የዴሞክራሲ አብዮትን “በኢኮኖሚ አብዮት” ማጨናገፍ አይቻልም!

ባለፈው ሳምንት “የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት – በስህተት ላይ ስህተት በመድገም ስህተትን ማረም” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። በፅሁፉ ዙሪያ ከተሰጡኝ አስተያየቶች ውስጥ በአብዛኛው “ፅሁፉ የኢኮኖሚ አብዮቱን ዓላማና ግብ በትክክል አይገልፅም” የሚሉ ነበሩ።

በመሆኑም ጉዳዩ በዝርዝር ለማብራራት እየተዘጋጀሁ ሳለ የአማራ ክልል ተመሣሣይ የኢኮኖሚ አብዮት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን የሚገልፁ ዘገባዎች ወጡ። በዘገባው መሰረት የአማራ ክልል “ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር” የተሰኘ ግዙፍ አክሲዮን ማህበር እየተቋቋመ መሆኑንና በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች 22 ፕሮጀክቶችን ለይቶ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህ ፅኁፍ በሁለቱ ክልሎች “የኢኮኖሚ አብዮት” በሚል የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር አያይዤ በዝርዝር ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

በመሰረቱ ባለፉት ጥቂት አመታት የኢትዮጲያ የውጪ ንግድ እያሳየ ያለው ማሽቆልቆል እየተባባሰ መጥቷል። በዘንድሮው ግማሽ ዓመት ከውጪ ንግዱ ዘርፍ ይጠበቅ የነበረው የውጪ ምንዛሪ ገቢ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የተገኘው ግን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ሊገኝ ከታቀደው 56% ብቻ ነው። በ2008 የበጀት ዓመት ሊገኝ ከታቀደው ውስጥ 67.7% ብቻ የተገኘ ሲሆን ይህም በ2007 የበጀት ዓመት ከተገኘው በ139.3 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር።

ከጥቂት ቀናት በፊት መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከላኪዎች ጋር ስብሰባ አድርጎ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) መሪነት በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ለውጪ ንግዱ ማሽቆልቆል በምክንያትነት ከተጠቀሱት ነጥቦች ውስጥ የመንግስት ቢሮክራሲያዊ አሠራር የፈጠራቸው ችግሮች ትልቁን ድርሻ ይዘዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሀገሪቱ የተከሰተው የውጪ የፀጥታ ችግር፣ በፀጥታው መናጋት የተፈጠረው ሥጋት ለውጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ዋቢ መደረጋቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል።

በጠ/ሚ ፅፈት ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኢትዮጲያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳነት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፤ “ዋናው መሰረታዊ ለውጥ ትርፍ ምርት እንዲመጣ ማድረግ፣ አዲስ ምርት ወደ ኢኮኖሚው ማምጣት መቻል እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ ምርቶች የሚተኩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል ነው’ ብለዋል። አያይዘውም “ስንዴ ከውጪ እያስመጡ ያንን ለዱቄት ፋብሪካዎች ሰፍሮ በመስጠት ለውጥ አይመጣም” ብለዋል። እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የግብርና ጥሬ ዕቃዎችን በላክ ላይ የተመሰረተውን የውጪ ንግድ ወደ ኢንዱስትሪ ምርቶች ማሸጋገር አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፣ የንግድ ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት የኢንዱስትሪ ምርቶች የውጪ ንግድ እየቀነሰ መሆኑንና ለዚህም የግብዓት አቅርቦት፣ የጥራት ችግር፣ የመንግስት አገልግሎቶች የአሰራር ቅልጥፍና አለመኖር እና የገዢ ኩባኒያዎች በተለያየ ምክንያቶች ውል መሰረዝን በምክንያትነት ጠቅሷል።

በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ የውጪ ንግድ በየአመቱ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ በምክንያትነት የተጠቀሱትን ነጥቦች በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛ፡- የመንግስት ቢሮክራሲያዊ አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ ሁለተኛ፡- በሀገሪቱ የተከሰተው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር፣ ሦስተኛ፡- አነስተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ናቸው።

በተለይ የውጪ ንግዱ ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገባው የኢህአዴግ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 14/2009 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ “የአማካሪ ምክር ቤት” ለማቋቋም ወስኗል። ከዚህ ጎን-ለጎን፣ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በየፊናቸው “የኢኮኖሚ አብዮት” በሚል ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን ለይተው ወደ ስራ ገብተዋል። ስለዚህ፣ መንግስት በፌደራልና በክልል ደረጃ የሚያደርገው እንቀስቃሴ ከውጪ ንግድና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ጋር በተያያዘ የተጠቀሱትን ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ ይችላል? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ከላይ የተጠቀሱት ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል።

በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ ለተፈጠረው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ዋናው ምክንያት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የታየው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው። ከ60% በላይ የሀገሪቱ ሕዝብ በሚኖርባቸው እነዚህ ሁለት ክልሎች የተከሰተው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር የኢህአዴግ መንግስትን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል። ለአመፅና ተቃውሞ አንቅስቃሴው ዋናው ምክንያት የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት ባለመከበሩ፣ የመንግስት ሥራና አሰራር በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በማስነሳት ነበር። ስለዚህ፣ በሀገሪቱ ለተከሰተው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ዋናው ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ማክበርና ማስከበር፣ እንዲሁም በመንግስታዊ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋለውን ስር-የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ ስለተሳነው ነው።

ሀገሪቱ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር የተዳረገችበት ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ረገድ ከሕዝቡ የለውጥና መሻሻል ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ስለተሳነው። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት መልካም አስተዳደርና ቀጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መገንባት ስለተሳነው፣ እንደ ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል፣ ለንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶችና ድርጅቶች አስፈላጊውን አገልግሎትና ድጋፍ እየሰጠ አይደለም።

የሀገሪቱ የውጪ ንግድ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ሦስት መሰረታዊ ችግሮች ውስጥ አንደኛው “የመንግስት ቢሮክራሲያዊ አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር” ነው። ስለዚህ፣ አንደኛው ችግር ዋና መንስዔ ራሱ የኢህአዴግ መንግስት ነው።

በተመሣሣይ፣ በመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ረገድ የሚደረገው ጥረት ሲጨናገፍ ሕዝቡን ለአመፅና ተቃውሞ፣ ሀገሪቱን ለፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ዳርጓታል። የሀገሪቱ የውጪ ንግድ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መሰረታዊ ችግሮች ውስጥ ሁለተኛው “በሀገሪቱ የተከሰተው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር” ነው። በድጋሜ ለሁለተኛው ችግር ዋና መንስዔ ራሱ የኢህአዴግ መንግስት ነው።

እስካሁን ድረስ የሀገሪቱ የውጪ ንግድ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ የመጀመሪያ ሁለት ችግሮች ዋና መንስዔ ራሱ የኢህአዴግ መንግስት እንደሆነ ተመልክተናል። በመቀጠል ደግሞ በሦስተኛ ለይ የተጠቀሰው “አነስተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት” ችግርን የኦሮሚያና አማራ ክልላዊ መስተዳደሮች ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩት የኢኮኖሚ አብዮት ጋር አያይዘን በዝርዝር እንመለከታለን።

የኦሮሚያና አማራ ክልሎች በሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዓምራዊ ለውጥ ያመጣል፣ ለብዙ ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል፣ …ወዘተ በሚል እሳቤ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ገብተዋል። ለምሳሌ፣ የአማራ ክልላዊ መስተዳደር “የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበርን” 25 በመቶ ድርሻ የአክሲዮን ድርሻ እንደሚገዛ ተጠቅሷል። በተመሣሣይ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር በኢኮኖሚ አብዮቱ ከሚቋቋሙት የአክሲዮን ድርጅቶች ውስጥ እስከ 35% የአክሲዮን ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል በማህበራዊ ድረገፆች ላይ እየተገለፀ ይገኛል።

እንደ ማንኛውም መንግስት ሁለቱም ክልላዊ መስተዳደሮች ከሕዝብ ከሚሰበሰበው በስተቀር የራሳቸው የሆነ የገቢ ምንጭ የላቸውም። ስለዚህ፣ ሁለቱም የክልል መንግስታት ከሕዝቡ በግብርና ቀረጥ መልክ የሰበሰቡትን ገንዘብ የቢዝነስ ተቋማት አክሲዮን ድርሻ ለመግዛት አውለውታል።

በኢኮኖሚ አብዮቱ የሚቋቋሙት በአገልግሎት፣ ማምረቻና ግንባታ ዘርፍ የሚሰማሩ የቢዝነስ ድርጅቶች ናቸው። የአማራና ኦሮሚያ ክልል መንግስታት የእነዚህን ድርጅቶች የአክሲዮን ድርሻ በመግዛት በኢኮኖሚው ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ስለመግባታቸው ጥርጥር የለውም። ስለዚህ፣ ይህ ጣልቃ ገብነት የኢህአዴግ መንግስት ከሚያራምደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር ምን ያህል ተቀባይነት አለው?፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ከማሻሻል አንፃር ምን አስተዋፅዖ ያበረክታል? ከዚህ ቀጥሎ፣ እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ከገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት (market economy) አንፃር የአማራና ኦሮሚያ ክልል መንግስታትን ጣልቃ ገብነትና ውጤታማነት በዝርዝር እንመለከታለን።

ከገበያ መር ኢኮኖሚ (market economy) ስርዓት አተገባበር ጋር ተያይዙ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች መኖራቸው እርግጥ ነው። በዋናነት ግን፤ “መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም” እና “መንግስት በተመረጡ የኢኮኖሚ መስኮች ጣልቃ መግባት አለበት” የሚሉት አመለካከቶች የሚጠቀሱ ናቸው። የኢህአዴግ መንግስት የመጀመሪያውን የኒዮ-ሊብራሊዝም አቀንቃኞች አመለካከት እንደሆነ በመጥቀስ “መንግስት በተመረጡ የኢኮኖሚ መስኮች ጣልቃ መግባት አለበት” የሚለውን አመለካከት እንደሚያራምድ ይታወቃል። ስለዚህ፣ የኦሮሚያና አማራ ክልል መንግስታት በኢኮኖሚው ውስጥ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነት ከኒዮሊብራሊስቶች እይታ ሳይሆን ከራሱ ከኢህአዴግ መንግስት እይታ አንፃር መመልከት ይኖርብናል።

ከላይ እንደተገለፀው፣ የኢህአዴግ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ “መንግስት በተመረጡ የኢኮኖሚ መስኮች ጣልቃ መግባት አለበት” የሚለው ነው። በኢኮኖሚ አብዮቱ በሚቋቋሙት ድርጅቶች አማካኝነት የኦሮሚያና አማራ ክልል መንግስታት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የአገልግሎት፣ ማምረቻና ግንባታ ዘርፎች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን፣ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ውስጥ ጣልቃ መግባት ያለባቸው መቼ ነው?

በገዢው ፓርቲ የኢኮኖሚ ፖሊስ መሰረት መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት ያለበት “የገበያ ውድቀት” (market failure) ሲኖር ነው። አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ሁኔታውን፤ “Government legitimacy in a market economy arises from market failures” በማለት ይገልፁታል።

“የገበያ ውድቀት መቼ ነው የሚኖረው?” ለሚለው ደግሞ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነሱም፣ 1ኛ፡- የምርትና አገልግሎቶች ማምረቻ/ማቅረቢያ ወጪ ከተጠቃሚዎች የመክፈል አቅም በላይ ሲሆን (Incomplete markets)፣ 2ኛ፡- የትክክለኛ መረጃ አቅርቦት ችግር ሲኖር (Information failures)፣ 3ኛ፡- የሕዝብ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመገንባት ሲሆን (Public goods)፣ እና 4ኛ፡- ውጫዊ የሆኑ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተፅዕኖዎችን በምርቱ የገበያ ዋጋ መመለስ የማይቻል ሲሆን (Negative/ positive Externalities) ናቸው።

ከላይ ከተጠቀሱት አራት መሰረታዊ ምክንያቶች አንፃር፣ የኦሮሚያና አማራ ክልላዊ መንግስታት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ለመግባት በወሰኑባቸው የአገልግሎት፣ ማምረቻና ግንባታ ዘርፎች “የገበያ ውድቀት (market failure) አለ” ማለት አይቻልም። ምክንያቱም፣ የግልና የማህበር ቢዝነስ ተቋማት በተጠቀሱት የኢኮኖሚ መስኮች ለመሰማራትና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያግዳቸው የገበያ ችግር የለም። ስለዚህ፣ የሁለቱም ክልል መንግስታት “የኢኮኖሚ አብዮት” በሚል በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ለመግባታቸው የገበያ ውድቀትን በምክንያትነት መጥቀስ አይችሉም። ስለዚህ፣ የአማራና ኦሮሚያ ክልል መንግስታት “የኢኮኖሚ አብዮት” በሚል በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ውስጥ ጣልቃ የገቡት የገበያ ውድቀት በሌለበት ሁኔታ ነው።

የኦሮሚያና አማራ ክልል መንግስታት የገበያ ውድቀት በሌለበት ሁኔታ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው እንደተባለው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተዓምራዊ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ? የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ያዋሉት የሕዝብ ገንዘብ የዘርፉን ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳድገዋል? በዘርፉ ካሉት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በምርትና ጥራት ተወዳዳሪ ሆነው ትርፋማ ይሆናሉ? በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ የውጪ ንግድ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ በምክንያትነት የተጠቀሰውን “አነስተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት” ችግርን መቅረፍ ይችላሉ? በዚህም፣ እንደተባለው ለብዙ ሺህ የአማራና ኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና አርሶ አደሮች የስራ ዕድልና የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ?

በመሰረቱ፣ መንግስት ከምንም ይሻላል እንጂ ከማንም ግን አይሻልም። ምክንያቱም፣ ምንም ነገር ከባዶ ይሻላልና ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሌለበት የገበያ ውድቀት (market failure) ውስጥ መንግስት ጣልቃ ቢገባ ይመረጣል። ነገር ግን፣ የገበያ ውድቀት በሌለበት መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ግን በፍፁም ውጤታማና ተወዳዳሪ ሊሆን አይችልም። ምን ግዜም ቢሆን መንግስት በምርታማነትና ጥራት ከግል ተቋማት የተሻለ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ፣ የኦሮሚያና አማራ ክልል መንግስታት የኢኮኖሚ አብዮት ለውጪ ንግድ ማሽቆልቆል ምክንያት የሆነውን “አነስተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት” ችግር ከመቅረፍ አንፃር የጎላ አስተዋፅዖ አያበረክትም።

የገበያ ውድቀት በሌለበት ሁኔታ የመንግስት ሥራና ድርሻ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ቢዝነስ ተቋማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። በዚህም፣ የመንግስት ዋና የሥራ ድርሻ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት በመቅረፍ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ሁኔታ መፍጠር እና የመንግስትን ሥራና አሠራር ወደ ላቀ ደረጃ በማሻሻል የተቀላጠፈ የአገልግሎትና ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ነው።

የሀገሪቱ የውጪ ንግድ እንዲያሽቆለቁል በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ሦስተኛው “አነስተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ምርት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት” ችግር ነው። በመሆኑም፣ ለሀገሪቱ የውጪ ንግድ ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ የሄደበት ምክንያት የፌደራልና ክልል መንግስታት ድርሻና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ስለተሳናቸው ነው። በተለይ የአማራና ኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደሮች እንደ መንግስት የሚጠበቅባቸውን ሥራና ኃላፊነት በሚገባ ባለመወጣታቸው ምክንያት ተፈጠረ ችግር ነው። አሁንም ከህዝብ ከተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

በመጨረሻም፣ አብዛኞቹ የአማራና ኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ደጋፊዎችና አቀንቃኞች ከላይ ከተገለፀው የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ይልቅ የአብዮቱ ዓላማና ግብ ላይ ማተኮር ይቀናቸዋል። ስለዚህ፣ አብዛኞቹ “የኢኮኖሚ አብዮቱ ከተቀመጠለት ከግብ (objective) አንፃር መታየት አለበት” የሚል መከራከሪያ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ከላይ በኢኮኖሚ አብዮቱ አማካኝነት የሁለቱ ክልል መንግስታት ጣልቃ በሚገቡባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ “የገበያ ውድቀት አለ” የሚል መከራከሪያ ሊቀርቡ ይችላሉ።

ነገር ግን፣ “Market Efficiency and Government Intervention” በሚል ርዕስ የቀረበ ጥናታዊ ፅሁፍ በጉዳይ ዙሪያ የሚከተለውን ሃሳብ አስቀምጧል፡-

“Though the presence of, market failure implies that there may be a scope for government intervention, it does not imply that a particular government program aimed at correcting the market failure is necessarily desirable. To evaluate government program one must not only take into account their objectives but how they implement it.” Journal of International Business and Economics, Vol. 3(1), June 2015

በእርግጥ በኢኮኖሚ አብዮት አማካኝነት ለብዙ ሺህ የአማራና ኦሮሚያ ወጣቶች የሥራ እድል እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የተቀመጠው ግብ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን፣ የሁለቱ ክልላዊ መስተዳደሮች በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት መመዘን ያለበት ካስቀመጡት ግብ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከፕሮግራሙ አተገባበር ጭምር መሆን አለበት። ለብዙ ሺህ የአማራና ኦሮሚያ ክልል ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው?፣ የመንግስት ዕቅድና ፕሮግራም በምን ላይ ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባል? ሁለት የዘርፉ ምሁራን “Human Capital and Sustainability” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ እንዴት ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚቻልና የመንግስት ዕቅድና ፕሮግራም ትኩረት በምን ላይ መሆን እንዳለበት እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡-

“Contrary to popular belief, the principal source of new jobs is social development, not economic policy. Public stimulus programs, manipulation of the money supply and interest rates can certainly have short-term impact, but it is the growth and development of society that serves as the foundation and context for economic growth. Full employment can be achieved by broad-based social strategies that accelerate social development, including measures that improve the quality and quantity of education and training, promote entrepreneurship and self-employment, increase the speed of communication and transportation, encourage research and innovation, and more fully utilize the power of social organization, e.g., the Internet.” Journal of Sustainability ISSN 2071-1050

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ እንደተገለፀው፣ ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር መሰረቱ “ማህበራዊ ልማት” (social development) ነው። ለዚህ ደግሞ መንግስት ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ዋና ትኩረት በሰው ሃብት ልማት ላይ መሆን አለበት። በመሆኑም፣ የመንግስት ሥራና ኃላፊነት፤ ተግባር ተኮር ትምህርትና ሥልጣና መስጠት፣ ሥራ ፈጣሪነትን ማበረታታት፣ የተቀላጠፈ የብድር አገልግሎት መስጠት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አቅርቦት ጥራትና ተደራሽነትን ማሳድግ፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማበረታታት፣…ወዘተ የመሳሰሉ የድጋፍ ተግባራትን በማከናወን በሀገሪቱ ወይም በክልሉ የሰው ኃብት ልማት ማረጋገጥ ነው።

ስለዚህ፣ ለብዙ ሺህ ወጣቶች የሥራ-ዕድል ከመፍጠር አንፃር የመንግስት ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ትኩረት ማድረግ ያለባቸው የሰው ሃብት ልማት ነው። ነገር ግን፣ የአማራና ኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ከሰው ሃብት ልማት ይልቅ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። በመሆኑም፣ የሁለቱም ክልሎች የኢኮኖሚ አብዮት ግቡን አይመታም።

በአጠቃላይ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ ለሚስተዋለው ችግር ዋና መንስዔው ያለው የሀገሪቱ ፖለቲካ ነው። የኢትዮጲያ ፖለቲካ መሰረታዊ ችግር ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ማክብር/ማስከበር አለመቻሉ ነው። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እየታየ ያለው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ዋና መነሻ ምክንያቱ የኢህአዴግ መንግስት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ማክበርና ማስከበር፣ እንዲሁም በመንግስታዊ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋለውን ስር-የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ ስለተሳነው ነው። “3ኛው ማዕበል፡ የልማታዊ መንግስት ፈተና” በሚለው ፅሁፌ በዝርዝር እንደገለፅኩት ይህ የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ በትክክለኛው ግዜና ሁኔታ ውስት የተነሳ የዴሞክራሲ አብዮት ነው።

ይህን የዴሞክራሲ አብዮት አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል በማድረግ በተገቢው ሁኔታ ማስተናገድ ከተሳነን ሀገሪቷን ወደ ባሰ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ውስጥ ይከታታል። ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱና ነፃነቱ እንዲከበር፣ የመንግስት ሥራና አሰራር እንዲሻሻል፣ ስር የሰደደው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲቀረፍና የብዙሃኑን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ የሚያነሳቸውን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በኢኮኖሚ አብዮት ምለሽ ለመስጠት መሞከር ችግሩን ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ የለውም።

በአጠቃላይ፣ አንደኛ፡- የኢኮኖሚ አብዮቱ የዴሞክራሲ አብዮቱን ለማጨናገፍ ያለመ ነው፣ ሁለተኛ፡- የኢኮኖሚ አብዮቱ ግቡን አይመታም፣ ሦስተኛ፡- የኢኮኖሚ አብዮቱ አለመሳካቱ የዴሞክራሲ አብዮቱን መልሶ ያቀጣጥለዋል። ምክንያቱም፣ የዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት እስካልተከበረ እና የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት እስካልተቀረፈ ድረስ፣…ወዘተ አሁን በውጪ ንግዱ ላይ እየታየ ያለው ማሽቆልቆል ወደ አጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ይስፋፋል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲቀዛቀዝ ፖለቲካዊ ችግር ያስከትላል፣ በዚህም ሕዝቡ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ይወጣል። ስለዚህ፣ የዴሞክራሲ አብዮት በኢኮኖሚ አብዮት አይጨናገፍም!

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories