የአ.አ ከተማ ሴፍቲኔት፡ ልመናን በብድር ማስፋፋት

ትላንት አንድ ጓደኛዬ ከአዲስ አበባ ደውሎ “ከንቲባ ድሪባ ኩማ የተናገሩትን ሰማኽ?” አለኝ። ከአነጋገሩ በጣም እንደተገረመ ያስታውቃል። ቀጠለና በአዲስ አበባ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከቀጣዩ ሀምሌ 1 ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሆነና በቀጣይ 10 ዓመታት 1.2 ሚሊዮን የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነገረኝ። ነገሩ ምንም ስላላስገረመኝ፣ “ታዲያ ምንድነው ጉዱ?” አኩት። ከቀጣዩ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሊደረግ ስለታሰበው ድጋፍ ሲነግረኝ፤ “ኧረ ጉድ ፈላ! …ይሄ ልመናን በብድር ማስፋፋት ነው!?” ብዬ ጮኹኩ። በጉዳዩ ላይ የቀረበውን የዜና ዘገባ ሳነብ የሚከተለውን አገኘሁ።

በአዲስ አባበ ቁጥራቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ከድህነት በታች እንደሚኖሩ የተነገረ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊየኑ በከተማ ሰሴፍቲ ኔት ታቅፈው በከተማዋ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል። … የከተማዋ የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ከነዚህ ዜጎች በተጨማሪ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በቀጥታ ድጋፍ የሚደረግላቸው ዜጎች ተለይተዋል። በዚህ መልኩ ከተለዩት ውስጥ በቀጣይ 10 ዓመታት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ውስጥ “መስራት የማይችሉ” ተብሎ 245 ሺህ ዜጎች የተለዩ ሲሆን፥ ለነዚህም በየቀኑ እስከ 50 ብር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ በባንክ ደብተራቸው ላይ እንደሚገባላቸው ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናግረዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ብዛት ስንት ነው? በከተማ መስተዳደሩ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የተዘጋጀ ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ብዛት 3,048,631 ነበር። ከአጠቃላዩ የከተማዋ ነዋሪ ውስጥ እድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ህፃናት (ከ14 ዓመት በታች) እና አረጋዊያን (ከ65 ዓመት በላይ) በድምሩ 832,886 ሲሆኑ ከ15-65 ዓመት የእድሜ ክልል ያለው ነዋሪ ብዛት 2,228,510 ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከከተማዋ ነዋሪ ውስጥ 2,504,853 ሚሊዮን የሚሆነው ሥራ መስራት የሚችል እንደሆነና ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1,148,974 ሚሊዮን ሥራ እንዳለው ያትታል። በጥቅሉ ሲታይ በሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ድጋፍ ያስፈልገዋል የተባለው 1.5 ሚሊየን ነዋሪ ከየት እንደመጣ ግራ ያጋባል። (በተጠቀሰው ሪፖርት ውስጥ ያለው መረጃ ደግሞ ይበልጥ ግራ የሚያጋባና እርስ-በእርሱ የሚጋጭ ነው።)

በዘገባው መሠረት በቀጣዩ በ2009 በጀት ዓመት ብቻ በየቀኑ የ50 ብር ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ብዛት 60ሺህ ሲሆኑ፣ በቀጣዩ 10 ዓመት ደግሞ 245 ሺህ እንደሆኑ ተጠቅሷል። በዚህ መሰረት፣ በቀጣዩ የ2009 የበጀት ዓመት ብቻ፤ በየቀኑ 3 ሚሊዮን ብር፣ በየወሩ 90 ሚሊዮን ብር፣ በዓመቱ ውስጥ 1.08 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል። ይህ በበጀት ዓመቱ ለከተማ ሴፍቲኔት ከተመደበው የ3.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ 30%ቱን ይሸፍናል።  ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች ብዛት 1.5 ሚሊዮን ይሁን፣ “ሥራ መስራት የማይችሉ” ምን  ማለት ነው?

ኧረ ለመሆኑ ሥራ መስራት የማይችል ሰው እንዴት ያለ ሰው ነው፤ እድሜያቸው ለሥራ ያልደረሰ ሕፃናት ናቸው? እድሜያቸው የገፋ አረጋዊያን ናቸው? የአካልና የስነ-ልቦና ችግር ያለባቸው ሰዎች ናቸው?  እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ካልሆኑ ደግሞ እነማን በሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግልፅ ይደረግ። በእርግጥ ሥራ መስራት የማይችል ሰው ራሱን-በራሱ መምራት የማይችል “በሽተኛ” ነው። ለታመመ ሰው የህክምና ድጋፍ እንጂ የኪስ ገንዘብ አይስፈልገውም። ነገር ግን፣ ከላይ ከተጠቀሱት “መስራት የማይችሉ” በሚለው ውስጥ የሚካተቱ ከሆነ ፍፁም አላዋቂነት ነው፡፡

አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት የሚያስፈልጋቸው የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋም እንጂ በየቀኑ የሚሰጥ የ50 ብር ድጎማ አይደለም። ድጋፍ ሊደረግ የታሰበው እድሜያቸው የገፋና ጧሪ የሌላቸው አረጋዊያን ከሆኑ ደግሞ ለእነሱ የሚያስፈልገው የተደራጀ የአረጋዊያን ማረፊያ ቦታና የተቀናጀ ድጋፍ ነው። የሥነ-ልቦናና ሌሎች አካላዊ ችግሮች ያጋጠማቸው ዜጎች የሚያስፈልጋቸው የህክምና እርዳታ እንጂ ለመድሃኒት መግዣ የማይበቃ የ50 ብር ዱጎማ አይደለም። አካል ጉዳተኞች ከሆኑ ደግሞ የሚያስፈልጋቸው ምቹ የመስሪያ ቦታና የሥልጠና ድጋፍ እንጂ የ50 ብር የኪስ ገንዘብ አይደለም።

ታዲያ 3 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ከተማ ውስጥ “መስራት የማይችሉ” ተብሎ የተለዩት ሩብ ሚሊዮን ሰዎች ምን ዓይነት ችግርና አፈጣጠር ያላቸው ሰዎች ናቸው? ነገር ግን፣ ከየትም ይምጡ፣ ምንም ዓይነት ችግር ይኑርባቸው፣ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሊደረግ የታሰበው የከተማ ሴፍቲኔት ድጋፍ በሚከተሉት ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች የተቀመጠለትን ግብ አይመታም።

1ኛ) ውጤታማነት፡- በእርግጥ የሰው ልጅ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጤንነቱን እንዲያሻሽል ድጋፍ ያስፈልገዋል። በዚህ ረገድ ከመንግስት የሚጠበቀው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበትን የተቀናጀ አደረጃጀትና የተቀላጠፈ አሰራር መዘርጋት ነው፡፡  ይሁን እንጂ “መስራት ለማይችሉ” ዜጎች በሚል ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ግን ውጤታማ አይደለም። በመሰረቱ ሥራ መስራት የማይችል “ጤነኛ” ሰው አይደለም። እንዲህ ያለ ሰው ካለ ሲጀመር ጤነኛ ስላልሆነ የሚያስፈልገው የሕክምና ድጋፍ እንጂ የኪስ ገንዘብ አይደለም። በዚህ መልኩ የሚደረግ ድጋፍ ሌላኛው ችግር ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። በጣም ሥር የሰደደ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ባለበት ሕብረተሰብ ውስጥ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ ሙስናና አድሏዊ አሰራር በሰፈነበት አስተዳደራዊ ሥርዓት ውስጥ በዚህ መልኩ የሚደረግ ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

2ኛ) አዋጭነት፡- ለከተማ የሴፍቲኔት ፕሮጀክት እንዲውል ከተመደበው 9 ቢሊዮን ብር ውስጥ 6ቢሊዮን ብር የተገኘው ከዓለም ባንክ በተሰጠ ብድር ነው። በመርሃ-ግብሩ መሰረት “መስራት የማይችሉ” ተብለው ለተለዩ ዜጎች በየቀኑ የሚደረገው የ50 ብር ድጋፍ ከጠቅላላ በጀቱ 30%ቱን ይሸፍናል። በዚህ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ ለእለት ፍጆታ ከመዋል የዘለለ የሚጨምረው እሴት የለም። ነገር ግን፣ በብድር የተገኘ ገንዘብ ወለድን ጨምሮ የተለያዩ ወጪዎች አሉት። በተለይ ይህ ገንዘብ እንደ ግብርናና ኢንዱስትሪ ባሉ ዘርፎች ላይ ቢውል ኖሮ ይገኝ ከነበረው ተጨማሪ ዕሴት አንፃር ሲታይ (opportunity cost) በአ.አ ከተማ ሴፍቲኔት ለዕለት ፍጆታ ብቻ በሚውል መልኩ የሚደረገው ድጋፍ አዋጭነት የለውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚደረገው ድጋፍ በተቀናጀ ሁኔታ በጋራ ቢሰጥ ኖሮ ከብዛት አንፃር ይቆጥብ የነበረውን (economies of scale) ወጪ ያሳጣዋል። 

3ኛ) ዘላቂነት፡- ለአስር አመት ብቻ የሚቆይ፣ ያውም በብድር ገንዘብ የሚደገፍ እና ለዕለታዊ ፍጆታ የሚውል ድጋፍ የሚያደርግ ፐሮጀክት ዘላቂነት የለውም። እንዲህ ያሉ የማህበራዊ ዋስትና ፕሮግራሞች በጀት መሸፈን ያለበት በቋሚ የገቢ ምንጮች መሆን አለበት። ለምሳሌ፣ ከመንግስት ሰራተኞች ወራዊ ገቢ የሚሰበሰበው የጡረታ መዋጮ በአብነት የሚጠቀስ ነው። በአጠቃላይ ግን፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ዲሪባ ኩማ በገለፁት መሠረት ሊደረግ የታሰበው የ50 ብር ድጋፍ ዛላቂ የሆነ ልማትና ለውጥ አያመጣም። ከዚህ ይልቅ በብድር ገንዘብ ልመናን እንደማስፋፋት ይቆጠራል።

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories