ካፒታሊዝምን ጨርሰን ሳንገነባ ካፒታሊስቱ በዛ

(ይደነቅ ስሙ)

ይህን አባባል በአንድ አጋጣሚ ከኔ በተሻለ እርከን የሚገኙና የማከብራቸው ሰው ሲናገሩት ውስጤን ቢኮረኩረው ርእስ አደረግሁት፡፡ ከዚህ አባባል ውጪ ያለው አስተሳሰብም ሆነ ትችት የግሌ ነውና የሀሳብ ባለቤትነት መብቴ ይጠበቅልኝ፡፡

ሀገራችን ባለፉት ኃያ ስድስት ዓመታት ራሱን በራሱ እያሳደገና ተፈጥሯዊ በሆነ ክስመት ወደ ተሻለ የማህበረሰብ እድገትና ርእዮተ ዓለም የሚያድግ አብዮት በመከተል እነሆ ከደረሰችበት ደርሳለች፡፡

ተበተነች ሲሉ ስትጠናከር፤ ተጠፋፉ ሲሉ ህዝቦቿ ከምንም በላይ ሀገራዊ ክብራቸውን በየውበቶቻቸው ህብረ ብሔራዊነት እያደመቁ የተሻለውን ለነገ እየሰነቁ ጋሬጣ መስሎ የታያቸውን እየነቀሱ በገባቸው ልክና አግባብ ልክም ይሁን ከመንገድ የወጣ ብቻ በተገነዘቡት ልክ ትግል እያደረጉ እዚህ ደርሰዋል፡፡

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለም በህዝቦች ምሉዕ ተሳትፎ እውን የሚሆን ፈጣን ለውጥ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ቀዬ የማምጣት ኃላፊነቱን ለራሱ ለህዝቡና ለመስተዳድሮቹ በመስጠት በጋራ በሚኖረን ፈርጣማ የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ክንድ በቀጠናው ጎልተን በመውጣት አንድ እየሆነ ካለው ዓለም የኑሮ ገበያ መወዳደር የሚያስችል እድልን የማጎናጸፍ ዓላማ የያዘ ነው፡፡

ከዚህም በላይ በፍጥነትና ሁሉንም ህዝብ እኩል በሚያሳትፍ ልማት ጉዞ እያንዳንዱ ህዝብ ባደረገው ርብርብ ልክ ተጠቃሚ የሚሆንበት እድልንና በዚሁ ደረጃ የሚገኝ ንቃትን የመጎናጸፍ መብትንም ሳይገድብ በሁሉም የህግ አግባቦች ያረጋገጠበት ሁኔታ የፈጠረው መተማመን ቀላል አይደለም፡፡

ነገሩ የተፈጠረውን መተማመን በጠለቀ አስተሳሳብ ተረድቶ መተግበር፤ ሁኔታዎች ያስገኙትን ድል ብቻ በማሞገስ ከመኖር ባሻገር ለላቀ ድልና አቅም የመረባረብ፤ ሁሉንም አቅሞች አሟጦ የማወቅና በታወቀው ልክ አቅምን /የኢኮኖሚ፤የፖለቲካና የማህበራዊ ልማት አቅም/ የመጠቀም፤ ከዚህም የሚገኘውን ትርፍ በቅድሚያ ያስገኘውና ባለቤት የሆነው ህዝብና ዜጋ የትሩፋቱ ተቋዳሽ እንዲሆን የማድረግ ንቃተ ህሊናን በራስ ጥረት የመጎናጸፍ እድልን የሰጠ ነው፡፡

ይሁንና የሆነው እንደዚህ አይደለም፡፡ ከህዝቡ ቀድመው የነቁት ከነሱ ቀድመው በነቁት ሃሳባቸውም እድላቸውም ሲነጠቅ በወቅቱ ሳይሆን ጉዳዩ ከጎመራ በኋላ የደረስንበት ይመስለኛል፡፡

አጋነንከው አትበሉኝና ሀገራችን በምንላት ሀገር ውስጥ እኩል እየኖርን ለምን አንዳችን እድሎቻችንን በአንክሮ ማየት እንደተሳነን፤ ማየት ብቻም ሳይሆን ባየነው ልክ ለጥቅማችን ማዋል እንዳቃተንና ራሳችንን የበይ ተመልካች እንዳደረግን ይገርመኛል፡፡

እንቶኔ አሊያም እከሌ እንዲህ እንድንሆን ፈረደብን ብዬ የምወቅስው ህዝብ የለኝም፡፡ አይኖርምም፡፡ የእከሌ ወገን ግለሰብም ብዬ ለማለት አልደፍርም፡፡ ራሴን በራሴ እንዳስተዳድር ተከልሎ በተሰጠኝ ቀዬ ደባ ሲፈጸም ተወቃሹ የቄው አባወራ ነኝ ባይ ነኝ፡፡

የዚህ ተወቃሹ ማንም አይደለም፡፡ አስኳላ የደፈነው፤ ከአስኳላ ባገኘው ንቃት ልክ ሰልጣን የጨበጠው፤ በጨበጠው ስልጣን የያዘውን ርእዮት በአግባቡ መተግበር ያቃተው፤ ከአብራኩ ከተገኘው ህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሱና የመሰሎቹ ደላሎች ጥቅም ቀድሞ የታየው፤ የአባቱ ቀዬና የራሱም አንጡራ ለራሱም ለወገኑም ሳይሆን ለጥገኞችና በአቋራጭ ህጉም ሀቅም ሳይፈቅድላቸው ለመበልጸግ ለሚተጉት ሲጠነፈፍ ጆሮ ዳባ ያለው እሱ ነው፡፡

አዎ በታሪክም በትውልድም ተወቃሹ እሱ ነው፡፡ የወላድ መካን የሆነች ሀገርና ወገን ያሰኘን እሱ ነውና፡፡

እንዲሁ በደፈናው እርግማን አላድርገውና አንዳንድ ማሳያዎችን ልጠቁም፡፡

አሁን በዚያ ሰሞን የኢኮኖሚ አብዮትን እንደ አንድ አማራጭ አድርጎ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሲያውጅ በደላሎችና በጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች በሱ ላይ የታወጀው አዋጅ መቼም ስፍር ቁጥር አልነበረም፡፡

እውነትና ንጋት እያደር…. እንዲሉ ክልሉ በውስጡ ያያዛቸውን የኢንቨስትመንት ተቋማት ወይም ፕሮጀክቶች ቆጠራ ሲያካሂድ በዞንና በከተማ ደረጃ ብቻ ከ750 በላይ የሚሆኑት የኢንቨስትመንት ተቋማት በ460 ሄክታር መሬት ላይ ለረጅም አመታት ምንም እሴት ለመጨመር መሻት ሳያሳዩ ሳር እየሸጡ መኖርን ባህል አድርገው በህዝብ ላይ ሲቀልዱ የኖሩ መሆናቸው ተጋለጠ፡፡

የጩኸቱ ዋና ነጋሪት መቺዎችም እነዚህ ናቸው፡፡

እነዚህ እንግዲህ አብዮታዊ ዴሞክራሲያችን ጎልብቶና አእላፍ ባለሀብቶችን አፍርቶ ወደካፒታሊዝም ሳይሸጋገር ቀድመው የተፈጠሩ ካፒታሊስቶች መሆናቸው ይያዝልኝ፡፡

በግንባታው ዘርፍ የሚሰማሩት ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች የዚሁ ህዝብ አብራክ የወለዳቸው የደሀ ሀገር ምሁራንና የወደፊት ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ለነገሩማ በድህነት ውስጥ ላለ ህዝብኮ የትውልዱ ምሁራን መስዋእት ከፋዮች ነበሩ፡፡ በላባቸው፤ በእውቀታቸውና እልፍ ሲልም በደማቸው የህዝባቸውን ብልጽግና አረጋግጠው ለማለፍ የማሉ፤ ከኔ በፊት ሀገሬና ህዝቤ ብለው በሀቅ ያለ እንቅልፍ የሚሰሩ፤ የተሰማሩበትን መስክ ጥራትና ብቃት አስጠብቀው ከህዝብ የጀግና ኒሻን ለመሸለም የሚጥሩ መሆን ነበረባቸው፡፡

ያለመታደል ሆኖ የኛዎቹ አብዛኞቹ፤ በጣም አብዛኞቹ ከደሃው ገበሬ ዓይን ስር ፕሮጀክት የሚሰርቁ፤ እሰይ ሊያልፍልኝ ነው ብሎ ሲል ተስፋውን ለዓመታት እንዲራዘምና እንዲቆዝም የሚያደርጉ እኩይ ምሁራንና ባለሀብቶች፡፡

አንድ የዘርፉ ሰው በቁጭት ሲናገሩ እንደሰማሁት እነዚህ ዜጎች ታዲያ የፕሮጀክት መወዳደሪያ ሲያቀርቡ ለማንኛውም ግንባታ ከመሬት ስርና በላይ ያለውን የግንባታ ክፍል የታችኛውን ከፍ አድርገው ከመሬት በላይ ያለውን ከገበያው በወረደ ዋጋ ያቀርቡና ያሸንፋሉ፡፡

የመሬት ስር ግንባታ አዋጭ መሆኑም በመስኩ ባለሞያዎች የተመሰከረ ነው፡፡ ታዲያ የመሬት ስር ግንባታውን 30 ከመቶ ቅድሚያ ይወስዱና መሬቱን ቆፍረው፤ ዲንጋይና አሸዋ በመጠኑ አራግፈው ሌላ ግዳይ ለመጣል እብስ ነው፡፡ ህዝብና መንግስትን ለወጪም ለቁጭትም ጥለው ሌላ ምንተፋ ይገባሉ፡፡ እነዚህም ካፒታሊዝምን ሳንገነባ ካፒታሊስት የሆኑ የደሃ ህዝብ ኪስ አውላቂዎች መሆናቸው ነው፡፡

ከነዚህ የሚንጠባጠበውን ለቃቅሞ የሚኖረው ባለስልጣንም ቤት ይቁጠረው፡፡

ሌላ ማሳያ ደግሞ ላክል፡፡

የማእድን ፍለጋ ፈቃድ የሚሰጠው እስካሁን ባለው አሰራር ፌዴራሉ አካል ነው አሉ፡፡ ለነገሩ ከ85000 ሜትር ኪዩብ በላይ አሸዋም ለመዛቅ ፈቃድ የሚሰጠው እሱ ነው፡፡

የሚገርመው አፈር ለመዛቅ ሰልጣን መስጠት የነበረበት ለአፈሩ ቅርብ ሆነው መስተዳደር ነበር፡፡ ከፍተቱ ሆን ተብሎ የተደረገ የሚያስመስለው ደግሞ እነዚህ አካላት ግብር የሚጥሉት አፈሩን ለዛቁበት ክልል ወይም ከተማ ሳይሆን መኖሪያቸው ላለበት ከተማ ወይም የመንግስት አካል መሆኑ ነው፡፡

ለነገሩኮ አብዛኞቹ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንቶች መስሪያቸው እዚህ ማደሪያቸውና ግብራቸው እዚያ ነው፡፡

ታዲያ እነዚህ ቀድመው የነቁ ምሁራንና ባለሃብቶች የሆነ ጥግ ፈልገው የማእድን ፍለጋ ፈቃድ ያወጡና በተፈቀደላቸው በሳምንቱ ናሙናውን ወደ ዱባይ ወይም ወደ አውሮፓ ማሾለክ ይጀምራሉ አሉ፡፡ ከዚያ ወዲያማ ማን ባለፓጃሮ ማን ባለ ራቫ ፎር ማን ባለ ብዙ አፓርታማ እንደነሱ፡፡

እዚሁ ቅርባችን ሰላሌ ውስጥ አንድ የከበረ ማእድን ቢገኝ እነዚህ ጮሌዎች ማእድኑን አውጥተው፤ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ሰርተው፤ በድብቅ ከሀገር ለማስወጣት ሲጥሩ በቆራጥ ጥቂት የወቅቱ ካቢኔዎቻችን ትግል በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ስሰማ ጆሮ ለባለቤቱ እንዲሉ ሆኖ እንጂ ለካ ህዝቤ እየታረደ ነበር አልኩኝ፡፡

የሩቁን ትቼ አሁን ከሰሞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ካቆሙ አስር ዓመትና ከዚያም በላይ ያስቆጠሩ፤ ቃሪያና ሳር የሚሸጡ የአበባ ኢንቨስትመንት ተብዬ ቦታዎችን ቆጥሮ የማስመለስ ህጋዊ ተግባር በተጀመረበት እዚሁ መሀል ሀገር ከሰበታ ወረድ ብሎ ተፍኪ የሚባል ቦታ ላይ ያለ ጎልደን ሮዝ የሚባል የአበባ እርሻ ተይዞ የነበረ 26 ሄክታር መሬት ውል የማቋረጥ ስራ መጀመሩን የሰማው ባለቤት ነኝ ባይ ግለሰብ ፋይሎቹን ይዞ በየባለስልጣናቱ በር ላይ እዬዬ ማለት መጀመሩን ሰማሁ፡፡

ታዲያ የዞኑ ትልቅ ሰውም ለአካባቢው ህዝብና ተቀጥረውበት መስራት ሲችሉ ሜዳ ላይ ለፈሱት የአርሶ አደር ልጆች ስራ ባለመፍጠሩ መቆጨት ትተው….የአዞ እንባ ላነባው ጥገኛ፤ ከኋላው ያሰለፋቸውን ትላልቅ መሳይ ቀላሎች መተማመኑን ፈርተው አሊያም ጭራ ቆልተው፤ ከባንክ የተበደረው ገንዘብ ብዙ በመሆኑና ከሰሞኑ ስራ ለመጀመር ቃል ስለገባ ተዉት ብለው አማላጅ መሄድ ጀመሩ አሉ፡፡

እንግዲህ ማንን ልወቅስ ይፈለጋል? አስራ አንድ ዓመት ያለ ስራ ያስቀመጠውን መሬት ዛሬ የህዝብና የመንግስት ዓይን መከፈት ሲጀምር እውነት ሊሰራበት ወይስ መልሶ ዓይናችንን ሊያጠፋ ብሎ ያላሰበው የራሳችን ልጅ ከሆነ ወዴት ወዴት ነው ነገሩ ጎበዝ!!!

ለዛሬው ካፒታሊዝምን በወጉ ሳንገነባ ኮርቻውን የተፈናጠጡ ካፒታሊስቶቻችንን ጥቂቶች ቆራጦች ከብዙሃኑ ህዝብ ጋር ሆነው አደብ እንዲያስገዙልን አደራ እላለሁ፡፡

ሌሎች የቀያችን ጉዶችንም በቀጣይ ይዤ ቀርባለሁ እስከዛው ቸር ሁኑልኝ!

*********

Guest Author

more recommended stories