“ፖለቲካዊ ቀውሱን ለማርገብ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋል” ~ ሌ/ጄኔራል ፃድቃን

(አዲስ ዘመን)

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ ወሳኝ መፍትሄ ሳያገኝ ያዝ ለቀቅ እያደረገ ቀጥሏል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲሁም በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር በተነሳው ግጭት ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ለአካል ጉዳትና ለሞት ተዳርገዋል፤ በርካቶችም ግጭቱን ሽሽት ቀያቸውን ለቀው ለመሄድ ተገደዋል፡፡

 አገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግም ሰሞኑን እያደረገ ባለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባው ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ለማምጣት ምክክር ይዟል፡፡ በተለይም አመራሩ ለችግሩ መፈጠር ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ለመከተል መወሰኑን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ የተለያዩ ምሁራንና የህብረተሰብ ክፍሎችም ከጉባኤው የሚጠብቁት ውሳኔና አቅጣጫ እየገለፁ ይገኛሉ፡፡  የቀድሞው ታጋይና ከመከላከያ ሰራዊት በጡረታ የተገለሉት ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ለዚህች አገር መረጋጋት ወሳኝ  መፍትሄ ያሉትን ሃሳብ በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን በደቡብ ሱዳን ለስምንት ዓመታት በጸጥታ አማካሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ አሜሪካ ከሚገኘው ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በኢንተርናሽናል ፖሊሲ እና ፕራክቲስ የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፤ ቃለ ምልልሱን እነሆ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ እምነት በአገሪቱ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የፖለቲካ አለመረጋጋት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡- እኔ እንደሚታየኝ ለፖለቲካ አለመረጋጋቱ መሰረታዊ ምክንያት ህዝብ ስልጣን በያዘው መንግሥት ላይ እምነት ከማጣቱ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ህዝቡ እምነቱን ያጣው ደግሞ ለዓመታት እንዲሻሻሉ ሲጠይቃቸው የነበሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ምላሽ ባለማግኘታቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ስርዓቱ የህዝብ አመኔታ እንዳጣ ደግሞ ኢህአዴግም ራሱን አሁን አሁን አምኖ በግልፅ እየተናገረ ነው የሚገኘው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የችግሩ መንስኤዎች አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ነው እያለ ለመሸፋፈን ቢሞክርም በአሁኑ ወቅት ግን እውነታውን ወደመቀበል መጥቷል፡፡ በተለይም የመንግሥት ስልጣን ለግል መጠቀሚያ መዋሉን፣ጸረ ዴሞክራሲያዊነት መኖሩን፣ ህገ መንግሥቱ በተቀመጠው አግባብ አለመተግበሩ፣  ፓርቲውን በመሰረቱት  ድርጅቶች መካከል አለመተማመን መፈጠሩን ይህም ለስርዓቱ ከፍተኛ አደጋ እየሆነ መምጣቱን በግልፅ ማስቀመጡ ማሳያ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ናቸው ፖለቲካዊ ችግሩን ያባባሱት ወይስ ፖለቲካዊ ስርዓቱ  ራሱ መሰረታዊ  የአስተዳደራዊና  የቴክኒክ  ችግር አስከትሏል ?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡- በእኔ እምነት ፖለቲካዊ ስርዓቱ ነው አስተዳደራዊ ችግሮችን ያባባሰው፡፡ አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ህዝብን በፖለቲካ ስርዓቱ እምነት እስከማሳጣት አያደርሱም፡፡ ለእነዚህ መፍትሄው ፖለቲካዊ ስርዓቱን ማስተካከል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካላት ብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን መሰረት አድርጎ የተዋቀረውን የፌዴራሊዝም ስርዓት በችግርነት ያነሳሉ፤ የፖለቲካዊ ስርዓቱ እጥረት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል  ?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡-  አወቃቀሩ  በራሱ ለችግሩ መፈጠር መሰረታዊ ምክንያት ነው ብዬ አላስብም፡፡ ደግሞም በወቅቱ ብሄር ብሄረሰቦችን መብት የሚጨቁን መንግሥትን በጋራ ለማስወገድና በእኩልነት ላይ የተመሰረተች አገር ለመፍጠር ሲባል በብሄር መደራጀቱ ተገቢ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ አደረጃጀት ባይኖርም ችግሮቹ መከሰታቸው አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ የህዝብን የልብ ትርታ አድምጦ ፍትሃዊ አሰራር መዘርጋቱ ላይ ነው፡፡

በእርግጥ በብሄር የተዋቀረው አደረጃጀት ወደአላስፈላጊ ጫፍ ደርሶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና አገሪቱ ውስጥ ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ዋነኛ መንስኤ ሊሆን አይችልም፤ በእኔ እምነት ስራ አስፈፃሚው የመንግሥትን ስልጣን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠሩና የቁጥጥር ስርዓቱ የላላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው፡፡ ‹‹የህዝብን እምባ ያብሳሉ›› ተብለው የተቋቋሙ የዴሞክራሲ ተቋማትም በስራ አስፈፃሚው ጥላ ስር በመውደቃቸው ለሙስና እና ለስልጣን መባለግ ሰበብ ሆኗል፡፡

አዲስ ዘመን፡-  እርስዎም እንደገለፁት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በተለይም ሰሞኑን እያደረገ ባለው ስብሰባ ለችግሩ መባባስ የአመራሩ ድክመት ምክንያት እንደሆነና ከዚህ ቀደም ሲያካሂደው የነበረው ተሃድሶም ጥልቀት በሚፈለገው ደረጃ እንዳልነበር ተቀብሏል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ራሱን ያየበትን መንገድ እንዴት ነው የሚረዱት?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ፡- አሁንም ቢሆን ኢህአዴግ ችግሮቹን ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ  አድርጎ ነው እየገለፀ ያለው፡፡ በእኔ እምነት ካሉት ችግሮች ጋር የሚመጣጠን ውሳኔ እያስተላለፈ አይደለም፡፡ እየተደረገ ያለው ግምገማ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ያለፉትን ህፀፆች ፈትሾ ራስን ማረቅ ብሎም ተጠያቂነትን ማበጀት ተገቢ ነው፡፡ ይሁንና ዋናው ጉዳይ ሊሆን የሚገባው ‹‹ወደፊት ይህችን አገር እንዴት እንምራት›› የሚለው ነው፡፡ በተለይም አሁን ያለው ገዢ ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህዝብ አመኔታ ያጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስርነቀል የሆነ ለውጥ በማምጣት የህዝብን እፎይታ ማረጋገጥ መቻሉ ላይ ነው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፡፡

 አዲስ ዘመን፡- እርስዎ  ከአንድ ዓመት በፊት ሆርን አፌርስ በመባል በሚታወቀው ድረ ገጽ ላይ በአገሪቱ ከተከሰተው የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ ባሰፈሩት ጽሁፍ ችግሩ አስመልክቶ ወደፊት ይሆናሉ (Scenarios) ብለው ያስቀመጧቸው ጉዳዮች ነበሩ፤ አሁን በአገሪቱ እየተከሰተ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ምን ያህል  ይዛመዳል?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ፡- በድረ ገጹ ባሰፈርኩት ፅሁፍ ሦስት ቢሆኖችን (Scenarios)  አስቀምጬ ነበር፡፡ አንደኛው በአገሪቱ ያለው ብጥብጥ እየገፋ ይሄድና ሌሎችም የውጭ ሃይሎች በገንዘብና በተለየዩ መንገዶች በመደገፍ ገብተውበት ቀውሱ ተባብሶ የመንግሥት መፈራረስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሲሆን፣ ይህ ግን የመሆን እድሉ አነስተኛ ነው የሚል አመለካከት ነበረኝ፡፡ ይሁንና አሁን ሳየው እየዘገየ ሲሄድ ይሄ የመሆን እድሉ እየሰፋ ሊመጣ ይችላል፡፡ የተደራጀ የመረጃ ምንጭ ባይኖረኝም መንግሥት ከሚያወጣው መግለጫ አንፃር  ሌሎች ሃይሎች እጃቸውን እያስገቡ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዋናው ችግር ራሳችን ብንሆንም የውጭ ሃይሎች እያባባሱት መሆኑን ከሚታዩት ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህን ሁኔታ ተሸክሞ የመቆም ዕድሉ አነስተኛ ነው የሚሆነው፡፡

ሁለተኛው ይሆናል ብዬ ያስቀመጥኩት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ፖለቲካ ቀውስ ይኖራል የሚል ነው፤ በተለይም ኢህአዴግ ‹‹ራሴ በውስጤ እፈታዋለሁ›› እያለ አንዳንድ ያልፈለጋቸውን አመራሮች እያወጣ መሰረታዊ ችግሮቹን ይዞ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምታዊ አስተሳሰብ ነበረኝ፡፡ የመሆን እድሉ የሰፋ ነው ያልኩትም ይህንኑ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት አሁን እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ መንግሥት ለችግሩ ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ውስጡን የማጥራት ስራ ሲሰራ ቆይቷል፤ በዚህም እርምጃው ስልጣኑን ለማቆየት ዕድል ፈጥሯል፡፡

  ሦስተኛውና ዋነኛው ይሆናል ብዬ የገመትኩት ሰላማዊ፥ ስርዓት ያለውና በንቃት የሚመራ ለውጥ መጀመርን ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን በአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳለ በማመን ይህንን ቀውስ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ በሰፊ የፖለቲካዊ ሃይሎችና የምልዓተ ህዝቡን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችል ፖለቲካዊ ሂደት መጀመር ነው፡፡ ይህ አማራጭ እንደስጋት ያስቀመጥኳቸውን ቢሆኖች እንዳይከሰቱ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም አሁን ያለው ሁኔታ አስቀድሜ ለማሳየት ከሞከርኳቸው በተለይም ከሁለተኛው ‹‹ሴናሪዮዬ›› ጋር ትልቅ ተመሳሳይነት አለው፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ኮሚቴው በስብሰባው ከሌላው ጊዜ በተለየ ነባር አባሎችን አሳትፏል፡፡ ይህም ደግሞ በሌሎች ወገኖች ዘንድ ሌላ ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡ አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚ ሃሳብ የማፍለቅ አቅም የሌለውና አገርንም ለማስተዳደር ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ ከመግባቱ ጋር የሚያይዙትም አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰነዝሩት አስተያየት ካለ?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ፡- ነባር አባላትን ማሳተፉ ብቻውን አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአቅም ውስንነት አለበት ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል ብዬ አላምንም፡፡ ትክክለኛ ምክንያቱን በቅርበት ባላውቅም ድርጅቱ እንደ ድርጅት የራሱ አሰራር ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡  በእኔ አረዳድ ዋናው ጉዳይ ከችግሩ ጋር የሚመጣጠን አዲስ አቅጣጫ ካላስቀመጡ በስተቀር  ነባር አመራር ይኑር አይኑር ውጤት አይመጣም፡፡ ምክንያቱም  አሁን ያለው ውስብስብ ችግር  ከአንድ ፓርቲ አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ይህንን ቢሉም ኢህአዴግ ከዚህ ቀደምም መሰል ችግሮች  ሲያጋጥሙት በተለየየ አቅጣጫ ሲፈታ ቆይቷል፤ ውጤትም አምጥቷል፡፡ አሁንም በዚያው አግባብ ይፈታዋል በማለት የሚሞግቱ  የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ለእነዚህ አካላት የሚሰጡት ምላሽ ይኖር ይሆን?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ፡- ከዚህ ቀደም የነበሩት ችግሮችና አሁን ያለው ችግር አንድ አይደለም፡፡ የሚፈቱበትም መንገድ አንድ አይነት ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ቀደም በተለየዩ ፅሁፎቼ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ይህችን አገር ከመበታተን ለመታደግ ጉዳዩን በቅጡ ማየትና ማስተዳደር የሚችል አካሄድ መከተል ይጠይቃል፡፡

በእኔ እምነት አሁን ያለውን ፖለቲካዊ  አለመረጋጋት መፍታትም ሆነ በቀጣይ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው ነፃና ገለልተኛ የሆነ  ኮሚሽን አዋቅሮ መስራት ሲቻል ነው፡፡

ይሄ ኮሚሽን የተለያዩ አደረጃጀቶችና ሲቪክ ማህበራትን አካቶ ከፓርቲ ተጽእኖ ነጻ ነው ተብሎ ስለሚወሰድ በፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤቱ  ስር ሆኖ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እውቅና ሊቸረው ይችላል፡፡ ዋና ስራውም እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ አሁን ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ማስወገድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን መቀየስ፥ የማያሰሩ ህጎችን በማስወገድ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲረጋገጥላቸው ማድረግ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ታዲያ ገዢው ፓርቲ መንግስታዊ ስራዎችን ብቻ እየሰራ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል፡፡ የተለያየ አመለከከት ያላቸው ፓርቲዎችም  ከተፅዕኖ ተላቀው አቅማቸውን በማጎልበት ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተዋውቁበትና ቀጣዩ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ  ኮሚሽኑ ምቹ መደላደል የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ከአገር ውጭ ያሉ ተቃዋሚዎችም በሃይል ይህንን መንግሥት እንገለብጣለን እስካላሉ ድረስ በሰላም መጥተው እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ህዝቡም ወደፊት የሚኖረውን ብሩህ ተስፋ እያሰበ የእለት ተእለት ኑሮውን እንዲመራ ያደርገዋል፡፡ እዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው ጉዳይ ይህ ኮሚሽን ለኢህአዴግ ተጠሪ ሊሆን አይገባም፡፡ በእኔ አመለካከት የዚህ ኮሚሽን መቋቋም የፖለቲካ ውጥረቱን ያስተነፍሰዋል፡፡ በተለይም የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ካሉ እንዲፈቱ፣  ህገ መንግስቱ የሚፈቅደው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ያለምንም ገደብ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካዊ ውጥንቅጡ መልክ እንዲይዝ ይረዳዋል፡፡ ለዚህ መነሻ ግን ህገ መንግስቱ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ህገ መንግስት አንቀበልም ካልን የሚኖረው ምርጫ የእርስ በእርስ ጦርነት ይሆናል፡፡

  ይህን ስል ግን ህገ መንግስቱ ላይ የሚሻሻል ሃሳብ አለ የሚል አካል እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ነገር  ግን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ አገርን ማረጋጋት ነው፡፡  አገር ከተረጋጋችና ነፃ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ማሻሻል ይችላል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የሚቀጥለው ምርጫ ያለምንም ተፅእኖ ሲካሄድ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ የሽግግር ኮሚሽኑ የምርጫ ስርዓቱን በሚፈለገው መንገድ  ፈር ሲያሲዝ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ሂደት ያሸነፈው ፓርቲ በቀጥታ ስልጣን የሚይዝበት ሁኔታ መፈጠር ይጠይቃል፡፡ ውጤቱንም በፀጋ ለመቀበል ራስን ማዘጋጀት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት አለመኖራቸው በብዙዎች ዘንድ ይነሳል፤ በዚህ ሁኔታ በህዝብ ተቀባይነት ያለው ኮሚሽን ማቋቋም ይቻላል?

  ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ፡- እንደተባለው ጠንካራ ተቋማትና ማህበራት የሉም የሚለው ነገር በተወሰነ መንገድ ትክክል ነው፡፡ ይሁንና አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በህዝብ ተቀባይነት ያገኙ ተደማጭ ምሁራንና  የህብረተሰብ ክፍሎች ፈፅሞ የሉም ብሎ አገር ስትበታተን ዝም ብሎ መቀመጥ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ስለሆነም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሚወክሉ ግለሰቦች አማካኝነት ኮሚሽኑን በማቋቋም በሰላማዊ መንገድ በህዝብ ይሁንታን ያገኘውን ፓርቲ ወደስልጣን ማምጣት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሚያቀርቡት አማራጭ በኢህአዴግ ተቀባይነት ያገኛል ብለው ያምናሉን?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡-  እኔ የማቀርበው አማራጭ በአገር ውስጥ ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ያመጣል በሚል ነው እንጂ ኢህአዴግ ይቀበለዋል ወይም አይቀበለውም በሚል አይደለም፡፡ እኔ ከተሞክሮዬ እንደተገነዘብኩት የኮሚሽኑ መቋቋም አሁን ያለውን  ፖለቲካዊ  ቀውስ ወደ ጥሩ አጋጣሚ  ይቀይራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ  ግን ብቸኛ አማራጭ ነው ማለት አይደለም፤ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ሃሳብ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እንደዜጋ ለዚህች አገር ይበጃል ያልኩትን አማራጭ ማቅረብ እንጂ ሃሳቤን ኢህአዴግ ተቀበለውም አልተቀበለውም አያሳስበኝም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ድረስ የሚያስችል ድርድር ጀምሯል፡፡ ይህም  ፓርቲው አሁን ያለው ችግር ለመፍታት የሌሎችም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አምኖ መቀበሉ አንድ እርምጃ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡- ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር  ድርድር  መጀመሩን አልቃወምም፡፡ ነገር ግን በኢህአዴግ ጥላ ስር ሆኖ የሚደረግ እንደመሆኑ ተዓማኒነቱን ይቀንሰዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ከማንኛውም ፓርቲ ነፃ የሆነ በፓርላማ የቆመ ኮሚሽን ሲቋቋም ነው ችግሩን መፍታት የሚቻለው፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባ  የሚጠብቁት ነገር ካለ?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡- አሁን በአገሪቱ  ውስጥ ያሉት ችግሮች ከፖለቲካዊ ተዓማኒነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ቢሆንም  በሱማሌና ኦሮሚያ ክልል የእርስ በርስ ግጭት የሚመስሉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብሄር ተኮር የሚመስሉ አለመረጋጋት ይሰተዋላል፡፡ በመሆኑም የዚህ ኮሚሽን መቋቋም በአንድ በኩል ከፖለቲካ አመኔታ ማጣት የሚነሳውን ችግር ያረግበዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት የዕለት ተዕለት ስራውን ጠንከር ብሎ እንዲሰራ ያግዘዋል፡፡ እንደአጠቃላይ አገር እየፈረሰ ዝም ብሎ ማየት ስለማይቻል ጠንከር ባለ አካሄድ ህግን ተከትሎ አጥፊን የሚቀጣ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ስራ አስፈፃሚውም በሰጠው መግለጫ መሰረት ግለሰቦች ሂስና ግለሂስ ማድረግ ለተጠያቂነት ቢጠቅምም እንዲሁም መልሰን እንታደሳለን የሚለው ነገር ብዙ ርቀት እንዳላስኬዳቸው እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም  ችግሩ ከዚያ በላይ በመሆኑ የአካሄድና ከችግሩ ጋር የሚመጥን የአቅጣጫ ለውጥ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አጥፊን የሚቀጣ ጠንካራ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲባል ‹ጥያቄዬ በአግባቡ አልተመለሰም› የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል የበለጠ አይገፋውም ?

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡- ይህ ችግር ከህዝብ ጋር ያያይዘዋል የሚለው ነገር ብዙም አላውቀውም፡፡  የራሳቸውን ጥቅም ከህዝብ ጋር እያያዙ አገራዊ አጀንዳ በማስመሰል የሚሸሸጉ አንዳንድ ባለስልጣናት እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ጉዳዩ በተሸፋፈነ ቁጥር የበለጠ እድል እያገኙና መሸሸጊያቸው እየጠነከረ ነው የሚሄደው፡፡ ጉዳዩ በተገላለጠና ህዝብ እያወቀው በሄደ ቁጥር ደግሞ መሸሸጊያ ያጣሉ፡፡ ለውጥ የምንፈልግ ከሆነ ደግሞ ማድረግ የሚገባን እነዚህን አካላት አጋልጦ መስጠት ነው፡፡ ይህ ካልሆነና መሸሸጊያቸው በተጠናከረ ቁጥር የበለጠ ቁስሉ እየመረቀዘ መጨረሻ ላይ ብዙ ነገር ጠራርጎ የሚሄድ ነው የሚመስለኝ፡፡ግን አጥፊዎችን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ችግሩን በመሰረታዊነት የሚፈታ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ !

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን፡- እኔም አመሰግናለሁ !

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories