የሥራ ዕድል በብር አይገዛም

አንድ ወዳጄ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል “የሥራ-ዕድል ለመፍጠር አንቅስቃሴ ተጀምሯል” በሚል ርዕስ የቀረቡ ዘገባዎችን ሰብስቦ በፌስቡክ ገፁ ላይ ለጥፎ አነበብኩ። ጏደኛዬ “በክልሉ ከተፈጠረው የሥራ-ዕድል ይልቅ ‹የሥራ-ዕድል ሊፈጠር ነው› የሚለው ዜና ቁጥር ሊበልጥ ነው” የሚል ትችት ሰንዝሯል። ለምሳሌ፣ ታህሳስ 26/2009 ዓ.ም የቀረበው የዜና ዘገባ፤ “የኦሮሚያ ክልል 6.6 ቢሊዮን ብር ለሥራ-ዕድል ፈጠራ ለማዋል ወስኗል” ይላል። 

በእርግጥ የተመደበው በጀት በጣም ከፍተኛ ነው። በጀቱ የተመደበለት ዓላማ ደግሞ ይበልጥ ወሣኝ ነው። ምክንያቱም፣ አንዳንድ የጥናት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት፣ ሥራ-አጥነት (unemployment)፤ ከድህነት፥ ከማህበራዊ መገለል፥¸ከወንጀል፥ ከጤና ችግር፥ ከቤተሰብ መበተን፣ ከማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት፣ ከአመፅ፣ እንዲሁም ከሽብርተኝነት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ተያያዥነት እንዳለው ይጠቁማሉ። በመሆኑም፣ የሥራ-አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የሚመደብ በጀት በማንኛውም መለኪያ ችግሩ ከሚያስከትለው ጉዳትና ወጪ አይበልጥም። ስለዚህ፣ በዘርፉ እየተመደበ ያለው ከፍተኛ የበጀት መጠን ተገቢነቱ አያጠራጥርም። 

የዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረት “በኦሮሚያ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር፣ እየተመደበ ያለውን ከፍተኛ በጀትን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል እና የሚፈለገውን ያህል የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል አደረጃጀት፣ አሰራርና አመራር አለ ወይ?” የሚለው ነው። ለምሳሌ፣ ለፅሁፉ መነሻ በሆኑት የዜና ዘገባዎች መሰረት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ “በኦሮሚያ ክልል የሥራ-ዕድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ ተጀመረ” በሚል በቢሊዮን የሚቆጠር በጀትና ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጠቀሱ ተዘግቧል። ይህ በራሱ ለዘጠኝ ወራት ያህል የክልሉ መንግስት ከዝግጅት ባለፈ በተጨባጭ ሊታይ የሚችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለመጀመሩን ይጠቁማል።

Photo - Merkato market in Addis Ababa, Ethiopia (Photo - Shutterstock.com)
Photo – Merkato market in Addis Ababa, Ethiopia (Photo – Shutterstock.com)

ስለዚህ ሊሰራ የታቀደው ሥራ ከዝግጅት ምዕራፍ አልፎ በተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው? በእርግጥ ችግሩ ከላይኛው አመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው የድጋፍ አሰጣጥ ድረስ የተወሳሰበ ነው። ሆኖም ግን፣ ዋናው ችግር በመንግስት አመራሮች ዘንድ ያለው የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡

መንግስት አመራሮች ዘንድ የሚስተዋለው የግንዛቤ ችግር ስለ ከሥራ-ዕድል (Employment) ምንነትና ፋይዳ ይጀምራል። የሥራ-ዕድል የዜጎችን አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም ዋንኛ መንገድ ስለመሆኑ ግንዛቤ የሌለው አመራር አለ ማለት ይከብዳል። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ አመራሮች የሥራ-ዕድል ፈጠራን የሰው ሀብት (human capital) እድገት፣ ልማትና ዘላቂነት የሚረጋገጥበት ዋንኛ መንገድ ስለመሆኑ በቂ ግንዛቤ አላቸው ለማለት አያስደፍርም። 

በመሠረቱ የሰው ሀብት ልማት በሌለበት ዘላቂ ልማት (Sustainable development) ማረጋገጥ አይቻልም። ዘላቂ የሰው-ሃብት ልማት ለማረጋገጥ ደግሞ በቂ የሆነ የሥራ-ዕድል መፍጠር የግድ ነው። ስለዚህ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ በሙሉ ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት ልማት በማረጋገጥ ላይ ማዕክል ማድረግ አለበት። በመሆኑም፣ “የሥራ-ዕድል ለመፍጠር” በሚል የሚመደበው በጀት ሆነ የሥራ አፈፃፀም መመዘን ያለበት የሥራ-ዕድል ከተፈጠረላቸው ሰዎች አንፃር ብቻ መሆን የለበትም። ከዚያ ይልቅ፣ “የተሰራው ሥራ ዘላቂ የሆነ የሰው ሃብት ልማት ማረጋገጥ አስችሏል ወይ?” ከሚለው አንፃር ነው። የሥራ-ዕድል የሚፈጠረው ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት እድገትና ልማት ለማረጋገጥ እስከሆነ ድረስ አፈፃፀሙ ከዋናው ግብ ተለይቶ ሊታይ አይችልም። ለዚህ ደግሞ “ዘላቂ የሰው ሀብት ልማት እንዴት ይረጋገጣል?” በሚለው ላይ ግልፅ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። 

በመሰረቱ ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት ልማት የግለሰባዊ ልማት (individual development) እና የማህበራዊ ልማት (Social development) ጥምር ውጤት ነው። በዚህ ረገድ፣ ሁለት የዘርፉ ምሁራን “Human Capital and Sustainability” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ከሰጡት ትንታኔ የሚከተለውን እንመልከት፡-  

“Social development is a product of individual development and vice versa. Social progress begins with the generation of new ideas, higher values, more progressive attitudes leading to pioneering initiatives by individuals, which are later accepted and imitated by other individuals, organized and multiplied, and eventually assimilated by the social collective. … So too, the development of individuality is itself a product of social organizations, institutions and a cultural atmosphere, which impart knowledge, skills and values, make available to each member the cumulative advances of the collective, and provide freedom and opportunity for unique individual characteristics to develop. The sustainability of human capital depends on finding the right balance and relationship between these two poles of human existence.” [Human Capital and Sustainability]

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ በግልፅ እንደተገለፀው፣ ግለሰባዊ ልማት (individual development) የሚረጋገጠው የተለየና አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውና ለራሳቸውና ለማህብረሰቡ የሥራ-ዕድል መፍጠር የሚችሉ ግለሰቦችን በማፍራት ነው። በተመሣሣይ፣ ማህበራዊ ልማት (Social development) ሊረጋገጥ የሚችለው ሥራ-ፈጣሪ ለሆኑ ግለሰቦች ምቹ የሆነ ማህበራዊ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት፣ ዕውቀት፥ ሞያና ልምዶቻቸውን ለብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል በማጋራት፣ እንዲሁም የተለየ አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸው ሰዎች ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ በመፍጠር ነው።

ግለሰባዊ ልማት እና ማህበራዊ ልማትን በጥምረት ማረጋገጥ ሲቻል ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት ልማትን ማረጋገጥ ይቻላል። ነገር ግን፣ ሁለቱን በጥምረት ማረጋገጥ ካልተቻለ ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት ልማት አይመጣም። ስለዚህ፣ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር በሚል የሚሰራው ሥራ የግለሰባዊ ልማት እና ማህበራዊ ልማትን እኩል ማረጋገጥ አለበት፡፡ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚሰራው ሥራ ወደ ግለሰባዊ ልማት ወይም ማህበራዊ ልማት ያዘነበለ ከሆነ ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት ልማት ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚሰራው ሥራ ከሁለት ወደ አንዱ ያዘነበለ ከሆነ መሠረታዊ ዓላማውን የሳተ ነው። 

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ አብዛኞቹ የመንግስት አመራሮች የሥራ-ዕድል ፈጠራን ከግለሰባዊ ልማት አንፃር ብቻ የማየት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ለምሳሌ፣ የሥራ-ዕድል ከመፍጠር ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ አብዛኞቹ የአፈፃፀም ሪፖርቶች እና የዜና ዘገባዎች የሥራ-ዕድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች ብዛት እንደ ዋና የአፈፃፀም መለኪያ የሚጠቀሙ ናቸው። እንዲሁም ለውጥና መሻሻልን ለመለካት ካፒታል እና/ወይም የሰራተኞች ብዛትን እንደ መስፈርት ይጠቀማሉ። ይህ የሥራ-ዕድል ፈጠራን ከግለሰባዊ ልማት አንፃር ብቻ አጥብቦ ከማየት የመነጨ ነው።

ነገር ግን፣ የሥራ-ዕድል የሚፈጠረው ዘላቂ የሆነ የሰው-ሃብት ልማት ለማምጣት ነው። ከላይ እንደተገለፀው የግለሰባዊ ልማት (individual development) እና ማህበራዊ ልማት (Social development) ጥምር ውጤት ነው። የሥራ-ዕድል ለመፍጠር በሚል የተሰራው ሥራ በማህበራዊ ልማት ረገድ ከተመዘገበው ለውጥና መሻሻል አንፃር ካልታየ ዋና ግቡን ስለማሳካቱ ሆነ አለማሳካቱ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በመሆኑም፣ የሥራ-ዕድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች ብዛት እና የድርጅት ካፒታል/የሰራተኞች ብዛትን እንደ መለኪያ በመውሰድ የሚያቀርቡት ሪፖርቶች ለውጥና መሻሻልን በግልፅ አያሳዩም። ስለዚህ፣ አብዛኞቹ የመንግስት ኃላፊዎች በቅድሚያ ሊያስተካክሉት የሚገባው ነገር የሥራ-ዕድል ፈጠራን ከግለሰባዊ ልማት በተጨማሪ ከማህበራዊ ልማት አንፃር ማየት ነው። 

የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ከማህበራዊ ልማት አንፃር ለማየት በቅድሚያ በዚህ ረገድ ለሥራ-ዕድል ፈጠራ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በግልፅ ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ከላይ በተጠቀሰው ጥናታዊ ፅሁፍ ውስጥ ለማህበራዊ ልማት ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል፡-   

“Some forms of social organization actively support the development and flowering of individual capacity, whereas others retard, suppress or stifle it altogether. …All forms of violence are examples of human capital directed for self-destruction as well as for destruction of other forms of capitals. Lack of education and education that degenerates into indoctrination prevents the effective development and utilization of human capital. Social structures that demand conformity´ and uniformity can suppress both the development and expression of human capacity.” [Human Capital and Sustainability]

 ከፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ትምህርት አሰጣጥ እና ተቋማዊ አሰራር አንፃር የተጠቀሱት ዋና ዋና ችግሮች በሀገራችን በስፋት የሚስተዋሉ ናቸው። ከፖለቲካና ትምህርት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለሌላ ግዜ እንተውና፣ በማህበራዊ መዋቅሮች ረገድ ያሉ ችግሮችን እንመልከት። በአጠቃላይ፣ ለሥራ-ፈጠራና ሥራ-ፈጣሪዎች ምቹ ያልሆኑ አደረጃጀቶች፣ ተቋማዊ አሰራሮች እና የአመለካከትና አቅም ችግሮች ናቸው። ሥራ-ፈጣሪ ለሆኑ ግለሰቦች ምቹ የሆነ አደረጃጀትና አሰራር በበቂ ሁኔታ አልተዘረጋም፣ የዳበረ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ሥራ-ፈጣሪዎች ልምድና ዕውቀታቸውን ለብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እንዲያጋሩ ምቹ ሁኔታ አልተዘረጋም፣ ከተለመደው ውጪ የሆኑ ሃሳቦችና አስተያየቶች በነፃነት የሚንፀባረቁባቸው ነፃ መድረኮች የሉም፣ ከተለመዱ የሥራ መስኮች ዉጪ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ተቀብሎ ለማስተናገድና አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ምቹ የሆነ አሰራር አልተዘረጋም። 

ከማህበራዊ ልማት ጋር ተያይዞ በተግባር ከሚስተዋሉት ችግሮች ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፤ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማትና ድጋፍ አሰጣጥ በግል ብቃትና ችሎታ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ፍፁም የሚያገልና ለኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የተጋለጠ ነው። ከሥራ-ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያለው አደረጃጀትና አሰራር ለሥራ-አጦች እንጂ ለሥራ-ፈጣሪዎች ምቹ አይደለም፣ በተለያየ ደረጃ ያሉ የድጋፍና አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች ዘርፈ-ብዙ የሆነ የአቅምና አመለካከት ችግር ይስተዋልባቸዋል። ከሥራ-ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ የተመዘገቡ ስኬቶችን፣ እንዲሁም ልምድና ተሞክሮን ለማጋራት የሚሰራው ሥራ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ ባለመሆኑ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተዓማኒነት አሳጥቶታል፣ ከከፍተኛ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የማማከርና ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር አልተዘረጋም፣ በአብዛኛው የሥራ-ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ በገበያ ጥናት የተደገፈ አይደለም፣ …ወዘተ።

በአጠቃላይ፣ የሥራ-ዕድል ፈጠራ ዋና ግብ ዘላቂ የሆነ የሰው ሃብት ልማትን ማረጋገጥ እንደሆነ በሁሉም አካላት ዘንድ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ግዜ ሊሰጠው አይገባም። የሥራ-ዕድል ለመፍጠር በሚል የሚሰራው ሥራ ግለሰባዊና ማህበራዊ ልማትን እኩል ማረጋገጥ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡ በተለይ ለማህበራዊ ልማት ማነቆ የሆኑ ከፖለቲካ፣ ትምህርትና ማህበራዊ መዋቅሮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረት፣ የሥራ-ዕድል ፈጠራ ረገድ ያለው አፈፃፀም ከአደረጃጀት፣ አሰራርና ከአቅም-ግንባታ አንፃር ከተመዘገቡ ለውጦችና መሻሻሎች አንፃር መገምገም አለበት። 

በዚህ መልኩ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ካልተደረገ ብዙ ቢሊዮን ብር በጀት መመደብ ብቻውን የሥራ-ዕድል አይፈጥርም። “ይሄን ያህል ቢሊዮን ብር ለሥራ-ዕድል ፈጠራ ለማዋል ተወስኗል…እንቅስቃሴ ተጀምሯል” በማለት ብቻ የሥራ-ዕድል አይፈጠርም። የሥራ-ዕድል ፈጠራ በዕውቀት የሚመጣ ለውጥ እንጂ በብር የሚገዛ ቁስ አይደለም። ይህ የፀሃፊው የግል አመለካከት ብቻ ሣይሆን ከላይ በተጠቀሰው ጥናታዊ ፅሁፍ ድምዳሜ (conclusion) ላይ በግልፅ የተቀመጠ ሃቅ ነው፦

“In the history of the collective as in the history of the individual, everything depends on the development of consciousness. Thus, the progressive development of human capital made possible by the continuous evolution of human consciousness is the ultimate determinant of sustainability. [We] call for a much more profound shift in thought and action to make the development of human capacities and fostering of human welfare and well-being the centre-piece of sustainable development strategy.”[Human Capital and Sustainability]

***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories