የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 6 | ቀጣዩ የመንግስት አቋምና ዉጤታማነቱ የማያስተማምነው የዲተረንስ ፖሊሲያችን

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የቀደሙ ክፍሎቸ ለማንበብ በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

Highlights

* መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደርገዋል ተብሎ በሚጠበቀዉ ኤርትራን የሚመለከት ፖሊሲ ላይ አንዳንድ አስተያየቶችን ከመሰንዘሬ በፊት አስካሁን ስንከተለዉ በነበረዉ ዲተረንስ (ሌሎች አገሮች እንዳይተናኮሉን ተብሎ የሚተገበር የዝግጁነት ፖሊሲ) እርምጃችን ዙሪያ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

* ዲተረንስ ጠላት ድጋሚ እንዳይለምደዉ ደህና አድርጎ በመቅጣት (deterrence by punishment) ወይም ደግሞ አስከነአካቴዉ ጥቃት እንዳይሰነዝር እድል በመንፈግ (deterrence by denial) ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛዉንም መንገድ ብንከተል ዲተር ማድረግ የምንችለዉ ዞሮ ዞሮ ጠላት ጠንካራ ኃይል እንዳለን አድርጎ እንዲገነዘብ ማድረግ ስንችል እንጂ በባዶ ቃላት ስላስፈራራነዉ አይደለም፡፡ ይህ ሲባልም ጠላትን ዲተር ማድረግ የሚቻለዉ በወታደራዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ወታደራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ በሆኑ የተቀናጁና የተቀነባባሩ እርምጃዎች ነዉ፡፡

* ወደኛ ሁኔታ ስንመጣ ኤርትራን ዲተር በማድረግ ወረራዉን ማስቀረት አለመቻላችን ከሁለት ድክመቶቻችን ቢያንስ ባንዱ ምክንያት የመነጨ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ የዲተረንስ ፖሊሲ የሚባል ነገር ጭራሽ ያልነበረን ስለሆነ  (failure to conduct a policy of deterrence) ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛዉ ምክንያት ደግሞ የዲተረንስ ፖሊሲ እያለንም ፖሊሲዉን ተጠቅመን በአግባቡ ዲተር ማድረግ አለመቻላን (deterrence failure) ሊሆን ይችላል፡፡

* መንግስታችን ኤርትራን በሚመለከት ሊወስድ እየተዘጋጀ ስላለዉ አዲስ ፖሊሲ የተለየ የዲተረንስ ፖሊሲ ነዉ ወይንስ የጦርነት አማራጭ ነዉ በሚለዉ ላይ በትክክል መናገር አልችልም፡፡ አስካሁን ስንከተል የነበረዉ ፖሊሲም ይሁን አቅጣጫ ዉጤታማ አልነበረም የተባለበት አግባብ ራሱ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

* ኢሳይያስን ወይም የሻእቢያን አገዛዝ ነጥለን በመምታት ኤርትራን እንደ አገርና የኤርትራን ህዝብ እንደ ወዳጅ ህዝብ ማዳን ሲገባን በተቃራኒዉ ኢሳይያስና ሻእቢያ ሳይነኩ ኤርትራን እንደ አገር ጎድተናታል፡፡ ይህ ሲባል ኢሳይያስን የምናስወግድበት መንገድ እያለ አልተጠቀምንበትም እያልኩ አይደለም፡፡ በእኛ አቅም ኢሳይያስን ከስልጣን የምናወርድበት ቀላል መንገድ ስለ መኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከዚህ በኋላ ለመዉሰድ የታሰበዉ አዲስ ፖሊሲ ይሄን በኢሳይስና በኤርትራ ህዝብ መካካል ያለዉን ልዩነት በሚገባ ታሳቢ የሚያደርግ የመፍትሄ መንገድ ይዞ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

* ትላንት በነበረብን የአቅም ዉስንነትና የተቀባይነት ችግር ምክንያት “ለግመል መፈንጫ” ብለን እንደዋዛ  ያጣጣልነዉን አሰብን ሳይቀር ለማስመለስ ሰፊ እድል አለን፡፡ የሚያስፈልገን አንድነገር ብቻ ነዉ፡፡ የመሪዎቻችን ራዕይና ራዕዩን እዉን ለማድረግ የሚያስችል ቁርጠኝነት!

* ስለጦርነቱ በተነሳ ቁጥር በድንገት  ወረራ የተፈጸመብን  የሻእቢያ ደደብነትና የኢሳይስ ጅልነት በፈጠረዉ የግምገማ ችግር ነዉ እያልን ነጋ ጠባ እነሱን ከመራገም ይልቅ እኛ ለምን ለጥቃት ተመቻችተን ተገኝንላቸዉ? ለምንስ ተገቢዉን ጥንቃቄ አላደረግንም? ብለን ራሳችንን ጠይቀንና እርስበርስም ተወቃቅሰን አናዉቅም፡፡ ለኛ ስንፈትና ድክመት መሸፋፈኛ  እንዲሆነን የሻእቢያን የግምገማ ችግር ደጋግሞ ደጋግሞ መናገሩን የመረጥን አስመስሎብናል፡፡ ዛሬም ነገም ስለ ኢሳይያስ ክፋት ነዉ የምናወራዉ፡፡

* ማናችንም ለሀገራችን የምንቆረቆር ዜጎች እንምንረዳዉ ከምንግዜም በላይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ዉስጣዊ አንድነታችን አደጋ ላይ መዉደቁን ነዉ፡፡ ከተጠቀሰዉ ግዜ ወዲህ አርስበርሳችን መደማመጥን አቁመናል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገራችን የሚታየዉ ዓይነት በዘርና በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥላቻ በታሪካችን በዚህ መጠን ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ ፌዴራላዊ ስርአቱ ችግር ስላለበት እንዳልሆነ አስካሁን ለሁለት አስርተ ዓመታት በሰላም መኖራችን ራሱ ምስክር ነዉ፡፡

—-

1/ ለኤርትራም ሆነ ለሌላ አገር በሚመለከት አንዳችምየዲተረንስ ፖሊሲየሚባል ነገር አልነበረንም!

ማንኛችንም እንደምናዉቀዉ ከጦርነቱ በፊት እንኳን ወዳጅ ከነበረችዉ ከኤርትራ ጋር ቀርቶ ከሌሎች አገሮች ጋርም ቢሆን በሆነ ጉዳይ ሊተናኮሉን ይችሉ ይሆናል ተብሎ የሚተገበር አንዳችም የዲተረንስ ፖሊሲ አልነበረንም፡፡ ከጦርነቱ በፊት ስለዲተረንስ ተነስቶ የተወያየንበትም አጋጣሚ አላስታዉስም፡፡

እንደ ደንቡ ከሆነ ለኤርትራ ተብሎም ባይሆን የዲተረነስ ፖሊሲ መከተል ነበረብን፡፡ የዲተሬንስ ፖሊሲ እንዲኖረን የሚጠረጠር ምናልባታዊ ጠላት ወይም በግልጽ የሚታወቅ ጠላት መኖርም የግድ አልነበረም፡፡ ኤርትራን ሆነ ሱዳንን ወዘተ  እንደ ጠላት መፈረጅ ወይም አስቀድሞ የሚታወቅ ጠላት መኖሩ የዲተረነስ እርምጃዎን ይበልጥ ዉጤታማ ሊያደርግ እንደሚችል ቢታወቅም በጠላትነት የፈረጅነዉ አገር አለመኖሩና ከሁሉም ጋር ወዳጅ መሆናችን ራሳችንን አዝረክርከን እንድንቀመጥ አያደርገንም፡፡

የዘወትር ዝግጁነትን ጠብቆ ለመቆየት የዉጭ ስጋት መኖር የግድ አይደለም፡፡ ከጠላት የበለጠ ኃይል መኖርም የግድ አይደለም፡፡ ዋናዉ ቁምነገር ባላጋራዉ መተናኮል አያዋጣኝም የሚል አስተሳሰብ በአይምሮዉ እንዲቀረጽበት በማድረግ ወደ ትንኮሳ ለመግባት ከመወሰኑ በፊት ደጋግሞ ደጋግሞ እንዲያስብበት ማድረጉ ነዉ፡፡

(“Deterrence does not imply overpowering the adversary but rather it is intended to impress a vision of defeat on his mind”) ይላል የዲቴሬንስ ነድሃሳብ ለመጀመሪያ ግዜ በ1940 ዓ/ም ላይ ያስተዋወቀዉ አሜሪካዊዉ ዲፕሎማት ጆርጅ ኬናን (George kennan)፡፡

የጆርጅ ኬናን ንድፈ ሃሳብ ትክለኛነት የሩሲያ ወታደራዊና የፖለቲካ ጠበብቶችም ተቀብለዉት በተግባር እየተጠቀሙበት ነዉ፡፡ በኬናን እምነት መሰረት የዲተረነስ ዋናዉ ፋይዳ ጠላት በእኛ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ እንደማያዋጣዉ እንዲገነዘብ  ወይም ፍርሃት እንዲነግስበት በማድረግ የጥቃት ሃሳቡን እንዲቀይር ማድረግ መቻል ነዉ፡፡ (Deterrence is the art of producing in the mind of the enemy… the FEAR to attack.”)

ዲተረንስ ጠላት ድጋሚ እንዳይለምደዉ ደህና አድርጎ በመቅጣት (deterrence by punishment) ወይም ደግሞ አስከነአካቴዉ ጥቃት እንዳይሰነዝር እድል በመንፈግ (deterrence by denial) ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛዉንም መንገድ ብንከተል ዲተር ማድረግ የምንችለዉ ዞሮ ዞሮ ጠላት ጠንካራ ኃይል እንዳለን አድርጎ እንዲገነዘብ ማድረግ ስንችል እንጂ በባዶ ቃላት ስላስፈራራነዉ አይደለም፡፡ ይህ ሲባልም ጠላትን ዲተር ማድረግ የሚቻለዉ በወታደራዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ወታደራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ በሆኑ የተቀናጁና የተቀነባባሩ እርምጃዎች ነዉ፡፡ .

ስለ ዲተረንስ ሲነሳ አንዳንዴ ጠላት ደካማ መሆኑንና ወደ ጦርነት ቢገባ በቀላሉ እንደሚሸነፍ እያወቀም ቢሆን ሆነ ብሎ ጥቃት ሊሰነዝርብን ይችላል፡፡ ደካማ የተባለዉ ጠላት ድንገተኛነትን ተጠቅሞ በኃይለኛ ባላጋራ ላይ ጥቃት በመሰንዘር  የተወሰነ ፖለቲካዊ ዓላማ ለማሳካት ሊሞክር እንደሚችል የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ያሳያል፡፡

ለምሳሌ በ2ኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓን ተሸቀዳድማ በአሜሪካ ፕርል ሃርበር የባህር ኃይል መደብ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰችዉ አሜሪካን በጦርነት መቋቋም እንደማትችል ሳታዉቅ ቀርታ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ሶሪያና ግብጽ በ1973 ዓ/ም በእስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘሩት እስራኤልን እናሸንፋታለን በሚል እምነት አልነበረም፡፡ በወቅቱ እስራኤልን መቋቋም እንደማይችሉ በደንብ አርገዉ ያዉቁ ነበር፡፡ እንዲያዉም በዚያ ጦርነት የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ድል ማግኘት ቢችሉ ባይጠሉም ነገር ግን እንደሚሸነፉ በጣም እርግጠኛ ነበሩ፡፡

ጦርነቱን የፈለጉት የ1967 ዓም የስደስቱ ቀን ጦርነት በሚባለዉ ጦርነት የደረሰባቸዉን አሳፋሪ ሽንፈት ምክንያት በመላ አረብ አገሮች ተፈጥሮ የነበረዉን ሃፍረትና ቁጭት ለማካካስ የሚያበቃቸዉን የተወሰነ ግርግር መፍጠር ነበር፡፡ እንዲያዉም በአጋጣሚ ካሰቡት በላይ በእስራኤል ላይ ብዙ ጉዳት ማድረስ ችለዉ ነበር፡፡ ከስድስት ቀኑ ጦርነት በኋላ አረቦች የትም  አይደርሱም በሚል ንቀት እስራኤል ተዘናግታ ስለነበረች ባልጠበቀችዉ ሁኔታ የተሰነዘረባትን ጥቃት ለመቋቋምና በኋላም ለማሸነፍ ብዙ ኪሳራ አስከፍሏታል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በ1982ዓ/ም በፎክላንድ ደሴት ምክንያት በኢንግሊዝና በአርጀንትና መካከል የተነሳዉ ጦርነትም በአስተማሪነቱ መጠቀስ የሚችል ነዉ፡፡ ጦርነቱ የተጀመረዉ ከእንግሊዝ ያነሰ አቅም በነበራት አርጀንቲና ቆስቋሽነት ሲሆን በወቅቱ እንግሊዝ ለዓመታት ስትጠቀምበት የነበረዉን የዲተረንስ ፖሊሲዋን ችላ በማለት አርጀንትናን በመናቅ ጨርሶ አትዳፈረኝም በሚል ስሜት ተዘናግታ በነበረችበት ወቅት ነበር አርጀንቲና የእንግሊዝ ግዛት የሆነዉን ፎክላንድ ለመዉረር የበቃችዉ፡፡

አርጀንቲና እንግሊዝን ለመቋቋም የሚያስችላት ጥንካሬ አንደለላት እያወቀች መዳፈሯ የእንግሊዝ መዘናጋት በፈጠረዉ አመቺ ሁኔታ ተበረታታ እንጂ አሸንፋለሁ በሚል ምኞት አልነበረም፡፡ አርጀንቲና ወደዚህ ጦርነት የገባችበት ዋነዉ መነሾ በቦነስ አይረስ ስልጣን ላይ የነበረዉ ወታደራዊ ጁንታ መሪ ጄነራል ጋልትየሪ የህዝቡን አድናቆትና ድጋፍ ለማግኘት ስለፈለገ ብቻ መቋቋም ከማይችለዉ ባላጋራ ከእንግሊዝ ጋር ጦርነት ገጠመ እንጂ እንግሊዝን በተአምር እንደማያሸንፍ ጠፍቶት አልነበረም፡፡ በኋላ ግን እንግሊዝ ብዙ ኪሳራ አስከፍሏትም ቢሆን  ደሴትቱን መልሳ ልትቆጣጠር ችላለች፡፡

ወደኛ ሁኔታ ስንመጣ ኤርትራን ዲተር በማድረግ ወረራዉን ማስቀረት አለመቻላችን ከሁለት ድክመቶቻችን ቢያንስ ባንዱ ምክንያት የመነጨ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ የዲተረንስ ፖሊሲ የሚባል ነገር ጭራሽ ያልነበረን ስለሆነ  (failure to conduct a policy of deterrence) ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛዉ ምክንያት ደግሞ የዲተረንስ ፖሊሲ እያለንም ፖሊሲዉን ተጠቅመን በአግባቡ ዲተር ማድረግ አለመቻላን (deterrence failure) ሊሆን ይችላል፡፡

የመጀመሪያዉ የሚጠቁመን በወቅቱ የሀገራችን ፖሊሲ አዉጭዎች ዲተረንስን እንደ አንድ የፖሊሲ መሳሪያ እንደማይጠቀሙና እንዲያም የዲተረንስ ፖሊሲ የሚባል ነገር ያልነበራቸዉ መሆኑን ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ የዲተረንስ ፖሊሲ እያለም ነገር ግን በሚገባ መጠቀም ባለመቻላችን ጠላትን ከድርጊቱ እንዲቆጠብ በተግባር ማድረግ ተስኖናል ማለት ነዉ፡፡

እዚህ ላይ ለአብነት እንዲሆነን አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ አሜሪካ ወዳጇ የነበረችዉንና እንደራሷ የምትቆጥራትን ኩዌትን ከኢራቅ ወረራ ለመታደግ ያልቻለችዉ ለምንድነዉ?ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካ የኢራቅን የኩዌት ወረራ ማስቆም ያልቻለችዉ  አስቀድሜ በጠቀስኩት  የመጀመሪያዉ ችግር ምክንያት ነበር ፡፡

አንድ ሀገር የዲተረንስ ፖሊሲ እንዳትጠቀም የሚያደርጋት ተጠርጣሪዉ ወይም ምናልባታዊዉ ጠላት ለጦርነት የሚያደርገዉን ዝግጅት እጅግ በከፍተኛ ምስጢር በማድረግ መረጃ መደበቅ በመቻሉ ወይም ድግሞ ትክክለኛ ባህሪዉን ፍላጎቱንና ስትራቴጂዉን ወታደራዊ አቅሙን ለመደበቅ በመቻሉ የሚፈጠር ችግር ነዉ፡፡ በሌላ አባባል ስለ ጠላት በቂና አስተማማኝ  መረጃ ካለመኖር  የተነሳ የሚፈጠር ችግር ነዉ ማለት ነዉ፡፡

እንዳንዴ ደግሞ ስለ ጠላት ፍላጎትና ዝግጅት የሚገልጽ መረጃ ከሞላ ጎደል አያለም በግምገማ ድክመት ምክንያት  ስለ ጠላት ትክክለኛዉን ስዕል ለመያዝ ባለመቻል ተገቢዉ እርምጃ ሳይወሰድ መዘናጋት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ሳዳም ሁሴን ኩዌት ላይ ኢሳይያስ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ያደረጉትን ጥቃት እንዳይደርስ ማድረግ ያልተቻለዉ መረጃ ሲላልነበረ ወይም ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ስላነበረ አይደለም፡፡

ሳዳምም ሆነ ኢሳይያስ ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆኑን ለመደበቅ ያደረጉት አንዳችም ሙከራ አልነበረም፡፡ ሳዳም ኩዌትን ሊወር እንደሚችል ከበቂ በላይ መረጃ ነበር፡፡ የአሜሪካም ሆነ የኩዌት ባለስልጣናት በሚገባ ያዉቁ ነበር፡፡ የሳዳምን የኩዌት ወረራ የኢሳይያስን የኢትዪጵያ ጥቃት ማስቀረት አለመቻሉ ተጠያቂዉ ሳዳም ወይም ኢሳይያስ አይደሉም፡፡ የአሜሪካ መረጃ ተቋማትም ቢሆኑ መረጃዉን ለአመራሩ በጊዜ ባለማድረሳቸዉ  አልነበረም፡፡

ጥፋቱ የነበረዉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የቅርብ አማካሪዎች አካባቢ ነዉ፡፡ የአሜሪካ የመረጃ ተቋማት ፕሬዝደንቱን ስለእራቅ ወረራ አይቀረነት ቢያስጠነቅቁም የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አማካሪዎቹ ግን ፈጽሞ የማይደረግና የማይታሰብ ነዉ በሚል መረጃዉን አጣጣሉት፡፡ የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች ወደዚህ ድምዳሜ ሊደርሱ የቻሉት እራቅ ከዚያ በፊት ከኢራን ጋር በጦርነት ቆይታ ከጉዳት ገና ያላገገመች በመሆኑ ወደ ሌላ ጦርነት አትገባም በሚል የተሳሳተ ግምገማ ነዉ፡፡ ፕሬዝዳንቱም በበኩላቸዉ የቬትናም ጦርነት መጥፎ ትዉስታ ገና ከአይምሮአቸዉ ያልተፋቀ ስለነበር ለመዘናጋታቸዉ ተጨማሪ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በእኛ በኩልም ስለኤርትራ የጦርነት መዘጋጀት ከሞላ ጎደል መረጃዉ እያለን ተገቢዉን ጥንቃቄ አለማድረጋችን ኢሳይያስን አጉል በማመናችንና ኤርትራ በፍጹም ለጦርነት አታስበንም በሚል ራሳችንን በማታለላችን ነዉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ለማሳሳት ጥቂት የተዛቡ መረጃዎች ማድረስ በቂ ነበር፡፡

በዚህ ላይ በጦርነት የመሰላቸትና ለልማት ላይ ማተኮራችን መረጃዎችን በሚገባ ለማጣጣም እድል አልሰጠን ሊሆን ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ጉዳይ ሲሳሳቱም በድፍረት ዉሳኔያቸዉን ለማስቀየር ራስ ወዳድነታችን አልፈቀደልንም፡፡ መለስን አስቀድሞ በግልጽ ታግሎ ለማረም ከመሞከር አስከሚሳሳቱ ጠብቆ ሃሜትና ዉንጀላን ነዉ የመረጥነዉ፡፡

2/ ኤርትራን በሚመለከት የጠ/ ኃይለማርያም ቀጣዩ ፖሊሲ

መንግስታችን ኤርትራን በሚመለከት ሊወስድ እየተዘጋጀ ስላለዉ አዲስ ፖሊሲ የተለየ የዲተረንስ ፖሊሲ ነዉ ወይንስ የጦርነት አማራጭ ነዉ በሚለዉ ላይ በትክክል መናገር አልችልም፡፡ አስካሁን ስንከተል የነበረዉ ፖሊሲም ይሁን አቅጣጫ ዉጤታማ አልነበረም የተባለበት አግባብ ራሱ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

ኤርትራ ከትንኮሳዋ አልታቀበችም በሚል መንፈስ ከሆነ የዚህ ዓይነቱ ትንኮሳ መቼም ቢሆን ሊቀር የሚችል አይመስለኝም፡፡  በሌላ በኩል በደህንነታችን ላይ የከፋ ጉዳት እስካላመጣ ድረስ የዚህ ዓይነቱ መተናኮል ዝንጉ ለሆነ እንደኛ ላለ መንግስት  ነቃና ጠንቀቅ እንዲል ስለሚያደርገዉ ብዙም የሚጠላ አይደለም፡፡ በተጨማሪ ኤርትራን ለዘለቄታዉ ለማዳከም መነሻ ይሆነናልና፡፡

በርግጥ የኤርትራ ትንኮሳ እጅግ እንዳስመረረን ግልጽ ነዉ፡፡ በተለይ በኤርትረ አዋሳኝ የሚገኘዉ ህዝባችን ሁልግዜም በስጋት ዉስጥ መኖሩና ሰላሙን ማጣቱ በዚህም በመንግስት ላይ ቅሬታ ሊይዝ እንደሚችል ግልጽ ነዉ፡፡ በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ ድንበር ላይ ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት በምሽግ ዉስጥ ሆኖ ነቅቶ ሲጠብቅ ለኖረዉ መከላከያ ሰራዊታችንም ቢሆን የምሽግ ህይወት አሰልቺ በመሆኑ አንደኛዉኑ የለየለትን ጦርነት ሊመርጥ መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡

ነገር ግን ኤርትራ በእኛ አሳሳቢነት በተጣለባት ማእቀብና ከአለም ህብረተሰብ መገለል  እየደረሰባት ያለዉን ጉዳት ቀለል አድርገን መቁጠር አይኖርብንም፡፡ ኤርትራ እኛን በመተነኳኮል በኛ ላይ ካደረሰችዉ ጉዳት ይልቅ ራሷን በእጅጉ እየጎዳች መሆኗ ግልጽ ነዉ፡፡ በአስመራ ያለዉ መንግስት ለዜጎቹ አንዳችም ሃላፊነት የማይሰማዉ በመሆኑ እንጂ ጤነኛና ለህዝብ የሚጨነቅ መንግስት ቢሆን ኖሮ ህዝቡ ላይ በራሱ ጥፋት ለደረሰዉ መጎሳቆል ሃላፊነት ተሰምቶት ስልጣኑን አስከመልቀቅ በደረሰ ነበር፡፡ ቢያንስ ባህሪይዉን አስተካክሎ ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ በሆነ ነበር፡፡

ስለዚህ ኢሳይያስና የሻእቢያ መንግስት በድርጊታቸዉ መቀጠላቸዉ አስካሁን በተጣለባቸዉ ማእቀብ አለመጎዳታቸዉን ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ አዉጥተዉ ባይናገሩትም እጅግ እየተጎዱ መሆኑን ሀገር ለቆ የሚሰደደዉን የስደተኛ ብዛትና ሁኔታ በማዬት ማረጋጋጥ ይቻላል፡፡

2.1/ መንግስት በኤርትራ ላይ የፖሊሲ ለዉጥ ማድረግ ለምን አስፈለገዉ?

መንግስት አስካሁን ያለዉ አካሄድ እንደታሰበዉ ዉጤታማ አለመሆኑን በመጠቆም አዲስ ፖሊሲ በመቅረጽ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲነግሩን መንግስት ዉጤታማ አይደለም ማለቱ ምን እንዲሆን ወይም እንዲፈጠር ጠብቆ ሳይሆን ቀርቶ ነዉ ዉጤታማ አይደለም ለማለት ያበቃዉ የሚል ጥያቄ ማንሳታችን የግድ ነዉ፡፡

አስካሁን ከሄድንበት የዲተረንስ  መንገድ ወጣ ባለ ሁኔታ ምናልባት በሰላማዊ መንገድ ኤርትራን ወደ ድርድር ለማምጣት የሚገፋፋትን ለኤርትራ አጓጊና በጭራሽ እንዳያመልጣት የማትፈልገዉን መልካም እድል ይዘን ልንቀርብ ተዘጋጅተን ከሆነ ምናልናት አዲሱ ፖሊሲ የተሻለ ዉጤት ሊያመጣ ይችላል ብለን ለመገመት እንችላለን፡፡ ኤርትራ በፍርድ ተወሰኖልኛል የምትለዉን አንድም ሳናስቀር ካላስረከብናት በስተቀር ከዚያ በመለስ አንዳችም ድርድር ወይም ማባበያ ወይም ሌላ ማካካሻ አልፈልግም የሚል የቆየ ግትር አቋሟን ካልቀየረች በስተቀር በኛ በኩል የሚታሰብ ሌላ የድርድር መንገድ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

ጉዳዩን የበለጠ ግለጽ ለማድረግ አንደንድ ሰዎች “ኤርትራ በፍርድ ተወስኖልኛል የምትለዉን ባድመና ሌሎች አካባቢዎችን በስጦታም ይሆን በፈቃደኝነት ለቀንላቸዉ በምትኩ የባህር በር የምናገኝበት ሁኔታ ከተመቻቸልን ለኛ ከበቂ በላይ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል የባህር በር ማግኘት ከቻልንና በሌላ በኩል  ከኤርትራ ጋር የነበረን የጠላትነት ፍጥጫ ቀርቶ በምትኩ ወደ ሰላማዊ ጉርብትና ከተቀየረ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ አያስፈልጋትም” የሚሉ አሉ፡፡

በተለይ አንዳንዶቹ ደግሞ ኤርትራዉያን ከማንም ሌላ አገር ህዝብ በላይ የምንቀርባቸዉ ወንድሞቻችን ስለሆኑ ወደ ቀደመዉ ወዳጅነታችን መመለሱ ከሁሉም የበለጠ ተፈላጊ ስለሆነ ያለምንም ቅድሜ ሀኔታ የሚጠይቁትን ሁሉ እንስጣቸዉ የሚሉም አሉ፡፡

እንግዲህ የግለሰቦችን ስሜታዊነት የፈጠረዉ አስተያየትን ወደ ጎን አድርገን ሃላፊነት ያለበት መንግስታችን በምን መንገድ ወደ መግባባት ሊመጣ እንዳሰበ ለማወቅ መጓጋታችን አልቀረም፡፡ ምናልባት አዲሱ የመንግስት ፖሊሲ ኤርትራን በማሳመን በፈቃደኝነት ወደ ዉይይት ጠረጰዛ ሊያመጣ የሚችል አዲስና ያልተሞከረ መፍትሄ ይዞ የሚቀርብ ካልሆነ በስተቀር ኤርትራን በማስገደድና በማስፈራረት ለኛ ፍላጎት ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ የታሰበ የመፍትሄ አማራጭ ከሆነ ዉጤታማ እንደማይሆን ከአሁኑ ለመገመት አያዳግተንም፡፡

የአንድ ወገንን ጥቅም ብቻ ታሳቢ ያደረገ የመፍትሄ  ሀሳብ ይዞ የሚመጣ ፖሊሲም በፍጹም ዉጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ የዚህ አይነቱ አስገዳጅ የሆነ የድርድር መንገድ ኤርትራን የበለጠ ተስፋ በማስቆረጥ ወደ አዲስና አጠቃላይ ጦርነት ድጋሚ ለመግባት ለሰበብ የሚረዳን ካልሆነ በስተቀር ፋይዳዉ ብዙም አይታየኝም፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ በብዙ ረገድ ከኤርትራ የተሻለች በመሆኗ የተሻለ አጓጊ የሆነ መፍትሄ ነዉ ይዛ መቅረብ ያለባት፡፡ ሰጥቶ መቀበል የተባለዉ የቀድሞዉ ፖሊሲም ሙሉ በሙሉ ዉድቅ የሚደረግ ስላልሆነ የኤርትራን ፍላጎት በሚገባ ለይቶ አንዳንድ ማስተካከያዎችም በማድረግ ለመተግበር ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

በቅድሚያ ኤርትራዉያን ሰላማዊ ከሆነ ድርድር ተጠቃሚ እንሆናለን ብለዉ እንዲያስቡ ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ የራሳችን ፍላጎት ብቻ እነሱ ላይ በመጫን ወደ ድርድር እንዲመጡ ማድረግ አንችልም፡፡ ድርድሩን ወይም ሰላማዊ መንገዱን ከሩቁ እንዲሸሹ ማድረግ ሳይሆን ከዚያ ይልቅ ተበረታትተዉ በተስፋ እንዲመጡ ማድረጉ ነዉ ለሁለታችንም የሚበጀዉ፡፡

2.2/ ቀጣዩ የመንግስታችን ፖሊሲ ጦርነትን አማራጭ ማድረግ አይገባዉም

እስካሁን ያለዉ ፖሊሲ ኤርትራን በእጅጉ መጉዳቱ ላይ የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ኤርትራ ምናልበት በጦርነቱ ከደረሰባት ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ በበለጠ ከጦርነቱ በኋላ በተጣለባት ማእቀብና በደረሰባት መገለል የተጎዳችዉ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ በእስካሁኑ አካሄዳችን የኤርትራን አገዛዝ ከስልጣን የማዉረድ እቅድ የነበረን አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪ ኢሳይያስን በግድ ለኛ ፍላጎት እንዲገዛ የማድረግ አላማም አልነበረንም፡፡

በእርግጥ ኤርትራ በተለያዩ መንገዶች በሶስተኛ ወገን ስታደርግ የቆይችዉን ትንኮሳና ሰላማችንን መበጥበጥ ለአፍታም እንዳላቆመች ቢታወቅም አስካሁን የሄድንበት መንገድ የተሳሳተ ስለነበረ አይመስለኝም፡፡ የአስካሁኑ አካሄዳችን ድክመት አለዉ ከተባለ ኢሳይያስንና የኤርትራን ህዝብ፤ ኤርትራንና የኢሳይስን አገዛዝ ሳይነጥል በጅምላ ዒላማ ያደረገ በመሆኑ ከሻእቢያ ይልቅ የሀገሪቱንና ህዝቡን ይበልጥ ለጉዳት መዳረጉ ነዉ፡፡ ዋነኛዉ ጠባችን ከኢሳይያስ ጋር ሆኖ እያለ ኢሳይያስ ስልጣን ላይ ቁጭ ቢሎ ህዝቡን ለችጋር ዳርገነዋል፡፡

ኢሳይያስን ወይም የሻእቢያን አገዛዝ ነጥለን በመምታት ኤርትራን እንደ አገርና የኤርትራን ህዝብ እንደወዳጅ ህዝብ ማዳን ሲገባን በተቃራኒዉ ኢሳይያስና ሻእቢያ ሳይነኩ ኤርትራን እንደ አገር ጎድተናታል፡፡ ይህ ሲባል ኢሳይያስን የምናስወግድበት መንገድ እያለ አልተጠቀምንበትም እያልኩ አይደለም፡፡ በእኛ አቅም ኢሳይያስን ከስልጣን የምናወርድበት ቀላል መንገድ ስለ መኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከዚህ በኋላ ለመዉሰድ የታሰበዉ አዲስ ፖሊሲ ይሄን በኢሳይስና በኤርትራ ህዝብ መካካል ያለዉን ልዩነት በሚገባ ታሳቢ የሚያደርግ የመፍትሄ መንገድ ይዞ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

የዲተረንስ ፖሊሲያችንም በተጠና ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ አዲሱ ፖሊሲ ሰላማዊ መፍትሄ ገሸሸ ያደረገ ሊሆን አይገባዉም፡፡ ሰላማዊ መፍትሄ ምንግዜም መቼም ቢሆን በሌላ መተካት ያለበት አይደለም፡፡ ወታደራዊ ጡንቻን እያሳዩና ወታደራዊ ማስፈራሪያ እያደረጉ ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት መሞከር ብዙ የሚያዋጣ አይደለም፡፡

ኢሳይያስ ጦርነትን የሚፈራ አድርገን አስበን ከሆነ ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡ ኢሳይያስ በስልጣን ላይ አስካለ ድረስ ማንኛዉም የጦርነት መንገድ የመጀመሪያ ምርጫዉ ነዉ፡፡ ጦርነቱ በተለይም በኛ ቀደምትነት የሚጀመር ጦርነት ኢሳይያስ እጅግ በደስታ የሚጠብቀዉ ነዉ፡፡ ህዝቡን ከሞላ ጎደል ከጎኑ ለማቆም ያስችለዋልና፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ የኃይል እርምጃን እንደማስፈራሪያ ይዘን ሰላምን ማምጣት አንችልም፡፡

መንግስታችን በወታደራዊ ኃይል በጦርነት መፍትሄ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት ካለዉ ይሄን አቋሙን እንደገና ሊያጤነዉ ይገባል፡፡ የጦርነት መንገድ ከመንግስታችን ቋሚ መሪህ ጋር የሚሄድም አይደለም፡፡ ለዚያ የሚያበቃን ወታደራዊ ኃይል ዝግጅት መኖሩን በቅድሚያ ማረጋገጥም ተገቢ ነዉ፡፡ አለም አቀፍ ድጋፍም ሊኖር የግድ ነዉ፡፡ ምድረ ሽብርተኛ ሁሉ ኢሳይያስን ለማዳን በሚል ሰበብ ሊያጥለቀልቀን እንደሚችልም መዘንጋት የለብንም፡፡

ጦርነትን የምንመርጠዉ በኢሳይያስ ድርጊት እልህ ተጋብተን መሆንም አይገባዉም፡፡ በኛ ቆስቋሽነት የሚጀመር ጦርነትን ኢሳይያስ እንደሚፈልገዉ መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ በእኔ እምነት አስካሁን የሄድንበት አካሄድ ኢሳይያስን ከመተናኮል እንዲቆጠብ ማድረግ ባይችልም ነገር ግን ለዚህ ብቻ ብለን ወደ ጦርነት እንድንገባ የሚያደርገን አይይለም፡፡ ከአስካሁኑ አካሄዳችን ይልቅ ጦርነት የሚሻልበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም፡፡

2.3/ ኢሳይያስን ከስልጣን አለማዉረዳችን የኛ ድክመት ተደርጎ ሊቆጠር አይገባዉም

የኛ የአስካሁኑ ድክመት የሻእቢያን አገዛዝ ወይም ኢሳይስን በኃይል ከስልጣን ማዉረድ አለመቻላችን አይደለም፡፡ እኛ ብዙም ያልሄድንበትና እንደ ድክመት መቆጠር ያለበት ራሳቸዉን ኤርትራዉያን ተቃዋሚዎችን ለጸረ- ኢሳይያስ ትግል መጠቀም ወይም ማንቀሳቀስ አለመቻላችን ነዉ፡፡ ለዚያ ድክመታችን ዋነኛዉ ማሳያ የሚሆነዉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን ስደተኞች በእጃችን እያሉ በሚገባ አደራጅተን ማንቀሳቀስ አለመቻላችን ነዉ የኛ ድክመት፡፡

በኤርትራ የመሸጉ ጥቂት ኢትዮጵያዉያን ጸረ ሰላም ኃይሎችን እያሰማሩብን እንዴት ሰላማችን እየበጠበጡና ለደህንነታችን የስጋት ምንጭ እንደሆኑ እያየን ነዉ፡፡ ኢሳይያስ የኛን ያህል ምቹ ሁኔታ ቢኖረዉ ኖሮ የአንድ ወርም እድሜ አይሰጠንም ነበር፡፡

ኤርትራዉያኑን መንከባከባችን ላይ ጠብ የለኝም፡፡ የኢሳይያስ አፋኝ አገዛዝ ከሰፈነባት አገራቸዉ ኤርትራ ይልቅ እኛን መምረጣቸዉና በእርግጠኝነት ተማምነዉብን ወደኛ በመምጣታቸዉ ሁላችንም እጅግ ደስተኞች ነን፡፡ ቀድሞዉኑ እኛ አንፈልጋችሁም ሂዱልን አላለልናቸዉም፡፡ እነሱ ናቸዉ ጥለዉን የሄዱት፡፡ በዚህ ድርጊታቸዉ ቅሬታ ቢሰማንም ቂም አልያዝንባቸዉም፡፡ እነሆ መንግስታችን ማድረግ የሚችለዉን ሁሉ እንክብካቤ እያደረገላቸዉ ነዉ፡፡

እዚህ ላይ ግን መዘንጋት የለሌባቸዉ ነገር እዚያዉ ጥለዉት የመጡት ህዝባቸዉ በሻዕቢያ ጭቆና በየዕለቱ እየተሰቃየ መሆኑንና ከዚህ ጭቆና ለማላቀቅ የዜግነት ግዴታቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉ ልናስታዉሳቸዉ ይገባል፡፡ ለስደት የዳረጋቸዉን የኢሳይያስን አገዛዝ ከጠሉ ከሽሽቱ ባሻገር ለሽሽት የዳረጋቸዉን ጨቋኝ ስርአት ለማዉረድ መሳሪያ አንስተዉ መታገል አለባቸዉ፡፡

የእኛ ስራ ይሄን ሃላፊነታቸዉን በማስታወስ ላይ የተገደበ ነዉ፡፡ እናም መንግስታችን አንድ ያልሰራዉ ስራ አለ ብዬ የጠቀስኩት ሌላ ሳይሆን ይሄንኑ ነዉ፡፡ ህዝባችን  በኤርትራ አገዛዝ ምክንያት ምን ያህል አንደተሰቃየን ሊነገራቸዉ ይገባል፡፡ እኛ እያደረግን ላለነዉ ዉለታ እንዲከፍሉን አንጠይቅም፡፡ ወዳጅነታቸዉን ፈልገንና የድሮ ዝምድናችንን አስታዉሰን እንጂ እኛ የራሳችን የሆነ ብዙ ችግር ያለብን ነን፡፡ እናም ራሳቸዉን አዘጋጅተዉ ለመስዋእትነትም ቆርጠዉ ኢሳይያስን ለመፋለም መንቀሳቀስ መጀመር አለባቸዉ፡፡

ይሄን ሁሉ ሰደተኛ (የሱዳንን ሳይጨምር) ማስተናገድ ለደህንነታችን ምን ያህል አደጋ እንደሆነ ሊረዱት ይገባል፡፡ አንዳችም የገንዘብ ችግር የሌለባቸዉ የአዉሮፓ ሃገራት ስደተኞችን ለመቀበል ያንጋራገሩበት ዋነኛ ምክንያት በደህንነት ጉዳይ እንደሆነ ኤርትራዉን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ከዚህ በኋላም ለምን ያህል ግዜ ልንቸገርላቸዉ እንደምንችል ለመናገር እንደሚከብደን ሊያዉቁት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንጂ  ካናዳ ወይንም ጀርመን አይደለችም፡፡ ስለዚህ ህዝባቸዉን አገራቸዉን ከዚህ ጨቋኝ ስርአት ለመገላገል ከአሁኑ ቆርጠዉ መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስታችንም በግልጽ ሊነግራቸዉ ይገባል፡፡

2.4/ አስካሁን ኢሳይስ ጉዳቱ ያልተሰማዉ የመሰለን ለህዝቡና ለሀገሩ ባለማሰቡ እንጂ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰበትማ አያጠራጥርም

ኢሳይያስ አገሩና ህዝቡ ይጎዳብኛል ብሎ ካልሰጋና ለገዛ ሀዝቡ ካልተጨነቀ በስተቀር እሱን ማስፈራራታችንና ማእቀብ እንዲጣልና እንዲገለል ማድረጋችን ለሱ ብዙም የተሰማዉ አይመስልም፡፡ ኢሳይያስ ስለኛ ማስፈራራትም ሆነ ስለማእቀቡ ሊያሳስበዉ የሚችለዉ በህዝቡ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል ከሚል ሳይሆን  በራሱ ስልጣን ላይ አደጋ የሚፈጠር ከመሰለዉ ብቻ ነዉ፡፡ በእስካሁኑ አካሄዳችን እንደ እዉነቱ ከሆነ ሻዕቢያ እንኳን ተጎድቻለሁ ማለት ይቅርና ዲተር እያደረግነዉ መሆናቸንን እንከዋን ባልተረዳበት ሁኔታ በኛ ምክንያት ተጎድቶታል ሰግቷል ማለት አንችልም፡፡

ሻእቢያ የባህሪይ ለዉጥ ለማምጣቱና ከጠላትነት ደርጊቱ ለመታቀቡ አንዳችም ምልክት አላሳየንም፡፡ በኛ ዲተረንስ የተነሳ ጉዳቱ ተሰምቶት እንደሆን ያሳየዉ ምልክት የለም፡፡ ያ ማለት ግን በተጨባጭ አልተጎዳም ማለት አይደለም፡፡ አስቀድሜ እንደገለጽኩት እያመመዉም ቢሆን ህመሙን መቻል መርጧል፡፡ ስልጣኑን የሚያሳጣዉ አስካልሆነ ድረስ ተጎድቻለሁ ቢሎ ወደ ሰላማዊ መንገድ በጭራሽ አይመጣም፡፡

በኛ በኩል  የአስካሁን የሄድንበት አካሄድ ችግር አለበት ለማለት የሚበቃን ነገር የለም፡፡ ምናልባት የዲተረንስ አካሄዳችንን የበለጠ አጠናክረን መቀጠል የምገባን ይሆናል እንጂ እንዱን ጥለን ሌላዉን የሚናነሳበት ምከንያት አይታየኝም፡፡  በኛ በኩል የዲተረንስ አካሄዳችንን በሚመለከት ትንሽ መስተካካል ያለበት ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡

አስካሁን ለምናልባቱ ሻዕቢያ ድንገት ትንኮሳ ቢያካሂድ ተብሎ የተለመደዉን የዘወትር የድንበር አካባቢ የተጠናከረ ጥበቃ ከማድረግ ዉጭ ለዚያ ተብሎ የተዘጋጀ የዲቴሬንስ መዋቅር ወይም ቁመና (deterence posture) እንዲሁም በሚገባ የተቀመረ የዲተረንስ ፖሊሲም ያለን አይመስለኝም፡፡ በዚህ ረገድ በሚገባ የተጠና የዲተረንስ ፖሊሲና ተግባራዊ ማድረጊያ ሜካኒዝም ሊናዘጋጅ ይገባል፡፡

ስለ ሻእቢያ ትዉስ የሚለን የሆነ ሰርጎ ገብ አሾልኮ ባስገባ ቁጥር ብቻ በመሆን አይገባዉም፡፡ ዲተረንስ ራሱን የቻለና የዕለት ከእለት ክትትል የሚፈልግ ስራ እንጂ የሻእቢያን ድርጊትና የመንግስትን ይፋ መግለጫ እየተከተለ ብቻ የሚሰራ ስራ አይደለም፡፡ በወታደራዊ መንገድ ዲተር የማድረጉ ጉዳይ አስካሁን የሄድንበትና ዉጤታማ ነዉ ብዬ የማስበዉን በዲፕሎማሲ መንገድ ሻእቢያን የማዳከም አካሄዳችን ይበልጥ ተቀናጅቶና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነዉ፡፡

የዲተረንስ አካሄዳችን ከአንዳንድ ማስተካከያ ከሚፈልጉ ጉዳዮች ዉጭ የሚናቅ አይደለም ስል ዲተረነስ በባህሪይዉ ዉጤታማነቱን በእርግጠኝነት ለመናገር የማያስችልና ሁለግዜም አጠራጣሪ መሆኑን ሳልዘነጋ ነዉ፡፡ የዲተረነስን ስኬት በተጨባጭ የምንለካበት መንገድ የለንም፡፡ ከዚህ አኳያ ከላይ አስከ ታች ባሉ በመላዉ የሰራዊታችን አባላት ዘንድ ሻዕቢያን በሚገባ ዲተር እያዳረግን መሆናችንን በርግጠኝነት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነዉ፡፡

ነገር ግን ሻዕቢያ በርግጥ ዲተር ስለ መደረጉ ማንኛችንም በርግጠኝነት መናገርና መስረጃ ማቅረብ አንችልም፡፡ ሻዕቢያ ለምን ዳግመኛ ጦርነት እንዳላወጀብን ምክንያቱ በኛ የዲቴሬንስ ዉጤታማነት አንደሆነ አድርገን ልናስብ እንችላለን፡፡ ሻዕቢያ በየግዜዉ ከሚያደርገዉ ትናንንሽ ትንኮሳዎች ዉጭ ወደ አጠቃላይ ጦርነት አስካለሁን አለመግባቱም ሆነ ወደፊት ይገባል ተብሎ የማይታሰብ መሆኑ እርግጥ ነዉ፡፡ ይህ ግን በቀጥታ የኛን ዲቴረንስ ዉጤታማነት የሚያመላክትና የሚመሰክር ሊሆን አይችልም፡፡

ሻዕቢያ ወደ አዲስ ጦርነት ያልገባዉ እኛ ዲተር ሲላደረግነዉ እንደሆን ራሱ ካልነገረን በስተቀር እንዲሁ በግምት ብቻ ማወቅ አንችልም፡፡ ምናልባት ራሱ እንደማያዋጣዉ ተረድቶና ተስፋ ቆርጦ ድጋሚ ወደ ትልቅ ጦርነት ከመግባት ይልቅ እንደዚህ መተነኳኮሉ የበለጠ ይሻለኛል ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ዲተረንስ በባህሪይዉ ዉጤቱን መናገር ስለማይቻል የተሻለ የሚሆነዉ ሁልግዜም በተጠናከረ ሁኔታ አዳዲስ ዜዴዎችን እየቀየሱ አጠናክሮ መቀጠሉ ነዉ፡፡

በሌላ በኩል ሻእቢያን ዲተር ማድረጋችን ካልቀረ ለወደፊቱም ቢሆን መዘዙ የከፋ መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ አለብን፡፡ መልእክቱ ሻዕቢያ መድረሱንም ማረጋገጥ ይገባናል፡፡ ሻእቢያ አርፎ ካልተቀመጠ በስተቀር ይሄ መተነኳኮሱ ለወደፊቱ መዘዙ የከፋ (consequence) እንደሚኖረው እንዲገነዘብ ለማድረግ ደግሞ በባዶ ቃላት ብቻ ሳይሆን ሊያስፈራረዉ የሚችል ጠንካራ ኃይል እንዳለን እንዲረዳ ማድረግ ስንችል ነዉ፡፡ ስለዚህ ዲተረንስ አካሄዳችን ጠንካራ መከላከያና ከጠንካራ ዲፕሎማሲ ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡

ሌላዉ በተለይ ስለኢሳይስ ሲነሳ መዘንጋት የለለብን ነገር ኢሳይያስን በግል ዲተር በማድረግ ለኛ ፍላጎት ተገዢ ማድረግ የማይቻል መሆኑን ነዉ፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ ነገር ኢሳይያስ ዲተር ሊሆን የሚችል አይደለምና፡፡ (undeterable ) ነዉና፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነዉ፡፡ ኢሳይያስ የኤርትራ ህዝብ ቢጎዳ ሕይወቱ ቢመሰቃቀል ሀገሪቱ ብትፈረካከስ ደንታ ስለሌለዉ ነዉ፡፡

ስለዚህ በኤርትራ ህዝብና በአገሪቱ ላይ የሚደረግ ዲተረንስ ኢሳይያስን ስለማያሳሳበዉና ስለለማይስፈራዉ ትርጉም አይኖረዉም ወይም ግቡን አይመታም፡፡ ኢሳይያስን ሊያስደነግጥና ሊያስፈራ ይችል የነበረዉ በግል በኢሳይያስና በስልጣኑ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ከተወሰደ ብቻ ነዉ፡፡ ያን ሊሰጋ ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻል ይሆናል፡፡

ኢሳይያስን ለማስፈራራት በቅድሚያ እሱ አጅግ የሚሳሳለት፤ በጭራሽ ማጣት የማይፈልገዉና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠዉ ነገር ምን እንደሆነ ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ያን ካደረግን በኋላ ኢሳይያስ በሚሳሳለት ጉዳይ ላይ ዒላማ ያደረገ ዲተረንስ ካደረግን በርግጥ ለኢሳይያስ እጅግ አሳሳቢ ሊሆን ይችላል፡፡

አስካሁን ባለን ግምት በዚህ ረገድ ኢሳይያስ እጅግ የሚሳሳለት ጉዳይ ቢኖር “ስልጣኑ” እንጂ የኤርትራ ህዝብ አይደለም፡፡ ከስልጣኑ ዉጭ በኤርትራ ህዘብና በሀገሪቱ ላይ ለሚደርስ የትኛዉም አይነት ችግር ብዙ አያስጨንቀዉም፡፡ ስለዚህ ይህን የኢሳይያስን ሰስ ብልት የማይነካ መፍትሄ ጠቀሜታዉ ብዙም አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ምን ያህል ተሰርቷል የሚለዉ ላይ መረጃዉ የለኝም፡፡

ቢያንስ በግምት ደረጃ መንግስታችን የሉአላዊቷን ኤርትራ አገዛዝ በኃይል መቀየር (forced regime change) የእኔ ሃላፊነት አይደለም የሚል አምነት እንዳለዉ ስለማዉቅ በዚህ ረገድ የተሰራ ስራ ባይኖር አይገርመኝም፡፡ እንደዚያ አለማድረጉም ስህተት ነዉ አልልም፡፡ ይህ የመንግስታችን አቋም ወደፊትም ይቀጥላል ወይንስ አዲሱ ፖሊሲ በዚህ ላይም የአቋም ለዉጥ ያደርግ እንደሆነ ከግምት ዉጭ በርግጠኝነት መናገር አልችልም፡፡

በተረፈ ኤርትራን በጦር ኃይል እንዘምትባቸዋለን የሚል አቋም በኛ በኩል ካለ በጦርነት ኢሳይያስን ማስፈራራት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ኢሳያስ እጅግ በተስፋ የሚጠብቀዉን ነገር እንዳደረግንለት ስለሚቆጥር ደስታዉን አይችለዉም፡፡ ምክንያቱም እጅግ የተራቆተበትን የህዝብ ድጋፍ ዳግመኛ ሊያገኝ የሚችለዉ በዚህ ብቻ ነዉና፡፡ የኤርትራ ህዝብ ሀገሩ ሉአላዊነት ተደፍሮ ባለበት ሁኔታ ከመንግስት ጋር ተባብሮ ይሰለፋል እንጂ በምንም ምክንያት ጸረ- ኢሳይያስ አቋም አይዝም፡፡  ስለዚህ በጦር የመዝመት ጉዳይ ለግዜዉ ከአጀንዳነት ቢወጣ እመርጣለሁ፡፡

ሌላዉ መዘንጋት የለለብን ጉዳይ የሻእቢያን አመራር ዲተር ስናደርግ ኢሳይያስ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያሰማራቸዉን ጸረ ኢትዮጵያ የሽብር ኃይሎችንና ሰርጎ ገቦችን አብሮ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ነዉ፡፡ ስለኤርትራ ስናስብ አነዚህን ኃሎችንም እያሰብን መሆን አለበት፡፡ በርግጥ ለነዚህ ኃይሎች ብቻ ተብሎ የሚመጣ አዲስ የዲተረንስ ወይም የፖሊሰ ለዉጥ አይኖርም፡፡ የኢሳይያስ የስራ ዉጤት በመሆናቸዉ ኢሳይያስን በማዳከም ነዉ በተዘዋዋሪ መንገድ እነሱን ማዳከም የምንችለዉ፡፡

እነዚህ ኃይሎች ለኢሳይያስና አገዛዙ ህልዉና ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑና የእኛን ደህንነት በማናጋት ረገድ ዋነኛ የሻዕቢያ መሳሪያዎች መሆናቸዉ ላይ ለአፍታም መጠራጠር አይኖርብንም፡፡ እነዚህ ኃይሎች ኤርትራ በቀጥታ ትንኮሳ አደረገች ለሚለዉ ክስ “የእኔ እጅ የለበትም፡፡ የራሳቸዉ ጸረ- መንግስት ኃይሎች ናቸዉ” በማለት ለመሸፈን እንደረዱት እናዉቃለንና፡፡ ስለዚህ ቋሚ አድራሻ የለላቸዉ በሽብር ተግባር የተሰለፉ ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎችን በቀጥታ አግኝተን ዲተር ማድረግም ሆነ አስከነአካቴዉ ለመደምሰስ ባይቻለንም አስካሁን ባለዉ ሀኔታ ድንበር እያቋረጡ ተሸሎክልከዉ እየገቡ በአነስተኛ የሰዉ ኃይል ትናነሽ የጸጥታ ችግሮች ሲያደሰርሱብን የመከላከልና ተስፋ የማስቆረጥ ስራ ነዉ ስንሰራ የቆየነዉ፡፡

እነዚህን ኃይሎች በተቻለ መጠን ሳይቀድሙን ቀድመን መደምሰስ ይገባን ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኃይሎች በቀጥታ አግኝተን ለመደምሰስም ሆነ ከድርጊታቸዉ እንዲቀጠቡ ለማድረግ ስለማንችል ያለን አድል ዋነኛ መፈልፈያቸዉ የሆነችዉን ኤርትራን ዲተር በማድረግ ብቻ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ እነዚህ ኃይሎች በቀጥታ ከነሙሉ ኃይላቸዉ አግኝተን ማጥፋት አንችልምና፡፡

መንግስት ስለ አዲሱ ፖሊስ ጥቆማ ከሰጠ በኋላ በኤርትራ የመሸጉ ጸረ ኢትዮጰያ ኃይሎችን ለመታደግ ታስቦ ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰጠ አስተያየት ላነበበ ሰዉ ቀጣዩ የመንግስት አርምጃ ምን ያህል እንዳሰጋቸዉ ለመገመት ያስችለዋል፡፡

ሁልግዜም መንግስትን መጠራጠርን ስራዬ ቢለዉ በያዙና ለጸረ -ሰላም ኃይሎች ቋሚ ጠበቃ በሆኑ አንዳንድ ሰዎች ግምት አዲሱ የመንግስት ፖሊሲ በዋነኛነት ያተኮረዉና እንደ ዓላማም የያዘዉ  ከኤርትራ እየተነሱ ሰላም የሚነሱትን ተቃዋሚ ተጣቂ ኃይሎችን ተጽኢኖ በመቀነስ ላይ ስለሆነ መንግስት እነዚህን ኃይሎች እንዲያስታግስለት ሻእቢያን ለማግባባት ቢሎ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ አስከመስጠት ሊደርስ ይችላል የሚል አስተያየት ነዉ፡፡

በእኔ እምነት መንግስታችን ከኤርትራ እየተነሱ ችግር የሚፈጥሩብን ጥቂት ሽፍታ ታጣቂ ቡድኖች ተጽእኖ ያን ያህል አስግቶት ለዚያ ብሎ የሀገር ጥቅምን የሚያህል ነገር ለኤርትራ አሳልፎ አስከመስጠት ይደርሳል የሚል ግምት ስለሌለኝ መንግስት እንደዚህ ዓይነት ተልካሻ ስህተት ይሰራል ብየ አላስብም፡፡ ነገሩ ግን ሻዕቢያ ሲነካ እነዚህ ኃይሎችም አብረዉ እንደሚነኩ ያመላከተ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ፡፡

2.5/ ፌዴራላዊ ስርአታችን ከአንድነታችንና ከኢትዮጵዊነት ጋር ጠብ የለዉምና ለጠላት ጥቃት ላለመጋለጥ ዉስጣዊ አንድነታችን ማጠንከር ይገባናል

ሀገሪቱ እያስመዘገበች ባለዉ እድገት ጠላቶቻችን ደስተኛ እንደማይሆኑ ይልቁንም ከአድገት ግስጋሴያችን ሊያደናቅፉን እንደሚሞክሩ ለማናችንም ግልጽ ነዉ፡፡ ትላንት በድህነታችን ምክንያት የትም አይደርሱም ብለዉ ስለ መኖራችን እንኳን ክደዉ ንቀዉን የተዉን ሀገሮች የዛሬዉ እድገት ግስጋሰአችን ነገ ለነሱ የስጋት ምነጭ እንደሚሆን ስለሚያዉቁ ካሁኑ ሊያስተጓጉሉን መጣራቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡

ትላንት ደካማ በነበርን ግዜ ወሳኝ ብሄራዊ ጥቅም (vital national interst) አድርገን የምንቆጥረዉና ነገ ጉልበት ስናበጅ፤ የህዝባችን ፍላጎት ሲጨምር ፤ተጽእኖ ፈጣሪነታችንና ተደማጭነታችን ባደገ ቁጥር  ሊኖረን የሚችለዉ  ብሄራዊ ጥቅም ከበፊቱ ጋር አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገ የምንዋደቅለት አጀንዳ ትላንት ከተጋደልንለት ብሄራዊ አጀንዳ በዓይነቱም በደረጃዉ የሚልቅ ሊሆን መቻሉ ሊያስገርመን አይገባም፡፡

ትላንት እንኳን ተጨማሪ ጥቅም ለሀገር ማምጣት ቀርቶ የራሳችንን እንኳን ጠብቀን ማቆየትና ተሟግተን መርታት የተሳነን ነበርን፡፡ ዛሬ ሀገራችን በአለም አቀፍና በሪጂኑ ተደማጭ መሆን በመቻሏ መብታችንን ለማስከበር እንደ ድሮዉ ደጅ መጥናትና መለማመጥ ሳያሻን የጠየቅነዉን ሁሉ ማስፈጸም የምንችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል፡፡ መሪዎቻችን ይህን የተፈጠረ መልካም አጋጣሚ ለራሳቸዉ የግል ዝና ግንባታ  ሳይሆን ለሀገርቱ በሚጠቅም መልኩ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ትላንት በነበረብን የአቅም ዉስንነትና የተቀባይነት ችግር ምክንያት “ለግመል መፈንጫ” ብለን እንደዋዛ  ያጣጣልነዉን አሰብን ሳይቀር ለማስመለስ ሰፊ እድል አለን፡፡ የሚያስፈልገን አንድነገር ብቻ ነዉ፡፡ የመሪዎቻችን ራዕይና ራዕዩን እዉን ለማድረግ የሚያስችል ቁርጠኝነት!

ኤርትራ በጭራሽ አትወጋንም ከሚለዉ ከኛ የተሳሳተ ግምገማና የስጋት ትንታኔ (national security threat assessment) ችግር ይልቅ ኤርትራ ጥቃት ለመሰንዘር የበቃችዉ “የተከፋፈሉ ናቸዉ፣ እርስበርስ መግባባት አይችሉም” የሚል የተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርታ ነዉ” የሚለዉ የኛ ድምዳሜ ብዙ ተደጋግሞ ሲነገር በአንጻሩ የኛ የስጋት ትንታኔ ወይም ግምገማ ችግር እንደዋዛ ታለፈ፡፡ ከኛ የግምገማ ችግር ይልቅ ስለኤርትራ የግምገማ ችግር ብዙ ተነገረ፡፡

“አስቀድመን ለምን ተገቢዉን የጥንቃቄ አርምጃ ሳንወስድ ቀረን?” የሚል ቁጭትን መነሻ ያደረገ አስተያየት በኛ በኩል አልተሰማም፡፡ በተለይ አመራሮቻችን በነሱ የግምገማ ችግር ምክንያት በተቀሰቀሰዉ ጦርነት የደረሰብንን መጠነ ሰፊ ጉዳት ብዙም የተሰማቸዉና የተጸጸቱ አይመስሉም፡፡ ጦርነቱ ጭራሽ እንዳይነሳ አድርገን ቢሆን ኖሮ አንድም ሰዉ ባልሞተ ነበር ፡፡ እነዚያ የአይደር ጨቅላ ህጻናት በሻዕቢያ ክላስተር ቦንብ ባልተጨፈጨፉ ነበር፡፡ ዛላ አንበሳ ዶግ አመድ ለመሆን ባልተዳረገ ነበር፡፡ ከኤርትራ ጋርም ከጦርነቱም በኋላ ይሄን ያህል ዘመን በጠላትነት ባልቆየን ነበር፡፡ ኤርትራ ሽብርተኞችን እያስታጠቀች በመላክ ሰላም ባልነሳችን ነበር፡፡

ስለጦርነቱ በተነሳ ቁጥር በድንገት  ወረራ የተፈጸመብን  የሻእቢያ ደደብነትና የኢሳይስ ጅልነት በፈጠረዉ የግምገማ ችግር ነዉ እያልን ነጋ ጠባ እነሱን ከመራገም ይልቅ እኛ ለምን ለጥቃት ተመቻችተን ተገኝንላቸዉ? ለምንስ ተገቢዉን ጥንቃቄ አላደረግንም? ብለን ራሳችንን ጠይቀንና እርስበርስም ተወቃቅሰን አናዉቅም፡፡ ለኛ ስንፈትና ድክመት መሸፋፈኛ  እንዲሆነን የሻእቢያን የግምገማ ችግር ደጋግሞ ደጋግሞ መናገሩን የመረጥን አስመስሎብናል፡፡ ዛሬም ነገም ስለ ኢሳይያስ ክፋት ነዉ የምናወራዉ፡፡

ሌላዉ ቢቀር ኢሳይያስ ጦርነት ናፋቂና ጀብደኛ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ይሄን ሁሉ ሲያደርግ የነበረዉ ለራሱ ለኤርትራ ህዝብ ጥቅም አስቦ እንደሆነ ለመቀበል የከበደን ይመስላል፡፡ የኤርትራን ጥቅም ለማስጠበቅ የመረጠዉ መንገድ የተሳሳተና አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ መንግስት ለሀገሩ ጥቅም በመዳከሩ ሊደነቅ ይገባል፡፡ እኛ ወደ ጦርነት ገብተን  እስከምናስቆማቸዉ ድረስ በነበሩት ሰባት ዓመታት ዉስጥ ለኤርትራ ጥቅም ቢሎ ሀገራችንን ሲግጣት እንደነበር እንዴት እንዘነጋለን፡፡ በዚህ የዘረፋ ድርጊቱ የኤርትራ ህዝብ አለመሰገነዉ እንጂ አላወገዘዉም፡፡ መቃወም የሚገባዉ መስሎ የሚሰማን ከሆነ መሳሳታችንን ልናዉቅ ይገባል፡፡

በኛ በኩል አምነን መቀበል ያቃተንና ልንሸሸዉ የማንችለዉ ሃቅ ቢኖር ኤርትራ ለስህተት የተዳረገችዉ በኛ ድክመት መሆኑን ነዉ፡፡ ይሄንን እዉነታ ለማመን አንፈልግም፡፡ የኛን መንከርፈፍ አይተዉ ነዉ ጥቃት የሰነዘሩብን፡፡ ሻዕቢያ ኢትዮጵያዉያን የተከፋፈሉ ስለሆኑና በአንድነት መቆም ስለማይችሉ በቀላሉ እናሸንፋቸዋለን የሚለዉ የዘጠና ዓመተ ምህረቱ ግምገማቸዉ የተሳሳተ መሆኑን እኛ ብቻ ሳንሆን እነሱም እዉቀዋል፡፡

ይህ ግምገማቸዉ ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ሆኖ ቢሆን ኖሮ እዉነትነት አለዉ ብለን እኛዉ ራሳችን ማረጋገጫ መስጠት በቻልን ነበር፡፡ ሻዕቢያ የያነዉ ግምገማቸዉ ለዛሬ ቢሆን ኖሮ ተሳስተዋል ለማለት አንደፍርም ነበር፡፡ ምክንያቱም እጅግ የሚያሳዝን እዉነት ስለሆነ፡፡ ማናችንም ለሀገራችን የምንቆረቆር ዜጎች እንምንረዳዉ ከምንግዜም በላይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ዉስጣዊ አንድነታችን አደጋ ላይ መዉደቁን ነዉ፡፡ ከተጠቀሰዉ ግዜ ወዲህ አርስበርሳችን መደማመጥን አቁመናል፡፡

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገራችን የሚታየዉ ዓይነት በዘርና በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥላቻ በታሪካችን በዚህ መጠን ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ ፌዴራላዊ ስርአቱ ችግር ስላለበት እንዳልሆነ አስካሁን ለሁለት አስርተ ዓመታት በሰላም መኖራችን ራሱ ምስክር ነዉ፡፡

የአንድነት መንፈሳችን እየራቀን ስለመሆኑ፤ አገራችን አደጋ ላይ እየወደቀች ስለመሆኗ፤ ፌዴራላዊ ስርአታችን ከኢትዮጵያዊነት ጋር መሰረታዊ ጠብ ያለዉ አስኪመስል ድረስ ስለ ልዩነት እንጂ ከነ ልዩነታችን አብረን መኖር እንደምንችል፤ ስለ አንድነት በጎ ገጽታ የሚናገር መጥፋቱ፤ ሁኔታዉ እያሰጋቸዉ በጎ አስተያየት የሚሰጡ ዜጎችን  ስርአቱን ለማጥላላት የተፈለገ አስመስለዉ የሚያሸማቅቁ ሰዎች መብዛታቸዉ አካሄዳችን መፈተሸ እንዳለበት አመላካች ነዉ፡፡

አንዳንድ የዋሆች ባልገባቸዉ ነገር ስርአቱ ለአንድ የተለየ ህዝብ ብቻ የመጣና ሌላዉን ህዝብ የማይፈልግ አድርገዉ በመቁጠር አንዱን ቋንቋ ተናጋሪ ለስርአቱ ፍጹም ታማኝ ሌላዉን ደግሞ ከስርአቱ ጋር አብሮ የማይሄድና ጠበኛ አድርገዉ የመፈረጅ አደገኛ አዝማሚያ በሰፊዉ እያየን ነዉ፡፡ በእኔ እምነት በስርአቱ ላይ የትኞቹም የሀገሪቱ ህዝቦች ልዩነት የላቸዉም፡፡ ሁሉም ከስርአቱ ተጠቃሚ እንደሆነና ስርአቱም ለሁሉም እንደመጣ እገነዘባለሁ፡፡

በመሰረቱ በሀገሪቱ ዉስጥ የሚታዩ ጸረ አንድነትና ከፋፋይ አዝማሚያዎችና አመለካከቶች የስርአቱ ባህሪይ እንዳልሆነም ከበፊቱ ይልቅ አሁን በሚገባ ግልጽ ነዉ፡፡ ችግሩ ግን የመንግስትን አንዳንድ ደካማ ጎኖች በመጠቀም ዉስጣዊ አንድነታችንን ለማናጋት ለሚፈልጉ ኃይሎች ምቹ ሆነን መገኘታችን ነዉ፡፡ ስርአቱን በሆነ መንገድ ለብቻቸዉ በተለየ ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ሆን ብለዉ በሚፈጥሩት ተንኮል ዜጎች ስርአቱን እንዲጠራጠሩ እየተደረጉ ነዉ፡፡

ሁላችንም አንዳችን ከሌላዉ ባልተለየ ሁኔታ ስለምንከተለዉ ፌዴራላዊ ስርአት ትክክለኛነትና ስለ መንግስት የልማት ጥረት በአደባባይ በጠራራ ጸሀይ እናወራለን፡፡ በጎን ግን ጨለማን ተገን አድርገን አገር ለማፈራረስ እንዶልታለን፡፡ እጅግ ስግብግብ የሆኑ አንዳንድ ወገኖች ዘለቄታ ለሌለዉ ግዜያዊ ጥቅም ቢለዉ ሀገር ከማፍረስና ህዝብን ከህዝብ ጋር ከማጋጨት እንደማይመለሱ በግላጭ እያየን ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ሰዉ ሰራሽ በሆኑ ተንኮሎች መብዛት የተነሳ ዉስጣዊ አንድነታችንና አብሮነታችን አደጋ ላይ እየወደቀ ነዉ፡፡

ክፋቱ ደግሞ ማንም ደፍሮ አደጋዉን ለመናገርና ለማመላከት አለመፈለጉ ነዉ፡፡ ሁላችንም በሀገሪቱ ላይ የፈረድንባት ነዉ የሚመስለዉ፡፡ ሁላችንም በሀጋራችን ላይ በጭካኔ ልናፈራርሳት ተማምለን የተነሳን ነዉ ያስመሰለብን፡፡ በምንቸገረኝነት ዝም እያልን ነዉ፡፡ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በጽኑ እናምናለን የምንባል ሰዎች እንኳን ሳንቀር በምንቸገረኝነት ታዉረን ስርአቱንና ሀገሪቱን ለመታደግ አንንቀሳቀስም፡፡ ይሄ አጅግ አሳዛኝ ክሰተት ነዉ፡፡

3/ ማጠቃለያ

ዛሬ ዜጎች ለሀገራችን መጻኢ ዕድል እጅግ የምንሰጋበት ወቅት ላይ እንዳለን መካድ አንችልም፡፡ በየስርቻዉ በሰበብ አስባቡ የሚደረጉ መቆራቆዞች፤ የርስበርስ ግጭቶች እንደቀድሞዉ በሌሎች አሳበን ንቀን የምናልፈዉ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዘመናት ተፋቅረዉ በጉርብትና የኖሩ ወንድማማች የሆኑ ህዝቦች በተለያዩ ሰበቦች ለግጭት እየተዳረጉ ነዉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከብሄሩና ከጎሳዉ ዉጭ ለሌላዉ የሚያስብና የሚቆርቆር አንድም ሰዉ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አንችልም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ቤታችንና አገራችን መሆኗ ቀርቶ የአንድ ብሄር ብቻ ተደርጋ በመቆጠሯ ተሟጋችና የሚታደጋት እያጣች ነዉ፡፡ ኢትዮጵያን በደህና የሚያነሳት ጠፍቷል፡፡ ህገመንገስቱ ባጎናጸፈን መብት ተጠቅመን ለሁላችንም ምቹ የሆነች አገር በጋራ ለመፍጠር  በአንድነት እንቁም ሲባል እንዴት የኢትዮጵያ ስም ይነሳል ቢለዉ ቱግ የሚሉ እየበዙ ነዉ፡፡

ከስንት አንዴ ደፋር ሰዉ ተገኝቶ ስለኢትዮጵያዊነት ስለአቀነቀነ መብታችን የተነካ ይመስል ለበርካታ ወራት በስድብና በዛቻ እርስበርስ የምንቆራቀዝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ዛሬ እንደ ትላንቱ የሻእቢያን ትንኮሳ ሰምቶ በቁጣ ከዳር አስከዳር ተቀንቀሳቅሶ እንደተነሳዉ ዓይነት የህዝብና የመንግስት አንድነት ለመኖሩ እየተጠራጠርኩ መጥቻለሁ፡፡ ይሄን ያህል የሚያሰጋ ነገር የለም የሚለኝ ካለ ማብራሪያዉን ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡

የኛ እርሰ በርስ መነጣጠልና መኮራረፍ ደንታ የማይሰጣቸዉ የማያሳስባቸዉና ምናልባትም የሚያስደስታቸዉ አንዳንድ ራስ ወዳድ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠርም ደግ ነዉ፡፡ በግልጽ ያፈጠጠ ችግር በገሃድ እየታየ ችግር እንደለለ ለማስመሰል መሞከርም ሆን ቢሎ ችግሩን ለማባባስ እንደመፈለግ የሚቆጠር ነዉ፡፡ ኤርትራም ሆነች ሌሎች ጠላቶቻችን እኛ ለመደበቅ ብንሞክር እንኳን መደበቅ የማንችለዉን በአንድነት በጋራ የመቆም ባህላችን ክፉኛ መሸርሸር ለመገንዘብ የሚቸግራቸዉ አይመስለኝም፡፡

ሽንፈትንም ሆነ ድልን ፤ ደስታንም ሆነ ሃዘንን ተጋርቶ የመኖር የቆየ ባህላችንና ኩራታችን በተለይም የዉጭ ጠላት ሲነሳብን ልዩነቶቻችን ወደ ጎን አድርገን በአንድነት እንድንቆም ያደርገን የነበረዉ የኛ ብቻ የሆነዉ ባህሪያችን አሁን እየከሰመ መሆኑ መንግስታችን ሊያሳስበዉ ይገባል፡፡ እርስበርሱ የማይደማመጥ ህዝብ በችግር ግዜ ከመንግስት ጎን ይቆማል ተብሎ አይታሰብምና መንግስት በዚህ ረገድ ተግቶ መስራት ይገባዋል፡፡

ስለዚህ ስለ ኤርትራም ሆነ ሌላ አገር ሁኔታ ሲታሰብ መጀመሪያ ስለራሳችን ገመና መነጋገርና መፍትሄ ማስቀመጥ መቅደም ይኖርበታል፡፡ መንግስታችን ከምንግዜም በላይ አሁን ከልማቱ ጥረታችን ጎን ዲሞክራሲዉንም እኩል ለማስኬድ የሚያስችለንን ተጨባጭ ስራ እየሰራ ነዉ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን የማስፋቱ ትልቁ ፋይዳ በሀገራችን እጅግ ተንሰራፍቶ አላፈናፍን ላለን የመልካም አስተዳዳር እጦትና ስር የሰደደ ሙስናን በተሻለ ለመታገል የሚያስችል ትልቅ መሳሪያ ሊሆነን ይችላል በሚል እምነትም ነዉ፡፡

በግዜያዊ ችግሮች መኖር ምክንያት የስርአቱን ትክክለኛነት የምንጠራጠርበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም፡፡ የምንከተለዉ ስርአት የሁሉንም ህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋጋጥና በማንነታችን እንድንኮራ የሚያደርገን መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ ሀገራችን የሆነችዉ ኢትዮጵያን በጋራ ካልተንከባከብናት ለሀገራችን ፍቅር ከሌለን በስተቀር ለየብቻ የምናደርገዉ ሩጫ ለዉድቀት ይዳርገናል፡፡ ስለዚህ ፌዴራላዊ ስርአታችንና ኢትዮጵያዊነት ጠብ የለለቻዉ መሆናቸዉን አዉቀን በአንድነታን ጸንተን ለመቆም እንሞክር እላለሁ፡፡

***********

(የዚህን ፅሁፍ የመጨረሻ ክፍል በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories