ባርነት ልማድ በሆነበት ዴሞክራሲ ቅንጦት ይሆናል!

ሺህ አለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ “As an African citizen democracy is a luxury” በሚል ለቢቢሲ ሬድዮ ጋዜጠኛ የሰጠው አስተያየት በማህበራዊ ድረገፆች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ትላንት በጉዳዩ ላይ የራሴን አስተያየት ሰጥቼ ነበር። ሆኖም ግን፣ አንዳንድ ጓደኞቼ የሃይሌ አስተያየት ትክክል ነው የሚል አቋም ሲያራምዱ ታዝቤያለሁ።

“ለአንድ አፍሪካዊ ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው” የሚል ጭብጥ ያለውን አስተያየት ትክክል ነው ብሎ ማሰብ በራሱ ስሁት ከመሆኑም በላይ አፍሪካዊያንን የሰውነት ክብር የሚያሳጣ እሳቤ ነው። እኔ በግሌ የሰውነት ክብሬ ተገፍፎ ከተራ ግዑዝ ፍጥረት ተርታ መሰለፍ አልሻም። ስለዚህ፣ በዚህ ፅኁፌ “ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው” የሚሉ ሰዎች ባርነትን እንደ ልማድ የተቀበሉ፣ የነፃነትን ትርጉምና ፋይዳ የማያውቁ ስለመሆናቸው ለማሳየት እሞክራለሁ።

በእርግጥ ኢህአዴግ አምባገነኑን ደርግ በማስወገድ የዲሞክራሲያዊ እሴቶችን መሰረት ያደረገ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ዘርግቷል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ለመንቀሳቀስ የሚሞክር ግለሰብ ወይም ቡድን በሕገ-መንግስቱ ስም ከስራ ይባረራል፣ ለእስር፣ ስደትና ሞት ይዳረጋል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ በመኖሬ የጣኹት ነገር ምንድነው? ብዙም ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ሳያስፈልግ፣ ይህን ፅሁፍ ብቻ መነሻ አድርጎ “ሕገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ አሲሯል” በሚል ዘብጥያ ሊያወርደኝ ይችላል።

ለምሳሌ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ሃሳቤን በነፃነት ስለገለፅኩ ብቻ ለ8 ወር ያህል ግዜ ኢንተርኔት እንዳልጠቀም ታግጄያለሁ። ሁለተኛ፣ ጥናታዊ ፅሁፍን በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በማውጣት የአንድ ሚኒስተር ድኤታን ሃሳብ ተቃውሜ ስለተከራከርኩ ብቻ በመስሪያ ቤቴ በኩል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል። በዚህም እንደ አንድ የከፍተኛ ት/ት ተቋም ሰራተኛ መስራት ያለብኝን ሥራ ስለሰራሁ ብቻ ከሥራዬ እንድባረር ተፈርዶብኝ ነበር፡፡ ሥራዬን ላለማጣት “እብድ…የቀን-ጅብ….” እያለ በጣም ብዙ ፀያፍ ስድቦችን በይፋ የሰደበኝ ባለስልጣን በራሴ ወጪ አዲስ አበባ ድረስ ሄጄ ይቅርታ እንድጠይቅ ተገድጄያለሁ፡፡ ይህም ሆኖ “አንተ እድለኛ ነህ!” የሚባልበት ሀገር ነው ያለነው፡፡ ብዙዎች እንደኔ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ ብቻ፣ መብታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ከሀገር ተሰደዋል፣ በእስር-ቤት ማቅቀዋል፣ በመማቀቅ ላይ’ም ይገኛሉ። ሌሎች ነገሮችን ወደ ጎን ትተን፣ እነዚህ የህይወት አጋጣሚዎች ብቻ የኢትዮጲያ መንግስት ጨቋኝ ስለመሆኑ ማሳያ ናቸው።

Image - democracy

ስለዚህ፣ በእንዲህ ያለ አስተዳደራዊ ሥርዓት ውስጥ መኖሬ ያጣሁት ነገር ምንድነው? ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የእኔና የጓደኞቼ ተፈጥሯዊ መብት፦ በነፃነት የማሰብ፣ የመናገርና የመፃፍ መብታችንን ተነፍገናል። በአጠቃላይ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታችን በኢህአዴግ መንግስት ተጥሷል። በተቃራኒው፣ “ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት” የእነዚህ መሰረታዊ መብቶች የሚከበሩበት አስተዳደራዊ ሥርዓት ነው፡፡ “ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው” የሚለው አመለካከት ነፃነትን (ሰብዓዊ መብትን) እንደ የቄንጠኞች መለያ ባህሪያት አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የሰው-ልጅን ተፈጥሯዊ ባህሪ በጥልቀት ለሚያጠና ነፃነት መብት ብቻ ሳይሆን ሰውነት (ሰው መሆን) እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ፣ “ለአንድ አፍሪካዊ ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው” ማለት ይህ ሰው እንኳን የተሻለ ሕይወት የመኖር መብቱ ይቅርና እንደ ሰው የሰብዓዊነት ክብር አይገባውም እንደማለት ነው፡፡

በመጀምሪያ፣ “ሰው” የሚለው ቃል “ሰብ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን “ሰብዓዊ” የሚለው ቃል ደግሞ የሰው-የሆነን ነገር ያመለክታል። በመሆኑም፣ “ሰብዓዊ መብቶች” የሚለው “የሰው መብቶች” ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ፣ “ሰብዓዊ-መብት” ሲባል፣ ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ የሚገኙ መብቶች ናቸው፡፡ በመቀጠል፣ በእንግሊዘኛ “human rights” የሚለው ሐረግ ብንወስድ “የእያንዳንዱ ሰው ‘ነፃ’ የመሆን መብት” የሚል ትርጓሜ አለው። ስለዚህ ነፃነት ለሰው-ልጅ መብት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ መለያ ባህሪው ነው፡፡

“ሰብዓዊ መብቶች” ሲባል ‘ሰው-ሆኖ በመወለዱ ብቻ የሚገኙ መብቶች’ እንደሆኑ እርግጥ ነው። “ሰው-ሆኖ በመወለድ ብቻ” የሚለው ሐረግ የተጠቀሰው መብት “ሰው-ከመሆን” ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑ ይጠቁማል። ምክንያቱም፣ የ“ሰብዓዊ-መብት” ባለቤት ለመሆን በቅድሚያ “ሰው-መሆን” ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ፣ “ሰብዓዊነት” (humanity) የሚለው ቃል ደግሞ “ሰው-መሆን፣ የሰብዓዊነት/የሰውነት መለያ ባሕሪያት ወይም ብቃቶች’ የሚል ትርጓሜ አለው። ነገር ግን፣ “ሰብዓዊነት” በሚለው ስር የተገለፀው የሰው-ልጅ መለያ ባህሪ ወይም ልዩ ተፈጥሯዊ ብቃት ምንድነው?

ማንኛውም ግለሰብ አንድን ነገር በእራሱ ፈቃድ ለመፍጠር ወይም ለማድረግ የሚያስችለውን አካላዊ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት፣ በቅድሚያ በጉዳዩ ላይ ሃሳባዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም፣ በተወሰነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ከመሆኑ በፊት ስለ እንቅስቃሴው ማወቅ አለበት። ሰው አንድን ተግባር በፈቃዱ ለመከወን ማሰብ ያለበት ሲሆን፣ ስለ ተግባሩ ለማሰብ ግን በቅድሚያ ፍቃደኛ መሆን አለበት። ስለዚህ፣ ለመፍቀድ ማሰብ – ለማሰብ ፍቃደኛ መሆን አለበት፣ ለማወቅ መፍቀድ – ለመፍቀድ ማወቅ አለበት። በዚህ መሰረት፣ ፈቃድ (will) እና መረዳት (understanding) የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ናቸው።

ሰው፣ አንድን ተግባር በፈቃዱ ለማከናዎን መረዳት፣ ተግባሩን ለመረዳት ደግሞ በቅድሚያ መፍቀድ ካለበት፣ ፈቃድ እና መረዳትን በተናጠል ማየት አይቻልም። በመሆኑም፣ ፈቃድን ከመረዳት ወይም መረዳትን ከፈቃድ መነጠል እስካልተቻለ ድረስ፣ ሁለቱን በጥምረት ማየት ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው፣ ፈቃድ እና መረዳትን እንደ መነሻ ምክንያት፣ የሁለቱን ድምር ውጤት በማጥናት ይሆናል። ከፈቃድ እና መረዳት ጥምረት የሚፈጠር ወይም የሁለቱ ድምር ውጤት የሆነው የሰው-ል ተፈጥሯዊ “ነፃነት” (liberty) ነው።

በነፃነት የማሰብ፣ የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራትና የመጠቀም መብቶች ለማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የተሰጡ ናቸው። ስለዚህ ሰብዓዊ መብቶች በዋናነት የሰውን ነፃነት በማስከበር ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው። መብት ማለት አንድ ሰው ወይም አካል በአንድ ነገር ወይም ጉዳይ ላይ የሚፈልገውን ለማድረግ ሆነ ላለማድረግ የሚያስችለው ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ ሰው በሰብዓዊነት እና በሕግ ያገኛቸው መብቶች የፍላጎት እና የምርጫ ነፃነትን በመጠበቅ ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት ሁሉን-አቀፍና ምሉዕ የሆነ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሲሆን መብት ደግሞ ከዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪ የመነጨ መርህ ነው። ነፃነት ፍላጎትና ምርጫ ጥምር ውጤት፣ የመብትና ግዴታ እኩሌታ ነው።

በአጠቃላይ፣ ሁሉም ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ተቋማት የተመሰረቱት የሰውን መሰረታዊ መብት፣ ነፃነትን ለማክበርና ለማስከበር እንዲቻል ነው። የተለያዩ የመንግስት አካላት፤ ሕግ አውጪዎች፣ አስፈፃሚዎችና ትርጓሚዎች፣ የሞያና ሲቭል ማህበራት፣ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ በአጠቃላይ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ስለ “ነፃነት” የጠራ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል። ከተቋማዊ መዋቅሮች ባለፈ፣ ሕይወትን በነፃነት መምራት የሚሻ ማንኛውም ግለሰብ፣ ስለ ነፃነት አጥብቆ በመጠየቅ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ሊያዳብር ይገባል። ምክንያቱም፣ ነፃነትን ማወቅ፣ ማክበርና ማስከበር የሰለጠነ ማህብረሰብ መገለጫ፣ የዳበረ ፖለቲካዊ ሥርዓት ማሳያ ነው። ይህ ሲሆን፣ በተለያዩ አዋኞች፣ የሕግ አንቀፆች፣ ደንቦችና የአፈፃፀም መመሪያዎች የሰዎች ነፃነት እንዳይጣስ የሚታገልና የሚያታግል ንቁ የፖለቲካና ሲቪል ማህብረሰብ እንዲኖር ያስችላል።

የጋራ ግንዛቤ ባልዳበረበት የሕብረተሰብ ክፍል ነፃነት በተፈጥሮ የተቸረው መሆኑ ይዘነጋና እንደ ቁሳዊ ንብረት በሰዎች – ለሰዎች ይቸረቸራል።

ነፃነትን ለመጠየቅም ሆነ ለመገንዘብ መማር…መመራመር ሳይሆን ሰው መሆን ብቻ በራሱ በቂ ነው።

*************

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories