ልማትና ዴሞክራሲ፡ የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና – ክፍል 3

በ ባለፈው ክፍል ሀገራችን ኢትዮጲያ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ለመውጣት የምታደርገው ጥረት በዋናነት በማህበራዊ ልማት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አይተናል፡፡ ለዚህም በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ያሉና ለተፋጠነ ልማትና እድገት ምቹ “ያልሆኑ” ማህበራዊ እሴቶችን፣ ልማዶችንና ደንቦችን መቀየር ወይም መለወጥ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ መታየት ያለበት ነገር፣ “እንደ ኢትዮጲያ ባለ ሀገር ውስጥ፤ የእርስ-በእርስ ጦርነት ለረጅም ግዜ ሲያምሳት በቆየች፣ በድንቁርና ክፉኛ በተጎዳች ሀገር፣ ህዝቡ ድህነትን እንደ ቋሚ ሁኔታ በተቀበለበት፣ እንዲሁም፣ እነዚህን ማህበራዊ እሴቶች ለማዳበር የካፒታል ሆነ የጥሬ-ዕቃ እጥረት ባለበት ሀገር፣ እንዴት ‘ማህበራዊ ልማት ግንባታን ማካሄድ ይቻላል?” የሚለው ነው፡፡ በዚህ ክፍል፣ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በጉዳዩ ላይ የነበራቸውን አቋምና አመለካከት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

በመሰረቱ፣ ማህበራዊ ዕሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች እንደ ሁኔታው የሚቀያየሩ እንጂ ቋሚ ውርሶች አይደሉም፡፡ እንደ ጠ/ሚ መለስ አገላለፅ “በሕይወት ውስጥ በሚያጋጥመው የነገሮች መለዋወጥ ምክኒያት ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶች እና ደንቦች እንደ አዲስ የሚፈጠሩ፣ የሚቀረፁ፣ እንዲሁም በድጋሜ ሊፈጠሩ እና ሊቀረፁ የሚችሉ እንጂ ቋሚና የማይለወጡ የማህብረሰብ ውርሶች አይደሉም፡፡ ነገር ግን፣ በተለያዩ የሕይወት አጋጣሚዎች ምክንያት እንደ አዲስ ሊፈጠሩና ሊቀየሩ የሚችሉ ከሆነ ከድህነትና ረሃብ በላይ አስከፊ የሆነ ነገር ከቶ ምን አለ? ለዘመናት እድገት-አልባ ጉዞ ስንጓዝ፣ በድህነት አረንቋ ውስጥ ስንዳክር…፣ እንዴት ድህነትና ኋላ-ቀርነትን የሚጠየፍ ትውልድ መፍጠር ተሳነን? እንዴት ከድህነትና ኋላ-ቀርነት ለመውጣት የሚያስችሉ ለውጥና መሻሻልን የሚያበረታቱ፣ ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ ዕሴቶችን ሳይፈጠሩ ቀሩ?

አቶ መለስ፣ ማህበራዊ ልማትን እንዴት መገንባት እንደሚቻል፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን እና ኢጣሊያን እንደ ማሳያ በመውሰድ አብራርተዋል። እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ ማህበራዊ ልማትን መገንባት የሚቻለው ሕብረተሰቡን እርስ-በእርስ በማደራጀት እና የጠበቀ የግንኙነት መረብን በመፍጠር፣ በተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ለእድገቱ ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች እንዲፈጠሩና እንዲሰርፁ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ታዋቂው ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ (Friedrich Nietzsche) “Thus Spake Zarathustra” በሚለው መፅሃፉ፣ እሴት የሚፈጠረው በመጀመሪያ በግለሰብ ደረጃ እንደሆነ፣ በመጨረሻ ግን ግለሰብ ራሱ የፈጠራ ውጤት እንደሚሆን ይገልፃል፡፡ የሌሎች ሀገራትን ልምድና ተሞክሮ መውሰድ ጠቃሚነቱ ባያጠራጥርም፣ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው የአውራ አምባ ማህብረሰብ፣ አቶ መለስ ከጠቀሷቸው ምሳሌዎች በተሻለ ሁኔታ በሀገራችን የሚያስፈልገውን ማህበራዊ ልማት፣ እንዲሁም የፍሬድሪክ ኒቼን የዕሴት አፈጣጠር ሂደት በተግባር የሚያሳይ ነው።

Photo - Zumra Nuru founder of Awra amba community
Photo – Zumra Nuru founder of Awra amba community

የአውራ አምባ ማህብረሰብ ማህበራዊ ዕሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች ለልማትና ዕድገት ምቹ ከመሆናቸው በተጨማሪ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ፍትህና እኩልነትን የሚያረጋግጡ ናቸው። ነገር ግን፣ የማህብረሰቡ የጋራ መገለጫ እሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች ከመሆናቸው በፊት፣ በመጀመሪያ የማህብረሰቡ መስራች የክቡር ዶ/ር ዙምራ ኑሩ የግል እምነት፣ መርህና መመሪያ ነበሩ። በ1972 ዓ.ም እነዚህ የግለሰቡ የሞራልና የዕውቀት ስብዕና ውጤቶች በ19 የአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘታቸው የቡድን የጋራ እምነት፣ መርህና መመሪያ ሆኑ። በመቀጠል፣ በሁሉም የማህብረሰቡ አባላት ዘንድ እንዲሰርፁና ተቀባይነት እንዲያገኙ በማድረግ፣ በአሁን ሰዓት ከ400 በላይ የሚሆኑ የማህብረሰቡ አባላት የጋራ መገለጫ ለመሆን በቁ፡፡ የመስራቹ ዶ/ር የዙምራ የግል ስብዕና በአብዛኛው የማህብረሰቡ አባላት ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሌሎች አባላት፣ በተለይ ወጣትና ህፃናት በተጠቀሱት ማህበራዊ ዕሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች ታንፀው የሚያድጉ ይሆናል። በዚህም የግለሰቡ የግል ስብዕና፤ በመጀመሪያ የቡድን፣ ቀጥሎ የማህብረሰብ የጋራ መገለጫ እየሆነ ከሄደ በኋላ፣ ኒቼ እንዳለው፣ በመጨረሻ “ግለሰብ ራሱ የፈጠራ ውጤት እንደሚሆን በግልፅ ያሳያል።

አቶ መለስ ዜናዊ በፅሁፋቸው እንደ ምሳሌ ካነሷቸው አንዱ የደቡብ ኮሪያ የማህበራዊ ልማት ግንባታ ሂደት ነው። በዚህ ረገድ፣ ደቡብ ኮሪያኖች አሁን ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፆ ያለው የሥራ ባህላቸው እንደሆነ በመጥቀስ ይህንንም ከጃፓን ኢምፔሪያሊዝም አገዛዝ እንደወረሱት ይጠቅሳል። በዚህ ረገድ፣ የአቶ መለስ ዜናዊ ፅሁፍ፣ ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ የማህበራዊ ዕሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች በአስተዳደራዊ መዋቅር እንጂ፣ በግለሰብ ደረጃ፥ በግል የሞራል ስብዕና እና ግንዛቤ ላይ ተመስርተው የሚፈጠሩ እንደሆነ አያሳይም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ለብዙ ዘመናት በኢትዮጲያ ውስጥ አስፈላጊውን የማህበራዊ ልማት እንዳይገነባ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት የሚያስችል ጥልቀትና ድፍረት የለውም።

በቀጣዩ ክፍል-4፣ የአውራ አምባ ማህብረሰብን የተግባር ተሞክሮ ከአውሮፓ የህዳሴ ዘመን እንቅስቃሴ እና ከጃፓን ሥልጣኔ ጋር በማቀናጀት በኢትዮጲያ ማህበራዊ ልማት ግንባታ ከየትና እንዴት መጀመር እንዳለበት በከፊል እንመለከታለን።    

ይቀጥላል…
***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories