ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 3 | በመጭዉ ምርጫ የኢህአዴግን ዕጣ ፈንታ ሊወስኑ የሚችሉ የስጋት ምንጮችና ተግዳሮቶች

(/ አስጨናቂ /ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ እና ሁለተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ ማግኘት ይችላሉ)

መጭዉን የ2012 ሀገርአቀፍ ምርጫ በሚመለከት ካሁኑ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት የሚያስችለን ጥቂት ፍንጭ ሰጪ ሁኔታዎች አይጠፉም፡፡በርግጥ የ2102 ምርጫ ኢህአዴግ በተስፋ የሚጠብቀዉ ምርጫ እንደማይሆን ይሰማኛል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ እንደ ከዚህ በፊቶቹ በመልካም የልማት ስኬቶች የታጀበ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ገዥዉ ፓርቲ በበርከታ ችግሮች ዉስጥ መቆየቱና አሁንም ሙሉ በሙሉ ከችግሮቹ ያልተላቀቀበት ወቅት በመሆኑ ኢህዴግ ምርጫዉን በተስፋ ሊጠብቅ አይችልም፡፡

ለአብነት ያህል ፤ባለፉት ሁለት ዓመታት በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና በአማራ በከፊልም በደቡብ ክልል የተከሰተዉ ቀዉስና ያን ተከትሎ በሰዉና በንብረት ላይ የደረሰዉ ጉዳት ፤ኢህአዴግ የፈጠረዉ ችግር ባይሆንም በክልሎች መካካል የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ለነዚህ ችግሮች ሁሉን በእኩል ደረጃ ሊያረካ የሚችል ዘላቂ መፍትሄ ፈጥኖ ማስቀመጥ ያለመቻሉ ለአብነትም አሁንም ድረስ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አጎራባች ወረዳዎች መካካል በድንበር ሰበብ የሚታዉ ግጭት እንዲሁም በምዕራብ አማራ አንዳንድ አካባቢ የሚገኙ ህዝቦችን መነሻ ባደረገ መልኩ በአማራና በትግራይ ክልል መካካል የተከሰተዉ አሰጣገባ የተነገረለትን ያህል አመርቂና ዘላቂ መፍትሄ ባለማግኘቱ ለግጭት በር እንዳይከፍት መሰጋቱ ፤የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ተብሎ በገፍ የሚደረገዉ ህገወጥ ስደት መበራከትና በዚሁ ጦስ በተለያዩ አጋጣሚዎች የበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት ፤ የአየር ንብረት መዛባት መነሾ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ተፈጥሮአዊ ድርቅ ተደጋግሞ መከሰቱና በዚህ ላይ የመንግስት ቅድመ ዝግጅትና ምላሽ አጥጋቢ አይደለም በሚል እየቀረበበት ያለዉ ትችት፤ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለዉ ፈጣን አድገት በተለያዩ ዉጫዊ ተጽኢኖዎችና ዉስጣዊ ተግዳሮቶች ምክንያት ሊቀዛዝ ቢሎም አስካናካተዉ ለቀዉስ ሊዳረግ ይችላል ተብሎ መሰጋቱ፤ ፤ከሰሞኑ ደግሞ “ከሰብአዊ መብት አያያዝ” ረገድ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ “ኤች አር-128” የተሰኘ የዉሳኔ ሃሳብ ለህግ መወሰኛ ም/ቤት አቅርቦ በማስወሰን ሀገራችን ላይ የተለያዩ ማእቀቦችና እገዳ ለመጣል እንቅስቃሴ መጀመሩንና ይህም ሁኔታ ከአሜሪካ ጋር አስካሁን የነበረንን መልካም ግኑኝነት በማበላሸት ሀገራችንን ክፉኛ ሊጎዳት ይችላል የሚለዉ ስጋት ማየሉ፤ ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳዉ በተወሰኑ የአሜሪካ ባለስልጣናት አካባቢ የኢትዮጵያን ወዳጅነት በኤርትራ ለመቀየር የመለፈለግ አዝማሚያ ላይ አንዳንድ ፍንጮች መታየታቸዉ ፤ በሀገሪቱ ደህንነትና ብሄራዉ ጥቅምና ሉአላዊነት አኳያ የባህር በር ጉዳይ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ከገዥዉ ፓርቲ አካባቢም ሳይቀር የቁጭት አነጋገሮች መደመጣቸዉና ጉዳዩ ይብልጥ አንገብጋቢ እየሆነ መምጣቱ፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢህአዴግ አባል ደርጅቶች ዉስጥ የሚሰማዉ የእርስበርስ መወነጃጃልና አንዱ ሌላዉን በነገር ጎሸም ማድረግና በመካከላቸዉ የቀድሞዉ ዓይነት አንድነት ያለመኖሩን ማሳያ ተደርጎ መቆጠሩ ይህም ሁኔታ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ለመገመተ ማዳገቱ ፤ተቃዋሚዎች ይህንን ክስተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢህአዴግን በምርጫ ነጥብ ለማስጣል ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መገመቱ፤ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኦሮሚያን በአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚነት በሚመለከት በህገመንግስቱ ተደንግጎ እያለ አስካሁን ሳይተገበር የቆየዉን አሁን ላይ ለመተገበር ታስቦ የወጣዉ ማስፈጸሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በርካታ የተቃዉሞ ድምጾች መሰማት መጀመራቸዉ ፤በተጨማሪም በዚህ ሰሞን በነጋዴዎች የእለት ገቢ ግምት ላይ የተመሰረተወ የግብር ጭማሪ ዉሳኔ ላይ እየታየ ያለዉ ቅሬታና ቅሬታዉን ወደ አልተፈለገ አመጽ ወይም ሁከት ለመለወጥ የሚሹ የዉጭ ኃይሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ካሁኑ አጥፊ ዘመቻ መጀመራቸዉ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገሪቱ ዉስጥ ሙስና ፈጽሞ መቆጣጠር የማይቻልበትና የሀገሪቱ ብሄራዊ ስጋት ተደርጎ የሚቆጠርበት ደረጃ ላይ መድረሱና መንግስት እየወሰድኩ ነኝ በሚለዉ እርምጃም በህዝቡ ዘንድ እርካታ አለመኖሩ ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ የሚጠቀሰዉ እጅግ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸዉ ግዙፍ ፕሮጄክቶች በደካማ አፈጻጸም ምክንያት አለቅጥ መጓተታቸዉ ሳያንስ ለግለሰቦች ምዝበራና ብክነት መዳረጋቸዉ፤ ህዝቡን እያስመረረ ያለዉ የመልካም አሰተዳደር ችግር በተነገረለት ደረጃና በታሰበዉ ፍጥነት ሊቀረፍ አለመቻሉ ወዘተ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የኢህአዴግን የህዝብ ድጋፍ በእጅጉ በመቀነስ በቀጣዩ ምርጫ ላይ በድጋሚ የመመረጥ ዕድሉን አጠራጠሪ ማድረግ መቻሉ እዉነት ነዉ፡፡

ኢህአዴግ በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ምናልባት ለስድስተኛ ግዜ መመረጥ ባይችል ላለመመረጡ ሌላ ሰበብ ለመደርደር ሁኔታዉ አያመቸዉም፡፡ምክንያቱም ህዝቡ ከዚህ ቀደም እንዳደረገዉ “ምንም ቢሆን ኢህአዴግ ይሻለኛል” በሚል ከነ እንከኑም ቢሆን ኢህአዴግን ለመምረጥ ካልወሰነ በስተቀር በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን ለሽንፈት የሚዳርጉ ምክንያቶች ከሚፈለገዉ በላይ እጅግ የበዙ ናቸዉ፡፡ኢህአዴግም ቢሆን ይህን ሁኔታ መረዳት የሚሳነዉ አይመስለኝም፡፡ዋናዉ ጥያቄ እንዴት አድርጎ ነዉ ከችግሩ ሊወጣ የሚችለዉ? እንዴትስ አድርጎ ነዉ በዚህ አጭር ግዜ ዉስጥ የመራጩን ህዝብ አመኔታ መልሶ ለማደስ የሚችለዉ? የሚለዉ ነዉ፡፡

ገዥዉ ፓርቲ ከሰሞኑ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የጀመረዉ ደርድርም ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ዓይነተኛ ድርሻ ስለሚኖረዉ በቀጣዩ ምርጫ ዉጤት ላይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ያልታየ መሰረታዊ ለዉጥ ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህም በሁለት መንገድ እዉን እንደሚሆን ማሰብ ይቻላል፡፡አንደኛዉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለዉ የተነገረለት ከፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ጀምሮ ሌሎች ከምርጫ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች በድርድሩ በስምምነት በርካታ ማሻሻያ ይደረግበታል የሚል እምነት በመያዙ ሁኔታዉ ለተቃዋሚዎች ለቀጣዩ ምርጫ ቀና ስለሚሆንላቸዉ የተወሰነም ቢሆን የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ያስችላቸዋል የሚል ግምት መሰጠቱ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ከዚህ ቀደም በርከታ ትችት ሲቀርብባቸዉ የነበሩና የተቃዉሞ ፖለቲካን እንደልብ ለማራመድ እንቅፋት ሆነዉብናል በሚል “አፋኝ!” ናቸዉ እየተባሉ በተቃዋሚዎች ክፉኛ ሲነቀፉ የነበሩ አንዳንድ ህጎች (አዋጆች)ላይ ተቃዋሚዎች በሚፈልጉት ደረጃ በደርድር ማሻሻያ ቢደረግም ባይደረግም ጉዳዩ ለአደባባይ ዉይይት መቅረቡ በራሱ ገዥዉ ፓርቲን ለመንቀፍና ለማሳጣት ቀና ያደርግላቸዋል፡፡ በዚህ ምክንትም የ2012 ምርጫ ኢህአዴግን ማሸነፍ ይችላል ተብሎ የሚገመትና በስም የሚጠቀስ ጠንካራ ፓርቲ ለግዜዉ ባይኖርም ቢያንስ የተቃዋሚ “ድርቅ” ያጠቃዉን የተፋዘዘ ፓርላማ ለማነቃቃት ያህል ተቃዋሚዎቸ የተወሰኑ መቀመጫዎች እንዲያገኙ ዕድል ሳይሰጣቸዉ እንደማይቀር ይገመታል፡፡

ስለዚህ በአንድ በኩል በሀገሪቱ ለተከሰቱት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ ሃላፊነትም ተጠያቂነትም ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የህዝብ አመኔታ ሊቀነስበት እንደሚችል ሲገመት በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች የተጀመረዉን ድርድር በማስፋት ለነሱ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ለማድረግ ሰፊ ዕድል መኖሩ እንዲሁም እንደቀላል ሊታይ የማይገባዉ የዉጭ ተጽኢኖ በተለያዩ መንገዶች ሊፈጥረዉ የሚችለዉ ጫና በድምር ሲታይ ለገዥዉ ፓርቲ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች በመበራከታቸዉ ቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግ በተስፋ የሚጠብቀዉ እንደማይሆንለት መገመት አያዳግትም፡፡

ኢህአደግን ድምጽ የመንፈግ ጉዳይ ከመጣ ዲሞክራሲ አነሰኝ ሰብአዊ መብት ጎደለብኝ የሚዲያ ነጻነት አነሰኝ ወዘተ በሚል እንደማይሆን አስባለሁ፡፡እነዚህ የኢህአዴግ እጥረቶች አይደሉም እያልኩ አይደለም፡፡የህዝብ አመኔታ ለመቀነስ በቂ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም እያልኩም አይደለም፡፡ኢህአዴግን በቀጣዩ ምርጫ ለሽንፈት ባይዳርጉት እንኳን በርካታ ወንበር ለማስጣል ተጨማሪ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ነገር ግን ኢህአዴግ መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ተሸንፎም በሌላ ምርጫ አገግሞ ዳግም እንሰራርቶ እንዳይመጣና እዚያዉ ተቀብሮ እንዲቀር ሊያደርገዉ የሚችል ጉዳይ ካለ ሙስና ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለዉስጣዊ አንድነታችን አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ የርስበርስ ግጭቶችና አለመግበባቶች ናቸዉ፡፡ከነዚህ በተጨማሪ ሁኔታዉ በማባባስና በገዥዉ ፓርቲ ላይ ጫና በማድረግ ረገድ አስተወጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ተግዳሮቶችም እንደሚኖሩ ግልጽ ነዉ፡፡ኢህአዴግ እነዚህ ተግዳሮቶች እንዳሉ አምኖ ሊቀበልም ላይቀበልም እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ችግር ሊኖር አንድሚችል አምኖ ለማስተካከል ጥረት ቢያደርግ ጫናዉን ሊቀንስ ይችላል፡፡አንድም ችግር የለም በሚል ከተዘናጋ ግን ለዉድቀት ወይም ለሽንፈት ሊዳረግ እንደሚችል እልጠራጠርም፡፡

ሁሉም ተግዳሮቶች በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ያሉ በመሆናቸዉ ተገቢዉን እርምጃ መዉሰድ ከቻለ ጫናዉን በእጅጉ ለመቀነስ ሰፊ እድል አለዉ፡፡በዚህ ረገድ ትልቅ ተግዳሮት የሚሆንበት አስከሚቀጥለዉ ሀገር አቀፍ ምርጫ የቀረዉ ግዜ አጭር መሆኑ ሲሆን በዚህ የተጣበበ ግዜ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ከችግር ነጻ ለመሆን ፈጽሞ አይችልምም ባይባል እንኳን አዳጋች መሆኑ ግን እርግጥ ነዉ፡፡እንደዚያም ሆኖ ኢህአዴግ የትኛዉንም ችግር ቢሆን ህዝቡን ማሳተፍ ከቻለና ቃል የገባዉን ለማረም ቁርጠኝነቱ ካለዉ ከችግሩ ሊወጣ እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡

1. ኢህአዴግን በቀጣዩ ምርጫ ለሽንፈት ሊዳርጉት የሚችሉ ተግዳሮቶች፡

1.1 ሙስና፤- የስርአቱ ዋነኛ አደጋና የኢህአዴግ ቁልፍ ችግር፤

ህዝብ አደራ ሰጥቶት ስልጣን የያዘዉ ኢህአዴግ አንዳንድ ባለስልጣናቱ የሚጨነቁት የሀገሪቱን ህዝብ ህይወት እንዴት እናሻሽል በሚል ሳይሆን እንዴት አድርገዉ ሃብት እንደሚያፈሩና እንዴትስ አድርገዉ የሰረቁትን ገንዘብ ወደ ዉጭ እንደሚያሸሹ ነዉ፡፡ስለዚህ ከኢህአዴግ ባለስልጣናት መካካል አንዳንዶቹ በስልጣን ላይ የመቆየት ፋይዳዉን የሚገነዘቡት ለህዝብ ሊሰሩ በሚችሉት በጎ ስራ ሳይሆን በአጋጣሚዉ በህገወጥ መንገድ ሃብት ማጋበስ በሚችሉት ሁኔታ አንጻር ነዉ፡፡ስለዚህ ለነዚህ ዘራፊ ባለስልጣበናት ስልጣን ማለት ትርጉሙ ለስርቆት አመቺ መሆኑነዉ፡፡ ለነዚህ ባለስልጣናት ስልጣን ማለት ሀብት ለማፍራት አቋራጭ መንገድ መሆኑን ነዉ፡፡ከአመታት በፊት ኢህአዴግ ራሱ በአንድ ሰነዱ ላይ እንዳስቀመጠዉ ሙስና በተንሰራፋበት ህብረተሰብ ዉስጥ መንግስት ህዝባዊ አገልግሎት የሚበረከትበት ሳይሆን ዝርፊያ የሚከናወንበት መድረክ እየሆነ የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ፉክክርም በዘራፊዎች መካከል የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል እንዲሚሆን የነገረንን በተግባር አሁን እዉን ሆኖ እያየን ነዉ፡፡

የመንግስትን አመኔታ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለዉ የሚታወቀዉ የሙስና መስፋፋት ነዉ፡፡መንግስት የሙስና አደጋ ሀገሪቱን ህልዉና አስከመፈታተን ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ከተረደና ለዚያ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ ወስዶ መቀነስ ካልቻለ ዜጎች በመንግስት ላይ ብቻ ሳይሆን በየትኛዉም መንግስታዊ ተቋማት ላይ አመኔታቸዉ መቀነሱ የማይቀር ነዉ፡፡ሙስና ጥቂትግለሰቦች ጨለማን ተገን አድርገዉ በድብቅ የሚሰሩት ተራ ስርቆት መሆኑ አብቅቶ የመንግስትን ስልጣን በያዙ ሰዎች ስልጣናቸዉን መከታ በማድረግና ፖለቲካዉን እንደመሳሪያ በመጠቀም በግላጭ የሚዘርፉበት ደረጃ ላይ ደርሶ ዝርፊያዉ ተቋማዊ ባህሪይ በያዘበት ሁኔታ ከዚህ አደጋ ማምለጥ የሚቻለዉ ቁርጠኛ የሆነ አመራር ሲኖር ብቻ ነዉ፡፡

በዘራፊዎች ላይ እርምጃ ልዉሰድ አልዉሰድ እያለ የሚያመነታና ለሌባ የሚራራ እንደ ኢህአዴግ ላለ መንግሰት ሙሰናን ለማጥፋት ቀርቶ ለመቀነስም በእጅጉ ይቸግረዋል፡፡ በየደረጃዉ ያለዉ ባለስልጣንና የመንግስት ተሿሚ በሙስና በተዘፈቀበት ሁኔታ( kleptocracy) ሙስናን መታገል ከባዶ ቃላት ያለፈ ወይም የይስሙላ እርምጃ ከመሆን ባለፈ አንጄት የሚያርስ እርምጃ ሊሆን አይችልም፡፡የመንግስት ስልጣንን መከታ በማድረግ የሚሰራ ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገል ጥቂት ፈቃደኛና ቆራጥ የሆኑ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ባይጠፉም ስር የሰደደና በጠንካራ መዋቅርና ኔትዎርክ የተጠናከረዉን ምናልባትም በታጠቀ ኃይልም ጭምር የሚደገፈዉን የሀገራችንን ሙስና ለመታገል የመንግስታችን ፍላጎት ከሆነ በቅድሚያ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል አስፈላጊ ሲሆን ስልጣንንም ሆነ ራስን መስዋእት አስከማድረግ የሚደርስ ቁርጠኝነት እንዳለዉ እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡

በሙስና የተዘፈቀ መንግስት የህዝብ አመኔታ የጎደለዉ ስለሚሆን የዚህ ዓይነቱ መንግስት ስልጣን ላይ ለመሰንበት ፍላጎት ካለዉ ሌሎች ተጨማሪ ዜዴዎችን ካልተጠቀመ በስተቀር በመደበኛዉ የምርጫ ስርአት ብቻ የህዝብን ድምጽ ማግኘት ዘበት ይሆንበታል፡፡ምክንያቱም ሙስና ከሌሎች ችግሮች ሁሉ በከፋ ሁኔታ ፖለቲካዊ ቅቡልነትን በማሳጣት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለዉና ፡፡በ2006 እ.ኢአ. የወጣዉ የመንግሰታቱ ድርጅት ሰነድ እንዲህ ይላል (“-…. Corruption, therefore, is critical for trust in both the local and national political leaders and institutions. Literature investigating the dyad of trust and corruption establishes that citizens everywhere are watchful of the lack of honesty and unethical behavior in their respective governments. Therefore, it becomes almost axiomatic to say that any government that wants to build or reinforce trust needs, first and foremost, to work towards eradicating corruption”

ለፖለቲካ መሪዎች ሙስናን ለመታገል ሲወስኑ በቅድሚያ ራሳቸዉም ከሙስና የፀዱና ጨርሶ የማይጠረጠሩ ሊሆኑ እንደሚገባ የመስኩ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ፡፡ያለበለዚያ ድፍረቱ አይኖራቸዉም፡፡ ዜጎች በመንግስት ባለስልጣናት ላይ በተወሰነ ደረጃ የሙስና ችግር ቢኖርባቸዉም በጥንካሬ የሚገለጹ ሌሎች ጠንካራ ስራዎቻቸዉን ከግምት በማስገባት መንግስትን ያን ያህልም አመኔታቸዉን ላይነፍጉት ይችላሉ፡፡ በተለይ በሀገሪቱ ዉስጥ ግልጽነት የሰፈነበትና ዜጎች ሃሳባቸዉን በነጻነት በሚያንሽራሽሩበትና ያለአንዳች መሸማቀቅ በነጻነት የሚዘግቡ ነጻ ሚዲያዎች ባሉበት ሁኔታ አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሙስና ችግር ቢታይባቸዉ እንኳን ህዝቡ በመንግስት ላይ በግልጽ ትችት ከመሰንዘር ባለፈ አስከነጭራሹ አመኔታ አይነፍገዉም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ የግለሰቦችን ችግር ከስርአቱ ችግር ለይቶ ለማዬት የሚችል መሆኑ አንዱ መክንያት ሆኖ ሌላዉ ደግሞ የህግ የበላይነት በሰፈነበት ሁኔታ ጥፋት የተገኘበትን ባለስልጣንን በማንኛዉም ወቅት ላይ ያለምንም ችግር ለፍርድ ለማቅረብ አንዳችም ዉስብስብነት ባለመኖሩ ነዉ፡፡ በዚህ መነሻም በብዙ ሀገሮች በሙስና የተጠረጠረ ፕሬዝዳንታቸዉን፤ ጠቅላይ ሚኒስትራቸዉን ፤ ጄነራሎቻቻዉን ዳኛና የፓርላማ አባል ሳይቀር ፍርድ ቤት ሲገትሩ ዜናዉን ተከታታለናል፡፡በዚህ ረገድ ቻይና ፤ታይላንድ፣ደቡብ ኮርያ፤ ብራዝል ፤እስራኤል፤ ጣሊያን ወዘተ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ስለዚህ በነዚህ ሀገሮች አንድ ባለስልጣን የሆነ ግለሰብ ሲላጠፋ ብቻ መንግስታቸዉን ሆነ ገዥዉን ፓርቲ በጭፍን አይጠሉም፡፡ይህ ሁኔታ ግን ለኛ ቀላል አይደለም፡፡ ድብቅነት በሰፈነበትና ሃሳብን በነጻነት የማንሸራሸር ባህሉም ምቹ ሁኔታዉም በሌለበትና ቀድሞዉኑ በመንግስት አመራሮች ላይ የተጠራቀሙ ሌሎች ቅሬታዎችና ብሶቶች ባሉበት እንደኛ ባለ ሁኔታ መንግስት ሙስናን በቁርጠኝነት የማይታገል ከሆነ የዜጎቹን አመኔታ ለማግኘት እጅግ ፈታኝ ይሆንበታል፡፡ አንድ ሙሰኛ ባለስልጣን ሲገኝ እንዳይነካ የተለያዩ ጫናዎች በሚደረጉበት በኛ ሀገር ሁኔታ ሙስናን መታገል እጅግ አዳጋች ነዉ፡፡እንግዲህ አቶ ኃይለማርያም ሙስናን ለመታገል ሲወስኑ በዚህ አስቸጋሪ ጫና ዉሰጥ መሆኑን ከግምት ልናስገባላቸዉ ይገባል፡፡

የሙስና ጥፋት ልክ የለዉም፡፡ሙስና ህዝባዊ አመኔታን በሟሟጠጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አድገትን በማቀጨጭና አስከነጭራሹም በመግታት አጥፊ ደርሻ ይኖረዋል፡፡መንግስት ሙስናን በብቃትና በቁርጠኝነት በመታገል በተግባር ተጨባጭ ለዉጥ አምጥቶ ሳያሳይ እንዲሁ በባዶ ህዝባዊ ተአማንነትን ማግኘት መቻሉ የማይታሰብ ነዉ፡፡በአዉሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በብዛት የሚታወቅና አዘዉትረዉ የሚጠቅሱት አንድ አባባል አላቸዉ፡፡“Smart societies prevent corruption before it happens.” የምትል፡፡ከአዉሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካካል ሙስናን በተሳካ ሁኔታ መቆጣጠር የቻሉት በአሰራራቸዉ ግልጽነትን (Transparency) በከፍተኛ ደረጃ ማስፈን የቻሉት ናቸዉ፡፡ህዝባዊ አመኔታን ማትረፊያዉ ምርጥ መንገድ ለሙስና ተጋላጭነትን ማስወገድ ነዉ፡፡ሙስና አንድ ግዜ ስር ከሰደደ ከዚያ በኋላ መልካም አስተዳዳርን ለማደስ አዳጋች እንደሚሆን የመስኩ ምሁራን ያስጠነቅቃሉ፡፡“Once a country has widespread corruption even the most advanced repression in the world can no longer repair and completely restore good governance.”

በሀገራችን ከሙስና በላይ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ብዙ ህዝባዊ መድረኮች ፤በርካታ ግዜ የጠየቁ የሬዲዮና የተሌቪዥን ድስኩሮች፤ ዉይይቶችና ዉግዘቶች፤ ብዙ ሺህ ገጾች የፈጁ የጋዜጣ ላይ ትንታኔዎች የአደባባይ ቢል ቦርዶችና መፈክሮች ወዘተ በሙስናና በመልካም አስተዳዳር ዙሪያ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ግዜ ሙስና ተራ ችግር መሆኑ አብቅቶ ለሀገሪቱ መበታተንና ለስርአቱ መቀልበስ ምክንያት ሊሆን የሚችል መቅሰፍት ተደርጎ አስከመቆጠር ደርሷል፡፡ ሙስና እንኳን በመፈክርና በአዳራሽ ጩሄት ቀርቶ በህግ በተቋቋመ የመንግስት መዋቅርም ሊገታ ያልቻለ አደጋ ሆኗል፡፡በመካካለኛዉ ምስራቅና በሌሎች አካባባዎች እጅግ በስጋት ዓይን ከሚታየዉ ሽብርተኝነት ባልተናናሰ ለሀገራችን ህልዉና ስጋት እየሆነ ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ ስጋታችንን ያከፋዉ ከዚህ አደጋ ይታደገን ይሆናል ብለን ተስፋ የጣልንበት መንግስታችን እንኳን ሙስናን ሊያጠፋ ቀርቶ በተቃራኒዉ ሙስና ተመልሶ ራሱን መንግስትን እንዳያጠፋዉ መስጋታችን ነዉ፡፡ ቢያጠፋም ቢያለማም ለመንግስት አመኔታዉን ነፍጎት የማያዉቀዉ ህዝባችንም ከሙስና ጋር በተያያዘ በመንግስት ብቃት ላይ ጥርጣሬ ገብቶት አመኔታዉን ቢሸረሸርበት አይፈረድበትም፡፡ህዝቡ በሙስና ጦስ ከዚህ በፊት ለሆነዉ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ወደፊት ሊሆን በሚችለዉ ላይ ይበልጥ የመስጋቱ ዋነኛዉ ምክንያት ይሄዉ የመንግስት አቅመቢስ መሆን ነዉ፡፡

መንግስት በሰፊዉ ዝርፊያ እየተከናወነ መሆኑን እያወቀ አንዳችም የረባ እርምጃ ሳይወስድ ለዓመታት ሲያደፍጥ ቆይቶ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሊያደርገዉ ይችላል ብልን ባልጠበቅነዉ ደረጃ ሙሰኞችን እየመነጠረ ለፍርድ እያቀረበና በህገወጥ መንገድ የተገኙ ንብረቶችን እያገደ ይገኛል፡፤ይህ የመንግስት እርምጃ ሊበረታታ የሚገባዉ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደታዘብነዉም ዘላቂነት የሌለዉና የአንድ ሰሞን ግርግርና ዘመቻ እንዳይሆን መጠርጠራችን አይቀርም፡፡ሙስና የስርአቱ አደጋና የሀገሪቱ ህልዉና ላይ የተጋረጠ መቅሰፍት መሆኑን መንግስት በሚገባ ተረድቶ ከሆነ አሁን የጀመረዉ ጸረ- ሙስና ዘመቻ በአጭር ግዜም ባይሆን በሂዴት ዉጤት ሊሰጥ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ነገር ግን ጸረ- ሙስና ዘመቻዉ እንደ አንዳንዶች ስጋት ከልብ የመነጨ ሳይሆን ለፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃነት ከሆነ የጥርጣሬያችንን ትክክለኛነት ለማረጋጋጥ ጥቂት ግዜ መታገስ ከቻልን ፍንጭ ማግኘታችን አይቀርም፡፡መንግስት በጀመረዉ መንገድ አጠንክሮ መቀጠል ካልቻለና ሰበብ እየደረደረ ወደኋላ ማለት ከጀመረ ሀገሪቱንም ሆነ ራሱ መንግስትንም ቢሆን ለከፋ አደጋ እንደሚያጋልጥ ለአፍታም መዘንጋት አይኖርበትም፡፡

በእኔ እምነት ቀጣዩ ምርጫ ለኢህአዴግ እጅግ ፈታኝ የሚሆነዉና ምናልባትም ለሽንፈት ሊዳርጉት ከሚችሉት ጉዳዮች መካካል በዋነኛነት የሙስናና መልካም አስተዳዳር ችግሮች ናቸዉ፡፡ኢህአዴግ መሸነፍ ካለበት ሊሸነፍ የሚችለዉም በሙስና ምከንያት ነዉ፡፡ተቃዋሚዎችም ማሸነፍ ካለባቸዉ ኢህአዴግን ማሸነፍ የሚችሉት በሌላ ሳይሆን በሙስና ምክንያት ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ሙስና ከመሻሻል ይልቅ ጭራሽ እየባሰበት በመሄዱ ኢህአዴግን ለሽንፈት ሊዳርገዉ መቻሉን መጠራጠር አይቻልም፡፡ሙስና በግዜ መፍትሄ ካልተቀመጠለት በስተቀር ሀገር የመበታታንና ስርአት የማፍረስ ኃይል ያለዉ ከፍተኛ አደጋ በመሆኑ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ሊኖረዉ የሚችለዉን አንድምታ ኢህአዴግ ሌላዉ ቢቀር ቢያንስ ስልጣኑን ላለማጣት ብሎ ንቆ የሚያልፈዉ ጉዳይ ሊሆን አይገባም፡፡

ሙስና በሰፊዉ በተንሰራፋበት እንደኛ ባለ ሀገር ዉስጥ መንግስት ህዝባዊ አገልግሎት የሚበረከትበት ሳይሆን ዝርፊያ የሚከናወንበት መድረክ እየሆነ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ፉክክርም በዘራፊዎች መካከል የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል እንዲሆን ፤ እንዲሁም ዲሞክራሲ ከስረ መሰረቱ እንዲናድና ስርአቱ እንዲቀለበስ በር የሚከፍት አደገኛ መቅሰፍት መሆኑ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ሙስና ልማታችንን አደናቅፎ ፤የዲሞክራሲ ስርአታችንን ከዉስጡ እንዲበሰብስ አድርጎ የልማትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ተስፋችን እንዲጨልም ለማድረግ ከፍተኛ ኃይል ያለዉ መሆኑ ቀድሞዉኑ የሚታወቅ ሆኖ እያለ መንግስት አደጋዉን በተረዳበት ደረጃና ፍጥነት ለመቅረፍ ቸልተኝነት ሲያሳይ ከርሞና እጅግ ዘግይቶ ነዉ አሁን ገና መንቀሳቀስ የጀመረዉ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በፓርላማ በነበራቸዉ ቆይታ የፌዴራል ጠቅላይ ኦዲቴር ያቀረበዉን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከተከበረዉ ምክር ቤት አባላት ከቀረቡላቸዉ ጥያቄዎች መካከል የመንግስት ገንዘብ ብክነት ጋር በተያያዘ ምን እርምጅ እንደተወሰደ ለማወቀ የቀረቡ ጥያቄዎች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ምላሽ ለመረዳት የቻልነዉ የችግሩ ምንጮች ሁለት መሆናቸዉና አንደኛዉ ከአቅም ማነስ የሚመጣና ሁለተኛዉ ደግሞ ብልሹ አሰራር የፈጠረዉ እንደሆነ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ ችግር አለባቸዉ የተባሉት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወይም ድርጅቶች አጎደሉ ከተባለዉ በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ አንጻር ሲታይ ይህን ያህል ግዙፍ ባጀት የተመደበለትን ፕሮጄክት እንዲያንስቀሳቅሱ ሃላፊነት የተሰጠቻዉ መስሪያ ቤቶች ላደረሱት የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ ብክነት የአቅም ማነስ ችግርን እንደምክንያት መጥቀስ አሳማኝ አይሆንም፡፡አንደኛ የታማኝነት ጉድለት ችግር እንጂ የአቅም ማነስ ችግር እንደሌለባቸዉ ግልጽ ነዉ፡፤ሁለተኛ እነዚህ ድርጅቶች ይህ ችግር በተዳዳጋሚ በየአመቱ የታየባቸዉ እንጂ በአጋጣሚና ለአንድ ግዜ ብቻ የተከሰተ አይደለምና ከአቅም ማነስ ይልቅ ሆን ተብሎ የተደረገ ነዉ፡፡የአቅም ማነስ አለበት ለተባለ መስሪያ ቤት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚመደብበት ምክንያትስ ተገቢነቱ ምን ያህል ነዉ የሚለዉ ጥያቄም መልስ የሚሻ ነዉ፡፡በሌላ በኩል በሁሉም የሙያ ዘርፍ የተማረ የሰዉ ኃይል የማፍራት ሃላፊነቱም ብቃቱም እንዳላቸዉ የሚገመቱ ዩኒቬርስቲዎቻችን በተደጋጋሚ በሚሊዮኖች ለሚቆጠር ገንዘብ ብክንት መዳረጋቸዉ የአቅም ማነስ ሲላለባቸዉ ነዉ መባሉ የሚያስማማን መልስ አይደለም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተገለጸዉና ብልሹ አሰራር የተባለዉ ዝም ተብሎ ቴክኒካል ችግር ተደርጎ የሚቆጠር ሳይሆን ሆን ተብሎ በተደራጀና መዋቅራዊ በሆነ መንገድ የመንግሰት ስልጣንን መከታ በማድረግ ሲሰራ የቆየ ነዉ፡፡

ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ተደጋጋፊና እርስበርስ የተቆራኙ አንዱ ያለሌላዉ የማይኖር በመሆኑ ከምንግዜም በላይ የሀገራዊ ደህንነታችን ዋነኛ አደጋ የሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

የሀገሪቱ ዜጎች ስለዝርፊያዉ እየሰሙ ሁኔታዉን በዝምታ እንዳያልፉ የሚያደርጋቸዉ ዋናዉ ምክንት እየተዘረፈ የሚገኘዉ መጠነ ሰፊ ገንዘብ በአብዛኛዉ በእያንዳንዱ ደሃ ዜጋ ስም ከዉጭ የሚመጣ በብድር የተገኘ በመሆኑ ጭምር ነዉ፡፡የጥቂት ግለሰቦችን ኪስ ለማደለብ ተብሎ 100 ሚሊዮን ህዝባ ለሚቀጥሉት በርካታ ዓመታት ሁሉ ባለዕዳ የሚሆንበት ምክንያት ነዉ እጅግ አሳሳቢ የሚሆነዉ፡፤ስለዚህ መንግስት ሙስና ሀገሪቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ እያስገባት መሆኑን ተገንዝቦ ስለ ችግሩ ንድፈ ሃሳባዊ ትንታኔ ከመስጠት ወጣ ቢሎ በቅርቡ በጀመረዉ መንገድ በአጥፊዎች ላይ ቆራጥ የሆነ እርምጃ መዉሰዱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡በዚህ ምክንያትም በቀጣዩ ምርጫም የኢህአዴግ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነዉም ከሌሎች ጉዳዮች በበለጠ በጸረ- ሙስና ትግሉ ላይ በሚያመጣዉ ስኬት ይሆናል፡፡ኢህአዴግ ሙስናናን እሽሩሩ እያለና አጉል ርህራሄ እያሳየ ድጋሚ ሊመረጥ እችላላሁ ብሎ ማሰብ አይኖርበትም፡፡

1.2 የርስበርስ ግጭቶችና አለመግባባቶች ፤

በአጎራባች ህዝቦች መካካል በድንበር ወይም በሌላ ምክንያት ሳቢያ በተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸዉና ይልቁንም ህገመንግሰስቱ ባስቀመጠዉ አግባብ መሰረት ሁነኛ መፍትሄ ማስቀመጥ አየተሳነን አንድ ግጭት በሌላ ግጭት እየተደራረበ መምጣት ሀገራችንን ለወደፊቱ አደገኛ ሁኔታ ዉስጥ ሊያስገባት እንደሚችል በማሰብ መስጋታችን አልቀረም፡፡

መነሻዉ ምንም ይሁን ምን በህዝቦች መካካል የሚከሰቱ ግጭቶችና የጥላቻ አመለካካቶች ካሁኑ መፍትሄ ካልተቀመጠላቸዉ ለሀገራችን ህለዉና አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በዉስጣዊ አንድነታች ላይ ስለተጋረጠብን አደጋ በጭራሽ መስማት የማይፈልጉና በዚህ መነሾም መስጋታችንንም መቀበል የማይፈልጉ እንዲያዉም ይህ ጉዳይ ጭራሽ እንዳይነሳ የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡በመሰረቱ ፌዴራላዊ ስርአታችን በምንም ሁኔታ ቢሆን የግጭት መነሾ ሊሆን እንደማይችል ጠንቅቄ አዉቃለሁ፡፡የህዝባችን የእስካሁኑ የአብሮነት ባህልም ቢሆን ለርስበርስ ግጭት መነሾ የሚሆን አይደለም፡፡ ችግሩ ያለዉ የርስበርስ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት የመንግስታችን የእስካሁኑ የችግር አፈታት መንገድና የችግሮቹ አያያዝ አስተማማኝ አለመሆኑ እንዲዉም ብቃት የጎደለዉ መሆኑ ነዉ፡፡ አለምግባባቶች ገና ሳይባባሱና ለግጭት መንስኤ ሳይሆኑ በፊት ህገመንግስቱ ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መፍታት እየተቻለ ጭራሽ ችግር እንደሌለ ለማስመሰል ለመደበቅ መሞከር ፤መፍትሄ ተሰጥቶአቸዋል የተባሉትም ቢሆኑ ገለልተኝነት የጎደላቸዉና ሁሉንም ወገን በእኩል የሚያረካ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን ባለመቻሉ መፍትሄ አግኝቷል የተባለ ችግር በድጋሚ የሚያገረሽበት ሁኔታ ነዉ የሚታየወዉ፡፡ሌላዉ ቀርቶ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካካል የሚሰማዉ አተካሮና በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አጎራባች ወረዳ ህዝቦች መካካል የሰዉ ህይወት መጥፋት ያስከተለ ግጭት መኖሩ ከተሰማ የቆየ ቢሆንም አስካሁን የረባ መፍትሄ ባለመሰጠቱ ለከፋ የርስበርስ ግጭት እንዳይዳርገን ከፍተኛ ስጋት ገብቶናል፡፡በዚህ ረገድ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ትልቅ ድክመት እንዳለበት አምኖ ሊቀበል ይገባዋል፡፡ (ይህን ጽሁፍ እያጠናቀቅኩ ባለሁበት ሰዓት የቅማንትን ጉዳይ በህዝበ ዉሳኔ ለመወሰን ዝግጅት መጀመሩን በዜና ሰምቼ ተደስቻለሁ፡፡ዉጤቱ ምንም ይሁን ምን ዉሳኔዉን ለህዝቡ መተዉ ትልቅ እርምጃ ነዉ፡፡በጀመራችሁት መንገድ ፈጥናችሁ ወደኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ፊታችሁን አዙሩ እላለሁ፡፡)

የኢህአዴግ ዋነኛዉ ሃላፊነት የሀገሪቱን ህዝቦች አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ በመሆኑ በዚህ ረገድ ብቃቱን በሚገባ ሊያሳየን ይገባል፡፡ ስለዚህ በቀጣዩ የ2012 ምርጫ ኢህአዴግ ህዝባዊ ድጋፍ በሰፊዉ የሚያጣ ከሆነ አንዱ ምክንያት ይሄ ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ እንደምንም ተላልጦ መንግስት ለመመስረት የሚያበቃዉን ወንበር ቢያገኝ እንኳን ችግሮቹ ተባብሰዉ አስከቀጠሉ ድረስ ተረጋግቶ ሀገር ለመምራት መሰናክል እንደሚሆንበት አያጠራጥርም፡፡ስለዚህ ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ ካለበት ግዙፍ ሃላፊነት አኳያ በየቦታዉ የሚታዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መነሾ ምን እንደሆነ በገለልተኛ አካል አጣርቶ ሀዝብ ባሳተፈ መንገድ አለመግባባቶቹን ፈጥኖ ሊፈታ ይገባል፡፡፡፡

1.3 የተቃዋሚዎች የኢህአዴግን እንከን ያለቅጥ ማጋነን፤

አንድ ፓርቲ በመንግስት ስልጣን ላይ መሆኑ ( incumbent party) በራሱ እርግማንም በረከትም ሊሆን ይችላል፡፡ ገዥዉ ፓርቲ አድሉን በሚገባ ከተጠቀመበት የመንግስት ስልጣን ላይ መገኘቱ በራሱ የሚሰጠዉ ጠቀሜታ እጅግ ብዙ ነዉ፡፡የመንግስት መዋቅር፤ ፋይናንስ፤የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ፤ሚዲያ ፤ኢንፍራስትራክቼር ፤ሴኩሪቲ ወዘተ ሁሉ እንዳሻዉ በመጠቀም ለምርጫ አሸናፊነት የሚረዱትን ተግባራት ለማከናወን ሰፊ ዕድል አለዉ፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ገዥ ፓርቲ መሆን ጎጂ ጎን እንዳለዉም መዘንጋት አይኖርበትም፡፡በተለይ በምርጫ ሰሞን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በበለጠ በገዥ ፓርቲ ላይ ትችቶች ይበረታሉ፡፡ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ያለዉ ፓርቲ ከሰራቸዉ በጎ ስራዎች ይልቅ ያልሰራዉንና ድክመቱንና እንከኑን ከዚህም ከዚያም ሲቃርሙ ከርመዉ ልክ መድረኩን እንዳገኙ ስራቸዉ ማብጠልጠልና የተሰራዉን ሁሉ ዋጋ ማሳጣት ነዉ፡፡ መራጭ ዜጎችም የተቃዋሚዎችን ቅስቄሳ ሰለባ በመሆን መንግስት በተጨባጭ ከሰራዉ ይልቅ ያልተሰራዉና ጎደለ በሚሉት ላይ ይበልጥ በማተኮር መንግስትን የማማረር ልማድ አላቸዉ፡፡በዚህ ምክንትያም የህዝቡ ማለቂያ የሌለዉ አዳዲስ ፍላጎት ከተቀዋሚዎች አፍራሽ ዘመቻ ጋር ተዳምሮ ለገዥዉ ፓርቲ ሁኔታዉ እጅግ ፈታኝ ይሆናል፡፡

በሀገሪቱ ዉስጥ ለሚከሰቱ የትኛዉም ዓይነት ችግሮች ወይም ቀዉሶች ሁሉ ገዥዉ ፓርቲ ተቀዳሚ ተጠያቂነትና ሃላፊነት ስላለበትም በሰራዉም ባልሰራዉም፤ባጠፋዉም ባላጠፋዉም ሁሉ የሚቀርብበትን ወቃሳ በትዕግስት መቀበል ይኖርበታል፡፡የአየር ንብረት ለዉጥ ባስከተለዉ ድርቅ ለተፈጠረ ችግር ፤ በዉሃ ሙላትና ጎርፍ ማጥለቅለቅ ወዘተ ለመሳሳሉት በፈጣሪ ትዕዛዝ ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ ሳይቀር መንግስት ተጠያቂነትና ሃላፊነት አለበት፡፡ስለዚህ መራጩ ህዝብ ሁኔታዎችን በሚገባ አመዛዝኖ ለመረዳት ካልሞከረ በስተቀር ገዥዉ ፓርቲ ያለሀጥያቱ ለሁሉም ችግሮች ተወቃሽ መሆኑ የተለመደ ነዉ፡፡ተቃዋሚዎች እነሱ ስልጣን ላይ ቢሆኑ ኖሩ ሊሰሩት ወይም ሊቀይሩት የማይችሉትን ጉዳይም ሳይቀር የገዥዉን ፓርቲ የህዝብ አመኔታ ለማሳጣት ሊጠቀሙበት ይሞክራሉ፡፡ በየትኛዉም ሀገር የሚገኙ ተቀዋሚዎች የዚህ ዓይነት የጋራ ባህሪይ ስላላቸዉ የኛዎቹን ብቻ ነጥለን በዚህ ጉዳይ ላይ መዉቀስ አንችልም፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲ ዋነኛዉ ተግባሩም ከገዥዉ ፓርቲ የተሻለ መሆኑን ለመራጩ ህዝብ ማሳመን ነዉ፡፡በሌላ አባባል ገዥዉን ፓርቲ በማሳጣት የህዝብ አመኔታ እንዲያጣ ማድረግ ነዉ፡፡ይህ ጤናማና የተለመደ አሰራር በመሆኑ ገዥዉ ፓርቲ ተቃዋሚዎች ለምን ነቀፉኝ በሚል ሊከፋ አይገባዉም፡፡ለምሳሌ በገፍ የሚደረገዉን ስዴት መነሻ አድርገዉ ገዥዉን ፓርቲን ተጠያቂ በማድረግ ክፉኛ በመተቸታቸዉ ልንወቅሳቸዉ አይገባም፡፡ስልጣን ቢይዙ እነሱ ራሳቸዉ ሊያስቀሩት የማችሉት ችግር እንደሆነ ራሳቸዉ እያወቁ ነዉ የሚተቹት፡፡በስልጣን ላይ ያለዉ ፓርቲም በበኩሉ ነገ ራሱ ከስልጣን ወርዶ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲሆን ልክ ተቃዋሚዎች ዛሬ እያደረጉ እንዳሉት ራሱም ማድረጉ አይቀርም፡፡ዋናዉ ቁምነገር ገዥ ፓርቲ መሆን ጠቀሜታዉ ከፍተኛ የመሆኑን ያህል በተለይ በምርጫ ወቅት በርካታ ነጥብ ለሚያስጥሉ ብዙ ትችቶች እንደሚያጋልጥ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ ሊጠቀስ የሚችለዉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ ዉስጥ ለተፈጠሩት ቀዉሶች መንስኤ የነበሩት የመልካም አስተዳዳር እንከኖች፤ በልማቱ ፍትሃዊ የተጠቃሚነት መብት ጥያቄዎች፤ያልተሟሉና የተሸራረፉ የዲሞክራሲ /መብቶችን ወዘተ ጉድለቶች ለማስተካከል ወይም ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ገዥዉ ፓርቲ ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ጥረት እያደረገ መሆኑ ቢታወቅም ነገር ግን ሁሉንም ችግሮች በአጭር ግዜ መፍታት እንደማይቻልና ግዜ የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ሲነሱ የነበሩና አሁንም እየተነሱ ያሉ የመብት ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢነት እንዳላቸዉ ባያጠራጥርም ተገቢ ስለሆኑ ብቻ ሁሉንም ችግሮች በአንድ ግዜ መፍትሄ መስጠት የሚቻል አይደለም፡፡ከፍላጎቱም በላይ ተጨባጭ አቅም ይወስነናልና፡፡ የችግሮቹ መኖር ብቻ ኢህአዴግን በምርጫ ከስልጣን ለማዉረድ እንደ በቂ ሁኔታ ሊታይ የሚችል ባይሆንም ተቃዋሚዎች እነዚህ ችግሮች የበለጠ በማጮህ የኢህአዴግ ድክመት እንደሆኑ በማድረግ ገዥዉ ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድሩበት እንደሚችሉ የሚጠበቅ ነዉ፡፡

1.4 ኢህአዴግ ለሁሉም የሀገሪቱ ችግሮች ሁሉ ከሚገባዉ በላይ ራሱን ተጠያቂ ማድረጉና መፈጸም የማይችለዉን ሁሉ ቃል መግባቱ፤

ኢህአዴግ በቅርቡ በሀገራችን በተከሰተዉ ሁከት በመንስኤነት የተዘረዘሩ ጉዳዮች ላይ ሁሉ የእኔ ድክመት ነዉ ቢሎ በፈቃደኝነት ራሱን ተጠያቂ ማድረጉና ለችግሮቹም መፍትሄ ለማስቀመጥ ደፋ ቀና ማለቱ የሚያስመሰግነዉ ቢሆንም ነገር ግን ይሄን ሁኔታ ሊጠቀሙበት ለሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሱን በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ እንደሰጠና ለሚቀጥለዉ ምርጫ ዉድድር ገና ከመቅረቡ በፊት ቢያንስ 25% አካባቢ የድጋፍ ድምጽ ሊያሳጣወዉ እንደሚችል መጠበቅ አለበት፡፡ኢህአዴግ ስህተቱን ሲላመነ ብቻ ተወዳጅና ተመራጭ መሆን አይችልም፡፡ስህተቱን አምኖ ተቀብሎ አርማለሁ በሚል ቃል የገባላቸዉ ጉዳዮች ላይ በተግባር ለዉጥ ማምጣት መቻል አለበት፡፡ኢህአዴግ የህዝብ ድጋፍን ላለማጣት ማድረግ የሚችልበት አንድ ብቸኛ አማራጭ ቢኖር አስተካክላለሁ ቢሎ ቃል የገባቸዉን የቀዉሱ መንስኤ የነበሩ ችግሮችን ሁሉ በተግባር መፍትሄ መስጠት ሲችል ብቻ ነዉ፡፡

የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን በተግባር መቅረፍ መቻል አለበት፡፡በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ የመጣዉን ሙስና ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባይችል እንኳን ቢያንስ መቀነስ መቻል ሊኖርበት ነዉ፡፡ሌሎች ጉዳዮችን ለግዜዉ ትተን በነዚህ ብቻ እንኳ ምን ያህል ሊሳካለት እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አንችልም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የራሱ ችግሮች የሆኑትን ብቻ ሳይሆን ከሱ ቁጥጥር ዉጭ የሆኑትን ችግሮች ሁሉ እንደራሱ ችግር አድርጎ ተቀብሎ አስተካክላለሁ ቢሎ ቃል መግባቱና እንደሚጠበቀዉም ለዉጥ ማምጣት ካልቻለ ለቀጣዩ ምርጫ የራሱን ገመድ እንደሚያሳጥር ምንም ጥርጥር የለዉም፡፡ድክመቶቼ ናቸዉ ባላቸዉ ላይ ሁሉ ቃል በገባዉ መሰረት ተግባራዊ ማድረግ ካልቻለ ተመልሰዉ ለሽንፈቱ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ ኢህአዴግ የራሱን ገመና በአደባባይ ይፋ ሲያወጣም ይሄ እንደሚሆን በቅድሚያ ሳያስብበት ይቀራል ብዬ አላስብም፡፡ኢህአዴግ በዚህ ረገድ የታየበት ቁርጠኝነት ስልጣኑን ሊያሳጣዉ እንደሚችልም ተገንዝቦ የዚያ ዓይነት ዉጤት ቢመጣም በፀጋ ለመቀበል ተዘጋጅቶ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በምርጫዉ ወሳኝ የሆነዉ መራጩ ህዝብ ይህንን የኢህአዴግን አቋም ይገነዘብለታል ብዬም አስባለሁ፡፡ኢህአዴግ ጥፋቱን አድበስብሶና በሌሎች አላኮ ምርጫዉን ሸዉዶ ማለፍ እየቻለ እንደዚያ አለማድረጉ ሃላፊነት የሚሰማዉ በመሆኑና ለህዝቡ ካለዉ ከበሬታ በመነጨ እንደሆነ ህዝቡ ይረዳል የሚል እምነት አለኝ ፡፡

ኢህአዴግ ካለፈዉ ቀዉስ በኋላ ብዙ ብዙ ነገር ቃል ገብቷል፡፡ እንደእኔ እምነት ገና ለገና ችግር ተፈጥሮአል ተብሎ መንግስት ከሀገሪቱና ከመንግስት የማስፈጸም አቅም በላይ ለመስራት ቃል መግባት ይገባወዋል ብዬ አላስብም፡፡ከዚህ ቀደም በዚሁ “በሆርን አፈየርስ” መንግስት ቅድሚያ ሊሰጣቸዉ የሚገባዉን ጉዳዮች እየለየ በእቅድ ከመስራት ዉጭ አላስፈላጊ ቃል ከገባ ተመልሶ ነገ ተጠያቂነት ሊያስከትልበት እንደሚችል ጠቆም አድርጌ ነበር፡፡አሁን መንግስት እንደሰጋነዉም ቃል የገባዉን ሁሉ አንድ በአንድ እየተገበረ እንዳልሆነ እያየን ነዉ፡፡መንግስት በተጨባጭ እየሰራ ያለዉ አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህልና መስራት የሚችለዉን ያህል ነዉ ፡፡ ከዚያ ዉጭ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ነግር ግን እየሰራ ያለዉና አስቀድሞ ቃል የገባዉ አልጣጣም በማለቱ የህዝብን አመኔታ እያሳጣዉ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡

ህዝብ ከሚገባዉ በላይ ከመንግስት መጠበቁ በራሱ ችግር ሆኖ እያለ ጭራሽ መንግስት የተጋነነና የማይተገበር ቃል መግባት(over-promising ) ጋር ሲደመር በህዝብ ዘንድ ተአማኒነቱን በእጅጉ ይሸረሽርበታል፡፡መንግስት ማንም ሳያስገድደዉ በራሱ ተነሳሽነት ከሚገባዉ በላይ የገባዉን ቃል መፈጸም ይገባዋል፡፡ራሱ ቃል የገባዉን ላለመፈጸም (under-delivery) አንዳችም ምክንያት መደርደር አይችልም፡፡መንግስት ምናልባት የገባዉን ቃል ለመፈጸም የማይችልበት አሳማኝ ምክንያት ካለዉ ለህዝቡ በግልጽ መንገር ይገባዋል፡፡ለምሳሌ የከተማ ባቡር በየአስር ደቂቃ ልዩነት በየፈርማታዉ እንዲደርስ አደርጋለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ከሆነና በየደቂቃዉ ማድረጉ ከዉጭ አኳያ አክሳሪ መሆኑን ተረድቶ በአንድ ሰዓት ልዩነት ማድረጉ የተሻለ እንደሆነ ከተረዳ መንግስት ለዉጡን ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ለህዝቡ ማስረዳት መቻል አለበት፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ አስር የሱኳር ማምረቻ ፋብሪካ እገነባለሁ ብሎ አንዱን እንኳን በታቀደዉ የግዜ ገድብ መጨረሽ ተስኖት መቸገሩ እየታየ ለምን በቃሉ መሰረት መፈጸም እንደተሳነዉ ለሀዝቡ ማስረዳት ካልቻለ በስተቀር መንግስት በህዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ ላይ መዉደቁ የማይቀር ነዉ፡፡ የፕሮጄክቶቹ መጓተት ለከፍተኛ ዝርፊያና ብክነት ተጋላጭ እንደሚያደርግም ህዝቡ መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ በዚህ አጋጣሚም መጥቀስ የሚገባኝ የሲንጋፖር ዜጎች አንድ አባባል አለ ፡፡“Over-promising is more of a problem than under-promising, but under-promising creates an expectation that government is not very competent. ከአቅም በታች በማቀድ ቃል መግባት የመንግስትን ደካማነት የሚያንጸባርቅ ሲሆን ነገር ግን ከአቅም በላይና የማይቻለዉን እሰራለሁ ብሎ ቃል መግባት ደግሞ ተአማኒነት የሚያሳጣ በመሆኑ ለመንግሰት ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ከአቅም በላይ ማቀድ በአጭር ግዜ ከድህነት ለመዉጣት ከመፈለግ የመነጨ ቅን አስተሳሳብ ሊሆን ቢችልም ነገር ግን ተጨባጭ አቅምን ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

1.5 የመንግስት የማስፈጸም አቅም እጥረት መኖር ፤

የመንግስት አፈጻጸም አቅም ሲባል ትክክለኛ ፖሊሲ ከመቅረጽ ጀምሮ በማስፈጸም እንዲሁም ለዜጎች ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ በተግባር በመስጠት ረገድ ያለዉን አቅም ሁሉ የሚመለከት ሲሆን በተጨማሪ በሃገሪቱ የሚከሰቱ ግዙፍ ችግሮችና ቀዉሶችን የመፍታት አቅሙን ባጠቃላይ እንደ መንግስት ሃላፊነት የመሸከም አቅሙን የሚሳይ ነዉ፡፡መንግስት በአንድ ወይም በሌላ ጉዳይ ላይ የማስፈጸም አቅም ማነስ እየታየበት በሌሎች ጉዳዮች ላይ ደግሞ የተሻለ አፈጻጸም ሊኖረዉ ስለሚችል በተወሰነ ጉዳይ ላይ ብቻ የታየ ችግርን መነሻ አድርጎ መንግሰት መምራት አልቻለም የሚል ድምዳሜ መስጠት አይቻልም፡፡በመሰረቱ የአፈጻጸም ጉድለት የመንግስትን አመኔታ ሊቀነስ መቻሉ እርግጥ ቢሆንም ነገር ግን መንግስት ስልጣን መልቀቅ አለበት የሚል ዓይነት ዉሳነ-ህዝብ(ሪፌረንደም) እንደተደረገ የሚያስቆጥርም አይደለም፡፡

የመንግስት የአፈጻጸም አቅም ማነስ ከተጋነነ የህዝብ ፍላጎት፤ ግብታዊ ከሆነ የመንግስት ዕቅድና የሀገሪቱ የፋይናናስ አቅም ደካማነት ወዘተ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ከግምት መግባት ይኖርበታል፡፡የመንግስት የማስፈጸም አቅም ማነስ መገለጫዎች ብዙ ሲሆኑ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ራሱ የሾማቸዉን ባለስልጣናትና ሰራተኞች በአግባቡ መቆጣጠርና መቅጣት አቅቶት ሙስናና የመልካም አስተዳዳር እጦት አስከፊ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ መደረጉ፤ራሱ ያቀዳቸዉን ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የፈሰሰባቸዉን ፕሮጀክቶች ማስጨረስ አቅቶት ለከፍተኛ ብክነት መዳረጋቸዉ፤ህገመንግስቱን መነሻ አድርገዉ ከወጡ ህጎች ጀምሮ ራሱም በየግዜዉ የሚያወጣቸዉን ፖሊሲዎች በሚፈለገዉ ደረጃ ማስፈጸም አለመቻሉ፤እንዲሁም በየአካባባዉ የሚነሱ የእርስበርስ ግጭቶችንና አለመግባባቶች አፈታቱ ፍጥነትና ብልሃት የጎደለዉ መሆኑ..ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸዉ፡፡እንግዲህ መንግስት ከተሸከመዉ ከባድ ሃላፊነት አንጻር እንዲኖረዉ ከሚጠበቀዉ የማስፈጸም አቅም አኳያ ሲታይ ትልቅ ክፍተት መኖሩ ይህንንም ተከትሎ በመንግሰት ላይ አመኔታ መቀነስ መቻሉን መቀበል ያለብን እዉነታ ነዉ፡፡በተለይ በመንግስት ዳተኝነት የተነሳ አለቅጥ የተንሰራፋዉን ዝርፊያ የተመለከተ ሰዉ “ለመሆኑ በሀገሪቱ መንግስት አለ ወይ?” ቢሎ ቢጠይቅ አያስደንቅም፡፡ይህን መሰሉ ጥርጣሬ የብዙዎቹ ዜጎች ከሆነ በርግጥም መንግስታችን የአቅም ችግር እንሚኖርበት ማረጋገጫ ይሆነናል፡፡

1.6 ኢህአዴግ ከልማት ስኬቱ በተጓዳኝ ጠንክሮ ያልሰራቸዉ ጉዳዮች መኖራቸዉ፤

በገዥዉ ፓርቲ በኩልም አስካሁን በተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ህዝቡ ድምጹን ለምን እንዳልነፈገዉ ምክንያቱን በሚገባ ለይቶ ማወቅ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ፤ የፍትህ ፤ሰብአዊ መብት፤ የባህር በር ጥያቄን ያነሱ ሌሎች ፓርቲዎች እያሉ ኢህአዴግን ለመምረጥ የወሰነበትን ምክንያት የኢህአዴግ አመራሮች ቁጭ ቢለዉ ሊወያዩበትና የህዝቡን አርቆ አሳቢነት እንዲረዱ ይገባል፡፡ ከዚህ በኃላ በሚደረገዉ ምርጫ ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ የባህር በርና የወደብ ጉዳይን ችላ ቢሎ የኢህአዴግ የልማት ስኬቶች ላይ ብቻ ያተኩራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን ይፋ አያድርግ እንጂ የባህር በር ጥያቄን መላ እየፈለገለት እንደሆነ ከተባራሪ ወሬዎች ሳንሰማ አልቀረንም፡፡እንዴት ሊያሳካ ይችላል የሚለዉ ጥያቄ እጅግ አስቸጋሪ ስለሆነ ከአሁኑ መናገር አንችልም፡፡ኢህአዴግ የወደብ ጉዳይ አሳስቦት በራሱ ተነሳሽነት ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር ለምርጫ ስኬት ቢሎ ያደርገዋል ብለን አንገምትም፡፡ምክንያቱም ይህች አንዲት ጥያቄ የቱንም ያህል ጠቃሚ ብትሆን ብቻዋን ኢህአዴግን ለሽንፈት አንደማትዳርገዉ በርግጠንነት መናገር ይቻላል፡፡ይህችን ጥያቄ ሲላራገቡ ብቻ ተቃዋሚዎችንም አሸናፊ ማድረግ አትችልም፡፡

የወደብ ጉዳይን የሉአላዊነትና የብሄራዊ ጥቅም ጥያቄ ከሌሎች የኢህአዴግ ጉድሌቶች ጋር አንድነት ተዳብለዉ ሲቀርቡ ኢህአዴግ ላይ ጫና ማሳደራቸዉ አይቀርም፡፡ኢህአዴግ በኩራት ማሳመን በሚችለዉ ልማት ጉዳይ ላይ ብቻ እንነጋገር ሲላለ ብቻ ተቃዋሚዎች ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡እነሱ ለክርክር የመመርጡት አጀንዳ ለኢህአዴግ ብዙም ምቾት የማይሰጡትን ነዉ፡፡ኢህአዴግ ይህን እንደሚገነዘብ እርግጠኛ ነኝ፡፡

በኢህአዴግ በኩልም የህዝብ ፍላጎት በልማት ብቻ እንደማይገደብ ተረድቶ ለወደፊቱ ከልማቱ ጎን ለጎን የፍትህ፤ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳዳር፤ የብሄራዊ ድህነትና የሉአላዊነት ጉዳዮች ዙሪያ የሚታዩ እንከኖችን ለማስተካካል ከፍተኛ ርብርብ ካላደረገ በስተቀር በማንኛዉም ወቅት ላይ የህዝብ ድጋፍ ክፉኛ ሊመናመንበት እንደሚችል መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ስለዚህ ኢህአዴግ አስካሁን ሲሰራ በቆየዉ ጠንካራ ስራዎች ምክንያት የህዝብን ድጋፍ አግኝቶ በተደጋጋሚ ለመመረጥ ቢበቃም ከዚህ በኋላ ለሚመጣዉ ምርጫ በመልካም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የታጨቀ የቆየ ፋይሉን እየጠቀሰ ብቻ ሊመረጥ አይችልም፡፡ከጠንካራ ስራዎቹ በተጓዳኝ በጉድለት ሲጠቀሱበት የነበሩትን እንከኖቹን ሁሉ አንድ ባንድ ለማስተካካል ዝግጁ ካልሆነ በስተቀር ራሱን ከገዥ ፓርቲነት ወደ ተቃዋሚነት ተቀይሮ እንደሚያገኝ ጥርጥር የለዉም፡፡በተለይ አንዳችም ይቅርታ የማያሰጡት የሙስና ፤መልካም አስተዳዳር እጦት፤ የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት መከበር ፤የሚዲያ ነጻነት ወዘተ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ እየመረረዉም ቢሆን ጠንክሮ በመስራት ተጨባጭ ለዉጥ ካላመጣ በስተቀር ቤተመንግስቱን ለቆ መዉጣቱ የማይቀር መሆኑን ካሁኑ ሊያዉቅ ይገባል፡፡

1.7 በህገመንግስቱ አንቀጽ 49/5 መሰረት የወጣዉ ረቂቅ አዋጅ የፈጠረዉ ቅሬታ፤

በቀጣዩ ምርጫ ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል በሚል ካሁኑ ስጋት ያጫረ ጉዳይ ቢኖር ኦሮሚያን በአዲስ አበባ/ፊንፊነ ላይ የልዩ ተጠቃሚነት መብት የሚደነግገዉ የአፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 49/5 መሰረት የወጣዉ ረቂቅ አዋጅ ነዉ፡፡በስራ ላይ ለማዋል የህግ አዉጭዉን ዉሳኔ ብቻ የሚጠብቀዉ ኦሮሚያ በአዲስበባ ልዩ ተጠቃሚነት የሚደነግገዉ አወዛጋቢዉ ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ በስራ ላይ መዋል ሲጀምር በቀጣይ በክልሎችም ሆነ በተለይ በአዲስ አበባ ላይ በሚደረገዉ ምርጫ ላይ የሚኖረዉን አንድምታ ገና ከአሁኑ ለመተነበይ ይከበዳል፡፡ከአዲስ አበባ መራጭ ህዝብ መካካል አብዛኛዉ በአዋጁ አኩራፊ በሆነበት ሁኔታ ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ መልካም ዉጤት እንደማይገጥመዉ መጠርጠር እንችላለን፡፡አዋጁ ይሁንታ አግኝቶ በስራ ላይ መዋል ሲጀመርና አንደ አንዳንዶች ምኞት አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለኦሮሚያ ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ላይ ማሸነፍ ከፈለገ ልክ በመላዉ ኦሮሚያ ሲያደርግ እንደነበረዉ አጩዎችን የሚያቀርበዉ በኦህዴድ ስም ነዉ ወይንስ በፊት ሲያደርግ እንደነበረዉ በኢህአዴግ ስም ነዉ? የሚለዉ በራሱ ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ነዉ፡፡፡ለማንኛዉም ከአዲሱ አዋጅ ጋር ተያይዞ የኢህአዴግ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ቢያንስ በአዲስ አበባ ላይ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ አስተያቶች ሲሰጡ ስለቆዩ እኔ የተለየ የምለዉ አይነኖረኝም፡፡በግሌ ግን ህገመንግስታችን እስከፈቀደ ድረስ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባትና አስካሁን የተነፈገችዉ ጥቅም ካለ እንድታገኝ ቢደረግ በእኔ በኩል የተለየ ተቃዉሞ አኖረኝም፡፡ሆኖም በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል ልዩነት ፈጥሮ ለሌላ ያልተፈለገ ችግር እንዳይዳርገን ተገቢዉ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ያለበት ይመስለኛል፡፡በህገመንግስቱ ስለተቀመጠ ብቻ የግድ ማድረግ አለብን ተብሎ በእልህ ከማድረግ በቂ ግዜ ተወስዶ ሁሉንም ህዝብ ማሳመን ተገቢ ይሆናል፡፡ ለነገሩ የተለየ ጥቅም ተብለዉ የተዘረዘሩት ጉዳዮች አዋጅ ማዉጣትም ሳያስፈልገዉ እንደዚሁ መተግበርም ይቻል ነበር፡፡ልዩ መብት ከተባሉት መካከል በተለይ ኦሮሚኛ ቋንቋን በተመለከተ እንኳን በአዲስ አበባ ቀርቶ ከአማርኛ ጎን ለጎን የፈዴራሉ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ቢሆን የሚከፋዉ ሰዉ ያለ አይመስለኝም፡፡ባህሉንም በተመለከተ ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ህዝብ ባህሉን እንዳያከብር በህግ ክልከላ የተደረገበት ይመስል አዋጅ ማዉጣት ያስፈለገበት ምክንያትም ትርጉም አይሰጠኝም፡፡አሁን አዲስ ነገር ያመጣን ይመስል ከበሮ መደለቃችንና አስር ግዜ አዋጅ !አዋጅ! ማለታችን እንጂ ጫጫታ ያስነሳዉ ፡፤እርስበርሳችን ሊያበጣብጡንም ሆነ ሁከት ለመፍጠር ሰበብ ለሚፈልጉ ኃይሎች ጥሩ አጋጣሚ ነዉ የፈጠርንላቸዉ፡፡ለማንኛዉም ይሄ ጉዳይ ኦሮሚያ ዉስጥ ተነስቶ ከነበረዉ ህዝባዊ ተቃዉሞና ሁከት ተከትሎ በዚህ ወቅት ላይ መነሳቱ የግዜ አመራረጡ ችግር ያለበት ስለሚመስለኝ የነ ጃዋርና ኢሳይያሰ ሰዎች ካልተኙልን በቀጣዩ ምርጫ በኢህአዴግ ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል አገምታለሁ፡፡

1.8 የግብር ጭማሪዉ የፈጠረዉን ቅሬታ ለሁከት መነሻ ለማድረግ እየተዶለተ ያለዉ ሴራ ፤

መንግስት የነጋዴዉ ህብረተሰብ እለታዊ የገቢ ግምት ላይ የተመሰረተ ግብር ዉሳኔ ሲወስን ለሀገር የሚኖረዉን ጠቀሜታ ተረድቶ እንደሆነ ጥርጥር አይኖረኝም፡፡ከጉዳዩ ክብደት አንጻር የግዜ አመራራጡ ላይ ጥንቃቄ አለማድረጉ ሲታይ ኢህአዴግ ለቀጣዩ ምርጫ ብዙ እንዳልተጨነቀ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡የኦሮሚያ የአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚነት የሚደነግገዉ አወዛጋቢ አዋጅ ገና እልባት ባላገኘበት ሁኔታ ይሄኛዉ መጨመሩ ለመንግስት ሁኔታዉ እጅግ አስቸጋሪ እንደሚያደርገዉ ግልጽ ነዉ፡፡አስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሰጡ ከነበሩ አሰተያየቶች እንደተከታተልኩት መንግስት ግብር ጭማሪ ጋር ተያይዞ ከነጋዴዉ ህብረተሰብ አካባቢ በደፈናዉ የግብር ጭማሪዉን የተቃወመ አስተያየት አልነበረም፡፡ከዚያ ይልቅ የተወሰነዉ ግምት የተጋነነ ስለሆነ እንደገና ይታይልን የሚል ብቻ ነዉ፡፡ የሀገራችን ግብር ድርሻ ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ሲታይ ጨርሶ ሊወዳዳር የማይችልና እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ አዉቃለሁ፡፡መንግስት ይሄንን ተረድቶ በማንኛዉም ወቅት ላይ የግብር ስርአቱን ሊያሻሽል እንደሚችል ለብዙ ግዜ ሲጠበቅ የነበረ ነዉ፡፡አሁን የታየዉ ሁኔታ የተጋነነ ነዉ መባሉ ሲሆን ሁኔታዉን ለግብር ከፋዩ በሚገባ ግልጽ ባለመደረጉ እንጂ እንደተነገረለት ብዙም የተጋነነ ሆኖ አይደለም ፡፡

ከዚህም ሌላ የግብር ጭማሪዉ ከወቅቱ የሙሲና ወሬ ትኩሳት ጋር አብሮ በአንድ ወቅት ላይ የቀረበበት አጋጣሚ ምክንያት አንዳንድ ሰዎች መንግስት ከኛ በግብር ስም የሚሰበስበዉን ገንዘብ ለዘራፊዎች አሳልፎ እየሰጠ ወዘተ የሚሉ ቅስቄሳዎች መኖራቸዉ ነዉ፡፡ መቼም ገና ለገና በግለሰቦች የተወሰነ ገንዘብ ይሰረቃል ተብሎ መንግስት ግብር መሰብሰብ አያቆምም፡፡ደግነቱ ግብሩን አስመልክቶ የነበረዉ ማጉረረምረምና ቅሬታ በአሁኑ ሰዓት ብዙም አይሰማም፡፡መንግስትና ግብር ከፋይ ነጋዴዎች የተግባቡ ይመስላል፡፡አብዛኛዉቹም ግብራቸዉን አጠናቀዉ ከፍለዋል፡፡ጥቂት አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር አሁን ሁኔታዉ የሰከነ ይመስላል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ለማጋጋል የሚሞክሩ የዉጭ ኃይሎች ገና ተስፋ ቆርጠዉ ስራቸዉን አላቆሙም፡፡ከሌሎች ብሶቶች ጋር እያዳበሉ ሁከት ለመቀስቀስ መፍጨርጨራቸዉ አልቀረም፡፡የግብር ጉዳይ በምንም ምክንያት የሁከት መነሾ ሊሆን አይችልም፡፡ለሌሎች ብሶቶችን ማዳመቂያ ማድረግም አይኖርብንም ፡፡ለማንኛዉም ይሄ ጉዳይ በሚገባ መልኩን አስከሚይዝ ድረስ ትንሽ አድካሚ ሊሆንብን ይችላል፡፡ግልጽ የሆነዉ ጉዳይ ግን በመጪዉ ምርጫ ላይ በገዥዉ ፓርቲ ላይ የተወሰነ ጫና ሊያደርግበት መቻሉ ነዉ፡፡

1.9 ሃላፊነት የጎደላቸዉ አንዳንድ ሚዲያዎች ሊፈጥሩት የሚችሉት ጫና፤

በአሁኑ ግዜ ምንጫቸዉ ከየት እንደሆነ የማይታወቁና አጠራጣሪ መረጃዎች ጭምር በስፋት ወደ ህዝቡ መምጣት በመቻላቸዉ መራጩ ህዝብ በገዥዉ ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲን የሚመለከቱ የተዛቡ መረጃዎችን አንዱን ከሌላዉ ሳያጣራ እንደወረደ ለማግኘት ሰፊ ዕድል አለዉ፡፡ ባለቤትና ተጠያቂነት ከሌለባቸዉ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚገኘዉ መረጃና ከዉጭ ከሚሰራጩ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉ መልእክቶች በአብዛኛዉ መንግስትን በማጠልሸት ላይ ያተኮሩ ናቸዉ፡፡ በዚህ መንገድ የሚገኘዉን መረጃ የምንነቅፈዉ ገዥዉን ፓርቲና መንግስትን በማጥላላታቸዉ ሳይሆን ከዚያ ይልቅ ሆን ብለዉ ሰለማችንን ለማደፍረስና አንድነታችንን ለማናጋት ግጭት ቀስቃሽ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ከመረጃ ፍላጎት አንጻር የመረጃ ጥማትን ለማርካት ተብሎ የተገኘዉን ሁሉ ያለልዩነት ለመቃረም ለሚፈልጉ ወጣቶች መሬጃዎቹ ከምንም ይሻላሉ ለማለት ካልሆነ በስተቀር ትክክለኛ መረጃ ነዉ ተብሎ ለመቀበል የሚያስችሉ አይደሉም፡፡

በአሁኑ ሰዓት መንግስት በሚቆጣጠራቸዉ በራሱ ሚዲያዎች ወደ ህዝቡ ከሚያደርሰዉ መረጃ ባልተናነሰ ደረጃ ህዝቡ ከሌሎች አማራጭ ምንጮች ያሻቸዉን መረጃ ያገኛል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የመንግሰት ሚዲያዎችን ችላ በማለት መንግስትን በማጥላላት ላይ አትኩረዉ ሃያ አራት ሰዓት ያለመታከት የተዛባ መረጃ የሚያቀብሉ ምንጮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መከታታሉ በሂዴት ሊጎዳን እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች መረጃ ብለዉ ለህዝቡ ከሚያቀርቡት መረጃዎች መካካል ዘጠና ከመቶ(90%) የሚበልጠዉ ሃሰትና ከሃቁ ዉጭ የሆነ የተዛባና የፈጠራ ዜናና በየጥላቻ ቅስቀሳ የተሞላ ነዉ፡፡ እነዚህን አፍራሽ መረጃዎችን (negative information)ህዝቡ ያለ ከላካይ ማግኘት ቢችልም መረጃዉን ክፉና ደጉን ፤ጠቃሚና ጎጂዉን መለየት ይችላል ለማለት አያስደፍርም፡፡ወደ ህዝቡ የሚደርሱ መረጃዎች የተዛቡም የተጋነኑም እንደሆኑ ቢታወቅም መንግሰትንና ገዥዉ ፓርቲን በማስጠላትና የተዛባ አመለካከት እንዲኖር በማድረግ ተስፋ በማስቆረጥ (disillusionment )ረገድ የማይናቅ አፍራሽ ድርሻ እንዳላቸዉ መካድ አይቻልም፡፡ቀስ በቀስ አንዱ ሃሰተኛ መረጃ በሌላ ሃሰተኛ መረጃ ላይ እየተደማማረ በመጨረሻም መራጩ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ በገዥዉ ፓርቲ ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖረዉ ያደርጉታል፡፡ይህ ሁኔታ ለገዥዉ ፓርቲ እጅግ ፈታኝ ነዉ፡፡ለዚህ ሁሉ ችግር ለመጋለጣችን ዋናዉ መንስኤ መንግስት ሀገር በቀል የሆኑ ሚዲያዎችን ማበረታት ባለመቻሉና ራሱን ብቸኛ የመረጃ ምንጭ ለማድረግ መሞከሩ ነዉ፡፡ መንግስት አሁን በሚታየዉ ሁኔታ ከተለያዩ ምንጮች የሚለቀቁ መረጃዎችን ለማስተባባልም ሆነ ወደ ሀዝቡ እንዳይደርሱ ለማድረግ አቅም የለዉም፡፡መፍትሄዉም በሁሉም አሰራሮቹ ግልጽነትን ማስፈን፤ የህዝቡን ዙሪያ መለስ ተሳትፎ ማሳደግና ሀገር በቀል የሆኑ የግል ሚዲያዎችን ማበረታትና የራሱ ሚዲያዎችንም የህዝብ አንደበት ሆነዉ እዉነቱን ብቻ እንዲዘግቡ ማድረግ ነዉ፡፡

እንግዲህ መንግስት እነዚህን ሁኔታዎች ማስተካካል ካልቻለና በነበረዉ ሁኔታ መቀጠል ከፈለገ ሚዲያዎች በፀረ-መንግስትነት አቋማቸዉ ፀንተዉ የህዝቡን ድጋፍ መሳጣት ብቻ ሳይሆን ለአመጽ ከመቀስቀስ እንደማይመለሱ አስካሁን ያለፍንበት ሁኔታ ያረጋገጠዉ ነዉ፡፡ ፀረ-መንግስት ሚዲያ ገዥዉ ፓርቲና የመንግስት ህልዉና ላይ የሚያደርጉት ጫና አንድ ብርገድ በሚገባ የታጠቀ ሽፍታ ሊያደርስ ከሚችለዉ ጫና የሚተናናስ አይደለም፡፡ስለዚህ ሚዲያዉ ብቻዉን ኢህአዴግን ከቤተ-መንግስት ለማስወጣት ባይቻለዉም ተቀናቃኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማበር ኢህአዴግ ላይ ቀላል የማይባል ጫና መሳደር መቻሉ ጥርጥር የለዉም፡፡

2. ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ምናልባት ሽንፈት ቢገጥመዉ ሊከሰቱ የሚችሉ ተጠባቂ ሁኔታዎች ፤

ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ብዙ ስለቆየ ብቻ “ተወደደም ተጠላ ወርዶ በሌላ ፓርቲ መተካት አለበት” የሚሉ አይጠፉም፡፡ይሄን ማለታቸዉ ብዙም የሚያስገርም አይደለም፡፡የሚያስገርመዉ ግን ኢህአዴግን ከምርጫ ዉጭ በራሱ ፈቃድ ስልጣን በቃኝ ቢሎ እንዲወርድ የሚፈልጉና እንደዚያም ሊያደርግ ይችል ይሆናል ብለዉ በተስፋ የሚጠብቁ መኖራቸዉ ነዉ፡፡እንደዚህ የሚያስቡ ሰዎች ኢህአዴግ ማለት ድርጅት እንጂ አንድ ግለሰብ አለመሆኑን የዘነጉ ነዉ የምመስለኝ፡፡ምናልባት አቶ ኃይለማሪም አሁንስ መረረኝ ስልጣን በቃኝ ብለዉ ሊለቁ ይችሉ ይሆናል፡፡ምናልባት ምክትላቸዉ አቶ ደመቀ መኮንን ብለፋ ብደክም ትንሽ እንኳን ጠብ ለማይል ነገር ምን አደከመኝ፡፡ጎመን በጤና ብለዉ ስልጣን ለቀዉ ሊወርዱ ይችላሉ፡፡ይሄ በግለሰብ ደረጃ ስለሆነ በዚህ መልክ ቢታሰብ ችግር የለዉም፡፡በኛ ሀገር ታሪክ ያልተለመደ ቢሆንም ቢያንስ በንድፈሃሳብ ደረጃ ቢታሰብ ክፋት የለዉም፡፡፡ነገር ግን አንድን ድርጅት በተለይም ኢህአዴግን ገና ለገና በስልጣን ላይ መቆየቱን ብቻ እንደ ምክንያት በመዉሰድ የመንግስት ስልጣን በነጻ እንዲያስረክብ መጠበቅ የዋህነት ነዉ፡፡ ኢህአዴግን ከስልጣን ማዉረድ ከተቻለ መዉረድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ በምርጫ ካርድ ብቻ ነዉ፡፡

ህዝብ ኢህአዴግን ካልፈለገ ይሄን ማድረግ አያሳነዉም፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ ኢህአዴግ ለተወሰነ ግዜ በሌላ ሊተካ የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር ማንኛችንም የምንጠላ አይመስለኝም፡፡ኢህአዴግ ከዚህ ሁሉ ግዜ በኋላ ትንሽ እረፍት ቢጤ ቢያደርግ እኔም ቢሆን አልጠላም፡፡ቢያንስ ለአንድ ምርጫ ዘመን ያህል አረፍ ብልና እንደገዥ ፓርቲ ሳይሆን እንደ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ ብናየዉ ብዙም አያስከፋም፡፡ምክንያቱም ተቃዋሚ ፓርቲነትን ኢህአዴግ በሌሎች እንጂ በራሱ አያዉቃትምና፡፡

ኢህአዴግ በታሪኩ ተቃዋሚ ሆኖ አያዉቅም፡፡በደርግ ዘመን ትጥቅ ይዞ በረሃ ሆኖ የተዋጋ በመሆኑ የዛ ዘመኑ ህወኃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲ ነበር ለማለት አያስችለንም፡፡በገዥ ፓርቲነት የሚሊዮኖች ድጋፍ ለማግኘት የተሳካላትን ያህል በተቃዋሚ ፓርቲነት ይሄ ድጋፍ ይቀጥል እንደሆን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ኢህአዴግ በአሳፋሪ ሽንፈት ስልጣን ከመልቀቅ በትንሽ ድምጽ ተበልጦ ስልጣን መልቀቁ ለራሱም ቢሆን ይበጀዋል፡፡ ተቃዋሚዎች አስካሁን ቤተመንግስት መግባት ያልቻሉበት ብቻ ሳይሆን አንድም ተቃዋሚ በሀገሪቱ ፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የተሳናቸዉ ለምን እንደሆነ ኢህአዴግ ሊገነዘብ የሚችለዉ አሁን በስልጣን ላይ እያለ ሳይሆን ከስልጣን ወርዶ በተቃዋሚ ፓርቲነት ደረጃ ሆኖ ነዉ፡፡የተቃዋሚ ፓርቲን ፈተና ለመገንዘብ ተቃዋሚ ሆኖ ከማየት ዉጭ የተሻለ አጋጣሚ አይኖርም፡፡ትንሽ ከስልጣን ራቅ ቢሎ መቆየቱ ራሱን አስተካካሎ በደንብ ተዘጋጅቶ ለመምጣትም በቂ ግዜ ይሰጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢህአዴግ በባዶ ስልጣን እንዲለቅ መጠበቅም ጅልነት ነዉ፡፡ ስልጣን በነጻ ይልቀቅ እየተባለም አይደለም፡፡ኢህአዴግን በምርጫ ብቻ ነዉ ከስልጣን ማዉረድ የሚቻለዉም የሚፈቀደዉም፡፡ሊሆን የሚገባዉም እንደዚያ ነዉ፡፡እናም ኢህአዴግ ምናልባት ሽንፈት ቢገጥመዉ ያለምንም እገጭእጓ በፈቃደኝነት ስልጣን አስረክቦ እንዲለቅ ሊያበረታታዉ የሚችል ሁነኛ ነገር ልናስቀምጥለት ይገባል፡፡ኢህአዴግን በገዥ ፓርቲነት ብቻ ለለመደ ህዝብ ኢህአዴግን ከስልጣን ዉጭ ማሰብ በራሱ እንደሟርተኝነት እንደሚያስፈርጅ አልጠፋኝም፡፡ነገር ግን ኢህአዴግን ከመንግስት ስልጣን ዉጪ ማሰብ የማይፈቅዱ ወገኖች ከኢህአዴግ ዉጭ ሌላ እንዲመጣብን አንፈልግም ከሚል ነዉ ወይንስ ኢህአዴግ ቢሸነፍም በፋደኝነት ስልጣን አይለቅም ከሚል ስጋት ይሁን ግልጽ አይደለም፡፡ማንም የፈለገዉን ቢያስብ በሀገራችን ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አስከተካሄዴ ድረስ ማን ስልጣን ይያዝ የሚለዉ ጉዳይ ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡ኢህአዴግንም ቢሆን ከአስካሁኑ አቋሙ ለመገንዘብ እንደቻልኩት ስልጣን ለመልቀቅ ይሰጋል ከተባለ ሊሰጋ የሚችልበት ዋነኛ ምክንያት ቢኖር ለዘመናት የደከመበት ህገመንግስታዊ ስርአት እንዳይቀለበሰና የተጀመረዉ ልማት እንዳይደነቃቀፍ ከመስጋት የመነጨ ነዉ የሚመስለኝ፡፡ኢህአዴግ ቢሸነፍም ፈቃደኛ ሆኖ ስልጣን በጭራሽ እንደማይለቅ የሌሎቹን አቋም ባለዉቅም የኢዴፓ እምነት እንደዚያ እንደሆነ ይፋ ባደረገዉ አንድ ሰነዱ ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ኢህአደግ ቢሸነፍም ስልጣን በጭራሽ አይለቅም በሚለዉ መላምት ተስፋ ከምንቆርጥ ራሳችንን በኢህአዴግ ቦታ በማድረገ ኢህአዴግ በምርጫ ቢሸነፍ ያለ አንዳች ግርግር ለመልቀቅ የሚደፋፈረዉ ቢያንስ ጥቅት ቅድመ-ሁኔታዎች ማሟላት ስንችል ይመስለኛል፡፡ቢያንስ ኢህአዴግ ከአምስት ዓመት በኋላ ተመልሶ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት እንደሚገባ እንዲተማመን ማድረግ ይኖርብናል፡፡መቼም ኢህአዴግ ባቀናዉ ሀገር ቤተ መንግስት ለቆ ሲወጣ በባዶ ሂድ አይባልምና አንዳንድ ቅድመ-ሁኔታዎችን ልናመቻችለት የሚገባን ይመስለኛል፡፡አስኪ እነዚህን በጥቅቱ ለመጥቀስ ልሞክር፤

· ተተኪዉ ፓርቲ የተጀመረዉን የዲሞክራሲና የልማት ጉዞ አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኝነቱም አቅሙም ያለዉ ሊሆን ይገባል፡፡

· የሀገሪቱን ሉአላዊነት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ ብቃት ያለዉና ከፍተኛ ብሄራዊ ቀዉስ ወይም አደጋ ወይመ ስጋት ሲፈጠር የሰከነ አመራር በመስጠት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ማስጠበቅ የሚችል ሊሆን ይገባል፡፤

· ህገመንግስቱንና በህገመንግስቱ መሰረት የተቋቋሙ ዲሚክራሲዊ ተቋማትን ከህዝብ ፈቃድና ህገመንግስታዊ አግባብ ዉጭ በስሜት ተነሳስቶ ወደ ቅልበሳ የማይገባ በስርአቱና በህገመንግስቱ ጠንካራ እምነት ያለዉ ሊሆን ይገባል፡፤

· ኢህአዴግ በስልጣን ዘመኑ ለማስተካካል የተሳነዉን የመልካም አስተዳዳርና የሙስና ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመቅረፍ የሚችል ሊሆን ይገባል፡፡ኢህአዴግ አሰካሁን የሰራቸዉን እዉቅና በመስጠት ሊያሟ ያልቻላቸዉን ደግሞ ለማሟላትና የቀድሞ ስኬቶችን ይበልጥ አጠንክሮ ከመሄድ ዉጭ ኢህአዴግን ለማጥላላት ሲባል ብቻ ቀድሞ የተሰራዉን መልካም ስራ ሁሉ ዋጋ ለማሳጣት ወይም ለመደምሰስና ስርአቱንም ለመቀልበስ የሚደረግ ሙከራ እንደማይኖር በእርግጠኝነት የሚታመን ሊሆን ይገባል፡፡

· በኢህአዴግ በኩልም ለዚህ ዓይነቱ ያልተጠበቀ ክስተት ራሱን በቅድሚያ ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ሽንፈት ከመጣም በፀጋ ለመቀበልና ከአሸናፊዉ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጅ ሊሆን ይገባል፡፤ ኢህአዴግ አመራሩ ብቻ ሳይሆን አባላቱንም ለዚህ አይነቱ ክስተት በቅድሚያ በማሳመን የስነሊነቡና ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል፡፤

· የኢህአዴግ አባላት በግላቸዉ ከሰሩት ወንጀል ወይም የህግ መተላለፍ ዉጭ እንደ ድርጅት በጅምላ አንዳችም በቀል ወይም የጅምላ ዉንጀላ ተጠያቂነት እንደማይኖር ተገቢዉ ማራጋገጫ ዋስትና ሊኖር ይገባል፡፤

· ኢህአኤግ ምናልባት ተሸናፊ ሆኖ ስልጣን ከለቀቀ በኋላ እንዴ ድርጅትም ሆነ አባላቱ በግል ለምርጫ ለመወዳዳር አንዳችም ገደብና ጫና የማይደረግባቸዉ ሊሆን ይገባል፡፡የድርጅቱ አባላትና አመራሮች በሙያቸዉና በአቅማቸዉ መስራት በሚፈልጎት የመንግስት፤ የድርጀትም ሆነ የግል ስራ ላይ ለመሳተፍ የሚያግዳቸዉ ሁኔታ ሊኖር አይገባዉም፡፡

· ሽንፈት አይቀሬ ከሆነ ኢህአዴግ እንደ መንግስትም እንደገዥ ፓርቲም የተረከባቸዉን የሀገሪቱን ሃብትና የመንግስት ሃላፊነቶች፤ ተጀምረዉ ፍጻሜ ያላገኙ ብሄራዊ ጉዳዮችን በአግባቡ ርክክብ ለማድረግ በሚያስችለዉ ደረጃ በቂ ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል፡፡

· ኢህአዴግ የሀገሪቱ የመከላከያ የፖሊሲና፤ የደህንነት አካላትና ከፓርቲ ዉገና ዉጭ በገለልተኝነት ስራቸዉን እንዲሰሩ የሚጠበቁ ሌሎች አካላት ሁሉ ወደ ፊት የኢህአደግን ሽንፈት ተከትሎ የሚገጥማቸዉ አንዳችም ችግር እንደማይኖርና ወገንተኝነታቸዉን ለህገመንግስቱና ለህዘቡ እንዲሆን በሚገባ ሊያስተምሯቸዉና ዋስትና ሊሰጣቸዉ ይገባል፡፡

· ምርጫን ተከትሎ ምናልባት በራሱ ደጋፊዎች ሆነ በተቃዋሚ ደጋፊዎች ሊከሰት የሚችልን ሁከት ለመቆጣጠር እንዲቻል ካሁኑ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል፡፤

· ኢህአዴግ አስካሁን አመኔታ ሰጥቶት ለመረጠዉ ህዝብ ከበሬታ ሊኖረዉ ይገባል፡፡ምርጫዉ ካልቀናዉ ሽንፈቱን በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀት አለበት፡፡ በምርጫዉ ድል ከቀናዉ ደግሞ የከዚህ ቀደሙ ዓይነት 90 እና 100 ከመቶ አሸናፊነት የምርጫውን ተአማኒንት የሚያሳጣ መሆኑን ተረድቶ የዚህ አይነቱ ሁኔታ ዳግም እንዳይከሰት ከአሁኑ ጠንከሮ መስራት ይገባዋል፡፡ኢህአዴግ በ100 % ድምጽ አግኝቶ አሸናፊ ከሚባል በትንሽ ድምጽ ተበልጦ ተሸናፊ ቢሆን በህዝቡ ዘንድ የበለጠ ከበሬታ እንደሚያሰጠዉ ሊያዉቅ ይገባል፡፡

3. ለሀገርና ለህዝብ ሲባል እርምት ሊደረግባቸዉ የሚገቡ አንዳንድ የተዛቡ አመለካካቶች ፤

· በገዥዉ ፓርቲ አካባቢ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከለለ ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚለዉ የአንዳንድ አባላቱ ማሰፈራሪያ ጎጂነቱ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለህዝቡም ጭምር መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡አንዳንድ ከድርጅቱ ዓላማ ያፈነገጠ ጽንፈኛ አቋም ያላቸዉ የገዥዉ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች አንዳሉና በባለፈዉ 97 ምርጫ ማግስት በቁጭትና በደም ፍላት በጣም አደገኛ መልእክት ለማስተላለፍ የሞከሩና ዲሞክራሲን የህጻናት መጫወቻ አድርገዉ የሚያስቡትን በሀገሪቱ ምርጫ የሚደረገዉም እነሱ የሚደግፉትን ፓርቲ ብቻ ህጋዊ ለማድረግ እንደሚደረግ እንጂ ሌሎችም ስልጣን ለመያዝ ህገመንግስታዊ መብት እንዳላቸዉ ፈጽሞ የማይረዱ አባላቱን ገዥዉ ፓርቲ ሊያርማቸዉና ሊገስጣቸዉ ይገባል፡፡ ይህን ተከትሎም ኢህአደግ ቢሸነፍም ፈቃደኛ ሆኖ ስልጣን አይለቅም የሚለዉ አመለካከት ህዝቡን ተስፋ ከማሰቆረጥና ሁከት ለመቀስቀስ ሰበብ ለመፈለግ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ጥቅም ስለማይኖረዉ ለዚህ መሰረተቢስ አስተያየት ህዝቡ ጆሮዉን ማዋስ አይኖርበትም፡፡ምናልባት ይህ ጉዳይ እየተነሳ ያለዉ የአንዳንድ የገዥዉ ፓርቲ አባላትን ንግግርን በማስታወስ ከሆነ በዚህ ረገድ እርምት ሊደረግበት ይገባል፡፡

· በተቃዋሚዎች በኩልም በምርጫ መሸነፍን በጸጋ ለመቀበል በጭራሽ የማይፈልጉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በተግባር ሁከት የማስነሳት አቅም ባይኖራቸዉም ቢያንስ ህዝቡ በምርጫዉ አመኔታ እንዳይኖረዉና በዉጭዉ ህብረተሰብ ዘንድም የሀገሪቱን መልካም ገጽታ የሚያበላሸ ጎጂ ስራ ከመስራት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ልክ እንደ ገዥዉ ፓርቲ ይብዛም ይነስም የህዝብ ዓላማ ያነገቡና በርካታ ደጋፊ ህዝብ ያላቸዉ በመሆኑ ዓላማቸዉን ለህዝብ ለማስተዋዋወቅና የህዝብ ድጋፍን ለማግኘት ዕድሉን ሊነፈጉና እንቅፋት ሊበዛባቸዉ አይገባም፡፡መራጩ የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን ተቀዋሚ ፓርቲ በሌለበት ዲሞክራሲ ትርጉም አንዳማይኖረዉ ተረድቶ ተቃዋሚዉንም ገዥዉ ፓርቲንም በአንድ አይን በእኩል ማዬት እንደሚገባዉ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ተቀዋሚዎች ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እንደ አጋር እንጂ እንደ ጥፋት ኃይልና እንደ እንቅፋት የመቁጠር ልማድ ለሀገሪቱ የማይበጅ መሆኑ ታዉቆ ሊታረም ይገባዋል፡፡ተዋሚዎቸም ቢሆኑ ኢህአዴግን በጭፍን መጥላታቸዉንና የጠላትነት አመለካከታቸዉን ሊያርሙ ይገባል፡፡

· የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ደጋፊዎቻቸዉ ማወቅ የሚገባቸዉ አንድ ጉዳይ ቢኖር ሰላማዊ ባልሆነ የኃይል መንገድ ኢህአዴግን ከስልጣን ማዉረድ ተገቢ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ቢሞክርም በዚህ መንገድ ፈጽሞ እንደማይቻል ነዉ፡፡ይህን የኃይልና የአመጽ መንገድ በተግባር መሞከር ቀርቶ ስለዚህ ጉዳይ ማሰብም ሆነ ማለም አይገባቸዉም፡፡ይህ መንገድ ቢሳካም ባይሳካም መሞከሩ በራሱ ሀገሪቱን ወደ ለየለት ቀዉስ የሚያስገባት በመሆኑ ነዉ፡፡ በተጨማሪ ማንኛዉም ዓይነት የኃይል መንገድ ኢህአዴግን ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ላይ እንዲቆይ መልካም አጋጣሚና ምክንያት እንዲሆንለት ከማማቻቸት ባለፈ በግርግርና በጉልበት ከስልጣን ማዉረድ የሚቻልበት አንድም ዕድል እንደሌለ መዘንጋት አይኖርባቸዉም፡፡ኢህአዴግን ለማሸነፍ በጣም ቀላል ባይሆንም የተሻለዉ መንገድ ህጋዊዉን የምርጫ መንገድ መከተል ብቻ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ሌላ አቋራጭ ሰላማዊ መንገድ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

· በኢህአዴግ በኩልም ሰላማዊና ህገመንግስታዊዉን መንገድ የመረጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተስፋ ቆርጠዉ የኃይል መንገድን እንደ አማራጭ እንዲያማትሩ መገፋፋት አይኖርበትም፡፡እኔ ካልገዛሁ ስርአቱ ይቀለበሳል ሀገሪቷም ትበታታናለች የሚለዉን (የአንዳንድ ካድሬዎቹን)ማስፈራሪያዉን ከዚህ በኋላ እንደማያዋጣዉ ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ህዝቡ ኢህዴግን ሲመርጥ የቆየዉ የኢህአዴግን ማስፈራራሪያ ሰግቶ ሳይሆን ከኢህአዴግ የተሻለ ለግዜዉ አለመኖሩን በመረዳት ነዉ፡፡ባጭሩ ኢህአዴግን ለመምረጥ ስለፈለገ እንጂ ፈርቶ ወይም ሰግቶ አይደለም ፡፡በዚህ ረገድ በሁለት ጉዳይ እንስማማ፡፡ አንደኛ፡ኢህአዴግ ከስልጣን ስለወረደ ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት መንገድ አትበታተንም፡፡ስርአቱም በፍጹም አይቀለበስም፡፡ሁለተኛ፤ ኢህአዴግን የሚመርጡ ዜጎች ይህን የሚያደርጉት ኢትዮጵያ ትበታተን ይሆናል በሚል ሰግተዉና ፈርተዉ አይደለም፡፡ሶስተኛ ኢህአዴግን ስልጣን ላይ ለማቆየት ተብሎ ወይም ኢህአዴግን ከስልጣን ለማዉረድ ተብሎም አንድትም ጥይት እንድትተኮስና የህዝባችን ሰላም እንዲናጋ አንፈቅድም፡፡ስልጣን ለመንጠቅም ሆነ ስልጣን ላለመልቀቅ ተብሎ በሚደረግ ትንቅንቅ ምክንያት የአንድም ኢትዮጵያዊ ህይወት መጥፋት አይኖርበትም፡፡ አራተኛ በ97 ምርጫ ማግስት እንደተደረገዉ ሁከት ወይም አመጽ ቆስቋሹ ማንም ይሁን ማን -ተቃዋሚም ሆነ ኢህአዴግ በምርጫዉ ምክንያት ለሚፈጠር ማንኛዉም ዓይነት ቀዉስና በዜጎች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሁለቱም ማለትም ገዥዉ ፓርቲም ተቃዋሚዎችም በህዝብ እኩል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሊያዉቁት ይገባል፡፡በቁጣ ተነሳስቶ አደጋ ያደረሰዉ ብቻ ሳይሆን እንዲቆጣ በማድረግ የገፋፋዉ አካል ጭምር ተጠያቂ ይሆናል፡፡ማንም ይቆስቁሰዉ ማንም በሚፈጠረዉ ሁከት ምክንያት በዜጎቻችን ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ጣት እየተጠነቋቀሉ መወነጃጃሉና “ይሄን ያህል ረብሸኛ በምህረት ተለቀቀ !”ማለቱ ለህዝቡ መጽናኛ አይሆንም፡፡ስለዚህ ህዝቡ የሚፈልገዉ “ሰላም!” ብቻ መሆኑን ተረድተዉ ገዥዉ ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ለመንቀሳቀስ በቅድሚያ በጋራ ለህዝቡ ቃል መግባት ይኖርባቸዋል፡፡በበኩሌ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የማይጠናቀቅ ምርጫ ከማድረግ ምርጫ የሚባለዉን ነገር አስከነአካተዉ ባይደረግ እመርጣለሁ፡፡

· ሙሰኞችን የማደኑ ፀረ-ሙስና ትግል ዒላማዉን ወደ ታችና ወደ ጎን ብቻ ሳይሆን ወደ ላይም ጭምር ሊያደርግ ይገባል፡፡መንግስት ሀገር ሊያጠፋ ቆርጠዉ የተነሱትን ጥቂት ዘራፊዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገና በጀመረበትና ቀንደኞቹ ገና አልተነኩም እየተባለ ባለበት ሁኔታ ቀንደኞቹ ሙሰኛ ባለስልጣናት ስማቸዉ አብሮ ባለመካተቱ መንግስት በሙሴኞች ላይ እየወሰድኩ ነዉ ባለዉ እርምጃ ላይ ህዝቡ እርካታ እንዳልተሰማዉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ህዝቡ መንግስትን ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ማበረታታቱ ይሻላል በሚል በመንግስት ሚዲያዎች “የሰራችሁት ጥሩ ነዉ ፡፡አጠናክራችሁ ቀጥሎ!” ማለቱ ባይቀርም ኢህአዴግ በሙስና ላይ በጭራሽ ሊጨነክን የሚችል አንጀት እንደሌለዉ ከበፊቱ በበለጠ ተስፋ የቆረጠበት ሁኔታ ነዉ የሚታዬዉ፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ሙስና አሁን የደረሰበት አደገኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቃዉ በራሱ በመንግስት ስንፍና ምክንያት መሆኑን ብቻ ሳይሆን ዝርፊያዉ እየተከናወነ ያለዉ የመንግስትንና የፓርቲ መዋቅርን በመጠቀም መሆኑን ጭምር ተገንዝቦም እያለ ነገር ግን የባለስልጣናቱ ስም ከሙስና ጋር እንዲነሳ አለመፈለጉ አስገራሚ ነዉ፡፡ ሙስና በዋነኛነት የመንግስትን ስልጣንና መዋቅርን በመጠቀም የሚሰራ መሆኑ እየታወቀም ዘራፊዎቹ ከመንግስት መዋቅር ወጭ ያሉ ለማስመሰልም መሞከሩም አንዱ አሳዛኝ ነገር ነዉ፡፡ኢህአዴግ በቀጣዩም ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ በሚመጡት ምርጫዎች ሁሉ ያለጥርጥር ስልጣኑን ላለማስነጠቅ እንደሚፈልግ ግልጽ ነዉ፡፡በዚህ ማንም የሚከፋ አይኖርም፡፡ቅር የሚያሰኘዉ ጉዳይ ግን ህዝቡን በድጋሚ እንዲመርጠዉ የሚፈልግ ገዥ ፓርቲ ህዝቡን እየበደሉት ላሉት ጥቂት ሙሴኞች ርህራሄ እያሳየ የህዝብን ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ ማሰቡ ነዉ፡፡ስለዚህ ኢህአዴግ ጸረ -ሙስና ዒላማዉን ወደጎንና ወደታች ብቻ ሳይሆን ወደ ላይም ጭምር ማድረግ

ይኖርበታል፡፡በዚህ ረገድ የሰሞኑ አያያዙ ሊበረታታ የሚገባዉ ነዉ፡፡

ማጠቃለያ

ኢህአዴግ በስልጣን ላይ በቀየባቸዉ ዘመናት በርካታ ግዙፍ ስራዎችን ሰርቷል፡፡እኛም ሆን የዉጭ ሀገር ታዛቢዎች ለማመን አስከሚያዳግተን ሀገሪቱን እጅግ በአጭር ግዜ ዉስጥ ትልቅ ቦታ አድርሷታል፡፡ኢህአዴግ ለዚህ ሀገርና ህዝብ የሰራዉን ስራ ደጋፊዎቹና መላዉ የሀገሪቱ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ባላንጣዎቹም ጭምር አምነዉ ለመቀበል ተገደዋል፡፡አሁን ኢህአዴግን የገጠመዉ ችግር እንዲህ ነዉ ተብሎ በአንድ ቃል ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ችግሮቹ ዘርፈ ብዙ ናቸዉ፡፡መፍትሄዉም እንደ ችግሩ ባህሪይ ዉስብስብ አስቸጋሪና ዘለግ ያለ ግዜም የሚጠይቅ ነዉ፡፡

የኢህአዴግ ቀጣይ እጣ ፈንታ እነዚህን ችግሮች በመፍታትና ባለመፍታት የሚወሰን ነዉ የሚሆነዉ፡፡ከሁሉም በላይ ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ የህዝብ ይሁንታን አግኝቶ ለመመረጥ ካሰበ በአንድ ነገር ላይ ብቻ በጀግንነት ሰርቶ ሊያሳየን ይገባል፡፡ሙስናን ማጥፋት ቢያንስ መቀነስ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢህአዴግን ህዝብ ሊመርጥ የሚችለዉ በሌላ ሳይሆን ፤በፀረ- ሙስና ትግል ስኬት ላይ ተመስርቶ ብቻ ነዉ፡፡ በተቃዋሚዎች በኩልም ኢህአዴግን በምርጫ ሊገዳደሩት የሚችሉበትና ከኢህአዴግ የተሻሉ መሆናቸዉን ህዘብን ሊያሳምኑ የሚችሉበት አንድ ምርጥ አጀንዳ ቢኖር ሙስናን እንደሚያጠፉ (ቢንያስ እንደሚቀንሱ)ቃል በመግባት ነዉ፡፡ ኢህአዴግን መገዳደር የሚችሉትም በሌላ አጀንዳ ሳይሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ነዉ፡፡

ስለዚህ ቀጣዩ አብይ የምርጫ አጀንዳ ሙስና መሆኑን ኢህአዴግ ሊረዳ ይገባል፡፡ለኢህዴግ ለሚቀጥለዉ ምርጨ ድል በማድረግ በስልጣን ለመቆየት ወሳኝ ጉዳይ ይሄዉ ነዉ፡፡ኢህአዴግ አስከ ቀጣዩ ምርጫዉ በቀሩት ሶስት ዓመታት ዉስጥ ሙስና ላይ አንድ ተአምር መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡አሁን የጀመረዉን በሙሰኞች ላይ እርምጃ የመዉሰድ ትግል አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ለተቃዋሚዎችም ከእንግዲህ የሚኖራቸዉ ተስፋ እንደ ከዚህ ቀደሙ የባህርበር፤ ፌዴራላዊ ስርአት፤ አንቀጽ 39 ፤ሚዲያ ወዘተ ሳይሆን በሙስና ላይ የሚኖራቸዉ አቋም ነዉ፡፡በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቢዉ ጥያቄ ከሙስናና ዝርፊያ መገላገል ነዉ፡፡ ኢህአዴግም ይሁን ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ ይህን እዉን ማድረግ የሚችል ከሆነ ያለ ጥርጥር የህዝብን ከበሬታ ያገኛል፡፡

በሀገሪቱ ዉስጥ ለተፈጠሩት ቀዉሶች መንስኤ የነበሩት የመልካም አስተዳዳር እንከኖች፤ በልማት ፍትሃዊ የተጠቃሚነት መብት ጥያቄዎች፤ያልተሟሉና የተሸራረፉ የዲሞክራሲ መብቶችን ወዘተ ጉድለቶች ለማስተካከል ወይም ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ገዥዉ ፓርቲ ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ጥረት እያደረገ መሆኑ ቢታወቅም ነገር ግን ሁሉንም ችግሮች በአጭር ግዜ መፍታት እንደማይቻልና ግዜ የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ሲነሱ የነበሩና አሁንም እየተነሱ ያሉ የመብት ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢነታቸዉ ባያጠራጥርም ተገቢ ስለሆኑ ብቻ ሁሉንም ችግሮች በአንድ ግዜ መፍትሄ መስጠት የሚቻል አይደለም፡፡ከፍላጎታችንም በላይ ተጨባጭ አቅማችን ይወስነናልና፡፡ስለዚህ የችግሮቹን መኖር ብቻ በማየትና እንደ ኢህአዴግ ድክመት ቆጥሮ ኢህአዴግን በምርጫ ከስልጣን ለማዉረድ እንደ በቂ ሁኔታ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡እነዚያ ችግሮች ለኢህአዴግ ድክመት እንደተጨማሪ ነጥብ ሊያገለግሉ መቻላቸዉና በምርጫዉ ላይ ጫና ማሳደር መቻላቸዉ የሚያጠራጥር ባይሆንም ነገር ግን በዚህ ምክንያት ብቻ በገዥዉ ፓርቲ ላይ ሽንፈት ሊያስከትሉ አይችሉም፡፡

ገዥዉ ፓርቲ በህዝቡ ዘንድ የነበረዉ ተአማኒነት በነዚህ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት እንደቀድሞዉ አለመሆኑንና ይልቁንም እየተሸረሸረበት መምጣቱን ተቀብሎ የህዝቡን ድጋፍና አመኔታ መልሶ ለማደስ የሚያስችለዉን ስራ ይገባዋል፡፡ህዝቡ አሁንም እንደ ድሮዉ እየደገፈኝ ነዉ በሚል ራሱን ማታለል አይኖርበትም፡፡

ኢህአዴግ ቢያሸንፍም ቢሸነፍም ስርአቱ ከዚህ በኋላ ሊቀለበስ የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ይሁን እንጂ በአንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች አካባባቢ በስርአቱና በገዥዉ ፓርቲ መካከል የግድ እንዲኖር የሚፈልጉት የአንዱ ህልዉና በሌላዉ ላይ የተመሰረተ ቁርኝትና የስርአቱ የብቻ ባለቤትነት አመለካካከት ከእንግዲህ እንደማያወጣ ሊታወቅ ይገባል፡፡ስርአቱን በማምጣቱና እዉን እንዲሆን በማድረግም ኢህአዴግ ባለዉሌታ መሆኑ ባይካድም ባለቤትነቱ ግን የመላዉ የሀገራችን ህዝቦች መሆኑን መቀበል አለበት፡፡ከእንግዲህ ኢህአዴግን የምንመርጠዉ ስርአቱን ስላመጣልን ለዉሌታዉ ብለን አይሆንም፡፡ከእንግዲህ ኢህአዴግን የምንመርጠዉ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ከሌለ ስርአቱ ስለሚፈርስ ሀገራችንም ስለምትበታታን በሚል ሰግተን አይሆንም፡፡ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ ከዚህ በኋላ ስርአቱን ወደፊት ማራመድ ከተሳነዉና ከተደቀኑብን ችግሮች ሊያላቅቀን ካለቻለ አዉርደን በሌላ እንተካዋለን እንጂ እሱ ከሌለ ስርአቱ ይፈርሳል ብለን ሰግተን አንተዉም፡፡ በመሰረቱ ስርአቱ ሲፈጠርና ሲገነባ ኢህአዴግ በሌለበት ህልዉና እንዳይኖረዉ ተደርጎ ከሆነ የዚህ ዓይነት ስርአት አያስፈልገንም፡፡ደግነቱ ግን ስርአቱም ሆነ ሀገሪቱ ኢህአዴግ ቢኖርም ባይኖርም ያለጥርጥር ይቀጥላሉ፡፡

ኢህአዴግ አስካሁን በተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ህዝቡ ድምጹን ለምን እንዳልነፈገዉ ከነ እንከኖቹም ቢሆን ለምን እንደመረጠዉ ወደፊትም ለምን ሊመርጠዉ እንደሚችል ጠንቅቆ ሊያዉቅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ፤ የፍትህ ፤ሰብአዊ መብት፤ የባህር በር ጥያቄን ያነሱ ሌሎች ፓርቲዎች እያሉ ኢህአዴግን ለመምረጥ የወሰነበትን ምክንያት የኢህአዴግ አመራሮች ቁጭ ቢለዉ ሊወያዩበትና የህዝቡን አርቆ አሳቢነት እንዲገነዘቡ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ህዝቡ የወደብ ጉዳይን፤የሚዲያ ነጻነት የዲሞክራሲ መብት ጉዳይን ያነሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እያሉ ኢህአዴግን መምረጡ ለነዚህ ጉዳዮች ደንታ ስለአልነበረዉ ወይም ደግሞ ጠቀሜታዉን ስለማይረዳ እንዳልሆነ ኢህአዴግ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ከዚህ በኃላ በሚደረገዉ ምርጫ ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ የባህር በርና የወደብ ጉዳይን የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉዳይን ችላ ቢሎ የኢህአዴግ የልማት ስኬቶች ላይ ብቻ ያተኩራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫን ዲሞክራሲያዊ፤ ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ሰላማዊ እንዲሆን ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች እኩል ሃላፊነት እንዳለባቸዉ አዉቀዉ ለዚያ መትጋት ይገባቻዋል፡፡

ልማት ያለ ሰላም፤ልማት ያለ ዲሞክራሲ፤ ልማት ያለ ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል ፤ዲሞክራሲ ያለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፤ዲሞክራሲ ያለ ነጻ ሚዲያ ፤ዲሞክራሲ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ፤የህግ የበላይነት ያለ ነጻ የፍትህ አካል ፤ዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያለ ጠንካራ ፓርላማ እዉን ሊሆን እንደማይችል ተረድቶ ገዥዉ ፓርቲ በዚህ ረገድ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማስተካካል በቁርጠኝነት ሊተጋ ይገባዋል፡፡

ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ሊሸነፍ ይችላል የሚል ግምት ባይኖረኝም ምናልባት ሽንፈት ቢገጥመዉ ወይም በርከት ያለ ወንበር መልቀቅ የግድ ከሆነበት በሱ ጦስ እርስ በርሳችን እንዳንበላላ ካሁኑ ራሱንም ሆነ አባላቱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡

***********

የዚህን ፅሁፍ ያለፉ ክፍሎች

* የመጀመሪያ ክፍል የኢህአዴግ የወቅቱ ተአማኒነትና የቀጣዩ ምርጫ ዕጣ ፋንታዉ

* ሁለተኛ ክፍል ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 2 | ያለፉ የምርጫ ተሞክሮዎችና ለኢህአዴግ ማሸነፍ ዋነኛ ምክንያቶች

*የኮ/ አስጨናቂ /ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories