‘ጄኔራል ብርሃኑ ቀጣዩ ኤታማጆር ሹም እንዲሆን ነው የምመርጠው’ – ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ

(ሪፖርተር ጋዜጣ)

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በሽግግሩ ጊዜና ከሽግግሩ በኋላም በአጠቃላይ ለሰባት ዓመታት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም የነበሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ በወቅታዊ ጉዳዮችና በቅርቡ ሹመት ስላገኙ ጄኔራሎችና የጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም የሥልጣን ቆይታን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከዮሐንስ አንበርብር ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ የነበረውን ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ በተመለከተ በሚዲያዎች ባቀረቡት ጽሑፍ ሦስት ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ቢሆኖች አቅርበው ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ አገሪቱን የሚመራው ኢሕአዴግ መሠረታዊ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ ትንንሽ ጥገናዎችን እያደረገ አገሪቱ በግጭትና በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ልትቆይ ትችላለች በማለት ያቀረቡት ነጥብ ከሌሎቹ ሁለቱ ቢሆኖች የመሆን ዕድል እንዳለው ገልጸው ነበር፡፡ እንዳሉትም አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ በወቅቱ ይህንን ሲገልጹ ከነበረው የቀውሱ መነሻ የተለየ ለምሳሌ በገዥው ፓርቲ ውስጥ አለመተማመንና ፉክክር ተፈጥሯል፡፡ ሌሎች ክስተቶችም ይታያሉ፡፡ ይህንን መሠረት አድርገው የፖለቲካ ቀውሱ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- የአገሪቱ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ስለተሰማኝ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ያለውን ሁኔታና የመፍትሔ አማራጮችን ለመጠቆም አንድ ጽሑፍ አውጥቼ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሦስት ‘ሴናሪዮስ’ (ቢሆኖችን) አስቀምጬ ነበር፡፡ አንደኛው ሊሆን ይችላል ያልኩት ነጥብ የፖለቲካ ጫናው በጣም በርትቶ የውጭ ኃይልም ይጨመርበትና መንግሥት ከሚችለው በላይ ሆኖ፣ መንግሥት እስከማፍረስ ሊሄድ ይችላል የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን የመሆን ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው ብዬ ነበር፡፡ ሁለተኛው ሊሆን ይችላል ያለኩት የፖለቲካ ቀውሱን መንግሥትና ገዥው ፓርቲ አውቆ በራሴ እፈታለሁ ብሎ ጊዜ የጣላቸውን አንዳንድ ኃላፊዎች በማንሳትና አንዳንድ ዕርምጃዎችን በመውሰድ፣ አንዳንድ ችግሮችን በግልጽ በማመንና ለመፍታት በመምከር ቀውሱ መሠረታዊ በሆነ መንገድ ሳይፈታ ሊቀጥል ይችላል የሚል ነበር፡፡ ይህ ነጥብ የመሆን ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ነበር የገለጽኩት፡፡ ሦስተኛው ሊሆን ይችላል ያልኩት ችግሩን በደንብ ተገንዝቦ መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል የሥልጣን ሽግግር ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ ነበር፡፡ ይህ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው የሚል አመለካከቴን ነበር ያቀረብኩት፡፡ እየሆነ ያለው ሁለተኛው ቢሆን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ችግሩን ራሴ እፈታዋለሁ ብሎ አንዳንድ ሰዎችን እያባረረና ችግሮችን እያመነ ለመፍታት የሚያስችል አካሄድ ነው እየሞከረ ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር መሄድ የሚችለውን ያህል ሄዷል፡፡ ቀላል የማይባሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ከሥልጣን አባሯል፡፡

የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደነበሩበት አምኗል፡፡ አሁንም ገና በጥልቅ ተሃድሶ ላይ ነን እያለ እየፈታ ይሄዳል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደርና ከሕገ መንግሥቱ ወጣ ያለ ተቃዋሚዎችን ፓርላማ ውስጥ ልትገቡ የምትችሉበትን ዕድል አመቻቻለሁ እስከማለት ድረስ ሄዷል፡፡ እና ራሱ ኢሕአዴግ በሚቆጣጠረው መንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ የቻለውን ያህል መንገድ ገፍቷል፡፡ በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል ያለው እኔ ከምገምተው በላይ በውስጥ ትልቅ አለመግባባትና መጠራጠር እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይህ ለእኔ ድርጅቱ በውስጡ ችግሮችን በራሱ ለመፍታት የሚችልበት አቅም እየቀነሰ መምጣቱን ነው የሚያሳየኝ፡፡ አሁንም በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጥኩት ቢሆን ነው እየሆነ ያለው፡፡ ችግሮችን ለመፍታት የሚችልበት አቅም እየቀነሰ መምጣቱን ነው የሚያሳየኝ፡፡ ችግሮችን ለመፍታት እየከበደውና እያቃተው መሆኑን ነው የምመለከተው፡፡ አሁን በተጨባጭ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ተቃውሞና ወንጀልን በትክክል መለየት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ የመንግሥትና የግል ንብረት እየወደመ ነው ያለው፡፡ ሰው በዘሩ ምክንያት እየተጠቃ ነው ያለው፡፡ ይህንን ማቆም ፖለቲካዊ አንድምታ አለው ተብሎ የሚፈራበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ተቀባይነት ያለው ተቃውሞ እንደፈለገው እንዲሆን ሰፊ ዕድል ስላልተሰጠው፣ ፖለቲካዊ ቅሬታዎችና በተለያየ ምክንያት የሚነሱ የወንጀል እንቅስቃሴዎች አብረው እየተጋመዱ እየሄዱ ነው፡፡

ወንጀል የመሥራቱ ሒደት ቆቦ ላይ፣ መርሳ ላይ፣ ወልድያ ላይ፣ ጎንደር ላይ የሰው ሕይወት በማጥፋትና ንብረት በማቃጠል ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ድንበር ላይ ሰው በመግደል ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሞስነዋል፣ የመንግሥት ሀብት ዘርፈዋል እየተባለ ማን እንደዘራውና የት እንደገባ ሳይታወቅ ተደብቆ የሚቀመጥበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ደርሰናል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የሚያሳዩት አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት በኢሕአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ታጥሮ ለመፍታት እንደማይቻልና የበለጠ እንደሚያባብሰው ነው የሚታየኝ፡፡ ሌላ መፍትሔ ካልተቀመጠለት አገሪቱ መውጣት ወደማትችለው ማጥ ውስጥ ትገባለች፡፡ ወደዚያም እየሄድን ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ወጣ ብለን ካየነው ደግሞ ይህንን ሁኔታ ወደ ዕድል መቀየር የምንችል ይመስለኛል፡፡ በዚህም በጣም መሠረታዊ የሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማምጣት የምንችልበት መሠረት መጥቷል የሚል አመለካከት ነው ያለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የፖለቲካ ተቃውሞ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ነው? የመንግሥት ለውጥ ጥያቄ ነው? ወይስ ምንድነው? ለእርስዎ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- ብዙ የተደበላለቁ ነገሮች ነው የሚታዩት፡፡ ኢሕአዴግ የያዘው አንድ አማራጭ አለ፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ በተሟላ መልኩ ተደራጅቶ እንዲቀርብ ዕድል አላገኘም፡፡ በአንድ በኩል መንግሥትና ኢሕአዴግ እነዚህን ተቃዋሚዎች ሆነ ብሎ በከፍተኛ ደረጃ ሲያጠቃቸው ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ራሳቸው ተደራጅተው፣ ሐሳባቸውን በሚገባ አደራጅተው ወደ ሕዝብ የቀረቡበት አጋጣሚ የለም፡፡ በተጨማሪም በአማራጭነት የሚነሱት ሐሳቦች ድብልቅልቅ ያሉ ናቸው፡፡ አንዳንዱ የሊበራል ዴሞክራሲ አቀንቃኝ ነው፡፡ ራሱን የቻለ አማራጭ ሆኖም ለሕዝብ ሊቀርብ ይችላል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀሩም ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ከሚሆን ጂኦግራፊያዊ ፌዴራሊዝም ቢሆን ይሻላል የሚል አማራጭ አላቸው፡፡ ማዕከላዊ ሥርዓት መፈጠር አለበት የሚልም አለ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሐሳቦችን በፓርቲ ደረጃ መልክ ይዘው አልቀረቡም፡፡ ሐሳቦቹ ይነሳሉ ነገር ግን ጠንካራ ሆነው ኢሕአዴግን ለመወዳደር የቀረቡበት ሁኔታ የለም፡፡ በአንድ በኩል የራሳቸው ችግር ነው፣ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ የፈጠረው ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ መኖራቸው ፀጋ ነው፡፡ ተደራጅተው፣ የፖለቲካ ኃይል ሆነው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማኅበረሰቡ የፈለገውን እንዲመርጥ ቢቻል ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ የአንድ ብሔር የበላይነት አለ የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ ይህ ትልቅ መሠረት አለው የለውም የሚለው ሌላ ነገር ቢሆንም፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ሳቢያ የእርስ በርስ ጥላቻው እየበረታ ነው የሚገኘው፡፡ አንዳንዱ የእርስ በርስ ጥላቻ በወንጀል መልክም ጭምር የሚገለጽበት ደረጃ ደርሷል፡፡ የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ ንብረት ማውደም፣ ለረዥም ዘመናት አብረው የኖሩ ማኅበረሰቦች አብረው መኖር የማይችሉበት ደረጃ ተፈጥሯል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ይኼ መንግሥት ቢቀየርስ እንደ አንድ አገርና ሕዝብ በሰላም የሚኖርበት ሁኔታ ይኖራል ወይ? ትልቅ የሚያሳስበኝ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ሕዝብ የሚፈልገውን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚመርጥበትና ወደ ሥልጣን የሚያመጣበት መንገድ አልተስተካከለም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ይህንን የሚያባብሱ ሌሎች የተሳሳቱ አመለካከቶች ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መነሻ ሆነዋል፡፡ ይህ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ማጥ ውስጥ ነው የሚከተን፡፡ እንደ አገር መቀጠላችንን ጥያቄ ውስጥ እየከተተ ነው የሚሄደው፡፡

ሪፖርተር፡- የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች አሁን የውስጥ ፉክክር ውስጥ ያሉ ነው የሚመስለው፡፡ ይህንን እንደ ዕድል ነው የሚያዩት ወይስ ሥጋት አለው?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- እኔ በፓርቲዎች ውስጥ ስላለው መተረማመስ የውስጥ ሰው ስላልሆንኩ ብዙ አላውቅም፡፡ እነሱ ከሚያወጡት መግለጫ ነው የምረዳው፡፡ አብረው ለመሥራት እያስቸገራቸው እንደሆነ ምልክት ይሰጣል፡፡ ይህ ከሆነ ምን እያደረጉ ነው የሚል ጥያቄ ይፈጥራል፡፡፡ ጥያቄ እንዳነሳ ነው የሚያደርገኝ እንጂ እንደ ዕድልም እንደ ሥጋትም ለማየት ያስቸግረኛል፡፡ ኢሕአዴግ የያዘው የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ፕሮግራም እዚህ አገር ሊቀርብ እንደሚችል እገምታለሁ፣ እስማማለሁ፡፡ ከዚህ ተፃራሪ የሆነ የተደራጀ የፖለቲካ ፕሮግራም እንዲመጣም በፅኑ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ከውጭ ነው የሚመጣው? ወይስ አሁን በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ተነጣጥለው ነው? ወይስ እንዴት ነው የሚመጣው? የሚለውን አላውቅም፡፡ ለእኔ ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ይስማማሉ አይስማሙም ከሚለው ይልቅ፣ በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ላለው የፖለቲካ ቀውስ ከኢሕአዴግ ውጭ ያሉትንም የፖለቲካ ኃይሎች አሳትፎ ለረዥም ጊዜ የሚወስደን የፖለቲካ መሠረት የምናነጥፍበት ሁኔታ ቢመቻች ነው ችግሩ የሚፈታው እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድነው መሠረት ሊሆን ይችላል የሚሉት የመፍትሔ ሐሳብ?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- ትልቅ መሠረት ሊሆን ይችላል ብዬ ያነሳሁት የመፍትሔ ሐሳብ የተወሰነ ማጭበርበር ፈጽሞም ቢሆን ኢሕአዴግ ምርጫ አሸንፎ እየመራ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የተከተለ የሥርዓት ለውጥ እንዲኖር ለማድረግ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ የአገር ደኅንነትና ሕግ እያስከበረ፣ ታክስ እየሰበሰበ ይቀጥል፡፡ ጎን ለጎን ግን ኢሕአዴግ እንደ ማንኛውም ፓርቲ የሚሳተፍበት ገለልተኛ የሆነ ኮሚሽን መቋቋም አለበት፡፡ ይህ ኮሚሽን ሊቋቋም የሚገባው በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ሥር ነው፡፡ ምክንያቱም የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ገለልተኛ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፡፡ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንደ ርዕሰ ብሔርነት ይህንን የፖለቲካ ቀውስ የመፍታት የሞራልም የፖለቲካ ግዴታም አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሁሉም ያለ ኢሕአዴግ ፈቃድና ዕውቅና በዚህ ኮሚሽን ውስጥ የመሳተፍ መብት ኖሯቸው፣ የሚቀጥለው ምርጫን ለማስተካከል ቢሠሩ ነው የሚሻለው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ይህንን ሐሳብ ባቀረብኩበት ወቅት አንዳንድ ወገኖች የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ነው እያለ ያለው በሚል ተርጉመውታል፡፡ በተለይ ከመንግሥት ወገን ያሉ፡፡ ይህንን ልል የምችልበት መነሻ የለኝም፣ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍም የለውም፡፡ በአገሪቱ የሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ በመሆኑ፣ ይህ ሥልጣን የሚያዝበት መንገድ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ሲለቀቅም እንደዚያው ማድረግ የምንችልበትን ዕድል እየሰጠን ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን በፓርላማ ነው መቋቋም ያለበት፡፡ ኢሕአዴግ ወዶ የሚያቋቁመው ሳይሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ የፈጠረው ሆኖ ነው መቋቋም ያለበት፡፡ ነፃ ሆኖ የሚሠራ፣ ዋና ዓላማውም ከሁለት ዓመት በኋላ የሚደረገው ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ማስተካከል መሆን አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ መንግሥት እንደ ጀመረው የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት አለበት፣ በውጭ ላሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጥሪ ማድረግና እንደ ልባቸው በኢትዮጵያ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ፣ በአገር ውስጥ ያሉትንም እንደዚሁ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አለበት፡፡

ውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ቤት ማቃጠል፣ ኢንዲስትሪ ማፍረስ እስካቆሙ ድረስ ያለምንም ቅድመ ሁኔት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪ ማድረግ አለበት፣ መፈቀድ አለበት፡፡ ኢሕአዴግም ሥልጣንን በመጠቀም፣ በገንዘብ በመደለል ወይም ኃይል በመጠቀም የምርጫ ውድድር ውስጥ መሳተፍ ሳይሆን ያለበት ማሸነፍ የሚችል የፖለቲካ ሐሳብ አለኝ ብሎ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ መሄድ አለብን፡፡ ሁለተኛው መንገድ መሆን አለበት የምለውና ከዚሁ ኮሚሽን ጋር አብሮ መከናወን ያለበት አገራዊ መግባባት መፍጠር ላይ ነው፡፡ በድንበር አካበቢ በአማራና በትግሬ መካከል ያለው መናቆር፣ መሀል አገር በብሔሮች መካከል ያለው ያለመተማመን መንፈስ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ ማንነትን መሠረት ያደረገ መናቆር በአጠቃላይ የሚጠፋበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ግን መሠራት አለበት፡፡ ምክንያቱም ይህ መንግሥት በኃይል ከወረዳ የሚመጣው ጎርፍ የት ላይ እንደሚያቆም አይታወቅም፡፡ እስካሁን ያጠራቀምናቸውን ድሎች ብቻ አይደለም የሚጠርገው፣ የማንነታችንና የአንድነታችን ገመድ ሁሉ ነው የሚበጣጠስው፡፡ ይህ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ነው መደረግ ያለበት፡፡

ኢትዮጵያ በምትገኝበት አካባቢ እያንጃበቡ ያሉ የደኅንነት ክስተቶች አሉ፡፡ ይህንን መቋቋም የምንችለው አንድነታችንን በማጠናከር ነው፡፡ አንድነታችን ደግሞ የሚጠናከረው አንደኛ ሕዝብ የመረጠውና የሚያምነው፣ ሲሸነፍም በትክክለኛ መንገድ ነው የተሸነፍኩት ብሎ ማመን የሚቻልበት ሥልጣን አያያዝ ሥርዓት ሲፈጠር ነው፡፡ አሁን ሥልጣል ላይ ያለው ፓርቲ እየለካ በሚሰጠው መንገድ ብቻ አይደለም መሠራት ያለበት፡፡ ሕዝብ በሚመስለውና በአንድ ወቅት ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣም ሥልጣን አያያዝ ሥርዓት መቀረፅ አለበት፡፡ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ነው ማንኛውም ኃይል ወደ ፖለቲካ ሥልጣን በሚመጣበት ወቅት አገር ልማቷ የሚቀጥለውና እንደተረጋጋች ልትቀጥል የምትችለው፡፡ የኮሚሽኑ መቋቋም አሁን ያለውን የፖለቲካ ቀውስም ያስተነፍሳል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሰው ቀልቡን ወደዚህ ኮሚሽን ያደርጋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ በምርጫ የሚፈልገውን መምረጥ እንደሚችል ይተማመናል፡፡ ስለዚህ ቤት ማቃጠል፣ ሰው መግደልና ኢንዱስትሪ ማፍረስ ይቆማል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ሒደት በራሱ ወንጀልንና ትክክለኛ የፖለቲካ ጥያቄን ይለያል ብዬ አስባለሁ፡፡ በወንጀል መንገድ እሄዳለሁ በሚሉት ላይ የፀጥታ ኃይሉ ያለምንም ማቅማማት ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት የቆየ ሕዝብ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት መታገስ አይችልም ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ኮሚሽን እንዳሉት ቢቋቋም ምን ያህል ተዓማኒ ሊሆን ይችላል? ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን ለራሱ ዓላማ ይጠቀምባቸዋል እንደሚባለው ሊጠቀምበት አለመቻሉን በምን ማስተማመን ይቻላል?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- ይህንን ጥያቄ በጥያቄ ነው የምመልሰው፡፡ ታዲያ ምን አማራጭ አለን? በየመንደሩ ሠልፍ በማድረግ፣ ንብረት በማውደም መንግሥት በኃይል እንዲወርድ ማድረግ ነው ሌላው አማራጭ? ይህ ደግሞ ልክ እኛ በረሃ ገብተን ታግለን አሸንፈን ወጥተን ባለውለታ እንደሆንነው ከተማ ውስጥ ታግዬ ሥልጣን ያመጣሁ ነኝ የሚል ባለውለታ ነው የሚያመጣብን፡፡ ይህንን ባለውለታ በምን መንገድ ነው በኋላ ማውረድ የምንችለው? እኔ ያቀረብኩት አማራጭ ሐሳብ ምንም ጉድለት የለውም ብዬ አልናገርም፡፡ ከሌላው አማራጭ የተሻለ ነው ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ አሁን የደረስንበት ደረጃ የደረስነው እኮ በሕዝብ ትግል ነው፡፡ ሕዝብ ስለታገለ ነው የመጣው፡፡ እንዴት ነው የሚጠብቀው ከተባለም እየታገለ ነው የሚጠብቀው፡፡ ኢሕአዴግ ቆንጥጬ አስተካክላለሁ የሚል ከሆነ ከነበረው ሁኔታ ነው የሚሻለው፡፡ በሌላ በኩል በፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሥር ነው የሚቋቋመው፡፡ በነገራችን ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጠንካራ አቋም ከያዙ በኋላ ነው፣ ይህ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖረው ተደርጎ የነበረው፡፡ ተሽመደመደ እንጂ የአገሪቱ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንደዚህ ዓይነት ፖለቲካዊ ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት ሚና ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ አንድ ፓርቲ በታመሰ ቁጥር አገር መታመስ የለበትም፡፡ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከፖለቲካ ነፃ በመሆኑ በዚህ ወቅት አገርን የሚያሠጋ ችግር አይኖርም ነበር፣ ባይሽመደመድ ኖሮ ለማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ የተሻለ አማራጭ አሊያም አለ ከተባለ ኃይል ብቻ ነው የሚመስለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ሐሳብ ለመንግሥት አቅርበው ተወያይተውበታል? ካልሆነስ ይህንን ሐሳብ ወደ መንግሥት ማን ይውሰደው?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- በጽሑፍ በሚዲያዎች ላይ ከማቅረብ ውጪ ያደረግኩት እንቅስቃሴ የለም፡፡ ጽሑፉን ባቀረብኩበት ወቅት የሕዝብ ለሕዝብ መናቆር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ምልክቶቹ ይታዩ ነበር፡፡ በተለይ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለው ጥላቻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከትግራይ የወጡ ሌቦች ካሉ እነሱ ይቀጡ፡፡ ከጥቂት ባለሥልጣናት ጋር ተጣብቀው የሚሰርቁ የሚገባቸውን ያግኙ፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላው ሕዝብ እንደ ጠላት የሚታይበት ሁኔታ በፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡ የዘር ጥላቻው በትግራይ ላይ በረታ እንጂ በሌሎች ብሔሮችም ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ለማለት የፈለግኩት ምንድነው? ለሕዝብ ይፋ የወጣ ሐሳብ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በጠማማ መንገድ ያቀረብኩትን ሐሳብ ተርጉመው የሽግግር መንግሥት ይመሥረት እያልክ ነው ያለኸው ይሉኛል፡፡ እኔ እንደዚያ አላልኩም፡፡ ትክክኛ ነው ብዬ ካመንኩበት ለማለት የምፈራው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ሐሳብ ነው፡፡ ሕግን መሠረት አድርገን ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ አንዳንድ የሕወሓት አመራሮች ደግሞ ይኼ መጀመርያውንም ከመንግሥት ተጣልቶ ነው የወጣው፣ በጎ ነገር አያመጣም ብለው ከመጀመርያው ያጣምሙታል፡፡ አሁን ሕወሓትን ጠፍረው ይዘው የነበሩ የድርጅቱ አመራሮች ተባረዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ምን ይመጣል? ሐሰቡን ይቀበሉታል ወይ? የሚለውን እናያለን፡፡ እንደ ዜጋ የሚሰማኝን ገልጫለሁ፡፡ ከዚህ በዘለለ የማደርገው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ በርካታ ምሁራን ስላሉ እነሱንም መስማት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው ያነሱት ፀረ ትግራይ ሕዝብ አመለካከት እያደገ ለመምጣቱ ዋናው ምክንያት የአንድ ብሔር የበላይነት አለ የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ ሆኖ፣ በአንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ይህንን ስሜት የማቀጣጠል ጥረትስ የለም? የዚህ ሥርዓት ጠባቂ ነኝ የሚል አመለካከት ሌላው መነሻ አይሆንም?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- የትግራይ ሕዝብ ይህንን ሥርዓት ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ ጠባቂውም እኔ ነኝ የሚል አመለካከት የለውም አልልም፡፡ ይህ አስተያየት በስፋት ይንፀባረቃል፡፡ አንዳንዱ ከዚህ ይነሳና ከባለሥልጣናት ጋር ተጣብቆ የኢኮኖሚ ጥቅም ያደርገዋል፡፡ አሁን የመጣው የሕወሓት አመራር እንደገለጸውም በየመጠጥ ቤቱ ለጉራ እየተጠቀሙበት የትግራይን ሕዝብ ስም የሚያጎድፉ አሉ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በቅንነት ስለሚያምንበት ዋጋ የከፈልኩበት ሥርዓት ነው የሚል አመለካከት አለው፡፡ ወግ ያጣው አስተሳሰብ መስተካከል አለበት፡፡ ከባለሥልጣን ተጣብቆ የሚመጠምጠው መቀጣት አለበት፡፡ ከዚህ በመለስ ያለው የትግራይ ተወላጅ አመለካከት ግን መከበር አለበት፡፡ ሥርዓቱን ለመጠበቅ መከፈል ያለበትን እንከፍላለን ማለት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ መስተካከል ያለበት ነገር ግን መስተካከል አለበት፡፡ ይህንን መንግሥት እንደ መንግሥት ለማቆም የትግራይ ሕዝብ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ይህ ይታወቃል ብቻውን ግን አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ብቻ የሥርዓቱ ጠበቂ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት የለም፡፡ የኦሮሞ ወጣት የሌላውን አልነካም፣ ነገር ግን ኦሮሚያ ውስጥ ፖለቲካዊ ሚና ሊኖረኝ ይገባል በማለቱ የትግራይ ሕዝብ ሊደሰት ነው የሚገባው፡፡ እኔ ያልኩትን ተቀበሉ እስካልተባለ ድረስ ችግር ያለው አልመሰለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የተደረገው የጄኔራሎች ሹመት ምክንያቱ ብሔር ማመጣጠን ነው ብለው ይገምታሉ?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- ትክክለኛ ምክንያቱን ማወቅ አልችልም፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ሹመት በአንድ ጊዜ ሲመጣ ፖለቲካዊ ግፊትና በሌላ በኩል ፖለቲካዊ አንድምታም አለው፡፡ ሲመጣ በፖለቲካ ግፊት ነው የሚመጣው፡፡ በኋላ ደግሞ ፖለቲካዊ ግብ ይኖረዋል፡፡ ትክክለኛ ምክያቱን አላውቅም፡፡ ነገር ግን ስገምት አሁን ያለውን ብሔር ተኮር መናቆር ለማስተንፈስ ይሆን ብዬ እጠራጠራለሁ፡፡ ትክክል ከሆነ መዘግየቱ ካልሆነ በስተቀር ተገቢና ትክክለኛ ዕርምጃ ነው፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ ብቻ አይደለም ይህንን ሥርዓት የሚጠብቀው፡፡ አልነበረምም፣ አይችልምም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚሁ ሹመት ውስጥ ሦስት ጄኔራሎች በምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹምነት ተመድበዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበረ ኃላፊነት በመሆኑ፣ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሙን ለመተካት ነው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም በሌላ አገር ያለ አሠራር ነው፡፡ በእኛ አገር ይህ ኃላፊነት የለም ነበር፡፡ ነገር ግን ሥራው ሲከናወን ቆይቷል፡፡ አሁን በዚህ መልኩ እንዲደራጅ የተፈለገበትን ምክንያት አላውቅም፡፡ ነገር ግን ሠራዊቱ እየሰፋ ሲሄድ ራሳቸውን ችለው ስትራቴጂካዊ አመራር የሚሰጡና ሠራዊቱን የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሙን ለመተካት መሆኑን አላውቅም፡፡ ነገር ግን በሥልጣን ላይ ያሉት ኤታ ማጆር ሹም ከሚገባው በላይ በሥልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ለ17 ዓመታት በጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹመት መቆየት ማለት ምን ማለት ነው? የፈለገውን ያህል አቅም ይኑረው፣ አላስፈላጊ የሆነ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ እንዲፈጥር ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የፖለቲካ ቀውስ ሲፈጠር አገር በጦር ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ትወድቃለች የሚል ሥጋት ስለነበር ነው ይህንን የሚሉኝ?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- አይደለም፡፡ ይህ ሥጋት በፊት ነበረኝ፡፡ አሁን ግን የለኝም፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው የሕዝብ መነሳሳት ለዚህ ዕድል አይሰጥም፡፡ እንደ አሠራር ግን ለረዥም ጊዜ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም አንድ ሰው መሆን የለበትም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ አራት ዓመት በቂ ነው፡፡ አሥራ ሰባት ዓመት በጣም ረዥም ነው፡፡ ይህንን የምልበት የግል ምክንያት የለኝም፡፡ ከአገር ሁኔታ ጋር ነው የማያይዘው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሙን የመተካት እንቅስቃሴ ካለ ከተሾሙት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሞች ማን የሚሆን ይመስልዎታል?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- የተሾሙትን ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሞች ሁሉንም አውቃቸዋለሁ፡፡ ከተሾሙት መካከል ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን ነው ለውድድር የማቀርበው፡፡ ጄኔራል ሰዓረን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ነው የማውቀው፡፡ ረዥም ልምድ ያለውና በብቃቱም በስትራቴጂካዊ አመራሩም የሚታወቅ ነው፡፡ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላንም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አውቀዋለሁ፡፡ ክፍለ ጦር እየመራ በብቃት ኃላፊነቱን የተወጣ ነው፡፡ እኔ የክፍለ ጦር አዛዥ እያለ ነው የወጣሁት፡፡ ከዚያ በኋላ በሱዳን ሰላም ማስከበር ተሳትፏል፡፡ የምዕራብ ዕዝ አዛዥም ነበር፡፡ እኔ ካወቅኩት 17 ዓመት አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥልጣን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ግዳጆችን ተወጥቶ የመጣ አመራር ነው፡፡ ጄኔራል ብርሃኑ ከጄኔራል ሰዓረ በልምድ በትንሹ ዝቅ ቢልም፣ ቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም እንዲሆን ነው የምመርጠው፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ትልቅ ነው የሚሆነው፡፡ የትግራይ ተወላጆችን እንደ እንቁላል የሚጠብቅ ሥርዓት ነው የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲቀር ለማድረግና የብሔር መመጣጠንን ለማምጣት ጠቃሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ሲባል የአገር ደኅንነት አቅምን ማዳከም አይሆንም?

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፡- እኔ በግሌ ያለኝ አስተሳሰብ የአገሪቱን ደኅንነት በተመለከተ ስትራቴጂካዊ አመራር የመስጠት ጉዳይ በአንድ ሰው ላይ ከተንጠለጠለ አገር እየሞተ ነው ወይም ሞቷል ማለት ነው፡፡ አይደለም ግለሰብ ላይ መከላከያ ላይ ወይም አንድ ተቋም ላይ ብቻ ከወደቀ አገር ሞቷል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ደኅንነትን አስመልክቶ የሚሰጥ ስትራቴጂካዊ አመራር ከመከላከያ ወጣ ባለ እንደ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ነው መመራት ያለበት፡፡ አሁን እንደሚደረገው የክልል ፖሊስ ኃላፊዎችን ብቻ እየሰበሰቡ ሳይሆን የተወሰኑ ተቋማት ማለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የፋይናንስ ሚኒስትሩ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የደኅንነት ኃላፊው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች እንደ አገር የሚጨመሩትን አካቶ ነው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የሚዋቀረው፡፡ የትም አገር የሚደረገው እንዲህ ነው፡፡ የደኅንነት ጉዳይ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ የፋይናንስ ደኅንነትንም ያካትታል፡፡ በመሆኑም የሚፈጠር ችግር ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም የሚሆን ሰው ስትራቴጂካዊ ግንዛቤ እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ በዚህ ምክር ቤት ውስጥም በመሳተፍ አስተዋጽኦ እንዲኖረውና የሚወሰነውን ማስፈጸም ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ አራቱም የተሾሙት ጄኔራሎች በእኩል ሊያደርጉት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories