣ ፈንታዉ እንዲህ መሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡

አሁን አሁንማ የኤርትራ ህዝብ ግፉና በደሉ ሲበዛበት በዚያ በተረገመ ሪፌሬንደም ስም ከእናት ሀገሩና ከወንድሞቹ የተነጠለበትን ቀን ሳይረግም የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነቱን የማፍያ ቡድን እንደ መንግስት እዉቅና መስጠታችን እንደ ጥፋት ተቆጥሮብን ጭራሽ ጦር ሲሰብቅብን በጣም ያሳዝናል፡፡ ሻዕቢያ አዲስ ባህሪይ ካላመጣና ድሮም የምናዉቀዉን ክፉ ምግባሩን አሁንም በየጊዜዉ አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን እያየን እኛ ላይ ጥቃት ማድረሱን “ያልተጠበቀ ነዉ” መባሉን ለመቀበል የሚከብደዉም በዚህ ምክንያት ነዉ፡፡ ቢያንስ በአካባቢዉ ከሚገኙ  አገሮች ሁሉ ጋር ሲጋጭ የነበረ መንግስት ቀጣዩ ከኛ ጋር እንደሆነ ለመረዳት እንዴት ተሳነንና ነዉ “ያልተጠበቀ” የምንለዉ?

6.2/ የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራን ቅጥ ያጣ ብዘብዛ ለማስቆም የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ኤርትራን ሊያስቆጣ እንደሚችል በመገመት ተገቢዉን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዉ ነበር

የጦርነቱ ዋነኛዉ መንስኤ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጥያቄ በመሆኑ ሻዕቢያ የራሱን ፍላጎትና ጥቅም በኃይል በኛ ላይ ለመጫን የቆሰቀሰዉ ጦርነት እንደነበር በሚገባ ይታወቃል፡፡ የኤርትራ መንግስት ለዓመታት በግላጭ የኢትዮጵያን  ሃብት ሲዘረፍ ኖሮ መንግስታችን ሁኔታዉ ገደቡን በማለፉ በርካታ ማስተካከያ እርምጃ በመዉሰድ ቁጥጥር ማድረግ ሲጀምር በፊት በነበረዉ ብዝበዛ አንጀቱ እያረረ ሲበግን የነበረዉ ህዝባችን የመንግስትን ቆራጥ እርምጃ መዉሰድ በእጅጉ ያስፈነደቀዉ ቢሆንም ያን ተከትሎ ሌላ መዘዝ ሊከተል እንደሚችል ስጋታቸዉንና ጥርጣሬአቸዉን ሲገልጹ የነበሩ አልጠፉም፡፡

መንግስታችን የኤርትራን ብዝበዛ የሚያስቀር ቆራጥ እርምጃ ሲወስድ (የራሱን አሳልፎ ላለመስጠት) ኤርትራ የለመደችዉ ጥቅም ሲቀርባት ሊያስኮርፋትና ሊያስቆጣት እንደሚችል ለመረዳት አያዳግትም፡፡ መንግስታችን ሻዕቢያን በማበሳጨቱና በማስቆጣቱ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስትን አደነቀ እንጂ ለምን ሻዕቢያን አስቆጣህብን ቢሎ አልወቀሰዉም፡፡ ነገር ግን የመንግስት እርምጃ ሻዕቢያን ማስቆጣት መቻሉ ብቻ ሳይሆን ዝርፊያዉ የኤርትራ ዋነኛዉ የገቢ ምንጫቸዉን የሚያደርቅባቸዉ በመሆኑ ዝም ብለዉ ያያሉ ብሎ ማሰቡ ነዉ ትልቁ ስህተት፡፡

የኢኮኖሚ ጥቅም ከድንበር ግጭት የበለጠ የጦርነት ቀስቃሽ እንደሆነ መንግስት በሚገባ ይረዳል፡፡ መንግስታችንም የጦርነቱ መንስኤ የድንበር ጥያቄ ሳይሆን የኢኮኖሚ ጥገኝነት ነዉ ሲልም በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገሮች በብዙ ሺህ ማይሎች ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ጦርነት ዉስጥ ዘለዉ የሚገቡት የድንበር ወይም የወሰን ጉዳይ ሆኖባቸዉ ሳይሆን  የኢኮኖሚ ጥቅማቸዉ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለመከላከል መሆኑ ይታወቃል፡፡

ስለዚህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የዚህ ዓይነት ቆራጥ ዉሳኔ ለመዉሰድ ሲያቅድ ያን ተከትሎ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ተረድቶ አስቀድሞ የመከላከያ ሰራዊቱን የዝግጁነት ደረጃዉ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን እንዲሰሩ ከማድረግ በተጨማሪ በኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ላይ ወይም በቅርብ ርቀት የተወሰነ መልስ ሰጪ ሊሆን የሚችል የተጠናከረ ኃይል ማስፈር ይገባዉ ነበር፡፡ መንግስት ግን ይህን አላደረገም፡፡ ከወትሮዉ የተለየ አንዳችም የጥንቃቄ እርምጃም አልወሰደም፡፡

ሌላዉ ቀርቶ መንግስት በኤርትራ ላይ የዚህ ዓይነት የኢኮኖሚ ቁጥጥር እርምጃ ስለመዉሰዱም በሰራዊቱም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የሚታወቅ ነገርም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ከሻዕቢያ ጋር አድርጎት ስለነበረዉ  የንግድ ስምምነት በድርጅት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ህዝብን በሚወክለዉ ፓርላማ ደረጃ የተወሰነም የሚታወቅም ስለማይመስለኝ ነዉ፡፡ በኤርትራ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ሲጀመርም አሁንም ጉዳዩ በገዢዉ ፓርቲ አመራሮች ደረጃ ካልሆነ በስተቀር እንደ መንግስት በህግ አዉጭዉም ሆነ በአስፈጻሚዉ ካቢኔ ምክር ቤት ደረጃ ምክከር ተደርጎበት የተወሰነ ነገር አይመስለኝም፡፡

ኢህአደግ የኤርትራን ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የሚመለከተዉ የጋራ አጀንዳ አድርጎ ሳይሆን የሁለት ግንባሮች ጉዳይ ብቻ አድርጎ በመቁጠሩ የተፈጠረ ችግር ይመስለኛል፡፡ አስመራና አዲስ አባበ እየተመላለሱ በኢትዮጵያ ስም ድርድር ሲያደርጉ የነበሩት የመንግስት ባለስልጣናት ሳይሆኑ የፓርቲዉ አመራሮች ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ የኢህአዴግ (መንግስት) ሶስት ስህተቶችን እንደፈጸመ መገመት ይቻላል፡፡

አንደኛ ከኤርትራ ጋር ተመስርቶ የነበረዉ ግኑኝነት ዝርዝር ጉዳይ ህዝብ እንዲያዉቅ አላደረገም፡፡ በህግ አዉጭዉም ቀርቦ የተመካከሩበትና የተወሰነበት አይመስለኝም፡፡ ሁለተኛ ይሄዉ ግኑኝነት ሲቋረጥም አሁንም ለህዝቡ አንዳችም ነገር አልነገረም፡፡ ሶስተኛ የኢህአዴግን እርምጃ ተከትሎ በኤርትራ በኩል ሊኖር ስለሚችለዉ ግብረ መልስ (reaction) በሚገባ ታስቦበት ለምናልባቱ ተብሎ እንኳን መከላከያ ሰራዊታችን ተገቢዉን ጥንቃቄ አድርገን አለመዘጋጀታችን እንደ ድክመት መቁጠር የሚገባን እንጂ ድንገተኛ ነዉ የሚያሰኝ አይሆንም፡፡

6.3/ ከጦርነቱ በፊት ኤርትራ ስታደርግ የነበረዉ ወታደራዊ ዝግጅቶች ጦርነት ሊኖር እንደሚችል ከበቂ በላይ አመላካች ነበሩ  

የሻዕቢያን ለወረራ መዘጋጀት ከጥርጣሬም በላይ እንድናምን የሚያደርገን ሻዕቢያ ሲያደርጋቸዉ የነበሩ ወታደራዊ ዝግጅቶች ናቸዉ፡፡  እነዚህ ዝግጅቶች ማንኛዉም አገር ለጦርነት ሲዘጋጅ  የግድ መፈጸም የሚገባዉ ተግባራት እንደሆኑ ስለሚታወቅ ሻዕቢያም ለጦርነት እየተዘጋጀ እንደነበር ከበቂ በላይ አመላካችና ፍንጭ ሰጪ ናቸዉ፡፡  እሰኪ አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ እያልን እንመልከት፤

* ሻዕቢያ ደርግ እንደወደቀ በእጁ ከነበረዉ 85 ሺህ የሚገመት የሰዉ ኃይል ዉስጥ አብዛኛዉን ሰራዊት ቀንሶ ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሱ እርግጥ ነዉ፡፡ ሻዕቢያ ደርግ ከወደቀ በኋላ ከ27 ሺህ የማይበልጥ ሰዉ ኃይል ብቻ ይዞ ነዉ እንደመንግስት የቀጠለዉ፡፡ በዚህ እርምጃዉ ሻዕቢያን ለልማት የቆረጠ አስመስሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በጀመረዉ የብሄራዊ ዉትድርና የግዴታ አገልግሎት አስከ ሰባት ዙር ድረስ አሰልጥኖ ከ117 ሺህ የማያንስ የሠዉ ኃይል ሲያዘጋጅ እንደዋዛ እየሰማን ዝም አልን፡፡ ያን ያህል ወታደር አሰልጥኖ ሲያስመርቅ ሻዕቢያ ከእኛ ለመደበቅ ያደረገዉ ሙከራ አልነበረም፡፡ ሁሉን ነገር በይፋ ነዉ ያደረገዉ፡፡

ስለዚህ ኤርትራ ሰፊ የሠራዊት ዝግጅት እያደረገች መሆኑን መንግስታችን በሚገባ ያዉቅ ነበር ማለት ነዉ፡፡ መጀመሪዉኑ ሃያ ሰባት ሺህ ወታደር ኤርትራን ለምታክል ትንሽ አገር ከሚገባዉ በላይ ብዙ ነዉ፡፡ ኤርትራ እጅግ ደካማ በሆነ ኢኮኖሚያዋ ለዚያዉም አንዳችም የዉጭ ወረራ ስጋት በሌለበት ሁኔታ ያን ያህል ሰራዊት ለኤርትራ እጅግ ብዙ ነበር፡፡ ነገር ግን በጥቂት ዓመታት ዉስጥ ከአምስት እጥፍ በላይ አሰልጥና በይፋ ስታስመርቅ ያለምክንያት እንዳልሆነ መጠራጠር ይገባን ነበር፡፡ ኤርትራ ሰራዊቷን በፊት ከነበረዉ 27 ሺህ ወደ ሩብ ሚሊዮን ከፍ ስታዳርግ ምን አስበዉና ለምን እንደዚያ እንደሚያደርጉ መጠርጠር ይገባን ነበር፡፡

* የኤርትራ የጦርነት ዝግጅት የሰራዊቷን ቁጥር በመሳደግ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ለጦርነት እስፈላጊ የሆነ የዉጊያ አስተሳሰብ ለዉጥ ማድረግንም ጭምር የሚያካትት ነበር፡፡ በዚሁም መሰረት ኤርትራ ሰራዊቷን በፊት ከነበረዉ የጉሬላ (guerilla) ቁመና አላቃ ወደ መደበኛ ሰራዊትነት ቀይራ ከፍተኛ ወታደራዊ ስልጠናና ልምምዶችን ሲታደርግ ቆይታለች፡፡ ከዚያ በኋላም ወታደራዊ አቅሟን በተግባር ለመፈተሽ እዚህም እዚያም የጎረቤት አገሮች ላይ ትንኮሳ በማድረግ እንደ ወታደራዊ ልምምድ (military exercise)ና እንደ ኢላማ መለማመጃ ወረዳ ስትጠቀምበት ነበር፡፡

በዚህም መሰረትም ኤርትራ ከሱዳን፤ ከጂቡቲና ከየመን ጋር በተለያዩ ጊዜያት በራሷ ተንኳሽነት ሲታደረግ የቆየችዉን ግጭቶች የዚህ ማሳያ ናቸዉ፡፡ ኤርትራ ከነዚህ አገሮች ጋር ሲታደርግ የነበረዉን ግጭቶችና የገባችበትን ቅራኔዎች  ለተከታተለ ለማንኛዉም ሃላፊነት ለሚሰማዉ ዜጋም ሆነ ባለስልጣን ቀጣዩ ኢላማ እኛ ልንሆን እንደምንችል ለመገመት ባላዳገተዉ ነበር፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል ለጥንቃቄ ያህል እንኳን ያደረግነዉ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ልክ እንደማያሳስበን ሆነን የኤርትራና የየመን ዉዝግብ በሚዲያዎቻችን ቀዳሚ ዜና አድርገን ከማቅረብ ባለፈ ለመጠርጠር እንኳን አልሞከርንም፡፡

* ኤርትራ በኛ ላይ ጦርነት ከመክፈቷ ትንሽ ቀደም አድርጋና  ጦርነቱን ለመጀመር የመጨረሻዉ የዥግጅት ምእራፍ ላይ እንደደረሰች የሁለት ዓመቱን የብሄራዊ ዉትድርና የግዴታ አገልግሎት ጨርሰዉ ወደ ሰላማዊ ህይወት የተመለሱትን በሙሉ ድጋሚ ጥሪ በማድረግ በአንድ ቦታ አሰባስባ ለሚሰጣቸዉ ግዳጅ እንዲጠባበቁ አድርጋለች፡፡ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም አታስፈልጉም ተብለዉ ከሰራዊቱ የተቀነሱ በርካታ ነባር ታጋዮችንና ሚሊሻዎችን ጥሪ ተደርጎላቸዉ ወደ ካምፕ እንዲከቱ ተደርገዋል፡፡ የዚህ ዓይነት “ክተት ሰራዊት” ሲደረግ በኛ በኩል በሚገባ ይታወቅ  ነበር፡፡

* ኤርትራ በዚህ ዓይነት የኃይል ማሰባሰብ በማድረግ ሃያ ሰባት ሺህ (27,000) የሰዉ ኃይል የነበራትን ባጭር ጊዜ ዘጠኝ እጥፍ አድርጋ ወደ ሩብ ሚሊዮን አካባቢ (232,000) አደረሰችዉ፡፡ ሻዕቢያ ያን ያህል ሰራዊት ማሰባሰቧ ብቻዉን ለጦርነት እየተዘጋጀች እንደነበር የሚያመላክት ነበር፡፡

* ሻዕቢያ ሌሎች ዝግጅቶችንም አጠናክሮ መስራት የጀመረዉ ከጦርነቱ ሰባት ወራት አስቀድሞ ነዉ፡፡ በዚህም መሰረት ለጦርነቱ ብቁ የሚያደርጉ ጠንከር ያሉ ስልጠናዎችን በስፋት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ቴክኒካዊ አቅማቸዉን ለማሳደግ የጥገና ስራ በስፋት ሰርተዋል፡፡ ለጦርነት የሚያስፈልጋቸዉንንና የሚጎላቸዉን ትጥቅ አቅም በፈቀደ ከዉጭ ሸምተዋል፡፡ ስለኢትዮጵያ ወታደራዊ አቋም የተሟላ መረጃ ለማግኘትም እንዲያስችላቸዉም በድንበር አካባቢ ባሉ የኢትዮጵያ ከተሞች ሰፊ የስለላ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

* ከዚህም በላይ ከወረራዉ አንደ ወር በፊት መከላከያ ሚኒስትራቸዉ ከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸዉን ሰብስበዉ ሊጀመር አንድ ወር ብቻ ለቀረዉ ጦርነት የመጨረሻዉን ዝግጅት እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ ለአዛዦች ዝግጀት እንዲያደርጉ መመሪያ ሲሰጣቸዉም ጦርነቱ ከማን ጋር እንደሆነ ለምስጥራዊነቱ ሲባል በግልጽ ባይነግሩአቸዉም አዛዞቹም ሆኑ የሰራዊቱ አባላት ባልተለመደ ሁኔታ ያን ያህል ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ያስፈለገዉ ለየመን ፤ለጂቡቲ ወይንም ከሱዳን ጋር ለሚደረግ  ጦርነት ሳይሆን  ይልቁንም ከኢትዮጵያ ጋር ሊሆን እንደሚችል አልጠረጠሩም ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጁ መሆኑን ጦርነት የተደገሰለት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያለጊዜዉ እንዳያዉቁ ለማድረግ የሻዕቢያ መሪዎች ጥንቃቄ ማድረጋቸዉ ባይቀርም ነገር ግን ያን ሁሉ መጠነ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አንዳችም ጥርጣሬ አለማድረጉ ኢሳይያስን ሳያስገርማቸዉ የቀረ አይመስለኝም፡፡

* የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጀመር ይፋ ከመሆኑ በፊት የኤርትራ ታጣቂዎች ወደ ትግራይ መሬት እየገቡ የነዋሪውን ሀብትና ንብረት መዝረፍ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ ላይ ጥላቻ አላቸዉ ተብለዉ የተገመቱ የአካባቢዉን ሰዎችም ጭምር እያፈኑ በመውሰድ ሲገድሉ  በነበረበት ጊዜ የትግራይ ህዝብ ሁኔታዉ ስላላማረዉ ሻዕቢያ ለጦርነት እየተዘጋጀ  ስለሆነ አንድ ነገር አድርጉ እያለ ለባለስልጣናቱ ሪፖርት ሲያደርግና ሲያስጠነቅቅ ባለስልጣናቱ ግን “ሻዕቢያ በጭራሽ አይወራችሁም”  በሚል የሕዝቡን አቤቱታና ጥቆማ ሲያጣጥሉ እንደነበር በጦርነቱ ወቅትና በኋላም በስፋት ሲነገር ነበር፡፡

ከዚህም ሌላ ከወረራዉ ሶስት ወራት አስቀድሞ በገዥዉ ፓርቲ አመራሮች በተለይም በህወኃት ስራ አስፈጻሚ ደረጃ ኤርትራ ለጦርነት ዝግጅት እያደረገች ነዉ የሚል ሀሳብ በስብሰባ ላይ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም “ኤርትራ ካላበደች በስተቀር አታደርገዉም” በሚል ሃሳቡ ዉድቅ እንደተደረገ ተሰምቷል፡፡ በወቅቱ በአስመራ ተመድቦ የነበረዉ አመባሳደራችን አቶ ሃዉአሎም ወልዶ (የአቶ አባይ ወልዱ ወንድም) ኤርትራ እያደረገች ስለነበረዉ የጦርነት ዝግጅት በጭራሽ አላውቅም ነበር ብለዉ እንደማይናገሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ኤርትራዉያን ከጠበቁት በላይ መዘናጋታችንን ከተረዱ በኋላ አንዳችም ዝግጅት ሳናደርግ በድንገት ወረራ ፈጸሙብን፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ጭብጦች መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራን የጦርነት ዝግጅት ለማወቅ የማይሳነዉ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ይብዛም ይነስም መረጃዉ እንደነበረዉ ነገር ግን ተገቢዉን ጥንቃቄ ማድረግ እንደተሳነዉ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ምናልባት የኤርትራ መንግስት ከጦርነቱ በፊት ሲያደርግ የቆየዉን ሰፋፊ የጦርነት ዝግጅቶች ለኢትዮጵያ መንግስት የተሰወሩና የመረጃ ሰዎቻችንም ጭራሽ ያልደረሱበት ምስጢር ከነበረ በመረጃ ተቋሙ አመራሮች አካባቢ ድክመት እንደነበረ መቀበል ይገባል፡፡

መንግስት ስለሻዕቢያ  የጦርነት ዝግጅት በቂ መረጃ እያለዉ ነገር ግን መረጃዉን በመጠራጠር ወይም ሻእቢያዎች አብደዉ ካልሆነ በስተቀር አያደርጉትም የሚል አቋም ይዞ ከነበረም መንግስት የግምገማ ችግር እንደነበረበት አምኖና በዝግጅት ማነስ ለጠፋዉ ህይወትና ንብረት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ በመጠየቅ ለወደፊቱ ትልቅ ትምርት እንዲሆን ማድረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡

የብዙ ሀገሮችን የጦርነት ታሪክ ስንዳስስ ከተጠቀሰዉ ከኛ ሁኔታ ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ የሆነ ችግሮችን እናገኛለን፡፡  የብዙ ሀገራት መሪዎች በሀገራቸዉ ላይ የዉጭ ወረራ እንደታሰበ የሚገልጹ አስተማማኝ መረጃዎች እየተሰጣቸዉም ቢሆን  መረጃዉን በማጣጣልና ችላ በማለት  አንዳችም ዝግጅት ሳያደርጉ ለጥቃት ሲጋለጡ እንደነበር በብዛት ተጽፎ አንብበናል፡፡

ለመሪዎች መዘናጋትና መረጃዎችን ችላ ማለት ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያቶች ዉስጥ፤ በወራሪ አገር መሪዎች በሚገቡላቸዉ ቃል በመታለል አስመሳይና አዘናጊ የሆኑ ዉሎች ላይ አጉል መተማመን፤ የራስን መረጃ ተቋም በማናነቅ ትክክለኛ መረጃዎች ላይ አለመተማመንና መረጃዉን በደንብ ሳያገናዝቡ ማጣጣል እንዲሁም  አርቆ ማሰብና ማመዛዘን በተሳናቸዉ “የቅርብ አማካሪ” በሚባሉ ጥቂት የአመራሩ የቅርብ ሰዎች ሃሳብ መጠለፍ ናቸዉ፡፡

ምናልባት ይህን ሃሳብ ለማጠናከር ሁለት አብነቶችን ቀጥዬ አቀርባለሁ፡፡ አንደኛዉ በ2ኛዉ የአለም ጦርነት ወቅት የናዚ ሰራዊት በሶብዬት ህብረት ላይ የሰነዘረዉን ጥቃት የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ በባህረ ሰላጤዉ ጦርነት የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ኩዌትን የወረረበትን ጦርነት የሚመለከት ነዉ፡፡

ሀ. የናዚ ወረራ

 በ2ኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ ሰራዊት ሶቭየት ህብረትን የወረረዉ በድንገትና ሳይጠበቅ ሳይሆን ለወረራ እየተዘጋጀ መሆኑ ከበቂ በላይ መረጃ በነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሂትሌር ሶቭየትን ለመዉረር እንዳሰበ የሶቭየት የመረጃ ሰዎች ለጥቃት የተመረጠዉን አቅጣጫና መቼ ጥቃቱን ለመሰንዘር እንደታሰበ ሳይቀር ለሶቭየቱ መሪ ስታሊን በተደጋጋሚ መረጃ ቢያቀብሉም መረጃዉን በማጣጣልና ከራሱ ሰዎች ይልቅ ሂትለርን በማመን ያለአንዳች ዝግጅት ተዘናግተዉ ቆዩ፡፡

ስታሊን ከሂትለር ጋር አድርጎት የነበረዉን ምስጢራዊ ስምምነት በመተማመን አንዳችም ዝግጅት ሳይደረግ  በመቆየቱ ሀገሪቱ ለናዚ ሰራዊት ጥቃት ክፉኛ ተጋለጠች፡፡ የናዚ ጀርመን ሰራዊትም ልክ እንደታሰበዉና የመረጃ ሰዎች እቀድመዉ በገመቱት አቅጣጫና ቀን ማጥቃት ሰነዘረ፡፡ የሚገርመዉ ደግሞ ጥቃት መሰንዘሩ ከታወቀም በኋላ እንኳን አንዳችም የአጸፋ እርምጃ እንዳይወስዱ ስታሊን መከልከሉ ነዉ፡፡

የስታሊን ግምት ከጦርነቱ በፊት ከሂትለር ጋር ያደረገዉ አንዱ ሌላዉን ያለመዉጋት ምስጥራዊ ስምምነት (Hitler-Stalin non agration pact) በመተማመን በሂትለር ቃል ተሸዉዶ ሲሆን ዝግጅት እንዳይደረግ የከለከለዉ ደግሞ ሁኔታዉን በጣም አቅልሎ በማዬትና የእለት ግጭት እንጂ ጦርነት ስላልሆነ አላስፈላጊ ከሆነ የጠብ አጫርነት ድርጊት ተቆጠቡ እያለ አዛዦቹን ይገስጽ ነበር፡፡ ስታሊን ከራሱ ሰዎች ይልቅ ለወረራ የተዘጋጀዉን ጠላቱን ሂትለርን በማመኑ ከሃያ ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎቹን ህይወት አስከፍሎታል፡፡

ስታሊን ከራሱ መረጃ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ከነበሩት ፍራንክሊን ሩዝበልት ሳይቀሩ ሂትለር ፈረንሳይን ከወረረ በኋላ ቀጥሎ ሶቭየትን ለመዉረር እቅድ እንዳለዉ ለስታሊን በምስጢር አሰጠንቅቀዉት ነበር፡፡ የተባለዉም አልቀረም ጁን 22 ፡1941 ዓ/ም ሂትለር በዓለም የጦርነት ታሪክ በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ የለለዉን በሚሊዮን የሚቆጠር ኃይል አሰልፎ ሶቭዬት ህብረትን ወረረ፡፡ ከጦርነቱ  ቀደም ብሎ ማለትም በ1937 እና በ1938 ላይ ስታሊን “ግሳንግሱን ሁሉ ማጽዳት” (purge) በሚል በሚታወቀዉ የጭፍጨፋ ዘመቻ በርካታ የሀገሪቱን ከፍተኛ የጦር አዛዦችን ያለምንም ምክንያት በማስገደሉና ወደ ሳይቤሪያ በግዞት በመላኩ ጦር ኃይሉ ያለ አመራር በመቅረቱ እጅግ ተዳክሞ በነበረት ሰዓት ነዉ ወረራዉ የተጀመረዉ፡፡

በወቅቱ ሂትለር የስታሊንን መዘናጋት በመጠቀም በርካታ ሰራዊት በሶቭዬት ህብረት ድንበር አካባቢ ማከማችት ከመቻሉም ሌላ የጀርመን አይሮፕላኖችም የሶቭየት የአየር ክልል ጥሰዉ በመግባት እንዳሻቸዉ የአየር ቅኝት እያደረጉ መሆናቸዉ ሪፖርት እየተደረገለትም ሂትለር የሚሰጠዉን የሃሰት ምክንያት እየሰማና የራሱን መረጃ ሰዎች ችላ በማለት ሀገሩን ለጥቃት አጋለጠ፡፡ ሂትለር “operation Barbarossa” ዘመቻ ባርባሮሳ የሚል ስያሜ በተሰጠዉ ዘመቻ በሶቭየት ድንበር በኩል ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ ወታደሮችን  አሰልፎ ጥቃት ሰነዘረ፡፡

ስታሊን ቢያንስ መረጃዉ ከደረሰዉ ጊዜ ጀምሮ  በቂ ዝግጅት አድርጎ ቢሆን ኖሮ ያን ያህል ጉዳት በህዝቡ ላይ ባልደረሰ ነበር፡፡ የሶቭየት መንግስት ዝግጅት ላለማድረጉና ለመዛናጋቱ ማሳያ የሚሆነዉ በወረራዉ የመጀመሪያ ሳምነት ብቻ 150000 በላይ የሶቭየት ህብረት ወታደሮች ማለቃቸዉና  ሉፍትወፍ (Luftwaffe) በተሰኘዉ የሂትለር አየር ኃይል  በሁለት ቀን ብቻ በቁጥር ከ2000 የሚበልጡ  የሶቭየት ህብረትን የጦር አይሮፕላኖችን  ገና መሬት ላይ እያሉ መዉደማቸዉ ነዉ፡፡ ሂትለር የንቀቱ ንቀት ሶቭየት ህብረትን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ስምንት ሳምንታት ብቻ ነበር የመደበዉ፡፡

በወቅቱ ብዙዎቹ የዉጭ ታዛቢዎች  ሁኔታዉን በመገምገም መላዋ ሶቭየት ህብረት በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ዉስጥ በጀርመን ቁጥጥር ስር እንደምትሆን ገምተዉ ነበር፡፡ ጀርመኖች በአጭር ጊዜ ዉስጥ ያን ሁሉ ሰፊ የሶቭየት ህብረትን ግዛት አቆራርጠዉ ሌንንግራድ (ፒተርስበርግ)ና ከዋና ከተማዋ  ከሞስኮም  በ25ኪ/ሜ ርቀት ላይ ለመድረስ ችለዉ ነበር፡ስታሊን ዘግይቶም ቢሆን  በኋላ ላይ ስህተቱን አርሞ  በጠቅላይ አዛዥነቱ  የሚደነቅ አመራር በመስጠቱ የጀርመንን ናዚ ሰራዊትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ከሶቭየት ህብረት ግዛት በማስወጣት ብቻ ሳይገደብ ምስራቃዊዉን የጀርመን ግዛት ዋና ከተማዉን በርሊን በቁጥጥሩ ስር በማድረግና መላዉን የምስራቅ አዉሮፓን አገሮችን ነጻ በማዉጣት ታሪክ የማይረሳዉ ታላቅ ስራ ስርቷል፡፡

በዚህም በሀገሩ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በምእራቡም ጭምር ታላቅ አድናቆት ተችሮታል፡፡ ይሁን እንጂ ስታሊን ስለ ናዚ የጦርነት ዝግጅት በግልጽ አየተነገረዉ ችላ በማለቱ ሂትለርን ለወራራ እንዳያስብ የማድረግ እድሉን ባለመጠቀሙ  በሀገሩ ላይ ለደረሰዉ መጠነ ሰፊ ጉዳት ጦርነቱ ካለፈ ከሰባ ዓመታት በኋላም አስካሁንም  ከመወቀስ አልዳነም፡፡

ለ. የሳዳም ሁሴን የኩዌት ወረራ

ሌላዉ አብነት በመጀመሪያዉ የባህረ ሰላጤዉ ጦርነት ወቅት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቡሽ (ትልቁ) በወቅቱ የእራቁ ሳዳም ሁሴን የአሜሪካ ወዳጅ የነበረችዉን ኩዌትን ለመዉረር እየተዘጋጀ መሆኑን መረጃዉ በተደጋጋሚ ቢቀርብላቸዉም የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አማካሪዎች መረጃዉን በማጣጣላቸዉ ፕሬዝደንቱ አንዳችም እርምጃ ባለመዉሰዳቸዉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሳዳም ሁሴን ጦር ኩዌትን ሙሉ በሙሉ በወረራ ተቆጣጠራት፡፡ ፕሬዝዳንቱ በደረሳቸዉ አስተማማኝ መረጃ መሰረት ተገቢዉን የዲቴረንስ እርምጃ አስቀድመዉ ወስደዉ ቢሆን ኖሮ ሳዳም የጥቃት ዉጥናቸዉን በሰረዙ ነበር፡፡ ያ ሁሉ ግርግርና ትርምስም ባልተፈጠረ ነበር፡፡

በዚህ አጋጣሚ የመሪዎች አማካሪዎች የሚባሉ ሰዎች ጉዳይ አጠያያቂ ነዉ፡፡ ምንድነዉ የሚያማክሩት?ስራቸዉ መልካም ነገር ማማከር ሳይሆን ማሳሳት የሆነ ይመስላል፡፡ አስቀድሜ ባነሳሁት ታሪክ ቡሽን አሳስተዉ እርምጃ እንዳይወስዱ  አደረጉት፡፡  ከጥቂት ጊዜ በኋላ በትንሹ ቡሽ ጊዜ ደግሞ የሌለዉን ነገር እንዳለ በማድረግ ኢራቅ የኑክሌር መሳሪያ አላት በሚል የተሳሳተ መረጃ አቅርበዉ  በቀሰቀሱት ጦርነት ጦስ እነሆ ኢራቅ መሪዋን ሳዳምን ማጣት ብቻ ሳይሆን  አገሪቷም ራሷ ተንኮታኮተች፡፡ በኛም ሁኔታ መለስን በማሳሳት በኤርትራ ጉዳይ ያዘናጉት የቅርብ ሰዎቻቸዉ እንደሆኑ እንገምታለን፡፡

7/ ማጠቃለያ

የኤርትራ ጥቃት በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህዝቡም ቢሆን ፈጽሞ ያልተጠበቃና ይሆናል ተብሎም ያልተገመተ ነዉ፡፡ የወረራዉ ድንገተኛነት እንዳለ ሆኖ በኛ በኩል እንደ መንግስት ማድረግ የሚገባንን ተገቢዉን ጥንቃቄ ባለማድረጋችን ለኤርትራ ጥቃት ሰለባ ለመሆን ችለናል፡፡ መንግስት የኤርትራን አመራሮች ባህሪይ በሚገባ እያወቀና ኤርትራ ከሁሉም አጎራባች ሀገሮች ጋር አንድ በአንድ ጦር ስትማዘዝ እያየ ይሄ ነገር ነገ ተራዉ ለኛ ነዉ ብሎ አለመጠንቀቁ እንደ መንግስት ጥፋተኛ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ከዚያ ዉጭ ግን መንግስት ከኤርትራ ጋር መልካም ጉርብትና መመስረቱና መረዳዳቱ እንደጥፋት ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በሚመለከትም ለዘለቀታዉ ለስተራቴጂክ ደረጃ ለሚገመት ጠላት አነስ ብሎ በግዳጅ አፈጻጸሙ ጠንካራ የሆነ ሰራዊት ለመገንባት ጥረት እያደረገ ስለነበረ ”የሀገሪቱን መከላከያ  ሰራዊት አፍርሶ ለጥቃት አጋልጦ ወዘተ “የመሳሰሉት ትችቶች ተገቢነት የለላቸዉና የመንግስትን ባህሪይ የማይገልጹ ናቸዉ፡፡

********

(የዚህን ፅሁፍ ቀጣይ ክፍሎች በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories