ከፊንጫኣና ከወንጂ-ሸዋ ፋብሪካዎች ተጨማሪ 1.8ሚ ኩ. ስኳር ምርት ይጠበቃል

*  የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ2006 አጋማሽ ምርት ይጀምራል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክት ስራው የተጠናቀቀው የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ከጥቅምት 10/2006ዓ.ም ጀምሮ ተጨማሪ ምርት እያመረተ ነው፡፡ ፋብሪካው በ2006 በጀት ዓመት 2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ያመርታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ የምርት መጠን በ2005 በጀት ዓመት ከተገኘው ምርት ጋር ሲነጻጸር የ900 ሺህ ኩንታል ልዩነት ይኖረዋል፡፡

ፋብሪካው በሂደት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በአመት ወደ 2 ሚሊዮን 700 ሺህ ኩንታል ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ አገልግለው ስኳር ማምረት ባቆሙት ነባሮቹ ወንጂ እና ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች ምትክ በተከናወነ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታው የተጠናቀቀው አዲሱ ዘመናዊ የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከጥቅምት 22/2006ዓ.ም ጀምሮ ስኳር ማምረት ጀምሯል፡፡

በ2005ዓ.ም መጨረሻ የሙከራ ምርት ያካሄደው ይህ ፋብሪካ በያዝነው በጀት ዓመት ከ950 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር እንዲያመርት የታቀደ ሲሆን፣ ለምርቱ የሚሆን በቂ ሸንኮራ አገዳና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ዝግጁ ሆነዋል፡፡

አሮጌዎቹ የወንጂ እና የሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች በዓመት 750 ሺህ ኩንታል ስኳር ያመርቱ የነበረ ሲሆን፣ በምትካቸው የተገነባው አዲሱ ፋብሪካ በመጀመሪያ ምዕራፉ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በዓመት ከ1 ሚሊዮን 460 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

በሌላ በኩል በያዝነው በጀት ዓመት 1 ሚሊዮን 300 ሺህ ኩንታል ስኳር እንደሚያመርት የሚጠበቀው የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ2006 አጋማሽ ምርት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጠቀሱት አራት የስኳር ፋብሪካዎች በበጀት ዓመቱ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ለማምረት የታቀደ ሲሆን፣ ይህም ከአምናው ምርት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ይሆናል፡፡ በዘርፉ ዘንድሮ የሚገኘው ምርት የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ምርቱን ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ሙሉ በሙሉ ያስቀራል፡፡

የፋብሪካዎች የማምረት አቅም እንዲያድግና የአመቱ የማምረት ተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲጀመር አመራሮችና ሠራተኞች ሰፊ ርብርብ አድርገዋል፡፡

***********

Source: Ethiopian Sugar Corporation, Press statement, Nov. 7, 2013, titled “የወንጂ ሸዋና የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካዎች በከፍተኛ የማምረት አቅም ሥራ ጀመሩ”

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories