ኢህአዴግ፡ አፍን ይዞ ከኋላ መጫን ለማፈንዳት

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተሰጡ ያሉ ሃሳቦችና አስተያየቶች በአብዛኛው በተቃራኒ ፅንፍ ላይ የቆሙና በጭፍን እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። አብዛኞቹ የግል/ውጪ ሚዲያዎች የመንግስትን አምባገነንነት ከመዘከርና በግጭቱ የተጎዱና የሞቱ ዜጎችን ቁጥር ከመቁጠር ባለፈ ሲዘግቡ አይስተዋልም። የመንግስት ሚዲያዎች ደግሞ በንብረትና በፀጥታ ኃይሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በመዘገብና የችግሩን አስከፊነት በማጣጣል ላይ ተጠምደዋል። ሁሉም ክስተቶችን ከመዘገብና አንዱን ደግፎ ሌላውን ከማውገዝ በዘለለ የችግሩን መሰረታዊ መንስዔዎችና መፍትሄዎች ለመለየት ጥረት ሲያደርጉ አይታይም። በዚህ ፅኁፍ ይህን ክፍተት ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

መነሻ እንዲሆነን፣ የት/ት ክፍል ኃላፊ ሆኞ በምሰራበት ወቅት ያጋጠመኝን ነገር ላካፍላችሁ። ከእለታት አንድ ቀን ጠዋት ወደ ቢሮ ስገባ አንዱ መምህር ወደ ቢሮ እየተጣደፈ መጣና እንዲህ አለኝ፤ “ሁል ቀን እጠይቃሃለሁ እያልኩ። ቆይ ለምንድነው በሁሉም ማስታወቂያዎች ላይ ስሜ 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ የሚፃፈው? …ምን የተለየ ነገር ስላለ ነው?” በማለት ቅሬታውን ነገረኝ። እኔም የእሱ ስም ብቻ በ“A” ስለሚጀምር እንደሆነ ስነግረው በጥያቄው እንደማፈር እያለ ወጣና ሄደ። እና ምን ለማለት ነው፤ በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ ሁን፣ በሕብረተሰቡ/በተገልጋዩ ዘንድ ያለውን ሃሳብና አመለካከትን በእርግጠኝነት ማወቅ አትችልም። ምክንያቱም፣ በአንተ እሳቤ መሰረት የወሰንከው ውሳኔ ትክክል ይሁን ስህተት የሚረጋገጠው ከተገልጋዮች ሃሳብና አመለካከት አንፃር ነው። በአጠቃላይ፣ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ሁኔታ ካልተመቻቸ መንግስት ትክክለኝነቱንና ስህተቱን በሚገባ ማወቅ አይችልም።   

በዴሞክራሲያዊ መንግስት ቤት ውስጥ አራት መስታዎቶች አሉ። እነሱም፡- በቀኝ በኩል የሚዲያዎች መስታዎት፣ በግራ በኩል የሲቭል ማህበራት መስታዎት፣ ፊት-ለፊት የተቃዋሚዎች መስታዎት፣ እና ከውስጥ ደግሞ የአባላት መስታዎት ናቸው። የመስታዎቶቹ ፋይዳ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስለ መንግስት ሥራና አሰራር የሚሰጧቸውን ሃሳቦችና አስተያየቶች እየተቀበሉ ማሳየት ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ፤ የህዝቡን ሃሳብ፣ ብሶትና ጥያቄ በቀጥታ የሚስተናግዱ ነፃና ተደራሽ ሚዲያዎች ከሌሉ፣ የተደራጁና ገለልተኛ የሙያና ሲቪል ማህበራት ከሌሉ፣ የሕዝብን ጥያቄ በቀጥታ ለመንግስት የሚያቀርቡ (ያለመከሰስ መብት) የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ከሌሉ፣ ገዢው ፓርቲ በውስጡ የሃሳብና አቋም ልዩነቶችን በቀላሉ የማስተናገድ ባህል ከሌለው መንግስት ምንም ነገር ማየትና መስማት ይሳነዋል። 

የኢህአዴግ መንግስት ኦነግን በማስወጣት የተቃዋሚዎች መስታዎትን፣ ቀጠለና በ1993ቱ የሕወሃት ክፍፍል የአባላቱን መስታዎት መስበር ጀመረ። የፀረ ሽብር ሕግን እና የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ በማውጣት በአራት አመታት ውስጥ ብቻ 60 ጋዜጠኞችን ለስደት፣ 19 ለእስር ቤት በመዳረግ የሚዲያ መስታዎትን ሰባበረ። የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕብረት መመሪያ በማውጣት የተደራጁ እና ገለልተኛ የሆኑ ሲቪል ማህበራት እንዳይኖሩ በማድረግ የማህበራትን መስታዎት ሰባበረ። በመጨረሻም፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እጅግ እንዲጠብ ለማድረግ ባደረገው ያልተቋረጠ ጥረት የተቃዋሚዎችን መስታዎት ሰባብሮ ጨርሶ፣ በ2002ቱ ምርጫ አንድ የመስታዎት ስባሪ ቀርቶት ነበር። ከ2007ቱ ምርጫ በኋላ ግን ምንም መስታዎት የለውም። ከዚያን ግዜ በኋላ ከፊት-ለፊቱ ያለ ነገር በሙሉ እንቅፋት ይመስለዋል። 

ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የመንግስት መዋቅር በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር ወድቋል። የሲቪል ሰርቪስ ስርዓቱ በሙያተኞች ሳይሆን በካድሬዎች ተሞላ። የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ የሚያዳምጥ ሆነ በግልፅ የሚናገር ጠፋ። ፓርቲው የሰራውን ለመደበቅ ሲሞክር፣ በስህተት ላይ ስህተት እየሰራ፣ ስህተቱን ከወድቀቱ በኋላ እንዲያውቅ ሆኗል። ኢህአዴግን ለዚህ እያደረጉት ያሉት ደግሞ አመራሮቹ ብቻ ሳይሆኑ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጭምር ናቸው። 

በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀመሮ የኢህአዴግ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ከሞላ-ጎደል ሁሉም አፋኞች ናቸው ማለት ይቻላል። በ2007ቱ ምርጫ “ሙሉ-በሙሉ አሸነፍኩ” ሲል ደግሞ “የህዝቡን ጥያቄ ሙሉ-በሙሉ ማየትና መስማት ተስኖኛል” እንዳለ አድርጌ ነበር የወሰድኩት። ይህ ዛሬ ላይ በድንገት የተገለጠልኝ ሃሳብ አይደለም። ገና የ2007ቱ ምርጫ ውጤት ይፋ ሲደረግ የተናገርኩት ሃቅ ነው። ለምሳሌ ሰኔ 14, 2007 ዓ.ም በጦማር ገፄ ላይ ethiothinkthank.com ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቼ ነበር፡-

“100% የሚባለውን አሰቃቂ ክስተት “የምርጫ ውጤት” በሚል ሰርግና ምላሽ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዞንና ወረዳ ደረጃ ያሉትስ አይፈረድባቸውም። በፌዴራልና ክልል ደረጃም ተመሳሳይ አቋም የሚያራምዱ ባለስልጣናት ካሉ ግን በጣም አስገራሚ ነው የሚሆነው ። ይሄ 100% ተብዬ ነገር’ኮ፣ ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ሀገሪቱ በዲሞክራሲ ረገድ ያሳየችውን ለውጥና መሻሻል ወደ ኋላ የቀለበሰ፣ ህዝቡ ሰላማዊ ፖለቲካ፣ በሕግ የበላይነት እና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ ያለውን እምነት ሽርሽሮ በመናድ ዴሞክራሲን በጭቅላቱ ዘቅዝቆ ያቆመ፣ ልክ እንደ ደርጉ ቀይ-ሽብር ህዝብን በፍርሃት ቆፈን የሚቀፈድድ እጅግ አስቀያሚ ድርጊት ነው”

በአንድ ሀገር ውስጥ፤ ጋዜጠኞችን፣ ተቃዋሚዎችን እና የተለየ ሃሳብ ያነሱ አባላትን ለእስር ቤት እና ለስደት፣ እንዲሁም የሲቭል ማህበራትን ለውድቀት ከዳረክ በኋላ ከተቃውሞ ሰልፍ ሌላ ሕዝቡ ምን ምርጫ አለው? ከገዢው ፓርቲ የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የሚያራምዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች የመንግስትን ሥራና አሰራር ለመተቸት፣ ድጋፋቸውንና ተቃውሟቸውን ለመግለፅ፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን ለመግለፅ ወደ አደባባይ ከመውጣት በስተቀር አማራጭ የላቸውም። ታዲያ፣ ምርጫና አማራጭ የሌለው ህዝብ ለተቃውሞ አደባባይ ሲወጣ መደብደብ፣ ማሰርና መግደል ምን ይሉታል። 

በተለይ በኦሮሚያ ሆነ አማራ ክልሎች ሕዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው ከዚያ ውጪ ሌላ ምርጫና አማራጭ ስለሌለው፥ ስለታፈነ ነው። መታፈኑን በመቃወም አደባባይ የወጣን ሕዝብ በኃይል መልሶ ለማፈን መሞከር የባሰ ፈንድቶ ያፈነዳል። አደባባይ ወጥቶ ቅሬታውን ስላሰማ በፀጥታ ኃይሎች እየተደበደበ፣ እየታሰረና እየተገደለ፣ ሕዝብ “ኧረ ታፈንኩ!” ብሎ ሲጮህ መንግስት መልሶ የሚያፍነው ከሆነ እንደ ፈንጂ ፈንድቶ ያፈኑትን ያፈነዳል። 

በኦሮሚያና አማራ ክልልች የታየው ችግር መንስዔው የሕዝቡ መታፈን ሲሆን መፍትሄው ደግሞ የታፈነውን ሕዝብ ማስተንፈስ ነው። መንግስት ይህን ማድረግ ከተሳነው ግን ሕዝብ ትዕግስቱ ያልቅና፤ የሚደበድቡትን ይደበድባል፣ አሳሪዎቹን ያስራል፣ ገዳዮቹን ይገድላል። ለዚህ ደግሞ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ የታዩ ክስተቶችን እንደ ማሳያ በመጥቀስ ፅሁፌን ልቋጭ። ደርግ በ1968 ዓ.ም ታፈንኩ ያለውን ሕዝብ መልሶ ሲያፍነው 15 የፀጥታ አስከባሪዎች እና 10 የመንግስት/ ደርግ ባለስልጣናትን በመግደል ነጭ-ሽብር ተጀመረ። ዘንድሮ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች 25 የፀጥታ አስከባሪዎች እና 14 የመንግስት ባለስልጣናት ተገድለዋል። የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በተከሰተው አመፅና አለመረጋጋት ግን 193 ሰዎች ሲገደሉ አንድም ባለስልጣን አልተገደለም ነበር።

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories