(ፃድቃን ገ/ትንሳኤ – ሌተናል ጄኔራል)

መግቢያ

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ በኤርትራ ላይ ሲከተለው የነበረውን ፖሊሲ እንደሚለውጥ አሳውቋል፡፡ እስካሁን ድረስ የነበረው የኤርትራን መንግሥት ከዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ነጥሎ የማዳከም አቅጣጫን መሠረት ያደረገ ፖሊሲን እንደገና ማየት መፈለጉ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡

ከዚህ ጋር የተያያዘ በሚመስል ሁኔታ ከአንድ ወር ተኩል ገደማ እስካሁን ድረስ ባለው የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የውይይት መድረክ በሸራተን ሆቴል ተዘጋጅቶ፣ እኔም ተጋብዤ በስብሰባው ተሳትፌያለሁ፡፡ በመቀጠልም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለዓመታት ይከተለው ከነበረው አቅጣጫ ወጣ ብሎ ቃለ መጠይቅ አድርጎልኝ ለአንባብያን አብቅቶታል፡፡ እነዚሁ በፖለቲካውና በአገር ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ለመወያየትና እንደገና ፖሊሲውን ለማየት የታዩት ፍላጎቶች፣ ትክክለኛና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሊበረታቱ የሚገቡ ዕርምጃዎች ናቸው እላለሁ፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ከመውጣቱ በፊት ማለት ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ማውጣትና የአገራዊ ደኅንነታችን አስተዳደር ከነበረው በበለጠና በተደራጀ መንገድ መሥራት ይገባል የሚል ሐሳብ የነበረ ቢሆንም፣ በተግባር ግን የወጣ ፖሊሲም የተሻሻለ አስተዳደርም አልነበረም፡፡ የሚነሱ የአገራዊ ደኅንነት ጉዳዮችም ለጊዜው ይዋቀሩ በነበሩ ኮሚቴዎች ነበር የሚታዩት፡፡

ለምሳሌ የሱዳን ጉዳይ፣ የሶማሊያ ጉዳይ በጊዜያዊ ኮሚቴዎች እየታዩ ነበር ለውሳኔ የሚቀርቡት፡፡ የደኅንነቱ ዋና ፈጻሚ አካላትም (የአገር መከላከያና የአገር ደኅንነት) በተናጠል ነበር ጉዳያቸውን የሚያቀርቡት፡፡ ነጥሮ የወጣና የፀደቀ የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሆነ ይኼንን መነሻ በማድረግ የአገር ደኅንነት ጉዳይ የሚያስተዳድር አካል አልነበረም፡፡

ይኼ ክፍተት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ማዕከላዊ ኮማንድ በሚባል አካል ተሸፍኖ ሥራው ይከናወን ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በተደረገው ግምገማ ጉድለቱ በግልጽ ከተቀመጠና የሕወሓት መከፋፈል ከተከሰተ በኋላ፣ ቀጥሎም በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ በዓለም አቀፋዊው ውሳኔ ሰጪ አካል ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ አሁን በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ፀድቆ ተግባር ላይ እየዋለ ነው፡፡

የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በእኔ አመለካከት ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ በክብደቱና በአገር ህልውና፣ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ለማስተዳደር እጅግ መሠረታዊ የሆነ ነው፡፡ በትክክል ከተሠራ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ፣ ይኼ ካልሆነ ደግሞ አገርን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ፖሊሲ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ በአገር አቀፍ ደረጃ መሠረታዊ መግባባት ሊደረስበት የሚገባ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን የተወሰኑና በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ፍላጎት መግለጫ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ የአንድ ፓርቲ የፖሊሲ ምርጫ ብቻ መሆንም የለበትም፡፡

ጠቅላላ ኅብረተሰቡና በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሥልጣን ያልያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሙሉ በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣን ቢይዝም እንደ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል፣ የፖለቲካውና የደኅንነት አስተዳደሩ የማይነቃነቅ የፖሊሲ መሠረት (Bedrock) ሆኖ እንዲያገለግል እየታሰበ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ፓርቲዎች እየተፈራረቁ ሥልጣን ሲይዙ ይኼንን ፖሊሲና ያስቀመጣቸውን ግቦች ተቀብለው የሚወስዱት ለውጥ ካለም በአፈጻጸሙ ላይ ብቻ እንዲሆን፤ ጊዜውን ጠብቆ መሻሻል ካለበትም፤ ለዚህ ተብሎ በተቀመጠው ሥርዓት የማሻሻል ሥራው እንዲከናወን እየታሰበ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ስለሆነም ለጉዳዩ የሚመጥና አፅንኦት (Attention) ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባዋል እላለሁ፡፡

ይኼ ሲደረግ ደግሞ ያለፈውን ፖሊሲ መገምገም ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ የሚወጣው ፖሊሲ ተፈላጊው ውጤት እንዲኖረው መሥራት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ጋርም የኤርትራን ፖሊሲ ብቻ ነጥሎ በመገምገም በሌላ ፖሊሲ ለመተካት ብቻ ከማሰብ ይልቅ፣ ይኼ የኤርትራ ጉዳይ ከአጠቃላዩ የአገራችን የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ተጣምሮ ቢታይና የኤርትራ ጉዳይም የዚህ አጠቃላይ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካል ሆኖ ቢታይ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የኤርትራን ጉዳይ ከአጠቃላዩ የአገራችን ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ተገናዝቦ ሲሠራ ነው ቀጣይነትና በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማነት የሚኖረው ብዬ አምናለሁ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ በመንግሥት በግልጽ የተቀመጠ ፍላጎትን መነሻ በማድረግ፣ ቢያንስ ኅብረተሰቡ በዚህ በጣም መሠረታዊ በሆነና ሁሉንም ጉዳያችንን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በሚነካ የአገር ደኅንነት ጉዳይ ላይ ሐሳብ ለመስጠት ነው፡፡ የጽሑፉ ዋና ይዘት አንዳንድ የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦችን ለመሰንዘር አይደለም፡፡ የአሁኑ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምንነቱን፣ የሚሰጠውን ጠቀሜታ፣ ከምን እንደሚመነጭ፣ እንዴት እንደሚፀድቅ፣ እንደሚተዳደርና ጊዜውን ጠብቆ እንደሚሻሸል ሐሳብ ለማቅረብ ነው፡፡ በጠቅላላ በሒደቱ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ይኼ ሒደት ተስተካክሎ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተዛመደ ተግባር ላይ ሲውልም፣ ውጤታማ የሆነ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይኖረናል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ለአገራችን የተረጋጋ ሰላምና ፖለቲካዊ ሕይወት እንዲኖር በማስቻል፣ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር አስተዋፅኦ ማድረግ ነው፡፡

1/ የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምንድነው?

የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በግልጽ የመንግሥት ፖሊሲ ሆኖ መካተቱ የሚታወቀው እ.ኤ.አ. ጁላይ 26 ቀን 1974 “National Security Act” ተብሎ በተሰየመው የአሜሪካን ሕግ አውጭ ምክር ቤት በፀደቀው ውሳኔ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ይኼ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት  ሃሪ ትሩማን መሪነት የመንግሥት ፖሊሲ ሆኖ የፀደቀው፡፡ ፖሊሲው መንግሥታት የሕግ አውጭ (parliament) ጠንካራ ድጋፍ አግኘተው አገራቸውንና ዜጎቻቸውን ከማንኛውም ጥቃትና አደጋ ለመጠበቅ ማንኛውንም የመንግሥት አቅም ተጠቅመውና (ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ወዘተ)  ይኼንን አቅማቸውን አስተባብረው ተግባራዊ የሚያደርጉት ፖሊሲ ነው ተብሎ ይታመንበታል፡፡

በመጀመርያ አስተሳሰቡ ሲመነጭና ተግባር ላይ ሲውል በወታደራዊና በኢንተለጀንስ የመንግሥት መዋቅሮች ላይ መሠረት ተደርጎ የወጣና በእነዚህ የመንግሥት መዋቅሮች ላይ ተንተርሶ የሚሠራ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በሒደት እየሰፉ ሌሎች የመንግሥት መዋቅሮችንና የሥራ ዘርፎችንም እያካተተ መጥቷል፡፡ ይኼ ሒደት በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1994 በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ይፋ ከሆነው ’’Human Security,’’ “Human Development Report”, “United Nations Development Rogram” ከሚለው አስተሳሰብ በኋላ የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በወታደራዊና ኢንተለጀንሲ መዋቅሮች ላይ ብቻ የታጠረ መሆኑ ቀርቷል፡፡

ይኼም ሆኖ የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያካትታቸው ጉዳዮች ከአገር አገር እንደ አገሪቱ ሁኔታ ይለያያል፡፡ አገሮች አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ወዘተ ሁኔታቸውን ታሳቢ በማድረግ የራሳቸው የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሠረታዊ ጉዳዮችን ይወስኑና ፖሊሲያቸውን ይቀርፃሉ፡፡ ሆኖም በብዙዎች አገሮች ፖሊሲው የሚያካትታቸው ነጥቦች አሉ፡፡ እነዚህም የአገር ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ፣ ዜጎች በመረጡት የፖለቲካ፣ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ የኑሮ አቅጣጫ ከውስጥ ሆነ ከውጭ በሚመጣ ተፅዕኖ እንዲቀየሩ የማይገደዱበት ሁኔታን መፍጠር፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲጠበቁ ማስቻል፣ ለአገር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሀብትና ተቋማትን መጠበቅና ሥራቸውን ሳይደናቀፉ መሥራት እንደ ዋናዎቹ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

እነዚህ ከላይ የተቀመጡትን ግቦች ሊያሳካ የሚችል የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ፣

* ጠላት ተብለው የተለዩትን ለመነጠልና ወዳጆችን ለማሰባሰብ ዲፕሎማሲያዊ አቅሙን ይጠቀማል፣ ይኼንን አቅም በየጊዜው ያዳብራል፡፡

* ኢኮኖሚያዊ አቅሙንና አገራዊ ፍላጎቱን ለማሳካት ጠላቶቹንም ለማንበርከክ ይጠቀምበታል፡፡ ይኼንን አቅም በቀጣይነት ይገነባል፡፡

* በጣም ተፈላጊ የሆነ የኢኮኖሚያሚና የማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከልና በጥቃት ጊዜም በአግባቡ ለመሥራት የሚያስችል አቅምና የመቋቋም ብቃት ያላቸው ተደርገው እንዲታነፁ ይደረጋል፡፡

* ሁልጊዜ ዝግጁ የሆነና ሊከሰት ይችላል ተብሎ ለሚታሰብ ጥቃት ተገቢውን አፀፋ ለመስጠት የሚያስችል ውጤታማ የጦር ኃይል በቀጣይነት ይገነባል፡፡

* የጠላትን መረጃ የመሰብሰብ አቅም የመከላከል ከዚህ አልፎም የማክሸፍ ብቃት ያለውና በተፃራሪው ደግሞ ለወገን አስፈላጊ የሆነውን መረጃ የመሰብሰብ አስተማማኝ ብቃት ያለው የኢንተለጀንስ አቅም በቀጣይነት መገንባት፣

* ተፈጥሮአዊም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋ ለመከላከል፣ ቢከሰትም ለመቋቋም የሚያስችል የአደጋ ዝግጁነት ብቃት እንዲኖር መገንባት፣

እነዚህንና ሌሎች መሰል ሥራዎችን መንግሥት ያለውን አቅም በመጠቀም ውጤት ለማምጣት በሚያስችለው መንገድ ይሠራል፡፡ ሁሉም የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያላቸው አገሮች በተቻለ መጠን ሁሉንም የመንግሥት አቅማቸውን አቀናጅተው ከላይ የተገለጹትን ግቦች ለማሳካት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ አገሮቹ ሁኔታ ለአንዳንዶቹ ጉዳዮች አፅዕኖት መስጠት፣ ወይም በዚህ ያልተካተቱ ጉዳዮችን ጨምረው በፖሊሲያቸው ያስቀምጣሉ፡፡

1.1/ ጠቀሜታው

የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአገር ህልውናና ቀጣይ ዕድገት ሊከሰት የሚችልን አደጋ አስቀድሞ በመተንተን እንዳይከሰት ለመከላከል፣ ከተከሰተም በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ዋጋ አደጋውን ለመግታት የሚያስችል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የሚፈጠርበት የፖሊሲ መመርያ ነው፡፡ በባህሪውም የአንድ ወይም የሁለት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራን ብቻ ያካተተ አይደለም፡፡ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ እንቅስቃሴ አቅጣጫ የሚያሲዝ ነው፡፡

የአገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊና የልማት ሥራዎችን አቅጣጫ ያስይዛል፡፡ በመሆኑም የአንድ አገር አስተዳደር ከሚመራባቸው መሠረታዊ መመርያዎች እንደ ዋነኛ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ ማንኛውም መንግሥት አገሩን የሚመራበት መሠረታዊ የተግባር መመርያ የሚያስቀምጥ ሰነድ ነው፡፡ የአንድን አገር ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ሕዝቦች እንዲተዳደሩበት ለመረጡት ፖለቲካዊ ሥርዓት ግንባታና ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ምቹ መደላደል ለመፍጠር ታስቦ የሚዘጋጅ መሠረታዊ የፖሊሲ ዶክመንት ስለሆነ፣ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሰነድ ነው፡፡

አገሮች በግልጽ በፓርላማቸው እየወሰኑ የሚያፀድቁት የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባይኖራቸውም ሥራቸውን የሚመሩበት አቅጣጫ የላቸውም ወይም አልነበራቸውም ማለት አይደለም፡፡ የ‹‹ንጉሡ ፍላጎት›› ወይም በአንድ ወቅት ሥልጣን የያዘ የፖለቲካ ኃይል ፍላጎት የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መመርያ ሆኖ ይሠራበታል፡፡ ይኼ በግልጽ በሕዝብ ተሳትፎ (በፓርላማ በኩል) ያልፀደቀና ተጽፎ ያልተቀመጠ አቅጣጫ ለሥርዓቱ ቅርበት ያላቸው ባላሥልጣናት በየጊዜው በሚሰጡት መመርያ ተግባር ላይ እየዋለ መጥቷል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ለአገር መመርያ ሆኖ ሲያገለግል በወቅቱ የፖለቲካ ሥልጣን የያዙ ኃይሎች ለእነሱ እንደሚስማማ በማድረግ ይቀርፁትና በሥልጣን እስካሉ ድረስ የሥራ መመርያ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ እነሱ ጊዜ ጥሎአቸው ከሥልጣን ሲወርዱ ደግሞ በሌላ መመርያ ይተካል፡፡

ባለንበት ዘመን የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተቻለ መጠን አሳታፊ በሆነ ሒደት መንጭቶና ዳብሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል (ፓርላማው) እንደ ፖሊሲ አፅድቆት ወደ ሥራ ይገባል፡፡ የዚህ አሠራር ጠቀሜታው አገር አደጋ ውስጥ ሲገባ ዜጎችና የመንግሥት መዋቅሮች ሙሉ አቅማቸውን በእምነትና በዕውቀት አቀናጅተው በመጠቀም አደጋው እንዳይከሰት፣ ከተከሰተም በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሳራ ለመግታት ያስችላቸዋል፡፡ የአገሪቱን አጠቃላይ አቅም ማለትም የመንግሥትን አጠቃላይ አቅም (Instruments of Power) የሚባሉትን (ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ) አቅሞች በቅንጅትና እንደ አስፈላጊነቱ ለመጠቀም የሚያስችል ግልጽ መመርያ ይሆናል፡፡

ከዚህ በላይ ከመንግሥት መዋቅር ውጭ ያለውን የሕዝብ አቅም ለማካተት የሚያስችል መመርያ ይሆናል፡፡ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይኼንን ከላይ የተገለጸውን ዓላማ እንዲያሳካ በማሰብ ነው የሚወጣው፡፡ ይኼ ደግሞ መሆን የሚችለው የፖሊሲው አወጣጥ ይዘትና አስተዳደሩ በጠቅላላ ሒደቱ በየደረጃው አሳታፊና አቅም እየሰበሰበ የሚሄድ ተደርጎ  ሲሠራ ነው፡፡

ይኼ ጉዳይ ማለትም የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሁን ባለንበት ዘመን ሲነሳ ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን በጥልቀት በማጤን ከአገራዊ ፖሊሲ ጋር ያላቸውን ዝምድናና ተቃርኖ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዘመነ ግሎባላይዜሽን የአንድ አገር አገራዊ የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተናጠል ለብቻው ማሰብ አይቻልም፡፡ እንደ አገራችን በመሰሉ በሽግግር ላይ ያሉ አገሮች ዓለም አቀፋዊውንና በተለይ አኅጉራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡

ይኼ ማለት በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደሚታየው የአገሮች ደኅንነት ከአካባቢው ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ይሆንና አገሮች ለብቻቸው የራሳቸውን ፖሊሲ ለማውጣት የሚቸገሩበት፣ በጋራ የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያወጡበት ሁኔታ ድረስ ይደርሳል፡፡ ከዚህ በመለስም የየራሳቸው ፖሊሲ ኖሮዋቸው በጋራ ደግሞ ደኅንነታቸውን የሚያስጠብቁበት ስምምነት ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ እያለ በየደረጃው በጣም ከጠበቀ የጋራ የደኅንነት ፖሊሲና አሠራር ጀምሮ እስከ ትንሽ ላላ ያለ የደኅንነት ስምምነት የሚያደርጉበት አሠራር እየተለመደ መጥቷል፡፡ አገሮችም በዚህ ይጠቀማሉ፡፡ ይኼ አሠራር በአገሪቱ የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መታሰብ ይኖርበታል፡፡

1.2/ ምንጩ

አንድ አገር አገራዊ ጥቅሞችን ተንትኖ በማስቀመጥ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ካስቀመጠ ይኼ ሁኔታ ለውጭ ግንኙነት ሥራ ዋናው መመርያ ይሆናል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከአገሩ ጋር ዝምድና ያላቸው አገሮችም ፖሊሲውን በመገንዘብ ግንኙነታቸው በዚህ በፖሊሲ በተቀመጠው አቅጣጫ እንዲያስተካክሉ ይረዳል፡፡ ፍላጎታችንና ማድረግ የምንፈልገው ጉዳይ በግልጽ ስለሚቀመጥ የግንኙነቱ መነሻ መሠረት ይሆናል፡፡

እንደዚህ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን በግልጽ ያስቀመጡ አገሮች ደግሞ እርስ በርሳቸው የሚያደርጉት ግንኙነት ለመተንበይ የሚቻል (predictable) ይሆናል፡፡ ይኼ ለመተንበይ የሚቻል ፖሊሲ መኖር በአገሮች የእርስ በርስ ግንኙነታቸው መካከል ያለውን “ያልጠራ ደመና” ያራግፈውና በሚያገናኛቸው ጉዳይ ላይ ፈጥነው ለመስማማትና አብሮ ለመሥራት የተሻለ አካባቢያዊ የደኅንነትና የሰላም ሁኔታ እንዲፈጠር ያግዛል፡፡ በማይስማሙባቸው ጉዳዮችም አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዲያስቡና እንዲያቅዱ ያስችላቸዋል፡፡

ከላይ የተገለጽው እንደተጠበቀ ሆኖ የአንድ አገር የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከምን ይመነጫል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ዋነኛዎቹ ሦስት የተያያዙ ምንጮች ናቸው፡፡ እነሱም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ አገራዊ ጥቅም (National Interest) ፣ አገራዊ የሥጋት ወይም አደጋ ትንተና (Threat Analysis) ናቸው፡፡

እነዚህን በየተራ እንያቸው፣

1.2.1/ ሕገ መንግሥቱ

ባለንበት ዘመን የአንድ አገር ሕገ መንግሥት የአገሪቱ ሕዝቦች ተደራጅተው የተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ብልፅግናና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ ቀጣይነት ያለው የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር ያስችለናል ብለው የሚያምኑበትን አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት፣ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ የሚመራበት፣ ለአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ መመርያ ነው፡፡ በአጭሩ መንግሥት ተብሎ ለአንድ ለተወሰነ ታሪካዊ ወቅት አገርን የሚያስተዳድረው የፖለቲካ ኃይልና የአገሪቱ ሕዝብ በጠቅላላ ያላቸውን ግንኙነት በሕግ የሚደነግግ ውል (Contract) ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

መንግሥት በሕገ መንግሥቱ በተቀመጡት መብቶችና ግዴታዎች፣ እዚያው በተተነተኑ የአሠራር አቅጣጫዎችና የሥልጣን ክፍፍሎች ብቻ ሕዝብን የሚያስተዳድርበት፣ ሕዝብ ደግሞ መብትና ግዴታውን አውቆ ተግባራዊ የሚያደርግበት ስምምነት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ሕዝቦች ራሳቸውን ለማስተዳደር ተስማምተው የሚያስተዳድራቸውን መንግሥት የሥልጣንና የኃላፊነት ገደቡን ወስነው ኃላፊነት የሚሰጡበት ግዴታውንና የዜጎችን መብትና ግዴታቸውን በጥቅሉ የሚያስቀምጡበት ኮንትራት ነው፡፡ ይኼ ኮንትራት ማንኛውም ወገን ቢጥሰው ተጠያቂ ይሆናል፡፡

እንደ ማንኛውም ሰው ሠራሽ ስምምነት በአንድ ወቅት ተፈላጊ የነበረ ስምምነት፣ በሌላ ጊዜ እንደገና እንየው ሊባል ይችላል፡፡ ይኼ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ስለሚባል እንዲሁ ለማለት ይሆን እንደሆን እንጂ፣ አጠቃላይ የሕገ መንግሥት ምንነትን መግለጽ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡

በዚህ ጽሑፍ ሕገ መንግሥት የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማውጣት መነሻ ይሆናል ስል፣ በሕዝቦች ተቀባይነት ያለውና ፈቅደው እንመራበታለን ብለው የተቀበሉት ሕገ መንግሥት አለ የሚለውን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ችግር ካለ የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ላይ ችግር ይከሰታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መሠረታዊ መግባባትና በብዙኃኑ ሕዝብ ተቀባይነት ካለ ደግሞ፣ ይኼንን ተንተርሶ የሚወጣው የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡

ከፍ ብሎ እንደተገለጸው የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንድና መሠረታዊ ዓላማው ሕዝቦች ተስማምተው ወደው የመረጡትን የፖለቲካ አስተዳደር አቅጣጫ፣ የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ የልማት አቅጣጫ፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕዝቦች የአኗኗር ዘይቤ፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በሚመጣ የኃይል ተፅዕኖ ተገዶ እንዳይቀየር መከላከል ነው፡፡ ይኼንን ተልዕኮውን በቀጥታ በሕዝቦች ፈቃድ ከወጣው ሕገ መንግሥት ነው የሚገኘው፡፡ ሌላው በአገሪቱ ያለውን የሥልጣንና የሥራ ክፍፍል መሠረታዊ በሆነ ይዘቱ የሚወሰነው በሕገ መንግሥቱ ነው፡፡

የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ሲቀረፅ የሚኖረው የሥልጣን ክፍፍልና የውሳኔ አሰጣጥ እርከን፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን መሠረታዊ ውሳኔ በቀጥታ ተቀብሎ ነው የሚሄደው፡፡ በተጨማሪም ፖሊሲው ሊያሳካው የሚፈልገው ዓላማ የአገሪቱን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነትን ማክበር ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ ደግሞ አንድ ሌላ መሠረታዊ በሕገ መንግሥት የሚወሰን ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች የአንድ አገር ሕገ መንግሥት የአገሩን የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማመንጨትና የፖሊሲው ዋነኛ ይዘት ለመወሰን ያገለግላል፡፡

1.2.2/ አገራዊ ጥቅም

ይኼ አገራዊ ጥቅም የሚባለው አጭር ጽንሰ ሐሳብ (Concept) ከ16ኛውና (በጣሊያን) 17ኛው (በእንግሊዝ) ክፍለ ዘመናት ጀምሮ በተለያዩ አገላለጾች (“የልዑል ወይም የንጉሡ ፍላጎት”፣ “የንግሥና ሥርዓቱ ፍላጎት”፣ “የሕዝብ ፍላጎት” “(Public Interest) ‹‹ብሔራዊ ክብር›› (National Honor) ፣ ወዘተ በሚሉ አገላለጾች የአገሮችን በዋናነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫዎቻቸውንና የሥራ እንቅስቃሴዎቻቸውን መልክ በማስያዝ ተግባር ላይ ይውል እንደነበረ የታሪክ ማኅደሮች ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እያደገና ዳብሮ አገራዊ ጥቅም በመባል ይገለጻል፡፡

ምን ማለት ነው? እንደ አንድ ራሱን የቻለ አምሮ ሲታሰብ በርከት ካሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚያነሱዋቸውና ጥቅማችንን ያስከብሩልናል ብለው ከሚያስብዋቸው አስተሳሰቦች በላይ ነጥሮ የወጣ፣ የጠቅላላ የአገሪቱን መሠረታዊና አጠቃላይ ጥቅሞችን ከሌሎች መንግሥታትና አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ አደረጃጀቶችና አሠራሮች ጋር በሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት፣ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መንግሥታት የሚጠቀሙበት የአስተሳሰብና የተግባር መመርያ ጥንቅር ነው፡፡ ይኼም ሆኖ ይኼ የአገራዊ ጥቅም አስተሳሰብ በጣም አነጋጋሪ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ በተለይ እንደ ፖለቲካዊ ሥራ የተግባር መመርያ ተደርጎ ሲወለድ፣ የማንን ጥቅም ያስከብራል የሚለው ጉዳይ ነው አነጋጋሪ የሚያደርገው፡፡

በማንኛውም ጊዜ ለአንድ አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደ መሠረታዊ ታሳቢ ተደርጎ የሚወሰደው አገራዊ ጥቅምን የማንጠርና የመቀመር ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ ግልጽ የሚሆንና የማያሻማ መሆን አይችልም፡፡ በአንድ አገር የሚኖሩ ሰዎች የአገራቸውን ጥቅም ከሌሎች እነሱ አባል ከሆኑባቸው አደረጃጀቶች ጥቅሞች ለይቶ በማውጣትና ሙሉ ስምምነት ላይ ለመድረስ መቸገራቸውና መለያየታቸው አይቀርም፡፡

ምክንያቱም ይኼ የአገራዊ ጥቅም ማንጠር ጉዳይ ከበስተጀርባው ሌሎች አስተሳሰቦች ስላሉትና መነሻውም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ዋጋና አስተሳሰብ ተንተርሶ ስለሚመጣ፣ በፈረንጆቹ አባባል (Value Laden) ስለሆነና ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ ባህላዊ (Subjective) ምርጫን የሚከተል ስለሆነ፣ ከዚህ በመነሳት ተጨምቀውና ተሰብስበው በሚቀመጡ የአገራዊ ጥቅሞች ላይ ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ ሒደቱን ውስብስብና አስቸጋሪ የሚያደርገውም ይኼ ጉዳይ ነው፡፡

ይኼ ከተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችም ሆነ የማንነት ጥያቄዎች የሚመነጨው መለያየት የሚያስከትለው አገራዊ ጥቅም በማንጠር ጉዳይ ላይ የሚነሳው የሐሳብ ልዩነት የሚፈታው፣ አሳታፊ በሆነ ሰፊ ሒደት እንዲያልፍ በማድረግ ነው፡፡ እነዚህ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በመካከላቸው በሚያደርጉት ውይይትና ይኼንን ሐሳብ ለማንጠር፣ የሚመለከታቸውና ያገባናል የሚሉ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በአንድ ወይም በሌላ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ኃይሎች መካካል በሚደረግ ውይይት ነው የሚወሰነው፡፡

ይኼ ማለት በአንድ ወቅት ጠንከር ያለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ወይም ፓርቲ የፈለገውን አስተሳሰብ የመጫን ዕድሉ ዝግ ነው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በሒደት ደግሞ ጉዳዩ እየተነሳ እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ ይኼ የአንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ወገኖች የራሳቸውን አስተሳሰብ በኅብረተሰብ ላይ ከጫኑ አገራዊ ጥቅምን አንጥሮ ማውጣት ላይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተቀባይነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኼ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን በመጥረግ ብቻ አይቆምም፡፡ ብዙ የአገር ሀብትና ጉልበት ወጥቶባቸው የተገነቡ ተቋማትንም (መከላከያ፣ የደኅንነት ተቋማት፣ ወዘተ) መጥረግ ይሆናል፡፡ አገር ተመልሶ በየጊዜው እየታመሰ ረዘም ያለ ጊዜ ያለው ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር፣ በዚህ ሳቢያ ደግሞ እንደ አገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማታችንና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው እየተጎተተ ይሄዳል፡፡

እጅግ አሳታፊና መሠረታዊ የሆነ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው አገራዊ ጥቅሞችን በማንጠር ለአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ግብዓት እንዲሆን አለማስቻል የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ በተወሰኑ የፓርቲ ኃላፊዎች የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ለብቻው የሚያስበውን አገራዊ ጥቅም ታሳቢ በማድረግ የሚያወጣው የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ እስካሁን ድረስ አገራችን ከመጣችበትና በየጊዜው ከሚከሰት ትርምስ አያወጣንም፡፡

የአንድ አገር ብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአብዛኛው የአገሪቱኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ የመጀመርያው ሥራ የአገሮቹን  ብሔራዊ ጥቅም የማንጠርና በዚህ ጉዳይ ላይ በተቻለ መጠን ሰፊ ስምምነት ላይለመድረስ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ጊዜም ወስዶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ መሠረታዊ ስምምነት ከተደረሰና አገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቁልን አስተሳሰቦች ተለይተው ከተቀመጡ፣ ይኼንን ተንተርሶ የሚመጣው የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፓርቲ፣ ከጎሳ፣ ከሃይማኖት፣ ከመደብ የዘለለ የአገር ደኅንነታችን ለማስጠበቅ መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ያስችለዋል፡፡ የቀሩት የፖሊሲና የስትራቴጂ አቅጣጫዎች ልዩነቶች ከዚህ በመለስ ባሉ ጉዳዩች ላይ ያተኮሩ ይሆናሉ፡፡ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው የሁሉም ሌሎች ፖሊሲዎች ጠንካራ መነሻ (Bedrock) ሆኖ እንዲያገለግል ያስችለዋል፡፡

በተለምዶ በአንድ ወቅት ፖለቲካዊ ሥልጣን የያዘ የፖለቲካ ኃይል አገራዊ ጥቅም የሚለውን አስተሳሰብ በተገቢው መንገድ ተንትኖም ሆነ እንዲሁ የማኅበረሰብ ቦታው እየመራው በመሰለው መንገድ ያስቀምጠዋል፡፡ ይኼ አስተሳሰብ ጊዜው እስኪደርስ ድረስ የአገሪቱ መመርያ ሆኖ ይቆያል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ በሌላ ይተካል፡፡ ይኼ በተለምዶ ሲሠራበት የቆየው አካሄድ ቀጣይነት ያለውና የተረጋጋ ሥርዓት እንዳይኖር አስተዋፅኦ ከሚያድርጉት ክስተቶች አንዱ ነው፡፡

አሁን በሠለጠነው ዓለም ደግሞ በወጉ ሰፊ ጥናትና ውይይት እየተደረገበት የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች (ፓርቲዎች፣ የሕዝብ አደረጃጀቶች፣ በጉዳዩ ላይ ዕውቀትና አስተዋፅኦ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ምሁራን፣ የዕድሜና የዕውቀት ባለፀጋዎች፣ ወዘተ) የሚሳተፉበት ሒደት በመጀመር መሠረታዊ መግባባት ላይ የሚደረስበት አገራዊ ጥቅሞችን የማንጠርና የመንግሥት መመርያ እንዲሆን በመስማማት ሥራው ይከናወናል፡፡

ይኼ ጉዳይ በጽሑፍ እንደሚገለጸው ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ሰፊ ሥራና ጊዜ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጭቅጭቅና መነታረክ ውስጥ የሚያስገባ ሒደትም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዴ በዚህ ሒደት ከታለፈ ግን የአስተሳሰቡ ይዘትም እየበለፀገ፣ ባህሉም እየተለመደ በቀጣይነት እያደገ የሚሄድ ይሆናል፡፡ ይኼ በመሆኑ ደግሞ ለአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን መሠረታዊ ግብዓት ሆኖ በማገልገል፣ የፖለቲካ ኃይሎች ፖለቲካዊ ሥልጣኑን እየተፈራረቁ በያዙ ቁጥር የአገራችንን መሠረታዊ ጥቅሞች ጥያቄ ውስጥ የማያስገቡበት፣ እነዚህን ጥቅሞች ለየት ባለ አመራር ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ እንዲያተኩሩ ይሆናል፡፡

ይህ ካልሆነ ሌላው አማራጭ አንድ በአንድ ወቅት የፖለቲካ ሥልጣን የያዘ ኃይል በሚያንምንበት መንገድ አገራዊ ጥቅማችንን ያስቀምጥና ሰፊ መግባባት እንዲደረስበት ስላልተደረገ፣ በሌላ ጊዜ ሌላ የፖለቲካ ኃይል ሥልጣኑን ሲይዝ አስቀድሞ የነበረውን ጠራርጎ እንደ አዲስ ይጀምራል፡፡ መቼም ቢሆን ፖለቲካዊ ሥልጣን የያዘ ኃይል በግልጽ በጽሑፍ ባያስቀምጠውም “አገራዊ ጥቅም” የሚለው ጉዳይ ይኖረዋል፡፡ አጠቃላይ የመንግሥት እንቅስቃሴም በዚሁ አስተሳሰቡ ነው የሚመራው፡፡ ምንም አስተሳሰብ የሌለው (Vaccum) አይሆንም፡፡ ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ ኃይሉ የአገር ጥቅም የሚለው በትክክል የአገር ጥቅም ይወክላል ወይ ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ከላይ በተገለጸው መንገድ ሲታለፍ ነው፡፡

የአንድ አገር ብሔራዊ ጥቅም ከብዙ ታሳቢ ነገሮች በመተንተንና እነዚህን በማጥናት የሚመጣ በጣም ሰፊ የሆነ መግባባት ሊደረስበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስካሁን ድረስ በተለምዶ ከሚታየው ብዙ አገሮች አገራዊ ጥቅማችንን ያስጠብቁልናል ብለው የሚስማሙባቸው ጉዳዮች እንደ አገሮቹ ሁኔታ የሚቀያየር ቢሆንም፣ ብዙውን ጊዜ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የሚቀመጠው የፖለቲካና የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር ዘይቤ፣ የአገር ሰላምና መረጋጋት የአገሪቱን ዕድገትና ልማት ወደፊት ያራምዳሉ ተብለው ስለሚታሰቡ፣ በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ አስተሳሰቦች ናቸው ተብለው ይወሰዳሉ፡፡

አገሪቱ የምትመራበት የፖለቲካ አስተዳደርና የማኅበረ ኢኮኖሚ የዕድገት አቅጣጫ ሕዝብ ፈቅዶና ወዶ የመረጠውና ጥቅሜ እንደ ሕዝብ ያስጠብቅልናል ያለው አቅጣጫ ስለሆነ፣ በሕዝቡ ፈቃድ ብቻ እንጂ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በሚመጣ ተፅዕኖ መለወጥ ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚፃረር ጉዳይ ይሆናል፡፡ ስለሆነም አገሪቱ ባላት ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊ፣ ወዘተ አቅም በማስተባበር መቃወም ይገባል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን የተለያዩ አገሮች የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ከታሪካቸው ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው፣ ካላቸው የተፈጥሮ ሀብት፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ዕድገታቸው ካለው ጠቀሜታ በመነሳት በማንኛውም ጊዜ ጥቃት እንዲደርስበትና ለአደጋ ከተጋለጠም ባላቸው አቅም ወታደራዊ አቅምም ጨምረው የሚከላከሉትን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ግልጽ ያደርጋሉ፡፡

ከዚህም በመነሳት በአገራችን ሊታሰቡ ከሚገባቸው ጥቂቶቹን እንግለጽ፡፡ እንደ ወንዞቻችን የመሳሰሉ ተፈጥሮ ያደለንን ፀጋ በማልማት ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ዕድገታችን መነሻ እንዲሆን መሥራት፣ በዚህ መንገድ የሚሠሩ ሀብቶቻችን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችና የማሰራጫ መስመሮች፣ ወዘተ ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቁ ስለሆነ የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲያችን ሊያስባቸው የሚገባ ጉዳዮች ይሆናሉ፡፡

እነዚህን ከማንኛውም ጥቃት መከላከል ማለትም በዘመኑ እየጠነከረ ከመጣው የሳይበር ጥቃት ጭምር መከላከል የብሔራዊ ደኅንነታችን የፖሊሲ አቅጣጫ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚያዊ ምሰሶና ማገር የሆኑት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችና የማሰራጫ መስመሮች በተጨማሪም፣ የባቡርና ዋና የትራንስፖርት አውታር የሆኑ አውሮፕላኖቻችንና ለእነሱ አገልግሎት የሚሰጡ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ አውራ መንገዶች በተለይ ከባህር በር ጋር የሚያገናኙን መንገዶች፣ የቴሌፎን፣ የኢንተርኔት መስመሮች፣ በጠቅላላው የኢኮኖሚው መሠረተ ልማቶች፣ የገንዘብ ተቋማት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በሚመጣ ተፅዕኖ ሳቢያ ባለመሥራታቸው በዕድገታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጠር መሥራት ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሕዝብ ማዕከላት የሆኑ ከተሞችንም ከማንኛውም አደጋ መጠበቅ ይገባል፡፡

በአገራችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፈ የመጣውን ተቻችሎና ተከባብሮ መኖር፣ የሃይማኖትና የጎሳ ልዩነት ለመለያየትና ለመበጥበጥ ምክንያት እንዳይሆን፣ ልዩነትን አቻችሎ አንድነትን እያጠናከሩ አብሮ የመኖር ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስከብር፣ ለሰላም፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ዕድገታችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ ታሪካዊና ባህላዊ ፀጋችንን ይበልጥ እንዲዳብርና ከዘመኑ ጋር እያደገ እንዲሄድ መሥራት፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በሚመጣ ተፅዕኖ ይኼንን ታሪክ በአሉታዊ ለመቀየር የሚደረግ ጥረት የብሔራዊ ደኅንነታችንና ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ትኩረት በመስጠት ሊሠራበት የሚገባ እንደሆነ መታሰብ  ይኖርበታል፡፡

የአንድ አገር ወታደራዊ ተቋማት የተለያዩ ጠቅላይ መምርያዎች (የመከላከያ፣ የአየር ኃይል፣ የምድር ኃይል፣ ወዘተ) ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች፣ የምርምርና የሥልጠና ተቋማት፣ ተዋጊ ክፍሎች፣ ወዘተ የደኅንነትና የመረጃ መዋቅሮች ከማንኛውም ጥቃት መከላከልና ሥራቸውን ያለምንም እንቅፋት እንዲሠሩ ማስቻል ሌላው አገሮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት የአገራዊ ደኅንነት ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አገሮች በዕለት ተዕለት ማንኛውንም ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የፀጥታ ኃይሉ በአጠቃላይ ያለምንም ተፅዕኖና ለአደጋ ሳይጋለጥ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ማስቻል፣ የአገራዊ ደኅንነት ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የአገርን ጥቅም የመለየትና ለዚህ እንዲሳካ የመሠረት ጉዳይ ከአኅጉራዊና አከባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብም መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት በአገራችን መሆኑ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይኼንን የአገራችንን ጥቅም ለማስከበር ሥንሠራበት እንገኛለን፡፡ ከዚህ ቀጥሎም በአፍሪካ ቀንድ ኢጋድ ላይ ያለን የጎላ ተሳትፎ በሰላም ማስጠበቅ ሥራ ያለን ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሌሎችን አጎራባች አገሮች ጥቅም ሳንፃረር የአገራችንን ጥቅም ማስጠበቅያ መድረኮች አድርገን ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡

በተለይ ከአገራችን የአጭር ጊዜ ታሪክ አንፃር፣ አሁን ያለው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ማለትም ከፍተኛ የዓለም የንግድና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ከሚደረግበት የቀይ ባህር መስመር በጣም ቅርብ ሆነን እያለንና ረዘም ካለው ታሪካችን አንፃርም የዚህ የባህር ቀጠና ዓይነተኛ ኃይል የነበረን አሁን ከዚህ መስመር ተገለን መቀመጥ አንችልም፣ አይገባንም፡፡ ከዚህ ሁኔታ አንፃር በፖሊሲ ደረጃ እኛ ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም በደቡባዊ በቀይ ባህር የሚደረግ እንቅስቃሴ እኛን ያገባናል የሚል ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ከዚህ የሚመነጭ ፖሊሲ እንዲኖረን ይገባል፡፡

ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ዋስትና ያለው አስተማማኝ የባህር በር መኖርና በቀጠናው ዋና ተዋናይ ከሆኑት ኃይላት አንዱ መሆን፣ በየጊዜው ለወደብ የሚከፈል የአገልግሎት ወጪ የመቀነስ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ከዚህ የከበደና ስትራተጂያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ አስተማማኝ በቀጣይነት እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲኖረን ወደዚያ ከፍተኛ የዓለም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት አካባቢ ድርሻ እንዲኖረን ይገባል፡፡

ከዚህ በላይ ደግሞ ለጠቅላላው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማታቻን መሠረት የሆነው አስተማማኝ ሰላም እንዲኖረን በዚህ ቀጠና ሊመጣብን የሚችለውን አደጋ ለመከላከልና ለመቋቋም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡ ይኼ አካባቢ ለወደፊት ጠላቶች ሊሆኑ በሚችሉ ኃይሎች ሙሉ ቁጥጥር ሆኖ የአገራችን ሰላም የተጠበቀ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የቀይ ባህር በር የማግኘት ጉዳይና በጠቅላላው በቀይ ባህር ዋነኛ ተዋናይ መሆን ከአገር ጥቅምና ደኅንነት አንፃር ሲታይ እጅግ መሠረታዊ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ፖለቲካዊ ስምምነት ከተደረሰና እንደየመንግሥት ፖሊሲ ሆኖ ከፀደቀ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመርያው ምርጫ በሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና፣ በሕጋዊ መንገድ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ ይኼ ሳይሳካ ከቀረ ግን አንድ መንግሥት ካሉት የፖለቲካ መሣሪያዎች (ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ) በአንድ ብቻ ፖሊሲውን ለማሳካት አይዋጋም፡፡ ሁሉንም የፖሊሲ መሣሪያዎች በማቀናጀት የበለጠ ውጤት እንዲያመጡ ነው መሥራት ያለበት፡፡

ከዚህ አንፃር ፖሊሲውን ተግባር ላይ ለማዋል ወታደራዊ አማራጭም ከመጀመርያው ዝግ መደረግ የለበትም፡፡ ይኼንን የፖሊሲ መሥሪያ አልጠቀምበትም ብለህ ወደ ድርድር አይገባም፡፡ የአካባቢያዊ ሰላምና ደኅንነት ሲታሰብ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለን ዝምድና እንዴት ይህን የሚለው ጉዳይ አሁን ያለው ሁኔታ (ሰላም የለም – ጦርነትም የለም) ብዙ ዕድሜ የሚኖረው አይመስልም፡፡

አሁን ያለው የኤርትራ መንግሥትም አጋሮቹን እያሰባሰበ ሁኔታውም ይበልጥ እያወሳሰበው ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የነበረውና ለወደፊትም መቀጠል ያለበት ወዳጅነት ይበልጥ እሚጠናከርበት አሁን ያለው መንግሥት ደግሞ ከሚሸርበው መሰሪ ተግባሩ እንዲቆጠብ ዕድሜው የሚያጥርበት የፖሊሲ አቅጣጫ የአገራችንን ብሎም የአካባቢያችንን ደኅንነትና ሰላም ያስጠብቃል ብዬ አምናለሁ፡፡

1.2.3/ አገራዊ የሥጋት/አደጋ ትንተና

የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማውጣት ሌላው መነሻ አገራዊ የሥጋት ትንታኔዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በዋናነት ከላይ በተገለጸው መንገድ የሚወጡ አገራዊ ጥቅሞችን ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በግልጽ ለተቀመጡት አገራዊ ጥቅሞች ምንና እንዴት ዓይነት አደጋ ሊመጣባቸው ይችላል የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል፡፡

የአገራዊ ደኅንነትን የሥጋት ምንጮች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጭ በተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የሚመነጩም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተፈጥሮአዊ (Environmental) አደጋዎች የድርቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ ወዘተ አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ የአገርን ደኅንነት የሚፈታተኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ ባህርይ የሚመጡ አደጋዎችን አስቀድሞ መተንበይና ለዚህ መዘጋጀት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ለዚህ የሚደረገው ዝግጅት በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማታችን በማፋጠን አደጋ እንዳይከሰት፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን መከላከል ወይም ሲከሰትም በኢኮኖሚያዊ አቅማችን መዳበር አደጋው ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ለመቋቋም ያለን አጠቃላይ አገራዊ አቅም ማሳደግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት” እየተባለ የሚጠራውን የመንግሥት መዋቅር ለሁሉም ዓይነት ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን የተሟላ ዝግጅት እንዲኖረው ማስቻል ይሆናል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ዋናው ትኩረታችን የፖለቲካዊ ሥርዓቱ ባህርይ ወይም ይኼንን ሰበብ አድርገው በሚመነጩ ሥጋቶች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ሥርዓቱን ተንተርሰው የሚከሰቱ ችግሮች የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች በተናጠልና በቅንጅት የሚፈጽሙዋቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋናው መነሻቸውም አገሪቱ የምትከተለውን የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓት፣ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ልማት አቅጣጫዎችና አስተሳሰቦች ካለመቀበል የሚመነጩ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ አገራችን ባሉ በሽግግር ላይ ያሉ አገሮች ዋናው የአገር ደኅንነት ሥጋታቸው አገር ውስጥ ባሉ ኃይሎች የሚመነጭ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ሥራ ላይ ያለው ሥርዓት ፖለቲካዊና ሰብዓዊ መብታችንን አላከበረልንም፣ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን አልጠበቀልንም፣ በአጠቃላይ ድምፃችንን አስተሳሰባችንን በሚገባው መንገድ አልወከለንም፣ አድልዎ እየተፈጸመብን ነው፣ ፍትሕ እየተጓደለብን ነው የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች እየተበራከቱ ሲሄዱ፣ ከፖለቲካዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሥልጣንና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ተገለናል ወይም በሚገባን ደረጃ አልተጠቀምንም ወይም ድርሻችን ከፍ ያለ መሆን አለበት የሚሉ ወገኖች ተደራጅተው የሚፈጥሩት ችግር ነው፡፡

ይኼ አንዴ ፖለቲካዊ ችግሩ ከተከሰተና አብዛኛው ሕዝብ ካመነበት አደጋው የሚከሰትበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም (ሰላማዊ ሠልፍ፣ የሥራ ማቆም አድማ፣ የከተማ አመፅ፣ ምናልባትም የትጥቅ ትግል፣ ወዘተ) በአገር ደኅንነት ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ችግር መፍጠሩና የአገሪቱን ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማቱን ማጓተቱ አይቀርም፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ይኼ ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ ይሆንና ሁለቱም ይቀናጃሉ፡፡

ከውጭ ኃይሎች የሚመነጨው አደጋ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው አገሪቱ የምትከተለው የፖለቲካ አስተዳደርና የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት አቅጣጫዎች በእነዚህ የውጭ ኃይሎች ላይ ችግር ይፈጥራል፣ አገራዊ ጥቅማችንን ይጎዳል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ የአገሮች አጠቃላይ አቅም ደግሞ በንፅፅር የሚታይ ስለሆነ አንድ አገር የሚከተለው አቅጣጫ በሌሎች አጎራባች አገሮች ላይ ችግር ይፈጥራል ተብሎ ከታሰበ፣ ከእነሱ የበለጠ አጠቃላይ አቅም አግኝቶ የበላይ እንዳይሆን እንቅፋት ለመፍጠር የተቻለውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡

ይኼ ጉዳይ በአንድ ወገን ብቻ የሚሠራ አይደለም፣ የሁለትዮሽ መንገድ ነው፡፡ ማለትም አንደኛው የአጎራባች አገር ችግር ይፈጥርብኛል ብሎ ሲያስብ ሌላው እንደዚሁ ሊያስብ ይችላል፡፡ ይኼ ሁኔታ ደግሞ በራሱ እየተደጋጋፈ በቀጣይነት አገሮች ወደ ችግርና የተካረረ ጠላትነት ያስገባቸዋል፡፡ ከዚህ ተነስተውም አንዱ ሌላውን ለማጥፋት በሙሉ አቅማቸው ይሠራሉ፡፡ ይኼ ደግሞ በአገሮች መካከል ችግር ይፈጥራል፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ሥራቸው እየተገናኙ አገራዊ ጥቅማቸውን መሠረት በማድረግ በግልጽ እየተወያዩ፣ በጥርጣሬና ካለመተማመን ሊከሰቱ የሚችሉ የሥጋት ምንጮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ይኼ እንቅስቃሴ የሚያስወግደውና የሚፈታው ችግር ይኖራል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዚህ በዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ብቻ የማይፈታና የማይታረቅ የጥቅም ተፃራሪነት ይኖራል፡፡ ይኼ ጉዳይ ተለይቶና ታውቆ የአገሮች አገራዊ ሥጋት ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ አገሮች ከአገራቸው ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ለሊከሰቱ የሚችሉ አገራዊ ሥጋቶችን በሰፊ ተከታታይነት ያለው ጥናትና ትንተና አንጥረው በማወቅ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እነዚህ አገራዊ ሥጋቶች ከምን ይመነጫሉ? በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ሊከሰቱ ይችላሉ? የተለያዩ መነሻ ያላቸው ሥጋቶች እርስ በርሳቸው እንዴት ይተሳሰራሉ? ወይም ይለያያሉ? እነዚህ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርሱ እንዴት መፍታት ይቻላል? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳትና ተከታታይ ጥናቶችን በማካሄድ ከዚህ የሚመነጩ ትንታኔዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ቢሆኖችን (Scenarios) በማዘጋጀት፣ ለእነዚህ ደግሞ የመፍትሔ አማራጮችን በቀጣይነት በማመንጨት ለአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ገና ሲመነጭም ሆነ በተግባር ላይ ሲውል ከፍተኛ ግብዓት በመሆን ያገለግላሉ፡፡

በዚህ አጋጣሚ በዚህ ሥራ ላይ የአገር የመረጃ መሰብሰቢያ መዋቅሮች (የተለያዩ የስለላና ፀረ ስለላ ተቋሞች፣ ዲፕሎማቶች፣ ሚሽኖች) ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃ በማቅረብ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከእነዚህ የመንግሥት መዋቅሮች ውጪ ያለው ለሁሉም ሕዝብ ክፍት የሆነ የመረጃ ፍሰት በተደራጀ መንገድ በመከታተል፣ መረጃውን እያጠሩ ለአገር ደኅንነት ማስጠበቂያ ግብዓት መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን (ዘመነ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ለማንኛውም መረጃ ፈላጊ ክፍት የሆነ መረጃ በጣም ብዙና እጅግ ጠቃሚም ነው፡፡ እነዚህ ሚስጥራዊ የመረጃ መሰብሰቢያ መዋቅሮችና ሚስጥራዊ ያልሆኑ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም፣ ክትትሉንና ትንተናውን በቀጣይነት በመሥራት የአገር ደኅንነትን ለማስጠበቅ በተደራጀ መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ይኼ ደግሞ ለአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መውጣት፣ መተግበርና ማሳደግ ላይ እንደ ዋነኛ ግብዓትና ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡

የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከላይ እንደተገለጸው ሦስቱንም ምንጮች እንደ መነሻ በመውሰድ የፖሊሲው መሠረታዊ ይዘትና አቅጣጫ ይወሰናል፡፡ እስካሁን ድረስ ከተገለጸው ማየት እንደሚቻለው የፖሊሲው ይዘትና ተቀባይነት፣ የአንድ አገር ሕዝብ እንደ መመርያው እንዲጠቀምበት ለማድረግ የአወጣጡ ሒደት ከይዘት ይበልጥ እንደሆን እንጂ ከይዘቱ የማይተናነስ ድርሻ አለው፡፡

በሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል፣ በተለይ ጉዳዩ ያገባናል የሚሉና እውቀትና አስተዋፅኦ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ በተለያዩ ሙያዎች ጥልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራን (የፖለቲካዊ ሳይንቲስቶች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ወታደራዊ ስትራቴጂስቶች፣ የዕድሜና የተሞክሮ ባለፀጋ የሆነ የአገር ሽማግሌዎች፣ የታሪክ ምሁራን፣ የኅብረተሰብ፣ የሃይማኖትና የጎሳ መሪዎች፣ ወዘተ) በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ አስተያየትና ሐሳብ ያላቸው አካላት ፖሊሲው ከመውጣቱ በፊት በስፋት እንዲወያዩበትና ሐሳባቸው በተገቢው መንገድ በፖሊሲው እንዲንፀባረቅ ይገባል፡፡ ይኼ ሒደት ለፖሊሲው የባለቤትነት መንፈስ ከመፍጠሩም በላይ ሲጽድቅም እንደ መሠረታዊ የአገር አስተዳደር ፖሊሲ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተቀባይነትና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡

ከላይ በተገለጸው መንገድ የሚወጣ ፖሊሲ አገሪቱ የመረጠችውን የፖለቲካዊ አስተዳደርና የልማት አቅጣጫ በኃይልና በተፅዕኖ ለማስቀየር የሚደረገውን ሙከራ፣ ሁሉንም የመንግሥት (Instruments of Power) ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊ አቅሞችን በመጠቀም አገራዊ አደጋው በመጀመርያ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከልና ለማስቀረት፤ ይኼ ሳይቻል ሲቀር ደግሞ በአነስተኛ አገራዊ ኪሳራ አደጋውን ለመመከት የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ የሚጠቅም ከፍተኛ የአገር አስተዳደር መመርያ ነው፡፡ በመሆኑም አገሮች በአግባቡ ከተጠቀሙበት ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው፡፡

ፖሊሲው ይኼንን አቅጣጫ በግልጽ ካስቀመጠ በኋላም የአፈጻጸም መመርያውንና የፈጻሚ አባላትን የሥራ ድርሻ አከፋፍሎ በመስጠት፣ ተግባር ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፖሊሲው በአስተማማኝ ሁኔታ ተግባር ላይ እንዲውል በፖሊሲ የተቀመጡትን ግቦችና እነዚህ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገው አገራዊ አቅም (የሰው፣ የገንዘብ፣ የማቴሪያል፣ ወዘተ) በጥቅሉ መታሰብ ይኖርበታል፡፡

ይኼ ማለት እያንዳንዱን ግብ ለማሳካት የሚያስችል በጀት መመደብ ማለት ሳይሆን፣ አስቀድሞ በሚደረግ ጥናትና ትንተና በአንድ ወቅት ያለውን የአገሪቱን አቅምና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሊደርስበት የሚችለውን አቅም ታሳቢ በማድረግ፣ አገሪቱ ለማሳካት እያቀደቻቸው ያለችው ግቦች መሠራት የሚችሉ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡ አለበዚያ የሚቀመጡት ግቦች ምኞት ብቻ ይሆናሉ፡፡

2/ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አስተዳደር

ፖሊሲው ከላይ በተገለጸው መንገድ ከወጣ በኋላ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት አገሪቱ ከፍተኛ የሕግ መወሰኛ አካል (ፓርላማ) ቀርቦ ይፀድቃል፡፡ ከዚህ በኋላ የአገሪቱ ከፍተኛ መመርያ ይሆናል፡፡ ይኼ ከሆነ በኋላ እንዴት ተግባር ላይ ይውላል? እንዴት ይተዳደራል (Manage) ይደረጋል? የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይኼ ጉዳይ በተለያዩ የመንግሥት አካላት ቅንጅት የሚሠራ ስለሆነ በመካከላቸው የተስተካከለና ግልጽ በሆነ የሥራ ክፍፍል ላይ የተመሠረተ ቅንጅት እንዲኖር የፖሊሲው መመርያ ያስቀምጣል፡፡

ከዚህ በላይ ግን እንደ አገራችን በሽግግር ላይ ያሉ አገሮች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን ሒደት ከተጠየቁ፣ የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት ሊመጣባቸው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከልም ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ እንደተቀመጠውና የተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባላቸው አገሮች እንደሚታየው፣ ሲቪሉ የፖለቲካ አሠራር የፀጥታ ኃይሎችንና የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይን በተመለከተ በተሟላ ዕውቀትና ሥልጣን እንዲመራው ያስችላል፡፡ ይኼ በመሆኑም በአገራዊ ሰላምና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡

ስለዚህ ፖሊሲው ተግባር ላይ ሲውል እንዴት ይመራል የሚለው የአወጣጡን ያህል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የአገርን ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተግባር ላይ መዋሉን የሚከታተሉ የየራሳቸው ግልጽ የሆነ የሥራ ድርሻ ያላቸው አራት አካላት ይኖራሉ፡፡

* የፓርላማው የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ

* የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ካውንስል፣

* የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት (Secretariat) ፈጻሚ አካላት ናቸው፡፡

ይኼ አወቃወር ከአገር አገር መጠነኛ ልዩነት ያለው ሲሆን፣ በረጅም ጊዜ ልምድ እየዳበረና በተግባር ውጤቱ እያታየ የመጣ የተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የገነቡ አገሮች የሚጠቀሙበት ነው፡፡ በጣም መሠረታዊ ለሆነው የአገር ደኅንነት ጉዳይና ከዚህም ጋር ተዛምዶ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክት አሠራር ነው፡፡

ይኼ በመሆኑ ደግሞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአገር ደኅንነት ጉዳዮችን አስቀድሞ ለማየትና ተገቢውን መፍትሔ (ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ) በመስጠት ሰላምና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ልማት የተመቻቸ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ከላይ የተገለጹትን አካላት አጠቃላይ የሥራ ድርሻቸውን እንይ፡፡

2.1/ የፓርላማ ኮሚቴ

ይኼ አካል እንደሚታወቀው በአገሮች ከፍተኛው የፖሊሲ አውጪ የሆነው አካል ፓርላማ አካል ነው፡፡ በፓርላማው ውስጥ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በተመለከተ በከፍተኛ ደረጃ ለሕግ አውጪው አካል የሚቀርብ ነው፡፡ የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦቹን በጥልቅ ጥናትና ከአገሮች ሁኔታ ጋር የተዛመደ አማራጮችን በመተንተን፣ የውሳኔ ሐሳቡን ለፓርላማው በማቅረብ ፓርላማውን ያማክራል፡፡ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላም አፈጻጸሙን ከሌሎች በተዋረድ ካሉ አካላት ጋር በመገናኘት ይከታተላል፣ ውጤቱንም ለፓርላማው ያቀርባል፡፡

ይኼ አካል የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲወጣም የፖሊሲውን ጠቀሜታና የሚያስገኘውን ውጤት በሚገባ በመረዳት አማራጭ ሐሳቦችም ለማቅረብ ሆነ አንዳንድ የሚቀርቡ አማራጮችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ውድቅ በማድረግ፣ ፖሊሲው ተግባር ላይ ሲውልም አፈጻጸሙን ለመቆጣጠር አባላቱ በጉዳዩ ላይ እውቀትና ልምድ ያላቸው ቢሆኑ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ከዚህ ጋርም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀትና ልምድ ያላቸው ሰዎች (ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር) በመጠቀም ዕውቀትና ልምዳቸውን በቀጣይነት ማሳደግና ለአገር ጥቅም ማዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፖሊሲውን አተገባበር በተመለከተ ከፈጻሚ አካላት ጋር ሥርዓት ባለው መንገድ እየተገናኙ መከታተል ይጠበቅበታል፡፡ ወቅቱን ጠብቆ ፖሊሲው መታየት ካለበትም (እንዲሻሻል፣ እንዲጎለብት፣ አስቀድመው ያልታዩ ጉዳዮች እንዲካተቱ ወይም እንዲወጡ) መመርያ ይሰጣል፡፡

2.2/ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ካውንስል

ይኼ አካል የሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት ቅርንጫፍ አካል ሆኖ፣ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ በፖሊሲው መሠረት እየተፈጸመ መሆኑን እየተከታተለ የአፈጻጸም ውሳኔዎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚወስን አካል ነው፡፡ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባር ላይ ሲውል የብዙ የመንግሥት አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ከእነዚህ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካላት ተውጣጥቶ ይመሠረታል፡፡

የእነዚህ አካላት የበላይ ኃላፊና በአገራችን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትርና የሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የበላይ ኃላፊ ስለሆነ የካውንስሉ ሊቀመንበር በመሆን ይመራዋል፡፡ ሌሎች የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አባላትም አባል ይሆናሉ፡፡

በብዙ አገሮች ከዚህ አባልነት የማይቀየሩት የመንግሥት አካላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ፕሬዚዳንት (እንደ አገሪቱ የመንግሥት አወቃቀር) በሊቀመንበርነት ይመሩትና ከዚህ በተጨማሪ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም፣ የደኅንነት ኃላፊ፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የአገር ውስጥ አስተዳደር ሚኒስትር፣ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ካውንስል ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ በብዙ አገሮች የዚህ ተቋም አባላት ይሆናሉ፡፡

ሆኖም መንግሥት እንደ ጉዳዩ ሁኔታ ተጨማሪ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን በጊዜያዊነት ሆነ በቋሚነት የካውንስል አባል ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ የዚህ አካል የሥራ ድርሻ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያዛመደ ተግባር ላይ የሚውልበትን አቅጣጫዎችና ከአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ሥራ አንፃር አገሪቱ ልታስመዘግባቸው የሚገቡ ግቦች ያስቀምጣል፡፡

እነዚህ የሥራ መደቦች ለፈጻሚ አካላት በማከፋፈል ይሰጣሉ፡፡ በመካከላቸው ያለውን ቅንጅት ይወስናል፡፡ መደበኛ የሆነ የስብሰባ ፕሮግራም ይኖረዋል፡፡ በዚህ መደበኛ የስብሰባ ፕሮግራሙ የሥራ መደቦችን ያወጣል፣ የአፈጻጸም አቅጣጫቸውን ይወስናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ብለው የወጡ የሥራ ዕቅዶችን የአፈጻጸም ሪፖርት ይሰማል፣ ውጤታቸውን ይገመግማል፣ መስተካከል ወይም መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ መመርያ ይሰጣል፡፡

የዚህ አካል አባላት በቀጥታ የሚመሩዋቸው ቋሚ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አላቸው፡፡ ስለዚህ ቋሚ ሥራቸው የተመደቡበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ የካውንስሉ አባልነት ሥራቸው በተደራቢነት የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ይኼ በመሆኑም የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ሥራውን፣ አፈጻጸምና ሌሎች ጉዳዮችን የሚከታተል ቋሚ አካል ይቋቋማል፡፡ ይኼ አካል በተለምዶ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት (Secretariat) እየተባለ ይጠራል፡፡

2.3/ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት

ይኼ አካል በቋሚነት የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ተጠሪነቱ ለአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ካውንስል በተለይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ካውንስሉ በየጊዜው እየተሰበሰበ ውሳኔዎችን እየወሰነ ሥራዎችን የሚከታተል አካል ሲሆን፣ ጽሕፈት ቤቱ ግን የካውንስሉን ውሳኔዎች ተግባር ላይ መዋላቸውን በመከታተል ለካውንስሉ ሪፖርት የሚያደርግ ነው፡፡

ይኼ አካል ከተለያዩ አካላት የሚያገኘውን መረጃና የሥራ ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ከአገር ደኅንነትና ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንፃር ጥልቅ ጥናትና ከዚህ ጥናትና ምርምር የሚመነጩ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦችን ለውሳኔ የሚያቀርብ አካል ነው፡፡ ይኼንን ሥራውን በተገቢው መንገድ ለመፈጸም የተለያዩ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች (Experts) በውስጡ ይይዛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የታሪክ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የውድድርና የደኅንነት፣ ወዘተ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲኖሩት ይፈለጋል፡፡ ከአገር ደኅንነት አንፃር የሚያገኙት መረጃዎች በግልጽ ለሕዝብ ከፍት ከሆኑ ምንጮችና ለሕዝብ ክፍት ካልሆኑ የመረጃና የዲፕሎማቲክ ምንጮች የሚገኙትን በማሰባሰብና በመተንተን፣ ከዚህ የሚመነጭ አማራጭ ቢሆኖችንና የዕቅድ መነሻ ሐሳቦችን ለካውንስሉ ያቀርባል፡፡

ካውንስሉ ውሳኔ ከወሰነ በኋላ ደግሞ የውሳኔውን አፈጻጸም ከፈጻሚ አካላት ጋር ካውንስሉን በመወከል በቀጥታ እየተገናኘ የሥራውን አፈጻጸም ይከታተላል፡፡ ወቅቱን ጠብቆም ከፈጻሚ አካላት የሰበሰውን የሥራ ሪፖርት ለካውንስሉ ያቀርባል፡፡ ሪፖርቱን መነሻ በማድረግም የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ተከታትሎ ያስፈጽማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሒደት ጊዜውን ጠብቆ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ውስጥ መታየት ያለባቸው የፖሊሲ ጉዳዮች ካሉ፣ እነዚህ ተመልሰው የሚታዩበትን ፕሮግራም ይነድፋል፡፡ በካውንስሉ ውሳኔ ሲሰጥበት ተግባራዊ እንቅስቃሴውን ይከታተላል፡፡ ይኼ በፈረንጆቹ አጠራር (Policy Review) የሚባለው ሥራ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በግልጽ እንደሚታየው ይኼ አካል የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ከሚቋቋሙት የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ውስጥ ዋናው የጥናት ምርምር ትንተና ሥራ የሚሠራበት የተለያዩ ቢሆኖች (Scenarios) የሚቀርቡበት፣ ከእነዚህ በመነሳትም አማራጭ የውሳኔ ሐሳቦች ተተንትነው (ጥንካሬያቸው፣ ድክመታቸው፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋት ወይም ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው፣ የሰው፣ የማቴርያልና የገንዘብ ፍላጎቶቻቸው፣ የአፈጻጸም አቅጣጫቸውና የተለያዩ አካላት ቅንጅት፣ ወዘተ) የሚታይበትና የሚተነተንበት አካል ነው፡፡ በመሆኑም የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ጭንቅላት ነው፡፡ የዚህን አካል መኖርና ሥራውን በተገቢው መንገድ መሥራትና አለመሥራት አጠቃላይ የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ሥራ ላይ ማዋልና አለመዋልን ይወስናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ይኼ አጠቃላይ አሠራር ሌሎች ከፍተኛ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንደኛው ዋናው የአገር ደኅንነትን የውሳኔ አሰጣጥ ከጠቅላላው የአገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊና ፀጥታዊ ሁኔታዎች ጋር በአግባቡ ተገናዝቦ እንዲወሰን ያስችላል፡፡ ይኼ በመሆኑም በተለምዶ በተወሰኑ የፀጥታ ኃይሎችና በጥቂት የመንግሥት ኃላፊዎች ብቻ ይከናወን የነበረ ጉዳይ በሰፊው ተመክሮበት ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ይሆናል፡፡

ከዚህ አልፎም በተለምዶ የአገር ደኅንነት ጉዳይ በፀጥታ ኃይሎች (መከላከያ፣ ደኅንነት) ብቻ ይያዝ የነበረው አሠራር፣ በዚህ ሳቢያ በኃይል ለመፍታት የሚያዘንብሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች አስቀርቶ ሁሉም የመንግሥት አቅም (Instruments of Power) አቀናጅቶ በመጠቀም፣ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚችልበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ የሲቪል ባለሥልጣናት የፀጥታውን ኃይሎች በብቃትና በሙሉ እምነት እንዲመሩና እንዲያዙ ያስችላቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአገር ደኅንነት ጉዳይ እጅግ መሠረታዊና በከፍተኛ ደረጃ እየተመከረበት መመራት ያለበት ሥራ ስለሆነ፣ (የአንድ መንግሥት የመኖሩ ምክንያትም ይኼው በመሆኑ)  ለዚህ የሚመጥን አሠራር እንዲኖር ያስችላል፡፡ ይኼ በቅጡ የተደራጀና በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራ ሥራ ስለሆነ ለአንዳንድ ፈጻሚ አካላት ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡

በተለምዶ የሚሠራው ግን የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ሥራን ለአገር ለመከላከያ ወይም ለደኅንነት ወይም ደግሞ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ይሆናል፡፡ ይኼ አካሄድ ተፈላጊውን ብቃት ያለውና የሥራውን ክብደትና ውስብስብነት ያገናዘበ አመራር ለመስጠት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አንድ ወይም ሌላ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ያጋደለ ውሳኔ እንዲሰጥና ሥራውም በዚህ እንዲቃኝ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይኼ አገሪቱን ይጎዳል፡፡

ይኼ ሁኔታ ከተከሰተ ብዙውን ጊዜ ይኼንን ሥራ የሚወስዱት የፀጥታ አካላት ስለሚሆኑ (መከላከያ፣ ደኅንነት) የእነዚህ አካላት ጡንቻና በአገር መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ይበረታል፡፡ ይኼ አሉታዊ ተፅዕኖ ቀስ በቀስ በሽግግር ወቅት የሚካሄደውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ኢኮናሚያዊ ልማት መሠረት የሆነውን ሰላምና መረጋጋትን ይሸረሽራል፡፡ ይኼ ተፈላጊ ውጤት አይደለም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በትክክል ሁሉም የሥራ ክፍሎች ሥራቸውን እየሠሩ ሲዘረዘር እንደቆየው ከተሠራ ደግሞ፣ ለሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅኦ በማበርከት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

2.4/ ፈጻሚ አካላት

በዚህ በአገር ደኅንነትና በውጭ ጉዳይ የሥራ ተዋረድ ቀጥለው የሚመጡት ፈጻሚ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ የመንግሥት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወይም በዚህ ደረጃ የተዋቀሩ መዋቅሮች ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም እንደ አገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን አወቃቀር ለፕሬዚዳንቱ ይሆናል፡፡ ከአገር ደኅንነትና ለውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ጋር በአገር ደኅንነትና ከውጭ ጉዳይ ካውንስል የወጡ ዕቅዶችና የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመፈጸምና ካውንስሉን በመወከል ላይ የተመሠረት የጠበቀ የሥራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ከዚህ በዘለለም በአጠቃላይ በአገር ደኅንነትና በውጭ ጉዳይ ላይ የመረጃ ልውውጥና ሰፋ ያለ ምክክር እንዲኖር ሥራው ራሱ ያስገድዳል፡፡

 ስለዚህ ለዚህ የሚመጥን የሥራ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች መንግሥት አስፈላጊ ናቸው ብሎ በማመኑ የሚያቋቁማቸው አካላት በሕግ የተደነገገ ሥራና ኃላፊነቶቻቸውን፣ የሥራ ድርሻቸውንና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚገልጽ አዋጆችና መመርያዎች ይኖራሉ፡፡ ስለሆነም ፈጻሚ አካላቱ ሥራቸውንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሕጉ መሠረት ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

3/ ማጠቃለያ

የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንድ መንግሥት አገር ለማስተዳደር ከሚጠቀምባቸው የፖሊሲ መመርያዎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ለመንግሥት መፈጠር ዋነኛ የሆነውን የአገር ደኅንነት የማስጠበቅን ሥራ በምን መመርያና ይኼንን የፖሊሲ መመርያ እንዴት ተግባር ላይ እንደሚያውለው የሚገልጽ ነው፡፡ ይኼ የአገርን ደኅንነት የማስጠበቅና የአገርን ጥቅም በየጊዜው እያሳደጉ የመሄድ እጅግ የተወሳሰበ ሥራ ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ አመራር ይጠይቃል፡፡ ይኼንን ለመምራት የሚጠቀመው ፖሊሲውን በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎና የሕዝብ አመኔታ ቢወጣ ይመረጣል፡፡ ቀጥሎም እጅግ የተቀናጀና በዕውቀት የሚመራ አመራር እየመራው ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡

ይኼ ከሆነ ከፍተኛ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር በማስቻል ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡ በመሠረታዊው የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ሰፊ መግባባት ተፈጥሮ አገራችንን ወደ ረጅም ዕድሜ የሚኖረው ሰላም፣ ይኼንን ተንተርሶ ወደሚመጣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ለማሸጋገር ከፍተኛ ጠቀሜታ ካላቸው የአገር አስተዳደር ፖሊሲዎች ዋነኛው ይሆናል፡፡

መንግሥት አሁን በሥራ ላይ ያለውን የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደገና ለማየት ውይይት መጀመሩ ትክክለኛና የሚደገፍ ሥራ ነው፡፡ ግን ደግሞ ፈራ ተባ እያለ ከሚገባበት በድፍረት ገብቶበት በአገር ደረጃ የሚፈለገውን ውጤት ማለትም ሰፊ አገራዊ ድጋፍና ተቀባይነት ያለው ፖሊሲ እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ በጥቂት የመንግሥት ወይም የፓርቲ ባለሥልጣናት ብቻ ታጥሮ የአንድን ፓርቲ አመለካከትና ፍላጎት ብቻ የሚያንፀባርቅ የአገራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጠቀሜታውና ዕድሜው አጭር ይሆናል፡፡

በተለይ ደግሞ አሁን በአገራችን ያለውን የጊዜያዊ አዋጅ በብቃት አልፈን ካለው የፖለቲካ መደነባበርና የአገር ደኅንነት ሥጋት ለመወጣት ካለው ጠቀሜታ አንፃር ሲታይ ይኼንን ሒደት መጀመር፣ በአገር ደኅንነት ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ መግባባት ላይ ለመድረስና የበለጠ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል እላለሁ፡፡

***********

ተዛማጅ:- የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች (ሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ)

Guest Author

more recommended stories