በስራ ላይ ያለው የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በቀይ ባህር ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጲያ ያላቸውን አንድምታ ታሳቢ ያላደረገ እና ችግር ያለበት ነው በማለት ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣኤ ተቹ።

የቀድሞው የሀገር መከላከያ ኤታማጆር ሹም ጻድቃን ገብረትንሣኤ ይህን የተናገሩት ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በቅርቡ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው። ጋዜጣው የጻድቃንን አስተያየቶች በከፊል ያላቀረባቸው ቢሆንም፤ ሆርን አፌይርስ ሙሉ የድምጽ ቅጂው ደርሶታል።

ጄኔራል ጻድቃን ‹‹ኢትዮጲያ ትልቅ ሀገር ነው። በቀይ ባህር የሚደረገው ሁሉ ያሳስበናል። እኛ የቀይ ባህር ሀገር ነን። ከቀይባህር የተነጠልን እንድንሆን መፍቀድ የለብንም።….በኤርትራ ሳቢነት  ሆነ  በራሳቸው በቀይ ባህር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ሀይሎች አሉ። ቀይ ባህር  እኛን እና  የባህረ ሰላጤው ሀገራትን የሚለይ ባህር ነው። ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው። የኛ የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዚህ ረገድ ውጤታማ ነው ብዬ አላስብም። እንደገና መታየት ያለበት ትልቅ ነገር አለ›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጲያን መልሶ የቀይ ባህር ሀይል ማድረግ የፖሊሲው ግብ ሊሆን እንደሚገባ የጠቆሙት ጻድቃን፤ ‹‹ይህ ማለት የግድ ወሮ በመያዝ ላይሆን ይችላል….ካለን የሕዝብ ብዛት፣ ለባህሩ ካለን ቅርበት፣ ከኢኮኖሚያችን እድገት አንጻር፤  ሌሎች ለዝንተ-ዓለም ቀይ ባህር የማንጠጋበት ሁኔታ እየፈጠሩ ባሉበት ሁኔታ ዝም ብለን ማየት የለብንም›› ብለዋል።

‹‹ይሄ ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ለመንቀል አስቸጋሪ የሆነ  ነቀርሳ እየተተከለ ያለ ነው የሚመስለኝ›› በማለት፤ ከዚህ አንጻር ነባሩ ፖሊሲ ‹‹ትልቅ ችግር ያለበት ነው›› በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ በሁለቱ ህዝቦች መሀል ካለው ጥብቅና ረጅም ትስስር አንጻር የሁለቱ ሀገራ ግንኙነት በቅርብ ገዜ ወደጥሩ ሁኔታ እንደሚመለስ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቡድን ስልጣን ላይ እያለ ይህ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁም አስምረውበታል። ከጦርነቱ በፊት የኢትዮጲያ መንግስት ለኤርትራ ‹‹የተመቸ›› እንደነበር ከዚያም በኋላ እስካሁን ለኤርትራ ‹‹ክፉ የማያስብ›› እንደሆነ በመጥቀስ በዚህ ሁኔታ ሰላምን ያልፈለገ ቡድን ወደፊትም ተስፋ እንደሌለው ገልጸዋል።

የመንግስት የውጭ ግንኙነት ስልት ኤርትራን በመነጠል ረገድ ተሳክቶለት የነበረ ቢሆንም በቅርብ ዓመታት የኢሳያስ መንግስት ወደባህረ ሰላጤው(Gulf) አረብ ሀገራት  በመጠጋትና ቤዝ በመስጠት  የኢኮኖሚና የደህንነት መሻሻል እያገኘ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጲያ ፖሊሲ ማጠንጠኛ የኢትዮጲያ እና የኤርትራ ህዝቦችን ወዳጅነት  በማጠናከር ላይ ያተኮረ እና የሻዕቢያ እድሜ በተቻለ ፍጥነት ማሳጠር መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።  ይህ በተለያየ መንገድ ሊተገበር እንደሚችል – ሻዕቢያ አካባቢውን የረጅም ግዜ አደጋ ውስጥ እየከተተ ከመሆኑ አንጻር – ካስፈለገ ከኤርትራ ተቃዋሚዎች ጋር በመተባበር በሀይል የማስወገድ አማራጭ ሊታይ ይገባል ብለዋል ጄኔራል ጻድቃን።

‹‹ይሄ እንደምናገረው ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል›› ያሉት ጻድቃን፤ አቅጣጫው በፖሊሲ ደረጃ ተይዞ በየደረጃው እየተገመገመ ሊኬድበት እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኢትዮጲያ መንግስት ኤርትራን አስመልክቶ ያለውን ፖሊሲ ስለመከለስ እየመከረ ከሆኑ ተያይዞ፤ ጻድቃን የፖሊሲ ክለሳው ግን በኤርትራ ብቻ ጠቦ መታየት እንደሌለበት አሳስበዋል። አጠቃላይ የብሔራዊ ደህንንትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክለሳ ተደርጎ በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ የኤርትራም ጉዳይ ቢከለስ  የተሻለ ነው ብለዋል።

እንደጻድቃን አመለካከት በ1993 የወጣው ነባሩ የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከዝግጅቱ ጀምሮ ችግር የነበረበት ነው።

ፖሊሲው ከሕገ-መንግስት ቀጥሎ ከፍተኛ ፋይዳ ካላቸው ሀገራዊ ሰነዶች የሚመደብ ቢሆንም፤ በፖሊሲው ዝግጅት የተለያየ  የሙያ፣ የልምድ እና የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ሀሳብ እንዲሰጡበትና እንዲካተት እንዳልተደረገ አስታውሰዋል። አሁንም ክለሳ የሚደረግ ከሆነ፤ የዝግጅት ሂደቱ ‹‹የፈለገ እውቀት ቢኖራቸውም በጥቂት ሰዎች የሚሰራ መሆን የለበትም፤ ሀሳብ ሊያበረክቱ የሚችሉ ግለሰቦችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ማሳተፍ  አለበት›› በማለት አሳስበዋል።

ጄኔራል ጻድቃን  የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አስተዳደርም መስተካከል እንደሚገባውም ገልጸዋል።

ይህን ሲያብራሩም፤ የፖሊሲውን ትግበራውን የሚቆጣጠርና በበላይነት የሚመራ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጣ አንድ አካል እንደሚያስፈልግ፤ በብዙ ሀገራት ይህ አካል ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት እንደሆነና በዚህ ምክር ቤት ስር ጠንካራ ሴክሬታሪያት መኖር እንዳለበት አውስተዋል፡፡ ሴክሬታሪያቱ በቋሚነት የብሔራዊ ደህንነት መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን ስራ በመስራት ለምክር ቤቱ የሚያቀርብ እና አፈጻጸሙን የሚከታተል ነው እንደሚሆን አብራርተዋል። አክለውም በፓርላም የብሔራዊ ደህንነትን ጉዳይ የሚከታተል ቋሚ እና ለዚህ ተገባር አስፈላጊው አቅም  ያለው ቋሚ ኮሚቴ ያስፈልጋል  ብለዋል።

ነባሩ ፖሊሲ ስለፖሊሲው አስተዳደር ያስቀመጠው ነገር አለመኖሩን አስታውሰው፤ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመ ቢሆንም ለምክር ቤቱ እንደጭንቅላት ሊያገለግል የሚችል የተሟላ ሴክሬታያት አልተደራጀለትም። የምክር ቤቱ ሂደት በአባል አካላት ሪፖርት ላይ የተመሰረተ ብቻ እንጂ፤ ራሱን ችሎ የምክር ቤቱን ውሳኔዎች አፈጻጸም የሚከታተል የሚገመግምና ሪፖርት የሚያደረግበት አሰራር አልተበጀም ብለዋል።

 ይህ ባለመደረጉ ምን ችግር እንደፈጠረ ጥያቄ ቀርቦላቸውም ምላሽ ሰጥተዋል።

‹‹የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሳንዘጋጅ የመጣው፤ የሀገር ደህንነትና የፀጥታ ኣሰራራችን የተደራጀ ስላልነበር፣ በተናጥል የሚመራ ስለነበር ነው›› ያሉት የቀድሞው ኤታማጆር ሹም፤ ይህ የግል አስተያየታቸው ብቻ ሳይሆን በወቅቱ  በተደረገው ግምገማ የተደረሰ  ድምዳሜ ነው ብለዋል።

‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ አሁንም ያለው አሰራር ያው ነው›› በማለት የአደጋ ተጋላጭነቱ መኖሩን አስምረውበታል።

የተጠናከረ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ትንተናና አመራር ቢኖር ኖሮ ባለፈው አመት በሀገሪቱ የተፈጠሩ የፖለቲካና የፀጥታ ቀውሶችን አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበት እድል እንደሚኖር ጠቁመዋል።

ባለፉት 15 ዓመታት የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ በአለም አቀፍ ተቋማት ዲፕሎማቲክ ተሰሚነት፣ በድህነት ቅነሳና መሰረተ-ልማት ስራዎች፣ በኤርትራና በግብጽ አንጻር የተገኙ ውጤቶችን ጄኔራሉ በአዎንታዊ ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ነባሩ ፖሊሲ ስኬታማ ነው ወይም አይደለም ብለው እንዲፈርጁት በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ጥያቄ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ባይቀርብ መርጣለሁ›› ብለው ወደጎን ገፍተውታል።

‹‹ባለፉት አመታት ለታዩ ለውጦች ፖሊሲው አስተዋጽኦ ነበረው። ነገር ግን ሁሉም ለውጦች ከዚያ የመነጩ አይደሉም።  ጥሩ የመጡ ነገሮች አሉ። [በሌላ በኩል ደግሞ] ባለፈው አመት ሀገር የተናወጠበት ችግር ደግሞ ነበር፤ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ነው የቆመው›› በማለት ውጤቱ የተቀላቀለ መሆኑን አስምረውበታል።

‹‹እስካሁን ድረስ ሀገር የሚጠራርግ ችግር ስላልመጣ ፖሊሲው ድል ብቻ ነው የሚባል ከሆነ የአመለካከት ጉዳይ ነው›› ብለዋል።

የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት አለመቻሉ፤ ይህም ውሎ አድሮ የፀጥታ ችግር የሚሆን በመሆኑ እና የውጭ ሀይሎችም እነዚህን ችግሮቻችንን በመጠቀም ችግር እየፈጠሩ መሆኑን እንደ ዋነኛ ስጋት አስቀምጠውታል።

በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እየተጠነሰሱ ያሉ ችግሮች በድምሩ ሲታዩ በቀጣይ አሳሳቢ ክፍተቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

‹‹ሻዕቢያን ተጠቅመው፣ ሕዝብን በመከፋፈል፣ በታጠቀ ሀይል ስልጣን ለመያዝ የሚሞክሩ ሀይሎች ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲ ያመጣሉ ብሎ መጠበቅ›› እንደማይቻል በመግለጽ፤ ‹‹መንግስት ያንን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል›› ብለዋል። 

ይሁን እንጂ የዚያ ዋና ምንጩ ሀገር ውስጥ ያለው  የፖለቲካ ችግር መሆኑን እና ሻዕቢያ ያንን  ለመጠቀም እንደሚሞክር በማስታወስ የውስጥ ችግሮችን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት አስፈላጊነቱን አስምረውበታል።

የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው መነሻ የውስጥ ፖለቲካዊ መረጋጋታችንን በማረጋገጥ እና ሀገራችን በቀጠናው ልትይዝ የሚገባትን ቁመና በማስቀመጥ፤ ያንን መነሻ አድርጎ ከእያንዳንዱ ሀገር ጋር የሚኖረንን ፖሊሲ የሚዘረዝር መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ፤ የኢትዮጲያ መንግስት ቀደም ሲል ይጫወት የነበረው ሚና  ግልጽ ባልሆነ ምክንያት መቀነሱ፤ በሌላ በኩል አሁን የደቡብ ሱዳን ፖለቲካ የሚዘውሩት ሌሎች ሀገራት መሆኑ አስጊ ነው ብለዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ብሔር የሆነው የዲንቃ ልሂቃን ፀረ-ኢትዮጲያ ዝንባሌ እየያዙ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ጅቡቲም የሀያላን ሀገሮች መሰባሰቢያና ፖለቲካ መተግበሪያ እየሆነች መሆኑ በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተጽዕኖ ሳይፈጥር ይቀጥላል የሚለው አጠያያቂ መሆኑን እና በጥብቅ መከታተል እንደሚያሻ መክረዋል።

የግብጽ ጉዳይ ከህዳሴ ግድብ አንጻር ብቻ ተያይዞ መታየት እንደሌለበትም አሳስበዋል። ግድቡ ትልቅ አጀንዳ መሆኑን እና በዚያ ረገድ  ግብጾች – ቢያንስ በይፋዊ መድረኮች ላይ – መለሳለስ እንዲያሳዩ ማድረግ እንደተቻለ ከሚዲያ ሪፖርቶች የተገነዘቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ግብጾች ከኢትዮጲያ ጋር ያላቸው ዝምድና የሚያዩት በባህረ ሰላጤው አካባቢ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና እና በአፍሪካ እንዲኖራቸው ከሚፈልጉት ተጽእኖ አንጻር ነው።  ስለዚህ እኛም በዚያ ስፋት እና ጥልቀት ማየት አለብን  ብለዋል። እኛን የቀይ ባህር ሀገር ከመሆን  የሚነጥል እንቅስቃሴ ከሌሎች ጋር በመቀናጀት የሚሰሩት ስራ መሆኑንና ይህ የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ግንኙነት ስራው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣኤ አስምረውበታል።

********

የጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣኤን ቃለ-ምልልስ የሆርን አፌይርስ ዩቲዩብ አካውንት ላይ ማግኘት ይችላሉ።

ሌሎች የጄኔራል ጻድቃን ጽሑፎችንና ቃለ-ምልሶችን እዚህ ማግኘት ይችላሉ፡፡

Published by Daniel Berhane

Daniel Berhane

6 replies on “ኢትዮጲያን መልሶ የቀይ ባሕር ሀይል የሚያደርግ ፖሊሲ ያስፈልጋል ~ ጻድቃን ገብረትንሳኤ [+Audio]”

 1. የይህ የውይይት መድረክ መፈጠሩ የሚመስለንን ሀገራዊ ጉዳይ አንስተን እንድንወያይ ይረዳናል፤፤ በመሆኑም አብይ አስተዋፅኦ አለው፡፡ አስተያየታችንን መስጠት እንቀጥላለን

 2. What I admire about the General is, that he is calm, try to be objective and pragmatic and mostly, many of the arguments he puts forward, also hold water. Whether I agree or not, I admire people who take some time to make a thought before opening their mouth.
  For me, his suggestion of the revising the policy towards Eritrea in such terms and form, sound a bit coarse. I see there a “non avoidable” risk of getting into a war (most probably as an aggressor) once we go forward. May be the difference lies between us since he was a military General and I am more comfortable with “pacifistic” thoughts.
  Again, I want to emphasize my at most respect for speaking up his mind in such bold but still in a very articulated and well though manner. At this point I also want to include the other veteran college of his (Gen. “Jobe”). Whichever feedbacks you became, keep your thoughts coming Sir’s! Thank you again for not trying to hijack my mind with your “bullshit”! (Sorry for the last (curse) word, but “Fuckup bullshit” will also be not appropriate, even if it was more suitable)

 3. የፖሊሲ መሻሻያ ማድረግ፤ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር መከለስና መፈተሸ ተገቢ ነዉ፡፡ቀጣዩ ፖሊሲ ሀገራችን አሁን የደረሰችበት ሁለንተናዊ አድገት ደረጃ የሚመጥን መሆን አለበት፡፡የሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም እያደገ የሚሄድ እንጂ ቋሚ አይደለም፡፡በብሄራዊ ጥቅማችን ላይ የሚነሱ ስጋቶችም በዚያዉ ልክ እየሰፉ እንደሚሄዱ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ ሃሳቡ የተሰነዘረዉ ከጻድቃን ስለሆነ ብቻ በጭፍን አናጥላለዉ፡፤መልእክቱን ነዉ ማዬት ያለብን፡፡

 4. Good points from the ‘General’.if the government is ready to listen. Except the government is in deep sleep.

  My objections are on the points he raised on Ethio-eritrea war. It is unacceptable to blame on a policy. It was his and colleagues incompetence puts us to war, not lack of information or policy. It was also noteworthy the military under his leadership using medeival military tactics costed us nearly hundred thousand young beautiful ethiopian lifes for nothing. The same was true for our Eritrean brothers in the other side of the boarder.

  Peace

 5. አስተያየታቸው ሙሉ ተቀባይነት አለው። ይሁን እንጂ አገራችን በአፍሪካ ቀንድም ይሁን በባህረ ሰላጤው ያላት/ሊኖራት የሚገባው ግንኘነት ወይም የአረብ አገራትን ከእኛ አንፃር ስናይ ጨለምተኛ መሆን ያለፈበት አካሄድ ነው። ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ እና የተለያዩ ሃይማኖቶች ያሉባት አገር ነች። የኽንን የሚያንፀባርቅ የፖሊሲ አቋም ያስፈልገናል።

  ፖሊሲው ከተዘጋጀበት ጊዜ አንፃር ሲታይ አሁን አለም ባለችበት ሁኔታ መሰረት መቅረፅ ያስፈልጋል፣ አሁን አለም ቋሚ የሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ስላለች ፖሊሲዎችን እንደየአስፈላጊነቱ የሚቀርጽ አካል መኖር አለበት። ይሁን እንጂ ኤርትራን በሚመለከት የኃይል እርምጃ አሃሳባችን ማረቅ እንዳለብን መስማማት ይኖርብናል። አሁን በስራ ላይ ያለው ፖሊሲ ውጤታማ በሆነ መልኩ መከለስ የሚችልበት አቋም አለው፣ ዋና ዋና መርሖቹ አሁንም ቢሆን ገዥ ናቸው። ስለሆነም ዋና ፈፃሚ አካልን ማዕከል ያደረገ የክለሳ ሂደት በሁሉም አህጉራት፣ ሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት መስመሮች፣ ቢዝነስና ዲያስፖራ እና የምርምር ተቋማት ግንኙነት ቀጣይነት ባለው መልኩ መደረግ አለበት። ለዚህ ጥቅም ላይ የሚውሉ መረጃዎች ደግሞ ከየሚሲዮናችን መሰብሰብ ይኖርባቸዋል ቀጥሎም በፈፃሚው አካል እንዲኁም ከየሴክተሩ በተዋቀረ ኮሚቴ መተንተን ይኖርባቸዋል።

Comments are closed.