ኢህአዴግን የጠለፈው “የአመራር ወጥመድ”

ከአስር ቀን በፊት አዲስ አድማስ ጋዜጣ በመንግስት አመታዊ ሪፖርቶች ዙሪያ ያቀረበውን ዘገባ ተመልክታችኋል? ነገሩ “ስህተትን መደባበቅና ማስመሰል መደበኛ የአሰራር ስልት ሆነ እንዴ?” ያስብላል። በእርግጥ ሁሉም ባለስልጣናት ያው እንደ እኔና እናንተ “ሰው” ናቸው። እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ። ችግሩ የእኛ ባለስልጣናት እንደ አምላክ ፍፁም መሆን ይቃጣቸዋል። በስህተት ላይ ስህተት እየሰሩ፤ “ተሳስታችኋል” ሲባሉ አይሰሙም፣ “ተሳስተናል” ብለው አያምኑም። እንዴ…ከደቂቅ እስከ አዋቂ የሚያውቀውን ነገር የእኛ ባለስልጣናት አያውቁትም፣ ቢያውቁትም እንኳን በግልፅ አይናገሩም። ይኼው በየግዜው ይሳሳታሉ፣ ሲነግሯቸው ስለማይሰሙ ስህተታቸውን መልሰው ይሳሳታሉ። በዘገባው መሰረት፤ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የብረታ-ብረት ከርፖሬሽን፣ የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ የከተማ ልማትና የቤቶች ሚኒስቴር እና የማዕድን ሚኒስቴር፣ በአመቱ ውስጥ ያስመዘገቡት ዝቅተኛ አፈፃፀም እንዳለ ሆኖ፣ በሪፖርታቸው ውስጥ ከፍተኛ የአስመሳይነት ችግር (Impostor syndrome) ይታያል።

በአጠቃላይ፣ ተዓማኒነት የሌለው የአፈፃፀም ሪፖርቶች፣ ከልክ ያለፈ የፖለቲካ ቁማር፣ ዕርስ-በዕርስ አለመተማመን፣ የክትትልና ባለቤትነት ስሜት ማጣት፣ የተለያዩ የአፈፃፀምና የሥነ-ምግባር ችግሮች ችላ የማለት እና የመሳሰሉት በአብዛኞች የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ይስተዋላሉ። ነገሩ በጣም ስላሳሰበኝ፣ በመጀመሪያ “ባለስልጣናት ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ ችግር ይኖር ይሆን?” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። በመቀጠል የተለያዩ የፍልስፍና፣ ሥነ-ልቦና እና የሥራ-አመራር ፅሁፎችን ማገላበጥ ጀመርኩ። በመጨረሻ የደረስኩበት እውነት ግን ለአብዛኞቻችን አስደንጋጭ፣ ለአንዳንዶቻችን ደግሞ የሚያስቆጭ ሊሆን ይችላል።

አዎ… አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናትን ብቻ ላይቶ የሚያጠቃ “የአመራር ወጥመድ” (Leadership Trap) የሚባል የሥነ-ልቦና ችግር አለ። ይህን ፅሁፍ አንብባችሁ ስትጨርሱ፣ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በሙሉ የተፈጠሩት የተቋማቱ አመራሮች በአመራር ወጥመድ ተጠልፈው በመውደቃቸው እንደሆነ ትረዳላችሁ።

አንድ ደቡብ አፍሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ “Getting out of the Political Leadership Trap” በሚል ዕርስ የአፍሪካ ሀገራት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ብቃት ያለው አመራር እንደሚያስፈልጋቸው ይገልፃል። ምክንያቱም፣ በበለፀጉ ሀገራት ሕብረተሰብ ውስጥ የዳበረ የዕውቀትና ልምድ ክምችት ከመኖሩ በተጨማሪ፣ የላቀ የአመራር ብቃት የሌላቸውን የፖለቲካ መሪዎች በቀላሉ ለማስወገድ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መኖሩን ይጠቅሳል። ነገር ግን፣ አንደ ኢትዮጲያ ያሉ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት፣ መሪዎቻቸው በአመራር ወጥመድ ውስጥ መውደቃቸውን ለማወቅ እንኳን ዕድሉ የላቸውም።

ግን ይህ የአመራር ወጥመድ (Leadership Trap) መቼና እንዴት ነው የሚጀምረው? በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ የሥራ-አመራር እና የሥነ-ልቦና ምሁራን እንደሚሉት የአመራር ወጥመድ ችግር መነሻው “ለምን መምራት ፈልግኩ?” (Why do I want to lead?) ከሚለው ጥያቄ ነው።

አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት ወደ አመራርነት የመጡበትን ምክንያት ሲጠየቁ ከራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎት ይልቅ “ሕዝብን ለማገልገል” በሚል የብዙሃንን ጥቅምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ሲገልፁ መስማት የተለመደ ነው። ነገር ግን፣ ይህ እሳቤ በምክንያታዊ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በመሰረቱ፣ ምክንያታዊነት የሚጀምረው ከውስጣዊ ማሰላሰል (introspection) ነው። “ለምን መምራት ፈልግኩ?” የመሳሰሉ ጥያቄዎች ደግሞ በራስ፥ በውስጣዊ ማሰላሰል የሚመለሱ ናቸው። ሆኖም ግን፣ አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት “ለምን ወደ ፖለቲካ/አመራርነት እንደመጡ” ሲጠየቁ “ሕዝብን ለማገልገል” የሚል በውጫዊ ማሰላሰል (extrospection) ላይ የተመሰረተ ምላሽ ይሰጣሉ።

አሜሪካዊ ፈላስፋ “Ayn Rand” አገላለፅ፣ ማንኛውም ሰው በእውን ስላለበት ሁኔታ ለምንና እንዴት የሚሉትን ጥያቄዎች ራሱን-በራሱ ጠይቆ ምክንያታዊ የሆነ ግንዛቤ ማዳበር ከተሳነው፣ ስላለበት ሁኔታ፣ የተግባራዊ እንቅስቃሴውን ምክንያትና ውጤት በሚገባ ማወቅ እንደማይችል ትገልፃለች። በዚህ ረገድ “Philosophical Detection” በሚለው ፅሁፏ እንዲህ ትላለች፡-

“… Without a ruthlessly honest commitment to introspection—to the conceptual identification of your inner states – you will not discover what you feel, what arouses the feeling, and whether your feeling is an appropriate response to the facts of reality, or a vicious illusion produced by years of self-deception.

The men who scorn or dread introspection take their inner states for granted, as an irreducible and irresistible primary, and let their emotions determine their actions. This means that they choose to act without knowing the context (reality), the causes (motives), and the consequences (goals) of their actions.”

ብዙውን ግዜ የሀገራችን ባለስልጣናት “ለምን ወደ ፖለቲካ እንደገቡ?” ወይም “ለምን ባለስልጣን እንደሆኑ?” ሲጠየቁ ከሚሰጧቸው ምላሾች ውስጥ “ሕዝብን ለማገልገል” የምትለዋ ሐረግ አትጠፋም። “ባለስልጣን የሆንኩት በግሌ ስልጣን የመያዝ ከፍተኛ ፍላጎት ስላለኝ ነው!” የሚለው ምላሽ ግን አልተለመደም። ነገር ግን፣ ባለስልጣናቱ ስለ “ስልጣን” (Authority) የተሳሳተ ግንዛቤ ስላላቸው ነው እንጂ ለጥያቄው ትክክለኛ ምላሽ መሆን የነበረበት ሁለተኛው ነው። እንደ ፕሮፌሰር “Bill George” ያሉ የዘርፉ ምሁራን፣ የመጀመሪያው ዓይነት አመለካከት ያላቸው ከፍተኛ አመራሮች/ባለስልጣናት “በአመራር ወጥመድ” ውስጥ የመውደቅ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ እያንዳንዱ ባለስልጣን ወደ አመራርነት ሲመጣ ከራሱ ጋር በማሰላሰል “ለምን ስልጣን ፈለግኩ?” ወይም “ለምን ባለስልጣን ሆንኩ?” እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መመለስ አለበት። በዚህ መልኩ ስለ ስልጣንና ነፃነት ግልፅ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል። በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ግልፅ የሆነ ግንዛቤ ያለ አይመስለኝም። “ስልጣን ነፃነት፣ ነፃነት ስልጣን ነው” በሚለው ፅሁፌ በዝርዝር ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ስልጣን ከኃላፊነት (responsibility) በተጨማሪ በውስጡ በራስ የመወሰን ወይም የምርጫ ነፃነትን (freedom of choice) ያካትታል። ነፃነት የመብትና ግዴታ ጥምርታ ነው። ስልጣን ደግሞ የመወሰን ነፃነት እና ኃላፊነት ጥምርታ ነው። በተፈጥሮ የእያንዳንዳችን መብት የሌሎች ሰዎች ነፃነትን ከማክብር ግዴታ ጋር ተጣምሮ እንደተሰጠን ሁሉ፣ ለእያንዳንዱ ባለስልጣን የሚሰጠው የመወሰን ነፃነት የሌሎች ሰዎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ኃላፊነት/ግዴታ ጋር የተጣመረ ነው። በዚህ መሰረት፣ “ለምን ባለስልጣን ሆንኩ?” ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሚሆነው “በራሴ የመወሰን ነፃነት እንዲኖረኝ ስለምፈልግ” የሚለው ነው። ምክንያቱም፣ ሁሉም ባለስልጣናት ወደ አመራርነት የመጡት ለራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎትና እርካታ ብለው እንጂ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትና ተጠቃሚነት ብለው አይደለም።

በዚህ መሰረት፣ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለአንድ ባለስልጣን ግዴታ ነው። ይህም በስልጣን ውስጥ በራሱ እንዲወስን ለተሰጠው ነፃነት የተጣለበት ግዴታ እንጂ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ የወሰደው ኃላፊነት አይደለም። በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ባለስልጣን ወደ አመራርነት የመጣው የራሱን ውስጣዊ ፍላጎት ለማርካት ነው። የዜጎችን መብትና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱ ደግሞ ግዴታው ነው። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ባለስልጣን “ለምን ባለስልጣን ሆንኩ?” የሚለውን ጥያቄ በውስጡ ማሰላሰል ከቻለ፣ “በራሱ ለመወሰን” ያለው ፍላጎትና ጉጉት “ሕዝብን ለማገልገል” ከሚለው የላቀ እንደሆነ ይረዳል። በአጠቃላይ፣ እያንዳንዱ ባለስልጣን ወደ አመራርነት የመጣው የራሱን ውስጣዊ ፍላጎት ለማርካት ስለሆነ “ባለስልጣን የሆንኩት ስልጣን የመያዝ ከፍተኛ ውስጣዊ ፍላጎት ስለነበረኝ ነው!” የሚል እሳቤ ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን፣ በተለምዶ “ሕዝብን ለማገልገል” የሚለው እሳቤ፣ እንደ “Ayn Rand” አገላለፅ፣ በረጅም አመታት ውስጥ የተገነባ ውል-አልባ ራስን-በራስ የማታለል (a vicious illusion produced by years of self-deception) ውጤት  ነው።

Jungian Type inventory” በተባለው የሰዎች ሥነ-ልቦና መለያ ዘዴን በመጠቀም፤ በውስጣዊ ማሰላሰል (introspection) ላይ የተመሰረተ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች “Introverts” የሚባሉ ሲሆን፣ በውጫዊ ማሰላሰል (extrospection) ላይ የተመሰረተ አመለካከት ያላቸው ደግሞ “Extroverts” ይባላሉ። በዚህ መሰረት፣ “ሕዝብን ለማገልገል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ አመለካከት ያላቸው አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት የ“Extroverts” የሚባለው ሥነ-ልቦና እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። የዚህ ዓይንት ሥነ-ልቦና ያላቸው አመራሮች የሥራቸውን ውጤታማነት የሚመዝኑት በራሳቸው ውስጣዊ እርካታ (Internal Satisfaction) ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ዘንድ በፈጠሩት ደስታ (External Gratification) ነው።

ፕሮፌሰር “Bill George” – “Why Leaders Lose Their Way” በሚለው ፅሁፋቸው እንደገለፁት እንደ አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት የ“Extroverts” ሥነ-ልቦና ያላቸው አመራሮች እንዴት በአመራር ወጥመድ (Leadership Trap) ውስጥ እንደሚወድቁ እንደሚከተለው ይገልፃሉ፡-

“When leaders focus on external gratification instead of inner satisfaction, they lose their grounding. Often they reject the honest critic who speaks truth to power. Instead, they surround themselves with sycophants who tell them what they want to hear. Over time, they are unable to engage in honest dialogue; others learn not to confront them with reality.”

የፖለቲካ ስልጣን በብዙሃን ሕይወት ላይ ስር-ነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል። ይሁን እንጂ፣ የፖለቲካ ሥራና ስርዓቱን በበላይነት የሚመሩት ባለስልጣናት አሳታፊ የሆነ አሰራር (participative approach) ሊኖራቸው የግድ ነው። ነገር ግን፣ “በስልጣን ውስጥ ያለውን በራስ የመወሰን ነፃነት” ፈልገው ወደ ፖለቲካ የገቡና “ሕዝብን ለማገልገል” በሚል ወደ ፖለቲካ የገቡ አሰራራቸው የተለያየ ነው። የመወሰን ነፃነት የሚፈልጉት ”Introverts” በቅድሚያ ነገሮችን በጥልቀት አጢነው ውሳኔ የመስጠት ባህሪ ስላላቸው አሳታፊ የውሳኔ አሰጣጥ የመተግበር እድላቸው ከፍተኛ ነው። በተቃራኒው የ“Extraverts” ሥነ-ልቦና ያላቸው ደግሞ ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ማሰብ የሚመርጡ አመራሮች ናቸው።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ “ሕዝብን ለማገልገል” በሚል አመለካከት ያላቸው አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት የ“Extraverts” ሥነ-ልቦና ያላቸው እንደመሆኑ አሳታፊ የውሳኔ አሰጣጥን ተግባራዊ የማድረግ ዕድላቸው ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። አሳታፊ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ በሌለበት ሁኔታ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ውሳኔዎች ይወሰናሉ። አሳታፊ ያልሆኑ ውሳኔዎች የሚፈፀሙ ስህተቶች ባለስልጣናቱን ለትችትና ነቀፌታ ያጋልጣቸዋል። ከራሳቸው ይልቅ ሌሎች ሰዎችን በማስደሰት (External Gratification) ላይ ስለሚያተኩሩ፣ እነዚህ ባለስልጣናት ለትችትና ነቀፌታ በሥራቸው ደስተኛ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም፣ በቀጣይ ስህተት-አልባ የሆነ ሥራ ለመስራት (perfectionism) ጥረት ያደርጋሉ። ነገር ግን፣ ከታች ባለው ጥቅስ ውስጥ በግልፅ እንደተጠቀሰው፣ ስህተት-አልባ የሆነ ሥራ ለመስራት የሚደርጉት ጥረት ድክመቶቻቸውን እንኳን ተለይተው እንዳያውቁ ያደርጋቸዋል።

በእርግጥ የሁለቱም ዓላማ በህዝቡ ውስጥ የተሻለ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ነው። ነገር ግን፣ በስልጣን ውስጥ ያለውን በራስ የመወሰን ነፃነት ፈልጎ ወደ ፖለቲካ የገባ ባለስልጣን፤ ሥራውን የሚሰራው በራሱ ውሳጣዊ ፍላጎት ሲሆን ውሳኔዎቹም በራሱ ምርጫና አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። “ሕዝብን ለማገልገል” በሚል ወደ ፖለቲካ የገባ ባለስልጣን፤ ሥራውን የሚሰራው ሌሎችን ለማገልገል ሲሆን ውሳኔዎቹም በሌሎች ሰዎች ምርጫና አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

የመጀመሪያዎቹ ባለስልጣናት በሥራቸው የሚያገኙት እርካታ ውስጣዊ (Internal Satisfaction) ስለሆነ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ከወሰኑ ወይም ዝቅተኛ የሆነ አፈፃፀም ካስመዘገቡ፣ ስህተታቸው በብዙሃኑ ሕብረተሰብ ዘንድ ቢታወቅም-ባይታወቅም በሥራቸው እርካታ አያገኙም። “ሕዝብን ለማገልገል” የሚሉት ባለስልጣናት ግን በሥራቸው የሚያገኙት እርካታ ውጫዊ (External Gratification) ስለሆነ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ከወሰኑ ወይም ዝቅተኛ የሆነ አፈፃፀም ካስመዘገቡ፣ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እውነቱን እስካላወቀ ድረስ በሥራቸው ይረካሉ። በዚህም የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ትክክል እንደሆኑ ወይም የጎላ ተፅዕኖ እንደሌላቸው አድርጎ በማቅረብ፣ ለምሳሌ ዝቅተኛ አፈፃፀምን በሪፖርት ላይ የተሻለ አስመስሎ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ይህ “ለአስመሳይነት ችግር” “Impostor syndrome” ይባላል። ፕሮፌሰር “Bill George”፣ ለዚህ ዓይነት የአመራር ሥነ-ልቦና ችግር የተጋለጡ ባለስልጣናት ብቃትና ክህሎት እንዳላቸው ለማሳየት በሚያደርጉት ጥረት ተደጋጋሚ ስህተቶችን እንደሚሰሩ፣ ስህተትን በሌላ ስህተት ለማስተካከል እንደሚጥሩ፣ በዚህም ለከፍተኛ ውድቀት እንደሚዳርጉ ይገልፃሉ።

“…..To prove they aren’t impostors, they drive so hard for perfection that they are incapable of acknowledging their failures. When confronted by them, they convince themselves and others that these problems are neither their fault nor their responsibility. Or they look for scapegoats to blame for their problems. Using their power, charisma, and communications skills, they force people to accept these distortions, causing entire organizations to lose touch with reality. …At this stage leaders are vulnerable to making big mistakes, such as violating the law or putting their organizations’ existence at risk. Their distortions convince them they are doing nothing wrong, or they rationalize that their deviations are acceptable to achieve a greater good.”

በመጨረሻም የተወሰኑ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመጠቆም እሞክራለሁ። በእርግጥ ከላይ የችግሩን መሰረታዊ መንስዔ በግልፅ መለየት ስለቻልን መፍትሄው መጠቆም ከባድ አይሆንም። አንድ ባለስልጣን በውጥመድ ውስጥ ለመውደቁ ዋናው ምክንያት ልክ ወደ አመራርነት እንደመጣ፤ “ለምን ባለስልጣን ሆንኩ?” ብሎ ራሱን መጠየቅ ባለመቻሉ እንደሆነ በዝርዝር ተመልክተናል። በተመሣሣይ፣ መፍትሄው ጥያቄውን በድጋሜ ማሰላሰል ነው። በመሰረቱ እያንዳንዱ ባለስልጣን ወደ አመራርነት የመጣው በውስጡ ያለውን በራስ የመወሰን ነፃነት ለመቀዳጀት ፈልጎ እንጂ ኃላፊነትን – “ሕዝብን ለማገልገል” ፈልጎ አይደለም።

ሁሉም ባለስልጣናት ወደ አመራርነት የመጡት ለራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎትና እርካታ ብለው እንጂ “ሕዝብን ለማገልገል” ብለው እንዳልሆነ በውስጣቸው አምነው መቀበልና ይህንንም በይፋ ለመናገር መድፈር እንዳለባቸው በችግሩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልፃሉ። በዚህም በሌሎች ሰዎች ዘንድ እውቅና እና ተቀባይነት ለማግኘት ሳይሆን ለራሳቸው ህሊና እና ውስጣዊ እርካታ (Internal Satisfaction) ሲሉ መስራት ይጀምራሉ። ይህ ሲሆን፣ አሁን በውስጣቸው ያለው የዝነኝነት ስሜት ወደ ሕዝብ አገልጋይነት ይቀየራል። ፕሮፌሰር “Bill George”፣ ባለስልጣናቱን ከራሳቸው ሕሊና እና ከሕዝብ ጋር የሚታረቁበትን የመፍትሄ ሃሳብ “Values-centered Leadership” በማለት እንዲህ ይገልፁታል።

“…Leaders who move up have greater freedom to control their destinies, but also experience increased pressure and seduction. …[They] can avoid these pitfalls by devoting themselves to personal development that cultivates their inner compass. This requires reframing their leadership from being heroes to being servants of the people they lead. This process requires thought and introspection because many people get into leadership roles in response to their ego needs. It enables them to transition from seeking external gratification to finding internal satisfaction by making meaningful contributions through their leadership.”

ማጠቃለያ

ለሁሉም የመንግስት ባለስልጣናት፣ በተለይ ለገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች፣ አብዛኞቹ የድርጅቱ አመራሮች “በአመራር ወጥመድ” (Leadership Trap) ውስጥ ወድቀዋል። በእርግጥ በአመራር ወጥመድ ውስጥ ተጠልፈው የወደቁ አመራሮች ያለባቸው መሰረታዊ ችግር ከማህብረሰቡ የሚሰጣቸውን ትችትና አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን ነው። በተመሣሣይ፣ በዚህ ፅሁፍ የቀረበላቸውን ሃሳብና አስተያየት ተቀብለው ራሳቸውንና አሰራራቸውን ለመፈተሽ ፍቃደኛ ባይሆኑ አይገርመኝም። ይሁን እንጂ፣ የተወሰኑ ቅንና ራሳቸውን ለመፈተሽ ዝግጁ የሆኑ አመራሮች ይጠፋሉ ብዬ አላስብም።

በመሆኑም፣ ይህን ፅሁፍ ለማንበብ እድሉ የገጠማችሁ አመራሮች፤ አንደኛ፡- የምትመሩትን መስሪያ ቤት የሥራ የአፈፃፀምና የሪፖርት አቀራረብ በጥሞና በማጤን ራሳችሁንና አመራራችሁን እንድትፈትሹ፣ ሁለተኛ፡- ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በተመሣሣይ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ግፊት እንድታደርጉ እለምናችኋለሁ። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን፣ እንደ መንግስትና ሀገር አወዳደቃችን የከፋ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። ከዚህ በመቀጠል ችግሩን ለመዳሰስ የሚደረገው ጥረት ከዬትና እንዴት መጀመር እንዳለበት ለመጠቆም እወዳለሁ።

በአመራር ወጥመድ ውስጥ የወደቁ አመራሮችን በአፈፃፀም ሪፖርታቸው ውስጥ ካለው የአስመሳይነት ችግር እና በሥራቸው ከሚያሳዩዋቸው አፍራሽ ባህሪያት አንፃር በቀላሉ መለየት ይቻላል። ለምሳሌ በቅርቡ በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት በኩል ተዘጋጅቶ የቀረበው የመንግስት አመታዊ ሪፖርትን እንደ መነሻ መውሰድ ይቻላል። በዚህ መሰረት፤ በስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት (ገፅ 116)፣ የብረታ-ብረት ከርፖሬሽን ሪፖርት (ገፅ 112)፣ የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ሪፖርት (ገፅ 224-226)፣ የከተማ ልማትና የቤቶች ሚኒስቴር ሪፖርት እና የማዕድን ሚኒስቴር አመራሮች በአመራር ወጥመድ ውስጥ ስለመውደቃቸው አይነተኛ ማሳያ ነው። በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ፣ በአብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናት ከሚስተዋሉ ባህሪያት/ተግባራት ውስጥ የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡- ተዓማኒነት የጎደላቸው ውይይቶች (a lack of honest conversations)፣ ከልክ ያለፈ የፖለቲካ ጨዋታ (too much political game playing)፣ ዕርስ-በዕርስ መረጃዎችን አለመለዋወጥ (silo thinking)፣ የክትትልና ባለቤትነት ስሜት ማጣት (lack of ownership and follow-through)፣ እና መጥፎ ባህሪያትን መታገስ (tolerating bad behaviors) ናቸው። በጉዳዩ ላይ የተሰራ ጥናት እንደሚያረጋግጠው ከላይ የተጠቀሱት የአስመሳይነት ችግሮች እና አፍራሽ ባህሪያት በቀጥታ በአመራር ወጥመድ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ስለመሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል

***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories