ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 1 | የኢህአዴግ የወቅቱ ተአማኒነትና የቀጣዩ ምርጫ ዕጣ ፋንታዉ

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ)

መግቢያ

ኢህአዴግ መጪዉን የ2012 ሀገር አቀፍ ምርጫ ተስፋና ስጋት በተቀላቀለበት መንፈስ እየጠበቀ እንደሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ ለኢህአዴግ መጪዉ ምርጫ በአንድ በኩል እንደቀደሙት ምርጫዎች ሁሉ በበርካታ ስኬቶች የታጀበ መሆኑና በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ቀዉሶችን የተስተናገዱበት ዘመን በመሆኑ መጪዉ ምርጫ አልጋ ባልጋ እንደማይሆንለት መገመቱ አይከብድም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም በመጪዉ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተለየ የተስፋ ጭላንጭል ሳይታያቸዉ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዥዉ ፓርቲ ከሀገሪቱ ዋነኛ ተፎካካሪ(ተቃዋሚ) ፓርቲዎች ጋር የጀመረዉ ድርድር መልካም ፍሬ አፍርቶ ሊፈጠር በሚችለዉ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ተቃዋሚዎች በምርጫዉ ማሸነፍ ባይችሉ እንኳን ቢያንስ በርካታ የፓርላማ መቀመጫ እንደሚያገኙ በመታመኑ በነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ቀጣዩ ምርጫ ከፍተኛ ሰላማዊ ትንቅንቅ የሚደረግበት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተስፋ በመደረጉ ካሁኑ ልብ ሰቃይ ቢሆንብን አያስገርምም፡፡

እንደሚታወቀዉ ስለ ምርጫ ሲነሳ ተቀዳሚዉ የህዝብ ፍላጎት ምርጫዉ ያለ አንዳች ሁከትና ትርምስ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሲሆን በአንጻሩ ኢህአዴግም ሆነ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለስልጣን ሲራኮቱ የሰላሙን ጉዳይ ችላ በማለት እንደ ዘጠና ሰባቱ ምርጫ ለችግር እንዳይዳርጉን ካሁኑ መስጋታችን አልቀረም፡፡

ኢህአዴግ በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኝ ገዥ ፓርቲ( incumbent) መሆኑ በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ የልማትና ማህበረ-ፖለቲካዊ ስኬቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ዉስጥ እነዚህን ስኬቶች ሊያደበዝዙበት የሚችሉ በርከት ያሉ ቀዉሶችና ፈተናዎችን ለማስተናገድ በመገደዱ በቀጣዪ ምርጫ ዉጤት ላይ ካሁኑ ስጋት ቢገባዉ አያስገርምም፡፡ በተፎካካሪ (ተቃዋሚ) ፓርቲዎችም በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ስልጣን ይዘዉና በተግባር ሰርተዉ ብቃታቸዉን ያስመሰከሩበት አንድም አጋጣሚ ባይኖራቸዉም በገዥዉ ፓርቲ ሙሉ ፈቃደኝነት ከሰሞኑ እየተመቻቸላቸዉ ባለዉ “የዲሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት” እንቅስቃሴ በመደፋፈር በተጨማሪም ዋነኛዉ ባላንጣቸዉ የሆነዉ ኢህአዴግ ለበርካታ ቀዉሶች በመጋለጡ ምክንያት ቀድሞ የነበረዉ የህዝብ ድጋፍ አሁን ላይ ስለማይኖረዉ በርካታ የፓርላማ መቀመጫ ሊያጣ ይችላል በሚል እምነት ለቀጣዩ ምርጫ ከፍተኛ መነሳሳትና ጉጉት ታይቶባቸዋል፡፡

በተለይም ከዚህ ቀደም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ሳይቀር አንድም ግዜ ተሳትፎ ሲያደርጉ የማይታየዉ ሁኔታ ተቀይሮ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ተቃዋሚዎች ከገዢዉ ፓርቲና ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠዉ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ መታየታቸዉ ቀድሞ ሻክሮ የቆየዉ የሁለቱ ግኑኝነት መሻሻል ለማሳየቱ ማረጋገጫ ነዉ፡፡ ይህ መልካም ግኑኝነትም ለተቃዋሚዎችም ሆነ ለገዥዉ ፓርቲ አርስበርስ መጣራጠርን በማስወገድ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ትልቅ እገዛ ሊያደርግ እንደሚችል ተስፋ ያጫረ ነዉ፡፡

በተቃዉሞዉ ጎራ ካሉት መካከል ሀገር በቀል ከሆኑት ሁለት ወይም ሶስት ከሚሆኑት ዉጭ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ተዳክሟል የሚለዉን መላምት ብዙም የሚያምኑበት አይደሉም፡፡ ከዚያ ይልቅ ለቀጣዩ ምርጫ መደላድል የሚሆናቸዉን ያህል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከገዥዉ ፓርቲ ጋር መደራደሩን መርጠዋል፡፡ ሌሎቹ በዉጭ ሀገር የመሸጉ የዲያስፖራ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከቅርብ ግዜዉ ሁኔታ በመነሳት ኢህአዴግ ፈጽሞ እንዳበቃለትና ዳግመኛ ማንሰራራት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል በሚል እምነት ወደፊት ሊፈጠር የሚችለዉን የስልጣን ክፍተት ለመሙላት በርግጠኝነት ስሜት ካሁኑ በተናጠልም ሆነ በጥምር መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡

ገዥዉ ፓርቲ ለበርካታ ተደራራቢ ችግሮች መጋለጡን ራሱም ባይክድም ነገር ግን በምርጫ ለሽንፈት ሊዳርገዉ የሚችለዉን ያህል ህዝባዊ አመኔታ (public trust) አሳጥቶታል ወይ? የሚለዉ ጥያቄ አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ራሱ የአመኔታ ቀዉስ አጋጥሞኛል የሚል እምነት ካለዉ ከዚህ በኋላ አስከምርጫዉ ድረስ በቀረችዉ አጭር ግዜ ዉስጥ ከዚህ የተአማኒነት ቀዉስ ለመዉጣት በሚያስችለዉ ደረጃ ራሱን በማስተካካል የተመናመነበትን ህዝባዊ አመኔታን ለማደስ (restoring trust) ይቻለዉ ይሆን? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ገዥዉ ፓርቲ ዕድል ፍቷን አዙራበት በምርጫዉ ድንገት ሽንፈት ቢገጥመዉ የህዝብን ዉሳኔ አክብሮ ስልጣኑን በፈቃዱ ይለቅ ይሆን ?ወይንስ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚነሳ ቀዉስ ልንዳረግ እንችላለን ብለን መስጋታችንም ተገቢ ነዉ፡፡

ሀገራችን በኢህአዴግ መሪነት እያስመዘገበችዉ ካለዉ ፈጣን አድገት በተጓዳኝ ከቅርብ ግዜ ጀምሮ እየታየ ያለዉ ምስቅልቅል ሁኔታ መነሻዉ ምንም ይሁን ምን ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲና መንግስት የመጀመሪያዉ ተጠያቂ መሆናቸዉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ በገዥዉ ፓርቲ ተአማኒነት ላይ ጥቁር ነጥብ በመሆን በምርጫ ዉጤት ላይ ጫና ሊያሳድርበት መቻሉ የሚጠበቅ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢህአዴግ ከገዥ ፓርቲነት ወደ ተቃዋሚ ፓርቲነት የሚለወጥበት ወቅት ላይ እንደደረሰ የሚገምቱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

እንግዲህ እኔም የወቅቱን ሁኔታ በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ሊኖር የሚችለዉን አንድምታ ከግምት በማስገባትና ጉዳዩም የሁላችንም ትኩረት ነጥብ መሆኑን በመረዳትም በዚያ ዙሪያ አንዳንድ አስተያየቶችን ለመሰንዘር ወደድኩ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ዜጎች በመንግስት(ገዥዉ ፓርቲ) ላይ ስለሚኖራቸዉ አመኔታ ዙሪያ(public trust in government) ለመንደርደሪያነት ያህል ጥቅል የሆኑ ጉዳዮችን ከነካካሁ በኋላ በቀጥታ የገዥዉ ፓርቲን ወቅታዊ የተአማኒነት ሁኔታ በመቃኘት በዚያ ላይም ተረማምጄ በቀጣዩ ምርጫ ላይ የሚኖረዉን አንድምታና የኢህአዴግን ዕጣፈንታ በግምት ደረጃም ቢሆን ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡

በተረፈ አንባቢዉ በዚህ ጽሁፍ ላይ የቀረበዉ አስተያየት ሁሉ የግል አመለካካቴ እንጂ ባጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር ማንንም የሚወክል አለመሆኑን ታሳቢ በማድረግ በጽሁፉ ይዘት ላይ ማንኛዉም ዓይነት እርምት ቢሰጠኝ ለመቀበል ዝግጁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ በታላቅ አክብሮት ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡

የጽሁፉ አደረጃጃት በሁለት አብይ ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያዉ ክፍል አጠቃላይ የተአማኒነት ጉዳይን በጨረፍታ በመንካት የኢህአዴግን ወቅታዊ የተአማኒነት ሁኔታን የሚቃኝ ሲሆን በሁለተኛዉ ክፍል ደግሞ ኢህአዴግ ወቅቱ ከፈጠረዉ መሰናኪሎችና ተግዳሮቶች በመነሳት በቀጣይ ምርጫ ላይ ዕጣ ፋንታዉ ምን ሊሆን እንደሚችል ግምታዊ አስተያየት የምሰጥበት ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ክፍል በኤዲተሩ ፍላጎት እንደ አስፈላጊነቱ እየተከፋፋለ ሊቀርብ እንደሚችል እያሳሳብኩ ዉድ ግዜያችሁን ሰዉታችሁ ለማንበብ ፈቃደኛ በመሆናችሁ በቅድሚያ ሳላመሰግን አላልፍም፡፡

1/ የመንግስት ተአማኒነት ምንነት፤

የመንግስታቱ ድርጅት(UN) በቭዬና ፣ኦስትሪያ ላይ በ2007 አዘጋጅቶት በነበረዉ አለምአቀፍ የምክክር መድረክ(ኢንተርናሽናል ፎሬም)ላይ ከቀረቡ የጥናት ጽሁፎች መካካል “Building Trust in Government in the twenty-first century” በሚል ርዕስ በቀረበዉ ጽሁፍ ዉስጥ የሚከተለዉ ይገኝበታል፡፡ “One simple question occupying the mind of an ordinary citizen in the streets today is the following: Whom should I be wary of if not the government who wields great power with great temptations to abuse it (Bentham 1999).” ደረጃዉ ሊለያይ ይችል ካልሆነ በስተቀር መልእክቱ የብዙዎቹን ሀገሮች ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ፡፡

በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲ ቁንጮ በሆነችዉ አሜሪካ ሳይቀር ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች መንግስታቸዉን መጠራጠራቸዉና አመኔታ መንፈጋቸዉ የተለመደ ክስተት ነዉ፡፡ በርግጥም ጸሃፊዉ እንዳለዉ በመንገድ ላይ በአጋጣሚ የምናገኘዉን የትኛዉንም ተራ ዜጋ ከሁሉም በላይ ምን እንደሚያሰጋዉ ብንጠይቀዉ ሊሰጠን የሚችለዉ አንድ ምላሽ “በአደራ የተሰጠዉን ስልጣኑን ያለ አግባብ ሊጠቀም ከሚችል መንግስት የበለጠ ከቶ ማንን መስጋት ይኖርብኛል?” የሚል እንደሚሆን ይህም ሁኔታ ይብዛም ይነስም የማይመለከተዉ ሀገር ይኖራል ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል፡፡

መንግስት ያለህዝብ ፈቃድ በጉልበት ስልጣን በያዘበት ሀገር ብቻ ሳይሆን ዜጎች ራሳቸዉ መርጠዉ ወደ ስልጣን ያወጡት ዲሞክራሲያዊ መንግስት ባለበት ሀገርም ቢሆን ዜጎች የገዛ መንግስታቸዉን ፤መጠራጠራቸዉና መስጋታቸዉ የተለመደ ነዉ፡፡ ባደጉ ሀገሮችም ሆነ ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የሚገኙ ዜጎች ደረጃዉ ሊለያይ ይችል ካልሆነ በስተቀር የተጠቀሰዉ ዓይነት የስጋትና የመጠራጠር ስሜት ሊሰማቸዉ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

አምባገነን ስርአት ባለበት ሀገር ደግሞ ዜጎች መንግስታቸዉን አመኔታ መንፈጋቸዉ ብቻ ሳይሆን ክፉኛ መጠራጠራቸዉና መፍራታቸዉ የግድ ነዉ፡፡ የሚገርመዉ ሁኔታ ግን ዜጎች በአንድ ወቅት ከፍተኛ አመኔታ ጥለዉበት በገዛ ፈቃዳቸዉ ወደ ስልጣን ያወጡትን መንግስት ጭምር መጠራጠራቸዉና መስጋታቸዉ ነዉ፡፡ ምክንያቱም የመንግስት ባለስልጣናት የቱንም ያህል መልካም ሰዎች ቢሆኑም የስልጣን ጉዳይ እጅግ ያሳሳልና በማንኛዉም ወቅት ላይ ለህዝብ የገቡትን ቃል ችላ በማለት ከህዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲሰሩ መገኘታቸዉ የተለመደ ስለሆነ ነዉ፡፡ የትኛዉንም መንግስት መቶ በመቶ ማመን ስለማይቻልም ነዉ እርስ በርሳቸዉ የሚቆጣጠሩ የስልጣን አካላትንና ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ማደራጀትና የተለያዩ የዕይታና ቁጥጥር መካኒዝሞችን መዘርጋት የግድ የሆነዉ፡፡

ህዝባዊ አመኔታ ለአንድ ፖለቲካዊ ስርአት ቅቡልነትና ቀጣይነት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ፡፡ በአስተዳዳር ዘይቤዉ እጅግ የተዋጣለትን መንግስትንም ሳይቀር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መጠራጠር ለጤነኛ ዲሞክራሲ ዋስትና ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በአብዛኛዎቹ የአደጉ ሀገሮች ዜጎች በመንግስታቸዉና በተናጠልም በመሪዎቻቸዉ ላይ የሚሰማቸዉን ስሜትና ያላቸዉን አመኔታ ላይ የጥናት ዳሰሳ በማድረግ ደረጃ የመስጠትና ዉጤቱንም ለህዝብ ይፋ ማድረግ የተለመደ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊም ጉዳይ ነዉ፡፡

በመንግስት ላይ በተወሰነ ደረጃና ለአጭር ግዜ የሚቆይ አመኔታ ማጣት ብዙም አንደ አደጋ የሚቆጠር አይደለም፡፡ አደጋ የሚሆነዉ መንግስት ለህዝብ አስተያየት ደንታቢስ ሆኖ ብልሹ ምግባሩን ለማረም ከመሞከር ይልቅ በድርቅና በያዘዉ የተሳሳተ መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ነዉ፡፡ የህዝብ አመኔታ ማጣት ገደቡን አልፎ ይህ መንግስት እኛን አይወክለንም በሚል አዉቅና አስከመንፈግና ጭራሽ የስጋት ምንጭ ተደርጎ አስከመቆጠር የሚያደርስ የከፋ የተአማኒነት ቀዉስ ከገጠመዉ መንግስት ማድረግ ያለበት ቢቻል ራሱን ማስተካከል ካልሆነም ደግሞ አስካሁን በፈቃደኝነት የተገዛለትን ህዝብ አክብሮና አመስግኖ ስልጣኑን አስረክቦ መዉረድ ብቻ ነዉ፡፡

የህዝባዊ አመኔታ ጉዳይ መንግስት አዲስ ፖሊሲና አዲስ ህግ ባወጣ ቁጥር እንደ አዲስ የሚያገረሽ፤ በአንድ ወቅት ደህና ነዉ ሲባልለት ቆይቶ በሌላ ግዜ ክፉኛ የሚሸረሸር ፤መንግስት የሕዝብ ድጋፍ ርቆታል ሲባልለት ቆይቶ በሌላ ግዜ ደግሞ ተመልሶ የሚታደስ እንጂ የተአማኒነት ጉዳይ ዘለአለማዊና ቋሚ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ በአሁኑ ወቅት በመንግስት ላይ ያላቸዉ መተማመን ከምንግዜም እጅግ በወረደ ደረጃ 20% ብቻ ሆኗል፡፡ በአሜሪካ በ1958 ላይ ሶስት አራተኛዉ(3/4) የአሜሪካ ህዝብ በመንግስታቸዉ ላይ አመኔታ የነበራቸዉ ሲሆን ይህም ትልቁ ቁጥር ተደርጎ ነዉ የተቆጠረዉ፡፡

ከዚያ በኋላ ግን በ1960ዉቹ ዉስጥ በቬትናም ጦርነት ጦስ እንዲሁም በ70ዎቹ ዉስጥ ደግሞ በሪቻርድ ኒክሰን ዘመን በወተር ጌት ቅሌትና በሀገሪቱ የከፋ ኢኮኖሚ ቀዉስ በመድረሱ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ ነበር፡፡ እንደገና በመስከረም 9/11 የኒዮርኩ የሽብር ጥቃት ማግስት ደግሞ በመንግስት ላይ የህዝብ አመኔታ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል፡፡ አሁን ደግሞ እጅግ ያሽቆለቆለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

የህዝብ በመንግሰት ላይ አመኔታ እጅግ መቀነስ በአሜሪካ ብቻ የሚታይ ችግር ሳይሆን በመላዉ ዓለም የሚታይ አዝማሚያ ነዉ፡፡ በአንድ ወቅትና በሆነ ጉዳይ ላይ ህዝቡ በመንግሰት ላይ አመኔታዉ ቀነሰ ማለት በድፍኑ መንግሰት ህገ ወጥና በስልጣን ላይ የሚገኘዉም ያለ ህዝብ ፈቃድ ነዉ የሚል ትርጉም አያሰጥም፡፡ መንግሰት ሁልግዜ ወይም አብዛኛዉን ግዜ ትክክለኛ ስራ ይሰራል (to do what`s right always or most of the time) ብሉ ህዝብ ሲያምን ክፍተኛ አመኔታ ይሰጠዋል፡፡ ከህዝብ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ስራ ሲሰራ ደግሞ አመኔታዉን ይነፍገዋል፡፡

መንግስት የህዝብ አመኔታ የመቀዛቀዝ ሁኔታ መኖሩን ሲረዳ ከህዝብ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ስራ እንደሰራ ተገንዝቦ ብዙ አድካሚ ቢሆንበትም እንኳን ተገቢዉን ጥረት ካደረገ የተነፈገዉን ተአማንኒት መልሶ ለማደስ እድል ይኖረዋል፡፡ በአንድ ወቅትና በአንድ አጋጣሚ የህዘብ ድጋፍ ሲቀንስበት ሁኔታዉ ሊስተካካል የሚችል መሆኑን ዘንግቶ መንግስት ራሱን በህዝብ እንደተጠላ በመቁጠር ከህዝብ ጋር እልህ በመጋባት ጭራሽ በጥፋት ላይ ጥፋት እየሰራ ህዝብን ለአመጽ ሊገፋፋ ይችላል፡፡

ጥቅል በሆነ መልኩ “የመንግስት ተአማኒነት” ሲባል ዜጎች በመንግስት ፤በመንግስት ተቋማትና መንግስት በሚያወጣቸዉ ፖሊሲዎች ላይ እንዲሁም ቁልፍ የፖለቲካ አመራሮች ለህዝብ የገቡትን ቃላቸዉን መጠበቅ በቻሉበት ደረጃ ፤በብቃታቸዉ፤ በሃቀኝነታቸዉና በታማኝነታቸዉ ላይ የህዝብ መተማማን መኖር ማለት ነዉ፡፡ የመንግስት ተአማኒነት ሲባል በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስትና ገዥ ፓርቲ ለህዝብ በሚሰጡት አገልግሎት በምላሹ ህዝቡ የሚሰጣቸዉ የይሁንታ ማረጋገጫ ሴርቲፍኬት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ባጭሩ ህዝባዊ አመኔታ ሲባል ህዝብ ለመንግስት የሚኖረዉ አመለካከት ነዉ ማለት ይቻላል፡፡

የመንግስት ተአማኒነት በአጠቃላይ በመንግስታዊ መስተዳዳሩ ላይና በተናጠልም ስርአቱን ለማሳለጥ በተቋቋሙ እያንዳንዱ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ ሲታይም በመንግስት ስልጣን ላይ ባሉ ቁልፍ አመራሮች ላይ የሚኖር መተማመንን የሚመለከት ነዉ፡፡

በመንግስት ተአማኒነት ላይ ትልቅ ድርሻ ያለዉ የመንግስት ፖሊሲ ሲሆን መንግስት በየግዜዉ የሚያወጣቸዉ ፖሊሲዎች የመንግስትን ባህሪይ መግለጫ ሆነዉ ስለሚያገለግሉ ፖሊሲዎች በቀላሉ መንግስትን ህዝባዊ አመኔታ ሊያስገኙለት ወይንም ሊያሳጡት ይችላሉ፡፡ ህዝቡ መንግስት ያወጣዉ ፖሊሲ ላይ ጥርጣሬ ካለዉ ወይም ፖሊሲዉን ካልወደደዉ ያን ፖሊሲ ባወጣዉ መንግስትና ገዥ ፓርቲ ላይ አመኔታ አይኖረዉም ማለት ነዉ፡፡

ዜጎች ለመንግስት በጥቅል ከሚሰጡት አመኔታ በተጨማሪ በተናጠል አንዳንድ የመንግስት ተቋማት ላይ በተለየ አመኔታ ሊያሳድሩ ወይም አምነት ሊነፍጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በህግ አዉጭዉ፤ በፍትህ አካላት፤ በመከላከያና በፖሊስ ፤በሃይማኖት ተቋማት፤ በሚዲያዎች ወዘተ ላይ መንግስትን በጥቅል ከሚያዩበት የተለየ እይታ ሊኖራቸዉ ይችላል፡፡ አንዳንድ ግዜ የአመኔታ ጉዳይ ለግዜዉ ስልጣን ከያዘዉ ፓርቲ ባሻገር ራሱ ስርአቱንም ጥያቄ ዉስጥ ሊያስገባ ይችላል፡፡ እንደ አሜሪካ ባሉ ፕሬዝዳንታዊ ስርአት በሚከተሉና ፕሬዝደንቱ በቀጥታ በህዝብ በሚመረጥበት ሀገር በግል በፕሬዝደንቱ ላይ የሚኖር የህዝብ መተማመን ለአጠቃላዩ ለአገዛዙ ተቀባይነት ማግኘት ወሳኝ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ አለ፡፡

እኛ በምንከተለዉ ፓርላሜንታዊ ስርአት መሰረት በሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለያዙት ሃላፊነት የበቁት በቀጥታ በህዝብ ተመርጠዉ ባለመሆኑ ለሳቸዉ በሚሰጥ የህዝብ አመኔታ ላይ ተመስርቶ አስፈጻሚዉን ሆነ በጥቅል መንግሰትን ለመመዘን አመቺነት አይኖረዉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግስት በህዝብ እንዲጠላም ሆነ እንዲወደድ ለማድረግ የሚያስችል የተወሰነ የግል ድርሻ ሊኖረዉ ቢችልም ከፓርቲያቸዉ ተነጥለዉ ለብቻቸዉ ወሳኝ የሚሆኑበት ዕድል ጠባብ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ በህዝብ ተወዳጅ ሆኖ አቶ ኃይለማሪያም የሚጠሉበትና ኢህአዴግ በህዝብ እየተጠላ ኃይለማርያም ከፓርቲያቸዉ ተነጥለዉ ለብቻቸዉ ተወዳጅ የሚሆኑበት ሁኔታ ብዙም አይኖሩም፡፡ ስለዚህ በኛ ልዩ ሁኔታ የህዝባዊ አመኔታ ጉዳይ ለአመራሩም፤ ለገዥዉ ፓርቲም ሆነ ለመንግስት ለአስፈጻሚዉም ሆነ ለህግ አዉጭዉ ጭምር የጋራ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

የሀገራችንን ህግ አዉጭ የእስካሁኑን አሰራሩን ለመታዘብ እንደቻልነዉ ከአስፈጻሚዉ በተለየ ተወዳጅ ለመሆን የሚያበቃዉ ስራ ሲሰራ አላየንም፡፡ አስፈጻሚዉን በጥብቅ በመቆጣጠር የህዝብ ተአማኒነት የማግኘት ዕድሉን አስካሁን ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡ ስለዚህ ህግ አዉጭዉን ከአስፈጻሚዉ ለይተን ለማየት የሚያስችለን ሁኔታ አይኖርም፡፡ በሌላ በኩል የአስፈጻሚዉ አካል የሆኑ መንግስታዊ ተቋማትን በሚመለከት አንዱ ከሌላዉ በመጠኑ የተሻለ ነዉ ለማለት ካልሆነ በስተቀር በኛ ሀገር ሁኔታ ከገዥዉ ፓርቲና ከአጠቃላዩ ከመንግስት ተነጥለዉ ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ሁሉም በአንድ ሳንባ የሚተነፍሱ አስኪመስል ድረስ የገዥዉን ፓርቲ የልብ ትርታ እያዳመጡ የሚንቀሳቀሱ ናቸዉ፡፡ ምናልባት ከመንግስታዊ ተቋማት መካካል በህዝቡ ዘንድ ከነ እንከኖቹም ቢሆን ገና ህዝባዊ አመኔታና ከበሬታ ያልተነፈገዉ ብቸኛ ተቋም ቢኖር የመከላከያ ሰራዊት ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ዛሬም የህዝብ አመኔታና አለኝታነት ያለተነፈጉት ከመንግስት ዉጭ የሚገኙት የተለያዩ እምነት ተቋማት ናቸዉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የተአማኒነት ሁኔታ በዋነኛነት መንግስት በየግዜዉ በሚያወጣቸዉ ፖሊሲዎችና ህጎች የተቃባይነት (credible policy-making) ደረጃ ላይ በእጅጉ የተመሰረተ ስለሚሆን ጤነኛ የሆነ መንግስት ፖሊሲዎችንና ሌሎች ህጎችን በዘፈቀደና በግብታዊነት ያወጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ እንዲሁም መንግስት አንድን የተለየ ህብረተሰብ ክፍል በልዩ ሁኔታ ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት አስቦ ህግና ፖሊሲ አያወጣም፡፡ መንግስት ፖሊሲና ህግ የሚያወጣዉ አብዛኛዉን ህዝብና ሀገሪቱን ለመጥቀም አስቦና በተግባርም ሊፈጽመዉ እንደሚችል አርግጠኛ ሲሆን ብቻ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

መንግስት የሚያወጣዉ ፖሊሲ ገና ከመነሻዉ ሙሉ የህዝብ ድጋፍ ካገኘ በስራ ላይ ለመተግበር እጅግ ቀና ይሆንለታል፡፡ የመንግስት ፖሊሲ በሚፈለገዉ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከቻለም ዜጎች በመንግስት ላይ አመኔታቸዉ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ያወጣዉን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከተሳነዉ ፖሊሲዉ የዜጎችን አመኔታ እንዳላገኘ በቀላሉ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡

መንግስት ራሱ ያወጣዉን ፖሊሲ ማስፈጸም ከተሳነዉ የማስፈጸም አቅሙ ደካማ መሆኑን ከሁሉም በላይ ደግሞ የህዝብ ድጋፍ እንደሌለዉ ራሱም ስለሚገነዘብ በራስ መተማማኑ እየተሸረሸረበት በመጨረሻም ለዉድቀት ሊዳረግ ይችላል፡፡ የመንግስት ፖሊሲ ከመነሻዉ የብዙዎች ተቃዉሞ ሲገጥመዉና በአተገባባርም እንከን ሲበዛበት ቀደም ሲል በደህና ሁኔታ ላይ የነበረ የህዝብ አመኔታም በአጭር ግዜ ሊያሽቆለቁል ይችላል፡፡

ከመንግስት ስህተቶች ሁሉ እጅግ የከፋዉ ራሱ ያወጣዉን ህግና ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ሲሳነዉ ነዉ፡፡ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የማይችለዉን የትኛዉንም ዓይነት ህግ ባያወጣ ይመረጣል፡፡ የሚያወጣዉ ህግ የአብዛኛዉን ህዝብ ድጋፍ ባጣ ቁጥር መንግስት “ፖሊሲዉን ሰርዤአለሁ” ማለት አንዴ ከጀመረ ከዚያ በኋላ እንደ መንግስት ሀገር የማስተዳዳር ብቃት እንደሌለዉ ራሱ ማረጋጋጫ እንደሰጠ ያስቆጥርበታል፡፡ በዚህ ግዜ የሚኖረዉ አማራጭ ከህዝብ ጋር እልህ ተጋብቶ ያሻዉን ህግ በሀዝብ ላይ በኃይል መጫን ሊሆን ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ የሚያራምድ አይደለም፡፡

መንግስት የህዝብን ፍላጎት ሳይጠብቅና ህዝቡን ሳያማክር የትኛዉንም ዓይነት ምርጥ ፖሊሲ ቢያወጣ ተግባራዊ ሊያደርገዉ ስለማይችል በሂዴት መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ መሆናቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ ስለዚህ መንግስት ከህዝብ ጋር እልህ ተጋብቶ ከህዝብ ፍላጎት ዉጭ“ እኔ አዉቅልሃለሁ!” በሚል የተሳሳተ መሪህ አወዛጋቢ ፖሊሲና ህግ የሚያወጣ ከሆነ ተመልሶ ራሱን መንግስትን እንደሚጎዳ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡

አንዳንድ ግዜ መንግስት ያወጣዉ ፖሊስና የደነገገዉ ህግ ተገቢ ሆኖ እያለ ነገር ግን ህጉ የወጣበት ወቅት የግዜ አመራረጡ(timing) ምክንያት ከፍተኛ ተቃዉሞ ሊገጥመዉ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሰት አመኔታ የሚለካዉ መንግስት ምርጥ የሚባል ፖሊሲ ወይም ህግን በወረቀት ላይ ስላሰፈረ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ነዉ፡፡ በግብታዊነት ታዉጀዉ አስፈጻሚ አካል ያጡና ከፍተኛ ተቃዉሞ የገጠማቸዉ የመንግሰት አዋጆችና ፖሊሲዎች ሁሉ የመንግሰት የማስፈጸም አቅም ደካማነትን የሚያሳዩ በመሆኑ በዚህ ምክንያትም መንግስት የህዝቡን አመኔታ ቢያጣ አያስገርምም፡፡

በመንግስት ላይ የህዝብ መተማማን ጉዳይ በግለሰብ ደረጃ በጭፍን የሚሰጥ ድምዳሜ ሳይሆን ራሳቸዉን በቻሉ ነጻ የጥናትና የምርምር ተቋማት በተለያዩ መንገዶች በሚያሰባስቡት የህዝብ አስተያየትና ዳሰሳ ላይ ተመስርተዉ የሚሰጡት መረጃ ዉጤት በመሆኑ አስካሁን በሀገራችን በኛዉ ሰዎች በዚህ መልክ የተሰራ ስራ ስለመኖሩ ያለመሰማቱ ምክንያት ይህን ማድረጉ ዉስብስብነት ሲላለዉ ሳይሆን የጉዳዩን ፋይዳ ካለመረዳት የመነጨ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ በዚሀ ምክንያትም በመንግስታችን ላይ ምን ያህል እንደምንተማመን ሆነ ምን ያህል እንደምንጠራጠረዉ ከኛ በላይ ስለኛ አዋቂ የሆኑት ፈረንጆች አስኪነግሩን መጠበቅ የግድ ሆኖብናል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ መንግስት ላይ ምን ያህል አመኔታ አለዉ ? መንግስትስ ምን ያህል የህዝብ ድጋፍ አለኝ ቢሎ ያስባል? የሚለዉን ለመናገር ከዉጭ ተቋማት ከሚናገኘዉ መረጃዎች ባለፈ እዚሁ በራሳችን የተዘጋጀ መረጃ አለመኖሩ አሳዛኝ ነዉ፡፡ ይህ ክፍተት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ልማዳዊ በሆነ መንገድ ህዝቡ በየዕለቱ ከሚያጋጥሙት ሁኔታዎችና ክስተቶች መነሻ በማድረግ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ስለ መንግስት የሚሰማዉን ስሜትና አመለካካት አይገልጽም ማለት አይደለም፡፡

መብራትና ዉሃ ለበርካታ ቀናት ሲቋረጥበት፤ የትራንስፖርት እጥረት ሲያበሳጨዉ ፤የምግብ ቁሳቁስ ዋጋ እንደ ሮኬት ሲመነደግ ወዘተ የመሳሳሉ በየዕለቱ የሚያጋጥሙትን ከስተቶች መነሻ አድርጎ መንግስትን ሳያማርር በሌላ ግዜ ደግሞ መልካም ስራዎችን ሲያይ ሳያመሰግን የዋለበት ዕለት አይኖርም፡፡ ህዝብ ስለመንግስትና ገዥዉ ፓርቲ የሚኖረዉ አመኔታ ጉዳይ በየእለቱ በማመስገንም ሆነ በማመረር የሚሰማዉን ስሜት (perception) ሁሉ ድምር ዉጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዚህ መሰረትም በጣም ዉስብስብ ጉዳዮች ትተን ህዝብ በመንግስት ላይ ያለዉን አመለካከት ሳይንሳዊ ባልሆነ በቀላሉና ልማዳዊ በሆነ መንገድ ለአብነት በተጠቀሱ በሚከተሉት ሁኔታዎች ሊገለጽ ይችላል፡፡

በመንግሰት መተማማን ሲባል፤

* የገዛሄዉ የምግብ ዘይት ቅቤና በርበሬ ጋር አብሮ ሌላ ባዕድ ነገር እንዳይቀላቀልበት መንግሰት አጥብቆ እንደሚቆጣጠርልህ እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* ለችግር ግዜ ይሆነኘል ብለህ ባንክ ቤት ያስቀመጥከዉን ገንዘብ በጠየቅህ ግዜ ወዲያዉኑ እንደምታገኝ ወይም እንደማትከለከል እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* መንግስትን በጋዜጣ ብትተችና ወደ ጎዳና ወጥተህ ሰላማዊ ተቃዉሞ ሰልፍ ብታደርግ እንዳማያስተኩስብህና ማረፊያ ቤት እንደማይከትህ እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* በስንት ድካምና ወጭ የሰራሄዉ መኖሪያ ቤትህና መጠለያ ጎጆህ ያለ አግባብ በአፍራሽ ግብረኃይል በላይህ ላይ እንደማፈርስብህ እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* በሀገርህ በፈለከዉ ክልልና አካባቢ ተንቀሳስሰህ ሀብት አፍርተህ መኖሪያ ቀልሰህ ማንም “ከዚህ ለቀህ ዉጣ!” ሳይልህ በነጻነት መኖር እንደምትችል መንግስትም ይህን መብት እንደሚያስከብርልህ መተማማን ማለት ነዉ፡፡

* ተከሰህም ሆነ ከሰህ ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ ተገቢዉን ፍትህ አንደምታገኝ መተማማን ማለት ነዉ፡፡

* ሌባና ሙሰኛን ስተጠቁም ሌባዉ እያለ ሌባ ጠቋሚ የሆንከዉ አንተ እንደማትታሰርና የደህንነት ክትትል እንደማይደረግብህ እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* ከቤትህ በሰላም ወጥተህ በሰላም ለመመለስ ወንጀለኛና ማጅራት መቺ እንዳይተናኮልህ መንግስት ለደህንነትህ ተገቢዉን ጥበቃ እንደሚያደርግ እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* አያት ቅድሜ አያቶችህ ለዘመናት በደምና በአጥንታቸዉ አስከብረዉ ያቆዩልህን ዳር ድንበርህንና ሉአላዊነትህን መንግሰት በዋዛ ፈዛዛ ለሌላ አሳልፎ እንደማይሰጥ ይልቁንም ሉአላዊነትህንና ብሄራዊ ጥቅምህን ለማስከበር ተግቶ እንደሚሰራ እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* የሀገሪቱ መከላከያና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ለህገመንግስቱ ተገዢና ተቆርቋርነታቸዉና ወገንተኝነታቸዉ ከማንም በላይ ለህዝቡ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* መንገድ ላይ በድንገት የፖሊስ ወይም የመከላከያ አባል ሲገጥምህ የማትደነግጥ ይልቁንም “አለኝታዬ! ” በሚል ስሜት ዉስጣዊ ኩራትና ደስታ ሲሰማህ ማለት ነዉ፡፡

* ከግብር ከፋዩ ህዝብ የተሰበሰበና በህዝብ ስም ከዉጭ በብድር የተገኘ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ከማዋል ይልቅ ለግለሰቦች ኪስ ማደለቢያ እንደማይሆን አርጠኛ መሆን ማለት ነዉ፡፡

* የትኛዉም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን በቴሌቭዥን መግለጫ ሲሰጥ በጥላቻ ስሜት ተሌቪዥኑን መዝጋት ትተህ በጽሞና ትኩረት ሰጥተህ ስታዳምጥ ማለት ነዉ፡፡

* በጠራራ ፀሀይ የደሃን ገንዘብ የሚዘርፉ ሙሰኛ ባለስልጣናት ሲገኙ መንግስት ሁለተኛ እንዳይለምዳቸዉ የሚያደርግ ተገቢዉን ቅጣት ከመቅጣት ይልቅ ለዘራፊዎች ራርቶ ከለላ እንደማይሰጥ መተማማን ማለት ነዉ፡፡

ባጠቃላይ አነጋጋር በህዝብ እምነት የሚጣልበት መንግስት የህዝብ ህመም ደስታና ሀዘኑ የሚሰማዉ፤የአቅም ዉስንነት ካልገደበዉ በስተቀር የህዝብን ፍላጎት ለሟሟላት ተግቶ የሚሰራ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህን ጎስቋላና ደሃ ህዝብ ገንዘብ እየዘረፉ ወደ ዉጭ በማሸሽ የለየለት የጠላትነት ተግባር የሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ ተገቢዉን እርምጃ ከመዉሰድ የማይመለስ መሆኑን በተግባር ማረጋጋጥ ማለት ነዉ፡፡

 2/ የመንግስት ተአማኒነት ፋይዳዉ፤

 በመንግስት ላይ ህዝባዊ አመኔታ መኖር ለሲቪሉ ህብረተሰብ ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርአቱ ከሚኖረዉ ፋይዳ ባሻገር ለራሱ ለመንግስት ህልዉናም ቢሆን እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንድ መንግስት የቱንም ያህል ዲሞክራት ቢሆን ምን ያህል የህዝብ አመኔታ አለኝ ብሎ በየግዜዉ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ በአንድ ወቅት በከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ተመርጦ ስልጣን የያዘ ፓርቲ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከህዝባዊ ወገንተኝነቱ ሸርተት እያለ ለህዝብና ለሀገር ማሰብ ቀርቶ ለስልጣኑ ብቻ መጨነቅ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍታት ሲሳነዉ ከዚያ በፊት ሰፊ ድጋፍ ሰጥቶት የነበረ ህዝብ ተመልሶ አመኔታዉን ሊነፍገዉ ይችላል፡፡

የትኛዉም መንግስት ለህዝባዊ አመኔታ ደንታቢስና ጨርሶ የማያስጨንቀዉ ከሆነ ያ መንግስት በርግጥም ወደ አምባገነንነት በፍጥነት እየገሰገሰ ለመሆኑ ምልክት ነዉ፡፡ “በህዝብ ተመርጨ ነዉ ስልጣን የያዝኩት” በሚል አጉል ተኩራርቶ ከእኔ በላይ የህዝብን ፍላጎት የሚያዉቅ አይኖርም በማለት በሚሰራዉና በሚያቅደዉ ሁሉ ህዝቡን ሳያማክር ያሻዉን ህግና ፖሊሲ በህዝብ ላይ እየጫነ እኔ የምነግራችሁን ብቻ ተቀበሉ ማለት ሲጀምር ሁሉነገሩ ከፍላጎቱ ጋር አልጣጣም ያለበት መራጭ ህዝብ ተስፋ በመቁረጥ እርግፍ አድርጎ ድጋፉን ይነሳዋል፡፡ ከዚያ በኃላ ህዝቡ ገዥዉ ፓርቲ ለአንድትም ጀምበር በስልጣን ላይ እንዲቆይ ፍላጎት አይኖረዉም፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ህዝቡ ለገዥዉ ፓርቲ ድምጹን በመንፈግ በቀይ ካርድ ያሰናብተዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ህዝቡ የሚሰማዉን የልቡን አዉጥቶ በግልጽ በአደባባይ የመናገር ባህል ባላዳበረበት ህብረተሰብ ዉስጥ መንግስት ህዝባዊ አመኔታ አለኝ በሚል ተማምኖ መቀመጥ አይኖርበትም፡፡ የኛ ህዝብ እንደሆን መንግስትን ለዓመታት ሲያሞግስና ሲያደንቅ ይቆይና በድንገት በአንድት ዕለት ተጀምሮ በሚጠናቀቅ ምርጫ ከገዥዉ ፓርቲ ይልቅ ከዚህ በፊት የማያዉቀዉንና ስሙን እንኳን አጣርቶ መናገር ለማይችለዉ ፓርቲ ድምጹን አስረክቦ መንግስትን ሊያስደነግጥ ይችላል፡፡ ይሄ ሁኔታ በዚሁ በሀገራችን በ97ቱ ምርጫ(በተለይ በአ.አበባ) ደርሶ በተግባር ያየነዉና በሌሎች ሀገሮችም ተደጋጋሞ የተስተዋለ ከስተት ነዉ፡፡ በመንግስትና በዜጎች መካከል ጠንካራ የእርስበርስ መተማማን መኖር ፋይዳዉ ለዲሞክራሲ መጠናከር፤ለፖሊሲዎች የተሻለ አፈጻጸምና የኢኮኖሚ ብልጽግና ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆን ብቻ ሳይሆን እንደቅድሜ ሁኔታም የሚቆጠር ነዉ፡፡

ዜጎች በመንግስታቸዉ ላይ አመኔታ የሚጥሉት መንግስት ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት እንደሚቆም እርግጠኛ ሲሆኑ ብቻ ነዉ፡፡ የመንግስት የመታመን ጉዳይ ሊመጣ የሚችለዉም መንግስት ራሱ ስለ ራሱ መልካም ስራዎች ሲላወራና ስለሰበከ ሳይሆን ዜጎች ራሳቸዉ መንግስት መልካም ነገር እየሰራላቸዉ መሆኑን ሲገነዘቡ ብቻ ነዉ፡፡ ስለዚህ በመንግስት ላይ የህዝብ አመኔታ የሚመጣዉ ያለመታከት በቋሚነትና በተጠናከረ ሁኔታ በሚሰራ ዘርፈ ብዙ ስራ እንጂ በአንድ ጀምበርና በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚገኝ አይደለም፡፡ በዚህ መሰረትም በላይ በላዩ እየጨመረና እየተጠናከረ የሚሄድና የተከማቸ ህዝባዊ አመኔታ ለመንግሰት አንደ ካፒታል የሚቆጠር ሲሆን መንግስት ይህን ካፒታል በአግባቡ ኢንቬስት በማድረግ ለሚቀጥለዉ ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ ያስችለዋል፡፡

የመንግሰት ተአማኒንት እየቀነሰ መሄድ በተለይ መንግስት ከዘላቂ የህዝብ ጥቅም አኳያ አስቦ በሚያወጣቸዉ ፖሊሲዎች ላይ ጭምር የህዝብ ድጋፍ እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ ዜጎች በመንግስት ላይ አመኔታ ካጡ የወደፊቱን በተስፋ ከመጠበቅ ይልቅ ግዜያዊና የቅርብ ግዜ ጥቃቂን ጥቅምች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ያደርጋቸዋል፡፡ አንዳንድ የመንግስት ፖሊሲዎች በባህሪያቸዉ ዉጤታቸዉን በአጭር የግዜ ማእቀፍ ዉስጥ የማይታይ ነገር ግን በረዥም ግዜ ሂዴት ለህዘቡ ዘለቃተዊ ጥቅም የሚያመጡ መሆናቸዉ እየታወቀም ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ ሲላጣ ብቻ ለመንግስት ፖሊሲ ድጋፍ የሚነፈግበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል፡፡

በመንግስት በኩልም አንድ ግዜ የህዝብ አመኔታ እንደቀነሰበት ከተረዳ ህዝብን የማገልገል ፍላጎቱ ስለሚቀዘቅዝበት ራሱ ያወጣዉን ፖሊሲም ማስፈጸም ስለሚሳነዉ በዚህ ምክንያትም በህዝቡም ሆነ በራሱ ግምገማ ደካማ መንግስት ተደርጎ ስለሚቆጠር ተአማኒነት ያጣል፡፡ በዚህ መነሾም ህዝብ በስልጣን ላይ ያለዉን ገዥ ፓርቲ ችላ በማለት ሌላ የተሻለ አመራጭ ፓርቲ ፍለጋ ማማተር ይጀምራል፡፡ ዜጎች በገዥዉ ፓርቲ ላይ እርካታ ሲያጡና ከልብ የሚታመን ሌላ አማራጭ ተፎካካሪ ፓርቲም አለመኖሩን ሲያረጋግጡ በምርጫ ፖለቲካዉ ተስፋ በማጣት አስከነአካቴዉ ወደ ምርጫ ጣቢያ የመሄድ ፍላጎታቸዉም የቀዘቀዘ ይሆናል፡፡ በመንግስት አመኔታ ባጡበት ወቅት በየትኛዉም የመንግስት ጉዳይ ዉስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት ስለማይኖራቸዉም በዚህ መነሾም ህዝባዊ ተሳትፎአቸዉ ስለሚዳከም በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ሀገር ለማስተዳዳር የሚቸገርበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡

ዜጎች ከመንግስት የሚጠብቁት (People’s expectations) ከመንግስት ጋር እንዳላቸዉ ቅርበትና እንደስራ ባህሪያቸዉ የተለየዬ ሊሆን ቢችልም ቢያንስ እንደ ዜግነታቸዉና እንደ ግብር ከፋይነታቸዉ አብዛኛዎቹ ዜጎች ከመንግስት በጋራ የሚጠብቁት ነገር አይጠፋም፡፡ ከዚህ አንጻር ሊጠቀስ የሚችለዉ መንግስት ለህዝብ ቃል የገባዉን በተግባር የሚፈጽም መሆኑ፤ ሃቀኝነት፤ በድርጊቱ ሁሉ ሃላፊነት የሚሰማዉ፤ ፍትሃዊነትና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር የሚከተል፤ የሀገር ደህንነትን ለማረጋገጥ አቅምና ተነሳሽነቱ ያለዉ ፤ለሀገራዊ ጥቅም መከበር ተግቶ የሚሰራ ፤ራሱ ላወጣዉ ህግ ተገዥ የሆነ፤ ከፋፋይ የሆነ ዝንባሌ የሌለዉና በህዝቦች አንድነት የሚያምንና ለተግባራዊነቱም ተግቶ የሚሰራ ፤ለጥቂት ግሰሰቦች ጥቅም ሳይሆን አብዛኛዉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የቆመ፤ ስህተት ሲሰራ ስህተቱን በአደባባይ አምኖ ህዝቡን ይቅርታ ለመጠዬቅ የማያመነታ፤ በህዝብ ወሳኝነት የሚያምን ፤ የህዝቡን ተቃዉሞ የማሰማትና ሃሳብን የመግለጽ መብት የሚያከብር ወዘተ…. በጥቅል አነጋጋር እንደ መንግስት እምነት የሚጣልበት (trustworthy ) እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ የሁሉም ዜጎች የጋራ ፍላጎት እንደሆነ ይታመናል፡፡

3. የኢፌዲሪ መንግስትና የገዥዉ ፓርቲ (ኢህአዴግ) ተአማኒነት ሁኔታ ሲፈተሸ፤

ቀደም ባሉት የሀገራችን አገዛዞች ዘመን ህዝቡ ፍላጎቱ የሚጠየቅበት ወይም በመንግስት ፖሊሲዎች ላይ አስተያየት የሚሰጥበትና ቅሬታዎቹንም የሚያቀርብብት ፤ የመንግሰትን አሰራርም የሚገመግምበትና የሚተችበት አንዳችም እድል አልነበረዉም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ፍላጎቱ ሳይጠየቅ ከላይ ወደ ታች የተወረወረለትን ፖሊሲ ለመቀበል ይገደድ ነበር፡፡ የቀድሞ ገዥዎች ህዝቡን በማንኛዉም መልኩ ማሳተፍ ስለማይፈልጉ ዜጎች በሀገራቸዉ ዉስጥ ለሚሰራዉ ሁሉ ባይተዋር ለመሆን ተገደዉ ነበር፡፡ ህዝባዊ ተሳትፎ የጎደለዉ ማንኛዉም የመንግስት ፖሊሲ ዉጤት ይሰጣል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ያለፉት የሀገራችን መንግስታት የበላይን ትዕዛዝ ያለአንዳች ማንገራገር ተቀብሎ እንደሚፈጽም የሰለጠነ ወታደር ህዝቡን ስለቆጠሩት ያሻቸዉን ህግ አዉጥተዉ እንዲፈጽም ሲያስገድዱት ትንሽም አልከበዳቸዉም ነበር፡፡ ህዝባዊ ተሳትፎን የሚያበረታታ አንዳችም እድል ባለመኖሩ መንግስትና ህዝብ ከጊዜ ወደግዜ እየተራራቁ አጥፊና ጠፊ የሆኑበት ደረጃ በመድረሳቸዉ በመጨረሻም አገዛዙ በተራዘመ ትጥቅ ትግል ሊወገድ ችሎአል፡፡

የኢፌድሪ መንግስት ካለፉት መንግስታት እጅግ በተሻለ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ሊነጻጸርም በማይገባዉ ደረጃ ሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነት እያገኘና በህዝብና በመንግስት መካከልም ጠንካራ መተማማን እየተፈጠረ የመጣ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡ የኢፌድሪ መንግስትም ሆነ በሰልጣን ላይ ያለዉ ገዠ ፓርቲ ለህዝብ ከፍተኛ ከበሬታ ያለዉና በተቻለ መጠን የህዝብን የደሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ተግቶ የሚሰራና በተግባርም በርካታ አስመስጋኝ ዉጤቶችን ያስመዘገበ መሆኑ ስለሚታወቅ ህዝባዊ አመኔታ የማግኘቱ ጉዳይ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ የኢፌዲሪ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዚህ ቀደም እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ለብዙ ፈተናዎች መጋለጡና በዚህ መነሾም ህዝባዊ አመኔታዉ በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስበት እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ መንግስት ለተከሰቱት ችግሮች ሁሉ ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ በመዉሰድ የችገሮቹ ምንጭ ናቸዉ የተባሉትን ሁሉ አንድ በአንድ ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ገዥዉ ፓርቲ(መንግስት) በቅድሚያ የራሱን ቤት ማጽዳት ስለነበረበትም ጥልቅ ተሃድሶ በሚል ራሱን እየፈተሸ ችግሮችን ወደ መፍታት ተሸጋግሮአል፡፡

መንግስት በጀመረዉ ጥልቅ ተሃድሶ ያሉበትን ችግሮች ወይም ድክመቶች በሚገባ በመመርመር ራሱን በማደስ በተሻለ ሁኔታ የህዝብን ፍላጎት ለሟሟላት ጥረት እያደረገ መሆኑ ቢታወቅም ነገር ግን በተግባር የህዝብ ድጋፍና አመኔታ በሚፈለገዉ ደረጃ አስገኝቶለታል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለዚህ ምክንያቱም በአንድ በኩል የመንግስት እጅ ያልደረሰባቸዉ የችግር አካባቢዎች መኖራቸዉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ችግር መኖሩን ተገንዝቦና በሚገባ ለይቶትም እያለ ነገር ግን ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ለመዉሰድ ማመንታቱና በተጨማሪም ህዝቡ ከመንግስት የማድረግ አቅም በላይ ሁሉንም ችግሮች በአንድ ግዜ እንዲወገዱለትና ሁሉም ጥያቄዎቸ በአንድ ግዜ እንዲፈጸሙለት ከመንግስት መጠበቁ ነዉ፡፡

መንግስት የቱንም ያህል ፈቃደኝነቱ ቢኖረዉ መፈጸም ከሚችለዉ በላይ ሁሉንም ነገር በአንድ ግዜ መፈጸም አይችልም፡፡ ህዝቡ ይህን ሁኔታ ሊገነዘብ ካልፈቀደ ሁኔታዉ ለመንግስት ፈታኝ መሆኑ አይቀርም፡፡ መንግስት ካለበት የማስፈጸም አቅም ዉስንነትና ካሉበት የአሰራር ድክመቶቹ ባሻገር አንዳንድ ችግሮች በባህሪያቸዉ ዉስብስብነት ስለማያጣቸዉ በአጭር ግዜ እልባት ሊያገኙ እንደማይችሉ ህዝቡ በሚገባ ያጤነዉ አይመስለኝም፡፡ መንግስት የቱንም ያህል ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ቢኖረዉ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በሙሉ በአንድ ጀምበር መቅረፍ አይችልም፡፡

በሌላ በኩል የመንግስት ጥረትን ህዝብ እንዲገነዘብ በማድረግ ረገድ የህዝብ ግኑኝነት ስራዉ ደካማ መሆን ለህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ መቀዛቀዝ ተጨማሪ ምክንያት ነዉ፡፡ መንግስት ከራሱ መረጃ ምንጮች ዉጭ ስለአከናወነዉ መልካም ስራዎቹ ሊመሰክሩለት የሚችሉ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን ሲላላዘጋጀ ህዝቡ መንግስት የሚነግረዉን ብቻ ሳይሆን በተግባር ያየዉን ለዉጥ ሁሉ በእምነት ለመቀበል ሲያመነታ ይታያል፡፡

መንግስት እየካሄደ ያለዉ ሪፎርም (በጥልቀት መታደስ) ፋይዳዉ ለራሱ ለህዝብ ጠቀሜታ መሆኑን ህዝቡ በሙሉ ልብ አምኖበትና ገብቶት ተቀብሎታል ለማለት አይቻልም፡፡ እንዲያዉም አንዳንዶቹ ከተሃድሶዉ መልካም ዉጤትን በተስፋ ከመጠበቅ ይልቅ ተሃድሶዉን እንደ ስጋት የመቁጠር አዝማሚያ ነዉ የሚታየዉ፡፡ ለዚህ የተዛባ አረዳድ ዋነኛዉ ምከንያት መንግስት በህዝቡ ዘንድ ሊታመን የሚችል የመረጃ ምንጭ (ሚዲያ) ባለማዘጋጀቱ ነዉ፡፡ የመንግስት ሚዲያ የሚናገረዉን አብዛኛዉ ህዝብ እዉነት ነዉ ቢሎ አይቀበልም፡፡ ሚዲያዉም ህዝቡ አምኖ እንደማይቀበለዉ እያወቀም መናገሩን አያቆምም፡፡ ስለዚህ ነጻና ገለልተኛ የሆነ ሚዲያ አለመኖር ምክንያት ህዝብና መንግስት እርስበርስ ሳይደማማመጡና ሳይተማማኑ እንዲያዘግሙ የግድ ሆኖባቸዋል፡፡

መንግስት ፖሊሲ ቀርጾ በዕቅድ እያከናወነ ስለአለዉ ግዙፍ ስራዎች ስኬትና ስለገጠሙት ተግዳሮቶች ለህዝቡ ጆሮ በግልጽ መድረሱንና ህዝቡ በትክክል መረዳቱን እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ በአንድ በኩል የተፈጠሩ ችግሮችን እጅግ አቃለዉና ሸፋፍነዉ የሚያቀርቡና በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት የሰራቸዉን መልካም የሚባሉ ስራዎች እጅግ አጋነዉ ወደ ህዝብ የሚያደርሱ የገዥ ፓርቲ ካድሬዎችና የመንግስት ሚዲያዎች ህዝቡን ከመንግስት ጋር ምን ያህል እያራራቁት እንደሆነ መንግስት ሊገነዘብ ይገባል፡፡

መንግስትን ይበልጥ የሚጠቅመዉ እዉነቱን ሳይደባብቁና ግነትም ሳያበዙ ህዝብ ሊገባዉ በሚችል መንገድ ወደ ህዝብ ሲያደርሱ ብቻ ነዉ፡፡ ህዝብ መንግስት እየሰራለት ያለዉን መልካም ስራዎች ሳይቀር አስከ መጠራጠር የሚደርስበትን ምክንያት መንግስት መርምሮ ሊደርስበት ይገባል፡፡ አንድ ግዜ ህዝብ መንግስትን መጠራጠር ከጀመረና እመኔታ ከነፈገዉ በካድሬ ቅስቀሳና በEBCና ENN ጉትጎታ ቀርቶ BBC ና CNN እንኳን ቢያግዙት አንድ ግዜ የተዛባን የህዝብ አመለካካት መልሶ ማስተካካል አዳጋች ይሆንበታል፡፡

ለነገሩ እኮ መንግስት የሚመራዉን ሕዝብ ስነልቡና ጠንቀቆ መረዳትም በተገባዉ ነበር፡፡ አርሶ አደሩና የከተማዉ ነዋሪ የሚያሳስባቸዉ አጀንዳ ለየቅል መሆኑን መንግስት ሊረዳ ይገባዋል፡፡ አርሶአደሩ አጥብቆ መስማት የሚፈልገዉ ዜና በአዲስአባባና በክልል ከተሞች ስለተሰሩ የጋራ ህንጻ ግንባታዎች ሳይሆን የሞት ሽረት ጉዳይ የሆነበትን የድርቅ፤ የመጤ ተምች ፤የማዳበሪያ ዋጋ መናር የሚፈታ ዘላቂ መፍትሄ ነዉ፡፡ አርሶአደሩ ከስኳር ማምረቻ ፋብሪካ ይልቅ በጉጉት የሚጠብቀዉ የማዳበሪያ ፋብሪካን ነዉ፡፡

በሌላ በኩል አጠቃላይ የህዝባችን ባህሪይ ሲታይ ከረዥም ግዜ በኋላ ከሚመጣ ዘላቂ ጥቅም ይልቅ በአጭር ግዜ የምትታይ ፈጥኖ ሊያገኛት የሚችላትን ትንሽ ጥቅምን መሻቱ ፤ወደፊት ከሚጠብቀዉ ዘለቀታዊ ጥቅም ይልቅ ግዜያዊና አላፊ በሆነ የአጭር ግዜ ጉዳት ( short-term disadvantages )የበለጠ መማረሩ፤ከመልካም ዜና ይልቅ አፍራሽ ወይም ጎጂ ለሆነ ዜና (bad news) ጆሮዉን ማዋሱ ወ.ዘ.ተ የተጠናወተን መጥፎ ልማድ ነዉ፡፡ ስለዚህ ይህን ዝንባሌ ለዘለቀታዉ ማስተካካል በሚቻልበት መፍትሄ ላይ መንግስት ተግቶ ሊሰራ ይገባዋል፡፡

አስቀድሜ የገለጽኩት ይህ የህዝቡ የተጠራጣሪነት ባህሪይ ሳያንስ ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግስት ራሱ ሊተገብር የማይችለዉን ሁሉ ከአቅሙ በላይ ቃል የመግባት (over-promising) ልማድ ማምጣቱ ሲሆን ቃል እንደተገባዉም መፈጸም ካልተቻለ የህዝብ አመኔታ ይበልጥ እየተሸረሸረበት እንደሚሄድ መንግስት ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ፍቱን መድሃኒት የሆነዉ ከመንግስትና ከሀገሪቱ ዓቅም በላይ የሆነን ነገር አደርግላችኋሁ ብሎ ቃል መግባት ሳይሆን በሁሉም ጉዳይ ላይ ግልጽነትን ማስፈንና የህዝብ ተሳትፎን ማሳዳግ ነዉ፡፡ በተለይ የህዝብን አመራጭ መረጃ የማግኘት እድል ማስፋት አማራጭ የለዉም፡፡

ይህ ሁኔታ በሚገባ ከተሟላ ህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ ስለሚሰማዉ በመንግስት አቅም ማነስ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ እንደራሱ ችግር አድርጎ ስለሚቆጥር መንግስትን በረባና ባልረባዉ ሁሉ መጣራጠር አቁሞ እምነቱን ይጥልበታል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳይንም ዛሬዉኑ ካልተሟላልኝ ብሎ መንግስትን አያስጨንቅም፡፡ ህዝቡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ በተለያዩ መልኮች የሚሳተፍና በፖሊሲ ዝግጅትና በዉሳኔ አሰጣጥ ላይም የራሱን አማራጭ የሚያቀርብ ከሆነ ባጠቃላይ አነጋጋር መንግስት ህዝብን እያማከረ የሚሰራ ከሆነ (Public consultations) የህዝብና የመንግስት እርስበርስ መተማማን እጅግ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

ዛሬ የሀገራችን ዜጎች በልማት ፤ በማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና በሌሎችም የሀገር ግንባታ መስኮች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የመንግስት ፖሊሲዎችን በመተቸት በማረምና አተገባባሩን በመገምገም እንዲሁም አዳዲስ ልማት ጥያቄዎቻቸዉን መንግስት እንዲፈታላቸዉ በግልጽ ለማቅረብ ሰፊ ዕድል ያገኙበት ወቅት በመሆኑ የሚጠበቀዉን ያህል ባይሆንም የዜጎች ህዝባዊ ተሳትፎ ከዓመት ወደ ዓመት እያደገና እየተሻሻለ መምጣቱን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ህዝቡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ በባለቤትነትና በሃላፊነት ስሜት የሚሳተፍበት ህዝባዊ መድረኮች በስፋት በመኖራቸዉ ዜጎች አልተደመጥንም ሰሚ አላገኘም ለማለት የሚያስችል ሁኔታ እምብዛም የለም፡፡ ችግሩ ያለዉ ከህዝባዊ መድረኮች መጥበብ ሳይሆን ከኋላ ቀር ባህልና የዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ተሞክሮ አናሳ መሆን ጋር ተያይዞ የተገኙትን መድረኮች በአግባቡ ተጠቅሞ መንግስትን በግልጽ ለመተቸት አለመድፈር ሲሆን የመንግስት ሚዲያዎችም ይህን የህዝብን ተሳትፎ የሚያጎለብት ተግባር ሲፈጽሙ ብዙም አለመታየታቸዉ ነዉ፡፡

በመሰረቱ የህዝባዊ መድረኮች ፋይዳ ህዝቡ አንድ የመንግስት ወይም የፓርቲ ባለስልጣን የሚሰጠዉን ድስኩር በዝምታ አዳምጦና አጨብጭቦ የሚሄድበትን ሁኔታ ማመቻቻት አይደለም፡፡ ህዝቡ በተሰራዉ ስራና ባየዉ መልካም ነገር መንግስትን ማመስገኑና ማበረታታቱ ተገቢ ቢሆንም ዋናዉ የመድረኩ ጠቀሜታ ህዝቡ ቅሬታዎቹንና ብሶቶቹን ለመንግስት እንዲደርስ የሚያደርግበት አጋጣሚ መፍጠር ሲሆን በተለይም ሙሰኛ በሆኑና የመልካም አስተዳዳርን እያጓደሉ ሲያሰቃዩት የቆዩ ጸረ- ህዝብ ሹማምምቱን በስምና በምግባራቸዉ እየጠቀሰ አስከማጋለጥ የሚደርስ እርምጃ ለመዉሰድ ማስቻሉ ነዉ፡፡ ያለበለዚያ የባለስልጣን ንግግርና መግለጫ ለመስማት ከሆነ በአዳራሽ መሰብሰቡ ለምን ያስፈልጋል?በመንግስት ሬዲዮና ቴሌቭዝን መከታታል ይቻላል እኮ፡፡ ከመድረክ የሚነገረዉን አድምጦ መፈክር አሰምቶ መለያየት እንኳን አሁን ቀርቶ ለነ ለገሰ አስፋዉ ዘመንም አልበጀም፡፡

በተለያዩ ግዜያት ህዝቡ የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቃዎችን አንግቦ ወደ አደባባይ መዉጣቱ የሚታወቅ ሲሆን ለጥያቄዉ ተገቢዉን መልስ እንደሚያገኝና በዚያ መንገድ መብቱን መጠየቁም ተገቢና ማንም ሊሰጠዉና ሊነፍገዉ የማይችል ህገ መንግስታዊ መብቱ መሆኑን ተረድቶ ነዉ፡፡ ህዝብ ተጨማሪ የልማት ጥያቄ ለመጠየቅም ሆነ የመንግስትን ፖሊሲና አሰራርን ለመቃወምም ሆነ ማስተካካያ እንዲደረግ ለመጠየቅ አደባባይ መዉጣቱ ከመንግስት ተገቢዉን ምላሽ እንደሚያገኝ ያለዉን መተማመን የሚያሳይ ካልሆነ በስተቀር የመንግስትን ተቀባይነት ማጣት የሚያሳይ አይደለም፡፡ በሆነች ጉዳይ ላይ ህዝብ ለተቃዉሞ ወደ አደባባይ ስለወጣ ብቻ መንግስት የህዝብ ተአማኒነት የሌለዉና በህዝብ የማይፈለግ ተደርጎ የሚያስቆጥር አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ መንግስትን በደፈናዉ የመጠራጠር ልማድ መኖርና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህላችን አለመዳበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግስትን አመኔታ ለማሳጣት ታጥቀዉ በሚሰሩ አንዳንድ መሰሪ ኃይሎች ሴራ የተነሳ የዋህ ዜጎች በመንግስትና በስርአቱ ላይ አመኔታቸዉ እንዲሸረሸርና በጥቃቅን ችግሮች ሁሉ የመንግስትን የማስፈጸም ብቃት እንዲጠራጠሩ እየተዳረጉ እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

በዚህም ምክንያት ህዝቡ በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ አመኔታ እንዳይኖረዉና ገዥዉን ፓርቲንም ጨምሮ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም ሀገር በቀል የፖለቲካ ፓርቲዎችን አንዳችም በጎ ነገር የሌላቸዉ የልዩነትና የክፍፍል መሳሪያዎችና ችግርና ሁከት ከመፍጠር ዉጭ መፍትሄ ማምጣት የማይችሉ የጥፋት ኃይሎች አድርጎ በጅምላ በመፈረጅ የፓርቲ ፖለቲካን በደፈናዉ የመጥላት ዝንባሌ እንዲይዝ ትልቅ አፍራሽ ሚና ተጫዉተዋል፡፡

በመንግስት ላይ ህዝባዊ አመኔታ የመሸርሸር ችግር ዜጎች ህገመንግስቱ ያጎናጸፋቸዉን የስርአቱን ጸጋዎች ለመቋደስ እንኳን እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በህገመንግስታዊ ስርአቱና በአመራሩ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡና ዛሬን ብቻ ሳይሆን መጪዉንም ዘመን ጭምር አጨልመዉ እንዲያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በመንግስትና በስርአቱ ላይ አመኔታ ማጣት ካለ በስንት ድካም የተገኙ ምርጥ የመንግስት የልማትና የዲሞክራሲ ስኬቶችንና ህዝቡ የተቀዳጃቸዉን የልማት ድሎች ሁሉ እዉቅናና አድናቆት እስከመንፈግ የሚያደርስ አፍራሽ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህ ምክንያትም መንግስት የህዝብ አመኔታ የሚፈጥሩለትን ስራዎች ጠንክሮ መስራት ይገባዋል፡፡ የህዝብ ሙሉ ድጋፍ ያለዉ መንግስት በሚያወጣቸዉ ፖሊሲዎችና ህጎች ሁሉ ላይ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ስለሚያገኝ ፖሊሲዉን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግም ያግዘዋል፡፡ መንግስት ህዝባዊ አመኔታ ካለዉ በማንኛዉም ጉዳይ ላይ የህዝቡን ትብብር በቀላሉ ማግኘት ያስችለዋል፡፡ ህዝባዊ አመኔታ ያለዉ መንግስት በሀገሪቱ ዉስጥ ትላልቅ ቀዉሶችና አደጋዎች ሲያገጥሙ ህዝቡን በቀላሉ ሞብላይዝ የማድረግ ሰፊ ዕድልም ይኖረዋል፡፡

በዚህ መሰረት መንግስታችን የህዝብ አመኔታ አለኝ የሚል እምነት ካለዉ በሁሉም አሰራሮቹ ግልጽነትን ማስፈን ይገባዋል፡፡ ሰፊ ህዝባዊ አመኔታ ያለዉ መንግስት ነቀፌታና ትችት ሊያስበረግገዉ ስለማይገባ ነቀፌታ የሚያቀርቡ የግል ሚዲያዎችን ማበረታታት እንጂ ማስበርገግ አይገባዉም፡፡ በአንጻሩ መንግስት የህዝብ አመኔታ የለኝም ወይም የህዝቡ ድጋፍ እየተሸረሸረብኝ ነዉ የሚል ስጋት ከገባዉ ለዚህ ችግር ማንንም ሳይወቅስና ሰበብ ሳያበዛ የራሴ ድክመት ነዉ ብሎ በመቀበል ራሱን በማስተካካል የተመናመነበትን ህዝባዊ አመኔታን መልሶ ለማደስ መጣር ይኖርበታል፡፡ ህዝባዊ አመኔታ እየተሸረሸረበት መሆኑን እያወቀ ነገር ግን በአቋሙ ድርቅ ብሎ በድክመቱ መቀጠል የሚሻ ከሆነ ራሱን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱንም ገደል ይከታታል፡፡

4/ በኢህአዴግ ላይ ምን ያህል እንተማመናል?

ለመሆኑ ኢህአዴግ ህዝባዊ ተአማኒነቴ እንከን የለዉም የሚል እምነት አለዉ?ለዚህ ማረጋገጫዉና ማሳያዉ ምንድነዉ ? አንዲያዉም መንግስት /ኢህአዴግ ስለዚህ ጉደይ አስቦበትና የህዝብ ድጋፍ አለኝ ወይም የለኝም ብሎ ተጨንቆበት ያዉቃል? ኢህአዴግ የህዝባዊ አመኔታ አለኝ የሚል ከሆነ በያዘዉ የፓርላማ ወንበር ብዛትና የአባላት ቁጥር ብቻ ተማምኖ ነዉ ወይንስ ሌላ ማረጋገጫ ይኖረዉ ይሆን?

በዚህ የተአማኒት ጉዳይ ላይ ኢህአዴግ ስለ ራሱ ምን እንደሚሰማዉ ለማወቅ እንችልም፡፡ በኛ በኩል በዚህ ጥያቄ ላይ በጋራ ሊያግባባን የሚችል ነጻ መረጃ ምንጭ አስካሌለን ድረስ ለጥያቄዉ እንደ እያንዳንዳችን የግንዛቤ ደረጃና እንደ አመለካከታችን ሁኔታ የየግላችንን መልስ የምንሰጠጥበት ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ በቀበሌ አዳራሽ ተሰብስበን በጋራ በድምጽ ብልጫ የምንወስነዉም አይደለም፡፡ በኛ በኩል ኢህአዴግ ህዝባዊ አመኔታን ቀንሶብኛል ወይንም አልቀነሰብኝ ብሎ ራሱ እስኪነግረን መጠበቅ ሳያፈልገን የራሳችንን ግምት መዉሰድ አያሳነንም፡፡

ሀገራችን እንደማንኛዉም ሀገር ለብዙ ችግሮች የተጋለጠች ነች፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስትም እንደማንኛዉም መንግስት በሀገሪቱ ዉስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት፡፡ እንድ ገዢ ፓርቲ በሚሰራቸዉ መልካም ስራዎች ከቃላት ምስጋና በላይም ትልቁ የህዝብ ሽልማት የሆነዉን ድጋሚ ለመመረጥ የሚያበቃዉን የህዝብ ድምጽ ማግኘት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ በሌላ በኩል ገዥዉ ፓርቲ የያዘዉ ስልጣን የህዝብ መሆኑን ዘንግቶ አጉል መቅበጥ ከጀመረ ህዝብ ድምጹን በመንፈግ የመጨረሻዉን ቅጣት ይሰጠዋል፡፡

መንግስት የሚሰራዉ መልካም ስራ ከጥፋቱ የሚያመዝን መሆኑ የህዝብ ከበሬታ ለማግኘት በቂ ነዉ፡፡ መንግስት በሁሉም ነገር የተሳካለትና የተዋጣለት ሊሆን አይችልም፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ህዝባዊ ቅቡልነቱ መመዘን የሚኖርበትም ከዚህ አንጻር ነዉ፡፡ ለኢህአዴግ አመኔታ መስጠትም ሆነ መንፈግ የሚገባን የሀገራችን የሶስት ሺህ ዘመን ችግር ሁሉ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን መፍታት ችሏል ወይም አልቻለም በሚል ሊሆን አይገባም፡፡ የኢህአዴግ መልካም ስራዎቹ ከጥፋቱ የሚያመዝኑ ከሆነ አንዳንድ ድክመቶቹ ላይ ብቻ ተመስርተን ኢህአዴግ ተአማንነትና የህዝብ ድጋፍ የለዉም ብለን ድምዳሜ ላይ መድረስ አንችልም፡፡

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት በሀገራችን በዚህ ጉዳይ ዳሰሳ አድርጎ የመንግስት ተአማኒነት በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚል ተቋም ስለመኖሩ አላዉቅም፡፡ አንዳንድ መረጃዎች ቢኖሩም በዉጭ ዜጎችና ድርጅቶች የተዘጋጁ እንጂ እዚሁ በኛዉ ሰዎች የተደረገ ጥናት አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት መንግስታችንን በምን ያህል ደረጃ እንደምንደግፈዉ ከኛ ይልቅ ለሎች እንዲነግሩን መጠበቅ የግድ ሆኖብናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ አብዛኛዎቻችን ኢህአዴግን ለምን እንደምንደግፈዉ ወይም ደግሞ ለምን እንደምንጠላዉ አሳማኝ ምክንያት ያለን አይመስለኝም፡፡

ኢህአዴግ ራሱም ቢሆን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አለኝ የሚለዉ ምን ማረጋገጫ ይዞ እንደሆነ አናዉቅም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሊነግረን የሚገባዉ ማነዉ?እኛ በመንግስታችን ሙሉ አመኔታ እንዳለን ከኛ ዉጭ ሊነግረን የሚገባዉ ማነዉ?ራሱ ኢህአዴግ ፤ፓርላማ፤የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፤ዳያስፖራዎች ? ሻእቢያ ወይስ ጃዋር?እኛ መንግስታችንን እንደምንወደዉ ወይም እንደምንጠላዉ ወይንም ደግሞ እንደምንተማመንበት ወይም እምነት እንደማንሰጠዉ ከኛ ከባለጉዳዮቹ ዉጭ ሌላ የዉጭ አካል ወይም ፈረንጅ እንዲነግረን እንፈልጋለን ማለት ነዉ? ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ በኛዉ ሰዎች ዳሰሳ ጥናት አለመደረጉ ስራዉ ከባድ ስለሆነ ነዉ ወይንስ ስራ እንደ መፍታት የሚያስቆጥር የማይረባ ነገር ስለሆነ ነዉ?

“ኢህአዴግ ከመነሻዉ ጀምሮ አስካሁንም ድረስ አንዳችም የአመኔታ ቀዉስ ገጥሞት አያዉቅም” ከሚሉ ጀምሮ “ኢህአዴግ ድሮም ሆነ አሁን የህዝብ አመኔታ ኖሮት አያዉቅም ፤ አሁንም የለዉም፡፡ ” የሚሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንዲያዉም አንዳንድ ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸዉ ከተአማኒነት ጥያቄም በላይ ጭራሹን የመንግስትን ህጋዊነት (legitimacy)ለመቀበል የማይፈልጉና “ኢህአዴግ ማን ማንዴት ሰጥቶት ነዉ ግብር የሚሰበስበዉ ?በማንስ ፈቃድ ነዉ ከዉጭ መንግስታት ብድር የሚቀበለዉ ?”ወዘተ እስከማለት የደርሱም እንዳሉ ይታወቃል፡፡

እንደኔ እምነት ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በነበሩት ሃያ ስድስት ዓመታት ዉስጥ ህዝባዊ አመኔታዉ የመቀነስ ወይም የመዳከም አዝማሚያ የታየበቸዉ ወቅቶች ቢኖሩም በአብዛኛዉ ግን እየጨመረ የመሄድ አዝማሚያ ነዉ የሚታየዉ፡፡ የመንግስት ተአማኒነት አጠቃላይ አመላካች ግራፍ (ብናዘጋጅ) በአብዛኛዉ ከዓመት ዓመት ቀስ እያለ እየጨመረ የመጣና አንዳንድ አብይ ክስተቶች ባጋጠመ ግዜ ደግሞ በፍጥነት ያሻቀበበት በሌላ ወቅት ደግሞ በአንድ ግዜ ያሽቆለቆለበት ሁኔታም እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኢህአዴግ ተቀባይነት በእጅጉ የቀነሰባቸዉ ወቅቶች ለአብነት ለመጥቀስ ያህል የ93ቱ የድርጅቱ መከፋፈል ወቅት፤ የድህረ 97 ምርጫ ሁከት በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡ በ93 እና 97 መካከልም ቢሆን ኢህአዴግ በፊት ያልነበሩ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቃኙ አዳዲስ በርካታ አወዛጋቢ ፖሊሲዎችን (ሰነዶችን)ለማስተዋወቅ ሙከራ ባደረገበት ወቅት በተለይ ከምሁራኑ አካባቢ ክፉኛ ለትችት ተጋልጦ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በዚህ ሁለት ዓመት ዉስጥ በአብዛኛዉ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮች(ቀዉሶች)ለኢህአዴግ አመኔታ ያሽቆለቆለበት አጋጣሚዎች ናቸዉ፡፡

በሌላ በኩል ኢህአዴግ ህዝባዊ አመኔታና ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ካሳየባቸዉ ወቅቶች መካካል የኤርትራ ድንገተኛ ወረራ ማድረግን ተከትሎ ህዝብን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከመንግስት ጎን እንዲቆም የተደረገበት ትልቅ አጋጣሚ አንዱ ሲሆን ከዚያም ከ97 ምርጫ በኋላ የነበሩት ግዜያት ለኢህአዴግ ተአማንነት በእጅጉ የጨመሩ በርካታ ስራዎች በስፋት የተሰራበት ወቅት ነዉ፡፡ በዚህ ወቅት አስደናቂ የልማት ስኬቶች የተመዘገቡትና ሀገሪቱ በዉጭዉ ማህበረሰብ ዘንድም ከፍተኛ ተደማጭነትና ከበሬታ ማግኘት የቻለችበት፤ በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በፈጠሩ ጥቃቂን ማህበራት ተደራጅተዉ በልማቱ በመሳተፍ ሃብት ማፍራት የቻሉበት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ኢህአዴግን በፈቃዳቸዉ በመቀላቀል ደጋፊና ጉልበት የሆኑበት፤ ከቅንጅት ሽንፈት በኋላ በርካታ ወጣቶች አጋሪነታዉን ለኢህአዴግ ያደረጉበት ሁኔታ መፈጠሩ፤ መከላከያ ሰራዊታችን አዘዉትሮ በተሳተፈባቸዉ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ሁሉ ያከናወናቸዉ አኩሪ ስራዎች በተለይም በሶማሊያ አልሸባብን በመደምሰስ የሶማሊያን ሀዝብ ሰላም በማረጋጋጥ ባደረገዉ ታላቅ ተጋድሎ መንግስት በገዛ ህዝቡም ሆነ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ያስገኘለት መልካም ስምና ከበሬታ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ፤ በ2000 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሚለኒዬም ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ የታየዉ ከፍተኛ የህዝብ መነቃቃትና በወቅቱ ከዚያ በፊት ከነበረዉ በተሻለ ሁኔታ መንግስትና ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ መደማመጥ የጀመሩበት፤ በተጨማሪ የኢህአዴግ አመራሮች ቀደም ሲል ብዙም ያላጤኑት የነበረዉ የኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤት መሆኗን ጉዳይ በአደባባይ እዉቅና የሰጡበት አጋጣሚ መሆኑና ከለንደቅዓላማ ጋር በተያያዘም ኢህአዴግን በህዘቡ ዘንድ ለቅያሜ ዳርገዉት የነበረዉ ሁኔታ ተቀይሮ ለባንድራችን የሚገባዉን ክብር መስጠት በመጀመራቸዉ በህዝቡ ላይ የፈጠረዉ ደስታ በምላሹ ለኢህአዴግ መልካም አመለካከት እንዲኖር ከፍተኛ አግዛ ያደረገበት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዘመናት ፈጽሞ የማይታሰብና ሊተገበርም የማይቻል ተደርጎ ይቆጠር የነበረዉ የታላቁ ሂዳሴ የዉኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጄክት ግንባታ መጀመር ወደፊት ሊያበረክት ከሚችለዉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዉ በላይ መላዉን ህዝብ በአንድነትና በጋራ ለማሰለፍ ያስቻለና ከፍተኛ የአሰባሳቢነት ኃይል ያለዉ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠር መቻሉ ወዘተና ሌሎችም ያልተጠቀሱ ክንዉኖች በድምር ሲታዩ የኢህዴግን ቅቡልነት ሽቅብ እንዲመነደግ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የኢህኤዴግ ተአማኒነት ሁኔታ በ93ቱ የድርጅቱ ዉስጣዊ ቀዉስና በ97 ምርጫ ወቅት መዳከም ከማሳየቱ ዉጭ በቀሩት አብዛኛዎቹ ግዜያት ከፍተኛ መሻሻል ያሳየበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል፡፤

በሚያሳዝን ሁኔታ ከዚያ ሁሉ ዓመታት በኋላም ኢህአዴግ ዳግም እንደ አዲስ ለከፍተኛ ተአማኒነት ቀዉስ እየተጋለጠ የመጣዉ በዚህ ሁለት ዓመት ዉስጥ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ በዚህ ሁለት ዓመት ዉስጥ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ተከስቶ የነበረዉ አደገኛ ቀዉስና የችግሮቹ መነሻ የነበሩት የህዝቡ ጥያቄዎች አስካሁንም በሚፈለገዉ ደረጃ ሁኔኛ ምላሽ አላገኘም መባሉ፤ይሄ ችግር በራሱ በቂ ሆኖ እያለ ኦሮሚያን በአዲስ አበባ ልዪ ተጠቃሚነት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ ይፋ በተደረገዉ ረቂቅ አዋጅ በብዙ ወገኖች አካባቢ እያስነሳ ያለዉ የተበዳይነትና የመገፋት ስሜት የፈጠረዉ ተቃዉሞ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ በአዲስ አባባ ልዩ ተጠቃሚነት መብት ጉዳይ መነሾ የተነሳዉ የተቃዉሞ ድምጽ ገና ሳይረግብና እልባትም ሳይሰጠዉ በእሳት ላይ በንዚን የመጨመር ያህል ያስቆጠረዉ አዲስ የተፈጠረዉ ቀዉስ ደግሞ የነጋዴዉ ህብረተሰብ የገቢ ግብር ጭማሪ ነዉ፡፡

ነጋዴዉ ህብረተሰብ የእለታዊ ገቢ ግምት ያለቅጥ በዝቷል በሚል ተቃዉሞና ቅሬታ ሲያሰሙ መቆየታቸዉና ይህን አጋጣሚም እንደ ሁልግዜዉም ለመሰሪ ዓላማቸዉ መጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ክፉኛ እያራገቡት ለማጋጋልና ወደ አጠቃላይ ሁከት ለመቀየር ሲያሴሩ መታየቸዉ ሲታሰብ አጠቃላይ አዝማሚያዉ የኢህአዴግን ወቅታዊ ተአማኒነት በእጅጉ ሊጎዳ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ አንባቢዉ እንዲረዳልኝ የምፈልገዉ ኢህአዴግ በህገመንግስቱ የተደነገገዉን አሮሚያን የሚመለከተዉን አንቀጽ ለምን ለመተግበር ተንቀሳቀሰ እያልኩ አይደለም፡፡ በህገመንግስቱ የተደነገገዉን ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ አለበትና፡፡ ያን ማድረጉ ሳይሆን አለማድረጉ ነዉ መንግስትን ሊያስተች የሚገባዉ፡፡ የእኔም እምነት እንደዚያዉ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስትን የምወቅስበት አንዳችም ምክንያት አይኖረኝም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ መንግስት የገቢ አቅሙን ለማጠናከር የግብር ስርአቱን ማስተካከያ በማድረግ ግብር ለመጨመር መንቀሳቀሱ ላይም ትችት እያቀረብኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከግዜ አመራረጡ ጀምሮ ህብረተሰቡን በተሟላ ሁኔታ አሳትፎ ባለመንቀሳቀሱና ከሁሉም በላይ ለነጋዴዉ ለህብረተሰብ ግልጽ የሆነ መረጃ በመስጠት ረገድ ክፍተት በመፈጠሩ ከግንዛቤ ማነስ የተፈጠረ ቅሬታ እንደሆነ ነዉ የምረዳዉ፡፡ ከዚህ ሌላ ምናልባትም ይህን ሃላፊነት እንዲያስፈጽሙ መንግሰት ራሱ የመደባቸዉ አንዳንድ ሰዎች አካባቢ ሆን ተብሎ የተሰራ ዴባ እንዳይኖርም መጠርጠሩ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት አብዛኛዉ የነጋዴዉ ህብረተሰብ ላነሳዉ ቅሬታ ተገቢዉን ምላሽ እያገኘና ጭማሪ ተደረገ የተባለዉም ቢሆን ሆን ተብሎ ተጋኖ የተወራዉን ያህል እንዳልሆነ የጉዳዩ ባለቤት የሆነዉ የነጋዴዉ ህብረተሰብ ከበፊት ይልቅ አሁን ግልጽ ስለሆነለት የተጣለበትን ግብር አብዛኛዎቹ ከፍለዉ እያጠናቀቁ መሆናቸዉን ነዉ፡፡ አሁን ከመንግስት ጋር የሚያጣላ ቀረ የተባለ ነገር ባይኖርም ፀረ- ሰላም ኃይሎች ግን ሆን ብለዉ እያራገቡ የሁከት መነሻ ለማድረግ መፍጨርጨራቸዉን አላቆሙም፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ በዚህ መንገድ እልባት የተሰጠዉ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ በገዥዉ ፓርቲ ላይ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አመኔታ ሊሸረሽርበት እንደሚችል መገመቱ አይከብድም፡፡

5.የመንግስትን ህዝባዊ አመኔታ በመሸርሸር ረገድ ዋነኛ ምክንያቶች፤

 ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮም ሆነ ከኛ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሲታይ መንግሰትን ህዝባዊ አመኔታ ሊሸርሽርበት የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነዉ በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካካል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፤ ስር የሰደደ ሙስናና የመልካም አስተደዳር እጦት፤ የህዝብ ሀብት ላይ የሚደረግ አባካኝነት፤ የመንግስት አጠቃላይ የማስፈጸም የብቃት ችግር፤በተለያዩ ምክንያቶች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት (ልማት) መቀዛቀዝና ያን ተከትሎም የስራ አጥነት መበራከትና አስከፊ የኑሮ ዉድነት መከሰት፤ ፍትሃዊ የሀብት ክፍል አለመኖር፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት ይልቅ በጥላቻ ላይ የተመሰረተና ወደ አንድ ጫፍ ያዘነበለ አክራሪ አቋም በመያዝ በጥቃቂን ጉዳዮች ሁሉ የተከፋፋሉ ሲሆኑ፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ አመራር የህዝብን ፍላጎት ከግምት ሳያስገባ በዘፈቀደ ማቀድና፤ የህዝብ ፍላጎት ባልጠበቀ ሁኔታ የመሰለዉን ፖሊሲ እንዳሻዉ ማዉጣቱ፤ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የፈሰሰባቸዉ ግዙፍ ፕሮጄክቶች በደካማ አፈጻጸም ምክንያት ያለቅጥ መጓተትና ለዝርፊያ መዳረግ፤ እንደ አሜሪካዉ ወተር ጌት መሰል የፖለቲካ ቅሌት (Watergate scandal) ሲያጋጥም፤መንግስት የዜጎችን ደህንነትና ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር ሲሳነዉ፤ በተለያዩ መነሾዎች የሚቀሰቀሱ የርስበርስ አለመግባባቶችን መንግስት መፍታት ሲሳነዉና በተለያዩ ህዝቦች መካካል የርስበርስ ጥላቻ አመለካከት እየነገሰ በመሄድ ለግጭት መነሻ ሲሆን፤ ከፌዴራላዊ ስርአቱ ባህሪይና ከህገመንግስቱ አግባብ ዉጭ ከፋፋይና ዘረኛ አመለካካት ባላቸዉ አንዳንድ ባለስልጣናቱ ሆን ተብለዉ የሚፈጸሙ ከፋፋይና አግላይ አሰራሮች የተነሳ በዜጎች መካካል አንዱ የስርአቱ ልዩ ተጠቃሚነት መብት ያለዉ ሌላዉ ደግሞ የተበዳይነትና የመገለል ስሜት እንዲሰማዉ ሲደረግ በዚህ መነሾም እርሰበርስ መጠራጠር ሲሰፍን ..ወዘተ የመሳሰሉት ሁኔታዎች በተናጠልም ሆነ በጥምር ሲኖሩ ወይም ያሉ በመሰለ ግዜ ዜጎች በስልጣን ላይ ባለዉ መንግስት ላይ አመኔታ ሊያጡ ይችላሉ፡፡

ለዚህ አመለካካት ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ የሚያደርገዉ ደግሞ የህብረተሰቡ የፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና ዝቅተኝነትና ኋላቀር በሆነ ባህል ተጽእኖ ስር በመወደቅ፤ በህብረተሰቡ ዉስጥ ግልጽነት አለመኖሩና በዚህ መነሾም በዘፈቀደና በጭፍን መንግስትን የመጠራጠር ልማድ መኖር ነዉ፡፡

ማናችንም በቀላሉ መገመት እንደምንችለዉ ዜጎች ያለአንዳች ምክንያት መንግስታቸዉን ፊት አይነሱም ወይም አመኔታ አይነፍጉትም፡፡ መንግስት አምኖ ለመቀበል የማይፈልገዉ ዜጎች ግን ደስተኛ ያልሆኑበት አንድ ችግር ሊኖር እንደሚችል ምንግዜም መጠርጠር ይገባዋል፡፡ ዜጎች በቃሉ የማይገኝ፡ሙስናን ለመታገል ቁርጠኝነት የጎደለዉ፤በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎስቋላ ዜጎቹን ህይወት ከማሻሻል ይልቅ ራሳቸዉንና ለማበልጸግ ተግተዉ የሚሰሩ ዘራፊ ባለስልጣናት ላይ ቆንጠጥ የሚያደርግ እርምጃ ከመዉሰድ ይልቅ ለሌቦች ርህራሄ የሚያሳይ፤ ተቃዉሞና ቅሬታቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ በማሰብ ምንም እንሆንም በምል መንግስታቸዉን ተማማነዉ ባዶ እጃቸዉን ወደ ጎዳና የሚወጡ ዜጎች ላይ ከህገመንግስቱ አግባብ ዉጭና ከራሱ ከመንግስት ፍላጎት ባፈነገጠ ሁኔታ በራሳቸዉ ተነሳሽነት በዘፈቀደ በገዛ ዜጎቻቸዉ ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ የወሰዱ የጸጥታ ኃይሎችን ለይቶ ተገቢዉን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምት ለመዉሰድ የማይሻና ጭራሽ ጥፋታቸዉን የሚደባብቅ መንግስትና ፓርቲ ላይ አመኔታ ሊኖራቸዉ አይችልም፡፡ ራሱን በዚህ ደረጃ ያስቀመጠ መንግስትና ፓርቲም በምንም ምክንያት “ዜጎች አመኔታቸዉን ሰጥተዉኛል፡፡ ለህዝብ ጥቅም ነዉ የቆምኩት” ለማለት አይደፍርም፡፡ ይሄን እዉነታ እየመረረንም ቢሆን መቀበል አለብን፡፡

የሀገሪቱ መንግስት ሌላዉ ቀርቶ ምን እየሰራ እንደሆን ለገዛ ህዝቡ ለመግለጽ የማይሻና በሚሰራዉ ሁሉ ምስጥራዊ የሆነና ሁሉንም ነገር ከሚመራዉ ህዝብ የሚደብቅ መንግስት በምንም መስፈርት ቢሆን ህዝቡ ይወደኛል፤ይደግፈኛል ማለት አይችልም፡፡ ስለ ጥንካሬዉ እንጂ ስለድክመቱ አንዳችም ነገር መጻፍና መናገር አትችሉም በሚል የሚከለክል መንግስት ፤ ከትክክለኛ ትችት ይልቅ ለባዶ ሙገሳ ከበሬታና ቅድሚያ የሚሰጥ ፤በፈቃደኝነት መወደድንና ከበሬታን ከማትረፍ ይልቅ መፈራትን የሚሻ መንግስት፤ ህዝቡ በቀጥታ ከሚነግረዉና በተግባርም ከሚያየዉ ይልቅ የካድሬዎቹን የተዛባ ሪፖርት አምኖ የሚቀበል መንግስት ከቶ እንዴትስ ታምኛለሁ ለማለት ይደፍራል?

ከዚህ ደሃ ህዝብ በግብር መልክ የሰበሰበዉንና በህዝብ ስም ከዉጭ በብድር ያገኘዉን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለስራ የተመደበላቸዉን ባጄት በምን ላይ እንዳዋሉት ማስረዳት የማይችሉ ዘራፊ ባለስልጣናቱን አምርሮ ከመታገልና እርምጃ ከመዉሰድ ይልቅ የሚያድበሰብስ፤መልካም አስተዳዳር በመንፈግ ህዝብን በማማረርና በተለያዩ መንገዶች በህዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙ ባለስልጣናትን ህግ ፊት አቅርቦ ከመቅጣት ይልቅ ከአንድ ቦታ አንስቶ ሌላ ቦታ በመመደብ የሚሸሽግ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሃብት ደጋጋመዉ ደጋግመዉ ለሚዘርፉ ሌቦች የአቅም ማነስ ችገር ሲላለባቸዉ ነዉ …ወዘተ እያለ የሚራራላቸዉ መንግስት ህዝባዊ አመኔታ አለኝ ብሎ ለምን እንደሚተማማን አይገባኝም፡፡

በርግጥ ኢህአዴግ ለህዝብ የመቆርቆርና ለህዝብ የመወገን ጉዳይ ላይ በፊትም ሆነ አሁንም ቢሆን መሰረታዊ ችግር የለበትም፡፡ ኢህአዴግ ለዚህች ሀገርና ለዚህ ህዝብ የሰራዉን ዉለታም ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ በዚህ ስራዉም ከፍተኛ የህዝብ ፍቅርና አክብሮት አትርፎለትም እንደነበር አይካድም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ህዝቡ የለገሰዉን ከበሬታና ያሳየዉን ፍቅር ጠብቆ ለማቆየትና ለማስቀጠል አልተቻለዉም፡፡ ህይወታቸዉን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ለመክፈል ቅንጣት የማያመነቱ የነበሩ ጠንካራ ታጋዮቹ አሁን አሁን ይሄ አኩሪ ባህሪያቸዉ ከላያቸዉ እየሸሻቸዉ ህዝባዊ አመለካከታቸዉም ተረት ተረት እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡

በአንድ ወቅት በተለይም ኢህአዴግ የመንግስትን ስልጣን በተቆጣጠረበት ሰሞን አስር ብር የሠረቀ ሌባ ሲያገኝ በአደባባይ እዚያዉ በተገኘበት ቦታ ግምባሩን በጥይት ብሎ ሲጥል እንዳልነበር አሁን ላይ ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ የሰረቁ ሌቦች ላይ መጨከን እየከበደዉ እንደሆነ እያየን ነዉ፡፡ የሀገር ሃብት ያለአግባብ ሲባክንና ሀገሪቱ የማንም ዘራፊ መጫወቻ እየሆነች እያየ የረባ እርምጃ የማይወስድ መንግስትን እንዴት ተደርጎ ነዉ ህዝባዊ አመኔታ ሊኖረዉ የሚችለዉ?ይሄ ህዝብ በኢህአዴግና በሚመራዉ መንግስት ላይ ተስፋ ቆርጦ ፊት ቢነሳዉና የመራጭነት ድምጹን ቢነፍገዉ ይፈረድበታል እንዴ?በሚቀጥለዉ ምርጫ ኢህአዴግን አልፈልግም ብሎ ባዶ ወረቀት ምርጫ ሳጥን ዉስጥ ቢከት ጃዋርና ኢሳይስ አፈወርቂ ላይ ልያሳብብ ነዉ ማለት ነዉ? ስለዚህ መንግስት እነዚህንና መሰል ድክመቶቹን ተቀብሎ በተግባርም አስተካክሎ ካላረጋገጠ በስተቀር የህዝብ አመኔታን መልሶ ለማደስ እንደሚያዳግተዉ ካሁኑ ሊረዳ ይገባል፡፡

ኢህአዴግ ህዝባዊ አመኔታን መልሶ ለማደስ ማድረግ የሚገባዉ፤

ገዥዉ ፓርቲ የህዝብ አመኔታ እንደጎደለበት ከተረዳ የተመናመነበትን የህዝብ አመኔታ መልሶ ለማደስ የሚያስችለዉን አንዳንድ እርምጃዎችን መዉሰድ ይጠበቅበታል፡፡

* አዲስ ፖሊሲና ህግ ለማዉጣት በሚፈልግበት ግዜ ሁሉ በቅድሚያ ከህዘቡ ጋር በግልጽ መነጋገርና የተሻለ አማራጭ ሃሳቦችን በመቀበል በግብአትነት መጠቀም ይገባዋል እንጂ በእኔ አዉቅልሃለሁ መንፈስና በትእቢት ተወጥሮ የህዝቡን አስተያየት ማጣጣል አይኖርበትም፡፡

* ጥርጣሬን በማስወገድ መተማማንን ለመፍጠር በማንኛዉም ጉዳይ ላይ ግልጽነት ማስፈን ለህዝብ ጥያቄና ፍላጎት ፈጣን መልስ መስጠት ፤ የህግ የበላይነትን ራሱም አክብሮ ማስከበርና ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ ፤ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር ማድረግ ፤ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ፓርላሜንታዊ ቁጥጥር እንዲኖር ማድረግ ፤መንግስት በቃሉ የሚታመን ለህዝብ የገባዉን ቃል የማይጥስ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡

* ዜጎች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ማለትም በዉሳኔ አሰጣጥ በፖሊሲ ቀረጻና በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሁሉ በባለቤትነትና በሃላፊነት ስሜት በንቃት የሚሳተፉበትና በነጻነት በመንግስት አተገባባር ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ይህ ሁሉ ሁኔታ ማመቻቻት ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ መንግስት ነዉ፡፡

* ኢህአዴግ ህዝብ የማያዉቀዉና የማያምንበትን አንዳችም ጉዳይ ላይ መወሰንም ሆነ መፈጸም አይኖርበትም፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ሰፊ ነጻነት ያለዉ የመረጃ ተደራሽነት ሊኖር የግድ ነዉ፡፡ ህዝቡ ስለ መንግስት አሰራር ለማወቅ የመንግስትን ሚዲያ ዉትወታ፤ይፋዊ የመንግስት መግለጫ ወይም የከተማና የቀበሌ ሹማምንት በአዳራሽ ሰብስበዉ አስኪነግሩት መጠበቅ አይገባዉም፡፡ መረጃዎችን ከተለያዩ ምንጮች የሚያገኝበት ዕድል ሊነፈግ አይገባም፡፡ መንግስት የህዝብን አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመገደብ እሱ ብቻ በብቸኝነት በሚያቀርበዉ መረጃ ላይ ተመስርቶ የህዝብን አመኔታ ማግኘት አይችልም፡፡ በጎና ክፉዉን ለመለየትና ለመወሰሰን እድሉን ለህዝቡ መተዉ ይገባዋል፡፡

* ከሁሉም ጉዳዮች ሁሉ የመንግስትን አመኔታ በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና እንዳለዉ የሚታመነዉ ሙስናና የመልካም አስታዳዳር ዕጦት ነዉ፡፡ የከፋ የመልካም አስተዳደር እጦት በሰፈነበትና ሙሲና በግላጭ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅሞ ቀን በቀን በአደባባይ ዝርፊያ በሚያከናወንበት ሁኔታ መንግስት የህዘብን አመኔታ አገኛለሁ ቢሎ መጠበቅ ሆነ መመኘት አይኖርበትም፡፡ መንግስት ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ በህዝብ ዘንድ ተአማኒነትን ለማግኘት ከፈለገ ህዝብን እያስመረረ ያለዉን ሙስናና የመልካም አስተዳዳር እጦት ቅድሚያ ሰጥቶ መቅረፍ ይገባዋል፡፡

 ማጠቃለያ

 በየትኛዉም ህብረተሰብ ዉስጥ የሚገኝ አብዛኛዉ ሰዉ የሚስማማበት አንድ እዉኔታ ቢኖር ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ የሚያጣበት ዋነኛዉ መነሻ ምክንያት መንግስት ራሱ ለመታመን የማይበቃ በመሆኑ እንደሆነ የመስኩ ምሁራን ያስገነዝባሉ፡፡ ( “In much of the world, the core reason for public distrust in government is that government does not deserve to be trusted.”)

ህዝብ መንግስትን የማያምንበት ምክንያት መንግስት ራሱን ከህዝብ ያራቀና የገዛ ህዝቡን ስለማያምን ነዉ፡፡ መንግስት ራሱ የሚያስተዳዳረዉን ህዝብ በማያምነት ሁኔታ ህዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲኖረዉ መጠበቅ የዋህነት ነዉ፡፡

የአብዛኛዎቹ የመንግስት ባለስልጣናት ቋሚ ስራ ህዝብንና ሀገረቱን ማገልገል መሆን ቀርቶ ህዝቡን እያደሄዩ ለራሳቸዉና ለወዳጅ ዘመዶቻቻዉ ከሚገባቸዉ በላይ በስርቆት ሀብት በማካበት ተግባር መጠመዳቸዉ ነዉ፡፡ ከገዥዉ ፓርቲና ከመንግስት አመራሮች መካካል አንዳንዶቹ ድርጅቱ ከተነሳበት ህዝባዊ ዓላማ እያፈነገጡ የያዙትን ስልጣን ለግል ብልጽግና ማምጫ መሳሪያነት መጠቀማቸዉና የስርአቱንም ፋይዳ ከዚህ አካያ ስለሚያዩ ብዙ መንግስትን በእጅጉ ለትችት የዳረገዉን የዲሞክራሲ፤ የፍትህና የሰብአዊ መብት አከባባር ጉዳይ ለማሻሻል ያለመፍቀዳቸዉ ዋነኛ ምስጢር በሰፊዉ የለመዱት ይህ ጥቅም ወደፊት እንዳይቋረጥባቸዉ ስለሚሰጉ ነዉ፡፡ ይህ ጥቅም ደግሞ ከመንግስት ስልጣን ዉጭ ሊገኝ የሚችል ባላመሆኑ ስልጣናቸዉን ሊነቀንቅ የሚችል ሁኔታ እንዲኖር በጭራሽ አይፈቅዱም፡፡ ጥቂት ለለዉጥ ዝግጁ የሆኑ ባለስልጣናት ባይጠፉም ስርአቱን ከጥቅም አኳያ ብቻ በሚያዩት ግለሰቦች ጫና ምክንያት ድርጅቱ በራሱ ላይ ስር ነቀል የሆነ ለዉጥ ለማድረግ ተስኖታል፡፡

የመንግስት ባለስልጣናት የያዙትን ሃላፊነት ህዝቡ የሰጣቸዉ ለህዝብ ጥቅም እንዲሰሩበት እንጂ ለራሳቸዉ ጥቅም እንዲገለገሉበት ባለመሆኑ በተለያዩ መንገዶች ስልጣናቸዉን ለግል ጥቅማቸዉ ያለአግባብ የሚጠቀሙበት አጋጣሚ ሲኖር በህግ ሊጠየቁበት ይገባል እንጂ እንደቀላል ነገር ሊታለፉ አይገባም፡፡ ህገወጥ ብልጽግና ጥቂት አጥፊዎችን በመቅጣት ብቻ መፍትሄ የሚያገኝ ባለመሆኑ መንግስት ራሱን ሙሉ በሙሉ በማደስ ለሙስና የተመቻቸ ሁኔታ እንዳይኖር ሁሉንም ቀዳዳዎች ለመድፈን ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ህዝቡ በገፍ እየተደረገ ስላለዉ ዝርፊያ መስማት አንገሽግሾታል፡፡ ሀገሩ በጥቂት ግለሰቦች መበዝበዟ እጅግ አስመርሮታል፡፡ መንግስት በህዝብ ስም በየዓመቱ ከዉጭ የሚበደረዉ መጠነ ሰፊ ገንዘብ ሲታሰብ ወደፊት የሚጠብቀዉን ዕዳ እያሰበ ከአሁኑ ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ ለሙሰኞች ለምዝበራ የተመቻቹና በጅምር የሚቋረጡት ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸዉ ፕሮጄክቶች ጉዳይም እጅግ አሳሳቢ ነዉ፡፡ ህዝቡ ስለ አዲስ ግዙፍ ፕሮጄክት መሰረት ድንጋይ መጣል በሰማ ቁጥር ወደፊት ከሚኖረዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ይልቅ ቀድሞ የሚታየዉ ሆን ተብሎ የታቀደ አንድ ሌላ ተጨማሪ የብዝበዛ ምንጭ አድርጎ ነዉ፡፡

የመንግስት ተግባርና ሃላፊነትም መላዉን የሀገሪቱን ዜጎችን የልማቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግ እንጂ ጥቂት የተመረጡ ግለሰቦች ከአቅማቸዉ በላይ ሀብት እንዲያካብቱ ማድረግ አይደለም፡፡ ሙስናን ሳያጠፉ የህዝብን ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን እዉን ማድረግም ሆነ ሙስና በተንሰራፋበት ሁኔታ ድህነትን ማጥፋት አይቻልም፡፡ ከዚህ አንጻር የፊሊፒንሱ ፕሬዝዳንት Benigno Simeon Aquino III, በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሙሲናን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት “ሙስና ከሌለ ድህነት አይኖርም!” (“If there is no corruption, there is no poverty.) እኒህ የፍሊፕንስ ፕሬዝዳንት በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ 88% ከመቶ የህዝብ አመኔታ (high approval rating) ማግኘት የቻሉ ብቸኛ መሪ ናቸዉ፡፡ እኛም ሙስናን በቃላት የሚያወግዙ ሳይሆን በተግባር ሙሰኛንና ሙስናን አምርረዉ የሚታገሉ ጀግና መሪዎች ናቸዉ የሚያስፈልጉን፡፡ መሪዎቻችን ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገልም መጀመሪያ ራስን ንጹህ አድርጎ መገኘትም የግድ ነዉና በዚህ ረገድ ተገቢዉን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡

በመጨረሻም አብዛኛዉ ህዝብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ጎስቋላ ህይወት እየኖረ ጥቂቶች ግን ያልደከሙበትን በሚሊዮኖች እየዘረፉ መሆናቸዉን ለመስማት ከዚህ በላይ ብዙም ትዕግስት ያለዉ አይመስለኝምና መንግስት እንደከዚህ ቀደሙ ጉዳዩን ሳያድበሰብስ ከቻለ ዝርፊያዉን እንዲስቆም ያለበለዚያ ደግሞ ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ አልችልም ካለ ለሚችለዉ ስልጣኑን መልቀቅ ነዉ የሚኖርበት፡፡

——

የዚህ ፅሁፍ ቀጣይ ክፍሎች

* ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 2 | ያለፉ የምርጫ ተሞክሮዎችና ለኢህአዴግ ማሸነፍ ዋነኛ ምክንያቶች

* ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 3 | በመጭዉ ምርጫ የኢህአዴግን ዕጣ ፈንታ ሊወስኑ የሚችሉ የስጋት ምንጮችና ተግዳሮቶች (ገና ያልታተመ)

—-

*የኮ/ አስጨናቂ /ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

***********

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories