የመገንጠል ፖለቲካ፤ የንጉሱ መውደቅና የሀገሪቱ የኋሊዮሽ ጉዞ

(ነፃነት አካሉ)

ስለ መንግስት ወይም ዲሞክራሲያዊነት ስናነሳ የሰዎች መብት መነሻችንና መድረሻ ካልሆነ ከንቱ ነው፡፡ የሰው ልጅ መብቶቹ ላይ በተፈጥሮም ሆነ ማህበረሰቡ ላይ ከሚደርስበት ጫና በመከላከል ለማህበረሰቡ በጎ ነገር እንዲያበረክት መብቶቹ ሊረጋገጡለት ይገባል፡፡ መብቶቹ ላይ በደል የሚደርስበት ከሱ የተሻለ ሀይል ካላቸው ቡድኖች እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

የጉልበተኞች ሁሉ ጉልበተኛ ራሱ መንግስት በመሆኑ መብቶች በአንድ ሀገር ዋስትና አገኙ የሚባለው ሁለት ነገሮች ሲሟሉ ነው:-

1) በማንኛውም ሁኔታ የማይጣሱ መብቶች በግልፅ ተለይተው መደንገግ አለባቸው

2) መንግስት እነዚህ መብቶች እንዲያከብርና እየተከበሩ መሆኑን የሚያረጋግጡ ከመንግስት መሉ በሙሉ ነፃ የሆኑ ፍርድ ቤቶች በህገ መንግስት ሲቋቋሙ ነው፡፡

የህገ-መንግስት ዋና ጭብጥ መብትን በፅኑ መስቀመጥ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አገኙ ይባላል፡፡ ፍርድ ቤት ከተቋቋመ መብቶች በግልጽ ባይቀመጡም ተለይተው መታወቅ ይችላሉ፤ ከአለማቀፍ ሰነዶች ወይም ከዳኞች እውቀት በትርጓሜ ማወቅ ይቻላል፡፡

ማንም ሰው በአካሉ፤ በነፃነቱና በንብረቱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳደርስበት ማንኛዉም የሰለጠነ ሀገር መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ (በእኩልነት) ሙሉ ከለላ እንዲሰጥ የሚደነግገው የሰብዓዊ መብት አለማቀፋዊ ሰነድ ሆኖ የፀደቀው በ1949 ነው፡፡  እነዚህ መብቶች ለሁሉም የሰው ልጆች በእኩልነት የሚኖራቸው ስለሆኑ በእነዚህ ብይን መስጠት የማይችል የህግ ሰው የለም፡፡

በርግጥም መብቶች ተፈጥሯዊ እንደመሆናቸው የሰለጠኑ መንግስታት (civilized nations) የሚባሉት ቀድሞውኑ በነዚህ መርሆችን ዋስትና የሰጡ ሀገሮች ነበሩ፡፡ በእኛ ሀገር ፊውዳሎች ለነሱ ያልተዋጋ ወይም የጣሉበትን ማንኛውም ግዴታ መወጣት ያልቻለ መሬቱን መውረስ፤ ማሳደድና ቤተሰቡን መያዝ የተለመደ ተግባር ነበር፡፡ ይህን የሚከለክል ህግ ባለመኖሩ ዜጎች ዋስትናም መከራከሪያም የላቸውም፡፡

ኢትዮጵያም ለስሙ አንድ ሀገር ትባል እንጅ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስም ሆነ ሰርቶ ማደር፤ ንብረት ማፍራት አንድን ሀገር አቋርጦ ከመግባት በማይሻል ደረጃ የፊውዳሎችንና የአካባቢዉን ህዝብ ይሁንታ ያስፈልገው ነበር፡፡

ይህንን መቀየር የቻሉ አንድ መሪ ብቻ ናቸው፡፡ ገና ከአልጋ ወራሽነታቸው በተራማጅነታቸው በሸዋ መኳንንቶች ዘንድ የማይወደዱት ራስ ተፈሪ መኮንን በነገሱበት ማግስት ያወጧቸው ህጎችና አዋጆች የሀገሬውን ህዝብ ያስፈነደቁና ፊውዳሊዝምን የበጣጠሱ ነበሩ፡፡

Photo - Emperor Haile Selasie with BBC in1954
Photo – Emperor Haile Selasie with BBC in1954

ባርነትን ባስወገዱ ማግስት በ1931 ህገ-መንግስት ቀርፀው ጀምሮ ማንም ሰው በአካልና በንብረት ከሚደርስበት ጉዳቶችን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ (በእኩልነት) በህግ ፊት እንዲታይ ህገ-መንግስታዊ ከለላ ከሰጡ ቀደምት ሀገሮች ኢትየጵያ አንዷ መሆን ችላለች፡፡ ኢትየጵያዊ ንብረቱን የመሸጥና የመለወጥ፤ በሀገሪቱ ውስጥ በፈለገው ቦታ የመንቀሳቀስና መብቶቹ እንዲጠበቅ ዋስትና አገኘ፡፡

በጣሊያን ወረራ የተቋረጠው አስተዳደር ተመልሶ ሲገነባ የተባበሩት መንግስታት መስራች አባል ሀገር በመሆን በ1955 የመናገርና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትን ጨምሮ ሌሎች መብቶች እንዲኖሩ በመደንገግ መሰረታዊ ነፃነቶችን ሙሉ በሙሉ የምታከብር ሀገር ለመሆን ተቃርባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ በየትኛውም አለም እንደነበረው ቅን አሳቢ ነገስታት ኖረዋት ሊሆን ይችላል፡፡  ነገር ግን ዘላቂ ሀገር መፍጠርና የዜጎቻቸው ህይወትም ሆነ የአለምን ዘመናዊነት ያሸጋገሩ ሀገሮች ነገስታት ብቻ ያደረጉት አንድ ነገር አለ፡፡ የሀገሪቱን ጉዳዮች ከነገስታት ጓዳ እያወጡ ስርዓት እየፈጠሩ መሄድ፡፡ ይህም እነሱ ኖሩ አልኖሩ የሚቀጥል ትውልድን መሻገር የሚችል ዘላቂ ስረዓትን መፍጠር ነው፡፡

እንደ መንግስት ምስረታ ካየነው የኃይለስላሴ ንግስና በኢትየጵያ መሬት መንግሰት የተባለ ነገር እንደፀሀይ የወጣበት ዘመን ነበር ማለት የይቻላል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሺህ አመት የኖረውን ስርዓት በመቀየር ዜጋና ሀገር፤ መንግስትና ግዛት፤ ንጉስና አስተዳደር፤ ህግና ቢሮክራሲ፤ ፖሊስና መከላከያ፤ ትምህርትና እምነት በሂደት እየተለየ የመንግስት ምስረታ ሂደቱ ስርዓት መያዝ የተጀመረበት ጊዜ ነው፡፡

በነዚህ ተራማጅ ለውጦች ምክንያት ኢትዮጵያ ከፊዉዳሊዝም እየወጣች ወደ ከፒታሊዝም መሄድና የህዝቧም ሂወት መሻሻል ጀመረ፡፡ ይህንን ለማድረግም የመንግስት ግብር ተሰብስቦ የጋራ የህዝብ ገንዘብ እንዲኖር ማሻሻያ የተደረገውም በዚህ ዘመን ነበር፡፡

የሀገሪቱ ግብር ከፊውዳሎች ወጥቶ ወደህዝብ ካዝና እንዲገባ የአሁኑ ገቢዎች ዲፓርትመንት በመቋቋሙ ሀገሪቱ በአምስት አመት ትሰበስበው የነበረውን ግብር በአንድ ወር መሰብሰቡ መቻሏን ለመንግስት ሰፊ ፕሮግራሞች መጀመር እንዳገዘ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ያነሳሉ፡፡ በዚህ ስሌት በዚያ አመት የተሰበሰበው ግብር ከዘያ በፊት በ60 አመት የሚሰበሰብ ገቢ ነበር ማለት ነው፡፡

ይህ ማለት ግን በሀገሪቱ ግብር አይሰበሰብም ነበር ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ ያክል የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ተብሎ የሚታወቀውን ግዛት የሚያስተዳድሩት ደጃዝማች ባልቻ ከቡና፤ የጎንደር ነገስታት መተማ ኬላ ከሚገቡ ነጋዴዎች፤ እንዲሁም ራሳቸው ተፈሪ መኮንን በሀረር ሰፊ ግብር ይሰበስቡ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የጎጃሙ ራስ ሀይሉ ገበሬውን በማስከፈል ብቻ ሳይሆን እቃ እያስመጣ እንዲገዙት ማስገደድ ደርሶ ነበር፡፡

የማዕከላዊ ንጉሶችም ከነዚህ ገዥዎች የሚጣለውን ግብር መሰብሰብ እስከቻሉ ድረስ የትና እንዴት እንደመጣ ጉዳያቸው አልነበረም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉት አፄ ዮሀንስና አፄ ምኒሊክ ግብር እስከተከፈላቸው ድረስ አንድን ገዥ ከስልጣኑ አያወርዱም፤ በሚፈፅመው ስራም ጣልቃ አይገቡም ነበር፡፡

የጅማው ንጉስ አባ ጅፋር ለአፄ ሚኒሊክና ጣይቱ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡ የሚያስገቡት ግብር የሚመጣው ግን በጅማ መስመር ከተቆጣጠሩት የጊቤ ወንዝን ተከትሎ የሚወጣውን ዋና የባሪያ ንግድ ነበር፡፡ ከዚ በፊት ሚኒሊክ የሸዋ ንጉስ ሆነው የዮሀንስ ገባሪ ነበሩ፡፡

የዘመናዊነት አስተሳሰብ ባለቤቱ ገብረሕይወት ባይከዳኝ የኢትዮጵያ ገንዘብ የሚኒሊክ የግል ገንዘብ ተደርጎ መቆጠር እንደሌለበት ንጉሱን ያሳስቡ ነበር፡፡ ስለዚህ ሰው ይከፍላል፡፡

ይህ ግብር አይደለም፡፡ ወደ ንጉሱ ወይም ፊውዳሉ ኪስ ገቢ ነው፡፡ ይህ ስርዓት ከቅኝ ግዛት ያለፈ ነው፤ ምክንቱም አንዱ የተሻለ ኢኮኖሚ ያለው ሌላውን የገዛበት ሁኔታ የለም፡፡ ባርነትም አይደለም፤ ባርነት ሰውን ያለ ክፍያ ማሰራት ብቻም አልነበረም፡፡ አንድ ሰው የሰራው፤ ያመረተው ብቻ ሳይሆን ሕይወቱም ሙሉ በሙሉ ለአካባቢው ፊውዳል የሆነበት የጨለማ ዘመን ነው፡፡

ይህ ቅድመ-መንግስትና ቅድመ-ዘመናዊነት የነገሰበት ዘመን ነው፡፡ ፊውዳሊዝም ማለት ይሄ ነው፡፡

አውሮፓ ከፊውዳሊዝም ወጥቶ ወደመንግስትነት ደረጃ መሸጋገር የቻለው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነው፡፡ ቴድሮስ ከዘመነ መሳፍነት ለማውጣት የሞከራት ኢትዮጵያ፤ ኃይለስላሴ እስኪነግሱ የተቀየረችው ነገር ቢኖር ፊውዳሎቹ ማዕከላዊ አዲስ አበባ ላይ ንጉስ ስላላቸው ብቻ ነው፡፡

በመንግስትነትና በስርዓት ደረጃ ካየነው ሌላ ምንም የተቀየረ ነገር አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ከሀይለ ስላሴ በፊት ምንም አይነት የመንግስት ስርዓት ስላልነበር የሀገሪቱ የመንግስት አሰራር ፍቅር እስከመቃብር ላይ እንዳለው ሁኔታ ነው፡፡

ስለዚህ የኃይለስላሴ መንግስት ያልመለሳቸውን ጥያቄዎችን ለማየት እንሞክር፡፡

ከዚህ ጋር ቀድሞ የሚነሳው የብሔረሰብ መብት ነው፡፡ የብሄር መብት የግለሰብ እኩልነት መብት ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ሁለት ሰዎችን በጎሳቸው ሳይመዘኑ እኩል ማየት ማለት ነው፡፡

በወቅቱ አንድ ሰው በህግ ፊት እኩል እንዲታይ፤ መብቶቹ በዘር በቋንቋ ሳይለይ በእኩልነት እንዲሰጥ በኢትዮጵያ የተረጋገጠ መብት ነበር፡፡ አንድ ሰው በቋንቋው አንዳይናገርና እንዳይፅፍ ግልፅ የህግ ገደብ በህግ የተጣለበት ሁኔታ እስከሌለ ድረስ የብሔረሰብ መብቱ ተከብሯል ማለት ነው፡፡

እኩልነት በብሄር ጥቅም ማግኘት ማለት አይደለም፡፡ ይህ መድሎ ነው፡፡

እንደ እድል አማርኛ ተናጋሪ ሆኖ አማርኛ የስራ ቋንቋ የሆነበት መስሪያ ቤት ባይቀጠር መስሪያ ቤቱ ህግ ነው፤ መብቱ አልተጣሰም፤ አመልካቹ ያጣው ጥቅም ነው፡፡ ጥቅም ማጣት እንዳለ ሁሉ ጥቅም ማግኘት ያለ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ መንግስት ከቻለ ጉዳቱን ለመካስ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህ ሲሆን ግን በብዛትና በትንሽ አይደለም፤ ለሁሉም ነው፡፡

ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ አልተማርኩም ማለት መብት አይደለም፡፡ ቋንቋን የማሳደግ፤ በቋንቋው ትምህርት ቀርፆ ማቅረብ የመንግስት ግዴታም አይደለም፡፡ መንግስት እስከቻለ ድረስ እንጅ ካልቻለ ከነጭራሹኑ ትምህርት በግል እንጅ በመንግስት ማቅረብም የማያስፈልግበት ሁኔታ ቢፈጠር፤ እንኳን በወቅቱ አሁንም መሰረታዊ የሚባል መብት ነው ለማለት ይከብዳል፡፡

የብሔረሰብ መብት በኢትዮጵያ አብዮት እንደዋና መደራጃ መንገድ እንጅ ዋና አጀንዳ ነበር ለማለት ከባድ ነው፡፡ ይህንን መብት አስፈላጊነት አምኖበት ለማስከበር የሚያስችልበትን ስርዓት ቀርፆ ይህን እውን ለማድረግ ተደራጅቶ የወጣ የፖለቲካ ቡድን በጊዜው የነበረው በኤርትራ አማፂዎች በኩል ብቻ ነበር፡፡

የኤርትራን አማፂዎችን ስናይ ያነገቡት የመገንጠል አጀንዳና የተደራጀ ሀይል እንደነበራቸው ስናይ ከጥያቄ የዘለለ ዋና አጀንዳ እንደነበር ማየት ይቻላል፡፡ በማንኛውም የፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ የተደራጀ ያልተደራጀን ይመራዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ምንም አይነት የተጠናከረ አደረጃጀት እንዳልነበረው ስንመለከት ከአጀንዳና አመራር ተመሳሳይነት ባለፈ በኤርትራ አማፅያን ከፍተኛ ጫና የነበረበት እንደነበር ብዙ አስረጅዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

በጥቅሉ የኢትዮጵያ የብሔረሰብ መብት አጀንዳ የኤርትራ መገንጠል አጀንዳ የወለደውና የኤርትራን መገንጠል እውን አድርጎ መጠጊያ አጥቶ የሚንከላወስ አደረጃጀት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከነጥላሁን ግዛው አስከነ አማን አንዶም፤ ከኢህአፓ እስከ ህወሓት፤ ስር የሰደደው የኤርትራ መገንጠል አደረጃጀት ሀገሪቱን ወደታች ደፍቆ ጉዞውን ከሀያ አመት በኋላ ሲያጠናቅቅ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ አራጊ ፈጣሪ ሆና ነበር፡፡

የመገንጠል አጀንዳ የወለደው የብሔር ፖለቲካችን አሁንም አለ፡፡ ይህ አደረጃጀት ከገዥውም ይሁን በተቃውሞ ፖለቲካው ዋና አሰላለፍ ነው፡፡ ህዝባዊ መሰረቱ ግን የበለጠ አጠያያቂ ሆኗል፤ ምክንያቱ አንድ ነው፡፡ አሁንም የጨዋታዉ ህግ አንድ ነው፡፡ የተደራጀ (ለጊዜውም ቢሆን) ያልተደራጀን ይገዛል፡፡

የዜጎችን መብት ያከበረች ዘመናዊት ኢትየጵያን ለመገንባት ያለው ሚና ምንድነው? አሁን ሊነሳ የሚችል ያልተመለሰ የሚባል የብሔረሰብ አጀንዳ አለን? ከብሔረሰብ መብት አጀንዳ ይልቅ የመሬት አጀንዳስ ምን ያህል መሰረት ነበረው? እንዴትስ ተመለሰ?  የኢትየጵያና የኤርትራ ግንኙነት በኢትዮጵያ የበላይነት እንዴት ተቀየረ? በምን መንገድስ መቀጠል አለበት?

ለነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ያለውን የድህረ አብዮት ዘመን ጉዞ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡ በሚቀጥለው ክፍል እመለስበታለሁ፡፡

ኢትየጵያ ለዘላለም ትኑር!

***********

 

Guest Author

more recommended stories