ህልሜና የኤርትራ ነባራዊ ሁኔታ

(አማኑኤል አለማየሁ)

ወደ ሰማይ ቀና ብየ ሳይ እጅግ የጠቆረ ደመና እና ጥላሸት የመሰለ ካፊያ ያካፋል፡፡ ከካፊያው ለመሸሽ እየሮጥኩ ስሄድ እጅግ ትልቅ ወንዝ የሚመስል ከፊት ለፊቴ ጠበቀኝ ካፊያው እና የደመና ጥቁረት እየጨመረ ወንዙን ተሻግሮ እኔ የነበርኩበት ቦታ አልፎ ከወንዙ ማዶ ጥቁሩን ዝናብ ከረመጥ ጋር ቀላቅሎ ጣለው፡፡ እኔ ያለሁበት የወንዙ ሌላኛው ማዶ ግን ብራ እየሆነና ጥቁር ደመናው እየ ተገፈፈ ይታየኝ ጀመር፡፡ እሩቅ ማየት ያስቸግር የነበረው እየተገፈፈ አርቄ ማየት ጀመርኩ በዚህ ማሃል “አባቢ አባቢ” ብላ ትንሸ ልጂ ከእንቅልፊ ቀሰቀሰችኝ ያሁሉ ያየሁት ህልም ነው ለካ፡፡

ያው ህልም እንደፈቺው ነው እደሚባው እኔም ያለምኩትን ነገር መፍታት ጀመርኩ እና፡- ያጥቁር ደመና ጦርነት ነው ብየ ፈታሁት፣ ካፊያው ተኩስ፣ የጥፋት አረር ነው ብየ ተረጎምኩት፣ ስሮጥ ያገኘሁት ትልቅ ወንዝ ቀይ ባህር ነው አልኩት ማዶ ተሸግሮ እሳት (ረመጥ) ጨምሮ የዘነበው ቀይባህር ማዶ ያለ እየወረደ የሚገኘው ወይም በደመና መልክ ያረገዘ የሰው ልጅ እልቂት በየመን ምድር ነው ብየ ህልሜን (ቅዠቴን) ፈታሁት፡፡

ይህ ሰሞኑን በኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስቴር በዶ/ር አብይ አሕመድና በፕሬዜዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈረመውና ለ20 ዓመታት በሁለት ወንድማማች ህዝቦች መካከል አንዣቦ የቆየውን በዶ/ር አብይ አገላለፅ “ሞት አልባው ጦርነት” በህልሜ እንዳየሁት ጥቁር ደመና እና ካፊያ መስል አረር ተርጉሜ ከኢትዮጲያና ኤርትራ ድንበር ቀስበቀስ ሲለቅ ያየሁት እንዳየሁት አድርጌ ተረጎምኩት፡፡ ይህ ከድንበራችን ለቆ የሄደው ደመና ግን ባህር ተሻግሮ ቀይ ባህር አልፎ ጥቁረቱ ጨምሮ ዶፍ ዝናብ ሆኖ ረመጥ ጨምሮ ሲዘንብ ያየሁት እዚያ ማዶ የመን ምድር ላይ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት መፍትሄ ዙርያ እስከ አሁን በኢትዮጲያ መሪ ሆኖ ችግሩን በሰላም እንፍታው የሚል ጥያቄ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ያላቀረበ አልነበረም፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ ሬድዮ አሰና የተባለ ጣቢያ ባለቤት አቶ አማኑኤል እያሱ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውንና ይህንኑም ለተባበሩት መንግስታት በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ገልፀውለታል፡፡ በተጨማሪም በሞ-ኢብራሂም ፋውዲሽን አመታዊ ስብሰባ የተገኙት ሌላው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጉዳዮን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጲያ መንግስት መቀበሉን ጠቅሰን ለተባበሩት መንግስታት በተደጋጋሚ ማመልከቻ አስገብተናል ነገር ግን በኤርትራ በኩል ጀሮ ዳባ ልበስ ነው ያገኘነው መልስ ሲሉ በመድረኩ ገልፀዋል፡፡ ከነዚህ ሁለት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴሮች ቃል እና ማብራርያ የወሰድኩት እውነታ ቢኖር ኢትዮጲያ ችግሩን በአልጀርስ ስምምነት መሰረት ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ታደርግ እንደነበር ነው፡፡ አልቀበልም አሻፈረኝ ያለው የኤርትራ መንግስት መሆኑ ነበር፡፡

አሁን ምን ተፈጠረ?

የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለሪካዊ ሁኔታ ብዙዎቻችን እንደምናየው በፍጥነት እየተቀያየረ ይገኛል፡፡በጎረቤት አገር ጅቡቲ ውስጥ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና ጃፓን የጦር ሰፈር ገንብተው ቀይባህርን በተለይ ደግሞ ባብ አል መንደብ የተባለውን መተላለፊያ ይቆጣጠራሉ፡፡ በተጨማሪም ቱርክ በሶማሊያ እና በሱዳን በተመሳሳይ የጦር ካምፕ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ትገኛች፡፡ ከቱርክ በተፃራሪ ከቆሙት አገራት ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሳኡዲ አረብያ በኤርትራ የጦር ካምፕ በመስራትና በአካባቢው ወታደራዊ ፍጥጫ ተሳታፊ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከየመን ጋራ መውጣቱ ያስቸገራቸው የጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም በየመን ውስጥ ባለው ጦርነት ኢራን የሑጢ አማፅያንን ትረዳለች ታስታጥቃለች ተብላ ከመታማቷ በተጓዳኝ የሑጢ አማፅያን በቀላሉ በሳኡዲ መራሽ የጥምረት ሃይሎች ሊሸነፉ የሚችሉ አልሆኑም ከጊዜ ወደጊዜ አቅማቸው እያጎለበቱ ሳኡዲ አረብያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሊወጡት እማይችሎት አዘቅጥ ውስጥ ከተዋቸዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ቀጣና እጅግ ውስብስብ ባለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ግጭትና ውዝግብ የተሞላ ሆኗል፡፡ በዚህ እጅግ ውጥንቅጡ በወጣ ቀጣና ውስጥ አስፈላጊ ሚና ልትጫወት የምትችል አገር ብትኖር በቀዳሚነት ኤርትራ ናት፡፡ ኤርትራ በዚህ ቀጠና ውስጥ የተፈላጊነቷን ሚና እንድትጫወት ከተፈለገ ደግሞ፡-
* ከኢትዮጲያ ጋር የገችበትን ፍጥጫ ማስወገድ
* ከወደቦችዋ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራት ማድረግን
* በአለማቀፍ ደረጃ ያላት የጠለሸ ስም ማስተካከል
* የኤርትራ ጦር ሰራዊት ለግዳጅ ዝግጆ የሚሆነበት ቁመና ላይ እንዲገኝ ለማድረግ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ምሽግ ነፃ እንዲሆን ማድረግን
* የኤርትራ መንግስት ጦር ሰራዊቱን በበቂ ማስታጠቅ እዲችል በኢትዮጲያ መንግስት ጠያቂነት የጦር መሳርያ ማእቀቡ እንዲነሳ ማድረግን
የመሳሰሉት ሌሎቸ ቅድመ ሁኔታዎች እጅግ አስፈላጊ እርምጃዎችን በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸው ሲሆኑ የኤርትራ መንግስት በቀጠናው ያለውን ተፈላጊነት አሁን አገሪቱ ባለችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ቁመና ሆና መወጣት እንደማትችል በማመን አስፈላጊ እርምጃዎች መውሰድን የግድ ይለዋል፡፡

የመን እና ቀጠናው

የመን አሁን ባለችበት ሁኔታ የአለማችን 40% (አርባ ከመቶ) የሚሆን ንግድ እና የንግድ መርከቦች የሚንቀሳቀስበትን የቀይ ባህር፣ የየመን ባህር ሰላጢ እና የህንድ ውቅያኖስ ለመቆጣጠር የሚያስችል ቁልፍ (strategic) ቦታ ያላት አገር ናት፡፡ ይህ አለማቀፍ ተፈላጊነቷም እኔ እቆጣጠር እኔ በሚል የሃያላን እና ሃያላን መሰል አገሮች ሽኩቻ አሁን ወዳለችበት መቀመቅ የከታታት ከመሆኑም በላይ ጥቅማችንን እናስከብራለን ብለው ወደ የመን የገቡት የተባበሩት ሃይሎች (the coalition forces) እየተባሉ የሚታወቁት ሳኡዲ መራሽ አገሮች ተገብቶ የማይወጣበት ማጥ ሆናባቸዋለች፡፤

ጦርነቱ የጀመረበትን ወቅት እንተወውና የቅርቡን አራት ወራት በተለይ ያለፈውን አንድ ወር እንቅስቀሴ (development) ብናይ የተባበሩት አገራት የመውጫ በሩ ከገቡበት በር እጅግ የጠበበ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሳኡዲ መራሹ ሃይል ከሶማልያ፣ ከሱዳን እንዲሁም ከፓኪስታን በቀጠሯቸው ወታደሮች አማካኝነትና በአሜሪካና እንግሊዝ እጅግ ውስብስብ የጦር መሳርያ አስታጣቂነት የጀመሩት ጦርነት የመንን እንዳልነበረች ከማፈራረሱ በተጨማሪ አንዱ የአረብ አገር በሌላው የአረብ አገር ላይ ምን ያክል የጭካኔ በትር ለማሳረፍ እንደማያቅማማ ማሳያ ነው፡፡

* ዶ/ር አብይ አሕመድ April 2/2018 የኢትዮጲያ ጠ/ሚር በመሆን ቃለ ማሃላ ፈፀሙ እንዲሁም ለኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪ አቀረቡ
* May 18/2018 ዶ/ር አብይ አሕመድ ሳኡዲ አረብያ ጎበኙ
* May 20/2018 ዶ/ር አብይ አሕመድ የተባበሩት አረብ ኤምሬትን ጎበኙ
* June 5/2018 የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት በአልጀርስ ስምምነት መሰረት እዲጠናቀቅ ውሳኔ አሳለፉ
* June 12/2018 በሑጢዎች ቁጥጥር ስር ያለቸውን ሆዴድ ፖርት ለመቆጣጠር የሳኡዲ መራሹ ህብረት ያልተሳካ ማጥቃት አደረጉ
* የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ አልጋወራሽ ልኡል ሼክ ቢንዛይድ ኢልናሕያን ኢትዮጲያን የዒድ አልፈጥር ቀን June 15/2018 ጎበኙ
* June 20/2018 የኤርትራውን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጲያን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን በመግለፅ ልኡክ ወደ አዲስ አበባ እደሚልኩ አስታወቁ
* June 26/2018 በአቶ ኦስማን ሳልሕ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ የልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ
* July 3/2018 የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አቡዳቢን በመጎብኘት ከልኡል አልጋ ወራሹ ጋር ተገናኙ
* July 8/2018 የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒሰቴር ዶ/ር አብይ አሕመድ አስመራን በመጎብኘት ለ20 አመታት አፋጦና ጦር አማዞ የነበረውን የድምበር ግጭት ማብቃቱን የሚያበስር ጉዞ አደረጉ፡፡

በዚህ ጉዞ በዋናነት አጀንዳ ሆኖ የቀረበው ከድንበር ማካለል በበለጠ የህዝብ ለህዝብ ግንኝነት (normalization) ሂደቱን ማፋጠን ነበር፡፤ በዚህ መሰረት የሁለቱ አገሮች የቀጥታ ስልክ፣ የአየር መንገዶች በረራ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እዲሁም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፍጥነት ለመጀመር መስማማታቸው ነው፡፤

ከላይ የገለፅኳቸው አስር ነጥቦችና ጉብኝቶች እንዲሁም ያልተገለፁ ሌሎች ጉዳዮች ገጣጥመን ብናነብ፤ በኢትዮጲያና ኤርትራ ብቻ ሳይሆን ግጭት ላይ በነበሩ ሁለት አገራት ታሪክ እጅግ በፍጥነት እና ያለማቋረጥ ከፍተኛ ለውጥ የታየበት አንድ ወር ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቲር ዶ/ር አብይ አሕመድ ይህ በተመቻቸ እድል (chance on a silver plate) ማለፍ የፈለጉ አይመስሉም በመሆኑም እጅግ ቀርፋፋና አካባቢውን አንብቦ ለመረዳት የሚቸገረውን እና በዘገምተኛነት አጋጣሚውን ሊያሳልፈው ከሚችለው የስራ አስፈፃሚም ይሁን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጋር በመወያየት ጊዜ ለማጥፋት የፈለጉ አይመስሉም፡፡ በመሆኑም ሁኔታዎችን በፍጥነት አንብበው ተጠቅመውበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ለኤርትራ እና ለኢትዮጲያ ምን ጥቅም አለው፡-

በዋናነት የኢትዮጲያ ጥቅም ሰራዊቷን ከአካባቢው በማስወጣት በአንዳድ የማህል አገር አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉትን የሰላም መድፍረስ ለመቆጣጠር ከመጠቀሟም በላይ ጦር ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ሁኔታ (stand by status ላይ በመሆኑ ምክንያት አገሪቱን ከሚያስወጣት ከፍተኛ ወጪ ከማዳኑም ባሻገር በአካባቢው ሰላም በመፈጠሩ ምክንያትና በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል በሚፈጠረው የተስተካከለ ግንኙነት በተለይ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው አካባቢ የተቀላጠፈና በአነስተኛ ወጪ የወደብ አገልግሎት እንዲያገኝ የረጋል፡፡

ኤርትራ

ኤርትራ ደቡባዊ የአገሪቷ ክፍል ከጦርነት ስጋት ነፃ እንድትሆንና በአካቢው ያስፈረችውን የጦር ሰራዊት ነፃ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ይህ ነፃ የሆነው ወታደር የኤርትራ መንግስት በውስጥ ውስጥ ከአረብ ከነ ሳኡዲ ጋር ለሚስማማው አገልግሎት ወደ የመን ለመዝመት የሚያስችለው ወታደር (deployable army) ይኖረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳርያ ማእቀብ እዲያነሳ ኢትዮጲያ መጠየቋ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ የኤርትራ መንግስት ተፈላጊውን የጦር መሳርያ በመሸመት ሰራዊቱን እሰከ አፍንጫው በማስታጠቅ በየመን ለማሰማራት አይቸገርም ማለት ነው፡፡
ኤርትራ ከኢትዮጲያ ጋር የነበረውን የድንበር ግጭትና መፋጠጥ በመፍታቷ ምክንያትና የኤርትራ ህዝብ ወደ ድንበር ሰላም በፍጥነት በመግባቱ ምክንያት በየመን የሚሰማራውን የኤርትራ ወታደር ለኤርትራ ህዝብ ትልቅ አጀንዳ ስለማይሆን ከውስጥ ሊፈጠርበት የሚችለው ፓለቲካዎ ጫና እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

ኢትዮጲያ ለምትጠቀምበት የወደብ አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ ስለምትፈፅምና ቀላል የማይባል የስራ እድል ስለምትፈጥር ከነበረው ሁኔታ ሻል ባለ መንገድ ህዝቡ የኢኮኖሚ መረጋጋት ውስጥ እዲገባ እድል ስለሚሰጥ አሁን ከኤርትራ ህዝብ የሚነሳበትን ፖለቲካዊ ጫና ለመቀነስ ይረዳዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት ጦር ሰራዊቱን በየመን በማሰማራትና አጣብቂኝ ውስጥ ያሉትን ሁለት አገሮች ከገቡበት ማጥ ለማውጣት በመሰለፍ እጅግ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝለት እንደሚችል ታሳቢ ሊደረግ ይችላል፡፡
በንፅፅር ሲታይ የኤርትራ ጦር አሁን የውጊያ ስልታቸውን ወደ ተንቀሳቃሽ (guerilla style) የቀየሩትን የሁጢ አማፅያንን ለመዋጋትና ከሌሎች በዚህ ህብረት ካሉት ተሳታፊዎች የተሸለ እንደሆን ታሳቢ አደርጋለሁ፡፡

ይህ ተልእኮ የኤርትራ መንግስት ከውስጥ ከህዝብ ሊፈጠርበት የሚችለው ጫና እጅግ አነስተኛ ስለሆነ በይፋ ሊሳተፍበት የሚችል እኳን ቢሆንም አንደምርጫ ግን በድብቅ ሊያደርገው እንደሚችል እሙን ነው፡፡
ጥላሸት የተቀባችውና የተነጠለችውን ኤርትራ ወደ አለማቀፍ ማህረሰብ ለመቀላቀል ትላልቅ የመገናኛ ብዙሃን የአገሪቱን በጎ ገፅታ የመገንባት ስራ ላይ በኢትዮ-ኤርትራ ሰላም ምክንያት አድርገው ይሰማራሉ፡፡

ለማጠቃለል

አሁን በኢትዮጲያና በኤርትራ የድንበር ጉዳይ የተፈጠረ አዲስ ነገር ኖሮ ወደ ሰላም ስምምነት መጡ የሚል እምነት የለኝም ነገር ግን በየመን አጣብቂኝ ውስጥ ያሉት አገራት ከገቡበት ማጥ ለመውጣት ካለመቻቸው ምክንያትና ሌሎች ትልልቅ አገራት እንደ አሜሪካና እንግሊዝ የመሳሰሉት የጦር ሃይላቸውን አሰማርተው ወደ የመን ጦርነት ሊገቡ ስለማይችሉ በተነፃፃሪነት በቀላሉ ሊሰማራ የሚችለውና በብዙ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ የተተበተበቸውን አገር ዜጎች በመማገድ ኤርትራም ከፍተኛ ገንዘብ እንድታገኝ አገራቱም ሰራዊታቸውን ቀስ በቀስ ለማስወጣት የሚያስችላቸው ሁኔታ ለመፍጠር የታለመ ነው፡፡ ተመልካች አልባው የየመን ጦርነት ካልተቋጨ በተራዘመ ቁጥር ተሳታፊ የሆኑት አገራትን እያደቀቀና ብሎም ውስጣዊ ፖለቲካዊ ቀውስ እየፈጠረ ያለ ፤ በተለይም በሳኡዲ አረብያ ውስጥ በቅርቡ በተለይም የተፈጠረው የልኡሎች ማሰርንና የመፈንቀል መንግስት መኩራ በአገሪቱ ያለውን የተጨናነቀና ውጥረት የሞላበት ፖለቲካ ማሳያ ይመስለኛል፡፡

 

ወደ ህልሜ ለመመለስ የጦርነት ተምሳሌት ሆኖ የታየኝ ጥቁር ዳመና ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ተሻግሮ ወደ የመን ምድር እየሄደ ያለ ይመስለኛል፡፡
************

Guest Author

more recommended stories