መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ከማራዘም ሌላ አማራጭ የለውም

የኢህአዳግ መንግስት በየመድረኩ የሚናገረውን ሁሉ አምነው የሚቀበሉ፣ ችግሮቹን “በጥልቅ ተሃድሶ” ይፈታል የሚሉ አባላትና ደጋፊዎች አሉት። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያን ፖለቲካ በቅርበት ለሚከታተል ሰው ኢህአዴግ የሚለውን ከማመን ይልቅ ቀጣይ ተግባሩን መገመት በጣም ይቀላል። ለቀጠይ አራት ወራት እንዲራዘም የተወሰነውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እስኪ እንደ ማሳያ ወስደን በዝርዝር እንመልከት።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታወጀው መስከረም 28/2009 ዓ.ም ነው። ነገር ግን፣ ተግባራዊ የተደረገበት ዕለት መቼ ነው? አዋጁ እንዲራዘም የተወሰነው ዛሬ ነው። ነገር ግን፣ አዋጁ እንደሚራዘም እርግጥ የሆነው መቼ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በተግባር የታወጀበትን ዕለትና ምክንያት፣ እንዲሁም ካለፈው አመት ጀምሮ የታየውን የሕዝብ የአመፅና ተቃውሞ እና የኢህአዴግ መንግስትን እንቅስቃሴን በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከ15 ቀናት በፊት የሰጡትን መግለጫ እንደ መነሻ መውሰድ ይቻላል። በሚኒስትሩ መግለጫ መስከረም 28/2009 ዓ.ም በታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በዜጎች ላይ ከተጣሉት ገደቦች ውስጥ የተወሰኑት እንዲነሱ መደረጋቸው ጠቁመዋል። ለምሳሌ፣ ዜጎች ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በተቋማትና በኢንቨስትመንት ፐሮጀክቶች አከባቢ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግደው የሰዓት ገደብ ተነስቷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ኮማንድ ፖስቱ በአዋጁ መሰረት አነሳሳሽ (inciting) የሆኑ የሚዲያ መረጃዎችን መከታተል እንደሚያቆም ገልጧል። የሚኒስትሩ መግለጫ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ሊራዘም እንደሚችል ጠቋሚ ነበር።

Photo - Oromo protests, Shewa zone
Photo – Oromo protests, Shewa zone

አዋጁ ተግባራዊ የሆነው በይፋ ከመታወጁ በፊት ነው

አስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታወጀበትን መሰረታዊ ምክንያት በዝርዝር ስንመለከት ግን ነገሩ ከጠበቅነው ውጪ ይሆናል። ምክንያቱም፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተግባራዊ የሆነው ከመታወጁ አንድ ወር በፊት ቀደም ብሎ፣ በነሃሴ 2008 ዓ.ም ነበር። ሌላው የአስኳይ ግዜ አዋጁ መራዘሙ እርግጥ የሆነው ዛሬ ሳይሆን ከስድስት ወራት በፊት ገና አዋጁ ሲታወጅ ነበር። ለምንና እንዴት?

በእርግጥ ብዙዎቻችን የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታወጀበት ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ስለተከሰተ እንደሆነ እናስባለን። ነገር ግን፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ በስፋት የተጀመረው ከታህሳስ 2008 ጀምሮ ነው። ከዚያ በኋ ችግሩ ይበልጥ እየተስፋፋ ሄዶ በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት መንግስት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴውን በሃይል ለማዳፈን መሞከሩ ይታወሳል። ሆኖም ግን፣ የፀጥታ ኃይሎች በሕዝቡ ላይ የሚወስዱት ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞውን ይበልጥ አባብሶታል። በመጨረሻም መስከረም 2009 ዓ.ም መገባደጃ ላይ በኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች በመንግስትና ግል ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታወጀ።

በእርግጥ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ነሃሴ 24/2008 ዓ.ም “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት የሰጡት መመሪያ በተግባር ከአስቸኳይ ግዜ አወጁ ጋር ፍፁም ተመሣሣይ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ለ10 ወራት ያህል ሀገሪቱ በአመፅና ተቃውሞ ስትናጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በግልፅ አልታወጀም ነበር። የአመፅና አለመረጋጋት ችግሩን ለመግታት ከሆነ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መታወጅ የነበረበት በ2008 ዓ.ም የታህሳስ ወይም ነሃሴ ወር ላይ ነበር።

በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ የታወጀበት ምክንያት ላለፉት አስር ወራት ባልታየ መልኩ በሕዝብና መንግስት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰ ነው። ስለዚህ፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እንጂ የአመፅና አለመረጋጋት ችግሩን ለመቅረፍ አይደለም። ምክንያቱም፣ ከ15 ቀናት በፊት የመከላከያ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ መሰረት፣ በተለይ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በተቋማትና በኢንቨስትመንት ፐሮጀክቶች አከባቢ እንዳይንቀሳቀሱ በዜጎች ላይ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እገዳ መነሳቱ በሕዝብና መንግስት ንብረት ላይ ጉዳት ይደርሳል የሚለውን ስጋት ከሞላ ጎደል ማስወገድ እንደተቻለ በግልፅ ይጠቁማል። ታዲያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ማራዘም ለምን አስፈለገ? ጥያቄውን በግልፅ ለመመለስ በ2008 ዓ.ም የጀመረው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴው በዝርዝር መመልከት ያስፈልጋል።

የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲጀመር በመጀመሪያ በቦታው ደርሶ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርገው የአከባቢው ፖሊሶች ናቸው። ሁኔታው ከከተማ፥ ወረዳና ዞን ፖሊስ አቅም በላይ ሲሆን የክልል ልዩ ፖሊስ ይመጣል። ከዚያ በመቀጠል የፌዴራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይከተላሉ። ከታህሳስ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የተነሳውን የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት በዚህ ቅድም-ተከተል መሰረት ነበር።

በዞን፥ ወረዳና ከተማ ደረጃ ያሉ የፖሊስ አባላት ሕዝባዊ መሰረት ያለው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴን መቆጣጠር አይችሉም። ምክንያቱም፣ ፖሊሶቹም የማህብረሰቡ አባላት እንደመሆናቸው መጠን ከአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መነጠል አይሹም። በተመሣሣይ፣ የክልል ልዩ ፖሊሶች በአብዛኛው ከከተማው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር ረዘም ላለ ግዜ በአብሮነት ያሳለፉ፣ በብሔር እና ቋንቋ የሚግባቡ ስለሆነ ለሕዝቡ ጥያቄ የእኔነት ስሜት አላቸው። እነዚህ ኃይሎች ከታህሳስ እስከ ነሃሴ 2008 ዓ.ም በተለይ በኦሮሚና አማራ ክልል የተነሱ የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ተስኗቸው እንደነበር ይታወቃል።

በእርግጥ የፌደራል ፖሊስ አደረጃጀት ከክልል ልዩ ፖሊስ እና ከአከባቢው ፖሊሶች የተለየ ቢሆንም በተወሰነ ግዜ በተለያዩ አከባቢዎች የሚነሱ የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ግዜ ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የለውም። ስለዚህ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚነሱ የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ረዘም ላለ ግዜ በአንድ አከባቢ በመቆየት ችግሩን መቆጣጠር የሚችለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው።

በተለይ በ2008 ዓ.ም የመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የነበረው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ከአከባቢ ፖሊሶች፣ ከክልል ልዩ ኃይል እና ከፌዴራል ፖሊሶች አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ ይታወሳል። ነበክልል ደረጃ ያሉ የፀጥታ ኃይሎች፡- የክልል ልዩ ፖሊስ፣ እና የዞን፥ ወረዳና ከተማ ፖሊሶች በአከባቢያቸው የሚነሱ የአመፅና አለመረጋጋት ችግሮችን ያለ ፌዴራል ፖሊስ ወይም መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ መቆጣጠር ተስኗቸው ነበር። በዚህ ረገድ በአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ እና በፌዴራል ፖሊሶች መካከል የነበረውን ክፍተት እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የፌደራል ፖሊስ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚፈጠሩ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግሮችን በአንድ ግዜ ለመቆጣጠር የሚያስችል ተቋማዊ አቅም የለውም። ስለዚህ፣ በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት መመሪያ የሰጡበት መሰረታዊ ምክንያት የመከላከያ ሠራዊቱን እንደ ፖሊስ በመጠቀም የተፈጠረውን ክፍተት ለማስወገድና የፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ ነበር።

በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማሪያም የሰጡት መመሪያ ዝርዝር የአፈፃፀም ስላልወጣለት እንጂ ከወር በኋላ ከወጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ጋር ፍፁም ተመሣሣይ ነው። ስለዚህ፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በነሃሴ 2008 ዓ.ም ሲሆን በይፋ የታወጀው ደግሞ መስከረም 28/2009 ዓ.ም እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ሆኖም ግን፣ ከአከባቢው ፖሊስ እስከ መከላከያ ሠራዊት ድረስ ያለው የሥልጣን እርከንና የአሰራር ቅደም ተከተል የጠ/ሚ መመሪያ በታሰበው ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ አልነበረም።

ሁኔታው በዚህ መልኩ ለአንድ ወር ከቀጠለ በኋላ የኢሬቻ በዓል ደረስ። በበዓሉ ላይ የተከሰተው አደጋና እሱን ተከትሎ የተፈጠረው የአመፅና ሁከት መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶታል። በወቅቱ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከማወጅ በስተቀር ሌላ ምርጫና አማራጭ አልነበረውም። በአዋጁ አማካኝነት ከላይ የተጠቀሰውን የአሰራር ቅድመ ሁኔታ በማንሳት የመከላከያ ሠራዊቱን በቀጥታ እንደ ፖሊስና ፀጥታ አስከባሪ በመጠቀም ሁኔታዎችን ካልተቆጣጠረ በስተቀር የመንግስታዊ ሥርዓቱ ሕልውና አደጋ ይወድቅ ነበር።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ቢነሳ እንደ መከላከያ ሠራዊቱ በአንድ ግዜ በተለያየ ቦታ ደርሶ ችግሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ያለው ኃይል አለ? የለም! ታዲያ፣ የኢህአዴግ መንግስት አዋጁ ከማራዘም ሌላ ምን አማራጭ አለው?

የመንግስትና ሕዝብ ምርጫ የሌለው አማራጭ!

ከላይ ለቀረበው ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ እንደየግዜው ይለያያል። በቅድሚያ ግን በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለተከሰተው የአመፅና አለመረጋጋት ችግር መንስዔን በአጭሩ እንመልከት። ሀገሪቱ አሁን ለገባችበት የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር መንስዔው የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት አለመከበሩ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት የፈጠረው ምሬት፣ የብዙሃኑን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ የመንግስት ሥራና አሰራር የፈጠረው ብሶት፣ እና የመሳሰሉት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት የሚቻለው ከግዜ ወደ ግዜ እየዳበረ በሚሄድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አማካኝነት ነው። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት በተለይ የፀረ ሽብር አዋጅ የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ …ወዘተ የመሳሰሉትን ሕገ-መንግስቱን የሚፃረሩና የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችን በማውጣት እና እነዚህን አዋጆች አስታኮ በሚወስዳቸው ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎች ምክንያት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዋቅር ሙሉ በሙሉ አፍርሶታል። በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ዴሞክራሲያዊነትን እያጎለበተ ከመሄድ ይልቅ አምባገነናዊ ፈላጭ-ቆራጭነትን እያዳበረ መጥቷል።

ከገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ወገንተኝነትና ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ሃሳብና አመለካከቱን የሚገልፅበት ነፃ ሚዲያ ከሌለ፤ ድጋፍና ተቃውሞውን፣ አቤቱታና ቅሬታውን የሚያስተጋባለት አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ከሌለ፤ የላቀ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያግዙ የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ በውስጡ የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸው አባላትና አመራሮችን በአግባቡ ተቀብሎ የማያስተናግድ ከሆነ ሕዝቡን ለአመፅና ተቃውሞ እንዳይነሳሳ፣ ሀገሪቷንም ከፅጥታና አለመረጋጋት ችግር መታደግ አይቻልም?

በዚህ የፈረሰ መዋቅር ላይ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ የሚያስነሱ የልማት ሥራዎችና የአገልግሎት አሰጣጥ፣ እንዲሁም ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲታከልበት ከአመፅና ተቃውሞ በስተቀር ሕዝቡ ሌላ ምርጫ የለውም። ስለዚህ፣ የፈረሰውን የዴሞክራሲ መዋቅር መልሶ መገንባት እስካልተቻለ ድረስ ሕዝብ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ መውጣቱን አያቆምም። በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ከማራዘም በስተቀር ሌላ ምርጫ የለውም። ምክንያቱም፣ ሕዝቡን መብትና ነፃነት እየነፈገና አስተዳደራዊ በደል እየፈፀመበት፣ ሃሳብና ብሶቱን፥ አቤቱታና ምሬቱን እንዳይገልፅ በጉልበት የሚያፍነው ከሆነ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ከመውጣት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም።

ያለ ቅጥ የታፈነ ነገር በድንገት ይፈነዳል። የኢህአዴግ መንግስት በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እጦት የታፈነውን ሕዝብ መልሶ በጉልበት ሲያፍነው አመፅና ተቃውሞ በድንገት መፈንዳቱ አይቀርም። ስለዚህ፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በማራዘም የመከላከያ ሠራዊቱ የፖሊስና የፀጥታ አስከባሪዎችን ሥራና ተግባራ እያሰራ ካላስቀጠለው በስተቀር ሀገሪቷ በድንገተኛ አመፅና ተቃውሞ ልትናጥ፣ በዚህም የገዢው ፓርቲ ሕልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በቀጣይ ከሕዝቡ ሊነሳ የሚችለውን አመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ከመከላከያ ሠራዊት በስተቀር መቆጣጠር የሚችል ኃይል የለም። በመሰረቱ፣ መከላከያ ሠራዊት ድርሻና ኃላፊነት የሕዝብን ሰላምና የሀገርን ሉዓላዊነት ከጠላት መከላከል ነው። ሠራዊቱ የሰለጠነው ጠላትን ለመዋጋት እንጂ ሕዝብና መንግስትን ለመዳኘት አይደለም።

ሰለምና ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ የፖሊስን ተግባር እየተወጣ፣ የመንግስትን ክፍተት እየሸፈነ እና የሕዝብን ጥያቄ ወደ ጎን እየገፋ መቀጠል አይችልም። ስለዚህ፣ ከተወሰነ ግዜ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ለኢህአዴግ መንግስት የሥልጣን ማራዘሚያ ሆኖ መቀጠል ይሳነዋል። ይህ መቼ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መገመት ቢከብድም ግዜው የኢህአዴግ መንግስት መጨረሻ ስለመሆኑ ግን ጥርጥር የለውም። ከዚህ አንፃር፣ ሥር-ነቀል ታሃድሶ ከማድረግ ይልቅ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በማራዘም ችግሩን ለማድበስበስ መሞከር ራስን ለውድቀት ማመቻቸት ነው።

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories