ኢ/ር ይልቃል:- የብሔር ብሔረሰብ መብት የሚባለው በጥራዝ ነጠቅ ያመጡት ነገር ነው

Highlights:

* ‹‹እኔን ብትጠይቀኝ የምወዳት ባንዲራና በልቤ ውስጥ የታተመችው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ምንም ምልክት የሌላት ናት።››

* ‹‹[ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ካለ] ያለምንም ጥርጥር የኢህአዴግን 99 ነጥብ 6 ሰማያዊ ይወስዳል ማለት ነው። ምክንያቱም ኢህአዴግ አሁን ምንም የሚደግፈው የኅብረተሰብ ክፍል የለም።››

* ‹‹ብሔር ብሔረሰብ የሚባለው እኮ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ሰለቸኝ።….የግለሰብ መብት ሲከበር አብሮት ያለው ማንነቱም ይከበራል።….ኢህአዴግ ለመከፋፈል የሚያደርገውን ፕሮፓጋንዳ እኛ አብረን አንደናገርም፣…..በጥራዝ ነጠቅ ያመጡት ነገር ስለሆነ። ጥራዝ ነጠቅነት ደግሞ ሀገር ያጠፋል ስለዚህ ለዛ ነው እንደዛ ያለውን ነገር የማንደባልቅ።››

* ‹‹አንድን አገርን ለመምራት የሚያስፈልገው ሃሳብ ነው። ያን ሃሳብ የሚያስፈጽም ደግሞ ድርጅት ነው። ያ ድርጅት ደግሞ ያለው የሕዝብ ተቀባይነት ነው። እነዚህ ሦስት ነገሮች በሰማያዊ ፓርቲ በኩል በሰፊው ተሟልተዋል።››

* ‹‹ፌዴራል ድሮም በባህላዊውና በጉልበቱም ዘመንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ አስተዳደር ነው።››

* ‹‹እኛ በቢሮ ቁጥር ላይ ተመስርተን አንሰራም። …..አብረው በሚሰሩ (contact groups) ነው እንጂ የምናምነው ቢሮ ከፍቶ እንደ ቢሮ ስራ ማድረጉ አንደኛ የቴክኖሎጂ ዘመን ነው፤ ጥቃትም አለ እዛ አካባቢ፣ቢሮ ማግኘቱም ለእኛ ችግር አለብን እውነቱን ለመናገር።››

* ‹‹ትንሽዋን ትችት መቻል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢህአዴግ ትንሽዋን ትችት። የአንድ ሰው ንግግር መንግስትን ያፈርሰዋል፤ ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥሬ ይወጣሉ ብሎ በከባድ ሽብርና ድንጋጤ ውስጥ ነው ያለው።››

——-

(ዳዊት በጋሻው)

ሰማያዊ ፓርቲ የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጀ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። በ2007 ዓ.ም በሚካሄደው አምስተኛው አገራዊ ምርጫም ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን በተመለከተ ከፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ጋር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡- በ2007 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል፤ ምን ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?

ኢንጅነር ይልቃል፡- በመጀመሪያ ስለ ምርጫ ምን ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው ስትለኝ እኔ ደግሞ ምርጫ አለ ወይ? ነው የምልህ። ምርጫ ማለት ከአንድ በላይ የሆኑ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሃሳቦችም ይሁኑ አመለካከቶች ቀርበው በእነዚያ ላይ በነፃነት ሕዝብ የመወሰን ሥልጣን ኖሮት የሚደረግ የሃሳብ ትግል ነው። ስለዚህ ያንን የሚያሳይ ነገር አሁን በኢትዮጵያ ደረጃ (ኮንቴክስት) አለወይ? ብትለኝ ለእኔ ያለ ጥርጥርና በሙሉ ልብ የለም ነው የምልህ። ስለዚህ ያ ስለሆነ ምርጫ በሌለበት ሁኔታ ስለ ምርጫ ማሰብ መሬት የለቀቀ ነው። እና ነባራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው የሚሆነው። እና በእኔ እምነት ምርጫ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ተስማምታችኋል። ቀደም ብሎ ግን አብራችሁ እንደማትሰሩ ነበር የተገለጸው እስኪ ስለነበረው ሁኔታ ይንገሩን። በጋራ ለመስራት የደረሳችሁባቸው ስምምነቶችስ ምንድንነው የሚመስሉት?

ኢንጅነር ይልቃል፡- አንደኛ ነገር ሁለት የተለያየ ሃሳብ የተፈጠረ ነገር የለም። ሰማያዊ ፓርቲ የወሰዳቸውን አቋሞችም ሆነ በተለያየ ጊዜ የተናገርኳቸውን ንግግሮች ብትወስድ አንዱም ቢሆን አብሮ ለመስራት አያስፈልግም፤ አብረን አንሰራም ያልንበት ጊዜ የለም። ከወትሮው የተለየ ምን ነገር አለን? ምን ተምረናል? የባለፈው እንዳይደገምና በየጊዜው እየወደቅን ሕዝብ አቅመ ቢስነትና ተስፋ መቁረጥ እንዲሰማው ከማድረግ ያለፈ ስህተቶች ሳይደገሙ የምንሄድበት የበፊቱን ድካም በዝርዝር አውቀን ወደፊት የምንራመድበት መሆን አለበት። ያለእዚያ ግን ዛሬ ተገናኙ፤ ነገ ፈረሱ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል እያልን ነው። እና እስከዛሬ ያልሰራውን ነገር አሁን ይሰራል ብለን ስንገባበት ሰማያዊ ፓርቲ ለረጅም ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ሲያደርግ ነበር እንጂ አብረን አንሰራም ወይም መተባበር አያስፈልግም የሚል አንድም ቦታ አቋም ወስደን አናውቅም፤ እርሱ ሊታወቅ ይገባል።

ለአሁን ግን ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) መኖር ላይ፣ የአገር ብሔራዊ ደህንነትን በተመለከተ አጠቃላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል። እዚህ ለመድረስ ለሦስት ወሮች ያህል መጀመሪያ እስካሁን የነበሩት ድክመቶች ምንድንናቸው? የሚለውን የዳሰሳ ጥናት አድርገን በዚያ ላይ ከተስማማን በኋላ ደግሞ ፓርቲዎቹ የራሳቸው ነፃነትና ፕሮግራም፣ ዓላማና የፓርቲዎች ሉዓላዊነት እንደተጠበቀ በጋራ ልናከናውናቸው የምንችላቸው ነገሮች ምንድንናቸው? የሚለውን ዘርዝረን አውጥተን ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈራርመን አሁን እንዲያውም የጋራ የድርጊት መርሐግብር ቀርጸን እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- «ከዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት የተስማሙት ምርጫ ስለደረሰ ነው» የሚሉ አሉ። ለዚህ ምን ምላሽ አለዎት?Blue party - Pres. Yilkal Getnet

ኢንጅነር ይልቃል፡- ጥሩ ምርጫ ስለደረሰ አብሮ መስራትም ጥሩ ነው። ምንም የሚያስነቅፍ ነገር አይደለም። ምርጫ ስለደረሰ አብረው ቢሰሩ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ እንዲሆን አብረው ቢሰሩ ነውር አይደለም። አለመታደል ሆነና የምርጫው ሁኔታ መልክ አልያዘም ተብሎ እንጂ እነዚህ ፓርቲዎች እኮ የተሰበሰቡት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተቋቁመው በሰላማዊ ሽግግር ሥልጣን እንይዛለን ብለው የተመሠረቱ ናቸው። በዚያ መልኩም እንኳን ቢገናኙ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስነቅፍ ነገር አይደለም።

ሌላው የግንኙነታችን ደረጃ ከዚያ ያለፈ ነው። አንደኛ ይኼ በአጭር ጊዜ ያልነው የምርጫ ዘመን በመሆኑ ይኼ ነፃነት ባለበትና ፓርቲዎች በነፃነት ተደራጅተው፤ ሚዲያው በነፃ ጽፎ መንግሥትም የሚያደርገውን እመቃና አፈና ትቶ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ኖረውበት ምርጫው የኢትዮጵያን ሕዝብ የዴሞክራሲ ፍላጎት የሚመጥን እንዲሆን በጋራ እንሰራለን። ከዚያ አልፎ ደግሞ ይኼ ያሰብነውን ነገር በሕዝብ ንቅናቄም ሆነ በመንግሥት ተደማጭነት አግኝቶ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተደረገ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበትንና ስትራቴጂካሊ ተቋሞች ተሰባስበው የጋራ ኃላፊነት የሚወጡበትን መንገድ እናስባለን። ስለዚህ ሁለቱን ያቀናጀ ነው። ሁለተኛ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ በሚሆንበት መንገድ ደግሞ ከዚያም በኋላ አገራዊ ኃላፊነት ለመሸከምና ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትንም ነገር አብረን እየሰራን ነው። እና ሁለቱም ተከታታይ ናቸው። አንዱ የአንዱ ደጋፊ እንጂ ብቻውን የሚቆም አይደለም ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይካሄዳል። እርስዎ ደግሞ መጀመሪያ አካባቢ ምርጫ አለ ብዬ አላምንም ብለዋል። እና ሰማያዊ በ2007 ዓ.ም በምርጫ ይሳተፋል?

ኢንጅነር ይልቃል፡- በመጀመሪያ የተቋቋምነው በምርጫ ለመሳተፍ ነው። ግን በምርጫ ለመሳተፍ ምርጫ የሚመስል ነገር መኖር አለበት ነው። ቢያንስ ትንሹን መስፈርት እንኳን የሚያሟላ መሆን አለበት። ያለዚያ ታሪክ ካነበብክ በጃንሆይ ጊዜም ምርጫ አለ፤ በደርግ ጊዜም ምርጫ አለ፤ በኢህአዴግም አራት ጊዜ አድርጎ አምስተኛው ነው የሚባለው መሰለኝ ምርጫ አለ፤ በእነዚህ ምርጫዎች ውስጥ ግን፤ ኢህአዴግ በጠመንጃ መጣ እስካሁን ይኖራል፤ ደርግ በጠመንጃ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ጠልፎ በሥልጣን ኖሯል። ጃንሆይም በቤተሰባዊ ትውልድ የሚመጣውን ሥርወ መንግሥት ይዘው ሥልጣን ላይ 50ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ኖረዋል። ስለዚህ ሁሉም የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የኢትዮጵያን ሕዝብ የአገሩ ባለቤትነት የሚያረጋግጡ አይደሉም። ጃንሆይም ለማስመሰል ነው ያደረጉት፤ ደርግም ለማስመሰል ነው ያደረገው፤ ኢህአዴግም በጠመንጃ መጥቶ በጠመንጃ የሚያደርገውን ነገር ለማድረግ ነው የሚያደርጉት። በሌላ አነጋገር «ምርጫ አያስፈልግም ማህበራዊ ፍትህ» ብላ ከምታምነው ኤርትራ የተለየ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ በመደረጉ የሥልጣንም ሆነ የሕዝብ የበላይነት የተረጋገጠበት መንገድ የለም። እና ያንን የሚያደርግ ምርጫ እስካለ ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው የተቋቋምነው፤ ፓርቲዎች የሕዝብ ተጠሪ ናቸው። ያ እንድሆን እንሰራለን። ያለዚያ ግን ያ ከሌለ መሳተፋችንም አለመሳተፋችንም ለውጥ ስለሌለው ጊዜም ገንዘብም ማባከን በኢትዮጵያ ሕዝብም ላይ መቀለድ አገራችንን ማታለል ስለሚሆንብን መጀመሪያ የምንሠራው ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲኖር እዚያ ላይ አትኩረን ነው የምንሰራው። ያ ካለ ያለምንም ጥርጥር የኢህአዴግን99 ነጥብ 6 ሰማያዊ ይወስዳል ማለት ነው። ምክንያቱም ኢህአዴግ አሁን ምንም የሚደግፈው የኅብረተሰብ ክፍል የለም።

አዲስ ዘመን፡- ይህንን ለማድረግ ምን ታደርጋላችሁ? የጀመራችሁትስ ነገር አለ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- እሱም አሁን በፓርቲዎች ትብብር 9 ፓርቲዎች የአንድ ወር መርሐ ግብር ቀርጸን ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚያመጡ ነገሮችን በሰፊው እየሰራን ነው። ሰፋፊ የአደባባይ ስብሰባዎች ሰልፎች አሉ። ምርጫን በተመለከተ አስተሳሰቡን ለማብቃት የፓናል ውይይቶች አሉ። በአጠቃላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሰላማዊ ሰልፍ አለ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሕዝቡ የአገሩም የሥልጣኑም የምርጫም ወሳኝ ሕዝቡ እንደሆነ ራሱን እንዲያውቅ የሚያደርጉ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። እነዚያ ነገሮች ደግሞ መልክ ከያዙ ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ የሚያሸንፍበትን የራሱን ዕቅድ ስትራቴጂ የአፈጻጸም መመሪያ የራሱ መዋቅር አለው። በሁለቱም በኩል ዝግጅቱ አለ። ግን ሁለተኛው ሊሆን የሚችለው አንደኛው እስከተሳካ ድረስ ነው። ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እስካለ ድረስ፣ ስለዚህ መጀመሪያ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ያስፈልጋል። ነፃነት ከሌለ የሕዝብ አስተዳደር ሊኖር አይችልም። ምርጫ የሚኖረው አማራጮች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ሽጠው የተሻለው ለአምስት ዓመት ኃላፊነት የሚረከብበት ነው። በአሁኑ ወቅት ያንን የሚፈቅድ ሁኔታ ከሌለ ግን መጀመሪያ ያ ሁኔታ የሚፈጠርበትን መስራት ስለሆነ ፓርቲዎች በትብብር እሱን በሰፊው እየሰራንበት ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያሏቸውን መመሪያዎች፣ መዋቅሮችና የመሳሰሉት መንግሥት ለመመስረትና አገር ለመምራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተሟልተዋል-እንደ ሰማያዊ ፓርቲ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- እሱ ምንም ጥያቄ የለውም። አንድን አገርን ለመምራት የሚያስፈልገው ሃሳብ ነው። ያን ሃሳብ የሚያስፈጽም ደግሞ ድርጅት ነው። ያ ድርጅት ደግሞ ያለው የሕዝብ ተቀባይነት ነው። እነዚህ ሦስት ነገሮች በሰማያዊ ፓርቲ በኩል በሰፊው ተሟልተዋል። ሃሳባችን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ አስተዳደሩን፤ሥ ነ ልቦናውንና የፖሊሲ ድክመቶችን የሚፈታ ዝርዝር ፕሮግራም አለን። ይህን ለማስፈጸም የሚችል ደግሞ ንቁና ወጣት አመራር፤ ትላልቅ ሰዎች አማካሪ አለን። እነዚህን ባደረግንበት ውስጥ ደግሞ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጥያቄዎች ዘንድና በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ ይሁንታን አግኝተናል። ስለዚህ ሦስት ነገሮች አብረው እስካሉ የጠራ ሃሳብ ያንን የሚያንቀሳቅስ ድርጅትና የሕዝብ መሠረታዊ ድጋፍ እስካሉ ድረስ እነዚህ ነገሮች ሲቀናጁ ነው መሪ መሆንና ኃላፊነት መሸከም የሚቻለው። ስለዚህ እነዚህ ሦስት ነገሮች ስላሉ ሃሳብን የማዳበር የማጠንከር የበለጠ ስር የመስደድ ነገር እየተሰራበት ነው። ያለ ጥርጥር ግን እንችላለን።

አዲስ ዘመን ፡- አሁን ወደ ሕዝብ የምትደርሱባቸው መንገዶች ምን ምን ናቸው?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ቅድም ያልኩህ እኮ እሱን ነው። ምርጫ ይኖራል ወይ? የሚል ጥያቄ ነው የሚነሳው። ምርጫ ለመኖር አማራጮች መኖር አለባቸው። እኛ አማራጫችንን ለሕዝብ የምናደርስበት መንገድ ከሌለ ትግሉ መጀመሪያ ያንን ዕድል የማግኘትና የነፃነት ትግሉን የማረጋገጥ ነው የሚሆነው። የአንተ አለቆች ለፕሮፓጋንዳ እንዲመች ከሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ነው እኛ ቢሮ የሚመጡት። እነርሱ 24 ሰዓት ሙሉ ያደነቁሩናል። በመንግሥት በጀት የራሳቸውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ በተማሪዎች ላይ እንጨት እንጨት የሚል ነገር ይላሉ። በሲቪል ሰርቪሱ ላይ ያንኑ ያደርጉታል፤ በፖሊሱ ላይ ያንኑ ያረጉታል፤ በከተማ ነዋሪው ላይ ያንኑ ያደርጉታል፤ እና የእኛን ሃሳብ ደግሞ እንዲሰማም እንዲያይም አይፈልጉም። አባሎቻችንን ሁሉ ያስራሉ። እየገቡ ቢሯችንን ይዘርፋሉ። ይኼ በሆነበት ሁኔታ ምርጫ የሚባለው ሃሳብ የለም። ስለዚህ መጀመሪያ ነፃነት የሚለውን ያደረግነው ለዚህ ነው። ግን ይህንን በየትኛው መንገዳችን የኢትዮጵያ ሕዝብ አኗኗሩ እርስ በእርስ የተገናኘ ነው። ሰዎች ከሰዎች በዝምድና፣ በጓደኝነት፣ በአገር ልጅነት ማህበራዊ ትስስሩ በጣም ጥብቅ ስለሆነ ይህንን የነፃነት ትግሉ ሕዝቡ እንዲደግፍና የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን በቻልነው መንገድ ሁሉ እንሰራለን። ግን አንዱ ነገር የኢትዮጵያ ሀብት ንብረት ሥልጣን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ አዲስ ዘመንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሆን ከኢህአዴግ እጅ እንዲወጣ ትግላችንን እንቀጥላለን።

አዲስ ዘመን ፡- ሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ መርጦት ስልጣን ላይ ቢወጣ የሚከተለው የፖለቲካ ስርዓት ምን ሊሆን ይችላል?

ኢንጅነር ይልቃል፡- በብዛት በሰፊው ማህበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች የመጀመሪያው ሆኖ የሚነሳው ኢትዮጵያ ያላት ትልቅ ሀብት ነዳጅ አይደለም፤ ወይም ሌላ ወርቅና የከበረ ማዕድን አይደለም፤ያላት ነገር የሰው ሃይል፣ መሬትና ውሃ ነው። ይህንን ነጻ ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ነጻ እንዲሆኑ የመጀመሪያው ምሶሶ የሆነው ነገር ማህበረሰብ እንዲበለጽግ እንዲያድግ ፤ወደፊት እንድያይ ካስፈለገ መሬት ትልቅ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አለው። 85 በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በገጠርና ከመሬት ጋር በተያያዘ ነው ህይወቱ የተቆራኘው። ስለዚህ ያንን ነጻ ማድረግ የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ንቅናቄም፣ የፖለቲካ ዕድገትም እንዲኖር ያስፈልጋል ብለን ስለምናምን የኢትዮጵያ ገበሬ የሚያርሰው መሬት የራሱ መሆን ያስፈልጋል ብለን እናምናለን። ድሮ የንጉሱ ጭሰኛ ነበረ፤ አሁን ደግሞ የኢህአዴግ ጭሰኛ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ገበሬ ነጻ ሆኖ የማምረት አቅሙ እንዲዳብር የመዋቅር ሽግግርም እንዲደረግ የመሬቱም የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በገበያ መር እንዲሆን ካስፈለገ የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬት ባለቤት መሆን አለበት ብለን እናምናለን።

በሁለተኛው ደረጃ ደግሞ የዕድገትና የልማት መሰረቱ መነሻውም መድረሻውም ሰው ነው። መሬት የሚለማው ሰውን ለማልማትና የሰውን ህይወት ለማቃናትና ዘመናዊ ለማድረግ፣ ለማቀላጠፍ፣ ህይወትን ቀላል ለማድረግ ነው። መጀመሪያ ስለዚህ የሰው ልጅ ነጻ መሆን አለበት፤ የማልማት አቅሙም ያለው በሱ ውስጥ ነው፣ የሚለማውም እሱ ነው፣የሚያለማውም እሱ ነው። ያ ከሆነ ደግሞ ዜጎች በራሳቸው ነጻ መሆን አለባቸው ብለን እናምናለን። ስለዚህ ይህ ከሆነ የግለሰብ ነጻነት ቅዲሚያ የሚሰጠው መብት ነው ብሎ ደግሞ በዚህ ምሶሶ ላይ ያምናል። ይኼ የግለሰብ ነጻነት ከተከበረ ኢህአዴግ የሚያደና ግርባቸው መብት ብሎ የሚላቸው ነሮች ሁሉ ተያይዘው ይከበራሉ። የግለሰብ መብት ሲከበር ቋንቋውም፣ ባህሉም፣ ሙያውም፣ ሌላውም ሌላውም ነገር አብሮ ይከበራል። ስለዚህ የግለሰብ መብት የሚቆመው መሬትን ላራሹ ይሰጣል ማለት ነው። በአጠቃላይ ከዛሬ 40 ዓመት ጀምሮ «መሬት ላራሹ» የሚባለው ነገር እስካሁን ድረስ ስላልተመለሰ አሁንም መሬት ላራሹ የሚለው መፈክር በዚህ ትውልድም ቀጥሏል ማለት ነው።

ከዛ በሦስተኛ ደረጃና በተደጋጋሚ የሚነሳው አካባቢዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት ነው። የፌዴራል አስተዳደር ወይም የህብረት መንግስት የሚባለው። ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ነው። ማህበራዊ አደረጃጀቱም ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል። ሀብቱም፣ የሰውም ባህሉም፤ ቋንቋውም ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ግምት ውስጥ ያስገባ የራስ አካባቢን የማስተዳደርና እነዛ ደግሞ የህብረት መንግስት (ፌዴራል መንግስት) የመመስረቱ ነገር በኢትዮጵያ ታሪክም የተለመደ ነው፤ የሸዋ ንጉስ፣ የትግራይ ንጉስ፣ የጅማው ንጉስ እየተባለ ከዛ በኋላ ደግሞ ንጉሰ ነገስት እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ የሚያስከብር በድሮው በባህላችን ንጉሰ ነገስት የንጉሶች ሁሉ የበላይ ነው። ፌዴራል ድሮም በባህላዊውና በጉልበቱም ዘመንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ አስተዳደር ነው። ስለዚህ ያ ግን መልክ ይዞ ዘመናዊ ሆኖ ለአስተዳደር ምቹ በሆነ ሁኔታ የህብረተሰቡን ስነ ልቦና ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ሀብትን ግምት ውስጥ ያስገባ ለአስተዳደር ምቹነት የመሳሰሉትን ግምት ውስጥ አስገብቶ በዚህ በቋንቋና በልዩነት ላይ ሳይመሰረት ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብቶ የአካባቢ አስተዳደርና አጠቃላይ ደግሞ የህብረት የፌዴራል መንግስት እንዲኖር እንሰራለን ማለት ነው።እንግዲህ እነዚህ እነዚህ አንኳር የፖሊሲ ምሶሶዎቻችን ናቸው ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡-የግለሰብ ነጻነት ላይ እናተኩ ራለን ብላችኋል፤ ታዲያ በግለሰብ መብት ላይ ካተኮራችሁ የብሔር ብሔረሰቦችን ሉዓላዊነትስ እንዴት ታስከብራላችሁ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ብሔር ብሔረሰብ የሚባለው እኮ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ሰለቸኝ። አሁንስ እውነቱን ለመናገር በዚህ ጉዳይ ላይ ለመናገር ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ሦስት ቃላት በአንድ ላይ ደርድሮ መናገር ብሔር ማነው? ብሔረሰብ ማነው? ህዝቦች ማናቸው? በኢትዮጵያ የህብረተሰብ አደረጃጀት ከብሔርና ብሔረሰብ ማን ይበልጣል? ከህዝቦችስ? ከህዝቦች ብሔሮች ናቸው የሚበልጡት? ወይስ ብሔረሰቦች? አንዱ ከአንዱ የሚለያቸው ምንድነው? በኢህአዴግ ህገ መንግስት የለም፤ በኢህአዴግ ፕሮግራምም ላይ የለም፤ በምንም ላይ የለም። የግለሰብ መብት ሲከበር አብሮት ያለው ማንነቱም ይከበራል። ስለዚህ አንድ ግለሰብ ላይ የሌለ ሌላ አይነት መብት የለም። እንግዲህ ሃይማኖትህ፣ ጾታህ፣ ወጣትነትህ፣ ቋንቋህ፣ ስራህ ይከበርልሃል። የቡድን መብቶች የሚባሉት እነዚህ አይደሉም? በቡድን ወጣቶች ከፈለጉ፣ በሃይማኖት ሰዎች ከፈለጉ በሙያ ማህበር ከፈለጉ፤እሱ እሱ ነው አይደል የቡድን መብት የሚባለው። ስለዚህ የግለሰብ ያልሆነው መብት አሁን ከነገርኩህ የትኛው ነው? ኢህአዴግ ለመከፋፈል የሚያደርገውን ፕሮፓጋንዳ እኛ አብረን አንደናገርም፣ለማደናገር በስልጣን ለመቆየት ሲጠቀሙበት እኛ ልናደናግር ሳይሆን ልንመራ ስለመጣን አንደናገርም። የእኛ ግልጽ ነው። ብትነግረኝ እኔም እመልሳለሁ። በጥራዝ ነጠቅ ያመጡት ነገር ስለሆነ። ጥራዝ ነጠቅነት ደግሞ ሀገር ያጠፋል ስለዚህ ለዛ ነው እንደዛ ያለውን ነገር የማንደባልቅ።

አዲስ ዘመን ፡- በቅርቡ በአሜሪካ ዋሽንግ ተን ዲሲ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ አሁን በስራ ላይ ያለውን ሰንደቅ አላማ አውርደው ሌላ ሰንደቅ አላማ ተሰቅሎ ነበር። በዛ ላይ ያላችሁ አቋም ምንድነው? አጠቃላይ በሰንደቅ አላማው ዙርያስ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ምን ልዩነቱ እኮ እነዛ የመናገር ነፃነት ስላላቸው ውጭ ሀገር የሚኖሩት እኛ ሀገር ደግሞ ያው ነፃነት ስለሌለ ብትናገር ትታሰራለህ። ያንን መብትህን የምትለማመድብት መንገድ የለህም፤ ጉልበተኛ ውስጥ ነው ያለኸው እንጅ እንደዛም ሆኖ እኛ ዘመዶች ነን፣ ያንድ ሀገር ሰዎች ነን፣ ስለ አንድ ሀገር ነው ምናወራው፤ ይሄን ያህል የተራራቀ አስተሳሰብ ይኖረናል ማለት አይደለም። ስለዚህ ይሄ የሚያሳይህ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ምርጫ በራሱ ፍቅር በራሱ አስተሳሰብ የገነባው አንድ ነገር እንደሌለና አገዛዝ እየመጣ በላዩ ላይ የሚጭንበት ነገር መኖሩን። ያነው መሰረታዊ ቅድም እንደነገርኩህ የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩና የስልጣን ባለቤት ይሁን ስልህ አንድ ጠብመንጃ የያዘ ጉልበተኛ በመጣ ቁጥር የፈለገውን የሚያደርግበት ሀገር ሳይሆን ህዝቡ ስልጣን ካለው ለአምስት አመት ስልጣን ይሰጥሃል ፤ ያንን ነገር ካላከናወንክ ካልቻላችሁ ለሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅት/ፓርቲዎች እሰጣለሁ ብሎ የሚልበት ነገር ከመጣ ይሄ መገለባበጡ በየጊዜው ባንዲራ መቀያየሩ ይሄኛው ነው ባንዲራ ያኛው ነው ባንዲራ በአዋጅ በህግ የሚባለው ነገር ሁሉ አይኖርም እና እነዚህ ሁሉ ማሳያ ምልክቶች ናቸው። ህዝብ የፈቀደውን የሚያደርግበት ህዝብ በአገዛዝ ሳይሆን በራሱ በህዝብ አስተዳደር የሚኖርበት ነፃ ማህበረሰብ ስንመሰርት እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ለማንም አዕምሮ ጥያቄ መሆን ያቆማሉ ማለት ነው። ችግሩ በዛ መልኩ ነው የሚፈታው እንጂ ይሄኛው ነው ባንዲራ ያኛው ነው እኔን ብትጠይቀኝ የምወዳት ባንዲራና በልቤ ውስጥ የታተመችው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ምንም ምልክት የሌላት ናት። ግን ኢህአዴግ ያንን ማለት አትችሉም ብሎ አዋጅ አውጥቷል፣ ይከላከላል፣ ያስራል፣ ይቀጣል። አንድ ጓደኛዬ በዛ ሁኔታ የተቀጣ አለ።

አዲስ ዘመን ፡-የነበረው ሁኔታስ አሁን ለምሳሌ በስራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ይሄነው ስለዚህ ይሄን አውርዳችሁ ያን ስቅሉም ስለዚህ ህገወጥነት ነው የሚባልም ነገር አለ። ከዚህ ጋር ተያይዞስ ምንድነው የምትሉት ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- አንተም ስትናገር ከራስህ አነጋገር ብትረዳው በስራ ላይ ያለው ባንዲራ ነው የምትለኝ በስራ ላይ ያለው ባንዲራ ማለት በስራ ላይ ያለው መንግስት እንደማለት ነው። ያንተንም ንግግር በጨዋነት ሳየው እሱ አይደለም እነዛ ሰዎች የሀገሩን ባንዲራ የሚቀይር ሌላ ሀገር ሰምተሃል። እንደዛ አይነት ነገር የለም። ሀገሬ ነው ባንዲራችንም የጋራችን ነው ካልን ኢህአዴግ ይሄ ነው ባንዲራ ነው የሚልህ። ያኛው ይሄ የኔ ባንዲራ አይደለም የሚሉበት ውዝግብ ለምን ተፈጠረ? ትልቁ ችግር ይህ ነው። ሌላው ቴክኒካሊቲ ውስጥ ዲፕሎማሲ ምኑ ለምን ባንዲራ ወረደ ለምን ተሰቀለ የሚለው የህግ እና የፕሮሲውጀር ጉዳይ ውስጥ እኔ ገብቼ አልዘባርቅም።

አዲስ ዘመን ፡-እርስዎም እኮ ብለውኛል በአዋጅ ነው የተቋቋመው?

ኢንጅነር ይልቃል፡- በአዋጅ ባንዲራን ምን አመጣው። በዚህ አገር ውስጥ የህዝብ ነው እንጂ በስራ ላይ የዋለው ስትለኝ በስራ ላይ የዋለውና በስራ ላይ ያልዋለ የሚባል ባንዲራ በመጀመርያ መኖር አልነበረበትም። እዚህ ሀገር ውስጥ ባንዲራ ጥያቄው አንዱ የሚያወርደው አንዱ የሚሰቅለው አንዱ ሰልፍ የሚያወጣበት አንዱ የሚቃወምበት መኖር አልነበረ በትም። ይህ ማለት ገዢዎች እየመጡ የራሳቸውን ፍላጎትና አስተሳሰብ ስለሚጭኑ ነው። ያ ሲያበቃ ይሄም ጥያቄ አብሮ ያበቃል። ሌላው ነገር ዝርዝር ነው አልኩህ እኮ። በዛ መከፋት ውስጥ የሚፈጠር ግጭት ነው። ባንዲራው እንዲህ ይደረጋል ወይ? ኤምባሲ የተከበረ ነወይ? እነዛ ሰዎች ዜጋ ናቸው ወይ? ለኔ ምንም ነገር አይደለም ቅርንጫፍ ነው ያለኝ፤ ለኔ ግን ግንዱ እሱ ነው። ዜጎች በባንዲራ እንኳን መግባባት የማይችሉባት ሀገር ላይ ነው ያለነው። ገና ያንን ደግሞ ለመፍታት የህዝብ አስተዳደር ዋናው ቁልፍ ነው እንጂ ለፕሮፓጋንዳ የሚደለቀው በዛ ውስጥ ያለው ኢህአዴግ ለማደብዘዝ እነዛኞቹ መብታችን ነው ብለው ያደረጉትን ለማድረግ በሚደረገው ውስጥ ያለውን የህግ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቼ ምንም ማለት አልፈልግም ጥያቄም አይደለም ለኔ።

አዲስ ዘመን ፡-አረንጓዴ ቢጫ ቀይና መሀል ላይ ሰማያዊ ኮከብ ያለውን ሰንደቅ ዓላማ ምን ብለን እንጥራው?

ኢንጅነር ይልቃል፡-የኢህአዴግ ነዋ። ኢህአዴግ ያመጣው ኢህአዴግ ያደረገው ምን ጥያቄ አለው። እንግዲህ ኢትዮጵያ ቆይታለች አይደል ይህ የመጣው በኢህአዴግ ነው፤ ምንም የሚያሻማ ነገር የለም። ኢህአዴግ አንተ ያልከው ብሄር ብሄረሰብ ህዝቦች የሚለውን ማደናገርያ አምጥቷል። ያ እኩልነት በሰማያዊ አርማ ነው የሚለው ከየት መጣ ብሄር ብሄረሰብና ሰማያዊ ኮኮብ ምን አገናኘው? በኢትዮጵያ ሁኔታ ኢህአዴግ እንደዛ ነው አለ። ኢህአዴግ እንደዛ አደረገ ህዝብ ሲወስን ደግሞ መቼ ምን እንደሚደረግ ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ ያንን ነው ያደረገው። በአዋጅ አድርጎ ኢህአዴግ በጠብመንጃ መጣ፤ የሚፈልገውን ህግ አወጣ፤ የሚፈልገውን ባንዲራ አደረገ። እሱ ነው እኔ የሚገባኝ ስለዚህ ህዝብ የመወሰን መብቱ ሲረጋገጥ ያኔ ኮከብ ያለበትን ያደርገዋል፤ያቺ ንፁኋ ባንዲራ ነች ካለ ያደርጋታል። ያ ወደፊት በህዝብ ሲወሰን ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሲሆን የሚደረግ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፡-ሽብርተኝነት የኢትዮጵያ ስጋት ነው ብለው ያምናሉ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ምን አሁን መንግስታዊ የሆነ ሽብር ነው ያለው እኛ ሀገር። እኛ ሀገር እውነት የሚጠይቁ ሰዎች፤ መንግስትን ክፉኛ የሚተቹ ሰዎች፤ ለማህበረሰቡ የቆሙ ሰዎች እና ለነፃነታቸው የሚታገሉ ሰዎች እና አዕምሯቸው ላይ ያለውን እውነት የሚናገሩ ሰዎች ሁሉ ሽብርተኛ ናቸው። ስለዚህ የሽብር ትርጉም ኢትዮጵያ ውስጥ ቅጥ ያጣ ነው። ቦንብ በሆዱ ታጥቆ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ላይ ያፈነዳ ሽብርተኛ ነው። እስክንድር ሽብርተኛ፣ ርዕዮት ሽብርተኛ፣ አንዱአለም ሽብርተኛ፣ ውብሸት ሽብርተኛ፣ እነ አቡበከር ሽብርተኛ፣ ብሎገሮቹ ወጣቶቹ ሽብርተኛ፣ የኛ የፓርቲው መሪዎች አሁን ቅርብ ግዜ የታሰሩት ጓደኞቻችን ሽብርተኛ፣ በሚቀጥለው ደግሞ እኔ ሽብርተኛ፤ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አንድም አልሻባብ የሚፈፅመውን አልቃይዳ የሚፈጽመውን አላደረጉም፤ ያደረጉት ምንድነው መንግስትን ክፉኛ ተችተዋል። የሚያምኑበትን ነገር ተናግረዋል። ሰብዕናቸውም ሆነ የግል ባህሪያቸው በብዙ ሰዎች ውስጥ የሚወደድና የሚከበሩ በህዝብ መሀል ስራቸውን እየሰሩ የነበሩ ሰዎች ከየቢሯቸው እና ከየቤታቸው እየተለቀሙ የሄዱ ሰዎች ናቸው። አንዳንዶቹ በስልክ ተደውሎ እየተነገራቸው የተያዙ ሰዎች ናቸው። እነዚህ እና የአለም አቀፍ የሽብርተኝነትን ስታወዳድር የኢትዮጵያ ሽብር ሌላ ነው። በአለም አቀፍ የሚደረገው ሽብር የሚባለው ነገር ስም ያለው ትርጉሙ ሌላ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር የሚባለው ለነፃነት የሚታገሉ ሰዎችን ነው። ምን አልባት ታውቅ እንደሆነ የነፃነት ታጋይና የአዲስዋ ዴሞክራቲክ ደቡብ አፍሪካ አባት የሚባሉት ማንዴላም ሽብርተኛ ነበሩ። ከዛ የነፃነት ትግሉ ተሳክቶ ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ ደግሞ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። አየኸው ስለዚህ አንተም እንግዲህ የመንግስት ጋዜጠኛ ስለሆንክ እሱን ሽብርተኛ እያልክ ትቆያለህ። ምንአልባት በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነት ሲመጣ እስር ቤት ያሉ ሰዎች አሁን የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ይሆኑ ይሆናል። እንግዲህ እኛ ሀገር ያለው የሽብር ትርጉም እሱ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ እየታየ የሚገኘውን፤ ተጠርጣሪ ብሎገሮች፣ ጋዜጠኞች የፖለቲካ መሪዎች ስራቸውን ሽፋን አድርገው በሽብር ሴራ በመገኘታቸው ነው ወደ ህግ የቀረቡት ብሏል። ይህን በተመለከተስ ምን የሚሉት ነገር አለ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- አንደኛ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አለ። ማንም ሰው ባሰበው በተናገረው አይከሰስም። ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ የማሰራጨት የመቀበል የሚል በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ውስጥ የተፃፈ ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው። የህግ ባለሙያ አይደለሁም ወንጀል የሚባል አንድ ነገር በቦታ በግዜ በድርጊት የሚገለፅ ነው እንጂ ሀሳብን መግለፅ በራሱ ወንጀል ነው የሚባልበት ነገር ከሆነ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይጋፋል ያ ትክክል አይደለም። ሁለተኛ በፍርድ ቤት የተያዘ ነገር የሚለውን በሆነ፤ ደረጃ አንድ ሰው እስካልተፈረደበት ድረስ ነፃ ሆኖ የመታየት ህገ መንግስታዊ መብትም አለው እና ይሄንንም የጣሰ ነው። በኢህአዴግ በኩል የተጠረጠሩና የተያዙ ሰዎች ተጠርጣሪ ነው የሚባሉት ስለምን ወንጀለኛ ናቸው ካልክ አስቀድመህ ፈርደህባቸዋል እንደማለት ነው። እና ያንንም እንደ ህግ አስተያየቱ ውሳኔ ከተሰጠበትም በኋላ ትክክል አይደለም ፤ ውሳኔው በአግባቡ አይደለም ብሎ መተቸትም መብት ነው። እና በሁሉም በኩል ይሄን የሚከለክል በእስር ላይ ያሉትን አሁን የኔ ጓደኞች ነፃ ናቸው ብዬ ነው የማምነው። ኢህአዴግ ወንጀለኛ ናቸው የሚላቸው የእመቃ የአፈና እና አጠቃላይ የነፃነት ትግሉን ለመገደብ የሚያደርገው ነገር እንጅ እነዚህ ሰዎች የምር ቅድም እንዳልኩህ የህዝብ አስተዳደር ሲመጣ ነፃነት ሲመጣ የምንሸልማቸውና በየመማሪያው የልጆች መጽሀፍቶቻችን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዳደር ለመመስረት ነጻ ማህበረሰብ የመመስረት ልዩ አስተዋጽኦ ያደረጉ እየተባሉ ብዙ ወጣቶችን ለማነሳሳትና ልጆች ስለ ሀገራቸው እንዲያውቁ የሚያስተምሩ ጀግኖች ሆነው እንደሚፃፉ አልጠራጠርም። እና እንደውም የምናደደው እነዚህን ሰዎች ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት ቀጥሎ ኦልደስት ስቴት ነው የሚባለው ትልቅ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በዚህ ዘመን ውስጥ ከኛ በኋላ የተነሱ ሀገሮች ስንት ወደ መራቀቅና ወደተለያየ ነገር ሲደርሱ ገና ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አስተዳደር ለመመስረት የተናገሩ ሰዎች የሚታገቱበት በመሆኑ ያሳፍረኛል። የህግ ጉዳይ ነው። አጥፊ ናቸው ተብሎ መናገር አይደለም ማሰብ ያናድደኛል እና በምንም አይነት ወንጀለኞች አይደሉም።

አዲስ ዘመን፡- የመንግስት መገናኛ ብዙሀን በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው፣ ወደ ህዝብ እየሄዱ አይደለም፣ የግል መገናኛ ብዙሀን እየተዘጉ ናቸው የሚልም አለ፣ መንግስት በቅርቡ አምስት መፅሔቶችንና አንድ ጋዜጣ አመፅን የሚቀሰቅሱ ጽሁፎችን ወደ ህዝብ በማድረስና በማተም በሚል ክስ መስርቷል። በዚህ ላይ ያላችሁ አጠቃላይ ሀሳብ ምንድነው በዛ ላይ ያላችሁ ጠቅላላ አስተያየት ምንድነው?

ኢንጅነር ይልቃል፡- እንደው ምንም የተለየ ነገር የለም። በዚህ ሁኔታ ለመናገር አቅም አጣለሁ። ምንድነው አዋጁን በጆሮ ሚባል አይነት ነገር ነው። ኢህአዴግም ያውቀዋል የኢትዮጵያ ህዝብም ያውቀዋል፤ እኛም እናውቀዋለን። በእውነት እኛ ይሄ የሚቀየርበት ነገር ላይ ነው በመስራት ትኩረት ማድረግ የምንፈልገው እንጂ ኢህአዴግ ፈሪ ነው። መንግስቱ ይሁንታ እያጣ በህዝብ ውስጥ ከግዜ ወደግዜ የነበረችው የጉልበትና የጠብመንጃ ነገር አልቃበታለች። ስለዚህ ምንም ነገር ትንሽዋን ትችት መቻል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢህአዴግ ትንሽዋን ትችት የአንድ ሰው ንግግርን መንግስትን ያፈርሰዋል። ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥሬ ይወጣሉ ብሎ በከባድ ሽብርና ድንጋጤ ውስጥ ነው ያለው። ያንን ለመቆጣጠር ሲል ግለሰቦችንም ትናንሽ ጋዜጦችንም አጠቃላይ አስተሳሰቦችን ለመቆጣጠር ብቻ የቆመና የህዝብ ይሁንታ ያጣ መንግስት መሆኑን ያሳየኛል። ስለዚህ እኔ አፈናውም ሆነ የሚድያ ጥበቱም በጣም እንደሚቀጥል አምናለው። እናንተም ቢሆን በዛች በድርጅት ሰርክል ውስጥ እንኳን ያለቻችሁን ነፃነት ከግዜ ወደ ግዜ በግምገማ እየጠበበች እየጠበበች እንደምትመጣ ነፃነቱ እስከሚመጣ ድረስ የበለጠ እየቀነሰ የበለጠ እያነሰ እያነሰ እንደሚሄድ አልጠራጠርም። መፍትሄው መታገል ነው። መታገል፣ መተባበር፣ እውነትን መስበክ ፣ እውነትን መናገር፣ ለእውነት የሚያስከፍለውን ዋጋ መክፈል ተከታታይ ትግል ማድረግ ፣ እልህ አስጨራሽ የሆነውን ከጉልበተኛ ጋር ከባለስልጣን ጋር ከባለ ጠብመንጃ ጋር የሚደረገውን ትግል በወኔ በሞራል በሀገር ወዳድነት ጠንክሮ መያዝና የእውነትን አሸናፊነት አምኖ እኛም እንኳን ባንደርስ ለሚቀጥለው ትውልድ በቅብብሎሽ ማስቀጠል ነው። ሌላ ምንም አማራጭ የለም።

አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ ተቋማት ኢትዮጵያ እያደገች ነው ይላሉ። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ዲያስፖራዎች ደግሞ ኢትዮጵያ እያደገች ነው የሚለው ትክክል አይደለም ይላሉ። የነዚህ ሀሳቦች ማስታረቂያ ምንድ ነው ይላሉ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ለዚህ ማስታረቂያው አንደኛ ነፃ የሆኑ ባለሙያዎች ስለሙያው የሚናገሩበት ክፍት የሆነ የሙያ ነፃነት ያለበት ሀገር ያስፈልጋል። ነፃ የሆነ ሚድያ ያስፈልጋል። ነፃ የሆነ ህዝብ ያስፈልጋል። እነዚህ ሶስት ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ አገዛዝ ሌላውን ህዝብ ቀጥ ብለህ እንደ ጉንዳን በዚህ ሂድ በሚልበት ነገር እውነቱ የቱ ጋር እንዳለ ማወቅ አትችልም። ዳታዎች ሁሉ የተጋገሩና በየግዜው ባለሙያዎቹ ነፃ ስላደሉ ለምሳሌ የአንድን የግብርና እና የማዕከላዊ ስታስቲክስ ሪፖርቶች ብታይ ሁለቱም የተለያዩ ናቸው። ማዕከላዊ ስታስቲክስ የሚያመጣው ስለሀገር እድገት ሌላ ነው፤ የግብርና ሚኒስቴር የሚመጣው ዳታ ሌላ ነው። በሁለቱ መስሪያ ቤቶች መካከል ያለው የሙያ ነፃነት ይለያል ማለት ነው? እታች ገጠር ላይ ያለው ልማት ጣቢያ ሠራተኛ ወረዳ ላይ ያለውን ባለሙያ ይፈራል። ስለዚህ ስራውን እንዳያጣ ሪፖርቱን ጨመር አርጎ ይልክለታል። ወረዳ ላይ ያለው ባለሙያ የወረዳው ባለስልጣን እንዳይቆጣው ይጨምራል። የወረዳው ባለስልጣን ደግሞ በግምገማ የዞን ካቢኔ እንዳያባርረው ጨመር ያደርግበታል። የዞን ካቢኔው ደግሞ የክልሉ እንዳይቆጣው ያን ያደርጋል።

የክልሉ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ክልሎችም ነፃነት ስለሌላቸው ያንን ሪፖርት ያቀርባል። በመጨረሻ የውሸት ክምር ይሆናል ማለት ነው። ባለሙያው ነፃ ሲሆን። ማህበረሰቡ ነፃ ሲሆን። ፖለቲከኛው ነፃ ሲሆን የኢህአዴግ አባላት ራሱ እኮ ነጻ አይደሉም። የሚገቡትም አምነውበት ሳይሆን ለጥቅማቸው ኑሯቸውን ለማሻሻል ቤተሰባቸውን ለማሸነፍ ነው። ያን እንዳያጡ ኢህአዴግ የሚፈልገውን በበለጠ የካድሬያዊ ቋንቋው መናገር ነው። ስለዚህ በዚህ ሂደት ውስጥ የተገኘ ዳታ (መረጃ) እውነተኛ ነው ብለህ መውሰድ አትችልም። ነጻ አይደለም። ነጻ ተቋም፣ ነጻ ማህበረሰብ፣ነ ጻ ባለሙያ የለም እና ይህንን ዳታ እንደ እውነት መውሰድ አይቻልም። የማይጠረጠርው ነገር ኢትዮጵያ አሁን ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ባላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና በብዙ ምክንያቶች እርዳታና ብድር በሰፊው ያገኛል። ይኼ መንግስት ሌሎቹ ያላገኙትን ። ያንን ደግሞ ለተንዛዛ ቢሮክራሲውና ለሚታይ ነገር ለማድረግ ትላልቅ ህንጻዎች ተገንብተዋል፤ መንገዶች አሉ፤ የሚያብለጨልጭ ነገር አለ። ከዛ የሚጠቀሙት እነማን ናቸው? የዛ ሀብት ባለቤቶች እነማን ናቸው ያልከኝ እንደሆነ የሚታወቅ ነው ወደ ዝርዝሩ ባንገባ። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አሁን ባለው ትንሽ ሰዎች በከበሩበት ሁኔታ በተፈጠረው ቅጥ ያጣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፍዳውን የሚያይ ማህበረሰብ ነው ያለው። መንግስት ሰራተኛው፣ ጡረተኛው፣ ዝቅተኛ ነጋዴው ፣ እነዚህ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ገበሬው ብትል እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ የሚኖርባት አገር ነች። ጥቂት ሰዎች በበለጸጉበት ሁኔታ ጥቂት ሰዎችን ደግሞ በዓለም ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም እንደው በዓለም ትልልቅ ሀብታሞች የሚኖሩትን አይነት ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እና አጠቃለይ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይህንን ይመስላል።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የሚሰሩ መንገዶች፣ ህንጻዎች፣ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ግድቦችን በተመለከተስ ያላችሁ አቋም ምንድነው?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ግድቡና መንገዱ ዓላማው መጨረሻ ላይ ምን ለማድረግ ነው? ያንተን ህይወት፣ የኔን ህይወት የእሱን ህይወት (በቃለምልልሱ ወቅት ኢንጅነር ይልቃልን ጨመሮ እኔና አንድ ሌላ ሰው ነበርን) ለማሻሻል ነው? ግድብ በራሱ ምን ያደርጋል? ግድብ ያንተን ህይወት ለማቃለል፣ አስተሳሰብን ለማበልጸግ ፤ ለወደፊቱ መሻሻል ብሩህ ነገር ለማምጣት ነው፤ መንገዱ ጌጥ አይደለም። ያ ነገር ተቀላጥፎ ልማት እንዲመጣ፣ በዛ ፍጥነት ሰዎች ተገናኝተው ህይወታቸውንና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ፣ የመፍጠር አቅማቸው እንዲዳብር ኑሯቸው ቀለል እንዲል ማድረግ ነው። ይኼ መንገድ በመሰራቱ የትራንስፖርት ችግር ተቃሏል? ይኼ መንገድ በመሰራቱ የኢትዮጵያ ተራ ዜጎች ህይወት ተለውጧል? ህይወታቸው ተቀላጥፏል? ህይወት ምቹ ሆኗል? ተስፋ እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል? አገራቸውን እንዲወዱ አድርጓል? እሱ ነው ዋናው እንጅ መንገድ በመሰራቱ መንገድ እኮ መሰረተ ልማት ነው የሚባለው። በመሰረቱ የሰው ልጅ ለመብላት እንደ አገልጋይ ነገሮች ናቸው። እነዚህ በራሳቸው ልማት አይደሉም። እና ያን ስታየው መንገድ መሰራቱ ጥሩ ነው፣ ግድብ መሰራቱ ጥሩ ነው። ግን ያ ለሰው በሚጠቅም ሁኔታና የሰውን ልጅ መሰረታዊ ህይወት በመለወጥ እና ኑሮን በማሻሻል ላይ ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል? በዛ ደረጃ ስታየው በጣም ገና ገና ብዙ የተበላሸ ነገር አለ። ለፕሮፖጋንዳና እድገት አለ ለመባል የሚደረጉ ለታይታ የሚደረጉ ለእርዳታ የሚደረጉ፣ ለፕሮፖጋንዳ የሚደረጉ፣ በስልጣን ለመቆየት የሚደረጉ እንጅ የምር የህዝቡን መሰረታዊ ህይወት የሚለውጡና በፈረንጆች አነጋገር የእያንዳንዱን ቤት ማዕድ ቤትና የምግብ ጠረጴዛ (ኪችን ቴብል) ችግሮች የፈቱ አይደሉም። እነዚህ አይነት ቁጥሮች እና አንድ አይነት የተበላሸና የተጣመመ ነገር አለ በፖሊሲው ላይ ።

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ አሁን በትኩረት የሚሰራቸው መንግስት ለመሆን የሚያወዳድሩትና የሚያደርሱት፤ ህዝቡ እንዲያምነው የሚያደርጉት ዋና ዋና ጉዳዮች ምን ምን ናቸው? ወደ ህዝቡ የምታደ ርሷቸው? በጣም በትኩረት የምትሰሯቸው ስራዎች?

ኢንጅነር ይልቃል፡- የመጀመሪያው ነገር ሰው በልቶ እንዲያድር ማድረግ። ሰው ነው የእኛ መነሻችንም መድረሻችንም፤ ዜጋ፣ ሰው፣ ከሰው በላይ ሁሉም ነገር ማደናገሪያ ነው። በዚህ ተባለ በዚያ ተባለ አገር ተባለ ሉዓላዊነት ተባለ፣ ልማት ተባለ፣ መነሻውም መድረሻውም የኢትዮጵያ ዜጎች ህይወት መሻሻል ነው። በየትኛውም መንገድ ይገለጽ የነዚህን ሰዎች ህይወት ለማሻሻል ምን አይነት አስተዳደር ትከተላለህ? ፖለቲካ፣ ምን አይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትከታለለህ? ምን አይነት አማራጭ አስተሳሰቦች የሚዳብሩበት የመገናኛ ብዙሃን (ሚዲያ) ፖሊሲ አለህ? የሚሉት ነገሮች ሁሉ ይህንን መሰረታዊውና የሰው ልጅ ህይወት ማቅለል የሰውን ልጅ የፈጠራ ችሎታ ማዳበር፤ ሰውን ልጅ የወደፊት ተስፋ የሚያለመልሙ ነገሮች ለማድረግ፤ሰው የሁሉም ነገሮች መነሻና መድረሻ ነውና የሰውን ልጅ በእያንዳነዱ ቀን ውስጥ በጭንቀት እየኖረ ምንድነው መንገድ? ኢኮኖሚ ዕድገት እዚህ ደረሰ፣ መንገድ ይኼ ተገነባ፣ ምንትስ ሜጋ ዋት ተፈጠረ የሚባለው ለእኔ ምንም አያደርግልኝም ። መነሻየም መድረሻየም አንተ ሰው ነው። እሱ ላይ ነው የምናተኩረው።

አዲስ ዘመን ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ቢሮዎች አላችሁ? ከተማ አቀፍ ናችሁ ይባላል። በዚህስ ላይ ያላችሁ አስታየየት?

ኢንጅነር ይልቃል፡- በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምስራቅም፣ በምዕራብም የሰማያዊ አመራሮችን ታገኛለህ። ፓርቲያችን ከተማ አቀፍ አይደለም። እኛ በቢሮ ቁጥር ላይ ተመስርተን አንሰራም። ከዚህ በፊት የሚደረገው በማዕከል ደረጃ የተወሰነ ገንዘብ ይሰበሰባል። ወይም ደግሞ ትንሽ ደጋፊዎች ውጭ አገርም ያሉ አገር ውስጥም ያሉ ያን ፓርቲ አስተሳሰቡን የሚደግፉ ብር ይልካሉ። ያ ብር እንደ ስራ ድርሻ ሆኖ ለተለያዩ ነገሮች ይውል ነበር። እኛ ግን እንደዛ አናደርግም። ፕሮግራም፣ ደንብ ይላክላቸዋል። ስልጠና ይሰጣቸዋል። ራሳቸው የአባላት መመዝገቢያ ቅጽ ይላክላቸዋል። ደረሰኝ ይላክላቸዋል። እዛ አካባቢ ያሉ አባላት በዛ መሰረት እያደጉ የአባላት ቁጥር እየጨመረ ቢሮ መክፈት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ደግፉንና አቋቁሙን ሲሉን በዛ ደረጃ ይደረጋል። አብረው በሚሰሩ (contact groups) ነው እንጂ የምናምነው ቢሮ ከፍቶ እንደ ቢሮ ስራ ማድረጉ አንደኛ የቴክኖሎጂ ዘመን ነው፤ ጥቃትም አለ እዛ አካባቢ ፣ቢሮ ማግኘቱም ለእኛ ችግር አለብን እውነቱን ለመናገር። ቢሮ ያለበት አለ ለምሳሌ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ማርቆስ፣ አሉ። ግን ቢሮ መክፈቱ እንዳውም እንደ ጥገኝነትና እንደ ስራ ድርሻ ይሆንና ያችን ቢሮ የተቆጣጠራት ሰው ሌላ የተሻለ አባል ሲመጣ የተሻለ ሆኖ አላገኘነውም።

ለምሳሌ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጅግጅጋ አካባቢ ግንኙነት ጀምረናል። በጣም ያልገባንበት አካባቢ ቢኖር እሱ አካባቢ ነበረ እንጅ በሁሉም ኢትዮጵያ ዋና ዋና በምትላቸው ከተሞች እንደ ደብረ ማርቆስ፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ አሰላ፣ ኢሊባቡር፣ ጅማ ፣ ሼካ፣ እነዚህ ቦታዎች ላይ ከ25 በላይ ሰዎች እየተደራጁ አብረው በሚሰሩ (contact groups) አባላቸውን እያሰፉ ሄደዋል። ቢሮ ብትል እንዳው ስፔስፊክ ባልሆንም ጎጃም አካባቢ ምዕራብም ምስራቅም ወደ 34 ወረዳዎች አሉ። አዊን ጨምሮ በዛ ደረጃ ወረዳም መድረስ ችለናል። የጁቤ የሚባል ወረዳ አለ። እዛ አካባቢ ስትሄድ ደግሞ ገጠር ድረስ፣ ገበሬ ማህበር ድረስ ቢሮ ከፍተዋል። በአጭር አነጋገር ሰማያዊ ፓርቲ የከተማ ፓርቲ አይደለም። የመዋቅር መሰረቱ ከሱማሌ ክልል በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያ ጋር አለ። አንዳንዶቹ ላይ በዞንና በወረዳ ደረጃ አለ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ በዞን ደረጃ ሁኖ ወደ ታች የሚሰሩ አሉ። አርባ ምንጭ ቅድም ያልጠቀስኩልህ ቢሮ አለ፣ ሀዋሳ ላይ፣ ሀዲያ ላይ ቢሮ አለ። በትክክል ቢሮ የከፈቱ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በቁጥር ቢገለጽ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- እኔ ቁጥሩን በትክክል ስለማላውቀው ነው እውነቱን ለመናገር። ሁለተኛ እዛ ላይ መንጠልጠል አልፈልግም። የእናንተ ሰዎች ችግራችሁ የምትፈልጉለትን አንግል ስለምትመርጡ በዛ ደረጃ የሰማያዊን ገጽታ እንድታበላሹብኝ አልፈልግም። አንባቢ ስለሚረዳው ለምሳሌ አንተ ኢህአዴግ 5 ሚሊዮን አባል አለኝ ይላል። በመላ አገሪቱ የመንግስትንም መዋቅር ተጠቅሟል ከዛ ደግሞ አንተ ትነሳና ሰማያዊ ቢሮ ያለው እዚህ እዚህ ቦታ ነው ትለዋለህ ስትሰራ ማለት ነው። አንባቢህ አሁን ኢህአዴግንና ሰማያዊን በዚህ ደረጃ ማየት ይጀምራል ማለት ነው። ያ የተሳሳተ አመለካከት ይፈጥራል ማለት ነው። ሰማያዊ ደግሞ ቢሮ መክፈት አስፈላጊነቱ አንደኛ ታች ያሉ አባላት ቢሮ የማግኘት ስራ ብዙም አናገኝም። በነገራችን ላይ በስንት መከራ ነው አዲስ አበባ ያለውን ቢሮ ያገኘነው። ከሱማሌ ክልል በስተቀር ሁሉም ቦታ መክፈት እንችላለን። አባላት አሉ፤ ሪፖርቶች ይደርሱናል። በሁሉም ቦታዎች የግንኙነት ቡድን (contact groups) አሉን። ግን ቢሮ የማንከፍትባቸው ያለመድረሳችን ችግር ሳይሆን የአስተዳደር ችግሮች፣ የኢህአዴግ ጫና ነው። እኛ ደግሞ የነበረው ባህል ስራ የማድረግ ይህንን የፓርቲ ቢሮን መጠቀም እንደ ጥቅም ስለተቆጠረ ነው። ስለዚህ የቢሮ ቁጥር ትክክለኛውን የሰማያዊን ነገር ስለማይናገር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ በሚያካሂዳቸው ሰልፎች ተሳታፊዎች ከሚያሳዩት ስነ ምግባር አንጻርና ከአክራሪነትና ሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ስሙ እየተነሳ ነበር። አሁንስ ምን የተለየ ነገር አለ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- እንደሱ አይነት ነገር ኢህአዴግ ለፕሮፖጋንዳ ብሎ ሊናገር ይችላል እንደ ፓርቲ እኛን ለማጣጣል ሲፈልግ። ይታመንም አይታመንም በፕሮፖጋንዳ ማሽኑ የሚለውን ነገር ሊል ይችላል። ግን በዛ ደረጃ በአቋም ደረጃ ተፈርጀንም አናቅም። የኢትዮጵያ መንግስት የአማጺ ሃይላትን በፓርላማ የፈረጃቸው አሉ። አሱ የጠቀሳቸው። ሰማያዊ አዛ ውስጥ የለበትም። ስለዚህ አሸባሪም አክራሪም ብለህ መናገር አትችልም፤ አንተም ብትሆን የሚባል ነገር የለም። ሁለተኛ ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ ደረጃ ያለው ይዘት የተለየ ነው። ሰልፎቻችንን በሙሉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቦ ሰልፉ በሰላም ተጠናቋል እያለ ነው፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉትን ሰልፎች የግንቦት 25ቱን ጨምሮ ሰልፉ ፖሊስም ባደረገው ጥበቃና በነበረው ነገር በሰላማዊ መንገድ ተጠናቆ ተበትኗል ነው ያለው። ከዛ በኋላ የመጣም ነገር የለም፤ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከፍርሃታቸው አንጻር የተለያየ ነገር ተናግረዋል ። እሱን እኛ እንደ ቁም ነገር አንቆጥረውም። መደናገጣቸውን መፍራታቸውን፣ አባሎቻቸው እንዳይሸሹባቸው ለዛ የሚሆን ፕሮፖጋንዳ መስጠታቸውን እናውቃለን።

አንድ ፓርቲ ስብሰባም ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግ ሲል ለአዲስ አበባ መስተዳድር ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ያሳውቃል። ይህም የጥበቃና ደህንነት አገልግሎት ከመንግስት እንዲያገኝ ነው። ግብር ከፋይ በመሆናችን ስንወጣ ለዚህ ዓላማ ነው የምንወጣው፣ ይህን ያህል ሰው እናሳትፋልን፣ ከዚህ ሰዓት እስከዚህ ሰዓት እናደርጋለን፣ ቦታው ይኼነው ብለን እንናገራለን። ከዛ ውጭ የሚኖር ነገር ካለ ጠብቁን ህጋዊ ፓርቲዎች ነን ጥበቃ እድርጉልን። በዛ ሰልፍ ላይ ጸብ ቢነሳ እኔ አይደለሁም የምጠየቀው፣ ፖሊስ ነው። ነግሬህ ነበር እኮ የእኔ ሰልፍ ዓላማ ይህ ነው፣ የወጣሁት ለዚህ ነው፣ ከዚህ ውጭ የሆነ ነገር ስታይ ጠብቀኝ ብየህ ነበር። ችግር ካለ የሚጠየቀው ሰማያዊ አይደለም። ማዘጋጃ ነው፤ አንተ የምትጠይቀው አሁን የአዲስ አበባ ፖሊስን ወይም ፌዴራል ፖሊስን ሰማያዊ ሰልፍ ጠርቶ ህጋዊ እንድታውቁት ተነግሯችሁ፣ ጥበቃ እየፈለገ እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር ለምን አልነበርክም ብሎ እሱን ነው ሚጠየቀው።

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ጠርቶ በሰልፉ ላይ የሚሰግዱ አሉ፣ በዚህ ዙሪያ ምን የሚሉት አለ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ኢህአዴግ ስብሰባ ሲጠራ የሶላት ሰዓት ሲደርስ ሙስሊሞች አይሰግዱም? የሶላት ሰዓት ደረሰ ተብሎ እኮ ስብሰባ ይበተናል እኮ ኢህአዴግ ላይ። አላጋጠመህም? እኔ አፋር ሰርቻለሁ እንደዛ ይደረጋል። እና ያ ሃይማኖታዊ መብታቸው ነው። ኢህአዴግ ዋናው ታገልኩለት የሚለው ለሃይማኖት ነጻነት ነው አይደለም? ስለዚህ ሃይማኖቱ በሚያዘው ሰዓት የስራ ሰዓት እንኳን እያቋረጡ 5 ሰዓት ተኩል አርብ የሚዘጋው ኦፊሻሊ የሶላት ሰዓት ስለሆነ ለሙስሊሞች ነው። ያን ሰዓት ለሙስሊሞች አገልግሎት እንዲያደርጉ ለማድረግ ነው። እና ያ መብታቸውም ነው። ይገባልም፤ ህጋዊም ነው። የመረጃ ክፍተት ነው ይህንንም የሚጠይቁ ሰዎች ካሉ ካለማወቅ የሚመነጭ ነገር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ሃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባል ጭምጭምታ አለ። እስኪ ጥርት ያለ ነገር ይንገሩን?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ነገርኩህ እኮ ኢህአዴግ ያሰረውን ሰው ሁሉ ወንጀለኛ ነው እያለ ነው። እንኳን እኔና አንተ አሁን እኔ አሸባሪ ብሆን እኔ ቢሮ መጥተህ ፣ጋዜጠኛ ሆነህ፣ የመንግስት መኪና አስፈቅደህ እኔ ደግሞ ቢሮ ከፍቼ እንዴት እንኖራለን? ለምን እንኖራለን? ጥያቄውን በጥያቄ ነው የምመልስልህ። አንድ አሸባሪ ድርጅት እንዴት አዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ይንቀሳቀሳል አሸባሪ ከሆነ ? መዘጋት አለበት። እንደዚህ ይባላል ተብሎ ነገር የለም። አሸባሪ ማለት እኮ ቦንብ በሆዱ ታጥቆ የሚያፈነዳ ማለት ነው። ግን ኢህአዴግ ስለሚፈራን የተለያየ የሚያወራውን ወሬ እንደቁም ነገር አንቆጥረውም። ስለሚፈራን ነው። ኢህአዴግ ማሰር ሲፈልግ ሰማያዊ ፓርቲን ስለፈራሁት፣ የሰማያዊ ወጣቶችን ስለፈራኋቸው አሰርኳቸው አይልህም። የሚነግርህ በሁዋላ አጀንዳ እየተጋሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይላል።

አዲስ ዘመን ፡- ይህ ታዲያ እውነት ነው ውሸት?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ውሸት ነው። ማንዴላም ሽብርተኛ ነበሩ፣ ማንኛውም አገዛዝ ተቀናቃኞቹን የተለያየ ስም እየሰጠ ይፈርጃል፤ ያስራል፤ በስልጣን ለመቆየት ስለሚፈልግ። ያ የሚከፈል መስዋዕትነት ካለና የሀሰት ክስም ካለ ትግሉ የሚጠይቀው ነገር ነው። ብዙ ጊዜ በየትኛውም ዓለም ስታያቸው የነጻነት ታጋዮች በአገር ክህደት፣ በዘር ማጥፋት፣ በሽብር፣ በመንግስት ግልበጣ፣ የሚከሰሱ ናቸው። ያያ ታሪካቸው እውነት ሲሆን ደግሞ የሰላምና የነጻነት ታጋይ እየተባሉ በልጆች መማሪያ መጽሃፍት ውስጥ ሁሉ እየተጻፉ የነዛ ሰዎች ታሪክ ለልጆች ስነ ልቡና መቀረጽና ለጀግንነት ምሳሌና የእውነተኝነት አባት ይባላሉ። እና ይኼ የአንድ ሰሞን ፕሮፖጋንዳ ጩኸት እንጅ መሰረት የያዘ ነገር አይደለም። ምናልባትም እኔም አሸባሪ ተብዬ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቃሊቲ ታገኘኝ ይሆናል። ግን ደግሞ ነገሮች ሲገለበጡ ጀግናችን ነህ እያላችሁ ልትጽፉልን ትችላላችሁ። ለምሳሌ እስክንድር አሸባሪ ተብሎ 18 ዓመት ተፈርዶበት ታስሯል፤ ለእኔ ግን በጣም የማከብረውና የምወደው ልጅ ነው። እውነተኛ ልጅ ነው፤ እንኳን ሽብር ቀርቶ የሰውን ስሜት መንካት የማይወድ በጣም ጥንቁቅና የሚሰራውን የሚያውቅ ሰው ነው። ርዕዮት፣ አንዱአለም እንደዛው ናቸው። እኔ እንዳውም በቅርበት የማውቃቸውን ነው። ይኼ የኢህአዴግ ፍርሀትና ድንጋጤ ካልሆነ በስተቀር መሰረት የለውም።

አዲስ ዘመን ፡-በመጨረሻ መናገር የሚፈልጉት ነገር ካለ?

ኢንጅነር ይልቃል፡- ለገዥዎቻችንና ለኢህአደግ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር በማታለልና በማደናገር ብዙ ርቀት መሄድ አይቻልም። በተቻለ መጠን እነርሱም የልጅነትና የጨዋታ ዕድሜያቸውን እነርሱ በሚያምኑበት እኛ በማናምንበት ብዙ ርቀት ሄደው አይተውታል። ያ ግን ገደብ አለው የምንም ነገር፤ ስልጣኔም ይሁን፣ መንግስትም ይሁን ፣ የሰው ልጅም ቢሆን ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል፣ ይሞታል፤ ስለዚህ እንኳን ስልጣናቸው እነርሱም ይሄዳሉ። ይህንን ካመኑ የአንድ ዘመን ስልጣኔ ፣ የአንድ ዘመን አስተሳሰብ ሁሉ ነገሩ አላፊና በራሱ ተፈጥሯዊ ሂደቱን (natural process) ጨርሶ የሚያልፍ ነገር ስለሆነ ይኼ በእልህ፣ ራስን በማታለል፣ በጀብደኝነት፣ በፕሮፖጋንዳ እውነታን መሸሸግ አይቻልም። ይኼንን አምነው ሌላ እይታ አለን የሚሉ የኢትዮጵያ ልጆችን ሁሉ አክብረው ለዛ የሚሰሩ ሰዎችን ሁሉ ለአገራቸው እንደሚሰሩ አውቀው ለዛም ዕድል ሰጥተው ካልሆነ በስተቀር እነርሱ የሚሉትን 100 በመቶ ብናምንላቸው እና አምነን ብንነሳ እንኳን የኢትዮጵያ ችግር በጣም ሰፊና የተደራረበ ረጅም ጊዜ የፈጀ የተከማቸ ችግር ነው። ይኼን ችግር ለመፍታት ደግሞ እንደዚሁ ኢትዮጵያ ያላትን ሁሉ ሀብት መጠቀም አለባት። የሰው ሃይሉም፤ ሚዲያውም አጠቃላይ በብሔራዊ ክብርና በአንድነት ተነሳስቶ ካልተሰራ በስተቀር ኢህአዴግ በሚለው በራሱ ቋንቋ የቁጥ ቁጥና በካድሬ ፕሮፖጋንዳና እነርሱ በያዙት መንገድ ብቻ አሳክተናል የሚሉት እንኳን እውነት ቢሆን በስልጣን መቆየቱም ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ መስጠትም አይችሉም። እና አሳታፊነትና ክፍትነትን ትንሽ ለቀቅ ማለትም እየመረራቸውም ቢሆን እንዲማሩት ጥሪየን አስተላልፋለሁ።

*********************

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን (በ4 ክፍሎች)- ታህሳስ 22፣ 23፣ 24-2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories