ስዩም ተሾመ (MBA)

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን እንደ ኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በሀገር-አቀፍ ደረጃ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት እና ምርታማ የሆነ አከባቢ ነው። በአከባቢው ያለውን አንፃራዊ ሰላም ለመግለፅ ባለስልጣናቱ ሁሉ በንግግራቸው መሃል “ዞናችን በቀድሞው ጠ/ሚ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ “የሰላም ቀጠና” ተብሎ የመሰከሩለት….” የምትለዋን ሐረግ አዘውትረው ይጠቀማሉ። የዘንድሮ ህዳር ሲታጠን፣ ይቺ ላለፉት አስር አመታት እንደ “ታርጋ” ሆና ስታገለግል የነበረችው ሐረግ ከጥቅም ውጪ ልትሆን ሁለት-ሐሙስ እንደቀራት የገመተ አልነበረም። የአከባቢው ማህብረሰብ ተቃውሞውን በአደባባይ እንዲገልፅ ምክንያት ስለሆኑት ነገሮች የዘርፉ ባለሞያዋች ሃሳባቸውን ሊሰጡበት ይችላሉ። ይህ ፅሁፍ “የሰላም ቀጠና የነበረችው ወሊሶ እንዴት በሁለት ሐሙስ በህዝብ ተቃውሞ ተናጠች?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በግሌ የታዘብኩትን ለዚህ መድረክ አንባቢዎች ለማካፈል የተፃፈ ነው።

በወሊሶ የተካሄደው የሕዝብ ተቃውሞ የተጀመረው በዋናነት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች ሐሙስ፣ ህዳር 25/2008 ዓ.ም. ነበር። በቀጣዩ ቀን አርብ ዕለት የኦሮሚያ አድማ-በታኝ ፖሊሶች ወደ ካምፓሱ በመግባት ሰላማዊ የነበረውን የተማሪዎቹን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሃይል ለመበተን ጥረት አደረጉ። የክልሉ ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ የተቻኮለበት ዋና ምክንያት በካምፓሱ የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች ቦታዎች ይስፋፋል ከሚል ስጋት የመነጨ ነበር። ሆኖም ግን፣ የተቃውሞው እንቅስቃሴው በዚያኑ እለት በወሊሶ ከተማ ወደሚገኙት ሁለት የ2ኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች መስፋፋቱ አልቀረም። በተማሪዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ በወሊሶ ከተማ ለታየው ታላቅ የህዝብ ተቃውሞ እንደ መነሻ ይሁን እንጂ በቀጣዩ ሐሙስ፣ ታህሳስ 02/ 2008 ዓ.ም በተካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው በአከባቢው ካሉ የገጠር ከተሞች የመጣው ህዝብ ነበር።

በቅድሚያ፣ ሐሙስ ማታ በተማሪዎች ተጀምሮ የነበረው ተቃውሞ በማግስቱም ሲቀጥል፣ አርብ ጠዋት ወደ 2፡00 ሰዓት አከባቢ የኦሮሚያ ፖሊስ ወደ ካምፓሱ ቅጥር ግቢ በመግባት ተማሪዎቹን በአስለቃሽ ጭስና በዱላ ለመበተን ጥረት አደረገ። በመቀጠል፣ ተማሪዎቹ ከፖሊስ ዱላና አስለቃሽ ጭስ ለማምለጥ ግማሾቹ ወደ ዶርም ሮጡ፣ የተቀሩት የካምፓሱን አጥር ዘለው በመውጣት ከአከባቢው ማህብረሰብ ጋር ተቀላቀሉ። ከግቢ ከወጡት ተማሪዎች ውስጥ የተወሰኑት እዚያው ከተማው ውስጥ ሲቀሩ የተቀሩት ደግሞ ከካምፓሱ በስተጀርባ ያለውን የኢጀርሳ ወንዝን ተሻግረው ከወንዙ ባሻገር ካለው የገጠሩ ማህብረሰብ ጋር ተቀላቀሉ። አንዳንድ ተማሪዎች ከወሊሶ 9ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ጭቱ የምትባል ከተማ ድረስ የሄዱ ነበሩ። ሸሽተው ከሄዱት ተማሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ በእለቱ ወደ ካምፓሱ ሲመለሱ የተወሰኑት ተማሪዎች ግን እዚያው ከገጠሩ ማህብረሰብ ጋር ከ2-3 ቀናት ወደ ካምፓሱ ሳይመለሱ ቆዩ።

በተመሳሳይ፣ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ተቃውሟቸውን ማሰማት ቀጠሉበት። እዚያም የኦሮሚያና የዞኑ ፖሊሶች ተቃውሞውን በሃይል ለመበተን እርምጃ መውሰድ ሲጀምሩ፣ የተማሪዎቹ ተቃውሞ ደግሞ ጭራሽ እየጠነከረ መጣ። የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየበረታ ሲመጣ የመማር-ማስተማሩ ሂደት ለተወሰነ ግዜ ተቋረጠ። በዚህ ግዜ፣ ብዛት ያላቸው የሃይስኩል ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው በወሊሶ ዙሪያ ካሉ እንደ ኢጄርሳ፣ ጭቱ፣ ኦቢ፣ ገርቡ፣ ቆርኬ፣ ጉሩራ፣…ወዘተ የመጡ ናቸው። ታዲያ ተቃውሞው እየጠነከረ ሲሄድ ት/ት ብዛት ያለው የሃይስኩል ተማሪ ገጠር ወደሚገኙ ቤተሰቦቹ ሄደ።

እንደ አብዛኞቹ ከተሞች ሁሉ በወሊሶ’ም ቅዳሜ የገበያ ቀን ነው። እንደ ቅዳሜ ያለ የገበያ ቀን በከተማው ዙሪያ ካሉ አከባቢዎች የሚመጣው የገጠሩ ማህብረሰብ እርስ-በእርሱ ሆነ ከከተማው ማህብረሰብ ጋር የሚወያይበትና ሃሳቡን የሚለዋወጥበት መድረክ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት፣ “አንዳንድ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች ፖሊስ ወደ ግቢ ሲገባ ኢጄርሳ-ማዶ ወደሚባለው አከባቢ ሸሽተው እንደሄዱ አልተመለሱም” ስል ያጫወትኳት አንዲት ባለሱቅ ጓደኛዬ የነገረችኝ ነገር ጉዳዩን በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይቺ ጓደኛዬ እኔ የነገርኳትን ነገር ከኢጄርሳ-ማዶ አከባቢ የመጡ ደንበኞቿን ትጠይቃለች። ሰዎቹ የሰጧት ምላሽ በጣም ስላስገረማት ወዲያው ደውላ ነገረችኝ። እኔም በጣም ነበሩ የገረመኝ። ልጅቷ “የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እናንተ ጋር አሉ እንዴ?” ብላ ላቀረበችው ጥያቄ ከደንበኞቿ ያገኘችው ምላሽ “አዎ…ልጆቹ እኛ ጋር ናቸው፣ የእነሱ ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነው። ማክሰኞ ከእነሱ ጋር አብረን ተቃውሞ ሰልፍ እንወጣለን!” የሚል ነበር።

የዩኒቨርሲቲ እና ሃይስኩል ተማሪዎችን በሚማሩበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሆነው ሲያደርጉት የነበረውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማስቆም፣ እንዲሁም ነገሩ ወደ ከተማ ነዋሪዎች እንዳይስፋፋ በሚል ፖሊስ የተወሰደው እርምጃ “የቆጡን አወርድ ብላ…” አይነት ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ የኦሮሚያ ፖሊስ የተማሪዎቹ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወደ ከተማው ማህብረሰብ እንዳይስፋፋ የወሰደው እርምጃ ከከተማው ይልቅ ወደ ሰፊው የገጠሩ ማህብረሰብ ሄደው ሃሳባቸውን እና የፖለቲካ አቋማቸውን እንዲያሰርፁ ምቹ ዕድል ነበር የፈጠረላቸው። በመሆኑም፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በዋናነት በኢጄርሳ-ማዶ ለሚኖረው ማህብረሰብ፣ የሃይስኩል ተማሪዎች ደግሞ በገጠር ላሉ ቤተሰቦቻቸውን ስለተቃውሞው ምንነት እና አላማ እንዲያስረዱ አስችሏቸዋል። ታህሳስ 02/2008 ዓ.ም በወሊሶ ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ወደ 50,000 የሚጠጋ ህዝብ የተሳተፈበት ከመሆኑም በተጨማሪ አብዛኛው ተሳታፊ 15ኪ.ሜ እና ከዚያ በላይ ርቀት ካላቸው የገጠር ቀበሌዎች በእግርና በመኪና ተጉዞ የመጣ መሆኑ እንደ አንድ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

Photo - Ambo university Waliso campus

ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ነገር የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከተለመደው አካሄድ የተለየ መሆኑ ነው። አብዛኛውን ግዜ በተማሪዎች የሚጀመር የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ በቅድሚያ በዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች እና በ2ኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች ይጀምር። በመቀጠል፣ ብዛት ያላቸው የፖሊቲካ ሊሂቆች እና የተሻለ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ያለበት እንደመሆኑ መጠን፣ የከተማው ማህብረሰብ ከገጠሩ ቀድም ብሎ በተቃውሞው እንቅስቃሴ ተሳታፊ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በወሊሶ በተካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የታየው አካሄድ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ተማሪዎቹ የጀመሩትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተቀብሎ ያስቀጠለው የወሊሶ ከተማ ነዋሪ ሳይሆን በከተማው ዙሪያ ባለው የገጠሩ ማህብረሰብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የዩኒቨርሲቲው እና የ2ኛ ደረጃ ት/ት ቤቶቹ ተማሪዎች የገጠሩ ማህብረሰብ በተቃውሞ እንቅስቃሴው በንቃት እንዲሳተፍ በማድረጉ ረገድ የነበራቸውን ከፍተኛ ሚና የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ፣ በተማሪዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ በአከባቢው ማህብረሰበብ እንደገና ተጠናክሮ የቀጠለው ከማክሰኞ ህዳር 30/2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን በእንቅስቃሴው ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስደው የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች ሲሸሹ ተቀብሎ 3-4 ቀናት በቤቱ ያቆያቸው የኢጀርሳ-ማዶ አከባቢ ነዋሪዎች ናቸው። በእለቱ ነዋሪዎቹ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ሃይለኛ ግብግብ ውስጥ ገብተው ነበር። በማግስቱ ዕሮብ ደግሞ “ኦቢ” ከምትባለው ትንሽ ከተማ የተነሱ የተቃውሞ ሰልፈኞች ወደ ወሊሶ ከተማ ለመግባት ጥረት ያደረጉ ሲሆን የኢጀርሳ-ማዶ ነዋሪዎችም ቀኑን ሙሉ ተመሳሳይ ሙከራ ሲያደርጉ ነበር የዋሉት።

በመጨረሻም፣ ሐሙስ፣ ታህሳስ 02/04/2008 ዓ.ም የሆነው ነገር ግን ፍፁም የተለየ ነበር። በዕለቱ የታየው የህዝብ ተቃውሞ የአከባቢው አስተዳደር ባለስልጣናት ሆኑ የፀጥታ ሃይሎች፣ እንዲሁም ተማሪዎች ሆኑ የከተማው ህዝብ፣ ሁሉም አካላት ከጠበቁት ውጪ ነበር። ወደ ወሊሶ ከተማ በሚያስገቡት አራት መንገዶችን ተከትሎ ያለው ወጣት፣ አዛውንት፣ ሽማግሌ … በአጠቃላይ የገጠሩ ማህብረሰብ ግልብጥ ብሎ ወደ ወሊሶ ከተማ ተመመ። ሁሉም ሰው ትኩረቱን ላለፉት ሁለት ቀናት ተቃውሞ ሲደረግባቸው ወደነበሩት ኢጄርሳ-ማዶ እና ኦቢ አድርጎ ባለበት ሁኔታ፣ በጅማ መስመር ባለው የ“ጉሩራ” መስመር እና በስተሰሜን አቅጣጫ ባለው የ“ቆርኬ” መስመር፣ በአጠቃላይ ወደ ወሊሶ በሚያስገቡት አራት መንገዶች የገጠሩ ህዝብ በአንዴ ግዜ ነቅሎ በመውጣቱ የወሊሶ ከተማ ከፊቱ ያገኘውን ነገር ሁሉ እየደመሰሰ በሚያልፍ ኃይለኛ የህዝብ ሱናሚ የተመታች ይመስል ነበር። በየአቅጣጫው የነበሩ የፀጥታ ሃይሎችን ጥሶ የገባው የህዝብ ወጀብ በዋናው መንገድ ተቃውሞውን እያሰማ ከተማዋን ከጫፍ-እስከ-ጫፍ ዞራት። ይህ ሲሆን፣ የፖሊስ ድርሽ የነበረው ይህን የህዝብ ወጀብ ኋላ መከተል ብቻ ነበር።

በአጠቃላይ፣ ከሌሎች አከባቢዎች በተለየ “የሰላም ቀጠና…” ሲባል “በነበረው” የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በዋናነት በወሊሶ ከተማ በተደረገው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ዙሪያ በግሌ የታዘብኳቸውን ሦስት ነጥቦችን በመጥቀስ ፅሁፌን ልቋጭ፡-

1ኛ፡- ከዛሬ 50 አመት በፊት እንደነበረው ሁሉ፣ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ በኃይል ለመበተን የሚደረግ ጥረት ሁኔታውን ይበልጥ ከማባባስ የዘለለ ሚና የለውም። ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በተካሄደ ቁጥር ፖሊስ የተለመደ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ነገሩን ከማባባስ ይልቅ ዋና ተግባሩ በሆነው የሰውና የንብረትን ደህንነት በማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ የተሻለ ነው። የመንግስት ኃላፊዎችም በበኩላቸው የተነሳውን ተቃውሞ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በሚጥስ መልኩ የኃይል እርምጃ በመውሰድ አቋራጭ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የተነሳውን ጥያቄ በአግባቡ ተቀብለው ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ አለባቸው።

2ኛ፡- ሌላው በክስተቱ የታዘብኩት ነገር፣ “የገጠሩ ማህብረሰብ” እና “የከተማው ማህብረሰብ” የሚለው የመለያ መስፈርት ከሞላ-ጎደል መሰበሩ ነው። በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት በገጠሩና በከተማው ህዝብ መካከል ከአኗኗር ዘይቤ እና ለመረጃ ካለው ቅርበት አንፃር የነበረው ሰፊ ልዩነት በፍጥነት እየቀነሰ በመሆኑ፣ የተለያዩ መሰረተ-ልማቶች ለገጠሩ ማህብረሰብ ተደራሽ በመሆናቸው (በተለይ የገጠር መንገድና የኔትዎርክ አገልግሎት)፣ እንዲሁም አብዛኞቹ የገጠር ልጆች ት/ት የመማር እድል በማግኘታቸው፣…እና በመሳሰሉት ምክንያቶች በገጠሩና በከተማው ማህብረሰብ መካከል የነበረው ልዩነት እየጠበበ መጥቷል። እነዚህ ለውጦች በፈጠሩት እድል አማካኝነት የገጠሩ ማህብረሰብ ፖለቲካዊ ንቃተ-ህሊና እና ተሳትፎ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ለመረዳት ይቻላል።

3ኛ፡- በተለይ ታህሳስ 02/2008 ዓ.ም በተካሄደው ህዝባዊ ተቃዉሞ በከተማው ከነበሩት የክልል እና ፌዴራል ፖሊሶች አቅም በላይ ሆኖ የነበረበትን አጋጣሚ በመንተራስ በእለቱ በሰውና ንብረት ላይ ሊደርስ ይችል የነበረው ውድመት በጣም ከፍተኛ ነበር። ሆኖም ግን፣ ከዚህ አንፃር የነበረው እውነታ በሌሎች ከተሞች ከተለመደው ፍፁም የተለየ ነበር። ለዚህም ደግሞ እንቅስቃሴው በዋናነት በገጠሩ ማህብረሰብ የተመራ መሆኑ እንደ አንድ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። ከከተማው አንፃር ሲታይ፣ በገጠሩ ማህብረሰብ ዘንድ ዝቅተኛ የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መኖሩ እርግጥ ነው። በመሆኑም፣ አብዛኛው ተሳታፊ የገጠሩ ማህብረሰብ ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም የማይገባ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ ሙከራ፣ ዝርፊያና ቅሚያ አልነበረም። ከዚህ አንፃር በተወሰኑ ግለሰቦች ቤትና ንብረት እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ይህ ግን ሊደርስ ይችል ከነበረው አንፃር ሲታይ በጣም ኢሚንት ነው።

***********
* ጸሐፊው ስዩም ተሾመ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር ሲሆኑ፤ በ [email protected] ኢሜይል አድራሻ ሊያገኟቸው ወይም ሌሎች ጽሑፎቻቸውን http://ethiothinkthank.com ላይ ሊያነቡ ይችላሉ፡፡

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories