ያልተመጣጠነው “ተመጣጣኝ ፖሊሲ” እና መዘዙ

ኢህኣዴግ ከደርግ ውድቀት ማግስት በኣንድ በኩል የሚገነባው የኣገር መከላከያ ሰራዊት የሁሉም ብሄር ተዋጽኦ ያካተተ ለማድረግ ከነበረው መርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ እምነት በመነሳት ከትጥቅ ትግሉ ይዞት የገባውን በጦር የሰለጠነ እና በስነልቦና የታነፀ ሰራዊት ካለምንም ካሣ እና ጡረታ ወደየቤቱ ሲያሰናብት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዛት ያለው ሰራዊት ኣገሪቱ የመሸከም ኣቅም የላትም በሚል እሳቤ እጅግ ኣነስተኛ እና ለዚህ ትልቅ ኣገር የማይመጥን ሰራዊት ተይዞ እንድንቀጥል መደረጉ የሚታወስ ነው።

ሆኖም ፊታችን ወደ ልማት ኣጀንዳ በዞርንበት ጊዜ “ኤርትራ የግላችን ኢትዮጵያ የጋራችን” ብሎ ኣገራችንን ሲዘርፍ የቆየውን የሻዕቢያ መንግስት የግዛት ወረራ ፈጽሞብን ያልታሰበ የሂወት፣ የንብረት፣ የልማት እና የጊዜ መስዋእት እንድንከፍል ተገድደናል። ይህ በዚህ ሳያበቃ ሁልቱም ኣገሮች ሰላም እና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ወድቀው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የድንበር ነዋሪ ህዝቦች መቋጫ ወደ የሌለው የፀጥታ ስጋት ውስጥ እንዲገቡ ከመገደዳቸውም በተጨማሪ የኤርትራ መንግስት እየገነባው ከነበረው ጨቅላ የመነግስትነት ባህሪ ወጥቶ ራሱን ወደ ተራ ኣሸባሪ ቡዱን በመቀየር ኢትዮጵያን የማተራመስ እንቅስቃሴ ሳያቋርጥ በተለያዩ መንገዶች እንደገፋበት ይታወቃል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ባላት ጠንካራ የጸረ ሽብር ተቋም ምክንያት ከኤርትራ የተቃጣው የሽብር ሙከራዎች በኣብዛኞቹ ሊከሽፉ ቢችሉም መንግስት በኤርትራ እና ኤርትራዊያን (የሻዕቢያ ተላላኪዎቹ) ያለው የተለሳለሰ እና ብዙ ርቀት የማይጓዝ (short-sighted) ፖሊሲ ኣሁንም ለኣገሪቱ የጸጥታ ስጋት መባባስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ እየቀጠለ እንዳለ ብዙ ወገኖች ይገልፃሉ።

ከኣሁን ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት ይዞት የቆየው በርን ዘግቶ የማዳከም እና ከፍ ሲልም የተመጣጣኝ ቅጣት ፖሊሲ ግልፅ በማድረግ፣ እንዲሁም ከኤርትራ እጅግ የተሻለ የሚባል ኣለም ኣቀፍ ግኑኝነት በመገንባትና የበለጠ ተሰሚነት ኣግኝቶ ኤርትራን ለጥፋቷ ተጠያቂ በማድረገ ረገድ ትርጉም ያለው ስራ ተሰርቷል። ይህ ፖሊሲ እና ኣካሄድ ከባድመው ጦርነት በኋላ የነበሩት የተወሰኑ ኣመታት ኤርትራ ጥፋት የመፈጸም ኣቅሟን በማዳከም ውጤታማ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ኣመታት ጀምሮ ግን የኤርትራ መንግስት በተለያዩ መንገዶች የዲፕሎማሲያዊ እና የገንዘብ ኣቅሙን ሊገነባ በመቻሉ በዚህ ወቅት ከራሱ ኣልፎ የቀጠናውን ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ የመቀየር ኣቅም ፈጥሮ ይገኛል።

እንደሚታወቀው የመን ላይ የተለኮሰውን የውስጥና የውክልና ጦርነት እንደ እድል ተጠቅሞ ባህርን እና ኣየር ማረፊያ ለኣረብ ኣገሮች ወታደራዊ እንቅስቃሴ በማከራየት፣ በጦር መሳሪያ ድለላ እና ኣስተላላፊነት፣ የቢሻ ወርቅ መኣድን፣ የሻዕቢያ ንብረት የሆነውን የቀይ ባህር የንግድ ድርጅቶች ወደ የተለያዩ የኣፍሪካ ኣገሮችን በመላክ (ኢትዮጵያም ውስጥ ኣሉ ይባላል) የንግድ ስራ በማስፋፋት፣ ከኣውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ኣለም ኣቀፍ ተቋማት የገንዘብ እርዳታ በመቀበል ውስጣዊ ሁኔታውን ባይቀይርም የኣፍሪካን ቀንድ በተለይም ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ የመፍጠር ኣቅሙ በእጅጉ ከፍ ብሎ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከኣሁን ቀደም ኤርትራን ለቀው ከመውጣት በተጨማሪ ጀርባቸው ሰጥተውት የነበሩትን የምእራቡን ኣለም ኣገሮች (ለምሳሌ ኣሜሪካና እንግላንድ) ወደ ኣስመራ ተመልሰው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ እንደሆኑ እየተገለጸ  ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ ኣዲስ ክስተት በገንዘብም ሆነ በዲፕሎማሲ በኩል ተጨማሪ ኣቅም እንደሚፈጥርለት ኣጠያያቂ ኣይደለም።

ኣንዳንድ ምንጮች እንደሚገልጹትም በተባበሩት መንግስታት የተበየኑበት የተለያዩ ማእቀቦች በዚህ ወቅት ተገቢነታቸው ኣጠያያቂ እየሆነ ያለበት ሁኔታ ላይ በመደረሱ የማእቀቡ ቀጣይነት ጥያቄ ሊነሳበት እንደሚችል ኣንዳንድ ተንታኞች ይገልፃሉ። ለነገሩ የኤርትራ መንግስት ከኣረብ መንግስታት ጋር እያደረገው ያለውን ወታድራዊ እንቅስቃሴ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ማእቀቡን የሚጥስ መሆኑን ይታወቃል። ይህ ደግሞ የኤርትራ መንግስት ላይ ማእቀብ እንዲበየንበት ሙሉ ድጋፋቸውን የሰጡ እንደ ኣሜሪካ እና ሌሎች የምእራቡ ኣለም ኣገሮችም ያውቁታል ብቻ ሳይሆን ኣረቦቹ እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴም የጦር መሳሪያ ሽያጭን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች እጃቸው እንደሚያስገቡ ይታወቃል።

በመሆኑም ለኣስራ ሰባት ኣመታት ተይዞ የቆየውን የማዳከም (attirition) እና ተመጣጣኝ ፖሊሲ ኣሁን ካለው የኤርትራ መንግስት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲተያይ የማይመጣጠን፣ የማይሰራ እና ጭራሽ ኢትዮጵያን የሚያስጠቃ ፖሊሲ ሆኖ እናገኘዋለን።

የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ የያዘውን ፖሊሲ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያልሰራለት እንደሆነ በመገንዘብ ኣዲስና የሚሰራ ፖሊሲ በመቅረጽ የነበረውን ኣመቺ ሁኔታ ሊጠቀምበት እየቻለ የኤርትራ መንግስት እስኪያንሰራራ ድረስ በመቆየቱ ፖሊሲው ኢትዮጵያን እስኪጎዳ ድረስ የቆየበት ሁኔታ ነው ያለው። ኣሁን በቀጠናው ያለውን ሁኔታ እጅግ የተለየ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ያሻውን የማድረግ ዕድል የለውም ብቻ ሳይሆን የሚያወጣው ኣዲስ ፖሊሲም በቀጠናው የተከሰተውን ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ ከግምት ያስገባ መሆን ይኖርበታል።

እሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰላም እና ጦርነት በሌለበት በቀጠልንበት ሁኔታ የትግራይ ክልል ህዝብ ዋነኛ ተጠቂ ሆኖ ላለፉት 17 ኣመታት ኣስቸጋሪ በሆነ የፀጥታ ችግር ውስጥ እየኖረ ይገኛል። ይህ ድንበር እየጠበቀ ኣገራዊ ሃላፊነቱን (ኣገራዊ ሃላፊነት የሚለውን ይሰመረበት) እየተወጣ የሚኖር ህዝብ በፌደራል መንግስት ሊደረግለት የሚገባ የልማት ኣማራጭ ወይም ማካካሻ ኣንዳችም ባለመኖሩ በኣስቻጋሪ የፀጥታ ሁኔታ ላይ እንደሚኖር ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ከጦርነቱ በፊት ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ ላይ የነበሩት የድንበር ከተሞች እና የገጠር መንደሮች ዛሬ ጭር ብለው ምንም ኣይነት የልማት፣ የምጣኔ ሃብት እና የስራ እንቅስቃሴ ስለሌላቸው ህዝቡ በተለይም ድግሞ ወጣቱ ተስፋውን ተሟጦ መጀመሪያ ወደ ሌላ ከተሞች በመጉረፍ ቀጥሎም ኣደገኛ በሆነ ሁኔታ በህርን ተሻግሮ እየተሰደደ እንዳለ የሚታወቅ ነው።

የክልሉ መንግስት እና በኣገሪቱ ሉኣላዊ ስልጣን ባለው ምክርቤት (ፓርላማ) ውስጥ በየኣምስት ኣመቱ እየተመረጡ የሚገቡ 38 ወንበር ላይ የተቀመጡ የህዝብ ወኪሎችም የዚህ ፖሊሲ ውድቀት እና የህዝቡን ሰለባነት ለምክርቤቱም ሆነ በኣጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማሳወቅ ስራ ባለመስራታቸው የችግሩ ጥልቀት ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል። ኣሁንም ሁኔታውን ለመቀየር የተደርገ ነገር የለም። የኢዮጵያ መንግስት ሁኔታውን በግዜ በመረዳት ኣስፈላጊ የፖሊሲ ለውጥ ባለማድረጉ በፍጥነት እየተቀያየረ ላለው የምስራቅ ኣፍሪካ ሁኔታን የሚመጥን ፖሊሲ በማውጣት ረገድ ገና ምንም ኣልሰራም ብቻ ሳይሆን እስካ ኣሁን ተመኩሮ በወደቀው ፖሊሲ ላይ ተንጠልጥሎ እየቀጠለ ይገኛል።

ይህንን የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ክፍተት የተገነዘበ የኤርትራ መንግስትም ተነጥሎ ከቆየበት የኣለም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን በማሻሻል ከነበረበት ማጥ ወጥቶ በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ኣገሮች ስጋት ለመሆን በቅቷል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ከ17 ኣመት በፊት ለነበረችውን ኤርትራ ሳይሆን ኣሁን ላለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚመጥን ፖሊሲ በመቀየስ የተሻለ ስራ ሊሰራ የግድ ይላል። ኣዲሱ ፖሊሲ ኣገሪቱ ከተደቀኑባት የውስጥና የውጭ ተደራራቢ ፈተናዎች ሊታደጋት ካልቻለ የተጀመረውን ኣጠቃላይ የልማት ጉዞ ለተጨማሪ ፈተናዎች ተጋላጭ ከመሆነ ኣልፎ ወደ ኋላ የማይጎተትበት ምክንያት ኣይኖርም። ይህ እንዳይሆን ተጠንቶ በሚወጣው ኣዲስ ፖሊሲ በፊት የተፈጸሙ ስህተቶች የማይደግምና በዘላቂነት ችግር ፈቺ እንዲሆን የጠበቃል።

**********

ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ ኣብ ሃገራዊን ዞባዊን ከምኡውን ዓለም ለኻዊ ፖለቲካ ጉዳያት ዝከታተል፣ ኣብዝኾነ ፖለቲካዊ ውዳበ ዘይነጥፍ ውልቀ ሰብ እዩ። ንሃናፃይ ሪኢቶ ኣብ [email protected]

more recommended stories