በሽረ ጦርነት ዋዜማ ሻዕቢያ ተስፋ ቆርጦ ነበር – ጄኔራል ጻድቃን [+Video]

* የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለሻዕቢያ አሉታዊ የሆነ አቋም ያለማቋረጥ ይይዙና ይወተውቱ ነበር

* የህወሓት/ኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባ ሲገባ አብሮ የመጣው የሻዕቢያ ተዋጊ ብዛት 300 ገደማ ነበር

በሕወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) የትግል ታሪክ እንደ ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰደው የ1981ዱ የሽረ ጦርነት ከመካሄዱ ጥቂት ወራት በፊት ሻዕቢያ በትጥቅ ትግሉ ስኬት ላይ ተስፋ አጥቶ እንደነበር ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ገለጹ፡፡

በሽረ አካባቢ የነበረውን የቀድሞ ሠራዊት 604ኛ ኮር በጋራ የመምታት ሀሳብ ከህወሓት በቀረበ ግዜ፤ ከሻዕቢያ የተሰጠው ምላሽ ‹‹12 ክፍለሀገር ለ2ክፍለሀገር ሞቢላይዝ እያደረገ መቼ ድል እንምናደር አናውቅም – በረጅም ተነል ውስጥ የድል ጭላንጭል አይታየንም›› የሚል እንደነበር አውስተዋል፡፡

ጄኔራሉ ይህንን የተናገሩት ባለፈው ሳምንት ባደረግንላቸው ቃለ-መጠይቅ በሕወሓት እና በተለምዶ ሻዕቢያ ተብሎ በሚጠራው (ያኔ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሕግሓኤ) አሁን ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ ለፍትሕ) በሚባለው የኤርትራው ገዢ ፓርቲ መሀል ስለነበረው ግንኙነት በሰጡት ምላሽ ላይ ነው፡፡

ከሻዕቢያ ጋር የነበረው ግንኙነት ሚዛኑን የሳተ ነው የሚለውን ክስ የማይጋሩት ጄኔራል ጻድቃን፤ ህወሓት ከአልጀሪያ እስከ ቬትናም፣ ከኩባ እስከ ቻይና ከነበሩ የትጥቅ ትግል ታሪኮች ልምድ ለመውሰድ ይሞክር የነበረ ከመሆኑ አንጻር ከጎረቤቶቹ ከሻዕቢያና ጀብሀ ልምድ መውሰዱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ስለግንኙነቱ እንደማሳያ ሁለት ክስተቶች እንዲጠቀሱ ተጠይቀው ሲመልሱ፡-

በ1973 ገሩ ስርናይ፣ በማርዲ፣ ኡናሽሀቅ፣ ወዘተ በሚባሉት የድንበር አካባቢዎች (ዛሬ አህፈሮም ወረዳ) ለገበሬው መሬት የማከፋፈል ጉዳይ አወዛግቦ የነበረበትን ታሪክ አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቃን በማዕከላዊ ኮሚቴ ተመድበው በአካባቢው ያስተባብሩ የነበረ ሲሆን ከበላያቸው ደግሞ ከፖሊት ቢሮ የተመደቡት አቦይ ስብሓት ነጋ እንደነበሩ የጠቀሱ ሲሆን፤ በሻዕቢያ በኩል ደግሞ ስብሓት ኤፍሬም እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ የሻዕቢያ ከፍተኛ አመራር የመሬት ማከፋፈል አጀንዳውን የሚቃወም ቢሆንም፤ በህወሓት በኩል፡- በኛ መሬት እንደፈለግን እናደርጋለን፣ አወዛጋቢ በሆኑት አካባቢዎች ደግሞ በሕዝብ እናስወስናለን የሚል አቋም ይዘው፣ ሕዝቡም መሬት ማከፋፈሉን የሚፈልግ መሆኑን ስለገለፀ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሻዕቢያ ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ተደጋጋሚ ክርክር ይነሳ እንደነበር ያስታወሱት ጻድቃን፤ በዋናነት ያከራክሩ የነበሩት አጀንዳዎች ሻዕቢያን ለማገዝ የሄደው የህወሓት ጦር እንዲመለስ እና ከሻዕቢያ የነበረው ግንኙነት ባሕርይ ግምገማ ላይ ነበር ብለዋል፡፡ ደርግ የቀይ ኮከብ ዘመቻ በሚል ስያሜ እና ለጥቆ ካካሄዳቸው ዘመቻዎች ሻዕቢያን ለማስጣል፤ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ 5000 ታጋዮችን የያዘ 3ብርጌድ ከተሟላ ኮማንድ ጋር ተልኮ ለ3 ዓመታት ገደማ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ የሠራዊቱ ቆይታ አብቅቶ እንዲመለስ፣ በህወሓትና ሻዕቢያ መሀል ያለው ትብብር ስትራቴጂክ ሳይሆን ታክቲካዊ ተብሎ እንዲፈረጅ እና የመሳሰሉ ሀሳቦች በተደጋጋሚ እየቀረበ ያከራክር እንደነበር ያወሱት ጻድቃን፤ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለሻዕቢያ አሉታዊ የሆነ አቋም ያለማቋረጥ ይይዙና ይወተውቱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በቃለ-መጠይቁ በርካታ ታሪካዊ ቁምነገሮችን ያነሱት የያኔው የህወሓት ሠራዊት ቺፍ ኦፍ ስታፍ ጻድቃን ገ/ትንሳኤ፤

በሽረ ለተካሄደው ጦርነት ዝግጅት ለማድረግ ከሻዕቢያ ከፍተና አመራሮች ጋር በተገናኙበት ወቅት ተስፋ ቆርጠው እንዳገኟቸው እና ፈቃደኛ እንዳልነበሩ፤ ህወሓት ተከታታይ ውጊያዎችን አካሂዶ 604ኛ ኮርን ለመደምሰስ ሲቃረብ ግን ሻዕቢያ ለመሳተፍ ፈቃደኝነት እንዳሳየ ገልፀዋል፡፡ ያም ሆኖ ሻዕቢያ የላከው ሀይል፤ 8 ወይም 12 ታንኮች፣ 8 መድፍ፣ 8 ዙ23 ብቻ የያዘ እና እግረኛ ተዋጊ ግን ያላካተተ እንደነበር ጠቅሰው፤ ገና መንገድ ላይ እያለ ደርግ 4 ታንክ አቃጥሎበት መሸሹን አስታውሰዋል፡፡

የህወሓት/ኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባ ሲገባ አብሮ የመጣው የሻዕቢያ ተዋጊ ብዛት 300 ገደማ እንደነበር፤ እነሱም ከ1 ሳምንት ቆይታ በኋላ በግዮን ሆቴል ግብዣ ተደርጎላቸው በ10 አውቶብስ እንደተሸኙ ያወሱት ጄኔራል ጻድቃን፤ የቤተመንግስት ጥበቃ ሻዕቢያዎች ነበሩ የሚሉና መሰል ወሬዎችን እያሳደድክ መመለስ ሥራ መፍታት ነው ብለውታል፡፡

የጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ሙሉ አስተያየት ከታች ባለው ቪዲዮ ላይ ይመልከቱ፡፡

——

Watch Video below.

*************

ተዛማጅ፡-
*
ማሌሊት መሠረታዊ ወታደራዊ ለውጥ አምጥቷል – ጄኔራል ጻድቃን [Video]

* ጄኔራል ጻድቃን – የዕርዳታ ገንዘብ ከሕዝብ ቀምተን ለመሣሪያ ስናውል አላውቅም [Video]

 

Daniel Berhane

more recommended stories