ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ

ባለፈው ሳምንት ሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ ባወጡት ረጅም ፅሁፍ ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች መንስዔና መፍትሄ ስፊ ትንታኔ ሰጥተዋል። ፅሁፉ ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሄውና መንስዔው ያለው ሕገ-መንግስቱን በአግባቡ በመተግበርና ባለመተግበር ላይ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ይሄ ጽሑፍ ደግሞ እንዴት አንዲት አንቀፅ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ለሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች መንስዔና መፍትሄ እንደሆነች ለማሣየት ያለመ ነው፡፡ በዚህም የክልሉ ሕዝብና የከተማው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ መብትና ነፃነት እንደተጣሰ ጭምር ለማሣየት እሞክራለሁ፡፡

በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል እየታዩ ካሉ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ በጣም አጣዳፊና አስቸኳይ መፍትሄ ከሚሹት ውስጥ፤ ከተቀናጀ የአዲስ አባባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ፣ በአዲስ አበባ የሕገ-ወጥ ቤቶች ግንባታና ማፍረስ፣ በሰንዳፋ የገበሬዎች ተቃውሞ በአዲስ አባባ የተከሰተው የፅዳት ችግር በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። የፌደራል፣ የክልሉና የከተማ መስተዳደሩ የበላይ አመራሮች ለእነዚህ አጣዳፊ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ጥድፊያ ላይ ናቸው።

በእርግጥ አጣዳፊ የሆኑ ድንገተኛ ችግሮች መከሰታቸው የተለመደ ነው። ነገር ግን፣ በአብዛኛው እንደዚህ ያሉ ችግሮች በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ባሉ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ የሚሰጣቸው ችግሮች ናቸው። በመንግስታዊም ሆነ ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ የበላይ አመራሮች (Top Management) ዋና ሥራቸው፤ ለወቅታዊ ችግሮች መነሻ የሆነውን ነባራዊ እውነታ ማጥናትና የችግሩን ሥረ-መሰረት መለየት፣ በዚህም ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ስልት (ስትራቴጂ) መንደፍ ነው። ከፌደራል እስከ ከተማ መስተዳደሩ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች በዚህ መልኩ ሥራቸውን ቢያከናውኑ ኖሮ ከአንዲት ተአምረኛ አንቀፅ ላይ ይደርሱ ነበር።

ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ዋና መንስዔና መፍትሄ ያለው የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ላይ ሲሆን፤ እሱም እንዲህ ይላል፡-  

“የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጠሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅበታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”

ላለፉት 21 አመታት የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) በሚገባ ተግባራዊ አልተደረገም። በዚህ ምክንያት፤ አንደኛ፡-የኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዞቦች ሉዓላዊ መብት ተጥሷል፣ ሁለተኛ፡- የኦሮሞ ሕዝብና መንግስት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አልተረጋገጠም፣ ሦስተኛ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማህበራዊ መብት ተጥሷል። እነዚህ የሉዓላዋነት፣ የሕግና የመብት ጥሰቶች ከሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች አንፃር በዝርዝር እንመለከታለን።  

1ኛ፡- የኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዞቦች ሉዓላዊ መብት

የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) አለመተግባር የሚመለከተው የፌደራል፣ የክልል ወይም የከተማ መስተዳደርን ሳይሆን ሁሉንም የኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው።

ምክንያቱም ሕገ-መነግስቱ ለሁሉም ኢትዮጲያዊያን የሉዓላዊነትና የሕግ-የበላይነት ማረጋገጫ ነው። እኩልነትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ፣ በብዙሃነት፥ መቻቻል፣ መልካም ግንኙነት በጋራ ጥቅምና አመለካከት፣ እንዲሁም በተደጋጋፊነት የጋራ ማህብረሰብ ለመፍጠር እንዲያስችለን፣ ከፌደራል መንግስት እስከ ከተማ መስተዳደር መዋቅር የዘረጋንበት፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው። ስለዚህ፣ በየትኛውም ደረጃ ቢሆን ለሕገ-መንግስቱ ተገዢ መሆን ግዴታ እንጂ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ እያንዳንዱ አንቀፅ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት፥ የስልጣን የበላይነት መገለጫ፣ የመንግስት ስልጣንና ኃላፊነት ገደብና ቁጥጥር ማድረጊያ መሣሪያ ስለሆነ ለእንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ዋስትና ሆኖ ያገለግላል።

አሜሪካዊው ፀኃፊ “Thomas Paine” ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ ይገልፀዋል፡-   

“A constitution is not the act of a government, but of a people constituting a government…. The laws which are enacted by governments control men as individuals, but the nation, through its constitution, controls the whole government, and has a natural ability to do so. The final controlling power, therefore, and the original constituting power, are one and the same power.

The very existence of constitution is established: first – as creating a government and giving its powers; second – as regulating and restraining the powers so given. [therefore,] it is not for the benefit of those who exercise powers of government, that the constitutions is established. It is only to the constituting power that this right belongs.” [Thomas Paine, “Rights of Man”]

በአጠቃላይ፣ የአንቀፅ 49(5) አለመተግበር ብቻውን የሁሉም የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ መብት ተጥሷል። ይህ አንቀፅ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል ብቻ ያለውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይመለከታል፡፡ በመሆኑም፣ የዚህች አንቀፅ አለመተግበር ብቻ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት፣ ሰላም፣ ልማትና እድገት አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልል የታየው አመፅና አሁን በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ችግሮችን ማየት ይበቃል።

2ኛ፡- የኦሮሞ ሕዝብና መንግስት መብትና ተጠቃሚነት

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፤ አንደኛ፡- መሬት በሀገራችን ዋንኛ የሃብት ምንጭ ስለሆነ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፍትሃዊነት ተጠቃሚነት አንዱ ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን፣ ሁለተኛ፡- በሀገራችን ሁኔታ መሬት ከማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ብሔር ብሄረሰቦች የማንነት መገለጫዎቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና ሲያገኙ ነው የሚል መርህ አለው፡፡

አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የኦሮሞ ሕዝብን የመሬት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሕጎችና መመሪያዎች አልወጡም። በዚህም የክልሉ ሕዝብና መንግስት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው አልተከበረም። በእርግጥ አዲስ አባባ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ በዙሪያዋ ካለው የኦሮሞ ማህብረሰብ ጋራ የነበራት ግንኙነት ኢፍትሃዊ ነበር። ያንን በተመለከተ “ማስተር ፕላን – የችግሩ መነሻና መጨረሻ” በሚለው ፅሁፌ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ስጥቼበታለሁ። ስለዚህ፣ በዚህ ፅሁፍ በዋናነት ከቆሻሻ ማስወገድ ጋር በተያያዘ ባለው ችግር ላይ አተኩራለሁ።

Photo - Sendafa Landfill, A truck pushing the pile of garbage
Photo – Sendafa Landfill, A truck pushing the pile of garbage

የአዲስ አበባ መስተዳደር በሰንዳፋ የተገነባው የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታን ለግንባታ ከመረከቡ በፊት፤ የቦታ መረጣ (Site Selection)፣ የአከባቢ እና አዋጭነት ጥናቱን (Physical and Feasibility study) ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና Horn of Africa Regional Environmental Center and Network (HOARE&N) በጋራ ሆነው ነው። በመሰረቱ፣ እንዲህ ዓይነት የግንባታ ፕሮጀክት ቦታ መረጣና የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ ከሚያገለግሉት አመስት ዋና ዋና መስፈርቶች ውስጥ “የሕግ አዋጭነት” (Legal feasibility) አንዱ ነው። በመሠረቱ፣ የተጠቀሱት ሁለት ተቋማት ለአዲስ አበባ የቆሻሻ ማስወገጃ የሚሆን ቦታን ከከተማዋ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሄደው በአንድ ሉዓላዊ ክልላዊ መስተዳደር የመሬት ይዞታ ውስጥ ገብተው መምረጣቸው በራሱ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው።

በእርግጥ በዘመናዊ የአወጋገድና አስተዳደር ስርዓት መሰረት “ቆሻሻ” እንደ ስሙ አስቀያሚ ሳይሆን አዋጭ የሆነ ቢዝነስ ነው። ለምሳሌ፣ የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ መልሶ-መጠቀምና ማስወገድ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በ2006 የበጀት አመት ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን ብር ገቢ ከአገልግሎት ክፍያ ሰብስቧል። በቀጣይ 50ና 60 አመታት ከእያንዳንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ በአማካይ በቀን የሚጥለውን 2.1 ሜትር ኪዩብ ቆሻሻ እየሰበሰበ ወደ ሰንዳገፋ ወስዶ በመጣል ዳጎስ ያለ ገቢ እንደሚሰበስብ ይጠበቃል።

ሊጠናቀቅ ጥቂት የቀረው የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት በየቀኑ የ50 ሜ.ዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በአማካይ በአመት 22,265,000 ብር ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ገቢ ያስገኛል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ላለፉት 50 ዓመታት ከተጠራቀመው ቆሻሻ ስር የሚፈጠረው “Methane” የሚባለው ጋዝ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ 20 እጥፍ ከባቢ አየርን የሚበክል ነው። የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ይህን በካይ ጋዝ በመቀነሱ ረገድ በሚያበረክተው አተዋፅዖ ሀገሪቱ ከካርቦን ክሬዲት (Carbon Credit ) በየአመቱ 100,000 ዶላር (2,185,000 ብር) ታገኛለች። በአጠቃላይ፣ ከረጲ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጋር በተያያዘ ብቻ የከተማ መስተዳደሩና የፌደራል መንግስት በአመት 25.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ይገኛል። 

በኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 92 ከተዘረዘሩት የአከባቢ ደህንነት ጥበቃ አላማዎች እንዳሉ ሆነው፣ በሰንዳፋ የሚገነባው የቆሻሻ ማስወገጃ እንደ ተቋም ለአከባቢው ነዋሪዎች “ማህበራዊ ኃላፊነት” (Corporate Social Responsibility – CSR) አለበት። ነገር ግን፣ በሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት እና በወደፊት እቅዱ ውስጥ የአከባቢው ነዋሪዎችን ማህበራዊ ደህንነት (Social wellbeing) በጭራሽ ከግምት የገባ አይመስልም። አዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የ“HoARE&EN” ዋና ዳይሬክተር በሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ተመሣሣይ ከኤሌክትሪክ ኃይል እና ከካርቦን ክሬዲት ገቢ ሊገኝ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን፣ በቀድሞው ሆነ በአዲሱ ፕሮጀክት የሰንዳፋ አከባቢ ማህብረሰብ ከቆሻሻ ከሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ አልተደረገም። ለሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ 137 ሄክታር መሬት ከአከባቢ አርሶ-አደሮች ተወስዷል። ለአርሶ-አደሮቹ ተከፈለ የተባለው ጠቅላላ የካሣ መጠን 25 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ቢሆን በአግባቡ ለአርሶ-አደሮቹ አልተከፈላቸውም። 

እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ፣ የአከባቢው አርሶ-አደሮች ለመሬታቸው ይከፈላቸዋል የተባለው የ25 ሚሊዮን ብር ካሣ የፌዴራሉ መንግስትና የአ.አ መስተዳደር ከቆሻሻ ብቻ በየአመቱ ከሚያገኙት የ25.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያነሰ መሆኑ ነው። እስኪ አስቡት፣ አዲስ አበባ ቆሻሻዋን ሰንዳፋ ወስዳ ደፍታ በሚሊዮኖች ገቢ ስታገኝ፣ የአከባቢ ንፅህና እና የነዋሪዎቿ ጤንነት ሲጠበቅ፣ የሰንዳፋ አርሶ-አደር ግን 18 ብር በካ.ሜ ካሣ እየተከፈለው ከመሬቱ ሲፈናቀል፣ የአከባቢው ንፅህና እና የቤተሰቡ ጤንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ …ከዚህ በላይ ግፍና በደል ሌላ ምን አለ? በዚህ ሁኔታስ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ጥቅምና ተጠቃሚነት እንዴት ሊረጋገጥ ይችላል?

ስለዚህ፣ ሕገ መንግስቱ በሚያዘው መሰረት አስፈላጊው የሕግ ማዕቀፍና ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ እስካልተዘጋጀ ድረስ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች የመሬት ባለቤትነት መብትና ተጠቃሚነት በፍፁም ሊረጋገጥ አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ፣ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ፣ በክልሉ እና በከተማ መስተዳደሩ፣ በተናጠልም ሆነ በጋራ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን አስመልክቶ የሚወስዷቸው እርምጃዎች በሙሉ ሕጋዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሕገ-መንግስቱ መሰረት የራሱንና የሕዝቡን ልዩ ጥቅም ሊያስከብር የሚችልበት የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ከአዲስ አበባ ከተማ ሆነ ከፌደራሉ መንግስት ጋር የሚደርሰው ማንኛውም አይነት ስምምነት ተቀባይነት አይኖረውም። ውሎ-አድሮ ልክ እንደ አዲስ አበባ የማስተር ፕላን ህዝቡን ለተቃውሞና አመፅ ያነሣሣል። የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ የኦሮሚያ ሕዝብና መንግስት ጥቅሙ አይከበርለትም። በአጠቃላይ፣ በአንዲት አንቀፅ የኦሮሚያ አመፅና ተቃውሞ አሁንም፥ ወደፊትም ይቀጥላል።   

 3ኛ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማህበራዊ መብት ተጥሷል።

በሕገ-መንግስቱ መሰረት አዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ሉዓላዊ መስተዳደሮች ናቸው። ነገር ግን፣ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን በሁሉም ዘርፍ እየሰፋችና እያደገች መሄዷ የማይቀር ነው። የነዋሪዎቿ ብዛት በክፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ፣ የሀብት አጠቃቀሟ እና የአገልግሎት ፍላጎቷ በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል። በዚህ ምክንያት፣ የከተማዋ እድገት የራሷ ግዛት በሆነው የ54ሺህ ሄክታር ላይ ብቻ ተወስኖ ሊቀር አይችልም። ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል መሃል እንደመገኘቷና የመሬት ይዞታዋ ውስን እንደመሆኑ መጠን፣ ከተማዋ እያደገች በሄደች ቁጥር በዙሪያዋ ካለው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር መሬት እና አገልግሎት እንድትጋራ ያስገድዳል። ይህ ላይሆን የሚችልበት ብቸኛ አጋጣሚ የከተማዋን ተፈጥሯዊ እድገት ማቋረጥ ሲቻል ብቻ ነው። ማንም ቢሆን ዋና ከተማዋ እድገት አልባ እንድትሆን የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡

የሀገራችን ሕገ-መንግስት ሕብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት (Multinational federal system) ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ ስርዓት በተለያዩ መስተዳደሮች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ከውድድር ይልቅ የትብብር ፌዴራሊዝም (Cooperative Federalism) እንዲኖርረው የሚያስችል ነው። በዚህ መሰረት፣ እንደ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ያሉ ተጎራባች መስተዳደሮች በራሳቸው የስልጣን ወሰን ውስጥ ሆነው ፖሊሲዎቻቸውን በተናጠል በማውጣትና ለግጭቶች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ፖሊሲዎቻቸውን በጋራ የሚቀርፁበትና በተቀናጀ ሁኔታ የሚያስፈፅሙበትን እድል የሚፈጥር ነው። ለዚህ ደግሞ ከአንቀፅ 49(5) በላይ የተሸለ ማረጋገጫ የለም። በሁለቱ መስተዳደሮች መካከል፤ በአገልግሎት አቅርቦት፣ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ረገድ ግጭት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ ዝርዝር ጉዳዩ በሕግ እንዲወሰን በሕገ-መንግስቱ ተደንግጓል። ነገር ግን፣ ላለፉት 21 አመታት ይህ ድንጋጌ ተግባራዊ አልተደረገም። በዚህ ምክንያት፣ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች መነሻ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

አዲስ አበባ ከፈጣን እድገቷ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ከፍተኛ የሀብትና አገልግሎት ፍላጎት መጨመር ምላሽ ለመስጠት በሚል ከላይ ከተገለፀው መርህ ውጪ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መዘጋጀቱና ተግባራዊ ሊደረግ ቅድመዝግጅት እየተደረገ እያለ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞና አመፅ ተቀሰቀሰ። የብዙ የሰው ሕይወትና ንብረት ከጠፋ በኋላ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሣይሆን ቀረ። በእርግጥ ማስተር ፕላኑን በማቋረጥ ብቻ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል “ማስተር ፕላኑን ማቋረጥ ስህተትን እንደ መሳሳት ነው” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቼ ነበር። ምክንያቱም፣ የችግሩ ሥረ-መሰረት ማስተር ፕላኑ ሳይሆን የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ አለመሆን ነውና። 

የአዲስ አበባ እድገት ተፈጥሯዊና ሊቋረጥ የሚይችል ነው። ነገር ግን፣ ከተማዋ ላለፉት 129 ዓመታት ስታደርግ እንደነበረው፣ በዙሪያዋ ያለውን የኦሮሞ ገበሬ እያፈናቀለች መቀጠል አትችልም። ከዚያ ይልቅ፣ አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉት የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በጋራ እጅ-ለእጅ ተያይዘው አብረው ማደግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት ግልፅ የሆነ የሕግ ማዕቀፍና የአፈፃፀም መመሪያ ሊዘጋጅ ይገባል። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አዘገጃጀት ከዚህ መርህ ውጪ ስለነበረ በህዝብ አመፅና ተቃውሞ እንዲቋረጥ ተደርጏል። በዚህም የከተማዋ እድገት ባላት ውስን የከተማ መሬት ላይ ወደ ሰማይ እንዲሆን ተወሰነ። ነገር ግን፣ ወደ ሰማይ ለማደግም ከመሬት ላይ መቆም ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ የአዲስ አበባ መስተዳደር ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ለመስራት የሚያስፈልገውን ቦታ ለማግኘት በምድር ላይ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን በዘመቻ ማፍረስ ጀመረ። ላለፉት አስር አመታት ያልታየው ሕገ-ወጥ ወረራ ዛሬ ላይ በድንገት ተገለጠለት። 

በተመሣሣይ፣ በሰንዳፋ የተነሳውን የገበሬዎች ተቃውሞን አስመልክቶ፣ የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ ከ7 ዓመት በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ከአከባቢ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን እና በወቅቱ ከመግባባት ላይ ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን፣ በሕገ መንግስቱ መሰረት ልዩ ጥቅም ለማስከበር የሚቻልበት ዝርዝር ሕግና መመሪያ በሌለበት ከአከባቢው ማህብረሰብ ጋር መወያየት በራሱ ሕጋዊ መሰረት የለውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባን ጨምሮ የከተማ መስተዳደሩ ኃላፊዎች ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ጋር በሰንዳፋ ጉዳይ ላይ ለሰባት ቀናት ያህል በደረጉት ስብሰባ ከስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ተገልጿል። ነገር ግን፣ እንኳን ስምምነት ላይ መድረስ፣ ውይይቱ በራሱ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) የሚጥስ ነው።

በአጠቃላይ፣ ይህቺ አንቀፅ ተግባራዊ እስካልሆነች ድረስ በአዲስ አበባ በጣም ብዙ መኖሪያ ቤቶች ይፈርስሉ፣ ከፍተኛ የቆሻሻ ክምር ይኖራል። በዚህም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የራሳቸውን መኖሪያ ቤት የመገንባት እና ንፅህናው በተጠበቀ አከባቢያ የመኖር መብታቸው ሊረጋገጥ አይችልም፡፡

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories