ኢህአዴግ እና “የሰይጣን ጠበቆች”

አዲስ በረቀቀው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ እና በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ውስጥ ያሉ ሁለት አንቀፆች አሉ። የሁለቱም ፅንሰ-ሃሳብ ከመሰረታዊ የሕገ-መንግስቱ መርሆች ጋር ይጋጫል። ታዲያ፣ “እንደዚህ ያሉ አንቀፆችን በአዋጆቹ ውስጥ ማካተት ለምን አስፈለገ?” እያልኩ ራሴን እየጠየቅኩ ሳለ አንድ ነገር ት…ዝ አለኝ። ነገሩ፣ የቀድሞው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ፣ “የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ” በሚለው መፅሃፍ ውስጥ ያነበብኩትን አስታወሰኝ። መፅሃፉን ለማንበብ ስከፍት፣ መግቢያ ላይ “አቶ ኤርሚያስ ለገሰ…የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን ለመጀመሪያ ግዜ ለህዝብ ይፋ ያደረጉ ናቸው፣ …” የሚል ዓ.ነገር አንብቤ ተገረምኩ። ዋና ትኩረቴ ግን ምዕራፍ ሃያ አምስት ላይ ያለው “የሐመሩ (ሐ) ፖለቲካ” ርዕስ ነው። ፀሃፊው በመፅሃፉ ገፅ 356 ላይ እንዲህ ብሎ ፅፏል፤

“ፓርቲው [ኢህአዴግ] ከሌሎች አካላት ጋር ተወያይቶ የውሳኔ ሃሳብ ይዞ ከመጣ ሦስት መሰረታዊ ነጥቦች እንዲካተት ያደርጋል። ከእነዚህ ውስጥ ሦስተኛው ተቃዋሚዎች በህዝቡ የሚጠሉበትና ኢህአዴግ ውሉን መሰረት አድርጎ እነሱን የሚመታበት ሃሳብ መካተቱን ማረጋገጥ ይሆናል። ውስጥ አዋቂ ካድሬዎች “የሐመሩ (ሐ) ፖለቲካ” ብለን እንጠራዋለን። የሐመሩ (ሐ) ፖለቲካ ከኢህአዴግ የዜሮ ድምር ጨዋታ ህግጋት አንዱ ነው።”

ከዚያ በኋላ፣ ከላይ ወደ በተጠቀሱት አዋጆች ውስጥ ያሉትን አወዛጋቢ አንቀፆች ማንበብ ጀምርኩ። ከእነዚህ የሕግ አንቀፆች በስተጀርባ ያለው መሰረታዊ እሳቤና በተግባር እየሆነ ያለውን ነገር ለማገናዘብ ሞከርኩ። በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት፣ ልክ በፖለቲካው መድረክ እንደሚያደርገው ሁሉ በፍትህ ስርዓቱም ተመሣሣይ የዜሮ ድምር ጨዋታ እየተጫወተ ነው። አቶ ኤርሚያስ ለገሰ በመፅሃፋቸው “የሐመሩ (ሐ) ፖለቲካ” በማለት የገለፁት ነገር፣ በ2001 ዓ.ም በወጣው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ እና በዚህ ዓመት በወጣው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ውስጥ በግልፅ ይታያል።

በፀረ-ሽብርተኝነት አወጅ ክፍል ሁለት፥ አንቀፅ-3 ላይ “የሽብርተኝነት ድርጊቶች” በሚለው ስር፤” ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ ሃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ ዓለማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት፣ ወይም የሃገሪቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፍረስ” የሚፈፀሙ ተግባራት እንደሆኑ ይገልፃል። አንቀፅ-4ና 5 የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ስለማቀድ እና ድጋፍ ስለመስጠት የሚያትቱ ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ ያለው አንቀፅ-6 ግን የሐመሩ (ሐ) ሕግ ስለመሆኑ በግልፅ ያስታውቃል። “ሽብርተኝነትን ስለማበረታታት” የሚለው አንቀፅ-6 እንዲህ ይላል፡-

“ማንኛውም ሰው መልዕክቱ እንዲታተምላቸው የተደረገው የሕብረተሰቡ አባላት በከፊል ወይም በሙሉ በዚህ አዋጅ አንቀፅ-3 የተመለከተ ማናቸውም የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈፅሙ ወይም ለመፈፀም እንዲዘጋጁ ወይም እንዲነሳሱ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያበረታታቸው ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት ሆነ ብሎ ወይም በግዴለሽነት ያተመ ወይም ያሳተመ እንደሆነ ከ10 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።”

በተመሳሳይ፣ አዲስ በወጣው “የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ አዋጅ ንዑስ ክፍል ሦስት አንቀፅ-14 “በሕዝብ ደህንነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች” በሚል የሚከተለው አስቀመጧል፡-

“የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በወንጀል ህግ አንቀፅ 257 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በማንኛውም ሰው ሆነ ብሎ በህብረተሰቡ መካከል የፍርሃት ስሜት፣ አመጽ፣ ሁከት ወይም ግጭት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሁፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ድምጽ ወይም ማንኛውንም ሌላ ምስል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካኝነት ያሰራጨ እንደሆነ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል”

ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት አንቀፆች በተጨማሪ፣ በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ክፍል አምስት አንቀፅ-41፥2 እና አንቀፅ-43፥7 ላይ የተቀመጡትን ህጎች ስንመለከት፣ “የሐመሩ (ሐ) ሕግ)” በኢትዮጲያ የፍትህ ስርዓት ላይ ጥላውን እንዳጠላ እንረዳለን። እንደ አቶ ኤርሚያስ አገላለፅ፣ “የሐመሩ (ሐ) ፖለቲካ” በኢህአዴግ ውስጥ አዋቂዎች ዘንድ የተለመደ ተግባር ሆኗል። የፍትህ ስርዓቱም በተመሳሳይ እሳቤ የሚመራ ከሆነ ግን፣ እንደ ሀገር መጨረሻ ወደሌለው ዝቅጠት እየገባን ነው።

የሐመሩ (ሐ) ፖለቲካ በተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እና መሪዎች ላይ ከልክ ያለፈ ጫና በመፍጠር ለሀገሪቱ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ግንባታ እንቅፋት መሆኑ የማይቀር ነው። የሐመሩ (ሐ) የሕግ አንቀፆች ግን የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆችን የሚፃረሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ-6 እና የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ አንቀፅ-14 ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር እንኳን የሚጋጩ ናቸው። በመሰረቱ፣ በእነዚህ የሕግ አንቀፆች መሰረት “ጥፋተኛ” የተባሉ ግለሰቦች በአጠቃላይ ወንጀለኞች አይደሉም። ምክንያቱም፣ በመጀመሪያ አንቀፆቹ ሲረቁ በራሱ ዓላማው ወንጀልን መከላከል ሳይሆን በመንግስት ላይ የሚሰነዘርን ትችትና ነቀፌታ ማስቀረት ነው።

በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀፅ-6 መሰረት በወህኒ ቤት የታሰሩ ወይም ከሀገር የተሰደዱ፣ በማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ-ቤት ቀጠሮ የሚጠብቁ ወይም በየቤታቸው ሆነው የሚታሰሩበትን የማያውቁ፣… አሁን ደግሞ አዲስ በወጣው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ አንቀፅ-14 ላይ በተጠቀሰው የወንጀል ተግባር ተጠርጥረው ወደፊት እንዳይታሰሩ የሚፈሩ፣…ሁሉም መጠሪያቸው “አሸባሪ” ወይም “ወንጀለኛ” የሚለው አይደለም። ብዙውን ግዜ በእንዲህ ያለ ተግባር የሚሰማሩ፤ ጋዜጠኞች፣ ፀኃፊዎች፣ ጦማሪያን፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣…ወዘተ፣ ትክክለኛ ስማቸው “ሰይጣን” የሚለው ነው። ይህ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሚጠሩበት ስማቸው ይሄ ነው።

በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተቋማትን መተቸትና መንቀፍ ስራቸው የሆኑ “ሰይጣኖች” ስምና ተግባር ከታሪክ መዝገብ አይጠፋም። በአለም ታሪክ ደግሞ እንደ የሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን ረጅም እድሜ ያለው ተቋም የለም። በተለይ ከ12ኛው ክ.ዘመን መጨረሻ እስከ 18ኛው ክ.ዘመን መጀመሪያ ድረስ፣ በቤተ-ክርስቲያኗ በቅዱሳን (Saints) ላይ የሰላ ትችትና ነቀፌታ ሲሰነዝሩ የነበሩ የተሃድሶ (ፐሮቴስታንት) መሪዎችና የህዳሴው ዘመን ልሂቆች፣ “አሸባሪ ወይም ወንጀለኛ” አይባሉም ነበር። ከዚያ ይልቅ፣ ስያሜያቸው “ሰይጣን” የሚል ሲሆን፣ በዚህ ዘመን እንዳሉት ጋዜጠኞች፣ ፀኃፊዎች፣ ጦማሪያን፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች፤ ተወግዘዋል፣ ተገለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣

በአውሮፓ የተሃድሶ መሪዎች እና የህዳሴ ምሁራን ዋና ተግባር በፅሁፍ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያንን ሥራና አሰራር መተቸት ነበር። ለምሳሌ፣ ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር በ1520ቹ ከጀርመን ንጉሱና የሮማ ጳጳስ የተሰጠውን ትዕዛዝ የቤተ-ክርስቲያኗን አስተምኽሮት በመተቸት የፃፋቸውን ፅሁፎች እንዲያነሳ (retract) እንዲያደርግ ነበር። ትዕዛዙን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት፣ ጳጳሱ ከቤተ-ክርስቲያኗ ሲያባርሩት፣ ንጉሱ ደግሞ በወቅቱ በነበረው የጀርመን ህግ የመጨረሻውን ቅጣት፣ የህግ-ከለላን በማንሳት (outlaw)፣ በተገኘበት ቦታ እንዲገደል የሞት ፍርድ አሰተላለፉበት።

በእርግጥ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ እንቅስቃሴ በ1517 ዓ.ም በጀርመናዊ ማርቲን ሉተር እንደተጀመረ ይነገራል። ነገር ግን፣ ከማርቲን ሉተር በፊት እንቅስቃሴው ቢያንስ ለሃያ (20) ግዜ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ ቤተ-ክርስቲያኗ ሁሉንም በሃይል ለማዳፈን ችላ ነበር። ለ21ኛ ግዜ በማርቲን ሉተር መሪነት የተጀመረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ግን የሮማ ካቶሊክን ለሁለት በመክፈል የቤተ-ክርስቲያኗ ህልውናን አደጋ ላይ ጣለው። በዚህ መልኩ፣ በህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቋቋም ቤተ-ክርስቲያኗ በውስጧ የሚተቿትንና የሚነቅፏትን ሰዎች በፈለገች ግዜ ሁሉም የሉም።

ከተመሰረተችበት ግዜ ጀምሮ “ሰይጣኖችን” ስታወግዝና ስታስገድል የነበረችው ቤተ-ክርስቲያን፣ ህልውናዋን ለመታደግ በቤተ-ክርስቲያኗ ሲኖዶስ ውስጥ የሰይጣን ተወካይ መኖር እንዳለበት አመነች። ይህን ተከትሎ፣ በ1587 ዓ.ም በቤተ-ክርስቲያኗ ሙሉ እውቅና የተሰጠው “Promotor Fidei” የሚባል የሥራ ክፍል ውስጥ የሚሰራና “የሰይጣን ጠበቃ” (Devils’ Advocate) ቀጠረች።

በ18ኛው ክ.ዘመን መጀመሪያ ላይ በቤተ-ክርስቲያኗ ሲኖዶስ ውስጥ የሰይጣን ጠበቃ ከፍተኛውን የመወሰን ስልጣን ይዞ ነበር። ለምሳሌ፣ በ1913 ዓ.ም የታተመው የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የሰይጣን ጠበቃ የሥራ ድርሻ እንዲህ ገልፆታል፡-

“To prevent any rash decisions concerning miracles or virtues of the candidates for the honor of the altar. All documents of the canonization processes must be submitted to his examination, and the difficulties and doubts that he raises over the virtue and miracles are laid before the congregation and must be satisfactorily answered before any further steps can be taken in the processes. His duty requires him to prepare in writing all possible arguments, even at times seemingly slight against the raising of any one to the honors of the altar…”

በጣም ወግ አጥባቂ በነበረችው ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በመንፈሳዊና ዓለማዊ ምግባራቸው እጅግ የላቁ ቅዱሳንን ለመለየት የሰይጣን ጠበቃ አስፈላጊ ነበር። ይህ ጠበቃ፣ መንፈሳዊ ፅናትና ሃጢያትን መርምሮ ቅድስና በሚሰጠው የቤተ-ክርስቲያኗ ሲኖዶስ (congregation) ውስጥ ቁልፉ ድርሻ ነበረው። ምክንያቱም፣ በፈጣሪ ፊት ሞገስ ያላቸውን ቅዱሳን ብቻ ተለይተው፣ እምነትና ምግባራቸው በጥንቃቄ ተመርምሮ ቅድስና ለሚገባቸው ብቻ ለመስጠት የሰይጣን ሃሳብና አስተያየት የግድ አስፈላጊ ነበር። በመሰረቱ፣ ክፋት በሌለበት ደግነት ዋጋ አይሰጠውም። ከዚህ፣ የቅድስና መሰረቱ ሃጢያት ያለመስራት እንጂ፣ ስለ ሃጢያት አለመናገርና አለመፃፍ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል። በተመሣሣይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ስለ ሽብርና አሸባሪነት በነፃነት የሚያስቡ፣ የሚናገሩና የሚፅፉ ሰዎች በሌሉበት ሀገሪቱንና ህዝቧን ከሽብርና አሸባሪዎች መከላከል አይቻልም።

በኢትዮጲያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ሀገሪቷ ብዙ “ሰይጣኖች” ያስፈልጓታል። ነገር ግን፣ በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ እንደተገለፀው፣ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያለው “የሐመሩ (ሐ) ሕግ” ምክንያት ሰይጣኖቹ ለእስርና ስደት እየተዳረጉ ነው። በ2000 ዓ.ም የፀደቀውን የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እና የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅን ተከትሎ፣ በኢትዮጲያ የሰይጣኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኗል። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ተግባር ላይ ሲውል ደግሞ ሰይጣኖች ከሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፉ ይችላሉ።

ዛሬ በኢትዮጲያ “ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ወይም አሸባሪ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ አሲረዋል” እየተባሉ የሚከሰሱት፣ የሚሰደዱት፣ የሚታሰሩት የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ ፀኃፊዎች፣ ጦማሪያን፣ ተቃዋሚ ፖሊከኞች፣…ወዘተ፣ ሁሉም ሽብርና አሸባሪነትን ለመታገል ቁልፍ ሚና ያላቸው ወሳኝ ሰዎች ናቸው። እነሱ በፅሁፍና በቃል የሚሰጧቸው ሃሳቦችና አስተያየቶች ለመንግስት ውሳኔ ትክክለኝነት መለኪያ መስፈርቶች ናቸው። መንግስት በሚመራባቸው ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ላይ ነፃ ሂስና አስተያየት ካልተሰጠው በስተቀር፣ በሰይጣኖች ዘንድ በግልፅ የሚታይን ስህተትን እንኳን ለማየት በጣም ረጅም ግዜ ይወስድበታል። ከዚህ በተጨማሪ፣ መንግስት ስህተቱን ለማረም በሚወስደው የማስተካከያ እርምጃ ሌላ ስህተት ይሳሳታል። በመጀመሪያ ችግሩን በፈጠረው አመለካከትና አሳቤ ውስጥ ሆኖ የሚወስድ የመፍትሄ እርምጃ ለሌላ ችግር መንስዔ ይሆናል። በዚህ መልኩ፣ መንግስት በአንዱ ስህተት ላይ ሌላ ስህተት እየደገመ ይሄዳል። ነፃ ሚዲያና የፖለቲካ ውይይት በሌለበት ግን፣ ሃሳብና አስተያየትን በነፃነት መግለፅ አዳጋች በሆነበት ግን፣ መንግስት በስህተት ላይ ስህተት እየደገመ ራሱን-በራሱ ለውድቀት ይዳርጋል።

በመጨረሻም፣ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞችን፣ ፀኃፊዎችን፣ ጦማሪያንና ተቃዋሚዎችን ለእስርና ስደት እየዳረገ ያለው “የሐመሩ (ሐ) ሕግ” በተግባር ላይ እስካለ ድረስ ገዢው መንግስት ልክ እንደ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ስህተቱን እየተሳሳተ ህልውናውን ለአደጋ ማጋለጡ አቀይርም። ይሄኔ፣ የሀገሪቷ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን በ1587 እንዳደረገችው፣ ኢህአዴግም “የሰይጣን ጠበቃ” ፍለጋ መሄድ ሊኖርበት ነው፡፡

***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories