ልማትና ዴሞክራሲ፡ የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና – ክፍል 2

በባለፈው ክፍል ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶች እና ደንቦች ለአንድ ሀገር ብልፅግናና እድገት ወሳኝ የሆኑ ማህበራዊ ካፒታል (Social capital) ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ሀገራት ዘላቂ ልማትና ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግቡ በቅድሚያ እነዚህ ማህበራዊ ሃብቶች በሚፈለገው ደረጃ ሊኖሯቸው ይገባል፡፡ ይህ ክፍል በዋናነት በሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በቅድሚያ “እንደ ኢትዮጲያ ላሉ ሀገራት የተጠቀሱት ማህበራዊ ዕሴቶች አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ በመቀጠል፣ “እንደ ሀገር ለተፍጠነ ልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶች እና ደንቦች አሉን ወይ?” የሚለውን ጥየቄ እንመለከታለን፡፡ (ለተፋጠነ ልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶች እና ደንቦችን በዝርዝር ለማየት ይህን ሊንክ ይጫኑ፡- ልማትና ዴሞክራሲ፡ የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና – ክፍል-1)፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ ልማትና እድገት እንዲኖር፣ በዚህም የሀገሪቱ ህዝብ ቁሳዊ ሃብትና ጥቅም እንዲያገኝና የተሻለ ሕይወት እንዲኖር በቅድሚያ ለተፋጠነ ልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ሊኖሩ ይገባል፡፡ ለዚህም የዘርፉ ባለሞያዎች አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ የሚጠቅሱ ሲሆን፣ እነሱም፡- 

1ኛ፡- ለተፋጠነ እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች ለሀገር እድገትና ብልፅግና ግብዓት ከመሆን አንፃር ልክ እንደ መንገድ፣ መብራት፣ እና መገናኛ (ቴሌኮሚኒኬሽ) ቁልፍ የሆኑ “ማህበራዊ መሰረተ ልማት” (Social infrastructure) ስለሆኑ፣

2ኛ፡- አንድ ግዜ በሕብረተሰቡ ውስጥ ከሰረፁና በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ሥረዓት፣ በተለይ በመንግስት እና በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት በግልፅነት እና መተማመን ላይ የተመሰረተ እና ውጤት-ትኮር እንዲሆን ስለሚያስችሉ፣

3ኛ፡-እነዚህን ማህበራዊ ሃብቶች ለማዳበር የሚጠይቀው ወጪ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ባሉ ሀገራት ዘንድ በቀላሉ የማይገኙት እንደ ቴክኖሎጂ እና ካፒታል ያሉ ግብዓቶች ከሚጠይቁት ወጪና አቅርቦታ አንፃር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣

4ኛ፡- እነዚህ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች ሁሉን-አቀፍ እና በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት ስለሚኖራቸው የሀገሪቱን እድገት ቀጣይነት ስለሚያረጋግጡ፣ እንዲሁም

5ኛ፡- በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሀገራት እድገትና ብልፅግና አስፈላጊ እና በቂ (necessary and sufficient) የሆኑ ግባዕቶች ስለሆኑ ነው፡፡    

ከላይ በዝርዝር ከተጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች፣ የማህበራዊ ልማት ግንባታ ወይም የመልካም ማህበራዊ ዕሴቶች ማዳበር (social development or Social capital accumulation) ለአንድ ሀገር ልማትና እድገት ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ያሳያሉ፡፡ እዚህ’ጋ ሁለተኛውን ጥያቄ እናንሳ፡፡ አሁን በኢትዮጲያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ለፈጣን ልማትና እድገት የሚያስፈልገው ማህበራዊ ካፒታል አለ? በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያበረታቱ ማህበራዊ ዕሴቶች አሉን? ለምሳሌ፣ እንደ ከፍተኛ የሥራ ፍቅር እና ልማድ፣ ክፍተኛ የሆነ በእራስ የመተማመን መንፈስ፣ እራስ የመቻል፣ በየግዜው እራስን ማሻሻል፣ አዲስ ነገር የመፍጠር ፍላጎትና ተነሳሽነት፣ ከሌሎች ለመማር እና ልምድን ለማካፈል ፍቃደኛ መሆን፣ ቁጠባ እና የመሳሰሉት እምነቶች፣ መርሆች እና መመሪያዎች በየትኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ነው ያሉት?

በመሰረቱ፣ የኢትዮጲያ የኋላ ታሪክ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ለረጅም ዘመናት በድህነትና ኋላ-ቀርነት አረንቋ ተዘፍቃ የቆየች መሆኑ፣ ሀገሪቷ ለልማትና እድገት አስፈላጊ የሆኑት መልካም ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች በሚፈለገው ደረጃና ስፋት እንዳልነበሯት የሚያሳይ ነው፡፡ “የቀድሞው የኢትዮጲያ ታሪክ በዚህ ዘመን ተሸሯል” እንዳይባል አሁንም በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ያሉት ማህበራዊ ዕሴቶች ለለውጥና ሥራ ምቹ አይደሉም፡፡ “ከፍተኛ የሆነ የሥራ ፍቅር እና ልማድ አለ” እንዳይባል፣ በወሩ ውስጥ ሥራ ከምንሰራበት ቀን የማንሰራበት ይበልጣል።

ለአብዛኛው ኢትዮጲያ ስኬት እና ውድቀት የዕድለኝነት እንጂ የብቃት ውጤት አይደለም፡፡ ሙሉ የራስ መተማመን መንፈስ ያለው ኢትዮጲያዊ፣ በቴሌቪዥን ሳይሆን በአካል አጋጥሟችሁ ያውቃል? በራስ የመተማመን ባህሪይ ያለውን ሰው “ጉረኛ፣ እዩኝ-እዩኝ ባይ!….” በማለት አላወገዝነውም? …በየግዜው እራሱን ለማሻሻል የሚተጋን ግለሰብ “ገብጋባ፣ ስግብግብ፣ ስስታም፣ ቆንቋና፣ ሰላቢ፣ ሌባ፣…ወዘተ” አላልነውም? “አዲስ ነገር ፈጠርኩ…እዩልኝ፣ ሞክሩልኝ፣ አድንቁልኝ፣…” አያለ የመጣን ሰው፣ “ይሄ’ማ ድሮ እኔ አውቄ – ንቄ የተዉኩት ነው” ብለን ተነሳሽነቱን አላጣጣልነውም? …‘በኣለማወቃችን ኮርተን ከሌሎች ለመማር ፍላጎትና ተነሳሽነት ጭራሽ ኖሮን ያውቃል እንዴ?’ …“ኑ ልምዴን ላካፍላችሁ” የሚልን ሰው “አንተ ምን ታውቅና!” ብለን ዕውቀትና ክህሎቱን “የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ እንዲቀር አላደረግነውም?

ኧ…ረ ለመሆኑ፣ መልካም የሆኑ ማህበራዊ እሴቶቻችን የትኞቹ ናቸው? ..ካሉን የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከማምጣት አንፃር እውነት “ምቹ” የሚባሉ ናቸው?

በእርግጥ አብዛኛው ሰው የመቻል ፉከራ ሳይሆን የማቃት ስርቅርቅታ እያሰማ በሚያልፍባት ሀገር፣ ድህነትና ኋላ-ቀርነት አምሳሏ፣ ድርቅና ርሃብ መገለጫዋ የሆነች ሀገር፣… ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች አሏት ሊባል አይችልም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ለልማትና እድገት ማነቆ፣ ለለውጥና መሻሻል እንቅፋት የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች እንዳሉ ጠቋሚ ነው፡፡ እነዚህ አስከፊ የህይወት ገፅታዎች ለወደፊት የሀገሪቱ መገለጫ ሆነው እንዳይቀጥሉ ከተፈለገ፣ ለፈጣን ልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶች እና ደንቦችን መፍጠር፣ ማዳበርና ማስረፅ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጲያ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ለመውጣት አስፈላጊውን ማህበራዊ መሰረተ-ልማት መገንባት አለባት፡፡ ይህም፣ በአብዛኛው በማህብረሰቡ ዘንድ ያሉና ለተፋጠነ ልማትና እድገት ምቹ “ያልሆኑ” ማህበራዊ እሴቶችን፣ ልማዶችንና ደንቦችን ማሻሻል፣ መቀየር ወይም መለወጥ ይጠይቃል፡፡ በቀጣዩ ክፍል-3፣ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ ማህበራዊ እሴቶችን እንዴት መፍጠርና መቀየር እንደሚቻል የሰጡትን ትንታኔን እንደ Thomas Hobbes፣ Friedrich Nietzsche እና ከመሳሰሉት ፈላስፋዎች ሥራዎች አንፃር በመቃኘት በመለስ ዜናዊ ፍልስፍና ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመጠቆም እንሞክራለን፡፡

ይቀጥላል…
***********

 

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories