መ/ር ገብረኪዳን ደስታ፡- መቐለ ወደ መቀሌ ተቀይሮ የሚጻፍበት አግባብ የለም

(ዳንኤል ብርሃነ)

እውቁ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ መምህር ገብረኪዳን ደስታ የኢትዮጲያ መርከብ ድርጅት አዲስ በተረከበው መርከብ ላይ ‹‹መቀሌ›› ብሎ መፃፉ ስህተት መሆኑን ገለፁ፡፡

የኢትዮጲያ መርከብ ድርጅት ወደ ኢትዮጲያ የሚገቡና የሚወጡ ሸቀጦችን የማስናገድ አቅሙን ከ20% ወደ 50% ለማሳደግ በ2002 ዓ.ም. ዘጠኝ አዳዲስ መርከቦች እንዲሠሩለት ለአንድ የቻይና ኩባንያ በሶስት መቶ ሚሊየን ዶላር ወጪ ትዕዛዝ መስጠቱ እና መርከቦቹንም በዘጠኙ ክልሎች ስም ለመሰየም መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚሀም መሠረት እስካለፈው ጥቅምት ወር ድረስ ስምንቱን መርከቦች በተከታታይ የተረከበ ሲሆን እነሱም ፊንፊኔ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ተብለው ተሰይመዋል፡፡

ዘጠነኛዋ እና በትግራይ ክልል ዋና ከተማ የተሰየመችው መርከብ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የመጣች ሲሆን በመርከቡ የጎን አካል ላይ የሰፈረው ስያሜ ‹‹መቐለ›› ሳይሆን ‹‹መቀሌ›› የሚል መሆኑ በተለይ በሶሻል ሚዲያ ላይ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡Memhir Gebrekidan Desta

ተቃውሞው በሳምንቱ መጨረሻም ወደፊርማ ማሰባሰብ ያደገ ሲሆን፤ በቀናት ውስጥ በመቶዎች ድጋፍ ያሰባሰበው የፊርማ ደብዳቤ፡-

‹‹ [በመርከቡ] ላይ የሠፈረው “መቐለ” ሳይሆን “መቀሌ” የሚል መሆኑ፤ ለዚህ ቃል ሆነ ለሌሎች (ሽሬ፣ ትግሬ፣ ወዘተ) የተዛቡ የአፃፃፍ/አጠራር ልማዶች ዘለቄታዊነት የሚሰጥ ሆኖ ይሰማናል፡፡ በመሆኑም የመርከቧ ስያሜ እንዲስተካከል…. መሰል የአፃፃፍ/አጠራር ግድፈቶችን [እንዲታረሙ]›› የሚል ጭብጥ ሲኖረው፤

በአንፃሩ ጥያቄው ስህተትና ከስነ-ቋንቋ ያፈነገጠ ነው በሚሉ ግለሰቦች – በተለይ በፌስቡክ ላይ – ከፍ ያለ ተቃውሞና ክርክር ተስነስቷል፡፡(‹‹በመቐለና መቀሌ ስሞች የትርጉም ልዩነት የለም›› አብርሃ ደስታ)

በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡን ረቡዕ ምሽት ያነጋገርናቸው መምህር ገብረኪዳን ደስታ፤ በመርከቡ ላይ የሰፈረውን ‹‹መቀሌ›› የሚል ጽሕፈት እመልክቶ፡-

‹‹በቴሌቪዥን አይቸዋሁ – ስህተት ነው፡፡ እንግዲህ ምን ታደርገዋለህ?›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹መቐለ በአማርኛ ሲፃፍ መቀሌ ነው›› የሚል መከራከሪያ እንደሚቀርብ የጠቀስንላቸው ሲሆን፤ እሳቸው ሲመልሱም፡-

‹‹ስም አይተረጎምም፤ ካለማወቅና በተሳሳተ ልማድ አሳስቶ የመፃፍ ነገር ስላለ ነው እንጂ – በርኸ ወደ በርሄ፤ መቐለ ወደ መቀሌ ተቀይሮ ተብሎ ሊጻፍ የሚችልበት አግባብ የለም።›› ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ ሆሄ ያለውን ልዩነትና አመጣጥ ካማወቅ የማንጠቀምባቸው እንዲሁም አሳስተንና አቀያይረን የምንጠቀምባቸው የግዕዝ ሆሄያት መኖራቸውን ያብራሩ ሲሆን፤ አክለውም፡-

‹‹ መቐለ ተብሎ ነው መፃፍ ያለበት፤  እንደው ‹‹ ‹‹ቐ››ን ለመፃፍ> ይከብደኛል አይሆንልኝም የሚል ሰው <መቀለ> ብሎ ይጽፍ ይሆናል እንጂ <መቀሌ> የሚልበት ምክንያት የለም፡፡››

የኢትዮጲያ መርከብ ድርጅት ‹‹ኦፊሺያል ከሆነ አካል›› የማስተካከያ ጥያቄ ከቀረበ ድርጅቱ እርማት እንደሚያደርግ ም/ሥራ አስኪያጁ መግለፃቸውን ባለፈው ሰኞ በዚህ ብሎግ የእንግሊዝኛ ዜና ላይ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ለፌዴራል መንግስት በሚልካቸው ደብዳቤዎች ላይ መቐለ ተብሎ እንደሚጻፍ እና አንዳንድ የፌዴራል መንግስት ተቋማት ተመሳሳይ አፃፃፍ እደሚከተሉ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
**********

Related:-
* TigraiOnline:- Mekelle vessel’s name is misspelled please correct it

Daniel Berhane

more recommended stories