“በሂደት ግብፆች አደብ እየገዙ መሄዳቸው አይቀርም” | የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቃለ-ምልልስ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲስ ዓመትን በማስመልከት ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃል ምልልስ።

አዲስ ዘመን፦ መጪው ዓመት የሀገራችን ህዝቦች ከሚጠብቁት ትልቅ ጉዳይ አንዱ «ምርጫ 2007» መሆኑ ይታወቃል። መንግስት ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና እንከን የለሽ ለማድረግ ምንድን ዝግጅት እያደረገ ነው? በተለይ ገዥው ፓርቲ በዚህ በኩል ምን እየሰራ ይገኛል? አንዳንዶች በፕሬስ ህጉና በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት መንግስት አሁን እየወሰዳቸው ያለውን እርምጃ የዴሞክራሲ ሂደቱን ለማፈን ነው ለሚሉት መንግስት ምን ምላሽ አለው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፦ የመንግስት ቁርጠኝነት ምርጫው ሰላማዊ ፤ ዴሞክራሲያዊ፤ ፍትሀዊና ነፃ እንዲሆን ይሰራል። መንግስት ይህን የሚያደርግበት ዋናው ምክንያት ለተቃዋሚዎች ብሎ አይደለም። መንግስት ይህን የሚያደርግበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ያለ ዴሞክራሲ ህልውናዋ ተጠብቆ ለመቆየት አይችልም የሚል ሙሉ እምነት ስላለው ነው። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ብዙ ሃይማኖቶች በጋራ ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገርም ናት። ኢትዮጵያ በዕድሜ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ደግሞ በርካታ ወጣቶች (አሁን እንኳን ወደ 20ሚሊዮን ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ) ይገኛሉ። ይህ ሁሉ የህብረተሰብ ክፍል ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት ካልተገነባ በስተቀር የሀገራችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

እናም ሁሉንም አመለካካቶች፣ ፍላጎቶች ለማስተናገድ የሚስችል ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ነው። ይህንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የሚደረግን ትግል የሚያሰናክል ኃይል ካለ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በፅኑ ይታገላል። አለበለዚያ ዴሞክራሲ በሌለበት ሰላም ሊኖር አይችልም። ሰላም በሌለበት ዴሞክራሲ ሆነ ልማት ሊመጣ ስለማይችል ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ብሎ የሚያምን መንግስት ያላት ሀገር ናት።

ስለዚህ ተቃዋሚዎች ስላሉ ወይም ስላላሉ የሚደርግ ጉዳይ አይደለም። ይህ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ተቃዋሚዎችም ፣ የውጭ ኃይሎች ሆኑ ማንም ይበል ነገር ግን ዴሞክራሲ ለእኛ አማራጭ የሌለው የአስተዳደር ሥርዓት ነው። ይህ መከናወን አለበት። መራጩ ህዝብም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫውን ማካሄድ አለበት። ዴሞክራሲ ሲባል በርግጥ ምርጫ ብቻ አይደለም። ዴሞክራሲ ባህል ነው። ዴሞክራሲ የባህልና የተቋማት ግንባታ ነው። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ባህሉ እንዲገነባ ከምርጫም ባሻገር ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ ውይይት በማካሄድ ስህተቶች ሲኖሩም ህዝቡ በቀጥታ የሚናገርበትን የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች እየተካሄዱ የበለጠ ዴሞክራሲው ባህል እንዲሆን ይጠይቃል።

ምርጫ የአንድ ወቅት ስራ ነው። የአምስቱን ዓመት ምርጫ እስከሚመጣ መንግስት ዝም ብሎ አይቀመጥም። ህዝቡም ወሳኝነቱ በተለያየ መንገድ መግለፅ አለበት። ድምፁ በቀጥታ መሰማት አለበት። ስለዚህ የኢትዮጵያ (የኢህአዴግ) መንግስት ይህን ስራ በተከታታይ እየሰራ መጥቷል። ከህዝቡም ጋር እየተወያየ ህዝቡም የልማቱ ዋነኛ ባለቤት እንዲሆንና በማስፈፀም የሚከናወን ልማት እንደመሆኑ መጠን ከህዝቡ ጋራ በስፋት እየተወያየ ነው የመጣው። ይህ ራሱ ዴሞክራሲ ነው። ስለዚህ ዴሞክራሲ በዚህ ደረጃ መታየት አለበት። ይህን ካስቀመጥን በኋላ ግን ይህ ዴሞክራሲ ያለ ህግ የበላይነት ሊፈፀም አይችልም። የህግ የበላይነት ከሌለ ዴሞክራሲ ወደ ምን ይቀየራል? ወደ ብጥብጥ (ኪዮስ)ይቀየራል። ስለዚህ ዴሞክራሲ ሁልጊዜ የሚሰራው ዴሞክራሲ ግንባታ በሚካሄድባት ሀገር የህግ የበላይነትና ልዕልና ሲኖር ነው።

ማንም አካል አሸባሪ ለመሆን ከፈለገ የሽብር ህግ ወጥቶ ይጠየቃል። በህግና በሥርዓት መተዳደር አለበት። የሽብር ህጉ በሌለበት መንግስት ዝም ብሎ ሰውን ማሰር አይችልም። ወደ ፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስወሰን ደግሞ ህግ ያስፈልጋል። ስለዚህ አሸባሪነት ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ አይደለም። አሸባሪነት የአፍሪካም ሆነ የዓለም ችግር ነው። ዛሬ ዛሬ መላው ዓለም አሸባሪነትን ለመታገል ቆርጦ የተነሳበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በየቦታው ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ አሸባሪነት ይታያል።ኢራቅ ፣ ሶማሊያ፣ ናይጀሪያ ፣ አፍጋኒስታን ላይ እየሆነ ያለው ይታወቃል። በመላው ዓለም በተለያዩ ቦታዎች ማዕከላዊ አፍሪካን ጨምሮ በርካታ አሸባሪ ቡድኖች ሀገሮችን እያተራመሱ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ከሀገር ውስጥም የመነጨ ነው፤ ከውጭም የሚመጣ ነው። ስለዚህ ሽብተኝነትን መዋጋት ማለት ምርጫን ማደናቀፍ አይደለም። እንዲያውም ለምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት በምንም መልኩ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ሽብርተኝነትን የመዋጋት ስራውን ለአንድ አፍታም አያቆምም። በፊትም አላቆመም። ለምርጫን ብሎም አይደለም። የፀረ ሽብርተኝነት ትግል አሁን የጀመረውም ትግል አይደለም። ድሮም የነበረ ነው። ከዚህ በፊትም በርካታ አሸባሪዎች በሚታሰሩበት ጊዜ ይህን ተመሳሳይ ነገር ይሉ ነበር። አሁንም ይላሉ። ስለዚህ ይህ የሚቀጥል ትችት ስለሆነ ለዚህ ትችት ብዙ ቁም ነገር የምንሰጠው አይደለም። ምክንያቱም የመጀመሪያውና ትልቁ የኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነት ህዝቦችንና ዜጎችን ከሽብር ማዳንና መከላከል ነው። ስለዚህ ይህን ለመከላከል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ምን አልባት ከሽብርተኞች ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ አካላት ሊቃወሙት ይችላሉ እንጂ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊቃወመው አይችልም። እነዚህ አካላት ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው።

የፕሬስ ህጉንም በተመለከተ ፕሬስ ሀሳብን በነፃነት እንዲገለፅ መብት የሰጠ ህግ ነው ያለን። በተመሳሳይ ደግሞ ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጭ፣ ሽብተኝነትን የሚፈጥር እንደዚሁም ደግሞ ከመንገዱ አልፎ ከተሰጠው የፕሬስ ነፃነት ህግ ተላልፎ ከህዝብ ጋር የሚያጋጭና ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥር እንደዚሁም ሽብርተኝነትን የሚፈጥር የፕሬስ ውጤቶች ካሉ ደግሞ ህጉ በሚጠይቀው መሰረት መጠየቅ አለባቸው። ይህ ካልተጠየቀ ውጤቱ ምንድነው የሚሆነው የህዝብና የሀገር መተራመስ ነው የሚፈጠረው። በዚህም ሰፊው ህዝብ የሚጎዳበት ነው የሚሆነው። ይህን ደግሞ እንዲያስተባብርለትና እንዲከላከልለት ህዝቡ መርጦ ያስቀመጠው መንግስት ኃላፊነት አለበት። ማስፈፀም የሚችለው መንግስት ብቻ ነው። መንግስት ዝም ካለ ደካማ መንግስት ነው የሚሆነው፤ ህዝቡ የሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ የማይወጣ መንግስት ነው የሚሆነው ማለት ነው።ይህ እንዳይሆን መንግስት የፕሬስ ውጤቶች ተጠቅሞ ሽብር ለማካሄድ ህዝብ ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚፈልጉ አካላትን በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ መደበኛ ስራውና ኃላፊነቱን ተወጣ ተብሎ መነሳት ያለበት ነው እንጂ ከምርጫ ጋር መጣበቅ የለበትም የሚል እምነት ነው ያለን።

አዲስ ዘመን፦ በውጭ የሚኖሩ አንዳንድ ተቃዋሚ ዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖ ሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ከማየት ይልቅ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ መግባቷን ደጋግመው ይገልጻሉ። የዚህ ዓይነቱ ችግር ጎልቶ ሊሰማ የቻለው መንግስት በበቂ መጠን ራሱን በግልጽነት ለማስተዋወቅ፣ ስራውን ለመግለጽ ስላልቻለ ነው የሚሉ አሉ፤ይህ ምን ያህል ተጨባጭነት ይኖረዋል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፦እንግዲህ ይህ መረጃ ለማን ነው የሚሰጠው የሚል ጥያቄ አንስተን፤ መረጃው በሚያስፈልገው የህብረተሰብ ክፍል ከፋፍለን ማየት ይገባናል ማለት ነው። እንደዚሁም ደግሞ በሀገር ውስጥና በውጭ የመረጃ አሰጣጥ ሥርዓታችንን መገምገም ይጠይቀናል። ጭፍን የሆነ ድምዳሜ ላይ እንዳያደርሰን ስለምሰጋ ከፋፍለን ብናየው ይሻላል የሚል እምነት አለኝ ። ከዚህ አንፃር በሀገር ውስጥ ህዝቡ ራሱ የልማቱ ዋነኛ መሰረት፣ ተዋንያንና ባለቤት ነው። ስለዚህ ስለ ግብርና ልማት ለአርሶ አደሩ እንንገር ብትል አርሶ አደሩ ራሱ በዚህ ውስጥ ተሳትፎ ምርታማ እየሆነ የመጣ አርሶ አደር ነው። ስለዚህ አብዛኛውን ያውቀዋል ማለት ነው።

በእርግጥ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ሊኖር ስለሚችል ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ የተሻለ ተሞክሮ እንዴት ይተላለፍ የሚለው ነገር በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በመረጃ አሰጣጥ ሥርዓት መሄድ እንዳለበት ይታመናል።

በተከታታይም ደግሞ አርሶ አደሩ በሬዲዮና በቴሊቪዥን መረጃዎች በስፋት እያገኘ ነው። ለራሱ ስራ ብቻ ሳይሆን ስለ አጠቃላይ ሀገሪቷ መረጃ ማግኘት መለዋወጥ ያስፈልገዋል። እዚህ መረጃ መለዋወጥ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስትንግ ኮርፖሬሽን ሆነ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ስራ የሚሰሩ አካላት በሙሉ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል። የግል መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ማለት ነው። ከተሞች አካባቢ የሚሰራው ስራም በተመሳሳይ መንገድ በአብዛኛው የከተማ ልማት ስራዎች ህዝቡ ተሳታፊ ነው።

ነገር ግን እዚህ ላይ በቂ መረጃ በማግኘት ዙሪያ በቅርቡም የገመገምነው ምንድነው ለህዝቡ ሊገባው በሚችል መንገድ መረጃዎችን የማቅረብ ጉዳይ ላይ ጉድለቶች አሉብን የሚል ግምገማ አለ። በዚህ ዙሪያ ወደፊት ህዝቡ የበለጠ መረጃዎችን በደረቁ ብቻ ሳይሆን ሳቢ በሆነና ሊረዳው በሚችል መንገድ የሚያገኝበት ሥርዓት መዘርጋት አለብን የሚል እምነት አለኝ። ለዚህ ተብሎ ነው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሊቪዥን ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተቀየረው። ኮርፖሬሽኑ በዚህ ደረጃ ለውጥ ያመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በተመሳሳይ መንገድ የውጭውን ሁኔታ በምናይበት ጊዜ የመረጃን ምንጭንና መረጃ ማስተላለፍ በተመለከተ ተቃዋሚዎች የሚስተላልፉት መረጃ ተዋንያን የሆነውን ህዝብ በአይኑ የሚያየውን በእጁ የዳሰሰውንና የተሳተፈበትን ነገር አጣመውና ገልብጠው ነው የሚያቀርቡለት። ስለዚህ ህዝቡ ብዙውን ጊዜ ትግርት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ነው ያለው። «እኛ ጋር ያለው ነገር አብረን የተሳተፍንበት የምናየው ነገር ይህን ይመስላል። ተቃዋሚዎች ደግሞ ሀገር እንደተቃጠለ ምንም እንደሌለ አድርገው ያቀርባሉ። እነዚህ ሰዎች ለምንድነው መጥተው የማያዩት» ይላል-ህዝቡ። በአብዛኛው ደግሞ ሀገር ውስጥም ተመሳሳይ የእነሱን ተልዕኮ የሚያስፈፅሙ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ያሉትን ያህል በውጭ ያሉም መገናኛ ብዙሃን ናቸው ሀገሪቷ የተቃጠለች የሚያስመስል፤ ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም የማይገባበት የሚስመስል ፕሮፖጋንዳ የሚነዙት።

ስለዚህ ይህን የሚመክት የመገናኛ ብዙሃን ስራ ሊኖረን ይገባል የተባለው ተገቢና ትክክል ነው። በማህበራዊ ድረ ገፆች ሆነ በተለያዩ ኤሌክትሮኒክስና ህትመት ሚዲያዎች ይህን የሚመክትና ተዓማኒነት ያለው፤ ተጨባጩን ነገር በተገቢው ሁኔታ የሚያስረዳ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን በተጨማሪ በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ዘዴዎች ይህን ስራ መስራት ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲግ ኮርፖሬሽን በውጭ ሀገራት በራሱ ሳተላይት መረጃዎችን ማቅረብ በጀመረበት ወቅት በፊት ከነበረበት ሁኔታ ተገልብጧል።

አሁን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለሀገራችን የሚነገረው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሳይሆን ያለውን ተጨባጭ ነገር ማየትና መስማት ችለዋል። ይህ በመሆኑ ምክንያት በስፋት በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አመለካከታቸው እየተቀየረ መጥቷል። እነዚህ ተቃዋሚዎች (አብዛኛዎቹ ፀረ ሰላም ኃይሎች ናቸው) የሚሰጡት መረጃ የተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋለጠ የመጣበት ሁኔታ አለ። ይህን የማጋለጥ ስራ የበለጠ አጠናክረን መስራት የሚገባ መሆኑን ማየት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራትና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምን ይመስላል? በተለይ ወንጀለኞችን አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ማሳያ የሆኑ እርምጃዎች መኖራቸው ይታወቃል። ከዚህ አኳያ እየታየ ያለውን ውጤት እንዴት ይገልጹታል? አሁንም ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመው በተለያዩ ሀገሮች የሚገኙትን በሀገር ውስጥ ለፍትህ ለማቅረብ እየተሰራ ያለ ነገር አለን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፦ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ በከፍተኛ (በጥሩ) ደረጃ ላይ ነው ያለው። ከኤርትራ መንግስት ውጪ ከደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ከኡጋንዳ፣ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ነው ማለት ይቻላል። ይህ በየጊዜው እየተገነባ የመጣ ግንኙነት ነው። ግንኙነታችን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ወይም ደግሞ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ብቻ አይደለም። ግንኙነታችን አሁን በመሰረተ ልማት መተሳሰር፣የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር፣ በአካባቢው ባሉ የሰላም የፀጥታና የልማት ጉዳዮች ላይ በየጊዜው እየመከሩ የመወሰንና በቅርበት ደግሞ የመገናኘት አይነት ሆኖ በጣም የተቀራረበና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው። አንዱ ችግር ያለው ከኤርትራ መንግስት ጋር ነው። Hailemariam Desalegn

የኤርትራ መንግስት ጉዳይ ያው እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት ሰላም ባለመፈለጉ ምክንያትና ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ መቀበል ባለመፈለጉ ምክንያት አሁንም የረባ ሰላም በዚህ አካባቢ የተፈጠረበት ሁኔታ የለም። እኛ አሁን ጉርብትናውን ለማሻሻል የሰላም ጉዞ አብሮ ለመጓዝ በመሰረተ ልማትም ለመተሳሰር ዝግጁ ነን። ነገር ግን እዚያ ያለው መንግስት ፀረ ሰላም ኃይሎችን እያደራጀ ኢትዮጵያንና የአፍሪካን ቀንድ ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አሁንም አላቆመም። በስፋት እየቀጠለበት ያለበት ሁኔታ አለ።

ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት የወደሰው ቋሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ እርምጃ በየጊዜው እየወሰዱ ማስተካከል ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይህ ቋሚ ፖሊሲያችን የሚቀጥል ይሆናል ማለት ነው። ሂደቱን የማያቆም ከሆነና በተከታታይ ኢትዮጵያና አካባቢውን ለማተራመስ የሚንቀሳቀስ ከሆነ እርምጃ በመውሰድ ሁኔታውን ማርገብ አለብን የሚል እምነት ተይዞ በተከታታይ እየተሰራ ያለበት ሁኔታ አለ። ይህ ይቀጥላል።

ወንጀለኞችን እና አሸባሪዎችን በተመለከተ ያው ቋሚ ስራችን ነው። መደበኛ የመንግስት ስራ የራሱን ዜጎች የመከላከል፣ የራሱን ዜጎች በሰላም ሰርተው የሚኖሩበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣ በሰላም ገብተው የሚወጡበትን ሁኔታ ያማመቻቸት። አገሪቷ የተረጋጋችና ኢንቨስትመንትን የምትስብ አገር እንድትሆን ማድረግ ቋሚ ስራችን ነው። ይህንን የሚያደናቅፍ ማንኛውም ወንጀለኛ የትም ይኑር በህጉና ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት እየያዝን ለህግ የማቅረብ ነው።

የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ሰላምና ዴሞክራሲ ሊሰፍን አይችልም። ልማትም ሊጎለብት አይችልም። ስለዚህ ህግን ሥርዓትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛውና ቋሚ ተግባሩ ነው። ከዚህ አንጻር በጎረቤቶችም አገሮችም ይኑሩ በሌሎችም አገሮች ይኑሩ እነዚህ ወንጀለኞችን አሁን በጀመርነው መንገድ ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ መስራታችን የሚቀር አይሆንም። ወይም ደግሞ ማምጣት እንኳን ባንችል ባሉበት አገር በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ የግድ ይሆናል። ስለዚህ ይህ ስራችን መደበኛ ስራችን ነው። ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በክፍለ አህጉሩ ግንኙነት ለማጠናከር በየሀገሮች ያለው የእርስ በእርስ ግጭት እንቅፋት እንዳይሆን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፦ የእርስ በእርስ ግጭቶች ካሉባቸው ቦታዎች ሦስቱን ለመጥቀስ ያክል፤አንደኛ ሱዳን ውስጥ ያለ ነው። ሱዳን ውስጥ እንደሚታወቀው ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚለያዩበት ጊዜ ደቡብ ኮርዶፋንና ብሉ ናይል አካባቢ ያሉ አማጺያን ገና ስምምነት ሳይጨርሱ ነበር የተለያዩት። እነዚህ ከሱዳን መንግስት ጋር የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ግጭት አለ። ይህንን በኢጋድ፤ኢትዮጵያ ደግሞ እንደ ኢጋድ ሊቀመንበርነት እና የአፍሪካ ህብረት (ሀይ ሌቭል ኢምፕሊመንቴሽን ፓናል) የሚባለውና በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራው ሁለታችንም በጋራ በመሆን ሱዳን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ሰሞንም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ከሱዳን መንግስት ጋር እንዲደራደሩ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው ያለ ነው።ይኼ ጥረታችን የሚቀጥል ይሆናል።

ሁለተኛው በአቢዬ አካባቢ ያለ ነው። የሰላም አስከባሪ ሰራዊታችን እዛ ሰላም በማስከበር ሂደት ውስጥ እንዳለ ተደጋግሞ የተገለጸ ነው። በዚህም አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተለይም የሱዳን መንግስትና የደቡብ ሱዳን መንግስት በድምበርም ሆነ በአቢዬም አካባቢ ሁኔታቸውን ወደ ሰላም በሚያስኬድ መንገድ አልጨረሱትም ። ይህንንም ጉዳይ እንዲጨርሱ ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ ሊቀመንበርነቷ በፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ከሚመራው ቡድን ጋር አንድ ላይ በመሆን ስራችንን አጠናክረን እየቀጠል ነው ያለነው።ሌላው በደቡብ ሱዳን ውስጥ በራሱ የተፈጠረው ግጭት ነው። የአማጺው ቡድንና መንግስት እንዲደራደሩ ለማድረግ በኢጋድ አስተባባሪነት ኢትዮጵያን እንደ ሊቀመንበርነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች ያለችበት ሁኔታ አለ። ምናልባትም የእነዚህ የአካባቢ ግጭቶች ወደ ሰላም እንዲመጡ የምናደርገው ጥረት ጊዜያችንን (አብዛኛቸውን ጊዜያችንን) የሚሻማበት ሁኔታ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ይኼ ፈጥኖ እንዲያልቅና ፈጥኖ እንዲቋጭና እኛም የልማት ስራችንን፣ የቤት ስራችንን እዚህ በደንብ ለመስራት እንዲመቸን ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ያለንበት ሁኔታ አለ። በቅርቡም የተወሰነ ግጭት የማቆም ስምምነት የተፈራረሙበት ሁኔታ አለ። ግን አሁንም በሚገባ ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ በፓርቲዎቹ ውስጥ ያለው ሁኔታ የፈለግነው ደረጃ የደረሰ አይደለም። ስለዚህ ይህ የሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ እና የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ጫና እንዲያሳድር ለማድረግ ጥረት ማድረግና ይሄን መግፋት መቀጠል የሚገባን ይሆናል።

ሦስተኛው የግጭት ቦታ ተብሎ የሚወሰደው ሶማሊያ ውስጥ ያለው ነው። በቅርቡ ሶማሊያ ውስጥ አሚሶም ውስጥ ኢትዮጵያ ከገባች በኋላ አልሸባብን ከሶማሊያ ጠርጎ ለማስወጣት እና ህዝቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ ሰራዊታችን በሚከፍለው መስዋዕትነት አማካኝነት ሌሎች የአካባቢው ሰራዊቶች የዩጋንዳ፣ የኬንያ፣ የቡሩንዲ፣ የሴራሊዮን ገብተዋል። ከእነዚህ ጋር አንድ ላይ በመስራታችን ምክንያት አልሸባብን ከአብዛኛው ቦታዎች እየጠረግን ያለንበት ሁኔታ አለ። የበለጠ እንዲዳከም እያደረግን ያለንበት ሁኔታ አለ። ግን ስራው ቀጣይነት የሚጠይቅ ስራ ነው። የዓለም አቀፍ ህብረሰብ ድጋፉን የበለጠ እንዲሰጠን ማድረግ ይጠይቀናል። ይኼ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አሁንም ኢትዮጵያ በእነዚህ በአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማርገብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው። ከአሸባሪዎች ጋር የምታደርገው ትግልም ግምባር ቀደም ሆና የራሷን ድርሻ እየተጫወተች ያለችበት ሂደት ነው ያለው። ስለዚህ ይኼ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፦ በቅርቡ ግብፅ ሱዳንና ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፤ በዚህ ውይይት ምን አዲስ ነገር ተገኝቷል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- አንደኛ አዲሱ ነገር ግብፆች ተረጋግተው መወያየት መቻላቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ድሮም የያዘችው አቋም አሁንም አቋሟ ነው፡፡ አሁን የሆነው ነገር ካርቱም ላይ ባደረግነው ውይይት ድሮ እኛ ያቀረብነውን ነገር አሁን ተቀብለውታል፡፡ ግብፅ ላይ የመጣው አዲሱ ሥርዓትና መንግስት ማላቦ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በምናካሂድበት ጊዜ «በተረጋጋ ሁኔታ ይሄን ነገር ብንወያይበት ይሻላል፣ ለጋራ ጥቅም አብረን ብንሰራ ይሻላል» የሚል ስምምነት ነበረን፡፡ በዚያ ስምምነት መሰረት ተረጋግተው ተወያይተዋል፡፡ ያኔ በቀረበውም ተስማም ተዋል፡፡ ያን ጊዜም ቢሆን ግብፆች ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ነገር ትተው ሌላ ተጨማሪ ነገር እያመጡ ስላስቸገሩ ነው ስብሰባው የተበተነው፡፡ አሁን ደግሞ ያንን ተጨማሪ ነገር በሙሉ ጥለው ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘውን ነገር ብቻ ነው የተነጋገሩት፡፡ ስለዚህ ወደ አእምሯቸው፣ ወደ መስመር ገብተዋል ብለን ነው የወሰድነው፡፡ ይሄ ማለት ግን እያደር አዳዲስ ነገር ይዘው አይመጡም ማለት ግን አይደለም፡፡ በሂደት ተረጋግተን የራሳችንን አቋም ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ሆነ ለግብፃውያን በሚገባ እያስረዳን ስንሄድ ግብፆች በየጊዜው አደብ እየገዙ መሄዳቸው አይቀርም፡፡

በነገራችን ላይ ወደዚህ የመጡበት ወደው ሳይሆን እኛን ዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡ በሚገባ እንዲረዳን በማድረጋችን ነው። በየቦታው አንኳኩተው አንኳኩተው በቂ ድጋፍ ስላላገኙ ነው ወደ ውይይት የመጡት፡፡ ስለዚህ ይሄ የሚያሳየው ምንድነው አሁንም ዲፕሎማሲያችን ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑነ ነው፡፡ አሁንም የተረጋጋ አካሄዳችን ተጠብቆ መሄድ አለበት፡፡ አሁንም ለጋራ ጥቅም የምንሰራው ስራ ተጠናክሮ መሄድ እንዳለበት ነው የሚያሳየው፡፡ ስለዚህ ለውጡ በግብፅ በኩል አዲሱ አመራር አሁን ላለው ሁኔታ የጋራ ጥቅም ይዘን እንሂድ የሚል በመወሰኑ ምክንያት የመጣ ለውጥ ነው፡፡ በእኛ በኩል ያው ነን፡፡ የተለወጠ ፖሊሲ የለም፡፡ ነገር ግን እርምጃ ወደፊት ስለሄደ ደስተኞች ነን፡፡

አዲስ ዘመን፦ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን እና አሁን የሚቋቋመው የሶስትዮሽ የባለሙያዎች (አማካሪ) ኮሚቴ ልዩነታቸው ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- እዚህ ላይ ማየት ያለብን ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ያዘጋጁት ሁለት ምክረ ሃሳብ አለ፡፡ ሦስታችንም ለስራ እንጠቀመው ያልነውን፡፡ ይሄንን ነገር የሚመራው ማነው ከተባለ የሚመራው ከሦስቱ አገሮች አራት አራት ባጠቃላይ 12 ባለሙያዎች ያቋቋሙት የሦስትዮሽ ኮሚቴ ነው፡፡ ይሄ ኮሚቴ ምክረ ሃሳቡ የሚያጠናበትና ውጤቱን የመገምገም ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይሄን የሚያጠናው ማን ነው የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን የራሳቸውን አጥንተው የራሳቸውን ምክረ ሃሳብ አውጥተዋል፡፡ ይጠና ብለዋል፡፡ አሁን ልዩነት እንዳይመጣ የሚያስፈልገው ዓለም አቀፉ አጥኚ ቡድን ባስቀመጡት ምክረ ሃሳብ መሰረት ነው አማካሪው የሚሰራው፡፡

ዓለም አቀፍ አጥኚው ስራውን አልጨረሰም፡፡ ምክረ ሃሳብ (ሪከመንዴሽን) ሰጥቶ ነው የወጣው፡፡ ሁለት ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል፡፡ አንዱ ተፋሰሱ ላይ ያለው ሃይድሮሎጂ በሚገባ ይጠና የሚል ነወ፡፡ ሞዴሊንግ ይሰራ፡፡ ያ ሞዴሊንግ ባለሙያ የሚጠይቅ ነው፡፡ ማንም ተነስቶ የሚሰራው አይደለም፡፡ አማካሪው የተፈለገበት ዋናው ምክንያት በምክረ ሃሳቡ መሰረት ሞዴሉ መሰራት ስላለበት ሞዴል የሚሰራ አማካሪ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዓለም አቀፍ የባለሙያዎች አጥኚ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች አጥኚ ሞዴል አልሰራም፡፡ ስራው ደግሞ ሙያዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ሞዴል የሚሰራ አማካሪ መምጣት አለበት፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ነገሮች የተለያዩ ናቸው፡፡ እነሱ አማካሪውን አመኑ አላመኑ አይደለም ጥያቄው፡፡ አማካሪው ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሞዴሉን ሰርቶ ያመጣው ውጤት ይሄ ነው ብሎ ይሰጣል እንጂ ምክረ ሃሳብ አይሰጥም፡፡ ያ ውጤት ላይ ተመስርተው ደግሞ እነዚህ ባለሙያዎች ሱዳን በዚህ ትጎዳለች፣ ኢትዮጵያ በዚህ ትጎዳለች፣ ግብፅ በዚህ ትጎዳለች ስለዚህ ምን እናድርግ ብለው በአማካሪው ውጤት ላይ ተመስርተው ይሄ ቢሰራ ይሄ ጉዳት ይቀንሳል፣ ይሄ ይኖራል፣ ይሄ ደግሞ ትንሽ ጉዳት ቢቀርም ችግር የለውም እያለ አስራ ሁለት አባላት ያሉት ይወስናል፡፡ እነሱ ካልተስማሙ ደግሞ ሚኒስትሮች አሉ፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚሰጡ የውሃ ሚኒስትሮች ስላሉ እነርሱ ደግሞ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ አዲሱ ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ጊዜ የሚጠናቀቅበት መሆኑ ይታወ ቃል። እቅዱ ይፋ ሲሆን ብዙ ሰዎች «በጣም የተለጠጠ ነው ሊሳካ አይችልም» ይሉ ነበር። አሁን ያለው የእቅዱ አፈፃፀም ምን ይመስላል? በተለይ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የታየው አፈፃፀም እንዴት ይገለፃል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- በመጀመሪያ ደረጃ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስናዘጋጅ በጣም የተለጠጠ ዕቅድ ነበር ያዘጋጀነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተቺዎቻችን ጋር እንስማማለን፡፡ ነገር ግን ከተቺዎቻችን ጋር የማንስማማው አንድ ነገር ቢኖር «አይፈፀምም» በሚለው ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ይሄን ትልቅ ዕቅድ ስናዘጋጅ የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር አንድ መፈክር ይዘን ነበር፡፡ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል «ወገብ የሚያጎብጥ ዕቅድ ይዘን አንገታችንን ቀና እናድርጋለን» የሚል መልዕክት እያስተላለፍን ነው፡፡ ይሄን መርህ ይዘን ዕቅዳችንን ስናዘጋጅ በትልቁ አቅደን በትልቁ እንፈፅማለን ብለን ስንነሳ የተማመንነው በኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የተማመንነው የአገራችን ህዝብ በሙሉ አቅሙና ኃይሉ ከተነሳ ከዚህም በላይ መስራት ይችላል የሚል እምነት ይዘን ነው፡፡

ስለዚህ የዕቅዳችንን የእያንዳንዱን ዘርፍ እንኳን ከፋፍለን እንኳን ብናይ ግብርናችን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዋና ዋና ሰብሎች ከፍተኛ ውጤት አግኝተንባቸዋል፡፡ ይሄ የሆነበት ዋና ምክንያት አርሶ አደሮቻችን እና አርብቶ አደሮቻችን የሚፈለገውን የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስላደረጉ ነው፡፡ የመንግስት አመራሮችና ሙያተኞች እንደዚሁ አርሶ አደሩን ለመደገፍ ባደረጉት እንቅስቃሴ የመጣ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ዕቅዳችንን ስንይዝ ይህን ታሳቢ አድርገን ነበር፡፡ ሁለተኛ የአገልግሎትና የንግድ ዘርፍ በምናይበት ጊዜ በትልልቅ ከተሞቻችን ያለውን የንግድና የአገልግሎት እንቅስቃሴ ማንኛውም እንግዳ እንኳን መጥቶ ምን ያክል በኢኮኖሚ እየተንቀሳቀሰች እንዳለች ማየት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በንግዱም በአገልግሎቱም በተመሳሳይ መንገድ ይሄ ስራ እንደተሰራ ያሳያል፡፡ በተለይ በ2006 ዓ.ም ከፍተኛ የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ አገራችን የጎረፉበት ዓመት ነው፡፡ ይሄ በሚታይበት ጊዜ በተመሳሳይ መንገድ ጥሩ የሚባል ኢንቨስትመንት መሳብ የቻልንበት ዓመት ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ኢንቨስትመንት ሲባል እንግዲህ ተጀምሮ አልቆ ወዲያው ወደ ተግባር እስከሚገባ የተወሰኑ ዓመታትን የሚፈጅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር 2006 ዓ.ም መልካም ጅምር የታየበት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ብዙ ሰው የዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን ዕቅድ የሚያየው በሜጋ ፕሮጀክቶቻችን አማካኝነት ነው፡፡ በተለይ የግብርናው፣ የኢንዱስትሪው፣ የማኑፋክቸሪንጉ፣ የንግዱ እና የአገልግሎቱ ብዙ ሰው አያየውም፡፡ የኢኮኖሚ ዋና መሰረቶች እነዚህ ናቸው፡፡

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን አሁን እንገንባቸው እንጂ ወዲያው ለኢኮኖሚ ተግባሮቻችን ወዲያው የሚገቡ አይደሉም፡፡ እንደሚታወቀው የህዳሴ ግድብ ተገንብቶ አልቆ መጨረሻ ላይ ማምረት ሲጀምር ነው ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው፡፡ ነገር ግን ለሚቀጥለው ጊዜ ተስፋ የሚጥል ትልቅ ፕሮጀክት ተደርጎ ነው ያለው፡፡ ይሄ የህዳሴ ግድባችንም አሁን ባለው ደረጃ አርባ በመቶ ጭምር ለማሳካት ችለናል፡፡ ይሄ ማለት ግድቡን በዕቅዳችን መሰረት ለማሳካት ችለናል፡፡ መጀመሪያ ሲታቀድና 6000 ሜጋ ዋት የሚደርስ የኤሌክትሪከ ኃይል የማመንጨታችን በኢትዮጵያ አቅም ይሰራል ሲባል ብዙ ሰው አሹፎ ነበር፡፡ ይሄ በጭራሸ የሚታሰብ አይደለም፣ እነዚህ ሰዎች ይቀልዳሉ የሚል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ሁሉም ሰው ያንን አስተሳሰብ የቀየረ ይመስለኛል፡፡ አርባ በመቶ የሚሆነው የፕሮጀክቱ ዋና ስራ ማገባደዳችን በሚታይበት ጊዜ ትልቅ እርምጃ ወደፊት መሄዳችን የሚታይ ነው፡፡ ያኔ ሲቀርብ የተለጠጠ ነው አይፈፀምም ያሉ አካላትም ጭምር አላመኑም ነበር፡፡ አሁን ግን ተግባራዊ ሆኖ ሲታይ ይህ ነገር እውነት መሆኑን አረጋግጫለው ብለዋል፡፡

ይሄን ያስቻለው ማነው? ይሄን ያስቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ በጉዳዩ ላይ ከመንግስት ጋር አንድ ላይ ሆኖ በመረባረቡ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ እስከተረባረበ ድረሰ ትልልቅ ዕቅዶች ይሳካሉ የሚል እምነት እንድንይዝ መሰረተ ጥሎልናል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቶቻችንን በምናይበት ጊዜ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ልማትን በተመለከተ ብዙ ሰው እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ ያመነ አልነበረም፡፡ እነዚ ሰዎች ይቀልዳሉ የሚል የሚል ነበር፡፡ አሁን ግን በዓይኑ ሲያይ የውጭውም የአገሬውም ህዝብ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል። ነገር ግን ውጪ ሆነው የሚናገሩ ሰዎች ይሄን በማየት እውነትም ህዝቡ ከተነሳ፣ መንግስት አብሮ ከህዝቡ ጋር ከተንቀሳቀሰ ስራ የማይሰራበት ምክንያት የለም የሚለው ላይ መተማመን ተችሏል፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ በሚታይበት ጊዜ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተሳካ ሆኖ እየቀጠለ ነው። ህዝቡ የልማቱ ዋና መሰረት እና ተዋናይ እንዲሁም ዋነኛ ፈፃሚ መሆኑን እና ዋና ተጠቃሚ እርሱ ስለሆነ መንግስት ይሄን አመራር እየሰጠ ህዝቡ በፈፀማቸው ጉዳዮች እየተከናወነ ያለ ጉዳይ ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ በመላው ህዝብ ተሳትፎ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው። በዚህ ክንውን የዳያስፖራው ተሳትፎ በተጠበቀው መልኩ እንዲሆን ማድረግ ተችሏልን? በዚህ በኩል የተሰሩ ስራዎችና ያጋጠሙ ችግሮች ምንድን ናቸው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ በተመለከተ ትልቁን ድርሻ መጫወት ያለበት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ዋናው መሰረትም እርሱ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ አርሶ አደራችን፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ መከላከያ ሰራዊታችን፣ ፖሊስ ሰራዊታችን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ሁሉም ተረባርበውበታል፡፡ አሁን በደረስንበት ደረጃ ወደ ዘጠኝና አስር ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ባለሀብቶቻችንንም ጨምሮ የቦንድ ግዥ ቃል ተገብቷል። ከዚያ ውስጥ ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር አካባቢ ተሰብስቧል፡፡ የተቀረውም ይሰበሰባል የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡ ከ80 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ውስጥ ወደ አንድ ስምንተኛውን ከህዝቡ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ ይሄ ዋና መሰረት ነው፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ አለባቸው የሚል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ተሳትፎ ማየት ጀምረናል፡፡ ነገር ግን መሆን በሚገባው ደረጃ ነው ወይ ከተባለ ገና ነው፡፡ አሁን ጅምር ላይ ነው፡፡ ይሄን ጅምር የበለጠ በሚቀጥለው አዲስ ዓመት እና በሚቀጥሉት ጊዜያትም ግድቡ እስከሚያልቅ ድረስ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ ስራ ላይ የበለጠ እንዲሳተፉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ መረጃ ስለሚሰጣቸው በሚፈለገው ደረጃ ለመሳተፍ የሚያዳግ ታቸው ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን በውጭ እያጋጠመን ያለው ችግር ለምሳሌ አሜሪካ አገር ቦንድ መግዛት በአሜሪካ ሕግ አይፈቀድም፡፡ ስለዚህ ወይ በስጦታ መንገድ የሚሰጡ ከሆነ ወይም ደግሞ አገር ውስጥ መጥተው ገንዘባቸውን ልከው በአገር ውስጥ መግዛት ካልቻለ እዛው አሜሪካ ሆኖ ቦንድ መግዛት በሕጋቸው የተከለከለ ነው፡፡ ስለዚሀ እስካሁን ያደረግነው እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ያላሳየው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

አሜሪካ ያለው ሕግ እንደ ሌሎቹ አገሮች ሕግ አይደለም፡፡ በሕጉ ተጨማሪ ቦንድ የሚሸጥ ከሆነ ተጨማሪ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ እንድንከፍል ይጠይቃል፡፡ ይሄ ደግሞ ትልቅ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ማን ይከፍለዋል የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መልስ ያልተገኘበት ጉዳይ ነው፡፡ እና አሁን የምንመርጠው ምንድነው ገንዘባቸውን ወደዚህ ልከው ቦንዱን በአገር ውስጥ እንዲገዙት ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ የአሰራር እንቅፋቶች ስላሉ ነው የሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰው፡፡ አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ ዋናው ግን እርሱ ሳይሆነ የበለጠ አንቀሳቅሶ ወደ አገር ቤት ልከው እንዲገዙ ማድረግ ስራ የበለጠ መስራት አለብን የሚል ነገር ይዘን እየተንቀሳቀስን ያለንበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ የወጪ ንግዱ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ገቢ ቢገኝም ከእቅዱ አንፃር ዝቅተኛ መሆኑ ይገለፃል ይህ ለምን ሆነ? መንግስት ይህንን ለማስተካከል ምን እየሰራ ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የመጀመሪያው ጉዳይ የወጪ ንግዳችንን በተመለከተ ባለፈው ዓመትም በዘንድሮ ዓመትም ባቀድነው ልክ አላገኘንም፡፡ ያላገኘንበት የተለያዩ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ግን ወደ ውጭ የሚሄደውን ምርት በመጠን በከፍተኛ ደረጃ እንጨምራለን ባልነው ልክ አለመጨመራችን ነው፡፡ ምርቱ ተመርቶ እያለም ወደ ገበያ የማይመጣበትና ወደ ኮንትሮባንድና ወደተለያዩ መስኮች የመሄድ፣ በአገር ውስጥ የመሸጥ የመሳሰሉት ችግሮችም አጋጥመውናል፡፡ ለምሣሌ የኤክስፖርት ቡና በኮንትሮባንድ የመሄድና በአገር ውስጥ በሰፊው የመሸጥ ነገር አጋጥሞናል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ጫማና ጨርቃ ጨርቅም እንደዚሁ ወደ ውጭ መውጣት ሲገባው በአገር ውስጥ በስፋት የተሸጠበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይሄ በመጠን እናመጣዋለን ያልነውን ነገር አላሳካልንም፡፡

በተመሳሳይም እንደዚሁ የግብርና ምርቱ እራሱ ቡናን ጥራቱን በመንከባከብም ሆነ በተመሳሳይ መንገድ፤ ጨርቅንም በስፋት በማምረትና ወደ ልብሶች በመቀየር በገበያ ተወዳድረን መግባት ያለብን ይሆናል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ የተለያዩ ችግሮች ማነቆዎች መኖራቸውን አይተናል፡፡ ስለዚሀ በዚህ ምክንያት አልተሳካልንም፡፡ አሁን ዋና ጉዳይ የሚሆነው እነዚህን ማነቆዎች መፍታት ነው፡፡ ለምሣሌ የመብራት ማነቆ መፍታት፣ የጉምሩከና ተያያዥ ማነቆዎችን መፍታት፣ የትራንስፖርት ወጪ በመቀነስ ማነቆ መፍታት፣ የፋይናንስ አቅርቦት በማሻሻል ማነቆዎችን መፍታት የሚሉት አንድ በአንድ በዝርዝር ተለይተዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ 80 በመቶ የወጪ ንግድ ግኝታችን ከግብርና ስለሆነ የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ምርታማነቱ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ይጠይቀናል፡፡ ለምሣሌ የቡና ምርታማነትን መጨመር፣ ሰሊጥ በስፋት ማምረት፣ ጥራጥሬ በስፋት ማምረት እነዚህን የመሳሰሉት በእቅዳችን ውስጥ አካትተን ለሚቀጥለው ዓመት ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ካሻሻልን ዕቅዳችንን ተጠግተን ወይም ፈፅመን ለማሳካት ያስችለናል የሚል እምነት አለን፡፡ ከዚህ ተነስቶ ነው የወጪ ንግዳችን ችግር ያለበት ብለን የወሰድነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ የሀገራችን የእንስሳት ሀብት ህዝቡንና ሀገሪቱን በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ ያደርግ ዘንድ ምን እየተሰራ ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የእንስሳት ሀብት ልማታችን በምንመጣበት ጊዜ እንደሚታ ወቀው በአፍሪካ ትልቁ የእንስሳት ቀንድ ከብቶች የሚገኙባት አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቀንድ ከብቶች ለቁጥር ያሉን እንጂ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በሚያስችል ደረጃ ላይ ያሉ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ በበሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ በሽታን በመከላከል ጤናቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ይጠይቀናል፣ ዝርያቸውን ማሻሻል ይጠይቀናል፣ የሚፈለገውን ስጋና ወተት ማግኘት እንድንችል ዝርያቸውን ማሻሻል ይጠይቀናል፡፡ ለዚህም ዓምና የተጀመሩ በርካታ ስራዎች አሉ፡፡ ጥሩ ጥሩ ውጤቶችንም አግኝተናል፡፡ ነገር ግን አሁን የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ምን እናድርግ ብለን የእንስሳት ሀብት ልማት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በእንስሳት ሀብት ልማት ዙሪያ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ አለብን በሚል ለዚህ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ፣ ሙያተኞች እንደዚሁም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ተነሳሽነት እንዲኖረው በማድረግ የጀመርነው ስራ አለ፡፡ ይሄ ስራ ለእንስሳት ሀብት ልማታችን ማደግ፤ለሥጋና ለወተት ብቻ ሳይሆን ቆዳውም የቆዳ ፋብሪካችን የጥሬ እቃ እጥረት ስላጋጠመን ለዛም ጭምር የሚጠቅም ይሆናል፡፡

የእንስሳት ጤንነትን በመጠበቅ የመኖ አገልግሎታ ቸውንም በማሻሻል ጤናማ ሆነው ክብደታቸውም ለዓለም ገበያ በሚሆን መልኩ ከበሽታ ነፃ የሆኑ እንስሳት በማርባት መስራት አለብን፡፡ በዚህ ስራ የግል ባለሀብቶች ሚና በአገራችን አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የግል ባለሀብቱም በዚህ ስራ ውስጥ እንዲገቡ መሬት በማዘጋጀት በእስስሳት ማራባት እንዲሰማሩ በማድረግ ወደ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ዙሪያ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ አርሶ አደሩም ሜካናይዜሽን እንዲለምድ አድርገን በበሬ እጅ የሚጎተት እርሻ ደረጃ በደረጃ ማቆም አለብን፡፡ ምክንያቱም ለእርሻ የሚጎትት በሬ ለቆዳም ለስጋም አይሆንም፡፡ ፍኖተ ካርታው ይሄን የሚመልስ ስለሆነ በዚያ ላይ ተጠናክረን ከሰራን እናሻሽላለን የሚል እምነት አለን፡፡
********
ምንጭ፡ አዲስ ዘመን

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.