የብሔር ብሔረሰቦች ቀን፣ ዋለልኝ መኮንንና የከሸፈው ፕሮጀክት

(በፍቃዱ ወ/ገብርኤል)

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ዘጠነኛ አመቱን የያዘ ሲሆን በአገረ አሜሪካም ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሎምበስ ኦሃዮ ይከበራል።Wallelign Mekonnen - Struggle magazine 1969

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ ለዘመናት ተጨቁነውና ተመዝብረው፤ ተንቀውና ተገልለው በሁለተኛና ሶስተኛ የዜግነት ደረጃ ይታዩ የነበሩትን ብሄር ብሄረሰቦች መብትና ነጻነት ያረጋገጠውን የፌደራል ስርአት ለመዘከርና አጽናኦት ለመስጠት ሲሆን በዚህም በአል ብሄር ብሄረሰቦች በተወካዮቻቸው አማካይነት ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትና ከሌሎች የሚተዋወቁበት፤ ልምዳቸውንና አገራዊ ጉዳዮችን የሚወያዩበት፤ የጋራ እምነታቸውንና ተስፋቸውን የሚጋሩበት የአንድነታቸው የደስታ መግለጫ መድረክ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ስርአት የህዝቦችን እኩልነት ያረጋገጠና ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት ለአገሪቱ አንድነት ሰላም መረጋጋትና እድገት መሰረት የጣለ አዲስ ግኝት ነው። ይህ ህያውና አዳጊ ተመንዳጊ የሆነ የአንድነት መሰረት ዛሬ ኢትዮጵያ በጽናት እንድትቆም ያስቻላት ብቻ ሳይሆን በምታደርገው ፈጣንና ሁለገብ የዕድገት ጎዳና ጉዞ ከምትራመድበት ሁለት እግሮችዋ መካከል የመጀመሪያው ነው። እንደሚታወቀው ሁለተኛው ደግሞ የምትመራበት የልማታዊ መንግስት መርሃ ግብር ነው።

የብሄር ብሄረሰብች ቀን ሲታሰብና ሲዘከር የዛሬዋ ኢትዮጵያ የመንፈስና የነፍስ አባት (Founding Father) ከሆነው ከታጋዩ ከመለስ ዜናዊ ጋር ስሙ ሳይጠቅስ የማይታለፈው ዋልልኝ መኮንን ነው።

የብሄር ብሄረሰቦች የመብትና የእኩልነትን ጥያቄ በአደባባይ በማስተጋባት የአደባባይ ምስጢርንቱ ተገፎ በኢትዮጵያ የፖሊቲካ መድረክ የመሃል መስመር ስፍራ (main stream politics) እንድሆን ካበቁት ስመ-ጥር የመላው ኢትዮጵያ ህዝቦች ልጆች መሃል ዋለልኝ መኮንን አንዱ ነው።

ዋለልኝ መኮንንን የተለየ ቦታ እንዲሰጠው የሚያደረገው የንጉሱን ስርአት ጸረ-ህዝብነትና በህዝቦች ላይ የተጫነውን ‘fake’ የ”ኢትዮጵያዊንትን” ጭንብል በዛ በጭለማ ዘመን በሰላ ብዕሩ በአደባባይ ማራቆቱ ብቻ ሳይሆን የስራቱ ገዥ መደብ መሰረት ከሆነው ብሄር የወጣ በመሆኑ የብሄር ብሄረሰቦችን የነጻነት ጥያቄና ትግል የተጨቆኑ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ህዝቦች ጥያቄን ትግል እንዲሆን ማስቻሉ ነበር። ዋለልኝ መኮንን የአጼውን ስርአት በግንባር በመፋለሙና ለተገፉ ህዝቦች ጥብቅና በመቆሙ ውድ ህይወቱን በመስዋትነት የከፈለ ከብርቅዬና ድንቅዬ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች መሀከል አንዱ ነበር።

በ1991 ደርግን የጣለው ለውጥ የደርግ ስርአትን ብቻ ሳይሆን ያስወገደው የትናንትናዋ ኢትዮጵያ የቆመችበትን መሰረት ጭምር የለውጠ ነው።

“ … The overthrow of the military in 1991 amounted to more than the collapse of a particular regime, It effectively marked the failure of a project, dating back to Menilik’s accession in 1889 of creating a ‘modern’ and centralized state around a Showan core” (Peter Woodward & Murray Forsyth, 1994, 37)

የከሸፈው ፕሮጀክት

ኢምፓየሮች በብረትና በእሳት ተቀጥቅጠው ከተቀረጹ በህላ ተጠብቀው እንዲዘልቁ ለማድረግ ከሚመረጡት መንገዶች አንዱ የተሸናፊውን የቋንቋ፤ የባህል፤ የእምነትና የራስ ማንነት ከውስጡ ማጥፋትና በምትኩ የገዥውን መደብ እሴቶችና ማንነት ማሰርጽ assimilate ማድረግ ነው። የቅርቡ የኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው።

እስከ 1991 ድረስ የነበረችውን በአንድ ብሄር ቅኝት የተቃኘችው ኢትዮጵያ የተቆርቆረችው የሸዋ ኤክስቴንሽን በመሆን ሲሆን የአጼ ምኒሊክ ዋና ግብና አላማ የሸዋን ስረው መንግስት በማስፋፋትና በማጠናከር የአልጋ ተቀናቀኞቻቸው የሃይል ሚዛን ማዳከም ነበር። ለዚህም ነው ሸዋን ማዕከል ያደረገ ጠንካራና ዘመናዊ መንግስት ማቋቋም ዋናው ግባቸው የሆነው። ዛሬ እንደሚጻፍላቸውና እንደሚተረክላቸው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ህዝቦችን ለማሰባሰብ ያደረጉት ቅዱስ ጦርነት አልነበረም። እዚህ ላይ ሳይጠቅስ የማይታለፈው በደቡብ በምስራቅና በምዕራብ ግዛት ሲያሰፉ የስሜኑን የኢትዮጵያ ታሪካዊ የባህር በር መሬቶች ሆን ብለው ለጣሊያን አስልፈው የሰጡበት ዋናው ምክንያት ነው።

“ምንሊክ ኤርትራን ችላ ብሎ ከአድዋ የተመለሰበት ምሰረታዊ ምክንያት፤ የሸዋንና ክዚህ ግዛት የበቀለውን ስርወ መንግስት ጥቅም ከመላዋ ኢትዮጵያ መንግስታዊ ጥቅም በላይ አድርጎ በማየቱ ነው። ዳግማዊ ምኒሊክ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና የተጫወተ ቢሆንም ይህን ዕውነታ አይለውጠውም” ይላል የእነ አንድርዜይ የታሪክ ድርሳን። (አንድርዜይ ባርትኒስኮ፤ ዮአና ማንቴል የኢትዮጵያ ታሪክ ገጽ 355-356)

የምኒሊክ ፕሮጀክት ወራሽ የሆነው የሃይለስላሴም መንግስትም ሆነ ወታደራዊው መንግስት የኢምፓየሩን ጣራና ግድግዳ ለማደስና ለማሻሻል ቢሞክሩምና አዲስ ቅብ ቢሰጡትም የተቀመጡበት ቤት መሰረት በአሸዋ ላይ የተሰራ ነበርና ከውድቀት ሊያድነትም ሆነ እነሱንም ሊያድናቸውም አልቻለም።

ከጽንሱ ብዝሃነትን ማስተናገድ የማይችል ስርአት ህብረ ብሄር በሆነች አገር የማይታሰብ ነበርና ለማያባራ የህዝቦች ትግልና አመጽ በር ከፈተ። የምኒሊክ ፕሮጀክት አዲስ ኢምፓየርና አዲስ አገር ቢፈጥርም የፈጠረውን አገር መልሶ የሚያፈነዳና የሚበትን የጊዜ ቦንብ ነበረበት።

የህዝቦችን መብትና ነጻነት አላማቸው አድርገው በየግዜው የሚከሰቱ ግብታዊና የተደራጁ ህዝባዊ አመጾች የአገሪቱን አንድነት መሰረት ደካማነትንና በተደጋጋሚ ሲያጋልጡና ሲፈታተኑ ቆይተዋል። በኦጋዴን የሶማሌ ህዝብ ትግል፤ በደቡብ በየጊዜው ቦግ እልም የሚለው መነሳሳት፤ የባሌ ኦሮሞዎችና የጎጃም ገበሬዎች አመጽ፤ የመጀመሪያውና ሁለተኛው የወያኔ ንቅናቄ …ወዘተ ለናሙና የሚጠቀሱ ናቸው።

የትናንት ኢትዮጵያ የቆመችበት የምኒሊክ የእሳትና አመድ መሰረት መቀየር ነበረበት። ወደ አንድ ወገን ባዘነበለ መሰረት ላይ ላይ የቆመ ቤት ጊዜው ይቆይ ይርዝም እንጂ መናዱ አይቀርምና ጊዜውን ጠብቆ ተናደ። ከኢምፓየሩ ልደት ጀምሮ ለረዥም አመታት በዘለቀው የመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የተባበረ ትግል ለአንድ ዘመን የቆየው የአማራይዜሽን ፕሮጀክት በ1991 ግብአት መሬቱ ተጠናቀቀ።

የህዝቦችን መብትና ነጻነት የሚያከብር፤ የህዝቦችን እኩልነትን የሚያበስር በህዝቦች መፈቃቀድና ስምምነት ላይ የተመሰረተ ህገ-መንግስት በማጽደቅ አዲሲቱ ኢትዮጵያ ህልውናዋ የሚቆምበትን አዲስ የመሰረት ድንጋይ ጣለች።

ከሁለት አስርተ አመታት በህላ እነሆ አዲስቱ ኢትዮጵያ ፡ – ከምንም ግዜ በላይ ጠንካራ አንድነት ያላት ፤ በእኩልነትና በፍቅር የተሳሰሩ ህዝቦች የሚተጉባት፤ ገስጋሽ ኢኮኖሚ የምትደውር፤ ከራሷ አልፋ ለአካባቢውና ለአህጉሩ የሰላም ዋስትና በመሆን በዓለም መድረክ ተደማጭነቷ የጎላ አገር ሆና ትገኛለች።

ይህም ሆኖ ፌደራል ስርአቱ ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር እያደገና እየጎለመሰ የሚሄድ ህያው ሂደት እንደመሆኑ ለማሻሻያዎችንና ማከያዎችን ክፍት በመሆን እይተንገዋለለና እየነጠረ የሚወጣ ይሆናል።

የብሄር ብሄረስቦችም ቀን በዓልም ሲከበር ፌደራል ስርአቱ ያስገኝውን ፍሬዎች የምንዘክርበት ፤ ለዚህ ድል የወድቁ ሰማዕታትን የምናስታውስበትና መጭውንም የምንመትርበት የሚሆነውም ለዚህ ነው።

********

* The author Befekadu Wolde Gabriel is  a graduate student (MPA master of public administration) at Franklin University, Coulombs, Ohio. He is a guest writer on Horn Affairs.and can be reached at [email protected].

Published by Befekadu Wolde Gabriel

Befekadu Wolde Gabriel - Ph.D. in agriculture, B.Sc in Sociology and graduate student (MPA master of public administration) at Franklin University - Ohio, and can be reached at [email protected]