ለሀገሪቱም ለኢህአዴግም የሚበጀዉ ሀገር ወዳድ ምሁራንን ማዳመጡ ነዉ!

(ኮሎኔል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ)

መግቢያ

በሃገራችን የተከሰተዉን አደገኛ ሁኔታ ስጋት የገባቸዉ ቅን የሆኑ ኢትዮጵያዉያን አገሪቱን ከአደጋ መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የበኩላቸዉን ምክረ ሃሳብ እያቀረቡ ባለበት ሰዓት አንዳችም ኃላፊነት የማይሰማቸዉ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ አሁን ያለዉ ቀዉስ ተባብሶ  የበለጠ ምስቅልቅል ሁኔታ እንዲፈጠር ሆን ብለዉ መርዘኛ የሆነ ቀስቀሳ ከማድረግ አልተቆጠቡም::

መንግስት በሀገሪቱ የተከሰተዉ ሁኔታ አሳስቦት ራሱን በግልጽ ፈትሾና ራሱን ወቅሶ ለችግሩ ይበጃል ብሎ ባሰበዉ መንገድ መፍትሄ በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ጀምሮአል፡፡ መንግስት ችግሩን ያየበት መንገድና ራሱን የገመገመበት ጥልቀት ላይ ጥያቄ ቢኖረንም ከችግሩ ለመዉጣት ፍላጎት ማሳየቱ በራሱ የሚያስመሰግነዉ ነዉ፡፡

የኢህአዴግ ግምገማ ወቅታዊዉን የሀገሪቱን ችግር መሰረታዊ ምንጭ ቆፍሮ ከማዉጣት ይልቅ  ችግሩን ተከትሎ በተፈጠረዉ ዉጤት ላይ ማተኮሩ  ብዙዎቹ ታዛቢዎች  በመፍትሄዉ  ተገቢነት  ላይ እንዲጠራጠሩ ቢያደርጋቸዉ  አይፈረድባቸዉም፡፡  ኢህአዴግ ችግሩን በራሴ መንገድ እፈታዋለሁ ካለ ዉጤቱን በትዕግስት መጠበቅ ልኖርብን ነዉ፡፡  መፍትሄዉ ከዬትም ይምጣ ችግር ፈቺ አስከሆነ ድረስ ልናናንቅ አይገባንም፡፡

1/ የገዢዉ ፓርቲ አመራርን አላላዉስ ያሉ እንቅፋቶች

የገዥዉ ፓርቲ  የላይኛዉ አመራር በሀገሪቱ ዉስጥ  በተፈጠረዉ አጠቃላይ ሁኔታ በታሪክ ተወቃሽ  ላለመሆንና ካለበትም ተጠያቂነት አንጻር ሃላፊነት ተሰምቶት ለመፍትሄዉ ከሞላ ጎደል ቁርጠኝነት ማሳዬቱ የሚያስመሰግነዉ ነዉ፡፡

ይሁን እንጂ እንደምኞቱና እንዳሰበዉ ወደፊት መግፋት እንዳይችል  እንቅፋት የገጠመዉ ይመስላል፡፡  ከድርጅቱ አባላት መካከል  የኢህአዴግ  የላይኛዉ አመራር  በቁርጠኝነትና በወኔ ራሱን ለመለወጥ ያሳየዉን ተነሳሽነት በበጎ ያልተረጎሙት አልጠፉም፡፡ መንግስት ህዝብ እንደሚጠብቀዉ ባይሆንም ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ራሱን እየነቀፈ የዉስጥ ገበናዉንም በግልጽ እየነገረንና ራሱን ለማደስም በተግባር እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሁኔታ አንዳንዶቹ የራሱ ሰዎች ይህን “የመለወጥና የመታደስ ፍላጎት” እንደ መንግስት ድክመትና መፍረክረክ  በመቁጠር ከችግሩ እንዳይወጣ በተለያዩ መንገዶች ጫና እያደረጉበት ነዉ፡፡  ኢህአዴግ አሁን ከሚታየዉ ችግር ለመላቀቅ ጥረት ሲያደርግ ከማበረታታት ይልቅ ራሱን ሳያርም በችግር ማጥ ዉስጥ ተዘፍቆ እንዲቀርና ዓይኑን ጨፍኖ በስህተቱ እንዲገፋበት የሚፈልጉ አሉ፡፡

አገዛዙ በቁርጠኝነት ከችግሩ እንዳይላቀቅ ደንቃራ እየሆኑ ያሉት እነዚህ ወገኖች ቀድሞዉኑ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር በጥቅም ራሳቸዉን ያቆራኙና በግላጭ የህዝብን ኃብት ሲዘርፉ የቆዩ በመሆናቸዉ የኢህአደግን ስልጣን የሚቀንስ ወይንም እስከነ ጭራሹም ስልጣን የሚያሳጣ ሁኔታ ከተፈጠረ የለመዱት ጥቅም እንደሚቋረጥባቸዉ ስለተገነዘቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እነዚህ ስግብግብ የቀን ጅቦች ኢህአዴግ አሁን ካለበት ምስቅልቅል ሁኔታ ሳይላቀቅ በዚህ መንገድ ከቀጠለ ሀገሪቱ ልትበታተን እንደምትችል ጠፍቷቸዉ ወይም ሳይገነዘቡ ቀርተዉ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ህልዉና ይልቅ ለራሳቸዉ ቅድሚያ ስለሚሰጡና ኢትዮጵያ ብትፈራርስም የያዝነዉን ይዘን ዬትም  ሄደን መኖር እንችላለን በሚል ደካማ አስተሳሰብ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ የተማመኑበትና አስቀድመዉ ያዘጋጁት ሌላ ተለዋጭ አገር ሌላ አመራጭ ያላቸዉ ይመስል  ለህዝብ ብሶትና ቁጣ  ደንታ ቢስ መሆናቸዉ ምናልባት ለዚህ ይሆናል ብሎ መጠርጠሩ ተገቢ ነዉ፡፡ እነዚህ ሰዎች  የለመዱትጥቅም አይነካ እንጂ አገሪቱ ዘጠና ቦታ ብትበጣጠስ ጉዳያቸዉ አይደለም፡፡

ከነዚህ ዉጭ ያሉት ሌሎቹ ደግሞ  ያዉ ከመጀመሪያዉኑ የሀገሪቷን መበታተን ሲመኙ የነበሩና በተግባርም ለማተራመስ ብዙ ሲጥሩ የነበሩ የለየላቸዉ ጠላቶቻችን ናቸዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የሌሎች ኃይሎችን የጥፋት አጀንዳ ለማስፈጸም የቆሙ በመሆናቸዉ ቀዉሱ ተባብሶ እንዲቀጥል ቢመኙ ብዙም ሊገርመን አይገባም፡፡ ለአገራችን ትልቅ አሳሳቢ የሆነዉ ወቅታዊዉ አደጋ ግን የዉጭ ስጋት ሳይሆን እዚሁ በራሳችን ያለና እኛዉ የፈጠርነዉ ነዉ፡፡

ሻዕቢያና መሰል የዉጭ ጠላቶች ከሁልጊዜም በላይ አሁን ዉስጣዊ ድክመታችንን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ለአፍታም ባንዘነጋም ተቀዳሚ ትኩረታችን መሆን ያለበት የአንድነታችን ዋነኛዉ ስጋት ምንጭ የሆነዉ ከዉጭ ያልመጣና  እኛዉ ራሳችን መሆናችንን ተረድተን ራሳችንን ለማረም መረባረብ ይገባናል፡፡ በረባ ባልረባዉ ሁሉ ሻዕቢያና  ወኪሎቹን ከማማረርና ጣታችንን ወደ ዉጭ ከመቀሰር ልማድ ካልወጣን አደጋዉን ማስወገድ አንችልም፡፡

የችግሩን ምንጭ እዚሁ ያለ በመሆኑ ቁርጠኝነቱና ፍላጎቱ ካለን  መፍትሄ ማፈላለጉ አይከብደንም፡፡ መፍትሄዉም ምሁራኑ እንዳቀረቡት በክብ ጠረጰዛ ዙሪያ በግልፅ መወያየቱ ነዉ፡፡ እርቅ እንበለዉ ወይንም ሌላ ስም እንስጠዉ ዞሮ ዞሮ አባቶቻችን በለመዱት መሰረት ቁጭ ብለን መነጋገሩ ነዉ መፍትሄዉ፡፡ ከመነጋገሩ ይልቅ የተሸለዉ መፍትሄ “መታኮስ ነዉ! “የሚል ወገን ካለም ለመታኮሱ በኋላ ያደርሰናልና ለዚያ መጣደፍ አይገባንም፡፡

ሀገር ወዳድ በሆኑና ከጠብ ይልቅ እርቅ እንደሚሻል በተረዱ ምሁራን እየቀረበ ያለዉን ሰላማዊ መፍትሄ ሃሳብ የሚያጣጥሉ አንዳንድ ወገኖች “ከእንግዲህ ወይይት ምናምን የምትሉት ነገር ጊዜ ያለፈበት ስለሆነ አይሰራም፡፡” በሚል የሰላሙ ጥረት ላይ መሰናክል እያስቀመጡ ነዉ፡፡ መንግስት “አደጋዉ ተሰምቶኛል፡፡ የራሴን ድክመትም ተረድቻለሁ፤ ለመፍትሄዉም በጋራ እንስራ” ብሎ ጥሪ ሲያደረግ “የችግሩ ምንጭ አንተ ራስህ ስለሆንክ ከአንተ አንዳችም መፍትሄ አንጠብቅም፡፡ ከአንተ ጋር በጭራሽ አንወያይም” ከተባለ እንዴት ተደርጎ ነዉ ከችግር ልንወጣ የምንችለዉ?

ብሄራዊ እርቅ እናድርግ በሚለዉ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ መንግስት አቋሙን እስካሁን ስላልገለጸ በሃሳቡ ይስማማ አይስማማ መገመት አልችልም፡፡ የቀረበዉ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ አስተያት ከመስጠት መቆጠቡ እንደቀድሞዉ አሁንም በጥርጣሬ ዓይን እያየ ሊሆን ይችላል፡፡ መንግስት በራሱ ጥንካሬና በህዝቡ ዘንድ አለኝ በሚለዉ ተቀባይነት የሚተማመን ከሆነ የእርቅ ሃሳቡን ሊያጣጥል የሚችልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ግፋ ቢል ሌላ ምርጫ ቢደረግ እንኳን  መቶ በመቶም (100%) ድምጽ ላያገኝ ቢችልም በርከት ያለ ወንበር እንደማያጣ ለመገንዘብ የሚያዳግተዉ አይመስለኝም፡፡

ከሁኔታዉ እንደምንታዘበዉ ኢህአዴግ እየተጠራጠረ ያለ ይመስላል፡፡ እንዳይጠራጠር ማድረግ የሚያስችሉን ሁኔታዎች ካሉ እንዳይጠራጠር ማድሩ ተገቢ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ  ክፉኛ እየተጠራጠረ እያለ የዕርቅ ሃሳብን ሊቀበል ይችላል ብሎ አይታሰብም፡፡ መንግስት ከስጋትና ከጥርጣሬ ሊወጣ የሚችልበት መንገድ ቢኖር እስካሁን ለሰራቸዉ መልካም ስራዎች እዉቅና የማይነፍግና በቀጣይም እንደድርጅት ህልዉናዉንም አደጋ ላይ የማይጥል ሰላማዊ የመፍትሄ ሃሳብ ሲቀርብ ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከዚህ ዉጭ ግን ከመንግስት ጋር መነጋገር ጊዜ ያለፈበት ጉዳይ አድርገን መንግስትን ዓይንህን ላፈር ካልነዉ ልክ በሌሎች አገሮች እንደደረሰዉ አገዛዙ ሌላ አማራጭ ሲያጣ ለህልዉናዉ ስል በጀመረዉ መንገድ ለመቀጠልና ሁኔታዉ ከከፋ ደግሞ  ኃይል  ለመጠቀም ሊገደድ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ማናኛችንም ብንሆን የማንፈልገዉና ዉጤቱም አጥፊና  አደገኛ የሆነ አማራጭ ነዉ፡፡

Image - Two people reaching one another across the aisle
Image – Two people reaching one another across the aisle

2/ ህዝብን ማረጋጋትና ግጭቶችንማስቆሙ ላይ  ቅድሚያ እንስጥ

በተረጋጋ መንፈስና በአንድ ልብ በመነጋገር  መፍትሄ ለማምጣትም በቅድሚያ አሁን የሚታየዉን የጥፋት ድርጊት ፈጥነን ማስቆም ቅድሚያ የሚሰጠዉ ተግባር መሆን አለበት፡፡  ዜጎች እየሞቱና የአካል ጉዳተኛ እየሆኑ ፤ ንብረታቸዉ እየወደመና  ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ እየተፈናቀሉ እያየንና እየሰማን ስለሌላ ነገር መነጋገር አንችልም፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መደበኛ ስራና ማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጡ እንደቀድሞዉ በአስቸኳይ መጀመር አለበት፡፡

የሀገሪቱንና የዉጭ እንቬስቴሮችን  ንብረት እንደጠላት ንብረት ቆጥረን እያወደምንና በስንት ልመና ያስመጣናቸዉን የዉጭ ባለሃብቶችን እያስበረገግናቸዉ ……. የኢትጵያዉያዊነትን ስምና ክብር ዝቅ የሚያደርግ  ይህን  መሰሉን አሳፋሪ ተግባር በቅድሚያን  ካለስቆምን በስተቀር ልባችን ተረጋግቶ ቁጭ ብለን መነጋገር አንችልም፡፡ ለዓመታት የተለፋበት ንብረት በአንድ ጀምበር እንዴት እንደሚወድም በተግባር አይተናል፡፡ ከሁሉም  ደግሞ የራሳችንን ወገኖች ላይ በደም ፍላት እያደረስን ያለነዉን ጥቃት ዛሬዉኑ ማስቆም አለብን፡፡ እርስበርሳችንን እንድንገዳደል የሚያደርገን  አንዳችም ምክንያት የለምና!

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ ከሚስተዋሉ አንዳንድ ሁኔታዎች መካከል የሚያስገርሙም ፈገግ የሚያደርጉም አልጠፉም፡፡ ኢህአዴግ ወደፊት ከስልጣን ሲወርድ ለመክሰስ እንዲያመቻቸዉ ገና ካሁኑ “የኢህአዴግ ወንጄሎችና ጥፋቶች ናቸዉ” ብለዉ የሚያስቡትን ሁሉ ከዚህም ከዚያም በመቃረም የደለበ የክስ ዶሴ እያዘጋጁ የሚገኙ አሉ፡፡ ለመክሰሱም ለመከሰሱም ቢሆን በኋላ ልንደርስበት ስለምንችል ለዚያ የሚያስቸኩለን ነገር ባልኖረ ነበር፡፡ አሁን ዋናዉ አንገብጋቢ ጉዳይ ወደፊት ኢህአዴግን እንዴት ለፍርድ እንደምናቀርበዉ ሳይሆን አገራችን ከተጋረጠባት አደጋ እንዴት እናዉጣት የሚለዉ ነዉ የሚመስለኝ፡፡

ከሰሞኑ ሁኔታ ከታዘብኩት መካከል ሌላዉ በጣም የገርመኝና ምናልባትም እጅግ እንዳዝን ያደረገኝ ኢህአዴግን ተጠልለዉ በኢህአዴግ ስም እየማሉና ከሌላዉ ዜጋ የበለጠ ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸዉ ሳያንስ ሌላዉን ዜጋ  “የኢህአዴግን  ስም  በክፉ ታነሳለህ !ትተቻለህ!“ እያሉ  መግቢያ መዉጫ ሲያሳጡ የነበሩ የድርጅቱ አባላትና ካድሬዎች ቢያንስ ባለዉለታቸዉ የሆነዉን ድርጅታቸዉንና ከቻሉም ደግሞ አገሪቱን  ከተጋረጠባት አደጋ ለመታደግ አንዳችም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አለመታየታቸዉ ነዉ፡፡

በየከተማ መስተዳድሩ ባሉ  አደረጃጀቶች ፤ በወረዳም ሆነ በቀበሌዎ ደረጃ  ነዋሪዎችና በተለይም ወጣቶችን ከዚህ በፊት በረባ ባልረባዉም ጉዳይ ነጋጠባ እየሰበሰቡ ሲያወያዩና አንዳንዴም ሲነዘንዙ እንዳልነበር ዛሬ ግን በሃገሪቱ ዉስጥ አሳሳቢ ሁኔታ ተፈጥሮ እያዩ  ህዝቡን አወያይተዉ ለማረጋጋትና በሁኔታዉ ላይ የተሟላ መረጃ ለመስጠት አለመሞከራቸዉ እጅግ የሚያስተዛዝብ ነዉ፡፡ በየቦታዉ ያሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ህዝቡን በተለይም ወጣቶች ከዉጭ አገር በሚለቀቁ የተዛቡና የተጋነኑ መረጃዎች ሊወናበዱ እንደሚችሉ በማሰብ ወጣቱን ከአጥፊ ተግባር ለመታደግ ስንቀሳቀሱ አለመታየታቸዉ ኃላፊነታቸዉን የዘነጉ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡ ስለዚህ ኢህአደግ ለጥቅም ሲሉ ካልሆነ በስተቀር በችግር ጊዜ አንዳችም ጥቅም የማይሰጡትን ስድስት ሚሊዮን የሚበልጥ አባል ተሸክሞ ከሚጓዝ በዓላማ ጽናታቸዉና በብቃታቸዉ አስተማማኝ የሆኑትን ብቻ በማስቀረት ሌላዉን ማሰናበት ይገባዋል፡፡

3/ መንግስት ሃቀኛና ሀገር ወዳድ ምሁራን የሚሰጡትን አስተያት ማበር ይገባዋል፡፡

የሀገራችን ምሁራን የወቅቱ ሁኔታ አሳስቦአቸዉ በተለያዩ ሚዲያዎች ለመንግስትም ለህዝቡም የሚበጁ  ጠቃሚ አስተያየቶችንና ምክረ ሃሳቦችን እየሰነዘሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

እንደኔ እምነት በዉጭ አገር ሆነዉ ባላዩት ጉዳይ ላይ የነቀፈታም ሆነ የድጋፍ አስያተያየት   ከሚሰጡት ይልቅ እዚሁ ህዝቡ መሃል ሆነዉ ችግሩንም አብረዉ እየተጋሩ፤ የካድሬ ግልምጫንና የመንግስት ቁንጥጫን ችለዉ የመሰላቸዉን አስተያየት በድፍረት እየሰጡ ያሉ ምሁራንን ልናከብራቸዉና ልናዳምጣቸዉ ይገባል፡፡

በተቃዉሞ ጎራ ካሉትም አንዳንዶቹ በኢህአዴግ ክፉኛ ተቀይመዉና ሆድና ጀርባ ሆነዉ ቢቆዩም  ከሀገራቸዉ የሚበልጥባቸዉ ነገር የለምና መንግስትን “የራስህ ጉዳይ ነዉ፤ ራስህ ተወጣ!” ሳይሉት መፍትሄ በማስቀመጥ የበኩላቸዉን አስተያየት ከመስጠት አልተቆጠቡም፡፡ ለሀገራቸዉ ከመቆርቆር ዉጭ  ከየትኛዉም  ፖለቲካ ፓርቲ ጋር ያልተወዳጁና ገለልተኛ ናቸዉ ተብለዉ የሚገመቱ ምሁራንም የመፍትሄ ሃሳብ ከመሰንዘር ወደ ኋላ አላሉም፡፡ የሚያሳዝነዉ ግን በሀገሪቱ ከሞላ ምሁር መካከል ወደ መድረክ ወጥተዉ ሃሳባቸዉን በድፍረት የሚሰነዝሩት እጅግ ጥቂቶች ብቻ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ አብዛኛዎቹ ምሁራን “ወደፊት የሚሆነዉን እናያለን” በሚል ሃላፊነት በጎደለዉና በግደለሽነት ስሜት  አድፍጠዉ እየተጠባበቁ ነዉ፡፡   

በዚህ ሆርን አፌየርስ (Horn Affairs) ላይ ሳያሰልስ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የመሰለዉን የግል አስተያየት ከነ መፍትሄዉ በማስቀመጥና አስፈላጊ ከመሰለዉም መንግስትን ፍትለፍት በመንቀፍ የሚታወቀዉ ወጣቱ ምሁር ስዩም ተሾመ እንዲሁም ሁልጊዜም  በዉብ ብዕሩ ስለ ኢትዮጵያ ሲዘምርላትና ቅኔ ሲቀኝላት የምናወቀዉ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራም ከሰሞኑ “በአዲስ አድማስ ጋዜጣ “ላይ ያቀረበዉ ልብ የሚነካ ተማጽኖ አንብቦ  በሀገሩ መጻኢ ዕድል አንዳች ስጋት የማይሰማዉ ኢትዮጵያዊ ካለ እሱ ከገዛ አገሩ ጋር የተጣለና የሆነ ችግር ያለበት መሆን አለበት፡፡ ለአብነት ያህል ብዬ ከገለፅኳቸዉ ከሁለቱ ምሁራን ዉጭም ሌሎች ፖሊከኞችና  ምሁራን በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይና ተቀራራቢ ሀሳብ እያቀረቡ እንደሆነ አዉቃለሁ፡፡

አብዛኛዎቹ  አገር ወዳድ ኢትዮጵያን እያቀረቡት ያለዉ አስተያየትና ምክረ-ሃሳብ  ከሞላ ጉዳይ ተመሳሳይ ሲሆን  እሱም  “ብሄራዊ እርቅና ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት “የሚል ነዉ፡፡  ከወቅቱ አደጋ የምንወጣበትና ለዘለቄታዉም ለሁላችንም በእኩል ደረጃ  የምትመች ኢትዮጵያን ለዘለቀታዉ ለመመስረት የሚያስችለን ብቸኛዉ መንገድ ሰላማዊ ዕርቅና ብሄራዊ መግባባት ነዉ እያሉ ነዉ፡፡ ከዚህ ለየት በሚል መልኩ  በአዲስ እድማስ ጋዜጣ ላይ  የበለጠ ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ “ዳግማዊ አሮማይ!” (አበቃ!) በሚል አስበርጋጊ  ርዕስ ስርአቱ እያበቃለት መሆኑን እንድናዉቀዉ የመርዶ ያህል የነገሩንም አልጠፉም፡፡

እነሱ ያሉት  እዉነት ሆኖ  ሁሉም ነገር ያበቃለት ከሆነ እርቅ፤ ብሄራዊ መግባባት፤ የሽግግር መንግስት ወዘተ…..የሚባሉት የመፍትሄ ሃሳቦች ታዲያ ምን ሊያደርጉልን ነዉ ?እርቅ ወይም ሌላዉም ሰላማዊ መንገድ እኮ መልካም ነገር ሊያመጣ ይችላል በሚል ግምት ተስፋ በማድረግ እንጂ አንዳችም ነገር የማይፈይድ ከሆነ ላበቃለትና ላለቀ ነገር ለምን መመካከር ያስፈልገናል ?በርግጥ  የሃገራቸዉ ጉዳይ አሳስቦአቸዉ ሃሳባቸዉን ከነመፍትሄዉ በድፍረት በማጋራታቸዉ ከሌሎች አድፋጭ ምሁራን አንጻር ሲመዘኑ ምስጋና የሚገባቸዉ ነዉ፡፡ የዜግነታቸዉን ግዴታና  የምሁርነታቸዉን ኃላፊነት ተገንዝበዉ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ማንኛዉም ዓይነት ሃሳብ የሚሰነዝሩ ዜጎች ምንጊዜም ሊበረታቱ ይገባል፡፡ በተለይ እንደዚህ “ጭንቅ!“ ብሎን ማጣፊያዉ ባጠረን  ሰዓት እንደዚህ ደፋር ብለዉ የዉስጣቸዉን አዉጥተዉ የሚናገሩ ምሁራን በጣም  ያፈልጉናል፡፡

ብዙዎቹ ምሁራንም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የብሄራዊ ዕርቅ ሃሳብን ሲያመጡ አንድ በጋራ የተግባቡበት የሚመስለዉ ነገር ኢህአዴግ እያበቃለት መሆኑና  ቶሎ አንድ መፍትሄ ካልተፈለገ ለሀገሪቱ እንደማይበጃት በማመን ይመስለኛል፡፡

ምሁራን “ስለ ብሄራዊ እርቅና የሽግግር መንግስት“ ሃሳብ ሲሰጡ  መጪዉን አደጋ ታሳቢ በማድረግ ጭምር በመሆኑ ይህ ሁኔታ በገዢዉ ፓርቲ በኩል ምን ያህል ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል ብለዉ አስበዉ እንደሆነ አላዉቅም፡፡  ምክንያቱም ከዓመታት በፊትም በሀገሪቱ ዉስጥ የሆነ ዉጥረት በተፈጠረ ቁጥር ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ሲቀርብ እንደነበርና ገዢዉ ፓርቲም “ከማንም ጋር የግል ጠብ ስለለለኝ የምታረቀዉ ነገር አይኖርም” በማለት ሲላስደነገጣቸዉ ከዚያ በኋላ ደፍሮ ጉዳዩን በይፋ ያነሳም የለም፡፡

የሽግግር መንግስት የሚባለዉ  የመፍትሄ ሃሳብም ለገዢዉ ፓርቲ ምቾት የማይሰጥና የማይደገፍ ሆኖ ቆይቷል፡፡  ኢህአዴግ አሁንም በዚሁ “የግትርነት” አቋሙ ላይ ነዉ? ወይንስ አደጋዉ በትክክል ተሰምቶታል? የሚለዉን ጥያቄ በትክክል መመለስ የሚችለዉ ራሱ ነዉ፡፡ ቢያንስ አሁን ያለዉ የሀገሪቱ ሁኔታም ሆነ የራሱ የድርጅቱ ዉስጣዊ ጥንካሬ ከዚህ በፊት ይሄዉ ጥያቄ ሲቀርብለት በነበረበት ወቅት እንደነበረዉ ሳይሆን አሁን ሁሉም ነገር የተወሳሰበ መሆኑን ለመረዳት ስለማይቸግረዉ ጥያቄዉን እንደድሮዉ ያጣጥላል ብዬ አላስብም፡፡  ኢህአዴግ ይሄን ያህልም ለራሱ የሚጠቅመዉን የማያዉቅ “ጅል“ አድርጌም አልገምትም፡፡

መንግስት የቀረበለትን ምክር ለመቀበል መጀመሪያ ነገር ፈጦ የሚታየዉን  አደጋ “እዉነት” መሆኑን  ራሱን ማሳመን አለበት፡፤እኛ በምናስበዉ ደረጃ መንግሰትም አደጋዉን ተገንዞባታል ለማለት የሚቻለዉ አደጋዉን ለማስወገድ በተጨባጭ የሚወስደዉን እርምጃን በማዬት ነዉ፡፡ መንግስት ተዳክሟል ሃገሪቱም ልትፈራርስ ነዉ ሲባል “አጉል ስታሟርቱ ነዉ እንጂ ከመጠነኛ ችግሮች ዉጭ ይሄን ያህልም የሚያሳስብ  አደጋ የለም” ካለ ኢህአዴግ እኛ በሰጋነዉ ደረጃ ሁኔታዉ አላሰጋዉም ወይንም ችግሩን አልተገነዘበም ማለት እንችላለን፡፡

ችግሩን በቅጡ ተረድቶ ነገርግን ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት ጋር የሚመጥን መፍትሄ ማስቀመጥ ቸግሮት ከሆነ ከህዝብና ከምሁራን ጋር መመካከርና አግዙኝ ማለት ነዉ ያለበት፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን አደጋዉን ፈርቶ መፍትሄዉ ሲቀርብለትም አጣጥሎ ሁሉን ሸሽቶ መዝለቅ አይችልም፡፡  ኢህአዴግ ብቻ የሚያዉቀዉና ምሁራንና ህዝቡ ግን ያልተገለጠላቸዉ አስካሁን ያልተጠቀመበት ፍቱን የሆነ መፍትሄ ሊኖረዉ ከቻለ እሰዬዉ ነዉ፡፡ አስካሁን ያልሞከርኩት አዲስ ከችግር መዉጫ ዜዴ ሲላለኝ እሱን አስከሚሞክር ታገሱኝ ካለም መታገሱ አይከፋም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ አለኝ የሚለዉን የመጨረሻ አማራጭ ሞክሮ  እንደማያዋጣዉ ካልተረዳ በስተቀር እርቅ የተባለዉን እንደማይቀበለዉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ አደጋዉ ካልታየዉ ወይም ደግሞ አደጋዉን በሚገባ ተረድቶ ነገር ግን የፈለገዉ ይሁን እንጂ ከአቋሜ ዝንፍ አልልም ካለ ምንድነዉ ሊደረግ የሚችለዉ?ይሄ ነዉ አሳሳቢዉ ጉዳይ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እስካሁን በታሪካችን ሰምተን በማናዉቀዉና እንደዚህ ዓይነት ክስተት ሊፈጠር ይችላል ብለን በማንገምትበት ሁኔታ አንድን ብሄር ለይቶ የማጥቃት ዘመቻ እየተካሄደ መሆንኑን እየሰማን ነዉ፡፡ ለዘመናት በወንድማማቾነት ተፋቅረዉ በኖሩ ህዝቦች መሃል የዚህ ዓይነት ጥላቻ መስፈኑ እጅግ የሚያሳዝን ነዉ፡፡ አደጋዉም በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይገደብ በብርሃን ፍጥነት ሌላዉን የሀገሪቱን አካባቢ እያደራሰ መሆኑን እኛም መንግስት እኩል እንገነዘባለን፡፡ (በዚህች ሰሞን የመረጋጋት ሁኔታ ታይቷል መሰለኝ እሰዬዉ!) ነገርግን የኢህአደግ አመራር አደጋዉን አቃሎ ካየዉ ለመፍትሄዉ ይተጋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ አደጋዉን በቅጡ ካልተረዳ ትክክለኛ መፍትሄ ማምጣት አይችልም፡፤ከሁሉም የከፋዉ ነገር ደግሞ አደጋዉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ያለበት ፍጥነት ሌላ መፍትሄ ፤ሌላ ጥናት፤ ሌላ ፖሊሲ ፤ሌላ ሹም ሽር በማድረግ ለመፍታት ጊዜ የማይሰጥ መሆኑ ነዉ፡፡

አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ራሳቸዉ እንኳን የማያምኑበትን መፍትሄ  ህዝቡ እንዲያምንላቸዉ መፈለጋቸዉ አስገራሚ ነዉ፡፡ ብሄር ለይቶ እየተደረገ ያለዉን እስቀያሚ ትርኢት እያዩ እንደኛዉ ከንፈር ከመምጠጥ በዘለለ ድምጻቸዉን ከፍ አድርገዉ በግልጽ ለማዉገዝም ሆነ ቆራጥና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ለመዉሰድ አለመድፈራቸዉ መልካም አይደለም፡፡ ያለ ጥፋቱ በግፍ ለተገደለዉ፤ የአካል ጉዳት ለደረሰበትና ለዘመናት ከኖረበት ቀዬ ለተፈናቀለዉና ንብረቱ ለወደመበት ሁሉ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸዉ ህገወጥ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዉሎ ለፍርድ ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት ስለመኖሩ እስካሁን አልሰማንም፡፡ መንግስት የችግሩን ምንጭ ለመረዳት መዘግየቱ ሳያንስ አሁንም ነገሩን ቀለል አድርጎ ማዬቱና ቢያንስ የአደጋዉን መኖር ባመነበት ደረጃ የሚመጥን መፍትሄ ለማስቀመጥ እንኳን ባለመቻሉ ምክንያት አስካሁን ከደረሰዉ  በላይ የከፋ አደጋ ወደፊት እንዳይደርስ መስጋታችን አይቀርም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች ባለፈዉ የደርግ አገዛዝ  ሲደርስባቸዉ ከነበረዉ ጭቆና ራሳቸዉን ነፃ ለማዉጣት መራራ ትግል በማድረግ ጨቋኙን ስርአት አስወግደዉ  ይበጀናል ያሉትን አዲስ ስርአት መመስረት መቻላቸዉ ይታወቃል፡፡ በደርግም ሆነ በቀደመዉ ዘዉዳዊዉ ስርአት በሀገሪቱ ዉስጥ ግጭቶች ነበሩ ከተባለ የነበረዉ ግጭት በህዝብና በአገዛዙ መካከል እንጂ በህዝቦች መካከል አልነበረም፡፡ በወቅቱ በህዝቦች መካከል በግጦሽ መሬት ሰበብ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ዉጭ ከሰሞኑ እንደተከሰተዉ ዓይነት የዘረኝነትና አንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ጥቃት  ከዚህ  በፊት ስለመኖሩ አላዉቅም፡፡ አሁን በአገራችን የተከሰተዉ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ሊደርስ ይችላል ብለን ያልገመትነዉና መሆን የማይገባዉ መጥፎ ሁኔታ ነዉ፡፡ ይህን ሁኔታ ልንደብቀዉ የማንችለዉ መሬት ላይ ያለ ሃቅ ነዉ፡፡ ፈጥነን ሁኔታዉን ካልተቆጣጠርነዉ ከዚያ በኋላ ዘግይቶ የሚመጣ መፍትሄ ሁሉ ዋጋ አይኖረዉም፡፡ ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሚሆነዉ ከዚህ በኋላ ሁኔታዉን መቆጠጠር ብንችል እንኳን እርስበርሱ ደም የተቃባዉን ህዝብ በምን ተአምር ልናስታርቀዉ እንደምንችል ነዉ፡፡

አስቀድሜ  የጠቀስኩት ስዩም ተሾመ የተባለዉ አምደኛ  “ኢህአደግ ቀባሪ እንጂ መካሪ አይሻም!” በሚል  ርእስ በቅርቡ ለአንባቢያን ያደረሰዉ መልእክት ላይ ኢህአዴግ ብንመክረዉ ብንመክረዉ አልሰማ ብሏል በሚል በኢህአዴግ እጅጉን የተሰላቸና ተስፋ የቆረጠ በሚያስመስል ሁኔታ ቅሬታ ያዘለ ስሜቱን አካፍሎናል፡፡ ኢህአዴግ የዚህ መልክ በግልጽ የሚመክሩና የሚገስፁ ዜጎችን ማግኘት እንደ መታደልና እንደ ትልቅ ፀጋ ሊቆጥረዉ ሲገባ በሩን ጥርቅም አድርጎ መዝጋቱ የበለጠ እየጎዳ ያለዉ ራሱን ነዉ፡፡ ኢህአዴግ መስማት ከለመደዉ ዉጭና መስማት የማይፈልገዉን  ለየት ያለ ሃሳብ የሚሰጡ ምሁራን በዚህ በችግር ጊዜ የሚሰጡት ሃሳብ ለህዝቡም ለኢህአዴግም የሚበጅ ስለሆነ ከራሱ ካድሬዎች የበልጥ ለነሱ ጆሮዉን ማዋስ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ያለበለዚያ ስዩም እንዳለዉ ከመካሪዉ ይልቅ ቀባሪዉን ከመረጠ  ከምክር ይልቅ ከመከራ እንዲማር ይገደዳል ማለት ነዉ፡፡  

4/ ኢህአዴግ የዕርቅ ሃሳብን ለምን ይሸሻል?

“የመፍትሄ ያለህ በሚባልበት” በዚህ ሰዓት ኢህአዴግ እርቅና ድርድርን የማይፈልግበት ምክንያት ምንድነዉ? የሚለዉ ጥያቄ በደንብ መፈተሸ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሁልጊዜም ይሄን ጥያቄ ለምን ይሸሻል? በርግጥ ኢህአዴግን ተክተን ለጥያቄዉም ትክክለኛ መልስ መስጠት ባንችልም ነገር ግን መገመት የሚከለክለን ነገር አይኖርም፡፡

ኢህአዴግ ጥያቄዉን አንዲህ አምርሮ እንዲጠላ የተገደደበትን  ምክንያት ማወቅ የምንችለዉ  ከእርቅና ከሽግግር መንግስት ምስረታ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሊያጣ የሚችለዉ ነገር ምን እንደ ሆነ መገመት ከቻልን ብቻ ነዉ፡፡ ያን መገመት ከቻልን  በከፊልም ቢሆን ወደ መልሱ እንቃረባለን ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ እኔ አመለካከት የሚቀጥሉትን ሁኔታዎች ከግምት ማስገባት እንችላለን፡፡

አንደኛ፡- ከሥልጣን ስስት የመነጨ ፍርሃት

የኢህአዴግ ዋነኛዉ ችግሩ ስልጣኑን የሚያሳጣ አንዳችም ሁኔታ እንዲፈጠር አለመፈለጉና  የሚቀርብለትን የሰላም ሃሳብ ሁሉ በፍርሃት (ስጋት) ማዬቱ ይመስለኛል፡፡ ለሃያ አምስት ዓመታት በተከታታይ ያለማንም ጣልቃገብነት ሁሉንም ስልጣን ጠቅልሎ እንዳሻዉ ሲያደረግ የነበረ በመሆኑ ይሄን ሁኔታ ማጣት አይፈልግም፡፡ ስልጣን ደግሞ የብልፅግና አስተማማኝ ምንጭ በመሆኑ ከአመራሩ ጀምሮ ወደታች ያለዉ ተራ አባል ሁሉ ሳይቀር በዝርፊያ ሃብት ሲያካብት የቆየ ስለሆነ ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ በጭራሽ አይፈልግም፡፡

አስካሁን እንደተስተዋለዉ ኢህአዴግ በምርጫም ይሁን በሌላ ሰላማዊ መንገድ ስልጣን ሊለቅ የመቻሉን ጉዳይ ለጊዜዉ ትተን  ከዚያ በመለስ ቢያንስ በተወሰኑ የመንግስት ሃላፊነት ቦታዎች ላይ ከፓርቲዉ አባላት ዉጭ ያሉ ዜጎችን በመመደብ በሙያቸዉ እንዲሰሩ አለመፍቀዱ ከዚህ በኋላ በዚህ መቀጠል እንደማይችል ለመረዳት አያዳግተዉም፡፡ ሁሉም የሚስማማበት ነገር ኢህአዴግ ሀገሪቱን ለማልማት ካደረገዉ ጥረት ባልተናነሰ ደረጃ የራሱንም ሰዎች ለማልማት (ለማበልጸግ) ረዥም ርቀት መጓዙን ነዉ፡፡ (ቢያንስ ሀገር ሲዘረፍ አይቶ እንዳላየ በዝምታ ሲያልፍ ነበርና)

ስለዚህ ይሄን ጥቅም የሚነካ ማንኛዉም የመፍትሄ ሃሳብ በኢህአዴግ ዘንድ ተቀባይነት ቢያጣ  ልንገረም አይገባም፡፡  የስልጣን ጉዳይ በኢህአዴግ ዘንድ ለድርድር የማይቀርብ በመሆኑ ከዚያ መለስ ባሉት ጉዳዮች ላይ ነዉ መነጋገር የሚፈልገዉ፡፡ ለሰላማዊ መፍትሄ በሩን እንዲዘጋ ያደረገዉም ይሄዉ ለስልጣን ያለዉ ሰስት ነዉ የሚመስለኝ፡፡ የኢህአዴግ ግትር አቋም በሱ ለተማረሩ ሌሎች ዜጎች  ብቻ ሳይሆን እጅግ አስተዋይና ሚዛናዊ ለሆኑ ጥቂት የገዛ አባለቱና ደጋፊዎቹም  ጭምር ነዉ፡፡ የመንግስት ስልጣንን ይዞ ለመቆየት ስለተፈለገ ብቻ ከዚህ በላይ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይቻል የተረዱ የድርጅቱ ሰዎችም በዚህ ቅጥ ያጣ የሥልጣን ስስት ድርጅታቸዉን ሳይታዘቡት የሚቀሩ አይመስለኝም፡፤

ሁለተኛ:- በድርጅቱ ዉስጥ ባሉ አክራሪዎች የሚደርስበት ከፍተኛ ተፅእኖ አላላዉስ ሲላለዉ

ከዚህ በፊት የኢህአዴግ(መንግስት) አመራር በሃገሪቱ ላይ ሊከሰት ስለሚችለዉ አደጋ በተደጋጋሚ እየተነገረዉ አደጋዉ አልታይህ ብሎት ሃሳቡን ሲያጣጥል የቆየ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ዛሬ ከምንጊዜም በከፋ ችግር ዉስጥ ወድቆ  ሁሉም ነገር ሊያከትምለት ጫፍ ላይ መድረሱንና ከዚህ ቀዉስና አደጋ ማምለጫ መንገድ ሁሉ እየተዘጋ መሆኑን ኢህአዴግ ሳይገነዘብ ይቀራል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ዋናዎቹ አመራሮች ከማንኛችንም በተሻለ አደጋዉን እንደተገነዘቡት አልጠራጠርም፡፡  ይሁን እንጂ ከዚህ ችግር ለመዉጣት እየተጠቀሙበት ያለዉ ዜዴ ግን ያዉ እንደ ድሮዉ ይመስላል፡፡

ለዚህ ዳተኝነት ኢህአዴግን የዳረገዉም የራሳቸዉን ጥቅም ከህዘብ ጥቅም በላይ ያደረጉና በኢትዮጵያ ላይ በተጋረጠዉ አደጋ ድንገጥ እንኳን የማይሉ፤ የሀገሪቱ መበታተን ደንታ የማይሰጣቸዉ አንዳንድ አባላቱ እየተጫኑት እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ይሄ በሁሉም አገሮች የተከሰተ ጉዳይ ነዉ፡፡ ከደርግ ዘመኑ ኢሠፓ አመራሮችና አባላት ዉስጥ ጥቂት መልካም አሳቢዎች እንዳልጠፉ ሁሉ ከኢህአዴግም ዉስጥ እኩይ ዓላማ ያላቸዉ ጥቂት ሰዎች አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡ ለራሱ ለኢህአዴግ አመራርም ቢሆን የማይመለሱ፤ አመራሩን እጅና እግሩን ተብትበዉና አላላዉስ ብለዉ አንዳችም እርምጃ እንዳይወስድ  እንቅፋት የሆኑ አመራሮች  እንደማይጠፉ መገመት እንችላለን፡፡

በድርጅቱ ዉስጥ ያሉት የዚህ ዓይነቶቹ አደገኛ ሰዎች በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም ለአመታት ባካበቱት ሀብትና በዘረጉት የግኑኝነት መረብ እንዲሁም ከጀርባቸዉ ባሰለፉት ጠንካራ መቺ ኃይል እጅጉን የሚፈሩ በመሆናቸዉ የእነሱን ተፅኢኖ ተቋቁሞ ለመሄድ የሚችል ሰዉ ቢኖር ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲል ራሱን መስዋእት ለማድረግ የቆረጠ አመራር ብቻ ነዉ፡፡ የድርጅቱ ማነቆ የሆኑ የፓርቲዉን አመራሮች በስም ጠቅሶ ለመናገር ባይቻልም  ቢያንስ ግን ድርጅቱ ለመሰረታዊ ለዉጥ ቁርጠኝነቱ እንዳይኖረዉ ያደረገዉ ይህ ሁኔታ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በተለይ ሀገሪቱን በጠራራ  ፀሃይ እየዘረፉ ሲላሉ ሰዎች በቂ መረጃ እያለዉ የኢህአዴግ አመራር ጨከን ያለ እርምጃ ለመዉሰድ ማመንታቱ በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ ከህዝብ ጉዳይና ከፓርቲ ጉዳይ ቅድሚያዉን ለማን እንደሚሰጥና  ለመምረጥ ይቸግረዋል የሚባለዉም ያለምክንት አይደለም፡፤

ሶስተኛ፡- የተጠያቂነት ስጋት የፈጠረዉ ችግር

በየትኞቹም አምባገነን አገዛዝ በነበረባቸዉ አገሮች መሪዎች በፈቃደኝነት ስልጣን ለመልቀቅ ስለማይፈልጉ ያለዉደታቸዉ በግዴታ በኃይል ወይም በዉጭ ተጽኢኖ ከስልጣን ሲወርዱ ከዚህ በፊት ለፈጸሙት ጥፋቶች ሁሉ በህግ እንደሚጠየቁ  ይታወቃል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ከዚህ በባሰ ሁኔታ  የበቀል እርምጃ ሲወሰድባቸዉ እንደነበር ከበቂ በላይ አብነቶች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም አምባገነን መሪዎች  ከስልጣን ወርዶ ከመዋረድና የበቀል ጥቃት ሰለባ ከመሆን ይልቅ እዚሁ ስልጣን ላይ አስከ መጨረሻዉ ሙጭጭ ብለዉ መቆየትን ይመርጣሉ፡፡

ጊዜዉ ይጠር ወይንም ይርዘም እንጂ አንድ ቀን ከስልጣን ተጎትተዉ ከመዉረድ ስለማያመልጡ ከስልጣን የወረዱ እሌት ልክ እንደፈሩት ወደወህኒ መወርወራቸዉ የማይቀር ይሆናል፡፡ ይሄን ክስተትም ሁሉም አምባገነን መሪዎች ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ፡፡ ገነት አየለ የተባለችዉ ደራሲ የቀድሞዉን መሪ ኮ/ል መንግስቱን ቃለ መጠይቅ ባደረገችበት የመጽሃፏ ሁለተኛዉ ቅጽ ላይ ስለዚሁ ጉዳይ ኮሎነሉን ጠይቃ ነበር፡፡  “የአፍሪካ መሪዎች ለምንድነዉ ስልጣን ለመልቀቅ ፈጽሞ የማይፈልጉት?” የሚል ጥያቄ ነበር ያቀረበችዉ፡፡ ወይዘሮ ገነት ኮሎነል መንግስቱን “አርሶስ ኢህአዴግ በግድ አስከሚያባርሮት ድረስ ለምንድነዉ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ያሉት?” ብላ መጠየቅ አላስፈለጋትም፡፡  ኮ/ል መንግስቱም የሰጧት ምላሽ ለመጀመሪያ ጊዜ እዉነት የተናገሩበት አጋጣሚ ነበር የሚመስለኝ፡፡ በአጭሩ ኮሌነሉ የሰጡት ምላሽ የህዝቡን የበቀል እርምጃ በመስጋት እንደሆነ ነበር የገለጹት፡፡ ስለራሳቸዉ በቀጥታ መናገር ስላልፈለጉ  “እኔም ወያኔ በኃይል እስከሚያወርደኝ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ያልኩትም በዚህ ስጋት መነሾ ነዉ” የሚል ዓይነት ድምፀት የነበረዉ መልስ ከመስጠት አልቦዘኑም፡፡

ስለዚህ የኛዉ ኢህአዴግም እርቅና የሽግግር ስርአትን አለመመፈለጉና ስልጣን የሚገኘዉ በህዝብ ድምጽ በምርጫ ካርድ ብቻ ነዉ እንጂ በድርድር እንደ ቅርጫ የማከፋፍለዉ፤ እንደ አቁብ በዕጣና በተራ የማድለዉ  አይደለም “እያለ ብዙ ተአማንነት ባልነበረዉ ምርጫ  አስካሁን ስልጣን ላይ ለመቆየት የሞከረዉ በዚህ ምክንያት እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡  የሽግግር መንግስት ምስረታን  ተከትሎ በሚደረገዉና እሱ እንደቀድሞዉ ሊቆጣጠረዉ በማይችለዉ ምርጫ  አብላጫ ድምጽ ላየገኝ እንደሚችል ስለሚረዳ አስቀድሜ በጠቀስኳቸዉ ስጋቶች  መነሾ ይህን ጥያቄ ሲሸሽ ቀይቷል፡፡ የሽግግር መንግስት የሚባል ነገር ሳይኖርና እርቅም ሳይደረግ አንዳንድ ቀዶ ጥገናና እድሳት እያደረገ በራሱ ላይ አንዳችም መሰረታዊ ለዉጥ ሳያደርግና አሁን በሚታየዉ  ዉጥረት ዉስጥ ሆኖ  እሰከሚቀጥለዉ የምርጫ ዘመን ስልጣኑን  ሳያስነካ ለመድረስ የሚያበቃዉ ዕድሜ ይኖረዋል ብለን ለመናገር እንቸገራለን፡፡ ኢህአዴግ ግን በዚህ መንገድ መጓዝ  እንደፈለገ እየሰጠ ካለዉ መግለጫና ቃለምልልስ ለመረዳት አያዳግተንም፡፡

5/ የሽግግር መንግስት የግድ ነዉ? ድጋሚ ምርጫ ማድረግስ አይቻልም?

ኢህአዴግ የሽግግር መንግስት የሚባለዉን ተቀብሎ  በምርጫ ዕድሉን ለመሞከር ከፈቀደ ያለአንዳች የምርጫ ማጭበርበር  ሊያሸንፍ የሚችልበትም ሰፊ ዕድል ይኖረዋል፡፡ እንዲያዉም ከሌሎቹ ፓርቲዎች የተሻለ ዕድል ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢህአዴግ  አስካሁን  በገነባዉ ድርጅታዊ አቅምና በርካታ ቁጥር ያሉት አባላቱና በሚሊዮኖች የሚገመቱ ደጋፊዎቹ ፤ለዓመታት በከተማም ሆነ በገጠር በዘረጋዉ ኔትዎርክ፤ እንደድርጅትም የካበተ ልምድ መኖር ወዘተ ይሄን ሁሉ ተጠቅሞ አንዳችም የካድሬ ግርግርና የምርጫ ካርድ ማምታታት ሳያስፈልገዉ ምርጫዉን አሸንፎ ደጋፊዉንም ተቃዋሚዉንም ሁላችንንም እንድናደንቀዉ ሊያደርገን  እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡

ከዚህ ዉጭ ግን“ እርቅም የለም፡፡  ሽግግርም የለም ! ” ብሎ ድርቅ ካለ ዞሮ ዞሮ ስልጣን በግድ መልቀቁ ባይቀርለትም እንኳን ብዙ ዉድመት ካስከተለ በኋላ ስለሚሆን  ዉጤቱ ለማንም የማይበጅና አፍራሽ እንደሚሆን ለመረዳት አያዳግተዉም፡፡ ምናልባት ኃይል ለመጠቀም የሚፈልግ ወገን ካለ ኢህአዴግም ራሱን ለመከላከል ሲል ኃይል ለመጠቀም መገደዱ አይቀርም፡፡ ስልጣን ላለመልቀቅ ወታደራዊ ኃይልን እንደ መጨረሻዉ አማራጭ (last resort) የመጠቀም ጉዳይን “ያዋጣኝ ይሆን?” እያለ በአይምሮዉ የሚያሰላስል ከሆነ ሊከሰት የሚችለዉን የርስ በርስ ጦርነትና ያን ተከትሎም ሀገሪቱ ልትበታተን እንደምትችል ከማንኛችንም በበለጠ ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ አገሪቱ ከተበታተነች ደግሞ ኢህአዴግም ሆነ ሌላዉ ፓርቲ ሊመራ የሚችለዉ ህዝብም አገርም አይኖረዉም፡፡

የደርግ መንግስት የሰራዉን ስህተት ኢህአዴግ መድገም የለበትም፡፡ ኢህአዴግ ገና በረሃ እያለ የደርግን (ኢሠፓን )የሚያካትት ጊዜያዊ የሽግግር  መንግስት እንዲመሰረት ሃሳብ አቅርቦ እያለ ደርግ ግን ይህን “ወርቅ” የሆነ ዕድል ሳይጠቀምበት በመቅረቱ በኢህአዴግ ተገፍትሮ ወደቀና በወንጀለኛነት ለመፈረጅ በቃ፡፡ ደርግ እንዴት ትላንት ገንጣይ ወንበዴ ብዬ ከተፋለምኩት ጋር እኩል ቁጭ ብዬ እደራደራለሁ ብሎ በመናቁ እንደሆነ እናስታዉሳለን፡፡ ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችና ምሁራን የሚሉትን እንደደርግ ባያናነቅ መልካም ይመስለኛል፡፡  

6/ ተአማኒነት ያለዉ ምርጫ በድጋሚ ማድረግ ከሽግግር መንግስት የተሻለ አመራጭ ነዉ

ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ለመመስረት እንደ አንድ አመራጭ መታየቱ ባያስከፋም ነገር ግን መሰረታዊ ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ የበለጠ ትርምስና ቀዉስ ሊያስከትል የሚችል ነዉ፡፡ የዲሞክራሲና የመቻቻል ባህላችን አለመዳበርና የፓርቲዎች ከሀገራዊ አጀንዳ ይልቅ ጠባብ የአካባቢጉዳይን ከማስፈጸም ያላለፈ ዓላማ ያለለለቸዉ ፤ድርጅታዊ አቅማቸዉም ሆነ ተሞክሮአቸዉ ደካማ በሆነበት አገር ዉስጥ የሽግግር መንግስት መመስረት ሆን ተብሎ አደጋን እንደመጋበዝ ነዉ የሚቆጠረዉ፡፡ ሀገሪቱን በብቃት የመምራት ሃላፊነትን ለመቀበል የሚችል ጠንካራ መዋቅር በለለበት ሁኔታ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መሞከር የሚታሰብ አይደለም፡፡

ስለዚህ የተሻለ መፍትሄ ሊሆን የሚችለዉ የኢህአዴግ መንግስት አሁን ባለበት ሁኔታ ሆኖ የምርጫ ስርአቱን አስተካክሎና አፋኝ ናቸዉ የተባሉ ህጎች ላይ ከህዝብ ጋር በመወያየት አስተካክሎ  የዲሞክራሲ ምህዳሩን ህዝብ በሚፈልገዉ ደረጃ ካመቻቸ በኋላ ያለ አንዳች እንቅፋና ተጽዕኖ  ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግበትን  ሁኔታ መፍጠር ነዉ፡፡ በዚህ መልክ የሚደርግ ምርጫ መደበኛዉን የምርጫ ዘመን ድረስ ሳይቆይ ወይንም ቀጣዩን የምርጫ ዘመን (2012) ሳይጠብቅ ካሁኑ በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ሊከናወን ይችላል፡፡ ይህ አማራጭ ገዢዉን ፓርቲንም ሌላዉን ተቃወሚ ፓርቲንም ሊያስማማ የሚችል ከመሆኑም ሌላ በሀገሪቱ ዉስጥ ትርምስና  ቀዉስ  እንዳይፈጠር ሊያደርግ የሚችል ነዉ፡፡

ኢህአዴግ ራሱ ፈቅዶና ሁኔታዎችን ራሱ አመቻችቶ በምሁራኑ የቀረበለትን መፍትሄ ለመተግበር ለመንቀሳቀስ ሳይፈልግ ቀርቶ ስልጣኑን በኃይል የሚያጣበት ሁኔታ ከተፈጠረ የኢህአዴግ  ዕጣፈንታ ልክ ኢሠፓ ላይ እንደ ደረሰዉ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ወንጀለኛ ድርጅት ተደርጎ ስለሚፈረጅና በህግም የታገደ ድርጅት ስለሚሆን በሀገሪቱ ማናቸዉም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዉስጥ እንደ ድርጅት የመሳተፍ መብት ያጣል፡፡ ይህ ደግሞ ለኢህአዴግ ስልጣን ከመልቀቅም በላይ የከፋ መጥፎ ዕድል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

ይሄ ሁኔታ በብዙ አገሮች የደረሰና እንደ አሰራርም የተለመደ ነዉ፡፡ አዲስ መንግስት ለመመስረት ምርጫ ለማካሄድ የፓርቲዎች ምዝገባና እዉቅና የመስጠት ስራ ሲሰራ በቀድሞ አምባገነን ስርአት ገዢ የነበረ ፓርቲ በህግ እገዳ ስለሚጣልበት ተመዝግቦ መወዳደር አይፈቀድለትም፡፡ የቀድሞዉን አገዛዝ ሲያገለግልና ሲመራ  የነበረ ፓርቲ አገዛዙ ከስልጣን በግድ እንደተወገደ ፓርቲዉም ወዲያዉኑ እንዲፈርስ ነዉ የሚደረገዉ እንጂ እንደሌሎች ፓርቲዎች ህልዉና አይኖረዉም፡፡ የደርግ ዘመኑ ፓርቲ “ኢሠፓ” በታማኝኘት ሲያገለግለዉ የነበረዉ ስርአት መዉደቅ ተከትሎ አብሮ እንዲፈርስ መደረጉና በአዲሱ የኢህአዴግ መንግስትም እዉቅና መነፈጉ በዚህ መነሾ ስለሆነ የተወሰደዉ እርምጃ ተገቢ እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡

በአንዳንድ አገሮች ትንሽ ለየት ባለ መልኩ የቀድሞዉ ገዢ ፓርቲ በአዲሱ ስርአት እንዲወዳደር  የሚፈቀድለት የቀድሞዉን (ነባሩን) ስሙን ቀይሮ በሌላ ስም ከተመዘገበ ብቻ ነዉ፡፡ ለምሳሌ የግብጹ የ2011 ኩዴታ በኋላ በሀገሪቱ የነበሩ ፓርቲዎች ሁሉ ያለገደብ በነጻ እንዲወዳደሩ ሲፈቀድ የቀድሞዉ የሙባረክ አገልጋይ የነበረዉ “ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(National Democratic Party)” የሚባለዉ ግን በህገወጥነት ተፈርጆ እዉቅና ስለተነፈገዉ ለምርጫ ለመወዳደር አልቻለም፡፡ ወደ ሀገራችን ሁኔታ ስንመለስም በስልጣን ላይ ያለዉ ፓርቲ (ኢህአዴግ )የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ፈቃደኛ ሆኖ ከተገኘ በቅድሚያ ከዚህ በፊት አጥፍቷል ለሚባለዉ ሁሉ ያለመከሰስ (immunity)ና  በምርጫ እንደማንኛዉም ድርጅት የመፎካከር ሙሉ መብት የሚያረጋግጥ አስተማማኝ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል፡፡  የዚህ ዓይነት ዋስትና መኖር ስልጣን ከለቀቅሁ ችግር ዉስጥ ልገባ እችላለሁ የሚለዉን ስጋት የሚያስወግድ ስለሆነ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልን ቀዉስ የሚያስቀር ይሆናል፡፡

7/ አዲስ ስርአት የመመስረት ጉዳይ በኢህአዴግ መቃብርና በኢህአዴግ ፍርስራሽ  ላይ ሊሆን አይገባም

ኢህአዴግን ስልጣን ለማሳጣት ደፋ ቀና የሚሉ ወገኖች  “በኢህአዴግ አገዛዝ ስር ያለች ኢትዮጵያን ስለማንፈልጋት ኢህአዴግ ስልጣን ካልለቀቀ በስተቀር ኢትዮጵያ የራሷ ጉዳይ ነዉ”እያሉ ነዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች   ከሚቋምጡለት  ስልጣን በላይ ኢትዮጵያ እንደምትበልጥባቸዉ ለመረዳት የተሳናቸዉ ናቸዉ፡፡

በሌላ በኩል “ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት” የተባለዉን ነገር ኢህአዴግ ስልጣነን ያሳጣኛል ብሎ ጥያቄዉን ካጣጠለ ያዉ ወደ ፈራነዉ አደጋ መግባታችን አይቀርም፡፡ በዚህ መሰረትም ኢህአዴግ ስልጣን ለመልቀቅ ካለመፈለጉ  ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ማንኛዉም አደጋ ተጠያቂ የሚሆነዉ አህአዴግ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡  ኢህአዴግን የሚያካትት  አስከሆነ ድረስ ሁሉን አካታች የሆነ  ጊዜያዊ የሽግግር መንግስትን የመመስረት ሃሳብ  ለሁሉም ወገኖች የሚበጅ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡

አንዳንዶች እንደሚመኙት በስልጣን ላይ ያለዉን  መንግስት ህልዉናዉን ማሳጣት ሳያስፈልገን በስልጣን ላይ ባለበት ሁኔታ ብሄራዊ እርቅ  ተደርጎ አንድም እገጭእጓና ጓጓታ በለለበት ሁኔታ ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግስት ተመስርቶ ለቀጣይ ህዝባዊ ምርጫ መዘጋጀት ነዉ የሚበጀን፡፡  ይህ መሆን ሲገባ ኢህአዴግን በሆነ መንገድ ከስልጣን አስወግደን የሥልጣን ክፍተት ከፈጠርን በኋላ እንደ አሸን የፈሉ ጎጠኛና ጎሰኛ በየመንደሩና በየአድባሩ የተመሰረቱ  ድርጅቶች “ስልጣን እኔ ልያዝ እኔ” በሚል እርስበርስ ሲባሉ አገሪቱን ይበታትኗል፡በዚህ መሰረትም  የምንወዳትን አገራችንን ከነጭራሹ  ልናጣት እንችላለን፡፡

አዲስ ስርአት መመስረት የሚገባን ከሆነም በኢህአዴግ መቃብርና በኢህአዴግ ፍርስራሽ  ላይ ሊሆን አይገባም፡፡  ለነገሩ የቀረበዉ ሰላማዊ መፍትሄም ቢሆን  ኢህአዴግ ራሱ የሕዝብ ጥያቄን አክብሮ ለህዝብ ይበጃል ብሎ ሲያምንበት የሚተገበር እንጂ በሃይልና በጫና የሚሆን አይደለም፡፡ ኢህአዴግን በማስገደድ ከስልጣን ለማዉረድ ያለዉ አድል እጅግ ጠባብ ነዉ፡፡ በስልጣን ላይ ያለዉን አገዛዝ በኃይል ከስልጣን ለማዉረድ መሞከርም ሆነ ህገመንግስታዊ  ስርአቱን በኃይል ለመቀልበስ መሞከር ከኢህአዴግም በላይ የሚያጣላዉ ከህዝቡ ጋር ነዉ፡፡ የህዝብን ፍላጎት የማይወክል ድርጊት ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር የሚያጋጭ ነዉ የሚሆነዉ፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ የትኛዉም አካል ወይም ፓርቲ ስልጣን ቢይዝ የሚያሳስበዉ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገርግን በህገ-መንግስቱ በተቀመጠለት ኃላፊነት መሰረት በኃይል ስልጣን ለመንጠቅም ሆነ ስርአቱን በኃይል ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራን በዝምታ ያያል ብሎ የሚያስብ ወገን ካለ እንደዚያ እንደማይሆን ካሁኑ መረዳት አለበት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መከላከያ ሰራዊቱን ጣልቃ እንዲገባ ከመፈለግ ይሁን ወይንም ጣልቃ ሊገባ ይችላል ተብሎ ከመስጋት እንደሆነ ባላዉቅም መከላከያ ሰራዊቱን በነገር የመነካካትና በተዘዋዋሪ መንገድ የማነሳሳት ዓይነት  ነገር በጣም እየተደጋገመ ነዉ፡፡

ወታደር በፖለቲካ ዉስጥ ጣልቃ ገብቶ በህዝብ ዕጣፈንታ ላይ እንዲወስን እየጋበዝነዉ ከሆነ እጅግ አደገኛ  ሁኔታ በራሳችን ላይ እያመጣን መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡  የወታደሩን ጣልቃገብነት የሚጋብዙ ወገኖች ለኢትዮጵያ ህዘብ ከደርግም የከፋ ወታራዊ አገዛዝ እየተመኙለት እንደሆነ መዘንጋት የለባቸዉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለጊዜዉ ብዙ ማለት አልፈልግም፡፤ ለጊዜዉ  ግን ለመንግስትም ለተቃዋሚዉ ማሳሰብ የምፈልገዉ  “ እባካችሁን በፈጠራችሁ መከላከያ ሰራዊቱን ለቀቅ አድርጉት፡፡ በነገር አትነካኩት፡፤ያለ ፍላጎቱም ወደ ወንጀል እንዲገባ አትገፋፉትየሚለዉን መልእክ ነዉ፡፡

8/ ኢህአዴግ ለሰራቸዉ  መልካም ስራዎች እዉቅና መንፈግ ከሁሉም የከፋ ጥፋት ነዉ

ኢህአዴግ አንደመንግስት የሰራዉን በመካድና እዉቅና ለመስጠት ያለመፈለግ አመላከት ይታያል፡፡  ያለፉትን ሃያአምስት ዓመታት ኢህአዴግ ሲያጠፋ እንጂ አንዳችም በጎ ነገር እንዳልሰራ አድርጎ ማሰብ ተጨባጭ የሆነዉን በዓይናችን እያን ያለዉን መካድ ነዉ፡፡ ኢህአዴግን ስለጠላነዉ ብቻ ተብሎ  የሰራቸዉን መልካም ስራዎች እዉቅና መንፈግ ከሁሉም የከፋ ጥፋት ነዉ፡፡ ለሰራቸዉ ስራዎች እዉቅና ሰጥቶ በጉድለቱ ላይ ትችት ማቅረብ ሲገባ አንድም የተሰራ ነገር የለም ከተባለ ግን ትዝብት ላይ ከመጣል ዉጭ ኢህአዴግን በዚህ ጉዳይ እንዲጠላ ማድረግ አይቻልም፡፡

ኢህአዴግ የሠራቸዉን ግዙፍ ስራዎች መካድና  በኢህአዴግ አመራር ሰጭነት  በሀገሪቱ ዉስጥ የተመዘገበዉን  እድገት እንደለለለ መቁጠር  ለወደፊት ስልጣን ለሚመኘዉም ሌላ ፓርቲም ቢሆን የሚበጅ አመለካከት አይደለም፡፡  ምክንያቱም  ኢህአዴግን ለመተካት ፍላጎቱና ብቃቱ አለኝ የሚል  ፓርቲ  ኢህአዴግ ያን ሁሉ ሰርቶ ምስጋና ከተነፈገዉና  ምንም እንዳልሰራ ከተቆጠረ መጪዉ ፓርቲ መስጋቱና ከአሁኑ ተስፋ መቁረጡ አይቀርም፡፡ ቀጣዩ ፓርቲ ኢህአዴግ ካመጣዉ እድገት የበለጠ ማምጣት እንደማይችል ስለሚገነዘብ መስጋቱ የግድ  ነዉ፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ያገኘዉን ይዞ የጎደለዉ እንዲሟላለት ተጨማሪ የልማት ጥያቄ የሚጠይቅበት ሁኔታ እያለ  ወደፊት የሚመጣዉ ፓርቲ ግን ለህዝቡ አዲስ ነገር ማምጣት ይቅርና የነበረዉንም እንደማይነጥቀዉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ከኢህአዴግ ዉጭ የምንገኝ ገለልተኛ ዜጎች እንዲህ በግርግር የኢህአዴግን ስልጣን እንዲለቅ የማንፈቀድዉም ለኢህአዴግ ካለን ፍቅርና ወገንተኝነት ሳይሆን መጪዉን ዘመን በጥርጣሬ እንድናይ ሁኔታዎች ስለሚያስገድዱን ነዉ፡፡

በኢህአዴግ ዘመን አንድም የተሰራ ነገር የለም የሚል ፓርቲ እጅ የገባ ስልጣን ለህዝብ ይበጃል ብሎ መተማመን አይቻልም፡፡ የተሰራዉን ሁሉ ክዶና አፍርሶ ከባዶ መሬት ከዜሮ ለመነሳት የሚፈልግ ፓርቲ  አጥፊ እንጂ አገር የሚያለማ አይሆንም፡፡ ለዘመናት ተፋቅሮ የኖረን ህዝብ እርስበርሱ የሚያገጩና ዘሬኛ ቅስቀሳ የሚደርጉ ድርጅቶችን በምን መስፈርት ነዉ ማመን የሚቻለዉ? ሂዳሴ ግድብ ለምን ተሰራ ብሎ ቅስቄሳ የሚደርግ ድርጅት ወደፊት ራሱ ስልጣን በእጁ ቢገባ አገር ሊያለማ ይችላል ብሎ እንዴት መተማመን ይቻላል? መከላከያ ሰራዊቱ ህዝብ ሲተላለቅና አገር ሲፈርስ እያየ ለምን ጣልቃ ገብቶ ለማረጋጋት ሞከረ ? ለምን ዳር ቆሞ ዝም ብሎ አያይም? የሚል ፓርቲ ወደፊት መንግስት የመሆን እድል ቢገጥመዉ አሁን ያለዉን መከላከያና ደህንነት ተቋማትን አፍርሶ በምትኩ ለሱ በግል ታማኝና አሽከር የሆነ፤ ህዝብን ያለርህራሄ የሚጨፈጭፍ ተቋም እንደማይመሰርት እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

አንድ መንግስት ወይም ፓርቲ የሕዝቡን የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ ይሰራል ሲባል ህዝብ ጥያቄ ማንሳት የሚያቆምበት ዘመን ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ እጅግ የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ሰፍኖ የቆየባትን አገር በአስርና በሃያ ዓመታት ዉስጥ  ከአፍሪካ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ያላት አገር ማድረግ ጨርሶ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይሄ አሁን እየተተቸ ያለዉ ኢህአዴግ  ይሄን ተግባራዊ  አድርጎ በተግባር አሳይቶናል፡፡

የህዝቡ የልማት ፍላጎት እንደ እድገቱ መጠን በየጊዜዉ  እየሠፋና የአይነት ለዉጥ እያደረገ የሚሄድ እንጂ አንድ ቦታ ላይ የሚያበቃ አይደለም ፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ይልቀቅ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የአሁኑንም የወደፊቱን ጥያቄ ሁሉ በአንድ ምርጫ ዘመን  እፈታለሁ ብሎ የሚመጻደቅና  ዳግመኛ የልማት ጥያቄ የማይነሳባት አገር አደርጋታለሁ ብሎ  የሚቃዥ ፓርቲ ወይም ግለሰብ  ህዝብን በዚህ ለማሞኘት እንደማይቻል ተረድቶ አርፎ ቢቀመጥ እንደሚሻለዉ እንመክራለን፡፡

በኢህአዴግ በኩልም ለምን እንደሆነ ሊገባኝ ባይችልም በተገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ስለአከናወናቸዉ ስራዎች ደጋግሞ ደጋግሞ ለመናግርና ለማስታወስ መሞከሩ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ደጋግሞ ስለራሱ መናገር ሳያፈልገዉ የሠራቸዉ ታላለቅ ስራዎች በራሳቸዉ ቋሚ  ምስክር መሆናቸዉን ማወቅ  አለበት፡፡ ህዝብ የሰራሁለትን በሚገባ አልተረዳልኝም ይሆናል ብሎ መጨነቅ ያለበትም አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ማንም የሚነግረዉ ሳያስፈልገዉ ያገኘዉን የልማት ትሩፋት ለመገንዘብ አይሳነዉምና ፡፡ ኢህአዴግ የሰራቸዉን ስራዎች በሀገሪቱ ያመጣዉን ለዉጥ እድገት የሚክድ ሰዉ ካለ ጤነኛ ሰዉ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግ ለዚህች አገር  ቋሚና ዘመን ተሸጋሪ የሆኑ በርካታ ስራዎችን እንደሰራ ህዝቡ ማንም ሳነግረዉ ይረዳል፡፡ ኢህአዴግ ለዚህች አገር በሰራዉ ዉሌታና ለክብሩ ኃዉልት ቢቆምለት የሚከፋዉ ሰዉ ያለ አይመስለኝም፡፤ ህዝቡ ጥያቄ ሲያነሳ ይህን ዘንግቶ አይደለም፡፡ ህዝብ ትግስቱ የተሟጠጠበት በርካታ ችግሮች ሲላሉት እነዚህ ችግሮችና ጥያቄዎች እንዲመለሱለት ስለሚፈልግ ነዉ እንጂ ኢህአዴግ አገር አላለማም በሚል አይደለም፡፡

ኢህአዴግ አደጋ ሲጋረጥበትና አበቃለት ሲባል እንደምንም ብሎ ከአደጋዉ ወጥቶ ጭረሽ ተጠናክሮ መገኘት በተደጋጋሚ እንደተሰካላት እናዉቃለን፡፡ የአሁኑ አደጋ በራሱ በድርጅቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በሀገሪቷ ላይ ያንዣበበ ስለሆነ እንደ ቀድሞዉ ኢህአዴግ በተአምር አንድ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ  በተስፋ ለመጠበቅ ህዝቡ እንግዲህ ትዕግስቱ ብዙም ያለዉ አይመስለኝም፡፡

እንደመፍትሄ እየገለጸ ያለዉም ራስን ማደስን እንጂ ሌላ የተለየ መፍትሄ ሲያቀርብ አልሰማንም፡፡ የኢህአዴግ ራስን የማደስ ጉዳይ ከእንግዲህ ወዲያ ከችግር ሊያላቅቀን ስለመቻሉ አሁን አሁን  መጠራጠራችን አልቀረም፡፡ በተለይም ተሃዲሶዉ  የስልጣን እድሜን የማስቀጠል ዓላማ  ብቻ ያነገበ ከሆነ የተሃድሶዉ ፋይዳ  የአገዛዙን ጡንቻ ለማፈርጠምና ህዝቡን  ለተጨማሪ አስርና ሃያ ዓመታት ለመግዛት ተጨማሪ ጉልበት የሚያገኝበት ከመሆን አይዘልም፡፡

9/ እንዴት እንቀጥል? ምንስ ማድረግ ይገባናል?

* ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ሰጥተን ግጭቱን ማስቆም :

* ህዝቡን የማረጋጋት ስራ መስራትና  መደበኛ የመንግስት ስራና ማህበራዊ አገልግሎት እንደቀድሞዉ እንዲቀጥል ማድረግ ;

* ከህዝብ ጋር በመያየት ከራሱ ከህዝቡ የሚመነጭ መፍትሄን ለመተርጎም መሞከር ፤

የተጠጋጩና ደም የተቃቡ ወገኖችን ይቀር ለኢግዜር ተባለዉ እንዲታረቁና የተፈናቀሉትም ወደ ቀድሞ ቦታቸዉ  እንዲመለሱ  ማድረግ፤

* ለችግሩ መሰረታዊ ምንጭ በሆነዉ ጉዳይ ላይ መንግስት (ገዥዉ ፓርቲ ) ከሀገር ሽማግሌዎች ከምሁራን፤ ከታዋቂ ሰዎችና የፓርቲ አመራሮች ጋር ተመካክሮ ከእነሱ ጋር በሚደረስ መግባባት ወደ ተጨባጭ ለዉጥ መግባት፤

* ገዥዉ ፓርቲ የሀገር ሃብትን ሲዘርፉ የቆዩ የፓርቲና የመንግስት አማራሮችንም ሆነ ማንኛዉንም ህገወጥ ያለአንዳች ሃዘኔታ በቁጥጥር ስር አዉሎ ለህግ መቅረብ ፤

* ህዝቡን እየበደሉ ሲያማርሩ የቆዩና  ሃላፊነታቸዉን መወጣት ያልቻሉ ሃላፊዎችን ከስራ ማገድና እንደ አስፈላጊነቱ በህግ መጠየቅ፤

* በህዝቡና በምሁራን ክፉኛ ሲተቹ የቆዩና ተቀባይነት የጎደላቸዉ አንዳንድ ህጎችን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ፤

* ከዜግነትና  ከችሎታ ይልቅ የፓርቲ ዉገና ቅድሚያ የሚሰጥበት አሰራር ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ዜጎች የፓርቲ አባል ሆኑም አልሆኑም በችሎታቸዉ ተወዳድረዉ  በመንግስት ስራ የሚቀጠሩበትና በሃላፊነት የሚመደቡበት ሁኔታ ማፍጠር፤

* በሁሉም የስራ ዘርፎችና ሃላፍነቶችና  ብሄራዊ ተዋጽኦን  የጠበቀ አሰራር መከተልና አድለአዊ አሰራርን ማስቀረት፡

* በመጨረሻም የሽግግር መንግስት መመስረት ወይም ድጋሚ ምርጫ ማድረግ የሚሉ አማራጮች ቀርበዉ ከምሁራኑና ከፓርቲ መሪዎችና ከህብረተሰቡ ጋር  ጋር ተመካክሮ  በሚደረስ ስምምነት መሰረት መተግበር፡፡ የተሻለ አማራጭ የሚመስለኝም አሁን ያለዉን መንግስት አፍርሶ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መሞከሩ ሳሆን ከዚያ ይልቅ የኢህአዴግ መንግስት ባለበት ሁኔታ አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን (ለምሳሌ የምርጫ ህግ ወዘተ) በማድረግ ነጻ ታዛቢዎች ባሉበት ሁኔታ ዲሞራሲያዊ ምርጫ ማከናወን የሚሻል  ስለሚመስለኝ በዚሁ አማራጭ መሰረት ብንሄድበት  መልካም ይመስለኛል፡፡

ማጠቃለያ

በሀገራችን በተፈጠረዉ ሁኔታ ሁላችንም ተጎድተናል ፡፡ ሁላችንም አዝነናል፡፡ በታሪካችን አስካሁን አጋጥሞን የማያዉቅ  ዓይነት የርስበርስ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ የመጠቃቃት ሁኔታ ነዉ የተከሰተዉ፡፡ ከዚህ ሁኔታ በማንኛዉም መንገድ አድርገን መዉጣት ይገባናል፡፡ በተለይ መንግስት ህዝብን ወደቀድሞዉ የርስበርስ መተሳሰብ ግኑኝነቱ የመመለስ ተቀዳሚ ኃላፊነት ሲላለበት አስፈላጊዉን እርምጃ ሁሉ ፈጥኖ መዉሰድ ይገባዋል፡፤መንግስት ለጊዜዉ ሁኔታዉ ስለተረጋጋ  ዳግመኛ እንደማይከሰት አድርጎ  ሳይዘናጋ ከህዝብ ጋር የሚያወዳጀዉንንና  በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱንና ተአማንነቱን  የሚያረጋግጡ ስራዎችን በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀት ይገባዋል፡፡ በተረፈ ሁላችንም ህዝባችንን በማረጋጋትና ተስፋ እንዳይቆርጥ በማድረግ  ወደ ቀደመዉ አንድነታችን ፈጥነን ለመግባት እንጣር!

 ፈጣሪ ኢትዮጵን ይጠብቃት!

***********

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡