ወዳጄ አርዓያ ጌታቸው “የሁከቱ መንስዔ…” በሚል የፃፈውን አነበብኩት፡፡ የችግሩን መንስኤ እና መፍትሄ ለማሳየት ያደረገውን ሙከራ አደንቃለሁ፡፡ ነገር ግን፣ “የወፍ በረር” እይታ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ሳይገቡ ችግሩና መፍትሄውን ለመግለፅ የሚደረግ ጥረት ነው እንጂ እንደዚህ ነገሩን በአንድ ቀዳዳ ብቻ አሾልቆ ማየት አይደለም፡፡ የፀሃፊው የአቶ አርዓያ ጌታቸው እይታ ግን ቁንፅል ብቻ ሳይሆን ነባራዊ እውነታውን ማሳየት የተሳነው ሸውራራ እይታ ነው፡፡

“የችግሩ መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለሰ ያለበት መዋቅራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመንተራስ ነው። እኔ በበኩሌ በዚህ ፅሁፍ የችግሩን መንስኤ ለመለየት የማደርገው ጥረት የሚጀምረው የሀገሪቱ የምትተዳደርበት መንግስታዊ መዋቅር መሰረት ከሆነው ኢፌድሪ ሕገ-መንግስት ነው። ሕገ መንግስቱ፣ ስለመንግስታዊ አወቃቀር በሚደነግገው ምዕራፍ አራት፥ አንቀፅ 49.5፤ የፌድራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምተገኝ እንደመሆኗ፣ ከአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አንፃር የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንደሚከበርና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን በግልፅ ተቀምጧል፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በሥራ ላይ የዋለው “መጪው እድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል” የሚል አዋጅ አካቶ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው የህዝብ ተቃውሞ (እዚህ’ጋ የቃላትና የቁጥር ቁማር መጫዋት አልፈልግም) መሰረታዊው ምክንያት፤ የሕገ መንግስቱ ምዕ.4፥ አንቀፅ 49.5 ላይ ለክልሉና ለህዝቡ በግልፅ የተቀመጠው መብትና ጥቅም በአዋጁ ላይ በተቀመጠው መርህ መሰረት አለመተግበሩ ነው።

ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና ለኦሮሞ ህዝብ በሕገ-መንግስቱ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ ተከትሎ መከናዎን የነበረባቸው አብይ ተግባራት፤ በሕገ-መንግስቱ መሰረት የሕግ-ረቂቅ ማዘጋጀትና ማፅደቅ፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ ማዘጋጀት፤ በአ.አ መስተዳደር እና በኦሮምያ ክልል መካከል ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ ከድንበር/ወሰን አወሳሰን እና ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አስፈላጊው የሆኑ ውሎችና ስምምነቶችን መፈራራም ናቸው። ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከተጠቀሱት ተግባራት ውስጥ አንዱ እንኳን ‘ተገቢው ትኩረትና አፅንዖት ተሰጥቶት ተሰርቷል’ ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም፣ በሕገ መንግስቱ ለኦሮሚያ ክልልና ለህዝቡ የተደነገገው መብትና ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገው የሕግ ማዕቀፎች (Legal Frameworks)፣ የአፈፃፀም መመሪያዎች እና ደንቦች በሌሉበት ሁኔታ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ከተደረገ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ያለውን የ128 ዓመታት የተዛባ ታሪክ ከማስቀጠል የዘለለ ሚና አይኖረውም።

ስለዚህ፣ በኦሮሚያ ክልል ለታየው የሕዝብ ተቃውሞ ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። በዚህ ውስጥ ማስተር ፕላኑ የተቃውሞው መነሻ ምክንያት (Immediate Cause) ብቻ ሳይሆን የመሰረታዊ ችግሩም የመጨረሻ እንደሆነ ቀጥሎ ለማሳየት እሞክራለሁ።

Map - Ethiopia Oromia 

1ኛ) ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት

በሕገ መንግስቱ የተደነገገው ከአገልግሎት አቅርቦትና ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለኦሮሚያ ክልልና ሕዝቡ ሊከበርልት ይገባ የነበረው ጥቅም አልተከበረለትም። አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለበት ከ1987 ዓ.ም በፊት’ም ሆነ በኋላ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባው ልዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አላገኘም። የኦሮሚያ ክልል መብትና ጥቅሙን በቀጣይነት እንዲያገኝ የሚያስችል ግልፅ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እና አሰራር ባልተዘረጋበት ሁኔታ የአ.አ ማስተር ፕላንን ተግባራዊ ማድረግ የቀድሞውን የተዛባ ታሪክ ማስቀጠል ስለሚሆን፣

2ኛ) አስተዳደራዊ/ ሉዓላዊ መብት:-

ሀ) የአዲስ አበባ ከተማ መተዳደሪያ ቻርተር ላይ በግልፅ እንደተጠቀሰው፣ በከተማ አስተዳደሩ እና በክልሉ መንግስት መካከል በሚደረስ ስምምነት የሁለቱ የድንበር ወሰን በግልፅ ተለይቶ እንደሚታወቅ ቢጠቅስም እስካሁን ድረስ የተሰራ ስራ የለም። የሁለቱ የድንበር ወሰን በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 48.1 መሰረት በሁለቱ አስተዳደር አካላት መካከል በሚደረስ ስምምነት ወይም ደግሞ አንቀፅ 48.2 ላይ በተጠቀሰው መሰረት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት ግልፅ የሆነ ውስኔ ባልተሰጠበት ሁኔታ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ማድረግ የአ.አ ከተማ ከተመሰረተችበት ግዜ ጀምሮ እያደረገች ላለው ድንበር-የለሽ መስፋፋት ማረጋገጫ መስጠት ስለሆነ፣

ለ) በቀጣይ 25 አመታት በርዕሰ ከተማዋ እና በአምስቱ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የሚኖረው ህዝብ መጠን በድምሩ ወደ 8.1 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህ ማሰተር ፕላኑ ደግሞ ይህን የህዝብ ብዛት ለማስተናገድ የሚያስፈልገውን አሁን አ.አ ከተማ ካላት የቆዳ ሽፋን 20 እጥፍ የሚሆን ተጨማሪ ቦታ ታሳቢ ተደርጐ የተዘጋጀ። ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ እንደመሆኗ በማስተር ፕላኑ የሚካተተው ቦታ ሙሉ በሙሉ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ይዞታ ስር ያለ ነው። ሆኖም ግን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር አስፈላጊውን ቅድመ-ስምምት ሳያደርግ በክልሉ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን ማስተር ፕላን ማዘጋጀቱና ለተግባራዊነቱ መዋቅር ዘርግቶ መንቀሳቀሱ የክልሉን ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ሉዓላዊ ስልጣን በግልፅ የሚጋፋ ተግባር ስለሆነ፣

3) ማህበራዊ መብት

አፄ ሚኒሊክ በ1879 ዓ.ም ፊንፊኔን “አዲስ አበባ” ብለው ዋና ከተማ ሲያደርጓት፣ በአከባቢው ይኖር የነበረውን የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ አማክረውት አልነበረም፣ በጦር መሳሪያ ሃይል አፈናቅለውት እንጂ። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ባለው የአንድ ክ.ዘመን ግዜ ውስጥ አዲስ አበባ በፍጥነት እያደገች እና ያለ ወሰን እየሰፋች፣ በዙሪያዋ የሰፈረውን የኦሮሞ ህዝብ እያፈናቀለች፣ ቋንቋና ባህሉን እየገፋች፣ የአኗኗር ዘይቤውን እያጣጣለች፣ ማህበራዊ እሴቶቹን ቦታና ትርጉም እያሳጣች ኖራለች። ባለፋት 20 ዓመታት ውስጥ ደግሞ የከተማዋ እድገት ይበልጥ ጨምሮ የገበሬውን የእርሻ መሬት በርካሽ የካሳ ክፍያ እየተቀራመተች፤ የኑሮ ህልውናው ከእርሻ መሬቱ ጋር የተጣበቀን አርሶ አደር ገበሬን በዝቅተኛ ካሳ እያፈናቀለች፣ ያለ ምንም ዓይነት የስነ-ልቦና ቅድመ-ዝግጅት ለዘመናት ከኖረበት የአኗኗር ዘይቤና የሥራ ዓይነት እንዲቀየር እያስገደደች፣ ያለ ሞያዊ ድጋፍና ክትትል ከመሬቱና ኑሮው የተፈናቀለ ገበሬ ለሌላ ዓይነት ማህበራዊ ቀውስ እየዳረገችው ትገኛለች። እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ቅድመ-ዝግጅት እና የድጋፍና ክትትል ስርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ የአ.አ ማስተር ፕላንን ተግባራዊ ማድረግ ለአንድ ክ.ዘመን የተዛባውን ታሪክ ማስቀጠል ስለሆነ፣

መፍትሄ፦

የችግሩ መንስዔ አንድ ነው፣ መፍትሄውም እንደዛው! ከማስተር ፕላኑ በፊት፣ በቅድሚያ በሕገ መንግስቱ ለኦሮሚያ ክልልና ለህዝቡ የተደነገገው መብትና ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች፣ የአፈፃፀም መመሪያዎች እና ደንቦች በሚገባ በማዘጋጀት ከላይ የተጠቀሱትን የክልሉን መንግስትና ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊና ማህበራዊ መብቶች በአግባቡ በማስጠበቅ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ያለውን የተዛባ ታሪክ ማረም ነው።

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories