የእኛ ትምህርት እንቆቅልሽ – ክፍል 2 | ሥርዓተ ትምህርቱ የማን ነው?

[Read – የእኛ ትምህርት እንቆቅልሽ – ክፍል 1 | የሽምደዳ ዕውቀት ከቃላት አያልፍም]

በዚህ ክፍል “በሀገራችን የትምህርት ዘርፍ ሁሉም ነገር ሲጨምርና ሲሻሻል የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ብቃት ለምን እያሽቆለቆለ ሄደ?” የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ችግሩን ከሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት አንፃር ለመመልከት እንሞከርራለን። “A Relevant Education for African Development” በሚል ርዕስ በቀረበ ጥናታዊ ፅኁፍ ውስጥ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ነፃ ከወጡም በኋላ “አፍሪካዊ” ያደረጉት ነገር ቢኖር በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል እንጂ የትምህርት ሥርዓታቸውን እንዳልሆነ እንዲህ ለማሳየት እንዲህ ይላል፡- ‘

¨There has been little effort at domestication or an epistemological shift informed by the awareness that the site – or community -specific knowledge ties in with the language and textical structures of a given language, local cosmologies and worldviews…” A Relevant Education for African Development; African Development, Vol. XXIX, No. 1, 2004, pp. 161-184

በጥናቱ መሰረት፣ በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ፤ ኢትዮጲያ፥ ሶማሊያ፥ ኬኒያ፥ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ ብቻ የሀገር ውስጥ ቋንቋን በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በማስተማሪያ ቋንቋነት ይጠቀማሉ። ሆኖም ግን፣ እነዚህም ሀገራት ቢሆኑ የሀገር ውስጥ ቋንቋን ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጪ ለማስተማሪያነት አይጠቀሙም። ይህ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ከሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታና ከሕዝቡ ማህበራዊ ሕይወት የተነጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ በኮሌጅ ደረጃ የሀገር ውስጥ ቋንቋን በዋና የማስተማሪያ ቋንቋነት የምትጠቀም አፍሪካዊ ሀገር ታንዛኒያ ብቻ ናት፡፡ ከዚያ በተረፈ ኢትዮጲያን ጨምሮ ሌሎች ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት የማስተማሪያ ቋንቋቸው እንደ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ያሉ የባዕድ ሀገራት ቋንቋዎች ናቸው፡፡

ከትምህርት ሥርዓትና የማስተማሪያ ቋንቋ ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮች በዋናነት ከቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች እንደሆኑ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።ለምሳሌ፣ ታዋቂው የጋና ፈላስፋ “Kwasi Wiredu” የቅኝ-አገዛዝ ሥርዓትን አካላዊ ቅኝ-አገዛዝ እና የአስተሳሰብ (ሃሳባዊ) ቅኝ-አገዛዝ በማለት ለሁለት ይከፍለዋል። አካላዊ ቅኝ-አገዛዝ (Physical colonialization) አንድን ሉዓላዊ ሀገር ወይም ግዛት በጦር ኃይል አሸንፎ የፖለቲካ ስልጣንን መቆጣጠር ነው። የአስተሳሰብ ቅኝ-አገዛዝ (Conceptual colonialization) ደግሞ በተገዢው ሕዝብ ላይ የገዢዎችን እምነት፣ አመለካከት፣ ባህልና ሥርዓት በኃይል መጫን ነው። የመጀመሪያው በጦር መሣሪያና በወታደሮች አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በትምህርት ሥርዓትና በመምህራን አማካኝነት እንደሆነ ጋናዊው ፈላስፋ ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ የቅኝ-አገዛዝ ስርዓት ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊና ባህላዊ ጭምር እንደመሆኑ የአፍሪካ ሀገራትን የትምህርት ሥርዓት ክፉኛ በክሎታል።

በእርግጥ ኢትዮጲያ አካላዊ ቅኝ-አገዛዝን በአደዋ ድል በኃይል አሸንፋለች። ነገር ግን፣ የምዕራባዊያንን የትምህርት ሥርዓት በራሷና በሕዝቧ ላይ በመጫን በአስተሳሰብ ቅኝ-አገዛዝ ስር ወድቃለች። እንደ ሌሎች በቅኝ-አገዛዝ ሥር እንደነበሩ የአፍሪካ ሀገራት በነባራዊ እውነታና በሕዝቡ ሕይወት ላይ ያልተመሰረተ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ ራሷን በራሷ ለአስተሳሰብ ባርነት ዳርጋለች። በዚህ ምክንያት፣ እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት፣ የእኛም ትምህርት ሥርዓት ሦስት መዋቅራዊ ችግሮች (Structural Problems) አሉበት፡- ፅሁፍ-ወለድ ፅንሰ-ሃሳብ፣ ቋንቋና መዋቅር (text-borne concepts, languages, and structures)፡፡

ከሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ-ትምህረት ጋር በማያያዝ ከላይ የተጠቀሱትን መዋቅራዊ ችግሮች በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ እኔ የማስተምረው የሥራ-አመራር (Business Management) ትምህርት ሲሆን ከማስተምራቸው የትምህርት ዓይነቶች አንዱ “Financial Management” ይባላል፡፡ በዚህ የት/ት ዓይነት ስለ ካፒታል አፈጣጠር (Capital formation)፣ አክሲዮንና ቦንድ ዋጋ (Share and Bond Value)፣ አክሲዮን ገበያ (Stock Market)፣ …ወዘተ የመሳሰሉትን ፅንሰ-ሃሳቦች ከተቋሙ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች (Operational Activities) አንፃር ያላቸውን ተያያዥነትና ፋይዳ በተመለከተ አስተምራለሁ።

ነገር ግን፣ ኢትዮጲያ ውስጥ ከሰፈር ሱቆች እስከ የሀገሪቱ ዋና የገበያ ማዕከል፥ መርካቶ ድረስ ዋና የካፒታል ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው “ዕቁብ” እንጂ የአክሲዮን ወይም የቦንድ ሽያጭ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ኢትዮጲያ ውስጥ የአክሲዮን ገበያ የለም፡፡ እኔም ወደ ሌላ ሀገር ሄጄ ስለማስተምረው ትምህርት ተግባራዊ ዕውቀት የመቅሰም ዕድሉን አላገኘሁም። ስለዚህ፣ በዕቁብ ብር ለሚማር ተማሪ ስለ አሜሪካው “City Bank” እና ስለ እንግሊዙ “Barclays” ባንክ የአክሲዮን ገበያና ዋጋ፣ ገቢ መጨመርና መቀነስ በምሳሌነት እየተጠቀምኩ አስተምራለሁ፡፡

እንደ መምህር ስለአከሲዮን ገበያ በተግባር ላይ የተመሰረተ ልምድና ዕውቀት የለኝም። ስለዚህ፣ የእኔ ዕውቀት በተግባር ያልተደገፈ ፅሁፍ-ወለድ (text-borne concept) ነው። እኔም ሆንኩ ተማሪዎቼ በዕለት-ከዕለት ግንኙነታችን ለመግባቢያነት የምንጠቀመው ቋንቋ የሀገር ቤት ቋንቋ ነው። የተማርኩበትና የማስተምርበት ግን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። በመሆኑም፣ ሁላችንም በደንብ በማንግባባበት የባዕድ ሀገር ቋንቋ በተግባራዊ ዕውቀት ያልተደገፈ ትምህርት አስተምራቸዋለሁ። እኔ እንደ መምህር የሌለኝን ለተማሪዎቼ አልሰጥም። እነሱም እንደ ተማሪ ያልተሰጣቸውን ዕውቀት ከየትም ሊያመጡት አይችሉም። ከመማር ማስመሩ ጋር በተያያዘ ካሉት የዕውቀት እና የማስተማሪያ ቋንቋ ችግሮች በተጨማሪ ከጥናትና ምርምር ጋር በተያያዘም ሌላ ችግር አለ።

በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ፅሁፎች ላይ በጥራዝነት የሚያያዝ በእንግሊዘኛ እና በአማርኛ፥ ኦሮምኛ ወይም ሌላ የሀገር ቤት ቋንቋ ተተርጉሞ የተዘጋጀ የመረጃ መጠየቂያ (Questionnaire) ቅፅ አለ። ይህ ቅፅ በሀገር ቤት ቋንቋ የተዘጋጀበት ምክንያት ከተሳታፊው ወይም በጥናቱ መፍትሄ ሊሰጠው ስለታሰበው ችግር ሕብረተሰቡ በሚግባባበት ቋንቋ ትክክለኛውን መረጃ ለመሰብሰብ እንዲቻል ነው። ነገር ግን፣ ከመጠይቁ በስተቀር ያሉት የጥናቱ ክፍሎች፤ የጥናቱ ትንታኔ፣ መደምደሚያና የመፍትሄ ሃሳብ የሚፃፈው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። ለምን? በእርግጥ ይሄ ችግርን በሚያግባባ ቋንቋ ጠይቆ መፍትሄውን በማያግባባ ቋንቋ እንደመናገር አይደልም? ሌላው ብዙሃኑ የሀገራችን ማህብረሰብ በሚግባባቸው እንደ አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም ሶማሊኛ ቋንቋዎች የተሰሩ ጥናትና ምርምር ውጤቶች የሚታተሙባቸው የሣይንስ ጆርናሎች የሉም። በተመሣሣይ፣ የችግሩ ባለቤት ለሆነው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍልና ባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ በሀገር ቤት ቋንቋ የጥናትና ምርምር ሥራ ሰርቶ ያቀረበ ተመራማሪ የሙያና የደረጃ እድገት አያገኝም።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጲያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት በነባራዊ እውነታና ከሕዝቡ የዕለት-ከዕለት ሕይወት ላይ ተመስርቶ የተቀረፀ ባለመሆኑ ምክንያት ተማሪዎች ተግባራዊ ዕውቀት እንዳያገኙ እና ችግር-ፈቺ ጥናትና ምርምሮች እንዳይሰሩ ዋና ማነቆ ሆኗል፡፡ከዚህ በተጨማሪ፣ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋለው ሦስተኛው መዋቅራዊ ችግር ደግሞ ከመንግስት ፖሊሲና የተቋማት አሰራር ጋር የተያያዘ ነው።

የሀገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ አጀንዳዎችን በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው። በምሁራን ዘንድ ድጋፍ የሌለው የመንግስት ፖሊሲና አቅጣጫ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት እድሉ በጣም አነስተኛ ነው። ‘“Weiler, H.” የተባለው ተማራማሪ “Challenging the Orthodoxies of Knowledge” በሚል ርዕስ እ.አ.አ በ2006 ባቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በመንግስት ፖሊሲዎችንና አሰራሮች ዙሪያ ሙያዊ ድጋፍና ትንታኔ በመስጠት የመንግስትን ቅቡልነት (legitimacy) በመወሰን ረገድ ያላቸውን ቁልፍ ሚና “knowledge legitimizes power” በማለት ይገልፀዋል። መንግስት ደግሞ በተራው የትምህርት ሥርዓቱን ባለማሻሻል ምሁራኑን ውለታ ይመልሳል። ተመራማሪው ይህን ደግሞ “power legitimizes knowledge” በማለት ይገልፀዋል።

እነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን የተሳሳተው የትምህርት ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው። የእነሱ ዕውቀት ከንድፈ-ሃሳብ ያልዘለለና ተግባር-ተኮር ያልሆነ፣ በሀገሪቱና ሕዝቡ ሕይወት ላይ ተጨባጭ የሆነ ለውጥና መሻሻል ማምጣት የተሳነው ፋይዳ-ቢስ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ምሁርና ባለሙያ ጥቅምና ተጠቃሚነታቸው አሁን ካለው የትምህርት ሥርዓት ጋር የተቆራኘ ነው። የትምህርት ሥርዓቱ ከቀየረ ግን በሀገሪቱ በማህበራዊ፥ ፖሊተካዊና ኢኮኖሚያ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸው የዕውቀትና የሞራል የበላይነት፣ እንዲሁም ተጠቃሚነት ይቀራል። በዚህ ምክንያት፣ በትምህርት ዕድል፣ ተማሪዎች፣ የጥናት ወረቀቶች፣ ፅሁፎችና ሌሎች ትምህርት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል እንዳይመጣ በማድረግ ፋይዳ-ቢስ ለሆነው የትምህርት ሥርዓት ጥብቅና ይቆማሉ። በዚህ ላይ ከWeiler, H. (2006) ጥናታዊ ፅሁፉ ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፡-

“After all, it is the evaluation of scholars, students, research proposals, manuscripts, and publications that determines the principal rewards of academic life: peer recognition, institutional standing and influence, research grants and, most importantly, publication. It is no accident that this assessment process tends to be fundamentally conservative…Beyond being a reasonable safeguard for preserving valuable scientific legacies, this caution puts a strain and acts as a brake on the necessary process of constant renewal of our concepts of knowledge. It is here that the traditional hierarchies of knowledge manifest their power most clearly and effectively. “ Challenging the Orthodoxies of Knowledge: UNESCO Publishing, 2006, 61-87

ከመንግስትና ምሁራን በተጨማሪ፣ የተለያዩ የዓለም-አቀፍ ተቋማትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች የትምህርት ሥርዓቱ እንዳይቀየር ከፍተኛ ሚና አላቸው። ለምሳሌ፣ በኢትዮጲያ ለትምህርት መስፋፋትና ጥራት የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወተው የዓለም ባንክ የትምህርት ሥርዓቱ እንዳይቀየር በማድረግ ረገድ ዋና ተዋናይ ነው። ለምሳሌ፣ የአለም ባንክ ለኢትዮጲያ የትምህርት ዘርፍ ብድር ለመስጠት ባዘጋጀው ሰነድ ላይ እንዲህ በኢትዮጲያ የትምህርት ጥራት መቀነስ አንዱ ምክንያት ፈጣን የሆነ የትምህርት መስፋፋት እንደሆነ ይገልፃል። ነገር ግን፣ የትምህርት መስፋፋት በሀገራችን እየታየ ላለው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል በምክንያትነት ሊጠቀስ አንደማይችል በክፍል-1፡ “ትምህርት ሽምደዳ፥ ዕውቀት ቃላት ነው” ተመልክተናል። ከዚያ ይልቅ፣ እንደ “Weiler, H. (2006) አገላለፅ፣ ለኢትዮጲያ የትምህርት ጥራት መቀነስ አንዱ ምክንያት የተማሪዎች ቁጥር መጨመር ሳይሆን ራሱ የአለም ባንክ እንደሆነ እንዲህ ይገልፀዋል-

“The relationship of reciprocal legitimation between knowledge and power is particularly evident in the case of institutions such as the World Bank, whose role in the international system is by no means confined to exercising influence on economic activity and policy. Less well-known, but extremely effective is the influence the World Bank wields by imposing an orthodoxy of knowledge to which all countries and institutions that wish to enter into negotiations on financing and support with the World Bank must subscribe” Challenging the Orthodoxies of Knowledge: UNESCO Publishing, 2006, 61-87

በክፍል አንድ እንደተመለከትነው፣ ይህ የትምህርት ሥርዓት ከኢትዮጲያ ነባራዊ ሁኔታና ከሕዝቡ የእለት-ከዕለት እንቅስቃሴ አንፃር የተቃኘና ለተማሪዎችና አሰተማሪዎቻችን ተጨባጭ የሆነ ግንዛቤና ዕውቀት ለማስጨበጥ የሚያስችል አይደልም። በዚህ ክፍል በዝርዝር እንደተመለከትነው ደግሞ የትምህርት ሥርዓት በቅኝ-አገዛዝ ዘመን በአፍሪካዊያን ላይ የአስተሳሰብ ባርነት ለማስፈን እንዲያስችል ታስቦ የተቀረፀ ነው። በእርግጥ ይህን ሥርዓት በኢትዮጲያ ሕዝብ ላይ ተጭኖ የቆመበት ምክንያት፤ በአንድ በኩል መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ላለማጣት ሲል፣ የሀገሪቱ ምሁራን ጥቅምና ተጠቃሚነታቸውን ላለማጣት ሲሉ፣ እንደ አለም ባንክ ያሉ ድርጅቶች ደግሞ የኒዮሊብራሊዝም መርህን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ሲሉ በፈጠሩት ጥምረትና ትብብር አማካኝነት ነው። ስለዚህ፣ “ሥርዓተ ትምህርቱ የማን ነው?” ለሚለው ጥየቄ መልሱ “የአድርባይ መንግስት፣ የራስ ወዳድ ምሁራን እና የግብዝ ኒዮሊብራሊስቶች ነው!”

“የኢትዮጲያ ትምህርት እንቆቅልሽ” የመጨረሻ ክፍል-3፡ የእንቆቅልሹ ፍቺ ይሆናል ያልኩትን ሃሳብ ይዤ እቀርባለሁ፡፡

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories