የሌለው መለስ vs. አርከበ – የኢንዱስትሪ ልማት ንድፈ-ሀሳብ ሙግት

(Name withheld upon request)

በሀገራችን ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከቀን ወደ ቀን በግልፅ በህወሓት አዛውንቶች እየተራመደ የሚስተዋለው የኒዮ-ሊበራል ዘውግ የሆነው የአመቻች መንግስት (facilitatory state) መርሆዎችን የተቀበለ የኢኮኖሚ ልማት በተለይ ደግሞ የኢንዱስትሪ ልማቱ አቅጣጫ፣ ላለፉት በርካታ ተከታታይ ዓመታት በሃገራችን ፈጣን እድገት በተግባር ሲያስመዘግብ ከነበረው የልማታዊ መንግስት (developmental state) ፓሊሲዎች ጋር ያለው መሠረታዊ የንድፈ-ሃሳብ ልዩነት ግር ብሎዎት ከሆነ ምን አልባት ይህ ፅሁፍ የተወሰነ ግንዛቤ ይሰጥዎት ይሆናል፡፡

ልዩነቶቹን በተቻለ ግልፅ ለማድረግ የኢንዱሰትሪ ልማት ቁልፍና መሠረታዊ ጉዳይ በሆነው በቴክኖሎጂ ልማት ዙሪያ በሁለቱ ማለትም የአመቻች መንግስትና የልማታዊ መንግሰታት አስተምህሮዎች መካከል ያለውን መሠረታዊ ንድፈ-ሃሳባዊ ልዩነቶችና የሚወዛገቡባቸውን ጉዳዮች ለማሳይት በዚህ ፅሁፍ ጥረት ተደጓል፡፡

በልማታዊ መንግስታትና በአመቻች መንግስታት ዕይታ ዕድገት ማለት በዋናነት የቴክኖሎጂ አቅሞች የማከማቸትና የማያቋርጥ የቴክኖሎጂ ለውጥ የማስመዝገብ ሂደት ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከሌሎች የልማት አቅሞች በተለየ መልኩ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ ወይም ኢኖቬሽን በከፍተኛ መጠን ባለማቋረጥ እያደገ የሚሄድ ጥቅም የሚያስገኝ (increasing returns to scale ያለው) በመሆኑ ነው፡፡

ቴክኖሎጂ በተፈጥሮው የህዝብ ንብረት/ሸቀጥ (public good) ባህሪ ያለው ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ፉክክር ወይም ባላንጣነት ውስጥ የማይከት (non-rivalrous) ነው፤ ማለትም በአንድ የኢኮኖሚ ተዋናይ ጥቅም ላይ መዋሉ ለሌላ የኢኮኖሚ ተዋናይ የሚሠጠውን ጥቅም እንዲያንስ የማያደርገውና የጥቅም መፃረርን የማይፈጥር ነው፡፡ በተጨማሪም ቴክኖሎጂ በተፈጥሮው ክልከላ ሊደረግት የማይቻል (non-excludable) ነው፡፡ ማለትም አንድ ቴክኖሎጂ ለገበያ ከዋለና የህዝብ ምህዳር ውስጥ ከገባ በኋላ ለአንዱ ፈቅዶ ሌላውን ግን ተጠቃሚ እንዳይሆን ሙሉ በሙሉ መከልከል የሚቻልበት ተፈጥሯዊ መንገድ የለም፡፡

ያለባለቤቱ ፈቃድ ባለቤትነት የሌላቸው ሰዎች እንዳይጠቀሙ ክልከላ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎች የሆኑት የፓተንትና የንብረት ባለቤትነት መብት ጥበቃን የመሠሉ የህግ ማዕቀፎች መፈጠራቸውና በስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉ በእርግጥም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሊገደብ የማይችል መሆኑን ከማረጋገጥ ባለፈ በመንግስት ጣልቃ ገብነትና ገበያዊ ያልሆኑ አሠራሮችን (non-market mechanisms) በመጠቀም የገበያ ጉድለትን መቅረፍ አስፈላጊ ለመሆኑ ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡

ይሁንና እነዚህን መሠሉ ክልከላዎች፣ የንብረት መብት ጥበቃዎችና ተግባራዊነታቸው ጠንካራ በሆነባቸው የዳበረ ገበያ ባለባቸው ሀገራት እንኳን ሣይቀር እንከን አልባ (leakage free) አይደሉም፡፡ በመሆኑም ቴክኖሎጂ አቅሙና ችሎታው ላለው ለሁሉም ተጠቃሚ በእኩል ደረጃ ተደራሽ ከመሆኑም ባሻገር አጠቃቀሙንም መገደብ የሚቻለው እጅግ በተወሰነ ደረጃ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የኒዮ-ክላሲካል ኅልዩት ጭምር የገበያ ጉድለት (market failure) ብሎ እውቅና ከሚሠጣቸው የሕዝብ ንብረት መደብ የሚፈረጅ ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ንብረት ባህርያት እንዳሏቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቴክኖሎጂ በገበያ በበቂ ሁኔታ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ህብረተሰብን የሚጠቅም ቀልጣፋ ውጤት እንዲገኝ ገበያዊ ያልሆነ ጣልቃ-ገብነት፣ በሌላ አባባል የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው፡፡

በኢኮኖሚ ሳይንስ መዋቅራዊ ኢኮኖሚክስ (new structural economics) ተብሎ የሚፈረጀው የአመቻች መንግስት እሳቤም ከላይ በተጠቀሰው አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህም እሳቤ የፈጠራና የአእምሮ ውጤቶችን ለመከላከል ሲባል ገበያዊ ያልሆኑ ጣልቃ-ገብነቶች የሆኑት የፓተንትና የንብረት መብት ጥበቃ ህግጋት እንዲኖሩ ከመወትወቱም ባሻገር በተመረጡ መስኮች ላይ ያተኮረ የሰው ሃይል ልማትና በመንግስት የሚደገፉ ጥናትና ምርምሮች ማድረግ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል፡፡

የቴክኖሎጂ የሕዝብ ንብረት ባህርያት ትንተናና ቴክኖሎጂን ከማልማት ረገድ የሰለጠነ የሰው ሃይል ወሳኝነት ትንነተናዎች እንደሚያሳዩት ገበያዊ ያልሆነ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ለቴክኖሎጂ ልማት በተለይም ለእርሱ አስፈላጊ የሆነውን ካፒታል ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁንና ይሄ እሳቤ ለቴክኖሎጂ እድገት ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች አስፈላጊና ተያያዥነት ያላቸውን የገበያ ጉድለቶችን እንዲሁም ተቋማዊና መሰረተ-ልማታዊ እንቅፋቶችን (institutional and infrastructural impediments) ይዘነጋል፡፡

የአመቻቹ መንግስት እሳቤ የቴክኖሎጂ አቅሞች ክምችትና የቴክኖሎጂ ለውጥ በርካታ የገበያ ጉድለቶች የተጋረጡበት እንደሆነ ቢቀበልም ቅሉ ገበያ እራሱ ቀልጣፋ የሃብት ድልድልን (efficient resources allocation) በማምጣት የገበያ ጉድለቱን መቅረፍ እንደሚችል ያምናል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ወደ ገበያው በስፋት የሚገባበትን መንገድ መንግስት ‹በማመቻቸት› ለአለም-ዓቀፍ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ ከተቻለ በtrickle down effect የአገር ውስጥ የማምረት ዓቅም እንደሚጎለብት ያምናል፡፡ እዚህ ጋር በሃገሪቷ በተለያዩ ቦታዎች በብድር በተገኘ ከፍተኛ ወጪ እና ሩጫ እየተሰሩ ያሉትን የኢንዱስትሪ መንደሮች ግንባታና ወደነዚህ መንደሮች የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲገቡ እየተደረገ ያለው ተማፅኖ መመልከት ይቻላል፡፡

በአንፃሩ ልማታዊ መንግስት እንደ አመቻቹ መንግስት የገበያ ጉድለቶች መኖራቸውን አፅኖኦት ሰጥቶ የሚስማማ ቢሆንም የንግድ ልውውጥ አካሄዶች (international trade patterns) የሚወሰኑት በአገር ውስጥ ባለው የገበያ መጠንና ስፋት እንዲሁም አገር ውስጥ ባለው የማምረት አቅም (production capacity) ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይሄም የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት የቴክኖሎጂ ተፈጥሯዊ ባህርያት ከውድድር ገበያ ጋር ያማይጣጣሙ በመሆናቸው ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ልማት ከውድድር ገበያ ጋር የሚጣጣም የነበረ ቢሆን እንኳን የኤክስፖርት ገበያ በአለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ ድንበር (global technological frontier) ላይ የመወዳደር እድል ሊፈጥር ቢችልም የገበያ ውድድሩ በጠንካራ ውድድር ገበያ መዋቅር የሚከናወን ሳይሆን በሞኖፖሊስቲክ እና ኦሊጎፖሊስቲክ የገበያ ማዕቀፍ የሚከናወን ነው፡፡ አመቻቹ መንግሰት ይህን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ላይ ብዙም እምነቱን አይጥልም፡፡

ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የሀገር ውስጡ አቅም አይደለም በቅርብ ዓመታት በረጅም ጊዜም ተጠናክሮና ጎልብቶ በግዙፍ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች (multi-national companies) በሞኖፖል ተይዞ ያለውን የአለም ገበያ ሰብሮ መግባት አይችልም ከሚል ነው፡፡ ለዚህም ነው እንደ H&M ለመሳሰሉ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ የውጭ አምራቾች በቴክስታዬል ኢንዱስትሪ መንደሮቻችን ያሉ ሼዶችን ተከራዩ ተብሎ ብዙ ፈንጠዝያ ሲደረግ የሚሰማው፡፡ ይሁንና የአለም አቀፍ ገበያን የተቆጣጠሩት እንደ H&M የመሰሉት ኩባንያዎች ግዝፈት ሆነ የአለም ገበያ መዋቅር ሞኖፖሊስቲክ እና ኦሊጎፖሊስቲክ መሆኑ የቴክኖሎጂያዊ ለውጥ ከውድድር ገበያ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡

የውድድር ገበያ እርስ በርስ ለመወዳደር የሚያስችላቸው በቂ መመሳሰል ያላቸው ተመሳሳይ ሸቀጦች (homogenous goods) ለገበያ ይቀርባሉ በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይሁንና ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ አምጪ ፈጠራዎች በመሰረቱ አዳዲስ ሀሳቦች እንደመሆናቸው መጠን አንዳቸው ካንዳቸው በምንም ሁኔታ ተመሳሳይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚሀም የልማታዊ መንግስት መሰረታዊ እሳቤ የውድድር ገበያ ባለበት ቦታ ሁሉ የቴክኖሎጂ እድገት አይታሰብም፣ ቴክኖሎጂያዊ እድገት ባለበት ሁሉ የውድድር ገበያ የለም የሚል ነው፡፡

ስለሆነም የቴክኖሎጂ ዕድገት ማለት ኪራይ የማቅረብ ሂደት ነው፡፡ ኪራይ ከአንድ ሃብት ኦፖርቹኒቲ ኮስት ወይም ኢኮኖሚያዊ ዋጋ በላይ የሆነ ክፍያ ነው፡፡ የልማታዊ መንግስትና የአመቻች መንግስታት እሳቤዎች እንደሚጋሩት ኪራይ የኢኖቬሽን ውጤት ነው፡፡ ይህን መሰሉን ኪራይ አንተርፕሬነሮች ምርት ወይም አገልግሎታቸውን በርካሽ ዋጋ ወይም በተሸለ ጥራት የሚመረትበት ዘዴ በመፍጠር ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም መጀመሪያ ላይ ከማርጂናል ኮስት በላይና የላቀ ትርፍ ያገኛሉ፡፡

የአመቻቹ መንግስት ኪራይ አንዴ ከተፈጠረ ኪራዩ በመንግስት ድጋፍ በሚደረግለት የውድድር ገበያ የሚከፋፈል ነው ይላል፡፡ ይህም የሚሆው አንዴ ይህ ኪራይ እንዳለ ከታወቀ በኋላ ሌሎችም የቀደምቶቹን ፈለግ በመከተል በተመሣሣይ ኪራዩን ለማግኘት መጣራቸው ስለማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጥሮ የነበረው ኪራይ በውድድር ሂደት እየጠፋ ይሄዳል፡፡ ይህ መሠሉ ሂደት ደግሞ ደጋግሞ የሚከሰት ቀልጣፋ የሃብት ድልድልን የሚፈጥርና ፈጣን እድገትን የሚያመጣ ነው፡፡

ይህን መሠሉ ኪራይ በኒዮሊበራል የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፅሁፎች ኪራይ ሰብሳቢነት ተብሎ ከሚጠራው በተቃራኒ “ኪራይ ፈጣሪነት” (rent creation) በመባል ይታወቃል፡፡ ኪራይ ፈጣሪነት ሁለት መለያ መገለጫዎች አሉት፡፡ እነሱም በውድድር ሂደት ተፈጥሮ የነበረው ኪራይ እየጠፋ የሚሄድ መሆኑ እና ኪራዩ አዎንታዊም አሉታዊም (positive or negative) ሊሆን መቻሉ – ማለትም የኪራይ መፍጠር ሂደቱ ከኦፖርቹኒቲ ኮስት በላይ እና የላቀ ክፍያ ሊያስገኝ የሚችለውን ያህል ከኦፖርቹኒቲ ኮስት ያነሰ ክፍያ ሊያስገኝ የሚችል መሆኑ ናቸው፡፡

በዚህም ሃብት (ካፒታል) አዎንታዊ ኪራይ ወዳለባቸው መስኮች ሲፈስ በአንፃሩ ደግሞ አሉታዊ ኪራይ ካለባቸው መስኮች በመሸሽ ቀልጣፋ የሃብት ድልድል እንዲኖር ከማድረጉም ባሻገር የተፈጠረ ኪራይ እንዲጠፋና አዲስ እንዲፈጠር የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም ኪራይ ፈጣራ የገበያ ውድድር ሂደት አካልና የፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማዕከል ነው የሚል እሳቤ አለ፡፡

የልማታዊ መንግስት በሌላ ወገን ገበያ በራሱ ኢኖቬሽን እንዲስፋፋ የሚያበረታታ ኪራይን ሊፈጥር የማይችል በመሆኑ አፈፃፀምና ውጤትን መሰረት ያደረገ (performance based) በመንግስት የሚከናወን የኪራይ ምደባ (rent allocation) አካሄድ ብቸኛው የኢኖቬሽን ሆነ የእድገት ማምጫ መንገድ ነው ይላል፡፡ በዚህ ምክንያት መንግስት እንዲህ ዓይነት ሚና መጫወት ካለበት ደግሞ የመንግስትየው ባሕሪና የመንግስት አካላትና በውስጥ ያሉ ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦች መሠረታዊ ፍላጎትና ተነሳሽነት ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል፡፡

እርግጥ ነው በሃገራችን ለዘመናት በስፋት ተንሰራፍቶ ያለው በመንግስት አካላት የሚፈፀም ሙስናና የግል ጥቅምን ከህብረተሰብ ጥቅም አስቀድሞ የመንቀሳቀስ ሁኔታ መንግስት ይህንን ሚና በብቃትና በታማኝነት መጫወት ይችላል ተብሎ ማሰብ አያስችልም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሁሌም መጥፎ አማራጮች መካከል እንዲመርጡ የሚያስደገድድ ውስጥ ናቸው፡፡ ስር የሠደደ የገበያ ጉድለቶች ብቻ ሣይሆኑ ስር የሰደደ መንግስታዊ ውድቀት/ድክመት ፊታቸው እንደተጋረጠ ነው፡፡

ይሁንና የገበያ ጉድለት ስር የሠደደ ይሁን አይሁን ሊቀረፍ የሚችለው በመንግሰት ብቻ ነው፡፡ ያለፈው ክፍለ-ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የምስራቅ እስያ ሃገራት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ብቸኛው የገበያ ጉድለት ሆነ መንግስታዊ ውድቀትን ሊታደግ የሚችለው ተልዕኮ-ተኮር የሆነ አውራ ፓርቲ (mission oriented dominant party) ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው በልማታዊነትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለሞች የፌድራል ስርዓት መዋቅር ከፈጠራቸው በርካታ የስልጣን ማዕከላት (multiple centers of power) መካከል ከሚኖር ውድድር ውጪ ለፖለቲካዊ ውድድር ብዙም ደንታ የሌለው፡፡

ከላይ መረዳት እንደሚቻለው የአመቻችና የልማታዊ መንግስታት ልማት ለማምጣት የተለያዩ ተቋማዊ መሳሪያዎችን እንደሚጠቀሙ ያሳያል፡፡ የአመቻች መንግስታት በነፃ ገበያ ያላቸው እምነት ባመዛኙ ጠንካራ የንብረት መብት ጥበቃ ህግጋት ለኢኮኖሚ ልማት ባላቸው ፋይዳ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ በአንፃሩ በልማታዊ መንግስት የንብረት ባለቤትነት መብት በእድገት ላይ ያለው ተጽእኖ ከጊዜ ጊዜና ከቴክኖሎጂ ቴክኖሎጂ ሊለያይ የሚችልና የሚገባው ነው የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ከአንድ የሆነ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ የንብረት መብት ጥበቃዎች ከሕብረተሰብ ጥቅም አንፃር መልካም ወይም ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው እያንዳንዱ በተናጥል ፍተሻና የተግባር ሙከራ ምላሽ የሚሻ ጥያቄ (empirical question) ነው ፡፡

(ይቀጥላል)

***********

Guest Author

more recommended stories