የእኛ ትምህርት እንቆቅልሽ – ክፍል 3 | የእንቆቅልሹ ፍቺ

የኢትዮጲያ ትምህርት እንቆቅልሽ ክፍል አንድ በዝርዝር እንደተጠቀሰው የሀገራችን ትምህርት ሥርዓት መሰረታዊ የሆነ የሥነ-ዕውቀት (epistemological crisis) ችግር አለበት። በክፍል ሁለት ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱ ያሉበትን ሦስት መዋቅራዊ ችግሮች (structural problems) በዝርዝር ተመልክተናል። በሌላ በኩል፣ ላለፉት አስር አመታት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት በብዙ እጥፍ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የተማሪዎቻችን የትምህርት ዕውቀት/ብቃት በየአመቱ እያሽቆለቆለ ሄዷል። ስለዚህ ይህን እንቆቅልሽ እንዴት መፍታት ይቻላል?

የኢትዮጲያ ትምህርት እንቆቅልሽን መፍታት የሚቻለው በክፍል ሁለት በዝርዘር የተመለከትናቸውን መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ ሲቻል ነው። የትምህርት ሥርዓቱ መዋቅራዊ ችግሮችን፤ ፅሁፍ-ወለድ ፅንሰ-ሃሳብ፣ የማስተማሪ ቋንቋ እና አስተዳደራዊ መዋቅር (text-borne concepts, languages, and structures) ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ከየት መጀመር አለበት? የለውጥ እንቅስቃሴው በዋናነት መጀመር ያለበት ከሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው።

በዚህ ረገድ አንድ ሊጠቀስ የሚገባው ነገር የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን እንደመጣ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያደረገው ለውጥ ነው። በወቅቱ ህፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፍ-መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ ራስ-ወዳድ ምሁራንና የኒዮሊብራል ኃይሎች ሲከራከሩ እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የለውጡ እንቅስቃሴ የጀመረው ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ነው። ሆኖም ግን፣ የትምህርት ሥርዓቱን በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ፍላጎት መሰረት ለመቅረፅ የሚደረገው ጥረት መጀመር ያለበት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነበር።

የትምህርት ሥርዓቱ መዋቅራዊ ችግሮች ሥረ-መሰረታቸው ያለው በክፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ነው። የኢትዮጲያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት በሀገሪቱ ነባራዊ እውነታና በሕዝቡ የዕለት-ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ የተቀረፀ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። በዚህ ምክንያት መምህራን ለራሳቸው በተግባር ላይ የተመሰረተ ዕውቀትና ግንዛቤ የላቸውም፣ ችግር-ፈቺና ተደራሽ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እየሰሩ አይደለም። በዚሁ ልክ ለተማሪዎቻቸው ተግባር-ተኮር ዕውቀት እያስጨበጧቸው አይደለም።

ሌላው ደግሞ የሀገር ውስጥ ቋንቋን በማስተማሪያነት ተጠቅሞ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ መምህራንን የሚያሰለጥን ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ የለም። በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንግሊዘኛ ዋና የማስተማሪያ ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ የሀገራችን ተማሪዎችና አስተማሪዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚያነቧቸው፣ የሚናገሯቸውና የሚፅፏቸው ቃላትን ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ አይረዱም። ይህ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እስከ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን በግልፅ የሚታይ ሃቅ ነው።

ስለዚህ፣ የትምህርቱ ይዘት ፅሁፍ-ወለድና በተግባራዊ ዕውቀት ያልተደገፈ ከመሆኑ በተጨማሪ አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ መምህራን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሃሳባቸውን በደንብ ለመግለፅ ይቸግራቸዋል። በንድፈ-ሃሳብ ላይ ብቻ የተመሰረተ የትምህርት ዕውቀታቸውን ለራሳቸው በደንብ ሳይገባቸው ለተማሪዎቻቸው ያስተማራሉ። ይህን ፅሁፍ-ወለድ የሆነ የትምህርት ዕውቀትና ክህሎት የሚያስተምሩት ደግሞ አብዛኞቹ መምህራንና ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍል ውጪ በማይጠቀሙት ፅሁፍ-ወለድ ቋንቋ ነው። በደንብ ያልገባንን ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ በማይገባን ቋንቋ እየተማርንና እያስተማርን ምን ዓይነት የትምህርት ጥራትና ዕውቀት እንጠብቃለን?

ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ብቻ 68ሺህ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ተምረው በዲግሪና በዲፕሎማ ተመርቀዋል። እነዚህ የሁለተኛ ደረጃ መምህራንም በዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ የቀሰሙትን ፅሁፍ-ወለድ ዕውቀት ለራሳቸውም ሆነ ለተማሪዎቻቸው ግራ በሆነ ቋንቋ ያስተምራሉ። መምህራኑ ለራሳቸው የሌላቸውን ለተማሪዎቻቸው መስጠት አይችሉም። በደንብ ያልተገነዘቡትን ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ በማይግባቡበት ቋንቋ ተምረው እያስተማሩ ምን ዓይነት የትምህርት ጥራትና ዕውቀት እንጠብቃለን?

ባለፉት አስር አመታት የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ከ140ሺህ ወደ 400ሺህ ጨምሯል። ከእነዚህ ውስጥ 300ሺህ ያህሉ የኮሌጅ ዲፕሎማ ያላቸው ናቸው። እነዚህ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ትምህርታቸውን የተማሩት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። ለተማሪዎቻቸው የሚያስተምሩት ግን በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግሪኛ፣ ….ወዘተ ነው። የአራተኛ ክፍል ሂሳብ ትምህርትን በአማርኛ ቋንቋ የሚያስተምር መምህር በምን አግባብ ነው የኮሌጅ ትምህርቱን በእንግሊዘኛ የሚማረው?

“2 ጊዜ 4፣ ስንት ነው?” እያለ የሚያስተምር መምህር ¨2 times 4 is equal to how much?” ተብሎ የሚማርበት ምክንያት ምንድነው? ለምሳሌ በአማርኛ “2 ጊዜ 4” የሚለውን የሂሳብ ስሌት፤ “አራትን ሁለት ግዜ ብትደምረው ስንት ይሆናል?”፣ “በነበሩህ አራት እርሳሶች ላይ ሌላ አራት እርሳሶች ብትደምር ስንት ይሆናሉ?” እና የመሳሰሉትን ተጨባጭ ምሳሌዎች በመስጠት ተማሪዎቹ የስሌቱን ፅንሰ-ሃሳብ እንዲገነዘቡ ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን፣ በአንግሊዘኛ ¨2 times 4” ማለት “two times four” ማለት ብቻ ነው። ከላይ በአማርኛ የሰጠኋቸውን ተጨባጭ ምሳሌዎች በአንግሊዘኛ ቋንቋ እያብራራ የትምህርቱን ፅንሰ-ሃሳብ ማስገንዘብ የሚችል የኮሌጅ መምህር በጣም ውስን ነው።

በዚህ መልኩ የኮሌጅ ዲፕሎማቸውን የተማሩ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን በደንብ በማይግባቡበት ቋንቋ የተማሩትን ፅሁፍ-ወለድ ፅንሰ-ሃሳብ ወደ ተማሪዎቹ የአፍ-መፍቻ ቋንቋ እየተረጎሙ ያስተምራሉ። ነገር ግን፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ደረጃ ከሚያስተምሩ መምህራን በተሻለ ማስተማር ይችላሉ። የሁለተኛ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን በደንብ ስለማያውቁት ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ በማይግባቡበት ቋንቋ ስለሚያስተምሩ ነገሩ ሁሉ ትምህርት ሳይሆን መደናቆር ነው።

የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን የትምህርት አሰጣጥ ከተቀሩት የትምህርት ደረጃዎች የተሻለ ስለመሆኑ ለአስር አመት የተካሄደው ተከታታይ ጥናት ያስረዳል። በክፍል አንድ ያለውን ሰንጠረዥ ብትመለከቱት የአራተኛና ስምንተኛ አማካይ የፈተና ውጤት ከአመት-አመት እየቀነሰ እንደሄደ ያሳያል። ይሁን እንጂ፣ በሁሉም አመታት የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች አማካይ ውጤት ከስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ይበልጣል። ምንም አንኳን ለግዜው በጥናት የተደገፈ መረጃ ባይኖረኝም፣ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች አማካይ ውጤት ከዘጠንኛ ክፍል፣ የዘጠንኛ ክፍል ደግሞ ከዩንቨርሲቲ ተማሪዎች አማካይ ውጤት እንደሚበልጥ ጥርጥር የለኝም። ምክንያቱም፣ የትምህርት ደረጃው እየጨመረ በሄደ ቁጥር የትምህርት ይዘቱና የማስተማሪያ ቋንቋው ከነባራዊ እውነታውና ከተናጋሪው እየራቀ ይሄዳል።

በክፍል አንድ በዝርዝር እንደተጠቀሰው፣ ተማሪዎቻችን ለማሰብ፥ ለማስተዋልና ለመመራመር የሚያስችል ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚሰጣቸው ትምህርት ከንድፈ-ሃሳብ ባለፈ በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረተና ተግባር-ተኮር ሊሆን ይገባል፡፡ ዕውቀታችን ከተግባራዊ አንቅስቃሴያችን ጋር ተያያዥነት የሌለው ከሆነ በተግባር ለማሰብ፥ ለማስተዋልና ለመመራመር በቂ የሆነ የአዕምሮ ችሎታ ሊኖረን አይችልም፡፡ ምክንያቱም፣ ከማህብረሰባችን ሕይወት የተነጠለ ትምህርትና ዕውቀት ፋይዳ-ቢስ ነው።

Nyamnjoh, F. (2004)፣ “A Relevant Education for African Development” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፉ በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ ማህብረሰብ ተኮር የሆነ ዕውቀት ከማህብረሰቡ የመግባቢያ ቋንቋ፣ የአፃፃፍ ስልት፣ ሥነ-ትዕይንትና አመለካከት ጋር የተቆራኘ ነው። ስለዚህ፣ የትምህርት ሥርዓቱ ከሕዝባችን ቋንቋ፣ ሥነ-ትዕይንት፣ ባህል፣ እሴትና አመለካከት አንፃር በተቃኘ መልኩ በድጋሜ ሊቀረፅ ይገባል። ለምሳሌ፣ የሂሳብ ትምህርትን በአማርኛ፥ ኦሮምኛ፥ ሶማሊኛ ወይም ትግሪኛ የሚያስተምር የመጀመሪያ ደረጃ መምህር ለምን የኮሌጅ ትምህርቱን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይማራል? የኢትዮጲያ ትምህርት እንቆቅልሽ ፍቺው ይኼ ነው!

የትምህርት ሥርዓቱ ባለበት የሚቀጥል እስከሆነ ድረስ፣ የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ብቃት እንደ ባለፉት አመታት ሁሉ በቀጣዮቹ አመታትም እያሽቆለቆለ ይሄዳል። የተማሪዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን ወደ 21 ሚሊዮን ቢጨምር፣ የዲፐሎማ ያላቸው መምህራን ከ5ሺህ ወደ 300ሺህ፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ደግሞ ከ15ሺህ ወደ 80ሺህ ቢጨምሩ፣ ለስርዓተ ትምህርት ክለሳ፥ ለመማሪያ መፃህፍት ዝግጅትና ለህትመት 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ቢሆን፣ በ2 ቢሊዮን ብር 140 ሚሊዮን የመማሪያ መፃህፍት ቢታተሙ…ወዘተ፣ ይህን እንቆቅልሽ በዘላቂነት መፍታት አይሻሻልም።

በአጠቃላይ፣ በተሳሳተ መንገድ እየተጓዘን እስከሆነ ድረስ ምንም ያህል ብንፈጥን ከአሰብንበት አንደርስም። ስለዚህ፣ በተሳሳተ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ብዙ ሺህ መምህራን፣ ብዙ ሚሊዮን ተማሪዎች፣ ብዙ ቢሊዮን ብሮች ብናፈስ የትምህርት ጥራት፣ የአስተማሪዎችና ተማሪዎች ብቃት ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ እንጂ እየተሻሻለ አይሄድም።

—-

ማጣቀሻዎች

* የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል (1993 ዓ.ም፣ ገፅ፡-331)

* Julius_Nyerere, Education for Self-Reliance” (1968, p. 268)

* Abdi A. (2006), Eurocentric Discourses and African Philosophies and Epistemologies of Education, International Education, Fall 2006.

* Andrews N. and Okpanachi E. (2012), Trends of Epistemic Oppression and Academic Dependency in Africa’s Development: The Need for a New Intellectual Path፣ The Journal of Pan African Studies, vol.5, no.8, December 2012,

* Nyamnjoh, F.B. (2004), A Relevant Education for African Development – Some Epistemological Considerations, African Development, Vol. XXIX, No. 1, 2004, pp. 161-184

* Wiredu, K. (1998), Toward Decolonizing African Philosophy and Religion, African Studies Quarterly | Volume 1, Issue 4 | 1998.

* Weiler, H.N., (2006). Challenging the Orthodoxies of Knowledge: Epistemological, Structural, and Political Implications for Higher Education: UNESCO Publishing, 2006, 61-87

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories