በመከላከያ ሰራዊታችን የፖርቲ ፖለቲካ ገለልተኝነትና ተያያዥ ጉዳዮች (ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ)

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ)

[ከአዘጋጁ፡- ኮ/አስጨናቂ ይህንን ጽሑፍ የላኩልን ከሳምንታት በፊት ቢሆንም የኢንተርኔት ተደራሽነት ለአብዛኛው የሀገር ውስጥ አንባቢ ውስን ስለነበረ እና በተያያዥ ምክንያቶች አዘግይተነዋል፡፡ ከጽሑፉ ርዝመት አንጻር በሁለት በመክፈል የመጀመሪያውን ክፍል እዚህ አትመነዋል፡፡]

——

Highlights:

* ከመከላከያ ሰራዊት ምስረታ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ (1986 ላይ) ጂግጅጋ አካባቢ ለስራ ሄጄ ያገኙሁት አንድ ነባር ታጋይ እንደዚሁ ስናወራ በመሃሉ “ወደፊት የኢህአዴግ ሰራዊት የሚባል ነገር እንደማይኖርና ኢህአዴግንም ጨምሮ ሁሉን ያካተተ ህብረብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እንደሚመሰረት” ስነግረዉ “እንዴት እንዲህ ይሆናል? አህአዴግ ምን አጥፍቶ ነዉ?” ወዘተ በሚል በየዋህነትና በቅሬታ መንፈስ ነበር ምላሽ የሰጠኝ፡፡

* ኢህአዴግ መከላከያ ሰራዊቱን ገለልተኛ እና ለህዝብ የወገነ እንዲሆን በማሰብ በሀገሪቱ ህገመንግስት ዉስጥ በግልጽ ቋንቋ እንዲካተት የተደረገበትና ህገመንግስቱን ተከትሎም በመከላከያ ማቋቋሚያ አዋጁና በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በሰራዊቱ ግንባታ መመሪያ ላይ ጭምር ይህንኑ  በሚያንጸባርቅ መልኩ በግልጽ ተቀምጧል፤ በተግባርም ብዙ ተሰርቷል፡፡

* በሁለቱ የቀድሞ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ሲሰጥ የቆየዉ አስተያየት በአብዛኛዉ ነቀፌታና እንዳንዴም በጥላቻ የታጀበ ዘለፋ መሆኑን ለተገነዘበ ሰዉ ዳግመኛ ለመጻፍ ይቃጣሉ ብሎ ለመገመት ይቸግረዋል፡፡….. ጄ/ል አበበን ለመዝለፍ አመቺ ጊዜ ሲጠብቅ ቆይቶ, ልክ በድንገት ሲያገኟቸዉ የፈሪ ዱላ ይመስል በወታደር ቤት ዉስጥ “የጃርት ስልት“ (The Porcupine Approach) እንደሚባለዉ ያገኘዉን  ሁሉ በመወርወር ለማጥቃት መፈለጉን  ብቻ ነዉ ለመረዳት የቻልኩት፡፡

* አቶ መለስ ወታደራዊ ጠቢብ እንደነበሩና በወታደራዊ ጉዳዮች እጅግ የጠለቀ እዉቀት እንደነበራቸዉ መረጃዉ ብኖረኝም እሳቸዉን ለመካብ ተብሎ እሳቸዉ ራሳቸዉ በኤታማዦርነት ሹመዉ ሲያሰሩ የነበሩትን ጀ/ል ጻድቃን ማንኳሰሱ ተገቢ አይሆንም፡፡ አቶ መለስና የጄነራል ጻድቃን ሃላፊነት ድርሻም የተለያየ መሆኑን ዘንግቶ አቶ መለስ ጦር ግንባር ላይ ተገኝተዉ ዉጊያ እንደሚመሩ ዓይነት ማስመሰሉ አስገራሚ ነዉ፡፡

* “ስለ መከላከያ ሰራዊቱ ለምን ይጻፋል?ለምንስ በአደባባይ ስሙ ይነሳል? ለምንስ ትችት ይቀርባል?” የሚሉ ወገኖች ለመከላከያ ሰራዊቱ ካላቸዉ ፍቅርና ተቆርቋሪነት ስሜት እንዳልሆነ አዉቃለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ መከላከያ ሰራዊታችን ገንቢ አስተያትና እርምት የሚሰጡ ወገኖች ለመከላከያ ሰራዊቱ ጥላቻ ስላላቸዉ እንዳልሆነም አዉቃለሁ፡፡

* ያኔ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የ93ቱ ቀዉስ ጊዜ በመከላከያ  ከፍተኛ መኮንኖች ደረጃ በተለያዩ ሰነዶች ላይ ዉይይት በሚደረግበት ወቅት ጆቤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደማይዋጥላቸዉ በግልጽ ተናግረዉ ነዉ ስብሰባዉ ላይ መገኘት ያቆሙት፡፡ በወቅቱ ጭራሽ ለማንበብም እንዳልሞከሩ ወደፊትም የዚያ ዓይነት ጽሁፍ እንደማያነቡ በድፍረት ሲገልጹ አዳምጨአለሁ፡፡ ጆቤ “ማንም በዘፈነ ቁጥር አብሬ አልዘፍንም ማንም ባጨበጨበ ቁጥር አብሬ አላጨበጭብም“ በሚል አባባል ነበር የገለጹት፡፡

* “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ” ጉዳይም ሆነ “የሰራዊት ግንባታ ሰነዱ” ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በአንድ ሰሞን በተከታታይ ለዉይይት የቀረቡ ሆነዉ እያለ ዛሬ ከስንት ዘመን በኋላ ጆቤ ምን ታይቷቸዉ አስታዉሰዉ እንደ አዲስ እንደተቃወሙ አስካሁንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ …… ጆቤ የግንባታ ሰነዱ ላይ ትኩረት ከሚያደርጉ በቅድሚያ “መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አይደለም!” የሚሉበትን መከራከሪያ በማስቀመጥ ማሳመኑ ላይ ነበር ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባ የነበረዉ፡፡ እሳቸዉ ግን መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አለመሆኑን ሳያስረዱንና እንደተቀበልናቸዉም እርግጠኛ ሳይሆኑ “የችግሩ ምንጭ ነዉ“ ያሉት ሰነድ ላይ ለመፍረድ ተቻኮሉ፡፡

* የግንባታ ሰነዱ ላይ በወቅቱ እኔም ወግ ደርሶኝ የመወያየት እድል አግኝቼ ስለነበር አቶ መለስ ዜናዊ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሲሰጡ ከተወያዮቹ ከቀረቡላቸዉና የሳቸዉን ማብራሪያ ከሚፈልጉ በርካታ ጥያቄዎች መካከል በጥያቄ መልክም ሆነ በመሳሳቢያ መልክ የግንባታ ሰነዱ የሰራዊቱን ገለልተኝነት ይሸረሽራል የሚል ነገር በጭራሽ እንዳልተነሳ በሚገባ አስታዉሳለሁ፡፡

* በሀገሪቱ ዉስጥ ገኖ የወጣ አመለካከት ወይም አይዲኦሎጂ ሊኖር ይችላል፡፡ ያን አመለካከትና ርዕየተ-ዓለም ሰራዊቱ መጋራቱ የማይቀር ነዉ፡፡ ስህተት የሚሆነዉ አመለካከቱን መጋራት አለበት ማለትና አመለካከቱን ያመጣዉ ገዢዉ ፓርቲ ስለሆነ የገዢዉን ፓርቲ አመለካከቶች ሁሉ መቀበል አለበት መባሉ ነዉ፡፡ ይህ በጣም ስህተት ነዉ፡፡ ከፓርቲ ጋር በተቆራኘ መንገድ የሚገለጽ ነገር ላይ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

* ገዢዉ ፓርቲ ለዘመናት ስልጣን ሳያስነካ የሚቆይ ከሆነ በፊት ገለልተኛ የነበረና ወገንተኝነቱን ለህዝብ ያደረገ መከላከያም ቢሆን ቀስ በቀስ ከአገዛዙ ጋር እየተላመደና ቤተኛ እየሆነ ስለሚሄድ  ከገለልተኝነት ባህሪይዉ እየወጣ ለገዢዉ ፓርቲ ጥብቅና ወደ መቆም ሊገባ ይችላል፡፡

* 1997ቱ ምርጫ በአዲስ አበባ ላይ ቅንጅት ማሸነፉን በሚመለከት የተሰማቸዉን ስሜት ማንም ሳያስገድዳቸዉ በመግለጽ ራሳቸዉን ግለሂስ ያደረጉ የቀድሞ ነባር ታገዮች መካከል እንዲህ ያሉ ይገኙበታል፡፡ ‹‹“የአዲስ አበባ ህዝብ ኢህአዴግን ከዳዉ፤ ኢህአዴግን በቅንጀት ለወጠዉ፤ ትልቅ ክህደት ነዉ የተፈጸመብን” በማለት በህዝቡ ላይ ቅሬታ መያዜ ትክክል አይደለም፤ ከአንድ ህገመንግስታዊ ገለልተኛ ሰራዊት የማይጠበቅ አመለካከት ተንጸባርቆብኛል››  የሚል ግለ -ሂስ ማንም ሳይጠይቃቸዉና ሳያስገድዳቸዉ በራሳቸዉ ላይ ያቀረቡ ነበሩ፡፡

——–

መግቢያ

የየትኛዉም አገር መከላከያ ሰራዊት የህዝባዊ ወገንተኝነቱ የመጀመሪያ መለኪያ ሰራዊቱ በየትኛዉም ፖለቲካ ዉስጥ ጣልቃ የማይገባና ስራዉን በገለልተኝነት የሚሰራና ወገንተኝነቱንም ከፖለቲካ ፓርቲ ይልቅ ለህዝብ ያደረገ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ በይፋ በሚቀንቀሳቀሱበትና መድበለፓርቲ ስርአት ባለበት እንደ እኛ ባለአገር መከላከያ ሰራዊቱ አንዱን ፓርቲ ወግኖ ሌላዉ ፓርቲ ላይ ጫና የሚያሳድር ከሆነ በምንም መስፈርት ቢሆን ለህዝብ የወገነ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ለአንድ ፓርቲ ጥብቅና የሚቆም መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ሰራዊት ሊሆን ባህሪይዉ አይፈቅድለትም፡፡ ለአንድ ፓርቲ በተለይም በስልጣን ላይ ላለ ፓርቲ ዘብ የሚቆምና ራሱን የፓርቲዉ ጠባቂ አድርጎ የሚቆጥር ሰራዊት ለገዥዎች ስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ ከመሆን ዉጭ የሕዝቦች መከታ መሆን አይችልም፡፡ በአንድ ጊዜ ለፓርቲም ለህዝብም ወገናዊ መሆን ስለማይቻል ሰራዊቱ ከህዝቡና ከፓርቲ አንዱን መምረጥ ይገባዋል፡፡

ለህዝብ ከመወገን ይልቅ የፓርቲ ወገናዊነት ይበልጥብኛል ብሎ ራሱን ከአንድ ፓርቲ ጋር ያቆራኘ ሰራዊት ህዝባዊ ቅቡልነቱ የጎደለዉና ራሱን ከህዝቡ የነጠለ ነዉ፡፡ ወገናዊነቱን ከአንድ ፓርቲ ጋር ያቆራኘ መከላከያ ሰራዊትን ህዝብ እንደ ጠባቂዉ ሳይሆን አንደ ስጋት ምንጭ ነዉ የሚያዉ፡፡ ህዝቡ በገዛ መከላከያ ሰራዊቱ ላይ አሜነታ ካጣ በፍቅር ማዬት ቀርቶ በፍርሃትና በስጋት መንፌስ ነዉ የሚያየዉ፡፡ የራሴ ሰራዊት ነዉ ብሎ አያስብም፡፡ ህጋዊ እዉቅና የተሰጣቸዉ የሀገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ገለልተኛ አለመሆኑን ከተረዱ በነጻነት ለመንቀሳቀስ ድፍረት አይኖራቸዉም፡፡ ወታደሩን የሚተማመን ገዢ ፓርቲን በዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ከስልጣን ለማዉረድ ጨርሶ እንደማይቻል የተገነዘቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህጋዊዉን መንገድ ትተዉ ህገወጥ አማራጭ መንገድን ለመከተል ይገደዳሉ፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አለመሆንን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለዉ ችግር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ለህዝቡና ለራሱም ለመከላከያ ሰራዊቱ አባላትም ጭምር ነዉ፡፡ ለገዥዉ ፓርቲ በመወገኑ ምክንያት የገለልተኝነት ጸጋ የራቀዉ ሰራዊት የህዝቦችን ደህንነት፤ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅምና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ተነሳሽነቱም ብቃቱም አይኖረዉም፡፡ ለአንድ ፓርቲ አሽከርነት ያደረ ሰራዊት ለዉለታዉ በምላሹ ከሚያገኘዉ ጥቅማጥቅም ዉጭ የሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ከቶ አያሳስበዉም፤ የህዝቡ ብሶትም አያስጨቀንቀዉም፡፡ ስለዚህ ስለሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ሲወሳ ዋናዉ ጉዳይ መሆን ያለበት የገለልተኝነት ጉዳይ ነዉ፡፡ ከዚህ መሰረታዊ ሃቅ ስንነሳ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት የኢፌድሪ የመከላከያ ሰራዊትን ለመገንባት ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ ያደረገዉ ጥረትና የተገኘዉ ዉጤት መመዘን ያለበትም በተገነባዉ የሰራዊት ብዛት መጠን ወይም ተቋማዊ ግዘፈት ሳይሆን ሰራዊቱን ገለልተኛና ወገንተኝነቱን ከሁሉም በፊት ለህዝብ እንዲሆን ለማድረግ ባደረገዉ ጥረት ነዉ፡፡ ይህ ጥረት ምን ያህል ተሳክቶአል? ምን ጉድለት አለበት? በሚለዉ ላይ እንደ አመለካከታችን ልዩነት የተለያዩ አስተያየቶች ሊኖሩን ይችላሉ፡፡

በመከላከያ ሰራዊታችን ገለልተኝነትና ህዝባዊ ወገናዊነት ላይ የመጀመሪያ ምስክር መሆን ያለበት ራሱ ህዝቡ ነዉ፡፡ ይህ እንዳለ ሀኖ ማንኛዉም ዜጋ የራሱን መከላከያ ሰራዊት በሚመለከት መወያየትና ገንቢ አስተያየት መስጠት ይገባዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ማንኛችንም ብንሆን በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ያለን ግምገማ ለመከላከያ ሰራዊቱ ካለን አመለካከት ጋር በእጅጉ መቆራኘቱ የግድ ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱን “የእኔ ሰራዊት አይደለም” የሚል ወገን ስለ ሰራዊቱ መልካም አስተያየት እንዲሰጥ አይጠበቅበትም፡፡ ገዢዉን ፓርቲም ሆነ ስርአቱን በጭፍን የሚጠላ ወገን የስርአቱ ጠባቂ የሆነዉን መከላከያ ሰራዊት ገዥዉ ፓርቲን በሚያይበት ዓይን ማዬቱና የተቋሙን ገለልተኝነት አልታይህ ቢለዉ የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱን እንከን አልባ በማድረግ ፍጹማዊ ባህሪይ ለማላበስ የሚደረጉ ሙከራዎችም በራሳቸዉ ከጥቅማቸዉ ይልቅ በሂዴት ሊያስከትሉት የሚችሉት ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ሚዛናዊ የሆነ አስተያየት ለመስጠት በቅድሚያ መከላከያ ሰራዊቱ የራሴ ሰራዊት ነዉ ብለን ማሰብ መጀመር አለብን፡፡

መከላከያ ሰራዊታችን ፤ የኛኑ ደህንነትና የሀገራችንን ሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ዉጭ ሌላ ዓላማ የለለዉ መሆኑ ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ከህዝቡ መሃል የወጡ በመሆናቸዉ በህብረተሰቡ ዉስጥ ያሉ የሚታዩ አመለካከት ችግሮች ሰለባ ሊሆን ስለሚችል ህዝባዊ ባህሪዉን ጠብቆ እንዲቆይ የማድረግ ሃላፊነት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት መሆኑን መዘንጋት አይገባንም፡፡ አንዳንዴ በህብረተሰቡ ዉስጥ በሚከሰቱ ልዩ ሁኔታዎች ምክንያት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ያልተለመዱ ጫናዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ልዩ ሁኔታ ዉስጥ የመከላከያ ሰራዊቱን ሚና በቀና መንፈስ ካለማዬት የተነሳ ህዝባዊ ወገናዊነቱንና ገለልተኝነቱን አስከመጠራጠር የሚደርሱ ወገኖች አይጠፉም፡፡ ዜጎች በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዳይኖራቸዉ ለማድረግ በድክመቱም ሆነ በጥንካሬዉ ዙሪያ በግልጽ መነጋገር መለመድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችንን ገጽታ የሚያበላሹ ሁኔታዎችን በገራ ማስተካል አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

1/ በኢህአዴግ አመራር ሰጭነት ገለልተኛ መከላከያ ሰራዊት ለመመስረት የተደረገዉ ጥረት የሚያበረታታ ነዉ፡፡

የደርግ ስርአትን አስወግዶ ስልጣን የተቆናጠጠዉ ኢህአዴግ ሀገር የማስተዳዳር ሃላፊነት ከተረከበ በኋላ ካከናወናቸዉ ግዙፍ ተግባራት መካከል ከልማት ስራዉ ቀጥሎ ሊጠቀስ የሚችለዉ ገለልተኛ የሆነ መከላከያ ሰራዊት ለመመስረት ያደረገዉ ጥረት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምናልባት ኢህአዴግ በይበልጥ ተካስክቶለታል ከሚባሉ ስራዎቹ ዉስጥ አንዱ ተጠቃሽ ይህ ጉዳይ ነዉ፡፡ በምዕራባዉያን የዳበረ ዲሞክራሲ መስፈርት አኳያ ሲመዘን የመከላከያ ሰራዊታችንን ገለልተኝነት በሚመለከት “ገለልተኛ ነዉ/አይደለም“ የሚለዉ ጉዳይ ሊያከራክር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በቀና መንፈስ ከሀገራችን ልዩ ሁኔታ አንጻር ቢታይ ይሄን ያህልም የሚያስከፋ እንዳልሆነ መረዳት አያቅተንም፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ መጀመሪያ በጊዜያዊ መንግስትነት በኋላ ደግሞ በሽግግር ዘመን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሆኖ የቆየዉ የራሱ የኢህአዴግ ሰራዊት አንደነበረ የሚታወቅ ነዉ፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ በአንድ ጎኑ የፖለቲካ ድርጅት በሌላ ጎኑ ደግሞ ወታደራዊ ተቋም (ተዋጊ ክንፍ) ሆኖ እንደ ፓርቲም እንደ ወታደርም እየተወነ የቆየበት ወቅት ነበር፡፡ ሌላ አማራጭ መንገድ ባልነበረበት በዚያን ወቅት እንደዚያ መሆኑ የሚያስገርም አልነበረም፡፡

በሽግግሩ ዘመን መከላከያ ሰራዊቱ በድርጅቱ ስር የተዋቀረና አመራር የሚያገኘዉም በተዋረድ በቀጥታ ከድርጅቱ ስለነበር በኢህአዴግና በመከላከያ ሰራዊቱ መካከል አንዳችም ልዩነት አልነበረም፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ሁሉም የድርጅቱ አባላት በሆኑበት ሁኔታ በድርጅቱና በሰራዊቱ ተቋም መካከል ልዩነት እንዲኖር መጠበቅ አይገባም፡፡ ከፍተኛ የመከላከያ አዛዞች አብዛኛዎቹ የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስለነበሩ ኢህአዴግና መከላከያ ተቋሙ በአንድ ሳንባ ነበር ይተነፍሱ የነበሩት ማለት ይቻላል፡፡ የስራ ድርሻ መደረጉና ወታደሩ ጠበንጃ ታጥቆ በወታራዊ ካምፕ ዉስጥ መኖሩ ካልሆነ በስተቀቀር ሌላ ልዩነት አልነበረም፡፡ ለነገሩ በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወታደራዊ ዩኒፎርምም ሆነ ወታደራዊ ማዕረግ ያልነበራቸዉና አቶ/ጓድ/ታጋይ ወዘተ ከመሳሰለዉ ዉጭ በይፋ የሚጠሩበት ሌላ የማእረግ ስም አልነበራቸዉም፡፡

ምናልባት በሽግግሩ ጊዜ በወታደራዊ ማዕረግ የመጠራት እድል የነበረን ከቀድሞዉ ሰራዊት የመጣን ብቻ ነበርን፡፡ ደግነቱ አንዳንዴ እኛንም ብጻይ(ጓድ) እያሉ በስህተት ከመጥራት በስተቀር በነበረን በወታደራዊ ማዕረጋችን የመጠራት መብት አልተነፈግንም፡፡ እንግዲህ በዚህ መልክ መከላከያ ሰራዊቱ ከኢህአዴግ ጋር በመቆራኘት ለዘመናት ቆይቶ እንዳልነበር ከኢፌድሪ መንግስት ምስረታ በኋላ በህገ መንግስቱ መሰረት መከላከያ ሰራዊትም ሲመሰረት ከድሮ ከእናት ድርጅቱ መነጠሉ የግድ ሆነ፡፡ ከድርጅቱ በመነጠል ከድርጅት ሰራዊትነት ወደ ሀገር አቀፍ ገለልተኛ ሰራዊትነት ለመቀየር ተብሎ አመለካከቱን ለማረቅ የተደረገዉ ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡ ሰራዊቱን ከድሮ ድርጅቱ በአካል በመነጠል (physical separation) ብቻ ሳይገደብ በአመለካከት ደረጃም ራሱን ከድርጅቱ ፖለቲካ ተዋናይነት ለማላቀቅ የተደረገዉ ጥረትና የነበሩ ተግዳሮቶች እንዲህ በቀላሉ የሚታዩም አልነበሩም፡፡

የኢፌደሪ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን ህገመንግስቱ ላይ በተደነገገዉ መሰረት ገለልተኛ ተቋም እንዲሆን የማድረግ ጥረቱን የጀመረዉ ከቀድሞዉ ፖለቲካ ድርጅቱ – ኢህአዴግ የማላቀቅ (departicization) እርምጃ በመዉሰድ ነዉ፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረዉ ፈታኝ ስራ ስለህገመንግስታዊ ሰራዊት ባህሪይና ለየትኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን ስራዉን በገለልተኝነት የሚሰራ ለማድረግ አብሮት የቆየዉን አመለካከቱን በአዲስ አመለካከት የመቀየርና የማስረጽ (indoctrination) ስራ መስራት ነበር፡፡ በወቅቱ ነባሮቹን ታጋዮች ከቀድሞዉ ድርጅታቸዉ በአካል የመነጠል ነገር በራሱ ቀላል ባይሆንም ጭራሽ በአመለካከት ደረጃም “ስለፓርቲ ማሰብ አቁሙ፤ ለኢህአዴግ ጥብቅና መቆም ከእንግዲህ አይሰራም፤ እንደ ኢህአዴግ ሆናችሁ ማሰብ አቁሙ” ሲባሉ ይህ ነገር በቀላሉ ተቀብለዉታል ማለት የነበረዉን ነገር እንደመካድ ነዉ የሚቆጠረዉ፡፡ ከየትኛዉም ፖለቲካ ፓርቲ ያለመወገንና ለማንም ያለማዳላት አመለካከት (partisan neutrality and impartiality) ከልብ አምነዉበት እንዲቀበሉ ማድረጉ አስቸጋሪ ነበር፡፡ “ለየትኛዉም ፓርቲ አትወግኑም! ለኢህአዴግም ቢሆን” ሲባሉ ነገሩን እንደቀላል ተቀበሉት ማለት አይደለም፡፡ በታጋዮቹ ቦታ ሆኖ ነገሩን ላየዉ ሰዉ አስቸጋሪ እንደነበር ለመገንዘብ አያደግትም፡፡

ታጋዮቹ ጉዳዩ እየከበዳቸዉም ቢሆን በመጨረሻም ሊቀበሉ የቻሉት እንደእነሱዉ የሰራዊቱ አመራሮች የሆኑት ቀድሞዉኑ የግንባሩ ወታደራዊ አመራሮች ስለነበሩ እነሱ የሚነግሩዋቸዉን በመተማመናቸዉ ይመስለኛል፡፡ ሁኔታዉ ቀላል እንዳልነበር አንድ አብነት ላቅርብ፡፡ ከመከላከያ ሰራዊት ምስረታ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ (1986 ላይ) ጂግጅጋ አካባቢ ለስራ ሄጄ ያገኙሁት አንድ ነባር ታጋይ እንደዚሁ ስናወራ በመሃሉ “ወደፊት የኢህአዴግ ሰራዊት የሚባል ነገር እንደማይኖርና ኢህአዴግንም ጨምሮ ሁሉን ያካተተ ህብረብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እንደሚመሰረት” ስነግረዉ “እንዴት እንዲህ ይሆናል? አህአዴግ ምን አጥፍቶ ነዉ?” ወዘተ በሚል በየዋህነትና በቅሬታ መንፈስ ነበር ምላሽ የሰጠኝ፡፡ እኔ በቶሎ የጫወታችንን ርእስ ወደ ሌላ ቀይሬ ለማረሳሳት ብሞክርም ታጋዩ ግን እኔ ሆን ብዬ ፈጥሬ የማወራዉና ለኢህዴግ ጥላቻ እንዳለኝ አድርጎ እንደተገነዘበ በሌላ ጊዜ ለመረዳት ችዬ ነበር፡፡

የቀድሞ የኢህአዴግ ሰራዊትን ወደ ህገመንግስታዊ ሰራዊትነት የመለወጡ ሂዴት ላይ ትልቅ ችግር የነበረዉ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ ታማኝና ለህዝብ ወገንተኛ የማድረግ ነገር አልነበረም፡፡ ለኢህአዴግ ሰራዊት ይህ እንደችግር የሚታይ አልነበረም ምክንያቱም ለህዝብ ታማኝ የመሆን ጉዳይ የኢህአዴግ ሰራዊት ቀድሞዉኑ በእምነት የታገለለት ዓላማ ስለነበር በዚህ ረገድ ያጋጠመ ሊጠቀስ የሚችል ችግር አልነበረመም፡፡ በስርአቱ የማመን ያለማመን ጉዳይ የኢህአዴግ ሰራዊት ችግር ሆኖ አያዉቅም፡፡ ነገር ግን ለጊዜዉም ቢሆን የጋጠመዉ ተግዳሮት የሰራዊቱ አባላት ለአስራ ሰባት ዓመታት ታግሎ ያታገላቸዉና ለድል ያበቁትን ድርጅት “የተለየ ወገናዊነት አታሳይ ፤ከእንግዲህ ከድሮ ድርጅትህ የሚያገናኝህ ነገር አይኖርም፡፡ በኢህአዴግ ቋንቋ መናገር አቁም ፤የኢህአዴግ አፈቀላጤና ጠበቃ መሆን አቁሙ” ሲባሉ በጸጋ ለመቀበል መቸገራቸዉ እሙን ነዉ፡፡ በአንድ ጊዜ ወደዚህ ደረጃ ለማምጣት አስቸግሮ ነበር ለማለት ካልሆነ በስተቀር በኋላ ላይ የገለልተኝነቱን ጉዳይ ከህዝቦች መብት አኳያ ያለዉን ፋይዳ እየተረዱ ሲመጡ ቀስ በቀስ መቀበላቸዉ አልቀረም፡፡

ኢህአዴግ መከላከያ ሰራዊቱን ገለልተኛ እና ለህዝብ የወገነ እንዲሆን በማሰብ በሀገሪቱ ህገመንግስት ዉስጥ በግልጽ ቋንቋ እንዲካተት የተደረገበትና ህገመንግስቱን ተከትሎም በመከላከያ ማቋቋሚያ አዋጁና በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በሰራዊቱ ግንባታ መመሪያ ላይ ጭምር ይህንኑ በሚያንጸባርቅ መልኩ በግልጽ ተቀጧል፤ በተግባርም ብዙ ተሰርቷል፡፡ በሀገሪቱ የስልጣን ክፍፍል ረገድ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚችለዉ መከላከያ ሰራዊቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ነዉ፡፡ምንም እንኳን በሀገራችን ፓርላሜንታዊ ስርአት መሰረት አስፈጻሚዉ አካል በህግ አዉጭዉ አብላጫ ወንበር ያለዉ ገዢ ፓርቲ መሆኑ ባያጠያይቅም መከላከያ ሰራዊቱን በሚመለከቱ አብይ ጉዳዮች ላይ ስልጣኑን ለብቻዉ ለመጠቀም ሳይሞክር በህግ አዉጭዉ እያስወሰነና እዉቅና እያገኘ መስራቱን ስንመለከት ኢህአዴግ መከላከያዉኑ ያለተቀናቀኝ ብቻዉን እንደፈለገ እያዘዘ ነዉ የሚለዉን ትችት ዉድቅ የሚያደርግ ነዉ፡፡

2/ ስለ መከላከያ ሰራዊቱ አስተያየት መስጠትና መወያየት የሁሉም ዜጎች መብት ነዉ

በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየትም ሆነ ነቀፌታ ሲያቀርቡ የምናዉቃቸዉ ምሁራን ባይጠፉም በመንግስትና በገዢዉ ፓርቲ በከፍተኛ ሃላፊነት ሲሰሩ ቆይተዉ በተለያዩ ምክንያቶች ከሃላፊነታቸዉ የተነሱ ዜጎች የሚሰጡት አስተያየትና የሚሰነዝሩት ሃሳብ በአንክሮ መታየት የሚገባዉ ነዉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በሃገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ አስተያየት ሲሰጡ ከቆዩት መካከል የቀድሞዉ ኤታማዦር ሹም ሌ/ጄነራል ጻድቃን እና የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜ/ጄነራል አበበ (ጀቤ) ይጠቀሳሉ፡፡

ሁለቱ እዉቅ ጡረተኛ ጄነራሎች አልፎ አልፎም ቢሆን ብቅ እያሉ ለሀገርቱም ለመንግስትም ይበጃል ባሉት ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየታቸዉን መስጠታቸዉ ባይቀርም ለዚህ ጥረታቸዉ ግን በአብዛኛዉ የተሰጣቸዉ ምላሽ እነሱንም አንባቢዎችንም ተስፋ የሚያጨልም ሆኖ ነዉ ያኘሁት፡፡ በነሱ ተበረታትተዉና የእነሱን አርአያነት ተከትለዉ ሌሎችም ከስርአቱ ጋር በአንድ ወቅት ተኮራርፈዉ ድምጻቸዉን አጥፍተዉ የተቀመጡ የድርጅቱና የስርአቱ ባለስልጣናት ወደ ሚዲያዉ እንደሚመጡ ተስፋ ስናደርግ ለነበርን አንባቢዎች በነዚህ በሁለቱ ላይ በተሰነዘረዉ ሚዛናዊ ያልሆነ ነቀፈታ ምክንያት ተስፋችን እንዲጨልም ሆኗል፡፡

በሁለቱ የቀድሞ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ሲሰጥ የቆየዉ አስተያየት በአብዛኛዉ ነቀፌታና እንዳንዴም በጥላቻ የታጀበ ዘለፋ መሆኑን ለተገነዘበ ሰዉ ዳግመኛ ለመጻፍ ይቃጣሉ ብሎ ለመገመት ይቸግረዋል፡፡እስካሁን ሲቀርቡ የነበሩ አስተያየቶችን በሶስት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

የመጀመሪያዉ ጎራ ዉስጥ የሚካተተዉ የእነ ጄነራል አበበ ጽሁፎችን ዓላማ ለሃገሪቱና ለህዝቡ ታስቦ ሳይሆን ስርአቱንና ኢህአዴግን በተለይም ወያኔን ከተጋረጠበት አደጋ ለማዳን የተደረገ አጉል መፍጨርጨር ተደርጎ የተገለጸበት ነዉ፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ጄነራሎች በተለያዩ ጊዜያት ሲሰጡ የነበረዉ ቃለምልልስም ሆነ የሚጽፏቸዉ ጽሁፎች ዓላማ ለኢትዮጵያ ታስቦ የተደረገ ሳይሆን ወያኔን አሁን ከገባበት አጣብቂኝ ለማዉጣትና ብሎም የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ ነዉ የሚል ነዉ፡፡ በዚህ መሰረትም የመልእክቱ ይዘት ምንም ይሁን ምን ጸሃፊዎቹ መወገዝ አለባቸዉ በሚል በጅምላ የዉግዘት ዉርጅብኝ ሲወርድባቸዉ ቆይቷል፡፡

በሁለተኛዉ ጎራ ደግሞ የሚካተቱት ጄነራሎቹ ያነሱትን ሃሳብ ቁምነገርና ጠቀሜታዉን ተቀብለዉ ነገር ግን ለኢህአዴግና ለትግራይ ህዝብ በጭፍን ካላቸዉ ጥላቻ የተነሳ “ትግሬን ማመን አይቻልም፡፡ ‹‹ሌላ ተንኮል አስበዉ ይሆናል እንጂ እንዴት አንድ ባለስልጣን የነበረ ትግሬ በዚህ መንገድ ህወሃትን የሚያጥላላ ነገር ሊጽፍ ይችላል?›› ከሚል ጥርጣሬና ጥላቻ የመነጨ ነዉ፡፡

ሶስተኛዉ ጎራ ያሉት ደግሞ እነ ጄነራል አበበ የሰጡትን አስተያየት በበጎ ጎኑ በመመዘን “ጠቀሜታዉ ለሁላችንም ስለሆነ ለወደፊቱም በዚሁ እንዲገፉበት ሊበረታቱ ይገባል” የሚሉ ናቸዉ፡፡ “ትላንት የነበራቸዉን አመለካከት ሳይሆን ዛሬ የያዙት አቋም ነዉ ሊታይ የሚገባዉ፡፡ ስለዚህ ሊደመጡ ይገባል” የሚሉ ናቸዉ፡፡

እነ ጄነራል አበበን “ለኢትዮጵያ አስበዉ አይደለም የጻፉት” በሚል የሚተቹ ወገኖች እነሱ ራሳቸዉ እነ ጄነራል አበበ ላይ የትችት ዉርጅብኝ እያወረዱ ያሉት ለኢትዮጵያ አስበዉ እንዳልሆነ እኛም እነሱ ራሳቸዉም ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከትችት አቅራቢዎቹና ነቃፊዎቹ መካከል የቀድሞ የትግል ጓደቻቸዉ መኖራቸዉን ስናዉቅ መገረማችን አይቀርም፡፡ በተለይ ነባሮቹ (ትላልቆቹ) ኢህአዴጎች እያሉ ግልገል ካድሬዎቹ በጣም አምርሬዉ መቆጣታቸዉ አስገራሚ ነዉ የሆነብኝ፡፡ ለኢህአዴግ የወገኑና ኢህአዴግን የጠቀሙ እየመሰላቸዉ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ተፈጠረ የሚሉትን ሁኔታ ድጋሚ ነፍስ እየዘሩበት “ለምን አርፈዉ አይቀመጡም እንዴት ቢዳፈሩ ነዉ ኢህአዴግን የሚተች አስተያየት የሚሰጡት” እያሉ በቁጣና በደም ፍላት በእጃቸዉ ባለዉ ሚዲያ ሁሉ እየተቀባበሉ ይዘምቱባቸዋል፡፡

እኔ በዚህ ጽሁፍ በሁለቱ ሰዎች ላይ የተሰነዘረዉን ትችት ለማስተባበልና ለነሱ ጥብቅና ቆሜ ለመከራከር አልተነሳሁም፡፡ አንደኛ ለነሱም ሆነ ለማንም ጥብቅና ለመቆም ፍላጎቱ የለኝም፡፡ ሁለተኛ የተጠቀሱት ሰዎች ለትችት የማይነበረከኩ መሆናቸዉን ጠንቅቄ ስለምረዳ ከፈለጉ እነሱ ራሳቸዉ ማድረግ የሚገባቸዉን እኔ እነሱን ወክዬ ክርክር ለመግጠም ዓላማም አቅሙም የለኝም፡፡

በተለያዩ ሚዲያዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸዉ ጽሁፎችን ባነብም ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ እኔ አዘዉትሬ በምከታተለዉ ሆርን አፌየርስ (Horn Affairs) ላይ የተለቀቀዉ የአቶ መሃሪ ይፍጠር ጽሁፍ ነዉ፡፡ ጄነራል አበበ ከዚህ በፊት የመከላከያ ሰራዊቱን የግንባታ መመሪያን አስመልክተዉ በሰጡት የግል አስተያየት ላይ መልስ በመስጠት ሽፋን “አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት….”በሚል ርእስ በዚህ በሆርን አፋዬርስ ላይ ለመዝለፍ የተሞከረበትን ጽሁፍ ደጋግሜ አንብቤአለሁ፡፡ የአቶ መሃሪ ይፍጠር ጽሁፍ ዓላማዉን በቅጡ ለመረዳት ቢያዳግተኝም ጄ/ል አበበን ለመዝለፍ አመቺ ጊዜ ሲጠብቅ ቆይቶ, ልክ በድንገት ሲያገኟቸዉ የፈሪ ዱላ ይመስል በወታደር ቤት ዉስጥ “የጃርት ስልት“ (The Porcupine Approach) እንደሚባለዉ ያገኘዉን ሁሉ በመወርወር ለማጥቃት መፈለጉን ብቻ ነዉ ለመረዳት የቻልኩት፡፡ ጃርት መርዘኛ የሆኑ በብዙ ደርዘን የሚቆጠር ተፈጥሮአዊ ቀስት ያላት ሲሆን ድንገት አደጋ ሲገጠማት አንድም ሳታስቀር በአንድ ጊዜ ብትወነጭፍም ዒላማዋን ለመምታቷ ግን እርግጠኛ አይደለችም፡፡ አቶ መሃሪም ጆቤን የመሰለ መንፌሴ ብርቱ በዚህ ትችቶ ተደነጋግጠዉ ዳግመኛ ሃሳባቸዉን ከመግለጽ ተቆጥበዉ አርፈዉ ይቀመጣሉ ብለ ገምቶ ከሆነ እንደዚያ እንደማይሆን ከአሁኑ ቁርጡን ሊዉቀዉ ይገባል፡፡

ለህዝቦች መብት መከበር ብሎ ለሁለት አስርተ አመታት ላላነሰ ጊዜ በበረሃ ሲፋለምና በተደጋጋሚ በመቁሰል ደሙን ሲያፈስ ለኖረና ዛሬም በዚህ እድሜዉ ለወጣቶች ልምዱን ለማካፈል ጥረት ለሚያደርግ አዛዉንት ይሄን ያህል ዘለፋ የሚገባም አልነበረም፡፡ “ጆቤ ለምን ተነኩ፤ለምን ትችት ቀረበባቸዉ?” የሚል አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አፍራሽና ዘረኛ ቅስቀሳ እያደረጉ እርስ በርሳችን ሊያጫርሱን የሚፈለጉ ስንት መሰሪዎችን ተረባርበን ልንዘምትባቸዉ በሚገባን ሰዓት የሀገሩ ጉዳይ አሳስቦት ገንቢ አስተያየት በሰጠ በራስ ወገን ላይ መዝመት ተገቢ አይደለም፡፡ ሰዉ ለምን በሀገሩ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሰጠ፤ ለምን መከላከያዉ ላይ የእርምት ሃሳብ አቀረበ ተብሎ ሊዘለፍ ይገባዋል እንዴ? በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ ሽንጡን ገትሮ ለሻዕቢያ የሚሟገት ስንት መሰሪ በሞላበት አገር ለሃገሩ በታገለና ለዚህ ስርአት መምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ ባደረገ ጀግና ላይ ገና ለገና የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ይዟል ተብሎ ያን ያህል መረን የለቀቀና ጭካኔ የተሞላበት ክብርን ዝቅ የሚያደረግ ዉርጅብኝ ማዉረድ በጭራሽ የሚገባ አልነበረም፡፡

ለምን እንደሆነ ባይገባኝም በእኛ አገር እጅግ የተለመደ መጥፎ ልማድ ቢኖር ትላንት ስንት ሲባልላቸዉና ሲዘመርላቸዉ የቆዩ፤ ከህዝቡ ከበሬታን አትርፈዉ የነበሩ፤ የሀገር ባለዉለታ የሆኑ ሰዎች በሆነ አጋጣሚ ተደነቃቅፈዉ ሲወድቁ ወይም በአመለካከትና በአካሄድ ልዩነት ከመድረኩ ሲወርዱ የማሪያም ጠላት ይመስል ተረባርበን ማዋረድን እንደጥሩ ልማድ መያዛችን ነዉ፡፡ ለሀገራቸዉ ስንት የደከሙትን ማንም ይነሳና እንዳሻዉ ይሳደባል፡፡ ከዚህ በፊትም የቀድሞዉ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄ/ል ጻድቃን ታግለዉ ባመጡት ስርአትና በሀገራቸዉ ላይ አደጋ መጋረጡ አስግቷቸዉ ከችግር መዉጫ ሊሆን ይችላል ቢለዉ ያሰቡትን የመፍትሄ ሃሳብ በዚሁ በሆርን አፌየርስ ላይ ማቅረባቸዉን እናስታዉሳለን፡፡ ጄ/ል ጻድቃንን ለዚህ ጥረታቸዉ ከማመስገንና ከማበረታታት ይልቅ አንዳንዶቻችን የሌለ ስም እየሰጠን ለማብጠልጠል ሞክረናል፡፡ በዉጭ አገር ያሉ ስርአቱን በእጅጉ የሚጠሉ ዲያስፖራዎች የጄ/ል ጻድቃንን ጽሁፍ በበጎ ጎኑ ሊያዩት አልፈለጉም፡፡ ኢህአዴግ እየወደቀ ነዉ ብለዉ ለተማመኑት እነዚህ ዲያስፖራዎች የጻድቃን ጽሁፍ ዓላማ ለሀገሪቱ ታስቦ ሳይሆን ኢህአዴግን በተለይም ህወሃትን ከዉድቀት ለማዳን ያለመ ነዉ የሚል ትርጉም ሰጥተዉት ለበርካታ ሳምንታት በዘመቻ መልክ ከዚህም ከዚያም እየተቀባበሉ ሲዘልፉአቸዉ ነበር፡፡ ስርአቱን ለሚጠሉት እነዚህ ኃይሎች ከዘለፋም ባለፈ ሌላ ነገር ቢሉ ብዙም የሚያስገርም አይደለም፡፡

ነገር ግን እጅግ የሚያሳዝነዉ ለስርአቱ ደጋፊ ነኝ ከሚሉ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ ጻድቃን “እንዴት ቢዳፈር ነዉ የኢህአዴግን ድክመት በአደባባይ የሚናገረዉና የሚተቸዉ” በሚል እሳቤ ተነስተዉ የጭቃ ጅራፋቸዉን ሲያጮሁባቸዉ እኛም እየሰማን በጣም አዝነን ዝም አልን፡፡ አንዳንድ ዘረኞች ደግሞ ጄ/ል ጻድቃን ትግርኛ ተናጋሪና የቀድሞ የህወኃት ታጋይ ስለነበሩ ብቻ ያቀረቡት ሃሳብ ሁላችንንም የሚጠቅም መሆኑ ለመረዳት ሳይቸግራቸዉ ነገር ግን ዘረኛ አመለካካታቸዉ በማየሉ “አንድ ወያኔ መቼም ደህና ነገር ስለማያስብ ሌላ ስዉር ዓላማ ይኖራዋል እንጂ አለነገር እንዲህ አይጽፍም ነበር” ተብለዉ ሲነቀፉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ዉሌታቸዉ ልናመሰግናቸዉ የሚገባን ሰዎችም መሰሪ ዓላማ ካላቸዉ ሰዎች ባልተናነሰ ሁኔታ ተቸናቸዉ፡፡ በጄ/ል ጻድቃን ላይ ባልሰሩት ሃጥያት ከድሮ ጓዶቻቸዉ ሳይቀር እየቀረበባቸዉ በነበረዉ ዓላማ ቢስ ትችት ተቃወሚዎች ሳይቀሩ በሁኔታዉ በመገረም ኢህአዴግን በዚህ ደርጊቱ እጅጉን ተሳልቀዉበታል፡፡ “ድሮም ወያኔ እንኳን ለሌላዉ ህዝብ ይቅርና ብዙ ለደከመለትና ለሰራለትም ጭምር የሚጨክን ዉለታ ቢስ ነዉ” እያሉ ተዘባብተዉበታል፡፡

ጄ/ል አበበ ከጄ/ል ጻድቃን በበለጠ (በተደጋጋሚ) ሃሳባቸዉንና አመለካከታቸዉን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲገልጹ እንደነበር አዉቃለሁ፡፡ ጄነራል አበበ (ጆቤ) በየጊዜዉ ከሚያነሱአቸዉ ጉዳዮች መካከል እኔ የምስማማበትም የማልስማማበትም ቢኖርም ነገር ግን ለምን ጻፉ ብዬ ወደ መተቸት አልገባሁም፡፡ ጆቤ አሁን ያሉበት የስራ ባህሪይ በፈጠረላቸዉ ዕድል ምቹነት የተነሳ ከበርካታ ምሁራን ጋር የሃሳብ ልዉዉጥ የማድረግ፤ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ የመቅሰምና ድሮ እንደዋዛ ተቀብለዉ ወይም ተቃዉመዉ ባለፉት ጉዳይ ላይ ድጋሚ ምርምርና ጥናት በማድረግ የጠራ አመለካከት ለመያዝ ሰፊ አጋጣሚ ሲላላቸዉ አንዳንዴ እሳቸዉ የሚሰነዝሩት አስተያየት ላይመቸንና ላይስማማን ቢችል ችግሩ የሳቸዉ ሳይሆን የኛ አላዋቂነት ወይም ደደብነት ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ በአገራችን መጥፎ ልማድ ሆኖ ትላንት ሰማይ ጥግ ድረስ ስንክባቸዉ የነበሩትን ዛሬ ከኛ የተለየ አመለካከት ስለያዙ ብቻ እንደ ጠላት ተቆጥረዉ በአደባባይ ይዘለፋሉ፡፡ እኛ ስለ ጠላናቸዉ ሌላዉ ህዝብም እኛን ተከትሎ እንዲጠላቸዉ እንፈልጋለን፤ የቤተሰብ ሃላፊነት ያለባቸዉና እጃቸዉን ጠብቆ የሚኖር ቤተሰብ እንዳላቸዉ ይዘነጋና በገዛ ጥረታቸዉ ራሳቸዉን ለማሸነፍ የሚያደርጉት መፍጨርጨርን በበጎ ጎኑ አናይም፤ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ “ስለማሪያም፤ በአላህ ብላችሁ እርዱኝ” እያለ መጽዋእት ሲለምን ማየት እንመኛለን፡፡

ጄ/ል ጻድቃን በወጭ አገር ተቀጥረዉ በሙያቸዉ ሰርተዉ ኑሮን ለማሸነፍ ያደረጉትን መፍጨርጨር ማበረታታት ሲጋብን እንዴት ወደ ልመና አልገቡም ብለን በቅናት መንፈስ የፈጠራ ወሬ እናስወራባቸዋለን፡፡ ጆቤን በሚመለከትም እንዲያዉም ለብዙዎቻችን አርአያ በሆኑበት ተግባር ማድነቅ ሲገባንና የሁላችንም የጋራ ጥያቄ በሆነዉ በወደብ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ በጥናት የተደገፈ እጅግ ጠቃሚ ጽሁፍ በማቅረብ የዜግነታቸዉን ግዴታ ስለተወጡ ከማመስገን ይልቅ በንዴት ስንዘልፋቸዉ ነበርን፡፡ አሳቸዉ በአደባባይና በይፋ ያቀረቡትን ሃሳብ ያልጣመዉ ሰዉ ካለ ማስረጃ አቅርቦ በአደባባይ ለመሞገት ከመሞከር ይልቅ በር ተዘግቶ ማማትና የለለባቸዉን ስም መለጠፍ ወግ ተብሎ ተይዟል፡፡ አንዴ ኪራይ ሰብሳቢ፤ ሌላ ጊዜ ጠባብ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ትምክህት አራማጅ ወዘተ እያልን የፈሪ ዱላችንን ወረወርንባቸዉ፡፡ ለምን ለኢትዮጵያ ህዘብ ጥቅም ተከራከረ ተብሎ ሰዉ እንዴት ኪራይ ሰብሳቢ ትምክህተኛ ጠባብ ወዘተ ተብሎ ይዘለፋል?

ከሁሉም በላይ የጆቤን ትልቅ ሰብእና የሚያሳየዉ ነገር ጆቤ ከነበሩበት ትልቅ የኃላፊነት ቦታ በአንዴ ቁልቁል ወርደዉ ተስፋ ባለመቁረጥ ማንኛችንም ብንሆን ደግመን ልናደረግ በማንችለዉ ሁኔታና ድሮ በቅርብ ለምናዉቃቸዉ ሰዎች መገመት እንኳን በሚያስቸግረን መልኩ ከትግሉ በፊት አቋርጠዉት የነበረዉን የዩኒቬርስቲ ትምህርት ለመቀጠል እንደ ተራ ተማሪ እርሳስና ደብተር ይዘዉ ሳይሸማቀቁና ድሮ በነበራቸዉ ክብርና አሁን ባሉበት ሁኔታ ልዩነት ሳያፍሩ በዕድሜና በህይወት ተሞክሮ ከሚያንሷቸዉ ተማሪዎች ጋር እየተጋፉ ቀጥ አድርገዉ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ይሄዉ ዛሬ ደግሞ ለሶስተኛ ደግሪያቸዉ እየተዘጋጁ መሆናቸዉን ነዉ፡፡ ስለ ጆቤ ሁኔታ የሰማን ሰዎች ምን ዓይነት ታላቅ የሞራል ጽናት እንዳላቸዉ በመረዳታችን ሳናደንቃቸዉ አልቀረንም፡፡ እንደሳቸዉ ያለ ሰዉ ማግኘት ብርቅ በሆነበት በዛሬዉ ዘመን በሀገሪቱ ቴሌቪዥን እያቀረብን በአርአያነታቸዉ ወጣቶች ልምድ እንዲቀስሙ ከማድረግና በአርአያነታቸዉ መሸለምና መደነቅ ሲገባቸዉ ጭራሽ ለምን አስተያየት ሰጡ ብለን በሰበብ ባስባቡ መተቸታችን እጅግ የሚያሳዝን ነዉ፡፡ አንድ ዘፋኝ የዘፈን ክሊፕ አወጣ ተብሎ ነጋ ጠባ እንደ ጀግና በሚወደስበት አገር ለሀገራቸዉ ብዙ የደከሙ አንጋፋ ኢትጵያዉያን የሚያስታዉሳቸዉ መጥፋቱ ሳያንስ ጭራሽ “በአገራቸዉ ጉዳይ ለምን ጻፉ? ለምን ተናገሩ?“ ተብለዉ ይወቀሳሉ፡፡

ወደ ትችቱ አቅራቢዉ (አቶ መሃሪ) ልመለስና ፤ አቶ መሃሪ ጄ/ል አበበን በአካል አላዉቃቸዉም እያለ ያንን ሁሉ ወንጀል ለመደፍደፍ የሚያስችለዉን ክስ እንዴት ሊያዘጋጅ እንደበቃ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ጄ/ል አበበ ለክቡር ጄነራል ሳሞራ የኑስ፤ ጄል ሳሞራም ለቀድሞ ጓዳቸዉ ለጄ/ል አበበ፤ አንዳቸዉ ለሌላዉ በግላቸዉ ምን ያህል አክብሮትና አድናቆት እንዳላቸዉ በሚገባ ሳያጤን በግምት ብቻ ተነሳስቶ ሁለቱ ደመኛ ጠላት እንደሆኑ አድርጎ በመቁጠር ጭራሽ የበለጠ ለማጋጨት ሞክሯል፡፡

ጀነራል አበበ በወቅቱ በተፈጠረዉ መጥፎ አጋጣሚ ከታገሉለት ድርጅት አመራሮች ጋር ተቀያይመዉ ካገለገሉበትና ድንቅ አመራር ሲሰጡበት ከነበረዉ የመከላከያ ተቋም (የአየር ኃይል) ለቀዉ ቢወጡም ታግለዉ እዉን ባደረጉት ለዚህ ስርአት ጠንቅ እንደሆኑ ተደርገዉ ሊቆጠሩ ባልተገባ ነበር፡፡ ከድሮ የሥራ ጓዶቻቸዉ፤ ከመከላከያ ባለስልጣናትና ከፍተኛ ጄነራል መኮንኖች ጋር እንዲሁም ከድርጅቱ አመራሮች ጋርም በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚገናኙ እንደዚሁ በደመነፍስ መገመት አያዳግተኝም፡፡ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያዋ እንስት ጀነራል ማን እንደሆነች ጸሃፊዉ ጠይቆ ቢረዳ ኖሮ ጆቤ ቢያንስ ከመከላከያ ጋር ምን ያህል የማይበጠስ ቁርኝት እንዳላቸዉ መረዳት የሚያዳግት ባልሆነ ነበር፡፡

ጄነራል አበበም ሆኑ ጄነራል ጻድቃን በሆነ አጋጣሚ ከአመራሩ ጋር ለጊዜዉ ስለተቀያየሙ ብቻ ሃሳባቸዉን ለምን ገለጹ ተብለዉ ሊከለከሉና ሊዘለፉ ይገባል እንዴ? ለዚህ ስርአት እዉን መሆን ብዙ የደከሙ ሰዎች ራሳቸዉ በመሰረቱት ስርአት ዉስጥ ሃሳባቸዉን እንዳይገልጹ ገደብ ከተጣለባቸዉ ሌላዉ እንደእኔ ያለዉ ተራዉ ህዝብ እንዴት አድርጎ ነዉ ትንፍሽ ለማለት የሚደፍረዉ? በእዉነቱ አቶ መሃሪ በጆቤ ላይ ያን ሁሉ ዉርጅብኝና ክስ ያቀረበዉ ለኢህአዴግ ወይም ለመከላከያ ሰራዊቱ ተቆርቁሮ እንዳልሆነ ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡

እነጄ/ል ጻድቃንንና ጄ/ል አበበን በስርአቱ ጠንቅነት የሚፈርጅና የሚዘልፍ ሰዉ ዛሬ የሃገራችን መኩሪያ የሆኑትን ክቡር ጄ/ል ሳሞራን ባመሰገነበት አንደበት በሌላ ጊዜ ተመልሶ እንደማይዘልፋቸዉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ጄ/ል ሳሞራን ከፍ ከፍ ለማድረግ ተብሎ ከሳቸዉ በፊት በተመሳሳይ ሃላፊነት የሰሩትን ጄ/ል ጻድቃንን ክብር መንፈግ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ጄነራል ሳሞራን ስናከብራቸዉ የነበረዉ አሁን በያዙት ሃላፊነት ምክንያት ሳይሆን ገና ኤታማዦር ሹም ሳይሆኑ በፊት ጀምሮ ነዉ፡፡ እነ ጄ/ል ጻድቃንም በነበሩ ጊዜም ቢሆን ጄ/ል ሳሞራ እጅግ የምናከብራቸዉና የምንኮራባቸዉ ነበሩ፡፡ እሳቸዉን ያስደሰትን እየመሰለን የድሮ ጓዶቻቸዉን ዝቅ ዝቅ ስናደርግ እሳቸዉም ቢሆኑ ሳይታዘቡን የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡

የሰዎችን ዉለታ ለምን እንደምንክድ አይገባኝምም፡፡ ጊዜዉን በትክክል በማላስታዉሰዉ ከጥቂት ዓመታት በፊትም ተመሳሳይ ነገር ታዝቤአለሁ፡፡ ጄ/ል ጻድቃን ስለ ትግሉ ዘመንና በኋላም ከኤርትራ ጋር ስለተካደዉ ጦርነት የሰጡትን ቃለ ምልልስ ተንተርሶ አንድ የመከላከያ አባል ነኝ ያለ ግለሰብ በትግሉ ጊዜም ሆነ ከኤርትራ ጋር በነበረን ጦርነት ወቅት ጻድቃን ጭራሽ አመራር ሰጥተዉ እንደማያዉቁና አንድም ሚና እንዳልነበራቸዉ በማድረግ (በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ይመስለኛል) ደማቅ ታሪካቸዉንና ዉሌታቸዉን በመካድ የሞነጫጨረዉን ጽሁፍ አንብቤ እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ጸሃፊዉ በድርጊቱ ማፈር ሲገባዉ ጭራሽ ትልቅ ጀብዱ የሰራ ይመስል የመከላከያ አባል መሆኑን ገልጾ መጻፉን ሳስብ ለሱ ሃፍረት ነዉ የተሰማኝ፡፡ ጸሃፊዉ ከጄነራሉ ጋር አብሮአቸዉ በትግሉ ጊዜ ጀምሮ የነበረና ከሁላችንም በተሻለ ያዉቃቸዉ እንደነበረ ከአጻጻፉና ከሰጣቸዉ መረጃዎች ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡ የኦፕሬሽን ዕቅዶችና ሁሉ በቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር (ነፍሳቸዉን ይማርና በአቶ መለስ ዜናዊ) የተዘጋጁና የቅርብ አመራርም ሲሰጡ የነበረዉ እሳቸዉ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ በመግለጽ ጄ/ል ጻድቃን ግን አንዳችም ድርሻ እንዳልነበራቸዉ አድርጎ ነበር የጻፈዉ፡፡

አቶ መለስ ወታደራዊ ጠቢብ እንደነበሩና በወታደራዊ ጉዳዮች እጅግ የጠለቀ እዉቀት እንደነበራቸዉ መረጃዉ ብኖረኝም እሳቸዉን ለመካብ ተብሎ እሳቸዉ ራሳቸዉ በኤታማዦርነት ሹመዉ ሲያሰሩ የነበሩትን ጀ/ል ጻድቃን ማንኳሰሱ ተገቢ አይሆንም፡፡ አቶ መለስና የጄነራል ጻድቃን ሃላፊነት ድርሻም የተለያየ መሆኑን ዘንግቶ አቶ መለስ ጦር ግንባር ላይ ተገኝተዉ ዉጊያ እንደሚመሩ ዓይነት ማስመሰሉ አስገራሚ ነዉ፡፡ አብሮአቸዉ ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ የቆየ አንድ ነባር ታጋይ ይቅርና በተቃራኒዉ ጎራ ተሰልፎ የነበረዉ የደርግ ሰራዊት (አብዮታዊ ሰራዊት) ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ የኃየሎም አርአያን፤የሳሞራ የኑስን፤ የጻድቃንና የስዬ አብርሀን ጀግንነት ቀድሞዉን ጠንቅቀዉ ያዉቁ ነበር፡፡ እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ ይሄን ያህል ጫና አድርጌ መግለጼ ሁኔታዉ እጅግ ሲላሳዘነኝና የዚህ ዓይነት ክህደት አሁን ብቻ ሳይሆን ቀደም ቢሎም ጀምሮ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሲደጋገም የነበረና አሁንም እየታየ ስለሆነ ነዉ፡፡ርካሽ መወደድ ለማትረፍ ሲባል የሀገር ባለዉሌታ የነበሩ ሰዎችን በሰበብ አስባቡ ማዋረድ መቼ እንደምናቆም አይገባኝም፡፡

“ስለ መከላከያ ሰራዊቱ ለምን ይጻፋል?ለምንስ በአደባባይ ስሙ ይነሳል? ለምንስ ትችት ይቀርባል?” የሚሉ ወገኖች ለመከላከያ ሰራዊቱ ካላቸዉ ፍቅርና ተቆርቋሪነት ስሜት እንዳልሆነ አዉቃለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ መከላከያ ሰራዊታችን ገንቢ አስተያትና እርምት የሚሰጡ ወገኖች ለመከላከያ ሰራዊቱ ጥላቻ ስላላቸዉ እንዳልሆነም አዉቃለሁ፡፡ ህዝቡ በተለይም ሀገር ወዳድ የሆኑ ምሁራን መከላከያ ሰራዊቱን በሚመለከት በጥናትና በምርምር የተደገፈ አስተያየት ቢሰጡ ከሁሉም በላይ ተጠቃሚ የሚሆነዉ መከላከያ ተ,ቋሙ ነዉ፡፡ ህዝቡ ስለ ገዛ ሰራዊቱ እንዳይናገር እንዳይተች ከከለከልነዉ ማነዉ መከላከያን በሚመለከት ለመናገር የተለየ መብት ሊኖረዉ የሚችለዉ? በኛ ሀገር ያለዉ ችግር ስለመከላከያ ሰራዊቱ መተቸቱ ያመጣዉ ችግር ሳይሆን ጭራሽ ሲተች አለማየታችን ነዉ፡፡ ህዝቡ መተቸትና አስተያየት መስጠት ካለበትም ከሁሉም መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ይበልጥ በመከላከያ ተቋሙ ላይ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በግሌ ሳስበዉ ከሁሉም መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ሁሉ የተሻለ ህዝባዊ ተአማንነትና ቅቡልነት ወይም ከበሬታ ያለዉ መከላከያ ሰራዊታችን ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ፡፡ ከሀገሪቱ ህግ አዉጭዉና የፍትህ አካላትም በበለጠ በህዝቡ ዘንድ ተአማንነት ያለዉ መከላከያችን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከነጉድፉና ከነችግሩም ቢሆን ማለቴ ነዉ፡፡ አይደለም የሚል ሰዉ ካለ ማስረጃ አቅርቦ ልሞግተኝ ይችላል፡፡ ማንም ማስረጃ ሊያመጣ እንደማይችልም ጠንቅቄ አዉቃለሁ፡፡ እኔም ብሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ማስረጃ የለኝም፡፡ ቢያንስ ግን ዉስጡ ስለነበርኩና በሁሉም ነገረ ስራዬ ሆን ብዬ ይህን ጉዳይ አጥብቄ ስከታተል ስለነበርኩ ያለ ማስረጃ ከሚሞግቱኝ የተሻለ ምክንያታዊ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥናት አለመደረጉና የህዝብ አስተያየት አለመሰባሰቡ የእኔ የብቻ ችግር ሳይሆን የሁላችንም ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ፡፡ ምክንያቱም በአገራችን በምንም ነገር ላይ ጥናት አይደረግም፡፡ ማንም ምሁር በየትኛዉም ጉዳይ ላይ በተለይም መከላከያና ደህንነት በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጥናት በማድረግ በይፋ ለመወያትና አስተያየት ለመስጠት የሚፈልግ ወይም የሚደፍር አይኖርም፡፡ ቢናገር የሚያዳምጠዉ ቢጽፍ የሚያነብለት አያገኝም፡፡ በዚህ ምክንያትም በምርምር የተደገፈ መረጃ ማቅረብ የሚችል አካል ስለማይኖር ይሄን ነገር ከየት አመጣኸዉ ልባል አይገባኝም፡፡ ቢያንስ እየገለጽኩ ያለሁት ዉስጤ የሚሰማኝኝ ስለሆነ ነዉ፡፡

በሌሎች አገሮች ስለ ሃገራቸዉም ሆነ ስለ ሌሎች ሃገሮች የመከላከያና ደህንነት ተቋማት ምርምር የሚያደርጉ ዩኒቨርስቲዎች፤ፋካልቲዎችና የምርምር ተቋማት እንዳሉ ጠንቅቄ አዉቃለሁ፡፡በየጊዜዉ በምርምር የተደገፈ የጥናት ጽሁፎችን ያትማሉ፡፡ ስለ መከላከያ ሰራዊታቸዉ ዉይይትና ምክክር ያደርጋሉ፡፡ በወታደራዊ ኮሌጆች ከሚያስተምሩ መምህራን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሲቪሎች ናቸዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊታቸዉ ለህዝብ ታማኝ እንዲሆንና በኩዴታና የመሳሳሰሉት ጣልቃገብነቶች ዉስጥ እንዳይገባ ማድረግ የቻሉት በሲቪሉ ህዝብ፤ በምሁራን፤ በሚዲያ ሰዎች ወዘተ የጋራ ጥረት እንጂ በተአምር የሆነ አይደለም፡፡

በበባረሰላጤዉ፤ በአፍጋኒስታንና በዩጎዝላቪያ ጦር ለማዝመት ወታደራዊ ጣልቃ መግባት አግባብነትና አዋጭነት ላይ ምክክር ሲደረግ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሲመካከሩ የነበሩት ከጦር ጀኔራሎች ጋር ብቻ ሳይሆን በይበልጥም ከሲቪል ምሁራንና ፖለቲከኞች ጋር ነዉ፡፡ በአሜሪካ አንድ ጋዘጤኛ በሃገራችን ከመንግስት ቃል አቀባይ የበለጠ በህዝብ አሜነታና ተደማጭነት አለዉ፡፡ በአሜሪካ አንድ ዬኒቨርስቲ ምሁር የሚሰጠዉ አስተያየት ከኮንግሬስ አባል ጋር እኩል ተቀባይነት አለዉ፡፡ የሲ.ኤን.ኤን ጋዜጠኛ የሚሰጠዉ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ተንተናና አስተያየት የሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ምከር ቤት ኤክስፔርት ወይም የመከላከያ ሚኒስቴር ባለሙያ ከሚሰጠዉ አስተያየት ባልተናነሰ ደረጃ ይደመጣል፡፡

በአሜሪካ፤በካናዳ፤በኢንግሊዝና በሌሎች ዲሞክራትክ ሀገሮች በሲቪል-ወታደር ግኑኝነት(civil- military relation) ፤በወታደራዊ አንተርፖለጂ ፤ሶሲዮሎጂና ወታደራዊ ሳይኮሎጂ ወዘተ መስክ ምርምር በማድረግ እጅግ የከበረ ስም ያላቸዉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ሲቪል ምሁራን ናቸዉ፡፡ በዚህ መስክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ እጅግ የታወቁ ምሁራን መካከል ለአብነት ያህል ለመጥቀስ ሳሙኤል ሀንትንግተን (Samuel Huntington)፣ ሞሪዝ ጃኖዊትዝ (Morris Janowitz)፣ ቻርሊስ ሞስኮስና ጄምስ ቡርክ (Charles Moskos and James Burk )፣ ሬቤካ እስችፍ(Rebecca L. Schiff)፣ ፒቴር ፊቬር( Peter D. Feaver) ኤሪክ ኖርድሊንገር(Eric Nordlinger)ሪቻርድ ኮህን(Richard H. Kohn) እና ቡርኒኦ (Burneau) ወዘተ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፤

የአሜሪካን፤ የካናዳንና የኢንግሊዝን መከላከያ ሰራዊት ለሲቪሉ ፍጹም ታዛዥ እንዲሆን እየኮተኮቱ የቀረጹት ወታደራዊ ጄነራሎች ሳይሆኑ ሲቪል ምሁራን ናቸዉ፡፡ ሰራዊቱን ለህዝቡ ከበረታ እንዲኖረዉ ያደረጉት ህዝቡ፤ሚዲያዉ፤ ሲቪል ማህበረሰቡ፤ ፖለቲከኞች ሁሉም ተባብረዉ ነዉ እንጂ መንግስት ብቻዉን አይደለም፡፡ ዩንቨርስቲዎች፤ የምርምር ተቋማትና ነጻ ሚዲያዎች በመከላከያቸዉ አካባቢ አንድ ጉድፍ ካዩ ወዲዉኑ ነዉ ተረባርበዉ የሚያስተካክሉት፡፡ የቬትናምን ጦርነት ያስቆመዉ የአሜሪካ መንግስት ሳይሆን ሚዲያዉና ምሁራን ናቸዉ፡፡

በሶማሊያ የአሜሪካ ሰራዊት ለቆ እንዲወጣ ፕሬዝደንቱ ላይ ጫና ያደረገዉ የሀገሪቱ የሚዲያ አዉታር ሲ.ኤን. ኤን(CNN) ነዉ፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሀሪ ትሩማን በኮሪያ ጦርነት፤ ሊንደን ጆንሰን በቬትናም ጦርነት፤ ትልቁ ቡሽ በመጀመሪያዉ የገልፍ ጦርነት መከላከያዉን በሚመለከት የሰሩትን ጥፋቶች እየተከታተሉ ነጻ ሚዲያዉ ለህዝቡ በማድረሱ ነዉ ድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት እንዳይመረጡ የተደረጉት፡፡ በቬትናም ጦርነት ወቅት ያለአግባብ ጭፍጨፋ ያደረጉ የአሜሪካ ወታደሮችን በማጋለጥ መንግስትና መከለከያዉ ሆን ብለዉ ደብቀዉት ያቆዩትን ሚስጥር በማጋለጥና ወደ ህዝቡ ጆሮ እንዲደርስ በማድረግ አጥፊዎች ከስንት አመት በኋላ ለፍርድ ቀርበዉ እንዲቀጡ የተደረገዉ በሚዲያዎች ጥረት ነዉ፡፡ በአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ አባማ አስተዳዳር ዘመን ብቻ በደርዘን የሚቆጠሩ ሲኒየርና እዉቅ የሆኑ ጄነራሎችና አድሚራሎችን ያለ ጊዜያቸዉ በጡረታ እንዲሰናበቱ የተደረገዉም በሚዲዎች አማካኝነት ከህዝቡ በተሰበሰቡ አስተያቶች ላይ ተመርኩዘዉ እንጂ ኦባማ ከነዚህ እዉቅ ጄነራሎች ጋር የግል ጠብ ስለነበራቸዉ አይደለም፡፡ ያን ሁሉ ጄነራል አንድ በአንድ ሲያባርሩ ህዝቡ “ጎሽ አበጀህ!” አላቸዉ እንጂ አልተቃወማቸዉም፡፡

ሌላዉ ቀርቶ በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ ስምና በህዝቡ ዘንድ ከበረታ አትርፈዉ የነበሩትና በጀግንነታቸዉ ሲሞገሱ የነበሩት ጄነራል ዳግላስ ማካርተር በኮሪያ ጦርነት ወቅት ከፕሬዝደንት ሄሪ ትሩማን መመሪያ ዉጭ ጦርነቱን ወደ ቻይና ለማስፋፋት ባደረጉት ሙከራ ከሰራዊቱ እንዲባረሩ ነዉ የተደረጉት፡፡ ስለጉዳዩ በወቅቱ የሰማዉ የአሜሪካ ህዝብ ከዚያ ቀደም ለጄነራሉ አድናቆት የነበረዉ ቢሆንም ከፕሬዝዳንቱ መመሪያ ለማፈንገጥ ባሳዩት የማይገባ ባህሪይ የተነሳ እንዲቀጡ ህዝቡ ራሱ ግፊት እንዳደረገ ይታወቃል፡፡ ህዝቡም ሆነ ፕሬዝዳንት ትሩማን በጄነራሉ ላይ ጥላቻ ስለነበራቸዉ አልነበረም፡፡ ጄነራሉ ምን ያህል ትልቅ ስም የነበራቸዉ መሆኑን የሚያሳየዉ ገና ለገና ወደፊት ጡረታ ሲወጡ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት እጩ አድርጎ ለማስመረጥ የሪፖብሊካኑ ፓርቲ ጡረታ ሳይወጡ በፊት ጀምሮ ማግባባት ይዘዉ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ከሰራዊቱ ከወጡ በኋላ ያ እንደዚያ ሲያደንቃቸዉ የነበረዉ ህዘብ ስለጠላቸዉ በዚህ የህዝብ አስተያየት መነሾ ለእጩነትም አንዳይቀርቡ ተደርገዋል፡፡ የአሜሪካ ህዝብ በምንም ዓይነት ሁኔታ ቢሆን ራሱ በቀጥታ መርጦ በሾመዉ ፕሬዝዳንት ላይ የሚለግምና በአደባባይ ለሚተች ጄነራል ምህረት የለዉም፡፡

እንደዚያም ቢሆን ለሀገራቸዉ ብዙ የሰሩ ጄነራሎች በአሜሪካ እንደ አልባለ ነገር የትም አይጣሉም፡፡ ትላልቅ የሀገሪቱ ኩባኒያዎች ጡረታ የወጡ የቀድሞ ጄነራሎችን በባትሪ እየፈለጉ እግራቸዉ ላይ ወድቀዉ ነዉ የሚቀጥሯቸዉ፡፡ በህዝቡ ዘንድ ባላቸዉ ተቀባይነትና ከበረታ ምክንያት አብይ የሆኑ ክስተቶች በሀገር አቀፍም ሆነ በአለምአቀፍ ደረጃ በተፈጠረ ቁጥር የነሱን አስተያየት ለማወቅ ጥረት ይደረጋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በያንዳንዱ በአሜሪካ የግል የቴሌቭዥኖች፤ ጋዜጦችና ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ በመከላከያና በደህንነት ጉዳዮች የሚያማክሩና ሚዛናዊ የሆነ ሙያዊ ትንታኔ የሚሰጡ የቀድሞ ኮሎነሎችንና ጄነራሎችን ማዬት የተለመደ ነዉ፡፡ ለማንም ሳያዳሉ ሚዛናዊ የሆነ አስተያየትና ትንታኔ ስለሚያደርጉ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸዉ፡፡

በእኛ አገር ሌላዉ ህዝብ ይቅርና መከላከያንና የደህንነት አካሉን በመቆጣጠር ረገድ ሙሉ ስልጣን እንዳለዉ በምናዉቀዉ የሀገሪቱ ህግ አዉጭ (ፓርላማ) ስብሰባ ላይ ስለ መከላከያና የደህንነት ተቋማቱ የተለየ አስተያየትም ሆነ ትችት ሲቀርብ አስካሁን ሰምተን አናዉቅም፡፡ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ሆነን እንዴት ተደርጎ ነዉ ህዝቡና ምሁራኑ መከላከያ ሰራዊታችንን እያረሙና እየገሰጹ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚችሉት? ህዝብ ቀርቶ ለመከላከያ እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸዉ እንደነ ጄ/ል አበበና ጄ/ል ጻድቃን የመሳሰሉትም ጭምር “ለምን አስተያየት ሰጣችሁ“ እየተባሉ በአደባባይ በሚዘለፉበት አገር ሌላዉ ምሁር ምን በወጣኝ ቢሎ ነዉ ትችት የሚያቀርበዉ?መላዉ የሀገራችን ህዝብ በተለይም ምሁራኑ መከላከያዉ የጋራችን ነዉ ብለዉ አስተያየት እንዲሰጡ ከማበረታታት ይልቅ “ከኛ በስተቀር መከላከያን በሚመለከት መናገር አትችሉም” ከተባለና የህዝብ ተቋም መሆኑ ቀርቶ የአንድ ፓርቲ የግል ንብረት መሆን አለበት ብሎ የሚሟገት ሰዉ ባለበት ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነዉ ህዝቡ በመከላከያችን ላይ አመኔታ ሊጥል የሚችለዉ?

3/ እነ / አበበ ተቃዉሟቸዉን ያስተናገዱበት መንገድ የገለልተኝነት ችግር አንድ ማሳያ ነዉ፡፡

የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄ/ል አበበም ሆኑ የቀድሞዉ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄ/ል ጻድቃን ከሰራዊቱ የተገለሉት ወታደራዊ ኩዴታ ስለቃጡ ወይም በሀገር መክዳት ወንጀል ስለተከሰሱ ሳይሆን ከእነሱ በማይጠበቅ ሁኔታ በገለልተኝነት ችግር ምክንያት እንደነበረ እርግጠኛ ባልሆንም የተወሰነ መረጃ አለኝ፡፡ እነሱም ስለዚህ ጉዳይ ዛሬ ቢጠየቁ ጥፋታቸዉን የሚያስተባብሉ አይመስለኝም፡፡

በየትኛዉም ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች የተለመደዉ ነገር ቢኖር አዛዦች ወይም በጥቅሉ ሚሊታሪዉ በህዝብ የተመረጡ ሲቪል ባለስለጣናትን ዉሳኔ መጻረር፤ አልታዘዝም ማለት ወይም በአደባባይ መንቀፍ አይፈቀድለቸዉም፡፡ እንደ አሜሪካ ባሉ በሰለጠነዉ ዓለም ጄነራል መኮንኖች በጠቅላይ አዛዣቸዉ (ፕሬዝዳንቱ) ዉሳኔ ደስተኛ ካልሆኑ ተቃዉሟቸዉን (አለመስማማታቸዉን) የሚገልጹበት የተለመደ አሰራር አለ፡፡ በቅድሚያ ለሃገሪቱ መሪ (ለጠቅላይ አዛዡ) ሊከሰት ስለሚችለዉ አደጋ በመግለጽ ሙያዊ አሰተያየት ወይም ምክር የመስጠት ግዴት አለባቸዉ፡፡ ጠቅላይ አዛዡ በዉሳኔያቸዉ ከጸኑ በቀጣይ ጄነራሎች ሁለት አማራጮች ይኖራቸዋል፡፡ አንደኛዉ በዉሳኔዉ ሳይስማሙም ከነልዩነታቸዉም ሆነዉም እሬት እሬት እያላቸዉም ቢሆን የጠቅላይ አዛዣቸዉን ትእዛዝ አክብረዉ መፈጸም ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ አማራጭ ደግሞ ለጠቅላይ አዛዡ መልቀቂያ አቅርቦ ከሰራዊቱ መሰናበት ነዉ፡፡ ከዚያ በኃላ የሀገሪቱ መሪ ዉሳኔ የሀገሪቱን ጥቅም ይጎዳል የሚል እምነት ካላቸዉ በቀጥታ በሀገሪቱ ህግ አዉጭ ፊት ቀርቦ የተቃዉሞዉን ምክንያትና አደጋዉን በሚመለከት ማብራሪያ መስጠትም ይቻላል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ እንደ ሁኔታዉ ክብደት ሚዲያዎችን (ጋዘጤኞችን) ጋብዞ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ህዝቡ እንዲያዉቅ ማድረግ ነዉ፡፡

እነዚህ ሁለቱ የሀገራችን ከፍተኛ መኮንኖች (እነ ጄ/ል አበበ) የሰሩትን ስህተት ወይም ጥፋት በወቅቱ በትክክል በይፋ ስላልተገለጸ በግምት ብቻ ነዉ መናገር የምችለዉ፡፡ በወቅቱ ገዥዉ ፓርቲዉ የመከፋፈል አደጋ ባጋጠመዉ ወቅት አንዱን ወገን ደግፈዉ መቆማቸዉ እንደነበረ በሰፊዉ ሲወራ ነበር፡፡ የተወራዉ ትክክል ከሆነ ህገ መንግስታዊዉን ድንጋጌ በመጣስ ከገለልተኝነት መርህ ዉጭ ለአንድ ፖለቲካ ቡድን በመወገናቸዉ በሃላፊነት መጠየቃቸዉ ተገቢ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ጠቅላይ አዛዡ እስከሚያሰናብቷቸዉ ድረስ ከመጠበቅ ለምን አስቀድመዉ ራሳቸዉ መልቀቂያ እንዳላቀረቡ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ጥፋት አልሰራንም የሚል እምነት ነበራቸዉ ማለት ነዉ? ወይንስ መልቀቂያ ከማስገባታቸዉ በፊት ለትንሽ ስለተቀደሙ ነዉ? ይህም ሆኖ ሁለቱ እዉቅ ጄነራሎች ጥፋት ማጥፋታቸዉ ተገቢ ባይሆንም ነገር ግን የሀገሪቱን አመራር በአደባባይ ለመተቸት አለመሞከራቸዉና ከዚያም በላይ የትኛዉም ዓይነት አፍራሽ ድርጊት ዉስጥ አለመግባታቸዉ እጅግ የሚያስመሰግናቸዉ ነዉ፡፡ እንግዲህ በዚህ መልክ ከአስራ አምስት ዓመታተት በፊት ከሃላፊነተታቸዉ ለተነሱት ለእነ ጄነራል አበበ ዛሬ በሃገራቸዉ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ሲጀምሩ በአንዳንድ ወገኖች መዘለፋቸዉ ተገቢ አይደለም፡፡

በወታደሩ ልሂቃንና በሲቪል አመራሩ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ተቀራርበዉ ለመፍታት ከመሞከር ሁለቱም በየፊናቸዉ አንዱ ሌላዉን ለመጉዳት የሚጣደፉ ከሆነ የሀገሪቱ ደህንነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በተለይ ወታደራዊ አመራሮች በህዝብ የተመረጡ ወይም ሲቪል ባለስልጠናትን በተለይም ጠቅላይ አዛዣቸዉን በአደባባይ የሚተቹና የሚያናንቁ ከሆነ ለሀገሪቱ አደጋ ማስከተሉ የማይቀር ነዉ፡፡ ወታደራዊ አመራሮች ምንጊዜም ለሲቪል አመራሩ ተገዢና ታዛዥ መሆን አለባቸዉ፡፡ ጄነራል መኮንኖች ከጠቅላይ አዛዣቸዉ ጋር ስምምነት ባጡ ጊዜ ሲቪል አመራሩን በአደባባይ ለመሳጣት መሞከር፤ ወታደራዊ ምስጢሮችን ማዉጣትና በሚዲያ ጠቅላይ አዛዣቸዉን የሚያጥላላ ነገር መናገር አይገባቸዉም፡፡ የማይስማማቸዉ ፖሊሲ ዉሳኔ ወይም ትዕዛዝ ሲኖር በህግ አዉጭዉ ዉስጥ ባሉ አክራሪ ፖለቲከኞችና በተቃዋሚ ፓርቲዎች አማከይነት የማግባባት (ሎቢ) ማድረግ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች እጅግ እየተለመደ የመጣ ክስተት ነዉ፡፡ ያላመኑበትን ዉሳኔ ላይ ከጠቅላይ ኣዛዛቸዉ ጋር ቁጭ ብለዉ በመመካከር ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ በአፈጻጸሙ ላይ የመለገም፤የማጓተት፤ የማደናቀፍ ስልትን (shirking, foot dragging, slow rolling) ሲጠቀሙ ማዬት የተለመደ ነዉ፡፡

ወታደሮች በሲቪል አመራሩ ወሳኝነት ማመን አለባቸዉ፡፡ የሲቪል አመራሩና ወታደራዊ ልሂቃኑ እንደ አጋር መተያየት ሲገባቸዉ አንዱ ለሌላዉ ባላንጣ እንደሆነ አድርገዉ እርስበርስ መጠራጠር አይገባቸዉም፡፡ የሀገሪቱ ሲቪል አመራር ማንኛዉንም ሀገሪቱን ደህንነት የሚመለከቱ ዉሳኔዎችን የሚወስነዉ ከህዝብ የተሰጠዉን አደራና ሃላፊነት መነሻ አድርጎ እንጂ የግል ፍላጎቱን ለማርካት ብሎ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሲቪል አመራሩን ዉሳኔ መቃወም ወይም አልታዘዝም ማለት በሲቪሉ ወሳኝነት እንዳለማመን ነዉ የሚቆጠረዉ፡ ስለዚህ ጉዳይ የሰሜን ካሮላይን ዩኒቬርስቲ የጉዳዩ አጥኚ የሆኑት ሪቻርድ ኮህን ሲገልጹ ሲቪሎች አስፈላጊ መስሎ በታያቸዉ ጉዳይ ላይ ባሻቸዉ መንገድ የመወሰን ሙሉ ስልጣን እንዳላቸዉ ነዉ፡፡ (Richard Kohn: “civilians have the authority to issue virtually any order and organize the military in any fashion they choose“)

ወታደራዊ አመራሮች በሚመለከታቸዉ ወታደራዊና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ላይ ያለምንም መሸማቀቅ ሙያዊ አስተያየትና ምክር ለጠቅላይ ኣዛዣቸዉ የመስጠት ግዴታ አለባቸዉ፡፡ ነገርግን አስተያየታቸዉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና ማድረግና በተለያዩ መንገዶች ማስፈራራት ወዘተ አይገባቸዉም፡፡ ጠቅላይ አዛዡ የጄነራሎችን ምክርና አስተያየት የመቀበል ግዴታ አይኖርበትም፡፡ ስለዚህ አስተያያታቸዉ ለጊዜዉ ተቀባይነት ሲላላገኘ ማኩረፍና ሌላ ሴራ ማዉጠንጠን አይገባቸዉም፡፡

ዴቪድ ፒቴር የተባለዉ የመስኩ ባለሙያ አበክሮ እንደሚገልጸዉ ወታደሮች የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም ላይ የመወሰን ስልጣን እንደለላቸዉና ይህን የማድረግ ሙሉ ስልጣን ያላቸዉ ሲቪሎች ብቻ እንደሆኑ ነዉ፡፡ (Peter Feaver: “Military general is not a position to determine the value of the people. Only civilians can decide the level of acceptable risk for society. Civilians are supposed to remain the political masters. The military quantifies the risk, the civilians judges it. “)

የሲቪል አመራሩ ዉሳኔ የግድ ሊከበር ይገባል ሲባል የሲቪሎች ዉሳኔ ከስህተት የጸዳ ና ሲቪሎች የማይሳሳቱ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ሲቪሎች አስተያየትና ዉሳኔ አንዳንዴ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፡፡ የሰቪሎች አስተያየትና ዉሳኔ ወሳኝ የሚሆነዉም ስለማይሳሳቱ ሳይሆን ማንኛዉንም ዉሳኔ የሚወስኑት ከህዝብ ጥቅም አንጻር እያዩ ስለሆነ ነዉ፡፡ ሲቪል ፖለቲከኞች በሁሉም ጉዳይ ላይ ኤክስፔርት መሆን አይችሉም፡፡ ሁሉን እንዲያዉቁም አይጠበቅባቸዉም፡፡ ሊሳሳቱም ይችላሉ፡፡ ዴቪድ ፒቴር እንደሚለዉ “ሲቪሎች የመሳሳትም መብትም አላቸዉ”፡፡ (Peter Feaver፡ “civilians have the right to be wrong”.) በተመሳሳይ ሁኔታ ሮቤርት ዱልህ እንደሚለዉ በአንድ ጉዳይ ላይ አስፈላጊዉ ልምድና ክህሎት ባይኖራቸዉም እንኳን ሲቪሎች ዉሳኔ ለመወሰን የሚስችላቸዉ ብቃት አለቸዉ ይላል፡፡ (civilians are politically and morally competent to make decision even if they do not posses the relevant expertise.”)

ጄነራሎች የጠቅላይ አዛዣቸዉ ዉሳኔ የማይጥማቸዉ ከሆነ ቅሬታቸዉን ወይም አለመስማማታቸዉን የሚያስተናግዱበት በምዕራቡ ዓለም ተቀባይነት ያገኘ “calculus of dissent” የሚሉትን አማራጭ መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ በተለምዶ ሲሰራበት የነበረዉ “ጭፍን ታማኝነት ወይም ተቋሙን ለቆ መሄድ (loyalty or exit)” የሚባለዉ እጅግ ጠባብ አማራጭ ተቋሙን እጅግ እየጎዳ መምጣቱን ሳይረዱ አልቀሩም፡፡ አንድ ጄነራል በሆነ ጉዳይ ላይ ባልተስማማዉ ቁጥር መልቀቂያ እቀረበ ተቋሙን ለቆ መዉጣት ሀገሪቱን የሚጎዳ ነዉ፡፡ ሰላምታ ሰጥቶ መታዘዝ (salute and obey! ወይም ሰለምታ ሰጥቶ መልቀቂያ አቅርቦ ለቆ መሄድ (salute and resign) ሁለቱም የሚያስከዱ አይደለም፡፡ ቅሬታን አፍኖና ስህተት እያዩ ዝምቢሎ በጭፍን መታዘዝም ሆነ ለምክክር ዕድል ሳይሰጡ ጥሎ መሄድ ሁለቱም ተገቢ አይሆኑም፡፡ የአለመስማማት ምንጭ የሆነዉ ሁኔታ ክብደትና ፋይዳዉ ከግምት ዉስጥ መግባት አለበት፡፡ የጠቅላይ ኣዛዡ ዉሳኔ በሃገሪቱ ጥቅምና ደህንነት ላይ ሊያስከትል የሚችለዉ አደጋ (magnitude of threat) ከፍተኛ ነዉ ብሎ ካሰበ ያለፍርሃት ቀርቦ ማሳመን መቻል አለበት፡፡

4/ የመከላከያ ሰራዊቱን ገለልተኝነት በሚመለከት የጄነራል አበበ (ጆቤ) እይታ ችግር

በሃገሪቱ ዉስጥ የሆነ ችግር በተከሰተ ቁጥር የመከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛነት ጉዳይ እንደ አዲስ በጥያቄ ሲነሳ ይታያል፡፡ የተለያዩ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጡ ሰምተናል፡፡ አንብበናል፡፡ ስሜታዊ ሆነዉ አስተያየት የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ ሚዛናዊ አስተያየት የሚሰጡም አልጠፉም፡፡ በመከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ጉዳዮች ካሉ መንግስት በግልጽ ህብረተሰቡን ሆነ የሚመለከታቸዉ አካላት አወያይቶ አንድ ግንዛቤ ማስያዝ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ክፍተት ካለም ተለይቶ ማስተካከያ እንዲደረግ ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡ የሰራዊቱን ህዝባዊ ተአማንነት ጥያቄ ዉስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ሲኖር ዝም መባል የለበትም፡፡ ችግር መኖሩን የተገነዘበ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ሳይሸማቀቅ ሀሳቡን ማጋራት አለበት፡፡ ከዚህ መሰረታዊ ሃሳብ ስነሳ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሠጡ በርካታ ሰዎች እንደሚኖሩ ባዉቅም ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ የገፋፋኝ ስለዚህ ጉዳይ ጄነራል አበበ የጻፉትን አስተያየትና ያን ተከትሎም በሳቸዉ አስተያየት ላይ በአቶ መሀሪ ይፍጠር የተሰጠዉ ምላሽ ነዉ፡፡

የጄነራል አበበ (ጆቤ) ጽሁፍ ‹‹ህገመንግስቱን የሚጻረረዉ የሰራዊት ግንባታ ሰነድ ይታገድ›› የሚል ርዕስ ያለዉና ለክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኣዛዥ ለአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ ሲሆን ይህንኑ ጽሁፍ ለመተቸት ታስቦ በአቶ መሃሪ የተጻፈዉ ደግሞ “አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት…“ የሚል ርእስ የነበረዉ ነዉ፡፡ በጄ/ል አበበ ጽሁፍ ዉስጥ የቀረበዉ ቁም ነገር የሰራዊት ግንባታ ሰነዱ ከህገመንግስቱ ጋር ይጋጫል በሚል ስጋታቸዉን መግለጻቸዉ ነዉ፡፡ ጆቤ የመከላከያ ሰራዊታችን የገዥዉ ፓርቲ አገልጋይ ሆኗል የሚል ነገር በግልጽ ተናግረዉ ቢሆን እንኳን ሰራዊቱ ገለልተኛና ለየትኛዉም ፓርቲ የማይወግን መሆኑን ማስረጃ አቅርበን መሞገት ነዉ የሚገባን እንጂ “መከላከያ ለምን ተነካ” ብሎ ቡራ ከረዩ ማለት አግባብ አይደለም፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ እንከን ሲገኝበት ለማረምም ሆነ አስተያየት ለመስጠት የማንንም ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡

በርግጥ የጆቤም ጽሁፍ ከችግር የጸዳ እንዳልሆነ ከይቅርታ ጋር ሳልጠቁም አላልፍም፤ ችግሩ ከሁለት ሁኔታዎች የመነጨ ይመስለኛል፡፡

አንደኛዉ፤ ጄ/ል አበበ ለመግለጽ የፈለጉትን መግለጽ በሚገባቸዉ ደረጃ ለመግለጽ ያለመቻላቸዉ ነዉ፡፡ ይህ ስህተት የተፈጠረዉ ችግሩ መኖሩን እንደተረዱ በደንብ አብላልተዉና አስበዉበት ተጠንቅቀዉ ከመጻፍ ይልቅ ለመንቀፍ በመቻኮላቸዉ የተፈጠረ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ጆቤ መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አይደለም፤ የገዢዉ ፓርቲ አገልጋይ ሆኗልየሚል አቋም ካላቸዉ ማስረጃ ጠቅሰዉ በሚገባ አብራርተዉ መግለጽ ነበረባቸዉ፡፡ አመለካከታቸዉ ምንም ይሁን ምን ሌላዉ ሰዉ እንዲጋራቸዉ ከፈለጉ ሁሉም ሰዉ ሊረዳዉ በሚችል መንገድ ግልጽ አድርገዉ ማቅረብ እንደነበረባቸዉ የዘነጉ ይመስለኛል፡፡ የሰራዊቱን ገለልተኝነት ላይ የተጠራጠሩበት ሁኔታ ካለም በግልጽ መከራከሪያ አቅርበዉ ችግሩን ማሳየት ነበረባቸዉ፡፡ እንደዚያ ግን አላደረጉም፡፡ ስለዚህ እኔም ብሆን ደጋግሜ ደጋግሜ በማንበብ ለመረደት ጥረት ማድረጌ ባይቀርም ሃሳባቸዉን በደንብ ልረዳላቸዉ አልቻልኩም፡፡ ምናልባት የእኔ የመረዳት ችግር ይሆናል በማለት ነዉ ያለፍኩት፡፡

ሁለተኛ፤ የጆቤ ችግር የግንባታ መመሪያዉን በደፈናዉ ያጣጣሉበት አግባብ ነዉ፡፡ ጆቤን ለዚህ የዳረጋቸዉ ገና ከመጀመሪያዉም “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ከሚባለዉ ጋር መጣጣም ሲላልነበራቸዉ እንደሆነ ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡ ያኔ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የ93ቱ ቀዉስ ጊዜ በመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ደረጃ በተለያዩ ሰነዶች ላይ ዉይይት በሚደረግበት ወቅት ጆቤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደማይዋጥላቸዉ በግልጽ ተናግረዉ ነዉ ስብሰባዉ ላይ መገኘት ያቆሙት፡፡ በወቅቱ ጭራሽ ለማንበብም እንዳልሞከሩ ወደፊትም የዚያ ዓይነት ጽሁፍ እንደማያነቡ በድፍረት ሲገልጹ አዳምጨአለሁ፡፡ ጆቤ “ማንም በዘፈነ ቁጥር አብሬ አልዘፍንም ማንም ባጨበጨበ ቁጥር አብሬ አላጨበጭብም“ በሚል አባባል ነበር የገለጹት፡፡

በወቅቱ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ገለጻ ሲሰጥ አንድም ቁምነገር እንዳያመልጠኝ ማስታወሻ ስወስድ ለነበርኩት ለእኔ ስለአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚያወሳዉን ሰነድ እንደዚያ ማጣጣላቸዉ ግራ ሳያጋባኝ አልቀረም፡፡ በወቅቱ በዚያ ጽሁፍ ላይ ሲያወያዩና ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩትና በዚሁ የስብሰባ ቦታ (መኮንኖች ክበብ) ከጥቂት ቀናት በኋላ በአንድ ጥጋበኛ ሻለቃ በግፍ የተገደሉት የደህንነት ኃላፊዉ አቶ ክንፈ በወቅቱ ጆቤን ለማግባባት ብዙ ጥረዉ እንደነበር እስታዉሳለሁ፡፡ እንዲያዉም አቶ ክንፌ ስለጆቤ የተናገሩትን አስካሁንም አይረሳኝም፡፡ ጆቤ ድሮም በትግሉ ጊዜ በረሃ እያልን በስብሰባ ላይ እንደዚህ ሲያስቸግረን ነበር፤ አንድ ነገር ካልጣመዉ አይቀበልም፤ የሚገርመዉ ደግሞ ሁልጊዜም በመጨረሻ ትክክል ሆኖ የሚገኘዉ የጆቤ ሃሳብ ነበርነበር ያሉት አቶ ክንፈ፡፡ ጆቤ በየጊዜዉ የሚጽፏቸዉን ባነበብኩ ቁጥር ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላም ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር እርቅ እንዳልፈጠሩ ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡

ጀቤ የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ሰነዱን በሚመለከት ዛሬ ከስንት ዓመት በኋላ እንዴት በድንገት ትዝ ብሏቸዉ ትኩረት ሰጥተዉ ተችተዉ እንደጻፉ አልገባህ ብሎኛል፡፡ ጆቤ ስለ ሰራዊቱም ሆነ ስለተጠቀሰዉ ሰነድ የተሟላ መረጃ እያላቸዉ ለምን ይሄን ያል ጊዜ ቆይተዉ አሁን ለመጻፍ እንደተነሳሱ እሳቸዉ ራሳቸዉ ሊገልጹልን ይገባ ነበር፡፡ የጊዜ አመራረጣቸዉ (timing) በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዉስጥ የተከሰተዉ የወቅቱን ቀዉስ ታሳቢ ያደረገ ይሁን አይሁን ለመረዳት አልቻልኩም፡፡

ጆቤ ሰነዱን አስመልክተዉ ጠንከር ያለ ትችት መጻፋቸዉ ሳያንስ ከዚያም በላይ ሄደዉ ነገ ዛሬ ሳይባል ሰነዱ እንዲታገድ ለክቡር ጠቅላይ አዛዡ ያመለከቱበት ሁኔታ ለዚህ ሁሉ የገፋፋቸዉ በሰነዱ ላይ “መከላከያ ሰራዊቱ የአብዮታዊ ዲሚክራሲያዊ ስርአቱ የመጨረሻ ምሽግ ይሆናል” የሚለዉን አገላለጽ በማስታወስ ተገቢነቱን ባለመቀበላቸዉ እንደሆነ ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ” ጉዳይም ሆነ “የሰራዊት ግንባታ መመሪያዉ” ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በአንድ ሰሞን በተከታታይ ለዉይይት የቀረቡ ሆነዉ እያለ ዛሬ ከስንት ዘመን በኋላ ጆቤ ምን ታይቷቸዉ አስታዉሰዉ እንደ አዲስ እንደተቃወሙ አስካሁንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ምናልባት መከላከያ ሰራዊቱ “ገለልተኛ አይደለም!“ የሚያሰኝ አንዳንድ ምልክቶችን አይተዉና ይህ ለምን ሆነ ብለዉ ራሳቸዉን ሲጠይቁና መነሻ ምክንያቶችን ሲያፈላልጉ ቆይተዉ በመጨረሻም የደረሱበት ድምዳሜ “የችግሩ ምንጭ የግንባታ መመሪያዉ ነዉ” ብለዉ ከሆነ ይህን ግልጽ ማድረግ ይጠበቅባቸዉ ነበር፡፡

ጆቤ ግልጽ አድርገዉ ባይገልጹትም እሳቸዉ ለመግለጽ በሞከሩት ደረጃ ያቅሜን ያህል ለመረዳት የቻልኩት ዋናዉ የሃሳባቸዉ ጭብጥ “መከላከያ ሰራዊቱ የፓርቲ አገልጋይ መሆን የለበትም፡፡ በህገ- መንግስቱ መሰረት ለየትኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን በገለልተኝነት ስራዉን መስራት አለበት፡፡ የግንባታ ሰነዱ የሰራዊቱን ገለልተኝነት ለመሽርሸር በር ስለሚከፍት እንደገና ተከለሶና ተስተካክሎ አስከሚቀርብ ይታገድ!” የሚል መሰለኝ፡፡ የጆቤ ሃሳብ በትክክል ገብቶኝ ከሆነ መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ ካልሆነ ሊከተል የሚችለዉ አደጋ ስጋት ስለገባቸዉና የግንባታ ሰነዱንም ለዚያ ተጠያቂ በማድረግ እንዳለ የነቀፉት ይመስለኛል፡፡ ጆቤ የግንባታ ሰነዱ ላይ ትኩረት ከሚያደርጉ በቅድሚያ “መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አይደለም!” የሚሉበትን መከራከሪያ በማስቀመጥ ማሳመኑ ላይ ነበር ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባ የነበረዉ፡፡ እሳቸዉ ግን መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አለመሆኑን ሳያስረዱንና እንደተቀበልናቸዉም እርግጠኛ ሳይሆኑ “የችግሩ ምንጭ ነዉ“ ያሉት ሰነድ ላይ ለመፍረድ ተቻኮሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መሰለኝ ሃሳባቸዉን ለመቀበል የከበደኝ፡፡ አሁንም ቢሆን የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የአንድ ፓርቲ አገልጋይ ነዉ የሚል ጥርጣሬ ካላቸዉ በተጠናከረ ሁኔታ ሃሳባቸዉን በድጋሚ ቢገልጹ ጠቀሜታዉ ለሁላችንም ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ጆቤ የሃገሪቱን ህገመንግስት፡ የሰራዊቱን ሁኔታ፤አለም አቀፍ ተመክሮዎችን ሁሉ ከግምት በማስገባት ሚዛናዊ አስተያየት ለመስጠት ከሁላችንም የተሻለ እድል እንዳላቸዉ ስለማምን በጉዳዩ ላይ ጥናት ቢጤ አድርገዉ በተጠናከረ ሃሳብ ዳግመኛ ቢመጡ ፈቃዴ ነዉ፡፡

የተጠቀሰዉን የግንባታ ሰነዱ ላይ በወቅቱ እኔም ወግ ደርሶኝ የመወያየት እድል አግኝቼ ስለነበር የጦር ኃይሉ ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት (ነፍሳቸዉና ይማርና) ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሲሰጡ ከተወያዮቹ ከቀረቡላቸዉና የሳቸዉን ማብራሪያ ከሚፈልጉ በርካታ ጥያቄዎች መካከል በጥያቄ መልክም ሆነ በመሳሳቢያ መልክ የግንባታ ሰነዱ የሰራዊቱን ገለልተኝነት ይሸረሽራል የሚል ነገር በጭራሽ እንዳልተነሳ በሚገባ አስታዉሳለሁ፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ አይደለም የሚል አስተያየት የሰጠ ሰዉም አልነበረም፡፡ በርግጥ አሳቸዉ (አቶ መለስ) በበላይነት በሚመሩት ጦር ኃይል ላይ የገለልተኝነት ችግር አለ ቢሎ በድፍረት መናገር ቢከብድም ቢያንስ በጥያቄ መልክ እንኳን አልተነሳም፡፡ ጥያቄም ሆነ የተለየ አስተያየት በወቅቱ ሊቀርብ አይገባዉም ነበር በሚል ሳይሆን ሁሉም ተሰብሳቢ ተገቢ ነዉ ብሎ አምኖ ስለነበር ነዉ፡፡

በወቅቱ ለእኔና ሌሎች ጥቂት ከቀድሞ ሰራዊት ለመጣነዉ ከሀገሪቱ መሪ ጋር በነጻነት መወያየት ቀርቶ ከቅርብ አለቃ ጋር የተለየ ሃሳብ መስጠት በማይፈቀድበት በዚያ ሰራዊት ዉስጥ አገልግለን ለነበርነዉ ፈራ ተባ ማለታችን ባይቀርም ለነባሮቹ የቀድሞ ታጋዮች ከመለስ ጋር ቁጭ ብሎ መወያትና ሲያስፈልግም መከራከር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ እሳቸዉ ለእንዳንዱ ተናጋሪና ለእያንዳንዱ ጥያቄና አስተያየት ያለ ልዩነት እኩል ክብደት ሰጥተዉ ማብራሪያ ሲሰጡ ሳይ እኔም በሁኔታቸዉ ተበረታትቼ አንድ ሁለት ጥያቄዎች መጠየቄ አልቀረም፡፡ በርግጥ የማይካድ ነገር ወቅቱ በድርጅቱ ዉስጥ ተፈጥሮ በነበረዉ መሰነጣጠቅ አደጋ ምክንያት ዉጥረት የሰፈነበት ስለነበረ ‹‹ሰራዊቱ ለህዝቡ ታማኝ ነዉ/አይደለም፤ ገለልተኛ ነዉ/አይደለም›› የሚል የሰራዊቱን ተአማንነትን በጥያቄ የሚያነሳ ሃሳብ ማቅረብም ወቅታዊም አልነበረም፡፡ በተጨማሪ ዶክመነቱ ላይ የተነሳዉ ሃሳብ ለእኛ አገር አዲስና ዉስብስብነት የነበረዉ በመሆኑ ፈጥኖ ለመረዳትም ሳይቸግረን አልቀረም፡፡ እኔም ብሆን ሀሳቡ ይበልጥ ግልጽ እየሆነልኝ የመጣዉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የኢንግሊዝ ሮያል ሚሊታሪ ኮሌጅና ግራንስፍልድ ዩነቨርስቲ በጋራ ባዘጋጁትና ለሳምንታት በዘለቀዉ በሱኩሪቲ ሴክተርና ዲፌንስ ትራንስፎርሜሽን ኮርስ ከተታተልኩ በኋላ ነው፡፡

ወደ ሰራዊት ግንባታ መመሪያ ሰነዱ ልመለስና በወቅቱ አቶ መለስን ሰፊ ማብራሪያ የጠየቁና ክርክር ከተነሳባቸዉ ጉዳዮች ዉስጥ ስለ ሰራዊቱ ገለልተኝት እንደ ችግር ያልቀረበ ሲሆን በወቅቱ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በደንብ የማስታዉሳቸዉ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡

1ኛ/ ከከፍተኛ መኮንኖች ይልቅ ለስርአቱ ይበልጥ ታማኝ የሚሆኑትታችኞቹሰረታዊ አባላትና ዝቅተኛ ባለማእረግተኞች ናቸዉ የሚለዉ አንዱ ነዉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ሰዉ እንዴት ካንድ ጀነራል ይልቅ አንድ ተራ ወታደር ወይም ጁኒየር ኦፍሰር ለስርአቱ የበለጠ ታማኝ ሊሆን ይችላል? እያለ ከሰብሰባዉ በኋላም ሲነጋገሩበትና እርስበርስ ሲከራከሩ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡

2/ መኮንን መሆን ያለበት በቀጥታ ከትምህርት ቤት የሚመጣ ተማሪ ሳይሆንሰራዊቱ ተመልምሎ መሆን አለበት የሚለዉ ነዉ፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ የሀረር አካዳሚም ከሆለታም ምሩቃን የነበሩ የድሮ መኮንኖች ስለነበሩ ሲቀርብ በነበረዉ መከራከሪያ ላይ ያነሷቸዉን መከራከሪያ ሰዉዬዉ አቶ መለስ ባይሆኑ ኖሮ በቀላሉ ማሳመን ማስቸገሩ አይቀርም ነበር፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የተንሸራሸረ ሃሳብ ቢኖር አየር ኃይልን የሚመለከት ሆኖ የአየር ኃይል አዉሮፕላን አብራሪ (ፓይለት) ለመሆን ሰልጣኙ ከሰራዊቱ የተመለመለ መሆን አለበት እንጂ በቀጥታ ከሲቪል (/ቤት)የመጣ መሆን የለበትም የሚል ነዉ፡፡ መመዘኛዉን ሊያሟላ የሚችል ከሰራዊቱ ማግኘት ይከብዳል፤ እድሉን ጠባብ ያደርጋል በሚል ከአየር ኃይሉ አባላት አካባቢ ሰፊ ክርክር መደረጉን አስታዉሳለሁ፡፡

3/ ሰራዊቱን የሰዉ ኃይል ማሟያ ከዬት መሆን አለበት? በሚል በተነሳዉ ጉዳይ ላይም በደርግ ዘመን የነበረዉ ዓይነት ብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎት ለአሁኑ የሀገራችን ሁኔታ እንደማይበጃት በጠንካራና ደካማ ጎኑ ላይ ጥልቅ የሆነ ትንታኔ የተሰጠበት ቢሆንም ብዙዎቻችን ከቀደሞዉ ሰራዊት የመጣንና ስለብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎት ቀድሞዉኑ ግንዛቤዉ የነበረን የተሰጠዉን ማብራሪያ ለመቀበል ቸግሮን እንደነበረ አስታዉሳለሁ፡፡

4/ ከብሄራዊ ተዋጽኦ አተገባበር ጋር ተያይዞ በጥያቄ መልክ የቀረበም ነበር፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ ከጓዳዊነት ይልቅ በአካባቢ ልጅነትና በብሄር የመሳሳብና የመጠቃቀም ነገር ይታያል፡፡ ከችሎታ ይልቅ ብሄራዊ ማንነትን እንደመስፈረት እየተወሰደ ለሹመት፤ ለትምህርትና ለምደባ ወዘተ በኮታ የማድረጉ አሰራር ወታደራዊ ብቃትን እየጎዳ ነዉ በሚል በእኔ በራሴ ለሳቸዉ የቀረበ ጥያቄ ላይ በወቅቱ ሰፊ ማብራሪያና መመሪያ መስጠታቸዉን አስታዉሳለሁ፡፡ በትክክል የማስታዉሳቸዉ ዋና ዋና ጉዳዮች እነዚህ ይመስሉኛል፡፡ ከዚያ ዉጭ ስለመከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኝነት ላይ ሆነ የግንባታ መመሪዉ ላይ ቅሬታ ወይም ትችት ሲቀርብ አልሰማሁም፡፡

5/ መከላከያ ሰራዊቱ በህብረተሰቡ ዉስጥ ገዢ የሆነን አመለካከት መቀበል አለበት ማለት የገዢዉን ፓርቲ አመላከከት ሁሉ መቀበል አለበት ማለት አይደለም፡፡

ለዚህች ነጥብ መነሻ የሆነኝ አቶ መሃሪ ሁኔታዉን በቅጡ ሳያጤን “መከላከያ ሰራዊቱ የገዥዉ ፓርቲ ርዕየተ ዓለም ተከታይ መሆን አለበት” የሚል ሃሳብ መግለጹ ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ለህገመንግስቱ ታማኝ መሆን አለበት ቢባል ችግር ባልኖረዉ፡፡ ሰራዊቱ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ ታማኝ መሆን አለበት ከተባለም ተገቢ ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ የመንግስት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ አንድ አማራጭ ስለሆነ የመንግስትን መመሪያዎችና ፖሊሲዎች በእምነት የመቀበል ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አለበት የሚል አመለካከትም በጣም ትክክል ነዉ፡፡ ነገር ግን ስርአቱን መቀበልና የመጠበቅ ጉዳይን በቀጥታ የፓርቲን ርዕየተ ዓለም እንደመቀበል አድርጎ መረዳት ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡

ስርአቱን ያመጣዉ ኢህአዴግ ስለሆነና መንግስትን እየመራ ያለዉም ኢህአዴግ ስለሆነ መከላከያም ለመንግስት የመታዘዝ ግዴታ አለበት የሚለዉን ጉዳይ በመዉሰድ “ለመንግስት መታዘዝ ማለት ለገዥ ፓርቲ እንደመታዘዝ” ማለት ነዉ የሚል አመለካከት እጅግ አደገኛ አመለካከት ነዉ፡፡ አቶ መሃሪ መዘንጋት ያልነበረበት መከላከያ ሰራዊቱ የመላዉ ህዝቦች ማለትም የኦሮሞዉም፤ የትግራዩም፤ የአማራዉም፤የአፋሩም፤ የደራሼዉና የኮንሶዉም ጭምር እንጂ የሆነ ፕሮግራም ለማስፈጸም ቃል ገብቶ ለጊዜዉ ተመርጦ ስልጣን ለያዘ ፓርቲ አለመሆኑን ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ የክቡር አቶ አባዱላ፤ የአቶ ግርማ ሰይፉ፤ የአቶ ዳንኤል ብርሃኔም የሁላችንም ነዉ መሆን የሚገባዉ፡፡

የትኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ ስልጣን ላይ ያለም ሆነ ስልጣን ለመያዝ የሚታገል ፓርቲ መከላከያ ሰራዊቱን እንዲነጥቀንና የብቻዉ እንዲያደርግ መፍቀድ የለብንም፡፡ በዚህ ከተስማማን መከላከያ ሰራዊቱ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም አስፈጻሚና የአንድ ፓርቲ አይዲኦሎጂ አስረኛ የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በሀገሪቱ ዉስጥ ገኖ የወጣ አመለካከት ወይም አይዲኦሎጂ ሊኖር ይችላል፡፡ ያን አመለካከትና ርዕየተ-ዓለም ሰራዊቱ መጋራቱ የማይቀር ነዉ፡፡ ስህተት የሚሆነዉ አመለካከቱን መጋራት አለበት ማለትና አመለካከቱን ያመጣዉ ገዢዉ ፓርቲ ስለሆነ የገዢዉን ፓርቲ አመለካከቶች ሁሉ መቀበል አለበት መባሉ ነዉ፡፡ ይህ በጣም ስህተት ነዉ፡፡ ከፓርቲ ጋር በተቆራኘ መንገድ የሚገለጽ ነገር ላይ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ለነገሩ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እንደ አንድ ርዕዮተ-ዓለም በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ ርዕየተ ዓለም የሁላችንም ወይም የስርአቱ መሆን አለበት እንጂ የገዥዉ ፓርቲ የግል ንብረት ተደርጎ የሚቆጠርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በአሜሪካ የሊበራል ስርአት አይዲኦሎጂ ባለቤቱ የአሜሪካ ህዝብ እንጂ ሪፖብሊካን ወይም ዲሞክራትክ ፓርቲ አይደለም፡፡ የአሜሪካ ሰራዊት የስርአቱን ገዢ አመለካከት የተቀበለዉ የዲሞክራቲክ ወይም የሪፐብሊካን ስለሆነ ሳይሆን የአሜሪካ ህዝቦች የጋራ እምነት በመሆኑ ነው፡፡

ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ሲላስተዋወቀ የኢህአዴግ የግል ንብረት መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡ የአብየታዊ ዲሞክራሲን ህልዉና ከገዥዉ ፓርቲ ጋር እንዲቆራኝ የመፈለግ አዝማሚያ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ከሌለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊቀለበስ ስለሚችል ኢህአዴግ የግድ ስልጣን ላይ መቆየት አለበት የሚል መልእክት ለማስተላለፍ የተፈለገ ነዉ የሚያመስለዉ፡፡ ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ባሰተዋወቀበት ጽሁፍ ላይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ልዕልና እንዲፈጠር መስራት ማለት ኢህአዴግን አስከ ዘለአለሙ ስልጣን ላይ እንዲቆይ ማድረግ ማለት አለመሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ልዕልናም መፈጠር የሚችለዉ ሌሎች ተወዳዳሪ አስተሳሰቦች እንዳይኖሩ በማፈን ሳይሆን ከሌሎች አስተሳሰቦች ጋር በነጻ ተወዳድሮ በህብረተሰቡ በፈቃደኝነት ተቀባይነት ሲያገኝና ህብረተሰቡ የግሉ ሲያደርገዉ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በሀገራችን በአሁኑ ወቅት አብዮታዊ ዲሞክራሲ አሰተሳሰብን ለማስረጽና የህብረተሰቡ ገዢ አሰተሳሰብ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ጥረቶች መደረጋቸዉ ባይካድም ነገር ግን 80% አርሶአደር በሆነበትና ዲሞክራሲያዊ ባህሉ ደካማ በሆነበት አገር ዉስጥ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንደ ንድፈሃሳብና እንደተግባር መመሪያ አዋጭነቱና ተገቢነቱ ላይ በእምነት ተይዟል የሚባልበት ደረጃ ላይ ገና የደረስን አይመስለኝም፡፡

አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዉስጥ የገነነና ልዕልና ያገኘ አስተሳሰብ ከሆነ መከላከያ ሰራዊታችንም የዚያ አስተሳሰብ ተጋሪ መሆኑ የግድ ነዉ፡፡ ችግሩ ግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ላይ አስካሁንም ብዙ ጥያቄ በሚነሳበትና ብዥታዎች ባሉበት ሁኔታ ሰራዊቱን በአንድ ፓርቲ አይዲኦሎጂ ከመተብትብ ህገመንግስቱን መነሻ ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትና የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲሰርጽበትና ሙያዊ ነጻነት ያለዉና (professional autonomy) ጠንካራ ሙያዊ ስነምግባር የተላበሰ (professional integrity) ወገንተኝነቱን ከገዥ ፓርቲ ይልቅ ለህዝብ ያደረገና (loyalty to people) ከፓርቲ ፖለቲካ ገለልተኝነት (neutrality & impartiality) ነጻ የሆነ ተቋም እንዲሆን ማድረጉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ወታደር በባህሪይዉ ፖለቲካዊ ይዘት ካለቸዉ ቅስቀሳዎች ይልቅ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከሁሉም የበለጠ ቀስቃሽና በአንድነት ለማሰለፍ የሚችል አቅም ሲላለዉ ለጊዜዉም ቢሆን በዚያ ላይ ትኩረት ማድረጉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

6/ መከላከያ ሰራዊቱ አመራር የሚያገኘዉ ከመንግስት እንጂ ከገዢዉ ፓርቲ አይደለም፡፡

አቶ መሃሪ በጽሁፉ መከላከያ ሰራዊቱ አመራር የሚያገኘዉ ከገዢዉ ፓርቲ እንደሆነ አድርጎ በተዘዋዋሪ መንገድ ገልጾአል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ከገዥዉ ፓርቲ ጋር አንዳችም የሚያገናኘዉ ነገር በሌለበት ሁኔታ ከገዥዉ ፓርቲ በቀጥታ አመራር እንዲቀበል መፈለጉ አስገርሞኛል፡፡ ሰራዊቱን በበላይነት የሚያዙ ሲቪል ባለስልጣናት ለምሳሌ ሲቪል መከላከያ ሚኒስትሩም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰራዊቱን በበላይነት የሚያዙት በፓርቲዉ ስም ሳይሆን በአስፈጻሚ አካል ዉስጥ ባላቸዉ ሃላፊነት ነዉ፡፡ ስለዚህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ክቡር ጄ/ል ሳሞራ የኑስን የሚያዙት በጠቅላይ አዛዥነታቸዉ እንጂ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ስለሆኑ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ጋር ስለ ፓርቲያቸዉ ቁጭ ብለዉ ሊወያዩና ፓርቲዉን የሚመለከት መመሪያ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም አቶ ሲራጅም የኢህዴግ ፓርቲ አባል ስለሆኑና ሲቪል በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ እንዲያዉም ቢቻል የህግ አዉጭዉ አባልም መሆንም ይገባቸዋል ብዬም ስለማስብ ነዉ፡፡ መከላከያ ሚኒስትሩ ራሳቸዉ ከጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጋር ሲወያዩ የመንግስትን ፖሊሲን በሚመለከት እንጂ የኢህአዴግን የፓርቲ መመሪያ በሚመለከት አይደለም፡፡ ክቡር ጄነራል ሳሞራም እንደ ማንኛዉም ዜጋና እንደማንኛዉም የመከላከያ ሰራዊት አባል በግላቸዉ ለገዢዉ ፓርቲ ዝንባሌ ቢኖራቸዉ የሚያስወቅሳቸዉ አይሆንም፤ መብታቸዉ ስለሆነ፡፡

ከዚያ ዉጭ ግን ኢህአዴግን ተዋግቼ ለዚህ ስልጣን ያበቃሁት እኔ ስለሆንኩ የፓርቲዬ ጉዳይ ይመለከተኛል ብለዉ በአደባባይ ስለ ኢህአዴግ መልካምነትና ስለትግራይ አረና ፓርቲና ስለ ኢዴፓ ሃጥያት መናገር ከጀመሩ በቃ ነገር ተበላሸ ማለት ነዉ፡፡ ደግነቱ እንኳን እሳቸዉ ይቅርና ሌላዉ የሰራዊቱ አባልም ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ስህተት ይሰራል ብዬ አላስብም፡፡

በአቶ መሓሪ ጽሁፍ ዉስጥ የሰራዊቱን የግንባታ ሰነድ ጠቅሰዉ የጻፉት የስልጣን ክፍፍልን ፋይዳ በተዛባ ሁኔታ የተረዱበት ሁኔታ ላይ ትንሽ ማስተካከያ ማድረግ አንዳለብኝ ተሰምቶኛል፡፡ በተጠቀሰዉ የሰራዊቱ የግንባታ መመሪያ ዉስጥ “በስልጣን ላይ ያለዉ አካል ከሌላ ወገን ጋር በጭራሽ ስልጣን የማይጋራበት ሁኔታ ቢኖር መከላከያ ሰራዊቱን በሚመለከት ነዉ“ የሚለዉ ነዉ፡፡

እኔ እንደሚገባኝ በየትኛዉም ዲሞክራሲያዊ ሰርአት ዉስጥ የስልጣን ክፍፍል ማድረግ የግድ ከሚያደርጉ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚገባዉ የሃሪቱን መከላከያ ሰራዊት በሚመለከት ነዉ፡፡ በፕሬዝዳንታዊዉ ሆነ በፓርላሜንታዊ (ፓርላማዊ) ስርአት በህግ አዉጭዉና በህግ አስፈጻሚዉ መካከል ግልጽ የሆነ የስልጣን ክፍፍል አለ፡፡ አስፈጻሚዉ የመንግስት ቢሮክራሲን፤ ፖሊስና መከላከያ ኃይልንም ጨምሮ የሚቆጣጠርና፤ ገንዘብ የሚሰበስብ፤ ግብር የሚያስከፍል የመንግስት ባጀትን የሚያስተዳደር ፤መከላከያንና የጸጥታ ሃይሎችን በተግባር አሰማርቶ የሚጠቀመዉ አስፈጻሚዉ አካል በመሆኑ ከፍተኛ ስልጣንና ኃይል በእጁ እንዳለ ግልጽ ነዉ፡፡ ስለዚህ ስርአቱ ከፍተኛ ስልጣን በአንድ አካል (በአስፈጻሚዉ)ያለአግባብ ተከማችቶ ስልጣኑን ያለአግባብ በመጠቀም በዜጎች መብት ላይ ጥሰት እንዳያደርስ የስልጣን ክፍፍል ማድረግ የግድ ነዉ፡፡ ህግ አዉጭዉ አስፈጻሚዉ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከሚያደርግባቸዉ አብይ ጉዳዮች አንዱ መከላከያን በሚመለከት ነዉ፡፡ የመከላከያን መጠን (ግዝፈት) ባጄት መፍቀድና አጠቃቀሙን መከታተል፤ ወደጦርነት ለመግባት መፍቀድ፤ የመከላከያና የደህንነት አፈጻጸም፣ ወዘተ ሁሉ አስፈጻሚዉ ከሀገሪቱ ፓርላማ እዉቅና ዉጭ መስራት አይችልም፡፡

የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ የሻእቢያን ወረራ ለመቀልበስ ጦርነት ለማወጅ ፓርላማዉን አስፈቅደዉ ነዉ፡፡ ሰራዊት ወደ ሞቃዲሾ ለመላክም በቅድሚያ ለፓርላማ አቅርበዉ ሰፊ ክርክር ከተደረገ በኋላ ነዉ በመጨረሻ በማሳመን ያስፈጸሙት፡፡ የስልጣን ክፍፍል ማለትም ይሄ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አመራሩ ከማንም ጋር የማይጋራዉ የተባሉ የት ላይ እንደሆነ ግልጽ ቢደረግ ጥሩ ነዉ፡፡ ያለበለዚያ ኢህአዴግ እንዳሻዉ ያለማንም ከልካይ መከላከያ ሰራዊቱን እንደፈለገ የሚጫወት አድርጎ ማስቀመጥ ትክክል አይመስለኝም፡፡

ማንኛዉም የሀገሪቱ ፖሊሲዎች ከገዢዉ ፓርቲ የሚመነጩ በመሆናቸዉ ከዚህ እምነት በመነሳትም የሰራዊቱ የግንባታ መመሪያም ከገዥዉ ፓርቲ የሚመነጭ ከመሆን አያልፍም የሚል ድምዳሜ ካለ እኔም በዚህ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ ከዚህ ዉጭ የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ መከላከያን በቀጥታ ማዘዝ አለበት እየተባለ ከሆነና በተጨማሪ የገዢዉ ፓርቲ ለዚህ ስርአት መምጣትና ባለፉት ሃያአምስት አመታት ላስመዘገበዉ ዉጤት ለዉለታዉ ሲባል መከላከያ ሰራዊቱ ለገዢዉ ፓርቲ የተለየ ታማኝነት ማሳየት አለበት እየተባለ ከሆነ ቀድሞዉኑ የመከላከያ ሰራዊታችንን ገለልተኝት ሲጠራጠሩ ለነበሩ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለትችት አመቻችቶ እንደመስጠትና ዱላ እንደማቀበል ነዉ የሚቆጠረዉ፡፡

7/ የአዉራ ፓርቲ ስርአት መመስረት አለበት ቢሎ ህዝቡ ጥያቄ አቅርቦ አያዉቅም፡

አቶ መሃሪ አስቀድሜ በገለጽኩት ጆቤን ለመተቸት ቢሎ በጻፈዉ ትችት ላይ ካቀረበዉ ነገር እጅግ አድርጎ ያስገረመኝ ነገር ቢኖር ስለ አዉራፓርቲ በሰጠዉ ትንታኔ ላይ አዉራ ፓርቲን እንድንቀበል ያደረገዉ ቅስቄሳ ነዉ፡፡ ጸሃፊዉ አቶ መሃሪ ስለ አዉራ ፓርቲ ጠቃሚነት በሰጠዉ ማብራሪያ ላይ ህዝቡ አዉራ ፓርቲን ፈቅዶ መምረጡን የገለጸበት መንገድ አስገራሚ ነዉ፡፡ የሱኑ አባባል ቃል በቃል እንዳለ ላስቀምጠዉ፡፡ ባለፉት 25 ኣመታት በተከናወኑት አምስት ሃገራዊ ምርጫዎች መራጩ ህዝብ እዚህ አገር ዉስጥ የአዉራ ፓርቲ ስርአት (Dominant Party System) እዉን እንዲሆን ይሁንታዉን ሰጥቷልነበር ያለዉ፡፡

ህዝቡ አዉራ ፓርቲ ስርአት ለመመስረት ይፈልግ እንደሆን መቼ ተጠይቆ በየትኛዉ ህዝቤ ዉሳኔ ፍላጎቱን ገልጾ ወይም መቼና በማን በተደረገ የህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ (poll) ለማወቅ እንደተቻለ ላስታዉስ አልቻልኩም፡፡ ምናልባት በሃገራዊ ምርጫ ወቅት ህዝቡ ከምርጫዉ ጎን ለጎን ፍላጎቱን እንዲገልጽ የተጠየቀበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብዬ እንዳልል እኔ ራሴ ጡሬታ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱት ሁለት ሀገራዊና አንድ የአካባቢ ምርጫ ላይ የህዝብ ታዛቢ ሆኜ ሰርቼ ስለነበር እንደዚህ ዓይነት መጠይቅ ለህዝቡ ስለመቅረቡ አላስታዉስም፡፡ ስለዚህ ወንድሜ አቶ መሃሪ “ህዝቡ ፈቅዶ ይሁንታዉን ሰጥቶ” ያላት ነገር የተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሰጣት አስተያየት መሆን አለባት፡፡ ምናልባትም የወደፊት ምኞቱንና ፍላጎቱን የገለጸበት ሊሆን ይችላል፡፡

ኢህአዴግ 90% እና 100 % ድምጽ እያገኘ ማሸነፍ ይገባዋል በሚለዉ ላይ ባልስማማም ፍትሃዊ በሆነ ምርጫ በአብላጫ ድምጽ ቢያሸንፍ እኔም ብሆን አልጠላም፡፡ እንዲያዉም አስካሁን በተደረጉ ምርጫዎች ኢህአዴግ በአብላጫ ድምጽ እንዳሸነፈም አልክድም፡፡ ነገር ግን በሁለት ነገሮች ከአቶ መሃሪ ጋር አልስማማም፡፡

አንደኛ፤ እሱ እጅግ በኩራት እየገለጸ ያለዉን መቶ ከመቶ(100%) ድምጽ የሚገኝበት ምርጫ እንኳን እንደእኔ ዓይነቱ መራጭ ቀርቶ ኢህአዴግ ራሱ እንደዚያ እንዲሆን የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ይሄ ዉጤት (100%) ለኢህአዴግም ቢሆን ምቾት የሰጠ እንዳልነበረ እገምታለሁ፡፡ እንዲያዉም ኢህአዴግ አክራሪ የሆኑ የራሱን ሰዎች ትችትና ነቀፈታ ፈርቶ ነዉ እንጂ እንደ አንዳንዶቹ የአመራሩ አባላት ፍላጎት ቢሆን ኖሮማ “ምርጫዉ ተጭበርብሮአል፤ 100% አሸንፈሃል የተባልኩት ትክክል አይደለም” ብሎ ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ወይም ድጋሚ ቆጠራ እንዲደረግ የምርጫ ቦርድን ከመጠየቅ አይመለስም ነበር፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ “100% አሸንፈሃል” በመባሉ ብዙ ነገር ከሰረ እንጂ አትርፎአል ለማለት ስለማልችል ነዉ፡፡

ሁለተኛ፤ ኢህአዴግ በተከታታይ ሁሉንም ምርጫዎችን ማሸነፉ እዉነት ሆኖ እያለ ነገር ግን ህዝቡ አዉራ ፓርቲ እንዲሆን ስለፈቀደ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ በምርጫ በማሸነፍ መንግስት ለመመስረት የበቃዉ አብላጫ ድምጽ በማግኘቱ እንጂ አዉራ ፓርቲ እንዲሆን ህዝብ ስለፈረደለት አይደለም፡፡ እዉነቱን እንነጋገር ከተባለ በቁጥር ሰማኒያ ከመቶ በላይ የሚሆነዉ የአገራችን ህዝብ አርሶ አደር በሆነበት አገር ህዝቡ ኢህአዴግን የመረጠዉ ስለ አዉራ ፓርቲ ምንነት ገብቶትና ኢህአዴግን እንደ ጃፓን ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ( LDP) ወይም እንደ ደቡብ አፍሪካዉ ኤ.ኤን.ሲ (ANC) አዉራ ፓርቲ ማድረግ አለብኝ በሚል አስቦ ያደረገዉ ነዉ ተብሎ እንዴት ይታሰባል ?ሌላዉ ቀርቶ እዚሁ መሃል ከተማ ዉስጥ ያሉ መራጮች በምርጫ ወቅት የት ላይ ምልክት እንደሚደረግ ጠንቅቀዉ የማያዉቁ በቁጥር ብዙ በሆኑበት እንደ እኛ ባለ አገር በጃፓንና በደቡብ አፍሪካ ያለዉን የአዉራ ፓርቲ ስርአት ጠቀሜታዉን ተረድተዉ እንደዚያ እንዲሆን ፈልገዉ ያደረጉት ነዉ ተብሎ መነገሩ የገዛ ህዝብን ለማታለል እንደመሞከር ነዉ የምቆጥረዉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈቅዶ ኢህአዴግን አዉራ ፓርቲ እንዲሆን ስለአደረገ ሌሎች ፓርቲዎች ከእንግዲህ አርፋችሁ ቁጭ በሉ እንደማለት ነዉ የሚመስለኝ፡፡

ለነገሩ የአዉራ ፓርቲ ስርአት ድምጽ ተሰጥቶበት በአዋጅ ወይም በሪፌሬንዴም የሚሆን ነገርስ ነዉ እንዴ? እኔ እንደሚመስለኝ አዉራ ፓርቲነት ሆን ተብሎ ተፈልጎ የሚደረግ ሳይሆን ከማንም ተጽእኖ ዉጭ በራሱ ጊዜ ቀስ በቀስ እዉን የሚሆን ክስተት ነዉ፡፡ የተሻለ ነጻ፤ ሃቀኛና ግልጽነት ባለዉና ገለልተኛ ታዛቢዎች በተገኙበት በሚከናወን ምርጫ በተደጋጋሚ በህዝቡ የመመረጥ ዕድል ያገኘ ወይንም በተነጻጻሪ ዘለግ ላለ ጊዜ በህዝብ ሙሉ ፈቃድ በስልጣን ላይ ለመቆየት የቻለ ፓርቲ አዉራ ፓርቲ ቢሰኝ ችግር አይኖረዉም፡፡ በጃፓንና በሌሎች አዉራ ፓርቲ ስርአት በታየባቸዉ ዲሞክራሲያዊ አገሮች አዉራ ፓርቲ ለመሆን የበቃዉ ገዢ ፓርቲ በህግ አዉጭዉ ዉስጥ በተነጻጻሪ አብላጫ ድምጽ ስለኖረዉ እንጂ በስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት ሁሉንም ወንበር ጠቅልሎ ለብቻዉ በሚይዝበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ፓርላሜንታዊ ስርአት በሚከተሉ ዲሞክራሲያዊ አገሮች በህግ አዉጭዉ ዉስጥ ከገዢዉ ፓርቲ ሌላ በርካታ መቀመጫ ያላቸዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለሚኖሩ ወቅቱን የጠበቁ ምርጫዎች በዲሞክራሲያዉ አግባብ ያለተጽኢኖ እስከተከናወኑ ድረስ በተደጋጋሚ የተመረጠ ፓርቲ አዉራ ፓርቲ ቢሰኝ የሚያስከትለዉ ችግር አይኖርም፡፡ ነገር ግን አንድ ፓርቲ በህግ አዉጭዉ ዉስጥ ሌላ ተቀናቃኝ ሳይኖረዉ ለዘለዓለም ስልጣኑን ለብቻዉ ተቆጣጥሮ መቆየት ከቻለና በምርጫ መቀየርም የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ከሄደ በሀገሪቱ ዉስጥ ትልቅ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡

አንድ ፓርቲ ጥሩ ከሰራና ህዝብ ከፈቀደለት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሁለት ጊዜም ሶስቴም ፤ለአራተኛ ጊዜም ቢመረጥ የሚያስከፋ ነገር አይሆንም፡፡ ነገር ግን ሌላ ተወዳዳሪ ፓርቲ በሃገሪቱ የለለ ይመስል ለአርባና አምሳ ዓመት ስልጣን ላይ ለብቻዉ መቆየት አለበት የሚባል ህግ የለም፡፡ በህግ አዉጭዉ (ፓርላማ) ዉስጥ አንድም ተቃዋሚ በለለበት ሁኔታና በህዝብ ገንዘብ በሚተዳደሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከገዥዉ ፓርቲ አባላት ዉጭ አንድም ዜጋ በሃላፊነት መቀመጥ በማይችልበት አገር ዉስጥ አንድ ፓርቲ በብቸኝነት ስልጣንን በርስትነት እንዲይዝ ህዝብ የሚፈቅደዉ አይደለም፡፡ አቶ መሃሪ ለአዉራ ፓርቲ ስርአት ያን ያህል ጉጉት ያደረበት አንድም ተቃዋሚ በፓርላማ ዉስጥ በለለበት ሁኔታ አንድን ፓርቲ ያለተቀናቃኝ ስልጣን ይዞ እንዲቆይ ህጋዊ እዉቅና የሚሰጥ አድርጎ በመቁጠሩ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡ መቼም ይሄ ህዝብ ምንም ቢሉት አይቃወምም የሚል የተዛባ እምነት ይዘን መሆን አለበት እንጂ ህዝቡ የዚህ አይነት ሁኔታ ጨርሶ እንደማይቀበል መታወቅ አለበት፡፡ የህዝብ ትክክለኛ ስሜትና ፍላጎት ሳያጤኑ እንዲሁ በዘፈቀደ የምንሰራዉ ስራ ነገ በሀላፊነት ያስጠይቀናል፡፡ ህዝቡ ከኛ የበለጠ ስለዲሞክራሲ በተግባር እንደሚያዉቅ የኦሮሞን የገዳ ሰርአትና የኮንሶን ባህላዊ ስርአት በማዬት በቀላሉ መረዳት በተቻለ ነበር፡፡ አንድን ኦሮሞ ባህላዊ መሪ ለአርባና ሃምሳ አመት ስልጣን ላይ እንድትቆይ ተፈቅዶልሃል ብንለዉ እንደቀለድንበት በመቁጠር ይስቅብናል፡፡ የኦሮሞ አባቶችን ያህል እንኳን ለዲሞክራሲ ታማኝ መሆን አለመቻላችን አሳዛኝ ነዉ፡፡

ስለ “የአዉራ ፓርቲ ስርአት” እንደጥሩ ነገር የሚሰብኩን ወገኖች ሆን ብለዉ ህዝቡን አማራጭ ለማሳጣትና የበለጠ ተስፋ ለማስቆረጥ አስበዉ ካልሆነ በስተቀር ለህዝብ ይበጃል ብለዉ ጠጨንቀዉ እንዳልሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ ይህችኑ ጭል ጭል የምትል ዲሞክራሲ መሳይ ነገር እሷም በዛች ተብሎ ከነጭራሹ ለማጨለም ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣዉ መልካም ነገር አይኖርም፡፡ የአዉራ ፓርቲ ስርአትን እንደ ስርአት እንመስርት ተብሎ የሚሰራ ስራ ከገዢዉ ፓርቲ ዉጭ ሌላ ተቀናቃኝ ፓርቲ እንዳይኖር እናድርግ እንደማለት ይቆጠራል፡፡ እንደዚያ መሆን አለበት ከተባለ ሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጊዜያቸዉንና ጉልበታቸዉን ማባከን ለምን ያስፈልጋቸዋል?

ኢህአዴግ ሀገሪቱን ወደ ከፍተኛ እድገት ደረጃ እያደረሳት መሆኑ ላይ ጥርጣሬ ኖሮኝ ባያዉቅም “ከኢህአዴግ ዉጭ ሌላ ፓርቲ በዓይናችን አታሳዩኝ! ኢህአዴግ ከሌለ አገሪቱ ትበታታናለች ወዘተ“ የሚባል አነጋገር ግን በጭራሽ አይስማማኝም፡፡ የስንት ሺህ ዘመን አኩሪ ታሪክ ያላትን ታላቅ ሀገር ዕጣፈንታ በአንድ ፖለቲካ ድርጅት እንደሚወሰን አድርጎ ማሰብ አሳፋሪ ነዉ፡፡ በሀገራችን አዉራፓርቲ ተቀባይነት የሚያሳጠዉ አንዱ ምክንያት የሀራችን ፓርቲዎች የአንድን ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ የሚወክሉና በጠባ አጀንዳ ዙሪያ የተሰባሰቡ በመሆናቸዉ የሁሉምን ህዝቦች ፍላጎት መመለስ ባህሪያቸዉ አለመፍቀዱ ነዉ፡፡ ብሄር- ተኮር መድበለ ፓርቲ ስርአት (ethnic centered parties) ባለበት ሁኔታ ዉስጥ ጭራሽ በአዉራ ፓርቲነት ስም እድሜ ልክ እንዲገዛን ፈቃድ የሚንሰጥ ከሆነ በአጋጣሚ ስልጣን የያዘ አንድ ብሄርን የሚወክል ፓርቲ ሌሎች ህዝቦቸን (ብሄሮችን) ለዘመናት አፍኖ ለመግዛት እድል ይሠጠዋል፡፡

በጃፓንም ሆነ በሌሎች አገሮች ህዝቡ የአዉራ ፓርቲ ስርአት ይሻለኛል ብሎ ስለወሰነ ሳይሆን በየጊዜዉ ሲደረጉ በነበሩ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች አንድ ፓርቲ በተደጋጋሚና በተከታታይ አብላጫ ድምጽ ማግኘት በመቻሉ ነዉ፡፡ ወደእኛ ሁኔታ ስንመጣ የሀገራችን የምርጫ ሁኔታ ተአማንነት ያጣዉ እኮ በህግ አዉጭዉ ዉስጥ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ለመድሃኒት ያህል እንኳን መግባት ባለመቻሉ እኮ ነዉ፡፡ አሁን በሚታየዉ ሁኔታ ሳይሆን ሁኔታዎች ተሻሽለዉ በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች በህግ አዉጭዉ ዉስጥ ወንበር ማግኘት በቻሉበት ሁኔታ ኢህአዴግ አብላጫ ድምጽ እያገኘ ለ25 ዓመት ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት መቶ ዓመታትም በስልጣን ላይ ቢቆይ የሚከፋዉ ሰዉ ባልኖረ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ወንበር አንድ ፓርቲ ለብቻዉ ጠቅልሎ በያዘበት ሁኔታ ኢህአዴግ አዉራፓርቲ መሆን አለበት በሚል ጭራሽ ከኢህአዴግ ዉጭ ሌላ ፓርቲ ፓርላማ እንዳይገባ በህግ ገደብ የሚጥል አዋጅ ማዉጣት በህዝብ ላይ መቀለድ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ እኔ በበኩሌ “መቶ በመቶ” እየተባለ አንድም ተቃዋሚ በህግ አዉጭዉ ዉስጥ የለለበትን የፓርላማ ሁኔታ ሳይ በጣም ነዉ የሚያሸማቅቀኝ፡፡

በፊት በነበሩት ፓርላማዎች ዉስጥ ከሞላ ጎደል በርከት ያለ ቁጥር የነበራቸዉ ተቃዋሚዎች ስለነበሩ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር ሲከራከሩና በሃሳብ ሲፋጩ ሳይ እንዴት እኮራ እንደነበር አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡ በዚያን ወቅት በስራ አጋጣሚ በየእለቱ የማገኛቸዉ የዉጭ ሰዎች አንዳንዴ የፓርላማዉን የተጧጧፈ ክርክር በቴሌቭዝን እያዩ ስጠይቁኝና ስለሁኔታዉ ሳስረዳቸዉ ስለ ዲሞክራሲያችን በአጭር ጊዜ እንደዚህ መሆን መቻል አድናቆታቸዉን ይገልጹልኝ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ለቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር የተለየ አድናቆት የነበረዉ አንድ በስራ አጋጣሚ የማዉቀዉ የዉጭ ዜጋ በአንድ አጋጣሚ ያለኝኝ ምንጊዜም አልረሳም፡፡ ሩሲያኖች የሚስማማቸዉ መሪ አምባገነኑ ስታሊን ብቻ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያዉያንም የሚመጥናቸዉ የመንግስቱ ኃይለማርሪም ዓይነት አምባገነነ መሪ ነዉ፡፡ መለስ ግን ለናንተ የሚገባ አይደለም፡፡ የመለስ ትክክለኛ ቦታ ኢትዮጵያ ዉስጥ አይደለም ነበር ያለኝ፡፡ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ይህ ሰዉ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ነበር፡፡ ዜና እረፍታቸዉን እንደሰማ ግን እጅግ ማዘኑን በመጥቀስ በኢሜል ማጽናኛ ልኮልኛል፡፡ ዛሬ ይህ ሰዉ እዚህ ቢኖርና የዛሬዉን ፓርላማችንን ለመከታተል ችሎ ቢሆን ተደናግጦ በዚህች አገር የሆነ መፈንቀለ መንግስት የተካሄደ ሳይመስለዉ እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ በተገኙ ቁጥር ጉባኤዉን ለመከታተል ከፓርላማ የማይጠፉ የዉጭ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች ከ2002 በፊት የነበረዉ ፓርላማ ዛሬ እንደለለ ለመረዳት አያዳግታቸዉም፡፡ የዉጭ ታዛቢዎች ከዚህ በፊት ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ከአንዳንድ እንከኖች ዉጭ በአብዛኛዉ የሚያበረታታና ተስፋ ሰጪ መሆኑን በገለጹበት ሁኔታ ዛሬ ወደ ኋላ እየተንሸራተትን መሄዳችን ሲያዩ ሳይታዘቡን የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡ የአሁኑ የፓርላማ ስብሰባ ድሮ በደርግ ጊዜ ከነበረዉ ብሄራዊ ሸንጎ በምን እንደሚለይ የሚገልጽልኝ ሰዉ ካለ ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡ በደርግ ሸንጎ ለታሪክ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለዉ አንድ ብቸኛ አጋጣሚ ቢኖር ሚያዝያ 13 ቀን 1983 ዓ/ም የተከናወነዉ የደርግ የመጨረሻዉ አስቸኳይ ሸንጎ በስተቀር ከዚያ በፊት ሲደረጉ በነበሩት የሸንጎዎች የሸንጎዉ አባላት ሁሉንም ነገር በጭብጨባ በአንድ ድምጽ ድጋፍ ከመስጠት ዉጭ አንድም ጊዜ በአንድም ጉዳይ ላይ ሲከራከሩ ወይም የተለየ አስተያያት ሲሰነዘሩ ተሰምተዉ አይታወቁም ነበር፡፡

ዛሬም በሀገራችን ከ2002 ምርጫ ጀምሮ ባሉት ፓርላማዎች እያየን ያለነዉ ነገር አስቀድሜ ከገለጽኩት ከደርጉ ዘመን ሸንጎ ያልተለየ ነዉ፡፡ እንዲያዉም የደርግን ሸንጎ ለማየት እድሜያቸዉ ያልፈቀደላቸዉ ወጣቶች የአሁኑን ፓርላማ ካዩ የደርጉን ሸንጎ እንዳዩ አድርገዉ መቁጠር ይችላሉ፡፡ ልዩነቱ የሸንጎዉ አባላት ለዚያ ወንበር የበቁበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ላይ ብቻ ነዉ፡፡ እንግዲህ የዚህ ዓይነት ችግር ባለበት ሁኔታ ጭራሽ “ አዉራ ፓርቲ ስርአት….. ምናምን” እያልን እንደጥሩ ነገር የምንሰብከዉ ነገር በህዝብ ላይ ማሾፍና ህዝብን መናቅ አድርጌ ነዉ የምቆጥረዉ፡፡

8/ በአዉራ ፓርቲ ስርአት ዉስጥ የመከላከያ ገለልተኝነት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነዉ፡፡

ስለአዉራ ፓርቲ ስርአት ሲነሳ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በዚያ ስርአት ዉስጥ ምን ባህሪይ ሊኖረዉ እንደሚችል በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡ በአዉራ ፓርቲ ስርአት አስተሳሰብ መሰረት ብቸኛ ፓርቲ ለረዢም ጊዜ ብቻዉን ስልጣን ላይ የሚቆይ ከሆነ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ከሚችሉ የዲሞክራሲያዊና መብት መጓደሎችና ሰብአዊ መብት ጥሰትም በላይ እጅግ አሳሳቢ የሚሆነዉ የመከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኝነት ጉዳይ ነዉ፡፡ ገዢዉ ፓርቲ ለዘመናት ስልጣን ሳያስነካ የሚቆይ ከሆነ በፊት ገለልተኛ የነበረና ወገንተኝነቱን ለህዝብ ያደረገ መከላከያም ቢሆን ቀስ በቀስ ከአገዛዙ ጋር እየተላመደና ቤተኛ እየሆነ ስለሚሄድ ከገለልተኝነት ባህሪይዉ እየወጣ ለገዢዉ ፓርቲ ጥብቅና ወደ መቆም ሊገባ ይችላል፡፡ ገዢዉ ፓርቲም ለስልጣኑ ሲል ወታደሩን ቀስ እያለ ፖለቲካን እያላመደዉና በጥቅም እያባበለዉም፤ በፖሊሲ ዉሳኔ አሰጣጥ ዉስጥ እጁን እንዲያስገባ እያደረገዉ ያለ ፊላጎቱ የፖለቲካ ተዋናይ ስለሚያደርገዉ ከጊዜ በኋላ እንኳን ለህዝቡ ይቅርና ለራሱ ለገዢዉ ፓርቲና ለመንግስትም ቢሆን አደጋ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ ከቆየ ፓርቲ ጋር ራሱን ያቆራኘ ወታደር ከፓርቲዉ የሚነጥለዉን የ“ገለልተኝነት “ጉዳይን እጅግ ስለሚጠላ “ለአንድ ፓርቲ ጥብቅና አትቁም “ብሉትም እሺ አይልም፡፡

ለዚህ አብነት እንዲሆነን የቻይናዉን መከላከያ ሰራዊት ብንወስድ (የቻይና መከላከያ ሰራዊት አስካሁንም ነጻ አዉጭ ተብሎ መጠራቱ አስገራሚ ነዉ) ከኮሚኒስት ፓርቲዉ ጋር ተቆራኝቶ ለዘመናት በመቆየቱ አሁን አሁን በምዕራባዉያን ጫና ወታደሩን ከፓርቲዉ በመነጠል ገለልተኛና ፕሮፌሽናል ለማድረግ ሲሞከር ወታደሩ እምቢተኛ እየሆነ ማስቸገሩ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዉ ለዘመናት በብቸኝነት ያለተቀናቃኝ በስልጣን ላይ በመቆየቱ ምክንያት የሀገሪቱ ወታደርም ከፓርቲዉ ጋር እጅጉን በመላመዱ በፓርቲዉና በወታደሩ መካከል አንዳችም ልዩነት ባለመኖሩ “እንዴት ከፓርቲዬ ትነጥሉኛላችሁ?” ብሎ እንዳስቸገረ ብዙ መረጃዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለዉ የሀገሪቱ ብቸኛ ፓርቲ ያለተቀናቀኝ ስልጣን ላይ ለዘመናት በመቆየቱና በሰራዊቱ ዉስጥም ቀስ በቀስ መዋቅሩን በመዘርጋቱ የፓርቲ ጉዳይና የዉትድርና ጉዳይ ዳር ድንበሩ ሳይታወቅ በመደበላለቁ የተፈጠረ ሁኔታ ነዉ፡፡ “In dominant party system, the dividing line between civilians and the military is less clear.” የሚለዉን የምሁራንን ማስጠንቀቂያ ሁሌም ማስታወስ ይገባናል፡፡ ፓርቲና ወታደራዊ ተቋሙ፤ ሚሊታሪዉና ፖለቲከኞች እጅና ጓንት መሆን ሲጀምሩ ለህዝቡ ትልቅ አደጋ ይሆናል፡፡

ስለዚህ በሀገራችንም አዉራ ፓርቲ ስርአት ከተፈጠረና አንድ ፓርቲ ያለ ማቋረጥ በተከታታይ በስልጣን ላይ መቆየት ከቻለ ከቻይና ጋር ተመሳሳይ ነገር ሊገጥመን እንደሚችል ለአፍታም ቢሆን መጠራጠር አይገባንም፡፡

*********

* የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ያለፉ ጽሑፎችን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories