“አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት…” (ለሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ) (ክፍል 2)

(መሓሪ ይፍጠር [email protected]m)

(ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

ውድ አንባቢያን በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ “ጆቤ” በሰራዊቱ ግንባታ ሰነድ ላይ ያነሷቸውን ሃሳቦች ከተጨባጭ ሰነዱ ጋር በማመሳከር ነጥቦቹ ትክክል አለመሆናቸውን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ሰውዬው ለማንሳት የሞከሯቸው ሌሎች ጉዳዩችንም እንዲህ ተመልክቻቸዋለሁ። መልካም ንባብ።…

ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል ሰነዱን አስመልክተው ያነሷቸው ሃሳቦች ለእርሳቸው ፍጆታ በሚውል መልኩ ቀነጫጭበውና እውነት አስመስለው ለማቅረብ ሞክረዋል። ለዚህም “በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ደህንነት መከላከል ማለትና የሀገር ደህንነት መከላከል ማለት በመሰረቱ አንድ ነው ማለት ይቻላል” የሚለውን አባባል ለማብራራት የተቀመጡትን ሃሳቦች ሆን ብለው ለመመልከት አልፈቀዱም ወይም አይተው እንዳላዩ አልፈዋቸዋል። ይሁንና እኔ ግን ሃቁን ለመግለፅ እሞክራለሁ። በማንኛውም ሀገር ውስጥ ሀገርን በመምራት ላይ የሚገኝ ኃይልን በታጠቀ ኃይል የመቀየር ተቃውሞ በሚያጋጥምበት ወቅት፤ ስርዓቱ ምንም ዓይነት ይሁን (ፊውዳላዊም ሆነ አብዮታዊ፣ ሊበራላዊ ሆነ ሃይማኖታዊ…ወዘተ) ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ ያ ስርዓት ደህንነቱን ለማስጠበቅ ሲል የመከላከያ ኃይሉን ተጠቅሞ ራሱን መከላከሉ የሚቀር አይሆንም። ይህ ደግሞ ከፓርቲው ውጪ ሆኖ አንድን ፓርቲ አሊያም ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከመጠበቅ አንፃር ሊገለፅ እንደሚችልና ይህም የሀገርን ደህንነት መጠበቅ ማለት እንደሆነ መፅሐፉ ያስረዳል። እናስ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ከቶ ምን እያሉን ይሆን?

ያም ሆነ ይህ ግን በቅድሚያ በመፅሐፉ ላይ የተጠቀሰው “በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ…” የሚለው አባባል ከሀገራችን ነባራዊ ታሪክ እንዲሁም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሁኔታ አኳያ የተሳሰረ መሆኑን ግለሰቡ የሚዘነጉት አይመስለኝም። ይህ ማለት ደግሞ ባለፉት 25 ዓመታት በተከናወኑት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች መራጩ ህዝብ እዚህ ሀገር ውስጥ የአውራ ፓርቲ ስርዓት (Dominant Party System) እውን እንዲሆን ይሁንታውን ሰጥቷል። እንደሚታወቀው በአንድ ሀገር ውስጥ የአውራ ፓርቲ ስርዓት አለ የሚባለው፤ ገዥው ፓርቲ ለብቻው ወይም በጥምረት (ተጣማሪው ፓርቲ ተመሳሳይ ፖሊሲን የሚከተል ከሆነ) ለረጅም ጊዜ መንግስት ሆኖ የመሪነቱን ቦታ ሲይዝ ነው።

ይህ የፖለቲካ ስርዓት ዓይነት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አካሄድን የሚከተል በመሆኑም፤ በውስጡ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰውና ሃሳባቸውን በግልፅ አስረድተው በሀገሪቱ ውስጥ በሚደረጉ ምርጫዎች ተወዳድረው የማሸነፍ ህጋዊ መብት አላቸው። ስርዓቱን ከሚያራምዱ ሀገሮች ውስጥ ጥቂቱን በማሳያ ምሳሌነት ብናነሳ እንኳን፤ የናይጄሪያን፣ የሩዋንዳን፣ የኢኮቶሪያል ጊኒን፣ የደቡብ አፍሪካንና የጃፓንን አውራ ፓርቲዎች መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። ይህም የአውራ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በዓለም ላይ ያለና በርካታ ሀገራት የሚከተሉት መሆኑን ያሳያል። የሀገራችንም የአውራ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከዚሁ ነባራዊ ሁኔታ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

እናም በእኔ እምነት ይህ የአውራ ፓርቲ ስርዓት በህዝቡ ምርጫ እውን የሆነበት ተጨባጭ ምክንያት፤ የህዝቡን ቀልብ መሳብ የቻለ ወይም ለአቅመ-ተቃዋሚነት የደረሰ ፓርቲ ባለመኖሩ ነው። በሌላ አገላለፅ ህዝቡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ያመጣውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታን አካሄድን መተኪያ በሌለው አማራጭነት መቀበሉና ተቃዋሚዎችም ለይስሙላ በህገ መንግስቱ እየማሉ፣ በሌላ በኩል ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በመሞከራቸው በእነርሱ እምነት ማጣቱን የሚያሳይ ነው። እናም እንዲህ ዓይነቱ ተጨባጭ የህዝብ ፍላጎት ባለበት ሀገር ውስጥ፤ የሀገሪቱ ዘብ የሆነው የመከላከያ ኃይል ከገዥው ፓርቲ ርዕዩተ-ዓለም ተነጥሎ እንደምን ሊገነባ እንደሚችል የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ይመስሉኛል።

ምንም እንኳን እርሳቸው ”የምንገነባው መከላከያ ኃይል አላማው የስርአታችንን ደህንነት መጠበቅ ነው ሲባል የሚገነባውና የሚመራው በስርአቱ መሪ የሆነው አካል ብቻ ነው” የሚለውን የመፅሐፉን አባባል በሚያስገርም ሁኔታ “በጭንቀት፣ በልመና የተደጋገመ ጸሎት አይሉት ምህላ…” በማለት ሰራዊቱ የሚገነባው ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም ሲባል እንደሆነ አስመስለው ለመግለፅ ቢሞክሩም፤ ሃቁ ግን አሁንም በመፅሐፉ ላይ የተጠቀሰውን ማብራሪያ ሆን ብለው በመዝለል እርሳቸው ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ያልተገባ ስያሜ ለሰራዊቱ ለመስጠት ያለመ ይመስለኛል። አዎ! “ጆቤ” ከጠቀሱት አባባል በታች ሰነዱ ገፅ 28 ላይ፤ የመከላከያ ኃይሉን የመምራት፣ የመገንባትና የማሰማራት ሁኔታዎችን ከማንም ጋር በመከፋፈል ሊከናወን እንደማይችልና እንዲህ ዓይነቱ አሰራር በሌሎች ስርዓቶችም ገቢራዊ እንደሚሆን ያብራራል። አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ አካል መሪነቱን ከሌሎች ጋር የማይጋራበት ወይም የማይከፋፈልበት ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ብዙ ቢሆኑም፣ ወትሮና በማንኛውም ጊዜ የአመራሩን ጉዳይ በተመለከተ ወደ ድርድር የማያቀርበው ነገር ቢኖር የስርዓቱን የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ኃይል እንደሆነ መፅሐፉ በግልፅ ያስረዳል።

እርግጥም ሌላው ቀርቶ አድጋለች በምትባለው አሜሪካ ውስጥም ቢሆን የሚገነባ ሰራዊት እንኳን ሳይቀር የሊብራሊዝም ቀኖናን ከልጅነቱ ጀምሮ በተረትና ምሳሌ መፅሐፎች ላይ ሳይቀር እየተነገረውና እየተማረ ያደገ መሆኑን “ጆቤ” የሚስቱት አይመስለኝም። ካደገም በኋላ ቢሆን ሰራዊት ውስጥ ገብቶ “መኮንን” (officer) መሆን የሚችለው ለስርዓቱ ካለው ቀረቤታና ታማኝነት አኳያ እየተመዘነ ነው። ይህ ካልሆነና ግለሰቡ በስርዓቱ ላይ በቂ እውቀት ከሌለው ከ“ባለ ሌላ ማዕረግተኞች” (Non-Commissioned Officers /NCO’s/) ምድብ ይሆንና ወሳኝ በሆኑ የመሪነት ጉዳዩች ውስጥ እንዳይገባ ይደረጋል። ሊብራል ስርዓቱን የሚቃወም ከሆነ ደግሞ፤ ወደ ሰራዊቱ ሊቀላቀል አይችልም። እናስ ለጡረተኛው ሜ/ጄኔራል የእኛ ሀገሩ ሁኔታ አዲስ መስሎ የታያቸው ከምን መነሻ በመነጨ ይሆን?—በእኔ እምነት እንዲያው ዝም ብለው በደፈናው የሰራዊቱን የግንባታ መስመር በማጣጣል ጥላሸት ለመቀባት አስበው ይመስለኛል።  

እርግጥም ይህ የእርሳቸው ጥላሸት የመቀባት ፍላጎት “መጽሐፉ ሕገ-መንግስታችንን በውል መጥቀስ የጀመረው በገጽ 87 ነው” እስከሚለው የቅጥፈት ድርሰታቸው ድረስ የሚዘልቅ ነው። ለነገሩ ማንም ሰው ያንን መፅሐፍ ገለጥ ቢያደርገው ሩቅ ሳይሄድ በገፅ 23 ላይ ህገ መንግስቱን ቢያንስ ሁለቴ ተጠቅሶ ያገኘዋል። እናም እኔ ‘ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል ሆይ! ለምን ይዋሻል?’ ብዬ ልጠይቃቸው እወዳለሁ—እውን የሰራዊቱን ህገ መንግስታዊ ፅናት በሐሰት የገፅ ቁጥርን በመቀያየር ጭምር ኢ-ህገ መንግስታዊ ማድረግ ይቻላልን?—መቼም “ጆቤ” የህግ ምሁር እንደመሆናቸው መጠን፤ እንበልና አንድ ሰው እንዲከሰስ የሚመለከተው አንቀፅ ቁጥር 23 ሆኖ ሳለ፣ በአንቀፅ ቁጥር 87 ሊወነጀል እንደማይችል ከእኔ በላይ ስለሚያውቁ ስለ ቁጥር ምንነትና መዘበራረቅ ልነግራቸው አልሻም—እንዲህ ዓይነቱን የውሸት የቁጥር ጨዋታን ለምን ለመጫወት እንደሞከሩ የሚያውቁት እርሳቸው ናቸውና።

በዚህ ሁኔታ የሰራዊቱን የግንባታ ሰነድ ቁጥሩን ሳይቀር በሐሰት ያዘበራረቁት “ጆቤ” ዝቅ ብለውም “መዘባረቁን በማያሻማ ሁኔታ እየቀጠለ (ሰነዱን ማለታቸው ነው) ‘ኢህአዴግ ከሌለ ይህች ሀገር የለችም የሚለውን አባባል ሲያመላልሰው ይታያል’ ይሉናል። እኔ ግን እርሳቸው እንዳሉት አይመስለኝም። እናም አባባሉን ግን ከግሌ እምነት በመነሳት ለማብራራት እሞክራለሁ—ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል አውቀው የዘለሉትን የመፅሐፉን ክፍሎች በማጣቀስ ጭምር።

በእኔ እምነት በመንግስት የተዘጋጀው ይህ ሰነድ ትክክል ይመስለኛል። ምክንያቱም ገዥው ፓርቲ ባይኖር ኖሮ፤ የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ታጥቀው የነበሩ 17 የሚጠጉ የተለያዩ ብሔር-ተኮር ድርጅቶችን በአግባቡ ማስተናገድ ባልተቻለ ነበር። በወቅቱ ገዥው ፓርቲ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ህግን ተከትሎ ብርቱ ተግባር ባያከናውን ኖሮ፤ አንዳንድ ሟርተኞች “ኢትዮጵያ ትበታተናለች፤ አበቃላት” በማለት የተነበዩት ነገር ዕውን በሆነ ነበር። ምስጋና ለገዥው ፓርቲ ይሁንና ይህ የመበተን አደጋ ተፈፃሚ አልሆነም። የዛሬን አያድርገውና ራሳቸው “ጆቤ”ም ቢሆኑ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት (ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ማለቴ ነው) ይህን እውነታ ይጋሩት ነበር—አዲስ ኒዮ-ሊበራላዊ ካባን ተከናንበው ብቅ ካሉበት ከተሃድሶው መስመር በፊት። ታዲያ ምነዋ ዛሬ ላይ ይህን ዕውነታ ከ15 ዓመት በኋላ በተገለበጠ መነፅር ለመመልከት ፈለጉ?—ህገ መንግስቱን ስለተፃረሩ ከኃላፊነታቸው በመነሳታቸው ምክንያት ነው ወይስ በሌላ?—እርግጥ ምላሹ የእርሳቸው እንጂ የእኔ አይደለም።

“ጆቤ” ከመፅሐፉ ለመጥቀስ አልፈለጉም እንጂ ሰነዱ ዕውነታውን በራሱ መንገድ ገልፆታል። ይኸውም ስርዓቱ ከሌለ ህዝቦች ለዘመናት ሲጠይቁ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ዕውን እያደረጉ ያሉት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት ልማት፣ የማህበራዊ ዕድገት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት…ወዘተ የመሳሰሉ ጉዳዩች ሊኖሩ እንደማይችሉ ያትታል። እነዚህ ጉዳዩች ከሌሉ ደግሞ ሀገሪቱ ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ ተከስቶ ወደ ለየለት ብተና ማምራታችን እንደማይቀርም እንዲሁ።

እርግጥም እዚህ ሀገር ውስጥ የተፈጠሩት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎች ስርዓቱን የሚመራው ገዥ ፓርቲ በተከተለው ትክክለኛ የዕድገት መስመር የተገኙ ናቸው። ስርዓቱን የሚቃወሙ ወገኖች ካሉ፤ እየተቃወሙ ያሉት ይህን ሁለንተናዊ የዕድገት ጎዳና ነው። ይህ የዕድገት መስመር ከተቋረጠ ደግሞ ከፌዴራላዊ ስርዓቱ አኳያ ገና ጀማሪ የሆንባቸውና ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡት የገዥና ተገዥ ስንኩል አስተሳሰቦች የተፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በመሸርሸር ሀገራችንን የሁከትና የብጥብጥ አውድማ ማድረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም። በቅርቡ በኦሮሚያና በጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች የታዩትና ሀገራችን እንድትበተን የሚሹ የውጭ ሃይሎች እንዲሁም የውስጥ ጀሌዎቻቸው አማካኝነት የተቀነባበሩት የፀረ- ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና የህገ ወጥነት ዝንባሌዎች የዚሁ ሃቅ ጥሩ ማሳያዎች ይመስሉኛል።

እናም በእኔ እምነት ይህን ችግር መፍታት የሚችለው በህገ መንግስቱ መሰረት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትንና አንድነትን ዕውን ያደረገው እንዲሁም ህዝቦችን አስተባብሮ ዛሬ ለደረስንበት የህዳሴ ጉዞ ያበቃን ገዥው ፓርቲና እርሱ የሚከተለው ርዕዩተ-ዓለም ብቻ እንጂ፣ እነ “ጆቤ” የሚያቀነቅኑለትና ከሀገራችን ታሪክና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ የማይሄደው እንዲሁም ጥቂቶችን ቱጃር አድርጎ ሚሊዮኖችን በድህነት አረንቋ ውስጥ የዘፈቀው የኒዮ-ሊበራሊዝም ቀኖና አይደለም። ይህ የእኔ እምነት ነው፣ የጡረተኛው ሜ/ጄኔራል አስተሳሰብ ደግሞ ሌላ ሊሆን ይችላል—መብታቸው ነው።

አዎ! ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ሀገራችንን ከብተና ያደነ መስመር፤ ዛሬም ሆነ ነገ ከሚጋረጡብን ማናቸውም አደጋዎች የሚያድነን ገዥው ፓርቲ ብቻ መሆኑን አስረግጨ መግለፅ እወዳለሁ። ኧረ ለመሆኑ እውነት…እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፤ ኢህአዴግ ባይኖር ኖሮ ከቶ የትኛው ኃይል ነው የዚህን ሀገር ችግር በሰከነ ሁኔታ ተሸክሞ ሊሄድ የሚችለው? የትኛውስ አቅም ያለው ፓርቲ ነው እርሱን ሊተካው የሚችለው?…ለምን ሃቁን እያወቅን “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉት ይትብሃል ዓይነት እንደባበቃለን?…ያም ሆነ ይህ ግን እዚህ ሀገር ውስጥ በመተግበር ላይ ያለውን ስርዓት ያመጣው ገዥው ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን፣ ስርዓቱን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መከላከያ ሰራዊቱም ከዚህ አኳያ ዕውነታውን ቢገነዘበው ምንም ዓይነት ችግር ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም— እየተነገረ ያለው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከፓርቲ ወገንተኝነት ውጪ ስለመጠበቅና ስለ መከላከል ጉዳይ ነውና።

ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል በሰነዱ ላይ “እኛ ብለው የሚፅፉ አመራሮች በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሽፋን እኛን አገልግሉ ከሚል ውጪ፣ ያስቀመጡት የተለየ የግንባታ ዓላማዎችና አቅጣጫዎች የሉም” ይላሉ። ለጥቀውም “እኛ” ማነው? ብለው ይጠይቁና ወረድ ብለው ደግሞ፤ “በሰራዊት ግንባታ ላይ ያለው ‘እኛ’ አድሃሪ ነው፣ ፀረ-ዴሞክራቲክ ነው፣ ፀረ-ህገ መንግስት ነው” የሚል ብያኔ ራሳቸው ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ራሳቸው ይሰጣሉ። እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም ይመስለኛል የሀገራችን አርሶ አደር “አንቺው ታመጪው፣ አንቺው ታሮጪው” የሚለው። ለመሆኑ “እኛ” ማለት ችግሩ ምንድነው?—እርግጥ “እኛ”ን “ጆቤ” አያውቁትም ብዬ አላስብም። አዎ! መፅሐፉን ያዘጋጀው መንግስት “እኛ” ሲል ጥቂቶችን ሳይሆን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የሚያምነውን ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል ማለቱ ይመስለኛል—በተለይም የተሃድሶውን መስመር ለማሳለጥ የተሰለፈውንና ከታች እስከ ላይ ያለውን የህብተረሰብ ክፍል። “እነርሱ” ከተባለ ደግሞ ምናልባትም የተሃድሶውን መስመር ለማደናቀፍ የተሰለፉት እነ “ጆቤ” እና ጥቂት የሃሳብ አጋሮቻቸው ሊሆኑ የማይችሉበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም። እናም የሰነዱ ባለቤት የሆነው መንግስት “እኛ…እኛ ነን፤ ‘እናንተ’ ደግሞ እናንተ ናችሁ” ሊላቸው ቢችል ምላሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም።  

ያም ሆኖ ግን የ“እኛ” እና “የእነርሱን” የቃላትና የተግባር አሰላለፍን እዚህ ላይ ልግታውና ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል “እኛ የሚለው አድሃሪ፣ ፀረ-ዴሞክራቲክና ፀረ-ህገ መንግስት ነው” በማለት ስለገለፁት የተሳሳተ ምልከታ ላምራ። እርግጥ “እኛ” ማለት በዋነኛነት ከተሃድሶው መስመር ወዲህ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩን በመከተልና እርሱን የመጨረሻ አማራጭ በማድረግ ለሀገሩ ሁለንተናዊ ዕድገት ደፋ ቀና ብሎ ራሱን በየደረጃው በመጥቀም ሀገሪቱን ያሳደገ አብዛኛው ህዝብ መሆኑን ከተግባባን ዘንዳ፤ ይህ ህዝብና አመራሩ “ጆቤ” እንደሚሉት ከቶም አድሃሪ ሊሆን አይችልም። ይህ ሉዓላዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ በህገ መንግስቱ መሰረት አብዮታዊ ዴሞክራሲን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በካርዱ የመረጠ የተሃድሶው መስመር ህዝብ ፀረ-ዴሞክራቲክና ፀረ-ህገ መንግስት ተብሎም ሊፈረጅ አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ ጥቅልና ተገቢ ያልሆነ ፍረጃ አንድም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጉዳይ ያለመገንዘብ፣ ሁለትም አመራሩን እንኳን ብንተወው ህዝቡን መናቅ ከፍ ሲል ደግሞ በህገ መንግስቱ ላይ መዘባበት ይመስለኛል። ይህ ሃቅም በእኔ እምነት “እነርሱ” ወደ ሚለውና ተሃድሶውን ለማደናቀፍ ወደ ተሰለፉት ሃይሎች የሚወስደን ይመስለኛል። እነ “ጆቤ”ን ያንጠባጠበው የተሃድሶው ባቡር ለውጥና ዕድገት ፈላጊውን የሀገራችንን ታታሪ ህዝብ አሳፍሮ ተጠቃሽ የሚሆን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገትን ያስመዘገበ፣ ዴሞክራሲ እንደ ሸቀጥ ከውጭ የሚገባ ቁሳቁስ አለመሆኑን ተገንዝቦ ከሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ዴሞክራሲውን የቀመረ፣ በሀገር ውስጥ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ አስተማማኝ ሰላምን ከመፍጠር ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበሬታን ያገኘና ለጎረቤቶቹ ጭምር ቤዛ እየሆነ ያለን ሰራዊት የገነባ ህዝብ ነው ወይስ ከዚህ በተቃራኒ የተሰለፉት እነ “እነርሱ” ናቸው በአድሃሪነት፣ በፀረ-ዴሞክራቲክና በፀረ-ህገ መንግስትነት መፈረጅ የሚኖርባቸው?—መልሱን ለዚህ ፅሑፍ አንባቢ እተወዋለሁ። አንድ ጉዳይ ግን ለመግለጽ ፈለግሁ። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ገና በመግቢያው ላይ ሲጀምር “እኛ …” ብሎ ነው። ይህ ማለት ደግሞ የሀገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደሆነ ይጠፋዎታል ብዬ አልገምትም። እናም ሰነዱን በኢ-ህገ መንግስታዊነት እየተቹ መልሰው ራስዎ ህገ መንግስቱን እየተቃረኑ አይመስልዎትምን?

ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል በሰነዱ ላይ ያሉት ጉዳዩች በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይም የተቀመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል። ሆኖም ያ ሰነድ በአደባባይ ለህዝብ ሰራዊቱን “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም የኢህአዴግ የመጨረሻ መከላከያ ምሽግ ነው አይልም” የሚል የመቃወሚያ ሃሳብ በማንሳት “ለምን?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ይህ ጥያቄያቸው ሁለት ጉዳዮችን የያዘ ነው። አንደኛው የሰራዊቱ የግንባታ ሰነድ በድብቅ ለሰራዊቱ የተዘጋጀ ማስመሰል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሀገራዊ ስትራቴጂና በአንድ ተቋም መመሪያ መካከል ያለውን ልዩነት ሆን ብሎ ለማምታታት መፈለግ ነው። ይሁንና “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለው ሰነድ በህገ መንግስቱ መሰረት የተዘጋጀና ማንኛውም አካል በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል ነው። ለዚህም እኔ ራሴ እማኝ መሆን እችላለሁ። አንድ መከላከያ ውስጥ የማውቀውን ወዳጄን ‘መፅሐፉን ማንበብ ስለምፈልግ ወታደራዊ ምስጢር ከሌለበት አምጣልኝ’ ብዬ ስጠይቀው ሰነዱን እጄ ላይ ለማስገባት የሁለት ሰዓት ጊዜ እንኳን አልፈጀብኝም። እርግጥም መፅሐፉ የተደበቀ ነገር የሌለው በመሆኑ በእጅ ለማስገባት ይህን ያህል ቀላል ነው።

ፖሊሲንና ስትራቴጂን ከአንድን መንግስታዊ ተቋም መመሪያ ጋር ሆን ብሎ ለማጣረስ በጡረተኛው ጄኔራል መኮንን የተደረገው ጥረትም ግርምትን ያጭራል። እርግጥ እርሳቸው ስለ ስትራቴጂና መመሪያ ዕውቀት የላቸውም ባልልም፤ ፖሊሲና ስትራቴጂ አንድን ዓላማ ለማሳካት ስለ አጠቃላይ ጉዳይ ምስል የማስያዝና በአጠቃላዩ ውስጥ ያሉት ክፍልፋዩች የተተለመውን ዓላማ ለማሳከት እንዴት እንደሚዛመዱ የሚያሳይ ጥቅል አቀራረብ ነው። በተለይም ስትራቴጂ በማንኛውም ጊዜ የሚቀየር አይደለም። ለስትራቴጂው መነሻ የሆኑት ጉዳዩች ወይም የስትራቴጂው ዓላማዎች ሲቀየሩ ስትራቴጂውም አብሮ ይለወጣል። የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይም ከዚሁ አኳያ የመከላከያ ጉዳዩች በጥቅል በተቀመጡ ሃሳቦች ተገልፀዋል። ይህ ማለት ግን ተቋሙ በመመሪያነት የሚያወጣቸው ዝርዝር ጉዳዩችን ፖሊሲውና ስትራቴጂው ይመለከተዋል ማለት አይደለም። እናም በሰነዱ ላይ ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባይገለፅም፤ መንግስት በተቋሙ ዝርዝር አሰራር ውስጥ እንዲሰፍር ማድረጉ ተገቢ ይመስለኛል። ጥቅል ጉዳዩችን በሚይዘው ፖሊሲና ስትራቴጂ ውስጥ ሁሉንም ነገር ዘርዝሮ ማስገባት አይቻልምና።      

“ጆቤ” በሚያስገርም ሁኔታ “ከህገ መንግስቱ ጋር ይጋጫል” በማለት ያልተገባ ስም ሰጥተውት “ከስራ ይታገድ” የሚል “ብይን” እንደ ዳኛ ያስተላለፉበት ሰነድ፤ እርሳቸው ያልጠቀሷቸውን የሰራዊቱን ወታደራዊ ግንባታ እጅግ በሚበዙት ገፆቹ  ይተነትናል። ከእዚህ መካከል መፅሐፉ ጦርነት የፖለቲካ አንድ ገፅታና ተቀጥያ መሆኑን፣ ስለ መከላከያ አቅም በተለይም ስለ ጦርነት አቅሞች ምንነት፣ ኢኮኖሚ የመከላከያን አቅም ለማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ ስለመሆኑ፣ ስለ ወታደራዊ ግንባታ ምንነት፣ መነሻና አፈፃፀም እንዲሁም በአነስተኛ ወጪ ጠንካራ የመከላከያ አቅምን ስለመገንባት ብሎም በመከላከያ ግንባታና በኢኮኖሚ ልማት መካከል ስላለው መደጋገፍ ከወቅቱ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያስተሳሰረ በሳይንሳዊ መንገድ የሚተነትን ነው። እናም ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል “ከስራ ይወገድ” ያሉት ሰነድ እነዚህን ወታደራዊ ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን ጭምር የያዘ ነው። እርግጥ ሰውዬው ምን እያሉን ነው?…አንድ ስለ “ደርግ መጣ” አስተያየት የሚሰጥ ሰው፤ ማንኛውንም ነገር “ይወገድ” የሚል ከሆነስ ራሱ ስለ ደርግነት ማቀንቀን አይሆንበትምን?

በመጨረሻም ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል “ከስራ ይወገድ” በማለት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅፈው በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረጉት የሰራዊቱ የግንባታ ሰነድን የተመለከተው ደብዳቤያቸው በግብዓትነት የሚያገለግል ይመስለኛል። ግብዓትነቱ ግን ደብዳቤው እንደሚለው ሰነዱ ከህገ መንግስቱ ጋር በመጋጨቱ ዳግም እንዲታይ አይደለም—ቀደም ሲል ባቀረብኳቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ሰነዱ ህገ መንግስቱን የሚደግፍ እንጂ የሚቃረን አይደለምና። እናም ግብዓትነቱ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እርሳቸው ለሚመሩት ድርጅትና ሀገር ጭምር ነው። ይኸውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን ለተሃድሶው መስመር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዩችን ለመለየት ድርጅታቸው ሰፊ ውይይት ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ለገለፁበት አግባብ፤ የተሃድሶው መስመር ያንጠባጠባቸው ወገኖችም የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ሳይታክቱ በሚዲያ የሚለቋቸው አደናጋሪና ጥላሸት ቀቢ ፅሑፎች እስከ የት ድረስ ሊጓዙ እንደሚችሉ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳያቸው ይመስለኛል።

**********

Guest Author