ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካን ወደ ዳር ሊተዏት ይችላሉ?

(ስንታየሁ ግርማ)

የተጋነነ ቢመስልም ፖለቲከኞች በየትኛውም ዓለም ተመሳሳይ ናቸው የሚል አባባል አለ፡፡ በተለይ በምርጫ ወቅት “ወንዝ በሌለበት ድልድይ” ለመገንባት ቃል ይገባሉ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ወቅት አስገራሚ እና አነጋጋሪ ንግግሮች አድርገዋል፡፡ እንደመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ በመጀመሪያ ተናግረዋቸዋል የተባሉት ንግግሮች መካከል አንዳንዶቹ በአግባቡ እንዳልቀረቡ እራሳቸው ትራምፕ ተናግረዋል፡፡ በምርጫ ወቅት ተናገሯቸው የተባሉት ንግግሮች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይተገበራሉ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሕዝባዊ ተቀባይነት ለማግኘት የተጠቀሙባቸው በመሆናቸው ነው፡፡

ትራምፕ ከተናገሯቸው መካከል በጣም አከራካሪዎቹ “ታላቋ አሜሪካን እንደገና መገንባት፣ ሕገወጥ ስደተኞችን በሙሉ ጠራርጌ አስወጣለሁ፣ የንግድ ስምምነቶችን አፈርሳለሁ፣ አሜሪካን ከአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አስወጣለሁ” የሚሉት  ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ታላቋ አሜሪካን እንደገና መገንባት የሚለው አሁን ባለንበት ዘመን የአንድ ልዕል ኃያል ሀገር መገንባት አይቻልም በተለይ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከቀውስ ለማገገም የቻይና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ እድገት እንዲቀጥል የአሜሪካ ሸማች ማኀበረሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቀጣይነት አሰፈላጊ ነው፡፡ አሜሪካ በቻይና ምርቶች እና አገልግሎቶች ከፍተኛ ቀረጥ ብትጥል የሚጎዳው የአሜሪካ ሸማች ነው፡፡ በቻይና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል ጥቂት የአሜሪካ ባለሀብቶችን (1 በመቶ የሚሆኑትን) ማሳደግ ይቻላል፡፡ ሆኖም ሸማች የሆነውን አብዛኛውን ማኀበረሰብ በመጎዳት በሀታሞች እና በድሆች መካከል ያለውን ልዩነት በማስፋት ማኀበራዊ ቀዉስ ስለሚፈጥር ይህንን አካሄድ ትራምፕ ይተገብሩታል ማለት በቀኝ እጅ የግራ እጅን መቁረጥ እንደ ማለት ነው፡፡

Photo - President Donald Trump
Photo – President Donald Trump

ትራምፕ የቀረጥ ጭማሪ ቢያደርጉ ቻይና በበኩሏ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የቀረጥ ጭማሪ በማድረግ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዷ አይቀሬ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አሜሪከ ያለባት የቻይና በትሪሊዮን የሚቆጠር ዕዳ ይመለስልኝ ካለች የሁለቱ ሀገሮች  ብቻ ሳይሆን የዓለም ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ወደ ለየለት ብጥብጥ ማምራቱ እይቀርም፡፡

የንግድ ስምምነቶችን ማፍረስም ከዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ተቀባይነት የለውም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሀገራት የተሰማማባቸውን እና ያፀደቀችውን አለም አቀፍ ስምምነቶች በብሔራዊ ሕግ ምክንያት መሻር አይችሉም፡፡ ስለዚህ አሜሪካ የተስማማችባቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማለትም የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት ጨምሮ  የመሻር መብት የላትም፡፡

ትራምፕ አፍሪካን ወደ ዳር ይወረውሯታል ወይም ስለ አፍሪካ ትኩረት አይሰጡም የሚል ትንታኔዎች በስፋት እየቀረበ ነው፡፡ በተለይም PEPFAR (President Emergency  Plan For AIDS Relief) እና AGOA (African and Growth Opportunity Act) ፕሬዝዳንት ትራምፕ እውቅና ይነፍጓቸዋል ተብሏል፡፡ PEPFAR ፕሬዝዳንት ቡሽ ጊዜ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያቋቋሙት ሲሆን በአፍሪካ ኤችአይቪን በመከላልና በመቆጣጠር በኩል ግንባር ቀደም ሚና በተለይም በጀት በመመደብ ተጫውቷል፡፡ ለኤችአይቪ የሚሰጠው ድጋፍ መቀነሱ አይቀርም፡፡  ምክንያቱም ኤችአይቪ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ በመምጣቱ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ኢኮኖሚ እያደገ በመምጣት እና ለኤችአይቪ የሚመድቡት ገንዘብ እየጨመረ መምጣት ያለበት በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ አስቀድሞ ኤችአይቪ መከላከል ያለው ድጋፍ ትርጉም ባለው መልኩ እየቀነሰ የመጣ በመሆኑ የሚሰጠው ድጋፍ መቀነስ ከትራምፕ ሥልጣን መውጣት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ እርዳታው ሙሉ በሙሉ ግን ሊቆም አይችልም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በሪፓብሊካን ዘመን ዕርዳታ መጨመር አንጂ መቀነስ አይታይም፡፡   

በሁለተኛ ደረጃ እርዳታ እና ብድሩን የሚሰጡት ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ እንጂ ለአፍሪካ ብለው አይደለም፡፡ ለኤችአይቪ የሚሰጡት ድጋፍ ተመልሶ የሚውለው በአብዛኛው ከአሜሪካን ኩባንያዎች መድኃኒት፣ የመመርመሪያ መሣሪያ ወዘተ… ለመግዛት የሚውል ነው፡፡  ፕሬዝዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ኢትዮጵያ የምትገዛቸው ቦይንግ አውሮፕላኖች በአሜሪካ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን እንደተናገሩ ይታወሳል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ አፍሪካን ወደ ዳር መወርወር ማለት ለሽበርተኝነት መፈልፈል አመቺ ሁኔታ በመፍጠር የአሜሪካን ጥቅም መጎዳት ማለት ነው፡፡ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ምዕራብያውያን በተለይም አሜሪካ ትኩረቱን በሶቬየት ኀብረት በመካከለኛው ምሥራቅ እና ከካናዳ እና ከሜክሲኮ ባሉት የንግድ ግንኙነት አድርጋ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ የሶሻሊዝም ጎራ ትቶት የሄደውን ክፍተት በመሙላት አሸባሪዎቹ በአሜሪካ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ፡፡ ስለዚህ አፍሪካን ወደዳር መወርወሩ ለአሜሪካ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ በመሆኑ እንደገና ትሞክረዋለች ተብሎ አይታሰብም፡፡ 

በሦስተኛ ደረጃ አሜሪካ አፍሪካን ወደ ዳር መወርወር የማትችልበት ምክንያት የእነ ቻይና፣ ብራዚል መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የቀጥተኛ የውጭ እንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ እና የእነዚህ ሃገራት በአፍሪካ ሕዝቦች ላይ ተቀባይነት እያደገ መምጣት እና በአንፃሩ የአሜሪካ ተቀባይነት እና ተሰሚነት እየቀነሰ መምጣት ነው፡፡

በ2ዐዐ8 እ.ኤ.አ. የተፈጠረው የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት አንዱ በዓለም ላይ የምግብ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እና በኢንዱስትሪያላይዜሽን እና በከተሞች መስፋፋት ምክንያት ሊታረስ የሚችለው የመሬት መጠን እየቀነሰ መምጣት ነው፡፡ ትንቢያዎች አንደሚያሳዩት ወደፊትም ቢሆን የግብርና ምርቶች  በተለይም የምግብ ዋጋዎች በየጊዜው እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ደግሞ ነዳጅን ባዮ ፊዩል እንዲተካ ግፊቶች እየበዙ ነው፡፡ በዓለም ላይ ደግሞ 60 በመቶ ሊታረስ የሚችል መሬት የሚገኘው በአፍሪካ ነው፡፡  ስለዚህ በአፍሪካ እንቨስት ማድረግ አዋጭ ነው ፡፡

ሲጠቃለል ትራምፕ አፍሪካን ለአሜሪካ ጥቅም ሲሉ ወደዳር ለመወርወር የሚችሉ አይመስለኝም፡፡

*********

Guest Author

more recommended stories