የመደመር ቀና ሃሳቦን ለዘለቄታው የሚፀና መንገድ! (ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን)

(ሀብቶም ገብረእግዚያብሄር)

ይድረስ ለተከበሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን

አስቀድሜ የሃገራችን መሪ ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ የሰሯቸውን ስራ እና ለከወኗቸው መልካም ተግባራት ያለኝን ጥልቅ አክብሮት መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ ከሶስት ወራት በፊት በማንም የኢትዮጲያዊም ሆነ ኤርትራዊ ዜጋ የማይቻል እና የማይሳካ ይመስል የነበረውን የሁለቱን ሀገሮች ዕርቅ ጉዳይ የፈቱበት መንገድ መብረቃዊ የሚባል እና ምን ጊዜም ከስሞት ጋር ተያይዞ ሲዘከር የሚኖር ማንም ሊፍቀው የማይችል አንፀባራቂ ስኬቶ ነው፡፡ ለዚህም ታሪኮ የሁለቱም ሃገር ህዝቦች በልባቸው ከፃፉት ቀጥሎ ብዙ ቁሳዊ እና ስነጥበባዊ ማስታወሻዎች በማኖር ሲዘክሩት እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ዛሬ ይህንን ደብዳቤ የምፅፍሎት ግን ለዚህ ታሪክ ምንጊዜም ለሚዘክረው ስኬቶ ምስጋና ለማቅረብ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላ በተጨማሪ እንዲደርሶት የምፈልገው ሃሳብ ስላለኝ ነው፡፡ ይህም ሃሳብ ከታሪካችን እና በታሪካችን እንደህዝብ ያለን የሃሳብ አንድነትን ይመለከታል፡፡

ከዛ በፊት ግን ለተከበሩ እንግዳችን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀነው ግብዣ የተከሰተውን ክስተት እንደመነሻ መጠቀም እፈልጋለሁ፡፡ ይኸውም መነሻ በፕሮግራሙ ወቅት ስራቸውን ያቀረቡት አርቲስት ሀጫሉ እና አርቲስት ቴዎድሮስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ነገር ግን ጉዳዩ ከአቀራረባቸውና ይዘቱ ሳይሆን ከዛ በሗላ ሁለቱ አርቲስቶችን ተከትሎ በተለያዩ ሚድያዎች(በተለይ በሶሻል ሚድያው) የተነሳውን ክርክር እና ንትርክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ የታሪክ ጭቅጭቅ ወስጥ የስገባበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው፡፡ ሊያውም አፀያፊ የክርክር ሂደቶች የተስተዋለበትና በሊህቃኖቻችን መሃከል ከመደመር ይልቅ መከፋፈልን የሚያሰፋ ሂደት ሆኖ ተስተውሏል ምንም እንኳ አዲስ ነገር ባይሆንም፡፡

ይህ ክስተት የቀረበ ሆነ እንጂ በታሪክ የተነሳ ርዕስ ሁልጊዜም በመቆራቆስ እና ያለስምምነት የሚጠናቀቅ መሆኑ ብዙ ሰዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ የኔም የዘወትር ጭንቀት የሚመነጨው ከዚህ እውነት ነው፡፡

በመሆኑም የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እጠይቃለሁ
1. አብዛኛችንን የሚያስማማ የታሪክ ድርሳናት ሊኖሩን ያልቻሉበት ምክንያት ምንድነው?
2. እስከመቼ በታሪኮቻችን ላይ እየተቋሰለን እና እየተወቃቀስን እንኖራለን?
3. እንደህዝብ ከትናንት ወጥተን ዘሬ ላይ ትኩረት በማድረግ ለወደፊት የሚዘከር የራሳችንን ደማቅ ታሪክ መፃፍ የምንጀምረው መቼ ነው?

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስተር

የመጀመሪያውን ጥያቄ በርሶና አሁን ባለው ቀለም ብሄር ሳይለይ ባለው ትውልድ ሊመለስ ስለማይችል በርሶ የስልጣን ዘመን እና በትውልዱ ሊመለሱ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ሁለቱ ጥያቄዎች ላይ አተኩራለሁ፡፡

እንዴት ይፈቱ?

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር

በኔ እምነት እነዚህን ጥያቄዎች የሚመለሱት ሁላችንንም የሚያስማማ ማለትም፤ የተሰሩ መልካም ነገሮች በአንዱ ረድፍ እንዲሁም የተሰሩ ግድፈቶችን በሌላኛው ረድፍ ያለፍረጃ ከታሪክ ፀሃፊ በሚጠበቅ ገለልተኝነት እንደገና ታሪካችንን መሰነድ ስንችል ነው፡፡ በዚህ ሂደት ነገሮችን በጥሞና እና በሳይንሳዊ መንገድ ተከትሎ በማጥናት የጎደለውን መሙላት እና የተጣመመውን በማቃናት ሁላችንንም ከሞላ ጎደል ሊያስማማ የሚችል ቅቡል ታሪክ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ያስችለናል፡፡ መጪውን ትውልድ አዙሪቱ ከማያልቀው የታሪክ አስቀያሚ ንትርክ አውጥተን ሌሎች ነገሮች ላይ ለማተኮር የሚያስችለውን መሰረት ለመጣል ያስችለናል፡፡ ይህም የበለፀገች እና ሁሉም ህዝቦቿ ከዳር እስከዳር በፍቅር የኔ የሚሏትን ኢትዮጲያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመሰረቱ እድል እናመቻችላቸዋለን፡፡ ይሄኛው ትውልድ ሌሎች ሊደመሩ የሚችሉ ጠቃሚ ነገሮችን ዛሬ ላይ እያደረገ መዋል ሲችል በትናንት ላይ ተጠምዶ እንደሃገር እያባከነብን ያለውን ጊዜ እና ጉልበት የሚተመን ዋጋ የለውም፡፡

ባጠቃላይ ከሰራው እና ካበረከተው በታች ታሪኩ እንዲያንስ እና እንዲደበቅ የተደረገውን ህዝብ (በዚህም አባቶቹ ህይወታቸውን ገብረው ያቆይዋት ሃገር እንደራሱ ሳይቆጥር ባይተዋርነት የሚሰማው ህዝብ ቀላል አይደለም) እውቅና ተሰጥቶት በአግባቡ መሰነድ እና ታሪክ የዘገባቸው መጥፎ ክዋኔዎችን ለተወሰነ የህዝብ የመለጠፍ ሂደትን የሚያስቀር የታሪክ ሰነዶችን ጊዜ ወስደን ልናዘጋጅ ይገባል፡፡

በኔ እምነት ለሀገራችን ወርቃማ ታሪኮች የብዙ የሀገራችን ህዝቦች የተባበሩ ክንዶች ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ለተፈጠሩ የታሪክ ጠባሳዎችም አንድ ህዝብ እንደህዝብ ሃላፊነት የሌለበት መሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡

በመሆኑም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ሁላችንም የሚያስማማ የታሪክ ስነዳ ማከናወን የሚለው የመጀመሪያው ሃሳቤ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሚከወንበት መንገድን የሚጠቁም ነው፡፡

የታሪክ ዳግመ ስነዳው በምን መልኩ ይከናወን?

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚከተለውን እውነታ እንደሚያውቁት ባይጠፋኝም ሃሳቤን እንዲያስረዳልኝ ባጭሩ አስቀምጠዋለሁ፡፡

የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ምዕራባውያን ብዙ የአለምን ታሪክ የቀየሩ የሳይንስ ግኝቶችን ለአለም ያበረከቱበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ግኝቶች ግን በሳይንሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የዕውቀት መስኮች ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህን የስኬት ዘርፎች የሚያመሳስላቸው አንድ የጋራ ባህሪ ነበር፡፡ ይኸውም የጋራ ባህሪ በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ ታላቅ አበርክቶ ለማድረግ አላማ ያላቸው፣ ነገር ግን ገለልተኛ ሆነው በመንግስት አስፈላጊው ድጋፍ በሚደረግላቸው አደረጃጀቶች መመራታቸው ነበር፡፡

ለምሳሌ የመፍጠር ዝንባሌ ያላቸው የሳይንስ ማህበር ወይም የሳይንስ አካዳሚ የሚል ማህበር አላቸው፡፡ የሳይንስ ፈጠራውን በጀት ከመመደብ፣ ከመገምገም እና ሲሳካም እውቅና እስከመስጠት ተግባር እና ሃላፊነት ይዘው የተደራጁ ናቸው፡፡ በጂኦግራፊው መስክ ያሉትም ልክ እንደፈጠራው መስክ በዘርፉ በመጠቁ ሙሁራን የተደራጁ እና የበኩላቸውን ሃላፊነት የተወጡ ናቸው፡፡ በሌሎችም መስኮች በእንደዚህ አይነት በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ በመንቀሳቀስ ዛሬ የደረሱበት ከፍተኛ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ለመድረስ ችለዋል፡፡

በመሆኑም እኛም የታሪክ ስነዳውን ከላይ ከሰፈረው አካሄድ ተምሳሌቱን በመውሰድ መከናወን ይችላል፡፡

ሀሳቤን ባጭሩ ለማስቀመጥ፤ በሀገራችን የሚገኙ በታሪክ እና ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያለው ዕውቀት የሰነቁ ሊህቃን የሁሉንም የሀገራችንን ህዝቦች ውክልና ባረጋገጠ መልኩ፤ የኢትዮጲያ የታሪክ አካዳሚ ወይም የኢትዮጲያ የታሪክ ካውንስል እንዲቋቋም ማድረግ ለታሪክ ስነዳው የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል የሚል ጥቆማ እሰጣለሁ፡፡

በመቀጠልም የሞያ እና የአካዳሚ ነፃነታቸውን ባስጠበቀ መልኩ እርሶ በሚመሩት መንግስት ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል ማደረግ እና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑትን የሀገራችን ህዝቦች በንቃት እንዲሳተፉ እና የበኩላቸውን የማይተካ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማስቻል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት እንደታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መከወንና ከ10 አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎችን የሚያስማማ፤ ከስሜት የፀድቶ እውነታውን ያስቀመጠና እና የሀገራችንን አንድነት ከአደጋ የሚያወጣ የአስተሳሰብ አንድነት የሚያስገኝ አስማሚ ሰነድ እንዲፈጠር ማስቻል ሀላፊነት ወስደን መንቀሳቀስ አለበን፡፡ በቀጣይነትም ተመሳሳይ ስህተቶች እንዳይፈጠር እና ምክንያታዊ የታሪክ አተያየት በዜጎች ላይ እንዲፈጠር መስራትና የሚወጡ ታሪክ ቀመስ ፅሁፎች እውነተኛ መሆናቸውን አገራችን ወደተመሳሳይ የታሪክ ጭቅጭቅ እንዳትገባ እየሰራ መዝለቅ ይችላል፡፡

ክቡር መሪያችን በቅርቡ የገጠመኝ አንድ ክስተት ላንሳ

አብዛኛዎቻችንን ኢትዮጲያውያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአህመድ ግራኝ እና በሰሜኑ የሀገራችን ህዝቦች መሃከል የነበረውን ጦርነት ያነበብናቸው መፅሃፎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ባጭሩ ከታሪክ ፃሃፍት የሚጠበቀው ገለልተኝነት አይታይበትም፡፡ ታዲያ በዚህ አመት አፈንዲ ሙተቂ የተባለ ኢትኖግራፊስት ታዋቂ የሃገራችን ፃሃፊ ˝አዳል˝ የሚለውን መፅሃፍ ገዝቼ አነበብኩ፡፡ ለምን ቢባል ታሪክ በተለያየ እይታ ባላቸው ሰዎች ምን ይመስላል የሚለውን ሁናቴ የማወቅ ፍላጎት ስለነበረኝ ነው፡፡ እንዳሰብኩትም እይታዬን በሚያሰፋ መልኩ ብዙ ድርሳናትን ተጠቅሰው የተፃፈ እና ሌላ ቅቡል በመረጃ የተደገፈ የታሪክ እይታ ያሳየኝ ነበረ፡፡

ለማለት የፈለኩት ሁሉንም የሀገራችንን ሙሁራን በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እውነት የሆነውን እና ከሞላ ጎደል በአመክንዮ የሚያምኑ የሀገራችን ህዝቦችን የሚያስማማ ስነዳ ለማከናወን የታሪክ አካዳሚው ይቋቋምና ውጤቱን እንየው፡፡ በጀቱ በማያሳስብ ደረጃ ሀገሪቷ በአመት በሌብነት የምታጣውን ገንዘብ ለብዙ አመት እንኳ አይፈጅም፡፡ ውጤቱ ግን የላቀ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላያችን ይህንን ሀሳብ እንደ ዜጋ ማበርከት አለብኝ ብዬ የማስብውን እና ሸክሜን ለማቅለል ነው፡፡ ሀሳቡን ለመተግበርም ይከብዶታል ብዬ አላምንም፡፡ እንዲያውም ይዘውት የተነሱትን አንድነት የሚያመጣ መደመር የሚለውን መሪ ቃል ዘላለማዊ መሰረት ይሰጠዋል፡፡ ይህንን ብናደርግ የመደመር ፅንሰ ሃሳቦን በአለት ላይ እንደተሰራ ቤት አፅንተውት ለመሄድ ያስችሎታል፡፡ ከምንም በላይ ግን ይህንን እቅድ የሀገራችንን ታላላቅ ሙሁራን ሊያዳብሩት እና ወደመሬት የሚወርድበትን መንገድ ሊያመቻቹ ይችላሉ፡፡
ማድረግ ከተቻለ ግን ከምንም በላይ እስካሁን ካደረጉት ጋር ተደምሮ የርሶ ታሪክ እና የትውልዱ ማስታወሻ ይሆናል፡፡

ይህ ሃሳብ እንደሚያገኞት እንደሚሰሙት ተስፋ እያደረኩ ይህንን ታሪካዊ ዘላቂ የሀሳብ አንድነት ሊያመጣ የሚችል ታሪካዊ ሃላፊነት ለመከወን እንደሚያስቡበት እምነቴን እገልፃለሁ፡፡

ቸር ሁሉ ይግጠመን

*******
*  ለበለጠ ውይይት የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ሀብቶም ገብረእግዚያብሄር email: [email protected]

Guest Author

more recommended stories