ብሔራዊ ተዋጽኦን በመጠበቅ የሕዝቦች አምሳያ የሆነ ህብረ ብሔራዊ የመከላከያ ሰራዊት የመገንባት ጥረታችን

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

“የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የብሄሮች ፤የብሄረሴቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል“- የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 87 የመከላከያ መርሆዎች ተ.ቁ.1

መነሻ ጥያቄዎች

የኢፌዲሪ መንግስት የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ተዋጽኦን የጠበቀ መሆን እንደሚገባዉ በህገመንግስቱ የተቀመጠዉን ደንጋጌ እንዴት ነዉ የተረዳዉና በተግባርም እየተገበረ ያለዉ? መከላከያ ሰራዊቱ በአዋጅ በይፋ ከተቋቋመ በኋላ ባሉት ሁለት አሰርተ ዓመታት ዉስጥ ተዋጽኦን በሚጠበቀዉ ደረጃ አሳክቻለሁ የሚል እምነት አለዉ? መንግስት ተዋጽኦን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የሃያ ዓመታት ግዜ በቂ አይደለም ብሎ ያስባል? በዚህ ረገድ ከፍተት መኖሩን ካመነም እንቅፋት ሆነዉብኛል ያላቸዉ ተግዳሮቶች ባለፉት ሃያ አመታት ግዜ ዉስጥ ሊስተካከሉ የማይችሉ በመሆናቸዉ ነዉ ወይንስ መንግስት ከዚህ የተሻለ ለዉጥ ለማምጣት መጀመሪያዉኑ ፍላጎቱ ስላልነበረዉ ነዉ? ከዚህ በኋላስ እንዴት ለመቀጠል አስቧል?

መንግስት በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየዉ ተዋጽኦ በቁጥር ማመጣጠኑ ባሸገር በብሄራዊ ማንነት፤በጾታና በሃይማኖት እኩልነትንና እኩል አድል ተጠቃሚነትን በማስፈን ረገድ በርግጥ የሀገሪቱን ሕዝቦችን ዉክልና በሚያንጸባርቅ ደረጃ ነዉ ብሎ ያምናል? ለመሆኑ ዳይቨርሲቲን በመከላከያ ዉስጥ ማኔጅ የምናደርግበት ዘዴስ እንዴት ይገለጻል? ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ማስፈጸሚያ ፖሊሲ ወይም ፕሮግራም (diversity management programme) አለን ወይንስ ስራዉ እየተሰራ የነበረዉ በዘፈቀደና በግብር ይዉጣ ነዉ?

በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ተግባራዊነቱን በኃላፊነት የሚከታተል ራሱን የቻለ አካልስ ይኖር ይሁን? በዚህ ቁልፍ ጉዳይ ላይ በሚመለከታቸዉ መንግስታዊ የስልጣን አካላት (መከላከያንም ጨምሮ) አስካሁን አፈጻጸሙን በሚመለከት ዳሰሳና ምክከር ወይም ግምገማ የተደረገበት አጋጣሚስ ይኖር ይሆን? ካለስ ምን ድምዳሜ ላይ ተደረሰ? “አበረታች ነዉ አንዳችም ችግር የለም ነዉ የተባለዉ?

የጉዳዩ ባለቤት የሆነዉ ህዝብስ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጥበት ተደርጎ ያዉቃል? ወይንስ ህዝቡ አስተያየት መስጠትና ማወቅ የማይገባዉ ጉዳይ ነዉ? ዜጎች ለደህንነታቸዉ ዋስትና እንዲሆን ብለዉ የመሰረቱት መከላከያ ተቋም ዉስጥ ልጆቻቸዉ ተገቢዉን ቦታ እያገኙ ነዉ ብለዉ ያስባሉ? የመከላከያ ሰራዊቱ አባላትም ቢሆኑ እያገለገሉበት ያለዉ ተቋም የወጡበትን ህዝብ ባህላቸዉን፣ቋንቋቸዉን፣ታሪካቸዉን፣ማንነታቸዉን፣እምነታቸዉን፣ነዉራቸዉንና ኩራታቸዉን ጠብቀዉ እንዲቆዩ እዉቅናና እገዛ እያደረገ ነዉ የሚል እምነት አላቸዉ? የሰራዊቱ አባላት በተቋሙ ዉስጥ በማንነታቸዉ ምከንያት አንዳችም መድሎ እንደማይደረግባቸዉ ያስባሉ?

የመከላከያ ሰራዊቱ ባለቤት የሆነዉ ህዝብ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ አስከምን ድረስ አመኔታ አለዉ? ማለትም ህዝቡ መከላከያ ሰራዊቱን የሚያየዉ የደህንነቱ ጠባቂ አድርጎ ነዉ? ወይንስ ለደህንነቱ የሥጋት ምንጭ አድርጎ ? በተቃዉሞ ጎራ ያሉ ሌሎች ዜጎች ህገመንግስቱ ባጎናጸፋቸዉ መብት ተጠቅመዉ በመንግስት አሰራርና ፖሊሲ ላይ በአደባባይ ተቃዉሞ ለማሰማት ወይንም በጽሁፍና በሌሎች መገናኛ ዜዴዎች መንግስትን ለመንቀፍ ቢሞክሩ መከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ይተናኮሉናል ብለዉ አይሰጉም?

ጥቅል በሆነ አነጋገር መከላከያ ሰራዊቱ የማን ነዉ የሚሉ ጥያቄች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መልስ የሚሹ እነዚህንና መሰል ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ህብረተሰቡ መንግስትና የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለወደፊቱ በጋራ የሚወያዩበት አጋጣሚ ይፈጠር ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ (አስካሁን ካላደረጉት) በእኔ በኩል ግን ላደርግ የሚችለዉ ለወደፊቱ በዚህ ጉዳዩ ላይ ሊደረግ ይችላል ብዬ ለማስበዉ የሃሳብ ክርክር ወይም ዉይይት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉና ለጋራ ግንዛቤ የሚያግዙ ጥቅል የሆኑ የግል አስተያየቶች መስጠት ነዉ፡፡

ይህችን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋነኛ ዓላማም የመላዉ ህዝቦች የጋራ ተቋም የሆነዉ መከላከያ ሰራዊታችን ለወጣበትና ብሎም ለቆመለት ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ወገንተኝነትና ተቆርቋሪነቱ ተጠብቆ እንዲቆይና የህዝቡም አመኔታ እንዳይሸረሸርበት ማድረግ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነዉ ብዬ ስለማምን የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ በመፈለጌ ነዉ፡፡

በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ተዋጽኦ ተጠበቀ አልተጠበቀ ብዙ የማያሳስባቸዉና ፋይዳዉ ምን እንደሆነ የማይገነዘቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሀገሪቱ ህገመንግስት ዉስጥ መንደንገጉ ራሱ ጠቀሜታዉ ምን እንደሆነ የማይረዱ ዜጎች ሊኖሩ ቢችሉ አይፈረድባቸዉም፡፡ በህገመንግስቱ ማርቀቅና የህዝብ ዉይይት ወቅት መከላከያን በሚመለከት በተለይም ደግሞ በዚህ የተዋጽኦ ጉዳይ ላይ ከቁምነገር ቆጥሮ በጥያቄም ሆነ አስተያየት የሰጠ ስለመኖሩ አላስታዉስም፡፡ አብዛኛዉ ህዝብ ገና በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንኳን ባልጀመረበት ወቅት በተቃዉሞዉ ሆራ ያሉ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ግን መንግስትን ለማሳጣት ዋነኛ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ማድረጋቸዉ አልቀረም፡፡ አሁን ደግሞ ከድሮዉ በበለጠ ገዚዉ ፓርቲ አለበት ለሚባለዉ ጉድፍ ሁሉ እንደ ምክንያት እየተቆጠረ ያለዉ የመከላከያ ሰራዊቱ ተዋጽኦ አለመመጣጠን ጉዳይ ሆኗል፡፡

መንግስት ሙስናን ለመቀነስ ያለመቻሉ ምክንያት፤በስልጣን ላይ ዘለግ ላለ ግዜ መቆየት የቻለበት ምክንያት ፤ የመልካም አስተዳደር መበላሸትና ሊስተካከል አለመቻል ምክንያት፤ለኑሮ ዉድነት ምክንያት፤በአንዳንድ አካባቢዎች በህዝቡ መሃል አልፎ አልፎ ለሚከሰቱ የርስበርስ ግጭቶች ምክንያት ወዘተ ለመሳሰሉት ችግሮች ሁሉ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊትና ደህንነት ተቋሙ ከህዝቦች ይልቅ ለገዢዉ መደብ አባላት ጥቅም ማስጠበቂያነት የቆመ ስለሆነ ነዉ የሚሉት፡፡ህዝቡም ቢሆን ባልተለመደ ሁኔታ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠት መጀመሩ አስቀድሜ ከጠቀስኩት ለሁሉም የመንግስት ችግሮች ሁሉ መከላከያዉ ሰበብ መደረጉ ነዉ፡፡

በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ በቁጥር መገለጽ የነበረባቸዉ አንዳንድ መረጃዎች ሳይገለጹ እንደቀሩ አዉቃለሁ፡፤የመረጃ ምንጮቹና መረጃዎቹም በራሳቸዉ ትክክለኝነት የጎደላቸዉና አጠራጣሪ ሆነዉ ስላገኘኋዉ ከመጥቅስ ተቆጥበአለሁ፡፡ከዚያ ዉጭ በጉዳዩ ላይ የሰጠሁት አስተያየት ማንንም የማይወክልና ማንም ሃሳቤን እንዲጋራዉ የማይገደድበት የግል አመለካከቴ መሆኑን እንዲታወቅልኝ አንባቢያንን በቅድሚያ አሳስባለሁ፡፡

መግቢያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የየራሳቸዉ ቋንቋና ባህልና እምነት በለቤት የሆኑ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ተፈቃረዉና ተከባብረዉ የሚናሩባት አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በተለይ የፌዴራላዊ ስርአቱ እዉን ከሆነ ግዜ ጅምሮ ሁሉንም ህዝቦች መብት እዉቅና በመስጠት ብቻ ሳይገደብ ባህላቸዉን ቋንቋቸዉንና እሴታቸዉን የበለጠ እንዲያዳብሩ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ስርአት ነዉ፡፡ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝቦች ራሳቸዉ በመረጡት እንዴራሴዎቻቸዉ አማካኝነት እንዲወከሉ፤በቋንቋቸዉ ራሳቻዉን በራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩ፤እንዲዳኙና ልጆቻቸዉ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ እንዲማሩ ማድረግ ያስቻለ ብቻ ሳይሆን ህዝቦች የክልላቸዉን የልማት፤የዲሞክራሲ፤ የፍትህና የደኅንነት ጥያቄዎችን ከፌዴራል ተጽኢኦና ዉጭ ነጻነት ተሰምቷቸዉ ራሳቸዉ በመረጡት መንገድ መፍታት የሚያስችላቸዉን የራሳቸዉን መስተዳደር ለማቋቋም እድል የሰጠ ስርአት ነዉ፡፡ ይህ ስርአት በመሰረቱ የሁሉንም ህዝቦች እኩልነት ዋስትና የሰጠ ስርአት በመሆኑ በሁሉም መንግስታዊ መዋቅሮች ከፈዴራል እስከ ወረዳ ድረስ የእኩል እድል ተጠቃሚነት በተግባር ማረጋገጥ የግድ ነዉ፡፡ የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተዋጽኦ በተግባር ሊረጋገጥባቸዉ ከሚገባቸዉ ተቋማት መከላከያ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነዉ፡፡

የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ የወጣ በመሆኑ እነዚህን ህዝቦች መምሰል ብቻ ሳይሆን ባህላቸዉንና እምነታቸዉን ማክበርና አንዱን ህዝብ ከሌላዉ ሳይለይ በአኩል ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ሲባልም መከላከያ ሰራዊታችን የሁሉንም ህዝቦች ተዋጽኦ የጠበቀ እንዲሆን በህገመንግስቱ በተደነገገዉ መሰረት ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡መከላከያ ሰራዊቱ ሁሉንም ህዝቦች በጋራ ለማገልገልና የሁሉንም ህዝቦች የጋራ ጥቅም ለማስከበር የቆመ ሰራዊት እንጂ የተወሰኑ ወገኖችን ጥቅም አስጠባቂና ሌላዉን ህዝብ መብት የሚያፍን እንዳይሆን ለማድረግ በተቋሙ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን በሁሉም ደረጃና በተሟላ ሁኔታ መተግበር የግድ ይሆናል፡፡ ተዋጽኦ በሚገባ ተግባራዊ ያልሆነበት የመከላከያ ተቋም ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ስለማይኖረዉ የጥቂቶች አገልጋይ ከመሆን ዉጭ ለመላዉ ህዝቦች ጥቅም ለመቆም ባህሪዉ ከቶ አይፈቅድለትም፡፡ስለዚህ ተዋጺኦን በሰራዊቱ ዉስጥ የመተግበር ፋይዳዉ እጅግ ላቅ ያለና ከዜጎች ህልዉና ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነዉ፡፡

በህገ መንግስታችን ምዕራፍ አስር ዉስጥ የብሄራዊ ፖሊሲ መሪሆዎችና ዓላማዎች በሚለዉ ስር በአንቀጽ 87 የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት ሊከተለዉና ሊመራበት የሚገቡ አምስት ቁልፍ የሆኑ መሪዎች ይገኛሉ፡፡እነዚህን በጭሩ ለማስታወስ ያህል፡- መከላከያ ሰራዊቱ የህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ስለመሆኑ(ተ.ቁ.1)፣ መከላከያ ሚኒስቴርን ለመምራት በሚኒስትርነት የሚሾመዉ ሲቪል ስለመሆኑ (ተ.ቁ.2)፣ የመከላከያ ሰራዊቱ እንዲያከናዉን የሚጠበቅበት ተግባራት(ተ.ቁ.3)፣ መከላከያ ሰራዊቱ ለህገመንግሰቱ ተገዢ የመሆን ግዴታ እንዳለበት(ተ.ቁ.4)፣ መከላከያ ሰራዊቱ ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነጻና ገለልተኛ ስለመሆኑ (ተ.ቁ.5) የሚመለከቱ ናቸዉ፡፡

እነዚህ መርሆች ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ በፍጹም ድርድር የማይደረግባቸዉና የትኛዉም የሀገሪቱ ዜጋ ያለ አንዳች የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትና ብሄራዊ ማንነት በጋራ ሊያምንበት የሚገባ ነዉ፡፡ ከነዚህ መርሆች ዉስጥ አንዱም እንኳን በሚገባ ካልተተገበረ በህዝቦች መብትና ነጻነት እንዲሁም በሀገሪቱ ሉአላዊነትና አንድነት ላይ አደጋ ሊከተል መቻሉ እሙን ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ መላዉ ህዝቦች ለመከላከያ ሰራዊቱ እዉቅና ሊሰጡ የሚችሉትና ሰራዊቱ የእኔ ነዉ የሚል የባለቤትነት ስሜት ሊሰማቸዉ የሚችለዉ መከላከያ እጅግ የፈረጠመ ተቋማዊ ግዝፈት ስላለዉ ሳይሆን በተጠቀሱት መርሆች ተግባራዊ መሆን ነዉ፡፡

የመርሆቹ ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ህዝቡ መከላከያ ሰራዊቱን የራሴ ብሎ እንዲቀበል የሚያደርጉ ናቸዉ፡፡ ሰራዊቱ ለገዥዎች ስልጣን ማስከበሪያነት እንዳማይዉልና የአንድ ድርጅት መሳሪያ ሆኖ የሌሎችን መብት የማያፍን መሆኑ ማረጋገጫ ነዉ፡፡ የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች ፖለቲከኞችም የመንግስትን አሰራር ቢተቹና ገዥዉን ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ ቢገዳደሩት መካለከያ ሰራዊቱ ይተናኮለን ይሆናል ብለዉ እንዳይሰጉ የሚያደርጋቸዉ እነዚህ መርሆች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ህገመንግስታዊ መርሆች ራሱ መከላከያ ከተቋቋመበት አዋጅ የበለጠ ዋጋ ያላቸዉ ናቸዉ፡፡

በዚህ ጽሁፍም ለመዳሰስ የምሞክረዉ አስቀድሜ ከጠቀስኳቸዉ መከላከያን የሚመለከቱ የህገመንግስታዊ መሪሆዎች መካከል ቀዳሚ ስለሆነዉና መከላከያ ሰራዊቱ የሁሉንም ህዝቦች ተዋጽኦ ያካተተ መሆን አንዳለበት የሚደነግገዉ መርህ ነዉ፡፡ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 87 በመጀመሪያዉ ተራ ቁጥር ላይ የተደነገገዉ “የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የብሄሮች ፤የብሄረሴቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጺኦ ያካተተ ይሆናል“ የሚል ነዉ፡፡ ከተዘረዘሩት አምስቱ መሪሆዎች መካከል የተዋጽኦ ጉዳይ በአቀማመጥ ቅደም ተከተል በመጀመሪያዉ ረድፍ ላይ (ተ.ቁ.1) መቀመጡ እንዲሁ የአጋጣሚ እንዳልሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

ተዋጽኦ በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ የመተግበር አስፈላጊነቱና ፋይዳዉ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ በሆኑ አገሮች መንግስትና አጠቃላይ ፖለቲካዊ ስርአቱ የሁሉንም ህዝቦች የእኩል ተጠቃሚነት መብት የሚያረጋገጥ መሆን የግድ ነዉ፡፡መንግስት ለሁሉም ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት የሚቆም ካልሆነና በህዝቦች መካከል አድሎአዊ አሰራር ከተከተለ ስርአቱ ዘረኝነት የሰፈነበት ስርአት ከመሆን ዉጭ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ መንግስት በሁሉም መስኮችና እድሎች የህዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ቁርጠኝነት ሊኖረዉ ይገባል፡፡ የህዝቦች አከል ተጠቃሚነት ባልተረጋገጠነበት ሁኔታ ህገመንግስታዊ ስርአቱ ለሁሉም ህዝቦች የቆመ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡

ስርአቱ የጋራ ለመሆኑ ዋናዉ ማረጋጋጫ በህዝቦች መካከል ሆን ተብሎ የሚሰራ ልዩነትና አድሎ አለመኖሩ ነዉ፡፡ በተለይም ሁሉም ህዝቦች ያለ አንዳች አድሎ ሊካተቱበት የሚገባዉ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ለሁሉም ህዝቦች በሩን ክፍት ያደረገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የእኩል እድል ተጠቃሚነት በተግባር የተረጋገጠበት ሊሆን የግድ ነዉ በመከላከያ ተቋም ዉስጥ በማንነት ላይ የተመሰረተ አድሏዊ አሰራር ካለ መከላከያ ተቋማዊ ዘረኝነት (institutional racism) የሰፈነበት ተቋም ነዉ ማለት ይቻላል፡

በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ብዝሃነት ወይም ዳይቨርስቲ መጠበቅ ሲባል በተቋሙ ዉስጥ የብሄራዊ ማንነት ማለትም የብሄር፤ የጎሳ ፤ነገድ፣ ዘር ፤ ብሄረሰብ ወዘተ ፤ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በይማኖት፤.የጾታ ወዘተ ልዩነት ሳይደረግ ሁሉን ያለ አድሎ የማካተትና ያለ ምንም ልዩነት የእኩል አድል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ማለት ነዉ፡፡ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ተዋጽኦን የመጠበቅ አስፈላጊነት ለፖለቲካዊ ፍጆታ ወይንም ለመልካም ገጽታ ግንባታ ተብሎ የሚሰራ ሊሆን አይገባዉም፡፡ ተዋፅኦን መጠበቅ አስፈላጊነት ሌሎች ሀገሮች ሲላደረጉ እኛም ከነሱ በምን እናንሳለን በሚል መንፈስ የሚሰራ ሊሆንም አይገባም፡፡ ተዋፅኦን መጠበቅ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በፖለቲካዊ፤ማህበራዊ፤ኢኮኖሚያዊና በሌሎች መስኮች ሁሉ ማንም ከማንም ሳይበላለጥና በብሄራዊ ማንነቱ አድሎ ሳይደረግበት እኩል ተጠቃሚነትን የሚረጋገጥበት ነዉ፡፡ የተዋጽኦ ዋናዉ ፋይዳ ለሁሉም ህዝቦች እኩል ከበሬታና እዉቅና የመስጠት ጉዳይ ነዉ፡፡

በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ተዋጽኦን በመሪህ ደረጃ የመቀበል ብቻ ሳይሆን ከዚሀም በላይ በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት ይህን ጉዳይ ባሰኘዉ ግዜ ሊቀንስና ሊጨምር ወይም አስከነአካቴዉ ሊሰርዘዉ የሚችለዉ ጉዳይ ባለመሆኑ በአግባቡ ማኔጅ ለማድረግ ቁርጠኝነቱና ብቃቱ ሊኖረዉ ይገባል፡፡በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ለሁሉም ህዝቦች በእኩልነት የቆመ ለመሆኑ ማረጋገጫ ለተዋጽኦ መከበር የሚሰጠዉ ትኩረት ነዉ፡፡የሀገሪቱ ህዝቦች ይህን መብት ከቃላት ጋጋታና ከአደባባይ ጭፈራ በበለጠ ትርጉም ያከዉ ለዉጥን በተግባር ማዬት ይፈልጋሉ፡፡

የተዋጽኦ ጉዳይ ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ያለ አንዳች ሰበብ ተግባራዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ መከላከያ ተቋሙም ብሄራዊ ተዋጽኦን በመጠበቅና የአኩል ተጠቃሚነትን በተግባር በማረጋገጥ ረገድ ተምሳሌት መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ያለ አንዳች የጾታ፤ የብሄራዊ ማንነትና የእምነት ልዩነት በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ለማካተትና እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የመከላከያ ተቋም ከሌሎች የተሻለና የተመቻቸ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለ የህዝቦች እኩልነት ከተቋሙ ዉጭ ባለዉ ህብረተሰብ ዉስጥ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ተዋጽኦን በተግባር በማረጋገጥ መከላከያ ለሌላዉ ህብረተሰብ እንደተምሳሌት መሆን አለበት ሲባል ግን በመከለከያ ዉስጥ ተዋጽኦን ተግባራዊ ለማድረግ አተገባበሩ እጅግ ቀላልና አንዳችም ችግርና እንቅፋት ስለሌለበት አይደለም፡፡ እንዲያዉም ተዋጽኦን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ፈታኝ ችግሮች የሚገጥሙት በመከላከያ ዉስጥ ነዉ፡፡ ይህም ከሁለት ምክንያቶች የመነጨ ነዉ፡፡

አንደኛ፤ መከላከያ ወይንም ጦር ኃይሉ እንደተቋም በብቸኝነት በመንግስት በሞኖፖል የተያዘ የታጠቀ ግዙፍ ኃይል በመሆኑና እንደተቋምም ተገቢዉ ቁጥጥር ካልተደረገበት በቀላሉ ለህዝቦች ነጻነትና መብት ላይ የስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችል ተቋም በመሆኑ በዚህ ምክንያትም ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት ለማገልገል የቆመ፤ መላዉን ህዝብ በጋራ የሚወክልና ለዜጎች በተለይም አናሳ ቁጥር ላላቸዉ ህዝቦች መከታና አለኝታ እንጂ የስጋት ምንጭ የማይሆን ተቋም መሆኑ ዋነኛዉ ማረጋገጫ በተቋሙ ዉስጥ ሁሉም ህዝቦች ያለ አድሎ መካተት ሲችሉና እኩል አድል ተጠቃሚ መሆን ሲችሉ ነዉ፡፡

ሁለተኛ፤ ተዋጽኦን በመከላከያ ተቋም ዉስጥ መተግበር ቀላል የማይሆንበት ሌላዉ ምክንያት የዉትድርና ሙያ ዉስጥ በጭራሽ ለድርድር ከማይቀርበዉ የብቃት መስፈርት መሰረት በተቋሙ ዉስጥ ምርጥ ሰዎችን (high quality men) ብቻ ለማቀፍ ካለዉ ፍላጎት ጋር ተዋጽኦ ሊቃረን ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ሲቪል ሰርቪሱ ዉስጥ ለመተግበር እንደሚደረገዉ በወታደሩ ተቋም ዉስጥ በቀላሉ መተግበር ስለማይቻል ነዉ፡፡ ስለዚህ መንግስት ሙሉ ፈቃደኝነቱ እና ቁርጠኝነቱ እያለዉም ከሌሎች ዘርፎች ይልቅ በመከላከያ ዉስጥ ተዋጽኦን በመተግበር ረገድ ትልቅ ፈተና ይገጥመዋል፡፡ በመከላከያ ዉስጥ ተዋጽኦ የግድ መተግበር አለበት ሲባልም ቀላል ስለሆነ ሳይሆን በርካታና ፈታኝ የሆኑ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የግድ መተግበር አለበት ከሚል አስተሳሰብ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ተዋጽኦን በመከላከያ ዉስጥ መተግበር የቅንጦትና የይስሙላ ጉዳይ ሳይሆን የዜጎች ህልዉና ጉዳይ ስለሆነ ነዉ፡፡

በመከላከያ ዉስጥ ተዋጽኦን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ባልተቻለበት ሁኔታ በቀረዉ ህብረተሰብ ዉስጥ የህዝቦች እኩልነት ይረጋገጣል ተብሎ ከቶ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ መከላከያ ሰራዊት የህዝቦች የመቻቻል፤የአንድነትና የአብሮነት (integration) ተምሳሌት መሆን ይኖርበታል፡፡ መከላከያ እንደተቋም ሁሉንም ህዝቦች አስካላካተተ ድረስ ተቋሙ ሁሉንም ህዝቦች ያለ አድሎ ለማገልገል የቆመ ነዉ ተብሎ አይታሰብም፡፡

በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ተዋጽኦን ተግባራዊ ማድረግ ጠቀሜታዉ ለተቋሙም ጭምር ነዉ፡፡ ተቋሙ ሁሉን ህዝቦች በእኩልነት ያካተተ ከሆነ በህዝቡ ዘንድ መልካም ገጽታዉ ስለሚጎላ ህዝባዊ ቅቡልነትና መተማመን ይጨምራል፡፡ ህዝቡ ሰራዊቱን በፍርሃት፤በጥርጣሬና በጥላቻ ማየቱ ቀርቶ በሰራዊቱ የመኩራትና አለኝታዉ አድርጎ መቁጠር ይጀምራል፡፡ ህዝቡ ተቋሙን በርግጠኝነት የራሴ ተቋም ነዉ ብሎ ለማስብ የሚችለዉ የአፈናና የጭቆና መሳሪያ እንደማይሆን እርግጠኛ ሲሆን ብቻ ነዉ፡፡ ተዋጽኦ በአግባቡ ተግባራዊ የተደረገበት የመከላከያ ተቋም ተቆርቋሪነቱና ወገንተኝነቱ ያለጥርጥር ለህዝቡ ስለሚሆን ከህዝቡ በምላሹ በሚያገኘዉ ድጋፍ የተነሳ የሰራዊቱ አባላት ለሙያቸዉ ከፍተኛ ፍቅር እንዲኖራቸዉ ያደርጋል፡፤መከላከያም እንደ ተቋም ህዝባዊ መሰረቱ የሠፋ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ በድምር መከላከያ ተቋሙን እጅግ ጠንካራ ተቋም ያደርገዋል፡፡ በአግባቡ የተተገበረ ተዋጽኦ ለመከላከያ ተቋሙ የጥንካሬዉ ምንጭ ይሆናል፡፡

ህዝባዊ መሰረት ያለዉ ሰራዊት ለተቋሙ ጥንካሬ የሚያስፈልገዉን የሰዉ ኃይልና ባጄት ያለችግር ለማግነት ሰፊ እድል አለዉ፡፡ መከላከያ ህዝባዊ ከበሬታ ባተረፈበት ህብረተሰብ ዉስጥ ዉትድርና ወጣቶች ከወላጆቻቸዉ ተደብቀዉ የሚገቡበት ሳይሆን ወላጆች ራሳቸዉ መርቀዉ የሚልኩት የተከበረ ሙያ ይሆናል፡፡ ለማንነታቸዉ ከበሬታ የሚሰጣቸዉ ተቋም ዉስጥ የገቡ የሰራዊቱ አባላትም ተቋሙ ታላቅ የሕዝብ ፍቅርና ድጋፍ እንዳለዉ ስለሚገነዘቡ ማንኛዉንም መስዋእትነት ለመክፈል ወደኋላ አይሉም፡፡ በየትኛዉም የሀገሪቱ አካባቢ ካለ ህዝብ መሃል ቢገኙ ባይተዋርነት አይሰማቸዉም፡፡ እያንዳንዱ የሰራዊቱ አባልም በግሉ እሱ በወጣበት ህዝብ ላይ አንዳችም የሚደርስባቸዉ ብሄራዊ ጭቆናና አድሎ እንደሌለና ይልቁንም በማንነቱ እንዲኮራና ባህሉንና እምነቱን እንዲጠብቅ የሚበረታታ መሆኑን ከተገነዘበ ለሙያዉ ከፍተኛ ፍቅር ያድርበታል፡፡

በማንነቱ ምክንያት የተፈጠረ አንድም ቅሬታ የለለዉ የሰራዊት አባል የሁሉም የጋራ ቤት ለሆነችዉ ለእናት ሀገሩና ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከማሰብ ዉጭ በጠባብ አመለካከት ታጥሮ ነጋ ጠባ ስለወጣበት ጎሳ ወይም ብሄር ብቻ በማሰብ ራሱን አያስጨንቅም፡፡ ይህ ደግሞ ለተቋሙም ሆነ በአጠቃላይም ለሀገሪቱ የሚበጅ ነዉ፡፡ ህዝባዊ መሰረቱ የሠፋና የህዝብ ፍቅር ያተረፈ ተቋም አዳዲስ ወጣቶችንም ወደ ተቋሙ ለመሳብ አይቸግረዉም፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣት ከሚቆጠሩ አገሮች ዉጭ ብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎት አሰራር በቀረበትና ወደ መከላከያ የሚገባዉ ወጣት ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ እየተመናመነ በመጣበት በአሁኑ ዘመን አዳዲስ ወጣቶችን ወደ መከላከያ ለመሳብ ትልቅ እገዛ የሚያደርገዉ የተቋሙ ህዝባዊ ከበረታና ፍቅር መኖር ነዉ፡፡ በርካታ የግል ድርጅቶች በተሻለ ክፍያ ወጣቱን ለመማረክ በሚችሉበት በአሁኑ ወቅት ወደ መከላከያ የሚመጣዉ አዲስ ምልምል ከሚያገኘዉ የፋይናነስና ቁሳቁሳዊ ጥቅም ይልቅ የመከላከያ አባል በመሆኑ ከህዝቡ የሚያገኘዉን ከበረታና ፍቅር በመሻት ነዉ፡፡ እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ዋናዉ መሰረት መከላከያ ተቋሙ ለሁሉም ህዝቦች በሩን ክፍት ሲያደርግና አንድ ግዜ ወደ ተቋሙ የገቡትም ያለአድሎ በእኩልነት መንፈስ የሚያስተናግድ ከሆነ ብቻ ነዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ መከላከያ ወይም የዉትድርና ሙያ ከሌሎች ሙያዎችና ተቋማት በበለጠ ተመራጭና ተወዳደሪ መሆን የሚችለዉ ከሌሎቹ የተሻለ ደሞዝ ስለሚከፍል አይደለም፡፡ መከላከያ የተጠየቀዉን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ቢሆን እንኳን ለኢኮኖሚያዊም ሆነ ለቁሳቁስ ጥቅም ብቻ ብሎ ወደ መከላከያ የሚገባ ሰዉ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የመከላከያ ሰራዊት አባል በዉትድርና አገልግሎት ዘመኑ የሚገጥመዉ እጅግ አስቸጋሪ ዉጣ ዉረድ፤ አስከ ህይወት መስዋእትነትና የአካል መጉድል የሚደርስ ጉዳት በማንኛዉም ሰዓት ሊደርስበት እንደሚችል ለሚገነዘብ ማንኛዉም ሰዉ ያን ሁሉ ችግርና ፈተና እንዲሁም መስዋእትነት ሊያካክስለት የሚችል አንዳችም የክፊያ መጠን አይኖርም፡፡ ማንም ሰዉ በዚህ ቦታ ራሱን አስቀምጦ መልስ ለመስጠት ይሞክር፡፡ ለሙያዉ ፍቅር ከለለዉና የሀገር ሉአላዊነት የማስከበር ግዴታ ከልተጫነዉ በስተቀር ለገንዘብ ብሎ ወደ መከላከያ ሰራዊቱ የሚገባ ሰዉ ያለ አይመስለኝም፡፡

ለመሆኑ በደርግ ወቅት በኤርትራ በረሃ ወድቆ ለቀረዉ የኢትዮጵያ ወታደርና ለቤተሰቡ ሀገሪቱ ምን ያህል መክፈል ይገባት ነበር? በኤርትራ የእብሪት ወረራ ጦስ በጅግንነት የወደቁ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት አባላትስ ለዉሌታቸዉ ስንት ብር ይበቃቸዋል? በሶማሊያ በረሃ ከአልሻባብ ጋር ሲፋለሙ በክብር ለወደቁና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸዉ የሀገራችን ህዝቦች ኩራት የሆኑ ጀግኖች ለሰጡት አገልግሎትና ለከፈሉት የሕይወት መስዋእትነት ወዘተ ለእንዳንዳቸዉ ስንት ሚሊዮን ብር ቢከፈል ነዉ በቂ ነዉ ሊባል የሚችለዉ? እያንዳንዳችን አድሜያችን ለዉትድርና የደረሰ ልጆች ያለን ወላጆች ለመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ምን ያህል ወርሃዊ ክፍያ ቢሰጥ ነዉ ልጆቻችንን ወደ ሰራዊቱ እንዲገቡ የምናበረታታዉ?

አንድም ዓይነት የቁሳቁስም ሆነ የገንዝብ ብዛት ወደ ሰራዊት ተቋም ለመግባት ምክንያት አይሆንም፡፡ ለአንድ የመከላከየ ሰራዊት አባል ከሁሉም በላይ የሚያደስተዉ ከህዝቡ የሚያገኘዉ ክብርና ፍቅር እንዲሁም ከተቋሙ የሚያጋኘዉ የሙያ እርካታ ነዉ፡፡ የህዝብ ፍቅርና ከበረታ ለማግኘት ደግሞ ተቋሙ የሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች የመቻቻልና (tolerance) የአብሮነትና (integration) እርስበርስ ዝምድናና ቁርኝት (cohesion) ተምሳሌት መሆን ሲችል ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ በወሳኝ መልኩ ሊገኝ የሚችለዉ ብሄራዊ ተዋጽኦዉን በአግባቡ ማመጣጠን ሲቻል ብቻ ነዉ፡፡

ከዉትድርና ሙያ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ወገኖች የሚሰጡ የተዛቡ አስተያየቶች አይጠፉም፡፡ ዉትድርና ሙያ ከአለባበስ ጀምሮ በሁሉም ረገድ ወጥነት (uniformity) ከሌለዉ ተቋሙ ይዳከማል ይላሉ፡፡ ተዋጽኦን እንደ አደጋ የሚቆጥሩ ወገኖች ዜጎች ለዘመናት ያዳበሩትን የሚያኮራ እሴት ፤እምነት፤ቋንቋና ባህል በመጨፍለቅ በግዴታ ወደ አንድ በማምጣት ወጥነት መፍጠር አለበት ይላሉ፡፤ በመሰረቱ አስቀድሜን እንዳየነዉ ብዝሃነት (ተዋጽኦ ለተቋሙ ጥንካሬ ከመሆኑ ዉጭ የሚያዳክም እንዳልሆነ ግልጽ ቢሆንም ተቋሙን ያዳክማል በሚል የተሳሳተ አመለካካት ልዩነትን በማጥፋት ወደ አንድ ለማምጣት መሞከር የህዝቦችን ማንነት መካድና የተቋሙን ህዝባዊ መሰረት መናድ ብሎም የህዝቦች ጭቆና መሳሪያ ከማድረግ ዉጭ የዚህ ዓይነት ተቋም የሕዝብ ጠባቂ ለመሆን ባህሪይ ከቶ አይፈቅድለትም፡፡

የተለያዩ እምነት ተከታይ የሆኑ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባሉባቸዉ አገሮች ጦር ኃይሉ የህዝቡን ዓመኔታና ድጋፍ ለማግኘት የተሰጠዉን ተልእኮም በብቃት መወጣት እንዲችል ሰራዊቱ የወጣበትን ህዝብ ማንነት በሚገባ ማንጸባረቅና ህዝቡን መምሰል ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ በዉስጡ ያቀፋቸዉን ከተለያዩ ህዝቦች የመጡ አባላቱን ማንነት (አይደንትቲ) ባህልና እምነት በጠበቀ ሁኔታ ተልዕኮዉን በብቃት ለመወጣት የሚያስችለዉን አንድ የጋራ የሆነ ተቋማዊ እሴትና ባህል ሊኖረዉ የግድ ነዉ፡፡ ጦር ሃይሉ (መከላከያ) የራሱ የሆኑ ተቋማዊ እሴቶችና ባህልና ልማድ መኖር ብቻዉን እንደ አደጋ የሚቆጠር አይደለም፡፤ይሁን እንጂ ተቋማዊ አሴትና ባህል ለመገንባት ተብሎ የአባላቱን ማንነትና እምነትና ባህል በግድ ለመቀየር መሞከር አይገባዉም፡፡ የመከላከያ ተቋሙ ህዝቦች ለዘመናት ጠብቀዉ ያቆዩትንና ባህልና በህብረተሰቡ ዉስጥ የጋራ ጠቀሜታ ያላቸዉ ሀገራዊ እሴቶችን ከበረታ መስጠትና መንከባከብ ይገባዋል እንጂ ለተቋሙ ፍላጎት ተብሎ ለመሸርሸርና ለማንቋሸሽ መሞከር አይገባዉም፡፡ ከህዝቡ የወጡ የሰራዊቱ አባላት በፊት ይዘዉት የቆዩትን ልማድና እምነት እዉቅና ከበረታ በመስጠት ጠብቀዉት እንዲያቆዩ ከማገዝና ከማበረታታት ዉጭ ሌላ አዲስ ማንነትና ለመስጠት መሞከር ትልቅ ጥፋት ነዉ፡፡

የመከላከያ ተቋሙ እሴትና ባህል መቶ በመቶ ከህብረተሰቡ ባህልና እሴት ጋር መመሳሰል ወይም ፎቶ ኮፒ መሆን አለበት የሚባል ነገርም የለም፡፡ እንደዚያ እንዲሆን ቢፈለግም በተግባር ግን የሚቻል አይደፈለም፡፡ ወታደራዊ ተቋሙ የተሰጠዉ አስቸጋሪ ተልእኮ ከሚጠይቀዉ ጥብቅ ድስፕሊን፤ የሙያዉ ባህሪይና ልዩ ከሆነዉ የተቋሙ ባህሪያት የሚመነጭ የራሱ የሆኑ ተቋማዊ እሴቶችና ልማዶች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ወታደራዊ ተቋሙ ለሲቪሉ ህብረተሰብ እንግዳ የሆኑ ነገር ግን ለተቋሙ ግዳጅ አፈጻጸም የግድ አስፈላጊ ተደርገዉ የሚቆጠሩ አንዳንድ ልማዶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ እነዚህ ልማዶችና ተቋማዊ ባህል ጠብቆ ማቆየት ይጠበቅበታል፡፡

ነገር ግን እነዚህ የተቋሙ እሴቶችና ልማዶች የተቋሙ አባላት ከወጡበት ህብረተሰብ ጋር የሚያላትመዉ ወይም የሚያጋጨዉ ሊሆን አይገባም፡፡ ለምሳሌ ከእምነት ጋር ተያይዞ በአመጋገብ ስርአት አልፎ አልፎም ቢሆን ቅረታቸዉን የሚገልጹ አንዳንድ አባላት እንዳሉ መደበቅ አይቻልም፡፡ ከዚህ ጋር ብዙም ባልራቀ ከጸሎት ወይም አምልኮ ጋር የታያያዙ አንዳንድ ስሜቶችም አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡

ከሃይማኖት ጣጣ ወጣ ስንል ደግሞ ቋንቋን በሚመለከትም ከግንዛቤ ማነስ የመነጨ ግራ መጋባትም ይታያል፡፡ አባሉ የወጣበት ህብረተሰብ ራስን በራሱ ቋንቋ መተዳደሩንና መማሩን በማስታወስ በወታደራዊ ተቋሙ ዉስጥ ለምን እንደዚያ ሊሆን እንዳልቻለ ግራ የሚገባቸዉ የሉም ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ መሰል ጉዳዮች በሌሎች አገሮች ከበቂ በላይ አወዛጋቢ በመሆናቸዉ ለራሳቸዉ ልዩ ሁኔታ በሚስማማ ደረጃ ለችግሮቹ መፍትሄ ለማበጀት መጣራቸዉ አልቀረም፡፡ በኛ ሁኔታ ግን ህዝቦች ለዘመናት የቋንቋ፤የእምነት ልዩነት ሳያግዳቸዉ በሰላም ተቻችለዉ የመኖር ልማድ በማዳበራቸዉና በሰራዊቱ ዉስጥም ድሮም ቢሆን በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችል ችግር ተሰምቶ ስለማይታወቅና አሁን ደግሞ ከድሮዉ በበለጠ ህገመንግስታዊ ዋስትና የተሰጠዉና ህዝቦች በማምነታቸዉ ኮርተዉ እርስ በርሳቸዉ በጠንካራ የግኑኝነት ድሮች የተሳሰሩና ለአንድ የጋራ ዓላማ በአንድነት የቆሙ በመሆናቸዉ ይህ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ችግር የለም፡፡ ይሁን እንጂ በየግዜዉ በሚፈጠሩ ልዩ ሁኔታዎች እየተፈለፈሉ ያሉ ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸዉ ጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነት ወደፊት ችግር ለመፍጠር አይሞከርም ስለማይባል ከወዲሁ መዉጫ መንገድና መፍትሄ አፈላልጎ መቀመጡ የተሻለ ይሆናል፡፡ ዋናዉ መፍትሄ ግን የሰራዊቱ አባላትን በግልጽ በማወያየት በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ ግንዛኔ እንዲይዙ ማድረጉ ነዉ፡፡

አዳዲስ የሰራዊቱ አባላት ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ተቋሙ ሲካተቱ ስለ መከላከያ ልዩ ባህሪይና ስለ ተዋጸኦ ምንነትና አስፈላጊነት ወደፊት ከሌሎች ጋር በጋራ በሚኖሩበት አግባብ ላይ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ ሊሰጣቸዉ ይገባል፡፡ በቁጥር አናሳ በሆኑና በእድገት ወደ ኋላ ከቀሩ ህዝቦች ወደ ሰራዊቱ የሚቀላቀሉ በፌዴራሉ ቋንቋ እንደልብ ለመግባባት ከመቸገራቸዉም ሌላ የተቋሙን ባህል ለመልመድና ከሌላዉ ሰራዊት አባል ጋር ፈጥነዉ ለመቀላቀል ለግዜዉ መቸገራቸዉ ስለማይቀር ገና በማሰልጠኛ ማእከል ከገቡበት ቀን ጀምሮ ከዚህ ሁኔታ ጋር የሚያለማመዳቸዉ አሰራር (socialization) ስርአት ማበጀት ይገባል፡፡

ብሄራዊ ተዋጽኦን በሰራዊቱ ዉስጥ ተግባራዊ የማድረግ ጥረት በህዝቡ ዉስጥ ተዋጽኦን ማኔጅ ለማድረግ ከሚሰራዉ ስራ ተነጥሎ ሊታይ የሚገባዉ አይደለም፡፡ የሀገሪቱ ህገ መንግስትና ህገመንግስታዊ ሰርአቱ ባህሪይ መሰረት በህብረተሰቡም ዉስጥ ሆነ በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥ የሁሉንም ህዝቦች መብት መከበሩን የማረጋገጥና ለተግባራዊነቱም አስፈላጊዉን ክትትልና አገዛ የማድረግ ኃላፊነት ከሀገሪቱ ህግ አዉጭ ጀምሮ የአስፈጻሚዉ አካል፤ የፍትህ አካካላት ሲሆን የመከላከያ ተቋሙም በዕለት ከእለት እንቅስቃሴዉ ሁሉ ለተግባራዊነቱ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ብሄራዊ ተዋጽኦን በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥ የመተግበር ጉዳይ ለራሱ ለመከላከያ የሚተዉና እንዳፈቀደዉ ያድርግ የሚባል አይደለም፡፤ተዋጽኦ በአግባቡ መከበሩን መመስከር ያለበትም ራሱ መከላከያ ሰራዊቱ ወይም አስፈጻሚዉ ሳይሆኑ የሕዝብ ዉክልናና ያለዉ የህግ አዉጭዉ አካል ነዉ፡፡ በተጨማሪ ነጻ ሚዲየዉ፤ ሲቪክ ማህበራትና እምባጠባቂ ተቋሙ ወዘተ ናቸዉ፡፡ ህዝቡ ራሱ መመስከር የሚችልበት መንገድ ሊኖር ይባዋል፡፡፡ ልጆቹ በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥተገቢዉ ቦታ እያገኙ ነዉ ወይንስ የይስሙላ ነዉ የሚለዉን ከማንም በተሸለ ህዝቡ መመስከር ይችላል፡፡፡ ምክንያቱም በሰራዊቱ ዉስጥ ካሉት ከራሱ ልጆች መረጃዉን በቀላሉ ማግኘት ስለሚችል ማለት ነዉ፡፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ሁሉንም ህዝቦች ያለአድሎ የሚያካትት መሆን እንዳለበት በሀገሪቱ ህገመንግስት በግልጽ ተደንግጎ ህገመንግስታዊ ዋስትና የተሰጠዉ ጉዳይ አሰከሆነ ድረስ ቀጣዩ ስራ ሊሆን የሚገባዉ እንዴት ይተግበር የሚለዉ ነዉ፡፡ ችግር የሚፈጠረዉም እዚያ ላይ ነዉ፡፤ በህገመንግስቱ ተደንግጎም እያለ በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመቻል ወይም ያለመፈለግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላልና፡፡ በህገመንግስቱ መደንገጉ ህገመንግስታዊ ዋስትና ለመስጠት እንደ አስፈላጊ ቅድሜ ሁኔታ ሊወሰድ ይችል እንደሆን እንጂ ከዚያ ባለፈ ግን በተግባር ለመተርጎሙ ብቻዉን እንደ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሌሎችም በህገመንግስቱ የተደነገጉ መብቶችም በቀላሉ ሊጣሱ እንደሚችሉ ከልምድ ይታወቃልና ፡፡

የመከላከያ ሰራዊት እንደ ተቋም ያለ አንዳች አድሎ ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ ቀጣሪ ተቋም (equal-opportunity employer) መሆን ብቻ ሳይሆን ዉስጣዊ አሰራሩም ከማንኛዉም ዓይነት አድሎ የጸዳና እያንዳንዱ አባል የአቅሙን ያህል አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚያበረታታ ተቋም መሆን ይገባዋል፡፡

1/ የኢፌዲሪ መንግስት ተዋፅኦን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ለመተግበር ያደረጋቸዉ ጥረቶችና ለትችት የዳረጉት የአፈጻጸም ችግሮቹ

ከዚህ በፊት በዚሁ በሆርን አፋዬርስ (HORN AFFAIRS) ላይ የመከላከያ ሰራዊታችንን የፓርቲ ገለልተኝነት የሚመለከት አስተያየት ባሰፈርኩበት አንድ ጽሁፍ ላይ ኢህአዴግ ሀገር የማስተዳደር ስልጣን ከያዘ በኋላ ካከናወናቸዉ ግዙፍ ተግባራት መካከል ከልማቱ ቀጥሎ እጅግ የተሳካለትና ሊወደስበት የሚገባዉ ጉዳይ ቢኖር ከፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ ገለልተኛ መከላከያ ሰራዊት ለመመስረት ያደረገዉ ጥረት እንደሆነ መግለጼ ይታወሳል፡፡ ያን ጽሁፍ ተከትሎ ከአንባቢያን ሊነሱ የሚችሉ የተለያዩ ነቃፊና ደጋፊ አስተያየቶች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ግምት የሃሳብ ሙግት ለማድረግ በትዕግስት መጠበቄ ባይቀርም አስካሁን ድረስ “የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ለአንድ ፓርቲ የወገነና ገለልተኝነት የጎደለዉ ነዉ” የሚል አስተያየት አላጋጠመኝም፡፡

እኔም በመከላከያ ሰራዊታችን ገለልተኝነት ጉዳይ ላይ የነበረኝን አመለካከት የሚያስቀይረኝ አሳማኝ ምክንያት አስካሁንም ስላላገኘሁ በዚሁ አቋሜ እንደጸናሁ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ በፓለቲካ ፓርቲ ገለልተኝነቱና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ በእጅጉ የምመካበትን መከላከያ ሰራዊት ባለቤት ያደረገን የኢፌድሪ መንግስት አስካሁን በወሳኝ መልኩ ተጨባጭ ለዉጥ አምጥቶ ሊያሳየን ያልቻለበትና ስለጉዳዩ ባሰብኩ ቁጥር ምቾት የማይሰጠኝ ጉዳይ ቢኖር በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን በሚፈለገዉ ደረጃ መተግበር አለመቻሉ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት ያደረጋቸዉን ጥረቶችንም ሆኑ የገጠሙትን እንቅፋቶች ሳልረዳለት ቀርቼ አይደለም፡፡ ነግር ግን ከጉዳዩ አሳሳቢነት፤ዳፋዉና ለወደፊቱ ሊያስከትል ከሚችለዉ መዘዝ አንጻር በሚመጣጠን ደረጃ የተሟላ ቁርጠኝነቱን በተግባር አሳይቷል ለማለት አልደፍርም፡፡ መንግስት አስካሁን እያደረገ ካለዉ የበለጠ ጥረት አድርጎ ቢሆን ኖሮ አስካሁን ካሳየን የተሻለ ዉጤት ማሳየት ይችል እንደነበር አምናለሁ፡፡

የኢ.ፌ.ድ.ሪ መንግስትም ሆነ ገዥዉ ፓርቲ አስካሁንም ክፉኛ ከሚተቹባቸዉ ጉዳዮች መካከል ምናልባትም በተደጋጋሚ የተሰነዘረ ትችት ቢኖር መንግስት በህገመንግስቱ በተደነገገዉ መሰረት መከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን በአግባቡ ለመተግበር አልቻለም የሚል ነዉ፡፡ ጉዳዩን አስመልክተዉ መንግስትን የሚተቹ አንዳንድ ወገኖች እኔ ሁኔታዉን ቀለል አድርጌ “ተዋጽኦ በሚፈለገዉ ደረጃ ሊመጣጠን አልቻለም„ በሚል እንደገለጽኩት ሳይሆን እነሱ “መንግስት ብሄራዊ ተዋጽኦን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ አስካሁን ተግባራዊ ያላደረገዉ ከአቅም ማነስ ወይም ለትግበራ አስቸጋሪ በመሆኑ ሳይሆን ሆን ብሎ አንዱን ብሄር በልዩ ሁኔታ ለመጥቀምና ሌላዉን በማግለል በመፈለጉና ለስልጣኑ ይበልጥ ታማኝ የሆኑትን ለመጥቀም አስቦ ነዉ“ ነዉ እያሉ ያሉት፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዉስጥ በአደገኛ ሁኔታ ተንሰራፍቶ የሚገኘዉን ሙስናና ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ለመግታት ያልተቻለበት ዋነኛዉ ምክንያት ቁልፍ በሆኑና ከዝርፊያ ጋር ቁርኝት ባላቸዉ የሃላፊነት ቦታዎችና የሥራ መደቦች ላይ ለአገዛዙ ያለማንገራገር ታማኝ ናቸዉ ከሚባሉት ዉጭ የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችን መመደብ ለዝርፊያዉ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ከሚል ስጋት የመነጨ ነዉ ይላሉ፡፡ በተጨማሪ ትችታቸዉን የሚያጠናክሩበት አንዱ ጉዳይ ገዥዉ ፓርቲ ስልጣኑን ላለማስነጠቅ የሚነሱበትን ተቃዉሞዎችን በቀላሉ ለማፈን የቻለዉም ለአገዛዙ በተለየ ተቆርቋሪነት ባላቸዉና የተለየ ታማኝነት የሚያሳዩትን በዙሪያዉ በማድረጉ ነዉ፡፡ የሚል ነዉ፡፡ በአጭሩ ሲቀመጥ በመከላከያ ዉስጥ አስካሁን ተዋጽኦን በአግባቡ ለመተግበር ያልተቻለዉ ስለማይቻል ሳይሆን ለገደብ የለሽ ዝርፊያና የመንግስት ስልጣን ላለማስነጠቅ ካለዉ ፍላጎት በመነጨ መንግስት ሆን ብሎ ያደረገዉ ነዉ የሚል ነዉ፡፡

መንግስት ተዋጽኦን በማማጣጠን ረገድ እየቀረቡበት የነበሩትን ትችቶች አንድም ግዜ በይፋ ለማስተባበልም ሆነ ለማዉገዝ አለመሞከሩ የችግሩን መኖር ራሱም የተቀበለዉ መሆኑን እንደ ማረጋጋጫ ተደርጎ ነዉ የተቆጠረዉ፡፡ በርግጥም በዚህ ጉዳይ እየቀረቡ ካሉት ትችቶች መብዛት አንጻር መንግስት ትችቶቹን ከማስተባበል ይልቅ የተሻለ ነዉ ብሎ የመረጠዉ “የችግሩን መኖር ተረድቼ ለማስተካከል በርትቼ እየሠራሁ ነዉ” የሚል ምላሽ መስጠትን ነዉ፡፡

መንግስት በተጨባጭ ከሚታየዉ ችግር ጋር በሚመጣጠን ደረጃ ባይሆንም እሱ ራሱ ባመነበት ደረጃና አቅሙ በፈቀደ መጠን ጉድለቱን ለማስተካከል በርካታ እርምጃዎችን በየግዜዉ መዉሰዱና የወሰዳቸዉን የመፍትሄ እርምጃዎችንም ለህዝብ በይፋ ሲያሳዉቅ መቆየቱም የሚታወስ ነዉ፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ ከወሰዳቸዉ ማስተካከያ እርምጃዎች ዉስጥ በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለዉ በሰራዊቱ ዉስጥ የአንድ ቋንቋ (ትግርኛ) ተናጋሪ የነበሩትን በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን በጡረታ በማሰናበት ሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትን እጅግ ፈጣን የሚመስል የማዕረግ አሰጣጥ በማድረግ ወደ ላይ በማምጣት የነበረዉን ልዩነት ለማጥበብ ያደረገዉ ጥረት ነዉ፡፡

ለምሳሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ በአንዳንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የሻለቃም ሆነ የሌ/ኮሎነል ማዕረግ ያለዉ እንደ ብርቅ ይታይ እንዳልነበር ዛሬ ከኮሎነልነት ማእረግም አልፈዉ በአጭር ግዜ ዉስጥ የሜጄር ጀኔራልነት መዕረግ ደረጃ መድረስ የቻሉ እንዳሉ እናዉቃለን፡፡ እንደዚህም ሆኖ መንግስት ችግሩን መኖር ካመነበት ወቅት ጀምሮ የወሰዳቸዉ በርካታ ማስተካከያ እርምጃዎች አሁንም ከትችት ሊያድኑት አልቻሉም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል ፤

አንደኛ፤ በማመጣጠኑ ረገድ ተወሰደ የተባለዉ እርምጃ ለይስሙላ ነዉ እንጂ በቂ አይደለም በሚል ጥረቱን በደፈናዉ በማጣጣል የሚቀርብ ትችት፤

ሁለተኛ ደግሞ ከመጀመሪያዉ ለየት ባለ መልኩ መንግስት በማመጣን ሰበብ እጅግ ሰፊ ልምድ የነበራቸዉንና ሀገራቸዉን በሙያቸዉ ለማገልገል አቅሙና ፍላጎቱ የነበራቸዉን ያለ አግባብና ያለግዜያቸዉ በተጣደፈ ሁኔታ ከሰራዊቱ በማሰናበቱ የመከላከያ ተቋሙ ብቃት በእጅጉ እንዲጎዳ አድርጓል የሚል ነዉ፡፡

በርግጥ ሰፊ ልምድ ያላቸዉና ቢያንስ ተተኪ በማፍራት ረገድ ጉልህ ሚና ሊኖራቸዉ ይችሉ የነበሩ አንዳንድ አመራሮችን በተጣደፈ ሁኔታ በጡረታ ማሰናበቱን በሚመለከት የተወሰነ እዉነትነት ቢኖረዉም ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማሰናበትን ባላካተተ ሁኔታ አዳዲስ ተሿሚዎችን ከስር ወደ ላይ ወደ ከፍተኛ ሃላፊነት ማምጣት የሚቻልበት ዕድል አይኖርም፡፡ ምናልባት ለማመጣጠን ተብሎ በፊት ያልነበረ አዳዲስ መዋቅርና አደረጃጀት መፍጠር አለበት ካልተባለ በስተቀር አሁን ባለዉ የሰራዊት መዋቅር የተወሰኑትን በጡረታ ሳያሰናብቱ ማመጣጠን የተባለዉን ነገር መተግበር የሚቻል አይደለም፡፡ ምናልባት የትችቱ አቅራቢዎች በምን መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል እንደነበር ከትችቱ ጋር አብረዉ መፍትሄዉንም ለመንግስት ቢጠቁሙ ኖሮ ተገቢ በሆነ ነበር፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ፍቱን የሆነ የመፍትሄ ሃሳብ ካላቸዉ ቢያቀርቡ ጠቀሜታዉ ለሁላችንም ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ እየቀረበ ያለዉ ትችት ለታወዋጽኦ ተብሎ ለቦታዉና ለማዕረጉ የሚመጥናቸዉ ብቃትና ዝግጅት የሌላቸዉን ጭምር በዘፈቀደ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግና ሹሜት በመስጠት የሀገሪቱን ወታደራዊ አመራር በልምድ አልባና ብቃት የለሽ ሰዎች እየሞላ በመሆኑ በመከላከያ አጠቃላይ ብቃት ላይ በሚፈጠር የአመራር ክፍተት ለወደፊት በሀገሪቱ ላይ አደጋ መጋበዙ አይቀርም በሚል ሹመቱንና የተፋጠነ የማዕረግ አሰጣጡን ክፉኛ የሚተቹ አሉ፡፡

መንግስት በሰራዊቱ ዉስጥ የተመጣጠነ ተዋጽኦ እንዲኖር መስራት ያለበት ለትችቶች ምላሽ ለመስጠት ብሎ እንዳልሆነ ይልቁንም መንግስትን የሚመራዉ ገዥዉ ፓርቲ (ኢህአዴግ) ከማንም በበለጠ ብሄራዊ አድሎና ጭቆናን ሲታገል የነበረና በህዝቦች እኩልነት ላይ ጽኑ እምነት በመያዝ የተዋጽኦ ጉዳይ በእምነት ደረጃ የተቀበለዉና የታገለለት መሪህ በመሆኑ ነዉ፡፡ እንዲያዉም ኢህአዴግን ከመነሻዉ ጀምሮ ከብዙዎቹ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሲያላትመዉ የነበረዉ ጉዳይም በዚህ አቋሙ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በሀገራችን እዉን በሆነዉ ፌዴራላዊ ስርአትም የሀገራችን ህዝቦች በራሳቸዉ ቋንቋ እንዲተዳደሩ፤እንዲማሩና እንዲዳኙ፤ራሳቸዉ በመረጡት መንገድ ራሳቸዉን በራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩና ባህልና ወጋቸዉን ጠብቀዉ እንዲያቆዩ፤ የራሳቸዉን ዕድል በራሳቸዉ የመወሰን መብታቸዉን ተጠቅመዉ በነጻ ፍላጎታቸዉ ፤በህግ የበላይነትና በራሳቸዉ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በጋራ ለመመስረት የቃል ክዳን ሰነድ በሆነዉ በህገ -መንግስቱ መሰረት ቃል ተግባብተዉ በአንድነት እንዲቆሙ ለማድረግ ለዚህ ሁሉ ጥርጊያ መንገዱን ያደላደለዉ ኢህአዴግ እንደሆነ በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ሁሉም ህዝቦች ያለ አንዳች አድሎ እንዲካተቱና በተቋሙ ዉስጥ ከገቡ በኋላም በማንነታቸዉ ምክንያት አንዳችም የተለየ አድሎ እንዳይደረግና የእኩል ዕድል ተጠቃሚነት አንዲኖር ኢህአዴግ መራሹ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግስት ከፍተኛ ፍላጎትም ሆነ ቁርጠኝነቱ አለዉ ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡

መንግስት በህገመንግስቱ በተቀመጠዉ መሰረት መከላከያን ተዋኦዉን የጠበቀ ለማድረግ ቀላል የማይባሉ ጥረቶች ማድረጉ ባይቀርም የተፈለገዉንና ተስፋ የተደረገበትን ያህል አልተገበረም በሚል በተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበታል፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ ትችት በቀረበበት ግዜ ሁሉ ችግሩ መኖሩን አምኖ በመቀበል ለማስተካከል ጥረት እደረኩ ነዉ ከማለት ዉጭ ነቀፈታዉ ትክክል አይደለም በሚል ማስተባበያ የሰጠበትን ግዜ አላስታዉስም፡፡ ከተዋጽኦ ጋር የተያያዘ ችግር ካለ በምንም መንገድ ቢሆን መደበቅ ወይም ህዝቡም ሆነ ሌሎች ወገኖች እንዳያዉቁ ማድረግ ከቶ ስለማይቻል በቀላሉ መንግስትን የሚያሳጣ ነገር ነዉ፡፡ ችግሩን ነቅሶ ለማዉጣት እጅግ የቀለለ በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች በስም ዝርዝር ጭምር እየጠቀሱና በማስረጃ እያስደገፉ ሲያበጠለጥሉ ቆይተዋል፡፡ መንግስት የችግሩን መኖር በተቀበለዉ ደረጃ መፍትሄ እያስቀመጠ ነወይ? በሚለዉ ላይ ብዙዎቹን ሊያግባባ የሚችል የጋራ መልስ ቢኖር መንግስት ብዙ ጥረት እንዳደረገ ብናዉቅም ነገር ግን ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላም ሙሉ በሙሉ ከችግር መዉጣት አልቻለም የሚል ነዉ፡፡

መንግስት ከአምስት ዓመት በፊት ሲያቀርባቸዉ የነበሩ ምክንያቶች በወቅቱ በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት የነበራቸዉ ቢሆንም አሁን ከአምስት ዓመት በኋላም እነዚህኑ ምክንያቶች ለመቀበል የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ በከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ደረጃ ለማመጣጠን ብቃት ያለዉ ሰዉ አስከማፈራ ታገሱኝ ሲል የነበረዉን ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የቆየበትን ዘመን ብዛት እየቆጠሩ በዚህን ግዜ ሁሉ እንዴት ነዉ ብቁ ሰዉ ማፍራት የሚያዳግተዉ በሚል ቅሬታቸዉን ሳይደብቁ የሚናገሩ አሉ፡፡

ከዚህ በተለየ ደግሞ መንግስት ለማመጣጠን እንዲመቸዉ በርካታ ነባር አመራሮችን በጡረታ ማሰናበቱ ሃላፊነት የማይሰማዉና ግደየለሽ ተደርጎ እንዲቆጠር በማድረጉ ከመጀመሪያዉ ያለነሰ አቧራ ነዉ ያስነሳዉ፡፡ መንግስት በጦርነት ሰፊ ልምድ ያካበቱና የደለበ ተሞክሮ ያላቸዉን ሲኒየር ወታደራዊ አመራሮችን ለተዋጽኦ ብሎ ማሰናበቱ ሀገሪቱን ሆን ብሎ ለአደጋ ለማጋለጥ የተደረገ ደባ ነዉ የሚል ነቀፈታም ቀርቦበታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በተሰናበቱት ምትክ አዳዲስ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ መሰጠቱንም ያልወደዱለት በመብዛታቸዉ መንግስት አሁንም ከትችት ሊያመልጥ አልቻለም፡፡

በርግጥ ሁኔታዉ ለመንግስት አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ መንግስት እየወሰደ የነበረዉ ማስተካከያ እርምጃ ሁሉ ከትችት ለመሸሽ ብሎ ሳይሆን ያን ማድረግ ግዴታዉ ስለሆነና ስለሚያምንበትም ጭምር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ መንግስት በታዋጽኦ ምክንያት የተቋሙ ብቃት እየተጎዳ ነዉ በሚለዉና ማመጣጠኑ በበቂ ሁኔታ አልተሰራም በሚል በሚቀርቡ አርስ በርስ የሚቃረኑ ሁለት አስተያየቶች ግራ መጋባት አይኖርበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ የመካለከያ ተቋሙን ብቃት በማይጎዳ መንገድ ተዋጽኦን ለማስተካከል አስካሁን ከሄደበት መንገድ የተለየ ዜዴ ቀይሶ መስራት ያለበት ይመስለኛል፡፡

2/ ባለፉት ስርአቶች የብሄራዊ ተዋጽኦ ጉዳይ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ እንዴት ነበር ሲተገበር የነበረዉ?

በዘዉዳዊዉ አገዛዝ ዘመን ስለነበረዉ ሁኔታ በርግጠኝነት ለመናገር ባልደፍርም እኔ አስከማዉቀዉና እስከደረስኩበት ድረስ ለአስራ ሶስት ዓመታት ባገለገልኩበት የቀድሞ የደርግ ዘመኑ የመከላከያ ሰራዊት (አብዮታዊ ሰራዊት ) ዉስጥ ስለነበረዉ ሁኔታ በመጠኑ መናገር እችላለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን በንጉሱ ዘመን ስለነበረዉ ሁኔታ የተወሰነ ፍንጭ ሊሰጠን ከቻለ የቀድሞ የደርግ ባለ ስልጣን የነበሩት ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ ለንባብ ባበቁት “አብዮቱና ትዝታዬ” ከሚለዉ መጽሃፋቸዉ ላይ ያገኘሁትን መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ይላሉ ኮ/ል ፍሰሃ፤

“በአብዮቱ ዋዜማ ሀገሪቱ ፖሊስን ጨምሮ ከ70 በላይ ጄነራል መኮንኖች ነበሯት፡፡ ማዕረግ ያገኙት በችሎታ ሳይሆን ለስርአቱና ለንጉሰ ነገስቱ በነበራቸዉ ታማኝነታቸዉ ነዉ፡፡ አብዛኛዎቹ ጄነራል መኮንኖች ከባላባት ወገንና ታዋቂ ቤተሰቦች የተገኙ ናቸዉ፡፡ ከዝቅተኛዉ የህብረተሰብ ክፍል የመጡትም ቢሆኑ ከነበረዉ ስርአት ጋር ተቆራኝተዉና ተዋህደዉ ልክ በሲቪሉ ዓለም በስልጣን ላይ እንደነበሩት ጓደኞቻቸዉ ለዘዉዱ ፍጹም ታማኝና ባለሟል ነበሩ፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ በስተቀር አብዛኛዉ የጄነራልነት መዕረግ ያገኙት በወታደራዊ ብቃታቸዉና ችሎታቸዉ ሳይሆን ለስርአቱና በተለይ ለንጉሱ በነበራቸዉ ታማኝነት ነበር፤—ጄነራሎች ወታደሮቻቸዉን እንደግል አሽከራቸዉና እንደ ባሪያ ነበር የሚጠቀሙባቸዉ፡፡”

ኮሎኔል ፍሰሃ እንደሰጡን መረጃ ከሆነ በንጉሱ ዘመን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ቦታዎች በግል ለንጉሰ ነገስቱ ቅርብ በሆኑ ማሳፍንትና ንጉሳዊ ቤተሰቦች የተያዘ እንደነበርና የታችኞቹ የሰራዊቱ አባላት እንደባሪያ ወይም አንደ አሽከር ለአዛዦች የግል አገልጋይ እንደነበሩ ነዉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ስርአት ዉስጥ የህዝቦች እኩልነት ባልነበረበት ሁኔታ በሰራዊቱ ዉስጥም ከዚያ ዉጭ ይሆናል ተብሎ ስለማይጠበቅ በዚህ ላይ ብዙ መልፋት የሚገባን አይመስለኝምና ወደ ደርግ ስርአት እናምራ ፡፡

ባለፈዉ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ዘመን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ “ብሄራዊ ተዋጽኦን ማመጣጠን” ስለሚባለዉ ጉዳይ እንደ አጀንዳ ተነስቶ አይታወቅም፡፡ እኔ በበኩሌ ቃሉንም ለመጀመሪያ ግዜ የሰማሁት በዚህ አሁን ባለንበት ሰርአት ወቅት ነዉ፡፡ በደርግ ዘመኑ ሰራዊት ዉስጥ የተዋጽኦ ጉዳይ እንደ ችግር የሚቆጠር አሳሳቢ ጥያቄ ተደርጎ ተቆጥሮ አይታወቅም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በሰራዊቱ ዉስጥ አብረን ስንሰራ ከነበርነዉ ዉሰጥ ማን ከየትኛዉም ብሄር እንደሆነ ለማወቅ ሞክረን አናዉቅም፡፡ ማነዉ አማራ? ማነዉ አሮሞ? ማነዉ ትግሬ? ስንት አማራ፤ ኦሮሞ ወላይታ ፤ከምባታ ፤ትግሬ አለ? የሚባል ነገርም ተነስቶ አያዉቅም፡፡ አብሬያቸዉ ከሰራኋቸዉ የሰራዊቱ አባላት፤ የማእረግ አቻዎቼም ሆኑ አለቆቼም ጭምር የየትኛዉ ብሄር ተወላጅ እንደነበሩ በዚያን ግዜ ለማወቅ ሞክሬም አስቤም አላዉቅም፡፡

እኔ ራሴንም ብሆን ብሄራዊ ማንነቴን የጠየቀኝ ሰዉ አልነበረም፡፡ ከስንት ግዜ በኋላ ብሄራዊ ማንነቴን ለማወቅ ፍዳዬን ማየት የጀመርኩት እጅግ ዘግይቼ በዚህ ስርአት ዉስጥ ነዉ፡፡ ለዚያዉም አጣርቼ ለማወቅ ስለተሳነኝ በተጠየኩ ቁጥር አንድ ግዜ ሌላ፤ በሌላ ግዜ ደግሞ ሌላ የብሄር ማንነት ለራሴ ስሰጥ ነዉ የቆየሁት፡፡ በቀድሞዉ መንግስት ወቅት በስራ አስፈላጊነትም ሆነ ለቅጥር ተብለዉ በሚሞሉ መጠይቆችና መስፈርቶች ላይ ስለ ብሄር ማንነት የሚጠቅስ ነገር የነበረ ስለመሆኑ በጭራሽ አላስታዉስም ወይም አልነበረም፡፡

ባለፈዉ የደርግ ስርአት በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ጭቆናና አድሎ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብልኝ መልሴ አልነበረም የሚል ይሆናል፡፡ ስለአለፉት ስርአቶች በማንኛዉም ጉዳይ ላይ መንቀፍ እንደ ተገቢ ነገር በሚቆጠርበት ህብረተሰብ ዉስጥ ሆኖ እንደዚህ ዓይነት ምላሽ ለዉግዘት እንደሚዳርግ ባዉቅም ሲደረግ ያላየሁትን እንደ ተደረገ ቆጥሬ መናገር ግን አልችልም፡፡ የደርግ ስርአትም ሆነ አመራሩ ሊወገዝበትና ሊነቀፍበት የሚገባዉ አንድ ሺህ አንድ ምክንያቶችና ወንጄሎች እንዳለ አዉቃለሁ፡፡ ደርግ የለየለት አምባገነናዊና ጨቋኝ ስርአት የነበረ መሆኑ የሚያከራክርም አይደለም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በወቅቱ በነበረዉ ሰራዊት ዉስጥ በዘር በጎሳና በብሄር ልዩነት ላይ የተመሰረተ አድሎ ይደረግ ነበር የሚባል ክስ ካለ የተሳሳተ ክስ ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡

ደርግ በሚመራዉ ሰራዊት ዉስጥ በብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ ጭቆና አድሎና ልዩ ተጠቃሚነት አልነበረም ስል ከደርግ አገዛዝ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ባህሪይ ጋር በማነጻጸር እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በወቅቱ በሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ማንነትን መነሻ ያደረገ አድሎዊ አሰራና ጭቆና የለም ስል ደርግ የሁሉንም ህዝቦች እኩልነት በእምነት ደረጃ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ሆን ብሎ አስቦና ተጨንቆ የሠራዉ ስራ ነዉ እያልኩም አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ነገር የብሄር ማንነት ጉዳይ በሰራዊቱ ዉስጥ እንደ ጥያቄም እንደ ችግርም የሚታይ ስላልነበር በዚያን ወቅት ስለ ብሄራዊ ተዋጽኦ መነጋገር ትርጉም አልነበረዉም፡፡ ያልነበረ ነገር ላይ እንዴት መነጋገርም ሆነ መከራከር ይቻላል?

ሁለተኛ፤ ደርግ በወቅቱ እድሜዉና አካላዊ ብቃቱ ለዉትድርና የፈቀደለትን ጠበንጃ መሸከም የሚችል ወጣት ሁሉ ወታደር ለማድረግ በእግር በፈረስ በሚፈልግበትና ከፍተኛ የሰዉ ኃይል ፍላጎቱን ለማሟላት ከየመንዱ እያፈሰ ወደ ጦር ሜዳ በሚልክበት በዚያ ዘመን በማንነት ላይም ሆነ በእምነት ላይ የተመሰረተ ገዳቢ መስፈርት የሚያወጣበት አንዳችም ምክንት አልነበረዉም፡፡ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት እኔንም ጨምሮ በዚያን ዘመን ወደ ዉትድርና የገባን ወጣቶች ስለብሄራዊ ማንነታችንና ስለ ዘራችን አልተጠየቅንም፡፡ እሰከ መጨረሻዉም ስለዚህ ጉዳይ እንዴ ጥያቄ ተነስቶብን አያዉቅም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድበት በነበረበት የኤርትራ ምድር ከሠፈረዉ ሰራዊት መካከል በባለሌላ መዕረግተኞችም ሆኑ በከፍተኛ መኮንኖች ደረጃም ቢሆን ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተወላጆች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከአማጽያን ጋር ግኑኝነት ሊፈጥሩ ይችላሉ ከሚል ተገቢ ከሆነ ስጋት በመነሳት እንኳን የኤርትራ ተወላጅ የሆኑትን ለማግለል የተደረገ ሙከራ አልነበረም፡፡

በሃገሪቱ አመራር ደረጃም ከኦሮሞ፤ ትግራይ፤ ከአማራ ወዘተ የብሄር ማንነታቸዉ ከግምት ሳይገባ ለአመራሩ በነበራቸዉ ታማኝነት የተመደቡ እንደነበር በስም እየጠቀስን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ሌላዉ ቀርቶ የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ብሄራቸዉ ምን እንደነበረ እንኳን ያን ግዜ ቀርቶ ዛሬም ቢሆን በዉል አይታወቅም፡፡ በደርግ ዘመን በነበረዉ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት (አብዮታዊ ሰራዊት) ዉስጥም በከፍተኛ ወታደራዊ ማእረግተኞም ሆነ በታችኛዉ የሠራዊት አባላት ደረጃ አብላጫ ቁጥር የነበራቸዉ በግምት ደረጃም ቢሆን ኦሮሞዎች ይመስሉኛል፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ በጀግንነታቸዉና በወታደራዊ አመራር ብቃታቸዉ እጅግ የከበረ ስም ከነበራቸዉ ዉስጥ አብላጫዎቹ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡

በአየር ኃይልም ቢሆን እጅግ ብርቅ በነበረዉ የበረራ ሙያ ምልመላና ቀጠራ ሲደረግ የቀጠራ ቡድኖች ለቀጠራ ለመሄድ የሚጣደፉት በቅድሚያ ወደ ኦሮሚያ በተለይም ወደ ወለጋ አካባቢ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ በጦርሜዳ በሚሰሩት ጀግንነትም ሆነ በከፍተኛ ወታደራዊ አመራር እጅግ የከበረ ስም የነበራቸዉ ከፍተኛ መኮንኖች በአብዛኛዉ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ነበሩ፡፡ እንዲያዉም በደርግ ዘመን በቁጥር የሚበልጡ ጄነራል መኮንኖች ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ በንጉሱ ግዜም ቢሆን የገዘፈ ስም የነበራቸዉ ኦሮሞ ጄኔራል መኮንንች በርካታ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ አሁን እየተነጋገርን ባለነዉ ጉዳይ ላይ ባለፈዉ የደርግ ስርአት እኔ እንደ ማስታዉሰዉ ስለ ብሄራዊ ማንነት ጉዳይ በሰራዊቱ ዉስጥ እንደ አጀንዳ የተነሳበትና ወቅት አልነበረም፡፡ አለመነሳቱም ስህተት ነዉ ብዬ አላስብም፡፡ ፡

አሁን ላይ ሆኜ በደርግ ወቅት በሰራዊቱ ዉስጥ ስለ ነበረዉ የተዋጽኦ ጉዳይ ሳስታዉስ በወቅቱ ማንም ከጉዳዩ ያልቆጠረዉ አንድ መሰረታዊ ችግር እንደነበር እገነዘባለሁ፡፡ በወቅቱ ለምንድነዉ አንዳችን የሌላዉን ማንነት ለማወቅ ያልፈለግነዉ? ሌላዉ ቀርቶ የራሳችንን ማንነት እንኳን ለማወቅ ያለመሞከራችን ወይም ያለ መፈለጋችን መክንያት ከምን የመነጨ ነበር? ማንነትን ለመግለጽ የሚከለክል አሰራር ወይም መመሪያ ስለነበረ ነዉ ? እኔ ኦሮሞ ነኝ ፤እኔ ሲዳማ ነኝ፤እኔ አማራ ነኝ ወዘተ ብሎ ራሱንና ባህሉን ለማስተዋወቅ የሚፈልግ ሰዉ አለመኖሩ ከምን የመነጨ ነዉ?

ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ መስጠት ባልችልም ያነ የነበረዉን ሁኔታ አሁን ላይ ሆኜ ሳስታዉሰዉ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የራስን ማንነት ለመደበቅ የመፈለግ ነገር የነበረ ይመስለኛል፡፡ የዚህ መነሾም በወቅቱ በማንነትህ እንድትኮራ የሚያበረታታና ስለማንነት የሚጨነቅ አሰራር ስላልነበረ ይመስለኛል፡፡ የራስን ማንነት የመደበቅ ጉዳይ በደርግ ሰራዊት ዉስጥ በማንነት ላይ የተመሰረተ አድሎአዊ አሰራር ስለነበረ ሳይሆን በዘዉዳዊዉ ስርአት ወቅት ሰፍኖ ከቆየዉ የአማራ የበላይነት አስተሳሰብ ዘዉዳዊዉ ስርአት ከወደቀም በኋላ አመለካከቱ ቶሎ ሊጠፋ ባለመቻሉና በህብረተሰቡ ዉስጥም ይሄዉ ስሜት ሰፍኖ በመቆየቱ ከዚያ ህብረተሰብ የወጣ ወታደር ወደ ሰራዊቱ ከገባም በኋላ በማንነቱ ለመኩራት ድፍረት ማጣቱ ለዚያ ይመስለኛል፡፡

በደርግ ስርአት በንጉሱ ዘመን ነበረ እንደሚባለዉ ባይሆንም በአማራነት የመኩራትና በተለይ ከሌሎች አናሳ ብሄሮች የመጡት ደግሞ በማንነታቸዉ የመሸማቀቅና ከዚያም አልፈዉ ስማቸዉን ወደ አማራነት አስከ መቀየር የደረሱ የሰራዊቱ አባላትም እንደነበሩ አስተዉሳለሁ፡፡ እንደዚያ እንዲደርጉ ያስገደዳቸዉ አንዳችም አካል እንዳልነበር ግን ጠንቅቄ አዉቃለሁ፡፡ በወቅቱ ማንነትን በአደባባይ አዉጥቶ ለማስተዋወቅ የሚደረግ አንዳችም ጥረት አልነበረም፡፡ ከየትም ይምጣ ከየት ማንም ለማንም ግድ አልነበረዉም፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ተዋጽኦ ብሎ ነገር እንደ ቁምነገር ተነስቶ አይታወቅም፡፡ አመራሮች ራሳቸዉ ለጉዳዩ ግድም አልነበራቸዉም፡፡ ማንነት የግል ጉዳይ ተደርጎ ነበር ሲታይ የነበረዉ፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ ከጭቁን ብሄር የመጣ ነዉ ተብሎ በተለየ የሚደረግ ማበረታቻ አልነበረም፡፡ በስራ አፈጻጸም ግምገማ ኦሮሞዉም ትግረዉም ከንባታዉም ወዘተ እኩል ይገመገማል፡፡ የሰራዊቱ አባላት ስለብሄራዊ ማንነት ግድ የማይሰጣቸዉ መሆኑ አንድ ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችለዉ አብዛኛዎቹ የሰራዊት አባላት የትዳር ጓደኛ ያደረጉት ከብሄራቸዉ ዉጭ የነበሩትን ነዉ፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ የግል የርስበርስ ጓደኝነትም ቢሆን በማንነትና በቋንቋ የተመሰረተ ሳይሆን እንዲሁ በግል በመግባባት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነበር፡፡ ከስራ ወጭ ከጓደኞችህ ጋር ባሰኛችሁ ቋንቋ ትነጋገራላችሁ እንጂ የግድ በአፍ መፍቻዬ ቋንቋ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡

ይህ ሲባል የሆነ በማንነት ላይ የተለየ ስሜት የሚሰማቸዉ አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ አናሳ ከሚባሉ ህዝቦች የመጡ (ቁጥራቸዉ እጅግ አነስተኛ የነበረ ቢሆንም) ስለማንነታቸዉ፤ ስለ ባህላቸዉና እምነታቸዉ ለመነጋገር ድፍረቱ አልነበራቸዉም፡፡ በዚህ ምክንያትም ያን ግዜ ልንረዳላቸዉ ያልቻልነዉ በዉስጣቸዉ አፍነዉት ያቆዩት የሆነ ዓይነት የበታችነትና የመገፋት ስሜት እንደነበራቸዉ ለመገንዘብ የቻልኩት አሁን ነዉ፡፡ ያም ቢሆን በዚያን ዘመኑ ሰራዊት ዉስጥ የማንነት ጉዳይ እንደ ችግር የሚቆጠር ስላልነበር ተዋጽኦን ለማመጣጠን ተብሎ የሚሰራ ስራ አልነበረም፡፡

በደርግ ዘመን በሰራዊት ዉስጥ ከአንዳንድ ህዝቦች የወጡ የሠራዊት አባላትን ማግኘት ብርቅ የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሀራሪ ህዝቦች፤ከአፋር ፤ሶማሌ፤ በደቡብ ክልል ከሚገኙ አንዳንድ ህዝቦች የወጡ የሰራዊት አባላት ምናልባት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ለምንድነዉ ከሶማሌ፤ከአፋር ፤ከኮምሶ ወይንም ከሀረሪ ወዘተ ከብሄሩ ህዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ በሰራዊቱ ዉስጥ ሊካተቱ ያልቻሉት? የሚለዉ ነዉ፡፡ እንደ እኔ እምነት በወቅቱ ከእነዚህ ህዝቦች በርከት ያለ ቁጥር ያለዉ ወጣት ወደ መከላከያ ያልገቡበት ምክንያት በነሱ ላይ ገደብ የሚጥል ወይም በር የሚዘጋ የመግቢያ መስፈርት ስለነበረ ሳይሆን እነሱ ራሳቸዉ ወታደር ለመሆን ስላልፈለጉ ነዉ፡፡

ከእምነት፤ከባህልና ልማድ ወዘተ ምክንያት የተነሳ ለዉትድርና ሙያ ብዙም ፍላጎት የለላቸዉና ልጆቻቸዉን ወታደር ለማድረግ የማይፈቅዱ ህዝቦች እንዳሉም ሊዘነጋ አይገባዉም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ለዉትድርና ሙያ ከነበራቸዉ ጥላቻ የተነሳ የትኛዉም የቤተሰባቸዉ አባል ወታደር እንዲሆን የማይፈቅዱም ነበሩ፡አንድ በቅርብ የማዉቀዉና አብሬ ለአመታት የሰራሁት ማእረጉ ሻለቃ የበበረ መኮንን እዚሁ መሃል አገር አዲስ አባባ የነበሩ ወላጆቹ ሳይቀሩ ሻለቃ ማእረግ ደርሶና በ83 ዓ/ም ተፈናቅሎ ወደ ወላጆቹ አስከሚሄድ ድረስ ወታደር የነበረ መሆኑን አያዉቁም ነበር፡፡ ስለደበቃቸዉ ማለት ነዉ፡፡

በቀድሞዉ የደርግ ስርአት ይቅርና ዛሬም ቢሆን በሀገራችን በመከላከያ ሰራዊታችን ዉስጥ ያለዉ የህዝቦች ዉክልና በሀገሪቱ ካሉት ህዝቦች ቁጥር ጋር በመቶኛ የሚመጣጠን ነዉ ማለት አይችልም፡፡ የዚህ አይነት ነገር መቼም ቢሆን ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ በታችኛዉ የሰራዊት አባል ደረጃ ከህዝቡ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ዉክልና ሊኖር ባይችል እንደችግር የሚቆጠርም አይደለም፡፡ ወታደር ለመሆን ፈልጎ የተከለከለ ህዝብ አስከሌለ ድረስ አለመመጣጠኑ እንደችግር የሚታይ አይደለም፡፡ በደርግ ስርአትም ቢሆን ወደ ዉትድርና ሙያ እንዳይገባ የተከለከለ ወይም በሩ የተዘጋበትና የዚህ ብሄር አባል ስለሆንክ ወይም ደግሞ የዚህ እምነት ተከታይ ስለሆንክ አይፈቀድልህም ተብሎ የተከለከለ ሰዉ አልነበረም፡፡

በደርግ ዘመን በሰራዊቱ ዉስጥ በከፍተኛ አዛዦች ደረጃ ግልጽ አድሎ ይደረግ የነበረዉ በብሄር ማንነት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ በወጡበት የሆለታ ገነት የጦር ት/ቤት የ19 ኮርስ ምሩቃን የነበሩትን በቀዳሚነት በመሾም ነበር፡፡ በዚሁ መሰረትም በወቅቱ የነበረዉ ሰራዊት (አብዮታዊ ሰራዊት) አስከተበተነበት ግንቦት 1983ዓ/ም ድረስ አገሪቱ ከነበሯት ጄኔራል መኮንኖች መካከል ፤ሃያ አምስቱ የሊቀመንበር መንግስቱ ኮርስ ሜቶች ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ በደርግ ስርአት ዉስጥ አድሎአዊ አሰራር ሰፍኖ እንደነበር በግልጽ የሚያሳይ ቢሆንም ነገር ግን አድሎ ሲደረግ የነበረዉ በብሄር ማንነት፤በሃይማት ወይም በቋንቋ ላይ ተመሰርቶ ሳይሆን በግል ታማኝነት በፖለቲካ ዝንባሌና በይበልጥ ደግሞ በኮርስ ሜት ላይ ነበር፡፡

3/ በሌሎች አገሮች በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ተዋጺኦ ማኔጅ የሚደረግበት መንገድ

ተዋጽኦ በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ማኔጅ የሚደረግበት መንገድ ከአገር አገር የተለያየ ነዉ፡፤ተዋጽኦ ሲባል የብሄር፤የሃይማኖት፤የጾታ፤ የቋንቋ፤የባህል፤ የቀለም የወ.ዘ.ተ ሊሆን ይችላል፡፡ የተዋጺኦ ጥያቄ እንደ የሃገሩ ልዩ ሁኔታ ዘርፈ ብዙ ነዉ፡፡ የጉዳዩ ዉስብስብነትና የችግሩ ስፋት የሁሉም ሀገራት አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች የሃይማኖት ጉዳይ ጨርሶ እንደ ጥያቄ የሚነሳ ጉዳይ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ ሃይማኖት ብቻ በይፋ እዉቅና ባገኘበትና እንዲያዉም እንደ መንግስታዊ ሃይማት በሚቆጠርበት ሁኔታ በርካታ ተከታይ አለዉ ከተባለዉ ሃይማት በተጓዳኝ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከሃይማት እኩልነት አንጻር በመከለከያ ዉስጥ ታዋጽኦን ለመጠበቅ የዚያ ስርአት ባህሪይ ባይፈቅድለትም የመብት ጥያቄ እንዳይነሳ ማድረግ ግን አይችሉም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ህብረብሄራዊ ባልሆኑና የአንድ ብሄር አገር ናቸዉ በሚባሉ አንዳንድ አገሮችም ቢሆን የማንነት ጥያቄ ከብሄር ደረጃ ወርዶ በጎሳ በዘር በነገድ ወዘተ የሚሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል እንደሆን እንጂ የማንነት ጥያቄ ጭራሽ አይነሳም ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል የጾታ ተዋጺኦ ጉዳይም የሁሉም አገሮች የጋራ አጀንዳ ነዉ፡፡ በርግጥ እንደ ሀገራቱ ልዩ ሁኔታ እኩል አሳሳቢ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለዘመናት የሃይማኖት መቻቻል ሰፍኖ በቆየበትና በሃይማኖት ሳቢያ ሊጠቀስ የሚችል ችግር ባልነበረባት ሀገራችን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ በእምነት ላይ የተመሰረተ አንዳችም ገደብ ባለመኖሩ የእምነት ጉዳይ እንደ ችግር የሚቆጠርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የጾታ እኩልነት ጥያቄ በሰራዊቱ ዉስጥ በሴቶች ላይ የተለየ ክልከላና ገደብ አስከሌለ ድረስ የጾታ ጉዳይ እንድ ችግር የሚቆጠርበት ምክንያት አይኖርም፡፡

3.1/ በመከላከያ ዉስጥ ሁሉን ህዝቦች በማካተት ረገድ የተለያዩ ተሞክሮዎች

በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ አድሎአዊ አሰራር በማስወገድ እኩል ዕድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ወደ ተቋሙ ያለ አድሎ የሚገባበት ሁኔታ መፈጠር ይርበታል፡፡ በቅድሚያ ወደ ተቋም ለመግባት በሩ ለሁሉም ከፍት እንዲሆን ከተደረገ በቁጥር የማመጣጠንና የመብት እኩልነት ጉዳይ ቀጥሎ የሚመጣ ነዉ፡፡ ስለዚህ ከምልመላና ቀጠራ ጀምሮ የሚሰራ አድሎአዊ አሰራር ካለ በቀጣይም ተዋጺኦን በመጠበቅ ጥሬት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጸኢኖ ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ መወሰድ የሚገባዉ ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነዉ፡፡

ከዚህ አንጻር በተለያዩ አገሮች የሚሰራባቸዉ ሶስት አሰራሮች አሉ፡፡ እነሱም ቀጥለን ለማየት እንሞክር፡፡

አንደኛዉ መንገድ፤- አግላይና አድሏዊ አሰራር

የመጀመሪያ አሰራር ሆን ተብሎ በልዩነት ላይ የተመሰረተ የምልመላ አሰራር (differential mode) መከተል ነዉ፡፡ በዚህ መሰረት ሆን ተብሎ ልዩነት በመፍጠር አድሏዊነት የሚንጸባረቅበት አሰራር ነዉ፡፡ ገና ከምልመላ ጀምሮ የተወሰኑ ብሄር ፣ህዝቦች ወይም ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ በማካተት ለሌላዉ ህዝብ ግን በሩን ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋ ፍጹም አግላይ የሆነ አሰራር ነዉ፡፡ በምልመላና ቀጠራ ወቅት አንዳንድ ህዝቦች እንዳይካተቱ ለማድረግ ተብሎ ሆን ተብሎ የሚሰራ ደባ ነዉ፡፡

የዚህ መነሻዉ ብዙ ነዉ፡፤አንደኛዉ ከዚያ ህዝብ የወጡትን በመከላከያ ዉስጥ ማካተት ማለት ወደፊት ለአገዛዙ ወይም በስልጣን ላለዉ ብሄር አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ ከሚል ስጋት የሚመነጭ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ለነዚህ ህዝቦች ካላቸዉ ንቃት የሚመነጭ ሆኖ ለዉትድርና አይመጥኑም፡፡ ለጦርነት ወቅት ፌሪዎች ናቸዉ፤አንዳንዴም ደግሞ ከባህልና ከእምነት ጋር ተያይዞ እመነታቸዉና ባህላቸዉ ለዉትደርና ብቁ አያደርጋቸዉም በሚል ሰበብ የሠራዊቱ አባል እንዳይሆኑ ይደረጋሉ፡፡ በአጋጣሚ ወደ መከላከያ መግባት የቻሉ ካሉም በሰበብ በአስባቡ ከእድገት ሹሜትና ከትምህርት ወዘተ ይታለፋሉ፡፡ ህዝብን እንደ ህዝብ ለዉትድርና የሚመጥንና የማይመጥን የሚባል አመለካከት ካለ ልዩነቱ አጋጣሚ ነዉ የሚባል ሳይሆን ሆን ተብሎ እንደ ስርአት በፖሊሲና በመመሪያ የተደገፈ ተቋማዊ ዘረኝነት (institutional racism) ነዉ፡፡

ሁለተኛዉ መንገድ፤- የተመጣጠነ (equivalent mode) አሰራር፡

በዚህ መሰረት ሁሉንም ህዝቦች ያለአንዳች ክለከላ ወደ ተቋሙ እንዲገቡ የሚፈቅድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አንድ ግዜ ወደ ተቋሙ ከተገባም በኋላ የሁሉንም ህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ እንዲቻል የኮታ (quota) አሰራርን የሚከተል ነዉ፡፡

የኮታ አሰራር ከፍትሃዊነት አንጻር በእጅጉ የሚደገፍ ቢሆንም ነገር ግን ከወታደራዊ ተቋሙ የብቃት ፍላጎት አንጻር ሲመዘን ተቃባይነት የሚያሳጣዉ አንዳንድ ድክመቶች እንዳሉበት መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን እንመልከት፤

አንደኛ፡- የኮታ አሰራር እንደ ድክመት የሚቆጠርበት ሁኔታዎች ዉስጥ አንዱ በበቂ ሁኔታ ተወዳዳሪ የሚሆን ሰዉ ማግኘት ካለመቻል ጋር የተያያዘ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ የኮታ አሰራር በዋነናት ታሳቢ የሚያደርገዉ የህዝብን ብዛት በመሆኑ ወደ ተቋሙ የመግባት ዕድሉ ክፍት ቢሆንም በተጨባጭ ከሁሉም ህዝቦች ተመጣጣኝ የሆነ ቁጥር ይገባል ተብሎ ስለማይጠበቅ በዚህ መነሾ በእያንዳንዱ የስራ ሃላፊነትና ሹመት ቦታ ሊመጥን የሚችል ሰዉ ከየብሄሩ ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡

ሁለተኛ፡- በኮታ ለማመጣጠን ብቻ ተብሎ ለቦታዉ የማይመጥኑና ብቃቱ የጎደላቸዉን የመቀበል ዝንባሌ እየተዘወተረ ሲሄድ በሂደት ተቋሙን በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ያለ ብቃቱ ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የደረሰ አመራርም ለዚህ ቦታ ያበቃዉ የግል ብቃቱ ሳይሆን በማንነቱ ምክንያት በኮታ አሰራር መሆኑን ስለሚረዳ በራስ መተማመን አይኖረዉም፡፡ በዚህ መንገድ ለተሾመ አመራር በስሩ ያሉ የሰራዊት አባላትም በእምነት አመራሩን ለመቀበል ልባቸዉ አይፈቅድላቸዉም፡፡ የኮታ አሰራር በደፈናዉ የሚጣል ወይም የሚናቅ ባይሆንም የተቋሙን አቅም አስከሚያዳክም መድረስ አይገባዉም፡፡

የሀገሪቱ መንግስት በተለይ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ከሁሉም ህዝቦች በኮታ ለማዳረስ ፍላጎቱ ቢኖረዉ እንኳን ተግባራዊ ለማድረግ ግን የሚቻል አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያትም ይህን ዘዴ በዉስን ደረጃ ለመጠቀም የሚፈቅዱ አንዳንድ አገሮች ባይጠፉም በተግባር ሲጠቀሙ የሚታየዉ ግን በከፍተኛ አመራር ሃላፊነት ቦታ ሳይሆን ይልቁንም በታችኛዉ አመራርና መሰረታዊ የሰራዊት አባል ደረጃ ነዉ፡፡

ሶስተኛዉ መንገድ፤- (universality) ወይም ምሉእና ሁሉን አካታች የሆነ አሰራር፤

በዚህ መሰረትም መከላከየ ተቋሙ ማንንም ከማንም ሳይለይ ለማንም ሳያዳላና በማንም ላይ አድሎና ገደብ ሳያዳርግ ብቃቱ ላለዉና መስፈርቱን ለሚያሟላ ቅድሚያ የሚሰጥ አሰራር ነዉ፡፤ድሮ ባለፈዉ ስርአት ተበድሏል ወይም በዕድገት ወደኋላ ከቀረ አካባቢ የመጣ ነዉ በሚል የተለየ እገዛ ወይም ሮሮት አያደርግም፡፡ አንዱን ለመጥቀም ሌላዉን ለመጉዳት ቢሎ የተለየ መስፈርት አይጠቀምም፡፡ በሩን ለሁሉም ክፍት ያደርጋል፡፡ መሮጫ ሜዳዉ ለሁሉም እኩል ነዉ፡፡ የበረታ፤ ብቁ ሆኖ የተገኘና ከሌላዉ የላቀ ችሎታ ያለዉ የመጀመሪያ ተመራጭ የሚሆንበት አሰራር ነዉ፡፡

ይህ አሰራር ምርጥ የሆኑ ሰዎችን ብቻ (quality people) የሚመለምልና ለሃላፊነት ለማጨትም ከሁሉም በላይ ብቃት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ጠንካራ ተቋማዊ ብቃትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለዉ፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ፖለቲከኞች ዘነድ መተቸቱ አልቀረም፡፡ የትችቱም መነሾ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አግላይና ጨቋኝ አሰራርና ከኋላቀር ባህል ምክንያት ወደ ኋላ የቀሩ ህዝቦችን እንዲሁም ሴቶች ያለፉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ከግምት ሳያስገባ ሁሉንም በአኩል መመዘን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚገለጽ አድሎአዊነት ነዉ የሚሉ ናቸዉ፡፡ ይህ አሰራር ከትችት ባያመልጥም ከብቃት አንጻር እንከን የሚወጣለት አይደለም፡፡

3.2/ በመከላከያ ዉስጥ ተዋጺኦን ከመጠበቅ አንጻር በፖሊሲና በአደረጃጀት አንጻር የሚታዩ የተለያዩ አሰራሮች ፤

በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ በቁጥርም ሆነ በእኩል አድል ተጠቃሚነት አንጻር የተመጣጠነ ለማድረግ በተለያዩ አገሮች ለዚህ ይበጃል የሚሉትን የተለያዩ ፖሊሲዎችንና አደረጃጀቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በሶስት ዘርፍ ከፍሎ ማዬት ይቻላል፡፡

ምድብ-1፤- በዚህ ምድብ ዉስጥ የሚካተቱ አገሮች ጎን ለጎን የተለያዩ መዋቅሮችን (Parallel military structures) የሚከተሉ አገሮች ናቸዉ፡፡ ከነዚህ አገሮች መካከል ካናዳ ቤልጅየም፤ዩናይትድ ኪንግደም (U.K.), ስዊዘርላንድ ይጠቀሳሉ፡፡ ፡

እነዚህ አገሮች በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ የሁሉም ህዝቦች ተዋጽኦ እንዲጠበቅ ለማድረግ ሲሉ በማንነት ላይ ተመስርተዉ በሰራዊቱ ዉስጥ ጎን ለጎን የተለያዩ የሰራዊት ክፍሎችን ወይም አደረጃጀቶችን ይመሰርታሉ፡፡ ፤ጎን ለጎን ለማደረጃት አንደ መነሻ የሚጠቀሙት እንደ ሁኔታዉ በብሄር፤በጾታና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በስዊዜርላንድ በመጡበት ብሄር ወይም በሚናገሩት ቋንቋ ላይ ተመስርተዉ የወታደራዊ ክፍሉ አባላት እንደማንነታቸዉ እንደመጡበት አካባቢና እንደሚናገሩት ቋንቋ (cantonal or linguistics line) ከነ መሪዎቻቸዉ ለየብቻ በአንድ ዩኒት ወይም አሃድ የሚደራጁበት አሰራር ነዉ፡፡ ይህ ማለት አንድ ወታደራዊ ክፍል ለመሳሌ አንድ ሻምበል ጦር አባላት በሙሉ ከነአዛዣቸዉ ከአንድ ብሄር ወይም አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ይሆናሉ ማለት ነዉ ፡፡

የዚህ መብት ተጠቃሚ የሚሆኑት ግን የሀገሪቱ ዋነኛ ዜጎች (constituent nations) የሆኑት እንጂ ለሁሉም የሚያገለግል አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ለሚደራጁ የጦር ክፍሎች በአዛዥነት የሚመደቡት የክፍሉ አባላት የሚናገሩት ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ብቻ ተመርጠዉ ነዉ፡፡ ሌሎች የጦር ክፍሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ይደራጃሉ፡፡ በዚህ መንገድ በቋንቋም ሆነ በህዝብ ማንነት በአዛዥነት የሚመደቡት የቋንቋዉ ተናጋሪ መሆን ያለባቸዉ ሲሆን ይህ ሁኔታ የሚያገለግለዉ ለታችኛዉ የሰራዊቱ አደረጃጀት እርከን ብቻ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ በከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ደረጃ ወይም በመከላከያ ደረጃ በከፍተኛ የአመራር እርከን ሲሆን ለዚያ ቦታ የሚመደቡ ከፍተኛ መኮንኖች ሁለቱንም ቋንቋ መናገር የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆኑት ካናዳና ቤልጂየም ሲሆኑ ለምሳሌ በካናዳ የእንግሊዘኛ ተናጋሪና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ህዝቦች ናቸዉ በዚህ ደረጃ ታሳቢ የሚደረጉት፡፡ ለከፍተኛ አመራር የሚታጩ መኮንኖች ሁለቱንም ቋንቋ ጠንቅቀዉ የሚናገሩ (bilingual) መሆን ይገባቸዋል፡፡

ይህ አሰራር ለዋናዎቹ መስራች ለሚባሉ ህዝቦች ካልሆነ በስተቀር ለሌሎች በቁጥር አናሳ ህዘቦች (non-constituent minorities).ትኩረት የሚነፍግ አሰራር ነዉ፡፤በተጨማሪ ለአተገባበር ምቹነት የሌለዉና ከፍተኛ ወጭም የሚጠይቅ አሰራር ነዉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ለዘመናት ተፋቅሮ ለኖረ ብቻ ሳይሆን መጤና ሀገር ፈጣሪ ህዝብ የሚባል በለለበት አገር የዚህ ዓይነት አሰራር በመከላከያ ዉስጥ ለማምጣት መሞከር ቀርቶ ማሰብ በራሱ የሚገባም አይደለም፡፡

ምድብ-2፤-በዚህ ምድብ የሚካተቱት አናሳዎችን ለማመጣጠን ተበሎ የተለየ ፕሮግራም ያላቸዉና በሰራዊቱ ዉስጥም ቅይጥና ያለአንዳች ልዩነት ሁሉን አቃፊ የሆነ አደረጃጀት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ ከዚህ አኳያ በዋነኛነት ተጠቃሽ የሚሆኑት ዩናይትድ ሰቴትስ፤ አዉስትራሊያና ኒዉዝላንድ ናቸዉ፡፡ እነዚህ አገሮች በተለያዩ ግዜያት በፍልሰት የመጡ የተለያዩ ህዝቦች ያላቸዉ ሆኖ የሁሉንም መብት በእኩል ደረጃ ለማመጣጠን የሚረዳ ፖሊሲና ፕሮግራም የሚከተሉ ናቸዉ፡፡ በነዚህ አገሮች በየትኛዉም ደረጃ የሚገኙ የጦር ኃይሉ ክፍሎች ነጭ አሜሪካዉን፤ አፍሪካ አሜሪካዉንና ሴቶችም ጭምር ያለ አንዳች ልዩነት በአንድ ላይ የሚደራጁበት አሰራር ነዉ፡፡

በነዚህ አገሮች ተዋጺኦን ለተቋሙ ብቃት ችግር በማይሆንበት መልኩ በሚገባ የተጠናና በፖሲሲ የታገዘ የዳይቨርስቲ ማኔጅመነት አሰራር ይከተላሉ፡፡ በቁጥር አናሳ የሆኑ ህዝቦችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚረዱ የሚረዱ ተጨማሪ እርምጃዎችንም ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ አገሮች በታችኛዉ እርከን ደረጃ ተዋጺኦን በተሳካ ሁኔታ የተገበሩ ቢሆንም በከፍተኛ እርከን ደረጃ አሁንም ይቀራቸዋል፡፡ በቁጥር ከማመጣጠኑ ባሻገር እኩል አድል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አሰራርም ይከተላሉ፡፡

ምድብ-3፤ -ለተዋፅኦ ብለዉ አንዳችም የተለየ አሰራርም ሆነ አደረጃጀት የማይከተሉ በዚህ ምድብ ስር የሚካተቱ አገሮች ፈረንሳይ፤ ጀርመን፤ ሮማኒያና ቡልጋሪያ የመሳሰሉት አገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን አገሪች ለየት የሚያደርዉ በነዚህ አገሮች በታሪክ ሁልጊዜም የአንድ ብሄር የበላይነት ሰፍኖ የቆየበት መሆኑና በአንጻሩ ደግሞ እኩል ተደማጭነት ያልነበራቸዉ ሌሎች ህዝቦች መኖር ነዉ፡፡ በነዚህ አገሮች ወታደራዊ ከፍሎች ለአናሳ ህዝቦች አንዳችም ትኩረት ባላደረገ መንግድ የሚደራጁ ናቸዉ፡፡ በሰራዊታቸዉ ዉስጥ አናሳ ህዝቦችን መብት ለመጠበቅ ተብሎ የሚሰራ አንዳችም ተዋፅኦ ማመጣጠን የሚባል ጉዳይ በአጀንዳነት የሚነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡

ሁልጊዜም የበላይነት ያለዉን ማህበረሰብ (ብሄር) ጥቅም ለመጠበቅ ካልሆነ በስተቀር የሌሎች መብት ከቁምነገር የሚቆጠር አይደለም፡፡ ወደ መከላከያ መግባት ለሚፈልጉ የተለየ ማበረታቻ የለም፡፡ በሰራዊቱ ዉሰጥ ቁጥራቸዉ በርከት ያለ ከአናሳ ህዝቦች የሚገኙ ቢሆኑም በመኮንንነት ደረጃ ግን ቁጥራቸዉ እጅግ አነስተኛ ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሰራር ዓይነተኛ ቸግር የአናሳ ህዝቦችን መብት ከጉዳይ የማይቆጠር መሆኑ (non-issue) ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም በሰራዊቱ ዉስጥ ዉስጣዊ ዝምድናና ቁርኝት (cohesion) እጅግ ደካማ ከመሆኑም ሌላ በወታደራዊ ተቋሙ ዉስጥ ማህበራዊ ሰላም ለማስፈን አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡

3.3/ እኩል እድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተብሎ ልዩ ማበረታቻና እገዛ የማድረግ አሰራር

በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥ ማንም ከማንም ልዩነትና አድሎ ሳይደረግበት በሁሉም ረገድ እኩል መብት ሊኖረዉ ይገባል ሲባል ከዚህ ቀደም በነበረዉ ጭቆናና ኋላ ቀር ባህል ምክንያት እንደሌላዉ ተጠቃሚለመሆን ያልቻሉና ዕድሉን ለተነፈጉ አሁን ዕድሉ ለሁሉም ክፍት ስለሆነ ብቻ እኩል ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ነዉ፡፡ ፖሊሲዎች ስለተሻሻሉና በሀገሪቱ ህገመንግስት መብታዉ እዉቅና ሲላገኘ ብቻ በተግባር በአንድ ግዜ ተጠቃሚ መሆን አይችሉም፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ የሹመት የትምህርትና ሌሎች ዕድሎች ብቃትን እንደ ዋነኛ መስፈርት አስከተከተሉ ድረስ ከዚህ በፊት ወደ ኋላ ለቀሩ ህዝቦች እኩል ተወዳዳሪ ለመሆን እንደማይችሉ እሙን ነዉ፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ ተቋሙ ለነዚህ ለዘመናት ዕድሉን ለተነፈጉና በእድገትም ወደ ኋላ ለቀሩ ወገኖች የጠለየ ማበረታቻና ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ልዩ ማበረታቻ (affirmative action)የቀድሞ በደላቸዉን ለመካስ ወይንም ተጠቃሚ የነበረዉንና ያልነበረዉን ቦታ ለመቀያየር እንደሚሰራ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባዉም፡፡ የልዩ ማበረታቻ አሰራር በአሜሪካ ጥቁሮችንና ሴቶችን ለማበረታታት ተብሎ ለብዙ ግዜ ሲሰራበት ቢቆይም በኋላ ግን ራሳቸዉ ሴቶችና አፍሪካዊ አሜሪካዉያን ተቃዉሞ በማሰማታቸዉ አሰራሩ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ የተቃዉሞአቸዉ መነሻም ለነሱ ተብሎ ልዩ ማበረታቻ ማድረግ ከሚሰጠዉ ጥቅም ይልቅ ሁልግዜም የበታችነት እንዲሰማቸዉ ያደርጋል የሚል ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ለሴቶችና ለጥቁሮች ሲደረግ የነበረዉን ልዩ ማበረታቻ ሲቃወሙ የነበሩት ሌሎች ወገኖች ደግሞ ዘረኝነትንና የጾታልዩነትን በተለየ መንገድ እንደመተግበር ይቆጠራል በሚል ነዉ፡፡

4/ ተዋጽኦን በሚመለከት የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶች፤

4.1/ ከትምከህትና ጠባብነት የሚመነጩ አደገኛ አመለካከቶች፤

ተዋጽኦን በመተግበር ረገድ ደንቃራ የሆኑ አመለካቶችን ግዜ ሳይሰጡ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ከነዚህ አመለካከቶች መካከል የተወሰኑትን ቀጥዬ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

* አንደኛዉ አመለካከት ጭፍን ጥላቻ፤ ልዩነት፤ (prejudice and discrimination) ነዉ፡፤የዚህ ዐመለካከት አራማጆች ብዙዉን ግዜ ራሳቸዉን ከሌለዉ በተለየ እንደገዥ መደብ የሚቆጥሩ፤በስርአቱ ከሌላዉ የተሻለ ቦታሊኖረን ይገባል የሚል የገዥነትና የበላይነት ስሜት የተጠናወታቸዉ ሆነዉ ሁሉም መልካም አድሎች ሁሉ በቅድሚያ ለኛ መሆን አለበት በሚል እሳቤ በራስ ወዳድነት መንፈስ ሌላዉን የመናቅ እነሱ በጥጋብ ተወጥረዉ ሌላዉ የበታችነቱን አሜን ብሎ ተቀብሎ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር የመፈለግ አደገኛና አመለካከት ነዉ፡፡

ከዚህ ጋር በተጓዳኝ ሌላዉ ተጠቃሽ የተዛባ አመለካከት ደግሞ ለሁሉም ጉዳይ የራስን ብሄር ማዕከል በማድረግ (ethnocentrism) ሌላዉን ግን ችላ የማለት አመለካከት ነዉ፡ የራስን ማንነት እንደ ልቀት ምንጭና እንደ መታደል የመቁጠርና ሌለዉ ግን አዳናቂና አድማቂ ወይም ቆሞ አጨብጫቢ ከመሆን ያለፈ የረባ ቦታ እንዳይኖረዉ የመፈለግ እጅግ አስቀያሚ ዝንባሌ ነዉ፡፡

* ሁለተኛዉ አመለካከት ደግሞ አንድን ብሄር ወይም ህዝብ አንዱም ከሌላዉ የማይሻል አድርጎ በጅምላ ደካማና የማይረቡ አድርጎ የመቁጠር አመለካከት(stereotyping) ነዉ፡፡ ለምሳሌ እነሱ ከሚናገሩት ቋንቋ ዉጭ የወጣ ለሃላፊነትና ለአመራርነት ብቁ ሊሆን እንደማይችል ብቻ ሳይሆን ጭራሽ መታሰብም እንደለለበት የሚያስቡ ናቸዉ፡፡ ሰዎችን በግላቸዉ ከሚኖራቸዉ ብቃት አንጻር ሳይሆን ከወጡበት ህዝብ ማንነት ጋር በቀጥታ በማቆራኘት ማንነትን እንደመስፈርት በመዉሰድ በጅምላ ለአመራር ብቁ የሚሆኑና የማይሆኑ ለተራ ወታደርነት እንጂ ለኮሎነልነት ለጄነራልነት ሊታቡ እንደማይገባ የመቁጠር እጅግ አስቀያሚ አመለካከት ነዉ፡፡

ይህ ሁኔታ የሚታየዉ በብሄር ማንነት ላይ ብቻ ሳይሆን በእምነት ተከታነት ወይም ሃይማኖትን መነሻ ያደረገ እንዲሁም በጾታ ላይ ተመሰርቶ በተለይ ሴቶችን በጅምላ በመናቅ ለተሻለ ሃላፊነትና ለቁምነገር እንዳይታሰቡ የሚያደርግ አመለካከት ነዉ፡፡ ጭቆናዉና በደሉ የቱንም ያህል ቢሆን የተወሰኑ ጥቂት ሰዎች በራሳቸዉ ጥረት የተሸለ እዉቀት ያለቸዉን በብቃት ደረጃም የማይታሙ ሆነዉ እያለ የዚያ ወይም የዚህ ማህበረሰብ አባል በመሆናቸዉ ብቻ ያዉ አንድ ናቸዉ በሚል በጅምላ ዉድቅ ይደረጋሉ፡፤

* ሶስተኛዉ ደግሞ በህዝቦች መካከል ልዩነት የመፍጠር ጉዳይ ጥቅምና መልካም አድል ከማግኘትና ከማጣት አንጻር ብቻ የሚገደብ ሳይሆን እንዲያዉም ከሁሉም በላይ እጅግ የሚያስቀይመዉ ደግሞ ያለመታመን ወይም በጥርጣሬ የመታየት ጉዳይ ነዉ፡፡ በማንነት ላይ ተመስርቶ እንደ አደገኛ ወንጀለኛ በጅምላ የመታየትና ያን ተከትሎም ሁሉግዜም በደህንነት ኃይሎች ክተትል ስር መሆን ፤ያለ አንዳች ጥፋት በጥርጣሬ ብቻ የመታሰር፤በሌላ አካባቢ አንድ ወንጀል ድርጊት በተፈጠረ ቁጥር ሌላዉን ስለጉዳዩ የማይመለከተዉን ሁሉ በጭፍን በማንነቱ ብቻ ተለይቶ በኣይነ ቁራኛ የመከታተል፤ለሃላፊነት ምደባና ሹሜት በማንነት ላይ ብቻ በመመስረት እድሉን መንፈግን የመሳሰሉ አመለካከቶች አብሮ ለመኖር የማያስችሉ በመሆናቸዉ ሊወገዙ ይገባል፡፤

አስቀድሜ የጠቃቀስኳቸዉ አመለካከቶች እንዲሁ ከባዶ የሚፈጠሩ ሳይሆኑ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለዚህ የተመቻቸና የሚያበረታታ ሁኔታ ሲኖር ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ቢቻልም በአንድና ሁለት ግለሰብ ምክንያት መላዉን ተቋም መልካም ስም ማጠልሸት ተገቢ እንዳልሆነ ስለማምን ከመጥቀስ ለመቆጠብ ተገድጃለሁ፡፡ እነዚህ ጥቂት ሰዎች የመንግስት መመሪያ ስለሆነ ወይም መከላከያ እንደዚያ እንዲያደርጉ ስለአዘዛቸዉ ሳይሆን በራሳቸዉ በግላቸዉ የሚፈጥሩት ችግር በመሆኑ በዚህ መጥፎ ተግባራቸዉ መላዉን መከላከያን ሊወክሉ ስለማይችሉ በነሱ ምክንያት ተቋሙ ሊወቀስ አይገባዉም፡፡

4.2/ ራስን የአንድ ህዝብ ተወካይ አድርጎ የመቁጠር የተዛባ አመለካከት፤

በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥ ከየትኛዉም ህዝብ የወጣ ያለአድሎ መካተት አለበት ሲባል ልክ እንደ ሀገሪቱ ፓርላማ ወይም የፌዴረሽን ምክር ቤት በህዝቡ ተመርጠዉ በዉክልና የመጡ አድርገዉ ራሳቸዉን መቁጠር አይገባም፡፡ እያንዳንዱ የሰራዊቱ አባል የወጣበት ህዝብ ወኪል አድርጎ ራሱን ከቆጠረ ተቋሙ ከግዳጅ ይልቅ በመብት ላይ ብቻ የሚያተኩር ስለሚሆን መደበኛ ተልእኮዉን እርግፍ አድርጎ ትቶ ነጋ ጠባ በመብትና በማንነት ጉዳይ ላይ ሲነታረክ የዉዝግብና የመናቆሪያ መድረክ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡

ማንም የሰራዊት አባል በህዝቡ ተወክሎ የመጣ ሳይሆን በራሱ ፈቀድ ቢበዛ ደግሞ በወላጆቹ እዉቅና የሚመጣ ነዉ፡፡ አንድ አዲስ ወጣት ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ተቋሙ ሲመጣ ራሱን ብቻ ወክሎ እንጂ ከጀርባዉ ሌላ ዉክልና ይዞ አይደለም፡፡ የትኛዉም የሰራዊት አባል በሀገሪቱ ካሉት ቢያንስ የአንዱ ብሄር ወይም ህዝብ የተገኘ ስለሆነ እንደ ልዩ ተወካይ ራስን የሚያስቆጥር አይደለም፡፡ ዋናዉ ቁም ነገር ወደተቋሙ ለመግባት የሚከለከል ዜጋ ከለለና ወደ ተቋሙ ከገባ በኋላም በማንነቱ ላይ የተመሰረተ አድሎ የማይደረግበት አስከሆነ ድረስ የብሄሩ መብት ተሟጋች የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም፡፡ ከኮንሶ ፤ከከምባታ ወይም ከኦሮሞ ህዝብ የተገኘ የሰራዊት አባል በዚያ አካባቢ በሆነ አጋጣሚ የሆነች ችንሽ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ራሱን የዚያ ብሄር ልዩ ተቆርቋሪ አድርጎ አካኪ ዘራፍ ማለት አይገባዉም፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ የሁሉም ህዝቦች ደህንነት ላስከበር የቆመ ተቋም እንጂ የአንድን አካባቢ ህዝብ ለመጉዳት ወይም በተለየ ለመጥቀም የቀመ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድ ግዜ የተቋሙ አባል ከሆነ በኋላ ተቆርቋሪነቱና ወገንተኝነቱ ለሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች እንጂ በተለየ ሁኔታ ለወጣበት ህዝብ ወይም ጎሳ መሆን አይገባዉም፡፡ የዚህ ዓይነት ጠባብ አመለካከት ያለዉና ህገ-መንግስታዊ አደራዉን ዘንግቶ ለአንድ ጎሳ ብቻ ጥብቅና የሚቆም የሰራዊት አባል ካለ በምንም መንገድ ቢሆን ህብረብሄራዊ በሆነ የመከላከያ ተቋም ዉስጥ መቀጠል ስለማይገባዉ ተቋሙን በግዜ ለቆ መዉጣት ነዉ ያለበት፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓይነቱ አባል ከሚሰጠዉ ጥቅም ይልቅ የሚያስከትለዉ አደጋ የከፋ ነዉና ፡ በየደረጃዉ ያሉ አመራሮችም ለጉዳዩን ተገቢዉን ክብደት ሰጥተዉ ከሚመሩት ሰራዊት አባላት ዉስጥ የዚህ ዓይነቱ አደገኛ ዝንባሌ እንዳይፈጠር ጠንክረዉ ሊሰሩ ይገባል፡

5/ በአንዳንድ ብልሹ አመራሮች ምክንያት በማንነት ላይ የተመሰረተ አድሎአዊ አሰራር

እንደሚታወቀዉ አብዛኛዉ በጡረታ ተሰናባች ያችኑ የጡረታ አበሉን ይዞ በዚያችዉ ከቤተሰቡ ጋር ኑሮን እንዲገፋ ሲደረግ ሌሎች የደላቸዉ ደግም ጡረታ ከመዉጣታቸዉ ቀደም ተደርጎ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት ሁኔታ ሆን ተብሎ ይመቻችላችዋል፡፡ ለምሳሌ በሰላም ማስከበር ወደ ዉጭ መላክ ሊሆን ይችላል ወይንም ደግሞ የተሻለ ጥቅም ወደሚገኝበት የመንግስት የልማት ደርጅት በዝዉዉር ይላካል፡፡ ለምሳሌ ለሰላም ማስከበር አንድም ግዜ እድል ያልደረሳቸዉ እያሉ ከአንድም ሁለት ግዜ በድጋሚ የሚላኩ አሉ፡፡ ከዚህ በኋላም አንዳንዶቹ ያለ አንዳች የስራ አስፈላጊነት የጡረታ ግዜያቸዉ እንዲራዘም ይደረጋል፡፡

ከዚያ በኋላም የጡረታ ግዜ ደርሶ መሰናበት የግድ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ የጡረታ ደብተሩን እንደያዘ በኮንትራት በሰራዊቱ ዉስጥ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ከጡረታ በኋላም ወደ አንድ የመንግስታዊ የልማት ደርጅት ተመድቦ ቀጣይ ህይወቱን ያለችግር ይመራል፡፡ እንግዲህ አንዳንዱ የደላዉ ሰዉ እጅግ የተደራራቡ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲያገኝ ተደርጎ የተንደላቀቀ ህይወት እንዲመራ ሲደረግ ሌላዉ ደግሞ ለሶስት አስርተ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ያችኑ የጡረታ አበል ብቻ ይዞ አስቸጋሪ ህይወት ለመግፋት ይገደዳል፡፡

የዚህ መሰሉ አድሎ የሚደረገዉ መንግስት እንደዚያ እንዲሆን ስለፈለገ እንዳልሆነ በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ እንኳን መንግስት ይቅርና በመካለከያ ደረጃም ቢሆን የሚመለከታቸዉ ከበላይ ኃላፊዎች እዉቅና ዉጭ የሚደረግ ደባ እንጂ መከላከያ አድሎ ለማድረግ ስለፈለገ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ለሙያቸዉና መንግስት ለሰጣቸዉ አደራ የማይታመኑና በግል ጥላቻና ስር የሰደደና የማይለቅ የዘረኝነት በሽታ የተጠናወታቸዉ በጣም ጥቂት ግለሰቦች ሆን ብለዉ የሚፈጥሩት አድሎ ነዉ፡፡

6/ ትምክህት ዘረኝትና ጠባብ አመለካከት የተጠናወታቸዉ አንዳንድ አመራሮች ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ ሊደረጉ ይገባል፡

አንዳንድ አብሮአቸዉ የቆየዉ ዘረኛና ጠባብ አመላከከት ጭራሽ ሊለቃቸዉ ያልቻለ ፤በግዜ ሂደት እንኳን ራሳቸዉን ማረም ያልቻሉና ለሌላዉ ህዝብ ከፍተኛ ንቀት ያላቸዉ አመራሮች በግለሰቦች ላይ ሲያደርሱት የነበረዉ በደል ቀላል አይደለም፡፡ አንዳንዶቹን ወላጆቻቸዉ ባወጡላቸዉ ስም ይቀልዱባቸዋል፡፡ በተወለጋገደ የአማርኛ አነጋገርህ ይሳለቁብሃል፡፤ለሀገርህና ለስርአቱ በቁርጠንነት ለማገልገል በፈቃድህ የተሰለፍክ አድረገዉ ሳይሆን በማይገባህና በማይመጥንህ ቦታ በአጋጣሚና በስህተት የተገኘህ አድርገዉ ይቆጥሩሃል፡፡ በማንነትህ ብቻ ስለሚጠሉህ ለሻዕቢያና ለኦነግ የማይነፍጉትን በስራህ አጋጣሚ ፈቅዶልህ ማወቅ የሚገባህን ጉዳይ ላንተ ሲሆን ከፍተኛ ምስጢር አድርገዉ ሊያካፍሉህ አይፈልጉም፡፡

አስቀድሜ የጠቀስኩት ዓይነት በሽታ ያለባቸዉ ግለሰቦች ሌላም ደባል ችግር ሊኖርባቸዉ የግድ ነዉ፡፡ ይህም ዓይን ያወጣ ዘረፋ ነዉ፡፡ ተቋሙን የህዝብ ተቋም አድርገዉ ሳይሆን በግላቸዉ የመሰረቱት የግል የቢዝነስ ተቋም አድርገዉ ስለሚቆጥሩ እንዳሻቸዉ ሲመዘብሩና ሲሰርቁ ምህረት የላቸዉም፡፡ መንግስት ለሀገሪቱ እንዲሰሩበት የሰጣቸዉን ሃላፊነት ለግል ሃብት ማካበቻነት ይጠቀሙበታል፡፡ በራሳቸዉ የማይተማመኑ በመሆናቸዉም አንድ ቀን ሊያጋልጠኝ ይችላል ብለዉ የሚገምቱትን ሰዉ በሆነ ባልሆነዉ እንዲማረር በማድረግ ነገር ሲበዛበት ተበሳጭቶና ተማሮ ወደ ዉጭ እስኪሰደድ ፋታ አይሰጡትም፡፡

ሀገሪቷ አንድ ቀን ለቁም ነገር ይሆኑኛል ብላ በከፍተኛ ወጭ ያስተማረቻቸዉ በሸረኞች ተንኮል ደንብረዉ የሚወዷትን ሃገርና ቤተሰባቸዉን ጥለዉ ወደ ዉጭ ሲሰደዱ ለዚህ ሁሉ የዳረጓቸዉ አመራሮች ግን ስለ ሁኔታዉ ሲሰሙ በድርጊታቸዉ ይኮራሉ እንጂ በጭራሽ ጸጸት አይሰማቸዉም፡፡ ወደ ዉጭ ከኮበለሉ መካካል ለዚህ ስርአትና ለሀገሪቱ በታማኝነት ከማገልገል ዉጭ ሌላ ተንኮል ያልነበራቸዉም ጭምር በመሴሪዎች ዴባ ተደናግጠዉና ሰግተዉ የኮበለሉ እንዳሉ በሰፊዉ የሚነገርና በሰራዊቱም የሚታወቅ ነዉ፡፡

ሀገራችዉም ሆነ መንግስት አንዳችም ነገር ሳያጎድልባቸዉና አንዳችም በደል ሳይደርስባቸዉ እነሱም አገራቸዉን ከድተዉ የኮበለሉ አሳፋሪ ፍጡራን መኖራቸዉ እንደተጠቀበ ሆኖ አንዳችም የተለየ ዓላማ ሳይኖራቸዉ በፍርሃት ብቻ ደንብረዉ የኮበለሉ እንደነበሩም ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሰዎች ሲኮበልሉ የሚመለለታቸዉን አዛዦች በአስኮብላይነት ቢያንስ ደግሞ ተገቢዉን ክትትል ባለማድረጋቸዉ በይፋ ሲጠየቁበት አልሰማንም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያዉም ከሻዕቢያ ጋር የሆነ የቆየ ስምምነት እንዳላቸዉ በሚያስመስል መልኩ ሰዎች እንዲኮበልሉ ሆን ብለዉ የሚሰሩ ነዉ የሚመስለዉ፡፡ ፡፡

አንዳንድ አዛዦች ሁሉን የሠራዊት አባል በእኩል ዓይን ማዬትና እኩል የማስተናገድ ጉዳይ ህገመንግስቱ የደነገገዉና ሊሰርዙት የማይችሉት ሆኖባቸዉ እንጂ እንደ አንዳነሱ ፍላጎት ቢሆንማ ብሄራዊ ተዋጽኦ የሚባል ነገር ጭራሽ ባይነሳባቸዉ የሚፈልጉና እነሱ ከወጡበት አካባቢ ዉጭ የመጣ ሌላዉ አባል አንዳችም የመብት ጥያቄ ባያነሳ ደስታቸዉ የሆነ አይጠፉም፡፡

7/ ተዋጽኦን ተግባራዊ ማድረግ ማለት በተቋሙ ዉስጥ የቁጥር የማመጣጠን ጉዳይ ብቻ ተደርጎ ሊታሰብ አይገባዉም፡፡

በቁጥር ማመጣጠን ብቻዉን የተዋጽኦ የመጨረሻዉ ግብ ተደርጎ የሚቆጠር አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ተዋጺኦ ተግባራዊ ሆኗል ለማለትም አያስችልም፡፡ ወደ ተቋሙ መግባት መቻል አንደቅድሜ ሁኔታ መታየቱ መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡ ዋናዉ ቁምነገር ግን ወደ ተቋሙ የገቡ ሁሉ ያለአንዳች አድሎ የእኩል አድል ተጠቃሚ (equal opportunity) ናቸዉ ወይ? የሚለዉን ጥያቄ መልስ ማግኘት ሲቻል ነዉ፡፡ ወደ መከላከያ ለመግባት ለሁሉም ተመሳሳይነት ካላቸዉ ለምሳሌ አድሜ፤የትምህርት ደረጃ ፤ለዉትድርና ተስማሚ ቁመና መኖር ፤የጤና ሁኔታ፤ከወንጀል ነጻ መሆን፤ የየትኛዉም ፓርቲ አባል አለመሆን ወዘተ ከመሳሰሉት የጋራ የሆኑ መስፈርቶች ዉጪ ማንም ኢትዮጵያዊ ወደወታደራዊ ተቋም ለመግባት በተለየ ሁኔታ የሚከለከልበት ሁኔታ የለም፡፡

እንኳን አሁን ቀርቶ ድሮም ቢሆን ወታደር ለመሆን መብት የለህም ተብሎ የተከለከለ ኢትዮጵያዊ ስለመኖሩ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሰራዊት መግባት መቻል የፍላጎትና ተቋሙ የሚጠይቁ መስፈርት የሟሟላት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የመከላከያ አባል መሆን ስለቻለ ብቻ ተዋጽኦ ተግባራዊ ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡ በርግጥ በአንዳንድ አገሮች ወደ መከላከያ ለመግባት በሃማኖትና በዘር ከፍተኛ ልዩነት እንደሚደረግና ወታደር የመሆን መብት የተነፈጋቸዉ ህዝቦች እንዳሉ ዘንግቼ አይደለም፡፡ ስለዚያ ጉዳይ አለማንሳቴ ከኛ ሁኔታ ጋር ጨርሶ ስለማይስማማ ነዉ፡፡ በኛ ሁኔታ አፋር ሆነ ሀራሪ ትግራዋይ ሆነ አማራ ጉራጌ ሆነ ኮንሶ ኦሮሞ ሆነ ወላይታ ማንም ሰዉ ወደ መከላከያ ለመግባት ፈልጎ የሚከለከልበት ሁኔታ አልነበረም፤ አሁንም የለም፡፡

በአገራችን መከላከያ ዉስጥ ስንት ኦሮሞ፤ ስንት ሲዳማ፤ ስንት አማራ፤ ስንት ሃዲያ ወዘተ አለ በሚል መደመር መቀነስና በመቶኛ (%) ማነጻጸር በኛ ሀገር ሁኔታ ትርጉም አይኖረዉም፤ ይህ ጉዳይ ለተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችና ጾታን በተመለከተም ተመሳሳይ ነዉ፡፡ በሃይማኖትና በጾታ ልዩነት ላይ የተመሰረተ የመግቢያ መስፈርት በሃገራችን የለም፡፡ በብሄር ማንነት በሃማኖትና በጾታ ላይ የጠመሰረተ ክልከላ ወይም ገደብ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ለምልመላ ለቅጥር በይፋ በሚወጡ ማስታወቂያዎች ላይ ሃይማኖት ብሄርና ጾታ እንደ መስፈርት አይጠቀስም፡፡ በርግጥ ጾታን በሚመለከት ወደ ኋላ ላይ በዚሁ ጽሁፍ በተለየ የማነሳቸዉ ልዩ ሁኔታዎች ቢኖሩም እንደ አሰራር ግን በሀገራችን እንደጥያቄ የሚነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡

ተዋጽኦን በሚመለከት እንደ ጥያቄ ተነስቶ መነጋገር የሚያስፈልገን ጉዳይ ካለ ወደ ተቋሙ አንድ ግዜ ከተገባ በኋላ ሁሉም ያለአንዳች አድሎ ይስተናገዳል ወይ? የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ችግር አለ ከተባለም ሊኖር የሚችለዉ እዚያ ላይ ነዉ፡፡ ወደ ሰራዊቱ የተቀላቀሉ ሁሉ ብቃቱና ችሎታዉ አስካላቸዉ ድረስ ተቋሙ ለሚያቀርባቸዉ የተለያዩ ዕድሎች እኩል ተወዳዳሪ መሆን አለባቸዉ፡፤ከየትኛዉም ብሄር የወጣ ማንኛዉም የሰራዊት አባል በፈቃዱ አንድ ግዜ ወደ ተቋሙ ከገባ በኋላ ከሌሎች ጋር እኩል የማይስተናገድና በማንነቱ ልዩነት የሚደረግበት ከሆነና ጥሩ ከሰራሁ ልሾምና በማእረግም ላድግ እችላለሁ፤ በትምህርትና በስልጠናም ራሴን ላሻሸል እችላለሁ የሚል እምነት ከለለለዉ በተቋሙ ዉስጥ ሊቆይ የሚገደድበት አንዳችም ምክንያት ስለማይኖረዉ ለቆ መዉጣትን ይመርጣል፡፡

8/ ያልተመጣጠነ ብሄራዊ ተዋጽኦ ለብሄራዊ ጭቆናና አፈና መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡

የብሄር ጭቆና ባለበት ስርአት በስልጣን ላይ ያለዉ አገዛዝ ከሌሎች ህዝቦች የሚነሳበትን ተቃዉሞ አመጽ ለመቆጣጠር እንዲያስችለዉ በሀገሪቱ መከላከያና የደህንነት መዋቅር ዉስጥ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የሃላፊነት ቦተዎችን ለአገዛዙ የተለየ ታማኘነት ይኖራቸዋል ተብለዉ በሚገመቱ ወታደራዊ አመራሮች ማስያዝ ይጠበቅበታል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አገዛዝ እጅግ ዘረኛ በመሆኑ ለአገዛዙ ታማኝ ሊሆኑ የሚችሉት ገዥዎቹ ከወጡበት ህዝብ የወጡ ወይም ባልተለመደ ሁኔታ ህልናቸዉን ለጥቅም የሸጡ ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች ብቻ ናቸዉ ታማኝ ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ ለዚህ ዉሌታቸዉም በተለያዩ ቁልፍ ቦታዎች ስለሚመደቡ የሀገሪቱን ሃብት እንዳሻቸዉ ሲመዘብሩ ከልካይና ተቆጪ አይኖርባቸዉም፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሰራዊት ዉስጥ ተዋጽኦ መቼም ቢሆን በአግባቡ ሊከበር አይችልም፡፡

ተዋጽኦ በርካታ የሰዉ ኃይል በሚያስፈልግበትና ከጥቅም አንጻርም የተለየ ጥቅም በማይገኝበት በታችኛዉ የሰራዊት ደረጃ በቁጥር ደረጃ ብቻ ተመጣጣን ሊደረግ ይችላል፡፡ እንዲያዉም ከገዥዉ ቡድን ዉጭ ያሉት በቁጥር አብላጫ ቢኖራቸዉ ባይኖራቸዉም ገዥዎች ብዙም አያሳስባቸዉም፡፡

ሰለ ተዋጽኦ አለመመጣጠን በተጠየቁ ቁጥር ለማሳመኛነት ይዘዉ የሚቀርቡት በርከት ያለ ቁጥር የተካተተበትን የታችኛዉን የሰራዊት አባላት ቁጥር ነዉ፡፡ ወደ ሰራዊቱ ተቋም ለመግባት በሩ ለሁሉም ከፍት አሰከሆነ ድረስ በርከት ያለ ቁጥር ያለዉ የሠራዊት አባላት ከተለያዩ ህዝቦች መግባታቸዉ የማይቀርና የትክክለኛ ተዋጺኦ ገላጭ ሊሆን የሚገባዉም አይደለም፡፡ ተዋጽኦ በሚገባ ተተግብሮአል ሊባል የሚችለዉ በመካከለኛዉና በተለይም ቁልፍ በሆኑ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ተመድቦ የመስራት ዕድሉ ካለ ብቻ ነዉ፡፡

በሰበብ አስባቡ በከፍተኛዉ አመራር ደረጃ ማንንም ድርሽ ሳያደርጉ ይቆይና አልፎ አልፎ ፖለቲካዉን ትኩሳት እየለኩ ለገጽታ ግንባታ የሚያስፈልጋቸዉን ያህል ብቻ ጥቂት ሰዎችን ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ በመስጠት በተገኘዉ የመገናኛ አዉታር ሁሉ ግንባር ቀደም ዜና እንዲሆን ያደርጉታል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ለዚህ ዓይነቱ ዕድል የሚታጩት በብቃታቸዉ ከሌላዉ ስለሚበልጡ ሳይሆን ችግር የማይፈጥሩ፤ጥያቄ በመጠየቅ አመራሩን የማይገዳደሩ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ በማዕረግ ለሚያንሳቸዉ ጭምር የመታዘዝ ግዴታቸዉን የማይዘነጉት በጥንቃቄ ተመርጠዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት ጥቂት ሰዎች ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ደረጃ ቢደርሱም አንዳችም ወሳኝኘት የለላቸዉ በመሆኑ ተዋጽኦን ለመጠበቁ እንደማሳያ መሆን አይችሉም፡፡ ያለብቃት ለተዋጽኦ ተብሎ ብቻ በዚህ ደረጃ በመመደብ ተቋሙን ከመጉዳት ብቃት ያላቸዉ ከየትኛዉም አካባቢ ቢመደቡ በተሻለ ነበር ያስብላል፡፡

ለአንድ ህዝብ ወይም ቋንቋ ተናጋሪ የተለየ ታማኝነት ባላቸዉ ወታደሮች ብርታት ስልጣን የጨበጠ አገዛዝ እንደ ህዝብ ሌሎችን ህዝቦች ሲጨቁኑ በአብዛኛዉ የሚታወቀዉ በቁጥር አብላጫ ከሆኑ ብሄር የተገኘ የገዥ መደብ ነዉ፡፡ በቁጥር አናሳ ከሆኑ ህዝቦች የወጡ የቀረዉን አብላጫ ቁጥር ያለዉን ህዝብ የሚጨቁኑበት (ethnic minority rule) አጋጣሚም አልፎ አልፎም ቢሆን መከሰቱ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ በኢራቅ በሳዳም ሁሴን አገዛዝ ዘመን ሱኒዎች (sunnis)፤በሩዋንዳና በቡሩንዲ ደገሞ የቱትሲ (tutsi) ጎሳዎች፤በሶሪያ ደግሞ አላዊስ(alawis ) የሚባሉ ጎሳዎች ከሌሎቹ በቁጥር አነሰተኛ ሆነዉ ነገር ግን ስልጣን በአጋጣሚ በእጃቸዉ ስለ ገባ ብቻ በቁጥር የሚበልጣቸዉን ሌላዉን ህዝብ ረግጠዉ ሲገዙ ኖረዋል፡፡ ኢራቅና ሶሪያ አሁን ወደ ሚገኙበት አሳዛኝ ደረጃ ሊደርሱ የቻሉትም በነበረዉ ብሄራዊ ጭቆና ምክንያት ሰራዊታቸዉ ዉስጥ የአንድ ጎሳ የበላይነት የገነነበትና ሌሎች ገለል የተደረጉበት ሁኔታ ስለ ነበርነዉ፡፡

በሶሪያም ሆነ በኢራቅ ሰራዊቱ የጋራ ሀገርንና ሉአላዊነት ከመጠበቅ ይልቅ እርስበርሱ በጠላትነት ጎራ የተሰለፈ ስለነበር ሀገር ማዳን ላይ ሳይሆን እርስበርስ ሲፋለም ሀገራቸዉን ለዉድቀት ዳርገዋል፡፡ በህይወትም በስልጣንም አስካሁን መቆየት በመቻላቸዉ እድለኛ ናቸዉ የተባሉት የሶሪያዉ መሪ አላሳድ አስካሁንም በስልጣን ላይ ለመሰንበት የበቁትም የራሳቸዉ የጎሳ (አላዊስ) ተወላጅ በሆኑ ታማኝ ወታደሮቻቸዉ እገዛ ነዉ፡፡ ወታደሮቹ ከሀገሪቱ መፈራረስ ይልቅ ትልቁ ጭንቀታቸዉ የመሪያቸዉን ስልጣን መጠበቅ በመሆኑ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ከሚወርዱ ሀገሪቱ ብትበታተን ምርጫቸዉ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል፡፡ በሶሪያ የአላሳድ አገዛዝ ዘመን ሌላዉ ቀርቶ በዉትድርና ለማገልገል እንኳን ከአላዊስ አናሳ ጎሳዎች ዉጭ ለሌሎች ዕድሉ ዝግ እንደነበር ያለፈዉ ታሪካቸዉ ያሳያል፡፡

9/ በመከላከያ ሰራዊታችን ዉስጥ ተዋጽኦ በሚጠበቀዉ ደረጃ አለመተግበሩ የብሄራዊ ጭቆና መኖር ማሳያ አድርጎ መቁጠር ከፖለቲካ ፍጆታነት ባለፈ አንዳችም መሰረት የሌለዉ ባዶ ዉንጀላ ነዉ ፡፡

በሀገራችን በመከለከያ ሰራዊታችን ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን በምንፈልገዉ ደረጃና ፍጥነት እዉን ማድረግ ረገድ የተወሰነ ክፍተት መኖሩ ባይካድም ነገር ግን በሌሎች አገሮች በሚታየዉ መልኩ ክፍተቱ የብሄራዊ ጭቆና ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡ እንኳን ዛሬ ፌዴራላዊ ስርአት ተመስርቶና የሁሉም ህዝቦች ማንነት ተከብሮ ህዝቡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር በቻለበት ወቅት ይቅርና በደርግ አገዛዝ ዘመንም ቢሆን ሌሎች ጭቆናዎች ሞልተዉ የተረፉ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በጎሳ ወይም በብሄር ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ጭቆና በሀገሪቱ ሰፍኖ ነበር ብዬ አስቤ አላዉቅም፡፡

ዛሬ ደግሞ ስለ ብሄራዊ ጭቆና የተመቻቸ አንዳችም ሁኔታ በሌለበት በሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦ አለመመጣን ረገድ የተወሰነ ከፍተት በመኖሩ ብቻ ብሄራዊ ጭቆና መኖር ማሳያና አንድን ቋንቋ ተናጋሪ ሆን ብሎ ለመጥቀም እንደተፈለገ ተደርጎ የሚያስቆጥር አይደለም፡፡ ስለዚህ የችግሩን መኖር መጠቆም አንድ ነገር ሆኖ ነገር ግን የችግሩ ምንጭና ምክንያት ላይ የተዛባ ትርጉም መስጠት ለፖለቲካዊ ጨዋታ በመጠኑ ሊረዳ ይችል ካልሆነ በስተቀር ችግሩን ለዘለቄታዉ በመቅረፍ ረገድ አንዳችም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡

ተዋጽኦን ፖለቲከኞች ከፍትህ እኩልነት (justice) አንጻር ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ተዋጺኦን የሀገሪቱ ዜጋ መሆን ሊያገናጽፍ ከሚችለዉ መብት አንጻር የሚመዝኑም አሉ፡፡ ተዋጺኦ የባህል ፤የቋንቋ ፤ የእምነት የዘር፤ የቀለም ልዩነት አለመኖር ማረጋገጫ ተደርጎም ይቆጠራል፡፡ ከመከላከያ እንጻር ሲታይ ደግሞ ተዋጽኦ በመከላከያ ዉስጥ በሚገባ መተግበር የፍትህና የመብት ወዘተ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚቆጠር ሳይሆን ይልቁንም የመከላከያን ብቃት/ጥራት የማሳደግ ጉዳይ ተደርጎ ነዉ፡፡ ተዋጺኦን በመተግበርና ወታደራዊ ብቃትን ጠብቆ በማቆየት መካካል የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱም አንዱ ያለ ሌላዉ መኖር የማይችሉና ተደጋጋፊነት ያለቸዉ በእኩል ደረጃ አስፈላጊዎች ናቸዉ፡፡ ተዋጺኦ በተገቢዉ መንገድ ከተተገበረ የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆነዉ ወታደራዊ ተቋሙ ነዉ፡፡ ተዋጺኦ ለመከላከያ ሁለንተናዊ ብቃት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለዉ በዚህ ረገድ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች ያረጋገጡትና በተግባርም የተፈተነ ሃቅ ነዉ፡፡

በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ተዋጺኦን ከመተግበር ጋር በተያያዘ ሊሰነዘር የሚገባዉ ትችት ካለ የአማራ፤የኦሮሞ የጉራጌ የትግሬ እየተባለ ቁጥር በመጥራት ሊሆን አይገባዉም፡፡ አብረዉ ሊታዩ የሚገባቸዉ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በጥምረት ሳያዩ የቁጥር መብዛትና ማነስን ብቻ በማዬት ትክከለኛዉን ገጽታ ለመረዳት አይቻልም፡፡ ከአማራ ፤ ከኦሮሞ፤ ከወላይታ፤ከትግሬ የተገኘ ጄነራል አለመኖር ወይም በቁጥር ከሌላዉ አነስ ማለት ብቻዉን እንዴ ችግር ሊቆጠር አይገባዉም፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ ትግርኛ ተናጋሪ ጄነራሎች ወይም የክፍለ ጦር አዛዦች ቁጥር ከአማራ፤ ከኦሮሞ ወይም ከሲዳማ በለጥ ማለቱ ብቻዉን እንደችግር የሚቆጠርና የሚያስነቅፍም አይደለም፡፡

ችግር የሚሆነዉ የወላይታ፤ የኦሮሞ ወይም የአፋር ተወላጅ ከሆኑት መኮንኖች መካከል ለዚህ ቦታ በትክክል መመጠን የሚችሉ እያሉ ነገርግን ፍትሃዊነት በጎደለዉና ግልጽነት በለለዉ መንገድ ሆን ተብሎ አድሎአዊ በሆነ አሰራር ዕድሉን ተነፍገዉ ለሌላዉ የተሰጠ ከሆነ በርግጥ የሚያነጋግር ብቻ ሳይሆን የሚያጣላም ሊሆን ይችላል፡፡ ከእኛ ዉጭ ሌላዉ መሾም መሸለም የለበትም የሚል አመለካከት ካለ በርግጥ ችግር ነዉ፡፡ የእንትን ቋንቋ ተናጋሪ ከሆነዉ ዉጭ ሌላዉ ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ ሊመደብ ተፈጥሮዉ አይፈቅድለትም፤ታሪክ ሃላፊነት የጣለዉም በእኛ ላይ ስለሆነ እኛ ብቻ ነን መምራት ያለብን የሚባል ነገር ካለ በርግጥ አብሮ የሚያኖረን አይሆንም፡፡

ነገር ግን የትግርኛ ተናጋሪ ጄነራል ቁጥር ከሌላዉ መብለጡ ጥያቄ የሚያስነሳዉ የብቃት መስፈርቱን የሚያሟላ የጉራጌ ወይም የአማራና የሲዳማ ተወላጆች እያሉ ያለ ዉድድር ሆን ተብሎ ትግራዉያንን ብቻ ለመጥቀም ተብሎ የተደረገ ከሆነ ብቻ ነዉ፡፡ ብቃትን መነሻ ባደረገ ግልጽ መስፈረት መሰረት ሁሉም እኩል ያለ አድሎ መወዳደር ከቻለ ዉጤቱ ምንም ይሁን ምን ሊያሳስብ የሚገባ አይደለም፡፡ ሊያሳሰብ የሚገባዉ በሆነ መንገድ አድሎ የሚደረግበትና አንዱን ጠቅሞ ሌላዉ ችላ የሚባልበት ሁኔታ ካለ ያኔ ቁጭ ብለን መገማገም ይገባናል፡፡

ለምሳሌ በሰራዊቱ ዉስጥ የአጋጣሚ ሆኖ አስልምና እምነት ተከታይ ቁጥር ከክስርስትና እምነት ተከታዩ አነስ እንደሚል የሚታወቅ ነዉ፡፡ ይህን ብቻ ይዞ ለምን እንደዚያ ሊሆን እንደቻለ ለማጣራት ሳይሞከር እንዲሁ በደፈናዉ በሙስሊሙ ላይ አድሎ ይደረጋል የሚል ሰዉ ካለ ጤነኛ ሰዉ አይመስለኝም፡፡ ሆን ተብሎ አድሎ እንደሚደረግና ሙስሊሙ በሚገባ እንደማይወከል (under representation) አድርጎ ማሰብ እጅግ የተሳሳተና ተገቢ ያልሆነ አመለካከት ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሴቶች ቁጥር በሰራዊቱ ዉስጥ በቁጥር ከወንዶች ያነሰ መሆኑ መንግስትና መከላከያ ሆን ብለዉ ያደረጉት አድሎአዊ አሰራር ተደርጎ የሚቆጠር ከሆነ አጅግ የተሳሳተ ነዉ፡፡

የዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ከመድረስ በፊት ወደ መከላከያ ተቋሙ እንዳይገቡ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ፤በሴቶችና በሌሎች ብሄር ወይም ህዝቦች ላይ የተለየ ገደብ ተደርጎ እንደሆነ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ መስፈርት መኖር አለመኖሩን መጀመሪያ ለማረጋገጥ መሞከሩ መቅደም በተገባ ነበር፡፡ ወደ ሰራዊቱ ለመግባት የተለየ መስፈርት በሌለበትና በሩ ለሁሉም እኩል በሆነበት ሁኔታ ይህ ትችት ሊቀርብ ባልተገባዉ ነበር፡፡

ይህን እያልኩ ያለሁት በአገራችን ከተዋጽኦ ጋር በተያያዘ አንዳችም እንከን የለም ከሚል መንፈስ ተነስቼ አይደለም፡፡ እንኳን በእኛ አገር ይቅርና በዚህ ረገድ ብዙ ተራምደዋል በሚባሉ አንዳንድ አገሮችም በሰራዊታቸዉ ዉስጥ ገና በሚፈለገዉ ደረጃ ያልተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ በሚገባ የሚታወቅ ነዉና ፡፡ ይሄን ስል በሀገራችን በአተገባበር ረገድ የሚታየዉን ክፍተት ወይም እንከን ለማሳነስ መሞከሬም አይደለም፡፡ መንግስት ችግሩን መኖሩን አምኖና ተቀብሎ እያስተካከልኩ ነኝ ብሎ ከነገረን በኋላም የችግሩን መኖር በተረዳበት ደረጃ አለመተግበሩ በሁላችንም ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ በመሆኑ ለመደባበቅ ሆነ ለማድበስበስ መሞከር የሚያወጣ አይሆንምና እኔም ችግሩን በማሳየት በመፍትሄዉ ለይም እገዛ ለማድረግ እንጂ ችግሩን ለማድበስበስ ወይንም መንግስትን ያለ ስራዉ ለማወደስም አይደለም፡፡

በሰራዊቱ ዉስጥ ከህዝቡ ቁጥር ጋር ተመጣጣን የሆኑ የሰራዊት አባላትን ከአንዳንድ አካባቢዎች (ህዝቦች) አለመኖራቸዉን ብቻ በማዬት ተዋጽኦ ቸግር አለበት በሚል በጭፍን ማጥላላት አይገባም፡፡ ለምን በርከት ያለ ቁጥር ያለዉ የሰራዊት አባል እንደለለ ምክንያቱን ለማወቅ ከመሞከር በፊት ለመተቸት መጣደፍ ለችግሩ መፍትሄ አያመጣም፡፡ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች (ህዝቦች) በዉትድርና ለማገልገል ወይም ወታደር ለመሆን ዝንባሌና ፍላጎት ጨርሶ የለላቸዉ ሊኖሩ እነደሚችሉ ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ወትድርና ለመግባት አንዳችም ክልከላ ባልነበረበት በደርግ ስርአትም አንዳንድ ህዝቦች የመጡ በሰራዊቱ ዉስጥ ማግኘት ብርቅ እንደነበር በወቅቱ የነበርን እናስታዉሳለን፡፡ ክልከላ ስለነበር ሳይሆን ወታደር መሆን ስለማይፈልጉ ነዉ፡፡

በሌላ በኩል አሁንም ቢሆን እንደ ጥያቄ ተነስቶ ተገዉን ምላሽ ሊያገኝ የሚገባዉ ጉዳይ ወደ ወታደራዊ ተቋም መግባት ለአንዳንድ ህዝቦች የተሻለና ተቀዳሚ አማራጭ የሚሆንበትና ለሌሎች ህዝቦች ደግሞ ሌላ አመራጭ ካልጠፋ በስተቀር የማይገባበት የመጨረሻዉ አማራጭ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ መነሻዉ ምን እንደሆነ በሚገባ መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ ለአንዳንዶቹ በመከላከያ ዉስጥ ወደ ከፍተኛ እርከን ለመድረስ የሚያግዳቸዉ ነገር እንደለለ የሚተማመኑበት ሌሎቹ ደግሞ ምንም ያህል ቢደክሙ እኩል ማደግና መሻሻል አንችልም የሚል ጥርጣሬ ገና ከመነሻዉ ካላቸዉ በርግጥ በተቋሙ ዉስጥ የሆነ ችግር ለመኖሩ አመላካች ስለሚሆን የችግሩ ምንጭ በሚገባ ሊፈተሸ ይገባል፡፡ በደፈናዉ ደምዳሜ ላይ ከመድረስ የህዝቡን ስነሊቡና፤ ባህል እምነት፤የቆየ ታሪክ መፈተሸ ይገባል፡፡

በሀገሪቱ ዉስጥ ባሉ በሌሎች መስኮች ሰርተዉ ለመኖር ይቻላል በሚል አርግጠና የሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ወደ መግባት ባይፈልጉ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ዋናዉ ጉዳይ መከላከያ በሩን ለሁሉም ከፍት ማድረጉና አንድ ግዜ ለገቡትም ቢሆን በዉስጡ ለመቆየት የሚያስችላቸዉን ሁኔታዎችን ማሟላቱና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረጉ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ከአንዳንድ ህዝቦች ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸዉ በመከላከያ ዉስጥ አለመታየታቸዉ ብቻዉን ችግር ለመኖሩ አመላካች አይሆንም፡፡ ተዋጽኦ አተገባበር ላይ ከፍተት መኖሩ በራሱ የብሄራዊ ጭቆና መኖር ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባዉም፡፡

10/ ተዋጺኦን በመከላከያ ሰራዊታችን ዉስጥ ለመተግበር ሁኔታዎች ከሌሎች አገሮች ይልቅ ለኛ የተመቹ ናቸዉ፡፡

የሀገራችን የኋላ ታሪክ ሲወሳ እንደብዙዎቹ አገሮች በቅኝ አገዛዝ ስር ያልወደቅን መሆናችንና በሃማኖትና በብሄር እርስበርስ ተፋቅሮ ለዘመናት የኖረ እንጂ የቆየ ቅም በቀል ስሜት ያለበት አይደለም፡፡ በመከላከያ ሰራዊታችን ዉስጥ ዳይቨርስቲን ለመተግበር ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር ለኛ በእጅጉ የተመቸ ነዉ፡ይህን ያልኩትም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ለዚህ ድምዳሜ መነሻ የሆኑኝን ጥቂት ምክንቶችን ቀጥዬ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

* ኢትዮጵያን እንደሃገር በመመስረት ሂደት ዉስጥ እንዱን ህዝብ አገር ፈጣሪ ሌላዉን ደግሞ በይተዋርና ከግዜ በኋላ የተቀላቀለ አድርገን እንድንቆጥር የሚያስገድደን ችግር የለብንም፡፡ የዚህ ዓይነት ታሪክም አልነበረንም፡፡ በሌሎች አገሮች እንዳለዉ ቀደምት ህዝብ (Indigenous) እና ፈልሶ የመጣ የሚባል ጣጣ የለብንም፡፡

* የቅኝ አገዛዝ አሻራ /ዉርስ ጣጣ የለብንም፡፡ የቅኝ አገዛዝ ጥሎ የሚሄደዉ የተለየ መጤ ባህል፣ቋንቋ፤ አዲስ ማንነትና የበታችነት ስሜት በኛ ህብረተሰብ ዉስጥ የለም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ቋሚ መከላከያ ሰራዊት ለመጀመሪያ ግዜ በሀገራችን ለመመስረት ጥረት የተደረገዉ እንደ ሌሎቹ ቅኝ የተገዙ አገሮች በቅኝ ገዥዎቻቸዉ አምሳያ (ሞዴልነት) ሳይሆን በራሳችን መንገድ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

* በጎሳና በሃማኖት ሳቢያ የቆየ የርስበርስ ጠላትነትና ለበቀል የሚያነሳሳ ቁርሾ የለንም፡፡ እንዲያዉም ለብዙዎቹ አገሮች አብነት ሊሆን በሚችል መልኩ በህዝቦች መካከል የአብሮነት፤ የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል የሰፈነበት ህዝብ ነዉ፡፡

* በሃገራችን የዘመናዊ ዉትድርና ታሪክም አንድን ህዝብ ከሌላዉ ለይቶ ለመጨፍጨፍና ወይም ለመጨቆን የቆመ ሰራዊት አልነበረንም፡፡ ባለፉት አምባገነን ስርአቶች የነበረዉ ጭቆና በዘርና በይማኖት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን አንዱን ከሌላዉ ሳይለይ በሁሉም ላይ ያረፈ ነበርና፡፡ የንጉሱን ዘመን እንኳን ለጊዜዉ ትተን የባለፈዉ የደርግ ጨቋኝ መንግስት አንዱን ከሌላዉ ሳይለይ ሁሉንም ሲበድል እንጂ በዘር፤ በብሄር ወይም በእምነት ላይ የተመሰረተ ጭቆና ሲያደርግ አይታወቅም፡፡

* በደርግ ዘመን ከስርአቱ በተለየ ተጠቃሚ ነበር የሚባልና ሆን ተብሎ ከስርአቱ ገለል የተደረገ የሚባል የህዝብ ክፍል አልነበረም፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች ሆን ብለዉ ከሚፈጥሩት እዉነትነት የጎደለዉና የተጋነነ የዉንጀላ ታሪክ በስተቀር በደርግ ዘመን እንደ ህዝብ ገዥና ተገዥ፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ የሚባል የህዝብ ክፍል አልነበረም፡፡ በተለይ በሰራዊቱ ዉስጥ በዘርና በብሄር ላይ የተመሰረተ አድሎአዊ አሰራር አልነበረም፡፡

በተጠቀሱት በነዚህ ምክንቶች የተነሳ ዛሬ ተዋጽኦን በመከላከያችንም ሆነ በህዝባችን ዉስጥ በአግባቡ ለመተግበር ከሌሎቹ የተሻለ ምቹ ሁኔታ እንዳለን ይሰማኛል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ተዋጺኦን በመተግበር ረገድ ከሌሎች ተቋማት ይልቅ አዳጋች የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዳሉም ሊዘነጋ አይገባዉም፡፡ ወታደራዊ ተቋሙ በባህሪይዉ ከላይ ወደታች በተዋረድ የተዘረጋ መዋቅር (hierarchical structures) ያለዉና ጥብቅ የሆነ የዕዝ ጠገግ (chain of command) የሚከተል በመሆኑ ራሱን ከህብረተሰቡ የነጠለና ዉስጡን ለመሳየት የማይፈቅድ ዝግ የሆነና ከህብረተሰቡ ጋር የማይገጥም የራሱ ባህል ያለዉ ስለሆነ የትኛዉንም አዲስ ለዉጥ በጸጋ ለመቀበል ተነሳሽነቱ አነስተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም ተቋማዊ ብቃትንና ተቋማዊ ባህሉን ሊጎዳ ይችላል በሚል ተዋጺኦን እንደ ችግር የመቁጠር ዝንባሌ ይታያል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የተዋጽኦ ጉዳይ ፈጽሞ የማይጥማቸዉ አንዳንድ አመራሮች መኖር አጻጸጸሙን አዳጋች ማድረግ መቻሉ እሙን ነዉ፡፡ ሰለዚህ የሚመለከታቸዉ የስልጣን አካላት በመከለከያ ዉስጥ ተዋጺኦ እንዴት እየተተገበረ እንደሆነ በቅርብ መከታተል ሲገባቸዉ እንዳፈቀደዉ ያድርግ በሚል ለራሱ ለመከላከያ መተዉ አይገባቸዉም፡፡

11/ ተዋጽኦን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ መተግበር ከምንግዜም በላይ አሁን የግድ ያደረጉ ወቅታዊና አስገዳጅ ሁኔታዎች ፤

ከሃያ ዓመታት በፊት በሽግግሩ ዘመን ደርግን በጦርነት ያሸነፈዉ የኢህአዴግ ሰራዊት ማንንም ሳይደባልቅ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት እንዲሆን መደረጉ የወቅቱ ሁኔታ ያስገደደና ተገቢም ነበር፡፡ በዚያን ወቅትም ቢሆን ከብሄራዊ ተዋጺኦ አንጻር በኢህአዴግ ሰራዊት ዉስጥ በታችኛዉ አባልና በአመራር ደረጃ ወደ አንድ ወገን ያደላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም በትግሉ ዉስጥ ከነበረዉ ቆይታና አባል ድርጅቶቹ ከነበራቸዉ የሰራዊት ብዛት አንጻር ሲመዘን አለመመጣጠኑና ወደ አንድ ወገን ማድላቱ ሌላ አመራጭ ስላልነበረም ተገቢነቱ ታምኖበት የጋራ መግባባት የተወሰደበት ነበር፡፡

ከሽግግሩ በኋላ የኢፌድሪ መንግስት ሲመሰረት ሁሉን ህዝቦች የሚያካትትና ተዋጺኦን የጠበቀ ህብረ-ብሄራዊ የሆነ መከላከያ ሰራዊት በህገመንግስቱ መሰረት በአዋጅ ማቋቋም የግድ ስለነበር ማመጣጡን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያመች ተብሎም በርካታ የሕወኃት ነባር ታጋዮች ወደ ቤታቸዉ እንዲመለሱ የተደረገበትን ሁኔታ እናስታዉሳለን፡፡ እንግዲህ ተዋጾአን ለማመጣጠን ጥረት ማድረግ የተጀመረዉ ገና ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ ሲሆን ሀገር አቀፍ የሆነ የኢፌድሩ መከላከያ ሰራዊት ለመመስርት ሲባልም በርካታ የሰዉ ኃይል በመቀነስ ወሳኝ እርምጃ መወሰዱን ስናስታዉስ የኢህአዴግ መንግስት ለጉዳዩ በሚገባ ያሰበበት እንደነበር መረዳት አያዳግተንም፡፡

በወቅቱ ከትግርኛ ተናጋሪዎች ዉጭ ባሉት አካባቢ በሚገባ አልተወከልንም ከሚለዉ ቅሬታ ይልቅ የህወሃት ነባር ታጋዮች (ትግርኛ ተናጋሪዎች) አካባቢ በገፍ ዲሞብላይዝ መደረጋቸዉና የቀሩትም ቢሆኑ ከነበራቸዉ ወታደራዊ ብቃትና የአገልግሎት ዘመን አንጻር ተመዝኖ ማግኘት ይገባቸዉ ከነበረዉ ሁለትና ሶስት ማዕረግና የአገለግሎት ዘመን እንዲቀነስ በመደረጉ ቅሬታዉ በነሱ አካባቢ ያመዝን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላም አዳዲስ ወጣቶች ከሁሉም ክልሎች ወደ ሰራዊቱ በስፋት የመግባት አድል ስለተፈጠረ በታችኛዉ አባል ደረጃ ቀድሞ በመብለጥ ይታይ የነበረዉ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር ከሌሎች ክልሎች በመጡ አዳዲስ አባላት በእጅጉ እየተዋጠና በመቶኛ እየተመናመነ መምጣቱ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ በከፍተኛ አመራሩ ደረጃ አብዛኛዉ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ በቀድሞ የህወኃት ታጋዮች መያዙ ብሄራዊ ተዋጽኦን የማመጣጠኑ ጥረት ላይ እክል እንደገጠመዉ ያሳብቅ ነበር፡፡ በከፍተኛ ወታደራዊ የዕዝ ደረጃ ከሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ለመመደብ ለዚያ ከፍተኛ የሃላፊነት ደረጃ ብቁ የሚያደርግ አቅም የነበራቸዉ አለመኖራቸዉ አንደሆነ በምክንያትነት ሲቀርብ የነበረዉ እዉነት ቢሆንም ለአንዳንድ ወገኖች እዉነትነቱን ለመቀበል ግን አስቸጋሪ ሳይሆንባቸዉ አልቀረም፡፡ በተለይም የተዋጽኦ ጉዳይ በተቃዉሞ ጎራ ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ራሱን የቻለ መጫወቻ ካርድ ሆኖ በመገኘቱ ክፍተቱን እጅግ እያጋነኑ የብሄራዊ ጭቆናና አድሎ መኖር ማሳያ አድርገዉ ተጠቅመዉበታል፡፡

በርግጥ የኢፌድሪ መንግስትም ቢሆን የተዋጺኦ የማመጣጠን ጉዳይ ላይ እንከኖች ያሉበት በመሆኑ ሁኔታዉ ዉሎ ሲያድር በሀገሪቱ ፓርላማ ሳይቀር አንድ አጨቃጨቂ አጀንዳ ለመሆን በመብቃቱ መንግስት ከዚያ በኋላ ጠንከር ያሉ ማስተካከያ እርምጃዎችን መዉሰዱ አልቀረም፡፡ ግዜዉ እየገፋ ሲሄድም “ብቁ አመራር ለማፍራት በአጭር ግዜ አለተቻለኝም” የሚለዉ የመንግስት የተለመደዉ ምክንያትም ተቀባይነት እያጣ መሄዱ የግድ ሆኗል፡፡ ከሃያ ስደስት ዓመታት በኋላም ተፈላጊዉን ብቃት ያለዉ አመራር ለማፍራት አልቻልኩም የሚለዉን የኢህአዴግን ምክንያት ለመቀበል አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

የኢፌድሪ መንግስትም እንደተጠበቀዉ ባይሆንም ተዋጽኦን ለማመጣጠን ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን መዉሰዱ የሚካድ አይደለም፡፡ እጅግ ሰፊ ልምድ ያላቸዉን በርካታ የሰራዊቱን አመራሮች ያለግዜያቸዉ እስከማሰናበት የደረሱ እርምጃዎች በመዉሰዱ በተሰናበቱት እግር ለመተካት በተስፋ ሲጠብቁ ለነበሩት ትልቅ የምስራች መሆኑ ባይቀርም ነገር ግን በሰራዊቱ አጠቃላይ ብቃት ላይ ሊፈጠር የሚችለዉን ከፍተት አሳስቦአቸዉ በገፍ የተደረገዉን ማሰናበት ያለስደሰታቸዉ የሰራዊቱ አባላትና ዜጎች ብዙ ናቸዉ፡፡ መንግስት በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የነበረዉን የቁጥር አለመመጣጠን ለማጥበብ በሚል ያለ አቅማቸዉ ከፍተኛ ወታደራዊ የማዕረግ ሹሜት መስጠቱም ተሿሚዎቹን ያስደሰተ ከመሆኑ ዉጭ የመከላከያን ብቃት መጠበቅ እንደ ተቀዳሚ መስፈርት ለሚቆጥሩ ወገኖች ይህ ሁኔታ ጨርሶ የሚቀበሉት አይደለም፡፡

አሁን ባለንበት ወይንም በደረስንበት ሁኔታ በሰራዊቱ ዉስጥ ተዋጽኦን በአግባቡ ያለመመጣጠኑ ጉዳይ እንደቀድሞዉ በቸልታ የሚታለፍ ሳይሆን መጪዉን የሀገሪቱን የአንድነት ዕጣ ፈንታ ላይ የተጋረጠ አደጋ ተደርጎ የሚቆጠርበት ወሳኝ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡ የተዋጾኦን ጉዳይ ብቻዉን በተናጠል ለሚያዩ ሰዎች አደጋዉ ላይታያቸዉ ይችላል፡፡ ነገር ግን በየትኛዉ የሀገሪቱ አካባቢና የህብረተሰብ ክፍሎች ዉስጥ የምትከሰት እያንዳንዷ ቅንጣት ቸግር የመከላከያ ሰራዊቱን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ መንካቱ የማይቀር በመሆኑ እነዚህ ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከተዋጺኦ አለመመጣጠን ጋር ሲዳመሩ ሊፈጠር የሚችለዉ አደጋ ቀላል አይሆንም፡፡ የተወሰኑት ለአብነት ቀጥዬ ልጥቀስ፤

አንደኛ፤ በክልሎቾና በአንዳንድ አጎራባች ህዝቦች መካከል በወሰን፤በግጦሽ መሬት ወዘተ እየተባለ በሰበብ በአስባቡ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አንዳንዶቹ በፍጥነት እልባት ቢደረግላቸዉም አብዛኛዎቹ ግን ዘላቂ መፍትሄ ያልተቀመጠላቸዉ ናቸዉ፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያን ከሚያዋስኑ ክልልች ሁሉ ጋር ይብዛም ይነስም ግጭቶች መከሰታቸዉ አልቀረም፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት እንኳን ከሶማሌ ክልል ጋር ግጭቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከሁሉም የከፋዉ ደግሞ ከማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ያለዉ ዉዝግብ ነዉ፡፡ ምንም እንኳን የማንነት ጥያቄ በህገመንግስቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ መፍትሄ ያገኘ ጉዳይ ነዉ ቢባልም እስከዛሬም የግጭት መንስኤ ከመሆን አልዳነም፡፡

አንዳንዶቹ ከነበሩበት በለጥ ያለ ስታተስ የመፈለግ ወይም ልዩ ወረዳ ወይም ዞን የመሆን ጥያቄ የሚያነሱ ፤ሌሎች ደግሞ በሁለት ኩታ ገጠም ክክሎች መካካል አንድን ህዝብና ህዝቡ የሰፈረበትን አካባቢ “የእኔ ነዉ! የለም የኔ ነዉ!” በሚል ወደራስ የማጠቃለል ፍላጎት የጫረዉ አለመግባባቶችና የርስበርስ ግጭቶች ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል አንድ ህዝብ ላይ ሆን ተብሎ የተነጣጠረ ጥቃት ይፈጸማል የሚለዉ ቅሬታም በተደጋጋሚ የተደመጠ ነዉ፡፡ ህገመንግስቱ በፈቀደልን መሰረት የክልልችንን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም፤ በሌሎች መጤዎች እንበዘበዛለን፤ የሚለዉ ስሞታና ባለፈዉ ወራት የተከሰተዉ ዓይነት አጠቃላይ ህዝባዊ ቁጣና ሁከት ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች አካባቢ የተጠቂነትና የተበዳይነት ስሜት ሆን ተብሎ ተጋኖ እንዲነገር በመደረጉ በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች አንዳንድ የዋህ የሆኑ በመከላከያ ሰራዊቱ አባላትን ስሜት መግዛቱና በሂዴትም ሊያስኮርፍ መቻሉ የማይቀር ነዉ፡፡ ምክንያቱም ለወጡበት ህዝብ የመቆርቆር ጉዳይ መቼም ቢሆን የሚቀር ባለመሆኑ ነዉ፡፡

ሁለተኛ፤ በሀገሪቱ ዉስጥ እጅግ ስር የሰደደ ሙስና ወይንም ዝርፊያን አሁን የደረሰበት አደገኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደረጉና ከችግሩም ለመዉጣት የሚደረገዉን ጥረት እንዳይሳካ የሚጥሩ ወገኖች ቁልፍ የሆኑ መንግስታዊ ስልጣንን የተቆጣጠሩ በአብዛኛዉም የአንድ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ናቸዉ የሚለዉ ሃሜትና አመለካከት ገኖ መዉጣቱና አመለካከቱም ከህብረተሰቡ አልፎ በቀላሉ ወደ ሰራዊቱ አባላትም እንዲደርስ በመደረጉ ዝርፊያዉ በተደራጁና የመንግስት ስልጣንን መከታ ባደረጉ ኃይሎች በተቀነባበረ ሁኔታ የሚካሄድ እንጂ የአጋጣሚ አይደለም የሚል ግንዛቤ በመያዙ ይህ ሁኔታ እየፈጠረ ያለዉ ቁጭት ቀላል አይደለም፡፡

ሶስተኛ፤ ገዥዉ ፓርቲ ዘለግ ላለ ግዜ በስልጣን ላይ መቆየቱን ከዲሚክራሲ እጦትና ከአፈና ጋር ለሚያቆራኙ ወገኖች የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ ሆኗል በሚል ተጠያቂ የሚያደርጉት መከላከያና የደህንነት ኃይሉን በመሆኑ የተዋጺኦ አለመመጣጠን ዋነኛ ምክንያትም የገዢዉን ፓርቲ በስልጣን ላይ ለማቆየትና በተለይም ደግሞ ትግሪኛ ተናጋሪዉን ሁለንተናዊ የበላይነት ለማስጠበቅ ታስቦ ነዉ የሚል ነዉ፡፡

አራተኛ፤- አሁን በደረስንበት ወቅት ተዋጽኦ በአግባቡ አልተተገበረም ለሚለዉ ትችት መንግስት እንደ ቀድሞዉ “ብቃት ያለዉ ሰዉ ስላላዘጋጀሁ ነዉ“ የሚል ምክንያት መስጠት አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ፤ ከሃያ አምስት ዓመት በኋላም ብቁ ሰዉ አላፈራሁም የሚል ምክንያት አዋጭ ስላልሆነ፤ ሁለተኛ የዚህ ዓይነት ሰበብ ለመቀበል ትእግስቱ ያለዉ ሰዉ አሁን ባለመኖሩ ፤ሶስተኛ ደግሞ ብቁ ምትክ አመራር የማፍራት ሃላፊነትም ቢሆን የራሱ የመንግስት እንጂ የሌላ የማንም ባለመሆኑ ተወቃሹም ራሱ መንግስት በመሆኑ ነዉ፡፡

12/ የተዋጽኦ ከፍተት በባህሪዉ የመንግስትን ገመና በቀላሉ የሚያሳጣ ሊደበቅና ሊሸፋፈን የማይችል አሳጭ ነዉ፡፡

የተዋጺኦ ጉዳይ ክፋቱ ደግሞ መንግስት ድክመቱን ለመደበቅ ቢሞክር እንኳን ለመደበቅ የማይቻልና በቀላሉ የሚታወቅ መሆኑ ነዉ፡፡ በተዋጽኦ አካባቢ ክፍተት መኖሩን ለማወቅ ዜጎች የዉጭ ሚዲያን ማሰስ ወይም የሌሎች አጥፊ ኃይሎችን ምክርና ቅስቀሳ ማዳመጥ ሳያስፈልጋቸዉ ከፍተቱን በቀላሉ ለመረዳት ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ ብሄር ወይም ቋንቋ ተናጋሪ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ስንት ጄነራል፤ ስንት ኮሎነል፤ ሰንት የክፍለ ጦር አዛዥ፤ ስንት የዋና መምሪያ ኃላፊ ወዘተ እንዳለ በቀላሉ ለማወቅ ይችላል፡፤አንዳችም ምስጢራዊነት የሌለበት በመሆኑ እያንዳንዱ ተራዉ ዜጋ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፓርላማ አባላትና ከመከላከያ ሚኒስትሩም ሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተናነሰ መረጃ አለዉ፡፤ለዚያዉያም ከነ ስም ዝርዝርና ከብሄራዊ ማንነትና የሃላፊነት ደረጃን ጨምሮ ማለት ነዉ፡፡

መንግስትም ቢሆን አስካሁን ተዋጺኦን ለማስተካከል እርምጃዎችን በወሰደ ቁጥር ለህዝብ በይፋ ስገልጽ ስለቆየ ጉድለቱን ለመረዳት አዳጋችነት የለዉም፡፡ የአሁኑ ሁኔታ ከድሮዉ የሚለየዉ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሟላ መረጃ የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ሳይሆን ለክፍተቱ መንግስት የሚሰጠዉን ምክንያት እንደቀድሞዉ ለመቀበል ያለመፍቀድ ጉዳይ ነዉ፡፡ ክፍተቱ አስካሁንም ሊስተካከል ያልቻለበት ምክንያትን የተለመደዉ በአተገባበር ላይ የሚታይ የአፈጻጸም ችግር መሆኑ አብቅቶ ዋነኛ ፖለቲካዊ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡

የሀገሪቱ ህዝቦች ህገመንግስቱ ባጎናጸፋቸዉ መብት ተጠቅመዉ በማንነታቸዉ ከመኩራት ጀምሮ ፌዴራላዊ ስርአቱ ዉስጥ ተገቢዉ ዉክልና ያገኙና ራሳቸዉን በራሳቸዉ እያስተዳደሩ ቢሆንም ለህልዉናቸዉ ዋስትና አድርገዉ በሚቆጥሩት በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ተገቢዉን ቦታ አላገኘንም የሚል ቅሬታ ቢያነሱ ግራ ልንጋባ አይገባንም፡፡ የሀገሪቱ ህዝቦች በሆነ አጋጣሚ የሆነ የመብት ጥያቄ ብናነሳ አይምሮዉን ነካ በሚያደርገዉ አንድ የሆነ ወፈፌ ባለስልጣን ትእዛዝ መከላከያዉ ታዞ መብታችንን ሊደፈጥጥ ይችላል የሚለዉ ስጋት በመከላከያ ሰራዊቱና በደህንነት ተቋሙ ዉስጥ ባሉት የሃላፊነት ቦታዎች ላይ በተገቢዉ መንገድ አልተወከልንም ከሚለዉ ቅሬታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነዉ፡፡ ይህንን ቅሬታም ሆነ ስጋት መቅረፍ የሚቻለዉ ተዋጺኦን በሚገባ መተገበር ሲቻል ብቻ ነው፡፡

13/ የአመራር ብቃትን ከብሄራዊ ማንነት ጋር የማቆራኘት አደገኛ አመለካከት፤

የአመራር ብቃትን በዘርና በማንነት መፈረጅ ስህተት መሆን ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነዉ፡፡ በርግጥ የማይካድ ነገር አንዳንድ ግዜ ሃላፊነትን በመወጣት ሂዴት ከበላይ የሚጠበቅ የተለመደ እገዛን እኩል ላይገኝ ይችላል፡፡ አንዳንዴ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ከበላይ ጠይቆ ማስፈቀድ ለአንዳንዶች አዳጋች የሚሆንበት ለለሎች ደግሞ ሳይጠይቁም እገዛ የሚደረግላቸዉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለስራ አፈጻጸም የሚደረገዉ ግምገማ ወይንም ምዘናም በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን ማንነትን ተጽእኖ ዉጭ አይደለም፡፡ ይህ ግን አልፎ አልፎ በአንዳንድ ግለሰቦች አካባቢ የሚታይ በመሆኑ አጠቃላይ ስርአታዊ ተደርጎ ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡

ሌላዉ ተጠቃሽ ነገር መንግስትና መከላከያ ሁሉንም ያለአድሎ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንዳንድ መልካም ዕድሎችን የተነፈጉ ግለሰቦች ሁኔታዉን በቀጥታ የሚያያዙት ከማንነታቸዉ ጋር መሆኑ ነዉ፡፡ ማእረግ ያላገኘዉ፤ የትምህርት አድል የተነፈገዉ ወይም ለሰላም ማስከበር ተልኢኮ ያልተላከዉ ወዘተ ሁሉ በሌላ ምክንያት ሳይሆን በማንነቱ ምክንያት አደርጎ ያስባል፡፡ ሌላ ችግር ወይም የግል ድክመት ይኖርብኝ ይሁን ብሎ ራሱን አይጠይቅም፤ቢነገረዉም አይቀበልም፡፡

በዚህ ረገድ ከሁሉም በላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉት አንዳንድ የመብት መጓደልና የተለመዱ አስተዳደራዊ በደሎችን አለቅጥ እያጋነኑ ከጉዳዩ ባለቤት በላይ ተቆርቋሪ መስለዉ በመቅረብ አድሉን እንደ ሌሎች ተጠቃሚ ልትሆን ያልቻልከዉ በብሄራዊ ማንነትህ ምክንያት ነዉ ብለዉ ማስቆጨትና ለማስቆጣት የሚጥሩ መሰሪዎች መኖራቸዉ ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነት መሴሪ ሰዎች የአድሉ ተጠቃሚ መሆን ያልቻልኩት በማንነቴ ምክንያት ሳይሆን በግል ድክመቴ ነዉ ብሎ የሚነግራቸዉንም በጭራሽ አይቀበሉትም፡፡ አንዳንድ የዋሆች እዉነት እየመሰላቸዉ የተበዳይነት ስሜት በዉስጣቸዉ እንዲያቆጠቁጥ ያደርጋሉ፡፡

እኔን እንኳን ሳይቀር አንድንድ ድሮ አብረዉኝ የሰሩ የመስሪያ ቤቱ አባላት ለእኔ አዛኝ መስለዉ ቀርበዉ በዚሁ በሆርን አፋየርስ ላይ አንድ ግዜ የምሰጠዉን ገንቢ አስተያየት ያነበቡ “ስንት የተጠቀመ እያለ አንተ ሌላዉ ቀርቶ ይሄን፤ ይሄን… ወዘተ የተነፈክ ሰዉ ደርሰህ ለወያኔ ተሟጋች የምትሆንበት ምክንያት ምንድነዉ? ለምን ያልበላህን ታካለህ? የሚሉኝ ብዙ ናቸዉ፡፡ አንዳንዶቹ ደፋሮች እንዲያዉም ዘር በመጥቀስ እንትን ብትሆን ኖሮ ይሄን ይሄን ታገኝ ነበር በማለት ዘረኛ አመለካከታቸዉን ሊያጋቡብኝና ሊያስቆጩኝ ይሞክራሉ፡፡ እኔ በግሌ በተወሰነ ደረጃ ቁጭት የሚፈጥርብኝ የተበዳይነት ስሜት በዉስጤ ባይጠፋም በበደሉኝ መሰሪ ግለሰቦች ምክንያት እጅግ ግሩም አመራሮች የሞሉበትን የመከላከያ ተቋም መዉቀስ ተገቢ እንዳልሆነ ስለምገነዘብ ለዚህ ዓይነቱ የተንኮል ቅስቀሳ ቦታ ሰጥቼ አላዉቅም፡፡ እኔ በበኩሌ ይህን መሰሉን ሁሉን ነገር በማንንት ላይ የተመሰረተ ፍሬጃ ዉሎ ሲያድር በታታኝ እንዳይሆን ሁልግዜም ከስጋት ዉጭ ሆኜ አላዉቅም፡፡

14/ ተዋጽኦ በወታደራዊ ብቃት ኪሳራ የሚመጣ መሆን አይኖርበትም

ብሄራዊ ተዋጽኦን በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥ መተግበር ጉዳይ ሲነሳ ለተዋጸኦ ሲባል የመከላከያ ግዳጅ አፈጻጸም ብቃትን የሚጎዳ እርምጃ አስከመዉሰድ መድረስ አለበት ማለት አይደለም፤ ለተዋጽኦ ተብሎ ወታደራዊ ብቃቱ እንዲዳከም የሚደረግበት አግባብ አይኖርም፡፡ ምናልባት ተፈላጊዉ ጉዳይ ማመጣጠኑ ነዉ እንጂ ወታደራዊ ብቃትን መጠበቅ አሳሳቢ አይደፈለም የሚል የተዛባ አመለካከት ያለቸዉ ካሉ ተዋጸኦን በወታደራዊ ብቃት ኪሳራ ማምጣት ተገቢ ነዉ ብለዉ የሚያስቡ ጠባብ አስተሳሳብ ያላቸዉ ራስ ወዳድ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡

ለተዋጽኦ ተብሎ ብቃትን የማጣጣል አመለካከትም ሆነ ተዋጽኦ በአግባቡ መተግበር የመላከያን ብቃት ይጎዳል የሚለዉ አመለካከት ሁለቱም የተሳሳቱ ናቸዉ፡፡ መከላከያ ተቋሙ የሚደራጀዉ የሀገሪቱን ለኡላዊነት ለማስጠበቅ በአጭሩ ለጦርነት ተብሎ በመሆኑ ሊኖረዉ በሚገባ ብቃት ላይ አንዳችም ድርድር ሊደረግበት አይገባም፡፡ ተዋጺኦ በመከላከያ ዉስጥ መተግበር አለበት ስለተባለ ተቋሙ ራሱ ገና ከመነሻዉ የሚቋቋመዉ ለተዋጸኦ ተብሎ አለመሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡

ተዋጽኦን በመካለከያ ሰራዊቱ ዉስጥ መተግበር በምንም መንገድ ቢሆን የተቋሙን ብቃት የሚያዳክም አለመሆኑ ነዉ፡፡ ተዋጸኦን በአግባቡ ማኔጅ ማድረግ ከተቻለ ተዋጽኦ ለተቋሙ ብቃት እንቀፋት የሚሆንበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ እንዲያዉም ብዙዎቹ የጉዳዩ አጥኚዎች እንደሚስማሙት በተሳካ ሁኔታ ብሄራዊ ተዋጸኦን መተግበር ከተቻለ ወታደራዊ ተቋሙ ብቃት በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረዉ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም በሰራዊቱ ዉስጥ ተዋጽኦን በአግባቡ መተግበር የሚስፈልገዉ ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም ለይስሙላ ተብሎ ሳይሆን ለተቋሙ ጥንካሬ ስለሚበጅ ጭምር ነዉ፡፡ ተዋጽኦን የጠበቀ ወታደራዊ ተቋም ወይም አሃድ ከሌሎቹ በተሻለ የግዳጅ አፈጻጸም ብቃት ይኖረዋል፡፡

የተለያዩ እምነት፤ባህልና ቋንቋና ልማድ ፤ የተለያዩ የችግር አፈታት ብልሃቶች ያላቸዉ አባላት የተካተቱበት ተቋም ለሁሉም በዩኒቱ አባላት መካከል የሚመሰረተዉ የርስበርስ ቁርኝትና ዝምድና (unit cohesion) ለግዳጅ አወጣጣቸዉ ትልቅ ሃይል ይሆናችዋል፡፡ የዉጊያ ሞራላቸዉ ከፍተኛ ስለሚሆን በዉጊያ ወቅት ለአንዳችም ችግር በቀላሉ የሚበገሩ አይሆኑም፡፡ በቅርቡ የመከላከያ ሰራዊታችንን ቀን አከባበር ጋር በተያያዘ በሶማሊያ ከአልሻባብ ጋር እጅግ አኩሪ ገድል የፈጸመችዉ የሰራዊት ክፍል (አራተኛ ሬጅሜንት) አባላት ከተለያዩ የሀገራችን ህዝቦች የተዉጣጡ መሆናቸዉን ስናስታዉስ አብሮነታቸዉ ለዚህ የጀግንነት ታሪክ አስተዋጽኦ እንዳደረገለቻዉ መረዳት እንችላለን፡፡

በርግጥ ተዋጽኦን ለመጠበቅ ብቻ ተብሎ ለወታደራዊ ተቋሙ ተልኢኮ ስኬታማነት እጅግ ወሳኝ የሆነዉ የብቃት ጉዳይ ወደ ጎን ችላ የሚባልበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸዉ፡፡ በምደባ፤ ለስልጠናና ትምህርት መረጣ፤ ለሹሜትና ለመሳሰሉት ሌሎች አጋጠሚዎች ሁሉ ሆን ተብሎ አድሎአዊ አሰራር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ተገቢ ነዉ፡፡ ነገር ግን ለአንድ ስራ ወይም ምደባ የሙያዉ በተለየ ከሚጠይቀዉ ብቃትን መነሻ ያደረገ መስፈረት ወደ ጎን እየተደረገ በኮታ ለማዳረስ (ለማቃመስ) የሚደረግ ሙከራ ተቋሙን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ወታደራዊ ተቋሙ እንዲፈጽም በተሰጠዉ ተልኢኮ ላይ ደንቃራ በሚሆን መንገድ ተዋጽኦን ለመተርጎም መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡

ሁልግዜም ቀዳሚዉ መስፈርት መሆን ያለበት ብቃት ሆኖ ብቃቱ ያላቸዉ የተለያዩ ሰዎች በብሄራዊ ማንነታቸዉ ምክንያት አንዳችም ልዩነት ሳይደረግባቸዉ እኩል ሊወዳደሩ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ግዜ በብቃት ሰበብ ከሌሎች አካባቢ ለመጡት አስካናካተዉ ሁሉን ዕድል ዝግ ማድረግም በራሱ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል በቀጥታ ከግዳጅ ጋር ግኑኝነት በለላቸዉና ረዳት (እገዛ) ከተደረገላቸዉ ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈትሾ መስፈርቱ እንደ ሁኔታዉ ቀለል ሊደረግ የሚችልበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ የትኞቹ የስራ መደቦች ናቸዉ በዚህ ደረጃ መታዬት ያለባቸዉ በሚለዉ ላይ መስሪያ ቤቱ በቅድሚያ ሊወስን ይገባል፡፤ከዚያ ዉጭ ግን ብቃትን መስፈረት ባደረገ መልኩ ፍትሃዊና ግልጽነት የሰፈነበት ዉድድር ሳይደረግ በአንዳንድ ብልሹ አመራሮች ፍላጎት ብቻ ጥቂቶች ሁልግዜ በማንነታቸዉ ብቻ በተለየ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ሌሎች ደግሞ ችላ የሚባሉበት ሁኔታ ሊኖር አይገባዉም፡፡

15/ ለተዋጽኦ ተብሎ ብቃትን ችላ ያለ የከፍተኛ ማዕረግ አሰጣጥ ሊስተካከል ይገባል፡፡

በመከላከያ ሰራዊታችን ዉስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ከተዋጽኦ አለመመጣጠን ይልቅ አሳሳቢ ሊሆን የሚገባዉ ለማመጣጠን ተብሎ ከአቅም በላይ የመሾም ችግር ይመስለኛል፡፡ ለመወሰንና ለመምራት አቅም የሚያንሳቸዉ ሳይቀሩ ለተዋጽኦ ተብሎ መሾም ከግለሰቦቹ ዉጭ ማንንም ነዉ ሊያስደስት አይችልም፡፡ አንዳንድ ግዜማ የሆነ ብሄር ህዝብን ያስደሰትን እየመሰለን ያለ አቅማቸዉ የምንሾም ነዉ የሚመስለኝ፡፡

አንዳንዱ እድለኛ የሆኑ ያለብቃቱ የተሰጠዉን ማእረግ አይተህ ለምን እንደሌሎቹ መወሰንና ማስፈጸም እንደማይችል ለመረዳት ይከብድሃል፡፡ በአንድ ወቅት በዚህ ደረጃ የሚገኝን አንድ ከፍተኛ መዕረግተኛ በሆነ ጉዳይ ላይ ለምን እንደማያስፈጽም በጠየኩት ግዜ የሰጠኝ መልስ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” የሚል ነበር፡፡ ለስሙ ትልቅ ማእረግ ቢኖረኝም ምንም ማድረግ ስለማልችል አትፍረድብኝ ማለቱ እንደሆነ ስለገባኝ በሱ ላይ በግል አላዘንኩበትም፡፡ ማእረግና ሃላፊነት ሲሰጣቸዉ አቅሜ አይመጥነኝምና ይቅርብኝ የሚል የለም፡፡ አንዳንዱ በየዓመቱ ቢሾም የማይጠላም አለ፡፡ አንዳንድ ትልቅ ሃላፊነተ ተሰጥቶት እያለ ለምን እንደማይሰራበት ሲጠየቅ “አያሰሩህም!” በሚል የዉሸት ሰበብ ያበዛል፡፡

እኔ እንደተረዳሁት ከሆነ መንግስት ትልቅ ሃላፊነት (ማእረግ) ሰጥቶአቸዉ ነገር ግን ሃላፊነታቸዉን ለመወጣት የተሳናቸዉ በማንም ላይ ሰበብ መፍጠር አይገባቸዉም፡፡ ትልቅ ሃላፊነት ቦታ ተቀምጠዉ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸዉ ሰዎች የራሳቸዉ የግል ችግር እንጂ የመንግስት ወይም የስርአቱ ወይም ከሆነ አካባቢ ጫና ስለሚደረግባቸዉ አይደለም፡፡ በሁለት ማእረግ የሚያንሳቸዉን የበታቻቸዉን ማዘዝና መገሰጽ የተራራ ያህል የሚከብዳቸዉ ብዙ ናቸዉ፡፡ እኔ አስከማዉቀዉ ድረስ ለአማራዉም ለወላይታዉም ለትግሬዉም ይሁን ለሌላ መንግስት ከፍተኛ ማእረግ ሲሰጥ ሃላፊነታቸዉን በብቃት እንዲወጡ ለሁሉም ከአደራ ጭምር የማዘዝና የመምራት ስልጣን ይሰጣል እንጂ አንዱን ከሌላዉ በማንነት መስፈርት ለይቶ አይደለም፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂዉ ማነዉ ከተባለ መንግስት ወይም መከላከያ ሳይሆን ራሳቸዉ ግለሰቦቹ ናቸዉ፡፡ የዚህ ዓይነቶቹ በራስ መተማመን የጎደላቸዉና ጥላቸዉን ሳይቀር የሚጠራጠሩ ለዚህ ቦታ የበቁት አንዳንድ ሃላፊነታቸዉን የዘነጉ አመራሮች ከወታደራዊ ብቃት ይልቅ በግላቸዉ ታማኝና አደግዳግ የሆነዉን እየመረጡ ለበላይ በማቅረብ መንግስትን በማሳሳት በማሾማቸዉ ነዉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አመራሮች አስካሉ ድረስ ይህ ችግር ወደፊትም ቢሆን ይቀረፋል ብዬ አላስብም፡፡

መንግስት በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚመጥን ሰዉ ገና አላገኘሁም የሚለዉን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ማጣጣልም አይቻልም፡፡ አስካሁን ብቁ ሰዉ ማፍራት አለመቻሉ የራሱ የመንግስት ድክመት እንደሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ መንግስትም ራሱ ይህን አይክድም፡፡ ይሁን እንጂ ክፍተኛ ማእረግና ሹመት ተነፍገናል የሚሉና የጄኔራልነት ማዕረግ ለማግኘት የሚቋምጡ በሰራዊቱ ዉስጥ ያሉ ከፍተኛ መኮንኖች ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት ራሳቸዉን ለማብቃት ምን ያህል ጥረት እንዳደረጉ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ግን አብዛኛዎቹ ከፍተኛ መኮንኖች በሰራዊቱ ዉስጥ የነበራቸዉን የቆይታ ግዜ እንደ ብቸኛ መስፈርት በመቁጠር ተጨማሪ ማዕረግ ከመጠበቅ ባለፈ ትላልቅ ወታዳራዊ ዘመቻዎችን አቅዶ ለመምራት የሚያበቃቸዉን አቅም ለመፍጠር ብዙም የሚጨነቁና ጥረት የሚያደርጉም አይደሉም፡፡ እገለ ጄኔራል ከሆነ በዚህ ዓይነት እኔም ሳልሆን አልቀርም እያሉ የቀን ቅዤት የሚቃዡ ናቸዉ፡፡

በኤርትራ ወረራ ሳቢያ የተቀሰቀሰዉ ጦርነትም በዚህ ረገድ የማይዘነጋ ትምህርት የሰጠ አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ ከወረራዉ ቀደም ብሎ ተዋጽኦን ለማመጣጠን ተብሎ ብቃቱና ልምዱ ያልነበራቸዉ ሁሉ የከፍተኛ መዕረግ ሲሰጣቸዉ ወደፊት ችግር ሊከሰት ይችላል ብሎ የገመተ ሰዉ አልነበረም፡፡ በጦርነት ዉስጥ ተፈላጊዉ ነገር ወታደራዊ መዕረግ ሳይሆን የአመራር ክህሎት በመሆኑ ብዙዎቹ ከፍተኛ መኮንኖች (ኮሎነልና ጄኔራሎች) ሰራዊት ለመምራት የሚያበቃቸዉ አቅም እንዳልነበራቸዉ ታሳቢ በማድረግ መንግስት የሚያግዟቸዉን ሰፊ የጦርነት ልምድ ያካበቱትን ደርቦ ለመመደብ ተገዶ ነበር፡፡ እነሱም ቢሆኑ ጦርነቱን ለመምራት አቅም እንደሚጎድላቸዉ በመረዳታቸዉ በተወሰደዉ እርምጃ በወቅቱ ያሰሙት ተቃዉሞ አልነበረም፡፡

ተቃዉሞና ጫጫታ የተፈጠረዉ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኃላ በ93ቱ ቀዉስ ግዜ ነዉ፡፡ እኛ ወደ ጎን ተደርገን ሌሎች አመራር እንዲሰጡ ተደረገ እየተባለ በምሬት የታጀቡ ትችቶች እንደጉድ ተሰነዘሩ፡፡ ብሄራዊ ማንነታችን ተንቋል ፤መከላከያም ቤታችን አይደለም አስከማለትም ተደረሰ፡፡ የህወኃት የበላይነት በክልላችን ሰፍኗል የሚሉ ወቀሳዎች ጋር እየተዳበለ በሰራዊቱ ዉስጥም በማንነታችን ተንቀናል የሚል ብሶት በሰፊዉ ሲራገብ ቆየ፡፡ በወቅቱ በጦርነቱ ግዜ ሰራዊቱን በከንቱ ማስጨረስ ስለማይገባ መንግስት ወይም የሚመለከተዉ አካል በከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች ደረጃ ብቃት ያላቸዉን ለዚያዉም በአጋዥነት መመደቡ የሚያስተችና መብቴ ተደፈሬ የሚያስብል ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡ የሚያሳዝነዉ ደግሞ ዛሬም ድረስ ከዚያ ትምህርት የቀሰምን በማይመስል ሁኔታ በማንነት ሰበብ ከፍተኛ ማእረግ የመሻት ዝንባሌ አሁንም አመቅረቱ ነዉ፡፡

በመሰረቱ ለተዋጽኦ ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ከአቅም በላይ የሆነ ማዕረግ የመስጠት ጉዳይ ስርአት ሊበጅለት ይገባል፡፡ የጄነራልነት ማእረግ በፖለቲካ ዉሳኔ የሚሰጥ መሆኑ ባይካድም ነገር ግን መዕረጉ የሚጠይቀዉን ብቃት አሟልቶ መገኘት የግድ ነዉ፡፡ ፖለቲካዊ ሹመት ሲባል በሁሉም ረገድ ብቃቱ ካላቸዉ መካከል ለመምረጥ የሚያገለግል እንጂ በኮ/ል መንግስቱ ዘመን ሲደረግ እንደነበረዉ አምሳ አለቃና አስር አለቃ ባንድ ግዜ ጄኔራል የሚሆንበት አሰራር በሃገር ላይ የሚሰራ ወንጀል ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሽሬ እንዳስላሴ ላይ ያለቁት ለከ/ል መንግስቱ በግል ካለዉ ታማኝነት በስተቀር አንዳችም ወታደራዊ የአመራር ብቃት በለለዉ በሃምሳ አለቃ ለገሰ አስፋዉ እንዲመራ ስለተፈረደበት ነዉ፡፡

በየትኛዉም አገር የተለመደዉ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ከመስጠት አስቀድሞ ለዚያ ቦታ ተሳቢ የተደረጉት በቅድሚያ ከፍተኛ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ዉስጥ እንዲገቡ በማድረግ ለቀጣዩ ሃላፊነትና መዕረግ የሚመጥን አቅም ፈጥረዉ እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በኛ አገር ግን ደረጃዉን የጠበቀ የከፍተኛ አዛዥነትና የመምሪያ መኮንነት ኮሌጅ ባለቤት ሆነን እያለ እዚያ ገብተዉ እንዲሰለጥኑ ሳይደረግ ያለአንዳች ተጨማሪ እዉቀትና ልምድ በዘፈቀደ ማዕረግ መስጠታችን ሀገሪቱን ከመጉዳት በስተቀር አንዳችም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡ በመልካም ጎኑ ሊጠቀስ የሚገባዉ ተሞክሮአችንንም በአግባቡ መጠቀም ይገባናል፡፡

ለምሳሌ ከደርግ ዉድቀት በኋላ ወደ መከላከያ ሰራዊታችን የተደባለቁ ወጣቶች በየግዜዉ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰዱና በግዳጅም እየተፈተኑ ወደ ከፍተኛ መኮንንት ከደረሱ በኋላም በተጠቀሰዉ ከፍተኛ ኮሌጅ ገብተዉ በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላም በተግባር በሰራዊት አመራርነት ሰፊ ልምድ በማካበት ብቃታቸዉን በማስመስከር በመጨረሻም ለብ/ጄኔራልነት ማእረግ የደረሱ እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡ ለአብነት ከአየር ኃይል እንዴ ብ/ጄነራል ይልማ መርዳሳና ከአርሚዉም ቢሆን በርካቶች እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡ እነዚህን መሰል በልምድም በትምህርትና ስልጠናም የዳበረ አቅም እየፈጠሩ ያሉ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ከጥቂት ግዜ በኃላ በኦፕሬሽናልም ሆነ በስትራቴጂክ ደረጃ እጅግ የተዋጣላቸዉ ወታደራዊ መሪዎች የማይሆኑበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ለወደፊቱ እነ ጄነራል አብርሃምን (ኳርተር) ጄ/ል ሰአረን ጄ/ል ብርሃኑን ብቻ ሳይሆን ጄኔራል ሳሞራንም ቢሆን መተካት የሚገባቸዉ በዚህ መንገድ የመጡት ብቻ መሆን አለባቸዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን ለምን ሳሞራ ስልጣን ላይ ብዙ ቆየ? የዕዝና የከፍለጦር አዛዥ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ለምን ትግርኛ ተናጋሪዎች ቁጥራቸዉ በዛ? ብሎ መቆጨትና በንዴት ጸጉር መንጨት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለምን ለከፍተኛ ሹመት አልተሸምኩም ብሎ ከመጠየቅ በፊት መቅደም ያለበት በያዙት መዕረግ በሚገባ ሰርቶ በተግባር በማስመስከር ለቀጣዩም ራሰን ማብቃት ነዉ፡፡

16/ ለህገ መንግስታዊ ስርአቱ ታማኝነት በብሄራዊ ማንነት መመዘን አይኖርበትም!

ለስርአቱ ተማኝነት በማንነት ላይ ሊመሰረት አይገባዉም፡፡ ለስርአቱ ታማኝነትን በማንነት ለሚለኩ አንዳንድ ሰዎች ሲባል ለስርአቱ ታማኝ መሆንህን ለማረጋገጥ ወይም ለመታመን ከሌሎቹ የበለጠ ብዙ መድከም ይኖርብሃል፡፡ በነዚህ ወገኖች ዘንድ ተአማንነት ለማትረፍ በቀላሉ የሚቻል አይደለም፡፡ ለእናት አገርህና ለህገመንግስታዊ ስርአቱ ህይወትህን ለመገበር ዝግጁ መሆንህን እያወቁም ከማንነትህ በመነሳት በስርአቱ ታማኝነትህ ሊጠራጠሩህ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቸግር ግን ጥቂት ብልሹ ግለሰቦች የሚፈጥሩት በመሆኑ ልትሸበርና ልታኮርፍ አይገባህም፡፡

ህገመንግስታዊ ስርአቱንና ለህገመንግስቱ ታማኝ በመሆን ረገድ በማንነቱ ምክንያት ማንም ከማንም የተለየ ታማኝነትና ኃላፊነት ሊኖረዉ አይገባም፡፡ ስርአቱን ለመጠበቅም ሆነ የዚህችን አገር ሉአላዊነት ለማስከበር ወላይታዉም፤ ትግሬዉም፤ ሲዳማዉም ፤አማራዉም፤ ኦሮሞዉም፤አፋሩም ወዘተ ሁሉ ማንም ከማንም ሳይበልጥ እኩል ሃላፊነት አለበት፡፡ በማንነት ላይ ተመስርቶ የሚታመንና የማይታመን ወይም ታማኝነቱ አጠራጣሪ የሆነ የሚባል ፍሬጃ ሊኖር አይችልም፡፤ኦሮሞነትን ከኦነግ፤ አመራነትን ከግንቦት ሰባት፤ ትግሬነትን ከሻእቢያ ጉዳይ አስፈጻሚነት ወዘተ በቀጥታ በሚተረጉሙ ብልሹ አመራሮች ምክንያት ያለሃጥታቸዉ ለአስርና እንግልት የሚዳረጉ እንዳሉ ማንም የሚያዉቀዉ ነዉ፡፡ ይሄን የሚያደርጉ ጥቂት ብልሹ አመራሮች ምክንያት በሰራዊታችን ዉስጥ የዚህ ዓይነት ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ግልጽ ነዉ፡፡

በተጨማሪ መንግስት ከጣለባቸዉ አደራ በላይ ለግል ጥቅማቸዉ ቅድሚያ የሚሰጡ አንዳንድ አመራሮች ከህገመንግስቱ መንፈስና ከመንግስት ፍላጎት ዉጭ በሚያደርጉት አድሎአዊ አሰራርና በሚያሳዩት ንቀት የተነሳ አንዳንድ የሰራዊቱ አባላት ብሄራዊ ማንነታቸዉ የተናቀ ቢመስላቸዉ አይፈረድባቸዉም፡፡ መታወቅ ያለበት ግን ይህ ችግር የመንግስት ወይም የመከላከያ መመሪያና ፍላጎት ስለሆነ ሳይሆን ግለሰቦች የሚፈጥሩት ችግር መሆኑን ተደረድተዉ በሰራዊቱ ዉስጥ ባለት መድረኮችና ሌሎች አማራጮችን ተጠቅመዉ በድፍረት ማጋለጥ ይገባቸዋል፡፡ ይህ መሰሉን ብልሹ ባህሪይና ደርጊት እንዲከታተለኩና እንዲያርሙ ተብለዉ በሰራዊቱ ዉስጥ የተቋቋሙ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ሃላፊነታቸዉን በሚገባ ሊወጡ ይገባል፡፡

17/ የተዋጽኦ ጉዳይ የመከላከያ የዉስጥ ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም ህዝቦች የጋራ አጀንዳ ነዉ፡፡

ብዙዎቹ የዋህ ዜጎች ይሄ የተዋጽኦ ጉዳይ እነሱን የማያስጨንቃቸዉ፤ለአደባባይም የማይበቃና ለፖለቲካ አጀንዳነት የማይመጥን በዚያዉ በመከላከያ ዉስጥ ማለቅ ያለበት የወታደሩ የራሱ የዉስጥ ጣጣ አድርገዉ የሚቆጥሩ ይኖራሉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ሃላፊነት እንዳለበት በሚታወቀዉ የሀገሪቱ ህግ አዉጭ በዚህ ረገድ ምን ያህል ክትትል ሲደርግ እንደነበር የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ይህ ጉዳይ ለራሱ ለመከላከያ መተዉ አለበት የሚለዉ አመለካከት ፍጹም የተሳሳተና ፋይዳዉን ካለመገንዘብ የሚሰጥ አስተያየት ነዉ፡፡

በሰራዊቱ ዉስጥ የእኩል መብት መጠበቅ ጉዳይ በግሉ ለአባሉ ከሚሰጠዉ ጥቅም አንጻር ብቻ መመመዘን አይኖርበትም፡፤መብት መጓደል ሲደርስም በአንድ አባል ላይ የተደረገ መድሎ ተደርጎም የሚቆጠር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከአፋር ወይም ከወላይታ፤ ከኦሮሞ ወዘተ የመጣ አባል ሆን ተብሎ አድሎ የሚሰራበት ከሆነ በግል እንደደረሰ የአጋጣሚ ችግር ሳይሆን በቀጥታ አባሉ ከወጣበት ህዝብ ላይ በደል እንደደረሰ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታም ሊኖር እንደሚችል መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ ያለዉ አባል በጉዳዩ ላይ ከሚያስሳስበዉ በላይ እሱ የወጣበት ህዝብን የሚያሳስብ ሊሆን ይችላል፡፡ የሀገሪቱ ህዝቦች በተለይም ለዘመናት ወደ ኃላ እንዲቀሩ የተደረጉ ህዝቦች በስርአቱ ዉስጥ ያላቸዉን ቦታ ወይም ተቀባይነት የሚለኩበት አንዱ መንገድ በሰራዊቱ ዉስጥ ልጆቻቸዉ የደረሱበትን ደረጃ በማዬት ጭምር ነዉ፡፡

18/ ተዋጽኦን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ለወደፊቱ መሰራት ያለባቸዉ፤

* በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን የማመጣጠን ጉዳይ ከምንግዜም በላይ አሁን አንገብጋቢ አጄንዳ የሆነበት ደረጃ ላይ ስለደረስን መንግስት እንደበፊቱ ሰበብና ምክንት ሳያበዛ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የመንግስት ጥረት ላይ ደንቃራ እየሆኑ ሲያጓትቱ የነበሩ ግለሰቦች ተለይተዉ ማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድባቸዉ ይገባል፡፡

* ተዋጽኦን የመተግበር ስራ የመከላከያ ተቋሙን ብቃት በማይጎዳ መንገድ እየተፈተሸ ሊሰራ ይገባል፡፡ ለተዋጽኦ ሲባል የተቋሙን አቅም የሚያሽመደምድ እርምጃ መዉሰድ በእጅጉ የሚጎዳን መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም፡፡

* ተዋጽኦን መተግበር በቁጥር ብቻ የሚገለጽ ባለመሆኑ በሁሉም ረገድ የእኩል መብት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና አድሎአዊ አሰራርን ማስወገድ ይገባል፡፡

* በሰራዊቱ ዉስጥ የተዋጽኦ ጉዳይ ለሰራዊቱ አዛዦች ብቻ የሚተዉ ጉዳይ ባለመሆኑ ከህግ አዉጭዉ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢዉን ክትትል ሊያደርጉበት ይገባል፡፡

* ከተዋጽኦ ጋር በተያያዘ ሰፍነዉ የቆዩ የተዛቡ አመለካከቶችን ማረምና በጉዳዩ ላይ የጠራ አረዳድ እንዲኖር ማድረግ ይገባል፡፡

* ተዋጽኦ ትርጉም የሚኖረዉ በታችኛዉ የሠራዊት አባላት ደረጃ ሳይሆን ከዚያ ይልቅ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ በመሆኑ አሁን የሚታየዉ የተዛባ ሁኔታ ተስተካክሎ የተመጣጠነ ዉክልና እንዲኖር ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡

* የእኩልነት ጉዳይ በሰራዊቱ ዉስጥ በአገልግሎት ላይ ባሉበት ወቅት ብቻ ሳይሆን በጡረታ በሚገለሉበት ወቅት ጭምር ሊሆን ስለሚገባ በዚህ ረገድ በአንዳንድ ብልሹ አመራሮች ምክንያት ሲፈጠር የነበረዉ ልዩነትና አድሎአዊ አሰራር ሊስተካከል ይገባል፡፡

* መንግስት አስካሁን ሲያደርግ ከቆየዉ ጥረትና በገጠሙት ተግዳሮቶችና በሚነሱ ቅሬታዎች ላይ ከሚመለከታቸዉ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር ቢመካከርበት ጠቀሜታዉ የጎላ ይሆናል፡፡

* በተለያዩ አጋጣሚዎች አልፎ አልፎ በህዝቦች መካከል በሚቆሰቆሱ ግዜያዊ አለመግበባቶችና ግጭቶች ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በስሜታዊነትና በወጡበት ህዝብ የተለየ ተቆርቋሪነት ተገፋፍተዉ የግጭቱ አካል እንዳይሆኑ ተገቢዉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

* በሰራዊቱ ዉስጥ ጠባብ የጎጠኝነትና የትምክህተኝነት አመለካከት እንዳያቆጠቁጥ መታገልና ራስን የአንድ ብሄር ተወካይ አድርጎ የመቁጠር አመለካከትን ማረምና ከጎጤኝነት ይልቅ ኢትዮዊያነት ከልዩነት ይልቅ የአንድነት መንፈስ እንዲሰርጽ ሊደረግ ይገባል፡፡ የሰራዊቱ አባላት ከፋፋይ አፍራሽና በታታኝ ከሆኑና ቅም በቀል ያረገዙ የፈጠራ ታሪኮች ሰለባ እንዳይሆኑ በጥንካሬ መስራት ያስፈልጋል፡፡

* ተዋጽኦን የሚደግፍ የሚያበረታተና ለአፈጻጸም የሚያግዝ አግባብነት ያለዉ የተለየ ፖሊሲና ለአፈጻጸም የሚያግዝ መመሪያ ማዘጋጀትና ተግባራዊነቱን በጥብቅ መከታተል ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በሀገራችን በህገመንግስቱ አንደ መሪህ ከመቀመጡ ዉጭ ለአፈጻጸም የሚያግዝ ራሱን የቻለ ፖሊሲ ወይም መመሪያ ስለመኖሩ የማዉቀዉ ነገር የለም ፡፡

* በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ በማንነት ላይ የተመሰረተ አድሎአዊ አሰራር እንዳይኖር የሚከታተል አደረጃጀት መፍጠርና በተጨማሪ ይህን በሚመለከት ልዩ ቅሬታ ሰሚና አጣሪ አካል ማቋቋም የግድ ይሆናል፡፡

* በመከላከያ ተቋሙ ዉስጥ ጠንካራ የሆነ የወታደራዊ እምባ ጠባቂ ተቋም ኢንስፔክተር ጀነራል በማቋቋም የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግ ማድረግ ይገባል፡፡

* አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተለይ ተዋጽኦን በመጠበቅ ጋር የተያያዙ እንቀስቃሴዎችን ለማገዝ ሲባል ለዚህ ተብሎ የተለየ ባጄት የሚመደብበትና በዚህ መስክ በሰለጠኑ ሙያተኞች የሚታገዝበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡

* መከላከያ ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ በሰራዊቱ ዉስጥ አድሎአዊ አሰራር እንዳይኖር የእርስበርስ አለመግባባቶችና ቅጭቶች እንዳይፈጠሩና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የማድረግ ተቀዳሚ ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለ የሰራዊቱ አባላትንም ግንዛቤ በማሳደግ ረገድም በርትቶ መስራት ይገባዋል፡፤

* የህዝቦችን እኩልነት በሚጻረር መልኩ አንዱን ዝቅ ሌላዉን ከፍ የሚያደረግ አመለካከቶችና ተሞክሮዎች ሲኖሩ አጥፊዎችን ያለምህረት ተገቢዉን ቅጣት መቅጣት ይገባል፡፤

* ዘረኝነት፤ ጠባብነትና የትምክህተኝነት አመለካከቶች በግዜ እልባት ካልተሰጣቸዉ ስር እየሰደዱ ሲሄዱ የእርስበርስ ግጭት በመፍጠር አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ የዚያ ዓይነት አዝማሚያና ዝንባሌ አለመኖሩን በጥንቃቄ መከታተል ይገባል፡፡

* በማእረግ አድገት ፤በዝዉዉር ፤በሹመት፤ በትምህርትና በምደባ በተቋሙ ዉስጥ አድሎአዊ አሰራር እንዳይኖርና ሁሉም ሊረዳዉ በሚያስችል ደረጃ ግልጽነት የሠፈነበት አሰራር ማስፈን ይገባል፡፡

* በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ አናሳ ህዝቦች (minorities) ጸያፍና አዋራጅ የሆኑ ንግግሮች ፤ንቀት የሚንጸባረቅበት አስተያየት፤ጥላቻና ክብረነክ አስተያቶች እንዳይኖሩ ማድረግ ይገባል፡፤በተለይ አንዳንድ አመራሮች አብሮአቸዉ ለዘመናት በቆየ ቅም በቀልና ጥላቻና የዘረኝነት አመለካከት የተነሳ አስካሁንም ከአይምሮአቸዉ ሊፋቅ ያልቻለ ወደፊትም መቼም ቢሆን ከዚህ ዓይነቱ የትምክህትና የማአለብኝነት አመለካከት መላቀቅ የማይችሉ እንደሚኖሩ ታዉቆ በአንድና ሁለት ሰዉ ምክንያት አጠቃላይ ሰራዊቱ ተቋም ስም እንዳይጎድፍ ተገቢዉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፤

* በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ አብሮነትን የመፍጠሪያዉ አንዱ መንገድ የመቻቻል ባህልን ማዳበር ነዉ፡፡ መቻቻል ሲባል ግን አድሎአዊነትን የንቀት አመለካከትንና የመብተ የማንነት መደፈርን እያየ እንዳላየ ሆኖ የመብት ረገጣዉን በጸጋ ተቀብሎ በዝምታ ማለፍ አለበት ማለት አይደለም፡፡ መቻቻል ሲባል አንዱ * ለሌላዉ እዉቅናና ከበሬታ በመስጠት በአጋጣሚ ሊፈጠሩ የሚችሉ እንከኖች ሲኖሩ አለመግባባቶችና ቅሬታዎችን በዉይይትና በመደማመጥ በመከባበር መንፈስ መፍታ ማለት እንጂ የእኔን የበላይነት ያንተን የበታችነት የግድ መቀበል አለብህ የሚባል መቻቻል ከቶ ሊኖር አይችልም፡፡

ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ለጥቅም የሸጡና የወጡበት ህዝብን በግላጭ የሚያዋርድ ንቀት እየተሰነዘረባቸዉም በህጋዊ አግባብ መብታቸዉን ለማስከበር ከመጣር ይልቅ ራሳቸዉንና የወጡበትን ህዝብ ለሆዳቸዉ ብለዉ የሚያዋርዱ በራሳቸዉ የማይተማመኑ በቁጥር ጥቂትም ቢሆኑ ስለሚኖሩ በፍርሃታቸዉና በአድርባነታቸዉ መላዉን ሰራዊት እንዳይበክሉና ቅሬታቸዉንም አዉጥተዉ እንዲናገሩ ማደፋፈር ይገባል፡፡

* በሰራዊቱ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲሁም በጦር ክፍሎች ዉስጥ ስለተዋጽኦና ተያያዥ ጉዳዮች ራሱን የቻለ ስርአተ ትምህርት ተቀርጾለት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሊሰጥበት ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መከላከያ ሰራዊት ገና በህገመንግስቱ መሰረት በአዋጅ ከተቋቋመበት ወቅት አንስቶ የሁሉንም ዜጎች ደህንነት፤ብሄራዊ ጥቅምና ሉአላዊነት የሚጠብቅ ተቋም እንዲሆንና ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያለአንዳች አድሎ እንዲያገለግል ለማድረግ በሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን ማመጣጠን የግድ መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ መንግስት ተዋጽኦን በሚፈለገዉ ደረጃ ሊያሳካ እንዳልቻለ ባይካድም ነገር ግን ከብሄራዊ አድሎና አንድን ብሄር ወይም ቋንቋ ተናጋሪ በልዩ ሁኔታ ለመጥቀምና ሌላዉን ለማግለል ታስቦ ሆን ተብሎ የተደረገ አንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡

የችግሩ መኖር ብቻዉን አንዱን የስርአቱ ታማኝ ሌላዉን ደግሞ ፍጹም እምነት የማይጣልበት የሚል ትርጉም የሚያሰጥ አይደለም፡፡ በተዋጽኦ ማመጣጠን ረገድ ክፍተቱን እስካሁን ለማጥበብ አለመቻሉ መንግስት ሊወቀስበት የሚገባ መሆኑ እዉነት ሆኖ ነገር ግን እንደ ስርአት አንድን ህዝብ ፍጹማዊ ገዥ ሌላዉን ተገዢ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተዘረጋ ስርአት አስመስሎ ችግሩን እጅግ በማጋነን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም መሞከር ተገቢ አይመስለኝም፡፡

ሆኖም እንደእኔ እምነት ተዋጽኦ በሚፈለገዉ ደረጃ አስካሁን መተግበር አለመቻል የመንግስትን ዳተኝነትና ስንፍና ከማመላከቱ ዉጭ ሌላ ምንም አይነት ሰበብ ወይንም ምክንያት ሊቀርብበት አይገባዉም ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን ክፍተቱን ለብሄራዊ ጭቆናና ስርአታዊ አድሎ መኖር ማሳያ አድርጎ ማሰብ ግን ፍጹም የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አፈጻጸሙ ላይም መጓተትና መዝረክረክ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ጠለቅ ተብሎ ቢመረመር ከመንግስት ቁርጠኝነት ማነስ ይልቅ አንዳንድ በፊት ተጠቃሚ ሆነዉ የቆዩና ተዋጺኦ በአግባቡ ሲተገበር የለመዱት ጥቅም እንደሚቀርባቸዉ ስጋት የገባቸዉ ጥቂት ግለሰቦች የሚፈጥሩት መሰናክል እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

መንግስት ባደረገዉ ጥረት ልክና በሚፈለገዉ ደረጃና በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ሊሆን ባለመቻሉ መንግስትን ለአንዳንድ ወገኖች ትችት የዳረገ ሆኗል፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት ወቅት አንድነታችን ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን እያስተናገድን ባለንበት ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱ ተዋጽኦ ጉዳይ ከድሮዉ በበለጠ አነጋጋሪ አጀንዳ መሆኑ እርግጥ ነዉ፡፡ የተዋጽኦ ጉዳይ ለራሱ ለመከላከያ ሚኒስቴር ወይም ወታደራዊ ተቋሙ ብቻ የሚተዉ ባለመሆኑ መንግስትና መላዉ ዜጎች በተቃዉሞ ጎራ ያሉትም ጭምር በመንግስት ጥረትና በገጠሙት ተግዳሮቶች በቀጣይም መደረግ ባለበት ጉዳይ ላይ በጋራ ተነጋግረዉ የጋራ መፍትሄ ሊያስቀምጡ ይገባል፡፡ መንግስትም በበኩሉ አስካሁን ካደረገዉ የበለጠ ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡

*****************

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories