“The Constitution is right, You are fired, or jailed, or exiled, or dead!” – Constitutional Fanaticism

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 28/2008 ባደረገው ልዩ ስብሰባ “ልዩነት”ን የሚያጠፋ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የምክር ቤቱ ውሳኔ በሀገራችን ኢትዮጲያ፤ ልዩነት እንደ የሞያ ሥነ-ምግባር ጉድለት፣ ምክንያታዊነት እንደ ጥፋት፣ ጥያቄ እንደ ወንጀል የሚቆጠርበት… በሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ውስጥ መዘፈቋን በግልፅ ያረጋገጠ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ፣ ምክር ቤቱ ሦስት የፌዴራል ዳኞችን ለማባረር ያሳለፈውን ውሳኔ፣ ከፅንፈኛ አክራሪዎች ተግባርና መርህ ጋር ያለውን ተያያዥነት በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡ “ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት” የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ለመረዳት እንዲያመቸን ግን በቅድሚያ “ፅንፈኝነት ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ በመስጠት እንጀምር። 

“ፅንፍ” (ጥንፍ) …ፅንፈኛ…ፅንፈኝነት…፡፡ ቃሉ “ጠንፍ” ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ”ዳርቻ፥ ጠርዝ” እንደማለት  ነው፡፡ በዚህ መሰረት፣ ፅንፈኝነት በተቃራኒ አቅጣጫ ፅንፍ (ጠርዝ) ላይ መቆም፡ መገኘት ነው። “ፅንፈኛ” ሲባል ደግሞ ከተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል እምነትና አመለካከት ተቃራኒ ፅንፍ ወይም ጠርዝ ላይ የቆመ እንደማለት ነው፡፡

ፅንፈኝነት ግለሰባዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሊኖር አይችልም፡፡ ሰው በግሉ በሚያደርገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሆነ አመለካከት ፅንፈኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ፅንፈኝነት ማህበራዊ ነው፡፡ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች እና ግንኙነቶች ውስጥ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም፣ ፅንፈኝነት የግል እምንትና አመለካከትን ወደ አንድ ተቃራኒ ጥግ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሕብረተሰቡ አባላት በተመሳሳይ ጠርዝ ላይ እንዲሰለፉ ማስገደድ ወይም አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠር ነውና፡፡ በመሆኑም፣ ፅንፈኝነት የማህብረሰቡ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ፣ በተለይ የጋራ ጉዳዮቻችን በሚወሰንበት “ፖለቲካ” እና የጋራ በሆነው “ሃይማኖት” እቅፍ ውስጥ ያድጋል፡፡ በዋናነት ፖለቲካ እና ሃይማኖት የፅንፈኝነት ዋና መፈልፈያ እና መሸሸጊያ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ የትኛውም ሃይማኖት፣ ወይም የትኛውም ሀገር ፖለቲካ ቢሆን፣ ከመጠጊያነትና መሸሸጊያነት አልፎ የፅንፈኝነት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። የፅንፈኝነት ምንጩ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ “ጭፍን አገልጋይነት” (Unquestioned Servitude) ነው።

Photo - Ethiopian parliament

“Those who are one eyed would like others to be the same” የሚለው የሩሲያዊን አባባል የፅንፈኞችን መርህና ተግባር ጥሩ አድርጎ ይገልፀዋል። ፅንፈኝነት አንድን እምነትና አመለካከት ያለ በቂ ምክንያታዊ ግንዛቤ በጭፍን መቀበልና ማራመድ፣ ብሎም በሌሎች ላይ መጫን ነው። ፅንፈኞች፤ ከምሉዕነት ይልቅ ነጠላነትን የሚዘምሩ ናቸው። ሃሳብና ተግባራቸው ስለእውነትና ትክክለኝነት ሳይሆን ምክንያታዊነትንና ልዩነትን ስለማጥፋት ነው። “የትኛው ሃሳብና ተግባር ትክክል ነው?” የሚለውን ሁለትዮሽ ውይይት በጭራሽ አይፈቅዱም። “እኔ ትክክል ነኝ፣ እነሱ ግን ተሳስተዋል” በሚል ከራሳቸው ጋር እንኳን ለመወያየት አይፈቅዱም። በአጠቃላይ፣ ፅንፈኛ ሰው እንኳን የተለየ እምነትና አመለካከት ከሚያራምዱ ሌሎች ሰዎች ይቅርና ከራሱ ጋር እንኳን ለመወያየት ድፍረት የለውም።

ፅንፈኞች የሚመሩበት መርህና ተግባራቸው አንድ ዓይነትና ተመሣሣይ ነው። እንደ ናጄሪያዊው ገጣሚ ሎሬት Wole Soyinka አገላለፅ፣ የፅንፈኞች መርህና መመሪያ፣ “I am right, you are Dead!” የሚል ነው። ፅንፈኛ ትክክለኙነትን የሚያረጋግጠው አንተን ወይም ሌሎችን ገድሎ ወይም የግድያ ሙከራ አድርጎ ነው። በአጠቃላይ፣ ፅንፈኞች እምነትና አመለካከታቸው በሌሎች ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ እንዲያገኝ የሚያደርጉት በማህብረሰቡ ውስጥ የፍርሃት ቆንፈን በማስፈን ነው። ለምሳሌ፣ ISIS የሚባለውን የፅንፈኛ አሸባሪዎች ተቋም በኢትዮጲያኖች ላይ ሊቢያ ውስጥ የፈፀመውን ዘግናኝ ተግባር እናስታውስ። ለኢትዮጲያኖቹ የቀረበላቸው ብቸኛ ጥያቄ “Are you a Christian or Muslim?” የሚል ነበር። ምላሹ’ስ “I am right, you are dead!”

እዚህ’ጋ፣ “ከላይ የተገለፀው የአሸባሪዎች መርህና ተግባር ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ከሆነው “ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት” ሃሳብ ጋር ምን አገናኘው?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አግባብ ነው። በአክራሪዎች ፅንፈኝነት እና በሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት መካከል ያለውን ተያያዥነት ለመገንዘብ “I am right, you are Dead,” የሚለውን የWole Soyinka አገላለፅ፣ “The Constitution is right, you are fired or jailed, or exiled, or Dead” በሚለው ዓ.ነገር መተካትና አሁን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ዕውነታ አንፃር ማየት ነው። በዚህ መሰረት፣ በኢትዮጲያ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት በአራት ደረጃዎች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።

1ኛ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 28/2008 ባደረገው ልዩ ስብሰባ፣ በተለይ ደግሞ አቶ ግዛቸው ምትኩ ከዳኝነት ሥራቸው የተሰናበቱበት ምክንያት የመጀመሪያው የሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ደረጃ ማሳያ ነው። አንድ የፌደራል ዳኛን ከዳኝነቱ ለማባረር በምክንያትነት የቀረበው “ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ የሚጠቅሱ መሆኑ፣ ለህገ-መንግስቱ ታማኝ ባለመሆናቸው…” የሚል ነው። የሀገሪቱን ህግ ተርጉሞ ወንጀልና ቅጣትን የሚወስን ዳኛ፣ “ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ መጥቀሱን” እንደ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ጉድለት ወስዶ ከዳኝነት ሥራው ማባረር የለየለት ፅንፈኝነት ነው። ይህ “The Constitution is right, you are fired!” የሚባል ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ነው።

2ኛ፦ እንደ በቀለ ገረባ “Justice!”፣ እንደ ዞን9 ጦማሪያን “Freedom” ወይም እንደ አብርሃ ደስታ “It’s So!”፣ … ብለው ነፃ ሃሳባቸውን በማህበራዊ ደረገፆች ላይ የሚገልፁ ሁሉ  “ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት፣ ነውጥና ሁከት በማስነሳት፣… ሕገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ ተንቀስቃሰዋል” በሚል ወደ ዘብጥያ ይወረወራሉ። ይህ “The Constitution is right, you are jailed!” የሚባል ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ነው።

3ኛ፦ በገዢው ፓርቲ ውስጣዊ አሰራር ላይ የተለየ አቋም የያዙ እንደ ጅነዲን ሳዶ ያሉ አመራሮች፣ ወይም የሕብረተሰቡን የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ለማዳበር ጥረት የሚያደርጉ፣ ለምሳሌ የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች፣ … “ከፀረ-ሰላምና ሽብር ሃይሎች ጋር በመመሳጠር…ሕገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ አሲረዋል” ተብለው ወደ እስር ቤት ከመወርወራቸው በፊት ሀገር ጥለው ይሰደዳሉ። ይህ “The Constitution is right, and you are Exiled” የሚባል ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ውጤት ነው።

4ኛ፦ ‘መንግስት አምባገነንና ጨቋኝ እየሆነ ነው፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩ፣ ወይም ምርጫው ተጨበርብሯል’ የሚሉ የተቃውሞ መፈክሮችን ይዘው አደባባይ የወጡ፣ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት መንገድ ላይ ጐማ እያቃጠሉ መንገድ ስለዘጉ፣ ወይም የተወሰኑት የበርና መስኮት መስታዎት ስለሰበሩ፣ … “ሕገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ በአመፅና የሽብር ተግባር ተሰማርተዋል” በሚል፣ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልልና በ97ቱ ምርጫ እንዳየነው ብዙ ሰዎች ህይወታቸው ያጣሉ። ይህ የሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት የመጨረሻ ደረጃ ሲሆን “The Constitution is right, and you are Dead” ሊባል ይችላል። 

የሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ዋና አላማ ከአምባገነንነት ጋር አንድና ተመሣሣይ ነው፦ ህዝቡን በፍርሃት ቆፈን (Climate of fear) ማቆራመድ ነው። በፍርሃት ቆፈን በተያዘ ማህብረሰብ ውስጥ ነፃ ውይይትና መረጃ በሹክሹክታና አሉባልታ ይተካል። ተግባራዊ እንቅስቃሴያችን በዕውቀት ሳይሆን በፍርሃት ስሜት ይመራል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ዜጎች ስለራሳቸው መብትና ነፃነት መከበር አይጠይቁም፣ በአስተዳደራዊ ሥርዓቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ፍትህና እኩልነት እንዲያረጋግጥ አይጠይቁም። ከዚህ አንፃር፣ የአምባገነኑ ደርግ እና ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኛው ኢህአዴግ አንድ ናቸው። ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ባለመስጠት ብቻ ሳይሆን በፍርሃት ቆፈን ተይዞ በጭራሽ ጥያቄ እንዳያነሳ በማድረግ ሁለቱ አንድ ናቸው።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ፣ በተለይ ደግሞ አቶ ግዛቸው ምትኩ በተባሉት የፌደራል ዳኛ ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ የሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ማሳያ ከመሆኑም በላይ የሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለመክተት የተደረገ ነው። ከሁለት አመት በፊት አቶ ግዛቸው ምትኩ በዳኝነት በተሰየሙበት የእነ መላኩ ፋንታ (የቀድሞው የጉምሩክ ሃላፊ) የክስ መዝገብ የተፈጠረውን ክስተት የሪፖርተር ጋዜጣ “አቶ መላኩ ፈንታ ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ውሳኔ በማረሚያ ቤት እንዲነገራቸው ጠየቁ” ሲል ዘግቦታል። በዘገባው መሰረት፣ አቶ መላኩ ፈንታ ጠበቆቻቸውን ያሰናበቱበት ምክንያት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጠበቆች ሥነ-ምግባር ደንብ፣ የአገልግሎት ውልን ስለማቋረጥ በተቀመጠው አግባብ አይደለም። የከሳሽ ምስክር ለተጠየቀው መስቀለኛ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማብራሪያ ሲሰጥና ጠበቆቹ ችሎቱ እንዲያስቆምላቸው በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው “ችሎት ተዳፍራችኋል” ተብለው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው ነው።

ጠበቆቹን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የዘፈቃቸው ማስጠንቀቂያው ሳይሆን የችሎቱ ማስጠንቀቂያ በፍትሕ ሚኒስቴር ለጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ግልባጭ መደረጉ ነበር። ከዚያ ማስጠንቀቂያ በኋላ ጠበቆቹ ለደንበኛቸው በነፃነት ሊከራከሩ እንደማይችሉ ግልፅ ነው። ከዚህ በኋላ እውነቱን ለማፈላለግ አንዳች ሙከራ ቢያደርጉ የጥብቅና ፍቃዳቸውን እንደሚቀሙ ሲያውቁ፤ ጠበቆቹ በፍርሃት ቆፈን ተዘፈቁ፣ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ በፍትህ ሥርዓቱ ተስፋ ቆርጠው እጅ ሰጡ። ነገር ግን፣ በችሎቱ ተሰይመው የነበሩት ሌሎቹ ዳኞች እንደ የአቶ ግዛቸው ምትኩ “በችሎቱ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ በቂ ስለሆነ ጉዳዩ ወደ የጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት” መሄድ የለበትም ቢሉ ኖሮ’ስ? ይህ ቢሆን፣ ጠበቆቹ’ም በፍርሃት ቆፈን ባልተያዙ፣ አቶ መላኩ ፈንታ’ም ትክክለኛ ፍርድ ባገኙ ነበር። ይሁን እንጂ፣ የዳኞቹ ስም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ከተባረሩት ዳኞች ስም ዝርዝር፣ ከእነ አቶ ግዛቸው ምትኩ ጎን ሊኖር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።

የነፃነት ታጋይዋ “Aung San Suu Kyi” እንዳለችው “A shred of democracy is more dangerous than a Dictatorship” በእርግጥ ‘ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር’ እየተባለ፤ ከተማሪ… አስተማሪ… ጦማሪ፣ ፖለቲከኛ… ጋዜጠኛ… ሰራተኛ፣ … ከአርሶ-አደር እስከ ሚኒስተር፣ ከዳኛ እስከ ቀማኛ፣ የሚባረርበት…የሚታሰርበት…የሚሰደድበት…የሚገደልበት ሥርዓት አንድነቱን ከለየለት አምባገነናዊ ሥርዓት የባሰ ነው። ይህ፣ ጭፍን አገልጋይይነት የሚያሸልምበት፣ ለውጥና መሻሻል የሚያስከስስበት፣ መብት ወንጀል፥ ነፃነት ጥፋት የሚሆንበት ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት ለሀገራችን የወደፊት ጎዞ ትልቅ ጋሬጣ ነው።
***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories