ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ዴሞክራሲ

ሺህ አለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ በቢቢሲ ሬድዮ “News Hour” ፕሮግራም ላይ “As an African citizen, democracy is a luxury…” በሚል የሰጠው አስተያየት በተለይ በማህበራዊ ድረፆች ላይ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በመጀመሪያ ለአስተያየቱ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር፡፡ የሃይሌ አስተያየት በቅን እሳቤ የተሰጠና የግል አመለካከቱን ያንፀባረቀበት እንደሆነ ተደርጎ ቢወሰድ ኖሮ፣ ነገሩ ይህን ያህል ትኩረት የሚሰጠው አልነበረም፡፡ ነገር ግን፣ የቢቢሲ ሬድዮ ከላይ የተጠቀሰውን ዓ.ነገር የቃለ-ምልልሱ ዋና ጭብጥ እንደሆነ አድርጎ ያቀረበበት ሁኔታ፣ ከአስተያየቱ በስተ-ጀርባ ያለው እሳቤ እና አሁን በሃገራችን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም የአትሌቱ ስብዕናና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና ለአስተያየቱ እየተሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና ትርጓሜ፣ …ወዘተ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ያለኝን አሰተያየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

Photo - Screenshot of BBC news on Haile Gebrselassie

በመጀመሪያ ደረጃ፣ አስተያየቱ አሁን እንደሚታየው አነጋጋሪ እንዲሆን ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዘው ቃለ-ምልልሱ የተዘገበበት ሁኔታ ነው፡፡ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ቲም ክላርክ ከአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ፤ አትሌቱ ከሩጫው አለም ከተገለለ በኋላ ስላለው ህይወቱ፣ በአትሌትክሱ ዓለም ከአበረታች ዕፅ ጋር ተያይዞ ስለሚታየው ችግር፣ እና ሃይሌ በቢዝነሱ አለም እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ከጠየቀ በኃላ ነው ለአወዛጋቢው ምላሽ መነሻ የሆነውን የፖለቲካ ጥያቄ የሚያነሰው፡፡ ስለዚህ፣ ለምሳሌ ከውድድር ራሱን ካገለለ በኋላ እንኳን የተለመደውን የሩጫ ልምምድ (Training) አሁንም እየሰራ መሆኑ፣ አበረታች-ዕፅ መጠቀም አዲስ ወደ አትሌትክሱ አለም በሚገቡ ታዳጊዎች ስነ-ልቦና ላይ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ የተናገረው፣  ወይም ደግሞ በተለያዩ የቢዝነስ መስኮች በመሰማራት 1700 ሰራተኞች ያሉት ግዙፍ ቢዝነስ አንቀሳቃሽ መሆኑ የዘገባው ዋና ሃሳብ ተደርጎ ሊቀርብና በአርዓያነት ሊያስጠቅሰው ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ የተጠቀሱት በጎ ተግባራት ሚዲያው ላለበት የተቃርኖ ዜና ጥማት አርኪ አይደሉም፡፡ ነገር ግን፣ ለሀገሪቱ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር አንፃር ሺህ አለቃ ሃይሌ ብቻውን እንደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ካለ ትልቅ መንግስታዊ ተቋም እኩል መሆኑ በራሱ እንደ ትልቅ ነገር ሊዘገብ የሚችል ነገር ነው፡፡

ሁለተኛው ነገር፣ ለአወዛጋቢው አስተያየት መነሻ የሆነው ጥያቄ የቀረበበት ሁኔታ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ጥያቄውን ያቀረበው የቢዝነስ ሥራ ለመጀመር ካላቸው አመችነት አንፃር የአለም ባንክ ያዘጋጀውን ሪፖርት አስታውሶ፣ “ኢትዮጲያ ከ189 የአለም ሀገራት 176ኛ መሆኗን በመጥቀስ፣ ችግሩ ሃይሌ በሚያደርገው የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይም እንቅፋት ሆኖበት እንደሆነ?” ነበው የጠየቀው፡፡ ሃይሌ ለጥያቄው በሰጠው ምላሽ፣ “የተጠቀሱት ተግዳሮቶች ሁሉ እንዳጋጠሙት እና ይህንንም መደበቅ እደማይችል….ነገር ግን፣ እናት አመሏ የማይመች ስለሆነ ብቻ እናትነቷን መካድ ወይም ደግሞ በምን-አገባኝ ስሜት እናትን መተው እንደማይቻል፣…እሱም ደግሞ ሀገሩ ኢትዮጲያ የተጠቀሱት ችግሮች ስላሉባት “ምን-አገባኝ” ብሎ ሥራውንና ኑሮውን ምቹ ወደ ሆኑ ሀገራት ይዞ እንደማይሄድ ገልጿል፡፡ እዚህጋ ነው እንግዲህ፣ ሃይሌ “As an African citizen democracy is a luxury…” (እንደ አንድ አፍሪካዊ ዴሞክራሲ [ለእኔ]ቅጦት ነው” በማለት በማለት አወዛጋቢውን ዓ.ነገር የተናገረው፡፡ ከላይ ከተጠቀሰው የንግግር ሁኔታ (context) አንፃር ሲታይ ሃይሌ የተጠቀሰውን ዓ.ነገር የተናገረበት አግባብ [“ከሕግ-ማዕቀፍ፣ ከሥራና አሰራር ቅልጥፍና፣ ከግልፅነትና ተጠያቂነት፣ ከሰለጠነ የሰው-ሃይል አቅርቦት፣….ወዘተ መስፈርቶች አንፃር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸው ሀገራት የቢዝነስ ሥራ ለመጀመር አመቺ ናቸው” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመሆኑም፣ “በኢትዮጲያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ቀልጣፋ የሆነ የአሰራር ሥርዓት እስካልተዘረጋ ድረስ ሥራና ኑሮዬን በውጪ ሀገር አደርጋለሁ” ብዬ አልቀናጣም፡፡ ሀገሬን ከነችግሮቿ ተቀብዬ ለመቀየር የተቻለኝን ያህል ጥረት አደርጋለሁ እንጂ “ዴሞክራሲ ቢኖር ኖሮ” በሚል የቢሆን-አለም እሳቤ ምንም ሳላደርግላት ማለፍ አይቻለኝም] የሚል ነው፡፡

በመጨረሻ ከግንዛቤ መግባት ያለበት ነገር የሃይሌ የፖለቲካ ግንዛቤ ደረጃ ነው፡፡ በእርግጥ ሃይሌ ለዚህ ሀገር ውለታው እጅግ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከተወሰኑ አመታት በፊት የቢቢሲ ጋዜጠኛ “in Ethiopia, Haile is a living God” በማለት ነበር የገለጸው፡፡ ለእኔ ሃይሌ አትሌት ብቻ ሳይን የድል አድራጊነት ምልክት፣ ሀገር ጌጥ ነው! ይሁን እንጂ፣ በግንዛቤ ደረጃ ሆነ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን አምባገነንነት ከመታገል አንፃር ያበረከተውን አስተዋፅዖ ከግል ስብዕናው እና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሙ አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ፣ በተመሳሳይ ፕሮግራም ላይ አስተያየቱን የሰጠው የዞን-ዘጠኝ ጦማሪያ ቡድን አባል በፍቃዱ እጅግ በሳል የሆነ ግንዛቤ እንዳለው ያሳየ ከመሆኑም በላይ ይህን አምባገነንና ጨቋኝ መንግስታዊ ሥርዓት በመታገሉ ረገድ ከፍተኛ መስዕዋት እንደከፈለ መረዳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ፣ ሺህ አለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ታላቅ ሯጭ፣ እንዲሁም ታላቅ የቢዝነስ ሰው እንደሆነ አለም የመሰከረለት ነው። ነገር ግን፣ የዜጎች መብትና ነፃነት በገፍ በሚጣስበት ሀገር “ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው” ዓ.ነገር እንዲሁ በደረቁ ከተወሰደ  “ዴሞክራሲ” የሚለው ቃል ሃይሌ ከከፈታቸው ምርጥ ሆቴሎች  የአንዱ ሆቴል ስያሜ ነው የሚመስለው።
*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories