በከተሞች ፎረም ያወዛገበው “ትግሬ”

(አዲስ – ከድሬዳዋ ከተማ)

በድሬዳዋ በመካሄድ ላይ ያለው ስድስተኛው ሀገር-አቀፍ የከተሞች ፎረም መማር ለሚፈልግ አስተማሪ፣ መዝናናት ለሚፈልግ አዝናኝ ሁነቶችን እያስተናገደ በዓሉ እየቀጠለ ነው፡፡ በዚህ ሂደት በተለይ ከ20 በላይ የውጭና የሐገር ውስጥ ምሑራን ያዘጋጇቸው ጥናታዊ ፅሑፎች የሚቀርቡባቸው የፓናል ውይይቶች – የተመደበላቸው ጊዜ ባያንስና ከየከተሞቹ የሚመለከታቸው አመራሮችና ከፍተና ባለሙያዎች እንዲሳተፉባቸው ቢደረግ/እየተሳተፉ መሆኑ ቢረጋገጥ – እጅግ አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ስለ ፎረሙ ሌላ ጊዜ፡፡

አሁን ግን ከዚህ በፊት በሶሻል ሚዲያዎች ከአንዳንዶች ጋር ሳልስማማባቸው ከቀሩ አንዳንድ ሐሳቦች መካከል አንዱ ያልጠበቅኩት ቦታ ከተሞች ፎረም ላይ ሲነሳ ብሰማ ነው የሚሰማኝን ሰፋ አድርጌ ለመግለፅ የተነሳሁት፡፡

የፓናል ውይይት መክፈቻ ላይ የቀረበው ‹‹ድሬዳዋ ከየት ወደየት›› በሚል ርዕስ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና ድሬዳዋ አስተዳደር ትብብር የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሑፍ ነበር፡፡

በጥናታዊ ፅሑፉ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ በአስተዳደሩ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚዘረዝርበት ክፍል ላይ ትግሬ የሚል ቃል መኖሩ ሁለት የትግራይ ክልል ተወላጆችን ቃሉን ተቃዉመው አስተያየት እንዲሰጡ ያስገደደ ነበር፡፡ የተቃዉሟቸው መነሻ ደግሞ ብሔሩ ትግራይ እንጂ ትግሬ አይባልም የሚል ነበር፡፡ህገ መንግስቱን ሁሉ ዋቢ ያቀረቡ አሉ(ምንም እንኳ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የክልሉ ስም እንጂ የብሔሩ ስም ባይሆንም)፡፡Dire Dawa city

‹‹እነኚህ ሰዎች በአማርኛም፣ በኦሮምኛም ሆነ በሶማሊኛ፣ . . . .ትግራይ የሚባለው ክልሉ እንደሆነና የክልሉ ተወላጆች ግን ትግሬ እንደሚባሉ ሳያውቁ ቀርተው ነው እንደዚህ የሚከራከሩት እንዴ?›› ብዬ ራሴን ስጠይቅ፤ ትግሬ የሚል ቃል ‹‹ትምክህተኞች ለትግራይ ህዝብ ያወጡለት የስድብ ስም ነው›› እያሉ አንዳንዶች በፌስቡክ ላይ የሚያደርጉት ክርክር ነበር ትዝ ያለኝ፡፡ እነኚህ ከክልሉ ከተሞች የተወከሉ አመራሮች/ባለሙያዎችም እንደዚያ ነው የሚያስቡት ማለት ነው?

ትግሬ የሚለውን ቃል ስልጣን ወደትግራይ ከመሔዱ፣ ከትግራይም ወደሸዋ ከመሻገሩ በፊት፣ ሁሉም ጠቅላይ ግዛቶች ተመሳሳይ በነበሩበት የአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ሁሉ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተገጠሙ ግጥሞች ማስረጃ ናቸው፡፡ እርግጠኛ ነኝ በዘመነ መሳፍንት የነበሩ የአማርኛ ፅሑፎችንም ቢያገላብጡ ህዝቡ በአማርኛ ወይም አገውኛ ትግሬ እንደሚባል ማረጋገጥ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ መቼም በዛ ዘመን የአሁን ፖለቲከኞቻችን የሚያወሩት መናናቅ/መሰዳደብ አለ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ እናም ቃሉ ስድብ አለመሆኑን መግባባት ይቻላል፡፡

ያለፈው እንዳለ ሆኖ አሁን ያለውን አጠቃቀምን ያየን እንደሆነም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትግሬን ከብሔር ስምነት ባለፈ ለሌላ አላማ አስቦትም እንደማያውቅ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ትግሬዎች አማራን አምሓራ ብለው እንደሚጠሩ፣ የእንግሊዝኛ amhara(and so amharic)ስያሜውም ይህንኑ የትግርኛ ስያሜ መሰረት ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሕዝቡን እንወክላለን የምንል ፖለቲከኞች /አክቲቪስቶች እሴት በማይጨምሩ፣ ይልቁንም በሒደት ከጥቅማቸው ጉዳታቸው በሚያመዝኑ የቃላት ጨዋታዎች ውስጥ እንወክለዋለን የምንለውን ህዝብ ማስገባት ያለብን አይመስለኝም፡፡አሁን እያየሁት ያለሁት ችግር ይሔ ነው፡፡

አሜሪካ ውስጥ ጥቁሮች ያልተቀየረላቸው ስም የለም፤ ግን ጥቁሮቹ ውስጥ የሰረጸው የበታችነት ስሜትና በሌሎች ዘንድ ያለው ለጥቁሮች እኩል ክብር ያለመስጠት ችግር – ችግሮችን ለመቅረፍ ከመታገል ይልቅ እነኚህ ስሜቶች ይንጸባረቁባቸዋል ተብለው የሚገመቱ ቃላትን ሲታገሉ ስንት ጉልበት ያላግባብ ባከነ መሰላችሁ፡፡ በፊት ኔግሮ ሲባሉ ራሳቸውን ዋይት/ነጭ እያሉ(በዘራቸው ካውካሶይድ ሳይሉ) እኛን ግን በቀለማችን ሳይሆን በዘራችን ኒገር/ ኔግሮ እያሉ ይጠሩናል እያሉ ለሚነጫነጩ ጥቁሮች ጥቁሮች/ብላክ እያሉ መጥራት እንደመፍትሔ ታይቶ ነበር፡፡ አሁንም ጥቁር እየተባሉ ቢጠሩም አጠራሩ ግን የማክበር መንፈስን የተላበሰ ስላልነበር ሌላ ሐሳብን አስከተለ ፤ ግን ጥቁር እኮ የጨለማ፣ የሲኦል፣ የሼጣን፣የመጥፎ ነገር. . . ምልክት ነው . . . .እኛ ደግሞ ጥቁር አንባልም፤ ይልቅ እነሱ ይብላኝላቸው ቀለም ለሌላቸው እንጂ ተብሎ በነጮች ቀለም አልባነት ለመሳለቅ ሁሉ ተሞከረና እና ትክክለኛ ስያሜአችን ቀለማማዎች(ከለርድ) ነው ፤እንደዚህ ካልተጠራን ሞተን እንገኛለን አሉ፡፡ ቃሉ ጥቁሮች በተፈጥሮ ሜላኒን የተባለ ቀለምን እንደታደሉና ነጮች ግን ይህ እንደሌላቸው የሚያሳብቅ በመሆኑ ምናልባት ነጮች ቢያኮርፉ እንጂ ለጥቁሮች ትልቅ ደስታን የሚፈጥር ስያሜ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው፤ አሁንም በሐብት፣ ስልጣኔ፣. . .ሁሉ ነገር የበላይ የሆኑት ነጮች ውስጣቸው ያለው ንቀት ሳይጠፋ ከለርድ እያሉ ጥቁሮችን ሲጠሩ ጥቁሮችም በዚህ ስያሜ እንደገና ማፈር የጀመሩት ብዙ ሳይቆዩ ነበር፡፡ አሁን አሁን ደግሞ አፍሪካ አሜሪካውያን ተብለን እንጠራ እያሉ ይሔው ስያሜ የክብር ስም ሆኖ እያገለገላቸው ነው፡፡በዚህ መሐል የጥቁሮችን እኩልነት የሚያረጋግጥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጅምሮች ተጠናክረው እኩልነቱ ከሰፈነ ከአሁን በኋላ ስያሜ መቀየር ላያስፈልግ ይችላል፤ ከሞላ ጎደል በሁሉም ዘመናት ተፈላጊነቷ ከፍና ዝቅ ቢልም ጥቁሮች የሚለው ስያሜ ወደ መደበኛ መጠሪያነት ከፍ ሊል ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን በእኛ እድሜ አፍሪካ አሜሪካውያንም ወደ ታቡነት ሊቀየር ይችላል – ነጮች አውሮፓ አሜሪካውያን ሳይባሉ እና ግን ለምን አፍሪካ አሜሪካውያን እንባላለን ብለው የሚጠይቁ ጥቁሮች ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ቀድሞ ጥቁሮችን በክብር ለመጥሪያነት ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ቃላት አሁን ታቡ/ ስድብ ሆነዋል፡፡ ከቃላት ጋር የሚደረግ ጦርነት በክብር መጥሪያ የነበረ ቃልን ወደ አፀያፊ ስድብነት ከመቀየር በስተቀር ምንም የሚቀይረው ነገር የለም፡፡ አሁን ከለርድ ብላችሁት በንዴት እብድ የማይሆን ጥቁር አሜሪካዊ ማግኘት ከባድ ነው፡፡አባቶቹ ግን ከለርድ ተብሎ ለመጠራት ያላዩት አበሳ አልነበረም፡፡

በዚህ ረገድ ቀድሞ በመሐል አገር እና ኤርትራ ውስጥ አጋሜ እና ወያኔ ስድብ ይመስለን ለነበርን ሰዎች ቃላቱን በስድብነት ስንጠቀምበት ከመቆጣት ይልቅ እነሱ ራሳቸው በክብር በመጠቀም ቃላቱ ክብር ያላቸው መሆናቸውን (መግለጫ በማውጣት ሳይሆን) በተግባር እየተጠቀሙ በማሳየት የብዙዎቻችንን የተሳሳተ አመለካከት ያስተካከሉ የሕወሐት ሰዎች አሁን አያት ቅድመአያቶቻቸው ይጠሩ በነበሩበት ስያሜ ለምን ትግሬ ተባልን በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ማየት ምንነካቸው ያስብላል፡፡ በወቅቱ አዳራሽ ውስጥ ከነበሩት ከ 1ሺ በላይ ተሰብሳቢዎች መካከል አብዛኛዎቹ ተሰብሳቢዎች ለምን ትግሬ ተብሎ ተፃፈ ብለው 2 የትግራይ ልዑካን ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ የተቃዉሟቸው ምክንያት አልገባቸውም፡፡

በመሰረቱ አንድ ሕዝብ መጠራት በማይፈልገው ስያሜ ሊጠራ አይገባም፡፡ በመከባበር እና እኩልነት ላይ የተመሰረተው ፌደራላዊ ስርዓታችንም ሆነ ባህላችን ይህንን እንድናደርግ አይፈቅዱልንም፡፡ነገር ግን አሁን የትግራይን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ ጥቂት ግለሰቦች በውሐ ቀጠነ ይህንን የመከባበር መንፈስ ያላግባብ ጥቅም ላይ ሊያውሉት(አብዩዝ ሊያደርጉት) አይገባም – ማለትም የሚጨበጥ ምክንያት ሳይኖረን ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲጠቀሙበት የነበረውን ቃል እንዲቀይሩ ልንጫናቸው፣ ይንን ሳያደርጉ ቀርቶ የለመደባቸውን ቃል ሲጠቀሙ ደግሞ በትምክህተኝነት ልንወነጅላቸውና ልናሸማቅቃቸው አይገባም፡፡

ከዚህ በፊትም የአዳዲስ መርከቦች ስያሜ ላይ ሌሎች መርከቦች በሐገሪቱ ያሉ ክልሎች ዋና ከተማ ባለክልሎቹ በሚጠሩበት ስያሜ ተሰይመው(ለምሳሌ ሐዋሳ፣ ፊንፊኔ፣ ጅግጅጋ፣ . . .) በትግራይ ዋና ከተማ የተሰየመችው መርከብ ግን በትግርኛ ስያሜዋ/መቐለ ሳይሆን በአማርኛ ስያሜዋ/መቀሌ በመባሏ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፤ እኛም ተቃውሞውን ደግፈነው ነበር፡፡ ስያሜው ከተስተካከለ በኋላ ግን የከተማዋ አማርኛ ስያሜ በአማርኛ ቋንቋም ቢሆን ለኦፊሴላዊ አገልግሎት እንዳይዉል ዘመቻዎች ተጀመሩ፡፡ ይህ የአማርኛ ተናጋሪውን መብት መጣስ እንጂ ከትግርኛ ተናጋሪው መብት መከበር ጋር የማይገናኝ ቢሆንም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ግን ለዚህ ከቋንቋ ሳይንስና አለምአቀፍ ተሞክሮዎች ጋር የተጣላ መቐለ አማርኛ ውስጥ ትግባልን ጥያቄ በከፊል ሲያጎበድድ አይተን ብስጭታችንን ገልፀን ነበር፡፡

ጣቢያው ግን እንደዚህ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ አማርኛና ትግርኛ የግዕዝ ፊደላትን ቢጠቀሙም አንዳንድ ቃላት ላይ እንደሚለያዩ እየታወቀ (ለምሳሌ አ-ኣ-ዐ-ዓ-በአማርኛ አነባበባቸው አንዳይነት ነው፤ ትግርኛ ላይ ግን ይለያያል፡፡ሀ-ሃ-ሐ-ሓ-ም እንዲሁ አማርኛ ላይና ትግርኛ ላይ የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በትግርኛ ሀ፣ሐ፣አ፣ዐ- የ ኧ ድምፅ ሲኖራቸውሓ፣ሃ፣ኣዓ ደግሞ የኣ ድምፅ ነው ያላቸው፡፡ በአማርኛ ግን ሐ፣ሃ፣ሀ፣ሓአ፣ኣ፣ዓ ዐ፣ ሁሉም የኣ ድምፅ ነው ያላቸው፡፡ በርሀ በአማርኛ ሲነበብ barhaa/berha ሲሆን በትግርኛ ግን barha/berhe ነው፡፡

ይህንን የአነባበብ ልዩነት ትግሬዎች ያውቃሉ፡፡ አብዛኞቹ አማሮች ግን አያውቁም፡፡ እንደዚህ የአነባበብ ልዩነት እያለ ቴሌቪዥኖች የአማርኛ ፕሮግራም ላይ በትግርኛ ስርዓት እየፃፉ ሰውን ግራ ሲያጋቡ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ አሁንም እየተደገመ ያለው ገመና1 ድራማ ላይ ከአዘጋጆቹ ስም ዝርዝር ተደጋጋሚ የሚታየው በርኸ የሚል ስም በምን መልኩ እንደሚፃፍ ማየት ይቻላል -በርሀ ተብሎ ነው የተፃፈው፡፡ ገመና1 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተላለፍ ብዙ ሰዎች ስሞቹን በረሃ እያሉ እያነበቡ ግራ ይጋቡ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን ሲያደርግ የነበረው ኢቴቪ አሁን ደግሞ አማርኛ ላይ የሌለችውን ቐ ፊደል እያስገባልን ነው፡፡ መቀሌ ከተማ በአማርኛ መቀሌ እንደምትባል እየታወቀ ቀድሞ ነገር ለምን መቀየር አስፈለገ፣ ይቀየርልን ጥያቄ ከቀረበስ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች በምን መልኩ ይስተናገዳሉ፣ በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ የአማርኛ ተናጋሪው ምንም መብት የለውም ወይ፣ በዚህ ረገድ ያለው አለም አቀፍ ተሞክሮ ምን ይመስላል፣ አማርኛ የፌደራሉ የስራ ቋንቋ በመሆኑ ሊያስገባቸው የሚገቡ ቃላት አሉ ወይ. . . . የሚሉ ጉዳዮችን የሚመልስ ወጥ መመሪያ ሳይኖር በዘፈቀደ አዚህና እዚያ እየረገጠ፣እኛንም እያስቀየመ ይገኛል ቴሌቪዥናችን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህዝባችን እንደዚህ አይነት ነገሮችን ንቆ የሚተው አይነት ህዝብ ቢሆን ደስታዬ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የወሎዬዎችን ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን በእስር ላይ የሚገኘው እስክንድር ነጋ በ1990ዎቹ ሚኒልክ ጋዜጣ ላይ በቋሚነት “ወሎ በትክክለኛ ስሙ ላኮመንዛ ተብሎ ይጠራ” የሚል ማስታወቂያ ያወጣ ነበር፡፡ የአባባሉ መነሻ በክፍለሐገሩ የሚኖረው አብዛኛው ሰው(ባልሳሳት እስከ 80 ፐርሰንት) አማራ ሆኖ እያለ ሐገሩ ግን ከክፍለሐገሩ ነዋሪ 10 ፐርሰንት ድርሻ በሌላቸው ኦሮሞዎች መጠራት የለበትም የሚል ይመስላል፡፡ በርግጥ ወሎ የኦሮሞ ጎሳ ስም ነው፡፡ ኦሮሞ ወደ አካባቢው ከመስፋፋቱ በፊትም አካባቢው ላኮመንዛ ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡አሁን ግን ይህ አስተሳሰብ የለም፤ ወሎ የኦሮሞ ጎሳ ስምነቱ ሳይሆን የፍቅር አገርነቱ፣ የውበት መገለጫነቱ ነው የሚታወቀው፡፡ ድምፃዊው “ወሎዬ ነኝ ብትይ ስሙ ይበቃሻል” እያለ ማቀንቀኑ የአካባቢው ተወላጅ ራሱን ማን ብሎ እንደሚጠራና በዚህም ምን ያህል እንደሚኮራ የሚያሳይ ነው(በነገራችን ላይ ወሎ ብቻ ሳይሆን ጎጃምም፣ ቤጌምድርም፣ ሸዋም እንዲሁ አማርኛ ስሞች አይደሉም)፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች የሕዝቡን ስሜት ማክበር ነው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው፡፡

ሆኖም ህዝባችን ልክ እንደ1990ዎቹ ወሎዬዎች እንደዚህ አይነት ቃላት ስንጠቃዎችን ንቆ የሚተው ሳይሆን ቀርቶ ስሱ/ሴንሲቲቭ ህዝብ ከፈጠርን ግን እንደዚህ አይነት ነገሮችን በሕግና መመሪያ መመለስ ይገባል እንጂ ጥያቄዎች ስለቀረቡ ብቻ ያለፍተሻ ማስተናገድ ፣ አንድም የአማርኛ ተናጋሪውን በእኩል አይን የመታየት መብት መጣስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአማራና አማርኛ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ሁሉ በአሉታዊ አይን የሚያዩ ጥቂቶች ከተሳሳተ አመለካከታቸው እንዳይማሩ ማድረግም ጭምር ነው፡፡ እንደዚህ መጠየቄንም የህዝቦችን እኩልነት መቀበል ያቃተው ሰው ኑዛዜ አድርገው የሚወስዱ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገባኛል፡፡

*********

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories