የእኛ ትምህርት እንቆቅልሽ – ክፍል 1 | የሽምደዳ ዕውቀት ከቃላት አያልፍም

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በማህብረሰብ አምዱ “’2 ጊዜ 4’ ተማሪዎችን እያስጨነቀ ነው”በሚል ርዕስ ያቀረበው ዘገባ የሀገራችንን የትምህርት ጥራት ደረጃ ወደየት እየሄደ እንደሆነ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ ለትምህርት ጥራት መቀነስ በዋና ምክንያትነት ሲጠቀስ የነበረው የተማሪዎች ቁጥር በፍጥነት መጨመሩ፣ የመምህራን ብዛትና የትምህርት ደረጃ፣ የትምህርት መሳሪያዎች አቅርቦት እጥረት፣ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ነበሩ፡፡

በአስር አመታት ውስጥ የተማሪዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን ወደ 21 ሚሊዮን ቢጨምርም በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ብዛት ከ74 ወደ 54 ቀንሷል፤ የመምህራን ብዛትና የትምህርት ደረጃ፣ የመማሪያ መፅሃፍት ብዛትና ጥራት የተማሪዎች ቁጥር ከጨመረበት ፍጥነት ሁለትና ሦስት እጥፍ ፍጥነት ጨምሯል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከታች ባለው ሰንጠረዥ ላይ በግልፅ እንደሚታየው የተማሪዎች የትምህርት ብቃት በየአመቱ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

Chart - Average exam results of Grade 4 and Grade 8 students
Chart – Average exam results of Grade 4 and Grade 8 students

በኢትዮጲያ ትምህርትን ለማስፋፋትና ጥራቱን ለማሳደግ የሚወጣው ወጪ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የተማሪዎቻችን የትምህርት ዕውቀት ደረጃ በተመሣሣይ ፍጥነት እየቀነሰ ነው፡፡ ታዲያ ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነው ጥያቄ “ለምን?” የሚለው ነው፡፡ ይኼን እንቆቅልሽ ለመፍታት ከመሞከራችን በፊት ግን በአንድ ነገር ላይ በግልፅ ልንግባባ ያስፈልጋል።

የሞባይልና ኢንተርኔት ትውልድ ከራዲዮና ጋዜጣ ትውልድ የተሻለ የመረጃና ዕውቀት አቅርቦት አለው፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን፣ የ2002ቱ ተማሪ ከ1992ቱ ተማሪ የተሻለ ንቃተ-ህሊና እና የግንዛቤ ደረጃ አለው። ስለዚህ፣ የአዲሱ ትውልድ የትምህርት ብቃት ደረጃን ለችግሩ መንስዔ አድርጎ ለመጥቀስ መሞከር ፍፁም ስህተት ነው። ነገር ግን፣ በተሻለ ኑሮና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት አብዛኞቹ ተማሪዎች የላቀ ግንዛቤ እያዳበሩ ከሆነ ታዲያ የትምህርት ብቃታቸው ለምን ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ይሄዳል?

በዚህ ረገድ የሚቀርቡ አብዛኞቹ የጥናት ውጤቶች እና ትንታኔዎች የጨመረውን ከመደመር እና የቀነሰውን ከመቀነስ አያልፉም፡፡ ይሁን እንጂ፣ በትምህርት ዙሪያ ሁሉም ነገር በፍጥነት ሲጨምርና ሲቀንስ፣ ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረበት ግዜ ጀምሮ ያለ ምንም ለውጥ በነበረበት የቆሞ አንድ ነገር አለ፡- የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት፡፡

ከትምህርት መስፋፋት፣ ጥራትና ብቃት ጋር ተያይዞ ለሚስተዋሉት ችግሮች ዋናው መንስዔ፥ የእንቆቅልሹ ፍቺ ያለው ከትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ይህን ችግር መረዳት ከራሱ ከችግሩ በላይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ችግሩ የሥርዓት ብቻ ሳይሆን የዕውቀት ጭምር ነው፡፡ በተሳሳተ መንገድ የሚሰጥ ትምህርት ዕውቀታችንን በዙሪያችን ካለው ነባራዊ እውነት ይልቅ በምናባዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ አድርጎታል፡፡ በተሳሳተ መንገድ የቀሰምነው ዕውቀት ስህተት ብቻ ሳይሆን ስህተታችንን ከማወቅ አግዶናል።

በተሳሳተ የትምህርት ሥርዓት አማካኝነት የምናገኘው በነባራዊ እውነታ ላይ ያልተመሰረተ ዕውቀት የሚፈጥረው ችግር “የሥነ-ዕውቀት ቀውስ” (Epistemological crisis) ይባላል፡፡ ኢትዮጲያን ጨምሮ፣ ከሞላ-ጎደል ሁሉም ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት የሥነ-ዕውቀት ችግር አለባቸው፡፡ በእርግጥ ችግሩ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ባህሪ አለው፡፡ ስለዚህ፣ ችግሩን በደንብ ለመረዳት እንዲያመቸን ከአህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ኩነቶች ጋር አያይዘን መመልከት አለብን፡፡ በዚህ መሰረት፣ አንዳንድ የአፍሪካ ምሁራን የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎችን ዋቢ በማድረግ ችግሩን በግልፅ ለመረዳት እንሞክራለን፡፡ በመጀመሪያ “ዕውቀትና ትምህርት ምንና ምን ናቸው?” ከሚለው ጥያቄ እንጀምራለን።

የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ዕውቀት” የሚለውን ቃል “የሰው ልጅ በትምህርት ወይም በልማድ የሚያገኘውና ለማሰብ፥ ለማስተዋል፥ ለመመራመር የሚያበቃው የአዕምሮ ችሎታ” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል፡፡ በእርግጥ ሰው ትምህርት የምንማረው ዕውቀት ለማግኘት ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ በትምህርት የምናገኘው ዕውቀት ምን መሆን አለበት? ይህን ለመረዳት “የትምህርት መሰረታዊ ዓላማ ምንድነው?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የቀድሞው የታንዛኒያ ፕረዜዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ (Julius_Nyerere) የሰጡት ትንታኔ በዋቢነት የሚጠቀስ ነው፡፡ እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ የትምህርት መሰረታዊ ዓላማ ሕብረተሰቡ ለዘመናት ያከማቸውን ዕውቀትና ጥበብ ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ፣ ወጣቱን ትውልድ ለቀጣዩ ማህበራዊ ሕይወት ማዘጋጀትና ማብቃት፣ እንዲሁም የማህብረሰቡን ሕልውና እና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ማስቻል ነው፡፡

ከላይ ስለ ዕውቀት ምንነት እና ስለ ትምህርት ዓላማ ከተሰጡት ትንታኔዎች ሊሰመርባቸው የሚገቡ ሁለት ነጥቦች አሉ፡፡ አንደኛ፡- ለማሰብ፥ ለማስተዋልና ለመመራመር እንድንችል ዕውቀታችን ከንድፈ-ሃሳብ በተጨማሪ በነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ፣ ተግባር-ተኮር ሊሆን ይገባል፡፡ ሁለተኛ፡- የትምህርት ሥርዓት በነባራዊው እውነታና በሕዝቡ ማህበራዊ ሕይወት ላይ መሰረት አድርጎ ሊቀረፅ ይገባል፡፡ የአንድ ሀገር የትምህርት ሥርዓት በሀገሪቱ ነባራዊው ሁኔታና በሕዝቦቿ ኑሮና አኗኗር ላይ ካልተመሰረተ በትምህርት የምናገኘው ዕውቀት ፋይዳ-ቢስ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም፣ ዕውቀታችን በአብዛኛው ከራሳችን እውነትና ሕይወት ጋር ተያያዥነት ከሌለው ለማሰብ፥ ለማስተዋልና ለመመራመር በቂ የሆነ የአዕምሮ ችሎታ ሊኖረን አይችልም፡፡

አሁን በሀገራችን ባለው የትምህርት ሥርዓት መሰረት አንድ ኢትዮጲያዊ ስለ ሀገሩ ታሪክና ሕዝብ ከሚያውቀው በላይ ስለ አሜሪካና አውሮፓ የሚያውቀው ይበልጣል። ለእሱ ከሀገሩ ይልቅ አሜሪካና አውሮፓ፣ ከዘርዓያቆብ ይልቅ አርስቶትልና ፕሌቶ ይቀርቡታል። ነገር ግን፣ በአሜሪካ እና አውሮፓ ስላለው ነባራዊ እውነታና ሕይወት የተግባር ተሞክሮና ዕውቀት የለውም። አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን እንደሚገልፁት፣ የዚህ ዓይነት የትምህርት ስርዓት ከተፈጥሮ ሳይንስ ይልቅ ወደ ማህበራዊ ሳይንስ የሚያደላና የትምህርት አሰጣጡም ተግባር-ተኮር ሳይሆን ቃላትን አኝኮ በመትፋት “chew and pour” – “ሽምደዳ” ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡

በእርግጥ ኢትዮጲያ ውስጥ ትምህርት ማለት በወረቀት ላይ የተፃፉ የእንግሊዘኛ ቃላትን በአዕምሮ መሸምደድ ነው። ዕውቀት ደግሞ የተሸመደዱ ቃላትን መልሶ መናገር ወይም በወረቀት ላይ መፃፍ መቻል ነው። በዚህ መልኩ የተማርነው ትምህርት፣ የቀሰምነው ዕውቀት ሁላችንንም ለዝቅተኛ የአዕምሮ ችሎታ ዳርጎናል። መምህራን ይህን ተጨባጭ ያልሆነ ፅሁፍ-ወለድ ፅንሰ-ሃሳብ በባዕድ ሀገር ቋንቋ ተምረው፣ ይሄንኑ መልሰው ያስተምራሉ።

በተማሪነት የተማርነውና በመምህርነት የምናስተምረው ከሀገራችን ነባራዊ እውነታ የራቀና በተግባር ተሞክሮ ያልተደገፈ ፅንሰ-ሃሳብ ነው። ይህን የምናስተምርበት ቋንቋ ደግሞ በእለት-ከእለት ግንኙነታችን ለመግባቢያነት በማንጠቀምበት፣ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ብቻ ተወስኖ በሚቀር የባዕድ ሀገር ቋንቋ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ፤ በእኛ ሀገር “ትምህርት” ማለት ሽምደዳ ነው፣ “ዕውቀት” ማለት ደግሞ የተሸመደዱ ቃላት ነው። “2 ጊዜ 4፣ ስንት ነው?” የሚለው ጥያቄ ግን ማሰብ፥ ማስተዋልና መመራመር – ዕውቀት – የሚጠይቅ የሂሳብ ስሌት ነው። ያልተማርነውን፥ ያላስተማርነውን ከየት እናምጣው?

በቀጣዩ ክፍል “በሀገራችን የትምህርት ዘርፍ ሁሉም ነገር ሲጨምርና ሲሻሻል የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ብቃት ለምን እያሽቆለቆለ ሄደ?” የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት “ሥርዓተ ትምህርቱ የማን ነው?” በሚል ርዕስ እንመለሳለን።

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories