የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት – በስህተት ላይ ስህተት በመድገም ስህተትን ማረም!

በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል በአንድ የማደሪያ ክፍል ውስጥ በአማካይ 100 ሰልጣኞች (እስረኞች) አብረው ያድራሉ። እኔ በነበርኩበት ክፍል ውስጥም 98 ሰልጣኞች (እስረኞች) ነበርን። የተሃድሶ ሥልጠናው ከቀኑ 11፡00 ላይ ይጠናቀቃል። ከምሽቱ 12፡30 በኋላ የመኝታ ቤቶቹ በሮች ከውጪ ይዘጋሉ። ከዚያ በኋላ እስከ ንጋቱ 12፡30 ድረስ በጣም አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የመኝታ ክፍሉ በር አይከፈትም። ማታ ማታ አብዛኛው ሰው ከአንዱ ፍራሽ ወደ ሌላው ፍራሽ እየተዟዟረ “ወሬ” ይሰልቃል። ከአንድ ሰው በስተቀር አብዛኞቻችን ሥራ-ፈቶች ነበርን። ይህ ብቸኛ ሰው ከአርሲ ሮቤ የመጣው “ገመቹ” ነው። (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ትክክለኛ ስሙ ተቀይሯል)

ገመቹ የአምስት ልጆች አባትና በጣም ታታሪ ሰው ነው። ዘወትር በሥራ እንደተጠመደ ነው። ከስልጠና መልስ የተለያየ ቀለም ያላቸውን የሲባጎ ገመዶችን በመጎንጎን የኢትዮጲያና የኦሮሚያ ባንድራ ምስል ያላቸው የጥርስ መፋቂያዎችን እየሰራ አንዱን በ10 ብር ይሸጣል። ለእኔም አንድ መፋቂያ ሰርቶ በአስር ብር ሸጦልኛል። አንድ ቀን “ገሜ… እስካሁን ስንት መፋቂያ ሰርተሃል?” ብዬ ስጠይቀው “አንድ መቶ በላይ ነው” ብሎኛል። የተሃድሶ ሥልጠና ሊጠናቀቅ አከባቢ የገመቹ ገበያ በጣም ደርቶ ነበር። በማዕከሉ የሚገኙ የፌደራል ፖሊሶች ሳይቀሩ የገመቹን የእጅ-ሥራ ለመግዛት ሲሻሙ ነበር። በዚያ ምንም መስራት በማይቻልበት፣ ሁሉም ሰው ሥራ-ፈት (ሥራ-አጥ) በሆነበት ቦታ ገመቹ ከጥርስ መፋቂያ ብቻ ከአንድ ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝቷል።

የተሃድሶ ሥልጠናው ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ከማዕከሉ ስንወጣ በየትኛው የሥራ መስክ ተደራጅተን መስራት እንደምንፈልግ መጠይቅ ሞልተን ነበር። ከዚያ በፊት ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው በክልሉ እና በፌዴራሉ መንግስት ትብብር ተግባራዊ ሊደረግ ስለታቀደው የሥራ እድል ፈጠራና ድጋፍ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተውናል። ገመቹም ወደ አርሲ ሮቤ ሲመለስ በየትኛው የሥራ መስክ ተደራጅቶ መስራት እንደሚፈልግ በመጠይቁ ላይ ሞልቷል። ያን ዕለት ማታ “ገሜ… አሁንማ መንግስት በማህበር አደራጅቶ የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግልህ ነው። በየትኛው የሥራ-መስክ ለመሰማራት አቀድክ?” ስል ጠየቅኩት። የገመቹ ምላሽ ግን በጣም አስገራሚ ነበር። “ማ… እኔ?! እኔ አምስት ልጆች አሉኝ። ከማንም ሰነፍ ጋር ተደራጅቼ አገልጋይ ከምሆን ከልጆቼ ጋር ተደራጅቼ ብሰራ ይሻለኛል። የመንግስት ድጋፍ ከምር ከሆነ ለእኔና ልጆቼ ብድር ቢሰጠን መልካም ነበር” አለኝ።

የጦላይ የተሃድሶ ማዕከል ዋና አስተባባሪ የነበሩት ኮሚሽነር በስልጠናው መጠናቀቂያ ላይ ካቀረቡት ሪፖርት ላይ ብቻ በመነሳት በማዕከሉ ከነበሩት 5670 አከባቢ ሰልጣኞች (እስረኞች) ውስጥ 1474 (26%) በአመፅና ረብሻ ተግባር ተሳትፈዋል በሚል ማስረጃ የቀረበባቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። የተቀሩት 74% ደግሞ በአመፅና ረብሻ ተግባር ስለመሳተፋቸው ይሄ ነው የሚባል ማስረጃ ያልቀረበባቸው፤ እንዲሁ በአጉል ጥርጣሬ፣ በተሳሳተ መረጃ፥ ጥቆማ ወይም በተሳሳተ ሰዓትና ቦታ በመገኘታቸው ምክንያት ተይዘው የታሰሩ ናቸው። ገመቹ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው። በአጠቃላይ፣ ከተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ተይዘው እንደ ጦላይ ባሉ የስልጠና ማዕከሎች የወንጀል ምርመራና የተሃድሶ ስልጠና ሲሰጣቸው ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ያለ በቂ ማስረጃ የታሰሩ ነበሩ።

በእርግጥ እንደ አንድ የክልሉ ተወላጅ ሆነ እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ባለፉት አመታት የኦሮሞ ሕዝብ ሲያነሳቸው የነበሩትን የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትህ ጥያቄዎችን በሞራልና ሃሳብ ደግፈው፣ እንዲሁም በተግባር ጭምር ተንቀሳቅሰው ሊሆን ይችላል። የክልሉና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ይህን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ በኃይል ለማፈን ያደረጉት ጥረት ሁኔታውን ወደ አላስፈላጊ ግጭትና ሁከት አንዲያመራ አድርጎታል። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ለታየው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ዋናው ምክንያት ሕዝቡ ለሚያነሳቸው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት ተገቢ የሆነ ምላሽ አለመስጠታቸው መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከዚህ አንፃር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው “የኢኮኖሚ አብዮት” ያሉበትን መሰረታዊ ክፍተቶች እንመልከት። 

በመጀመሪያ ደረጃ፣ የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ “የክልሉ ህዝብና መስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት ይከበር!” የሚል ነው። ይህን በመብትና ነፃነት ላይ ማዕከል ያደረገ የዴሞክራሲ ጥየቄ “በኢኮኖሚያዊ አብዮት” ምለሽ ለመስጠት መሞከር ፍፁም ስህተት ነው። “ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይ በዝርዝር እንደተገለፀው፣ ከኢኮኖሚ አብዮት በፊት የሕግ-የበላይነት መቅደም እንዳለበት በዝርዝር ተገልጿል። ለምሳሌ፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ማድረግ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። ይህን የክልሉን ሕዝብና መስተዳደር ልዩ ጥቅም እንዲረጋገጥ የተቀመጠን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በተጨባጭ የፖሊሲ ጥናት ያልተደገፈ የኢኮኖሚ ዕቅድን ተግባራዊ ለማድረግ መጣደፍ ተገቢ አይደለም።

ሁለተኛ፡- በኢኮኖሚ አብዮቱ የመሪነት ሚና የሚጫወተው ክልላዊ መስተዳደሩ መሆኑ ራሱን የቻለ ሌላ ችግር ነው። በእቅዱ መሰረት ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት፣ ኬኛ የመጠጥ ማቀነባበሪያ፣ አምቦ ፕመር ማምረቻ፣ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ እና የኦሮሚ የግንባታ ኩባኒያዎች እንደሚቋቋሙ ተገልጿል። ይህን የክልሉን ወጣቶችና አርሶ-አደሮች ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለለት ዕቅድ ተግባራዊ የሚያደርገው ግን የክልሉ መስተዳደር ነው። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ሕዝብ ሲያነሳቸው ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ፤ የክልሉ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች የአብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አለማረጋገጡ፣ የክልሉ መስተዳደር በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ውስጥ የተዘፈቀ መሆኑ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አለመሆኑ፣ …እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህና ሌሎች ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሆነው መስተዳደሩ ነው፡፡ ይሄው አስተዳደራዊ ስርዓት ዕቅዱን በአግባቡ ተግባራዊ ያደርጋል ብሎ ማሰብ በራሱ የዋህነት ነው።

ሦስተኛ፡- በእርግጥ አብዛኞቹ የክልሉ ወጣቶች በአመፅና ተቃውሞ አንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉት በመብትና ነፃነት እጦት እንጂ በሥራ-አጥነት ምክንያት አይደለም። ይሁን እንጂ፣ ሥራ-አጥነት በራሱ ሕዝቡ ከሚያነሳቸው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች አንዱ ነው። ነገር ግን፣ እሱም ቢሆን አሁን በተቀመጠው አቅጣጫ ዘላቂ መፍትሄ አያገኝም። “የሥራ-ዕድል በብር አይገዛም” በሚለው ፅሁፍ በዝርዝር እንደገለፅኩት፣ የክልሉ መንግስት ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት በተሳሳተ እሳቤ እና የአገልግሎት አስጣጥ ሥርዓት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ተጨባጭ የሆነ ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይቻልም። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ክፍተቶች አንዱ ከላይ በፅሁፌ መግቢያ ላይ ገመቹ “ከማንም ሰነፍ ጋር ተደራጅቼ አገልጋይ ከምሆን…” በማለት የገለፀው የአሰራር ሥርዓት ነው። በክልል ሆነ በሀገር ደረጃ “ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የሥራ-ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ…” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተው አሰራር ከሥራ-ሰሪዎች ይልቅ ሥራ-አጦችን የሚያበረታታ ነው።

በመሰረቱ ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ መሰጠት ያለበት ለሥራ-ፈጣሪዎች እና/ወይም ለሥራ-ሰሪዎች እንጂ ለሥራ-አጦች አይደለም። ሥራ-ፈጣሪዎች ወይም ሥራ-ሰሪዎች የሚባሉት የራሳቸውን የቢዝነስ ተቋም ለመመስረት እና/ወይም ለመምራት የሚያስችል ልዩ ክህሎት፥ ልምድና ብቃት (entrepreneurial qualities) ያላቸው ናቸው። እነዚህ መንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍና ማበረታቻ በመጠቀም በዋጋና ጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ ይችላሉ። በዚህም ድጋፍና ማበረታቻው የተቋማቱን ምርትና ምርታማነት፣ እንዲሁም ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል። ይህ በኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ እሴትና የሥራ-ዕድል ይፈጥራል። ሙያዊ ክህሎትና ብቃት ላላቸው ወጣቶች አማራጭ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። ሁሉም ወጣቶች ባላቸው ዕውቀትና ክህሎት ልክ ተወዳድረው የመስራትና የተሻለ ገቢ የማግኘት እድል ይኖራቸዋል።

ነገር ግን፣ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር በሚል ሥራ-አጥ ወጣቶችን በማህበር ሰብስቦ ድጋፍና ማበረታቻ መስጠት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከማስፋፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ሥራ-አጥ ወጣቶች የራሳቸውን የቢዝነስ ተቋም ለመመስረት እና/ወይም ለመምራት የሚስችል ልዩ ክህሎት፥ ብቃትና ልምድ የላቸውም። ምንም ያህል ድጋፍና ማበረታቻ ቢደረግላቸው በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ የሚስችል ግለሰባዊና ተቋማዊ አቅም መገንባት ይሳናቸዋል። በመሆኑም፣ ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍና ማበረታቻው ተጠቅመው ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ እሴት ለመፍጠር፣ እንዲሁም ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅማቸው በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው። በዚህ ረገድ በጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ላይ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ተቋማት የ“Sub-contracting” ውል በመስጠት ከሥራ ጥራትና አገልግሎት አቅርቦት ጋር ተያይዞ፣ እንዲሁም ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት አንፃር የነበረው ክፍተት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

በአጠቃላይ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው “ኢኮኖሚ አብዮት” የክልሉን ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ የማይመልስ፣ ክልላዊ መስተዳደሩ ያለበትን የመልካም አስተዳደር ችግርና አቅም ማነስ የማይቀርፍ እና በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ግቡን አይመታም። ይህ የኢኮኖሚያ አብዮት በስህተት ላይ ስህተት በመደጋገም፣ አንዱን ስህተት በሌላ ስህተት ለማረም መሞከር ነው። ስህተት የሰራ አካል በተመሣሣይ ግንዛቤና እሳቤ ውስጥ ሆኖ የቀድሞ ስህተቱን በሌላ ስህተት ለማረም ጥረት የሚደረግበት ዕቅድ ግቡን ሊመታ አይችልም፡፡

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories