የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 7 | መቼም ቢሆን የማይዘነጉት የአየር ኃይላችን ባለዉለታዎች  

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የቀደሙ ክፍሎች ለማንበብ በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

Highlights

* ጄ/ል አበበ ወደ አየር ኃይል ሲመጡ አንዳችም የበረራ ግንዛቤዉ ያልነበራቸዉ ቢሆንም በተፈጥሮ ከታደሉት አስተዋይነት፤ በትግሉ ወቅት ካዳበሩት የአመራር ተሞክሮ በተጨማሪ ከእያንዳንዱ ባለሙያ ጋር በቅርበት ተመካክሮ ለመስራት ባላቸዉ ፈቃደኝነት የተነሳ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለአየር ኃይል አመራርነት ብቁ የሚያደርጋቸዉን አቅም መፍጠር ችለዉ ነበር፡፡

* በአየር ኃይሉ ታሪክ አየር ኃይሉን በጠንካራ መሰረት ላይ የገነቡትና የመጀመሪያዉ የአየር ኃይል አዛዥ መሆን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የመጀመሪያዉ ጄት አብረሪ ከነበሩት ከሌ/ጀነራል አሰፋ አያና ጀምሮ አስከ አስከ ደርግ መዉደቂያ ድረስ በአዛዥነት ከተመደቡት መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ አብራሪ ሳይሆኑ በአየር ኃይል አዛዥነት ለመሾም የበቁት ስምንተኛዉ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ዓለማየሁ አጎናፍር ብቻ ነበሩ፡፡

* የቀድሞዉ የበረሃዉ ታጋይ ጆቤ ግን በአዛዥነት መመደባቸዉ ሲነገራቸዉ ጄ/ል ዓለማዬሁ እንዳደረጉት “እኔ  የበረራ ሰዉ ስላልሆንኩ መመደብ የለብኝም” በሚል ተቃዉሞ ያቀረቡ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ጆቤ ወደ አየር ኃይል በአዛዥነት ተመድበዉ ሲመጡ የበረራ ክህሎት መኖር ይቅርና የተለመደዉ ወታደራዊ ማእረግ እንኳን ያልነበራቸዉ በመሆኑ አቶ “አበበ ተብለዉ” ነበር ሲጠሩ የነበሩት፡፡

* ወያኔ በድብቅ ዉጭ አገር እያላከ በአየር ኃይል ሙያ ያስተምር ካልነበረ እንዴት አንድ ከበረሃ የመጣ ታጋይ በአጭር ግዜ የዚህ አይነት አመራር ሊሰጥ ይችላል እያሉ አድናቆታቸዉን የገለጹም ነበሩ፡፡ እነዚህ ታጋዮች ለካስ የዋዛ አይደሉም፡፡  ድፍረታቸዉ ሳያንስ ጉብዝናቸዉ!” ያሉም ተብሎ ነበር፡፡

* አብዛኛዎቹ ነባር ታጋዮች እጅግ ዉስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ከተለመደዉ ዉጭ እጅግ በፈጠነ ሁኔታ የሚረዱበት፣ “አልችልም” የሚሉት አንድም ነገር አለመኖሩና አንዴ ትንሽ ገለጻ ከተሰጣቸዉ ከተነገራቸዉ የበለጠ በተግባር መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ከምን የመነጨ  እንደሆነ ሁልግዜም ይገርመኝ ነበር፡፡

*ለስራ ጉዳይ ቢሮአቸዉ በገባሁበት በጣም ጥቂት አጋጣሚዎችም ቢሆን ተደጋጋሞ ሲደረግ በመመልከቴ የገረመኝ ነገር ቢኖር ከማን ጋር እንደሆነ ማወቅ ባልችልም ነገር ግን ጆቤ ስልክ ከበላዮቻቸዉ በተደወለላቸዉ ቁጥር ከመቀመጫቸዉ ተነስተዉ ልክ የበላይ አለቃቸዉ አጠገባቸዉ ያለ ይመስል ተጠንቅቀዉ የስልኩን ንግግር አስከሚጨርሱ ቆመዉ ማናገራቸዉ ነዉ፡፡

* ሌላዉ ተጠቃሽ ጉዳይ ደግሞ ጆቤ ከድርጅታቸዉ የወረሱት የበረሃ ትግል ተሞክሮ ይሁን ወይንም የትኛዉ የሊደርሽፕ መርህ እንደሆነ ባለዉቅም ደጋግመዉ እንደመመሪያ ሲሰጡ የነበረዉና እኛም በኋላ ለምደን መተግበር የጀመርነዉ አንድ መርህ ነበረቻቸዉ፡፡ እሱም በየትኛዉም ደረጃ ያለ አመራር አስፈላጊ ሲሆን ቢያንስ አንድ ደረጃ ወርዶ ለመስራት የሚያስችለዉ ብቃት ሊኖረዉ ይገባል የሚል፡፡

* ጆቤ ከሁሉም ባህሪያቸዉ ተጠቃሽ የሚሆነዉ እዉነትነት የሌለዉ የተጋነነ ሪፖርት እጅግ የሚያስቆጣቸዉ መሆኑን ነዉ፡፡ ድክመቱን ለመሸፋፈን ሆን ብሎ ከሚዋሽ ሰዉ ይልቅ እቅም አንሶኛልና አልቻልኩም አግዙኝ ቢሎ እዉነቱን የሚናገረዉን ያከብራሉ፡፡ በስብሰባ ላይ የዉሸት ሪፖርት ሲቀርብላቸዉ ተናደዉ ተናጋሪዎቹን በቁጣ ያስደነገጡበትን አጋጣሚዎች አስታዉሳለሁ፡፡

*ከዚህ አኳያ የጆቤ ሁኔታ ሳስታዉስ እንዳደንቀቸዉና እንዳከብራቸዉ ያስገድደኛል፡፡ ጆቤ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ አስከታችኛዉ የስራ አካባቢ ድረስ በመገኘት ስራዎች እንዴት እንደሚሰሩ የመጎብኘትና ከሰራዊቱ ጋር የመመካከርና የሚቀርብላቸዉ ጥያቄ ካለም ያለ አንዳች ቢሮክራሲያዊ ማንዛዛት እዚያዉ ዉሳኔና ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ የጆቤን ጉብኝት አመራሩም ሰራዊቱም በደስታ ነዉ የሚጠብቁት፡፡

* ከጆቤ ባህሪያት ሁሉ አንድ የሚስደስተኝ ነገር ቢኖር በጽሁፍ የቀረበላቸውን ሪፖርት ወይም የጥናት ዉጤት የሆነ ጽሁፍ (ጽሁፉ የቱንም ያህል ቢረዝም) በትዕግስት አንድ በአንድ አንብበዉ ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም ማስተካከያ በሚፈልግና  የማያምኑበት ጉዳይ ሲያገጥማቸዉ  በየመስመሩ ላይ በቀይ ቀለም “ለምን? እንዴት? መቼ? ማን?” ወዘተ የመሳሰሉ አፋጣጭ ጥያቄዎችን መጠየቃቸዉ የተለመደ ነዉ፡፡

* ጆቤ አንድ ብዙዎቻችንን በወቅቱ ያልወደድንላቸዉ ምናልባትም ያስከፋን የነበረ ባህሪቸዉ ለግል ደህንነታቸዉ ከሚገባዉ በላይ መጨነቃቸዉና እጅግ የተጋነነ ጥበቃ እንዲደረግላቸዉ ማስደረጋቸዉ ነዉ፡፡ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ መኖሪያ ቤታቸዉ ዘወትር ማለዳ ወደ አየር ኃይል ደብረዘይት ሲመጡ የነበረዉን ትዕይንት ሁሉም ሰዉ ያስታዉሰዋል፡፡ ጆቤ ከሌሎቹ በማእረግም በሃላፊነትም አቻዎቻቸዉ ከሆኑት በተለየ ለግል ደህንነታዉ የዚያን ያህል የተጨነቁበትና በወቅቱ የሚሰጉበት ነገር ምን እንደነበረ  እስከዛሬም አይገባኝም፡፡

* ኮ/ል በዛብህ በተለያዩ መንግስታት ዘመን ሁሉ ለሀገሩ በጀግንነት ሲዋጋ የነበረና በስነምግባሩ፤ በሙያ ብቃቱና ለሀገሩ ባለዉ ጥልቅ ፍቅር አሁን ላሉትም ሆነ ለወደፊቱ ወጣት ፓይለቶች ተምሳሌትና አርአያ የሆነ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅ ለማስታወሻ የሚሆነዉ በስሙ አንድ ነገር እንኳን ተደርጎለታል?

* ይህ ጀግና በስሙ ሃዉልት ባይቀረጽለት እንኳን ሌላዉ ቀርቶ ለዘመናት ባገለገለበት አየር ኃይል ዉስጥ የሚታወስበት በስሙ የሚጠራ አንድ ነገር እንኳን አለመሰየሙ እጅግ የሚያሳዝን ነዉ፡፡ ከአየር ምድቦቹ ዉስጥ አንዱ ወይም የአየር ኃይል ስልጠና ማዕከል ሌላዉ ቢቀር አንድ በረራ ስኳድሮን  በስሙ ቢጠራና ታሪኩ በሚገባ ተቀምሮ ቢጻፍ የሚቃወም ሰዉ ያለ አይመስለኝም፡፡

* የእነ ኮ/ል በዛብህንና ሌሎቹንም ጀግኖች ስም ሳይጠራና የጀግንነት ታሪካቸዉ ሳይወሳ እንዴትስ ተደርጎ ነዉ የወጣት ፓይለቶችን የዉጊያ ሞራልና የሀገር ፍቅር ስሜት ማነሳሳት የሚቻለዉ? በማንስ አርአያነት ነዉ የምንቀርጻቸዉ? በዛብህ እኮ ባለፈዉ ስርአት ለኢትዮጵያ አንድነት ከሻእቢያ ጋር ሲዋጋ ተመቶ በመዉደቁና በሻዕቢያ ተማርኮ በሳህል የበረሃ አስር ቤት ለ8ዓመታት ሲሰቃይ ኖሮ ደርግ ከወደቀና መንግስት ከተቀየረ በኋላ ነበር ዳግመኛ ቢያገኙት እንደሚገድሉት በግልጽ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነው የተለቀቀዉ፡፡

* በዛብህ በወቅቱ እኔ ብዙም ያላጤንኩትና በዚያን ግዜ ፋይዳዉ ብዙም አልታይህ ቢሎኝ የነበረዉ የፌዴራላዊ ስርአት ጉዳይ በዛብህ ግን በስርአቱ እጅግ ደስተኛ ከመሆኑም ሌላ በከፍተኛ ሁኔታ ስሜቱን የነካዉ አጋጣሚ ደግሞ የደቡብ ክልል ተወላጅ የሆኑ በርካታ አዳዲስ ወጣት ወታደሮችን በጦር ካምፑ ዉስጥ መመልከቱ ነዉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ስለበዛብህ ማንነት አንድ ግዜ ከተረዱ በኋላ ዘወትር ምሽት ከስራ መልስ ቋሚ ስራቸዉ የሆነዉ ከእሱ ጋር ማዉጋት ነበር፡፡ እሱም በሁኔታዉ እጅግ ደስተኛ እንደነበር ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡

* የሻዕቢያ አይሮፕላኖች በመቐለ አይደር ህጻናት ተማሪዎች ላይ ያደረሱትን ግፍ በማዬት እልህ ተናንቆት የሻዕቢያን ማስጠንቀቂያም ከቁብ ሳይቆጥር ሻዕቢያን ሊቀጣና ቁጭቱንም ሊወጣ ሲሄድ ነዉ ተመትቶ በድጋሚ በእጃቸዉ ሊወድቅ የቻለዉ፡፡

* በዛብህን ይዘዉ ወደ አስመራ መሃል እንደገቡ አንድ ተመቶ የወደቀ ፓይለት ስለ መኖሩን የሰማዉ የአስመራ ህዝብ እሱን ለማየት ከየቤቱ እየወጣ እንዲሁም በርካታ መኪናዎቻቸዉ ግፊያ ትልቅ ትርምስ እየተፈጠረ በነበረበት ሰዓት በመካከሉ ዘግይቶ የደረሰዉ የድምጺ ሃፋሽ (የኤርትራ ራዲዮ) ጋዜጠኛ የነበረዉ አስመሮም በዛብህን ገና እንዳየዉ ለይቶት በመደነቅ ስሜት ሆኖ “…እንዴ ሻለቃ በዛብህ! አሁንም በድጋሚ ተመልሰህ መጣህ እንዴ?” ሲለዉ በዛብህ በራስ መተማመን ባልተለየዉ መንፈስ “እኔ ኮሎነል በዛብህ ነኝ እንጂ ሻለቃ በዛብህ አይደለሁም” በማለት ነበር የመለሰለት ፡፡

መግቢያ

አየር ኃይላችን በተለያዩ ዘመናት በአዛዥነትም ሆነ በተዋጊነት  በጥገናም ሆነ በአብራሪነት  በአየር መከላከያ ሙያም ሆነ በዘመቻ ስራ ..ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩ ስመ ገናና ምርጥ ልጆች የነበሩትና ዛሬም ቢሆን የሀገር ኩራት የሆኑ በርካታ ወጣት ጀግኖች ባለቤት መሆኑ  የሚታወቅ ነዉ፡፡

አየር ኃይላችን ከተመሰረተበት ወቅት አንስቶ በቆየባቸዉ በርካታ አስርት ዓመታት ታሪኩ ለአየር ኃይሉም ሆነ ለሀገሪቱ ባለዉለታ የነበሩና ስራቸዉ መቼም ቢሆን የማይዘነጉ ጀግኖች በርካታ ናቸዉ፡፡ በዚህ አጭር ማስታወሻ ላይ እግረመንገዴን ለማስታወስ የፈለኩት አጠቃላይ ስለአየር ኃይላችን ጀግኖች ገድል ለመተረክ ሳይሆን ከዚያ ይልቅ ከደርግ ዉድቀት በኋላ አየር ኃይሉን በአዲስ መሰረት ላይ ለመገንባትና በኤርትራ ጦርነትም ድንቅ አመራር በመስጠት የሀገር ባለዉለታ ስለሆኑት ስለ ሜ/ጄ.አበበ ተ/ሃማኖት (ጆቤ) እንዲሁም በዚሁ ጦርነት ወቅት በግዳጅ  ላይ እያለ ተመትቶ በጠላት እጅ በመዉደቁ ሳይመለስ ስለቀረዉ ዘመን የማይሽረዉ የኢትዮጵያ ጀግና ስለሆነዉ ኮ/ል በዛብህ ጰጥሮስ ጥቂት ነገሮችን ለትዉስታ ያህል ለማንሳት ነዉ፡፡

መቼም ስለ አየር ኃይላችን ሲጠቀስ ስለጆቤም ሆነ ስለበዛብህ  ሳይጠቅሱ ማለፍ ፈጽሞ የሚሞከር አይደለም፡፡ በተለይ ጄኔራል አበበን በሚመለከት ስለ ሰዎች ክፋት እንጂ ስለ መልካም ስራቸዉ መናገር ባልተለመደበት ህብረተሰብ ዉስጥ እንደ ጆቤ ከስርአቱ የተገለለን ሰዉ በበጎ ማንሳት ጅልነት እንደሆነ ባይጠፋኝም ስለ እሳቸዉ እግረመንገዴን እንዳወሳ ህሊናዬ ያስገድደኛል፡፡ ይሄን ማድረጌ ባለዉለታዎቻችን በማስታወስ ተገቢው ክብር እንዲሰጣቸዉ ለማሳሰብና ለነገዉ  ተተኪዎቻቸዉ  አርአያ እንዲሆኗቸዉ ለማስገንዘብ ነዉ፡፡

/ /ጀነራል አበበ /ማኖት (ጆቤ)

አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት ሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) በኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥነት ዘጠነኛዉ አዛዥ ሆነዉ በሃላፊነት ተመድበዉ ከመጡበት ከ1986 ዓ/ም ጀምሮ ወቅቱን ባልጠበቀ ጊዜ በጡረታ አስከተሰናበቱበት 1993 ዓ/ም ድረስ አየር ኃይሉን ለማጠናከር ያደረጉት ጥረት የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ጄ/ል አበበ ባለፉት መንግስታት ዘመን አየር ኃይልን በአዛዥነት ከመሩት ዉስጥ እጅጉን ከሚወደሱት መካከል ስማቸዉ ጎልቶ የሚጠቀሰዉ ሜ/ጄ ፋንታ በላይና ሜ/ጄ አምሃ ደስታ አዛዥ በነበሩበት ዘመን የነበረዉን አየር ኃይልን እንደ ማነጻጸሪያ በመዉሰድ በዚያን ወቅት ከነበረዉ አየር ኃይል ጋር የሚመጣጠን ከተቻለም በሂዴት ከዚያ የተሻለ ብቃት ያለዉ አየር ኃይልን ለመመስረት ሲተጉ ነበር፡፡

በጦርነቱ ጊዜም የአየር ኃይሉ አባላት የቀድሞዉና የአሁኑ፤ ታጋይ የነበረ ያልነበረ ሳይባባሉ ለሀገራቸዉ በአንድነት እንደ አንድ ሰዉ ሆነዉ በመቆም የሻዕቢያን የእብሪት ወረራ በጋራ እንዲመክቱ ሲሰጡ የነበረዉ የአመራር ብቃት የሚደነቅ እንደነበር በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡

ጄ/ል አበበ ወደ አየር ኃይል ሲመጡ አንዳችም የበረራ ግንዛቤዉ ያልነበራቸዉ ቢሆንም በተፈጥሮ ከታደሉት አስተዋይነት፤ በትግሉ ወቅት ካዳበሩት የአመራር ተሞክሮ በተጨማሪ ከእያንዳንዱ ባለሙያ ጋር በቅርበት ተመካክሮ ለመስራት ባላቸዉ ፈቃደኝነት የተነሳ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለአየር ኃይል አመራርነት ብቁ የሚያደርጋቸዉን አቅም መፍጠር ችለዉ ነበር፡፡

በተለይም ከመከላከያም ሆነ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በነበራቸዉ መቀራረብና ተደማጭነት የተነሳ እንዲሁም ባዳበሩት ከፍተኛ የራስ መተማመን ምክንያት በማንኛዉም ጉዳይ ላይ ፈጥኖ የመወሰን ችሎታ ስለነበራቸዉ በአጭር ጊዜ ለዉጥ ማምጣት ችለዉ ነበር፡፡ ለአየር ኃይሉ መጠናከር አስፈላጊ የሆኑ ከበላይ እንዲሟላላቸዉ የሚጠይቁት ሁሉ ያለ አንዳች ተቃዉሞ ይፈቀድላቸዉ ስለነበር አየር ኃይሉን ለማጠናከር አመቺ ሁኔታ ፈጠሮላቸዋል፡፡

1/ ጆቤ ፓይለት ሳይሆኑ ለአየር ኃይል አዛዥነት ስለመሾማቸዉ

እንደሚታወቀዉ የአየር ኃይል አዛዥ ለመሆን በአየር ኃይል በረራ ሙያ የረዥም ጊዜ ልምድ መኖርና በተጨማሪ በኤሮኖትክስ ኢንጂኔርንግ ወይም በአቭየሽን ሜንቴናንስ መስክ ብቁ የሚያደርግ ስልጠና ያገኘና ከፍተኛ የአካዳሚክ እዉቀትም ያለዉ መሆንን የግድ ነዉ፡፡ ይህም  በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገሮች የተለመደ አሰራር ነዉ፡፡ ከአየር ኃይል ሙያ ጋር የማይተዋወቅ ሰዉ በምንም ሁኔታ አዛዥ ሆኖ አይመደብም፡፡ ስለ አየር ኃይል በቂ ግንዛቤ የሌለዉና  በበረራ ዉስጥ ላላለፈ እንደ ጆቤ ላለ ሰዉ የአየር ኃይል አዛዥ ሆኖ እንዲሰራ መሾም ፈጽሞ የማይታሰብ ጉዳይ ነዉ፡፡

ጆቤ ቢያንስ በመረጃ ደረጃ ስለ ጄ/ል ፋንታ በላይ፣ ሰለ ጄ/ል አምሃ ደስታ ወዘተ ያዉቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ጄነራል አበበ እነዚህ ምርጥ የአየር ኃይል አዛዦች አመራር ሲሰጡበት በነበረዉ አየር ኃይል በአዛዥነት ሲመደቡ ሃላፊነቱ ቀላል እንደማይሆንላቸዉ አስቀድመዉ ሳይረዱ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ምክንያትም የኢህአዴግ መንግስት አንዳችም የበረራ ልምድ ያልነበረዉን አንድ ታጋይ “ለታላቁ አየር ኃይል” አዛዥነት መሾሙን  የሰሙ ብዙ ሰዎች ኢህአዴግ አየር ኃይሉን ሆን ብሎ ለማፍረስ እንዳሰበ አድርገዉ ነበር የቆጠሩት፡፡

በርግጥም ኢህአዴግ በአየር ኃይል ላይ ከበረሃ ጀምሮ ክፉኛ ቂም ቋጥሮአልና መበቀሉ አይቀርም፡፡ አየር ኃይሉንም  ልክ ባህር ኃይሉ ላይ እንዳደረገዉ “ከዚህ በኋላ አየር ኃይል የሚባል ነገር አያስፈልገንም” በሚል ሙሉ በሙሉ እንደሚያፈርስ በሃሜት ደረጃ ሲወራ ቆይቶ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ የአየር ኃይሉን አባላት በሙሉ ይበቀላል የሚለዉ ስጋት የወለደዉ ወሬም በሰፊዉ ሲነገር ነበር፡፡ እንግዲህ ጆቤ ወደ አየር ኃይል ሲመጡም  “በቃ የተወራዉ ሁሉ ትክክል ነዉ ማለት ነዉ” ነበር የተባለዉ፡፡

በአየር ኃይሉ ታሪክ አየር ኃይሉን በጠንካራ መሰረት ላይ የገነቡትና የመጀመሪያዉ የአየር ኃይል አዛዥ መሆን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የመጀመሪያዉ ጄት አብረሪ ከነበሩት ከሌ/ጀነራል አሰፋ አያና ጀምሮ አስከ አስከ ደርግ መዉደቂያ ድረስ በአዛዥነት ከተመደቡት መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ አብራሪ ሳይሆኑ በአየር ኃይል አዛዥነት ለመሾም የበቁት ስምንተኛዉ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ዓለማየሁ አጎናፍር ብቻ ነበሩ፡፡

በወቅቱ አየር ኃይሉ ከግንቦት 8/1981 ኩዴታ ሙከራ ጋር በተያያዘ ቢያንስ ስድስት ምርጥ ጄነራሎቹን በሞት በመነጠቁ አየር ኃይሉን በአዛዥነት ሊመራዉ የሚችል ለቦታዉ የሚመጥን ሰዉ ባለመገኘቱ ደርግ አማራጭ ሲያጣ ጄኔራል አለማየሁን ከሌላ መስሪያ ቤት መልሶ ለማምጣት ተገዶ ነበር፡፡

በዚሁ መሰረት ጄ/ል ዓለማዬሁ ከዓመታት በፊት ለቀዉት ወደሄዱት የቀድሞ ከፍላቸዉ አየር ኃይል ለዚያዉም በአየር ኃይል አዛዥነት ሃላፊነት ሊመደቡ እንደሆነ እንዳወቁ ወዲያዉኑ የተቃዉሞ ማመልከቻ ለመከላከያ ሚኒስትሩ አስከማቅረብ ደርሰዉ ነበር፡፡ የተቃዉሞአቸዉ መነሻም “አኔ አብራሪ ወይም ፓይለት ሳልሆን ለአየር ኃይል አዛዥነት መመደብ አይገባኝም፡፡ ለዚህ ትልቅ ሃላፊነት አልመጥንም” የሚል ነበር፡፡

ጄነራሉ በራሪ ባይሆኑም ስለ አየር ኃይል በቂ እዉቀት ነበራቸዉ፡፡ በአየር ኃይል የቴክኒክ ዘርፎች በአገር ዉስጥም ሆነ በአሜሪካ አገር ተልከዉ በርካታ ስልጠናዎችን እንደወሰዱ ይታወቃል፡፡ በአይሮፕላን ምህንድስና ትምህርት እንዲሁም በአሮኖቲካል ኢንጂነርንግ ሙያ በተለያዩ ጊዜያት ተምረዉ ከመመረቃቸዉም በተጨማሪ በሀገር ዉስጥም አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ገብተዉ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

በአየር ኃይል ዉሰጥም በተለያዩ ኃላፊነቶች በድምሩ አስራ ስድስት ዓመታት ከማገልገላቸዉም ሌላ በጥይት ፋብሪካ ዋና ዳሬክተርነት፣ በመከላከያ ሚኒስቴር ሎጂስትክስ ዋና መምሪያ ሃላፊነት በመቀጠልም በመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ አንዱስትሪ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ሆነዉ በመስራት በስራ ዓለም ከፍተኛ የአመራርነት ልምድ ያካበቱ ሆነዉ እያሉ ሃላፊነቱን ላለመቀበል ተቃዉሞ ያቀረቡበት ዋናዉ ምክንያት የአየር ኃይል አዛዥነት ኃላፊነት እጅግ ከባድ እንደሆነ በመረዳታቸዉ ነዉ፡፡ በኋላ ግን በሌሎች ሰዎች ግፊትና ማግባባት ሃላፊነቱን መቀበላቸዉ አልቀረም፡፡

የቀድሞዉ የበረሃዉ ታጋይ ጆቤ ግን በአዛዥነት መመደባቸዉ ሲነገራቸዉ ጄ/ል ዓለማዬሁ እንዳደረጉት “እኔ  የበረራ ሰዉ ስላልሆንኩ መመደብ የለብኝም” በሚል ተቃዉሞ ያቀረቡ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ጆቤ ወደ አየር ኃይል በአዛዥነት ተመድበዉ ሲመጡ የበረራ ክህሎት መኖር ይቅርና የተለመደዉ ወታደራዊ ማእረግ እንኳን ያልነበራቸዉ በመሆኑ አቶ “አበበ ተብለዉ” ነበር ሲጠሩ የነበሩት፡፡

እናም ያለ አንዳች ወታደራዊ ማዕረግ “አቶ” ና “ታጋይ” እየተባሉ የሚጠሩት ጆቤ ዘጠነኛዉ የአየር ኃይል አዛዥ እንዲሆኑ ተመድበዉ ወደ አየር ኃይል ሲመጡ የሚጠብቃቸዉን የሃላፊነቱን ክብደት አስቀድመዉ ተረድተዉ በሚገባ ያሰቡበት ይመስል በቀጥታ ወደ ስራ ከመግባታቸዉ በፊት ያደረጉት ነገር ቢኖር የጉብኝትና የገለጻ ፕሮግራም እንዲዘጋጅላቸዉ በማድረግ ስለ አየር ኃይል አጠቃላይ ባህሪይ ለማወቅ እያንዳንዱን የሥራ አካባቢ በአካል ተገኝተዉ ገለጻ በማዳመጥና ከሰራዊቱ ጋር በመወያዬት ነበር፡፡

በርካታ ቀናት በጠየቀዉ በዚህ የገለጻና ጉብኝት ፕሮግራም ጆቤ ስለ አየር ኃይል መሰረታዊና ቁልፍ ጉዳዮች በሚገባ ለመረዳት አስችለአቸዋል፡፡ በዚህ ጥረታቸዉም ብዙ ሰዉ አድንቆአቸዋል፡፡ ወደ መደበኛ ስራቸዉ ከገቡም በኋላ ፍርስርሱ ወጥቶ የነበረዉን አየር ኃይልን ለማቋቋም ሌት ተቀን ያደረጉት ጥረትም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በሳቸዉ መመደብ ከፍተኛ ጥርጣሬ ገብቶት የነበረዉ ብዙ ሰዉም የጆቤን አያያዝ ካዩ በኋላ ጥርጣሬአቸዉ ትክክል እንዳልነበረና ጆቤ ከታሰበዉ በላይ አየር ኃይሉን እያቋቋሙ እንደሆነ ለመገንዘብ ችለዉ ነበር፡፡

ከመጀመሪያ ጀምሮ ከአየር ኃይል ጋር ቤተሰባዊ የሚመስል ጥብቅ ቁርኝት የነበረዉ የደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ ህዝብ  ኢህአዴግ ሐረር ሜዳን ከረገጠበት ዕለት ጀምሮ በፊት የለመደዉ የጄት አይሮፕላኖች ድምጽ ቀርቶበት ተደብሮ እንዳልነበር ጭራሽ ይባስ ተብሎ አንድ ከበረሃ የመጣ ታጋይ ለአየር ኃይል አዛዥነት መመደቡን ከሰማ ዕለት ጀምሮ በሁኔታዉ ሲያዝኑ እንዳልነበር በጆቤ አመራር ሰጭነት አየር ኃይላችን በአጭር ግዜ ወደ ቀድሞ ክብሩ እየተመለሰ መሆኑን ሲረዱ ግን አድናቆታቸዉንና አግራሞታቸዉን ይገልጹ ነበር፡፡ በዚህም “ጆቤ” እየተባለ ስለሚጠራዉ ሰዉ መመደብ እጅግ ደስተኛ ሆነዉ ነበር፡፡

ወያኔ በድብቅ ዉጭ አገር እያላከ በአየር ኃይል ሙያ ያስተምር ካልነበረ እንዴት አንድ ከበረሃ የመጣ ታጋይ በአጭር ግዜ የዚህ አይነት አመራር ሊሰጥ ይችላል እያሉ አድናቆታቸዉን የገለጹም ነበሩ፡፡ እነዚህ ታጋዮች ለካስ የዋዛ አይደሉም፡፡  ድፍረታቸዉ ሳያንስ ጉብዝናቸዉ!” ያሉም ተብሎ ነበር፡፡ በርግጥ እኔ ራሴ ከቀድሞዎቹ ታጋዮች ጋር በሰራሁበት ረዥም አመታት ዉስጥ ከሚቀርቡኝ ከድሮዎቹ ጓደኖቼና የስራ ባልደረቦቼ ጋር እንደ ጥያቄ እያነሳን ስንነጋገር የነበረዉ አስቀድሜ የጠቀስኩት ዓይነት ነገር በመታዘባችን ነዉ፡፡

አብዛኛዎቹ ነባር ታጋዮች እጅግ ዉስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ከተለመደዉ ዉጭ እጅግ በፈጠነ ሁኔታ የሚረዱበት፣ “አልችልም” የሚሉት አንድም ነገር አለመኖሩና አንዴ ትንሽ ገለጻ ከተሰጣቸዉ ከተነገራቸዉ የበለጠ በተግባር መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ከምን የመነጨ  እንደሆነ ሁልግዜም ይገርመኝ ነበር፡፡

አንድ አብነት ልጥቀስ፡፡

በ1985 ወደ ስራ በድጋሚ ተመልምለዉ የገቡና በአየር ኃይል ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ኮ/ል ሙሉብርሃን መኮንን የሚባሉ የቅርብ ጓደኛዬ የበ1986 ላይ በወቅቱ ብርሃነ ዝቅአርገ ከሚባል ታጋይ ጋር ያጋጠማቸዉን ለአብነት ልጥቀስ፡፡  መኮንኑ ያኔ ሻለቃ የነበሩ ሲሆን ስለ አየር መከላከያ ትጥቆችና የግዳጅ አፈጻጸም ባህሪይ ለማስተዋወቅ በየዕለቱ ከዚህ ታጋይ ጋር ቢሮ ዘግተዉ ገለጻ ያደርጋሉ፡፡

ታዲያ አስገራሚዉ ነገር ኮ/ል ሙሉብርሃን ከአንድ ሰአት ላላነሰ ግዜ ማስታወሻ ደብተራቸዉን እያዩ ያደረጉትን ገለጻ ታጋዩ ወዲ ዝቅአርገ ምን ያህል እንደተረዳ እንዲነግራቸዉ ሲጠይቁት ያለአንዳች ማስታወሻ በቃሉ ከዳር እስከዳር ለዚያዉም በተሻለ ሁኔታና ቅደም ተከተሉንም ሳይለቅ ማብራራቱ ነዉ፡፡ ይህ ክስተት በመደጋጋሙ ነዉ ተገርመዉ በወቅቱ ያጫወቱኝ፡፡

በርግጥ በኋላ ላይ እኔ ራሴም ብሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ነባር ታጋዮቹ ነገሮችን በጥልቀት የመገንዘብ፣ ሁኔታዎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየመዘኑ የመተንተንና ሃሳባቸዉን በሚገባ አደራጅተዉ የመግለጽ ብቃት የአብዛኛዎቹ የጋራ መገለጫ እንደነበረ ለመረዳት ችዬአለሁ፡፡

ይሄን ነገር አልችለዉም የሚሉት አንዳችም ጉዳይ ያለመኖሩና በተግባርም በተዋጣለት መንገድ ለመስራት ያስቻላቸዉ ምናልባት በረሃ በነበሩ ግዜ በትግሉ ወቅት ያዳበሩት ባህሪይ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ እንግዲህ ጆቤም ከታሰበዉ በላይ የተሳካ ስራ መስራት የመቻላቸዉ ምስጢር የተፈጥሮ ማስተዋል ተጨምሮ በዋነኛነት በትግሉ ወቅት  ካዳበሩት ልምድ የተገኘ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

2/ አየር ኃይሉ የሻዕቢያን የመስፋፋት ህልም ለማክሸፍ ባደረገዉ ጦርነት ለሰራዉ አኩሪ ስራ አመራር ሰጭነት ወሳኝ ነበር  

ጄ/ል አበበ (ጆቤ) አየር ኃይሉን በአዲስ መልክ የማቋቋሙን ስራ ገና ከዳር ሳያደርሱ ነበር ኤርትራ ወረራ የፈጸመችብን፡፡ ከኤርትራ ጋር ስናካሂድ በነበረዉ ጦርነትም በሳቸዉ አመራር ሰጭነት አየር ኃይላችንን በአጭር ጊዜ ዉስጥ በማዘጋጀት በጦርነቱ ላይ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

አየር ኃይሉ በጦርነቱ ላይ ላይ የማይናቅ ድርሻ የነበረዉ መሆኑ ባይካድም ነገር ግን በመጀመሪዎቹ ቀናት አካባቢ በተለይም በግንቦት 28 እና 29 የታየዉ መደነቃቀፍ ከዝግጅት ማነስና ከአመራር ድክመት የመነጨ እንደነበር እሳቸዉም ቢሆኑ ያጡታል ብዬ አላስብም፡፡

በተለይ ግንቦት 28 1990ዓ/ም በመቐለ ዓይደር ት/ቤት ህጻናት ላይ በኢሳይያስ ትዕዛዝ ሆን ተብሎና ታቅዶ በሻዕቢያ አይሮፕላኖች የደረሰዉን አረመናዊ ጭፍጨፋ እንዳይደርስ ማድረግ አለመቻላችን የአየር ኃይላችን አጠቃላይ ለጦርነቱ በሚገባ ያለመዘጋጀቱ ያስከተለዉ ዉጤት እንደነበር ይታወቃል፡፡

በወቅቱ መላዉ የአየር ኃይል አባላት በሃፍረት አንገታቸዉን መድፋት ነበረባቸዉ፡፡ በዚያን ሰሞን በየደረጃዉ ለነበረዉ አመራርም ከህዝቡ ጋር ለመቅረብም አሳፋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ እንደማስታዉሰዉ በሻዕቢያ አረመናዊ ደርጊት በቀጥታ ሰለባ ከነበረዉ የመቐለ ከተማ ወይም የትግራይ ክልል ህዝብ ይልቅ ስለ ሁኔታዉ የሰማዉ በየክልሎቹ የነበረዉ መላዉ የሀገሪቱ ህዝብ እጅግ መበሳጨታቸዉና መቆጣታቸዉ ነዉ፡፡

በቅርብ ለነበረዉ ለትግራይ ህዝብና ለክልሉ መስተዳድር አመራሮች ሁኔታዉ እጅግ መራር ቢሆንም ነገር ግን የጦርነትን አስከፊነት በሚገባ የሚያዉቁ ስለነበረ ቁጭቱንና ብስጭቱን ዋጥ አድርገዉ ሳያሰልሱ በአየር ኃይሉ የምድቡ ማዘዣ ጣቢያ በመገኘት የአየር ኃይሉ አባላት ሞራላቸዉ እንዳይነካ አይዟችሁ እያሉ ከማበረታታት ወደ ኋላ አላሉም፡፡

በሻእቢያ አውሮፕላኖች በአይደር ህጻናት ላይ አሰቃቂ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ስለሁኔታዉ መቐለ ድረስ በመሄድ እንድናጣራ በእኔ የሚመራ አንድ ቡድን ለመላክ አቅደዉ መመሪያ ለመቀበል ቢሮአቸዉ በገባንበት ወቅት ጀቤ በፊት የሚናዉቀዉ ዓይነት ከነግርማ ሞገሳቸዉና በራስ መተማመን መንፈስ ሳይሆን በደረሰዉ አደጋ እጅግ በማዘናቸዉ ቅስማቸዉ ተሰብሮና ለብዙ ቀናት ሃዘን የተቀወመጠ ሰዉ ይመስል ጉስቁልቁል ብለዉ ነዉ ያገኘናቸዉ፡፡

በርግጥ ሁኔታዉ በተለይ ለሳቸዉ ከባድ ቢሆን የሚስገርም አይደለም፡፡ ከተመሰረተ ጀምሮ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር አኩሪ ገድል ሲፈጽም ለኖረና እጅግ ገናና ስም ለነበረዉ ታላቁ አየር ኃይል አዛዥ ሆነዉ እያለ አንድ መናኛ አየር ኃይል  አይሮፕላን የአይር ከልልችንን ጥሶና ያን ሁሉ ርቀት አቋርጦ ሰተት ቢሎ መቀሌ ድረስ በመምጣት ህጻናትን ሲጨፈጭፍ መታደግ አለመቻላቸዉ በሳቸዉ ቦታ ሆኖ ላየዉ ሰዉ ሁኔታዉ እጅግ ከባድ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ጆቤ ምናልባት ስልጣኑን ከተረከቡ ከአራት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ የአየር ኃይል አዛዥነቱ ሃላፊነት ክብደት ለመረዳት የቻሉ ይመስለኛል፡፡ ጆቤ በጦርነት ዉስጥ የኖሩ መስዋእትነትና ኪሳራ፣ ድልና ዉድቀት ምን እንደሆኑ በተግባር የሚያወቁ በመሆናቸወዉ በደረሰዉ ሁኔታ ሳይደናገጡ ይልቁንም ብዙ ግዜ ሳያባክኑ ሻእቢያን ለመበቀል መስራት የሚገባቸዉን ስራ በመስራት የሻዕቢያ አረመናዊ ድርጊት ቁጭት የገባዉን ሰራዊታቸዉን በማንቀሳቀስ አኩሪ ስራ በመስራቸዉ በጆቤ አመራር ሰጭነት  ቀንና ሌሊት የተደረገዉ ዝግጅት ፍሬ አፍርቶ በዉጤቱም ዳግመኛ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉ ብቻ ሳይሆን የሻዕቢያ አዉሮፕላኖች አስከመጨረሻዉ የጦርነቱ ፍጻሜ ድረስ ወደ ድንበራችን ከ40 ኪ/ሜ መቅረብ ያልቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡

በአንጻሩ የኛ አየር ኃይል አብራሪዎች ኤርትራ ክልል ዉስጥ  ያለ አንዳች ከልካይ በቀንም ሆነ በምሽት ባሰኛቸዉ ሰዓት ሁሉ እየተመላለሱ  ወታደራዊ ኢላማዎችን እየመረጡ ሲያደባዩ ለቅሶዉና ዋይታዉ የኢሳይያስና የሻዕቢያ አመራሮች ተራ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ጄ/ል አበበ በሠጡት ድንቅ አመራር አየር ኃይላችን አኩሪ  ስራ እንዲሰራ አስችሎታል፡፡

Photo - Col Bezabh Petros in Eritrea after capture
Photo – Col Bezabh Petros in Eritrea after capture

3/ በልዩ ሁኔታ የማስታዉሳቸዉ የጆቤ አንዳንድ መልካም ባህሪያቶቻቸዉ

3.1/ የኢህአዴግን ታጋዮች ድስፕሊን በጆቤ በኩል ለማየት ያስቻለኝ አጋጣሚ  

የጄል አበበ (ጆቤ) ጉዳይ ሲነሳ ሁልግዜ ይገርመኝ የነበረና በዚህ አጋጣሚ  መጥቀስ ያለብኝ አንድ ባህሪያቸዉ ነዉ፡፡

ለስራ ጉዳይ ቢሮአቸዉ በገባሁበት በጣም ጥቂት አጋጣሚዎችም ቢሆን ተደጋጋሞ ሲደረግ በመመልከቴ የገረመኝ ነገር ቢኖር ከማን ጋር እንደሆነ ማወቅ ባልችልም ነገር ግን ጆቤ ስልክ ከበላዮቻቸዉ በተደወለላቸዉ ቁጥር ከመቀመጫቸዉ ተነስተዉ ልክ የበላይ አለቃቸዉ አጠገባቸዉ ያለ ይመስል ተጠንቅቀዉ የስልኩን ንግግር አስከሚጨርሱ ቆመዉ ማናገራቸዉ ነዉ፡፡

በስልክ የምንጋገሩት ሁልግዜም በትግርኛ ስለነበረ ስለምን እንደሚነጋጋሩ ማወቅ  ባልችልም ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ወይም ከአቶ ስዬ አብርሃ ወይንም ደግሞ ከጄ/ል ጻድቃን ጋር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ከዚህ ጋር ተቀራራቢ የሆነና ስለ ጀርመን መኮንኖች ድስፕሊን ጥንካሬ በአሜሪካኖች የተጻፈ አንድ ጽሁፍ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡

በጆቤ ላይ ያየሁት የተለመደዉ አይነት ደረቅ የሆነ ዲስፕሊን ሳይሆን በእምነት ላይ የተመሰረተ ጓዳዊነትና የዓላማ አንድነት የመነጨ በዓይነቱም ለየት ያለ ድስፕሊን ነበር፡፡ ይህ የጆቤ የግላቸዉ ባህሪይ ወይንም ደግሞ የጠቅላላዉ የቀድሞ ታጋዮች የጋራ መገለጫ ይሁን በርግጠኝት መናገር አልችልም፡፡ አጋጣሚዉ ግን ምን ዓይነት በእምነት ላይ የተመሰረተ ወታደራዊ ድስፕሊን እንደነበራቸዉ የተረዳሁበት ነዉ፡፡

3.2/ የጆቤ ለየት ያለች  

ሌላዉ ተጠቃሽ ጉዳይ ደግሞ ጆቤ ከድርጅታቸዉ የወረሱት የበረሃ ትግል ተሞክሮ ይሁን ወይንም የትኛዉ የሊደርሽፕ መርህ እንደሆነ ባለዉቅም ደጋግመዉ እንደመመሪያ ሲሰጡ የነበረዉና እኛም በኋላ ለምደን መተግበር የጀመርነዉ አንድ መርህ ነበረቻቸዉ፡፡ እሱም በየትኛዉም ደረጃ ያለ አመራር አስፈላጊ ሲሆን ቢያንስ አንድ ደረጃ ወርዶ ለመስራት የሚያስችለዉ ብቃት ሊኖረዉ ይገባል የሚል፡፡

አንድ አመራር እታች የሚሰራዉን ስራ ጠንቅቆ የማያዉቅ ከሆነ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገዉን በራስ መተማመን ለመፍጠር እንደሚቸግረዉ በተግባር ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ወታደሮች አንዳችም የሚጠቀስ የግል ብቃት ከሌለዉ አዛዥ ይልቅ ቴክኒካል፣ ታክቲካልና ኮንሴፕቸዋል እዉቀትን አጣምሮ የያዘና ያለፍርሃት እርምት ለመስጠት የሚችል በራሱ የሚተማመን አመራርን የመከተልና የማክበር ዝንባሌ እንዳላቸዉ በተግባር ማረጋገጥ መቻላችን የጆቤ መሪህ ትክክለኛነት የሚያሳይ ነዉ፡፡

3.3/ እዉነትነት የሌለዉ የሀሰት ዘገባና የተጋነነ መግለጫ ያስቆጣቸዋል

ጆቤ ከሁሉም ባህሪያቸዉ ተጠቃሽ የሚሆነዉ እዉነትነት የሌለዉ የተጋነነ ሪፖርት እጅግ የሚያስቆጣቸዉ መሆኑን ነዉ፡፡ ድክመቱን ለመሸፋፈን ሆን ብሎ ከሚዋሽ ሰዉ ይልቅ እቅም አንሶኛልና አልቻልኩም አግዙኝ ቢሎ እዉነቱን የሚናገረዉን ያከብራሉ፡፡ በስብሰባ ላይ የዉሸት ሪፖርት ሲቀርብላቸዉ ተናደዉ ተናጋሪዎቹን በቁጣ ያስደነገጡበትን አጋጣሚዎች አስታዉሳለሁ፡፡

ጆቤ በተለይ አየር ኃይሉ ዉስጥ በተደጋጋሚ የአይሮፕላን ሆነ ሌላ አደጋ  ሪፖርት መስማት ያሰለቸቻቸዉን ያህል ሌላ መጥቀስ የሚቻል አይመሰለኝም፡፡ ሁልግዜም ስለተከሰተ አደጋ  መስማት አበሳጭቷዉ “የናንተ ሃላፊነት ስለደረሰ አደጋ ማዉራት ሳይሆን አደጋዉ እንዳይደርስ ማድረግ ነዉ ፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ችግር መስማት አልፈልግም” በማለት የሴፍቲና ኢንስፔክሽን ሃላፊዉን በቁጣ ያስደነገጡበትን አጋጣሚ አልዘነጋም፡፡

በርግጥም አየር ኃይሉ በፊትም ሆነ ዛሬም ሊለቀዉ ያልቻለ መጥፎ በሽታ ቢኖር ይሄዉ ስለ ደረሰ አደጋ ሪፖርት ማድረግ እንጂ አደጋን ለመቀነስ ወይንም እንዳይደርስ ማድረግ አለመቻሉ ነዉ፡፡

3.4/ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ጆቤ ሁሉም ቦታ አይታጡም

አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ከቢሮአቸዉ መውጣት የማይፈልጉና ሰራዊታቸዉ ያለበትን ሁኔታ በሪፖርት ከሚቀርብላቸዉ ዉጭ እታች ወርደዉ እየጎበኙ በዓይናቸዉ ለማዬትና ሰራዊታቸዉን የማነጋገር ልማድ የሌላቸዉ እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አመራሮች ተጨባጭ ሁኔታዉ ጋር ስለማይተዋወቁ ራሳቸዉንና የሚመሩትን ተቋም ለዉድቀት ይዳርጋሉ፡፡ ይህ ችግር በተግባርም ደርሶ አይቻለሁ፡፡

ከዚህ አኳያ የጆቤ ሁኔታ ሳስታዉስ እንዳደንቀቸዉና እንዳከብራቸዉ ያስገድደኛል፡፡ ጆቤ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ አስከታችኛዉ የስራ አካባቢ ድረስ በመገኘት ስራዎች እንዴት እንደሚሰሩ የመጎብኘትና ከሰራዊቱ ጋር የመመካከርና የሚቀርብላቸዉ ጥያቄ ካለም ያለ አንዳች ቢሮክራሲያዊ ማንዛዛት እዚያዉ ዉሳኔና ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ የጆቤን ጉብኝት አመራሩም ሰራዊቱም በደስታ ነዉ የሚጠብቁት፡፡

በጦርነቱ ጊዜ ጄ/ል አበበ በጦርነቱ ቀጠና  በሳቸዉ አመራር ስር ባሉ የጦር ክፍሎች ዘወትር ይገኙ ነበር፡፡ ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸዉ የዉጊያ ልምምዶች ሲደረጉ ጄ/ል አበበ ከአሃዱዎች (ዩኒቶች) ባንዱ ዉስጥ አይታጡም፡፡ አዳዲስ ስልቶችና የዉጊያ ጥበቦችንና ትጥቆች እሳቸዉ በሚገኙበት ወቅት መፈተሽ የተለመደ ነበር፡፡ እንደ ሞዴል የሚታይ አስኳድሮንና ፍላይት የመፍጠርና ከቦታ ወደ ቦታ በማዘዋወር በተለያዩ የጠላት ሁኔታና (situation) የመሬት አቀማመጥ ሁኔታዎች ዉስጥ እንዲሰራና ልምድ እንዲያካፍል የማድረግ አሰራርም ነበራቸዉ፡፡

ጆቤ የዉጊያ ልምምዶች ሲደረጉ በሶስተኛ ወገን በኩል በሪፖርት ከመስማት ይልቅ እዚያዉ በቦታዉ በአካል ተገኝተዉ መመልከትና ከልምምዱ በኋላም በመገምገም ጠቃሚ መመሪያ የመስጠት መልካም ተሞክሮ አዳብረዋል፡፡ በተለይ በጦርነቱ ወቅት በሰሜን አየር ምድብ ማዘዣ ጣቢያም ሆነ በየእስኳድሮኑ እየተገኙ እኛ ባለሙያዎቹ ሊታየን ያልቻለዉን በርካታ እርምት በመስጠትና ሰራዊቱን በማበረታታት የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነበር፡፡

በጠቅላይ መምሪያ ቢሮ ተጎልቶ እዉነትነት የሌለዉ ሪፖርት ከመቀበል ዉጭ የአየር ኃይል ሰራዊት ለግዳጅ በሰፈረበት ቦታ በየምድቡና በየስኳድሮኑ በመገኘት ሰራዊቱን ለመጎብኘትና መመሪያ ለመስጠት ፈጽሞ የማይሹ አመራሮችን ካየን በኋላ ነዉ ጆቤ ሊከበሩ የሚገቡ መሆናቸዉን ለመረዳት የቻልነዉ፡፡

ሌላዉ ቀርቶ በርካታ አይሮፕላን በአንድ ግዜ የሚሳተፍበት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠዉና እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቅ አደገኛም የሆነ የዉጊያ ልምምድ በሚደረግበት ግዜ በቦታዉ ተገኝተዉ ለመከታተል የማይሹና ሃላፊነታቸዉን በቅጡ ያልተረዱ አመራሮች በአንድ ወቅት እንደነበሩ አስታዉሳለሁ፡፡

3.5/ ግልጽና ጥርት ያለ ትዕዛዝ አሰጣጣቸዉና ግዳጅን በሚመለከት በቸልታ ንቀዉ የሚያልፉት አንዳችም ነገር አለመኖሩ

የጆቤ ሌላዉ ጠንካራ ጎን ለትዕዛዝ ተቀባዩ ግልጽና ጥርት ያለ ትዕዛዝ አሰጣጣቸዉና የቀረበላቸዉን ጉዳይ ላይ ሳያጓትቱና ሳያንዛዙ ወዲዉኑ ፈጣን ዉሳኔ መስጠት መቻላቸዉ ነዉ፡፡

ከጆቤ ባህሪያት ሁሉ አንድ የሚስደስተኝ ነገር ቢኖር በጽሁፍ የቀረበላቸውን ሪፖርት ወይም የጥናት ዉጤት የሆነ ጽሁፍ (ጽሁፉ የቱንም ያህል ቢረዝም) በትዕግስት አንድ በአንድ አንብበዉ ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም ማስተካከያ በሚፈልግና  የማያምኑበት ጉዳይ ሲያገጥማቸዉ  በየመስመሩ ላይ በቀይ ቀለም “ለምን? እንዴት? መቼ? ማን?” ወዘተ የመሳሰሉ አፋጣጭ ጥያቄዎችን መጠየቃቸዉ የተለመደ ነዉ፡፡

በዚህ ምክንያትም ለሳቸዉ በሚቀርብ ጉዳይ ላይ ጠንቀቅ ቢሎ ተጨንቆ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ከአንድ ገጽ የማትሞላ ጽሁፍ ሪፖርት ለማንበብ ትእግስት የለላቸዉን አንዳንድ አመራሮች ካየሁ በኋላ ነዉ ጆቤ አንዳችም ጉዳይ በቸልታ አንደማያልፉ የተገነዘብኩት፡፡ በመስክ ጉብኝት ወቅትም ሆነ በእለታዊ ስራቸዉም ላይ ቢሆን እያዩ በዝምታ የሚያልፉትና መፍትሄ ሳያስቀምጡለት ንቀዉ የሚተዉት ምንም ነገር የለም፡፡

3.6/ ለሙያተኞች የሚሰጡት ከበሬታ

ጆቤ ሌላዉ የሚደነቅ የአመራር ብቃታቸዉ ማሳያ የሚሆነዉ ለባለሙያዎች አሰተያየት ትልቅ ከበሬታ መስጠታቸዉ ነዉ፡፡በየግዜዉ በሚደረጉ የእስታፍ ስብሰባዎች ላይ ከመምሪያ ሃላፊዎች አንድ ደረጃ ወደታች የሚገኙ ልዩ ልዩ ባለሙዎችም እንዲገኙ በማድረግ ሙያቸዉን በሚመለከት የመሰላቸዉን አስተያየት እንዲሰጡ ስለሚያበረታቱ ባለሙያዎች በሳቸዉ ዘንድ ሞገስ በማግኘታቸዉ በሙያቸዉ ከፍተኛ ደስታ እንዲሰማቸዉ ያደርጉ ነበር፡፡

ጆቤ ለርካሽ መወደድ ብለዉ አጉል ከሚያሽቋለጥላቸዉ ይልቅ ፊት ለፊት በሃሳብ የሚጋተራቸዉን ባለሙያ እጅግ አድርገዉ ያከበራሉ፡፡ ማንም ሰዉ ጠቃሚ የመሰለዉን አስተያየት በነጻነት መስጠት ይችላል፡፡ መጠንቀቅ የሚያስፈልገዉ አንድ ነገር ቢኖር አለመዋሸት ብቻ  ነዉ፡፡

 

4/ የጆቤ አንዳንድ እንከኖች

4.1/ አዉቴሪቴሪያን ዓይነት የአመራር ዘይቤ

ጆቤ ትንሽ አዉቶሪቴሪያን ዓይነት የአመራር ዘይቤ የነበራቸዉ ይመስለኛል፡፡ ፈልገዉት ይሁን የአጋጣሚ እንደሆን ለመናገር ባልችልም በከፍተኛ ደረጃ የመከበርና የመፈራትን ባህሪይ አጣምረዉ የያዙና በሂደትም ያዳበሩት ስለሚመስለኝ  ለብዙዎቻችን charismatic የሚባለዉ ዓይነት አመራር እንዳልነበሩ አስታዉሳለሁ፡፡

 4.2/ እጅግ የተጋነነ የግል ደህንነት ጥበቃ ማድረጋቸዉ

ጆቤ አንድ ብዙዎቻችንን በወቅቱ ያልወደድንላቸዉ ምናልባትም ያስከፋን የነበረ ባህሪቸዉ ለግል ደህንነታቸዉ ከሚገባዉ በላይ መጨነቃቸዉና እጅግ የተጋነነ ጥበቃ እንዲደረግላቸዉ ማስደረጋቸዉ ነዉ፡፡ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ መኖሪያ ቤታቸዉ ዘወትር ማለዳ ወደ አየር ኃይል ደብረዘይት ሲመጡ የነበረዉን ትዕይንት ሁሉም ሰዉ ያስታዉሰዋል፡፡

አንድ ፓትሮል ከአዲስ አበባ ወደ ደብረዘይት የተወሰነ ርቀት ሲቀር አጅቦ ካደረሳቸዉ በኋላ ሲመለስ ሁለተኛዉ ፓትሮል ደግሞ በአስደንጋጭ ፍጥነት  አንደ ሚግ እየበረረ የአየር ኃይሉን  ዋና በር (ተከፍቶ ስለሚጠብቀዉ) ፍጥነቱን ሳይቀንስ ግቢ ገብቶ ጠቅላይ መምሪያ ፊት ለፊት ይቆማል፡፡ ከዚያም ልዩ ጠባቂያቸዉ በፎቁ መዉጫ ደረጃዉ ላይ ያገኘዉን ሰዉ ሁሉ እየገፈታተረ አንደኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘዉ ቢሮአቸዉ በሩጫ ቀድሞአቸዉ ይሄዳል፡፡ ወደ ግቢ ሲገቡ የሳቸዉ አጀብ በሚያልፍበት ወቅት እግረኛም ሆነ  ባለመኪና  ወደ ዳር ፈጥኖ በመዉጣት ማሳለፍ አለበት ፡፡ ያለዚያ ሊገጭ ይችላልና፡፡

ሌላዉ ቀርቶ እዚያዉ እሳቸዉ በሚያዙበትና እጅግ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት አየር ኃይል ግቢ ዉስጥም እንደልባቸዉ ነጻነት ተሰምቶአቸዉ አይንቀሳቀሱም ነበር፡፡ ለምሳሌ አልፎ አልፎም ቢሆን በእረፍትና በስፖርት ሰዓት እዚያዉ ግቢ ዉስጥ የሚገኝ እግር ኳስ ሜዳ በትራኩ ላይ በሚሮጡበት ወቅት ይሄዉ አጃቢያቸዉ መሳሪያ አንግቶ ከኋላ ከኋላቸዉ መከተል ነበረበት፡፡ ሁኔታዉ ለተመልካች ምቾት የማይሰጥ መጥፎ ክስተት ነበር፡፡

ጆቤ ከሌሎቹ በማእረግም በሃላፊነትም አቻዎቻቸዉ ከሆኑት በተለየ ለግል ደህንነታዉ የዚያን ያህል የተጨነቁበትና በወቅቱ የሚሰጉበት ነገር ምን እንደነበረ  እስከዛሬም አይገባኝም፡፡

4.3/ በጆቤ አመራር ዘመን በርካታ የፍትህ እጦትና የመልካም አስተዳዳር ችግሮች ነበሩ

በጆቤ አስተዳደር ዘመን የፍትህ ጉዳይ ከፍተኛ ችግር የነበረበት ነዉ፡፡ የሰራዊቱ አባላት ያለአግባብና በሰበብ አስባቡ እየተያዙ ያለጥፋታቸዉና ያለፍርድ ታስረዉ ለአመታት እንዲማቅቁ ይደረጋሉ፡፡ የግል ጠባቂዎቻቸዉና የግቢዉ የጥበቃ ክፍል አለቅጥ መረን የለቀቀ ስልጣን ሰለተሰጣቸዉ በሳቸዉ እዉቅና ይሁን አይሁን ባላዉቅም አለአግባብና ያለፍርድ የሰራዊቱ አባላት የሚታሰሩበት ሁኔታ እጅግ አስቀያሚ ክስተት ነበር፡፡ የመልካም አስተዳዳር ችግርም እጅግ ስር ሰደደ ስለነበር ሰራዊቱ ምሬትና ብሶት ያሰማ ነበር፡፡

ጆቤ በደንብ ያለጤኑት ሌላ ችግር ቢኖር በሳቸዉ ስም ብዙ ነገር ይሰራ እንደነበር ነዉ፡፡ የሳቸዉ ስም ካልተጠራ ወይም ጆቤ ነዉ ያዘዘዉ ካልተባለ በስተቀር ለመንግስት ስራ አንድ ጉዳይ ጠይቆ ማስፈጸም የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ አሳቸዉ አዘዋል ተብሎም ለግል ጉዳይ የመንግስት ገንዘብና ንብረትም ይባክን ነበር፡፡ በየግዜዉ አለቅጥ የተንዛዛ ግብዣና ተሃድሶ  ወዘተ እየተባለ የተጋነነ ወጪ ይወጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡

4.4/ ከጠላት ባላነሰ የራሳቸዉን ስታፎችና አመራሮችን ያሰልሉ ነበር

አንድ አስቀያሚ ነገር ቢኖር ጠቅላላ የአየር ኃይሉ ከፍተኛ መኮንኖች በየእለቱ የሚደርጉት የስልክ ንግግር በቋሚነት እንዲጠለፍ በማድረግ ማን ምን እንደተናገረ በሰራዊቱ ዉስጥ አስቀያሚ የስለላ ስራ እንዲሰራ አድርገዋል፡፡ የመረጃ የደህንነት ሰራተኞች ዋነኛ ስራ የነበረዉ ከዉጭ ጠላት ይልቅ የሰራዊቱን አባላት በተለይም ከፍተኛ መኮንኖችን መሰለል ነበር፡፡

ይሄ የስልክ ንግግርን የመጥለፍ ጉዳይ መኖሩ ለመጀመሪያ ግዜ የታወቀዉ እሳቸዉ ከቦታዉ ከተነሱ በኋላ ሲሆን በወቅቱ  ድርጊቱ ለአጭር ግዜ እንዲቋረጥ መደረጉ ባይቀርም እሳቸዉ ምትክ ሌላ ሰው ከተተካ በኋላ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጠለፋዉ እንዲያዉም በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል መደረጉ ይታወሳል፡፡

5/ ማጠቃለያ

ሜ/ጄነራል  አበበ እንደማንኛዉም ሰዉ የሰሩት ስህተት ወይም ድክመት ባይጠፋባቸዉም ነገር ግን አየር ኃይሉን በሁለት እግሩ እንዲቆምና ወደ ቀድሞዉ ከብሩ እንዲመለስ በማድረግ በተለይም የኤርትራን ወረራ ለመመከት በተደረገዉ ጦርነት አየር ኃይሉን ለግዳጅ በማዘጋጀትና አመራር በመስጠት ረገድ ያደረጉት አስተዋጽኦ መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ጆቤ ከጦርነቱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በመነሳታቸዉ በፊት ጀምረዉት የነበረዉን አየር ኃይሉን የማጠናከር ስራ ከዳር ሳያደርሱና ዉጠቱን ሳያዩ ነዉ አይር ኃይሉን ለመልቅ የተገደዱት፡፡ ጆቤ አየር ኃይሉን ከለቀቁ በኋላ ትኩረታቸዉን ወደ ትምህርት በማድረግ ድሮ ከትግሉ በፊት አቋርጠዉት የነበረዉን የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸዉን በመቀጠል ለማስተርስ ድግሪ የበቁ ሲሆን ለሶስተኛ ድግሪ እየተዘጋጁ መሆናችዉን ሰምተናል፡፡

ጆቤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀገራቸዉን በሚመለከት ጠቃሚ የሆነ አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ በተለይም የሀገሪቱ የመከላከያና የደህንነት ዘርፉ ሊኖረዉ በሚገባ ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ ተጠያቂነት ዙሪያ እንዲሁም የሀገሪቱ ሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም በበለጠ በሚመከበርበት አግባብ ላይ ጠንካራ አስተያየት በመስጠት የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ጆቤ በተገኘዉ የግል ሚዲያ የሚሰጡት አስተያያት ላነበበ ሰዉ የቀድሞ ድርጅታቸዉንና መንግስትን በነገር ጠቀም የሚያደርግ አስተያየቶች ባይጠፋበትም በአብዛኛዉ ግን ሚዛናዊነት ያለዉና በምሁርነታቸዉ እዉነቱን ለማሳየትና ከችግር መዉጫ መንገዱን ለማማላከት ከመሞከራቸዉ በስተቀር እስካሁን የተቃዉሞ ፖለቲካ ጎራ ለመቀላቀላቸዉ አንዳችም ፍንጭ የለም፡፡

ጆቤ በአመለካከት ልዩነት የተነጠሉትን ቀድሞ ድርጅታቸዉን ሆነ አንዳችም እምነት የማይጣልባቸዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ንክኪ የሌላቸዉና ለማንም አፈቀላጤ ሳይሆኑ በምሁርነታቸዉና በዜግነታቸዉ ብቻ የሚሰጡት ነጻ አስተያየት የበለጠ ተደማጭነት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተረፈ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎአቸዉን በዉስን ዘዴዎች (በጽሁፍ) ብቻ ከሚገድቡት ሰፊ ተደራሽነት ባላቸዉ አንዳንድ መድረኮች ላይ ሰፋና ጠለቅ ያለ ጥናታዊ ስራዎችን በማቅረብ መሳተፍ ቢጀምሩ ጠቀሜታዉ የጎላ እንደሚሆን ጥርጥር የለዉም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ቢሆኑ በወታደራዊ፣ በሴኩሪቲ፤ በሀገር ደህንነትና ዓለምአቀፍ ህግን ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች  ላይ በተግባርም በትምህርትም ሰፊ ተሞክሮ ያለዉን እንደ ሜ/ጀነራል አበበ (ጆቤ) ዓይነቱን ለእንጀራ ብሎ ሳይሆን  ለእዉነት ብሎ የሚሰራ ያለፍርሃትና ያለመሸመቀቅ እዉነትና እዉነትን ብቻ የሚያማክር ምሁርን በአማካሪነት ለመጠቀም ቢሞክሩ ለሀገሪቱ ጠቀሜታዉ የጎላ ነዉ ብዬ አስባለሁ፡፡

/ /  በዛብህ ጰጥሮስእንደወጣ ሳይመለስ የቀረዉ ጀግና

የአየር ኃይላችን የጦርነት ታሪክ ከተነሳ ሳይጠቀስ ማለፍ የማይቻለዉና ብዙዎቹን ቅር ያሰኘ ነገር ቢኖር የራሱን ጀግኖች እዉቅና ሰጥቶ ማክበርና በታሪክ እንዲታወሱ ማድረግ አለመቻሉ ነዉ፡፡ ለመሆኑ አየር ኃይሉ ለአሁኑ ትዉልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪዉም ትዉልድ የኩራት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ምርጥ ጀግኖቹን አስቧቸዉ ያዉቃል?

አየር ኃይሉ እንደነ ጄ/ል ለገሰ ተፈራ (የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ ተሸለሚ የነበሩ በሶማሊያ ጦርነት ወቅት ብቻቸዉን ስድስት የጠላትን አይሮፕላኖች በማደባየት ተአምር የሚሰኝ ገድል የፈጸሙና በመጨረሻም ተመትተዉ ወድቀዉ በጠላት ሰራዊት እጅ ወድቀዉ ለአስራ አንድ ዓመታት በሶማሊያ  እስር ቤት ሲሰቃዩ ኖረዉ በመጨረሻም ለመለቀቅ የበቁና በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ)፤ እነ ጄ/ል ተጫነ መስፍን (ከኤርትራ ጋር በተደረገዉ ጦርነት የኢፌድሪ አየር ኃይልን በማዘጋጀት ረገድ ጄ/ል አበበን በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉና በአለፈዉ መንግስትም ቢሆን በሰሩት የጀግንነት ስራ የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን የበቁ)፣ ብ/ጄ አሸናፊ ገ/ጻዲቅ፤ ሻለቃ ጥላሁን ቦጋለ፤ ብ/ጄ ብርሃኑ ዉቤነህ፤ ብ/ጄ ተሻለ ዘዉዴና ብ/ጄ ንጉሴ ዘርጋዉ (በ81 ኩዴታ ወቅተ በግፍ የተገደሉ) ወዘተ የመሳሰሉ በርካታ ምርጥ ጀግኖች ባለቤት የሆነ ተቋም ነዉ፡፡

እነዚህን ጀግኖች አለማክበርና በታሪክ እንዲታወሱ አለማድረግ የሚቻል አይደለም፡፡ ሌሎቹን ለጊዜዉ ትተን በዚህ ስርአትና መንግስት ወቅትም ሲያለግል የነበረዉና ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ጦርነት በሻዕቢያ አየር መቃወሚያ ተመትቶ ሻእቢያ እስር ቤት ገብቶ ለዓመታት ሲያሰቃዩት ቆይተዉ በመጨረሻም የገደሉትን ኮሎነል በዛብህ ጰጥሮስን አየር ኃይሉ በተገቢዉ መንገድ አስታዉሶት ያዉቃል?

ኮ/ል በዛብህ በተለያዩ መንግስታት ዘመን ሁሉ ለሀገሩ በጀግንነት ሲዋጋ የነበረና በስነምግባሩ፤ በሙያ ብቃቱና ለሀገሩ ባለዉ ጥልቅ ፍቅር አሁን ላሉትም ሆነ ለወደፊቱ ወጣት ፓይለቶች ተምሳሌትና አርአያ የሆነ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅ ለማስታወሻ የሚሆነዉ በስሙ አንድ ነገር እንኳን ተደርጎለታል?

በዛብህ በ1969/70 በሶማሊያ ወረራ ወቅት የሀገሩን ዳር ድንበርና የአየር ክልል ለማሰከበር ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረጉ የአየር ኃይላችን ጀግኖች አንዱ ሲሆን በወቅቱ የሰራዉን ጀግንነት እንኳን እኛ ኢትዮጰያዉን ቀርተን ራሳቸዉ ሶማሊያዉን ቢጠየቁ መናገር የሚችሉት ነዉ፡፡ በዛብህ ጵጥሮስን የለገሰ ተፈራን የተጫነንና የሌሎችንም የአየር ኃይል ጀግኖች  ጀግንነት አንድ የድሮ የዚያድ ባሬ ዘመን ወታደርን አግኝተን ብንጠይቀዉ አሳምሮ ሊነግረን ይችላል፡፡

ይህ ጀግና በዛብህ በህይወት ትንሽ ግዜ ቢቆይልን ኖሮ በርካታ ተተኪ  ጀግኖችን በራሱ አምሳያ በመቅረጽ ብዙ መስራት በቻለ ነበር እያልን እንዲህ በጥድፊያ ማጣታችን በጣም ያስቆጨናል፡፡ በተለይ አየር ኃይሉን እንደገና በማጠናከር ሂደት በዛብህ በአካል ቢኖር ሊሰጥ ይችል የነበረዉን አበርክቶት ሲታሰብ እሱን ማጣት በጣም የሚያስቆጭ ነዉ፡፡

ኮ/ል በዛብህ በበረራ ችሎታዉ ምስጉን የሆነና በተለያዩ ግዳጆች ላይ በመሰማራት አኩሪ ስራ የሰራና ለሀገሩ አለኝታነቱን ያረጋገጠ ዉለታዉ መቼም ቢሆን የማይረሳ ጀግና ሲሆን ለሀገሩ በሰራዉ ስራም ተገቢዉ እዉቅና ተሰጥቶት ባለፈዉ መንግስት ዘመን የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ነዉ፡፡

ይህ ጀግና በስሙ ሃዉልት ባይቀረጽለት እንኳን ሌላዉ ቀርቶ ለዘመናት ባገለገለበት አየር ኃይል ዉስጥ የሚታወስበት በስሙ የሚጠራ አንድ ነገር እንኳን አለመሰየሙ እጅግ የሚያሳዝን ነዉ፡፡ ከአየር ምድቦቹ ዉስጥ አንዱ ወይም የአየር ኃይል ስልጠና ማዕከል ሌላዉ ቢቀር አንድ በረራ ስኳድሮን  በስሙ ቢጠራና ታሪኩ በሚገባ ተቀምሮ ቢጻፍ የሚቃወም ሰዉ ያለ አይመስለኝም፡፡

የእነ ኮ/ል በዛብህንና ሌሎቹንም ጀግኖች ስም ሳይጠራና የጀግንነት ታሪካቸዉ ሳይወሳ እንዴትስ ተደርጎ ነዉ የወጣት ፓይለቶችን የዉጊያ ሞራልና የሀገር ፍቅር ስሜት ማነሳሳት የሚቻለዉ? በማንስ አርአያነት ነዉ የምንቀርጻቸዉ? በዛብህ እኮ ባለፈዉ ስርአት ለኢትዮጵያ አንድነት ከሻእቢያ ጋር ሲዋጋ ተመቶ በመዉደቁና በሻዕቢያ ተማርኮ በሳህል የበረሃ አስር ቤት ለ8ዓመታት ሲሰቃይ ኖሮ ደርግ ከወደቀና መንግስት ከተቀየረ በኋላ ነበር ዳግመኛ ቢያገኙት እንደሚገድሉት በግልጽ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነው የተለቀቀዉ፡፡

የታዋቂዉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የፕሮፈሴር በየነ ጰጥሮስ ታናሽ ወንድምና የሶስት ወንዶችና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የነበረዉ ኮ/ል በዛብህ በሻእቢያ ከተሰጠዉ ማስጠንቀቂያ ሌላ በቤተሰቡና ወዳጅ ዘመድ ጭምር ወደ አየር ኃይል እንዳይገባ ቢማጸኑትም ከአየር ኃይል ዉጭ ህይወት የማይታሰብ ለሆነበት በዛብህ የቤተሰብ ምልጃ ሳያግደዉ ፈጥኖ ወደ ቀድሞ እናት ክፍሉ ወደ አየር ኃይል ለመቀላቀል ችሏል፡፡ ኮ/ል በዛብህ ወደ አየር ኃይል የተመለሰዉ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስወሩት  በማንም አስገዳጅነት ሳይሆን በራሱ ፈቃድ ነዉ፡፡

በዛብህ ወደ አየር ኃይል ከተመለሰ በኋላ  አዲስ ተተኪ ወጣቶችን በበረራ ለማሰልጠን ባህርዳር በግዜያዊነት ተመድቦ ለጥቂት ወራት በቆየበት ወቅት በቅርበት እንዳጠናሁት በዛብህ ለቤተሰቡ ልዩ ፍቅር የነበረዉና ናፍቆታቸዉን እንኳን ገና ያገልጠገበ በመሆኑ በየእለቱ ወደመኝታ ክፍሉ በገባሁ ቁጥር በጽህፈት ጠረጰዛዉ ላይ በትልቁ አሳድጎት ያስቀመጠዉ ከቤተሰቡ ፎቶግራፍ ላይ ዓይኑ ሳይነቀል የሚያወጋኝ ለቤተሰቡ የነበረዉን ከፍተኛ ፍቅር ነበር፡፡

በዛብህ በወቅቱ እኔ ብዙም ያላጤንኩትና በዚያን ግዜ ፋይዳዉ ብዙም አልታይህ ቢሎኝ የነበረዉ የፌዴራላዊ ስርአት ጉዳይ በዛብህ ግን በስርአቱ እጅግ ደስተኛ ከመሆኑም ሌላ በከፍተኛ ሁኔታ ስሜቱን የነካዉ አጋጣሚ ደግሞ የደቡብ ክልል ተወላጅ የሆኑ በርካታ አዳዲስ ወጣት ወታደሮችን በጦር ካምፑ ዉስጥ መመልከቱ ነዉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ስለበዛብህ ማንነት አንድ ግዜ ከተረዱ በኋላ ዘወትር ምሽት ከስራ መልስ ቋሚ ስራቸዉ የሆነዉ ከእሱ ጋር ማዉጋት ነበር፡፡ እሱም በሁኔታዉ እጅግ ደስተኛ እንደነበር ለመረዳት አላዳገተኝም፡፡ በዛብህ ሁልግዜም የሚያወጋቸዉና የሚመክራቸዉ ጀግና ወታደር እንዲሆኑ፤ ራሳቸዉን በትምህርት እንዲያሻሽሉና ለዲስፕሊን ተገዢ እንዲሆኑ ነበር፡፡

በዛብህ ከሌሎች በሱ ደረጃ ከነበሩት ነባር ፓለቶች ለየት የሚያደርገዉና ይበልጥ እንድወደዉ ያደረገኝ ሁኔታ ለአየር መከላከያ የሚሰጠዉ ትኩረት ከፍተኛ መሆን ነዉ፡፡

ብዙዎቹ ነባር የአየር ኃይላችን ፓይለቶችም ሆኑ አመራሮች ለአየር መከላከያ ግዳጅ ብዙም ግድ የሌላቸዉ ነበሩ፡፡ የጠላትንም ሆነ የወገንን አየር መከላከያ ሊያበረክት ስለሚችለዉ አስተዋጽኦ ተገቢዉ ግንዛቤ አልነበራቸዉ፡፡ በዛብህ ግን ለየት ይላል፡፡ በተለይ በየዕለቱ ለስልጠና በረራ ባደረጉ ቁጥር የነበረዉን የበረራ ሁኔታ የሚያሳይ ንድፍ አዘጋጅተን ማዘዣ ጣቢያ ጋብዤዉ ከተመለከተ በኋላ እጅግ በመደነቅ “በቃ ያደረግነዉን በረራና የደረስንበት ቦታ ሁሉ ከናንተ የሚሰወር አንድም ነገር የለም ማለት ነዉ?“ ብሎኝ ነበር፡፡ ከዚያች ቀን በኋላ አየር መከላከያ የተመደቡ ወጣት የኢህአዴግ ታጋዮች የነበሩና አዲስ የተቀጠሩትን ጨምሮ በአይሮፕላን አጋዥነት ለማለማማድ በጠየኩት ቁጥር እጅግ ተባባሪ ነበር፡፡

እዉነት ይሁን አይሁን ባላዉቅም ኮ/ል በዛብህ በታላቅ ወንድሙ ምክንያት በቋሚነት ክትትል እንደሚደረግበት ብዙ ሰዎች ቢያስጠነቅቁትም እሱ ግን በወንድሜ ምክንያት እኔን የሚያሰጋኝ አንዳችም ምክንያት የለም በማለት አጅግ ተረጋግቶ ነበር ስራዉን ሲሰራ የነበረዉ፡፡

በዛብህ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ ስለነበር ባህርዳር በነበረበት ወቅት ሁልግዜ እሁድና በሌሎች የእረፍት ቀናት እኔ ነበርኩ ወደ አምልኮ ቦታ የማመላልሰዉ፡፡ ለዚያዉም ካላደረስኩህ እያልኩት በእኔ ጉትጎታ እንጂ እሱ ግን ማንንም ማስቸገር ስለማይፈልግ በእግሩ ያን ሁሉ ርቀት ለመጓዝ ዝግጁ ነበር፡፡

ጀግናዉ ኮሎነል በዛብህ ጰጥሮስ  ወደ አየር ኃይል ከተቀላቀለ በኋላ አዲስ ወጣት ፓይለቶችን ለማፍራት በስልጠና ተጠምዶ በነበረበት ወቅት ነዉ የሻእቢያ ድንገተኛ የጥቃት ወሬ የተሰማዉ፡፡ ከወዳጅ ዘመድ የተሰጠዉን ማስጠንቀቂያና በሻእቢያ አስር ቤት የደረሰበትን የአመታት የስቃይ ህይወት ፈጽሞ ባይረሳም ነገር ግን ከሀገር ሉአላዊነት የሚበልጥበት አልነበረምና የሻዕቢያ አይሮፕላኖች በመቐለ አይደር ህጻናት ተማሪዎች ላይ ያደረሱትን ግፍ በማዬት እልህ ተናንቆት የሻዕቢያን ማስጠንቀቂያም ከቁብ ሳይቆጥር ሻዕቢያን ሊቀጣና ቁጭቱንም ሊወጣ ሲሄድ ነዉ ተመትቶ በድጋሚ በእጃቸዉ ሊወድቅ የቻለዉ፡፡

በዛብህ በአስመራ አየር ኃይል ጣቢያ የልቡን ካደረሰ በኋላ በሰላም መመለስ እየቻለ ነገር ግን በሻእቢያ ላይ ያደረሰዉን ጉዳት ተመልክቶ እርግጠኛ መሆን እንዳለበት በመገንዘብ  ለወትሮዉ መዉሰድ የሚገባዉን ጥንቃቄ ሁሉ ችላ በማለት እጅግ ወርዶ ለአየር መቃወሚያ ተኩስ በመመቻቸቱ ተመትቶ ያ ጀግና ዳግመኛ በሻዕቢያ እጅ ወደቀ፡፡

በዛብህ እንደተመታ በፓራሹት የወረደዉ አስመራ ገጠራማ የገበሬ መንደር ዉስጥ ስለነበር ቀድመዉ ያገኙት ገበሬዎች ነበሩ፡፡ በወቅቱ በዛብህ እጁን ላለ መስጠት በያዘዉ ሽጉጥ እስፈራርቶ ለማምለጥ መሞከሩ ባይቀርም ነግር ግን ሊሳካለት ባለመቻሉ በቁጥጥር ስር አድርገዉታል፡፡

ከዚያ ዘግይተዉ የደረሱ ሌሎች ሰዎች በመኪና ጭነዉት ወደ አስመራ ከተማ ሲወስዱት አንዱ ለምን አስመራ ድረስ መጥቶ በአየር ለማጥቃት እንደተነሳሳ ሲጠይቁት በዛብህ በአይደር ህጻናት ላይ የደረሰዉን ግፍ ባማስታወስ በጣም በተረጋጋ ሁኔታ ሆኖ “የናንተ አይሮፕላን መቀሌ ላይ ብዙ ጉዳት አድርሷል ድጋሚ ተመሳሳይ ጉዳት አንዳይደርስ ለማድረግ ወታደራዊ ኢላማዉን ለመምታት ነዉ ፡፡ ሲቪሉን ኢላማ አላደረኩም” ቢሎ መልሶለታል፡፡

በዚህ ግዜ ሁሉ በወቅቱ አብሮት በመኪና እየተጓዘ የነበረዉ ጠያቂ ይህ ፓይለት በሳህል አስርቤታቸዉ በእስረኝነት ብዙ ዓመታት አቆይተዉት ከአመታት በፊት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዉ የለቀቁት በዛብህ የሚባለዉ አብራሪ መሆኑን አላወቁም አልጠረጠሩምም ነበር፡፡

በኋላ ግን በዛብህን ይዘዉ ወደ አስመራ መሃል እንደገቡ አንድ ተመቶ የወደቀ ፓይለት ስለ መኖሩን የሰማዉ የአስመራ ህዝብ እሱን ለማየት ከየቤቱ እየወጣ እንዲሁም በርካታ መኪናዎቻቸዉ ግፊያ ትልቅ ትርምስ እየተፈጠረ በነበረበት ሰዓት በመካከሉ ዘግይቶ የደረሰዉ የድምጺ ሃፋሽ (የኤርትራ ራዲዮ) ጋዘጤኛ የነበረዉ አስመሮም በዛብህን ገና እንዳየዉ ለይቶት  በመደነቅ ስሜት ሆኖ “…እንዴ ሻለቃ በዛብህ! አሁንም በድጋሚ ተመልሰህ መጣህ እንዴ?” ሲለዉ በዛብህ በራስ መተማመን ባልተለየዉ መንፈስ “እኔ ኮሎነል በዛብህ ነኝ እንጂ ሻለቃ በዛብህ አይደለሁም” በማለት ነበር የመለሰለት ፡፡

ጋዘጤኛዉም “ አሃ ለካስ ኮሎነል ሆነሃልና” ብሎ እንደማሽሟጠጥ መልክ መልሶ  ተናገረዉ፡፡ በዛብህን ይዘዉት እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ሲወድቅ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በክንዱ አካባቢ ከሚሰማዉ ህመም ስሜት በስተቀር አንዳችም የፍርሃት ስሜት አይታበትም ነበር፡፡

እንዲያዉም “ሰምበል” በሚባለዉ አካባቢ በብዛት ተገንብተዉ የተመለከታቸዉን ድሮ የማያዉቃቸዉን አዳዲስ ህንጻዎች በመደነቅ ስሜት ከመመልከትና ኑሮ በአስመራ ምን እንደሚመስል እየጠየቃቸዉ ለማወቅ ሲሞክር እንጂ ምን ሊያደርጉኝ ይችሉ ይሁን ብሎ አንዳችም የስጋትና የፍርሃት ስሜት አይታይበትም ነበር፡፡ የበዛብህ መረጋጋትና ለፍርሃት ቦታ አለመስጠት አጋቾቹን ሳያስገርማቸዉ አልቀረም፡፡

በኋላ ላይ ተመትቶ የወደቀው ፓይለት በዛብህ መሆኑ እንደተሰማ የአስመራ ህዝብ በነቅስ ወጥቶ እሱን ለመመልከት በመሞከር ትርምስ ተፈጠረ፡፡ በዛብህ በዚያኑ ዕለት የተወሰደዉ በቀጥታ ወደ ኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቅ ጽ/ቤት ነበር፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ በዛብህ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሳይታወቅ ለብዙ ግዜ ቆይቶ ነበር፡፡

ከበዛብህ ጋር በተያያዘ በርካታ መሰረተ ቢስ አስተያየቶችና ሃሜቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በዛብህ ለመመታት የበቃዉ ሆን ተብሎ መረጃዉ ለሻእቢያ እንዲደርሳቸዉ በመደረጉ ነዉ ከሚለዉ አሉባልታ ጀምሮ የአትዮጵያ መንግስት በዛብህን ለማስለቀቅም ሆነ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ አንዳችም ጥረት አላደረገም አስከሚለዉ ዉንጀላ ድረስ ብዙ ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በቀይ መሰቀል በኩል ለማስለቀቅና ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ብዙ እንደጣረ በግልጽ የሚታወቅ ነዉ፡፡ በመጨረሻም አንድ የአለም ቀይ መስቀል ተወካይ የሆነ ጄ/ል አለምሸት ደግፌ አዛዥ በነበሩበት ወቅት ወደ አየር ኃይል ጠ/መምሪያ ደብረዘይት መጥቶ ስለበዛብህ በህይወት አለመኖር ከራሱ ከኢሳይያስ እንደተነገረዉ ነግሮን ቁርጣችንን እንድናዉቅ አድርጓል፡፡ ቤተሰቡ ስለዚህ ሁኔታ ከመቼ ጀምሮ እንደሰማ ግን እኔ የማዉቀዉ ነገር የለም፡፡

በዘብህ ሌላ ሰዉ ቢሆን ኖሮ የኤርትራዉ መሪ ይሁን ህዝቡ ብዙም ባልገረማቸዉ ነበረ፡፡ ነገር ግን ለዓመታት አስረዉት አቆይተዉ በማሰጠንቀቂያ የለቀቁት የድሮዉ በዛብህ መሆኑን ከተረዱ በኋላ ነዉ ያ ሁሉ ግርግር የተፈጠረዉ፡፡ የሻእቢያ አመራሮች አጉል ድፍረቱና የሰራዉ ስራ ቢያናድዳቸዉም ለዓላማዉ ባሳየዉ ቁርጠኝነት ሳያደንቁት የቀሩ አይመስለኝም፡፡ ሻዕቢያ እንኳን ለጠላቱ ቀርቶ ለራሱ ዜጋም ቢሆን አንዳችም ምህረት እንደማያዉቅ አብሮአቸዉ ኖሮ ጠንቅቆ ለሚያዉቀዉ  በዛብህ  የዚህ ዓይነት ድፍረት ማሳየቱ ማስገረሙ አይቀርም፡፡

ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ብርቅዬ ጀግና ተዘንግቶ እያለ የአየር ኃይሉ አመራር በስሙ የሚጠራ አንድ ማስታወሻ አለማድረጉ እጅግ አያስቆጭም ትላላችሁ? በርግጥም ያስቆጫል፡፡ በዛብህን በክብር ማስታወስ ጥቅሙ ለራሱ ለበዛብህ አይደለም፡፡ ጥቅሙ ለሀገርቱና  በተለይም ለአየር ኃይላችን ነዉ፡፡ ስለዚህ አሁን ያለዉ የአየር ኃይል አመራር ይህንን ጉድለት ለማረም የሚሳነዉ ስለማይመስለኝ  እንዲያስተካክለዉ  እንማጸናለን ደግሞም አንደሚተገብረዉም እንተማመናለን፡፡

በመጨረሻም የአየር ኃይል አባል የሆኑትና ዉብና ወኔ ቀስቃሽ  በሆኑ ግጥሞቻቻቸዉ በመላዉ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት የሚታወቁት ጋዜጠኛ  ሻ/ል ፈቃዱ እሸቱ በ2002 ዓ/ም ስለ ጀግናዉ ኮ/ል በዛብህ ጰጥሮስ “በራሪዉ ኮከብ” በተሰኘ ርዕስ በአንድ መጽሄት ላይ ካቀረቡት ግጥም ጥቂት ስንኞችን ቆንጠር አደርጌ ላቅርብ!

“በራሪዉ ኮከብ” (ሻ/ል ፈቃዱ እሸቱ፤ ከኢፌደሪ አየር ኃይል)

.ግንባር ቀደም ንስር ፋኖ-ደመ ቁጡ አራስ ነብር

 ትንታግ፤የሰማይ አርበኛ -ሳተና አስገምጋሚ ንስር…..

..የእናት ኢትዮጵያችን ካስማ -የቁርጥ ቀን ቆራጥ ጀግና

የሰንደቋ ግርማ ሞገስ-የየብስ አየሯ ዋስትና…

እስጨንቀህ ያስማጥካቸዉ

መዓት ያወረድክባቸዉ

የሰማይ በራሪ ኮከብ-ገናናዉ ስምህ ሲጠራ

ሀገራችን አማን ሆና -ሞገስ ክብሯ ተመልሶ

አየር አፈሯ ተባርኮ-ምድሯ አረንጓዴ ለብሶ

ዳር ድንበሯ ዙሪያዉ ታጥሮ-የእድገት ጉዞዋ ቀጥሏል

ከዘመን ዘመን የሚሻገር – ደማቅ ታሪክ ያኮራል”

**********************

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories